የወደፊቱ ፍርድ

ፍርድ አማኞች ሥራ ላይ 

ቤተ ክርስቲያን በመለውጥና በትንሣኤ ወደ ሰማይ ከተወሰደች በኋላ፥ እያንዳንዱ አማኝ በክርስቲያንነቱ ባከናወነው ሥራ መጠን ፍርድ ይሰጠዋል (1ኛ ቆሮ. 3፡11-15)። ፍርዱ ድነትን (ደኅነትን) እና የመንግሥተ ሰማያትን እርግጠኝነት የሚያመለከት ሳይሆን፣ ክርስቲያኑ መንግሥተ ሰማይ የሚገባው ከሽልማት ጋር፥ ወይም ያለ ሽልማት መሆኑን የሚመለከት ብቻ ይሆናል። አማኞች ፈተናውን ባለማለፋቸው ለስልክት ባይበቁም፥ ነፍሳቸው ግን እንደምትድን ጳውሎስ በጥቅሱ ውስጥ ግልጥ አድርጎታል (ቁ. 5)። እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ፥ ኃጢአቱ ይቅር የተባለለት ሰው እንዴት ለሥራው እንደገና በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ይቀርባል? የሚል ነው። ይቅርታ የመጽደቅን እርግጠኛነት ሲያሳይ፥ በሥራ መፈተኑ ግን ሽልማትን ያመለክታል። ከዚህ በኋላ ኅዘን ወይም ልቅሶ በመንግሥተ ሰማያት አይኖርም። ብዙ ጊዜ ሽልማቱ ምን እንደሚሆን ለማወቅ እንጓጓለን። መንግሥተ ሰማያት፣ መንግሥተ ሰማያት እስከሆነ ሽልማቱ ምን ልዩነት ያመጣል? በመጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ አልተሰጠም፤ ሽልማቶቹ ለክርስቲያን አገልግሎት ማነቃቂያ መሆናቸው ብቻ ነው የተገለጠው። ሽልማቱ ለምን ለምን አገልግሉት መሆኑ ግን ተጽፏል። ሰዎችን ወደ ክርስቶስ በማምጣት የደስታ አክሊል ይሰጣል (1ኛ ተሰ. 2፡19)፥ መገለጡን ለሚወዱ የጽድቅ አክሊል (2ኛ ጢሞ. 4:8)፥ ለጌታ ሲሉ መከራን ለሚታገሱ የሕይወት አክሊል (ያዕ. 1፡12)፥ እና በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ታማኝ ለሚሆኑ ሽማግሌዎች የከብር አክሊል ይሰጣቸዋል(1ኛ ጴጥ. 5፡4)። 

በፍዳው ዘመን ውስጥ የሚያልፉ አሕዛብ የሚጠብቃቸው ፍርድ 

አንዳንድ ሰዎች በፍዳው ዘመን በሕይወት የሚዘልቁ ሲሆን፥ እነርሱም የሺሁ ዓመት አገዛዝ ከመጀመሩ በፊት ይፈረድባቸዋል። የፍርድ ጊዜ መቼ መሆኑ ተጠቅሷል፡- “የሰው ልጅ በክብር በሚመጣበት ጊዜ” (ማቴ. 25፡31-46)። ፍርዱ በመሬት ላይ፥ ኢዮሳፍጥ ሸለቆ ውስጥ ይሆናል (ኢዩኤል 3፡2)። ይህ ሸለቆ ምናልባት በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ጊዜ በሚነሳ የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ በኢየሩሳሌም አካባቢ የሚፈጠር ይሆናል (ዘካ. 14፡4)። በብሉይ ኪዳን ምንባቦች ላይ “ጎይ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ትርጉሙም “ሕዝብ”፥ “አረመኔ” “መንግሥታት”፣ እና ብዙ ጊዜም “አይሁድ ያልሆነ” ማለት ነው። የአዲስ ኪዳን ምንባቦች ደግሞ “ኤትኖስ” የሚለውን የግሪክ ቃል ተጠቅመዋል። ይህም ብዙውን ጊዜ “አይሁድ ያልሆነ” በሚል ይተረጎማል። (ለምሳሌ ያህል ሮሜ 11፡11-12፥ 25ን ይመልከቱ።) ጻድቅ መንግሥት እስከሌለ ድረስ፥ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ፍርድ የግለሰቦች ፍርድ መሆን አለበት። ስለዚህ በዚህ ጥቅስ ላይ ቃሉ “አይሁድ ያልሆነ” በሚል ቢተረጎም የተሻለ ይሆናል። 

