መንፈስ ቅዱስ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንዲጽፉ በመምራት የሰጠው አገልግሎት

ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከቱ። 2ኛ ሳሙ 23፡1-4፤ ዕዝ. 2-4 ሚክ 3፡8፤ ማቴ. 22፡43-44፤ የሐዋ. 1፡16፤ 2ኛ ጢሞ 3፡16፤ 2ኛ ጴጥ. 2። ሀ) እነዚህ ጥቅሶች መንፈስ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔርን ቃል የመግለጥ ሚና እንደነበረው ምን ያስተምሩናል? ለ) እግዚአብሔር የተጻፈውን ቃሉን ይሰጠን ዘንድ ስለ ሠራው ሥራ ምን ያስተምረናል? ሐህ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ማመን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ምን ጥቅም ይሰጣል? 

ሰይጣን በዘመናት ሁሉ ውስጥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ እምነት ለመደምሰስ ከተጠቀመባቸው መንገዶች አንዱ የእግዚአብሔርን ቃል ቸል እንዲሉ ማድረግ ነው። ይህንን የሚያደርገው በሁለት መንገዶች ነው። በርካታ የተከበሩ ክርስቲያኖች በሥራ እጅግ በመጠመዳቸው የእግዚአብሔር ቃል አያነቡም። ደግሞም አያጣኑም። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን በግልጥ ቢናገሩም እንኳ በተግባር ስንመለከታቸው ስለማይሰሙትና ስለማይታዘዙት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ቃል አይደለም። 

ሌሎች ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል ትክክለኛነት በመጠራጠር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሕተት አለ ይላሉ። ይህ አመለካከታቸው መጽሐፍ ቅዱስ የጥሩ ሰዎች ጽሑፍ ስለሆነ መልካም ሥነ ምግባርን ያስተምራል እንጂ ከዚህ ሌላ ምንም አይደለም ወደ ማለት ያደርሳቸዋል። የእግዚአብሔርን ቃል ትክክለኛነት የሚጠራጠር ማንኛውም ክርስቲያን አደገኛ ጐዳና ላይ ሲሆን የዚህ አካሄድ መጨረሻም እምነትን መካድ ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያሉ እነዚህን ሁለት አመለካከቶች በኢትዮጵያ እንዴት አየኸው? ለ) በሰዎች መንፈሳዊ ሕይወት የሚያስከትለው የመጨረሻ ውጤት ምንድን ነበር? ሐ) እንተ ወይም የምታውቃቸው በርካታ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ቃል ቸል የምትሉት እንዴት ነው? 

መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለሰዎች በመግለጥ የፈጸመውን ነገር ለማስረዳት ትምህርተ ዘለቆች (ምሁራን) ሁለት የተለያዩ ቃሎችን ይጠቀማሉ። የመጀመሪያው «መገለጥ» የሚለው ነው። ይህ ቃል ተሰውሮ የነበረውን ነገር እግዚአብሔር ለሰዎች የገለጠበትን ሂደት ያሳያል። እነዚህ ነገሮች ስለ ባሕርይው፥ ስለ ፍላጐቶቹና ወደፊት ስለሚሆን ጉዳይ ያሉ እውነቶች ሊሆኑ ይችላሉ። እግዚአብሔር ፈቃዱን የገለጠባቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ «ነቢያት» በመባል ይጠሩ ነበር። 

ሁለተኛው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ ለሚገኘው የእግዚአብሔር ቃል የተሰጠ በእግዚአብሔር መንፈስ መነዳት የሚል ትርጉም የያዘ ቃል ነው። ይህ ቃል ከ2ኛ ጢሞ. 3፡16 የተገኘ ሲሆን፤ የግሪኩ ቃል አቻ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር እስትንፋስ” ነው ይላል። ስለዚህ ሊቃውንት መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ ተነድተው የጻፉት ነው ሊሉ እንዲህ ማለታቸው ነው። ምንም እንኳ ጽሑፎቻቸው የግል አስተሳሰባቸውንና ማንነታቸውን ቢያንፀባርቁም በኩረ ጽሑፋት ስሕተት የሌለባቸው፥ በተሟላ ሁኔታና በትክክል የእግዚአብሔርን አሳብ፥ ዓላማና ቃሎች እንዲያስተላልፉ ከሰብአዊ ጸሐፊዎች ጋር አብሮ የሠራው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው። 

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚብሔር ሰዎች ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ ተነድተው የጻፉት ነው ስንል ምን ማለታችን ነው? በዚህ ጉዳይ ልንረዳቸው የሚገባን በርካታ ቁልፍ መመሪያዎች አሉ። 

1) በመጀመሪያዎቹ ጸሐፊዎች ስለተጻፉት የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች መናገራችን ነው። ቅጂዎችን በማብዛትና ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች በመተርጐም ሂደት ውስጥ ስሕተት ሊታይ ይችላል (ለምሳሌ ዕዝራ 2፡3-70 ከነህ. 7፡4-73 ጋር አወዳድር)። ይሁን እንጂ የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ሙሉ በሙሉ ትክክል እንደነበሩ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይህ ማለት በእጃችን የሚገኘውን መጽሐፍ ቅዱስ መጠራጠር አለብን ማለት ነውን? አይደለም። ነገር ግን በታሪክ ሂደት ውስጥ በነበረው የትርጉምና ቅጂዎችን የማዘጋጀት ተግባር አንዳንድ ቀላል የሆኑ ለውጦች የተደረጉ ስለሆነ አሁን በእጃችን የሚገኘው ቅጂ ስሕተት ፈጽሞ የሌለበት ነው ማለት እንችልም። አሁን በእጃችን በሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ላለን እምነት መሠረቱ በታሪክ ሁሉ ይዘቱን ጠብቆ የተላለፈ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያህል ሌላ ጥንታዊ ጽሑፍ ያለመኖሩ አስደናቂ እውነታ ነው። በተለያዩ ቅጂዎች ውስጥ ባሉ በአንዳንድ ቃሎች ላይ እጅግ ቀላል የሆኑ ልዩነቶች ሲኖሩም እንኳ በእነዚህ ልዩነቶች ምክንያት የተፋለሰ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የላም። የሒንዱ መጻሕፍትንና ቁርአንን በመሳሰሉ ሌሎች መጻሕፍት ውስጥ ይህ ሐቅ አይታይም። አንዳንድ ጊዜ እስላሞች በቅጂ ሂደት የሚታዩትን ተራ ግድፈቶች ነቅሰው በማውጣት መጽሐፍ ቅዱስ በስሕተት የተሞላ ነው የሚሉት ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ ተነድተው ጻፉት ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ ስላልተረዱ ነው። 

2) መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የጻፉት ነው ስንል መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ ትክክል ነው ማለታችን ነው። የሚያስተምረው ሙሉ በሙሉ እውነት ነው ማለታችን ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የድነት (የደኅንነት) ብቸኛ መንገድ ኢየሱስ ነው ሲል እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተናገረው እውነት መሆኑን በእርግጠኝነት እናውቃለን። 

(ማስታወሻ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዘመኑ ሰዎች አስተሳሰብ የሚናገረውንና ለለ አመለካከታቸው የሚያቀርበውን ማብራሪያ በመሠረታዊነት ከሚያስተምረው እውነት ለይተን ለማየት ጥንቁቅ መሆን አለብን። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ፀሐይ ትጠልቃለች ይላል። ይህ አባባል በዚያን ዘመን የነበሩ ሰዎች ስለ ፀሐይ መጥለቅ የነበራቸውን ትክክለኛ መረዳት የሚዘግብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ሳይንሳዊ መጽሐፍ የተጻፈ ስላልሆነ ምድር ከፀሐይ ጋር ስላላት ቀንኙነት የሚናገረው ምንም ነገር የለም። አሳባቸው ሳይንሳዊ መሆኑንና አለመሆኑን ሳያስረግጥ ሰዎች ዓላማቸውን (አካባቢያቸው) እንዴት ያስተውሉት እንደነበር አስፍሯል። 

3. መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የጻፉት ነው ማለት የእግዚአብሔር ሙሉ ሥልጣን አለው ማለት ነው። የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ እግዚአብሔር ከፊታችን ቆሞ አንድ ነገር በሚነግረን ወቅት የሚኖረውን ያህል ሥልጣን እለው። በእርግጥ ይህን የሚያህል ሥልጣን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ዛሬ የምናልመው ሕልም ወይም መገለጦች ወይም የምንሰማቸው ድምጾች ወዘተ… የተጻፈውን የእግዚአብሔር ቃል ያህል ሥልጣን የላቸውም። የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት ቃል ወይም እስትንፋሰ-እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። 

ጥያቄ፡- መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ መንገድ የእግዚአብሔርን መንፈስ የተላበሰና የራሱ የእግዚአብሔር ቃል ከሆነ፥ ይህ እውነታ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አስፈላጊነት፥ ለምን ማጥናትና ማወቅ፥ ደግሞም ግንዛቤያችንን ሰዎች በሚያስቡትና በሚያስተምሩት ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቃል ላይ መመሥረት እንደሚገባን ምን ያሳያል? 

በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር መልእክቱን ለሕዝቡ የሚያስተላልፍበት ተቀጻሚ መሣሪያ ነቢያቶች ሲሆኑ የእግዚአብሔርን መላእክት የመግለጥ ተቀዳሚ ኃላፊነት የወሰደው የሥላሴ አካል መንፈስ ቅዱስ ነበር። [ማስታወሻ፡- ኢሳ. 6፡8-10 ከሐዋ. 28፡25-27 ጋር ሲወዳደር ለኢሳይያስ የተናገረው መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ግልጽ ይሆንልናል]። ከእነዚህ ነቢያት አብዛኞቹ መልእክቶቻቸውን አልጻፉትም። ይልቁኑ ለትውልዳቸው የእግዚአብሔር አፈ ጉባኤ ነበሩ። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ለነቢያት በቀጥታ ድምፅ ተናግሯቸዋል (ዘፀአ 19፡9፥ 17-19፤ 1ኛ ሳሙ. 3፡1-14)። በሌላ ጊዜ ደግሞ በሕልም (ዘፍ 20፡3-7፤ 31፡24) እና በራእይ ይናገር ነበር (ዘፍ 15፡1፤ ኢሳ 1፡1)። 

እግዚአብሔር ጥቂት ነቢያትን ተጠቅሞ በሁሉም ዘመናት ላሉ ሕዝቦች ሁሉ ፈቃዱ እንዲተላለፍ ዘላለማዊ መጽሐፍ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ አደረገ። ከመንፈስ ቅዱስ ዋና አገልግሎቶች እንዱ ብዙ መተ ዓመታት (2000 ዓመታት ያህል የፈጀውን እና የተለያዩ ጸሐፊዎች የጻፉትን የእግዚአብሔርን ቃል የመጻፍ ሥራ ሂደት በበላይነት መቆጣጠር ነበር። በ2ኛ ጴጥ. 1፡21 ላይ እንደምንመለከተው የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ምንጭ እግዚአብሔር እራሱ ነው። እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ ሰዎችን ተጠቅሟል። ሰዎችን መሣሪያ እድርጐ የተጠቀመ ብቸኛው የመጽሐፉ ደራሲ ግን መንፈስ ቅዱስ ነው። ለዚህም ነው የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ክብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሚጠቅሱበት ጊዜ ቃሎቹ የመንፈስ ቅዱስ እንደሆኑ የሚናገሩት (ለምሳሌ ማቴ. 22፡43፤ የሐዋ. 1፡16፤ 4፡24-25፤ 28፡25-27፤ ዕብ 3፡7፤ 10፡6-17)፡፡ ኢየሱስ እራሱ ሲናገር ዳዊት የጻፈው በመንፈስ ቅዱስ እንደነበር መላክሯል (ማር. 12፡36)። 

ስለዚህ የአዲስ ኪዳን ጻሐፊዎች ብሉይ ኪጓንን የእግዚአብሔር መንፈስ ያረፈበት (ያለበት) አድርገው ማየታቸው ግልጽ ነው ደሞም መጽሐፍ ቅዱስ የራሱ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ለማረጋገጥ የሥላሴ አንዱ አካል የሆነው መንፈስ ቅዱስ ከጸሐፊዎቹ ጋር አብሮ እንዲሠራ እርግጠኛ ነው ይናገራሉ። አዲስ ኪዳንም በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ የተጻፈ መህኑን ለማረጋገጥ ትንሽ ያስቸግራል፤ ምክንያቱም አዲስ ኪጻን የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን የሚናገሩ የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች ጥቂት ስለሆኑ ነው። ነገር ን ሙሉው አዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ ጸሐፊዎችን በሚጣጠርበት አሠራሩ በመጠቀም ያላገኘው የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ለማመን በቂ ማረጋገጫ እለ። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ተለይቶ ከሄደ በኋላ፥ መንፈስ ቅዱስ ከሚያደርጋቸው ተግባራት አንዱ እርሱ ያስተማራቸውን ነገሮች ማስታወስ እንደሚሆን ኢየሱስ የገባውን ተስፋ ወደፊት እንመለከታለን ( ዮሐ 14፡26)። ይህ በአመዛኙ ስለ ኢየሱስ ሕይወት ታሪክ የሚያወሱ ወንጌላትና ስለ ሕይወቱ የሚያብራሩ መልእክቶችን መጻፍን ያጠቃልላል። ጳውሎስ በ1ኛ ጢሞ. 18 ላይ ከዘዳ 25፡4 እና ከሉቃስ 10፡7 በመጥቀስ ክፍሎቹ የቅዱሳት መጻሕፍት አካል እንደሆኑ ይናገራል። ጴጥሮስም ደግሞ የጳውሎስን ጽሑፎች በመጥቀስ ቅዱሳት መጻሕፍት ብሎአቸዋል (2ኛ ጴጥ. 3፡6-16)። 

ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ የብሉይ ኪዳን ጸሐፊዎችን እንደመራ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎችንም መምራቱን ያስተምራሉ። ሐዋርያት ከሞቱ በጥቂት ምእተ ዓመታት ውስጥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የላቸው መጻሕፍት የትኞቹ እንደሆኑ በመለየት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማካተትና ሌሎችን ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለይተው በሌላ ደረጃ ላመመደብ የቻሉት በመንፈስ ቅዱስ በመመራታቸው ነው። 

መንፈስ ቅዱስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የተያያዘ አንድ ሌላ አገልግሎት አለው። መጻሕፍት የእግዚአብሔርን አሳብ ብቻ የያዙ ሆነው እንዲጻፉ ሰዎችን ያንቀሳቀሰና የሚጽፉትንም ነገር የተቆጣጠረ መንፈስ ቅዱስ እንደነበረ ተመልክተናል። እንደዚሁም፥ በዓለም ካሉት በርካታ መጻሕፍት ውስጥ የትኞቹ በትክክል የእግዚአብሔር ቃል እንደሆኑ ለመለየትና ስድሳ ስድስቱን የብሉይና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ብቻ ለመምረጥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን አእምሮ የተቆጣጠረው መንፈስ ቅዱስ ነበር። የተጻፈውን ቃል በመጠቀም የሰዎችን ልብ እንዲነካ የሚያደርግ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይህን ሂደት አብርሆት ይሉታል። ይህም መንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊ እውነትን ወደ ብርሃን የሚያመጣስት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የመጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ጭብጦች ሊታወቁ የሚችሉት በመንፈሳዊ ሰዎች ብቻ ነው ብሏል። ያልዳኑ ሰዎች ሊረዷቸው አይችሉም (1ኛ ቆሮ. 2፡12-16)። ስለዚህ ከመንፈስ ቅዱስ ዋና ዋና ሥራዎች እንዱ መንፈሳዊ ዓይኖቻችንና ጆሮዎቻችንን በመክፈት እርሱ በተጻፈው ቃል ውስጥ ለሚናገርበት ጊዜ እንድንሰማው ማድረግ ነው። 

ጥያቄ፡– በተጻፈው እግዚአብሔር ቃል አማካይነት ወይም አንድ ሰባኪ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየሰበካ ሳለ በዚያ አገልግሎቱ መንፈስ ቅዱስ እንዴት እንደተናገረህ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: