ቅዱስ ቁርባን (የጌታ እራት) ማለት ምን ማለት ነው?

የጌታን እራት ምንነት አለመገንዘብና ለህተት በሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮር ቀላል ነው። ሰቀላሉ የጌታ እራት ኢየሱስ በአቀደው መሠረት እንዲክበር፥ በዘመናት ሁሉ ውስጥ ለሚኖሩት ተከታዮቹ ኢየሱስ ለምን እንደሰጠ ልንገነዘብ ያስፈልጋል። ኢየሱስ የጌታን እራት አከባበር ሥርዓት ሲጀምር ምን ማለቱ እንደሆነ ከመግለፃችን በፊት፥ ቅዱስ ቁርባን ምን እንዳልሆነ በማብራራት እንጀምር። 

ሀ. የጌታ እራት የሚከተሉትን ነገሮች ማለት አይደለም 

1 የጌታን እራት መቀበል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላሉ ሁሉም አይደለም። ኢየሱስን እንደ ግል መድኃኒታቸው አድርገው ያልተቀበሉ፥ ወይም በኢየሱስ ፊት የቅድስና ሕይወትን ለመኖር ፈቃደኛ ያልሆኑ የጌታን እራት መውሰድ የለባቸውም። ጳውሎስ እንዳለው ሕይወታቸውን በወንጌል ትምህርት ለመምራት የማይፈልጉ ሥጋውንና ደሙን ለመውሰድ ብቁ አይደሉም (1ኛ ቆሮ. 11፡27)። 

2. የጌታ እራት ምስጢራዊ ስብሰባ እንዲሆን የታቀደ አይደለም። ምስጢራዊ የሆነ ነገር እንደምንሠራ ዓይነት ስሮችንና መስኮቶችን የምንዘጋበት ምክንያት የለም። ጳውሎስ እንደሚለው የጌታን እራት መውሰድ ወንጌልን የማብሰሪያ መንገድ ነው (1ኛ ቆሮ. 11፡26)። ወንጌልን ለማያምኑ ሰዎች ወይም ላልገባቸው ልጆቻችን የምናውጅበት አንዱ መንገድ የጌታን እራት በምንወስድበትና ትርጉሙንም በምንገልጽበት ጊዜ እንዲገኙ (እንዲያዩ) ስመፍቀድ ነው። 

3. የጌታ እራት እጅግ ቅዱሳን ሆነው ለሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ አይደለም፡፡ ኢየሱስ የመጀመሪያውን የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ሲፈጽም ከደቀ መዛሙርት ማናቸውም በጣም ቅዱስ አልነበሩም። ጴጥሮስና ሌሎችም ደቀ መዛሙርት ወዲያውኑ ኢየሱስን ክደውታል። ስለሆነም ኢየሱስ ተከታዮቹ የጌታን እራት ለመካፈል የሚያሟሉት የተለየ የቅድስና ቅድመ–ሁኔታን ትኩረቱ አላደረገም። 

4. የጌታ እራት የአንድ ቤተ እምነት የአባልነት ምልክት እንዲሆን የሚሰጥ አይደለም። ይልቁንም፥ ለሁሉም እውነተኛ አማኞች የተሰጠ መብት ነው እንጂ። የጌታ እራት አማኞችን ከመከፋፈል ይልቅ፥ የሁሉም አማኞች የጋራ መሠረት መሆን አለበት። ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው፥ ሁሉም አማኛች ኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞቱ የደኅንነታቸው መንገድ እንደሆነ ማመናቸውን ለሕዝብ በግልጽ (በይፋ) የሚመሰክሩበት ነው። 

5. የጌታ እራት ለኃጢአት ይቅርታን የሚያስገኝ የቅዳሴ ሥርዓት አይደለም። አንዳንድ ቤተ ክርስቲያናት ሰው ከመሞቱ በፊት የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ከተካፈለ (ሥጋ-ወደሙ ከወሰደ) ይድናል ብለው የሚያስተምሩ አሉ። ነገር ግን አዲስ ኪዳን በግልጽ እንደሚያስተምረው የሚያድነን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን የግል እምነት እንጂ ቅዱስ ቁርባንን መውሰድ አይደለም (ኤፌ. 2፡8)። 

6. የጌታን እራት ሥርዓት ስንፈጽም ማተኮር የሚገባን በኢየሱስ አካላዊ ሕመም ላይ አይደለም። አዎን፥ ኢየሱስ ስለ እኛ በመስቀል ላይ እጅግ በጣም ተሰቃይቷል። የመስቀል ላይ ሞት የጥንት ሰዎች የፈጠሩት አሰቃቂ ሞት ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ አካላዊ ሕመም ላይ ትኩረት አያደርግም። ይልቁንም ትኩረቱ እግዚአብሔር አባት ለእኛ ካለው ፍቅር የተነሣ ልጁ ኢየሱስ ስለ ኃጢአታችን መሥዋዕት እንዲሆን በመላኩ ላይ ነው። የእግዚአብሔር ቃል የሚያተኩረው ለኃጢአታችን ሊሞት በመጣውና የእግዚአብሔር ልጆች ባደረገን በኢየሱስ ጸጋና ምህረት ላይ ነው። እኛም የጌታን እራት ስንወስድ ያ ሞት የሚሰጠንን ጥቅም ሁሉ እንደገና ማስታወስ እንድንችል ነው። 

7. ዋናው ስሜት የምስጋና እንጂ የኀዘን አይደለም። በሕይወታችን ስላለው ኃጢአት ለረጅም ጊዜ እንድናለቅስና እንድንፀፀት የሚያደርጉን አንዳንድ የፕሮግራም መሪዎች አሉ። ሕይወታችንን መመርመርና ኃጢአታችንንም መናዘዝ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ትኩረቱ በነፃነታችን እንጂ በኃጢአታችን ላይ አይደለም። የጌታን እራት ስንወስድ ልባችን ከእግዚአብሔርና ከኢየሱስ ፍቅር፥ ምህረትና ጸጋ የተነሣ በምሥጋና መሞላት ይገባዋል። ጊዜው የአምልኮና የውዳሴ ጊዜ ነው። 

ለ. የጌታ እራት ምን ማለት እንደሆነ 

ኢየሱስ የጌታን እራት ለምን ሰጠን? የጌታ እራት ምሳሌያዊ ሥርዓተ ቅዳሴ ነው። ውጪያዊው እንጀራውን የመብላትና ወይኑን የመጠጣት ተግባር ጥልቅ መንፈሳዊ እውነታዎችን ያመለክታሉ። የጌታን እራት ስንወስድ ተስናከብር/ ብዙ አስፈላጊ እውነቶችን ምሳሌያዊ እያደረግን ነው። 

1. ኢየሱስ የቅዱስ ቁርባንን ሥርዓት የሰጠን የምንቀበላቸው በረከቶች ሁሉ ኢየሱስ በእኛ ምትክ በመሞቱ ምክንያት የተገኙ መሆናቸውን ዘወትር እንዲያሳስበን ነው። በኑሮ ስመባከን ወይም በአንዳንድ አስተምህሮዎች በመሳት፥ የኢየሱስን ሞትና ምንነቱን እንዘነጋለን። የጌታን እራት ስንወስድ መዘንጋት የሌለብን የመንፈሳዊ ሕይወታችን መሠረት የሚያርፈው በምትካችን በሞተው ኢየሱስ ላይ መሆኑን ነው። 

2. ኢየሱስ ለተከታዮቹ የጌታን እራት የሰጠው በመታሰቢያነት እንዲያገለግል ነው። ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች እንዲካፈሉ የሚጠበቅባቸው ወይም የሚፈቀድላቸው ሥርዐት አይደለም። ኢየሱስ የጌታን እራት ያስጀመረው ትክክለኛ ላልሆነ ዓላማ ይከተለው በነበረው ሕዝብ ሳይሆን፥ በቅርብ በተከተሉት ደቀ መዛሙርት ነበር። ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቢሆንም እንኳን ይሁዳ የጌታን እራት እንዲወስድ አልተፈቀደለትም። የወንጌል ታሪክ እንደሚያመለክተው የጌታ እራት ሥርዓት የተካሄደው የአስቆሮቱ ይሁዳ ከወጣ በኋላ ነበር። ይህ የሚያሳስበው የጌታን እራት መውሰድ የሚኖርባቸው ክርስቲያን ነን ብለው የሚናገሩ ላይሆኑ፥ ለኢየሱስ በመገዛትና በመታዘዝ የሚኖሩ መሆናቸውን ነው። 

