ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያሉ መሠረታዊ አመለካከቶች

ሰዎች ስለ ወደፊቱ ለማወቅ ያላቸው ጉጉት አብሯቸው የኖረ ሲሆን ብዙ ነቢያት (እውነተኞቹም ሆኑ ሐሰተኞቹ) ይህን የሰው ፍላጎት ለማርካት ጥረት አድርገዋል። መተንበይ አደገኛ ሥራ ነው ምክንያቱም ትንበያው ስሕተት በሆነ መጠን፥ በአገልግሎቱ መቀጠሉ አስቸጋሪ እየሆነ ይሄዳል። በብሉይ ኪዳን ዘመን አንድ ነቢይ በእግዚአብሔር ስም መናገር ካቃተው፥ ወይም የተናገረው ትንቢት ባይፈጸም ያለ ምሕረት ይወገር ነበር (ዘዳግ. 13፡1-11፥ 18፡20-22)። አልፎ አልፎ ትክክለኛ ነገር ያመለከቱ ሐሰተኛ ነቢያት ቢነሱም (ይህ ዛሬም እንደተከሰተ ነው)፥ መልእክታቸው ቀደም ሲል እግዚአብሔር ለሕዝቡ በሰጠው እውነተኛ ትንቢቶች ይመዘን ነበር። እነዚህም ነቢያት ሚዛን ካላነሱ ይወገሩ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ የተነገሩ ትንቢቶች በትክክል መፈጸማቸው ተረጋግጧል። ይህም ያልተፈጸሙ ትንቢቶች በጽሑፍ በሰፈረው መሠረት በትክክል እንደሚከናወኑ እርግጠኛ ያደርገናል። 

የወደፊቱን ሁኔታ በሚመለከት ብዙዎች አይስማሙም። ከዚህም የተነሳ ትንቢትን በመተርጎም ረገድ በቤተ ክርስቲያን ሦስት መሠረታዊ አመለካከቶች አሉ። እነዚህም እግዚአብሔር ከአይሁዳውያን፥ በተለይ ከአብርሃም ጋር ከገባው ቃል ኪዳን ጋር የሚያያዙ ናቸው። 

እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው ቃል (ዘፍጥ. 12፡1-3) እየቆየ ሊረጋገጥና ይፋ ሊሆን ችሏል (ዘፍጥ. 13፡14-17፥ 15፡1-7፥ 17፡1-18)። አብርሃም በጊዜያዊና በመንፈሳዊ በረከቶች ሁሉ እንደሚባረክ በዚህ ቃል ኪዳን ተገልጧል። በዚህም መሠረት ርስት፥ ባሪያዎች፥ መንጋዎች፥ ብርና ወርቅ ማግኘቱ ሲታይ (ዘፍጥ. 13፡14-15፥ 17፤ 15፡7፣ 24፡34-35)፣ ከእግዚአብሔር ጋር ደስ የሚያሰኝ ኅብረት ስለነበረው የእግዚአብሔር ወዳጅ ተብሎ ለመጠራትም በቅቷል (ዘፍጥ. 18፡17፤ ያዕ. 2፡23)። እነዚህ ትንቢቶች ልክ በተነገሩት አኳኋን ተፈጽመዋል፡፡

ለአብርሃም ልጆችና ለእስራኤል ለራሷም በዚያ ቃል ኪዳን ተስፋ ተሰጥቷቸው ነበር። እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ከአብርሃም ልጆች ጋር እንደሚቀጥልና (ዘፍጥ. 17፡7)፣ ቁጥራቸው እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ ታላቅ ሕዝብ እንደሚያደርጋቸው ተናግሯል (ዘፍጥ. 12፡2፥ 13፡16፥ 15፡5)። የሚደንቀው የአብርሃም ልጆች የሆኑት አይሁዳውያን ዛሬ የሚኖሩበት መሬት ዳርቻውና ክልሉ ቀደም ብሎ በተስፋ መገለጡና ለዘላለምም የነርሱ ርስት እንደሚሆን መነገሩ ነው (ዘፍጥ. 15፡18፣ 17፡8)። 

ቃል ኪዳኑ ሌሎች ሕዝቦችን የሚጨምር ተስፋ ነበር። አብርሃምንና ልጆቹን የሚባርኩ እንደሚባረኩና፥ የሚረግሟቸው ደግሞ እንደሚረገሙ ተናግሯል። ይህ በአብርሃም የሕይወት ዘመን የተረጋገጠ ጉዳይ ነው (ዘፍጥ. 14፡12-20፥ 20፡2-18)። በእስራኤል ልጆች ልምምድ ውስጥ እንዲሁ (ዘዳግ. 30፡7፤ ኢሳ. 14፡12)፥ ትንቢቱ ወደፊት በሚጠበቀው የፍዳ ዘመንም ይሠራል (ማቴ. 25፡40)። የምድር ነገዶች ሁሉ በአብርሃም እንደሚባረኩ ተስፋ ነበር። እግዚአብሔርም በእስራኤል በኩል መጽሐፍ ቅዱስን በመስጠትና ከአብርሃም ዘር የሆነ ክርስቶስን በመላክ ቃሉን ፈጽሟል(ገላ. 3፡16)። 

