ኢየሱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ያስተማረው ትምህርት፤ ክፍል 2

ዮሐ 16፡5-16 

ጥያቄ፡ ዮሐ 16፡5-16 እንብብ። ሀ) መንፈስ ቅዱስ ይኖረዋል ብለው እነዚህ ጥቅሶች ስለ አገልግሎቱ የሚያስተምሩትን የተለያዩ አገልግሎቶች ዘርዝር። ለ) ኢየሱስ በእርሱና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት እንደሚያመላክት ግላጽ። 

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርት ጋር የሚቆይበት ጊዜ የተወሰነ እንደሆነ አውቆ ነበር። በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ተይዞ፥ ለፍርድ መቅረብና መሰቀል ነበረበት። ኢየሱስ ከሞት እንደሚነሣ ቢያውቅም እንኳ ከትንሣኤ በኋላ ደቀ መዛሙርትን የሚያስተምርበት ጊዘ ጥረት እንደሆነ አውቆታል። እንዲያውም ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ አንዳችም ጥልቅ ትምህርት ስለማስተማሩ የወንጌል ጸሐፊዎች አንዳቸውም አልዘገቡልንም። ትቶአቸው ከመሄዱ በፊት ሊረሱት የማይገባቸውን ቁልፍ እውነቶች አስታወሳቸው። ከእነዚህ ዋነኛ እውነቶች አንዱ የመንፈስ ቅዱስ መምጣትና በኢየሱስ ምትክ ስለሚሰጠው አገልግሎት ነበር። የኢየሱስ ትኩረት መንፈስ ቅዱስ በሚሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶች ማለትም ተአምራትን ስላማድረግ ኃይሉ፥ ሰዎች በልሳን እንዲናገሩ ስለሚሰጠው እገዛ፥ ወይም ስጦታዎች አልነበረም። ይልቁኑ ኢየሱስ ያተኮረው መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው አገልሎት እርሱ በምድር በነበረበት ጊዜ ከሰጠው አገልግሎት ጋር ስለሚዛመድበት ሁኔታ ነበር። እንደገና አንዳንድ ቁልፍ ጥያቄዎቹን በመጠየቅ ኢየሱስ ጥያቄዎቹን እንዴት እንደመለሳቸው እንመልከት። 

1. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ትቶአቸው መሄዱ ከሁሉም (የተመረጠው) የነበረው ለምንድን ነው? 

ከሚወዱት ጓደኛ መለየት ሁልጊዜ ከባድ ነገር ነው። ኢየሱስ ተለይቶአቸው መሄዱ ለደቀ መዛሙርት ትልቅ ሐዘን እንደሚያመጣ በመገንዘብ ሊያረጋጋቸው ሞከረ። ትቶአቸው ቢሄድ እንደሚሻል ነገራቸው። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ኢየሱስ በምድር ላይ በተመላለሰበት ወቅት ሥጋዊ አካል ነበረው። ልክ እንደ እኛ ሰው ነበር። የኢየሱስ ሰው መሆን ከሚያስከትላቸው ችግሮች አንዱ በአንድ ጊዜ መገኘት የሚችለው በአንድ ስፍራ ብቻ መሆኑ ነበር። ስለዚህ አንዴ በገሊላ ወይም በኢየሩሳሌም ይሆን ነበር። በአንድ ጊዜ በሁለቱም ስፍራዎች አይገኝም ነበር። ቤተ ክርስቲያን ኈፍጥነት በማደግ ከኢየሩሳሌም ጀምራ ወደ ይሁዳ ሰማርያ በመጨረሻም ወደ ኢትዮጵያ ሁሉ እየተስፋፋች ነበር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ቢፈልጉት በእነዚህ ስፍራዎች ሁሉ በሰብአዊ አካል በአንድ ጊዜ ለወመገኘት አይችልም ነበር። በሌላ በኩል ግን መንፈስ ቅዱስ በሁሉም ስፍራ በአንድ ጊዜ ይገኛል። ሥጋዊ አካል ስለሌለው በአንድ ጊዜ በሁሉም ስፍራ መገኘት ይችላል። በአንድ ጊዜ በኢየሩሳሌምና በኢትዮጵያ መሆን ይችላል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጆች በሙሉ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ህልውና ከእነርሱ ጋር ያለማቋረጥ እንዲሆን እያንዳንዳቸው ከኢየሱስ አካላዊ ህልውና ይልቅ የመንፈስ ቅዱስ ህልውና ያስፈልጋቸዋል። 

20ኛ ጥያቄ፡- አንድ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜ ከእርሱ ጋር እንደሚኖር ማወቅ ለምን ያስፈልገዋል? 

2. መንፈስ ቅዱስ በዓለም ላይ ምን አገልግሎት ይኖረዋል? 

ስለ መንፈስ ቅዱስ ስናስብ ብዙ ጊዜ የሚመጣልን በክርስቲያኖች በኩል ወይም በክርስቲያኖች ውስጥ የሚሰጠው አገልግሎት ነው። ሆኖም ግን ጌታ ኢየሱስ፤ መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ የሚሠራውን ከመናገሩ በፊት በዓለም ላይ የሚሠራውን ነግሮናል። ከመንፈስ ቅዱስ ተቀዳሚ ሥራዎች አንዱ ዓለምን ስለ ኃጢአት መውቀስ ነው። ይህ አባባል መንፈስ ቅዱስ «የዓለምን ጥፋተኛነት ያጋልጣል» ተብሎ ሊተረጐም ይችላል። መውቀስ ለሚለው ቃል የግሪኩ ትርጉም የሚያመለክተው በችሎት የተቀመጠ አንድ ጳኛ በተከሳሽ ላይ የቀረበበትን ማስረጃ በሙሉ ተመልክቶ በተከሳሹ ላይ የጥፋተኝነት ብያኔ ማወጁን ነው። መንፈስ ቅዱስ በዓለም ባለው አገልግሉቱ ይህ ዓይነቱን የዳኝነት ሥራ የሚሠራው ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኞች መሆናቸውና ከእግዚአብሔር ፍርድ ሊያመልጡ አለመቻላቸው እንዲሰማቸው በማድረግ ነው። በሚገባ ስላላወቅን ነው ብላው ሰበብ በማቅረብ ሊናገሩ አይችሉም። የኃጢአት ይቅርታ የሚያስፈልጋቸው ኃጢአተኞች መሆናቸውን ያውቃሉ። 

ጥያቄ፡- አንድ ክርስቲያን ያልሆነ ሰው ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ጥፋተኛ መሆኑን መገንዘቡ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? 

ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች ሌሎች ሰዎች ኃጢአተኛች መሆናቸውንና ንስሐ ካልገቡ በስተቀር እግዚአብሔር የዘላለም ሞት እንደሚፈርድባቸው ለመናገር እንፈራለን። ይህ መልእክት ሰዎችን በእኛ ላይ በቁጣ እንዲሁ ያደርጋል። እኛም እንዳንድ ጊዜ ይህ ጭከና ነው ብለን እናስባለን። ነገር ግን የእኛን ቃል ወስዶ የድነት (ደኅንነት)ን እስፈላጊነት በማሳየት ሰዎችን ወደ ክርስቶስ መምራት የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው። አንድ በሽተኛ መታመሙን እስካላረጋገጠ ድረስ ሕክምና ፍለጋ ወደ ሐኪም አይሄድም። እንዲሁም አንድ ኃጢአተኛ ጥፋተኛ መሆኑንና በጥፋቱ ምክንያት ከእግዚአብሔር የዘላለም ቅጣት እንዳለበት ካልተገነዘበ በስተቀር ለመቼውም ወደ ክርስቶስ እይመለስም። 

የመንፈስ ቅዱስ የወቀሳ አገልግሎት በሦስት ይከፈላል። 

ሀ. ዓለምን ስለ ኃጢአት ይወቅሳል፡- ይህ አሳብ ከመጀመሪያው ሰዎችን ስለ ጥፋታቸው ስለመውቀስ ከተነገረው ጋር በጣም የተቀራረበ ነው። ኢየሱስ የሚናገረው የኃጢአተኛነታችን ውጤት ሆኖ በየዕለቱ ስለምንሠራቸው በርካታ ኃጢአቶች አይደለም። ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ በአንድ ዋና ኃጢአት፥ ያም «ያለማመን ኃጢአት» ላይ እንደሚያተኩር ተናገረ። ሰዎች ወደ ገሃነም የሚሄዱት ኃጢአተኞች ስለሆኑ አይደለም። ወደ ገሃነም የሚጣሉት ባለማመናቸው ምክንያት ብቻ ነው። ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን። ሁላችንም የገሃነም ፍርድ ይገባናል። ነገር ግን ዘላለማዊ ቤታችን ገሃነም ወይም መንግሥተ ሰማያት እንዲሆን የሚወስነው ኃጢአት የአለማመን ኃጢአት ነው። ኢየሱስን በማመን በመስቀል ላይ የከፈለውን መሥዋዕትነት ካልተቀበልን በስተቀር መድኃኒት ቢኖርም እንኳ መድኃኒቱን አልወስድም ማለትም መሥዋዕትነቱን አለመቀበላችን ነው ወደ ኩነኔ የሚወስደን። ስለዚህ ከመንፈስ ቅዱስ ዋነኛ አገልግሎቶች አንዱ የማያምኑ ሰዎችን ጥፋተኛ የሚያደርጋቸውና የዘላለምን ፍርድ የሚያመጣባቸው ያለማመናቸው ውጤት መሆኑን ማሣየት ነው። 

ያለማመን ኃጢአት እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ድነት (ደኅንነት) እጦት የሰጠውን ምላሽ እምቢ ማለትና ወደ ሌሎች የድነት (ደኅንነት) መንገዶች በማዘንበል የሚደረግ የሕሊና ውሳኔ ነው። ብዙ ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያደርስ መንገድ ለራሳቸው በማበጀት ወይም የተለያዩ ዓይነት አማልክትን በመፈልሰፍና እነርሱን ደስ በማሰኘት ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ይሞክራሉ። ነገር ግን ይህን ሲያደርጉ «እግዚአብሔር ሆይ፥ የአንተን መንገድ እንፈልግም እኛ የምንፈልገው በዚያ ፈንታ የራሳችንን መንገድ ነው» ማለታቸው ነው። ይህ ዓመፃ ነው እግዚአብሔር ደግሞ ዓመቱን ሁሉ በዘላለም ሞት ይቀጣል። 

ለ. ዓለምን ስለ ጽድቅ ይወቅሳል፡- ክርስቲያኖች ጽድቅ የሚለውን ቃል ብዙ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ ይረዱታል። መሠረታዊ ትርጉሙ በመልካም ሥነምግባር መኖር ይመስላቸዋል። ጻድቅ የሚለው የግሪክ ቃል ከመንበረ ችሎት የተወሰደ ሌላው የሕግ ቃል ነው። ትርጉሙም ‹ጥፋተኛ አይደለም) የሚል ምስክርነት ከእግዚአብሔር ማግኘት ማለት ነው። ይህ ምስክርነት እንዴት ሊገኝ ይችላል? የሰው ልጆች፥ የተቻለንን ያህል ሕግን ስለምንጠብቅና መልካም ስለሆንን ጻድቆች ነን ብለው በማሰብ ክእግዚአብሔር ዘንድ ምስክርነትን ለማግኘት ይጥራሉ። ሰው በእግዚአብሔር ፊት «ጥፋተኛ አይደላህም» ሊባል የሚችልበት አንድ መንገድ ብቻ አለ። ይህም መንገድ የኃጢአታችን ዋጋ (ያለማመን ኃጢአትና ሌላ ማንኛውም ኃጢአት) በሌላ ሰው ከተከፈለ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ «የኃጢአት ዋጋ ሞት ነው» ይላል (ሮሜ 6፡23)። ኢየሱስ በመስቀል ላይ በመሞትና የኃጢአታችንን ዋጋ በመክፈል ጽድቃችን ሆነ (ሮሜ 5፡19)። መንፈስ ቅዱስ በእንድ ሰው ልብ ካልሠራና ያ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስን ጽድቅ ካልተቀበላ ጻድቅ ለመሆን አይችልም። 

ኢየሱስ ስለ ኃጢአት የከፈለው መሥዋዕትነት በእግዚአብሔር ዘንድ ለኃጢአት ዕዳ የተከፈለ ዋጋ ለመሆኑ የመጨረሻው ማረጋገጫ ምን ነበር? የመስቀል ሞት አልነበረም። ኢየሱስ ሞቶ ቢቀር ኖሮ እግዚአብሔር ይህን መሥዋዕትነት ይቀበላው እይቀበላው አይታወቅም ነበር። ይልቁኑ የመጨረሻው ማረጋገጫ ኢየሱስ ከሙታን በመነሣቱና ወደ ሰማይ ዐርጐ በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጡ ነው። ትንሣኤና ዕርገቱም እግዚአብሔር መሥዋዕቱን ለመቀበሉ ምልክት ሆኖ በዚህም ሰዎች በማመን ጽድቅን የሚያገኙበት መንገድ እንደሆነ አጸደቀ። በትንሣኤ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ እንዲህ ብሎ አውጇል። «ኃጢአትህ ይቅር እንዲባልና ጻድቅ እንድትሆን ከፈለግህ ልጄ በመስቀል ላይ የከፈለውን መሥዋዕትነት በመቀስል ለአንተ ያዘጋጀልህን ጽድቅ ውሰድ።» በሰው ልብና አእምሮ ውስጥ በመሥራት ይህን እውነት ወደ ሚረዳበትና ወደ ሚቀበልበት ነጥብ ማድረስ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ነው። 

ሐ. ስለ ፍርድ ዓለምን መውቀስ፡- አንድ ነገር ወይም አንድ ሰው መልካም ወይም ክፉ እንደሆነ በይፋ የሚነገርበት ሂደት ፍርድ ይባላል። ስለዚህ ከመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች አንዱ ዓለም (ለማያምኑ ሰዎች) የሚቀበለው ፍርድ የጥፋተኛነት» ወይም «ጥፋተኛ ያለመሆንን መሆኑን ማመን ነው። ኃጢአትና ኩነኔ ባለበት እግዚአብሔር ሁልጊዜ የበደለኝነት ፍርድን ያውጃል። ስለዚህ ሰዎች ኃጢአተኞች ከመሆናቸው የተነሣ በደለኞች እንደሆነ ዮስጠንቀቁ ሥራ የመንፈስ ቅዱስ ነው። ስለዚህ ከራሳቸው ጽድቅ ውጭ ሌላ ጽድቅ ካላገኙ በስተቀር ቅጣት ይቀበላሉ። 

ፍርድ በሰዎች ሁሉ ላይ የሚመጣ ቢሆንም (2ኛ ቆሮ. 5፡10)፥ በኢየሱስ የተጠቀሰው ፍርድ ቀን የሚመጣው በሰው ላይ ሳይሆን «የዚህ ዓለም ገዥ » በሆነው በሰይጣን ላይ ነው። ሰይጣን «አሁን የተኮነነ» ስለሆነ ይህ ፍርድ የሚፈጸመው ገና ወደፊት አይደለም። ተከናውኗል። ኢየሱስ በዚህ ስፍራ የሚናገረው ከጥቂት ሰዓታት በኋላ መፈጸም ስለነበረበት ፍርድ ነው። በሰይጣንና ሰይጣን ወደ ሰው ልብ በሚያዛምታቸው፥ እንደ ትዕቢት፥ ቅናት፤ ጥላቻ ዓመፅና አለማመን በመሳሳሉ ላይ የመጨረሻው ፍርድ የታወጀው በመስቀል ነው። የዚህ ሁሉ ምንጭ ሰይጣን ነው። ምንጩ ሊፈረድበት የሰይጣን ፍሬ የሆኑት እዚህ ከላይ የተጠቀሱት ኃጢአቶች ይፈረድባቸዋል። ሰይጣን በሰው ልጅ ላይ የነበረውን ኃይል እግዚአብሔር ያነግበት መንገድ መስቀሉ ነው። እነዚህ ኃጢአቶች ሊሸፈኑ እንደቻሉ የታወጀበት መንገድ መስቀሉ ነው። ሰይጣን ሊቀበለው ካለው ዘላለማዊ ፍርድ ያመልጡ ዘንድ እውነተኛው ጽድቅ ለሰዎች የሚሰጥበት የእግዚአብሔር መንገድ መስቀሉ ነው። 

ጥያቄ፡– አንድ ሰው ከማመኑ በፊት መንፈስ ቅዱስ እነዚህን ሦስት ነገሮች በሰውዬው ሕይወት መሥራት ያላበት ለምንድን ነው? 

ብዙ ሰባኪዎች ሰዎች ወደ ኢየሱስ ሲመለሱ ችግራቸው ሁሉ እንደሚቃላል፥ ሃብታምና ጤነኛ እንደሚሆኑ መስበክ ይወዳሉ። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ የሚሰብከው ይህን አይደለም። መንፈስ ቅዱስ የሚሰብከው ስለ ኃጢአት፥ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ የሚደረገውን ወቀሳ ነው። አንድ ሰው የችግሮቹ ሁሉ ሥር ለሆነው ኃጢአቱ ፈውስ ሊያገኝ የሚችለው ሰቅዱስ እግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኛ መሆኑን አንዴ ከተረዳ በኋላ በኢየሱስ ሞት የተሰጠውን የመስቀል ጽድቅ ሲፈልግና ከዘላለማዊ ፍርድ ሲያመልጥ ብቻ ነው። ኢየሱስ እንደምንሰደድ አስቀድሞ ተናግሯል። ሀብትና ጤንነትን እንደምናገኝ ቃል አልገባልንም። ነገር ግን ከፈራጁ ከእግዚአብሔር ፊት በምንቆምበት ጊዜ ‹ከበደል ነ› የመሆን ፍርድን እንደምንቀናጅ፥ የዘላለም ሕይወትና ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም እንደሚኖረን ቃል ገብቶልናል። 

ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ይህን አገልግሎት የሚሰጠው እንዴት ነው? መንፈስ ቅዱስ ይህን የመውቀስ አገልግሎት አንዳንድ ጊዜ ፍጹም ከሰው ነፃ ሆኖ በራሱ መንገድ ቢያከናውንም ብዙ ጊዜ ግን ሁለት መንገዶችን ይጠቀማል። በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ቃል ይጠቀማል፤ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ሐዋርያት ቃሉን እንደሰበኩ ሰዎችም እንዳመኑ ተጽፏል። ወንጌልን ለማብራራት የእግዚአብሔርን ቃል በጥንቃቄ መጠቀም አለብን። 

ከዚህ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ይህን ቃል የሰዎችን ልብ ለመታለ ይጠቀምበታል። በሁለተኛ ደረጃ የሰዎችን ምስክርነት ይጠቀማል። የእግዚአብሔር አምባሳደሮች ስለሆንን መንፈስ ቅዱስ የምንናገረውን ቃል ሰዎችን ለመውቀስ ይጠቀምበታል። ቃላችን ሰዎችን ከቶውንም መውቀላ አይችልም ነበር። መንፈስ ቅዱስ ግን ቃላችንን በመጠቀም ሰዎችን ስለ ኃጢአት፥ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ይወቅሳል። 

ጥያቄ፡- ሀ) ለማያምኑ ሰዎች ለመመስከር የእግዚአብሔርን ቃል ለመጨረሻ ጊዜ የተጠቀምከው መቼ ነበር? ለ) ወመንፈስ ቅዱስ የማያምኑትን ወደ ክርስቶስ ለማምጣት የእግዚአብሔርን ቃልና አንተን የተጠቀመው እንዴት ነበር? 

3. መንፈስ ቅዱስ ከእያንዳንዱ ደቀ መዝሙር ጋር ምን አገልግሎት አለው? 

አንድ ሰው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የድነት (ደኅንነት)ን ግንኙነት እንዲመሠርት እግዚአብሔር የሚጠቀምበት ዋና መሣሪያ መንፈስ ቅዱስ ነው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ እራሱ ደሞ በእማኝ ሕይወት ውስጥ እጅግ ጠቃሚ እገልግሎት አለው። ክርስቲያኖችን ወደ እውነት የሚመራው የእውነት መንፈስ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ነው። እርሱ መምህራችን ነው። መማር ደግሞ ጊዜ ይጠይቃል። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርት ጋር የቆየው 3 /2 ዓመት ብቻ ነው። ሆኖም ሊያስተምራቸው የሚፈልገው በርካታ ነገር ነበረው። ነገር ግን ወደ ሰማይ ሊያርግ ስለነበር ይህን እንዴት ነበር የሚያደርገው? በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ያስተምራቸዋል። ኢየሱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ የተናገረውን ስናስተውል መንፈስ ቅዱስ በራሱ መለኮታዊ ጥበብ እይናገርም ብሏል። የሚናገረውና የሚያስተምረው በሙሉ የሚመጣው ከኢየሱስ ነው። ይህ ማለት መንፈስ ቅዱስ አሁን የኢየሱስ አፍ ሆኗል ማለት ነው። በሌላ አነጋገር የኢየሱስ አፈ-ቀላጤ ነው ማለት ነው። ኢየሱስ ሊያካፍለን የሚፈልገውን ነገር ለእኛ መናገር የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው። 

ከትናንትናው ትምህርታችን እንደምታስታውሰው መንፈስ ቅዱስ ከሚያደርጋቸው ነገሮች አንዱ ደቀ መዛሙርትን ኢየሱስ ስላስተምራቸው ነገር ማሳሰብ ነበር። ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ይህን ስላ አራቱ ወንገላት መፍ መናገሩ ነበር ብለው ያስባሉ። ኢየሱስ በተጨማሪ እርሱ በሰማይ በሚሆንበት ጊዜ በምድር ያሉ ደቀ መዛሙርቱ እንዲያውቁ የሚፈልገውን እውነት መንፈስ ቅዱስ እንደሚያስተላልፍላቸው ተናግሯል። ይህ ደግሞ ከሐዋርያት ሥራ እስከ ይሁዳ ስላሉት መልእክቶች መናገሩ ሳይሆን አይቀርም። በመጨረሻም መንፈስ ቅዱስ ሊመጣ ስላለው ነገር እንደሚነግራቸው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርት ነገራቸው። ይህ ደግሞ ለለ ራእይ መጽሐፍ መናገሩ ይመስላል። 

ይሁን እንጂ ይህ የመንፈስ ቅዱስ የማስተማር አገልግሎት ዛሬም ቢሆን ይሠራል። አንዳንድ ጊዜ ለአማኞች በቀጥታ በመናገር ያዝዛቸዋል፥ ይመራቸዋል፥ ያስተምራቸዋል። ብዙ ጊዜ ግን መንፈስ ቅዱስ የሚጠቀመው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ወይም በሰባኪ በኩል የሚነገረውን የእግዚአብሔር ቃል ነው። አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በሚያነብበት ወይም በሚሰብክበት ሰዓት ቁጭ ብለን እያዳመጥን ልባችን ሊነካና እግዚአብሔር ሊያስተምረን ወይም ምን ማድረግ እንዳለብን ሲናገረን የሚካሄደው የመንፈስ ቅዱስ የማስተማር አገልግሎት ነው። በ2ኛ ጢሞ. 3፡16 እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን። «የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።» እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለእኛ የሚናገርበት ተቀዳሚ መንገድ በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) መንፈስ ቅዱስ በቃሉ አማካይነት እንዲናገርህ የእግዚአብሔርን ቃል በማንበብ በሳምንት ምን ያህል ጊዜ ታሳልፋለህ? ለ) ለመጨረሻ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለአንተ የተናገርህን (ሁኔታ) ግለጽ። 

4. ኢየሱስን አስመልክቶ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ምንድን ነው? 

ጥያቄ፡- ሀ) ወደ ፀሐይ ተመልክተህ ታውቃለህን? ዓይንህን ምን አደረገችህ? ለ) ፀሐይ ለሕይወት አስፈላጊ የሆነችው ለምንድን ነው? 

እግዚአብሔር ከፈጠራቸው እጅግ ጠቃሚ ነገሮች እንድዋ ፀሐይ ናት። ያለ ፀሐይ ሕይወት ፈጽሞ አይኖርም። ያለ ፀሐይ እግዚአብሔር የፈጣራቸውን ውብ ነገሮች ሁሉ ለማየት እንችልም። ወደ ፀሐይ ከተመለከትን ግን ነገሮች ይጠቁሩና ለማየት ይሳነናል። እንዲያውም ለረጅም ጊዜ ለማየት ብንሞክር ዓይናችን ሊጠፋ ይችላል። እግዚአብሔር ፀሐይን የፈጠራት እንድንመለከታት ሳይሆን በምትሰጠን ጥቅሞች ደስተኛ ሆነን እንድንኖር ነው። 

መንፈስ ቅዱስ የሚሠራውም በዚሁ ዓይነት መንገድ ነው። በዮሐ. 16፡14-16 ኢየሱስ የመንፈስ ቅዱስ ዓላማ በእራሱ ላይ እንድናተኩር ሳይሆን በኢየሱስ ላይ እንድናተኩር መሆኑን ይናገራል ። መንፈስ ቅዱስ ክብርን ለኢየሱላ እንጂ ለራሱ አያመጣም። ስለዚህ ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ የሚናገረው ቃል የእኔ ነው በማለት ገልጾአል። በተጨማሪ መንፈስ ቅዱስ ጥረቱ እራሱን ሳይሆን ኢየሱስን ማክበር ነው። መንፈስ ቅዱስ የሚሠራው ሥራ የሚመነጨው ከራሱ ሳይሆን ከኢየሱስ ነው፡፡

ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ ላይ የመመርኮዝና ትምህርቶቻቸውን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የመመሥረት አደጋ ላይ ይገኛሉ። ይህ በአንድ በኩል መልካም ነው። ያለ መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተዘጋጁልን በረከቶች ለእኛ ሊሆኑ አይችሉም። የእግዚአብሔርን በረከተች እንድንለማመድና እንድንደሰትባቸው የሚያደርግ መንፈስ ቅዱስ ነው። ነገር ግን ትኩረታችንን ሁሉ ወደ መንፈስ ቅዱስ ከመለስን በቅጽበት እንታወራለን። መጽሐፍ ቅዱስ ከትኩረታችን ውስጥ ይጠፋል። ሚዛናዊነታችንን እንላቅና አንዳንዶቻችን ስሕተት ላይ እንወድቃለን። በዚያ ምትክ ዓይኖቻችንን ኢየሱላ ላይ ማድረግና መንፈስ ቅዱስ ላኢየሱስ ክብርን ያመጣ ዘንድ ልንፈቅድ ይገባናል። ይህ ሲሆን ሕይወት ና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በሙሉ በተስተካከለ ሚዛን ላይ ይሆናሉ። 

ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ ፍቅር ከመወሰዳቸው [የተነሣ ዓይኖቻቸውን በኢየሱስ ላይ ማድረግና ለእርሱ ክብርን መስጠት ያልቻሉበትን ሁኔታ ያየኸው እንዴት ነው? ለ) ይህ ጉዳይ እንዳንድ ጊዜ 1 የሥነ መለኮት ሚዛናቸውን ያሳጣቸው እንዴት ነው? 

በወንጌላት ውስጥ ስለ መንፈስ ቅዱስ የተሰጡ ሌሎች ትምህርቶች 

መንፈስ ቅዱስ ከአማኞች ጋር ስላለው ግንኙነት የሚናገሩ ሌሎች ጥቅሶችን ስንመረምር አንዳንድ እጅግ ጠቃሚና የሚስቡ እውነታዎችን እናገኛለን። የሚከተለውን ማጠቃለያ አጥኑ። 

ሀ. ማቴ. 10፡17-20፡– አማኞች ስለ ኢየሱስ በሚመሰክሩበት ጊዜ በተለይ ደግሞ በመንግሥት ባለሥልጣኖች ፊት በስደት ምክንያት ተከሰው በሚቀርቡበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ውስጥ የሚናገር የእማኞች አፈ ቀላጠ ነው። 

ለ. ኢየሱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ የሰጣቸው ሌሎች ትምህርቶች መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርት ላይ እንደሚወርድ ኢየሱስ ከሰጠው የተስፋ ቃል ጋር የተያያዙ ናቸው። ከእግዚአብሔር ዋና ስጦታዎች አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው (ሉቃስ 11፡13)። መንፈስ ቅዱስ ከሰው ልብ የሚወጣና ያለማቋረጥ የሚፈስስ የበረከት ጅረትን ይመስላል (ዮሐ ፡37፡-39)። በተጨማሪ ለሰዎች ሁሉ ይመሰክሩ ዘንድ አስፈላጊውን ኃይል ይሰጣቸዋል (የሐዋ. 1፡8)። 

ሐ. ኢየሱስ በደቀ መዛሙርት ላይ እፍ በማለት መንፈስ ቅዱስ እስከ ወረደበት እስከ ስዓለ ኀምሳ ቀን ድረስ የሚያላግላቸውን ጊዜያዊ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ሰጣቸው (ዮሐ 20፡22)። ይህ ለመረዳት እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ክፍል ነው። ግልጽ የሆነው ጉዳይ በጊዜው ተሰጥቶአቸው የነበረው መንፈስ ቅዱስ በሙላት አለመሆኑ ነው። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ በሙላት የወረደው ከ50 ቀን በኋላ በጴንጠቆስጤ ዕለት ስለነበረ ነው። እና ምን ሆነ? አንዳንድ ሊቃውንት በጴንጠቆስጤ ቀን መንፈስ ቅዱስን ስሙላት እስኪቀበሉ ድረስ ለጊዜው መንፈስ ቅዱስ ተሰጥቷቸው ነበር ይላሉ። 

ነገር ቀን ይህ ጥቅስ ከሐዋ 1፡8 ጋር የሚያያዝ መሆኑ ይበልጥ አሳማኝ ነው። ኢየሱስ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከመሄዱ ጥቂት ቀደም ብሎ የመጨረሻዎቹን ትእዛዛት ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው። የመጀመሪያው ትእዛዝ ደቀ መዛሙርት የተማሩትን ነገር ለራሳቸው ብቻ መያዝ እንደሌለባቸው የሚያመላክት ነበር። ይልቁኑ ስለ ኢየሱስ ሕይወት፥ ሞትና ትንሣኤ በዓለም ሁሉ ምስክር መሆን ነበረባቸው። ነገር ግን ይሄን እንዴት ማድረግ ይችሉ ነበር? እንዴት መጓዝ ነበረባቸው? የባሕልና የቋንቋ ልዩነት ገደቦችን ማላፍ የነበረባቸው እንዴት ነው? ይህ እግዚአብሔር በሚሰጣቸው መንፈስ ቅዱስ ህልውናና ኃይል የሚከናወን ነበር። በመጀመሪያ በተምሳሌት እፍ ካለባቸው በኋላ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ እንደሚወርድ ነገራቸው። ይህ ተምሳሌታዊ ድርጊት ሁለት ዓላማዎች ነበሩት፡- ሀ) ኢየሱስ በደቀ መዛሙርት ላይ እፍ ያላባቸው መንፈስ ቅዱስ ባይታይም አብሮአቸው እንዳለ ለማመልከት ነው። አስታውሱ፡= በግሪክ ቋንቋ እስትንፋስና መንፈስ አንድ ዓይነት ቃል ናቸው ለ) ደግሞም መንፈስ ቅዱስ የሚመጣው በኢየሱስ ፈቃድና ትእዛዝ መሆኑን የሚያመለክት ነበር። እፍ እንዳለባቸው ሁሉ የእግዚአብሔር እስትንፋስ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው ነበር። በሁለተኛ ደረጃ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርትና በእማኞች ሁሉ ላይ እንደ ታላቅ ነፋስና እሳት ሆኖ ወረደ። 

ኢየሱስ የመንፈስ ቅዱስን መምጣት ለሌሎች ከመመስከር ጋር አያይዞ መናገሩን ልብ ማለት እጅግ ጠቃሚ ነው። እንደገና በቤተ ክርስቲያን ዘመን የመንፈስ ቅዱስ ተቀዳሚ ዓላማ ምንድን ነው? ወደሚለው ጉዳይ እንመለሳለን። መንፈስ ቅዱስ ደቀ መዛሙርት ብዙ ተአምራት እንዲያደርጉ የፈቀደ ቢሆንም እንኳ ተቀዳሚ ዓላማው ተአምራትን ማድረግ አልነበረም። ይልቁኑ የእርሱ ዓላማ ለእግዚአብሔር ክብርን በሚያመጣ መንገድ እንዲኖሩና እንዲመሰክሩ መርዳት ነበር። 

ጥያቄ፡- ሀ) የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከምስክርነት አገልግሎት ጋር መቆሙ በሕይወትህ ምን ያህል ተረጋግጦአል? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ በመላው ኢትዮጵያ ምስክር በመሆን የመንፈስ ቅዱስን ህልውና እያረጋገጠች ያላችው እንዴት ነው? 

ጥያቄ፡- ማቴ. 12፡22-32 አንብብ። ሀ) ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ስለሚደረግ ኃጢአት እንዲናገር ያስገደደው ሁኔታ ምን ነበር? ለ) አጋንንትን ማውጣት የምን ማረጋገጫ ነበር? ሐ) በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚደረግ ኃጢአት ነው ብሎ ኢየሱስ የተናገረው ስለ ምን ይመስልሃል? መ) ሰዎች ካደረጓቸው ኃጢአቶች ይቅር የማይባሉ ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን አንዳንዶቹን ኃጢአቶች ዘርዝር። 

መ. በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚደረግ ኃጢአት 

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ለሁሉም ለማሳየት ብዙ ተአምራትን እድርጓል። ሰዎችን ፈውሷል፥ አጋንንት አውጥቷል፥ ሰዎችን ከሞት አስነሥቷል። ይህም በጉዳዩ ላይ ሰዎች ሁለት ምርጫ ብቻ እንዲኖራቸው አድርጓል። ይኸውም፥ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር የተላከ መሆኑን ማመን፡ አለበለዚያ ደግሞ ኃይልን ያገኘው ከሰይጣን እንደሆነ ማመን ነበረባቸው። የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስ ከእግዚአብሔር የተላከ መሆኑን ከማመን ይልቅ ኢየሱስ አጋንንት እንዳደረበትና አጋንንትን የሚያወጣው በብዔል ዜቡል ኃይል ነው በማለት መወንጀልን መረጡ። ብዔል ዜቡል የሰይጣን ሌላው ስሙ ነው። ሰይጣን ኢየሱስ እጋንንትን እንዲያወጣ በመፍቀድ የራሱን መንግሥት ሊያፈርስ እንደማይችል በመግላጹ ኢየሱስ እባባላቸውን ዋጋ ቢስ አድርጓል። ቀጥሎም ኢየሱስ ለሕዝቡ ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው። ይኽውም እርሱን ቢሰድቡትም እንኳ ይቅርታን ለማግኘት ዕድል እንደሚኖራቸው፤ ነገር ግን ያደረጋቸው ተአምራት በመንፈስ ቅዱስ መሆናቸውን ክደው በሰይጣን የተደረጉ ናቸው ካሉ፥ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአትን ስለሚያደርጉ ይቅርታ የሌለውን ኃጢአት በመፈጸማቸው እደጋ ላይ እንደሚገኙ ማስጠንቀቁ ነበር። 