3. የጌታን እራት መውሰድ የኢየሱስን ሞት ምሳሌያዊነት ያመለከታል፡፡ እንጀራው ሲቆረስ፥ በመስቀል ላይ የሞተውን የኢየሱስን አካል በምሳሌያዊነት መቆረስ ያመለክታል። ጽዋው ሲቀዳም ኢየሱስ ደሙን ለእኛ እንዴት እንዳፈሰሰ ያመለክታል። የዚህ በዓል ምሳሌያዊነት ኢየሱስ ለእኛ መሞቱን ለሁሉም ሰዎች ማስተማር ነው። 

4. የጌታን እራት ስንወስድ ወደ ኋላ መለስ ብለን የምንመለከተው፤ በምትካችን፥ የደኅንነታችንና የመንፈሳዊ በረከታችንም መሠረት ወደሆነው ወደ ኢየሱስ የምትክነት ሞት ነው። በመካከላችን ካለው የትንሣኤ ጌታ ጋር ዘላቂ ግንኙነት እንዳለን ስንገልጽ፥ የምናተኩረው በአሁኑ ሕይወታችን ላይ ነው። ጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ወደፊት መመለስ ደግሞ በጉጉት ስንጠባበቅ፥ በማናየው መልኩ አዳኛችንን አንቀርበውም። ነገር ግን ፊት ለፊት ከእርሱ ጋር ኅብረት እናደርጋለን። 

5. የጌታን እራት መውሰዳችን ምን እንደምናምን የሚገልጥ ነው። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለ ሁላችን መሞቱን ማመናችን በቤተ ክርስቲያን ባሉት ሁሉ ፊት የምንፈጽመው ግልጽ ምስክርነታችን ነው። ሌሎች ብዙ ኃይማኖቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ቤተሰቦቻችንና ጓደኛቻችን ኢየሱስ ስለ እነርሱ ብሎ በመስቀል ላይ መሞቱን ላያምኑ ይችላሉ። ነገር ግን እኛ የጌታ እራትን ልንወስድ ለደኅንነታችን ኢየሱስን በግላችን እንዳመንን መናገራችን ነው። ጳውሎስ ይህን «ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና» ይለዋል (1ኛ ቆሮ. 11፡26)። የጌታን እራት ስንወስድ፥ ምሳሌ የምናደርገው ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤታችንና ወደ ጎረቤቶቻችን ተመልሰን ክርስቶስ ባስቀመጠን ቦታ ሁሉ፥ ክርስቶስ ያደረገልንን በግልጽ መመስከርን ነው። 

6. የጌታን እራት ስንበላ በግል ስኢየሱስ ሞት ውጤት ተካፋይ እንደሆንን ማሳየታችን ነው። እርሱ የሞተው ለዓለም ብቻ አይደለም። ይልቁንም፥ ኢየሱስ ለእኔ ኃጢአት ሞቷል እያልን ነው። በእርሱ ሞት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት የማድረግ ዕድል አግኝቻለሁ። የጌታን እራት ስንወስድ፥ እኛ ኃጢአተኛና የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍርድ የሚገባን መሆኑን እያረጋገጥን ነው። ነገር ግን ስንበላ የዘላለም ሕይወትን ሊያመጣልን የሚችለው በእኛ ምትክ የሞተው ኢየሱስ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ መሆን አለበት። እርሱ ሲሞት፥ በኃጢአት ምክንያት ያለብኝን የሞት እዳ ከፍሎልኛል። አሁን እኔ በኢየሱስ ሞት ምህረት አግኝቼአለሁ፥ ድኛለሁ፥ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኛለሁ፥ በመንግሥተ ሰማይም የዘላለማዊነት ተስፋ ተገብቶልኛል። 