ለአብርሃም የተገባው የተስፋ ቃል አብዛኛው የተፈጸመ ለመሆኑ ሰዎች ሁሉ ይስማማሉ። የእስራኤልን ምድር በተመለከተ የተሰጠው የተስፋ ቃል ግን ሙሉ በሙሉ ተፈጽሟል ለማለት አይቻልም። የምድሪቱ ዳርቻ “ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ” (ዘፍጥ. 15፡18) መሆኑ ተገልጧል። የምድሪቱ ምሥራቅ ዳርቻ የኤፍራጥስ ወንዝ እንደሚሆን ሰዎች ሁሉ ይስማማሉ። የግብፅ ወንዝ የተባለው የቱ ነው? ለሚለው ጥያቄ ነው የተለያየ መልስ ያላችው። አንዳንዶቹ ወንዝ የሚለው ቃል አባይን ያመለክታል ሲሉ፥ ሌሉቹ ደግሞ ዋደ ኤል አሪሽ የተባለውንና ከጋዛ እጅግም የማይርቀውን ወንዝ ይጠቅሳል ይላሉ። ከሁለቱም አመለካከት አቅጣጫ ሲታይ እስራኤል በታሪኳ እስከዛሬም ቢሆን እነዚህን ድንበሮች አልያዘችም፡፡

ለአብርሃም በተሰጠው ቃል ኪዳን ላይ የሚነሳው ሌላ ጥያቄ የተስፋው ቃል በታዛዥነት ላይ የተመሠረተ ነው፥ ወይስ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ይፈጸማል? የሚል ነው። ተስፋው በአይሁድ ታማኝነትና መልካምነት ላይ የተመሠረተ ከሆነ፣ ስለ ፍልስጥኤም የተባለው ነገር እና በቃል ኪዳኑ የተሰጠው በረከት ሁሉ ተሰርዟል ማለት ነው። ምክንያቱም የአይሁድ ሕዝብ ደግሞ ደጋግሞ ኃጢአት ሠርቷል። ተስፋው በእግዚአብሔር ታማኝነት ላይ የሚመሠረት ከሆነ ግን በሰው መታመን ወይም አለመታመን ሳይታገድ ይፈጸማል። 

ቃል ኪዳኑ በቅድመ ሁኔታ ላይ ለመመሥረት ወይም ላለመመሥረቱ ጥያቄ መልስ የሚሆነን ነገር ስዘፍጥረት 15፡9-17 ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ ይህም እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ለማጽናት ያደረገው ተግባር ነው። በእነዚያ ጊዜያት ቃል ኪዳንን ለማጽናት የተለመደው መንገድ በመጀመሪያ እንስሳትን መሥዋዕት ማድረግ፥ ከዚያም እንስሳቱን ቆራርጦ መሬት ላይ ማስቀመጥ ነበር። በቃል ኪዳኑና በተለመደው አሠራር መሠረት ቢሆን ሁለቱ ተስማሚ ወገኖች በመሥዋዕቱ መካከል መሄድ ይገባቸው ነበር። በዚህ አሠራር ግን አሰገራሚና ልዩ ሁኔታ ታይቷል። እግዚአብሔርና አብርሃም በመሥዋዕቱ መካከል አልተመላለሱም። በዚያ ፈንታ እግዚአብሔር በአብርሃም ላይ ከባድ እንቅልፍ ጣለበትና ብቻውን በመሥዋዕቱ መካከል አለፈ። ይህ የሚያሳየን እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ብቻውን የሚጠብቅ መሆኑን ነው። 

በተጨማሪም ቃል ኪዳኑ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅ፥ ለይስሐቅም ልጅ ለያዕቆብ፥ እንደገና ተረጋግጧል (ዘፍጥ. 26፡2-4፥ 28፡13-15)። በዚህ ጊዜ ሁሉ ለትንቢቱ ፍጻሜ ቅድመ ሁኔታ ያልተጠቀሰ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ለአብርሃም ማረጋገጫውን ያጸናለት ያለ ቅድመ ሁኔታ የገባውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ ብቻ ነው። ከዚህም ሌላ ቃል ኪዳኑ በተሰጠበትና ለይስሐቅ በተረጋገጠበት ጊዚ መካከል አብርሃም ኃጢአት ፈጽሞ ነበር። ታዲያ ቃል ኪዳኑ የታዛዥነት ቅድመ ሁኔታ ቢኖረው ኖሮ፥ በአብርሃም አለመታዘዝ ምክንያት በተሰረዘ ነበር (ዘፍጥ. 12፡10-20)። በትክክል ለመናገር ለቃል ኪዳኑ ተፈጻሚነት በአንዳንድ መለስተኛ ጉዳዮች ላይ ቅድመ ሁኔታዎች መኖራቸው ቢታይም፥ ለቃል ኪዳኑ አጠቃላይ ፍጻሜ ግን ግዴታ አልነበረም። በእስራኤል ታሪክ ውስጥ የተስፋይቱን ምድር ለጊዜውም ቢሆን፥ በከፊል ለመውረስ ታዛዥነት እግዚአብሔር የጠየቀው ግዴታ የነበረ ሲሆን፥ አለመታዘዝና ኃጢአት መፈጸምም የመበተንን ፍርድ ያስከትል ነበር (ዘዳግ. 28፡25፤ ኤር. 25፡11)። ይሁን እንጂ የቃል ኪዳኑ መጨረሻ በእግዚአብሔር ይከናወናል፤ እስራኤልም በመሢሁ በምትገዛበት ዘመን ወደ ፍጹም ታዛዥነት ትለወጣለች። 

ለዳዊትና ለልጆቹም እግዚአብሔር እንደዚሁ “በዳዊታዊ ቃል ኪዳን” በጣም ጠቃሚ የሆኑ ቃል ኪዳኖች ገብቷል (2ኛ ሳሙ. 7፡12-16)። ቤተ መቅደሱን የሚገነባው ዳዊት ሳይሆን ልጁ ሰሎሞን መሆኑን ጠቅሶ፥ ዙፋኑና መንግሥት በዳዊት ዘር ለዘላለም እንደሚጸና ቃል ገብቷል፡፡ ክርስቶስ ከዳዊት ዘር ለመሆኑና የተስፋ ቃል ፈጻሚ ለመሆኑ ሰዎች ሁሉ ይስማማሉ፤ ምክንያቱም ሉቃስ 1፡32-33 ይህን ስለሚያረጋግጥ ነው። እነዚህ ንጉሡንና መንግሥቱን የተመለከቱ ተስፋዎች በብሉይ ኪዳን የተደጋገሙ ቢሆንም፥ ከሁሉም ጠንከር ያለው ኃይለ ቃል በመዝሙር 89 ላይ የተጠቀሰው ነው። በዚህ ሰፍራ ጌታ አለመታዘዝን እንደሚቀጣና፥ ቃል ኪዳኑም በምንም ሁኔታ እንደማይሻር ወይም እንደማይለወጥ በተጠናከረ ሁኔታ ተገልጧል (ቁ. 30-37)። ሌሎች ተመሳሳይ ቃሎች ኢሳ. 9፡6-7፤ ኤር. 23፡5- 6፤ ሕዝ. 37 ፡24-25፤ ሆሴእ 3፡4-5፤ 152 አሞጽ 9፡11 እና ዘካ. 14፡4-9 ናቸው። እነዚህን ሁሉ የሚፈጽማቸው ክርስቶስ ስለመሆኑ የትምህርተ-መለኮት ሰዎች ሁሉ ይስማማሉ። መቼ? ለሚለው ጥያቄ የሚሰጡት መልስ ግን ተመሳሳይ አይደለም። አሁን ክርስቶስ በሰማይ ባለው የዳዊት ዙፋን ነው የተቀመጠው? ወይስ ቤተ ክርስቲያን ናት መንግሥቱ? ወይስ ይህ ሁሉ የሚፈጸመው ክርስቶስ ወደፊት መንግሥቱን ምድር ላይ በሚመሠርትበትና በሚገዛበት ጊዜ ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልሶች ናቸው ስለ ወደፊቱ ሁኔታ ያሉትን አመለካከቶች የተለያዩ የሚያደርጓቸው። ስለ ሺሁ ዓመት አገዛዝ [Millenium/ሚሌኒየም] ያሉት ሦስት የተለያዩ አመለካከቶች የተመሠረቱት ለአብርሃምና ለዳዊት የተሰጧቸው ቃል ኪዳኖች ቅድመ ሁኔታዎች ነበሯቸውን? በሚለው ጥያቄ ላይ ነው። 

የድህረ-ሺህ ዓመት አገዛዝ አመለካከት [Postmillennialism] 

ይህ አመለካከት የሚያስተምረው የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ከሺህ ዓመቱ አገዛዝ በኋላ ይሆናል በማለት ነው። የዚህ አመለካከት አራማጆች በቤተ ክርስቲያን ጥረት በምድር ላይ ፍጹም የሆነ አገዛዝ ይመሠረታል በማለት ያስተምራሉ። በወርቃማው ዘመን የአብርሃምንና የዳዊትን ቃል ኪዳን የምትለማመደው ቤተ ክርስቲያን እንጂ እስራኤል አይደለችም ይላሉ። ይህ መንግሥት ምድራዊ ስለሚሆን “የቤተ ክርስቲያን መንግሥት” እንጂ የአይሁድ መንግሥት አይሆንም። ንጉሡ ክርስቶስም በምድር ላይ አይኖርም፤ የሚገዛው በሰዎች ልብ ውስጥ በማደር ሲሆን፥ ሺሁ ዓመት የአገዛዝ ዘመን ሲያበቃ ነው ወደ ምድር የሚመለሰው። በዚያን ጊዜም የሙታን አጠቃላይ ትንሣኤ ይሆንና፥ ለሰዎች ሁሉ ፍርድ ይሰጣል፤ ከዚያ በኋላ ነው ዘላለማዊ ሕይወት የሚጀመረው። 

በድህረ-ሺህ ዓመት አገዛዝ እምነት ተከታዮች አመለካከት መሠረት፥ ለአብርሃም የተሰጠው ቃል ኪዳን የሚፈጸመው በቤተ ክርስቲያን በኩል ቢሆንም፥ አፈጻጸሙ ቃል በቃል በሚሰጠው ትርጉም መሠረት አይደለም። የአተረጓጎም ዘዴውም ትንቢቶቹን ምሳሌያዊ ትርጉም በመስጠት ነው።

የአልቦ-ሺህ ዓመት አገዛዝ አመለካከት [Amillennialism] 

ይህ አመለካከት ሺህ ዓመት የሚባል ነገር ጨርሶ የለም ብሎ ነው የሚያስተምረው። መንግሥት ቢኖር ያለው አሁን ነው፤ ይህም መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ላይ ያለው ሰማያዊ አገዛዝ ነው ይላል። ይህ የቤተ ክርስቲያን ዘመን እስከሚያበቃና ክርስቶስ ዳግም እስኪመጣ ድረስ፥ አሁን ያሉ ሁኔታዎች እየተባባሱ ይሄዳሉ። ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት በኋላ ወዲያውኑ ትንሣኤ፥ ሙታንና ፍርድ ተከታትለው ይፈጸማሉ፤ ከዚያም ዘላለማዊ ግዛት ይመሠረታል። 

አልቦ-ሺህ ዓመታውያን የአብርሃምን ቃል ኪዳን አፈጻጸም የሚገልጡባቸው ሦስት የተለያዩ መንገዶች አሏቸው። አንዳንዶቹ ስለ እስራኤል ርስት የተነገሩት ተስፋዎች በሰሎሞን አገዛዝ ዘመን ተፈጽመዋል ይላሉ (1ኛ ነገሥ. 4፡21)። ይሁን እንጂ በሰሎሞን አገዛዝ ዘመን የእስራኤል ምድር ሙሉ በሙሉ አልተያዘም። እስከዛሬም ቢሆን የቃል ኪዳኑ መሬት አልተወረሰም። እስራኤላውያን ለቅድመ ሁኔታዎች አልታዘዙም፥ ኃጢአት ፈጽመዋል፤ ስለዚህ ቃል ኪዳኖች ፍጻሜ ሊያገኙ አይገባም ይላሉ። የቀሩት ደግሞ (ምናልባት ብዙሀኑ)፥ ቤተ ክርስቲያን ነች ቃል ኪዳኑን ቃል በቃል ባይሆንም ቀጥተኛ ትርጉም በመስጠት የምታሟላ ይላሉ። ክርስቶስ በሰማያት በዳዊት ዙፋን ተቀምጦ አስፈላጊ የሆኑትን የብሉይ ኪዳን ተስፋዎች በቤተ ክርስቲያኑ እያሟላ ነው። ይህ አመለካከት ያላቸው አልቦ-ሺህ ዓመታውያን ስለ ቃል ኪዳኖቹ ተፈጻሚነት ኀላፊነት የሚሰማቸው ሲሆን፥ ቃል ኪዳኖቹን ከትምህርታቸው ጋር ለማስማማት የሚሞክሩም ይመስላል። 

አልቦ-ሺህ ዓመታውያን ስለ እስራኤል መንግሥትነት የተገባውን ቃል ኪዳን ሲተረጎሙ፥ ትንቢቶቹ በቤተ ክርስቲያን በኩል እየተሟሉ ነው በማለት ምሳሌያዊ (ቀጥተኛና ቃል በቃል ትርጉም ያልሆነ) ይዘት ይሰጧቸዋል። በዚህ አመለካከት መሠረት፥ ራእይ 20 የሚገልጠው በክርስቶስ የመጀመሪያና ዳግም ምጽአት መካከል በሰማይ ስላሉት ነፍሳት ሁኔታ ነው። 

የቅድመ-ሺህ ዓመት አገዛዝ አመለካከት [Premillennialism

ቅድመ-ሺህ ዓመታውያን የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ከሺህ ዓመት በፊት እንደሚሆንና መንግሥቱን የሚመሠርተውም ክርስቶስ እንደሆነ (እንደ ድህረ ሺህ ዓመታውያን እምነት ቤተ ክርስቲያን አይደለችም) ይናገራሉ። ክርስቶስ በምድር ይነግሣል፤ በዚህ የሺህ ዓመታት አገዛዝ ወቅት የአይሁድ ሕዝብ የአብርሃምንና የዳዊትን ቃል ኪዳን ሙሉ በሙሉ ይለማመዱታል። በዚህ አመለካከት መሠረት፣ የአሁኗ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ላይ ክህደት እየጨመረ ሲሄድ ታያለች፤ በጣምም የሚከፋው ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት በፊት የሚደርሰው የፍዳ ዘመን ይሆናል። ክርስቶስ ሲመጣም መንግሥቱን ለሺህ ዓመታት ይመሠርታል። ከዚያም የሙታን ትንሣኤ ተከናውኖ ላልዳኑ ሰዎች ፍርድ ይሰጥና ዘላለማዊ ግዛቱ ይቀጥላል፡፡

የቅድመ-ሺህ ዓመታውያን ትምህርት፥ የመጽሐፍ ቅዱስን የተስፋ ቃልና ትንቢት ትርጉም ቀጥተኛና ቃል በቃል በሆነ መንገድ የተከተለ ነው ለማለት ይቻላል። ይህ የቅድመ-ሺህ ዓመታውያን ጠንካራ የትርጉም ዘዴ፥ ከታሪክ፥ ከትምህርተ-መለኮትና ከትንቢቶች ጋር በቀላሉ ሊዛመድ የሚችል ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ግልጥ ሆኖ ሳለ፥ ቃል በቃል አለመወሰዱ መልካም አይደለም። ለአብርሃምና ለዳዊት የተገቡት ቃል ኪዳኖች በቀጥታ የሚመለከቱት የአብርሃም ዘር የሆኑትን መሆኑ እየታወቀ፥ ለምን በቤተ ክርስቲያን በኩል እንዲፈጸሙ ይጠበቃል? በዚህ አስተሳሰብ እስራኤል፥ እስራኤል ማለት ሳይሆን፥ ቤተ ክርስቲያን ሆኗል ማለት ነው። አዲስ ኪዳን አይሁድንና ቤተ ክርስቲያንን በመለየት የሚናገር ስለሆነ፥ እነኝህ የተስፋ ቃሎች በቤተ ክርስቲያን ሳይሆን በአይሁድ ሕዝብ ኩል እንደሚሟሉ ልንጠብቅ ይገባል (1ኛ ቆሮ. 10፡32፤ ሮሜ 11፡26)።

የቤተ ክርስቲያን ንጥቀት ገለጣ (ዮሐ. 14፡1-3፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡51-57፣ 1ኛ ተሰ. 4፡13-18) 

“መነጠቅ” [Rapture/ራፕቸር] የሚለው ቃል በ1ኛ ተሰሎንቄ 4፡17 ላይ ተጠቅሶ ይገኛል። እንዲሁም ፊልጶስ በሐዋርያት ሥራ 8፡39 እና ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 12፡2 4 ስለመነጠቃቸው ተገልጧል። በመሆኑም የቤተ ከርስቲያን መነጠቅ፥ ወደ ላይ መውጣት ማለት ነው። በዮሐንስ 14፡1-3 ላይ በተሰጠው ተስፋ መሠረት ወደ መኖሪያ ስፍራ መምጠቅ ነው። ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልዕክቱ ይህ ምስጢር ነው ይላል። “ምስጢር” የሚለው ቃል ትርጉም፣ ከዚህ በፊት ያልታወቀ፥ አሁን የተገለጠ ማለት መሆኑን ልብ ማለት ያሻል። ትንሣኤ ምስጢር አልነበረም፤ ምክንያቱም ብሉይ ኪዳን ሰዎች ከሞቱ በኋላ እንደሚነሱ በግልጥ አስተምሯል (ኢዮብ 19፡25፤ ኢሳ. 26፡19 ዳን. 12፡2)። የተወሰኑ ሰዎች ሞትን ሳይቀምሱ ወደ እግዚአብሔር እንደሚሄዱ ግን በምንባቦቹ ውስጥ አልተገለጠም። ለዚህ ነው ሁላችን “አናንቀላፋም” የሚለው ቃል ምስጢር የሆነው (1ኛ ቆሮ. 15፡51)። በመነጠቅ ጊዜ በሕይወት ያሉ ሰዎች የማይሞት አካል ይለብሳሉ። በሞት የበሰበሱትም በትንሣኤ የማይብስብስ አካል ይሰጣቸዋል። በሁለቱም መንገድ ወደ ሰማይ የሚደረግ ጉዞ ለውጥ ይሻል፤ ሕያዋን መለወጥ፥ ሙታንም መነሳት አለባቸው፤ የመጨረሻው የክርስቲያን ትውልድ ሞትን አይቀምስም፡፡

ይህ ለውጥና መነጠቅ የዓይን ሽፋን መርገብገብን ያህል ቅጽበታዊ” እንጂ አዝጋሚ ክንውን አይደለም። እንዲሁም መነጠቅ ሳይከፋፈል በአንድ ጊዜ ይሆናል። ጳውሎስም ሁላችን እንለወጣለን አለ እንጂ ስለተወሰኑ አማኞች አልተናገረም። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡51-58 ሦስት ነገሮች ያስተምራል። 

1. መነጠቅ የሞቱ አማኞችን ብቻ ሳይሆን፥ በጊዚው ሕያው የሆኑ አማኞችንም የአካል ለውጥ ያመለክታል። 2. በቅፅበት ይፈጸማል። 3. አማኞችን ሁሉ ያካትታል እንጂ፥ ለተወሰኑ ብቻ አይደለም። 

ከሌሎቹ ይልቅ በ1ኛ ተሰሎንቄ 4፡13-18 ያለው ጥቅስ ነው ጌታ ሲመጣ ምን እንደሚሆን የተብራራ አሳብ የሚሰጠን። በዚህ ክፍል አራት ነገሮች ተጠቅሰዋል። 

1. ክርስቶስ ራሱ ይመለሳል (ቁ. 16)፣ በአካል መገለጡ የሚያስከትላቸው በኃይል የተሞሉ ክስተቶችም ይኖራሉ፤ ታላቅ የትእዛዝ ድምጽ፥ የሊቀ መላእከት ድምጽ፥ የእግዚአብሔር መለከት ድምጽ ይሰማሉ። 

2. ትንሣኤ ይሆናል (ቁ. 16)። የሞቱት ይነሳሉ፥ ሕያዋንም ይለወጣሉ፥ ይህ ሁሉ በቅስበት የሚከናወን ይሆናል። የሰው ዘር በሙሉ ሳይሆን፥ የሞቱና ሕያዋን ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው ይህን መነጠቅ የሚቀምሱት። ይህ አማኛችን ብቻ የሚመለከት ይሆናል፤ ምክንያቱም አንድ አጠቃላይ ትንሣኤ ሳይሆን የተለያዩ ትንሣኤዎች ናቸው ያሉት። 

3. መነጠቅ ይሆናል (ቁ. 17)። የቃሉ ትርጉም፣ አንድን ሰው ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ መውሰድ ማለት ሲሆን ይህም ሕያዋን ሰዎችን ወደ መንግሥተ ሰማያት መውሰድ ማለትን በትክክል ያመለክታል (2ኛ ቆሮ. 12፡4)። 

4. ከዚያም እንደገና መገናኘት ይኖራል (ቁ. 17)፤ በጌታ ከሞቱና ከምንወዳቸው ሰዎች፥ እንዲሁም ከጌታም ጋር እንገናኛለን። ግንኙነቱም ዘላለማዊ ይሆናል። 

የመነጠቅ ጊዜ 

መነጠቅ ከጌታ ዳግም ምጽአት የተለየ ስለመሆኑ ብዙ ሰዎች ይስማማሉ። የመጀመሪያው መነጠቅ፥ ከርስቶስ የራሱ የሆኑትን ለመውሰድ የሚመጣበት ጊዜ ሲሆን ሁለተኛው ግን ከነርሱ ጋር በድል አድራጊነትና በክብር የሚመለስበት ወቅት ነው። አከራካሪው ጉዳይ በነዚህ ሁለት ክንውኖች መካከል ምን ያህል የጊዜ ልዩነት አለ? የሚለው ጥያቄ ነው። አልቦ-ሺህ ዓመታውያን፥ ሁለቱም በፍዳው ዘመን መጨረሻ ላይ የሚከናወኑ ሲሆን፥ ንጥቀት ይቀድምና ወዲያውኑ ዳግም ምጽአት ይከተላል (ወዲያውኑ፥ ያለ ሺህ ዓመት አገዛዝ) ይላሉ። በቅድመ-ሺህ ዓመታውያን ዘንድ ስለመነጠቅ ጊዜያት አራት አመለካከቶች እንዳሉ ይታወቃል። 

የድህረፍዳ ዘመን አመለካከት። ይህ አመለካከት የመነጠቅንና የዳግም ምጽአትን የጊዜ ቅደም ተከተል አስመልክቶ የሚያሰራጨው ትምህርት ከአልቦ-ሺህ ዓመታውያን የተለየ አይደለም (የሺህ ዓመቱ አገዛዝ ከዳግም ምጽአት በኋላ ይከተላል በሚለው አመለካከቱ ግን ይለያል)። በዚህ አመለካከት መሠረት ቤተ ክርስቲያን በፍዳው ዘመን ሁሉ በምድር ላይ ትኖራለች። የክርስቶስ ለቅዱሳኑና ከነሱ ጋር መምጣት፥ በዚህ ዘመን ማብቂያ ላይ ወዲያውኑ የሚከሰቱ ድርጊቶች ናቸው። 

ዋና ዋናዎቹ የመከራከሪያ ነጥቦቻቸው፡- 

1. መነጠቅና ዳግም ምጽአት በመጽሐፍ ቅዱስ በተመሳሳይ ቃላት ነው የተገለጡት። ይህ ሁለቱም በአንድ ጊዜ የሚከናወኑ መሆናቸውን ያመለክታል (1ኛ ተሰ. 4፡15፤ ማቴ. 24፡27)። 

2. በፍዳው ዘመን ቅዱሳን እንደሚኖሩ ስለተገለጠ፥ ቤተ ክርስቲያንም በዚያን ጊዜ በምድር ትኖራለች (ማቴ. 24፡22)። 

3. ትንሣኤ በሺሁ ዓመት አገዛዝ መጀመሪያ ላይ የሚከሰት ነው ተብሎ ይታመናል። ይኽው ትንሣኤም በመነጠቅ ጊዜ የሚከናወነው ትንሣኤ መሆኑ ስለሚገመት፥ መነጠቅ ልክ ከሺሁ ዓመት አገዛዝ በፊት የሚፈጸም ይሆናል (ራእይ 20፡4)። 

4. ቤተ ክርስቲያን ከፍዳው ዘመን ቁጣ በመለኮታዊ ኃይል ትጠበቃለች። ጥበቃው የሚከናወንላት በዚያው ዘመን እየኖረች እንጂ፥ ከዚያ ወጥታ ወይም ተነጥቃ አይደለም እስራኤላውያን በግብፅ እየኖሩ ከመቅሰፍት እንደተጠበቁ)። 

5. መጽሐፍ ቅዱስ ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት በፊት መፈጸም ያለባቸው ትንቢቶች እንዳሉ የሚያስተምር በመሆኑ፥ መነጠቅ ከታወቀው የፍዳ ዘመን ክንዋኔ በኋላ ይሆናል። 

6. ይህ ድህረ-ፍዳ ዘመን አመላካከት የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነበር። 

ማዕከላዊ የፍዳ ዘመን። የዚህ አመለካከት አቀንቃኞች ክርስቶስ ለሕዝቡ የሚመጣው በፍዳው ዘመን አጋማሽ ላይ ነው፤ ማለትም የፍዳ ዘመን ከጀመረ ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላና ሊያልቅም ሦስት ዓመት ተኩል ሲቀረው ነው፤ ያኔ ነው ክርስቶስ የሺህ ዓመቱን መንግሥት ለመመሥረት ከቅዱሳኑ ጋር የሚመጣው ይላሉ። 

የዚህ አመለካከት መከራከሪያ ነጥቦች፡- 

1. 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡52 ላይ የተጠቀሰው የመጨረሻ መለከት” በዮሐንስ ራእይ 11፡15 ላይ ከተጠቀሰው “ሰባተኛ መለከት” ጋር አንድ ነው፤ ይህም የተሰማው በፍጻሜው ዘመን መካከል ላይ ነው። 

2. እርግጥ ታላቁ የፍዳ ዘመን ከዳንኤል ሰባኛ ሳምንት ሱባኤ መጨረሻ የሳምንት አጋማሽ ሰለሆነ፥ ቤተ ክርስቲያን ከዚያ መከራ ነው የምትጠበቀው (ራእይ 11፡2፤ 12፡6)። 

3. የሁለቱ ምስክሮች ትንሣኤም የቤተ ክርስቲያን መነጠቅ ያመለክታል፤ የነሱም ትንሣኤ የሚከናወነው በመከራው ዘመን አጋማሽ ላይ ነው (ራእይ 11፡11)። 

ከፈል መነጠቅ። ይህ አመለካከት ያላቸው ወገኖች የሚያስተምሩት ደግሞ፥ ተገቢ የሆኑ አማኞች ብቻ የፍዳው ዘመን ከመጀመሩ በፊት ይነጠቃሉ፤ ሌሎች ግን ቁጣውን በትዕግሥት እንዲያልፉ ይተዋሉ ማለት ነው። በምድርም ለሚቀሩት ይህ ጊዜ የመጥራት ጊዜ ይሆንላቸዋል። አሳቡ የተወሰደው እንደ ዕብራውያን 9፡28 ካለው ጥቅስ ሲሆን፥ በዚህ ጥቅስ መሠረት ጌታን ለመገናኘት ቅድመ ዝግጅት ማስፈለጉ ግዴታ ይሆናል። ምንም እንኳን በዚህ አመለካከት መሠረት መልካም ሥራ አንድን ሰው ለመነጠቅ ያበቃዋል ሲባልም፥ ምን ያህል ጥሩ ሥራ ነው የሚያስፈልገው? ለሚለው ጥያቄ ግን የአሳቡ ደጋፊዎች መልስ አይሰጡም። እነዚህ ሰዎች በዚህ ሳይወሰኑ በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፡51 ላይ “ሁላችንም እንለወጣለን” የሚለውን ግልጥ ቃል ወደ ጎን ይሉታል። 

ቅድመ-ፍዳ ዘመን። ይህ አመለካከት ያላቸው ወገኖች ቤተ ክርስቲያን ሰባቱ የፍዳ ዘመን ከመጀመሩ በፊት ትነጠቃለች በማለት ያስተምራሉ። ከሰባቱ ዓመት በኋላ ማለት፥ የፍዳው ዘመን እንዳለቀ፣ የሺህ ዓመቱን መንግሥት ለመመሥረት ጌታ ከሕዝቡ ጋር ይመጣል ብለው ሲያምኑ፥ አሳባቸውን ለማጠናከር የሚከተሉትን ነጥቦች ይጠቅሳሉ። 

1. የፍዳው ዘመን “ታላቁ የቁጣ ቀን” (ራእይ 6፡17) ተብሎ ተጠርቷ፡፡ ከሚመጣው ቁጣ የሚታደጋቸው አዳኝ እንዳላቸው ያወቁ አማኞች (1ኛ ተሰ. 1፡10) እግዚአብሔር ለቁጣ እንዳልመረጣቸው እርግጠኞች ይሆናሉ (1ኛ ተሰ. 5፡9)። በዚህ ጥቅስ ምንባብ ጳውሎስ በጌታ ቀን ወይም በፍዳው ዘመን መጀመሪያ ስለሚኖረው ነገር ነው የሚናገረው (1ኛ ተሰ. 5፡2)፤ ከርስቲያኖች በዚያን ጊዜ እንደማይገኙና የቁጣው ዘመን ከመጀመሩ በፊት እንደሚወሰዱ ግልጥ አድርጓል። ይህ እውን የሚሆነው ግን መነጠቅ ከፍዳው በፊት የተፈጸመ እንደሆነ ብቻ መሆኑን በማስታወስ ነው። 

2. ከሞት የተነሣው ጌታ በፊላደልፊያ ላለችው ቤተ ክርስቲያን “በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ” (ራእይ 3፡10) በማለት ቃል ገብቷል። የቅድመ-ፍዳ ዘመን አመለካከት ተከታዮች ይሆን የተስፋ ቃል ለሌሎች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ከተጻፉት የተስፋ ደብዳቤዎች ጋር ያዛምዱታል (እርግጥ ይህን እውነት የሚያዩት ክርስቶስ ሲመጣ የሚኖሩት አማኞች ብቻ ቢሆኑም)። በመቀጠልም “የፈተና ሰዓት” የተባለው ጊዚ ዓለምን በሙሉ የሚያዳርስ ስለሆነ የፍዳን ዘመን ያመለክታል ይላሉ። የድህረ-ፍዳ ዘመን አመለካከት ያላቸው ወገኖች ይህ ተስፋ (ከዳቶ ዘመን ጋርም ያዛምዱታል) ክርስቲያኖች ምንም እንኳን በፈተናው ዘመን ውስጥ መኖር ቢኖርባቸውም ከፍዳው ዘምን ፍርድ የሚጠበቁበት ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ተስፋው ከችግሩ ሳይሆን ከችግር ጊዚው እንደሚጠበቁ ነው የሚያረጋግጠው። ይህ ክርስቲያኖች በዚያን ጊዜ ፍጹም ይወገዳሉ ማለት ይመስላል። “ከ..እጠብቅሃለሁ” የሚል ቃል በአዲሰ ኪዳን ሁለት ጊዜ ብቻ የተጠቀሰ ሲሆን፥ እዚህ ቦታና ዮሐንስ 17፡15 ላይ ይገኛል። በሁለተኛው ጥቅስ፥ ጌታ አማኞች ከክፉ እንዲጠበቁ ጸልዮላቸዋል። ይህም ጸሎት ከጨለማው ሥልጣን ነጻ አውጥቶ ወደ ውድ ልጁ መንግሥት አስገብቶናል (ቈላ. 1፡13)። አንድ ነገር በሚከናወንበት አካባቢ ተገኝቶ ከዚያ ጊዜ ነጻ መሆን ይቻላል ተብሎ አይታሰብም። ስለሆነም በመጨረሻው ዘመን በዓለም ሁሉ ከሚደርሰው ዳ ለመዳን የግድ ከምድር መወሰድን ይጠይቃል። 

እንግዲህ ይህ የቅድመ-ፍዳ ዘመን አመለካከት ተከታዮች አሳብ ትክክል ከሆነ፥ የተስፋ ቃል ሌላ ትርጉም ያሻዋል ማለት ነው። ምክንያቱም በፍዳው ዘመን የሚኖሩ ቅዱሳን ከመከራና ስደቱ ተካፋዮች ከመሆናቸውም ባሻገር ብዙዎች ስለ እምነታቸው ይሞታሉ (ራእይ 6፡9-11፥ 7፡9-14፥ 14፡1-3፣ 15፡1-3)። 

3. 2ኛ ተሰሎንቄ 2፡1-12 ላይ ጠቃሚ የሆነ የቅደም ተከተሎች ዝርዝር ሰፍሯል። ጳውሎስ አንድ ነገር ሳይሆን የጌታ ቀን አይመጣም የፍዳው ዘመን አይጀመርም ይላል (ቁ. 3)። በመጀመሪያ የዓመፅ ሰው ይገለጣል (ቁ. 3)። ነገር ግን የዓመፅ ሰው አንድ ነገር (ቁ.6) እና አንድ ሰው (ቁ.7) ከመንገዱ እስኪወገዱ ድረስ ሊወገድ አይችልም። ከዚያ በኋላ ብቻ ነው የዓመፅ ሰው ለክፉ ሥራ የሚገለጠው። ከልካዩም ምንም ይሁን ማን፥ የዓመፃው ሰው ያን ጊዜ በሙላት እንዳይንቀሳቀስ ያግደዋል። ተሰሎንቄያውያን ግን ያ ከልካይ ማን፥ ወይም ምን እንደሆነ ያውቁ ነበር። ከዚህም በላይ የዓመጻው ሰው በሰይጣን ኃይል የተሞላ በመሆኑ፥ እርሱን የሚያግደው ከልካይ ከሰይጣን የበረታ መሆን አለበት። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ይህ ከልካይ በጳውሎስ ዘመን የገነነውና የተራቀቁ የሕግ ሥርዓቶች የነበሩት የሮም መንግሥት ነው ይላሉ። ነገር ግን ከሰይጣን በኃይል የበለጠ ወይም የሚበልጥ መንግሥት አለ? እግዚአብሔር ብቻ ነው ኃይለኛው፤ ስለሆነም ዓመጻን ከሚከላከለው ነገር ጀርባ፥ የኃይል ሁሉ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር መኖር አለበት። እግዚአብሔር ክፋትን ለማስወገድ ያለጥርጥር በመልካም መንግሥታት፥ በተመረጡ መላእክት፣ በመጽሐፍ ቅዱስና በተለያዩ መንገዶች ይጠቀማል። ነገር ግን ከዚህ ሁሉ በስተጀርባ የርሱ ኃይል ብቻ መኖር አለበት። ብዙ የቅድመ-ፍዳ ዘመን ደጋፊዎች ስለ ዓመጻ ከልካዩ ሲናገሩ፥ ያን የሚሠራው ከሥላሴዎች አንዱ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ነው ይላሉ (ዘፍጥ. 6፡3)። ይሁን እንጂ በዚህ ክፍል ጳውሎስ የሚያመለክተው በትክክል ስለ መንፈስ ቅዱስ ነው ማለት አይቻልም። ያም ሆነ ይህ ሁኔታዎችን በትክክል ለመግለጥ መቻል አለመቻላችን የቅድመ-ፍዳ ዘመን አመለካከት ደጋፊዎችን የዚህ ምንባብ ክርክር አይለውጠውም። ክርክሩ እንዲህ ነው፡- 

የዓመጻው ከልካይ እግዚአብሔር፥ ዋና መሳሪያውም መኖሪያው የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ናት (ኤፌ. 4፡6፤ ገላ. 2፡20፤ 1ኛ ቆሮ. 6፡19 ይመልከቱ)። ይህችን ጌታ የሚኖርባትንና መለኮታዊ ኃይል የሚሰጣትን ቤት ክርስቲያን “የገሃነም ደጆች አይቋቋማትም” (ማቴ. 16፡18) ሲል ራሱ ተናግሮላታል። ከልካዩ ደግሞ የዓመፅ ሰው ከመገለጡ በፊትና፥ የጌታ ቀን ከመጀመሩ በፊት ሊወገድ ይገባል። ግን ከልካዩ እግዚአብሔር ስለሆነና እርሱም በአማኞች ውስጥ ስለሚኖር፣ ወይ አማኞቹ በፍዳ-ዘመን ውስጥ እንዲያልፉ በምድር በተተዉበት ጊዜ እርሱ ከልባቸው መውጣት አለበት፤ አለዚያም እርሱ ከምድር በሚመጣበት ጊዜ አማኞች ሁሉ ከእርሱ ጋር መነጠቅ አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ አንድም ቦታ ላይ ክርስቲያኖችን እግዚአብሔር ይተዋቸዋል አይልም። ስለዚህ ያለው ብቸኛ አራጭ አማኞች የፍዳው ዘመን ከመጀመሩ በፊት ከዓለም ይወሰዳሉ የሚል ይሆናል። ይህ ማለት መንፈስ ቅዱስ በዚያን ዘመን አይሠራም ማለት አይደለም። መኖሪያው የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ብትወሰድም ይሠራል። ዓመጻ ከልካይ ኃይል ይወገዳል ማለት፥ እግዚአብሔር ወይም ሥራው በምድር አይኖርም ማለት አይደለም። ብዙዎች በፍዳው ዘመን ይዋጃሉ፥ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው (ራእይ 7፡14)። ስለዚህ ይህን ክፍል በአግባቡ ከተረጎምነው ቤተ ክርስቲያን ከፍዳው ለምን ቀድማ የምትነጠቅ መሆኗን ያረጋግጥልናል።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.