መንፈስ ቅዱስ የክርስቲያኖች ሕይወት ኢየሱስን እንዲመስል የሚሰጠው አገልግሎት

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በጀርመን አገር ለተራቡ ሰዎች ምግብ ያድሉ ስለነበሩ የቃል ኪዳን አገሮች ወታደሮች የሚነገር ታሪክ አለ። በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ስለ ጦርነት ብቻ የሚያውቅ አንድ ትንሽ ልጅ ምግቡ ሊታደል ተራ ደርሶት ድርሻውን በሚቀበልበት ጊዜ ለወታደሩ እንዲህ ብሎ እንደጠየቀ ይነገራል «ጋሼ፥ እርስዎ ኢየሱስ ነዎት እንዴ?» 

ትናንትና ከእግዚአብሔር አብና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንድናደርግ ስላሚረዳን የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ተመልክተናል። ይህ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ስልባችን የሚኖረውን ዘላለማዊ አምላክ እንድናመልክና ወደ እርሱ እንድንጸልይ የሚረዳበት ነው። ዛሬ ኢየሱስን እንድንመስል ስለሚያደርገው የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት እናጠናለን። ትንሹ ልጅ ወታደሩን የጠየቀው ጥያቄ ዛሬም ዓለም እኛን በየዕለቱ የሚጠይቀን ጥያቄ ነው። ኢየሱስን እንመስል እንደሆነ ለማረጋገጥ ይከታተሉናል። ኢየሱስን እንመስል ዘንድ በልባችን ውስጥ መሥራት የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ነው። ጌታ ወዳለበት እስክንደርስ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት እይቋረጥም። መንፈስ ቅዱስ በባሕርያችንና በተግባራችን ኢየሱስን እንመስል ዘንድ ዕለት በዕለት በዝግታ፥ ቢሆንም ግን በእርግጠኝነት ውስጣዊ ኑባሬአችንን ለመለወጥ ይሠራል። 

ጥያቄ፡– በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ያሉና እግዚአብሔርን በሚፈሩ ክርስቲያኖች ሕይወት የሚታዩ ባሕርያትን ዘርዝር። 

ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት። 2ኛ ቆሮ. 3፡17-18፤ 4፡16፤ 1ኛ ዮሐ 3፡2-3፤ ሮሜ 8፡29። ሀ) በእነዚህ ጥቅሶች ለክርስቲያኖች የተሰጡ ተስፋዎች ምንድን ናቸው? ለ) ኢየሱስን የምንመስልባቸው ናቸው ብለህ የምታስባቸውን ከአንዳንድ ምሳሌዎች ጋር ጥቀስ። 

ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት። ሮሜ. 8፡29፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡47-49፤ 2ኛ ቆሮ. 3፡18-19፤ ፊልጵ. 3፡20-21፤ 1ኛ ዮሐ 3፡2። ሀ) የበለጠ ኢየሱስን እንድንመስል መንፈስ ቅዱስ የሚያደርጋቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) መንፈስ ቅዱስ ይህንን በማድረግ በሕይወትህ እንድታድግ ለመርዳት የሚጫወተውን ሚና ያየኸው እንዴት ነው? 

መንፈስ ቅዱስ በልባችን ያድር ዘንድ ወደ ሕይወታች ሊመጣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የበለጠ ወደ መምሰል እንድንለወጥ ወዲያውኑ ሥራውን ይጀምራል። አንዳንድ ጊዜ ለብዙ ዓመታት በባርነት ገዝቶን የነበረ ኃጢአትን ወይም ልማድን ለማሸነፍ እንድንችል መንፈስ ቅዱስ ከመቅጽበት ይረዳናል። ለምሳሌ፡= ሰካራም የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ወደ ክርስቶስ ሊመጡ ወዲያውኑ አልኮል መጠጥ የመጠጣት ፍላጐታቸው ይሞታል። ብዙ ጊዜ ግን መንፈስ ቅዱስ በጊዜ ብዛት ኢየሱስ እንድንሆን ወደሚፈልገው ደረጃ እንድንደርስ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ይሠራል። ይህ ሂደት በሽንኩርት ሊመሰል ይችላል። ሽንኩርት ብዙ የተደራረቡ ቆዳዎች ያሉት እንደመሆኑ መጠን መንፈስ ቅዱስም ለውጣችንን የሚያከናውነው ደረጃ በደረጃ ነው። መንፈስ ቅዱስ ኃጢአታችንን በሙሉ በአንድ ጊዜ በቅጽበት ክሕይወታችን አያስወግድም። (ማለትም እርሱን የሚያስከብሩ መጥፎ ልማዶቻችንንና፥ የተሳሳቱ የአስተሳሰብ ዘይቤዎቻችንን ወይም ባሕላዊ ልምምዶቻችንን በአንድ ጊዜ አያስወግድም) ይልቁኑ በሕይወታችን በአንድ ጊዜ አንድን የሕይወታችንን ክፍል በማሳየት ያንን እንድናስተካክል ያደርጋል። ኢየሱስን የማያስከብሩ ልማዶቻችንን ስናስወግድ ወደ ሌላ የሕይወት ክፍል ደግሞ ያልፋል። የዚህን ሂደት ጥሩ ምሳሌ «የመናኝ ጉዞ» በሚለው መጽሐፍ ውስጥ እናገኛለን። 

ቀደም ባለው ትምህርት በዳንን ወቅት መንፈስ ቅዱስ ኃጢአታችን እንዳጠበልን ተመልክተናል። ኃጢአት ብናደርግም እንኳ መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ደም ስለሚሸፍነን በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ተብለን እንጠራለን። 

እግዚአብሔር ጻድቅ ብሎ የሰጠንን ደረጃ ልናሟላ አንድ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታን መሥራት ይጀምራል። ይህ ክርስቶስን እንመስል ዘንድ በሕይወታችን የምናልፍበት የመለወጥ ሂደት ‹መቀደስ) ይባላል። 

ጥያቄ፡– የሚከተሉትን ጥቅሶች እንብብ። ኤፌ 1፡4፤ 4፡21-24፤ 5፡25-27፤ ቲቶ 2፡11-12፤ ዕብ 12፡14፤ 2ኛ ጢሞ 2፡21። እግዚአብሔር እንቀደስ ዘንድ ስላ መፈለጉ እነዚህ ጥቅሶች ምን ያስተምራሉ? 

ሀ. በንጽሕና በመኖር የኃጢአት ተፈጥሮአችንን በመቆጣጠርና በሕይወታችን ያሉ ኃጢአቶችን በማሸንፍ ኢየሱስን እንድንመስል መንፈስ ቅዱስ ይረዳናል (ሮሜ. 6፡16፤ 2ኛ ተሰ 2፡13፤ 1ኛ ጴጥ 1፡2፤ ሮሜ. 2፡29፤ 8፡4-13፤ ገላ 5፡16)። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ እግዚአብሔር «እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ ቅዱሳን ሁኑ» ብሎ አዞናል (ዘሌ 11፡44፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡4-15)። በአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ከዓለም ተለይተው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የእግዚአብሔር በመሆናቸው «ቅዱሳን” ተብለው ይጠራሉ። 

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቅድስና ወይም መቀደስ መሠረታዊ ትርጉሙ ‹መለየት» ማለት ነው። ሁለት ዓይነት ቅድስናዎች አሉ። የመጀመሪያው፥ የአቋም ቅድስና ነው። በትምህርት 6 እንደተመለከትነው በዳንንበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ ከሠራቸው ሥራዎች አንዱ ከኃጢአታችን እኛን ማጠር እንደሆነ ተመልክተናል (ቲቶ 3፡15)። በኢየሱስ ክርስቶስ በምናምንበት ወቅት ደሙ ኃጢአታችንን በመሸፈን በእግዚአብሐር ዓይን ፊት ንጹሕ ያደርገናል። ነገር ግን በአቋም መቀደሳችንን ወደ ተግባር እንድንለውጠው እግዚአብሔር ይፈልጋል። በሁለተኛ ደረጃ ፥ የምግባርና የአኗኗር ቅድስና አለ። በፊልጵ. 2፡12-13 «በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ መዳናችንን እንድንፈጽም» የታዘዝነው ለዚህ ነው። ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ድነት (ደኅንነት) ሊተገበርና እርሱን እንመስል ዘንድ ባሕርያችን ሊለወጥ ይገባዋል። 

ይህ ሁለተኛው ዓይነት ቅድስና ሦስት መልኮች አሉት። በመጀመሪያ፥ መቀደስ ማለት ከዓለም ክፉ ሥርዓት መለየት አለብን ማለት ነው። የምንመራው ሕይወት፤ አስተሳሰባችን በልባችን ያለው ውስጣዊ ዝንባሌ ከዓለም ሕይወት ፈጽሞ የተለየ መሆን አለበት። 

በሁለተኛ ደረጃ ፥ ከኃጢአት መለየት አለብን። ቅድላና ማለት የኃጢአት ሕይወት አንኖርም ማለት ነው። ከኃጢአት ስመሽሽ እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ መንገድ እንኖራለን። 

በሦስተኛ ደረጃ ፥ ለእግዚአብሔር ተለይተን ለአገልግሎት የተሰጠን ልንሆን ይገባል። የኃጢአት ሁሉ መሠረት ዓመፅ ነው። ኃጢአትን በምናደርግበት ጊዜ እግዚአብሔር በሕይወታችን ባደረጋቸው ሕጐች ላይ እናምፃለን ማለት ነው። በቅድስና ስንኖር ግን እግዚአብሔር ለሕይወታችን በደነገጋቸው ሕጐች ለመኖር እራሳችንን ሰጠን ማለት ነው። በቅድስና መራመድ ማለት ሕይወታችንን ለእግዚአብሔር በመስጠት ለራሳችን ሳይሆን ለእግዚአብሔር ክብር እንኖራለን ማለት ነው። 

ጥያቄ፡– ክርስቲያን ቅዱስ ሊሆን የሚችልባቸውን ሦስት መንገዶች በምሳሌነት ስጥ። 

መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ሁሉ የላቀው እንድንቀደስ እኛን መርዳቱ ነው። ይህ ማለት ከኃጢአት ቁጥጥር ውጭ የሆነ የተለየ ሕይወት እንድንኖር ማስቻሉ ነው። በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በርካታ ሕግጋትን በመስጠት እንዲታዘዟቸው ነገራቸው። ይሁንና የመንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው የማደርና ኃይልን የማስታጠቅ አገልግሎት በዚያ ዘመን ስላልነበር ሕግጋቱን መጠበቅ አልቻሉም። በዚህ ምትክ እነዚህ ሕግጋት ኃጢአትን የማድረግ ፍላጐት እንዳሳደሩባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይነገረናል (ሮሜ ፡14-24)። እግዚአብሔር የብሉይ ኪቶን ሕግጋትን ከሰጠባቸው ዓላማዎች አንዱ ሰው ምን ያህል ኃጢአተኛ እንደሆነ በማሳየት ለደኅንነታችን ለእግዚአብሔር አንድ ነገርን ለመሥራት ከመታገል ይልቅ ምሕረትን ፍለጋ ወደ እርሱ ዞር እንድንል ለማድረግ ነበር (ገላ 3፡21-25)። 

በአዲስ ኪዳን ግን እግዚአብሔር ሰውን ቅዱስ ለማድረግ የሚሠራበትን መንገድ ለወጠ። በመጀመሪያ፥ የእግዚአብሔር አትኩሮት የኃጢአት ፍሬ በነበረው ውጫዊ ተግባር ላይ አልነበረም። ይልቁኑ የኃጢአት ሥር በሆኑት ውስጣዊ ዝንባሌዎች ላይ ነው (ማቴ. 5፡20-48)። አሁን እግዚአብሔር አትኩርት የሚሰጥበት ነገር ለእርሱና ለሌሎች በሚገለጥ ፍቅር ላይ ነው። በእነዚህ ሁለት ውስጣዊ ዓላማዎች የብሉይ ኪዳን ሕግጋት በሙሉ ተጠቃለው ይፈጸማሉ (ማቴ. 22፡37-39፤ ሮሜ 3፡8-10)፥ በሁለተኛ ደረጃ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን በክርስቲያኖች ሕይወት እንዲኖር ስለሰጠ ኃጢአትን የማድረየ ፍላጐትን ለማሸነፍ አሁን ጉልበት አላቸው። 

ይሁን እንጂ በኢየሱስ በምናምንበት ጊዜ እግዚአብሔር ኃጢአት የማድረግ ችሎታችንን ከእኛ ይወለዳል ማለት አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነማ መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ኃጢአትን እንደምናደርግ ያስተምራል። በምድር ላይ እያላን ኃጢአት ወደሌለበት ፍጹምነት እንደምንደርስ መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምርም። ይህንን ለሚያስተምሩ ክርስቲያኖች ሐዋርያው የሚሰጠው መልስ የሚከተለው ነው «ኃጢአት የለብንም ብንል እራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። (1ኛ ዮሐ 1፡8)። 

ጥያቄ፡– ገላ. 5፡16-25 እንብብ። ሀ) በልባችን ስለሚካሄድ ጦርነት እነዚህ ጥቅሶች ምን ያስተምሩናል? ላ) ይህንን ጦርነት እንዴት እንዳየህ ከሕይወትህ ምሳሌ በመስጠት ግለጽ። 

ክርስቲያን በምንሆንበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ አዲስ ተፈጥሮ ይሰጠናል። ይህ አዲስ ተፈጥሮ ከእግዚአብሔር የሚገኝና እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት የሚፈልግ ተፈጥሮ ነው። ነገር ግን ከውስጥ ከልባችን፥ በእግዚአብሔር ላይ ለማመፅና ኃጢአትን ለማድረግ የሚፈልግ ተፈጥሮ ተሰውሮ ይኖራል። በገላ. 5፡16–26 እነዚህ ሁለት ተፈጥሮዎች በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ እንደሚኖሩና በእያንዳንዱ የክርስቲያን ሕይወት እንቅስቃሴ የበላይ ሆኖ ለመቆጣጠር እርስ በርስ በጦርነት ላይ እንደሚሆኑ እናነባለን። በሰይጣን ተጽዕኖ ሥር ያለ ኃጢአታዊ ተፈጥሮ የክርስቲያንን አእምሮና ተግባር በመቆጣጠር በእግዚአብሔር ላይ እንዲያምጽ ለማድረግ ይጥራል። ይህ እግዚአብሔር በልባችን ዙፋን እንዲቀመጥና ለእርሱም በመታዘዝ እንድንኖር ከመፍቀዱ ይልቅ፥ እኔነትን በሕይወታችን ዙፋን ላይ ማስቀመጥና ፍላጎታችንን መፈጸም መሆኑ ተገልጿል። በመንፈስ ቅዱስ ተጽዕኖ ሥር ያለው አዲስ ተፈጥሮ ግን እግዚአብሔርን የሚወድና እግዚአብሔርን በመታዘዝ ለመኖር የሚፈልግ ነው። እነዚህ ሁለት እርስ በርስ የሚቃረኑ ስሜቶች በልባችን ውስጥ ያላማቋረጥ የሚታገሉት ለዚህ ነው። አዲሱን ተፈጥሮአችንን የሚዋጋ ኃጢአታዊ ተፈጥሮአችን ብቻ ሳይሆን፥ የዓለም ሥርዓት ማታለልና ዲያብሎስም ጭምር ናቸው። ስለዚህ ምንም እንኳ መንግሥተ ሰማይ እስክምንደርስ ፍጹም መሆን እንደማንችል ብንገነዘብም፡ ይበልጥ ቅዱስ ለመሆንና ኢየሱስን ለምመሰል ከምናደርገው ጥረት የተነሣ የክርስቲያን ሕይወት የማያቋርጥ ውጊያ የሚካሄድበት ሕይወት ነው። 