7 ከሌሎች አማኞች ጋር በአንድነት መብላታችን በክርስቶስ አንድ አካል የመሆናችን ምሳሌ ነው። እኛ አንድ አካል፥ ያውም የክርስቶስ አካል ነን (1ኛ ቆሮ. 19፡7፥ 12፡12-13)። በአስተምህሮዎች ጉዳይ ላይ ጥቃቅን ልዩነቶች ሊኖሩን ይችላሉ። አንዳንዴም ላንስማማ እንችላለን። ነገር ግን የምንስማማበት አንድ ነገር አለ። የኢየሱስ በእኛ ምትክ መሞት በእምነታችን ውስጥ እጅግ አስፈላጊው እውነት ነው። በኢየሱስ ሞትም ያለን እምነት አንድ አካል እንድንሆን ያጣምረናል። የጌታን እራት ስንወስድ፥ የኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞት አንድ ሊያደርገን እንደሚገባ ኢየሱስ እየነገረን ነው። ልክ የመጀመሪዎቹ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ሁላቸውም ከእንጀራውና ከወይኑ እንዲበሉ እንደነገራቸው፥ እንዲሁ ሁሉም እውነተኛ አማኞች ጥቃቅን ልዩነቶቻቸውን አስወግደው ትኩረታቸውን አስፈላጊ በሆነው ጉዳይ ላይ እንዲያደርጉ ያስፈልጋል። እኛ ሁላችን የእግዚአብሔር ክብር የጎደለን ኃጢአተኞች እንደሆንን ማስታወስ አለብን። ነገር ግን እንደ አማኞች ይቅርታ ተደርጎልን እነዚያ ሰደሎች አይታሰቡብንም። ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች ነን። ይህ ሁሉ የሆነው በእኛ ፈንታ በመስቀል ላይ ከሞተው ከኢየሱስ የተነሣ ነው። 

8. የጌታ እራት ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለ እኛ መሞቱን የሚያንጸባርቅ እምነት እንዳለን በሚያሳይ መልኩ እየኖርን መሆኑን ለማረጋገጥ ሕይወታችንን ለመመርመር ተደጋጋሚ ዕድል ይሰጠናል። ጳውሎስ እንዳለው፥ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት፥ በዋጋ ገዝቶናል (1ኛ ቆሮ. 6፡20፥ 7፡23)። በሕይወታችን ላይ የፈለግነውን ለማድረግ ምንም መብት የለንም። ይልቁንም፥ የምንኖረው ኑሮ እግዚአብሔርን በመታዘዝና በዋጋ ለገዛን ለኢየሱስ ክብር እንዲሆን ያስፈልጋል። 

9. ኢየሱስ የመንፈሳዊ ሕይወታችን ምንጭ ስለመሆኑ በዚህ ምሳሌ እናረጋግጣለን። እንጀራ ለሰውነት ክፍሎቻችን ምግብ እንደሚሆን ሁሉ ዘላቂ መንፈሳዊ ምግብ የሚሰጠን ኢየሱስ ነው (ዮሐ 6፡53-57)። ስንበላ መንፈሳዊ ሕይወታችን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ ጥንካሬን እንዲሰጠን ከፈቀድንለት ከኢየሱስ ጋር ባለን ዘላቂ ግንኙነት ላይ የተደገፈ መሆኑን እየገለጥን ነው ( ዮሐ 15)። 

10. የጌታን እራት ስንበላ፥ ኢየሱስ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያረጋግጥልናል። ከእርሱ ጋር በግል ኅብረት ወደምናደርግበት ምግብ ይጋብዘናል። ልክ ጓደኞቻችን ወደ ቤታችን መጥተው አብረው እንዲመገቡ በመጋበዝ በኅብረታችን እንደምንደሰት ሁሉ፥ የጌታ እራት ከእርሱ ጋር ሆነን የምንበላው የኢየሱስ ግብዣ ነው። 

ምንጭ፡- “የጌታ እራት”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ ተሾመ ነጋሽ የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.