የመንፈስ ቅዱስ ተምሳሌቶች

ጥያቄ፡- ሀ) ለሰዎች ባሕርያቸውን ለመግለጽ የምንሰጣቸውን ስሞች [[እንደ አንበሳ) ዘርዝር። ላ) እነዚህ ላሞች የትኛውን ባሕርይ ይገልጻሉ? 

አንዳንድ ነገሮችን ለመግላጽ ብዙ ጊዜ ምልክቶችን እንጠቀማለን። ለምሳሌ፡ አንድ ሰው ፍርሃት የማያውቅና ጠንካራ መሆኑን ለመግለጽ «አንበሳው» እንላዋለን። አንዳንድ ሰዎች እራሳቸውን «የቤተ ክርስቲያን አህዮች» ነን በማለት ሲናገሩ ሰምቼአለሁ፤ ይህን ሲሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መሆናቸውንና ሸክሟን እንደተሸከሙ መናገራቸው ነው። በተመሳሳይ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ለመግለጽ ምልክቶችን ይጠቀማል። ለምሳሌ፥ ኢየሱስ አንበሳና በግ ተብሎ ተጠርቷል (ራእይ 5፡5-6)። እግዚአብሔር ዓለት እንደሆነ ተጽፎአል (ዘፍ 49፡24)። እምባ መሆኑም ተገልጧል (2ኛ ሳሙ. 22፡2)። እያንዳንዱ ምልክት ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ የሚገልጣቸው ነገሮች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የመንፈስ ቅዱስን ባሕርይ ወይም ሥራ ለመግለጽ የተለያዩ ምልክቶችን ተጠቅሟል። 

ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት። ሉቃስ 24፡49፣ 3፡22፤ 2ኛ ቆሮ. 1፡22፤ የሐዋ. 2፡3፤ ሉቃስ 4፡18፤ ዮሐ 7፡38-39፤ 3፡8 ሀ) መንፈስ ቅዱስን ለመግለጽ የሚጠቅሙ ወይም ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ምልክቶች ወይም መግለጫዎች ጥቀስ። ላ) እያንዳንዱ ምልክት ምን ማለት ይመስልሃል? መንፈስ ቅዱስ በዚህ ምልክት የተገለጠው ለምን ይመስልሃል? 

1. መንፈስ ቅዱስ እንደ ልብስ (ሉቃስ 24፡48-49) 

ይህን ጥቅስ ለመረዳት ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርት የገባው ቃል ኪዳን ምን እንደሆነና ወንጌልን የመስበክ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት መጠበቅ ያላባቸው ምን እንደነበር ማረጋገጥ መቻል አለብን። ሉቃስ በዚህ ስፍራ በገለጠው ታሪክ በሐዋ. 1፡8 በተጻፈበት ሁኔታ ኢየሱስ የሚናገረው ስለ መንፈስ ቅዱስ እንደ ነበር ግልጽ ነው። ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ የሰጣቸው ተስፋም መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ እንደሚወርድ ነበር። መንፈሱም ልክ እንደ ልብስ ስመለኮታዊ ኃይሉ ስለሚሸፍናቸው ስለ ኢየሱስ በብቃት እንዲመሰክሩ ያስችላቸዋል። (ኢየሱስ! በአእምሮው ያለው ነገር ምናልባት ኤልያስ ለኤልሳዕ ያስተላለፈው መጐናጸፊያ ይሆናል)። ልብ በል ልብሱ ላደቀመዛሙርቱ ይሰጣቸዋል እንጂ እነርሱ በእራሳቸው አይለብሱትም ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ መንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር በነፃ የተሰጠ ስጦታ እንጂ ሠርተን ወይም ጸልየን የምናገኘው አይደለም። መንፈስ ቅዱስ እኛን የሚያለብስበት ተቀዳሚ ዓላማ ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ኃይል እንድንሸፈን ነው። ይህ ኃይል ይጠብቀናል (ልብስ ከብርድ እንደሚከላከለን ሁሉ) በተጨማሪ እግዚአብሔርን በመወከል እንድናገለግል ይረዳናል። እንደ አንዳንድ ምሁራን አመለካከት መንፈስ ቅዱስን መልበስ በእግዚአብሔር ቅድስና መሽፈን እንደሆነ (ኤፌ. 4፡24) ይህም የክርስቶስ መሆንን እንደሚያሳይ ይናገራሉ። 

2. መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ ነው (ሉቃስ 3፡22) 

ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በተጠመቀ ጊዜ ከሰማይ የወረደ ርግብ በኢየሱስ ላይ እንዳረፈ ተጽፋል። ይህ ርግብ መንፈስ ቅዱስ እንደ ሆነም ተነግሮናል። ሕዝቡ ሁሉ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና በእግዚአብሔር መንፈስ እንደተሞላ ያውቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በኢየሱስ ላይ ወረደ። ታልሙድ በመባል የሚታወቀው የአይሁድ ሥነ ጽሑፍ በዘፍ 1፡2 ላይ አሳብ ሲሰጥ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ ሆኖ በውኃ ላይ ሰፍፎ እንደነበር ይናገራል። ይህ ማለት ለአይሁድ ርግብ የመንፈስ ቅዱስ ምልክት መሆኑ የተላመደ ነበር ማለት ነው። 

የርግብ ምልክት ትርጉም ምንድን ነው? ይህ ምልክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አገልግሎት ላይ የዋለው ብዙ ጊዜ ስላይደላ ስለ ትርጉሙ እርግጠኞች መሆን አንችልም። ሆኖም ግን ስለዚህ ጉዳይ ሁለት ዋና አስተሳሰቦች አሉ። በመጀመሪያ በማቴ. 10፡16 ላይ እንደ ርግብ የዋሆች» እንድንሆን ተመክረናል። የዋህ የሚለው ቃል ንጹሕ መሆንና የተደባለቀ የውስጥ አሳብ ያለመኖርን ያሳያል። ስለዚህ ለአይሁድ ርግብ የየዋህነትና ንጹሕ የመሆን ምልክት ነበር። ርግብ የሰላም ፇልክትም ሆኖ አገልግሏል። የተባበሩት መንግሥታት ዓርማ የሆነው ለዚህ ነው። ርግብ የሚያመለክተው ይህን ከሆነ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ወደ ኢየሱስ ሲልከው ንጹሕና ሰላማዊ የሆነው መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ላይ የወረደው የእግዚአብሔር ልጅ መሢሑ ኢየሱስ ንጹሕና ሰላማዊ እንደሆነ ለሰዎች ለማሳየት ነበር። 

ሁለተኛ፡ ርግብ በብሉይ ኪዳን ጊዜ ድሆች ሰዎች ከሚሠውት መሥዋዕት እንዱ ነበር (ዘሌዋ 12፡8)። ኢየሱስ እንደ ተወለደ ወላጆቹ ሁለት ርግቦች መሥዋዕት አድርገው እንዳቀረቡ ታስታውሳላችሁ (ሉቃስ 2፡24)። ስለዚህ አንዳንድ ምሁራን ርግብ የሚያመለክተው ኢየሱስ ለዓለም መሥዋዕት የመሆኑን ጉዳይ ነው ብለው ያስባሉ። 

ርግብ የሚያመለክተው ኢየሱስን ለምድራዊ አገልግሎቱ ያዘጋጀው ዘንድ በእርሱ ላይ የወረደውን መንፈስ ንጽሕናና ቅድስና ሳይሆን አይቀርም። ንጹሕ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ቅድስናውን ወደ ኢየሱስ አስተላለፈ። ኢየሱስ ያለኃጢአት ስለነበር መንፈስ ቅዱስ «ቅዱስ» አላደረገውም። ይልቁኑ ርግብ የሚያመለክተው ኢየሱስ ንጹሕና ቅዱስ እንደሆነ በተለይ ደግሞ የእስራኤል መሢሕ ይሆን ዘንድ በእግዚአብሔር እንደተመረጠ ነው። ይህ ክስተት ኢየሱስ እግዚአብሔር የሰጠውን ሥራ ይፈጽም ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ይፋ አገልግሎቱን መጀመሩን ያሳየናል (ዮሐ 17፡14)። የርግብ ከሰማይ መውረድ መንፈስ ቅዱስ ከሰማይ የመጣ መሆኑን ያሳየናል። 

3. መንፈስ ቅዱስ እንደ ማኅተም፥ እንደ ቃል ኪዳን፥ ወይም እንደ መያዣ (2ኛ ቆሮ. 1፡22፤ 5፡5፤ ኤፌ. 1፡13-14)

በጥንት ጊዜያት አንድ ሰው እንደ ንብረት ሊገዛ የተወሰነ ገንዘብ ቀድሞ በመያዣነት ይከፍልና የቀረውን ደግሞ በተወሰኑ ጊዜያት እንደሚከፍል መስማማቱን በወረቀት ላይ ይፈርማል። ይህ ስምምነት የእርሱ እንደሆነና በስምምነቱ መሠረት እንደሚፈጽም በጣቱ ያለ የቤተሰቡ ዓርማ ያለበት ቀለበት አውጥቶ እንደ ማኅተም በመጠቀም በሰም ላይ ያደርጋል። (ለምሳሌ ሐጌ 2፡23) ማኅተሙ (ቃል ኪዳኑን)፥ ወደፊት ሙሉ ክፍያውን እንደሚፈጽም የተሰጠ ዋስትና ነው። 

መንፈስ ቅዱስ ከዚህ ማኅተም፥ ወይም መያዣ ጋር ይነፃፀራል። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ለእያንዳንዱ ክርስቲያን እንደ ሰጠ እና ይህ መንፈስ በእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብ እንደ ማኅተም እንደ ተመታ ወደፊት እንመለከታለን። ማኅተም ብዙ ነገሮችን ያሳያል። በመጀመሪያ፥ ባለቤትነትን ያሳያል። ስማችንን በመጽሐፉ ላይ ስንጽፍ መጽሐፉ የእኛ እንደሆነ ማረጋገጣችን እንደመሆኑ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ማኅተምም የእግዚአብሔር መሆናችንን ያሳያል። ሁለተኛ፥ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር በክርስቲያኖች ልብ የጀመረው ሥራ እንደሚፈጸም የሚያመላክት ተስፋ ነው። አንድ ቀን በእግዚአብሔር ለክርስቲያኖች የተሰጡ በረከቶች ሁሉ ሙሉ በሙሉ በሰማይ ይላሉ። 

4. እሳት (የሐዋ. 2፡3) 

የበዓለ ኀምሳ ቀን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ልዩ ቀን ነበር። ይህ ቀን ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበት ቀን ነበር። ያችን ቀንና የቤተ ክርስቲያንን ዘመን ከብሉይ ኪዳን ጊዜያት ለመለየት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱሳን እንደሚልክ ተስፋ ሰጥቶ ነበር (ኢዩ. 2፡28-32)። ይህንን በበዓለ ኅምሳ ቀን አደረገው። ሰተዘጋው ክፍል ውስጥ በነበሩ ደቀ መዛሙርት ላይ የወረደው መንፈስ ቅዱስ በሁለት ነገሮች ታጅቦ ነበር- ነፋስና እሳት (ወይም በርካታ የእሳት ነበልባሎች) እነዚህም የመምጣቱ ማረጋገጫዎች ነበሩ። 

በኢሳ. 4፡4 መንፈስ ቅዱስ «የሚያቃጥል መንፈስ» ተብሎ ተጠርቷል። ሰሉቃስ 3፡16 ደግሞ ኢየሱስ ሕዝቡን «በመንፈስ ቅዱስና በእሳት» እንደሚያጠምቅ ተነግሯል። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እሳት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ተቆራኝቶ ቀርቧል። እሳት ምንን ያመለክታል? በብሉይ ኪዳን ውስጥ ሁሉ እሳት እጅግ ጠቃሚ ተምሳሌት ሆኖ የቀረበ ሲሆን የሚክተሉትን መልእክቶች ያስተላልፋል፡ 

ሀ. እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ስለመሆኑ፡- ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር እራሱን ለሕዝቡ በቀጥታ ወይም በሚታይ ራእይ ሲገልጥ በእሳት ይከበብ ነበር። (ለምሳሌ ዘጸአ 3፡2፤ 13፡21፤ ሕዝ. 1፡4-5) 

ለ. እግዚአብሔር ሕዝቡ የሚያደርገውን ለማረጋገጥ ሲፈልግ (ዘሌዋ. 9፡24) 

ሐ. የእግዚአብሔር ጥበቃ (ዘጸአ 14፡19-25) 

መ. የእግዚአብሔር የፍርድ፥ የማንጻት እና የማጥራት ሥራ (ዘሌዋ. 10፡2፤ ኢሳ. 6፡9-8) 

በበዓለ ኀምሳ ቀን የወረደው መንፈስ ቅዱስን የሚያመላክተው እሳት ለደቀ መዛሙርት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ሳያመለክት አልቀረም። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በመካከላቸው መሆኑን ያሳያቸው ነበር። ደቀ መዛሙርት ከኃጢአታቸው ነጽተው ነበር። እግዚአብሔር የተቀደሱ ልጆቹ እንደሆኑ አረጋግጦላቸው ነበር። የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ሆነው ለመቆም ዝግጁ ነበሩ። 

5. ዘይት (ሉቃስ 4፡18፤ የሐዋ. 10፡38፡ 2ኛ ቆሮ. 1፡21-22፤ 1ኛ ዮሐ 2፡20) 

በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ሰውን ለአገልግሎት ሲለይ በዘይት ይቀቡ ነበር (ዘጸኢ 40፡9-16፤ 1ኛ ሳሙ. 10፡1፤ 16፡13)። ዳዊት በዘይት በተቀባ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ ወዲያውኑ ወረደ። መሪዎችን የመቀባት ተግባር በእስራኤል ሁሉ ውስጥ የታወቀ ከመሆኑ የተነሣ የእስራኤል የመጨረሻ ንጉሥ የሚሆነው መሢሑ ወይም ክርስቶስ የተቀባው» የሚል መጠሪያ ተሰጥቶት ነበር። በዕብራይስጥ መሢሕ በግሪክ ደግሞ ክርስቶስ የሚሉት ቃሎች ትርጉም «የተቀባ» ማለት ነው። ኢየሱስ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንደተቀባ ተናግሯል (ሉቃስ 4፡18)። እኛ ክርስቲያኖችም በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተናል (1ኛ ዮሐ 2፡20)። ኢየሱስ ወይም ክርስቲያኖች «የተቀቡ» መሆናቸውን ሲናገር ስለ ቁሳዊ ዘይት መናገሩ አይደለም። መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ ከመውረዱ በፊት ኢየሱስ በዘይት ስለመቀባቱ የተጻፈ ነገር የለም። ይልቁኑ ቃሉ የመጣው በብሉይ ኪዳን መሪዎች መመረጣቸውንና በእግዚአብሔር ኃይል ለኦገልግሎት መሞላታቸውን ለማመልከት ከሚደረገው ድርጊት ምሳሌ የመጣ ነው። 

አዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ መቀባታቸውን ያስተምረናል። ይህ ማለት አንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምንና መንፈስ ቅዱስን ሲቀበል በዓለም ከሚገኙ ሕዝቦች ሁሉ ላይ ለእግዚአብሔር እገልግሎት ይለያል። በሕይወቱ ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን ያገለግል ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይሞላል። 

6. ውኃ (ዮሐ 4፡14፤ 7፡38-39) 

ኢየሱስ በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ የሕይወት ውኃ ምንጭ ከውስጣቸው ይፈልቃል እንጂ አይጠሙም ብሎ ሁለት ጊዜ ተስፋ ሰጥቷል። ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? ይናገር የነበረው ስለምን ነበር? ዮሐንስ እንደሚነግረን ኢየሱስ የሚናገረው የሕይወት ውኃ ከሞት ከተነሣና ካረገ በኋላ ሊሰጥ ቃል ስለገባው መንፈስ ቅዱስ ነው። ይህ ሥዕላዊ መግለጫ የሚያንጸባርቀው እውነት መንፈስ ቅዱስ ወደ ክርስቲያን ሕይወት በሚመጣበት ጊዜ የማያፈራና ባዶ የነበረውን ሕይወት ልክ የዝናብ ውኃ መሬትን ፍሬያማ እንደሚያደርጋት ሁሉ ፍሬያማና ለምለም ይሆናል። መንፈስ ቅዱስ በሕይወቱ ያላ ሰው ሕይወቱ ተለውጦ የተትረፈረፈ ደስተኛ ሕይወትና ለሌሎች የሚሆን አገልግሎት እንደሚኖረው ኢየሱስ ተስፋ ሰጥቷል። 

7. ነፋስ (ዮሐ 3፡8፤ የሐዋ. 2፡1-2) 

ቀደም ብለን «መንፈስ» የሚለው ቃል የመጣው «ነፋስ» ከሚለው ቃል እንደሆነ ተመልክተናል። ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር በተነጋገረ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በሰው ሕይወት ውስጥ የሚሠራውን ሥራ ከነፋስ ጋር አወዳድሮታል። ይህን ሲል መንፈስ ቅዱስ በሥጋዊ ዓይን ሊታይ አይቻልም ማለት ነው። ባይታይም እንኳ ህልውናው በነገሮች ላይ ባለው ውጤት ይታያል። የድነት (ድነት (ደኅንነት)) አዲስ ልደት በሥጋዊ ዓይን የማይታይ ቢሆንም እንኳ ህልውናው በሰዎች ሕይወት ውስጥ በሚያመጣው ለውጥ ሁልጊዜ ይረጋገጣል። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ የማይታይ ቢሆንም እንኳ ህልውናውን በሕይወታችን ባገኘነው ለውጥና በመንፈሳዊ ስጦታዎች እንመሰክራለን። ኢየሱስ በተጨማሪ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በሰው ቁጥጥር ሥር እንዳልሆነ መስክሯል። እርሱ ሉዓላዊ ነው። ወደፈለገበት ይነፍሳል። የፈለገውንም ያደርጋል። መንፈስ ቅዱስ እንዴት እንደሚሠራ ለመቆጣጠር ወይም ለማመልከት ስንሞክር እንሳሳታለን። መንፈስ ቅዱስ እንደ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ብርቱ ነው። 

ኢየሱስ ወደ መንግሥተ ሰማያት ባረገ ጊዜ በደቀ መዛሙርት ላይ እፍ እንዳለባቸው ወይም እንደተነፈሰባቸው ተጽፎአል። (ኢየሱስ የራሱን ነፋስ ፈጠረ ልንል እንችላለን።) በዚህም በደቀ መዛሙርቱ ላይ ጊዜያዊ መንፈስ ቅዱስ እንዲኖር አደረገ (ዮሐ 20፡22)። በበዓለ ኀምሳ ቀን እንደ ታላቅ ነፋስ መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርት ላይ በወረደ ጊዜ ያ ጊዜያዊነቱ በቋሚነት ተለወጠ። 

ጥያቄ፡- ከመንፈስ ቅዱስ ስምና ስለ እርሱ በተሰጡ ምልክቶች የምንማራቸውን እውነቶች ዘርዝር።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading