Site icon

«ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት»

ተመስገን ለአንድ ዓመት ያህል አማኝ ነበር። ለሃያ ዓመታት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባል ነበር። ነገር ግን ተመስገን ግልጽ የወንጌል ስብከትን ሲሰማ ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ መወለድ እውነተኛ የኢየሱስ ተከታይ እንደማያደርገው ተገንዝቧል። ኢየሱስን እንደ ግል አዳኙ ማመን ፈለገ። ከስድስት ወራት ትምህርት በኋላ ተመስገን ተጠሙቀ። በተጠመቀበት ዕለት ከሌሎች አማኞች ጋር የጌታን እራት (ቅዱስ ቁርባን) ለመቀበል ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገባ። እየበላም ሳለ የአሁኑ የጌታ እራት ሥርዓት ቀድሞ ከነበረው የጌታ እራት ሥርዓት ጋር ትልቅ ልዩነት እንዳለው ተገነዘበ። በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የጌታን እራት መቀበል ማለትም ቅዱስ ቁርባንን መውሰድ፥ የአምልኮ ሥርዓት ማዕከል ሲሆን፥ አፈጻጸሙም በየሳምንቱ በሚደረግ ውስብስብ ሥርዐት ነበር። ሰዎቹም የጌታን እራት በሚወስዱበት ጊዜ የክርስቶስን ሥጋና ደም እንደተቀበሉ አድርገው ያምናሉ። የጌታን እራት መብላቱ የኃጢአት ስርየት እንደሚያመጣላቸው ያምናሉ፥ ጠንካራ ስሜትም ይፈጥርላቸዋል። ነገር ግን አሁን ተመስገን በሚሳተፍበት ቤተ ክርስቲያን በተነጻጻሪነት ሲታይ የጌታ እራት ብዙም ትኩረት የማይሰጠው የአምልኮ ክፍል ነው። የሚካሄደውም በወር አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፥ ተሳታፊዎቹም የማኅበረ ምዕመናኑ ግማሽ ያህሉ ብቻ ነበሩ። ምንም እንኳን ሥርዓቱ ሞገስ ያለው ቢሆንም፥ አማኞቹ የክርስቶስን ሥጋና ደም የሚበሉ አይመስልም። ነገር ግን ሥርዓቱ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሠራላቸውን ሥራ እንዲያስታውሱ ረድቷቸዋል። ቤተ ክርስቲያንም የኢየሱስን ሞት ምሳሌያዊነት ብቻ የሚያመለክት መሆኑን ታስተምር ነበር። 

ተመስገን ግራ ተጋባ። «የጌታ እራት ዓላማው ምንድን ነው»? እንጀራው (ሕብስቱና ወይኑ ትክክለኛው የኢየሱስ ደምና አካል ነው ተብሎ ሲወሰድ የተለየ ተአምራዊ ነገር ይፈጸማል ወይ? መቀበሉስ የኃጢአትን ይቅርታ ያሰጣል ወይ? ሁሉም ክርስቲያኖች የጌታን እራት መቀበል (መብላት) አለባቸው ወይስ የቤተ ክርስቲያን አባላት ብቻ? የሥርዓቱ ጊዜስ የሐዘን ነው? ወይስ የደስታ?» በማለት ተገረመ። 

ብዙነሽ ያደገችው በወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን ነበር። የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኗም ምእመናን በወር አንድ ጊዜ ከእሁድ የአምልኮ ሥርዓት በኋላ በመቅረት የጌታን እራት መቀበል/መውሰድ ልምዳቸው ነበር። ሥጋና ደሙን ከመውሰድ በፊት ያለው ጊዜም እጅግ የተከበረ ነበር። መሪዎችም በኢየሱስ ስቃይ ላይ ትኩረት በመስጠት ይናገራሉ። ሰዎችም ስለ ኃጢአታቸው እንዲያለቅሱ ያበረታታሉ። ብዙነሽም አብዛኛውን ጊዜ የጌታ እራት ዓላማው ምንድን ነው በማለት ትገረም ነበር። 

አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች የጌታን እራት ቢወስዱም እንኳ፥ እንደ ተመስገንና ብዙነሽ ያሉ ሰዎች ሥርዓቱ ምን እንደሆነ አይገባቸውም። ይህች ጽሑፍ የጌታ እራት ትርጉም ምን መሆኑንና ሁሉም የእርሱ ተከታዮች በዚህ እንዲሳተፉበት ኢየሱስ ለምን እንደፈለገ ትገልፃለች። ስጽሑፍዋ መጨረሻም ክርስቲያኖች ስለ ጌታ እራት ዓላማ ያላቸውን የተለያየ አመለካከት እንቃኛለን። 

በአዲስ ኪዳን ዘመን የጌታ እራት ለመጀመሪያቱ ቤተ ክርስቲያን አምልኮ ማዕከላዊ ነገር ነበር። በየሳምንቱ ምእመናን ሲሰበሰቡ አምልኮአቸውን በልዩ ምግብ ይደመድሙ ነበር (የሐዋ. 2፡42-46፤ 20፡7)። በኋላም አማኞች ይህን ምግብ «የፍቅር ግብዣ» ብለው ጠሩት፥ ምክንያቱም ይህ ግብዣ ለእያንዳንዳቸው ያላቸውን ፍቅርና በተለይም ስለ እነርሱ ለሞተው ጌታ ያላቸውን ፍቅር የሚገልጽ ነበር። የኅብረተሰቡ ግብዣ ማዕከላዊው ክፍልም በእነርሱ ምትክ የሞተውን ጌታ ለማሰብ የሚደረግ ሕብስትን መቁረስና ወይንን መጠጣት ነበር። በተጨማሪም፥ ይህ ሥርዐት «የጌታ ማዕድ» (1ኛ ቆሮ. 10፡20፥ «ቁርባን»፥ «የበረከት ጽዋ» (1ኛ ቆሮ. 10፡16) እና «እንጀራን መቁረስ» (የሐዋ. 2፡42) ተብሏል። ከቤተ ክርስቲያን ጅማሬ አንስቶ የጌታን እራት መቀበል ለቤተ ክርስቲያን ዋንኛ የአምልኮ ተግባሯ ነበር። ጥምቀት እያንዳንዱ አማኝ ለክርስቶስ ያለውን ታማኝነት የአማኞችን ኅብረት እንደተቀላቀለ የሚያሳይበት መንገድ ነበር። ከትንሣኤው ጌታ ጋር ያላቸውን ቀጣይ ኅብረት ለማሳየት፥ አዘውትረው የጌታን እራት ይወስዱ ነበር።

ምንጭ፡- “የጌታ እራት”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ ተሾመ ነጋሽ የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Exit mobile version