አላግባብ የጌታን እራት ስለመውሰድ የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎች

በ1ኛ ቆሮ.11፡27-32 ጳውሎስ አማኞች «ሳይገባቸው» የጌታን እራት እንዳይወስዱ በጥብቅ ያስጠነቅቃል። «ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት።» አላገባብ የጌታን እራት መውሰድ የሕመምን ቅጣት ወይም ሞትን በአማኞች ላይ ሊያመጣ እንደሚችል ተናግሯል። ጳውሎስ ምን ለማለት እንደፈለገ መረዳት አስፈላጊ ነው። በአማርኛ ‘ሳይገባው’ የሚለው ቃል ሦስት ነገሮችን ማለት ሊሆን ይችላል። አንደኛ፥ «አንድን ነገር አለመረዳት» ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አንዳንዶች በስህተት እንደሚያስቡት ጳውሎስ በዚህ ክፍል የሚናገረው የጌታ እራትን ምሳሌነት ስለመረዳት ነው። የጌታ እራትን መውሰድ ምን ማለት እንደሆነ መረዳት ተገቢ ነው። ጳውሎስ ግን በደንብ ምንነቱን ሳይረዱ የጌታን እራት መውሰድ ፍርድን ያስከትላል ማለቱ አይደለም። ሁለተኛ፥ ወደ አንድ ቦታ ውስጥ ሳይገባ እንደ ማለት ሊሆን ይችላል። እንግዲህ ጳውሎስ እንደሚለው ችግሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥም ይሁን ወይም አንድ የቤተ ክርስቲያን አባል ሳይሆኑ የጌታን እራት መብላቱ ላይ አይደለም። ጳውሎስ ይህንንም ማለቱ አይደለም። ይልቁንም፥ ሦስተኛውን የዚህን ቃል ትርጉም ነው የወሰደው። ጳውሎስ ያለው የጌታን ሥጋና ደም ለመብላት ብቁ ሳንሆን ወይም የጌታን ሞት ምንነት በማያንፀባርቅ (በማይገልፅ) መልኩ ላለመውሰድ ጥንቃቄ የማድረግ ብቃትን ነው። 

እንግዲህ ክርስቲያኖች ሳይገባቸው የጌታን እራት የሚበሉባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? በመሠረቱ ጳውሎስ እንደሚለው በማናቸውም ጊዜ የምንኖረው ኑሮ ስለ ኢየሱስ ሥጋና ደም ምሳሌነት ያለንን እምነት ካላንፀባረቀ፥ ሳይገባን የጌታን እራት ወስደናል ማለት ነው። ስቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በአማኞች መካክል መከፋፈል ነበረ። በሃብታምና በድኃ መካከል እኩልነት አልነበረም። ይህም የጌታን እራት በሚወስዱበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር ይታይ ነበር። (ማስታወሻ፡ በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ የጌታን እራት መውሰድ ትንሽ የእንጀራ (የኅብስት) ቁራሽ መብላት ወይም ትንሽ ወይን መጠጣት ብቻ አልነበረም። ይልቁንም፥ በአምልኮው ፕሮግራም መጨረሻ ላይ ከየቤታቸው ምግብ ያመጡት አማኞች ሁሉ ማዕዱን በአንድነት ይመገቡ ነበር። ይህንንም ምግብ ‘የፍቅር ግብዣ’ ብለውታል። በማዕዱ መጨረሻም፥ ቅዱስ ቁርባንን በጋራ ይወስዳሉ። የጌታ እራት በኢየሱስ ሞት የተመሠረተ የፍቅርና የአንድነት መግለጫ ነበር።) የዚህ ፍቅር መጓደል ስቆሮንቶስ አማኛች መካከል አንድነት የፈጠረውን የኢየሱስን ሞት እውነት የመስደብ ያህል ነበር። ምንም ዓይነት ዘር፥ ፆታ፥ ብሔር ወይም ነገድ ወይም ምንም ዓይነት ቤተ እምነት ይሁን ሰዎች ኢየሱስ በመስቀል ላይ እንደሞተላቸው ካመኑ፥ የኢየሱስ አካል ክፍል ናቸው (1ኛ ቆሮ. 12፡18፥ ገላ. 3፡26-29)። ሁላችንም በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኞችና የዘላለም ሞት የሚገባን ነን። እያንዳንዳችን የዳንነው በተመሳሳይ መንገድ እምነታችንን ስለ እኛ ኃጢአት መሥዋዕት በሆነው በኢየሱስ ላይ ስማድረግ ነው። ሀብታምም ሆንን ድኃ፥ የተማርን ሆንን ያልተማርን፥ በከተማ የምንኖር ሆንን በገጠር፥ አማራ እንሁን ወይም ኦርሞ፥ ጥቁር ሆንን ነጭ፥ ወንድ ወይም ሴት፥ እኛ ሁላችንም አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን። ሁላችንም የአንዱ የኢየሱስ አካል ክፍል ነን። በቤተ ክርስቲያን አማኞች መካከል ያልተፈቱ ችግሮች እያሉ አማኞች የጌታን እራት ከወሰዱ፥ አማኞቹ ከቅዱስ ቁርባን ዓላማዎች ዋንኛውን አላሟሉም ማለት ነው። ይህም ዓላማ አማኞች ሁሉ በክርስቶስ ሞት አንድ መሆናችውን የሚገልጽ ነው። ስለዚህ ግብዝነት የእግዚአብሔርን ፍርድ አመጣባቸው። ይህም በዚህ ዘመን ለምንኖር ክርስቲያኖች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ነው። በቤተ ክርስቲያናችንና በቤተ እምነቶች አብዛኛውን ጊዜ መከፋፈል አለ። በዚህ የፍቅር ጉድለት የጌታን እራት ስንወስድ የምናምነውን መዘበቻ እንደማድረግ ይቆጠራል። የጌታን እራት ያለ አግባብ በመውሰድ ከእግዚአብሔር ቅጣት ሥር እንዳንወድቅ መጠንቀቅ ይገባናል። 

ደግሞ በሕይወታችን ምን ጊዜም ያልተናዘዝንበት የማያቋርጥ ኃጢአት ካለ፥ የጌታን እራት ሳይገባን ወሰድን ማለት ነው። በዝሙት ብንኖር እና ይህንንም የማንናዘዝና አኗኗራችንን የማንቀይር ከሆነ፥ የጌታን እራት ስንበላ የጌታን እራት ንቀነው፥ በማይገባ መልኩ እየወሰድን ነን። ወይም ገንዘብ ሰርቀን ካልተናዘዝንና ካልመለስን፥ ወይንም እግዚአብሔር አንድ ነገር እንድናደርግ ጠይቆን እምቢ ካልን የጌታን እራት ሳይገባን በላን ማለት ነው። 

ጳውሎስ እምነታችንን የሚቃረኑ ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ መኖር አለመኖራቸውን እራሳችንን እንድንመረምር የሚናገርበት ምክንያት ኃጢአታችንን ላንናዘዝና በመካከላችን ያለውን መከፋፈል ሳናስወግድ የጌታን እራት የምንወስድ ከሆነ፥ የጌታን ሞት ትርጉም ስለሚቃወም ነው። በሕይወታችን ጌታችን ኢየሱስ የሚፈልገውን ነገር ለመፈጸም ግድ የለንም እያልን ነው። ሕይወታችንን እርሱ በሚፈልገው መንገድ ሳይሆን፥ በእኛ ምርጫ እንመራለን ማለታችንም ነው። ሞቱን ስላስከተለው ኃጢአታችንም ቢሆን ምንም ግድ እንደሌለን መግለፃችን ነው። ኢየሱስ የሞተው እኛ ለፈጻምነው የዝሙት፥ የስርቆት፥ የሐሜት፥ የውሸት፥ የትዕቢት፥ የጥላቻ ኃጢአት ነው። ኃጢአታችንን የመናዘዝ ምንም ምልክት ሳናሳይ፥ በዚህ መንገድ ከኖርንና ለመለወጥም ፍላጎት ካላሳየን ለሞት ያደረሰው ኃጢአታችን መሆኑ ግድ አይለንም ማለት ነው። 

ነገር ግን የሰዎችን ኃጢአት ከመጠን በላይ ላለማጋነን መጠንቀቅ አለብን። ጳውሎስ ይህን ትምህርት የሰጠው፥ ከጌታ እራት ሰዎችን ለማራቅ ሳይሆን፥ ትርጉም ባለው መልኩ በአንድነት (በኅብረት) ማክበ ር እንዲችሉና ኃጢአታቸውን እንዲናዘዙ ለማበረታታት ነበር። ይልቁንም፥ በ1ኛ ዮሐ 1፡9 ያለውን ተስፋ ለአማኞች ማስታወስ አለብን። የጌታን እራት ሥርዓት ከመጀመራችን በፊት ባልተናዘዙበት ኃጢአት እራሳቸውን እንዲፈትኑ ለሕዝቡ ዕድል መስጠት አለብን። የኢየሱስ ደም እንዲያነፃቸው እነዚህን ኃጢአቶች እንዲናዘዙ መበረታታት ይገባቸዋል። እውነተኛ ኑዛዜ ሕይወታችንን እንዲለውጥ በዝሙት መኖርን ማቆም፥ የሰረቅነውን መመለስ፥ ወይንም ኅብረት ካቋረጥንበት ጋር ዕርቅ መሥርተን የምንኖርበት ቁርጠኝነት መሆኑን መገንዘብ ይገባቸዋል። ትክክለኛ ኑዛዜ ካለ፥ ግለሰቡ የጌታን እራት እንዲወስድ ሊፈቀድለት ይገባል። ይህ የኑዛዜ ጊዜ ከፍርድ ይልቅ፥ ይቅርታንና ከኀጢአት መንጻትን ወደሚያመጣው የኢየሱስን ሞትና ትንሣኤ ወደሚያደንቅ የመታደስ ሕይወት ሊመራ ይገባል። 

ምንጭ፡- “የጌታ እራት”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ ተሾመ ነጋሽ የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.