አዲሱ ተፈጥሮ ሙሉ በሙሉ የበላይ ተቆጣጣሪ ይሆን ዘንድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንዴት መተባበር እንችላለን? ይህ ሂደት ከሁሉ በላቀ ሁኔታ የተገለጸው በሮሜ 7-8 ላይ ነው። (ጊዜ ካላህ እነዚህን ትምህርቶች በጥልቀት ለመረዳት ከሮሜ የት.መ.ማ መጽሐፍ ላይ ተመልከት።) በዚህ ክፍል ጳውሎስ በርካታ እውነቶችን ያስተምረናል። 

ነገሩ የሚገርም ቢሆንም በመጀመሪያ፥ ቅድስና የሚመጣው የሰውን የልብ ክፋት በጥልቀት ክተገነዘብን በኋላ ብቻ ነው። «እኔ ደኅና ነኝ፤ ምንም እልልም፤ እንደ እከሌና እከሌ ኃጢአተኛ አይደለሁም፤» ብለን ካሰብን ፈጽሞ ልንቀደስ አንችልም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንኳ በሕይወት ዘመኑ መጨረሻ ከኃጢአተኞች ዋናው እኔ ነኝ ብሏል (1ኛጢሞ. 1፡15)። በእግዚአብሔር ፊት እውነተኞች ሆነን ወደ ውስጣዊ ልባችን ስንመለከትና ትዕቢታችንን፥ ስስታምነታችንን፥ ክፉ ምኞታችንን፥ ቁጣችንን፥ የተሳሳቱ አሳቦቻችንንና ማንም ሳያውቀው የምናደርጋቸውን ሌሎች ኃጢአቶቻችንን ስንመለከት ሁላችንም ከጳውሎስ ጋር «ከኃጢአተኞች ዋነኛው ነኝ» ማለት ይገባናል። ቅዱስ ለመሆንና በቅድስና ለማደግ በሕይወታችን ውስጥ ስላሉ ኃጢአቶች በበለጠ ጥልቀት ስናውቅ ማንነታችንን ልንጠላና ኢየሱስ እንዴት እንደ ወደደን ከፍተኛ አድናቆት ሊያድርብን ይገባል። ቅድስና የሚመሠረተው ለእግዚአብሔር ባለ የፍቅር ሕይወት ላይ እንጂ የተሻልን ለመሆን በምናደርገው ጥረት አይደለም። በሕይወታችን ምንም ችግር እንደ ሌለ፥ ከሌሎች የተሻልን እንደ ሆንን ማሰብ ስንጀምር ያኔውኑ ግብዞች እንሆናለን። በያዝነው ሕይወታችን እርካታ ከተሰማን ለጽድቃችን የክርስቶስ ስጦታ እንደሚያስፈልገን እንድንሻ ሳንረዳ እንቀራለን። ኢየሱስን ለመምሰል ማደግ እንደሚያስፈልገን መገነዘብ ይሳነናል። ኢየሱስን ለመምሰል እንድንሻ የሚያደርገን ኃጢአታችንን በጥልቀት ስንረዳ ብቻ ነው። እግዚአብሔር የማይንቀው የተዋረደውንና የተሰበረውን ልብ ብቻ ነው (መዝ. [51]:17)። 

በሁለተኛ ደረጃ ፥ የኃጢአት ተፈጥሮ በሕይወታችን ላይ ጉልበት እንደሌለው ተነግሮናል። ክርስቲያን ከመሆናችን በፊት እናደርግ እንደነበረው ለኃጢአት ተፈጥሮአችን መታዘዝ የለብንም። ጳውሎስ የጥምቀትን ምልክት በመጠቀም በድነት (ደኅንነት) ወቅት ከኢየሱስ ጋር በሞቱ፥ በመቃብሩና በትንሣኤው እንደተባበርን ይገልጻል። በምንጠመቅበት ጊዜ በእግዚአብሔር ዓይን በመስቀል ላይ ሞተናል፥ ተቀብረናል ከኢየሱስም ጋር ከሞት ተነሥተናል። የሞትነው ለኃጢአተኛ ተፈጥሮአችን ነው። ኃጢአታዊ ተፈጥሮአችን ተወገደና ለአዲስ ሕይወት ትንሣኤን አገኘን። የኃጢአት ተፈጥሮ፥ ኃይልና በእኛ ላይ የነበረው ሥልጣን በመስቀል ላይ ተቸነከረ (ሮሜ 6፡1-10፤ ገላ. 5፡24)። በአዲስ ሕይወት እግዚአብሔርን ደስ የማሰኘት እርሱን የማወቅ፥ የመውደድና የማገልገል ፍላጐት አለን። በተፃራሪ አሮጌው ሕይወት ገንዘብን፥ ትምህርትን፥ ኃይልንና ክብርን ወዘተ… ላራሳችን ጥቅም በመፈለግ የምንኖረው ነው። እሮጌው ሕይወታችን ወደ ራሳችን የሚያተኩር ሲሆን አዲሱ ሕይወታችን ግን የሚያተኩረው ወደ እግዚአብሔር ነው። 

በሦስተኛ ደረጃ፥ ኃጢአታዊ ተፈጥሮአችን በእኛ ላይ ያለው የበላይነት እንጓከተመ መገንዘብ አለብን (ሮሜ 6፡11)። የብዙዎቻችን ችግር ኃጢአትን ከማድረግ ሌላ ምንም ምርጫ እንደሌላን ማመናችን ነው። ስለዚህ ፈተና በመንገዳችን በሚመጣበት ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመቋቋም ኃጢአትን ከማሸነፍ ይልቅ ለኃጢአት እጃ ችንን እንሰጣለን። ጳውሎስ የሚነግረን በእኛ ላይ የበላይ ተቆጣጣሪ የነበረው ኃጢአታዊ ተፈጥሮአችን ስለተሸነፈ ኃጢአት ማድረግ እንደሌለብን ነው (ሮሜ 6፡11-12)። 

አራተኛ፥ እንታዘዘው ዘንድ እራሳችንን ለእግዚአብሔር ዘወትር ልናቀርብ ያስፈልጋል። ሰይጣንና እኔነታችን ተመልሰው በሕይወታችን የበላይ ለመሆንና ለመንገሥ የማያቋርጥ ጥረት ያደርጋሉ። ነገር ግን ጳውሎስ ክርስቶስን በሕይወታችን ሁልጊዜ ማንገሥ እንዳለብን ይነግረናል። ይህን የምናደርገው ያለመታከት ሙሉ በሙሉ እራሳችንን ለእግዚአብሔር በማቅረብ ነው። ይህን በምናደርግበት ጊዜ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ኃጢአትን እንድናሸንፍና በፈተና ድል አድራጊ እንድንሆን ይረዳናል (ሮሜ 6፡13-14፤ 12፡1-2)። 

በአምስተኛ ደረጃ፥ «አእምሮአችንን» መቆጣጠር መማር አለብን (ሮሜ 8፡5-14)። ኃጢአታዊው ተፈጥሮአችን የሚፈልጋቸውን ነገሮች ካሰብን በኃጢአታዊ ተፈጥሮአችን እንሸነፋለን። አዲሱ ተፈጥሮእችን የሚፈልጋቸውን ነገሮች ካሰብን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል የኃጢአታዊውን ተፈጥሮ ኃይል እንድናሸንፍና እግዚአብሔርን ደስ እንድናሰኝ ያስችለናል። እእምሮአችንን በጐ፥ ቅዱስና እግዚአብሔርን ለሚያስከብሩ ነገሮች ላይ እንድናደርግ በተደጋጋሚ የተነገረን ለዚህ ነው (ኤፌ. 4፡22-24፤ ቈላ. 3፡1-2፤ ፊልጵ. 4፡8-9)። የእግዚአብሔርን ነገሮች ማሰብ እንድንችል ይረዳን ዘንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃል ማጥናት አስፈላጊ የሚሆነውም ለዚህ ነው። 

እርስ በርሳቸው የማይዋደዱ አንድ ነጭና አንድ ጥቁር ውሾች ያሉት እንድ ሰው ነበር። ይህ ሰው በገበያ ቀናት ውሾቹን እያያዘ ወደ ተለያዩ መንደሮች በመሔድ እርስ በርሳቸው ሲነካከሱ ያሳይ ነበር። ሰዎች እየተሰበሰቡ የትኛው ውሻ እንደሚያሸንፍ ከባለቤትየው ጋር ይወራረዱ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ነጩ በሌላ ጊዜ ደግሞ ጥቁሩ ውሻ ያሸንፍ ነበር። ሰውዬው የትኛው ውሻ እንደሚያሸንፍ ሁልጊዜ ያውቅ ስለነበር በውርርዱ አሸናፊነት በሚያገኘው ገንዘብ እየከበረ ሄደ። አንድ ቀን አንድ ሰው አሸናፊውን ውሻ ሁልጊዜ እንዴት እንደሚያውቅ ጠየቀው። ባለቤትየውም ሲመልስ ‹የሚያሸንፈው በሚገባ የመገብኩት ውሻ ነው) በማለት መለሰለት። ‹ጥቁሩን ውሻ በሚገባ የመገብኩት ዕለት፥ ጥቁሩ ውሻ ያሽንፋል። ነጩን ውሻ በሚገባ የመገብኩት ዕለት ደግሞ፥ ነጩ ያሸንፋል› አለው። በኃጢአታዊ ተፈጥሮአችንና በአዲሱ ተፈጥሮአችን መካከል በሚደረገው ጦርነት መካከል ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። በሚገባ የመገብነው ተፈጥር እርሱ ያሸንፋል። መልካም የሆኑትን ነገሮች ካሰብን፥ መጽሐፍ ቅዱስን ካነበብንና ከጸለይን የኃጢአትን ተፈጥሮ እናሸንላን። መልካም ያልሆኑ ነገሮችን ካሰብን፥ በቴሌቪዥን የምንመለከታቸው+ ከመጽሐፍ የምናነባቸው ነገሮችም መልካም ካልሆኑ ኃጢአታዊው ተፈጥሮአችን አዲሱን ተፈጥሮእችንን ያሸንፋል። 

ጥያቄ፡– ሀ) ክርስቲያኖች ኃጢአታዊ ተፈጥሮአቸውን እንዴት ሊመግቡ እንደሚችሉ ምሳሌዎችን ዘርዝር። ለ) ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ተፈጥሮአቸውን እንዴት ሊመግቡ እንደሚችሉ ምሳሌዎችን ዘርዝር። ሐ) በመንፈሳዊ ብስለት እንድታድግ የሚያደርጉ ነገሮችን ለማሰብ የበለጠ ጊዜ መውሰድ እንድትችል አእምሮህን የምታዳብርባቸውን መንገዶች ዘርዝር። 

በእግዚአብሔር ሕግጋትና በቅድስና መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ልንታዘዛቸው የሚገቡ አንዳንድ ሕግጋትን ወይም የሥነ ምግባር ደንቦችን ሰጥተናል። (ለምሳሌ «አትግደል»።) እነዚህ ሕጐች የእግዚአብሔርን ባሕርያት የሚያንጸባርቁ እንደሆኑና እንደ ኢየሱስ መሆን ከፈለግንም ሕግጋቱን መጠበቅ እንደሚገባን ተገልጾአል። እግዚአብሔር ቅዱስ እንድንሆንና እያንዳንዱን የሕግ ክፍል የፈጸመውን ኢየሱስን እንድንመስል መጽሐፍ ቅዱስን መመዘኛ አድርጐ አኑሮልናል (ማቴ. 5፡17-18)። 

ይህ ለማድረግ ቀላል ነገር ይመስላል። ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር በርካታ ሕግጋትን መዘርዘርና በጥንቃቄ ትክክል ነው ወይስ ለሕተት እያልን መከታተል ነውን? አይደለም! በእንደዚህ ዓይነት በሕግና በቅድስና መካከል ስላለው ግንኙነት ክርስቲያኖች ከሁለት ስሕተቶች በአንዱ ላይ እንዲወድቄ ይገደዳሉ። መንፈሳዊ ያደርጉናል ብለው የሚያስቧቸውን ሰብዓዊ ደንቦች መጠበቅ ቅዱስ የመሆኛው መንገድ ነው ብለው የሚያስተምሩ በርካታ ክርስቲያኖች በአንድ ወገን አሉ። ካልጠጣን፥ ካላጨስን፥ ጣት ካልቃምን፥ ትክክለኛ ልብሶችን ከለበለንና ሌሎች መንፈሳዊ ነው ብለው የሚያስቡትን ነገር ካደረግን መንፈሳዊ ነን በማለት ያስተምራሉ።ወይም (በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጠቀሱ) አንዳንድ ነገሮችን የሚያደርጉ በእርግጥ ትክክለኛ መንፈሳውያንና እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ልምምዶች ይቃወማል ከሚሉ ሌሎች ክርስቲያኖች የተሻሉ ናቸው በማለት ያስተምራሉ። ይህ ‹የሕግ አጥባቂነት ስሕተት› ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ጳውሎስ የገላትያ ሰዎችን በመቃወም የጻፈውም ስለዚህ ኃጢአት ነው። ሕግ አጥባቂነት የሚመጣው በሁለት መልክ ነው። 

የመጀመሪያው፥ የሕይወት ገጽታዎችን በሙሉ የሚዳስሱ ሕጐችን በማውጣት ብንፈጽማቸው እግዚአብሔርን ደስ እናሰኛለን የሚል የተሳሳተ አሳብ ነው። የዚህ አስተሳሰብ ችግር ግን እግዚአብሔር ስለ ውዳዊ ሕግጋት ብቻ ሳይሆን ስለ ውስጣዊ ዝንባሌዎችም የሚገደው መሆኑን አላማጤኑ ነው። ለእያንዳንዱ ሁኔታ ሕግጋትን ከመስጠት ይልቅ እግዚአብሔር በሕይወት ለሚገጥሙን ነገሮች በሙሉ የምንከተለውን አጠቃላይ መርሕ ሰጥቶናል። 

ሁለተኛው፥ መልካም ከሆንን፥ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ቤተ ክርስቲያን ያስተምራል ብለን የምናስባቸውን የተለያዩ በርካታ የሆኑ ግዴታዎችን ካሟላን፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት የሚያበቃን ጽድቅ አለን የሚል እሳብ ነው። ዳሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያስተምረን «ጻድቅ የለም እንድ ስንኳ፤» (ኢሳ 64፡6፤ ሮሜ 3፡9-20)። «ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል» (ሮሜ 3፡23)። መንግሥተ ሰማያትን ለማግኘት ተስፋ የምናደርግበት ብቸኛ መንገድ ሰብዓዊ ጥረታችንን ሁሉ እንደማይረባ ምናምንቴ ነገር ቆጥረን ኢየሱስ የኃጢአታችንን ዕዳ ወደ ከፈላበት መስቀልና በእምነት ወደ ሚሰጠን ጽድቅ ፊታችንን መመለስ ነው። ድነት (ደኅንነት) በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት) ሁልጊዜ የሚሰጠን እንጂ በምናደርገው ነገር ፈጽሞ የምናገኘው እይደላም (ኤፌ. 2፡8)። 

ጥያቄ፡– እንዳንድ ክርስቲያኖች በልብ አሳባቸውና ዝንባሌያቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ፥ የሆኑ ልምምዶችን በመታዘዙ ላይና ቅዱሳን እንደሚያደርጓቸውም በማመኑ ላይ እንዴት እንደሚያተኩሩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ። 

ሌሎች ደግሞ የምንድነው ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን በኢየሱስ በማመን ብቻ ከሆነ፥ ከሕግም ነፃ ከሆንን የምንፈልጋቸውን ማናቸውንም ነገሮች ማድረግ እንችላለን ይላሉ። ሕግጋትን መጠበቅም ሆነ መቀደስ አያስፈልግም ይላሉ። ይኽኛውም እንደ መጀመሪያው አደገኛ ስሕተት ነው። ሕግጋት ሁሉ እጅግ ጠቃሚ እንደሆኑና እግዚእብሔር በቃሉ የሰጠውን ትእዛዝ ከመጠበቅ ማንም ፈቀቅ ማለት እንደሌለበት ኢየሱስ አስጠንቅቆአል (ማቴ. 5፡18-19)። 

የእግዚአብሔርን ሕግጋት በሕግ አጥባቂነት ወይም ልማዳዊ በሆነ መንገድ በመጠበቅና ንጹሕ ወይም ቅዱስ ሆኖ እግዚአብሔርን በሚያስከብር ግሩም ለ) መን ክርስቲያንን ላይ የት ምንድን ነው 

መንገድ በመታዘዝ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ልዩነቱ ድርጊቶቹን ሰምናደርግበት ውስጣዊ ዓላማ ላይ የተመሠረተ ነው። ሕግጋትን ወይም አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ልምምዶችን ሀ) እግዚአብሔር ይቀበለን ዘንድ፥ ወይም ለ) መንፈሳዊ መስሎ ለመታየት የምንጠብቅ ከሆነ የሕግ አጥባቂነት ጥፋት እንፈጽማለን። በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የምናደርገው አንዳችም ነገር የለም። እግዚአብሔር እኛን መቀበሉ ነፃ ስጦታ ነው። መንፈሳዊነት የልብ ጉዳይ እንጂ በውጫዊ ተግባራት የሚለካ አይደለም። እንደ እግዚአብሔር ልጆች እግዚአብሔርን ለመታዘዝ የምንፈልግበት ምክንያት የእግዚአብሔርን ችሮታ ለማግኘት ሳይሆን እግዚአብሔርን ስለምንወደውና እርሱን ደስ የሚያሰኘውን ለማድረግ ስለምንሻ ነው። የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ለኢየሱስ ፍቅሩን የሚገልጥበትን መንገድ ያውቃል (የኢየሱስን ፍቅር ለማግኘት ዋጋ የመክፈል ጉዳይ አይደለም።) ይህም ኢየሱስ የተናገረንን በመታዘዝ ነው (ዮሐ 14፡15)። ስለዚህ በመጨረሻ የምናየው ፍቅር የመቀደሳችን ውስጣዊ መነሻ አሳብ ነው። ኢየሱስ ሲናገር እግዚአብሔርንና ሌሎችን ስንወድ ሕግጋትን በሙሉ በመንፈስና በተግባር ጭምር እንፈጽማለን (ማቴ 22፡35-40)። ጳውሎስ ሰኋላ እንደተናገረው ያለ ፍቅር ሰዎችን ለማስደነቅ የምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ከንቱ ዋጋ የሌላቸው ናቸው (1ኛ ቆሮ. 13፡1-3)። ያላ ፍቅር ቅዱስ ለመሆን የምናደርገው ሙከራ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቅድስና ሳይሆን 

የሰውን ሕግጋት መጠበቅ ብቻ ነው። 

ቅዱስ መሆን መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን የሚሠራውና እኛ የተቀደሰ ሕይወት ለመኖር ያላን ፍላጐት ጥምር ውጤት ነው። መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር የሚሠራ እንጂ ያለ እኛ የሚሠራ አይደለም። እኛ ምንም ጥረት የማናደርግ ከሆነ እርሱም አንዳች አያደርግም። ይልቁኑ የምናደርጋቸውን ነገሮች እኛን ቅዱስ ለማድረግ ይጠቀምባቸዋል። ለምሳሌ፡- መንፈስ ቅዱስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን፥ ጸሎታችንን፥ አምልኮአችንን፥ የጥሞና ጊዜያችንን፥ ጾማችንን፥ ክርስቲያናዊ ኅብረታችንን፥ ወዘተ… ውስጣችንን ለመለወጥ ይጠቀምባቸዋል። መንፈስ ቅዱስ በተጨማሪ የምናስብበትና፥ የምንሰማበትን ወይም ልባችንን የምንመረምርበትን ጊዜ እኛን ለመቀደስ ይጠቀምበታል። 

ከጊዜ ወደ ጊዜ በኃጢአት ተፈጥሮአችን እየተሸነፍን በኃጢአት ብንወድቅም እንኳ መንፈስ ቅዱስ በትዕግሥት ይሸከመናል። በላያችን ያለው የኃጢአታዊው ተፈጥሮ ሥልጣን ቀስ በቀስ እስከሚገረሰስና አዲሱ ተፈጥሮአችን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የመመራት ብቃቱ እስከሚያድግ ድረስ በሕይወታችን ውስጥ የሚሠራው ሰፋ ባላ ጊዜ ውስጥ ነው። መንፈሳዊ ብስለት፥ እግዚአብሔርን ደስ በማሰኘት የመኖርንና ኢየሱስን የመምሰል ችሎታችንን መንፈስ ቅዱስ የሚያሳድግበት ሂደት ሲሆን ከኃጢአት መንጻትንም ያጠቃልላል። 

ጥያቄ፡- ሀ) በእነዚህ ሁለት ተፈጥሮዎች መካከል ያለውን ትግል [በሕይወትህ የምትመሰክረው እንዴት ነው? ለ) የምታስባቸው ነገሮች ብዙ ጊዜ የሚያሸንፈው ተፈጥሮ የቱ እንደሚሆን የሚወስኑት በምን ዓይነት መንገድ ነው? ሐ) በሕይወትህ የበለጠ በቅድስናህ እንድታድግ መንፈስ ቅዱስ እንዴት ነው እየሠራ ያለው? መ) የአሁኑ ሕይወትህን ባመንክበት ጊዜ ከነበረው ሕይወትህ ጋር አወዳድር። ለረጅም ጊዜ አብሮህ የኖረ መጥፎ ልማድህን እንድታሸንፍ ለመርዳት መንፈስ ቅዱስ የሠራባቸውን የሕይወትህን አቅጣጫዎች ጥቀስ። መንፈስ ቅዱስ አሁንም እየሠራባቸው ያሉ የሕይወትህ አቅጣጫዎች ምን ምንድን ናቸው? ሠ) ሕይወትህን እንደገና ለእርሱ በማስረከብ ለእርሱ ለመኖርና በቅድስና ለመመላለስ የምትችልበትን ኃይል እንዲሰጥህ በመጠየቅ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ። 

በሕይወታችን ዘመን ሁሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ እንድንቀደስና የበለጠ እንድንበላል ለማድረግ መንፈስ ቅዱስ ያለማቋረጥ በሕይወታችን ይሠራል። አንድ ቀን ወደ መንግሥተ ሰማያት ስንደርስ ይህ ሥራ ይጠናቀቃል። በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ፍጹም ሆነን እንቀርባለን። እንደ ኢየሱስ እንሆናለን። ይህ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ «መከበር» ይባላል። በዚያን ጊዜ ኃጢአታዊ ተፈጥሮአችን በሙሉ ከእኛ ይወገዳል። በአቋምም ሆነ በተግባር ጻድቅ እንሆናለን (ገላ. 5፡5)። ኃጢአትን ከማድረግ ወይም በእግዚአብሔር ላይ ከማመፅ ፍላጐት ጋር መታገላችን ያበቃል። በባሕርይ ኢየሱስን በመምሰል ፍጹም ቅዱስ እንሆናለን። ምን ዓይነት አስደናቂ ቀን ይሆን! እንዴት ያለ ሰናፍቆት የምንጠብቀው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው! 

ለ. መንፈስ ቅዱስ ለእግዚአብሔር ክብርን የሚያመጣ ነገር እንድንሠራ ይረዳናል። ይህ ማለት ‹የጽድቅ› ሕይወትን እንኖራለን ማለት ነው (ሮሜ 14፡17-18፤ 2ኛ ቆሮ. 6፡6)። ኢየሱስን እንመስላለን ማለት ኃጢአትን አናደርግም ማለት ብቻ አይደለም። እግዚአብሔርን ደስ በማሰኘት መኖርንም ያጠቃልላል። ይህ ማለት ለወዳጆቻችንና ላጠላቶቻችን ፍቅርን ማሳየትን፥ ድሆችንና ረዳት የሚያሻቸውን መርዓትንና ቃሉን መስማት ከሚገባቸው ጋር ወንጌልን ማካፈልን ይጨምራል። ይህ ማለት ለራሳችን ብቻ ከመኖር ይልቅ ሕይወታችንን ለሌሎችም ብሎ መኖር ማለት ነው። መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን በመሥራት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር በማድረግ እንድንኖር ይረዳናል። 

ጥያቄ፡- እግዚአብሔር እንድትፈጽማቸው የሚፈልገውንና መንፈስ ቅዱስም በቅድስና እንድትኖር እየረዳህ መሆኑን የሚጠቁሙ ተግባራትን ዘርዝር። 

ሐ. መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚመስል ባሕርይ እንዲኖረን ይረዳናል (ገላ. 5፡22-23፤ ሮሜ 5፡5፤ 15፡13)። መንፈሳዊነትን የምንለካው እንዴት ነው? አንድን ሰው መንፈሳዊ ነው ለማለት በሰውዬው ሕይወት ላይ በቀላሉ የምናመለክተው ነገር አለን? በልሳናት እንደ መናገርና ተአምራትን እንደ ማድረግ ያሉ አስደናቂ የሆኑ መንፈሳዊ ስጦታዎችስ መንፈሳዊ መሆናችንን ያረጋግጣሉ? የ1ኛ ቆሮንቶስ መጽሐፍን ስናጠና የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እስደናቂ የሆኑት እነዚህ መንፈሳዊ ስጦታዎች ቢኖሯቸውም እንኳ መንፈሳዊ እንዳልነበሩ እንመለከታለን። ይልቁኑ ሥጋዊ ክርስቲያኖች ነበሩ። ስለዚህ መንፈሳዊ ስጦታዎች የመንፈሳዊነት ጥሩ ምልክቶች አይደሉም። በሕዝብ መካከል ለመጸለይ ወይም ለመላክ መቻልስ? እነዚህም እውነተኛ መንፈሳዊነትን አያመለክቱም። የመንፈሳዊነት አንድ ብቸኛ ማረጋገጥ «የመንፈስ ፍሬ» ነው (ገላ. 5፡22-23)። በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር እስካልሆንን ድረስ የመንፈስ ፍሬ የሆኑትን ሁሉ በማያቋርጥ ሁኔታ በሕይወታችን ውስጥ ማሳየት የማይቻል ነው። ይህ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት እጅግ በጸጥታ የሚፈጸም ስለሆነ ብዙ ጊዜ ሥራው በሕይወታችን መቼ እንደተፈጸመ ለመገንዘብ እንኳ እንቸገራለን። 

ኢየሱስ ምን እንደሚመስል፥ ባሕርዩ ምን እንደሚመስል እራሳችንን መጠየቅ ቢያስፈልገን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እንደተላበሰ በቀላሉ መናገር እንችላለን። ፍቅርን የተላበሰ ስለ ነበር በደረሰበት ስፍራ ሁሉ በፍቅሩ ሰዎችን በመድረስ ሕይወታቸውን ይነካ ነበር። መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ፍቅሩን በልባችን እንዳፈሰሰ ተጽፏል (ሮሜ 5፡5)። 

ኢየሱስ በደስታ የተሞላ ስለነበር፥ ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ቁም ነገረኛ አይደለም ብለው ያስቡ ነበር። ኢየሱስ በወንጌላት ውስጥ እንደ ተጻፈው በተደጋጋሚ ወደ ግብዣ ስፍራዎች ይሄድ እንደነበር መመልከት የሚያስደስት ነገር ነው። ሕይወትን የሚወድድና በደስታ የተጥለቀለቀ ነበር። 

ብዙ ክርስቲያኖች ዛሬ ከውስጣዊ ደስታ ይልቅ በፊታቸው ላይ የሚነበበው ስሜት እጅግ ጥልቅ የሆነ መቆዘምና የሐዘን ምልክት ነው። ኢየሱስ የገባልን የተስፋ ቃል ግን መንፈስ ቅዱስ ከውስጥ ፈንቅሎ የሚወጣ ደስታን እንደሚሰጠን ነው (ዮሐ 7፡38-39፤ 10፡10፤ ሮሜ 5፡13)። 

ኢየሱስ ከእግዚአብሔርና ከሌሎች ጋር የኖረው በፍጹም ሰላም ነበር። በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ ዓላማዎች ሲታገል አናየውም። ይልቁኑ የወንጌልን እውነት ለመጠበቅ ወይም ለሌሎች ሰዎች ብሎ ይታገል ነበር። ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር በሰላም እንዲኖሩ ከእርሱ ዘንድ ወደሚገኝ እስ ግንኙነት ሊያደርሳቸው ያለማቋረጥ ይተጋ ነበር። በተመሳሳይ መንገድ መንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔርና ከሌሎች ጋር በሰላም እንኖር ዘንድ ይረዳናል (ሮሜ 8፡6፤ ገላ. 5፡22)። 

በልባችን ተስፋን የሚሰጣን መንፈስ ቅዱስ እንደሆነም ተነግርናል (ሮሜ 15፡13)። አሁን ያለንበት ሁኔታ የከፋ ቢሆንም እንኳ፥ ተስሩ በተለይ ኢየሱስ በሚመለስበት ጊዜ በሚገለጡት የእግዚአብሔር በረከተች ላይ ዓይኖቻችንን የምናሳርፍበት ችሎታ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ የደረሰበት ነገር በሙሉ ለብዙ ሰዎች መዳን ምክንያት እንደሚሆን ያውቅ ስለነበር በልቡ ተስሩ ነበረው (ዕብ. 12፡2-3)። ብንሰደድ፥ ልጆቻችን ሲሞቱ፥ ወይም ሌሎች ችግሮች ቢደርሱብንም እንኳ እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ እንደሚቆጣጠር ለበጐም እንደሚያደርጋቸው በመረዳት ሰሙሉ መተማመን መኖር መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን የሚሠራው ሥራ ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) በመንፈስ ፍሬ ውስጥ የሚጠቃለሉ ሌሎችንም ዘርዝር። ለ) የዘረዘርካቸው የመንፈስ ፍሬዎች በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ የነበሩ ባሕርያት መሆናቸውን አብራራ። ሐ) እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ሦስቱን ጨምሮ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያስፈልጉትና መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን የመሥራቱ እውነተኛ ምልክቶች የሚሆኑት እንዴት ነው? 

እያንዳንዱን የመንፈስ ፍሬ በጥንቃቄ ብናጠና የሚከተሉትን ነገሮች እንገነዘባለን። 

ሀ. የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በሰው ጥረት የሚገኝ እይደለም። ይልቁኑ ልዕለ ተፈጥሮአዊ ምንጭ ያለው ነው። እያንዳንዱ የመንፈስ ፍሬ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን በሚሠራው ሥራ ምክንያት የሚገኝ ነው። ጳውሎስ በገላ. 3 ላይ ሁለት ዓይነት ፍሬዎችን ያነጻጽራል። በመጀመሪያ የእሮጌው ሕይወት፥ የሥጋ ፍሬ አላ። እነዚህ ከስስታምነትና ከዓመፅ የሚመጡ ሁልጊዜም ወደ ጥፋት የሚመሩ ናቸው። ቀጥሎ መንፈስ ቅዱስ በሰው ሕይወት ውስጥ በሚሠራው ሥራ ምክንያት የሚመጡ የእዲሱ ሰው ፍሬዎች አሉ። እነዚህ በሰው ውስጥ ካለው ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ተቃራኒ ናቸው። መሠረታቸው እራስ ወዳድነት ስሌለበት እግዚአብሔርን ለማስከበርና ልክ እንደ ኢየሱስ ሌሎችን ለማቅረብ የሚተጋ ሕይወት ነው። ስለዚህ ክርስቶስን በመምሰል ለማደግ ያላን ችሎታ ወይም የመንፈስ ቅዱስን ፍሬ በሕይወታችን ለማሳየት ያላን ብቃት በራሳችን ጥረት ሳይሆን በሕይወታችን በሚሠራው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚወሰን መሆኑን ሁላችንም ማስታወስ ይገባናል። ስለዚህ እነዚህን ፍሬዎች በሕይወታችን ለማፍራት በመንፈስ ቅዱስ መደገፍን መማር አለብን። ፍሬው ይፋ ይወጣ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በኢየሱስ ውስጥ መኖርን መማር አለብን (ዮሐ 15፡4)። 

ለ. እነዚህ የመንፈስ ፍሬ በአንድነት የሚመጡ እንጂ እንዳንዶቹ የሚገላጡ ሌሎች ደግሞ የሚጐድሉ እይደሉም፡- ለዚህ ነው በነጠላ የመንፈስ ቁጥር «ፍሬ» እንጂ በብዙ ቁጥር የመንፈስ «ፍሬዎች» ተብለው ያልተጠቀሱት። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ፍቅርን ሰጥቶ ሰላምን አይከለክልም። የመንፈስ ፍሬ በጥቅል) በሙሉ በአንድነት የሚመጡ ናቸው። 

ሐ. በመንፈስ ቅዱስ ከሚሰጡ፥ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት የመጨረሻ ማረጋገጫ ተደርገው ከሚቆጠሩት፥ እንደ ልሳን ወይም ተአምራት ካሉ አስደናቂ ድርጊቶች ይልቅ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ከሌላ ከማንኛውም ነገር በተሻለ ደረጃ የመንፈስ ቅዱስ ሙላትን ይገልጣል። በእጆች ማጨብጨብ፥ ሃሌሉያ ማለት፥ ማሸብሸብና መንቀጥቀጥ ፈጽሞ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ምልክት አይሆኑም። ከላይ የተመለከትናቸውን ነገሮች ሁሉ እያደረጉ ነገር ግን የፍቅር፥ እራስን የመግዛት፥ የየዋህነት፥ ወዘተ… ሕይወት የማይኖሩ ይልቁኑ በትዕቢትና በስስታምንት የተሞሉ ስንት ሰዎችን እናውቃለን? እነዚህ ሰዎች በእርግጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተዋልን? ሁላችንም እይ በጭራሽ እንደምንል አስባለሁ። ደግሞስ ከላይ የተጠቀሱትን አስደናቂ የሚመስሉ ነገሮች የማያደርጉ ሕይወታቸው ግን በጨዋነት የተሞላ ፍቅርና ሰላም ያላቸው ስንት ሰዎች እናውቃለን? ኢየሱስ በሕይወታችን የሚፈልጋቸው ባሕርያት ያሏቸው እነዚህ ሰዎች አይደሉምን? ሁላችንም አዎን እነርሱ ናቸው እንደምንል አስባለሁ። ስለዚህ ውጫዊ ክሆኑ አስደናቂ ድርጊቶች ወይም ስማታዊ መግለጥ ከሞላባቸው ነገሮች ይልቅ በመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ውስጥ የሚታዩ ሥነ ምግባራዊ ባሕርያት ሰው በመንፈስ ቅዱስ መሞላቱን ያሳያሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዛትን በሙሉ ብንወስድ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን በሚያፈራቸው በእነዚህ የሕይወት ብቃቶች ሊጠቃለሉ ይችላሉ። እነዚህ ብቃቶች በሕይወታችንና በቤተ ክርስቲያን ያለማቋረጥ ቢታዩ እራስ ወዳድነት፥ ፀብና ክፍፍል አይኖሩም ነበር። የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በሰዎች ሕይወት ስለሚያመጣው ለውጥ ለዓለም እጅግ ብሩህ ምስክር እንሆን ነበር። 

መ. እነዚህ ብቃቶች «ፍሬ» ተብለው ይጠራሉ። ይህ የሚያሳየው እነዚህ የሥነ-ምግባር ባሕርያት በእኛ በኩል አንዳችም ድርሻ ሳይኖረን መንፈስ ቅዱስ ብቻውን የሚያፈራቸው እንዳይደሉ ነው። አንድ ፍሬ የሚያፈራ ዛፍ «ጥሩ ፍሬ ለማፍራት» አረሞች እንዲታረሙለት፥ ዙሪያው እንዲኮተኮትላት ማዳበሪያ፥ ውኃና የፀሐይ ብርሃን እንዲሰጠው እንደሚፈልግ ሁሉ፥ መንፈስ ቅዱስም ፍሬ የሚያፈራው በሕይወታችን አንዳንድ ነገሮችን ስናደርግ ነው። 

በገላ. 6፡7-8 ጳውሎስ በምንዘራበት ጊዜ ምን እንደሚሆን በመናገር ያስጠነቅቀናል። የምንዘራባቸው ሁለት መንገዶች አሉ። በሥጋ ልንዘራ እንችላለን። በሥጋ የሚዘሩት በገላ. 3፡19-21 ያሉ ባሕርያት በሰው ሕይወት እንዲከሰት የሚያደርጉ ናቸው። ሁለተኛው መንገድ በመንፈስ መዝራት ነው። እነዚህ ነገሮች በገላ. 3፡22-23 ያሉትን ባሕርያት የሚጨምሩ ወይም ወደዚያ የሚያመሩ ናቸው። ጳውሎስ የሚናገረው ሁልጊዜ የዘራነውን እንደምናጭድና በሕይወታችን የምናያቸው ነገሮች የዘራናቸው ነገሮች መሆናቸውን ነው። በእንግሊዝኛ ከቀድሞ ጊዜ ጀምሮ የሚነገር አንድ አባባል አለ። 

አሳብ ብትዘራ፣ ተግባር ታጭዳለህ፤ 

ተግባር ብትዘራ፥ ልማድ ታጭዳለህ፤ 

ልማድ ብትዘራ፥ ባሕርይ ታጭዳለህ፤ 

ባሕርይ ብትዘራ፥ ዕጣ ፈንታን ታጭዳለህ። 

የሥጋን ሳይሆን የመንፈስን ፍሬ እንድናጭድ ነገሮችን እንዴት መዝራት አለብን? 

1. የምናነበው ነገር የምናስበውን ይወስናል፤ የምናስበው ነገር ምግባራችንን ይወስናል። በእግዚአብሔር ቃል ላይ ጊዜ መውሰድ መንፈስ ቅዱስ ፍሬ እንዲያፈራ የሕይወታችንን ማግ ያዘጋጅልናል። የዓለምን ነገሮች ብቻ ካነበብን ወይም መጥፎ ነገሮች ካነበብን ውሎ ሳያድር በባሕርያችን የሚታዩት እነዚሁ ነገሮች ይሆናሉ። 

2. በቴሌቪዥን ወይም በቪዲዮ የምናያቸው ነገሮች መንፈሳዊ ወይም ዓለማዊ ፍሬ ማፍራታችንን ይወስናሉ። 

3. ጓደኞቻችን ወይም ብዙ ጊዜ አብረናቸው የምናሳልፍ ሰዎች እንዴት እንደምንኖር ይወስናሉ። እግዚአብሔርን በሚፈሩ ሰዎች ከተከበብን እነርሱን እንመስላለን። ነገር ግን እግዚአብሔርን የማይወድዱ ከሆኑ ደግሞ እነርሱን እንመስላለን። 

ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በፍጥነት ወደ ብስለት እንዲያድግ የነፍሳችንን ማሣ እንዴት በተሻለ ሁኔታ እንደምናዘጋጅ በጥንቃቄ ላማሰብ፥ ራሳችንን በሥነ ሥርዓት መምራትን መማር አለብን። 

ሠ. በመንፈስ ቅዱስ የሚፈጠሩት እነዚህ ባሕርያት «ፍሬ» በመባል ይታወቃሉ። ይህ የሚያመለክተው በብስለት በማደግ የሚደረስባቸው እንጂ ቅጽበታዊ እንዳልሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የግል ልምምጻችን የሚነግሩን፥ ልክ ፍሬ ከአነስተኛ አበባ ወደ እምቡጥነት፥ ከዚያም ከጥሬው ፍሬ ወደ በሳሉ ፍሬ እንደሚያድግ ነገር ግን ቅጽበታዊ እንዳልሆነ ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወትም የእድገት ሕይወት መሆኑን ነው። በተመሳሳይ መንገድ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በአዳዲስ ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ እንጭጭ መስለው ቢታዩም እንኳ ግለሰቦች ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለረጅም ጊዜ አብረው በተጓዙ መጠን ወደ ብስላት እያደጉ ይሄዳሉ። ፍሬው የሚያድግበት ፍጥነት በብዙ መንገዶች የሚወሰነው በማሳ አዘጋጃ ጀት ሁኔታችን ነው። መንፈሳዊ እርምጃ ችንን የሚያሳድጉ ነገሮችን ያለማቋረጥ ከዘራን ፍሬው በፍጥነት ያድጋል። ለመንፈሳችን እድገት ዕንቅፋት የሆኑ ነገሮችን ከዘራን መንፈስ ቅዱስ የበሰለ ፍሬን የማፍራት ችሎታው ይገደባል። 

ይህ ማለት ትዕግሥትን መማር አለብን ማለት ነው። እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ በሥራ ላይ ስለሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ለማደግ ወደ ፊት መግፋት አለብን። ሁልጊዜ ማስታወስ ያለብን ነገር እግዚአብሔር ራሱን ያዘጋጀው ለቅጽበታዊ እድገት ሳይሆን በሕይወት ዘመን ለሚካሄድ እድገት መሆኑን ነው። በሙላትና በፍጹምነት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የምንመስለው በመንግሥተ ሰማያት ብቻ ነው። የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ከሁሉ በመጠቀ ሁኔታቸው የሚገኙትም በዚያ ጊዜ ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) ስለ መንፈስ ፍሬ ልንመለከታቸው የምንችለውን አምስት የተላያዩ ነገሮች እስብ። ክርስቲያኖች ሁሉ የመንፈስ ፍሬን በግልጽ በሕይወታቸው ቢያሳዩ ቤተ ክርስቲያን በምን ዓይነት መንገዶች ትቀየር ነበር? ይህ ከተአምራት ይልቅ የወንጌልን ኃይል በበረታ ሁኔታ የሚገልጸው እንዴት ነው? ሐ) የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በሕይወትህ የበለጠ ይረጋገጥ ዘንድ ማሣውን በተሻለ ሁኔታ ለማዘጋጀት ልታደርጋቸው የምትችላቸውን ነገሮች ዘርዝር። 

መ. መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ በምድር በነበረ ጊዜ ያደረጋቸውን ነገሮች እንድናደርግ ኃይልን ይሰጠናል (1ኛ ቆሮ. 2፡4፤ ዮሐ 19፡12)። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ሙሉ ቁጥጥር ሥር ተመላልሷል። በውጤቱም የእግዚአብሔር ኃይል በሕይወቱ ተረጋግጧል። ልክ በኢየሱስ እንደሆነው ወንጌልን በሚሰብክበት ጊዜ የእግዚአብሔር ኃይል ይገለጥ እንደነበር ጳውሎስ ተናግሯል። በእርሱ ውስጥ በኃይል የሠራው መንፈስ ቅዱስ ነበር። እግዚአብሔር ኃይልን የተላበሰ አምላክ ነው። መንፈስ ቅዱስ ባለበት ሁሉ ይህ ኃይል ይገለጣል። ይህ ኃይል የሚገለጠው ሁልጊዜ ትላልቅና ግልጽ በሆኑ ተአምራት አይደለም። የሰው ድነት (ደኅንነት) በመንፈስ ቅዱስ የተሠራ ታላቅ ተአምር እንደሆነ አስታውስ። ይህ ማለት መንፈስ ቅዱስ በዚህ ዘመን ተአምራትን አያደርግም ማለት አይደለም። ያደርጋል። ለምሳሌ ብዙ ጊዜ የታመሙ ሰዎችን ይፈውሳል። (ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስ አጎልግሎት በወደፊት ትምህርቶቻችን በዝርዝር እንመለከታለን።) 

ጥያቄ፡- መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን እንድንመለል የሚያደርግበትን እራት መንገዶች ከልስ። ሀ) እነዚህ አራት መንገዶች በሕይወትህ ሲረጋገጡ እንዴት እንዳየህ ግለጽ። ለ) እነዚህ አራት መንገዶች በቤተ ክርስቲያንህ ሊረጋገጡ| እንዴት እንዳየህ ግለጽ።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.