የእነዚህ አሕዛብ ፍርድ የሚጀምረው ጌታ “ወንድሞቼ” ለሚላቸው ወገኖች ምን እንዳደረጉላቸው በመጠየቅ ይሆናል (ማቴ. 25፡40)። ማንነታቸው የሚወሰነውም እነሱን ደረጃ በደረጃ በማስወገድ ይሆናል። ክርስቶስ ዳኛ ከሆነ፥ ቤተ ክርስቲያን ከፍዳው ዘመን በፊት ከተነጠቀች፥ የሚፈረድባቸውም አሕዛብ ከሆኑ፥ በፍዳው ዘመን የሚቀሩት ሌሎች ወገኖች እይሁዳውያን ብቻ ይሆናሉ (በሥጋ “ወንድሞቹ”)። በዚያ ዘመን አይሁዳውያን በታላቅ ስደት ውስጥ ያልፋሉ። መልካም የሚያደርግላቸው፥ ጓደኛ የሚሆናቸው ሁሉም መጥፎ ይገጥመዋል። ከዚህ የተነሳ በሰብአዊነት የተነሳሱ ሰዎች አይሁዳውያኑን ማብላት፥ ማልበስ፥ ወይም መጎብኘት አይችሉም። ይህን የሚያደርጉ በከባድ ጥርጣሬ ይታያሉ፤ ከዚያም አልፎ እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ይመጣባቸዋል። እነዚህን በጎ ድርጊቶች የሚፈጽም ሰው ካለ በዚያ ሕይወት አዲስ ለውጥ ለመኖሩ ማስረጃ ይሆናል። በሌላ አነጋገር እነዚህ አሕዛብ ለአይሁድና ለክርስቶስ ወንድሞች የሚያደርጉት መልካም ሥራ፥ የዳግም መወለዳቸው ምልክት ነው። ዳግም በመወለዳቸው ይድናሉ፤ መልካምም ተግባራቸው የመወለዳቸው ማረጋገጫ ይሆናል። 

ሕይወታቸው ይህን የአዲስ ልደት ማረጋገጫ የሚያሳይ ሁሉ የመንግሥቱ ዜጎች ይሆናሉ (ማቴ. 25፡34)። ሥራቸው ለዘላለም ሕይወት የማያበቃቸው ደግሞ፥ ወደ እሳት ባሕር ይጣላሉ (ቁ. 41)። የመንግሥቱ ዜጎች የሚሆኑት ወደ መንግሥቱ የሚገቡት በሥጋዊ አካላቸው ስለሆነ ይጋባሉ፥ ይዋለዳሉ፥ በሺህ ዓመት መንግሥት ጊዜ ምድርን የሚሞሏት እነርሱ ናቸው። 

የመከራውን ዘመን አልፈው የወጡ አይሁዳውያን ፍርድ 

የመከራውን ዘመን አልፈው የወጡ አይሁዳውያንም ይፈረድባቸዋል (ሕዝ. 20፡34-38)። ጌታም ይህ ፍርድ እርሱ ከተመለሰ በኋላ እንደሚሆን በምሳሌ ተናግሯል (ማቴ. 25፡14-30)። ያልዳኑ አይሁዳውያንን ከሺህ ዓመቱ መንግሥትና ከዘላለም ሕይወት ማስወገድ ይሆናል፤ ማንኛውም ዓመፀኛ የሺህ ዓመቱ ተሳታፊ አይሆንምና (ሕዝ. 20፡37፤ ማቴ. 25፡30)። 

የወደቁ መላእክት ፍርድ 

ሰይጣንም በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ጊዜ ይፈረድበታል። በሺህ ዓመቱ አገዛዝ ወቅት፥ በጥልቁ ውስጥ በእሥር ቆይቶ በመጨረሻ ለጥቂት ጊዚ ዓመፅ ካካሄደ በኋላ፥ ለዘላለም ወደ እሳት ባሕር ይጣላል (ራእይ 20፡2-3፣ 7፥ 10)። መጀመሪያ በእግዚአብሔር ላይ ባመፀ ጊዜ የተከተሉት አጋንንትም ከሱ ጋር ይፈረድባቸዋል። ይህ ጊዜ ነው “ታላቁ ቀን” ተብሎ የሚጠራው (ይሁዳ 6)። ይህ ጊዚ ምናልባት በሺህ ዓመት ማብቂያ (የጌታ ቀን መጨረሻ) ሰይጣን ፍርዱን ለመጨረሻ የሚያገኝበት ይሆናል። አማኞችም ይህን ፍርድ በማስፈጸም ተግባር የሚሳተፉ ይመስላል (ኛ ቆሮ. 6፡3)። 

ያልዳኑ ሙታን ፍርድ (በነጩ ዙፋን ፊት) (ራእይ 20፡11-15) 

በሺህ ዓመቱ መጨረሻ የአሁኑ ከዋክብታማ ሰማይና ምድር ስለማይኖሩ፥ ህዋ ላይ ታላቅ ነጭ ዙፋን ይዘጋጃል። ከዚያ ላይ የሚቀመጠውም ክርስቶስ ይሆናል (ዮሐ. 5፡22)። የሚፈረድባቸው በዘመናት የሞቱ ኃጥአን ናቸው። የዳኑት ቀደም ሲል ከሞት ተነስተው ፍርድ ስላገኙ ያልዳኑት ብቻ ናቸው የቀሩት (ራእይ 20፡12)። 

ሕዝቦች የሚፈረድባቸው እንደ ሥራቸው ነው (ቁ. 12-13)። ወደ ፍርድ የገቡት ባለመዳናቸው ነውና፥ እዚያ እስከሆኑ ድረስ በሥራቸው ይፈርድባቸዋል። የሕይወት መጽሐፍ ሲከፈት፥ በዙፋኑ ፊት ከሚቆሙት ያልዳኑ ሰዎች የአንዱም ስም አይገኝም። አዳኙን አለመቀበላቸው ከሕይወት መጽሐፍ ውጭ አድርጓቸዋል። በሕይወታቸው ዘመን የሠሯቸው ክፉ ሥራዎች ዘላለማዊ ቅጣት እንደሚገባቸው ያረጋግጣሉ። 

ሆኖም እግዚአብሔር ለእነዚህ ሕዝቦች አንድ የመጨረሻ ዕድል በመስጠት ምሕረቱን ያሳየ ይመስላል። ምንም እንኳን ስማቸው በሕይወት መጽሐፉ ውስጥ ባይገኝም፥ በምድር ላይ በነበሩ ጊዜ የሠሩት ሥራ ወደ እሳት ባሕር የማያስጨምራቸው መሆኑን እንዲያሳዩ ዕድል ይሰጣቸዋል። ሁኔታው በገሃነም የተለያየ ደረጃ ያላቸው ቅጣቶች መኖራቸውን ያመለክታል (ሉቃስ 12፡47-48ን ይመልከቱ)። ለፍርድ የሚቀርቡ ሁሉ ተመሳሳይ ቅጣት ይጠብቃቸዋል፤ ያም ወደ እሳት ባሕር መጣል ነው። ይህ ሁለተኛ ሞት ሲባል፥ ለዘላለም ከእግዚአብሔር መለየትን ያመለክታል። ሞት (አካል የሚነጥቀው)፥ እና ሲኦል (ነፍስ የሚነጥቀው)፥ አገልግሎታቸው ስለሚያበቃ ወደ እሳት ባሕር ይጣላሉ።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: