በካሪዝማቲክ የሥነ መለኮት ትምህርት የሚገኙ ሚዛናዊ ያልሆኑ ነገሮች

ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ወንድሞቼና እህቶቼ ናቸው። አንድ ቀን በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አብረን ኢየሱስን እናመልካለን። ነገር ግን «እውነትን በፍቅር…» (ኤፌ. 4፡5) እንድንይዝ ስለተነገረን በፍቅር መንፈስ የካሪዝማቲክ ሥነ መለኮት ትምህርት በሚከተሉ ሰዎች ላይ ያለኝን አሳሳቢ ነገር እገልጻለሁ። ሕይወታችን መጽሐፍ ቅዱስ ለሚያስተምራቸው ትምህርቶች የተገዛ እንዲሆን ሁላችንም ለእውነት ሊገደን እንደሚገባ አምናለሁ። በአሁኑ ጊዜ በየቤተ ክርስቲያናችን የምናያቸው ልምምዶች የመጡት እውነትን ለማወቅና በእውነት ለመኖር ከመነጨ ፍላጎት ሳይሆን በሌሎች አደገኛ ምክንያቶች ነው። አብዛኛው ስጋቴ ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች በሚያስተምሩት ነገር ሳይሆን ምንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት በሌላቸው በየቤተ ክርስቲያኑ ተዘውትረው በሚታዩ ሚዛን-የለሽ ልምምዶች ላይ ነው። አንድ በሙላት የተገነዘብኩት ጉዳይ ሁሉም ቤተ ክርስቲያኖች በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ሚዛን ያጡ መሆናቸውን ነው። አንዳንድ እብያተ ክርስቲያናት የእግዚአብሔርን ቃል በማጥናት ላይ ብቻ ስለሚያተኩሩ ሕይወት ያለው እምልኮ ስለማቅረብ ደንታ እይሰጣቸውም። በእርግጥ ቀጥሎ የሚጠቀሱት እንዳንዶቹ ነገሮች አጠቃላይ አሳቦች ስለሆኑ ለሁሉም ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች የሚሠሩ ናቸው ማለት አይደለም። ሆኖም ግን አጠቃላይ አሳቦች የአንድን ሥነ መለኮት ትምህርት መሠረታዊ ባሕርይ ለመረዳት ይጠቅሙናል። በኢትዮጵያ ውስጥ አክራሪ ጫፎች እየተከሰቱ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ እራሳቸውን ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች ብለው የሚጠሩትም ሆኑ ካሪዝማቲክ ያልሆኑት በእምነታቸው በተግባራቸው ሚዛናዊ መሆን አለባቸው። ቀጥሎ በአንዳንድ ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች አብያተ ክርስቲያናት ይታያሉ ብዬ የማምነውን ደካማ ጎኖች እዘረዝራለሁ። 

1. ካሪዝማቲክ የሆኑም ሆኑ ያልሆኑት ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ትዕቢት በማሳየት አዝማሚያ ላይ ናቸው። ካሪዝማቲክ ያልሆኑት እመለካከታቸው እጅግ ትክክልና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ በመናገር ትምክህታቸውን ይገልጣሉ። ነገር ግን ካሪዝማቲክ የሆኑት ክርስቲያኖች ደግሞ የተላየ አዝማሚያ የሚያሳዩ ይመስላል። ይኸውም መንፈሳዊ ለመሆንና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ለመመላለስ ካላቸው ፍላጎት የተነሣ እነርሱ በሚያደርጉት ዓይነት መንገድ መንፈሳዊ አካሄዳቸውን ለመግለጽ የማይሹትን በንቀት ማየት ነው። በልሳናት የማይናገሩትን፥ በቤተ ክርስቲያን እምልኮ ጊዜ በማጨብጨብና በእልልታ የማይሳተፉትን በሚጸልዩበት ጊዜ እጆቻቸውን ለማንሣት «ሃሌሉያ» እያሉ የማይጮኹትን መንፈስ ቅዱስ የላቸውም በማለት ይንቋቸዋል። በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ከመቀበል ይልቅ ክርስትናን እነርሱ በሚገልጡበት መንገድ እንዲቀበሉ ካሪዝማቲክ የሆኑት ካሪዝማቲክ ባልሆኑት ላይ ከፍተኛ ግፊት ያደርጋሉ። ይህ ዝንባሌ ብዙውን ጊዜ እያንዳንዱ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሆኖ ለማየት እንፈልጋለን በሚል ቋንቋ የተለበጠ ቢሆንም፥ እንኳ እውነቱ ግን፥ ሌሎች መንፈሳዊ እንዳልሆኑ እነርሱ ግን ምን ያህል መንፈሳዊ እንደሆኑ ለማሳየት የሚደረግ ጥረት የመንፈሳዊ ትዕቢት ምልክት ነው። ኢየሱስ ስለዚህ ዝንባሌ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ «አትፍረዱ…ይፈረድባችኋል» ብሏል (ማቴ. 7፡1-2)። በአንድ ሰው ልብ ውስጥ በእርግጥ ምን እየሆነ እንዳላ ደግሞም መንፈሳዊ መሆንና ያለመሆኑን ለማወቅ ስለማንችል በራሳችን የመንፈሳዊነት መመዘኛ በሌሎች ላይ እንዳንፈርድ መጠንቀቅ አለብን። 

2. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩ አንዳንድ ስሜታዊ የሆኑ የአምልኮ ልምምዶች እውነተኛ የእምነት ወይም የአምልኮ መግለጫ ሳይሆኑ ሌሎችን የመቅዳትና በሌሎች ፊት መንፈሳዊ ሆኖ የመታየት ዘይቤዎች ናቸው። እግዚአብሔርን በማምለክ ላይ ከማተኮርና ለእኛ ጤናማ በሚመስለን መንገድ አምልኮአችንን ከመግላጽ ይልቅ ትኩረታችን የሚጎላው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሌሎች ሰዎች ስለ እኛ ምን ያስባሉ ሰሚለው ላይ ነው። አንድ ሰው «ሃሌሉያ» ብሎ ከጮኸ የሚቀጥለው ሰው የበለጠ መጮህ አላበት። እንዲት ሴት እጇን ካነሣች ሌላኛዋ ደግሞ መንፈሳዊ ሆና ለመታየት ክመጀመሪያይቱ ሴት ቀድታ ይህንኑ ማድረግ አለባት። አንዱ የመዘምራን ጓድ መዝሙሩን በማሸብሸብና በስግደት ካሳረገ የሚቀጥለውም መንፈሳዊ ለመምሰል ይህንኑ ማድረግ እንዳለበት ያስባል። ኢየሱስ ይህንን «ግብዝነት» ብሎ የጠራው ሲሆን ምናልባትም ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎችን ከከሰሰባቸው ኃጢአቶች ይህ ዋነኛው ነበር (ማቴ. 6፡1-18)። አንዳንድ ጊዜ ካሪዝማቲክ ያልሆኑ ክርስቲያኖች አምልኮ ካሪዝማቲኮች በሚያደርጉት መንገድ ካልተፈጸመ በቀር መንፈሳዊ መስሎ አይታያቸውም። 

3. የልባቸውን ስሜት ስለሚጠብቁ አምልኮአቸው በአመዛኙ ከልብ ሙላት ከሚፈስስ ትክክለኛ ስሜት የመነጨ አይደለም። ይልቁኑ በልዩ ዘዴዎች የሚቀሰቀስ ነው። አእምሮ መሥራት እስኪሳነውና ስሜት ብቻ እለኪጦዝ ድረስ መዝሙሮች በድግግሞሽ ይዘመራሉ። ማምላክ የምንችለው ስለምንዘምረው መዝሙር አእምሮአችን በንቃት በሚሠራበትና በቃሉ ትርጉም ሐሤትን በምናደርግበት ሁኔታ እንደሆነ አምናለሁ። ሰባኪዎች የሕዝብን ስሜት ለማነሣሣት ያሉትን ዘዴዎች በሙሉ ይጠቀማሉ። ከእነዚህም ጥቂቶቹ ሃሌሉያ ማስጮኽ፥ ለቅሶና ታላላቅ ስሜት ቀስቃሽ ድርጊቶች ናቸው። ይህ ነገር ዘላቂ የሆነ ውጤት ስለማምጣቱ እጠራጠራለሁ። ምክንያቱም ስሜቱ ሲጠፋ እግዚአብሔር የሚፈልገውን ነገር ለማድረግ ያለው መነሣሣት አብሮ ይጠፋል። አእምሮአቸውና ስለ እግዚአብሔር ያላቸው እውቀት የሚረጋጋ ሊሆን ሲገባው ስሜታቸው ካልተጋጋለ ኃጢአትን እንዳደረጉ ወይም ሰይጣን እንዳደናቀፋቸው ያስባሉ። ብዙዎችም እምነታቸውን ይተዋሉ። አንድ ሰው በእግዚአብሔር ቃል ላይ ካልተመሠረተ ስሜቱ የሚያዛልቀው ከእምነት እስከሚወድቅ ድረስ ብቻ ነው። በሮሜ 8፡5-8 ጳውሎስ በመንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ በመንፈስ ፍላጎት ላይ አእምሮአቸውን እንደሚያደርጉ ይናገራል። አእምሮአችን በመንፈስ ቁጥጥር ሥር መዋል አለበት። 

4. ብዙ የካሪዝማቲክ አማኞች በመካከላቸው የመንፈስ ቅዱስ ህልውና የመኖሩን መጠን ሊያዩት በሚፈልጉት ተአምራት መጠን ይለኩታል። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በተአምራት ላይ ተአምራትን እየጨመረ ብዙ ተአምራት እንዲሠራ ይፈልጋሉ። የፈውስ አገልግሎት ስብሰባዎችን በማዘጋጀት በዚያ ስብሰባ የተገኙትን ሁሉ ተፈውሳችኋል ይላሉ። አስደናቂ ነገር በመካከላቸው ሲፈጸም የማየት ጉጉታቸው እንደ አደንዛዥ ዕፅ ሱስ ይሆንባቸዋል። ከቀላል በሽታ ሰዎች ሲፈወሱ ባለፈው ባዩት ነገር ደስ ብሎአቸው ከሆነ በዚህ ዓመት ደግሞ ሽባ የሆኑ ሰዎች እንዲፈወሱ ይፈልጋሉ። በየዓመቱ አዲስና ልዩ የሆነ ነገር ለማየት ያላቸው ፍላጎት ይጨምራል። እናም ብዙ ክርስቲያኖች ታላላቅና የበለጠ አስደናቂ የሆነ ተአምራት ይጠብቃሉ። የሚጠበቀው ተአምራት እንደታሰበው ካልተፈጸመ ችግሩ የሰውዬው እምነት ማጣት ወይም የኃጢአት መኖር ነው በማለት ይደመድማሉ። እግዚአብሔር ተአምራትን እነርሱ በሚያያዙት መንገድ እንዲሠራ ይፈልጋሉ። መሪዎችን ከሌላው መሪ የበለጠና የላቀ ተአምራት እያደረጉ እንደሆነ በመናገር ሌሉችን መሪዎች ለማጣጣል ይሞክራሉ። የሚያሳዝነው ነገር አንዳንዶቹ ተአምራት ለመሥራት ኃይል እንዳላቸው ለሕዝቡ ላማሳየት ማታለያ ዘዴን ሁሉ መጠቀማቸው ነው። 

5. ስለ እጋንንት ህልውና ከሚገባው በላይ ትኩረት ይሰጣሉ። ከቤተ ክርስቲያን አጋንንትን ያስወጣሉ። ራሳቸው ያመጡአቸው ሁሉ እንኳ የአጋንንት ስሕተት እንደሆኑ በመቁጠር እንዲወገዱ ያዛሉ። ሰይጣን ወደ ገሃነም እንዲጣል ክርስቲያኖች ሲጸልዩ ሰምቼአለሁ። ሥልጣን ሁሉ የእርሱ የሆነ ኢየሱስ እንኳ እንደዚህ አልጸለየም። ሰይጣን ወደ ገሃነም የሚጣለው በመጨረሻው ዘመን ብቻ ነው። እግዚአብሔር የሰይጣንን ተግባር እንዲቋቋምልን መጸለይ ብንችልም እርሱንም ሆነ ሌሎች አጋንንትን ወደ ገሃነም የመጣል ሥልጣን የላንም። ያዕቆብ እንኳ ለኃጢአት ሁሉ ተጠያቂው ሰይጣን ነው አላለም፤ በራሳችን ክፍ ምኞትና ፍላጎት የተነሣ ኃጢአት እንደምንሠራ አስተምሮአል (ያዕ. 4፡1-3)። 

6. ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ቸል የሚሉና ለትክክለኛ አተረጓጐም እምብዛም የማይቆረቆሩ ናቸው። እውነትን ላማወቅና በእውነት ላመኖር ያላቸው ፍላጎት አነስተኛ ነው። የሚማሩት የሚያምኑትና የሚያደርጉት ነገር ሁሉ ግልጽ ከሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ይጣጣም እንደሆነ ለማረጋገጥ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት አይፈልጉም። መንፈስ ቅዱስ ያስተምረናል በሚል ፈሊጣቸው ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት አይገቡም። መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጣቸው እንዱ የማስተማር ስጦታ እንደሆነ ይዘነጋሉ። ነገሮችን ሁሉ ይዳኙበት ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ዋነኛ መለኪያ ካልተጠቀሙ በስተቀር እውነት የሆነውን ካልሆነው ለመለየት አንዳችም መንገድ አይኖራቸውም። እንዲህ ከሆነ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማንኛውንም ነገር ማድረግ የተፈቀደ ነው ማለት ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ከሆነ ልንጠቀምበት፥ ልናጠናው ደግሞም እውነቶች በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ሊመዘኑ ይገባል። ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ዘንድ «መገለጥ። አገኘን ይላሉ። የተቀበሉት መገለጥ ግን በእግዚአብሔር ቃል ሲመዘን የማይስማማ ሆኖ ይገኛል። ይህ ለእነርሱ ግድ አይሰጣቸውም። ምክንያቱም የእነርሱ መገለጥ ከተጻፈው ከእግዚአብሔር ቃል ጋር አንድ ነው ብለው ስለሚያምኑ ነው። ይህ ማለት ክርስቲያን እውነቱ ምን እንደሆነና ሐሰቱ የቱ እንደሆነ የሚመዝንበት ምንም መንገድ የለውም ማለት ነው። እንደታዘዝነው መናፍስትን መመርመር አንችልም (1ኛ ዮሐ 4፡1)፥ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፥ ይህ ዝንባሌ እየተለወጠ እንደሆነ አምናለሁ። የእግዚአብሔርን ቃል የሚያጠኑ ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች ቁጥር እየጨመረ ነው። በመሆኑም ከዚህ ቀደም ከነበራቸው አቋማቸው እየተላሳላሱ ነው። 

ጥያቄ፡– የካሪዝማቲክ ሥነ መለኮት ትምህርትን የሚያስተጋቡ የአንዳንድ ሰዎችን ዝንባሌ እና ሚዛን-አልባነት እንዴት ታቀርባለህ? 

ይህ አባባል እጅግ አጠቃላይ እንደሆነና አጠቃላይ የሆኑ ነገሮች በሚነጋገሩበት ጊዜ ደግሞ ስሕተቶቹ የማይመለከቱአቸው ብዙዎች እንዳሉ እገነዘባለሁ። እነዚህ ዝንባሌዎች በአንዳንድ ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች ብቻ የተያዙ ናቸው። ስለዚህ አንዳንዶች ብቻ ሚዛናዊ ያልሆኑበትን ነገር በሁሉም ላይ እንዳንጭን መጠንቀቅ አለብን። እነዚህ ሚዛናዊ ያልሆኑ ነገሮች ዝንባሌዎች ናቸው። ካልታረሙ በስተቀር ለቤተ ክርስቲያን አደገኛ ናቸው። 

ይህን ሁሉ ካልኩ በኋላ ለሁላችንም ማሳሰቢያ የሚሆን ነገር በመናገር አጠቃልላለሁ። ሁላችንም ብንሆን ከየትኛውም የእምነት ክፍል ብንመጣ ስሕተቶች አሉብን። በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ሁላችንም ሚዛናዊ ያልሆንበት ጉዳይ አለን። በየትኛው ግፍ ይሁን ማክረር አደገኛ ነገር ነው። ያለ ስሕተት የሆነ የእምነት ክፍልም ሆነ ሰው የለም። ከሁሉም በላይ በክርስቶስ ወንድሞችና እህቶች መሆናችንን እናስብ። አባባሌ በልዩነቶቻችንም ውስጥ ፍቅርና መከባበር ደግሞም መቀባበል ይኑር ነው። እርስ በርስ እንከባበር። ኢየሱስ ክርስቶስን የእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በተገለጠው መንገድ ወደ ማምለክ፥ መሠረታዊ ጉዳይ እንመለስ። እርሱን እናክብረው፥ እናመልከው። ይህንን ስናደርግ ጥቃቅን ልዩነቶቻችንን ይወገዳሉ። 

ጥያቄ፡- ሀ) ካሪዝማቲክ የሆኑም ሆኑ ያልሆኑ ክርስቲያኖች በጋራ የሚያምኑባቸውን የሥነ መለኮት ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህ መሠረታዊ የክርስትና እምነት ትምህርቶች ከማንስማማባቸው ልዩነቶች በቁጥር እጅግ የሚበልጡት እንዴት ነው? ሐ) ሳንጋጭ በአንድነት ሆነን ለመሥራት ስላለን ብቃት እነዚህ እውነቶች ምን ያስተምሩናል?

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.