መንፈስ ቅዱስን ማወቅ

ጥያቄ፡- ሀ) ዳን 11፡32 አንብብ። አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝቦች ምን ሲያደርጉ ነው ይህ ጥቅስ የሚናገረው? ለ) ኤፌ. 1፡17-20 አንብብ። ) ጳውሎስ ለቅዱሳን የጸለየው ጸሎት ምን ነበር? 2) እነዚህን ጥቅሶች በሕይወታችን ለመፈጸም የምንችለው እንዴት ነው? ሐ) እግዚአብሔርን ሳናየው ወዳጆቹ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? 

መንፈስ ቅዱስን ካላወቅነውና በኃይሉ ካልተመላለስን ስለ መንፈስ ቅዱስ ማወቅ ምንም አይጠቅምም። የሕይወታችን ዓላማ እግዚአብሔርን የቅርብ ጓደኛ ለማድረግ የምንችልበት መንገድ ማወቅ ሊሆን ይገባል። የሙስሊም እምነት ተከታዮችም ሆኑ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እግዚአብሔር ለመታወቅ በማይችል ሁኔታ በሩቅ የሚገኝ አድርገው ይቆጥሩታል። ብዙ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች እንደ መላእክትና ማርያም ያሉ አማላጆችን በእግዚአብሔር ፊት ይወክሉአቸው ዘንድ የሚጠቀሙበት አንዱ ምክንያት ላዚህ ነው። እግዚአብሔር ብቸኛ ታላቅና ኃያል ቢሆንም ቅሉ፥ ቅርብ ወዳጆቹ እንድንሆንና ከእርሱ ጋር በኅብረት እንድንኖር የሚፈልግ ስለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ አስደናቂ እውነትን ያስተምራል። 

ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር የቅርብ ወዳጅነት እንዴት መፍጠር እንችላለን? በምድር ላይ እንዳሉ ማናቸውም መልካም ግንኙነቶች ሊሆኑ የሚገባቸው ቢያንስ አራት ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ እግዚአብሔርን ለማወቅ ፍላጐት እንዲኖር ያስፈልጋል። ብዙዎቻችን አንድ ወይም ሁለት የቅርብ ጓደኞች አሉን። እነኚህ ጓደኞቻችን ወደ እኛ የቀረቡት ወዳጅ ልናደርጋቸው መልካም ፈቃድና ፍላጐት ስለነበረን እነርሱም ይህ ፍላጐት ስለነበራቸው ነው። የቅርብ ጓደኝነት ብዙ ድካምን ስለሚጠይቅ፥ የቅርብ ጓደኛ የመሆን ፍላጎት ሊኖር ይገባል። እንደ አብርሃም፥ ሙሴና ዳዊት የእግዚአብሔር የቅርብ ወዳጆች ልንሆን የምንችለው ከልባችን ስንፈልግና እንደፍላጎታችን ስንኖር ብቻ ነው። እግዚአብሔር ወዳጃችን ሊሆን ይፈልጋል (ዮሐ 15፡14-15)። እኛም በምድር ላይ ካሉ ነገሮች ሁሉ በላይ የእግዚአብሔር ወዳጆች ለመሆን በመፈለግ ምላሽ መስጠት አለብን። 

ሁለተኛው ጉዳይ ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑ ነው። ማንም በአንድ ጊዜ ወዳጃ ችን አይሆንም። መልካም የቅርብ ጓደኝነት ለመመሥረት ብዙ ጊዜ ዓመታት ይጠይቃል። ከእግዚአብሔር ጋር የቅርብ ወዳጅነት ለመመሥረትም እንደዚሁ ጊዜ ይፈልጋል። 

ሦስተኛ በእግዚአብሔር ፊት ግልጽ መሆን አለብን። ልባችንና እእምሮአችንን መክፈት አለብን። የምናስበውን፥ የጐዳናንን፥ የምንመኘውን፥ የምንታገለውን ነገር ሁሉ ልናካፍለው ይገባል። ከመዝሙረ ዳዊት እንደምንረዳው ዳዊት የእግዚአብሔር የቅርብ ወዳጅ የሆነበት አንዱ ምክንያት በእግዚአብሔር ላይ መቆጣቱን እንኳ ሳይቀር ውስጣዊ ነገሩን በሙሉ ሳይደብቅ ይገልጽላት ስለነበር ነው። ወዳጆቹ ለመሆን ፍጹም ልናምነውና በፊቱ ግልጽ ልንሆን ይገባል። ከሕይወታችን ከፊሉን ለመደበቅ መሞክር ምንም አይጠቅምም። እግዚአብሔር ሁሉን ስለሚያውቅ ከእርሱ የምንደብቀው የለንም። አስተሳሰባችንና ስሜታችንን ከእግዚአብሔር ለመደበቅ ስንሞክር ከእርሱ እንዲኖረን የምናስበው የቅርብ ወዳጅነት ሳያድግ ይቀራል።  

በአራተኛ ደረጃ ማንነቱን ማወቅ ይገባናል። የአንድን ሰው ማንነት ማወቅ፤ ታሪኩን፥ የሚወደውንና የሚጠላውን ባሕርይውን ማወቅን ይጠይቃል። ስለ ሰውየው ባወቅን መጠን፥ እርሱም ስለ እኛ ባወቀ መጠን አንዳችን ለሌላችን የበለጠ እየተመቸን እንሄዳለን። ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነትም ጉዳዩ ተመሳሳይ ነው። ስለ እግዚአብሔር ባወቅን መጠን የበለጠ ወዳጁ እንሆናለን። ቀንኙነታችንም ያድጋል። ስለ እግዚአብሔር ለመማር ጊዜ ካልወሰድን፥ ምን እንደሚመስል፥ የሚወደውንና የሚጠላውን የሚያስደስተውንና የሚያሳዝነውን ካልተረዳን የእግዚአብሔር የቅርብ ወዳጅ መሆን አንችልም። ነገር ግን እግዚአብሔርን ከፈለግንና እርሱን ማወቅ የምንሻ ከሆነ፥ እግዚአብሔር እራሱን ለእኛ ይገልጥልናልግንኙነታችንም በእያንዳንዱ ዓመት እየጠለቀና እየጣፈጠ ይሄዳል። 

ጥያቄ፡– እራስህን መርምር። ሀ) እግዚእብሔርን ምን ያህል በሚገባ ታውቀዋለህ? ለ) እንደ ቅርብ ወዳጅህ እርሱን ማወቅ ለአንተ ምን ያህል አስፈላጊህ ነው? ሐ) በእግዚአብሔር ፊት ምን ያህል ግልጽ ነህ? መ) የበለጠ ታውቀው ዘንድ ምን እያደረግህ ነው? 

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ ይኖራል። እኛ የእርሱ ቤተ መቅደስ ነን (1ኛ ቆሮ. 6፡19-20)። እንዲሁም የትውውቅ ብቻ ሊሆን ይችላል ወይም የቅርብ ወዳጃችን ሊሆን ይችላል። ምርጫው የራሳችን ነው። ወዳጆቹ የመሆን ፍላጐት አለን? ይህ ፍላጐት ታዋቂ፥ ሃብታም ወይም የተማረ ለመሆን ካለን ፍላጎት የላቀ መሆን አለበት። ከባድ ጥረት የሚጠይቅ ነው። ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ግንኙነታችንን እያዳበርን ስንሄድ እርሱ አጽናኛችን፥ መካሪያችን፥ አበረታቻችንና እጋዣችን ይሆናል። በእርሱ በኩል ከእግዚአብሔር አብና ከእግዚአብሔር ወልድ ጋር እጅግ ያማረ ኅብረት ውስጥ እንድንገባ የሚያስችለንን ኃይል ይሰጠናል። በእርግጥ በምድር ላይ ከዚህ የላቀ አስፈላጊ ነገር የለም። 

እግዚአብሔር ከእኛ የራቀ መስሎ የሚሰማን ከሆነ በልባችን ያለውን መንፈስ ቅዱስን ካለመስማታችን የተነሣ ነው። ተስፋ ቆርጠን ከሆነ መንፈስ ቅዱስ እንዲያጸናንና እንዲመራን አልፈቀድንለትም ማለት ነው፡፡ በኃጢአት ክመሸነፍ ይልቅ ለክርስቶስ በድል መኖር ሊመጣ የሚችለው መንፈስ ቅዱስን በማወቅና በሕይወታችን ውስጥ የሚሠራውን ኃይሉን ስንለማመድ ብቻ ነው። ዳሩ ግን መንፈስ ቅዱስን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? እርሱ እንደ ነፋስ ስለሆነ መቼ እንደሚመጣና ወዴት እንደሚሄድ አናውቅም (ዮሐ 3፡8)። በዓይናችን ልናየውም አንችልም። ከጓደኞቻችን ጋር እንደምናወራው በቃላት ከእርሱ ጋር ልንነጋገር እንችልም። እግዚአብሔር በጸጋው መንፈስ ቅዱስ ራሱ በጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈስ ቅዱስን ገልጦልናል። እግዚአብሔርን ማወቅ ከፈለጋችሁ፥ እና መንፈስ ቅዱስንም ማወቅ ከፈለጋችሁ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በተቀዳሚ እራሱን በቃሉ ይገልጥላችኋል። ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ በመውሰድ በቃሉ እንዲገልጥልን መጠየቅ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። መንፈስ ቅዱስን በእርግጠኛነት ለማወቅ ከዚህ ሌላ መንገድ ፈጽሞ የለም። 

በዚህ የጥናት መምሪያ መጽሐፍ የእኔው ግብ ስለ መንፈስ ቅዱስ የጠለቀ ተጨማሪ የእእምሮ እውቀት እንዲኖራችሁ አይደለም። መንፈስ ቅዱስን እራሱን እንድታውቁት እፈልጋለሁ። መንፈስ ቅዱስን ባለማወቃቸው ምክንያት ደካማ፥ ደረቅና ውጤታማ ያልሆነ ሕይወት ያላቸው በርካታ ክርስቲያኖች አሉ። ስለ መንፈስ ቅዱስ በጥልቀት እናጥና፥ ከሁሉም በላይ ደግሞ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እራሱን እንዲገልጥልን ቃሉን ስናጠና የበለጠ እንድናውቀው ይረዳን (ያግዘን) ዘንድ እንጠይቀው። 

ጥያቄ፡- የጸሎት ጊዜ በመውሰድ መንፈስ ቅዱስ በዚህ ጥናት ውስጥ እራሱን እንዲገልጥልህና የቅርብ ጓደኛው እንዲያደርግህ ጸልይ።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.