የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና የመንፈስ ቅዱስ ሙላት (ክፍል ሁለት)

2. የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት 

መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዱን ክርስቲያን ማደሪያ ስለማድረጉ ጉዳይ አናሳ ልዩነቶች ያሉ ቢሆንም ልዩነቱ እየሰፋና እያደገ የሚመጣው ወደ መንፈስ ቅዱስ የማጥመቅ አገልግሎት ስንገባ ነው። በሥነ መለኮት ትምህርታቸው ካሪዝማቲክ ያልሆኑት፥ የመንፈስ ቅዱስ የማጥመቅ አገልግሎት እያንዳንዱ ሰው ወደ ክርስቶስ መጥቶ በሚድንበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በልቡ ከሚፈጽማቸው ሥራዎች አንዱ ነው ብለው ያስተምራሉ። ይህ አገልግሎት መንፈስ ቅዱስ ወደ እያንዳንዱ አዲስ ክርስቲያን ልብ ውስጥ መጥቶ ማደሩን ከዚያም እያንዳንዱን ክርስቲያን የክርስቶስ አካል በሆነችው ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጨመሩን ያካትታል። ለካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች ግን ይህ መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የሚሠራው የተለየ ሥራ ሲሆን ብዙ ጊዜ የሚፈጸመው ከዳኑ በኋላ ነው። ይህ ልዩና አንድ ጊዜ የሚፈጸም ሁለተኛው በረከት ሲሆን መንፈስ ቅዱስ ልዩ በሆነ ኃይል ወደ ክርስቲያኑ ሕይወት ይመጣና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር እንዲችል ያደርገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ከእነዚህ ሁለት አመለካከቶች የትኛውን ይደግፋል? 

አዲስ ኪዳንን በምንመለከትበት ጊዜ ስለ መንፈስ ቅዱስ (ጥምቀት) በቀጥታ የጠቀሰባቸው ቦታዎች በጣም ጥቂት ሆነው እናገኛቸዋለን። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት መጥምቁ ዮሐንስ ለሕዝቡ ኢየሱስ በመንፈስና በእሳት እንደሚያጠምቅ ተናገረ (ማቴ. 3፡11)። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርት አንድ ቀን መንፈስ ቅዱስ በሕይወታቸው ለመኖር እንደሚመጣ ቢነግራቸውም ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ከተናገረው በቀር ሌላ በየትም ስፍራ ይህን አገልግሎት ጥምቀት ብሎ አልጠራውም። በሐዋ. 1፡5 ላይ ብቻ በመንፈስ ቅዱስ እስኪጠመቁ ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ አሳስቦአቸዋል። ወመንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ በወረደ ጊዜ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ እንጂ ተጠመቁ አልተባለም (የሐዋ. 2፡4)። በሐዋርያት ሥራ 2 ላይ የመንፈስ ቅዱስ በሰው ልብ ውስጥ ማደር የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና ሙላት በአንድ ጊዜ ስለ ተፈጸመ የማንኛውም ክርስቲያን ልምምድ ስእነዚህ ምዕራፎች የተገለጸውን ስለመከተሉ እነዚህን ጥቅሶች በማስረጃነት እንዳናቀርብ መጠንቀቅ አለብን። በቀረው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጥምቀት የሚለው ቃል ለውኃ ጥምቀት እንጂ ለመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አገልግሎት አልዋለም። ሆኖም ግን በአዲስ ኪዳን ውስጥ በድነት (ደኅንነት)፥ በውኃ በመጠመቅና መንፈስ ቅዱስን በመቀበል መካከል እጅግ የቀረበ ዝምድና አለ። (ቲቶ 3፡5 ተመልከት።) ውጫዊ ሥርዓት የሆነው የውኃ ጥምቀት የኃጢአት መታጠብን ብቻ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ መቀበልንም ያሳያል። 

ታዲያ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የሚያመላክተው ምንድን ነው? ስለ መንፈስ ቅዱስ የማጥመቅ ሥራ የተጠቀሰው ጥቂት በመሆኑ ይህን የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ለመረዳት ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚያወሳውን ሰፊ የአዲስ ኪዳንን ትምህርት መረዳት አለብን። «የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት» አንድ ሰው በሚድንበት ጊዜ ስለሚፈጸሙ ሁለት የተያያዙ የመንፈስ ቅዱስን አገልግሎቶች ለማመልከት የተጠቀሰ ነው። 

1. የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ክርስቲያን በልቡ እንዲኖር የሚሰጠውን የመንፈስ ቅዱስ ህልውና የሚያመለክት ነው። 

የአዲስ ኪዳን ትምህርት ይህ መሆኑን የምናምንባቸው ምክንያቶች ቀጥለው ተዘርዝረዋል። 

ሀ. የብሉይ ኪዳን ተስፋ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ለእግዚአብሔር ሰዎች በሙሉ እንደሚሰጥ ነው። ኢሳ. 32፡15፤ 44፡3፤ ሕዝ 36፡25፥ 27፤ 39፡28-29ና ኢዩ 2፡28። እነዚህ ጥቅሶች ሁሉም መንፈስ ቅዱስ በእግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ ላይ እንደሚፈስስ ይናገራሉ። 

ለ. መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ትንቢት ሰዎችን ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ እንደሚያጠምቅ ነበር (ማር. 1፡8)። ይህ የኢየሱስ አገልግሎት ሰዎችን ከኃጢአታቸው ከሚያጥብበት? አገልግሎቱ ጋር የተቆራኘ ነው። ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ ‹የእግዚአብሔር በግ› መሆኑን እና በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ መሆኑን ገለጸ (ዮሐ 1፡29፥ 33)። ስለዚህ ኢየሱስ ለሚያምኑት ሁሉ የሚሰጠው ሁለት ዋና አገልግሎቶች ሰዎችን ከኃጢአታቸው ማንጻትና በመንፈስ ቅዱስ ማጥመቅ ናቸው። 

ሐ. ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጥ ተስፋ የሰጠው አንዱን ከሌላው ሳይለይ ለደቀ መዛሙርት በሙሉ ነው (ዮሐ 14፡16-18፤ የሐዋ. 1፡5፡8)። ኢየሱስ ሲናገር መንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንጂ በጥረታቸው የሚያገኙት ነገር እንዳይደለ ገልጿል። የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ኢየሱስ በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስን ሲሰጥ ደቀ መዛሙርትን በመንፈስ ቅዱስ ከማጥመቅ ጋር አንድ ዓይነት ነገር ነበር ያደረገው ብለው ያስባሉ። እነዚህ ጸሐፊዎች ለክርስቲያኖች ይሰጣል ብለው ያሰቡት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ እንደሚያጠምቃቸው ቃል ከገባው የተለየ እንደነበር የሚያመለክት ነገር ፈጽሞ የለም። 

መ. ሐዋርያት ኢየሱስ የጀመረው አዲስ ኪዳን እነዚህ ሁለት ዋና ስጦታዎች ማለትም ድነት (ደኅንነት)ና መንፈስ ቅዱስን እንደሚያጠቃልል ተረድተው ነበር። ጳጥሮስ በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ከወረደባቸው በኋላ በሰበከው ስብከት ሰዎችን እንዲያምኑ ሲያነሣሣቸው እናያለን። በእምነታቸውም ሁለት ዋና ዋና ስጦታዎች እንደሚቀበሉ ተናገረ። የመጀመሪያው የኃጢአት ይቅርታ ሲሆን፥ ሁለተኛው በእምነታቸው ምክንያት መንፈስ ቅዱስን እንደሚቀበሉ ነው (የሐዋ. 2፡38)። የመጀመሪያዎቹን የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ሁለት ምዕራፍች በጥንቃቄ ብናጠና «የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ተስፋ» (የሐዋ. 1፡4፤ 2፡33፥ 39)፥ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት (የሐዋ. 1፡5) እና «የመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ» (የሐዋ 2፡17፥ 33) የሚያመለክቱት ክርስቲያኖች ስለሚቀበሉት መንፈስ ቅዱስ ነው። ለዚህ ነው ቆርኔሌዎስ መንፈስ ቅዱስን እንዴት እንደተቀበለ ሲናገር ጴጥሮስ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ መቀበልና በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ብሎ የተናገረው (የሐዋ. 11፡16-17)። 

ሠ. ሐዋርያትም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ለተወሰኑ ሰዎች ሳይሆን ለክርስቲያኖች ሁሉ መሆኑን ተረድተው ነበር። በብሉይ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ የሚወርደው በተወሰኑ ሰዎች ላይ እንደ ነበር ተመልክተናል። በአንዳንድ መሪዎች ላይ ሲወርድ በሌሎች ላይ አይወርድም ነበር። የሚመጣው ለተወሰነ ጊዜ ስለነበር የእግዚአብሔር ዓላማ ሊጠናቀቅ ወይም ሰውዬው ከፍተኛ ኃጢአት ሲያደርግ ትቶት ይሄድ ነበር። በኢዩኤል 2፡28 ላይ ግን እግዚአብሔር መንፈሱ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ እንደሚሆን አንድ ተስፋን ሰጠ። ሁሉ የሚለው ቃል በምድር የሚኖሩቱን ሁሉ የማያምኑ ሰዎችንም ጭምር የሚያጠቃልል ሳይሆን የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል የሆኑትን ሰዎች በሙሉ ለማለት ነው። መንፈስ ቅዱስ ዕድሜ፥ ፆታ፥ ሥራ፥ ዘር ሳይለይ በሰዎች ሁሉ ላይ ስለመውረዱ የሚናገር ነው። ስጳንጤቆስጤ ዕለት ጰጥሮስ ሲሰብክ ይህ የተስፋ ቃል መፈጸሙን በመግለጽ፥ አሁን የሚያምን ሁሉ እግዚአብሔር በኢዮኤል በኩል የሰጠውን የተስፋ ቃል ሊቀበል ይችላል አለ። ኢየሱስን በሚያድን እምነት የሚቀበሉ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ቃል ይቀበላሉ (የሐዋ. 2፡38-39)። 

ረ. በጰንጠቆስጤ ዕለት ሦስት ሺህ ሰዎች ሊያምኑና ሲጠመቁ በመንፈስ ቅዱስ ላለ መጠመቃቸው የተነገረ ቃል የላም። ሆኖም [ጴጥሮስ በስብከቱ መንፈስ ቅዱስ በሁላቸውም ላይ እንደሚወርድ ተናግሮ ስለነበር] መንፈስ ቅዱስን እንደተቀበሉ እናምናለን። አንዳንዶች ተቀበሉ ሌሎች ደግሞ እልተቀበሉም ተብሎ የተነገረ ቃል የለም። ወይም ደግሞ በሌሎች ደቀ መዛሙርት እንደሆነ ሦስቱ ሺህ ሰዎችም የእሳቱ ነበልባል በላያቸው ላይ እንደነበረና በልሳን እንደተናገሩ አልተጠቀሰም። ይልቁኑ . ያመኑትና የተጠመቁት ሁሉ ሳመኑበት ቅጽበት መንፈስ ቅዱስን እንደተቀበሉ እንድናምን እንገደዳለን። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መንፈስ ቅዱስን ተጠባብቀው እንዳገኙ የሚናገር ቃል የለም። በእርግጥ 120 ዎቹ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት በመጀመሪያ ካመኑ በኋላ ነበር። (ይህ የሆነበት ምክንያት እነርሱ ቀደም ብለው አምነው ስለነበርና መንፈስ ቅዱስ ደግሞ እስከ ጰንጠቆስጤ ቀን ድረስ ገና ስላልተሰጠ ነበር።) ሦስቱ ሺህ ሰዎች ግን መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት እንዳመኑ ነበር። ለ120 ዎቹ ሰዎች መጀመሪያ አምነው ከዳኑ በኋላ ቆይተው መንፈስ ቅዱስን መቀበላቸው ልዩ ሁኔታ ነበር። ሦስቱ ሺህ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉበት መንገድ እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ ለሰው ልጅ የሚጠቀምበት መንገድ ነው። ይኸውም መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት ባመኑበት ቅጽበት መሆኑ ነው። 

2. የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አሱን ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ወደሆነችው ወደ ክርስቶስ አካል ይጨምራል። በአብዛኛው ጊዜ ‹ጥምቀት› የሚለው ቃል በአዲስ ኪዳን ክፍሎች የተጠቀሰው የውኃ ጥምቀትን ለማመልከት ቢሆንም ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በግልጽ የተጠቀሰበት ሌላ ስፍራ እለ። በ1ኛ ቆሮ. 12፡3 «አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናል» የሚል ቃል እናገኛለን። ከዚህ ጥቅስ የሚከተሉትን እውነቶች መመልከት እንችላለን። 

1. ጳውሎስ የሚናገረው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ እንደተጠመቁ ነው። እንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንዳልተጠመቁ የሚያመለክት ነገር የለም። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በክርስቲያን መንፈሳዊነት ላይ የሚመሠረት ስለመሆኑም የተነገረ ነገር የላም። የቆሮንቶስን አማኞች ሁኔታ ብናጠና ቤተ ክርስቲያኒቱ ንጹሕና ቅዱስ አልነበረችም። በክርስቲያኖች መካከል ክፍፍሎች ነበሩ። አንዳንዶቹ አባላት ግልጽ የሆነ የፍትወተ ሥጋ ኃጢአት ይፈጽሙ ነበር። 

2 የጥምቀቱ ልምምድ በአሁኑ ወይም በወደፊት ጊዜ ሳይሆን በኃላፊ ጊዜ የተጠቀሰ ነበር። በጳውሎስ እመለካከት ክርስቲያኖች በሙሉ ቀደም ብለው ተጠምቀው ነበር። በመጠመቅ ሂደት ላይ እልነበሩም ወይም ወደፊት የመጠመቅም ፍላጎት አልነበራቸውም። የተሟላ ሆኖ ሳይደገም እንድ ጊዜ ብቻ የተፈጸመ ነበር። 

3 እንጠመቅ ዘንድ የተሰጠ ትእዛዝ የሌለ ሲሆን (በዚህም ሆነ በሌላ በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል) ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ ለመጠመቅ ጥረት ማድረግ እንደነበረባቸው የሚጠቁም ነገር አልተጻፈም። ጳውሎስ ክርስቲያኖች እንዲጠመቁ አልወተወታቸውም። ወይም መሪዎች ለመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በሰዎች ላይ እጅ ይጭኑ ዘንድ አልጠየቀም። 

4. የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ዘንድ በልሳናት መናገርን ይጨምር እንደነበር የተጠቀሰ አንድም ነገር የለም። አዎን እንዳንድ ክርስቲያኖች በልሳናት ይናገሩ ነበር። ነገር ግን ይህ ከመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ጋር ስለመያያዙ አንዳችም አመልካች ነገር የለም። 

5. የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ውጤት ወደ አንድ አካል መጨመር ነው። ይህም ስያታ በማኅበራዊ አቋም ወይም በዘር ላይ የተመሠረተ አይደለም። ይህ አካል የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ናት። በመንፈስ ቅዱስ ያልተጠመቁ ክርስቲያኖች በክርስቶስ አካል ውስጥ አይደሉም። ጳውሎስ በመቀጠል የሚገልጸው በክርስቶስ አካል ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ሰው ለመላው አካል ጤናማ አሠራር አስፈላጊ ነው። የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት በዚህ መንገድ መረዳት በብሉይ ኪዳን ዘመንና ኢየሱስ ሰሕይወት በነበረበት ዘመን ይህ አገልግሎት ካለመኖሩ፥ ጋር በሚጣጣም መልኩ ይያያዛል። በዚያን ጊዜ የክርስቶስ አካል አልነበረም ወይም ሰዎች የሚካተቱባት ቤተ ክርስቲያን አልነበረችም። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ ወደ መንግሥተ ሰማያት እስኪሄድና ቤተ ክርስቲያን እስክትመሠረት ሊያጠምቅ አይችልም ነበር። 

የጰንጠቆስጤ ሥነ መለኮት ትምህርትን የሚከተሉ ብዙ ሰዎች በ1ኛ ቆሮ. 12፡13 የተነገረው የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ሉቃለ፥ በሐዋ. 1፡3-5 ክተናገረው የተለየ ነው ይላሉ። በ1ኛ ቆሮንቶስ ያላው ጥምቀት በመንፈስ ቅዱስ ወደ ክርስቶስ አካል ውስጥ ለመግባት መጠመቅ ነው ይላሉ። ይህ የሚፈጸመው በመጀመሪያ ጌታን አምነን ስንድን ነው። ነገር ግን ሉቃስ የተናገረው የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በኢየሱስ አማካኝነት (ሉቃስ 3፡16፤ የሐዋ. 15) ወደ መንፈስ ቅዱስ ውስጥ ለመጠቅለል የሚደረግ ጥምቀት ሲሆን ይህ እምነን ከዳንን በኋላ የሚፈጸም ነው። ይሁንና የግሪኩን ትርጉም ብንመለከት እንደዚህ ዓይነት ልዩነት አያሳይም። በሁለቱም አገልግሎት ላይ የዋለው አንድ ዓይነት «ኤንኑማቲ» የሚል ሐረግ ነው። ‹ኤን) የሚለው ቃል ከ፥ ጋር ወይም በኀአማካኝነት የሚል ቢሆንም እንኳ፥ በጀመረው የመረጠውን ቃል ሳያወላውል ቢጠቀም ችግር አይፈጥርም። ጳውሎስ ሐረጉን የተጠቀመበት ስለ አንድ ዓይነት ጥምቀት ሲሆን ሉቃስ ደግሞ ስለሌላ ዓይነት ጥምቀት ለመናገር ነው የምንልበት አንዳችም የሰዋሰው ልዩነት አይኖርም። ሉቃስና ጳውሎስ በአንድነት እየተጓዙ ያገለግሉ የነበሩ ናቸው። ስለዚህ ሐረግ ያላቸው መረዳት አንድ ዓይነት ነው ብለን እናምናለን። የእግዚአብሔር ቃል በሚጻፍበት ወቅት ሰዎችን ይመራ የነበረው መንፈስ ቅዱስ በዚህ ዓይነት ውዥንብር ይተወናልን? የሚሆን አይመስልም። 

ማጠቃለያ፡- የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትን በተመለከተ እንደ አዲስ ኪዳን አጠቃቀም ከሆነ መንፈስ ቅዱስ በአማኙ ሕይወት ውስጥ የሚሠራውን ሁለተኛ ሥራ የሚያመለክት ነው ለማለት ምንም ማረጋገጫ የለንም። ማስረጃ ዎቹ በሙሉ የሚያመላክቱት፥ ክርስቲያን ያልሆነ፥ የእግዚአብሔር ጠላት የነበረ ሰውን በክርስቶስ አካል ውስጥ በመጨመር የእግዚአብሔር ልጅ ለላሚያደርገው፥ ለአንዴና ለመጨረሻ ስለተጠናቀቀው የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ነው። ይህ አንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመነ ወዲያውኑ የሚሆን ነው። ከመንፈስ ቅዱስ በሰዎች ልብ የማደር (ስጦታ) ጋር በቅርብ የተቆራኘ ወይም አንድ ዓይነት ነገር ነው። አዲስ ኪዳንን ስናጠና መንፈስ ቅዱስ በአዲስ መንገድ መምጣቱን ወይም አዲስ ልምምድን ወይም አዲስ በረከትን እንድንሻ እግዚአብሔር እያነሣሣንም። ይልቁኑ፥ በሕይወታችን የተደረገውን በማስታወስ በዚያ መሠረት እንድንኖር ይጠይቀናል። ሐዋርያት ከኃጢአት ጋር የሚፍገመገሙትንና ኃጢአት የሚያደርጉትን ክርስቲያኖች ሁለተኛ በረከት እንዲፈልጉ አልገፋፉአቸውም። መንፈስ ቅዱስ አዲስ ፍጥረት እንዳደረጋቸው እንዲያስታውሱ እና በዚሁ ደረጃ እንዲኖሩ (2ኛ ቆሮ. 5፡14) ሕይወታቸው እንዲለወጥ፥ ሰብለለት እንዲያድጉና ቅዱስ እንዲሆኑ ነው የጠየቁአቸው። ስለሆነም አዲስ የሆነ ወይም የበለጠ የመንፈስ ቅዱስ ነገርን አንጠብቅም። በክርስቶስ ኢየሱስ በእርሱም ላይ ባለን እምነት በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ ተባርከናል። የእግዚአብሔር ልጆች ነን የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ነን (ኤፌ. 1፡3፤ ዮሐ 1፡12፤ 1ኛ ቆሮ. 6፡19)። ይልቁኑ እግዚአብሔር እንደሚፈልግብን መሆን የሚያስችለን፥ ለሁላችንም የሆነ የኢየሱስ ስጦታ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን መኖሩን በመገንዘብ፥ ለማደና በመንፈስ ለመመላለስ መጣር ይኖርብናል። 

ጥያቄ. ሀ) ለሁለተኛ ጥያቄ የሰጠኽውን መልስ ክላይ ከተመለከተው መልስ ጋር አወዳድር። ተመሳሳይነቱ እንዴት ነው? ልዩነቱስ? ለ) መልሶችህን እሁን የምትከልሰው እንዴት ነው? ሐ) ሁላችንን እየተቋቋመን ያለው ልዩ ጉዛይ መንፈስ ቅዱስን በስፋት እለማስተናገድ ሳይሆን፥ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የቅርብ ኅብረት ለማድረግ እርሱን ለመታዘዝ አለመቻላችን መሆኑ ሰምን በምን እቅጣጫዎች ይታያል? 

3. የመንፈስ ቅዱስ ሙላት 

አዲስ ኪዳን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የማይደገም በደኅንነታችን ጊዜ ብቻ የሚፈጸም ድርጊት ነው ካለ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሙላት ምን ያስተምረናል? ስለ መንፈስ ቅዱስ ሙላት በጥልቀት ስንመረምር የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ከመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የተላየ መሆኑፃ እንመለከታለን። 

1. የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ለአንዴና ለሁልጊዜ የሚሆን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ሊሆን፥ በክርስቲያን ልብ ውስጥ የሚኖርና ትቶም የማይሄድ ነው። የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ግን ከእግዚአብሔር ፍላጎት አኳያ ማቋረጥ የማይገባው ልምምድ ቢሆንም እንኳ፥ ካልጠበቅነው በስተቀር ሊጠፋ የሚችልም ነው። በእርግጥ ከጠፋም በኋላ እንደገና ሊገኝ ይችላል። የመንፈስ ቅዱስ ሙላት በክርስቲያን ሕይወት የሚታጣበት ተቀዳሚ ምክንያት ኃጢአት ነው (ኤፌ. 4፡30)። የመንፈስ ቅዱስ ሙላት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በእማኝ ሕይወት አገልግሎት ውስጥ ለብዙ ጊዜ የሚደጋገም ተግባር ነው። ለምሳሌ፡ ጴጥሮስና ደቀ መዛሙርት በሙሉ በጰንጠቆስጤ ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ (የሐዋ. 2፡4)። ጴጥሮስ እንደገና ለአይሁድ መሪዎች ንግግር በሚያደርግበት ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶአል (የሐዋ. 4፡8)። እርሱና ሌሎች ደቀ መዛሙርት ከጸለዩ በኋላ እንደገና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ (የሐዋ. 4፡31)። ጳውሎስ ከሐናንያ ሲገናኝ ለመጀመሪያ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ተሞላ (የሐዋ. 9፡17)። ኋላ ደግሞ ሐሰተኛ አስተማሪ የነበረውን ኤልማለን በሚቋቋምበት ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ነበር (የሐዋ. 13፡9)። ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ታሪክ የምንረዳው፥ የመንፈስ ቅዱስ ውላት በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ በተደጋጋሚ በየዘመኑ ሁሉ የሚሆን ነገር መሆኑን ነው። 

በአዲስ ኪዳን ሦስት ዓይነት የሙላት ዓይነቶች ያሉ ይመስላል። 

ሀ. በመንፈስ ቅዱስ ሙሉ መሆን የክርስቲያን ሕይወት ታዋቂ ልምምድ ነው። እግዚአብሔርን በመፍራት በሕይወታቸው የሚመላለሱ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ እንደሆኑ ተነግሮአቸዋል (የሐዋ. 6፡3፣ 5፤ 11፡5)። ምንም እንኳ ክርስቲያኖች ሁሉ በዚህ መንገድ ባይኖሩ፡ እግዚአብሔር ቀን ክሁላችን ይህንን ይፈልጋል። 

ለ. በመንፈስ ቅዱስ «መሞላት ልክ በብሉይ ኪዳን ጊዜ እንደነበረው እግዚአብሔር ለአንድ ሰው የሚሰጠውን፥ እስክ ሕይወት ዘመኑ በሙሉ የሚዘልቅ ልዩ አገልግሎት ለማመልከትም ያገለግላል። መጥምቁ ዮሐንስ ለነቢይነት አገልግሎቱ ከውልደቱ ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ነበር (ሉቃለ 1፡15-17)። ጳውሎስ ለእሕዛብ ሐዋርያ ይሆን ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ እንደነበርም ተጽል (የሐዋ. 9፡17፤ 22፡12-15)። 

ሐ. በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ማለት ለአንድ ድንገተኛ እና አጣዳፊ ሁኔታ አንድን ሰው በአስፈላጊው ክህሎት የማስታጠቅ ተግባር ማለት ሊሆን ይችላል። «በመንፈስ ቅዱስ መሞላት። የሚለው ቃል በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ በአብዛኛው ሥራ ላይ የዋለው በዚህ ዓይነት ነው። ጴጥሮስ በሃይማኖት መሪዎች ፊት ቆሞ ሲናገር በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ነበር። በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ እንደሆኑ ተረጋግጦ ላዲቁና ከተመረጡት አንዱ የሀነው እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ ከመሞቱ በፊት በመንፈስ ቅዱስ መሞላቱን እናያለን። ጳውሎስ ጠንቋዩን በመቃወም ከመናገሩ በፊት በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንደነበር እናያለን (የሐዋ. 4፡8፤ 31፤ 7፡55፤ 13፡9)። 

2. በኤፌ 5፡18 ላይ «መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ» ተብሎ ተጽፎአል። ከዚህ ጥቅስ በርካታ ነገሮችን እንዘባለን። 

ሀ. ይህ ለክርስቲያኖች የተሰጠ ትእዛዝ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ልንወጣው የሚገባን ኃላፊነት ነው ማለት ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ አንድ ጊዜም እንኳ በመንፈስ ቅዱስ እንድንጠመቅ አልታዘዝንም። ምክንያቱም በመንፈስ መጠመቅ እግዚአብሔር የሚሰጠንን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የምንቀበልበት የመጀመሪያ ልምምድ ስለሆነ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የምንመላለሰው በዚህ ልምምድ ብርሃን ነው። ይህ «በመንፈስ ቅዱስ መሞላት» በመባል ይጠራል። ክርስቲያኖች ከሆንን በመንፈስ ቅዱስ ለመጠመቅ ወይም ላለመጠመቅ ምርጫ የለንም። ይህ ስጦታ ለክርስቲያኖች ሁሉ የተሰጠ ነው። ነገር ግን ሁላችንም በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ወይም ያለመሞላት ምርግ በእጃችን ነው። በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ትእዛዝ ሆኖ የቀረበው ለዚህ ነው። 

ለ. ትእዛዙ የተጻፈው በቀጣይና የአሁን የግሥ ጊዜ ነው። ይህ ለክርስቲያኖች ለአንዴና ለሁልጊዜ የሚከናወን ልምምድ አይደለም። (ማለትም በጰንጠቆስጤ የሥነ መለኮት ትምህርት ተከታዮች ዘንድ የመንፈስ ቅዱስ ሁለተኛ በረከት በዚህ ዓይነት ሁኔታ እንደሚታየው አይደለም ማለት ነው።) የመንፈስ ቅዱስ ሙላት በእያንዳንዱ ክርስቲያን ሕይወትና ልምምድ ውስጥ በተደጋጋሚ መሆን አለበት። ይህ በተጨማሪ የሚያመለክተን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ የመኖር ችሎታችን ማደግ እንዳለበት ነው (ኤፌ. 1፡17-19)። 

ሐ. የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ማለት ሙሉ በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር መሆን ነው። መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያን ሕይወት መኖሩን የሚያመለክት አይደለም። ይህ ጥቅስ በመንፈስ ቅዱስ መሞላትን በወይን ጠጅ ከመስከር ጋር እንዴት እንዳወዳደረው ልብ በል። አንድ ሰው በወይን ጠጅ ሲሰክር ሰውነቱን መቆጣጠር ያቅተዋል። ንግግሩ ይቀየራል። ቀጥ ብሎ የመራመድ ችሎታውም ይከዳዋል። የሰከረ ሰው ደም ውስጥ ያለው አልኮል ሰውዩው ደኅና ሆኖ የማያደርጋቸውን ነገሮች እንዲያደርግ ምክንያት ይሆናል። ልክ እንደዚሁ በክርስቲያን ልብ ውስጥ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ሕይወቱን ሲሞላ ያን ሰው ይቆጣጠረዋል። አስተሳሰቡንና ተግባሩን ሁሉ ይመራል። ሰውዬው በተግባሩ የሚሳተፈው እያወቀ ቢሆንም እንኳ፥ ራሱ የሚፈልገውን በአማኙ ሕይወት ለመፈጸም፥ የሚቆጣጠር፥ የሚመራና ኃይል የሚሰጥ መንፈስ ቅዱስ ነው። 

መ. ትእዛዙ የተሰጠው በብዙ ቁጥር ነው። ትእዛዙ የተሰጠው ለጥቂት ግለሰቦች ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ነው። ክርስቲያኖች ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ላመሞላት አጥብቀው መፈለግ አለባቸው። ይህ ዕድል የተሰጠው ለጥቂት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የተሰጠ ሳይሆን በኢየሱስ ለሚያምኑ ክርስቲያኖቹ ሁሉ ነው። 

ሠ. ትእዛዙ የተጻፈው በተደራጊ የግሥ ዓምድ ነው። ይህም እኛ በመንፈስ ቅዱስ የምንሞላ ሳንሆን መንፈስ ቅዱስ እራሱ እኛን ይሞላናል ማለት ነው። ይህ ትእዛዝ «መንፈስ ቅዱስ እንዲሞላባችሁ ፍቀዱ» በሚል ሊተረጎም ይችላል። 

ረ. በዙሪያው ያሉትን ጥቅሶች ብንመለከት የመንፈስ ቅዱስ ሙላት አግባብ ካልሆነ አምልኮና በኃይል የተሞላ ሕይወትን ከመኖር ጋር በጣም የተያያዘ መሆኑን እንገነዘባለን። ኤፌ. 5፡15-18 ጳውሎስ ክርስቲያኖች በሚኖሩበት ክፉ ዘመን ማስተዋል ባልጎደለው አካሄድ፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመፈጸምና በታታሪነት በማገልገል እንዲመላለሱ ያሳስባቸዋል። ቀጥሎ በቁጥር 19 ላይ ጳውሎስ፥ አሳቡን ወደ አምልኮ በመቀየር ክፉ ቀናትም እንኳ ቢሆን ለእግዚአብሔር ምስጋናን እየሰጡ ዝማሬንና አምልኮን ስለማቅረብ ችሎታ ይናገራል። የመንፈስ ቅዱስ ሙላት በሰው ሕይወት የሚረጋገጥባቸው አራት መንገዶች አሉ። 

1. በእግዚአብሔር ቃል እርስ በርስ በመነጋገር፡- በመንፈስ ቅዱስ መሞላት እርስ በርስ ኅብረት ወደ ማድረግ ይመራል። እርስ በርስ ለመነጋገር የምናሳየው ፈቃደኝነት በተለይም ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል ለመከፋፈል መቻላችን በእግዚአብሔር መንፈስ የመሞላታችን ማረጋገጥ ነው። በመካከላችን ባለው ግጭት ምክንያት መግባባት ካቃተን በመንፈስ ቅዱስ አልተሞላንም ማለት ነው። በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ማለት በመካከላችን ያለው ግንኙነት በፈሪሃ እግዚአብሔር የተሞላና በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው ማለት ነው። 

2. በመዝሙር፡- የመንፈስ ቅዱስ ፍላጎት ኢየሱስን ማክበር ስለሆነ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያስመልኩና የሚያከብሩ መዝሙሮችን እንድንዘምር ያደርገናል። በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ማለት ኢየሱስን ከልባችን ማምለክ ማለት ነው። 

3. ምስጋና በማቅረብ፡- በመንፈስ ቅዱስ ከተሞላን ነጭናጮችና አጉረምራሚዎች አይደለንም ማለት ነው። በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሰው እግዚአብሔርንና ሌሎችን ያመሰግናል። በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ሰዎች በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሐሴት ለማድረግና ምስጋናን ለማቅረብ የሚችሉ ናቸው። 

4. አንዱ ለአንዱ በመገዛት፡- ጳውሎስ ቆየት ብሎ በባልና በሚስት መካከል የሚታይ ትክክለኛ የንኙነት የሚስት ለባል መገዛት መሆኑን የሚያሳየን ቢሆንም፥ እዚህ ላይ ግን የሚናገረው ክርስቲያኖች በመንፈስ በተሞላ ሕይወት በሚመላለሱበት ወቅት አንዱ ለሌላው እንደሚገዛ ነው። ይህ ባሎች ለሚስቶች፥ ወላጆች ለልጆች፥ ወዘተ… መገዛታቸውን ያካትታል። ለራሳችን የማገልገል ፍላጎቶቻችንን ሌላውን ለማገልገል ከተጠቀምንበት ይህ በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ምልክት ነው። 

ማጠቃለያ- ከላይ በተመለከትናቸው ጥቅሶች መሠረት የመንፈስ ቅዱስ ሙላት መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያን ሕይወት የሚያከናውነው የማያቋርጥ ተግባር ነው። በመንፈስ ቅዱስ የታዘዘ ስለሆነ ይህ ክርስቲያን በንቃት የሚሳተፍበት ጉዳይ ነው። በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት መሠረታዊ አሳብ በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር መሆን ነው። የመንፈስ ቅዱስ ሙላት አስደናቂና ታላላቅ የሆኑ ነገሮችን ማድረግ አይጠይቅም። ይልቁኑ በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ነገር ማድረግ ማለት ነው። ይኸውም፥ ለእግዚአብሔር እውነተኛ ክብርን በሚሰጥ መንገድ ከእርሱ ጋር ኅብረት ማድረግና እርስ በርስ ደግሞ በአንድ አካል ውስጥ እንዳሉ ብልቶች በፍቅር መተሳሰር ማለት ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) ለ3ኛ ጥያቄ የሰጠኽውን መልስ ከላይ ከተመለከተው መልስ ጋር አወዳድር። ምን ያህል ተመሳሳይ ነው? ምን ያህል ይለያል? ለ) አሁን መልስህን የምትከልሰው እንዴት ነው? ሐ) በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያንን ማጥለቅለቅ የዛሬይቱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ትልቁ ፍላጎት መሆን የሚገባው በምን አቅጣጫ ነው? መ) የመንፈስ ቅዱስ ሙላት የሚገለጽባቸውን ከላይ የተጠቀሱትን እራት መንገዶች፥ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ከሚፈጽማቸው አንዳንድ ድንቅ ነገሮች እኩል አድርገን የማንመለከታቸው ለምንድን ነው? የመንፈስ ቅዱስን ድንቅ ሥራዎች ለመፈላጋችን ብዙ ጊዜ ስለምናቀርባቸው የተሳሳቱ ምክንያቶች ይህ ምንን ያሳየናል? 

በአሁኑ ጊዜ ላለች ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጓት አስደናቂ ተአምራት አይደሉም። በልሳናት የሚናገሩ ብዙ ሰዎች አያስፈልጓትም። እነዚህ ነገሮች በሙሉ የግድ በራሳቸው የተሳሳቱ ናቸው ማለት አይደለም። ይልቁኑ እነዚህ ነገሮች በቤተ ክርስቲያን እየበዙ እያሉም እንኳ፥ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ኑሮ ለመኖር ሕዝባችንን ወደ ፈሪሃ እግዚአብሔር ለመሳብ የሚያስችለን ኃይል የሚጎድለን ይመስላል። በጊዜው እጅግ የሚያስፈልጉን በመንፈስ የተሞሉ ክርስቲያኖች ናቸው። እነዚህ በመንፈስ የተሞሉ ክርስቲያኖች መኖራቸው የሚረጋገጠው በምንድን ነው? በመንፈስ ቅዱስ ለላ መሞላት ወደፊት በሚኖሩት ትምህርቶች የበለጠ በዝርዝር እንመለከተዋልን። 

ጥያቄ፡- ሮሜ 8፡3-13ና ገላ 5፡16-26 አንብብ። ሀ) እዚህ ጥቅሶች በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉትንና በኃጢአት ፍላጎቶቻቸው የሚኖሩትን የሚያነጻጽሩት እንዴት ነው? ለ) በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉና በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር የሚኖሩ ክርስቲያኖች ዛሬ የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ሐ) የመንፈስ ቅዱስን ህልውና በመንፈስ የተሞላ ሕይወት በመኖር ብንገልጽ ቤተ ክርስቲያናችንና ሕዝባችንን በሙሉ በምን ዓይነት አኳኋን ይለወጣሉ? 

አብዛኛዎቻችን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የክርስቲያን የመጀመሪያ ልምምድ መሆኑን ለመቀበል የሚያዳግተን በጸጥታ የሚፈጸም በመሆኑ ነው። የጰንጠቆስጤ ዕለት የመጀመሪያ ልምምድ በአእምሮአችን ስላለ ለማንኛውም ሰው መሆን ያለበት እንደዚህ ይመስለናል። ብዙዎቻችን በጰንጠቆስጤ የሥነመለኮት ትምህርት በመሳብ ‹የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት› ብለው የሚጠሩትን ሁለተኛ በረከት የምንፈልገው ለዚህ ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የመንፈስ ቅዱስ መምጣት ሁልጊዜ ተአምራዊ በሆነ መንገድ መሆን አላበት ይላልን? ለመጀመሪያዎቹ 120 ደቀ መዛሙርት የመንፈስ ቅዱስ መምጣት በታላላቅ ምልክቶች የተከሰተ ቢሆንም ወዲያው ከዚህ ሁኔታ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁትንና የተሞሉትን ሦስት ሺህ ሰዎች ስናይ ተመሳሳይ ተአምር ስለመፈጸሙ ምንም ጠቋሚ ነገር የለም። ኢየሱስ የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ጸጥ ባለ የማይታይ ነፋስ ይመስለዋል። እንደዚህም የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ጸጥተኛና የማይታይ ሆኖ ሊፈጸም ይችላል። 

ሌላው ችግራችን መንፈስ ቅዱስ በሚያዘጋጅላቸው ልዩ ኃይል የሚኖሩት ጥቂት ክርስቲያኖች ብቻ መሆናቸው ነው። እግዚአብሔር የሚፈልገው ይህ እንዳይደለ እናውቃላን ስለምንል ሌላ ነገር እንፈልጋለን። የመንፈስ ቅዱስን ኃይል እንድናገኝ «ሁለተኛ በረከት» ማግኘት እንዳለብን እናስባለን። አዎን ብዙ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት እይኖሩም። ችግሩ ግን የመንፈስ ቅዱስ ህልውና ላይሆን ለመንፈስ ቅዱስ ልብን ለመክፈት ፈቃደኛ ያልሆነው ክርስቲያን ነው። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ይገቡ ዘንድ ተስፋ ተሰጥቷቸው ባለማመናቸውና ባለመታዘዛቸው እንዳልገቡ ሁሉ ክርስቲያኖች ሁላችን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ አለን። (የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ብለን የምንጠራው)። በተመሳሳይ አለማመንና አለመታዘዝ ሙላቱን ሳናገኝ እንቀራለን። አንዳንድ ክርስቲያኖች አስደናቂ የሆኑ የመንፈስ ቅዱስ ልምምዶችን የሚለማመዱ ቢሆንም እግዚአብሔር የሚፈልገው መደበኛ ሕይወት ይህ አይደለም። ከዳንበት ቀን ጀምሮ በሕይወታችን የሚገኘው መንፈስ ቅዱስ ያለማቋረጥ በሙላት እንዲገኝ ይፈልጋል። ከላይ በተመለከትናቸው አራት መንገዶች) ጉዳዩ ይህ ከሆነ እግዚአብሔር የልባችንን ጠጣርነት በመንፈስ ቅዱስ ተአምራዊ አሠራር ለመስበር አይገደድም። 

እንግዲህ ተአምራዊ በሆነ አሠራር የሚገለጠውን «ሁለተኛ በረከት» ወይም «የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት» ብለው የሚጠሩትን የጰንጠቆስጤ ክርስቲያኖች ልምምድ እንዴት ልንረዳው ይገባል? እነዚህን ልምምዶች የምንረዳበት አራት መንገዶች አሉ። 

1. አንዳንዶቹ ምን ያህል እንደሆኑ አይታወቅም) ልምምዶች በመንፈስ ቅዱስ ሳይሆን በአጋንንት ኃይል የሚከሰቱ ናቸው። ብዙ ሰዎችን በማማከር አገልግሎት ያሳለፉ ሰዎች መንፈስ ቅዱስ በልሳናት መናገር ችሎታን እንዲሰጣቸው አጥብቀው የፈለጉ አንዳንዶች ይህን ችሎታ ከአጋንንት እንደተቀበሉት መገንዘብ ችለዋል። ይህ የሚሆነው መንፈሳዊ ሆነው በመቅረብ በቤተ ክርስቲያን ውስጥና በቀላሰቦች ሕይወት ውዥንብር እንዲፈጥሩ ነው። ይህ በሚፈጸምበት ጊዜ መከፋፈል ይኖራል፤ ኢየሱስ ክርስቶስም የሚገባውን ክብር አያገኝም። አንድ ሰው በልሳን እየተናገረ እግዚአብሔርን በማያከብር መንገድ ከኖረና ትልቅ መንፈሳዊ እብሪት ወይም ትዕቢት ከታየበት ወይም ውጤቶቹ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከፋፈል ከሆነ ሰይጣን የራሱን ዓላማ ለመፈጸም ላሰውዬው የሰጠው በልሳን የመናገር ስጦታ የማታለያ መሆኑን መጠርጠር እንችላለን። 

2. አንዳንዶች ምን ያህል እንደሆኑ አይታወቅም) የሥነልቦና አሠራሮች ናቸው። የሰው አእምሮ እስገራሚ የሆነ አፈጣጠር ስላለው አንድን ነገር ከሚገባ በላይ ከፈላግነው ያ የፈለግነው ነገር እንዲሆን አስደናቂ ነገርን ያደርጋል። ስለዚህ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ በራሳቸው በልሳን ለመናገር እስከሚለማመዱ ድረስ እንኳ በልሳን መናገርን እጅግ በጣም ከፈለጉ አእሞሮአቸው በልሳናት መናገርን የሚመስል መንተባተብን ሊሰጣቸው ይችላል። ይህ ደግሞ ፍጹም ከመንፈስ ቅዱስ አይደለም። 

3. አንዳንዶች (ምን ያህል እንደሆኑ አይታወቅም።) የተቀበሉት «ሁለተኛ በረከት» ን ሳይሆን ነገር ግን የሕይወት ለውጥ ያገኙበትን በረከት ብቻ ነው። ብዙ ጊዜ ይህን ልዩ ልምምድ የሚለማመዱት ክርስቲያን ነን የሚሉ ግን ወንጌል ፈጽሞ ያልገባቸው ናቸው። ስለዚህ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ ግንዛቤ በሚያገኙበት ወቅት አስቀድመው ክርስቲያን እንደነበሩ ቢያስቡም እንኳ ስላልነበሩ በዚህ ቅጽበት ላይ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ። ስለዚህ ልክ በሚድኑበት ጊዜ የመጀመሪያውን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ አስደናቂ በሆነ መንገድ ይቀበላሉ። 

4. አስቀድመው ክርስቲያን የነበሩ ብዙዎች የመንፈስ ቅዱስን ኃይል በአዲስ መንገድ ይለማመዳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ልምምድ ‹የመንፈስ ጥምቀት› እንደማይላው ተመልክተናል። ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀናል ስንል ይህ አባባል መጽሐፍ ቅዱሳዊ አባባል አይዴለም፡ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ስለ ሆነ በፈለገው መንገድ ከእኛ ጋር ሊገናኝ ይችላል። አስደናቂ በሆነ መንገድ ኃይሉን ሊገልጽልን ከፈለገ ያደርገዋል። ይህንን «በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ» ብለን ከምንጠራው ይልቅ መንፈስ ቅዱስ እኛን ከሚሞላበት መንገዶች አንዱ እንደሆነ ማሰብ የበለጠ ትክክል ነው። የተለያዩ ስለሆኑት መላእነዚህ ልምምዶች የሚከተሉትን ነገሮች መረዳት አለብን። 

ሀ. የሚከሰቱበት አንድ ብቸኛ መንገድ የላም። ለአንዳንዶች ሰልሳን ንግግር ይከሰታሉ። ለሌሎች በመጀመሪያ ታላቅ ሐዘን ቀጥሎም ታላቅ ዴስታ በሚፈጥር ስሜታዊ ልምምድ ይገለጣል። አዲስ በሆነ መንገድ እንዲሠሩ የሚያደርግ ሕይወትን የሚለውጥ ልምምድ ነው። እያንዳንዳቸው እውነተኛ የሆኑ መንፈሳዊ ልምምዶች ሊሆኑ አንዱ ከሌላው አይበልጥም። እያንዳንዱን ልብ ብለን ልንገነዘብና ለሁሉም ትክክላኛ እክብሮት ሊኖረን ይገባል። 

ለ. እዚህ ልዩ የሆኑ በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ በተደጋጋሚ በተለያዩ መንገዶች ሊፈጸሙ የሚችሉት) ልምምዶች ለክርስቲያናዊ ልምምጻችን መሠረት ሊሆኑ አይገባቸውም። እነዚህ ልምምዶችን ታላቅ ቢሆኑም እንኳ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆናችን እና የመዳናችን ተአምር ቀን ከሁሉ የላቀ ነው። የክርስቲያን አረማመድ ትላልቅ ተአምራዊ የሆኑ ልምምዶች መፈለግ ሳይሆን እግዚአብሔር የሚፈልገውን በታማኝነትና በመታዘዝ መኖርን መከታተል ነው። በየዕለቱ በፍቅርና ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ለማደግ መበርታትና ወደፊት መቀጠል አለብን። ታላቅ መንፈሳዊ ክርስቲያን የሚያደርገን አንድ ወይም ተደጋጋሚ ልዩ ልምምዶች ሳይሆኑ ይኸኛው ነው። ደስ ልንሰኝ የሚገባን በሕይወታችን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ስናይ ነው። 

ብዙዎቻችን ዶር ወጥ የምንወድ ቢሆንም ሁልጊዜ እንድንበላው ቀን አንፈልግም። ልዩ የሚሆንልን አንዳንድ ጊዜ ከበላነው ብቻ ነው። ለዕለታዊ ሕይወታችን ጤንነትና ብርታት የሚሰጡን ሥጋ ወጥ፥ የምስር ወጥቶ የአትክልት ወጥና የመሳሰሉት የተለመዱ ናቸው። እንደዚሁ መንፈሳዊ ቤታችንን አንዳንድ ጊዜ በሚሆኑ ስሜታዊ ልምምዶች መመሥረት የላብንም። ወይም ዘወትር አዳዲስና ትላልቅ ልምምዶችን መሻት የለብንም። በመንፈሳዊ ሕይወት ማደግ ማለት በጸሎት፥ የእግዚአብሔርን ቃል በማጥናትና በመመስከር በታማኝነት መኖር ነው። እነዚህ ብዙ አስደናቂ ያልሆኑ የሚመስሉ ነገሮች ናቸው ለሕይወታችን መሠረት የሚሆኑት። የመንፈስ ቅዱስ ድንቅ ልምምዶችን ብቻ ከፈለግን እንደ ባሕር ዛፍ ቅጠል እሳት ይሆናል። ለጊዜው በጣም የሚያሞቅ በሚቀጥለው ቅጽበት ግን የሚሞት ማለት ነው። እግዚአብሔር የሚባርከው ሕይወት በመንፈስ በጸጥታ ያለማቋረጥ በጽናትና በትዕግሥት የምንኖረውን ሕይወት ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) መንፈስ ቅዱስ ልዩ የሆነ አስደናቂ ነገር በሕይወትህ እንዲያደርግ ፈልገህ ታውቃለህን? እንዲያደርግልህ የፈለግኸው ነገር ምን ነበር? ይህን ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ የፈለግህበት ዋና ዓላማ ምን ነበር? ለ) ከእግዚአብሔር ዘላቂነት ያለው ሕይወት በመኖር መንፈሳዊ ሰው እንድትሆን ይህ በምን አቅጣጫ ይበልጥ አስፈላጊ ይመስልሃል? ሐ) መንፈስ ቅዱስ ሰዎችን የሞላበትን ሦስት የተለያዩ መንገዶች እንዴት እንዳየህ ምሳሌዎችን ጥቀስ። ከእነዚህ ውስጥ በሕይወትህ የተፈጸመው የትኛው ነው? ምሳሌዎችን ስጥ።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.