በክርስቲያኖች መካከል ከፍተኛ ልዩነት የሚፈጥሩ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ክፍሎች (ክፍል 2)

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሽግግርን ዘገባ የያዘ መጽሐፍ መሆኑን ተመልክተናል። እግዚአብሔር በአንዱ ክፍለ ሕዝብ ማለትም ከአይሁድ ሕዝብ ጋር ከመሥራት ከዓለም ሁሉ ጋር ወደ መሥራት እንዴት እንደተሻገረ ይነግረናል። የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን ለሚፈልጉ ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመናቸውና የመንፈስ ቅዱስ ህልውናን ማግኘታቸው ሁለት ዋና አጣማሪ ኃይል ስለመሆናቸው ይነግረናል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ምዕራፍ 2 መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በነበሩት ላይ በመውረዱ አዲስ የእግዚአብሔር ሕዝብ፥ ይኸውም ቤተ ክርስቲያን አድርጐ መሠረታቸው። በሐዋርያት 8 ላይ የቤተ ክርስቲያን ስር እንዴት ለሳምራውያን እንደ ተከፈተና በአዲሱ የእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ በእኩል አቋም አንድ ክፍለ ሕዝብ እንደተጨመረ እናያለን። በእርግጥ እኩል መሆናቸውን ለሁሉም ለማረጋገጥ እግዚእብሔር ለመጀመሪያው የሳምራውያን ክርስቲያኖች የመንፈስ ቅዱስ ህልውናን በልዩና አስደናቂ መንገድ አጐናጸፈ። ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሌላ ክፍላ ሕዝብ እንዴት እንደተስፋፋች እንመለከታለን። 

1. መንፈስ ቅዱስ በአሕዛብ ላይ ወረደ (የሐዋ. 10) 

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ወንጌል ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በይሁዳ፥ በሰማርያ፥ ከዚያም ለአሕዛብ እስከ ምድር ዳርቻ ሁሉ እንደሚሰበክ ነግሮአቸው ነበር። ደቀ መዛሙርት በመጀመሪያ ያጋጠማቸው ከዘር ጋር የተዛመደ በመዝለል ወንጌልን ለታሪካዊ ጠላቶቻቸው ለሰማርያ ሰዎች ማዳረስ ነበር። ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ደግሞም ለእይሁድ እንዳደረገው መንፈስ ቅዱስን ለሰማርያ ሰዎችም በመስጠት፥ የሰማርያ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ እኩል ደረጃ እንዳላቸው እግዚአብሔር ለአይሁድ ክርስቲያኖች እስተማራቸው። ሆኖም ግን ሊያልፉት የሚገባ ሌላ እንድ መሰናክል ነበረባቸው። ይህም ወንጌልን ለአሕዛብ የመስበክ ጉዳይ ነበር። ለብዙ መቶ ዓመታት አይሁዳውያን አሕዛብ ከእግዚአብሔር ጸጋና ድነት (ደኅንነት) ውጪ ናቸው የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው። ከእግዚአብሔር ቁጣ ሥር ለጥፋት ተመድበው ይኖራሉ የሚል አሳብ ነበራቸው። ከሳምራውያን ይብስ የተጠሉ ነበሩ። ሳምራውያን በግማሽ ጐናቸው አይሁድ የነበሩ፥ ሙሴንና እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ነበሩ። እሕዛብ ጣዖትን የሚያመልኩ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምራቸው ትምህርቶች ሁሉ ጋር የሚቃረኑ ነበሩ። አይሁዳውያን፥ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ግድ እንደሌለው ያስቡ ነበር። ስለዚህ ይህን ገደብ ማለፍ እንዲችሉ እግዚአብሔር እንደገና በእስደናቂ መንገዶች ለመሥራትና አሕዛብንም መውደዱን ለማሳየት የሐዋርያቱን ዓይኖች መክፈት ነበረበት። 

የመጨረሻውን ግድግዳ ለማፈራረስና ቤተ ክርስቲያንን ለሰው ዘር በሙሉ ክፍት ለማድረግ የመጀመሪያው አሕዛብ ክርስቲያን ቆርኔሌዎስ የእግዚአብሔር መሣሪያ ሆነ። መንፈስ ቅዱስ ለእርሱና ከእርሱ ጋር ላነበሩ ሌሎች አሕዛብ የተሰጠበትን ሁኔታ፥ እግዚአብሔር እሕዛብ ከአይሁድና ከሳምራውያን ጋር እኩል መሆናቸውን ላማሳየት የተጠቀመበት ምልክት ነው። 

ጥያቄ፡- የሐዋ. 10፡1-10፤ 23-48 እንብብ። ሀ) ቆርኔሌዎስ ከመዳኑ በፊት የነበረበትን ሁኔታ ግላጽ። ለ) ጴጥሮስ በቁ. 28 ላይ ምን ተምሬያለሁ በማለት ይናገራል? ሐ) ለሌሎች አሕዛብ ገና የማመናቸው ውጫዊ ምልክት እንኳ ሳይፈጸም መንፈስ ቅዱስን የላከላቸው ለምን ነበር? ሀ) መንፈስ ቅዱስ በአሕዛብ ላይ በወረደ ጊዜ የእይሁድ ምላሽ ምን ነበር? ረ) መንፈስ ቅዱስ በአሕዛብ ላይ የመውረዱ ውጫዊ ምልክት ምን ነበር? 

1. የሮም ወታደር የነበረው ቆርኔሌዎስ እግዚአብሔርን የሚወድና ከብሉይ ኪዳን ሕጐች ብዙዎቹን የሚጠብቅ ነበር። ነገር ግን አይሁድ በሚሆንበት ሥርዓት አላለፈም። ስለ ኢየሱስም አልሰማም ነበር። ወይም ኢየሱስን ለማመን የሚያበቃ በቂ መረጃ አላገኘም ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ለአሕዛብ የድነት (ደኅንነት) በር የሚከፈትበትን ወቅት በወሰነ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ካጴጥሮስ ጋር እንዲገናኝና ወንጌልን እንዲሰማ አደረገ። አሁንም እንደገና የምንመለከተው እግዚአብሔር ሐዋርያት ወንጌልን ወደ አሕዛብ እንዲወስዱ ሲያስገድዳቸው ነው። ነገሩ በመጀመሪያ የሐዋርያት ምርጫ እንኳ አልነበረም። 

2. ለሁለተኛ ጊዜ እግዚአብሔር ጴጥሮስን የድነት (ደኅንነት) በር ከፋች እድርጐ ተጠቀመበት። 

3. እግዚአብሔር ይህን ሁኔታ ጴጥሮስን እጅግ ጠቃሚ ትምህርቶችን ለማስተማር ተጠቀመበት። ይኸውም፥ አሕዛብን ያልነጹ እና የረከሱ ብሎ መናገር እንደሌለበት ነው። ደግሞ እግዚአብሔር እንደማያዳላም መማር ነበረበት። ይልቁኑ «እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ ከእርሱ የተወደደ ነው» (የሐዋ. 10፡35)። እግዚአብሔር ለጴጥሮስና ለቀሩት አይሁድ በሙሉ እርሱ አሕዛብን ልክ እንደ አይሁድ እንደሚወድና በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ በእኩልነት እንደተቀበላቸው ማስተማር ነበረበት። 

4. ጴጥሮስ መልእክቱን እንኳ ሳያጠናቅቅ እግዚአብሔርን ይፈሩ የነበሩ አሕዛብ ኢየሱስን ለማመን ገሃድ እንቅስቃሴ ለማድረግ ዕድል ከማግኘታቸው በፊት መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው። ይህ ሙላት ቆርኔሌዎስም ሆነ ሌሎቹ ከማመናቸው በፊት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል ማለት እይደለም። እነዚህ ሰዎች ልባቸው የተዘጋጀ፥ እግዚእብሔርን የሚወዱና የሚያመልኩ ነበር። የቀራቸው ነገር ኢየሱስን ለማመን የሚያስችለውን የመጨረሻ ቃል ማግኘት ብቻ ነበር። ይህንን በሰሙ ጊዜ ያመኑት ወዲያውኑ ነበር። 

5. አሕዛብ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት ባመኑበት ቅጽበት እንጂ በወንጌል ካመኑ በኋላ አልነበረም። መንፈስ ቅዱስ አሕዛብ ከዳኑ በኋላ ወደ ሕይወታቸው የመጣበት ሁለተኛ በረከት የሚባል ነገር አልነበረም። ይልቁኑ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና ሙላት በአንድ ጊዜ ነው የተፈጸመው። 

6. የመንፈስ ቅዱስ በአሕዛብ ልብ ውስጥ መሆኑ የተረጋገጠው፥ በጴንጠቆስጤ ቀን ለአይሁድ በሆነው መንገድ ነበር። እነዚህም፥ እግዚአብሔርን ያመሰግኑና በልሳናት ይናገሩ ነበር። ልሳናቱ በሚታወቁ የሰው ቋንቋዎች ይሁኑ አይሁኑ በቂ መረጃ የለንም። የእሕዛብ ክርስቲያኖች በልሳናት መናገርን የሚያጠኑት ነገር አልነበረም። ምክንያቱም ስጦታው የመጣው በቅጽበት ስለነበር ነው። 

7. አሕዛብ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ የተደረገው አይሁድ በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንደፈሰሰ እንዲያዩ ነበር (የሒ 10፡45)። የአይሁድ ክርስቲያኖች ከዚህ ጊዜ በኋላ አሕዛብን ለመለየት፥ ወይም የእግዚአብሔር ሕዝብ ተብለው ተቀባይነት ከማግኘታቸው በፊት ወደ ይሁዲነት እንዲገቡ ላማስገደድ አልቻሉም። ጴጥሮስ በአይሁድ ክርስቲያኖች ሕግ ተላልፈሃል ተብሎ ሲከሰስ እንዲህ አለ። «…በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመነው ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ ከሰጠ፥ እግዚአብሔርን ለመከልከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ?» (የሐዋ. 11፡17)። ከብዙ ዓመታት በኋላ እሕዛብ ወደ ይሁዲነት ሃይማኖት ሳይመለሱ ወደ ቤተ ክርስቲያን የመምጣታቸው ነገር አከራካሪ ነጥብ ሆኖ በተነሣበት ወቅት ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል «ልብንም የሚያውቅ አምላክ ለእኛ ደግሞ እንደሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው» (የሐዋ. 15፡8)። እንደ አይሁድና የሰማርያ አማኞች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በአሕዛብ ላይ መውረዱ በእኩልነት ደረጃ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነው ተቀባይነት ለማግኘታቸው ዋነኛ ማረጋገጫ ነበር። 

8. እግዚአብሔር አዲስ ማኅበረሰብን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማስገባት እንዲያነሣሣ ጴጥሮስን ለመጨረሻ ጊዜ የተጠቀመው በዚህ ወቅት ነው። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ወደ ክርስቶስ የሚመጡ ከአሕዛብ 

መንፈስ ቅዱስን ለመቀበላቸው ምልክት የሆነውን በልሳን የመናገር ስጦታ ለመጨረሻ ጊዜ የተቀበሉት አሁንም ነው። 

ጥያቄ፡- በዚህ ገጽ ላይ ያሰፈርካቸውን መልሶችህን ከልስ። በክፍሉ ምንባብ ላይ ከተሰነዘረው ውይይት እኳያ መልሶችህን እንዴት ትለውጣቸዋለህ? 

መንፈስ ቅዱስ በሦስት የተለያዩ ዘሮች ላይ የወረደበት ጊዜ ንጽጽር 

1. እግዚአብሔር ለክርስቲያኖች በተለይ ደግሞ ለአይሁድ ክርስቲያኖች፥ እያንዳንዱን ክፍለ ሕዝብ እግዚአብሔር እንደተቀበለው ለማሳየት መንፈስ ቅዱስን ከነማረጋገጫ ምልክቶቹ ልዩ ስሆነ መንገድ ላከ። 

2. በሦስቱም ሁኔታዎች፡ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስ በሚወርድበት ወቅት ከፍተኛ ሚና ነበረው። በመጀመሪያው ጊዜና ቆርኔሌዎስ ባመነበት ወቅት፥ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን የላከው በቀጥታ ቢሆንም ወንጌልን በማብራራት የተናገረው ግን ጴጥሮስ ነበር። በሌላ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በሳምራውያን ላይ እንዲወርድ መሣሪያ ሆኗል። 

3. ለአይሁድና ለአሕዛብ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበላቸው ምልክቱ በልሳን መናገር ነበር። ለሳምራውያን ግን መንፈስ ቅዱስን የመቀበል ምልክት የሆነው ነገር ምን እንደነበር አልተጠቀሰም። 

4. ከእነዚህ ቡድኖች ለማናቸውም ቢሆን በሚድኑበት ጊዜም ሆነ ከዳኑ በኋላ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን በተመሳሳይ ድንቅ መንገድ የላከበት ጊዜ የለም። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ በአስደናቂ መንገድ የተላከበት ተቀዳሚ ምክንያት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እኩልነት እንዳለ ለማሳየት ነበር። እነዚህ የመንፈስ ቅዱስ አሰጣጥ ሁኔታዎች ሰው በሚያምንበት ጊዜ ሁሉ ወይም አንድ ሰው ፍጹም የሆነ መንፈሳዊ ክርስቲያን ሊሆን መከናወን የሚገባቸው ለመሆኑ የሚያመለክት ምንም ነገር የለም። 

5. እሕዛብ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት እንዳመኑ ወዲያውኑ ነው። መንፈስ ቅዱስን ካመኑ በኋላ የተቀበሉት ሳምራውያን ብቻ ናቸው። 

ጥያቄ፡– ሀ) በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ ባሕላዊ ክፍፍሎች ግለጽ። ለ) እግዚአብሔር የክርስቶስ አካል በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እነዚህ ሁሉ በእኩልነት ተቀባይነት እንዳገኙ ማስታወሱ ላምን ይጠቅመናል? ሐ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በዘር፥ በኑሮ ደረጃ ና በጾታ ልዩነት የሚደረግባቸው አንዳንድ መንገዶች ምን ምን ናቸው? መ) መንፈስ ቅዱስ ክርስቲያኖችን ሁሉ በክርስቶስ አንድ ያደርጋል ከሚለው ትምህርት ጋር ይህ የሚቃረነው እንዴት ነው? (1ኛ ቆሮ. 12፡13)። 

4. የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት (የሐዋ. 18፡24-19፥ 7) 

በሐዋርያት ሥራ 18፡24-19፥ 7 ሉቃስ የሚነግረን የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ሆነው ግን በኢየሱስ ስላላመኑ ሰዎች ነው። የመጀመሪያው ታሪክ የሚነግረን ጵርስቅላና አቂላ ስለ ኢየሱስ ስላስተማሩትና አጵሎስ ስለሚባል ስጦታ ያለው መምህር ነው። ሁለተኛው ታሪክ የሚናገረው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ስለ መሰከረላቸው አሥራ ሁለት የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ጉዳይ ነው። እነዚህ ሁለቱም ታሪኮች የተሰጡት የዮሐንስ ጥምቀት ለድነት (ደኅንነት) በቂ እንዳልነበረ የመጀመሪያውን ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ለማስተማር ነበር። 

በአንደኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በርካታ የመጥመቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ነበሩ። ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ከማስተማሩ በፊት ሲያስተምር ሰምተዋል። መሢሑ እንደሚመጣ ዮሐንስ ያስተማረውን ትምህርት ያውቁ ነበር። አንዳንዶች ዮሐንስ ኢየሱስ መሢሑ መሆኑን ስለመመስከሩ ያስታውሳሉ። ነገር ግን እምነታቸው ሙሉ እንዲሆን እነዚህ ደቀ መዛሙርት ሳላ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ማወቅ ነበረባቸው። 

ጥያቄ፡– የሐዋ. 18፡24-19፥ 7 አንብብ። ሀ) አጵሎስ የተገለጸው እንዴት ነው? ለ) በእውቀቱ ውስጥ ምን ጉድለት ነበር? ሐ) የዮሐንስ አሥራ ሁለት ደቀ መዛሙርት የሚያውቁት የትኛውን ጥምቀት ነበር? መ) ጳውሎስ የሰጣቸው ተጨማሪ እውቀት ምን ነበር? ሠ) መንፈስ ቅዱስ የተሰጣቸው እንዴት ነበር? ረ) መንፈስ ቅዱስን የመቀበላቸው ማስረጃ ምን ነበር? 

1. አጵሎስም ሆነ የዮሐንስ አሥራ ሁለት ደቀ መዛሙርት ስለ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ አያውቁም ነበር። እንደ እውነተኛ እማኝ ለመጠራት የሚጐድላቸው ነገር ነበር። 

2. ደቀመዛሙርት ነበሩ። ነገር ግን የማን? የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ነበሩ። በአንዳንድ ሁኔታ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ቢመስሉም እንኳ ጳውሎስ የራሱ ጥርጣሬዎች ነበሩት። አንድ የጐደለ ነገር ያለ ይመስለው ነበር። ስለዚህ ባመኑ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው እንደሆነ ጠየቃቸው። (በግሪክ «ካመናችሁ በኋላ» የሚለው ትርጉም የሚቻል ቢሆንም በዚህ ስፍራ ግን የሚስማማ አይመስልም።) ጳውሎስ የሚጠይቀው ስክርስቶስ የነበራቸውን እምነት ጥልቀት ነበር። መንፈስ ቅዱስን ካልተቀበሉ ሙሉ በሙሉ በእዲስ ኪዳን መንገድ አላመኑም ነበር ማለት ነው። ያቀረበላቸው ትክክለኛ ጥያቄ የአዲስ ኪዳን አማኞች ናችሁ ወይ? የአዲሱን ኪዳን የመንፈስ ቅዱስ በረከት ተቀብላችኋል ወይ? የሚል ነበር። መልሳቸው እምነት እንዳልነበረው ያረጋግጣል። እስከዚህ ጊዜ ድረስ የአሮጌው ኪዳን እማኞች ነበሩ። ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን እንዳልተቀበሉ ሊሰማ በመንፈስ ቅዱስ እንዴት መጠመቅ እንዳለባቸው እንዳላስተማራቸው ልብ በል። ለመንፈስ ቅዱስ እንዲታዘዙ ወይም እንዲጸልዩ አልመከራቸውም። ስለ ኢየሱስና ስለ ጥምቀቱ አስተማራቸው። የድነት (ደኅንነት)ን መሠረታዊ ነገሮች አስተማራቸው። ክርስቶስን ከኃጢአታቸው እንደሚያድናቸው ገና አላመኑም ነበር። ኢየሱስን ይከተሉት የነበሩት የሚመጣው የእስራኤል መሢሕ እንደሆነ ብቻ ነበር። ስለዚህ በአዲስ ኪዳን አካሄድ ገና አልዳኑም ነበር። 

የዮሐንስ ጥምቀት የሚመጣውን መሢሕ የመጠባበቂያ ጥምቀት ነበር። ሊመጣ ባለው የማመን ጥምቀት ነበር። ያ ጥምቀት ለመስቀሉም ሆነ ለትንሣኤው ሥራ ባይተዋር ነበር። ከኢየሱስ ሞት በኋላ የዮሐንስ መልእክትና ጥምቀት ለድነት (ደኅንነት) ብቁ ሆነው አልተገኙም። 

3. መንፈስ ቅዱስ እነዚህ እሥራ ሁለቱ የውኃ ጥምቀት ከተጠመቁ በኋላ መጣ። የጳውሎስ እጅ መጫን ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የጥምቀት ሥርዓት አንዱ ነበር። ነገር ግን በኢየሱስ ስም ጥምቀትን መቀበላቸው እንደ ሳምራውያንና እንደ እሕዛብ አሁን ስለ ኢየሱስ ሙሉ እውቀት እንዳላቸውና ደኅንነታቸውም የተገኘው ኢየሱስ በመስቀሉ ላይ የፈጸመውን ሥራ በማመናቸው መሆኑን ለማሳየት ነበር። 

4. መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ በወረደ ጊዜ ህልውናው በልሳናት ንግግርና በትንቢት ተረጋገጠ። ትንቢትን መናገር የመንፈስ ቅዱስ ህልውና ምልክት ሆኖ ሲቀርብ ይህ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የመጀመሪያ ጊዜ ነው። 

ጥያቄ፡- ህ) በዚህ ክፍል ምንባብ ያሉትን መልሶችህን ከልስ። ከላይ ከቀረበው ገለጻ አንጻር መልሶችህን እንዴት ትቀይራለህ? ለ) እነዚህ አራት ክፍል ምንባቦች ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና ሙላት ምን እንደሚያስተምሩ የአንድ ገጽ ማጠቃለያ ጻፍ። የጻፍከውን አሳብ የሚቃረን እቋም ባላው ክርስቲያን ፊት ማጠቃለያህን እንዴት ትከላከላለህ? 

ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች «ሁላተኛ በረከትክ ወይም በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የሚመጣ የመንፈስ ቅዱስ ሁለተኛ ሥራ የሚለውን የሥነ መለኮት ትምህርታቸውን ለመደገፍ የሚጠቀሙባቸውን ዋና ዋና ጥቅሶች በዝርዝር እይተናል። የሥነ መለኮት ትምህርታቸውን ለመደገፍ ያለው ማስረጃ በጣም አነስተኛ ነው። ይልቁኑ ላሚያራምዱት ልምምጻቸው ድጋፍ የሚሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ የሚፈልጉ ይመስላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ የተደገፈ መሆኑን የሚያደርጉት ጥረት በአእምሮአቸው ያለውን መጽሐፍ እንደሰጠ እድርገው እንዲያነቡት ይገፋፋቸዋል። (ይህ ዝንባሌ በካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች ዘንድ ብቻ አይደለም ያለው። ሁላችንም አመለካከታችንን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲደግፍልን ፍላጐቱ አለን። ስለሆነም፥ አመለካከታችንን የሚደግፉትን ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያንፀባርቅልን፥ አመለካከታችንን የማይደግፉትን ደግሞ እንዲዘልልን አድርገን እናነብበዋለን። ይህ አደገኛ ነው። ምክንያቱም በመጨረሻም መጽሐፍ ቅዱስ የማይለውን ነገር ይላል ወደማላት ስለምንደርስ ነው።) 

ስለዚህ በጌታ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችን ስለሆኑት ስለ ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች እምነት ምን ለማለት እንችላለን? የሚለማመዱት ነገር እነርሱ እንደሚሉት የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት መሆኑ አጠራጣሪ ነው። ምናልባት የበለጠ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነው ትክክላኛ አገላለጽ ልምምዳቸው የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ማስረጃዎች መሆናቸው ነው። ስለዚህ ካሪዝማትኮችና ካሪዝማቲክ ያልሆኑት ከሚከራከሩስት ነገር ከፊሉ ለተለያዩ ቃሎች የተለያዩ ትርጉሞችን ከመስጠት የመነጨ ነው። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የሚሉት መጽሐፍ ቅዱስ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት የሚለውን ነው። 

ከእንቅስቃሴው ውጭ ሆኖ እንደሚመለከት ካሪዝማቲክ ያልሆነ ሰው የሚያሳስቡኝ ነገሮች መኖራቸውን መግለጽ እፈልጋለሁ። አንዳንድ ካሪዝማቲክ ያልሆኑ ሰዎች እንደሚሉት እንቅስቃሴው በሙሉ ከዲያብሎስ ነው አልልም። ይህን እንዳልል ጌታን የሚወዱና በፈሪሃ እግዚአብሔር የሚኖሩ በርካታ ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖችን አውቃለሁ። የሚያሳስበኝ ነገር በአምልኮ ጊዜያቸው የሚያደርጉት ነገር አይደለም። ከሚያደርጉት ነገር በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተው እጅግ ጥቂቱ መሆኑ ነው። አብዛኛዎቹ ተግባሮቻቸው በእግዚአብሔር ቃል አልተከለከሉም። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ቃል አካሄድ ጋር አይጣጣሙም። ስለዚህ እነዚህ የእግዚአብሔር ሰዎች ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች በተለይ እክራሪዎቹ ከሚያስተምሩት ነገር ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚያሳስብ ይሆናል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተለመዱ ሆነው ብዙ ጊዜ ላመንፈስ ቅዱስ ህልውናና ለመንፈሳዊ አምልኮ ማስረጃ ሆነው የሚቀርቡትን አንዳንድ ምሳሌዎች እንመልከት። 

1. በጸሎት ወይም በዝማሬ ወቅት እጆችን ወደ ላይ ማንሣት፡- ይህ ልምምድ የመጣው ከየት ነው? ይህን የምናደርገው መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል ብለን ስለምናምን ነው ወይስ ሌሎችን በማየት የተማርነው ነገር ነው? ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ከሄድን እጆቻቸውን ወደ ሰማይ ዘርግተው የሚጸልዩ ክርስቲያኖችን በምሳሌነት እናገኛለን (መዝ. [63]፡4፤ 1ኛ ጢሞ. 2፡8)። ደግሞም በጀርባቸው መሬት ላይ ተንጋለው፤ ተንበርክከውና ቆመው የጸለዩ ሰዎችንም በምሳሌነት እናገኛለን (ዘዳ 9፡18፤ ኢያ. 7፡6፤ ዕዝ. 9፡5፤ ነህ. 9፡2-5፤ ዳን. 6፡10፤ ማር. 11፡25)። ይህ የሚያመለክተው መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛ የሆነ የጸሎት መንገድን እንደማያስተምር ነው። በየትኛውም መንገድ መጸለይ የተለየ መንፈሳዊ አያደርግም። ለአንዱ ሰው በሚዘምርበት ወይም በሚጸልይበት ጊዜ እጆቹችን መዘርጋት ይመቸው እንደሆነ መልካም ነው። ነገር ግን ይህ ለመጸለይ ከሁሉም የላቀ መንፈሳዊ መንገድ ነው ብለን እንዳናስብ እንጠንቀቅ። በሚዘምርበት ጊዜ እጅን ለማንሣት በምሳሌነት የምናቀርበው ልምምድ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የለም። ይህ ስሕተት አይደለም። ነገር ግን ልዩ መንፈሳዊ የመሆን ምልክት ተደርጐ መቆጠር የለበትም። ይህ አምልኮአችንን የበለጠ እውነተኛ የሚያደርገው ከሆነ ክልክል የሆነበት ነገር ፈጽሞ የለም። ነገር ግን ሌሎች ስላደረጉት ብቻ ወይም የበለጠ መንፈሳዊ ለመምሰል ማድረግ የለብንም። 

2. በጸሎት ጊዜ መንቀጥቀጥ፡- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትም ሆነ ሙላት ክቁጥጥር ውጭ በሆነ መንቀጥቀጥ ለመገለጹ ማስረጃ የላም። ደቀ መዛሙርት በመንፈስ በተሞሉ ጊዜ የነበሩበት ቤት ስለ መናወጡ እናነባለን (የሐዋ. 4፡31)። ነገር ግን አካላቸው መንፈስ ቅዱስን መቀበላቸው እንዲረጋገጥ ስለመንቀጥቀጡ አናነብም። ይህ ጤነኛ የአምልኮ ሥርዓት አይመስልም። ቢሆንማ ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ይሰጠን ነበር። ተለይ በማስመሰል እንዳናደርግ መጠንቀቅ አለብን። በሌላ አባባል፥ ሌሎች ሲያደርጉ ስላየን ወይም መንፈሳዊ ለመምሰል ብለን ማድረግ የለብንም ማለት ነው። 

3. በጸሎት ጊዜ «ሃሌሉያና» «በኢየሱስ ስም» እያሉ መጮህ፡ በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት አንድ ሰው በሚጸልይበት ጊዜ እና ሌሎችም በሚያደምጡበት ጊዜ፥ ጸላዩም ሆነ አድማጮቹ እነዚህን ቃላት በከፍተኛ ድምፅ ማሰማታቸው የወቅቱ ወግ ይመስላል። ይህን የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ አይገባኝም። እግዚአብሔር ደንቆሮ ስላይደለ ጸሎታችንን ለመስማት እንድንጮህ አይፈልግም። የኢየሱስን ስም ጮክ ብሎ መጥራት ስሙ ካለው ኃይል ሌሳ የሚጨምረው ነገር የለም። እንደገና ይህ ከእኛ የሚጠበቅ የአምልኮ ዓይነት ለመሆኑ በቂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማረጋገጫ የለም። እንዲያውም በ1ኛ ቆሮ. 14፡ 30፥ 40 የተመለከተው ነገር ተቃራኒው ነው። ከቁጥጥር ውጪ ከሆነ አምልኮ ወይም ንግግር ይልቅ አምልኮ ሥርዓት ያለውና በሰዎች አእምሮ ቁጥጥር ሥር የሚመራ መሆን አለበት (1ኛ ቆሮ. 14፡14-17፥ 40)። ኢየሱስ እራሱ በምንጸልይበት ጊዜ ትርጉም አልባ የሆኑ ቃሎችን በመደጋገም እንዳናነበንብ አስጠንቅቆናል (ማቴ. 6፡7-8)። ጸሎት ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ልብን ማፍሰስ ነው። የሚሰሙትን በተለየ መንገድ ለመንካት የሚደረግ አይደለም። ስየዕለት ሕይወታችን እንደምንጠቀምበት ዓይነት ተፈጥሮአዊ ንግግር መሆን አለበት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ጸሎቶችን በሙሉ ብንመረምር ወደ እግዚአብሔር ለመጻላይ የተጠቀሙበት ልማዳዊውን ቋንቋ መሆኑን እንመለከታለን። በኃይል መጮህ ወይም እንዳንድ ሐረጐችን መደጋገም ትክክለኛ ለሚሆኑ የሚቀርብ ምንም ማስረጃ የለም። 

እነዚህን ልምምዶች በእግዚአብሔር ቃል ብርሃን መመርመር አለብን። ልናደርጋቸው የፈለግነውን ዓይነት ነገሮች ብንሞክርም፥ አምልኮአችን እግዚአብሔር በቃሉ ከሰጠን መመሪያ በተቃራኒ የሚሄድ ከሆነ እግዚአብሔርን ደስ አያሰኘውም። እነዚህን ነገሮች በማድረጉ እንግፋበት የሚሉ፥ ድርጊቶቹ አደብ የገዙ መሆናቸውንና የግል አምልኮን ብቻ ሳይሆን የኅብረት አምልኮንም እንደሚያነሣ ለማሳየት የማረጋገጡ ሸክም ይጠብቃቸዋል። በ1ኛ ቆሮ. 14 ጳውሎስ ሰዎች በግል የአምልኮ ጊዜያችው ስለሚያደርጉት ነገር ብዙ አልገለጸም። ዋናው ያሳሰበው ነገር ስለ ኅብረት አምልኮ ነበር። የጥቂት ሰዎች ልምምድ የሴሎች ክርስቲያኖች እምልኮ ወይም ቤተ ክርስቲያን በማያምነው ሕዝብ መካከል ያላትን ምስክርነት እንዲያጠፋ ፈቃዱ አልነበረም። 

4. በጸሎት ጊዜ መዘመር ወይም ማንጐራጐር፡- እንደገና መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ጊዜ ሐዋርያት በሚጸልዩበት ወቅት ስለማዜማቸው ወይም ስለማንጐራጐራቸው የተጠቀሰ ነገር የለም። ይህ ወደ ቤተ ክርስቲያን የገባና ከአንዱ ክርስቲያን ወደ ሌላው የተዛመተ ልምድ ነው። ሰውዬው ወደ እግዚአብሔር እንዲጸልይ የሚረዳው ከሆነና በጉባኤ ውስጥ የሌሎችን ጸሎት ካልረበሸ ስሕተት ላይሆን ይችላል። ነገር ግን የእኛ ጸሎት የበለጠ መንፈሳዊ ወይም ትርጉም ያለው መሆኑን አያመላክትም። አእምሮአችንን በእግዚአብሔር ላይ እንድናደርግ ከፈላግነው ብቻ ይረዳናል። 

5. በመንፈስ መገንደስ፡- የመጀመሪያዎቹ አራት ምሳሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይደገፉም እንኳ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተቃራኒ የሚሄዱ አይደሉም። ነገር ግን ጭራሽ ገደብ የለቀቁ አንዳንድ ልምምዶች አሉ። አንዳንድ የጴንጠቆስጤ ሰባኪዎች ከሚያደርጉት ከእነዚህ ልምምዶች አንዱ በመንፈስ መገንደስ የሚባለው ልምምድ ነው። መሪዎች ሕዝቡን ወደ ቤተ ክርስቲያን መድረክ ፊት በመጥራት እጆቻቸውን ከጫኑባቸው ሰኋላ እፍ በማለት ራሳቸውን ስተው ወደ መሬት እንዲወድቁ ያደርጉአቸዋል። ለዚህ የሚቀርበው የመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ የት አለ? ለዚህ ልምምድ ያለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ እጅግ አነስተኛ ነው። በግሌ እንደማምነው ደግሞ ይህ ለክርስቲያኖች የሚጠቅም እይደለም። ታዲያ ይህ ምንን ያረጋግጥልናል? ሰውዬው የበለጠ መንፈሳዊ መሆኑን እያሳይም። ይልቁኑ ለብዙዎች የሰባኪውን መንፈሳዊ ኃይል ለማድነቅ ብቻ የሚረዳ ነው። እግዚአብሔር በእንደዚህ ዓይነት ድርጊት እንደማይሳብ የተረጋገጠ ነው። በመንፈስ መገንደስ አደገኛም ሊሆን ይችላል። ሰዎች ሕሊናቸውን በሚስቱበት ጊዜ ለሰይጣን ተጽዕኖ እራሳቸውን ክፍት እንደሚያደርጉ አንዳንዶች ያስተምራሉ። ምንም ይሁን ምን ይህ ተግባር በመንፈስ የሚገደሰውን ሰው ይጠቅም እንደሆነና በእምነቱም ያበረታታው እንደሆነ ማስረጃ የለም። 

6. እንደ ዱር እንስሳ መጮኽ፡- በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ክርስቲያኖች እንደሚጮኹ፥ እንደሚያጓሩ ወይም የተላያዩ እንስሳት ድምፅ እንደሚያሰሙ ዘገባ አለ። ይህ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ምልክት እንደሆነ ግንዛቤ ይሰጠዋል። በእርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትንሽ እንኳ ይህን የሚመስል እንዳችም ነገር የለም። እንደዚህ ዓይነት ልምምድ የሚያስገኘው ጥቅም ወይም አስፈላጊነቱ ኢምንት ነው። 

7. ቅዱስ ሳቅ፡- የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ማረጋገጫ ነው የሚባልለት ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ይህ ሳቅ የሰዎችን ሕሊና አስቶ የሚጥላቸውም ጊዜ አላ። ለዚህም እምነትና ልምምድ ምንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለም። 

ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ መመለስና ከእነዚህ ልምምዶች የትኞቹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንዳይደሉና ግልጽ መቃወሚያ እንዳላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሶ በቀጥታ ለመናገር ያስቸግራል። የትኞቹም ቢሆኑ በሚቀርቡበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ የላቸውም። መሠረታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላይ የቆመ አይደለም። ይልቅ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለማቋረጥ እየተስፋፉ ያሉት ብዙውን ጊዜ እንድ ሰው ያደረገውን ሌላው ብዙውን ጊዜ በአጠያያቂ ዓላማ ተመርኩዞ በመቅዳት ስለሚያዛምተው ነው። ይህን ልምምድ የሚያደርጉ በአምልኮ ብቃትም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ምንም የተሻለ ለውጥ የላቸውም። ከእነዚህ ልምምዶች አብዛኛዎቹ እዘናጊዎች ናቸው። ሰዎች እግዚአብሔርን በማምላክ ላይ እንዳያተኩሩ ያደርጋሉ፤ በማያምኑ ሰዎች ፊት ምስክርነታችንን ያጠፋሉ። እንደ እነዚህ ዓይነት ልምምዶችን መመልከት ከጀመርን ቁጥራቸው እየጨመረ ነው ያለው። ክርስቲያኖች እንደ እነዚህ ዓይነቶቹን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌላቸውን ትላልቅ ስሜታዊ ልምምዶችን ለማድረግ እርካታ የለሽ ጥማት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ከሌለን ካጸናው የቃሉ መሠረት ላይ እየተናድን በሚናወጠው ስሜታዊ መሠረት ላይ ነን። እግዚአብሔር ከእንደዚህ ዓይነት አፈንጋጭ ልምምዶች ምን ክብር ሊያገኝ እንደሚችል ማየት ይሳነኛል። 

እንደ ክርስቲያን መንፈስን እንድንመረምር ታዝዘናል (1ኛ ዮሐ 4፡1)። ከዚህ ጥቅስ ዓውደ-አሳብ በመነሣት ልንደርስበት የምንችለው ማጠቃለያ ከመንፈስ ቅዱስ የሚመነጩ እሳቦች እንዳሉ ሁሉ ክርኩስ መንፈስም የሚመነጩ መኖራቸውን ነው። እምነታችንና ተግባራችን ከየትኛው እንደሆነ ለመረዳት መመርመር ያስፈልገናል። ይህን እንዴት ማድረግ እንችላለን? የትኛውን መመዘኛ መጠቀም እንችላለን? የሰውዬውን ሥነ ምግባር ሕይወት ወይም ተግባሩን የሚፈጽምበትን ዓላማ መመርመር የመሰለ ብዙ መፈተኛ መንገዶች ያሉ ቢሆንም፥ የመጨረሻው መመዘኛ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር መጣጣሙን ማረጋገጥ ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመሳሳይ አካሄድ 200 ካላገኘን በስተቀር ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ራሱን የብርሃን መልአክ አስመስሎ የሚያቀርበው ሰይጣን (2ኛ ቆሮ. 1፡14)፥ ሰዎች ከእውነተኛው ነገር መልካም ወደሚመስል እንዲያዘምሙ ማድረግን ይወዳል። የማስመሰል አምልኮ፥ ሃይማኖታዊ አምልኮ ሲሆን፥ እርሱም የሞተ ነው። 

ጥያቄ፡– ሀ) ከእነዚህ ልምምዶች የትኞቹ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደሚደረጉ ዘርዝር። ለ) ከእነዚህ ልምምዶች መካከል ራስህ የትኞቹን ታደርጋቸዋለህ? ) የምታደርጋቸው ለምንድን ነው? እንዴትስ ረድተሃል? መ) ወደ ቤተ ክርስቲያን በሚገቡ አዳዲስ ልምምዶች ቁጥጥር እላማድረግ ስለሚያስከትለው አዴጋ የምትሰጠው ምስክርነት ምንድን ነው? ሠ) እነዚህን ልምምዶች በመፈተን በአጠቃቀማቸው ላይ ለክርስቲያኖች ምክርን በመስጠት ሽማግሌዎች ያለባቸው ኃላፊነት ምንድን ነው ብለህ ታስባለህ? 

እነዚህ ልምምዶች ወደ አብያተ ክርስቲያናት የሚስፋፉበት ሁኔታ ያሳስበኛል። እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን አዳዲስ ልምምዶችን ከመመርመርና በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ መደገፉቸው ከመጠየቅ ይልቅ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ወይም ክርስቲያኖች ያደረጉትን የመቅዳትና የመተግበር ዝንባሌ ይጸናወታቸዋል። በጥንቃቄ ሳንመረምር አዳዲስ ትምህርቶችንና ልምምዶችን መቀበል እደገኛ ነው። እንደ እነርሱ መንፈሳዊ መስሎ ለመታየት ብቻ ሌሎች ያደረጉትን ነገር መቅዳት ስሕተት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ኃጢአት «ግብዝነት» ብሎ ይጠራዋል (ማቴ. 6፡1)። 

ጥያቄ፡- ሀ) ከላይ ከተጠቀሱት ልምምዶች አንዱ ወደ ቤተ ክርስቲያንህ እንዴት እንደገባ ግለጽ። ላ) አንዳንድ ጊዜ ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ የሚገለጥ አምልኮ ከማቅረብ ይልቅ ሌሎች የሚያደርጉትን ለመኮረጅ ተብሎ የሚፈጸመው እንዴት ነው? ሐ) አዳዲስ ልምምዶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ ያለ አንዳች መከላከል የመፍቀድ እደገኛነቱ ምንድን ነው? 

የእኔ መልእክት ወይም ሁላችንንም የምለምነው ነገር «እውነተኞች እንሁን» ነው። በአጠገባችን ያሉት ሌሎች ስላደረጉት ሳይሆን የእግዚአብሔር መንፈስ እጆቻችንን እንድናነሣ ካዘዘን እንደታዘዝነው ብናደርግ መልካም ነው። በተጨማሪ በዚህ መንገድ እንዲያመልኩ መንፈስ ቅዱስ ያላነሣሣቸውን ሰዎች ዝቅ እድርገን እንመልከት። እምነታችንና ልምዳችንን በተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ላይ ለማድረግ የምንፈልግ ሰዎች እንሁን። በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችና ምሳሌዎች በግልጽ የተቀመጡትን ነገሮች ሳንፈርድ ሰዎች እንዲጠቀሙባቸው ነፃነት እንስጣቸው። ከመጽሐፍ ቅዱስ እካሄድ ጨርሶ የራቁትን ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ እናድርግባቸው። 

ከላይ የተጠቀሱትን በልሳን መናገርን ወይም ፈውስን የመሳሰሉ ልምምዶችን አምርረው የሚቃወሙ ሰዎች በሚሉት የማልስማማበት ቢሆንም፥ የሚናገሩት ነገር ግን ለጥንቃቄ ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ፡ በልሳናት እንናገራለን የሚሉ ወይም በጣም ልምምዶችን የሚሹ ሰዎች እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉት በአጋንንት ተጽእኖ ለመሆኑ አንዳንድ ማስረጃዎች አሉ። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ማስረጃ ዎችን የበለጠ በመፈለጋችን ምክንያት ብቻ በካሪዝማቲክ ትምህርቶች ውስጥ ያየናቸውንና ቤተ ክርስቲያንን እጅግ በጣም የረዱ ልምምዶችን ሰይጣን እየወሰደ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት እንዲጠቀምበት ዕድል ልንሰጠው አይገባም። 

ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች አንዳንድ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን አምልኮ ወቅት መንፈሳዊ ሆነው ለመታየት የሚያደርጓቸውን ነገሮች ዘርዝር። ላ) እነዚህ ልምምዶች የመጡት ከየት ነው? ሐ) እነዚህ ልምምዶች የተገኙት ከመጽሐፍ ቅዱስ ለመሆኑ ምን መረጃ አለ? ማብራሪያ ስጥ። መ) በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያልተከለከሉትን በመቀበልና ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ የሌላቸውን ማናቸውንም ልምምዶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመጋበዝ መካከል መኖር የሚገባው ሚዛናዊነት ምንድን ነው ብለህ ታምናለህ?

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.