ሰይጣንን ድል የማድረግ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት

መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ኃይል ለእኛ ዝግጁ እንዲሆን ያደርጋል። (የሐዋ.1፡8) 

ጥያቄ፡- የሐዋ 1፡4፥ 8 አንብብ። ሀ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ የነገራቸው ለምንድን ነው? ለ) ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስን በሚቀበሉበት ጊዜ ምን እንደሚሆን ነው ኢየሱስ ተስፋ የገባላቸው? 

ኢየሱስ ወደ መንግሥተ ሰማያት የመመላሻው ወቅት በደረሰ ጊዜ ላደቀ መዛሙርት ግልጽ ትእዛዛትን ሰጣቸው። በኢየሩሳሌም ቆዩ አላቸው። ወደ ቀድሞ ኑሮአቸው ወደ ገሊላ መመለስ አልነበረባቸውም። ስለ ኢየሱስ ሕይወት ለሌሎች የመመስከር አገልግሎታቸውንም መጀመር አልነበረባቸውም። ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን እስኪልክ ድረስ መቆየት ነበረባቸው። መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ በሚወርድበት ጊዜ የእግዚአብሔር ኃይል በእጃቸው እንደሚሆን ነበር። ለኢየሱስ ለመሥራት ዝግጁ መሆን የሚችሉት በዚያን ጊዜ ብቻ ነበር። ስለዚህ ማንኛውም ሰው ሲድን መፈጸም ከሚጀምሩት ዐበይት የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች አንዱ አዲሱ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔርን በሚያስከብር አኗኗር እንዲኖር ኃይል ማስታጠቅ ነው። 

ብዙ ጊዜ ስለ መንፈስ ቅዱስ ኃይል ስናስብ ውጫዊ የሆኑትን የሚስቡ ነገሮችን እናስባለን። አስደናቂ የሆነ ፈውስና አጋንንት ማስወጣት መንፈስ ቅዱስ በሰው ሕይወት ውስጥ በኃይል ለመሥራቱ ማረጋገጫ ነው ብለን እናስባለን። የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ግን ሰሌሎች የተለያዩ መንገዶችም ይታያል። ውጤታማ በሆነ መንገድ መስክሮ ሰዎችን በኢየሱስ በኩል ወደሚያድን እምነት ለማምጣት ኃይል ይጠይቃል። አዲስ ክርስቲያን በሕይወቱ አድጐ ኢየሱስን እስኪመስል ባሕርይው እንዲለወጥ ለመርዳት ኃይል ይጠይቃል። ለደት ውስጥ በጽናት ለመቆየትና ያለ ፍርሃት ለኢየሱስ ለመኖር ኃይል ይጠይቃል። የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በክርስቲያን የትኛውም የሕይወት አቅጣጫ ተፈላጊ ነው። 

እዚህ ስፍራ ላይ በአጭሩ ልንነጋገርበት የሚገባን፥ ለመንፈሳዊ ሕይወትና አገልግሎት የግድ አስፈላጊ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል እቅጣሚ አለ። ይህም ሰይጣንና አጋንንትን በቁጥጥር ሥር የሚያደርግ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ዓለም በሁለት ዓይነት ሰዎች እንደምትከፈል ያሳየናል። እነርሱም የጻኑና ያልዳኑ፥ የጨለማው መንግሥት አካል የሆኑና የብርሃን መንግሥት አካል የሀኑ፥ ሰይጣን አምላካቸው የሆኑና እግዚአብሔር አምላካቸው የሆኑ ናቸው (ኤፌ 2፡1-3፤ 5፡8–13፤ 2ኛ ቆሮ. 4፡3-4፤ ዮሐ 12፡31፤ 16፡11)። አዳምና ሔዋንን ከመፈተኑ በፊት በኃጢአት ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ ሰይጣን እግዚአብሔርንና ዕቅዱን ለመዋጋት የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። እግዚአብሔርን የሚዋጋበት ልዩ መንገድ የእግዚአብሔርን ሕዝቦች በማጥቃት ነው። በአዲስ ኪዳን በተደጋጋሚ ከሰይጣን ማጥቃት እንድንጠነቀቅና እንድንዋጋው ማስጠንቀቂያ የተሰጠን ለዚህ ነው (ኤፌ. 6፡11-12፤ ያዕ. 4፡7፤ 1ኛ ጴጥ. 5፡6-9)። 

ሰይጣን ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎችን መዋጋት አያስፈልገውም። ምክንያቱም እንዴ በእርሱ ኃይልና ቁጥጥር ሥር የገቡ ስለሆኑ ነው። በእነርሱ ላይ የሚሠራው እንዳያምኑ መከላከልን ብቻ ነው። ነገር ግን በእግዚአብሔር ልጆች ላይ ጥቃቱን ያነጣጥራል። በንቃት ለእግዚአብሔር ክብር የማይኖሩና የማይመሰክሩ ዓለማዊ ክርስቲያኖችንም ሰይጣን አያጠቃቸውም። አንዴ አሸንፎአቸዋልና። 

ጥያቄ፡– ሰይጣን እማኞችን በማጥቃት ሊያሸንፋቸው የሚጥርባቸውን መንገዶች ዘርዝር። 

ሰይጣን ብዙ ጊዜ የሚያጠቃው እግዚአብሔርን በመፍራት የሚኖሩ ንቁ ከርቲያኖችን ነው። ይህንን በተላያዩ መንገዶች ያደርጋል። ኃጢአታዊ ተፈጥሮአቸውን የማባበልና የመሳብ ኃይል ያላትን ዓለምን በመጠቀም ያጠቃቸዋል። ዓላማውም ኃጢአትን አድርገው የክርስቶስን ስም እንዲያሰድቡ ነው። ስሜታቸውንና ሥነ ልቡናቸውን በማጥቃት ተላሩ እንዲቆርጡና ለኢየሱስ የድል ሕይወት እንዳይኖሩ ያደርጋቸዋል። አገልግሎታቸውን በማጥቃት ፍሬያማ እንዳይሆኑ ለማድረግ ይጥራል። ለእግዚአብሔር ክብር እንዳይኖሩ በጨለማው መንግሥት ላሉ ሌሎች ሰዎች ምስክር እንዳይሆኑ ለማድረግ ቤተሰባቸውን፥ ጓደኞቻቸውን፥ ጤንነታቸውንና ሌሎች ነገሮቻቸውንም ሁሉ ይዋጋል። በአንዳንድ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ በተለይ ክርስቲያኑ ወይም የቤተሰቡ አባላት ከዚህ ቀደም በአንዳንድ የጥንቆላና የመተት አሠራር የተያያዙ ከነበሩ ወይም ወንጌል ከዚህ ቀደም ፈጽሞ ተሰብኮ በማይታወቅበት ቦታ የደረሰ ከሆነ ሰይጣን ክርስቲያኖችን በታላቅ ኃይል ይጫጫናቸዋል።  

ክርስቲያኖች ስለ ሰይጣን ኃይልና በሰይጣን ሥራ ላይ ጽኑ የሆነ ተቃውሞን ስለማድረግ ሁለት እጅግ የተራራቁ አስተሳሰቦች አሏቸው። አንድ ሰው እንዲህ ብሏል። ሰይጣን የሐሰት ትምህርቶቹን ሁልጊዜ የሚያመጣው ሰዎች ከሁላት በአንዱ እንዲወድቁ ለማድረግ በሁላት አቅጣም ጥንድ ጥንድ እያደረገ ነው። ሰው ቢስት በሁለቱም አቅጣጫ መትረፍ በማይችልበት ነጠላ ግንድ ወንዝን እንደ መሻገር ያህል፥ ሰይጣን በአንድ ወይም በሌላ የሐሰት ትምህርት የክርስቲያኑን ውድቀት ይጠብቃል። ሰይጣን ይህን ሁኔታ አምርሮ እንዲቃወም ክርስቲያኑን በማነሣሣት ወደ ተቃራኒው ጽንፍ ተስፈንጥሮ በስሕተት ላይ እንዲወድቅ ያደርገዋል። ይህ ክርስቲያኖች ሰይጣንንና ሥራዎቹን በሚረዱባቸው የተለያዩ ሁኔታዎች ላይ ተከስቷል። በርካታ ክርስቲያኖች በተላይ በምዕራባውያን አገሮች የሚገኙ ስለ ዲያብሎስ እንቅስቃሴዎች እጅግ ተጠራጣሪ የሆኑና ሰይጣን ክርስቲያኖችን የሚዋጋባቸውን የተለያዩ በርካታ መንገዶች የማያውቁ አሉ። እነዚህ ሰዎች፥ በምድር ላይ የሚደረግ ማንኛውም ነገር በስተጀርባ ሆነው የሚያንቀሳቅሱት ሰይጣንና አጋንንት (በኃጢአት ምክንያት የተጣሉ መላእክት ናቸው ብለው የሚያስቡ አንዳንድ አክራሪዎችን ያያሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች፥ በሽታዎች ሁሉ መልካም ያልሆኑ አጋጣሚዎች ሁሉ፥ አደጋዎች ሁሉ፥ ሐዘን ሁሉ፥ ወዘተ… ቀጥኛ የሆነ የሰይጣን ውጊያ ነው ሲሉና ሰይጣንን በመገሰጽ ሊያስወግዱት ሲጥሩ ያያሉ። ስለዚህ፥ ወደ ተቃራኒው ጽንፍ ከመስፈንጠርና ማንኛውንም የሰይጣን ልዕለ-ተፈጥሮአዊ እንቅስቃሴ እቅልሎ በማየት በሕይወታቸው ሊመጣ የሚችለውን የሰይጣን ውጊያ ትኩረት ይነፍጉታል። በዚህ ምክንያት በሰይጣን ውጊያ ብዙ ጊዜ ይሸነፋሉ። ሰይጣን በዓለም ላይ ስላላው ኃይልና እንቅስቃሴ እናሳ ግምት ይሰጣሉ። የሰይጣንን ጥቃቶች አውቀው እራሳቸውን ስለማያዘጋጁ በቀላሉ ይሸነፋሉ። እነርሱና ቤተ ክርስቲያኖቻቸው ኃይል የሌላቸውና ውጤት አልባ ናቸው። 

በሌላኛው ጽንፍ ያሉት ሰይጣን ከሁሉ ነገር በስተጀርባ አለ በማለት ከሁሉ ነገር ውስጥ ሰይጣንን ለማስወጣት የሚሞክሩት ናቸው። ከበረዳቸው ሰይጣንን ያስወጣሉ። በቤተ ክርስቲያን ፕሮግራም ከመጀመራቸው በፊት ሰይጣንን ከሕንፃው ያስወጣሉ። በትምህርት ቤት ከፈተና ከወደቁ ሰይጣንን ያስወጣሉ። ሰይጣንን እጅግ ስለሚፈሩ ለሰይጣን የማይገባውን ስፍራ ይሰጡታል። እውነቱ በእነዚህ ነገሮች መካከል ላይ ስለሆነ ከእነዚህ ከሁለት አጽናፍ ስሕተቶች በአንዱ ላይ እንዳንወድቅ እጅግ መጠንቀቅ አለብን።ይህ የክርስትና ሕይወት ወደ የትኛውም ጽንፍ ክመስፈንጠር ተጠብቆ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ሚዛን አደላድሎ መኖር መሆኑን እንደገና ያስታውሰናል። 

ጥያቄ፡- ህ) እነዚህን ሁለት ጽንፎች በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያየኸው እንዴት ነው? ለ) ሚዛናዊ የሆነው አመለካከት የትኛው ነው ትላለህ? 

እንደ ክርስቲያኖች ሰይጣን መንፈሳዊ ሕይወታችንን፥ ስለ ኢየሱስ የምንሰጠውን ምስክርነትና በአኗኗራችን የምንሰጠውን ምስክርነት ለመደምሰስ ባለው ዕቅድ ላይ መንቃት አለብን። ሰይጣን እጅግ ኃይለኛ የሆነ ጠላታችን መሆኑን ብንገነዘብም እርሱን በመፍራት ግን መኖር የለብንም። ሁልጊዜ በእርሱ ላይ በድል ለመኖር እንችላለን። መኖር አለብን። ሰሚደርስብን ነገር ሁሉ ውስጥ የሰይጣን እጅ እንዳለ ማሰብ ግን ክሚገባው በላይ ለእርሱ ክብርንና ተፈሪነትን መስጠት ይሆናል። 

ሰይጣን በሕይወታችን ወይም በአገልግሎታችን አንዳንድ አቅጣጫዎች በብርቱ ሊያጠቃን እንደሚተጋ ካወቅን እንዴት እንቋቋመዋለን? ልናስታውሳቸው የሚገቡ ሦስት መሠረታዊ እውነቶች አሉ። 

ሀ. ሰይጣን ኃይለኛና ያልተሸነፈ ጠላት አይደለም። ይልቁኑ የተሸነፈ፥ በክርስቲያኖች ላይ ያለው ኃይል የተወሰደበት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊመለስ በእግዚአብሔር የሚሰጠውን ፍርድ ሊቀበል የሚጠባበቅ ነው። በቆላ. 2፡5 ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሰይጣንና አጋንንትን በስፍራው «ኃይላትንና ሥልጣናትን» ተብለው የተጠቀሱትን ስለማሸነፍ ተጠቅሷል። (ዕብ 2፡14-15 ደግሞ ተመልከት።) ሰይጣን ክርስቲያኖችን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኞችና የኃጢአት ደመወዝ ደግሞ ሞት ስለሆነ (ሮሜ 6፡23) ዘላለማዊ ቅጣት የሚገባቸው እንደሆነ አድርጐ የሚከስበትን ሥልጣን በመስቀል ላይ ተቀምቷል። ኃጢአታችንን ሁሉ በራሱ ላይ በማድረግና ስፍራችንን ወስዶ በመሞት ኢየሱስ ዕዳችንን ከፍሎ ጥፋተኛና ሞት የሚገባን ካደረገን ማንኛውም የሰይጣን ክስ ነፃ አድርጐናል። ኢየሱስን እንደ ግል አዳኛችን ስንቀበልና በእምነት ሞቱ በእኛ ምትክ እንደሆነ ስናውጅ በእግዚአብሔር ፊት ፈጽሞ ዳግመኛ በጥፋተኛነት ለፍርድ እንቀርብም። ምክንያቱም ኃጢአታችን በሙሉ በክርስቶስ ደም ተሸፍኗል። ኃጢአትን በምናደርግበት ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ያለን ግንኙነት ይበላሻል። ነገር ግን ከዘላለም ፍርድ በታች ወደሚጥለን የጥፋተኝነት ስፍራ እንደገና አንመለስም። ክርስቲያኖች ጥፋተኞች እንደሆኑ እንዲያስቡ በማድረግ ሊያታልላቸው መሞከሩን አይተውም። ነገር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም (ሮሜ 8፡1)። 

ሰይጣን የሥልጣንና የኃይሉን ስፍራ እንዳጣ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሊታገልና ሊዋጋ በቅርቡ ወደ ምድር ይጣላል (ራእ. 12፡12)። ይሁን እንጂ እንደሚጠፉ የተረጋገጠ ነው። እርሱና ተከታዮቹ፥ ማለትም አጋንንትና የማያምኑ ሰዎች ሁሉ ወደ እሳት ባሕር ይጣላሉ (ራእ 20፡10፥ 14-5)። ሰይጣን ሙሉ ለሙሉ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር ነው። የመጨረሻ ፍርድ የተወሰነበት ስለሆነ ስለ ፍርቶ ሊያደርግ የሚችለው ነገር የለም። ወደ እሳት ባሕር እስኪጣል ድረስ ግን በምድር ላይና በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ የቻለውን ያህል ጥፋት ለማምጣት ይታገላል። 

አንድ ሰው ሰይጣንና እጋንንቱ በአንዱ ወገን፥ እግዚአብሔርና ተከታዮቹ (ክርስቲያኖች) ደግሞ በሌላ ወገን ሆነው የሚያደርጉትን ጦርነት በሚከተለው መንገድ እወዳድሮታል። ረጅም ጊዜ በሚዘልቅ ጦርነት ውስጥ የተለያዩ ዐውደ ውጊያዎች አሉ። በጦርነቱ ፍጻሜ አካባቢ የጠላትን መሸነፍ የሚያስረገጥ ውጊያ ይኖራል። ከዚያ በኋላ ጠላት ሊያሸንፍ የሚችልበት ምንም መንገድ የለም። ሆኖም ግን ሙሉ በሙሉ እስከሚደመሰስበት ጊዜ ድረስ ጠላት እየተክመ መዋጋቱን አይተውም። እንደዚሁ ሰይጣን በኢየሱስ መስቀል ላይ በተደረገ ትልቅ ውጊያ ተሸንፏል። ኢየሱስ ዳግም መጥቶ በፍጹም ሥልጣን እስከሚገባ ድረስ አሁን ማድረግ የሚችለው ትንንሽ ውጊያዎችን በመቀስቀስ ጥቂቶችን ማሽንፍና በአብዛኛው ሽንፈትን መከናነብ ነው። 

ኢየሱስ በእኛ ምትክ ለሞተው ሞት ምልክት የሆነው የኢየሱስ መስቀል ሰይጣን ጥቃትን በሚከፍትብን ጊዜ በእርሱ ላይ በሥልጣን ለመውጣት የምንጠቀምበት መሠረት ነው። ሰይጣን የተሸነፈ ጠላት ነው። በእኛ ላይ በተቃውሞ በሚመጣበት ጊዜ እንደ ተሸነፈና በእኛ ላይ አንዳችም ሥልጣን እንደሌላው ልንነግረው ይገባል። 

መስቀሉ በሌላ በኩል በሰይጣን ላይ ባለ ድል የመሆናችን ማረጋገጥ ምልክት ነው። መስቀሉ ክርስቲያኖች ሁሉ የሞቱበት ቦታ ነው። በመስቀል ላይ ክርስቲያን ላእኔነቱና ለራስ ወዳድነቱ ሞቷል (ሮሜ 6፡1-22፤ ገላ. 2፡20፤ ራእይ 12፡11)። በመስቀል ላይ የሰይጣንን ሥልጣን በመጠቀም ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋጋው ሰብዓዊ ተፈጥሮአችን ተደምስሷል። ይህ ልናስታውሰው የሚገባ እውነት ነው። ሰይጣን በቀጥታ ሊያሸንፈን እይችልም። በፈተና ውስጥ እንድንወድቅና ኃጢአትን እንድናደርግ ሲፈለግ የኃጢአት ተፈጥሮአችንንና ዓለምን ብቻ በመሣሪያነት ይጠቀማል። ኃጢአት እንድንሠራ ሊያደርገን አይችልም። ይህን ማወቅ ጠቃሚ ነው። የራስ ወዳድነት ፍላጐታችን በመስቀሉ ላይ መቸንከሩን ማወቅ አለብን። ይህን እውነት በእምነት መያዝ አለብን። በየዕለቱ ለኃጢአታዊ ተፈጥሮእችን እንደ ሞትን በመቁጠር ኢየሱስን በእምነት ሙሉ ለሙሉ ለመከተል እራሳችንን መስጠት አለብን። በእምነትና በመታዘዝ ሳንኖር ስንቀር ሰይጣን እንዲያሸንፈን መንገድ እንከፍትለታለን። የሚያሽንፈን ከእኛ በላይ ኃይለኛ ስለሆነ ሳይሆን፥ ነገር ግን በውሸት ተታልላን እንዲቆጣጠረን በር ስለምንካፍትላት ነው። 

ለ. የእግዚአብሔር አብና የእግዚአብሔር ወልድ ሥልጣን በሰይጣንና በአጋንንት ሁሉ ላይ እንዳለን ማወቅ አለብን። ከመጽሐፍ ቅዱስ አስደናቂ እውነቶች አንዱ በአንድ ወቅት የእግዚአብሔር ጠላቶች የነበርን እኛ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችን ነው። የቤተሰቡ አካል አድርጐናል። እንደ እግዚአብሔር ቤተሰብ አባልነታችን አንድ የእግዚአብሔር ልጅ ያሉትን መብቶችና ሥልጣን ሁሉ እንወርሳላን (ገላ. 4፡5)። ይህ ሥልጣን በርካታ መንፈሳዊ ብልጽግናዎችን ይጨምራል (ኤፌ. 1፡18)። በእግዚአብሔር ጠላቶች ላይ የሚኖረን ሥልጣንም ይጨምራል። ሰይጣንን መታዘዝ ዕጣችን የሆነብን መብትና ዕድል የሌላን ደካማ ኃጢአተኞች አድርገን ራሳችንን ከመቁጠር ይልቅ፥ የነገሥታት ንጉሥ ልጆች መሆናችንን ማወጅ መማርና ይህን ማድረግም በሰይጣን ላይ የሚያጐናጽፈንን ሥልጣን መገንዘብ ያስፈልገናል። 

በሰይጣን ላይ ሥልጣን ያለን የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን ብቻ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን ስለተሰጠንም ጭምር ነው። ኢየሱስ ሥልጣን ሁሉ እንዳለው ተናግሮአል። በዚህ ሥልጣን መሠረት ወደ ዓለም ሁሉ እንዲሄዱና (የሰይጣን ክልል ወደሆነው) አሕዛብን ደቀ መዛሙርት በማድረግ ዓለምን እንዲያሸንፉ ደቀ መዛሙርትን አዘዛቸው (ማቴ. 28፡19-20)። ሰይጣን ድል ለመንሣት ኢየሱስ የነበረውና ወደ ደቀ መዛሙርት ያስተላለፈው ሥልጣን (ሉቃ. 10፡17-20 ተመልከት) ለእኛም ተሰጥቶናል። አሁን እኛ የእርሱ አምባሳደሮች ነን፤ ስለዚህ ጠላታችንን ለማሸነፍ የኢየሱስ ኃይልና ሥልጣን አለን (2ኛ ቆሮ. 5፡20)። 

ይህ ሥልጣን በምንወክለው በኢየሱስ እንጂ በእኛ እጅ አለመሆኑን መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው። ኃይል እንዳላንና ከሰይጣን እንደምንበልጥ ካሰብን ሰይጣን ሁልጊዜ ያሸንፈናል። ሥልጣኑና ከእርሱም የሚፈልቀው ኃይል የሚመጣው ከምንወክለው የተነሣ ነው። እኛ የኢየሱስ እምባሳደሮች ነን። እኛ የእግዚአብሔር አብ ልጆች ነን። ይህ ብቻ ነው ሰይጣንን ለማዘዝና ከእኛ እንዲሸሽ ላመቃወም ሥልጣንና መብትን የሚሰጠን (ያዕ. 4፡7)። 

በመንገዱ መካከል ላይ የቆመው የትራፊክ ፖሊስ መኪኖችን ለማቆም ወይም ለመምራት ያለው ኃይል በጣም አነስተኛ ነው። ከባድ ወይም ቀላል መኪና ገጭቶ ሊገድለው ይችላል። ነገር ግን ትላልቅ መኪኖችን ለማቆም ወይም በተለየ አቅጣጫ ለማስኬድ ችሎታ የሰጠው ምንድን ነው? የሚወክለው የመንግሥት ሥልጣን ነው። መንግሥትን ስለሚወክልና ሙሉ የመንግሥት ሥልጣን ከበስተጀርባው ስላለው በቀል ኃይሉ ሊያደርጋቸው ክሚችላቸው ነገሮች የሚበልጡ ድርጊቶችን ይፈጽማል። ልክ እንደዚሁ፣ ምንም እንኳ ከእኛ ይልቅ እጅግ ኃይለኛ ቢሆኑም፥ እንደ እግዚአብሔር ልጆች ስለምንኖርና ስለምናገለግል፥ ሰይጣንንና አጋንንቱን በኢየሱስ ሙሉ ሥልጣን ማዘዝ እንችላለን። (ማስታወሻ፡- ይህን የኢየሱስን ሥልጣን በውክልና እንደያዘ ሰው አጋንንትን «በኢየሱስ ስም» እናዛላን። የኢየሱስን ስም የምንጠቀመው ምንም ዓይነት እስማታዊ ኃይል ስላለው ሳይሆን ነገር ግን ትእዛዛችን በኢየሱስ በተሰጠን ሥልጣን ላይ የተመሠረተ መሆኑን በመገንዘባችን ነው። ይህ እውነት ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ሰይጣንን ስሚያወጡበት ጊዜ «በኢየሱስ ስም) በማለት አጥብቀው መጥራታቸው ታላቅ ኃይል ይሰጥ ይመስል ከሚያደርጉት ልምምድ በጣም ተቃራኒ ነው። ኃይሉና ሥልጣኑ የሚመጣው ከኢየሱስ ማንነትና በእርሱ ላይ ባለን እምነት ከምንቀዳጀው ሥልጣን ነው። የኢየሱስን ስም አጥብቀን ወይም አርዝመን መጥራት አያስፈልግም። የኢየሱስን ስም ደግመን ደጋግመን መጥራትም እያስፈልገንም። ስሙን ስንጠራ ሰይጣን ወይም እግዚአብሔር የማይሰሙ ደናቁርት ይመስል መደጋገም የለብንም። የሚያስፈልገው ነገር፥ ሰይጣንንና እጋንንትን የምናዝዘው በራሳችን ኃይል ሳይሆን፥ ነገር ግን ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሰይጣንን በማሽነፍ በእርሱ ላይ ሥልጣን ስለተሰጠን እንደሆነ በጸጥታ ለራሱ መንገር ነው። ይህን ስናደርግ ለቅቆ ይሄዳል።) 

251 

ጥያቄ፡- ብዙ ክርስቲያኖች ከአንድ ሰው በመካከላቸው ሰይጣንን ለማስወጣት ሲጸልዩ የኢየሱስን ስም አጥብቀውና አስረዝመው የሚጠሩት ወይም ደጋግመው የሚጠሩት ለምንድን ነው? ለ) ምክንያቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊና አስፈላጊ ይመስልሃልን? ለምን? 

ሐ. መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ይኖራል። የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ሥራና የእግዚአብሔር ልጆች የመሆናችን እውነታ በሰይጣን ላይ ላለን ሥልጣን መሠረትና መነሻ ናቸው። ነገር ግን ሥልጣኑንና ኃይሉን በሕይወታችን ስኬታማ የማድረግ ሥራ የመንፈስ ቅዱስ ነው። ሰማይንና ምድርን የፈጠረው ዘላለማዊው እግዚአብሔር በውስጣችን ይኖራል። ልንጠቀምበት የምንችለውን ኃይሉን ይዞ በውስጣችን ይገኛል። ሰይጣን ሊያደርግ የሚችለው እግዚአብሔር የፈቀደለትን ነገር ብቻ ነው። በውስጣችን ለሚኖረው መንፈስ ቅዱስ መታዘዝ ግዴታው ነው። መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ ሰላይ ታላቅ ኃይል ስላለው ላለመታዘዝ ምርጫ የለውም። ሆኖም ግን መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን በኃይል እንዲሠራ አንዳንድ ነገሮችን ማስታወስ አለብን። 

በመጀመሪያ፥ ለእርሱ ባለመታዘዝ የምንኖር ከሆነ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችንም ሆነ በእኛ በኩል ኃይሉን አይገልጥም። ለእርሱ የተሰጠ ሕይወት ሊኖረን ያስፈልጋል። ኃጢአታችንን በሙሉ ልንናዘዝና እርምጃ ልንወስድበት ያስፈልጋል። 

በሁለተኛ ደረጃ ፥ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በሕይወታችን ይሠራ ዘንድ እምነት ያስፈልገናል። ከሰይጣን ጥቃቶች ጋር ፊት ለፊት በምንጋፈጥበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ስለ እኛ እንደሚሟገት ካላመንና ከፈራን ኃይሉን በመስጠት በውስጣችን ሊሠራ አይችልም። 

በሦስተኛ ደረጃ ፥ በእምነት ልንወጣና በሰይጣን ላይ ውጊያ ልንከፍት ይገባናል። ዝም ብላን ያላንቁ ውጊያ የምንጸልይ ከሆነ እግዚአብሔር ፈጽሞ ሰይጣንን አስገድዶ አያስለቅቅልንም። ነገር ግን በእምነት በጠላት ላይ ስንነግ ሁኔታው ምንም ያህል አስቸጋሪና የማይቻል ቢሆንም እንኳ እግዚአብሔር ይዋጋልናል። እግዚአብሔር ድል እስከሚያደርግላቸው ድረስ እንደነ ጌዴዎን ያሉ ሰዎች እግዚአብሔርን በመታዘዝ አስፈሪውን የጠላት ሠራዊት መጋፈጣቸው በብሉይ ኪዳን ብዙ ጊዜ የሚሠራ ደንብ ሆኖ እናገኘዋለን። ስለዚህ ደግሞ ሰይጣን እኛን፥ የምናውቀውን ሰው፥ ወይም ቤተ ክርስቲያንን በአንድ ሁኔታ እየተዋጋ መሆኑን ካወቅን መጸለይ ይገባናል። ነገር ግን መጸለይ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር የሰጠንን ሥልጣን በመጠቀም ሰይጣን ይህን አጥፊ ሥራውን እንዲያቆም ልናዝዘው እንችላለን። 

ከሚያጋጥሙን ማናቸውም ችግሮችም ሆነ በሽታዎች በስተጀርባ ሰይጣንና አጋንንት እንዳሉ በመገመት ሚዛን እንዳናጣ ሰይጣን እኛን የሚያጠቃባቸውን አካባቢዎች ለይቶ ይጠቁመን ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ መታመን አለብን። በአንድ በተለየ መንገድ አጋንንት ወይም ሰይጣን እያጠቃን እንደሆነ መንፈስ ቅዱስ እንደተናገረን እርግጠኛ እስካልሆንን ድረስ ሰይጣን እየጨቆነን እንዳለና የችግሩ ምክንያት እርሱ እንደሆነ መደምደም የለብንም። መንፈስ ቅዱስ ሰይጣን እኛን እያጠቃ ያለበትን ቦታ ካመለከተን ልባችንን በመመርመር ንጹሕ መሆናችንንና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መልካም ግንኙነት እንላለን ማረጋገጥ አለብን። በጥሞና ከጸላይን በኋላ ማላትም እግዚአብሔር እንዲጠብቀን፥ እንዲመራንና ኃይል እንዲሰጠን ከጸለይን በኋላ የእግዚአብሔር ህልውናና ኃይል ከእኛ ጋር እንደሚሆን የተሰጠንን ተስፋ በመጠቀም ሰይጣን ይወገድ ዘንድ ማዘዝ እንችላለን። 

ጥቃቶቹን በንቃት እንቋቋም ዘንድ ሰይጣን እያጠቃን መሆኑን እንዴት ማወቅ እንችላለን? የችግሩ ምንጭ ሰይጣን እንደሆነ ከተረዳን በኋላ ምን ማድረግ አለብን? በእያንዳንዱ ሁኔታ ውስጥ መንገዱን ሊያሳየን የሚገባው መንፈስ ቅዱስ ቢሆንም ሊረዱን የሚችሉ አንዳንድ አሳቦች ቀጥሎ ተሰጥተዋል። 

1. ሰይጣን ወይም አጋንንት በአብዛኛው የሚገኙባቸው ቦታዎች 

ሀ. ሰውዬው ቀደም ሲል በጣዖት ወይም በመናፍስት አምልኮ የታወቀ ከሆነ ወይም ማናቸውንም ዓይነት አስማታዊ ተግባር ይጠቀም ከነበረ ወይም ቤተሰቡ እንደዚህ ባለ ልምምድ ውስጥ ከነበረ እንደነዚህ ያሉትን ተግባራት ይቆጣጠሩ የነበሩ አጋንንት በሰውዬውና በሁኔታው ላይ አሁንም ቁጥጥር ለማድረግ ይፈልጋሉ። አጋንንትን በኢየሱስ ስም ልንቃወማቸው ይገባል። 

ለ. የምትኖርበት ቦታ ከዚህ ቀደም የጥንቆላ ሥራ ይሠራበት ከነበር ወይም የጣዖት አምልኮና የጥንቆላ ሥራ የሚሠራባቸው ቁሳቁሶች የነበሩበት ከሆነ አጋንንት ከስፍራው ጋር የቅርብ ቁርኝት ሊኖራቸው ስለሚችል መባረር አለባቸው። 

ሐ. ወንጌልን ጨርሰው ሰምተው ወደማያውቁ ሰዎች የወንጌልን መልእክት የምትወስድ ወንጌላዊ ከሆንክ ሰይጣን ወደ ክልሉ መግባት እንዳትችል ከፍተኛ ጦርነት እንደሚከፍትብህ ማሰብና መጠባበቅ ትችላለህ። ያ መንግሥቱ ስለሆነ ያለ ውጊያ አይለቅልህም። በአንተና በቤተሰብህ ላይ የሚከፈተውን ውጊያ በተጠንቀቅ ተጠባበቅ፤ በሚመጣበትም ጊዜ ተቋቋመው። 

መ. እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ወይም በአንተ በኩል በአስደናቂ መንገዶች የሚሠራ ከሆነ ይህን ሥራ ለማሰናከል ሰይጣን ማንኛውንም መንገድ ይሞክራል። ጥቃቶቹን ለመከላከል የተዘጋጀህ ሁን። 

ሠ. አንድ ግለሰብ በእንግዳ በሽታዎች የሚሠቃይ ከሆነ፥ ምንነቱ በምርመራ በማይታወቅ በሽታ በተደጋጋሚ ከተጠቃ፥ ሊገለጥ የማይቻል ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከገባ፥ ከፍተኛ የባሕርይ ለውጥ በማምጣት ያላ አንዳች ምክንያት ሰዎችን ለመጉዳት ከተነሣሣ፥ በተደጋጋሚ በኃጢአት ወይም እንግዳ አስተሳሰቦች አእምሮው እየተጠቃ ከተሸነፈ፤ ሰውዬው በኦንድ ዓይነት አጋንንታዊ ጥቃት ውስጥ ለመሆኑ እነዚህ ሁኔታዎች አመልካቾች ሊሆኑ ይችላሉ። 

2. ሰይጣንንና አጋንንቱን ለመዋጋት የሚወሰዱ እርምጃዎች 

ሰይጣን ከእኛ እጅግ የበረታ ጠላት ነው። በራሳችን ብርታት ሰይጣንን ለመዋጋት መሞከር የለብንም። ደግሞም እንችልም። እንደዚህ ዓይነቱ ማንኛውም ሙከራ በሰባቱ የአስቄዋ ልጆች ላይ ለመጣው ዓይነት ችግር እራስን መጋበዝ ይሆናል (የሐዋ. 19፡13-16)። የዘላለማዊ አምላክ ሥልጣን ከእኛ ጋር ስለሆነ፥ አንዳንድ ቅድመ-ጥንቃቄዎችን እስክወሰድን ድረስ ሰይጣንን ወይም አጋንንትን የምንፈራበት አንዳችም ምክንያት የለንም። የአጋንንት እጅ እንዳለበት መንፈስ ቅዱስ ያመላከተንን ሁኔታ የምናስተናግድባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። ቀጥሎ ቀን ልብ ልንላቸው የሚገቡ አንዳንድ ቁልፍ ነጥቦች ቀርበዋል። 

ሀ. ከኃጢአት መሆናችንን፥ እግዚአብሔር የሰጠንን አጣቃላይም ሆነ የተናጠል ትእዛዛት ለመጠበቃችንና ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር በኅብረት ለመመላለሳችን እርግጠኞች መሆን አለብን። ይህ ማለት ወደ ጦርነቱ ከመግባታችን በፊት ሕይወታችንን በጥንቃቄ መመርመር አለብን ማለት ነው። ያልተናዘዝነው ኃጢአትና ያለመታዘዝ ካለ መከራችን ከንቱ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በእኛ በኩል የሚሠራ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ስለሌለን እራሳችንን ለሰይጣን ጥቃት እናጋልጣለን። 

ለ. ኃይሉና ሥልጣኑ በውስጣችን እንደማይኖር ማስታወስ አለብን። ሰይጣንን እንደምናሸንፍ ካሰብንና በችሎታችን ከተመካን ወይም በግድ የለሽነት ወደ ውጊያው ዐውድ ከገባን የሚኖረን ሰብዓዊ ኃይል ብቻ ስለሚሆን ከሰይጣን ወይም ከአጋንንት በጣም ደካሞች ሆነን እንገኛለን። ሥልጣኑና ኃይሉ የሚመጣው የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን ኢየሱስ ሰይጣንንና እጋንንትን ስላሸነፈ፤ ኢየሱስ ሥልጣንን ስለ ሰጠንና መንፈስ ቅዱስ በልባችን ስለሚኖር እንደሆነ በየጊዜው ራሳችንን ማስታወስ አለብን። 

ሐ. ጠላትን በምንዋጋበት ጊዜ ለጸሎት ጊዜ ሰጥተን መጸለይና ደግሞም ሌሎች እንዲጸልዩልን ማድረግ አለብን። ጸሎት ሰይጣንን ለመዋጋት ከእግዚአብሔር ዘንድ ኃይልን የማግኛ ዋና መሣሪያ ብቻ ሳይሆን በውጊያው ውስጥ የምንደገፈው በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በራሳችን አለመሆኑን ማሳያ ጭምር ነው። 

መ. እንዲታደገን ለምንጸልየው ጸሎት እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ጸሎታችንን በቀጥታ የሚመልስ ቢሆንም ጠላትን በመቃወም የትእዛዝ ቃል እንድንናገር እግዚአብሔር ከእኛ ይፈልጋል። ሥልጣናችንን ለጠላት ከምንገልጽባቸው አንዱ የሚከተለው ሊሆን ይችላል፡ «በኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ስለተሸነፍክ፥ እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆንኩና ኢየሱስ 

ክርስቶስ ሙሉ ሥልጣን ስለሰጠኝ ትለቅ ዘንድ አዝሃለሁ»። 

ሠ. አዳዲስ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ማመናቸውን በሕዝብ ፊት በሚመሰክሩበት ወቅት፥ እነርሱ ቤተሰቦቻቸው ያደርጉአቸው በነበሩት ነገሮች ሳቢያ ሰይጣንና እጋንንቱ በእነርሱ ላይ የሚያደርጉትን ተጽእኖ በቃል እንዲቃወሙ መጠየቅ መልካም ነው። በታወቀ የመተት አሠራር ውስጥ ተሳትፈው ከሆነ በግልጽ መናዘዝ አለባቸው። የባዕድ አምልኮ መሣሪያ የሆኑ ማናቸውንም ቁሳቁሶች ማጥፋት አለባቸው። 

ጥያቄ፡- ሀ) አጋንንት የእግዚአብሔርን ሥራ ለማደናቀፍ እንደተንቀሳቀሱ የምታውቃቸው ሁኔታዎች ካሉ ዘርዝር። ለ) እነዚህ ሁኔታዎች በቤተ ክርስቲያን መሪዎች የተያዙት እንዴት ነበር? ሐ) ከላይ በተጠቀሱት መመሪያዎች መሠረት እንዴት መያዝ ነበረባቸው ብለህ ታስባለህ?

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.