በዘመናት ሁሉ ውስጥ ክርስቲያኖች ይህ ይቅር የማይባል ኃጢአት ምን እንደሆነ በማሰብ ኖረዋል። በስደት ምክንያት እምነታቸውን የተው አንዳንድ ሰዎች ይህን ይቅር የማይባል ኃጢአት እንደሠሩ ይገምታሉ። ሌሎች በምንዝርና ኃጢአት ሊወድቁ ይህን ይቅር የማይባል ኃጢአት እንደሠሩ ያስባሉ። ይህ ይቅር የማይባል ኃጢአት ምንም ይሁን ምን የሚከተሉትን ነጥቦች መገንዘብ አለብን። 

1. ከኃጢአቱ ታላቅነት የተነሣ እግዚአብሔር ይቅርታ የነፈገው ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም። በመስቀል ላይ የነበረው ወንበዴ ይቅርታን ተቀብሏል (ሉቃስ 23፡40፡43)። በምንዝር የተያዘችው ሴት የኃጢአት ይቅርታን አግኝታለች (ዮሐ 8፡10–11)። እምነቱን የካዳውና ኢየሱስን ፈጽሞ አላውቀውም ብሎ የተናገረው ጴጥሮስ እንኳ ይቅርታን አግኝቷል ( ዮሐ 21፡15-19)። ይቅርታ የማይደረግላቸው ኃጢአቶችን እንዳይሠሩ ለሰዎች የተሰጡ ሌሎች ማስጠንቀቂያዎች አሉ (ለምሳሌ ዕብ 6፡4-6፤ 10፡26-30)፥ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይቅርታ ሊያገኝ አይቻልም ተብሎ የተጠቀሰ አንድም ሰው የለም። 

2. ኢየሱስ በአጽንኦት የሚናገረው በዓለም ላይ ሁለት ጎራዎች ብቻ የመኖራቸውን እውነት ነው። እነዚህም፥ ከሰይጣን ወገን የሆኑና ከኢየሱስ ወገን የሆኑ ሰዎች ናቸው። ሰዎች ላኢየሱስ ምላሽ ሳይሰጡ መሐል ሰፋሪ ሆነው ሊቀሩ አይችሉም። በሰይጣንና በኢየሱስ መካከል ባለ ጦርነት ሰዎች ሁሉ ከሰይጣን ወይም ከኢየሱስ ወገን ይሆናሉ። ከዳር ቆመው የሚመለከቱ የዋሆች አይኖሩም። ኢየሱስን የሚቃወሙም ሆኑ ከኢየሱስ ተቃራኒ የሆኑ ያው ከሰይጣን ወገን ናቸው ማለት ነው። 

3. ኢየሱስ እየተናገረ ያለው ሰለ ቀላል የኃጢአት ዓይነት አይደለም። ኢየሱስ ለአይሁድ ታላቅ ኃጢአት የሆነውን ሊያስረዳ እግዚአብሔርን መሳደብ የሚለውን ሐረግ ይጠቀማል። ይህ አሳብ እግዚአብሔርን በመቃወም በግልጽ መናገርን ያመለክታል። በብሉይ ኪዳን የኃጢአት መሥዋዕት ሊቀርብላቸው ከማይችሉ ኃጢአቶች አንዱ ነበር። 

ስለዚህ ይቅር ለማይባል ኃጢአት ሊቃውንት ያላቸው የተለያዩ አሳቦች ታዲያ ምንድን ናቸው? የሚከተሉት ሁለት ዋና አተረጓጐሞች ናቸው። 

1 በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚደረግ ኃጢአት መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ በኩል የሠራቸው ተአምራት የሰይጣን ናቸው ማለት ነው። ይህ አመለካከት የተመሠረተው በኢየሱስ በሕይወት ዘመን መንፈስ ቅዱስ ይንቀሳቀስ : እንደነበርና «የተአምራት ዘመንም» የተፈጸመው በዚህ ጊዜ ነበር በሚል አሳብ ላይ ነው። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ በኩል ይሠራ የነበረውን ተአምራት እያዩ ኢየሱስን እለማመን ወይም ኢየሱስ እነዚህን ተአምራት ያደረገው በሰይጣን ኃይል ነው ብሎ መናገር ይቅር የማይባል ኃጢአት ነበር። አባባሉ ኃጢአት የተሰኘበት፥ ኢየሱስ በሥጋዊ አካል ሳለ ታምራቱን ያደረገው በሰይጣን ኃይል ነው በማለት የተነሣ ስለነበር፥ እነዚህ ሊቃውንት ኃጢአቱ ሊፈጸም የሚችለው በኢየሱስ የሕይወት ዘመን ብቻ ነው ብለው ይናገራሉ። ስለዚህ ይቅር የማይባል ኃጢአት ዛሬ መሥራት አይቻልም። 

2. ኢየሱስ እየተናገረ ያለው በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚደረግ ኃጢአት እያወቁ ሆን ብሎ እውነትን ያለመቀበል ነው። በትክክለኛው አባባል እውነትን ውሸት ነው፤ መልካምን ነገር ደግሞ ክፉ ነው ማለት ነው። ፈሪሳውያን ኢየሱስ “መልካ እንደነበር ያውቃሉ። ተአምራትን ያደረገው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መሆኑንም ያውቁ ነበር። ነገር ግን እያወቁ እውነቱን ላለመቀበል ወሰኑ። እንዲያውም ኢየሱስን የክፋት ምንጭ አደረጉት። እነዚህ ሊቃውንት የሚሉት በኢየሱስ ላይ የሚደረግ ኃጢአት ካለማመን የተነሣ ወንጌልን ያለመቀበል ኃጢአት እንደሆነ ነው። በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚደረግ ኃጢአት፥ የወንጌልን እውነት እያወቁና በወንጌል እንቅስቃሴም ውስጥ በማለፍ እውነትነቱን እንኳ እየመሰከሩ ሆን ብሎ በወንጌል ላይ ጀርባን ማዞርና መካድ ነው። ይህ አመለካከት እንደሚለው አንድ ሰው እውነትን እያወቀ አልቀበልም ሲልና እውነትን ባለመቀበሉ ጸንቶ ቢኖር ልቡ እየጠነከረ በመምጣት ንስሐ ሊገባ እስከማይችልበት ደረጃ ድረስ ሊደነድን እንደሚችል ነው። ንስሐ ሳይገባም ይሞታል። ስለዚህም ዕድሉ የተዘጋ ስለሆነ ኢየሱስ የሰጠውን ይቅርታ ፈጽሞ ሳይቀበል ይቀራል። ይቅር ያልተባለው እግዚአብሔር ይቅር ሊለው ፈቃደኛ ስላልሆነ እይደለም። ነገር ግን ይቅርታን ለመጠየቅ ፈቃደኛ ካለመሆኑ የተነሣ እራሱን በመኮነኑ ነው። ጴጥሮስና ይሁዳ የሚመሳሰሉበት መገንድ አለ። ለ 3 1/2 ዓመታት ከኢየሱስ እግር ሥር ሆነው በመማርና ተአምራቱን በመመልከት ኖረዋል። በመጨረሻ ሁለቱም ኢየሱስን በመካዳቸው የሠሩት ኃጢአት ተመሳሳይ ሆነ። አንደኛው ሲክደው ሌላኛው አሳልፎ ሸጠው። ነገር ግን ጴጥሮስ ይቅር ሲባል ይሁዳ ይቅር አልተባለም። ልዩነቱ ምንድን ነበር? እግዚአብሔር ይሁዳን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ያለመሆኑ ነበርን? አልነበረም። እንደኛው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታን ለመቀበል ወደ እግዚአብሔር ዘወር አለ። ሌላኛው ከእግዚአብሔር በመሽሽ እራሱን ሰቅሎ ሞተ። እንደዚሁም ኢየሱስን ካደው። የሚሞቱ ሰዎች የመጨረሻውን ኃጢአት ስለሚፈጽሙ ንስሐ ለመግባት ፍጹም አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን አንድ የማያምን ሰው ወንጌልን አልቀበልም ሲል ልቡ መደንደን ይጀምራል። ባለማመኑ እየጠነከረ ሲሄድ ንስሐና እምነት ፈጽሞ ወደ ማይቻሉበት ደረጃ ይደርሳል። በእምቢተኝነት መጽናት ይቅር ወደማይባል ኃጢአት ማለትም ኢየሱስን ወደ አለማመን ያደርሳል። 

ስለዚህ ይቅርታ ስለሌለው ኃጢአት የተጀመረው ክርክር ያለማቋረጥ እንደሚቀጥል ጥርጥር የለውም። አንድ እውነት ግን ግልጽ ነው። ኃጢእቱ የፈለገውን ያህል ታላቅ ቢመስልም፥ ለይቅርታ ወደ እርሱ የሚመጣውን ኃጢአተኛ ኢየሱስ ከቶ አይተወውም። ዝሙት፡ ነፍስ መግደል፥ በስደት ምክንያት ለጊዜው ጌታን መተው፥ ሁሉም ይቅርታ ሊያገኙ ይችላሉ። ችግሩ ያለው እግዚአብሔርን ይቅር የማለት ፍቃደኛነት ማምጣቱ ላይ አይደለም። ችግሩ ያለው ሰዎች እግዚአብሔርን ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ ያለመሆናቸው ላይ ነው፡፡ 

ጥያቄ፡- ሀ) አንድ ሰው ወንጌል እውነት መሆኑን እያወቀ ሊቀበለውና ሊኖርበት ፈቃደኛ አለመሆኑን ያያችሁት እንዴት ነው? ለ) ሰውየው ሕይወቱን በሙሉ ባለማመን ቢኖር ይህ «ይቅር የማይባል ኃጢአት» ሊሆንበት የሚችለው እንዴት ይመስልሃል?

ኢየሱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ የሰጠው ትምህርት ማጠቃለያ። 

ጥያቄ፡- ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሰጠውን ያለፉት ሁለት ቀናት ትምህርት ከልስ። በዚያም ስለ መንፈስ ቅዱስ የተመለከትከውን ዐበይት እውነቶች በሙሉ ዘርዝር። 

ኢየሱስ የተመላለሰው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው። በምድራዊ አገልግሎቱ መጨረሻ አካባቢም ስለ መንፈስ ቅዱስ አስተምሯል። ከትምህርቶቹ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው። 

1. ኢየሱስ ይህችን ምድር ትቶ ከሄደ በኋላ አብና ወልድ መንፈስ ቅዱስን በልዩ መንገድ ለደቀ መዛሙርት እንደሚልኩ፡- መንፈስ ቅዱስ በመካከላቸው የሚሆን ብቻ ሳይሆን በውስጣቸውም እንደሚኖር ነበር። 

2. መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን በመተካት እንደ አጽናኝ፥ አማካሪ፥ ረዳትና ብቃት ሰጭ እንደሚሆን። አገልግሎቱ ሰዎች በራሱ ላይ ሳይሆን በኢየሱስ ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ እንደሚሆን፡- ኢየሱስን እንደሚያከብረው፥ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ የሰጠውን ቃል እንደሚናገር፥ እንዲሠራው የነገረውን ሥራ እንደሚሠራ ነበር። 

3. የማያምኑ ሰዎችን በተመለከተ መንፈስ ቅዱስ የሚሠራው ሥራ በኃጢአታቸው መውቀስና የእግዚአብሔር ፍርድ እንዳያገኛቸው ወደ ኢየሱስ መመለስ እንዳለባቸው ማሳሰብ ነው። 

4. አማኞችን በተመለከተ መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው አገልግሎት ለኢየሱስ ምስክር ይሆን ዘንድ በኃይል ማስታጠቅ ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ኢየሱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ያስተማራቸው ዋና ትምህርቶች የትምህርቶቻችንና የእምነቶቻችን ዋና አትኩሮት ያልሆኑት እንዴት ነው? ለ) እነዚህ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች በዚህ ዘመን ላለን ክርስቲያኖች አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: