የመንፈስ ቅዱስ ዋና ኃላፊነቶች ምንና ምን ናቸው?

ጥያቄ፡- ሀ) የመንፈስ ቅዱስ ዋና ኃላፊነቶች ምንና ምን ይመስሉሃል? ለ) የሚከተሉትን ጥቅሶች በማንበብ ከኃላፊነቶቹ ጥቂቶቹን /አንዳንዶቹን ጥቀስ። ዮሐ 15፡26፥ 16፡6-15፤ ሮሜ 8፡2፥ 4-6፥ 11፥ 14-16፣ 23፥26–27፤ 1ኛ ቆሮ. 9፡9-12፥23-25 

ከዚህ ቀደም እንደጠቀስነው ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ጉዳይ ላይ በከፍተኛ ደረጃ የማይስማሙባቸው ነጥቦች አሏቸው። አንዳንዶች የሚያስተምሩት መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ሕይወት ወይም በቤተ ክርስቲያን ታምራትን ለማድረግ እንደተሰጠ ነው። የመንፈስ ቅዱስ ተቀዳሚ ተግባር በልሳን ማናገር ወይም ታምራትን ማድረግ ይመስላቸዋል። ሌሎች ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ተቀዳሚ ተግባር እኛን መቀደስ እንደሆነ ያምናሉ። ሌሎች መንፈስ ቅዱስ እኛን የእግዚአብሔር ልጆች በማድረጉ ሥራ ላይ ያተኩራሉ። ትክክለኛው የትኛው ነው? ሚዛናዊ የሆነ መልስ መፈለግ አለብን። መንፈስ ቅዱስ በሁሉም የሕይወታችን ገጽታ ውስጥ ይገባል። እነዚህን እገልግሎቶቹን በቅደም ተከተል የማስቀመጫ መንገድ አለን? የዚህ ጥናት መጽሐፍ ጸሐፊ የመንፈስ ቅዱስ ገጸ-ብዙ አገልግሎቶች በሁለት ዋና ሥራዎቹ ተጠቃልላው መቅረብ ይችላሉ ብሎ ያምናል። 

1. መንፈስ ቅዱስ የተሰጠን እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ መኖር ይችል ዘንድ ነው። 

ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ። ዘጸአ 25፡8፥ 22፥ 29፡42 46፥ 33፡7፤ 1ኛ ቆሮ. 3፡16፥ 6፡19። ሀ) ስለ መገናኛው ድንኳን ዓላማ ምን ያስተምሩናል? ለ) አማኞችና ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ማደሪያ ስፍራ ስለ መሆናቸው ምን ያስተምሩናል? 

የብሉይ ኪዳን ታሪክ ተቀዳሚ ዓላማ እግዚአብሔር እስራኤላውያን ከሚባሉ ልዩ ሕዝቦች ጋር ስላለው ግንኙነት ማውሳት ነው። እግዚአብሔር በምድር ላይ ካሉ ሕዝቦች በሙሉ ለይቶ በመምረጥ ልዩ ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር ገባ። እግዚአብሔር ይህን ካደረገባቸው ዓላማዎች አንዱ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እጅግ ቅርብ በሆነ መልኩ ግንኙነት እንዲኖረው ላማድረግ ነበር። እግዚአብሔር እንደ አብርሃምና ዳዊት ያሉ ሰዎችን የመረጠ ቢሆንም እንኳ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለመጠበቅ የሚያመልኩበት አንድ የሚታይ ስፍራ ከሌላቸው በስተቀር አስቸጋሪ ሆኖ አግኝተውታል። ሰዎች ዛፎችን፥ ፀሐይንና ጨረቃን ወዘተ የመሳሰሉ የሚታዩ ነገሮችን የማምላክ ፈተና ሁልጊዜ ነበረባቸው። ስለዚህ እግዚአብሔር የእርሱን ህልውና ሕዝቡ ዘወትር የሚያስብበትን አንድ የሚታይ ነገር ላመሥራት ወሰነ። ከእስራኤላውያን ዘንድ የሚያደርገውን ልዩ መገኘት የሚያመላክት እንድ ሕንፃ እንዲሠሩ አዘዘ። እግዚአብሔር የእርሱን ልዩ መገኘት ማለትም የክብሩ ደመና የሚያርፍበትን፥ በመጀመሪያ የመገናኛ ድንኳን በኋላ ደግሞ ቤተ መቅደሱ እንዲሠራ አደረገ። . እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ለማደር ፈለገ (ዘፀኦ 25፡8)። ሕዝቡ እንዲያመልኩት እርሱም ቅርብ እንዲሆናቸው ፈለገ። የሚያሳዝነው እውነታ ግን የመገናኛው ድንኳንና የክብሩ ደመና በመካከላቸው እያለ እንኳ እስራኤላውያን ወደ ጣዖት አምልኮ አዘነበሉ። 

በመጀመሪያ እግዚአብሔር ያለምንም ሕንፃ እራሱን ከግለሰቦች ጋር አዛመደ። ቀጥሎም ለእርሱ ልዩ መገኘት ሕንጻ እንዲሠራ አደረገ። በአዲስ ኪዳን ግን እግዚአብሔር እራሱን ከሕዝቡ ጋር የሚያዛምድበትን መንገድ እንደለወጠ እናያለን። እግዚአብሔር በሕዝቡ ውስጥ ለመኖር ወሰነ። ይህን ያደረገው እንዴት ነበር? እግዚአብሔር አብ በልጆቹ ሁሉ ውስጥ ይኖራልን? ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በልባቸው ይኖራልን? በአንዳንድ መንገድ እግዚአብሔር እብና ኢየሱስ ክርስቶስ በልባችን የሚኖሩ ቢሆኑም እንኳ በሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች ልብ ውስጥ የሚኖረው የሥላሴ አካል እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው። በተቀዳሚ እርሱ በሕይወታችን በመኖሩ እግዚአብሔር እብና እግዚአብሔር ወልድ በልባችን ይኖራሉ (ዮሐ 4፡23)። አስደናቂው እውነት አሁን የእግዚአብሔር ልጅ በሆነ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በሕይወቱ በቋሚነት መኖሩ ነው። መንፈስ ቅዱስ አንድ ጊዜ ወደ ሕይወታችን የሚመጣ በሌላ ጊዜ ደግሞ የሚሄድ አይደለም። እርሱ ሁል ጊዜ በዚያ ይገኛል። ወዳጃችን ነው። መንፈስ ቅዱስ አጽናኛችንና ጠበቃችን ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት እውነተኛ ለማድረግ በዚያ አለ። 

ዘላለማዊና ኃያሉ አምላክ በልብህ ውስጥ ይኖራል! ምን ዓይነት አስደናቂ እውነት ነው! 

ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር በልብህ ውስጥ የመኖሩ እውነታ የሚያበረታታህ እንዴት ነው? ለ) ማስጠንቀቂያ የሚሆንህስ እንዴት ነው? 

ዓለምን የፈጠረው በአንተ ውስጥ ይኖራል! ይሁንና፥ ይህ በአንተ ውስጥ የሚኖረው እስራኤላውያንን ባለመታዘዛቸው በከባድ ሁኔታ የቀጣቸው እግዚአብሔር ነው። ምን ዓይነት አበረታችና አስፈሪ እውነት ነው። በምንዋሽበት ጊዜ በውስጣችን ያለው መንፈስ ቅዱስ ይሰማና ያዝናል። የፍትወተ ሥጋ ኃጢአት ስንፈጽም በውስጣችን ያለው መንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜም ይመለክተናል። መልካም ሆነ ክፉ ስሆንንበት ጊዜ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ነው። 

2. የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በተቀዳሚ ኢየሱስ ክርስቶስን ማሳየት ነው። 

ጥያቄ፡- ዮሐ 16፡5-15 አንብብ። እነዚህን ጥቅሶች ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥራ ምን ያስተምሩናል? 

መንፈስ ቅዱስ አምላክ ቢሆንም እንኳ እርሱ ትሑት ስለሆነ ለራሱ አትኩሮትን ወይም ከብርን ለማግኘት አይፈልግም። ግቡ ሰዎች ወደ እርሱ እንዲመለከቱ ወይም እርሱን እንዲያመልኩት አይደለም። የብርሃን ጨረር የሰዎችን አትኩሮት ወደ ሌላ ነገር እንደሚያመላክት የመንፈስ ቅዱስ ተቀዳሚ ተግባር ትኩረቶቻችንን በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንድናደርግ ነው። ይህንንም በአራት ዋና ዋና መንገዶች ይፈጽማል። 

1. መንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊ ዓይኖቻችን በመክፈት ለደኅንነታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንመለከት ያደርጋል። 

2. ኢየሱስ ክርስቶስን እንድናመልክ የሚረጃን መንፈስ ቅዱስ ነው። 

3. የመንፈስ ፍሬን በማፍራት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንመሰል በሕይወታችን የሚሠራው መንፈስ ቅዱስ ነው። 

4. መንፈሳዊ ስጦታዎችን በመስጠት ኢየሱስ ክርስቶስን ወክለን የክርስቶስ አካል የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንና ዓለምን እንድናገለግል የሚያደርግ መንፈስ ቅዱስ ነው። 

ጥያቄ፡- መንፈስ ቅዱስ በሕይወትህ እነዚህን እራት ነገሮች እንዴት እንዳደረገ ምሳሌዎችን ዘርዝር። 

ጥያቄ፡- ሀ) በዚህ ዘመን ያሉ ሰዎች አትኩሮታቸውን ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚያደርጉት ወይም ጨርሶ እንደሌለ አድርገው የሚቆጥሩት ለምን ይመስልሃል? ለ) ከዚህ ትምህርት ስለ መንፈስ ቅዱስ በጥንቃቄ የማጥናትን አስፈላጊነት በተመለከተ ምን ልትማር ትችላለህ?

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: