ጌታን እራት ለሚያስፈጽሙ መሪዎች አስተያየት

የጌታን እራት መውሰድ አነስተኛ ግምት የሚሰጠው አላስፈላጊ የኢየሱስ ተከታዮች ድርጊት ከመሆን ይልቅ፥ ለእያንዳንዱ አማኝ በጣም አስፈላጊ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያሳየናል። አባሎቻችን የመዘመር፥ የኳየር መዝሙር የማዳመጥ፥ ወይም ስብከት የማዳመጥን ያህል የጌታ እራትን መውሰድ ኢየሱስን የማምለክ አንዱ ክፍል መሆኑን እንዲያውቁ ማድረግ ይጠበቅብናል። ማንኛውም ያልተጠመቀ ሰው የጌታን እራት መውሰድ የለበትም ብላ ቤተ ክርስቲያናችን የምታስተምር ከሆነ፥ ሰዎች እንዲጠመቁና ከእኛ ጋር የጌታን እራት እንዲወስዱ ልናበረታታቸው ያስፈልጋል። በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ በቤተ ክርስቲያን የሥነ ሥርዓት እርምጃ ከተወሰደባቸው ምእመናን በስተቀር፥ አንድ ሰው ካመነ በኋላ የጌታን እራት ሳይወስድ ለረጅም ጊዜ የቆየበት ወቅት አልተሰማም። የጌታን እራት በአንድነት በመብላት የደኅንነታቸው መሠረት የኢየሱስ ሞት ብቻ መሆኑን አማኞች ሁሉ ቢያረጋግጡ ምንኛ መልካም ነበር? ስለ እኛ በመሞቱ ለኢየሱስ ምስጋናችንን የምንገልጽበት ቁልፍ መንገድ ይሆን ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን በአንዱ የክርስቶስ አካል ኅብረታችንን የምንገልጽበት ዋንኛ መንገድም ነው። 

የሚከተሉትን አስተያየቶች በመጠቀም መሪዎች፥ አማኞች የጌታን እራት ሲወስዱ ከኢየሱስ ጋር የመገናኘት ልምምዳቸው ከፍ እንዲል ሊረዷቸው ይችላሉ። 

1. አማኛች ሁሉ የጌታን እራት የአምልኮአቸው ተቀዳሚ ተግባር እንዲያደርጉ አበረታቱ። ወደ ቤት ቀድመው ከመሄድ ይልቅ መሳተፍ ያስፈልጋቸዋል። 

2. አባላት ኢየሱስን ለመገናኘት ሰአዕምሮአቸው ተዘጋጅተው እንዲመጡ አበረታቷቸው (አደፋፍሯቸው)። አማኞች አኗኗራቸው በኢየሱስ ሞት ላይ ያላቸውን እምነት ማንጸባረቅ ያለማንጸባረቁን የጌታን እራት ሲወስዱ እንዲገልጹ፥ በሳምንቱ ውስጥ ሕይወታቸውን በመፈተሽ ሊቆዩ ያስፈልጋል። አብዛኛው የኀጢአት ኑዛዜ መደረግ የሚገባው ከአምልኮ ሥርዓቱ በፊት እንጂ፥ በሥርዓቱ ጊዜ አይደለም። 

3. የጌታ እራትን የመውሰድ አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት፥ ለምእመናን የጌታን እራት መቀበል ምሳሌነት አስታውሷቸው። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ እንደተመለከትነው፥ የጌታ እራት በተምሳሌት የበለጸገ ነው። የጌታን እራት ስንወስድ ስንበላና ስንጠጣ ምን እየገለጽን እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል። 

4. አማኞች ያለአግባብ የጌታን እራት መብላታቸው አደጋ እንዳለው አስጠንቅቋቸው። እያንዳንዱ ምእመን እንደገና ልቡን መመርመርና ለጌታውና አዳኙ ኢየሱስ በትሕትና እየታዘዘ እየተራመደ እንደሆነ መፈተሽ ይገባዋል። ኃጢአታቸውንም እንዲናዘዙ አበረታቷቸው። በእውነት ከተናዘዙ የኢየሱስ ደም ከኃጢአታቸው ፍፁም ሊያነፃቸው እንደሚችል አስገንዝቧቸው። ነገር ግን የኑዛዜውን ጊዜ የሥርዓቱ ዋንኛ ክፍል እንዲሆን አታድርጉ፡፡ 

5. የኢየሱስ ሥጋና ደም ለእኛ ያደረገውን በማሰብ ሕዝቡ እግዚአብሔር አብንና ኢየሱስን እንዲያመሰግኑ የተለያዩ ነገሮችን አድርጉ። መዝሙር ዘምሩ፥ ደስ የሚያሰኙ የምስጋና ቃላትና ለጌታ መገዛትን በሚያሳዩ የማስተዋል ቃላት ተጠቀሙ። ሰዎች የኢየሱስ ሞት ያመጣላቸውን የሚያስደንቅ ነገር የሚገልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በማንበብ እንዲገልጹት ፍቀዱላቸው። አጫጭር የምስጋና ጸሎቶችንም ይጸልዩ። የጌታን እራት መውሰድ ትኩረቱ ኢየሱስን ለማመስገንና በእርሱ መመካታችንን እንደገና ለማረጋገጥ ነው እንጂ፥ በኢየሱስ ሥቃይ ላይ መሆን የለበትም። 

6. ይህን ምስጋና የሞላበትን የአምልኮ ጊዜ ኢየሱስ ባሳየን ወይም ጳውሎስ በገለጸው መሠረት ኅብስቱንና ጽዋውን በመውሰድ (1ኛ ቆሮ. 11፡23-26)። ሰዎች የጌታን እራት እየወሰዱ ያሉት በልምድ ብቻ ከሆነ፥ አወሳሰዱን መለወጥ ያስፈልግ ይሆናል። አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረታቸውን ለመግለጽ ሁሉም አማኝ እንዲቆይና አንድ ላይ እንዲበላ ያደርጋሉ። 

7. ሰዎች ሁለት እውነቶችን እንዲያስታውሱ በማድረግ ፈጽሙ። አንደኛ፥ የጌታ እራት የጌታቸውን በቅርብ መመለስ እንደሚያመለክት አስታውሷቸው። ሁለተኛ፥ የጌታን እራት መውሰድ የጌታን ሞት የማወጃ አንዱ መንገድ እንደሆነ አስታውሷቸው። ነገር ግን እንደ ኢየሱስ ተከታዮች የጌታን ሞት እግዚአብሔር በአስቀመጠን ኅብረተሰብ ውስጥም ማወጅ ይገባናል። የጌታን እራት ስንበላ፥ ምሳሌ አድርገን የምናስተላልፈው ሁሉም የምንደሰትባቸው በረከቶች ከኢየሱስ ሞት የሚመጡ ናቸው ማለታችን ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ስንወጣ ይህን ተመሳሳይ እውነት ለማያምኑ ሰዎች ለማካፈል ፈቃደኞች መሆን ይገባናል፡፡ ያም ኢየሱስ ስለ እነርሱ መሞቱን በማመን እግዚአብሔር ሊሰጣቸው ወደፈለገው ወደ ዘላለመአዊ በረከት ሊያደርሳቸው እንደሚችል ነው፡፡

ማጠቃለያ 

ዛሬ ዛሬ አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ስለ ጌታ እራት አስፈላጊነት ትኩረት (አጽንዖት) አይሰጡበትም። አብዛኛዎቹ ምእመናን ስላልተጠመቁ፥ የጌታን እራት አይወስዱም። የጌታን እራት መውሰድ የሚችሉት አባላትም ቢሆኑ የዚህ ክፍል አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት ይወጣሉ። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ጋር የሚቃረን ነው። ምናልባትም በአምልኮ እጅግ አስፈላጊው ነገር ሊሆን የሚችለው የጌታን እራት መውሰድ ነው። እንዲያውም፥ ሁሉም አማኞች የጌታን እራት እንዲወስዱ ታዝዘዋል። ምናልባት ብዙዎቻችን በእምነታችን የምንታገልበት ምክንያት ብዙ ጊዜ የጌታን እራት ስለማንወስድ የጌታ እራት የሚያስተምረንን እውነት ስለምንረሳ ነው። በእምነታችን ሚዛን የምናጣበት ምክንያት የቤተ ክርስቲያን ሕግጋትን እንደ ሕይወታችን መሠረት ለማድረግ በመመለስ ወይም በተአምራቶች ላይ ወይም በጊዜያዊ የምድራዊ በረከቶች ላይ በማተኮር የጌታ እራት ወደ ዘላለማዊ የበረከት እሴት የሚወስደን እርግጠኛው የኢየሱስ ሞት መሆኑን እንዲያስታውሰን ስለማንፈቅድለት ነው። የጌታ እራት በአንተ ሕይወት ውስጥ አስፈላጊ ነውን? ካልሆነ፥ ለምን አልሆነም? የኢየሱስ ሞት ምን ያህል ነገር እንዳደረገልህ ረስተሃልን? ወይስ ምናልባት እንደ ግል መድኀኒትህ አድርገህ ኢየሱስን ማመን እንዳለብህ አልተገነዘብክም? ካልተገነዘብክ ኢየሱስን አሁን እመን። ከእግዚአብሔር ቤተሰብ ጋር በደስታ የኢየሱስን ሞት ሥርዓት (የጌታን እራት) እንድታከብር ምን ማድረግ እንዳለብህ ከቤተ ክርስቲያንህ ሽማግሌዎች ጋር ተነጋገር። 

ምንጭ፡- “የጌታ እራት”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ ተሾመ ነጋሽ የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: