መንፈሳዊ ስጦታዎችና የማያምኑ ሰዎች (1ኛ ቆሮንቶስ 14፡20-40)

ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 14፡20-40 አንብብ። ሀ) ጳውሎስ በአምልኮ ስብሰባዎች ላይ በልሳናት ስለመናገርና ትንቢት ስለመናገር የሰጣቸውን የተለያዩ መመሪያዎችን ዝርዝር። ለ) የአምልኮ ስብሰባዎችን «ሥርዓት ያላቸው» ያደርጋሉ ብለህ የምታምንባቸውን አንዳንድ ነገሮች ጥቀስ። 

ጳውሎስ በልሳናት መናገር በተቀዳሚ ለአምልኮ ስብሰባዎች የተሰጠ ስጦታ እንዳልሆነ መግለጹን ይቀጥላል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በልሳናት በመናገር ላይ ባላቸው አቋም እንደ ልጅ ያደርጋቸው ነበር። ሌሎችን ከማነጽ ይልቅ በራስ ወዳድነት የራሳቸውን ክብር የሚያሳድዱ ነበሩ። የልሳን አጠቃቀማቸው መንፈሳዊ መሆናቸውን ሳይሆን ጨቅላነታቸውን ነበር የሚያሳየው። ሰለዚህ በልሳናት መናገር ላይ ከሚገባው በላይ ማተኮር በክርስቲያኑ ሕይወት መብሰልን ሳይሆን ጨቅላነትን ወደሚያመለክት ሚዛን አልባነት ያደርሳል። 

የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በልሳናት መናገር ተግባር ላይ የነበራቸውን አመላካከት መለወጥ ነበረባቸው። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ልጆች የመሆናቸው ዋነኛው ማረጋገጫ በልሳናት መናገር እንደሆነ ያስተምሩ ነበር። እንዲያውም መንፈሳዊ የመሆናቸው ዋነኛው ማረጋገጫ ይኸው እንደሆነ ይናገሩ ነበር። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በልሳናት የመናገር ዓላማ ይህ እንደሆነ ነው የሚያስተምረው? የሚያምኑ ሰዎችን በተመለከተ በልሳናት መናገርና ትንቢት የሚዛመዱት እንዴት ነው? በዚህ ክፍል ውስጥ በልሳናት ስለመናገር ሁለት እውነቶችን እንመለከታለን። 

በመጀመሪያ፥ በልሳናት መናገር እግዚአብሔርን በማያምኑ ላይ ስለሚያመጣው ፍርድ ምልክት ነው። ጳውሎስ በልሳናት በመናገርና በትንቢት መካከል ያደረገውን ንጽጽር ለማስተዋወቅ በብሉይ ኪዳን ወደሚገኘው ኢሳ. 28፡9-13 ይመለሳል። (ክፍሉን አንብበው።) ኢሳይያስ የሚተነብየው እስራኤልና ይሁዳ እንደሚማረኩ ነበር። ከይሁዳ ምድር እንደሚሄዱ ነበር። እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደ አሶርና ባቢሎን ባሉ የአሕዛብ መንግሥታት እጅ አሳልፎ በመስጠትና ወደ አገራቸው እንዲያግዟቸው በማድረግ በሄዱበት ምድር የማያውቁትን ሕዝብ ልሳናት (የማይታወቁ ቋንቋዎች) እንዲሰሙ አስገደዳቸው። የሌሎችን ልሳናት መስማት ችሮታ ከመሆን ይልቅ በቅጣት መልክ የምርኮአቸው ውጤት ሆኖ እንመለከታለን። ስለዚህ ለእስራኤላውያን የማይታወቁ ቋንቋዎች መስማት የበረከት ሳይሆን የፍርድ ምልክት ነበር። ልባቸውን የነካ አልነበረምና እስራኤላውያን ልሳናት በመስማት እግዚአብሔርን መታዘዝ አልተማሩም።

የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በልሳናት መናገር የእግዚአብሔር በረከት ምልክት እንደሆነ ያስቡ ነበር። ሆኖም ግን በልሳናት መናገር ለአማኞች ምልክት ሳይሆን ለማያምኑ ሰዎች ምልክት ነበር። ግን ምን ዓይነት ምልክት ነበር? በብሉይ ኪዳን «ምልክት» የሚለው ቃል አዎንታዊና ለምሳሌ ቀስተ ደመና (ዘፍ 9፡12) አሉታዊ ለምሳሌ (ዘኁ. 26፡10) በሆኑ መንገዶች ይታወቅ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ «ምልክት» የሚለውን ቃል ሲጠቀም እግዚአብሔር በአንድ ጉዳይ ላይ ስላለው አመላካከት ነበር። ይህ የሚገልጸው ደስታውን ወይም ቁጣውን ሊሆን ይችላል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በልሳናት መናገር እግዚአብሔር በመካከላቸው ስለመኖሩ ለማያምኑ ሰዎች ምልክት እንደሆነ ያስቡ ነበር። ነገር ግን ያልተተረጐመ ልሳን አሉታዊ ምልክት መሆኑን አልተገነዘቡም ነበር። በብሉይ ኪዳን ዘመን ልሳናት እግዚአብሔር ፍርድን ለማምጣት መወሰኑን የሚያመለክቱ ነበር። ስለዚህ ያልተተረጐሙ ልሳኖችን በቤተ ክርስቲያን መናገር ወደ ጉባኤው ለሚመጡና መልእክቱ ለማይገባቸው የማያምኑ ሰዎች የፍርድ ምልክት ነው። የእግዚአብሔርን እጅ አይተው ንስሐ ስለማይገቡ በፍርድ ሥር ይኖራሉ። (የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል ይሆኑ ዘንድ ክርስቶስን እንደ መሢሑ ባለመቀበላቸውና በክርስቶስ ላይ እምነት ባለማድረጋቸው ለአይሁድ ልዩ የፍርድ ምልክት ነበር።) ያልተተረጐሙ ልሳኖች የፍርድ መልእክትን የሚያውጁ ስለሆነ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ወደሚገኝ የሚያድን እምነት ሊደርሱ አይችሉም ነበር። 

ሁለተኛ ፥ በልሳናት መናገር ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡ የማያምኑ ሰዎች ለሚሰሙት የወንጌል መልእክት መሰናክል ነበር። የማያምኑ ሰዎች ክርስቲያኖች በልሳን ሲናገሩ በሚሰሙበት ጊዜ እግዚአብሔር እንደሚናገር ከመገመት ይልቅ ተናጋሪዎቹ ያበዱ ወይም እጋንንት ያደረባቸው ይመስላቸው ነበር። ስለዚህ በመካከላቸው የእግዚአብሔር ኃይል እንዳለ ምስክር ከመሆን ይልቅ ለወንጌል ዕንቅፋት የሚሆን ነበር። 

የትንቢት ስጦታ ግን ለሚያምኑም ሆነ ለማያምኑ በረከት ነበር። የእግዚአብሔር ፍርድ አሉታዊ ምልክት ከመሆን ይልቅ የእግዚአብሔር ህልውና አዎንታዊ ምልክት ነበር። አንድ ሰው ከእግዚአብሔር መልእክት ሲቀበልና ለአማኞች ጉባኤ በግልጽና በሚገባቸው ቋንቋ ሲያስተላልፈው እግዚአብሔር ጉባኤውን እንደተቀበለው የሚያሳይ ምልክት ይሆናል። እግዚአብሔር በመካከላቸው የመሆኑ፥ ችሮታው በእነርሱ ላይ የመሆኑና ፈቃዱን እየገለጠላቸው የመሆኑ ምልክት ነው። ወደዚህ ጉባኤ የማያምን ሰው ቢመጣና በኅብረት አምልኳቸው ትንቢት ሲነገር ቢሰማ እንዳበዱ ወይም አጋንንት እንዳደረባቸው ከማሰብ ይልቅ እግዚአብሔር በመካከላቸው መኖሩን ያውቃል። እንዲያውም በትንቢት በሚመጣው ቃል በሰውየው ሕይወት ውስጥ ያሉ የተደበቁ ነገሮች ሊገለጡና ወንጌልን ሰምቶ የማመን ዕድል ሊያገኝ ይችላል። ስለዚህ ሳይተረጐም የሚነገር ልሳን ለወንጌል ዕንቅፋት ሊሆን የሚችል ሲሆን ትንቢት ግን የወንጌል መሣሪያ ነው። ስለዚህ የቆርንቶስ ሰዎች የትንቢት ስጦታ በልሳናት ከመናገር የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ መረዳት ነበረባቸው። ይህም የማይተረጐሙ ልሳናትን በጉባኤ መካከል እንዳይነገሩ ለመቆጣጠር እንዲችሉ የሚረዳቸው ነበር። 

የዚህን ክፍል ዝርዝር አሳብ መረዳት አስቸጋሪ ቢሆንም የጳውሎስ አጠቃላይ ትምህርት ግን ግልጽ ነው። በልሳናት መናገር ለማያምኑ ሰዎች የፍርድ ምልክት በመሆኑ በጉባኤ መካከል በልሳናት ሲነገር ቢሰሙ ክርስቲያኖች «አብደዋል» በማለት ወደ እምነት ከመምጣት ይልቅ ይሰናከላሉ። በሌላ በኩል ግን ትንቢት ለአማኞች ምልክት ከመሆኑም ባሻገር የማያምኑ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ለመምራት ትልቅ መሣሪያ ነው። ስለዚህ በአምልኮ ስብሰባ ወቅት በልሳናት በመናገር ላይ ከማተኮር ይልቅ ግልጽ የእግዚአብሔር ፈቃድ ማስተላለፊያ መንገድ በሆነው በትንቢት ላይ ማተኮር ነበረባቸው። 

ጥያቄ፡- ሀ) ይህን ትምህርት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በልሳናት መናገርና ትንቢት ያላቸውን ሚና ከሚያውቁ ሰዎች ቁጥር ጋር አወዳድር። ተመሳሳይ የሆነው ወይም የሚለየው እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በእነዚህ ጥቅሶች የተሰጡትን ትምህርቶች የበለጠ ትክክለኛ በሆነ መንገድ ያንጸባርቁ ዘንድ መለወጥ ያለባቸው እንዴት ነው? 

1ኛ ቆሮንቶስ 14፡26-36 በአምልኮ ስብሰባዎች ወቅት የሥነ ሥርዓት አስፈላጊነት 

ጳውሎስ በኅብረት አምልኮ ወቅት አማኞችን በሙሉ የማያንጸው በልሳናት መናገር የትንቢትን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆነ ከተናገረ በኋላ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በልሳናት መናገርና መተንበይ እንዴት መከናወን እንዳለባቸው መመሪያዎችን ወደ መስጠት ይዞራል። በኅብረት አምልኮ ምን መደረግ እንዳለበት ግልጽና የማያሻሙ ደንቦችን ይሰጣል። 

በኅብረት አምልኮ ወቅት መደረግ ስላለባቸው ነገሮች ምሪት የሚሰጡ ሁለት መሠረታዊ መርሆዎች በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ይገኛሉ። በመጀመሪያ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ የሚደረጉ ማናቸውም ነገሮች ሁሉም በሚረዱበትና እምነታቸውን በሚያንጹበት መንገድ መሆን አለባቸው። ስለዚህ ማንኛውም ልሳን ሰዎች የተነገረውን ነገር ለመረዳት ይችሉ ዘንድ መተርጐም አላበት። ሁለተኛ አምልኮ በሥርዓት፥ በሰላምና በሚስማማን መንገድ መካሄድ አለበት። ሰዎች ሁሉ በአንድ ጊዜ በመናገራቸው ወይም በክርስቲያኖች መካከል በሚደረግ አምባጓሮ ግራ መጋባትና ውዥንብር መፈጠር የለበትም። 

ጥያቄ፡- ሀ) ከዚህ ቀደም ተካፍላኽው የምታውቀው ሥርዓተ አልበኝነት የተጸናወተውና ስርአት የጠፋበትን የአምልኮ ስብሰባ አስብ። እግዚአብሔርን በሙሉ ልብህ እንዳታመልክ የተከላከለና ሁከትን የፈጠረ ምን ነገር ተፈጸመ? ለ) አንድ የአምልኮ ስብሰባ ሥርዓት ያለው ወይም የሌለው፥ ተገቢ የሆነ አምልኮ የሚታይበት ወይም ተገቢ ያልሆኑ አዋኪ ድምጾች ያለበት እንዲሆን የሚያደርጉትን ነገሮች ዝርዝር፡፡ 

ጳውሎስ የሰጠውን የተለያዩ ትእዛዛት ለመረዳት የሰጠውን መመሪያዎች አንድ በአንድ በመጥቀስ ማብራሪያ እንሰጥባቸዋለን። 

1. በኅብረት አምልኮዎች ሰዎች ለራሳቸው እንዴት እንደሚባረኩ ከማሰብ አልፈው ለሌሎች የሚገዳቸው መሆን ይገባቸዋል። የኅብረት አምልኮ እግዚአብሔርን ለማክበር ከመፈለግ ባሻገር እያንዳንዱ በቤተ ክርስቲያን ያለ ሰው በሚታነጽበት መንገድ የሚፈጸም መሆን አለበት (1ኛ ቆሮ. 14፡26)። 

በቆርንቶስ ቤተ ክርስቲያን የነበረው ችግር ብዙ ሰዎች በአንድ ጊዜ በልሳናት በመናገራቸው ከፍተኛ ግራ መጋባት ተፈጥሮ ክርስቲያኖች ሁሉ ወደ በረከት ከመምራት ይልቅ አንዳንድ አማኞች ይረበሹ እንደነበር ነው። ይህ እውነት በሕይወታችን በተለያዩ መንገዶች ተግባራዊ ይሆናል። 

ሀ. የተለያዩ ስብዕናዎችና የአምልኮ ዘይቤዎች ያሏቸው ክርስቲያኖች እርስ በርስ በአምልኳቸው በጋራ እንዲባረኩ መሥራት አለባቸው። በልሳናት መናገርንና የተፈታ ነፃነት ያለበትን የአምልኮ ዘይቤ የማይወዱ ሰዎች አገልግሎት በሕግና ሥርዓት ጠፍንገው አምልኳቸው ሕይወት ያለው እንዲሆን የሚፈልጉትን ሰዎች ነፃነት እንዳይጋፉ መጠንቀቅ አለባቸው። በአምልኳቸው በጌታ መደሰታቸውን ለመግለጥ የሚፈልጉ ሰዎችን መሸክም መቻል አለባቸው። ስሜታዊ ደስታ የሞላበትን አምልኮዎችን ሁኔታዎች የሚወዱ ክርስቲያኖችም ጸጥታና ዝግ ያለ መንፈስ ያለበትን አምልኮ የሚወዱ ሰዎችን ስሜት መጠበቅ አለባቸው። ስለዚህ በከፍተኛ ድምጽ ሃሌሉያና እልል፥ ወዘተ… በማለት በሙላት ፍላጐታቸውን በማሰብ ለመግለጽ ከመሞከር ይልቅ ጸጥተኛ የሆነ አምልኮን የሚወዱ እንዳይርቁ በመገንዘብ ከነፃነቶቻቸው አንዳንዶቹን መሥዋዕት ማድረግ አለባቸው። ሁላችንም አንድ አካል ስለሆንን ተቀዳሚ ትኩረታችን ሁላችንንም በሚያንጽ መንገድ እግዚአብሔርን እናመልክ ዘንድ አንዳችን ሌላችንን በመርዳት መሆን አለበት። አንድ ቡድን ለራሱ ደስታ በሚሰጠው መንገድ ብቻ የማምላክ ልቅ ነፃነት ሊፈልግ አይገባም። የሌላውን ቡድን ፍላጐቶችና መሻቶች ማክበር አለበት። 

ለ. ክርስቲያኖች በሚያመልኩበት ባሕል ላይ ሰዎች ፍላጐት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። ለምሳሌ ጠንካራ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርቲያን ባለችበትና ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ክርስቶስ የመጡ ሰዎች ባሉበት አካባቢ ባለች ቤተ ክርስቲያን ያለን ከሆንን ኦርቶዶክሳዊ የአምልኮ ሥርዓት ለመፈጸም ለሚፈልጉ ሰዎች መጠናከር ስንል የአምልኮ አቀራረባችንን ማስተካከል አለብን። ወይም ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩበት አካባቢ ያሉ ነገር ግን መሠረታቸው ሙስሊም ያልሆነ ክርስቲያኖች፥ ሙስሊሞች ክርስቲያን በሚሆኑበት ጊዜ አመላለካቸውን ከሙስሊም መሠረት እንደመጡ ክርስቲያኖች ሁኔታ አድርገው ማስተካከል አለባቸው። ምክንያቱም የአምልኮው አወቃቀርና ሰው የሚጸናበት ነገር በአመዛኙ የሚመሠረተው በግለሰብ መነሻ ወይም አመጣጥ ላይ ነው። ስለዚህ ሰዎች ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት የነበሩባቸው የብሔር ወይም የሃይማኖት ባሕላዊ ልዩነቶች የሚሰሙን እንዲሆንና በሚረብሻቸው ሁኔታ ሳይሆን ጸንተው በሚተከሉበት መንገድ ማምለክ እንዲችሉ የምናበረታታ መሆን አለብን። 

ጥያቄ፡ የተለያዩ ዓይነት የአመላለክ ዘይቤዎችን የሚመርጡ ሰዎች እርስ በርስ የሚከባበሩበትና የአመላለክ ዘይቤያቸውን ሁሉም በሚጠነክርበት መንገድ የሚጠቀሙበትን ሁኔታ ግለጽ። 

2. አምልኮ ብዙ ሰዎች መንፈሳዊ ስጦታዎቻቸውን ሊጠቀሙ በሚችሉበት መንገድ ነፃ መሆን አለበት (1ኛ ቆሮ. 14፡26)። ዛሬ ከምናካሂዳቸው በርካታ አገልግሎቶች በተቃራኒ ቀደምቷ ቤተ ክርስቲያን በአምልኮ ስብሰባዎች አባላት በሙሉ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የምታበረታታ የነበረች ትመስላለች። የአምልኮ ስብሰባዎችን የሚቆጣጠሩላቸው ሰባኪና ዘማሪ አልነበራቸውም። ሰዎች የሚፈልጉትን ለመዘመር ነፃ ነበሩ። ሌሎች ለጉባኤው የምስክርነት ቃል ያቀርቡ ነበር። ሌሎች ደግሞ የትንቢት ቃል ይናገሩ ወይም በልሳንም ይናገሩ ነበር። ብዙዎች እግዚአብሔር በሰጣቸው ስጦታዎች በአምልኮ ስብሰባዎች ላይ ይሳተፉ ነበር። ጳውሎስ ይህንን ገድቦ አያውቅም ነበር። እንዲያውም በቤተ ክርስቲያን የሚገኙ በሙሉ ንቃት የመሳተፋቸውን ጉዳይ እንዳበረታታ አምናለሁ። አብዛኛዎቹን የአምልኮ ስብሰባዎቻችንን ያራቆተው ነገር የጉባኤ መዝሙር ከመዘመር በስተቀር በስብሰባው የሚሳተፉ ሰዎች ጥቂት የመሆናቸው ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን ንቁ የአምልኮ ተሳትፎ በሚደረግበትና መንፈሳዊ ስጦታዎች በኅብረት አምልኮ በአገልግሎት ላይ በሚውሉበት ወቅት እያንዳንዱ ሰው ማስታወስ ያለበት የራሱን ጥቅም ከመፈለግ ይልቅ በቤተ ክርስቲያን የሚገለገሉት ሁሉ የሚታነጹበትን መንገድ መፈለግ እንዳለበት ነው። 

3. በልሳናት መናገር ቢበዛ ሦስት ሰዎች በየተራ እንዲናገሩ ተደርጐ በቁጥጥር ውስጥ ሆኖ መካሄድ አለበት። አንድ ሰው በልሳናት መናገር ካለበት በጉባኤው ያለ ሌላ ሰው መተርጐም አለበት። የማይተረጐም ከሆነ ግን ልሳን መነገር የለበትም (1ኛ ቆሮ. 1427-28)። ይልቁኑ በልሳን መናገር የሚፈልግ ሰው በጸጥታ በሚካሄድ ጸሎት ምናልባትም በመንፈሱ በልሳናት በመጸለይ እግዚአብሔርን ማምለክ ነበረበት። ከዚህ ክፍል በርካታ እውነቶችን ማውጣት ይቻላል። 

ሀ. ጳውሎስ በኅብረት አምልኮ ላይ በልሳናት መጸለይን አይከለክልም። ነገር ግን መቼና እንዴት እንደሚጠቀሙበት ጥብቅ መመሪያን ይሰጣል። በልሳናት በመናገር ላይ ከፍተኛ አትኩሮት ለማናደርግ ክርስቲያኖች አዲስ ኪዳን ከሚላቸው ነገሮች አልፈን በመሄድ በልሳናት መናገርን ሙሉ በሙሉ እንዳንከለክል እጅግ መጠንቀቅ አለብን። የሥነ መለኮት አቋማችን የእግዚአብሔር ቃል ከሚደግፈው ውጭ እንዳይወስደን መጠንቀቅ አለብን። 

ለ. ጳውሎስ የኅብረት ጸሎት በሚደረግበት ጊዜ ብዙ ሰዎች በአንድ ጊዜ በልሳን መናገራቸውን አይደግፍም። ጳውሎስ በልሳን መናገር በየተራ መደረግ አለበት ነው የሚለው። 

ሐ. ጳውሎስ በአንድ የአምልኮ ስብሰባ በልሳናት የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር ከሶስት እንዳይበልጥ ይወስናል። 

መ. ጳውሎስ የተነገሩ ልሳናት ሁሉ መተርጐም አለባቸው ብሎ አጥብቆ ይናገራል። ትርጉም ከሌለ በልሳናት መናገር የሚፈልገው ሰው ዝም ማለት አለበት። በዚህ ቦታ ያለው አባባል የሚያመለክተው በልሳናት የሚናገረውና የሚተረጉመው ሰው የተለያዩ መሆናቸውን ነው። ጳውሎስ በልሳን የሚናገረው ሰው እራሱ ይተረጉማዋል የሚል አሳብ ያለው ለመሆኑ ያጠራጥራል። ይህ ዐረፍተ ነገር በግልጽ የሚያመለክተው ሌላው ነገር በልሳናት መናገር በሚናገረው ሰው ሙሉ ቁጥጥር ሥር ያለ መሆኑን ነው። 

ሠ. በልሳናት መናገርን በተመለከተ አንድ ሰው በልሳናት የሚናገር ከሆነ አስቀድሞ አውቆት የሚተረጉም ሰው መኖር አለመኖሩ አስቀድሞ መታወቅ አለበት። ይህ ካልሆነ ተርጓሚ ላለመኖሩና በልሳናት የመናገር ህነቱን ሊጠቀምበት ስላመቻሉ በምን ያውቃል? 

መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ በልሳናት መናገር ለዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያን የሚሆን አይደለም ብለን ለመናገር ባንችልም ልሳናትን በኅብረት አምልኮዎች መጠቀምን አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ የተሰጡትን ትእዛዛት ለመጠበቅ እንደ ቤተ ክርስቲያን መሪነታችን መጠንቀቅ አለብን። በልሳን የመናገር ስጦታ ዛሬ በዘመናችን እንደሚሠራ ካመንን እነዚህን መመሪያዎች በሚገባ እንከተል። አለበለዚያም በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር እየተናገርን ነው እያልን መንፈስ ቅዱስ በልሳናት ስለመናገር የሰጠንን ትእዛዝ እንጥላለን። 

ጳውሎስ በኅብረት አምልኮ መንፈስ ቅዱስ መልእክቱን ለክርስቲያኖች የሚያስተላልፍበትን ሌላውን መንገድ ማለትም በትንቢት የመናገርን መመሪያ ቀጥሎ ያነሣል። ጳውሎስ በተደጋጋሚ ስለ ልሳናት እንዳቀረበው በልሳናት መናገር የጸሎትና የምስጋና ቋንቋ ነው። የሚደረገውም በቀጥታ ወደ እግዚአብሔር እንጂ ወደ ሰዎች አይደለም። ነገር ግን ሌሎች የሚረዱትና ክርስቲያኖችን በእምነታቸው የሚያንጻቸው ስላልሆነ ተቀዳሚ አገልግሎቱ ለግል ጸሎትና አምልኮ ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአገልግሎት ላይ መዋል ያለበት የተነገረው መልእክት ለአድማጮች ይደርስ ዘንድ ልሳኑን የሚተረጉም ሰው ሲኖር ብቻ ነው። 

ጳውሎስ በልሳናት ስለመናገር ገለልተኛ አመለካከት ያለው ይመስላል። በልሳናት መናገር ከፈለግህ መመሪያውን እስከተከተልክና የክርስቲያኖችን ሁሉ እምነት የሚገነባ ነገር እስካደረግህ ድረስ መልካም ነው። በልሳናት መናገር ግን ሰውን የበለጠ መንፈሳዊ አያደርግም። ከእግዚአብሔር ቃል ግልጽ የሆነውን ነገር በማምጣት ሰዎች ሁሉ በእምነታቸው እንዲገነቡ ማድረግ ከሁሉ ይሻላል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚደረጉ ነገሮች ሁሉ ሊኖር የሚገባው አመለካከት ይህ ነው። በልሳናት የሚናገሩትን መታገሥ መቻል እንደሚገባ ትእዛዝ ተሰጥቷል። ነገር ግን በልሳናት የሚናገሩ ሰዎች ደግሞ የተሰጣቸው ማስጠንቀቂያዎች አሉ። እነዚህም በልሳን በመናገራቸው እግዚአብሔርን እንጂ ራሳቸውን እንዳያከብሩ የተሰጡትን መመሪያዎች እንዲከተሉ ነው። 

ጥያቄ፡- በኅብረት አምልኮ ወቅት ሰዎች በላሳናት የተናገሩበትን ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለህ አስብ። ሀ) ከእነዚህ መመሪያዎች የትኞቹን ተከተሉ? ለ) ከእነዚህ መመሪያዎች ያልተከተሉት የትኞቹን ነው? ሐ) በልሳናት የሚናገሩ ብዙ ሰዎች እነዚህን ትእዛዛት መከተል የማይፈልጉት ለምንድን ነው? መ) በቤተ ክርስቲያን ስብሰባ ላይ ሰዎች በልሳናት መናገር ሲፈልጉና እነዚህን ትእዛዛት ግን ሳይከተሉ ሲቀሩ የቤተ ክርስቲያን መሪ ምን ማድረግ ያለበት ይመስልሃል? 

4. በኅብረት አምልኮ የትንቢት አጠቃቀም በጥንቃቄና በቁጥጥር የሚመራ መሆን አለበት (1ኛ ቆሮ. 14፡29-33)። የሚከተሉትን መመሪያዎች ልብ ብለህ አስተውል። 

ሀ. በአንድ ስብሰባ ላይ ትንቢት እንዲናገሩ የተፈቀደላቸው ሰዎች ቁጥር ከሶስት መብለጥ የሌለበት ይመስላል። ይህ በልሳናት ለሚናገሩ ሰዎች ከተሰጠው ቁጥር ጋር አንድ ዓይነት ነው። አንዳንድ ሊቃውንት የጳውሎስ አባባል ሦስት ሰዎች በመደዳ ይናገሩ ማለት ነበር ይላሉ። ይህ ከሆነም የተነገረው ትንቢት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መጣጣሙ ወይም ከሌላ ምንጭ የመጣ ስጦታ መሆኑ የሚፈተሽበት ጊዜ በየመሀሉ መኖር አለበት። ከዚያ በኋላ ሌሎች በዚህ ዓይነት መንገድ ትንቢታቸውን ማቅረብ ይቀጥላሉ። 

ለ. ትንቢት የሚናገሩ ሁሉ በየተራ መናገር ይጠበቅባቸዋል። 

ሐ. የሚያዳምጡ ሁሉ ደግሞ ሰውዬው የተናገረውን በጥንቃቄ መመዘን አለባቸው። አንድ ሰው የተቀበልኩት መልእክት አለኝ ስላለ ብቻ ልናምነው ይገባል ማለት አይደለም። የተናገረውን ልንመዝንና ልንፈትን እንደሚገባ በተደጋጋሚ ተነግሮናል። የምንመዝነውና የምንፈትነው ከምን እንጻር ነው? የመልእክቱ ባለቤት መንፈስ ቅዱስ ይሁን ወይም ሰው የምንለየው እንዴት ነው? መመዘኛችን መጽሐፍ ቅዱስ ነው። የተነገረው መልእክት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ጋር ጐን ለጐን የማይሄድ ከሆነ መልእክቱ ከመንፈስ ቅዱስ እንዳልሆነ እናረጋግጣለን። የጳውሎስ አባባል ምናልባት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ «መናፍስትን የመለየት» (1ኛ ቆሮ. 12፡10) ስጦታ ያላቸው ሰዎች ትንቢት ከእግዚአብሔር ከሆነ ለምን እንደሆነ ካልሆነ ደግሞ ለምን እንዳልሆነ እንዲናገሩ ዕድል ሊሰጣቸው እንደሚገባ ሳይሆን አይቀርም። 

በመልእክታቸው ላይ ሌሎች የሚሰጡትን የፍርድ አስተያየት በትዕቢት እምቢ ማለት እንደሌለባቸው ይህ ትንቢት የሚናገሩ ሰዎች ማስጠንቀቂያ ነው። እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚገኙ ለአንዳንዶች በተለይ ለመሪዎች ትንቢቱ ትክክል መሆኑንና ያለመሆኑን የሚለዩበት ሥልጣን ወይም መንፈስን የመለየት መንፈሳዊ ስጦታ እንዲሰጣቸው መገንዘብ አለባቸው። ትንቢት የሚናገር ሰው የተናገረው ትንቢት በሌሎች ይመዘን ዘንድ የማይፈቅድ ከሆነ መናገር የለበትም። 

መ. ሌሎች እየተናገሩ እንኳ መንፈስ ቅዱስ ቃሉን ለሰዎች መግለጡን ሊቀጥል ይችላል። መንፈስ ቅዱስ ለአንድ ሰው ከዚህ ቀደም ቃልን ተናገሮ ሌሎች ሰዎች እየተካፈሉ እያለ በዚህ ወቅት መንፈስ ቅዱስ ሌላ አዲስ መልእክት ለጉባኤው ቢሰጥ አዲሱ መልእክት ከመጀመሪያው መቅደም አለበት። አንድ ሰው እግዚአብሔር የሰጠውን መልእክት እያስተላለፈ እንኳ ሳላ ሌላ አዲስ ሰው መልእክት ቢኖረውና ማስተላለፍ ቢጀምር የመጀመሪያው ሰው መልእክቱን አቁሞ መቀመጥ አለበት (1ኛ ቆሮ. 14፡30)። ጳውሎስ ይህን መመሪያ እየሰጠ ያለው ምንም ዓይነት ሁከት ሳይኖር አምልኮው በሥርዓት እንዲካሄድ ሳይሆን አይቀርም።

ሠ. ሁላችሁም በየተራ ልትተነብዩ ትችላላችሁ። ይህ ዐረፍተ ነገር በሊቃውንት መካከል ሰፊ የሚያወያዩ ነጥቦችን አስነሥቷል። የጳውሎስ አባባል እያንዳንዱ ክርስቲያን ከመንፈስ ቅዱስ ትንቢትን የመቀበልና ለቤተ ክርስቲያን የመናገር ችሎታ አለው ማለት ነው? ይህ አሳብ ጳውሎስ ቀደም ብሎ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ለአንዳንድ ሰዎች እንደሚሰጥ ከተናገረው ጋር እንዴት ይታረቃል? (1ኛ ቆሮ.12፡29) ለዚህ አባባል ትርጉም የሚሆኑ ሦስት የተለያዩ አሳቦች ይሰጣሉ። 

1. አንዳንድ ሊቃውንት «እናንተ ሁላችሁ» ማለት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሰዎች በሙሉ ማለት ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ምንም ዓይነት ሰዎች ወንድ፥ ሴት፥ ባርያ ወይም ጌታ ወዘተ… መንፈሳዊ ስጦታው ያላቸው ሁሉ ማለት ነው ይላሉ። ይህ መንፈሳዊ ስጦታ በተወሰኑ ሰዎች ክልል የተገደበ ሳይሆን የዘር፥ የጾታ፥ የማኅበረሰብ ደረጃን ሁሉ አካትቶ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች የሚሰጥ ስለሆነ ስጦታዎች ያላቸው ሰዎች ሁሉ ለመተንበይ ዕድሉ ሊሰጣቸው ይገባል ማለት ነው ይላሉ። 

2. ሌሎች ሊቃውንት ደግሞ «እናንተ ሁላችሁ» የሚለው ቃል የትንቢት መንፈሳዊ ስጦታ ያላቸውን ሰዎች ሲሆን የጳውሎስ አባባል ይህ መንፈሳዊ ስጦታ ያላችሁ ሁሉ እነዚህን መመሪያዎች እስከተከተላችሁ ደረስ መተንበይ ትችላላችሁ ማለቱ ነው ይላሉ። 

3. ወይም ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ ከመንፈስ ቅዱስ ትንቢትን ለመቀበል ይችላሉ ማለቱ ነው። መንፈስ ቅዱስ በማንኛውም ሰው ልብ ሊናገር ስለሚችል የተነገረው ሰው መልእክቱን ለሌሎች ሊያካፍል ይገባል። ይህም ማለት ሁለት ዓይነት ትንቢቶች አሉ ማለት ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ነቢያት የታወቁ የመተንበይ መንፈሳዊ ስጦታዎች ያላቸው አሉ። እንደገና ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላሉ ሰዎች ሁሉ ክፍት የሆኑ ማንም ሊናገራቸው የሚችሉ ትንቢቶች አሉ። 

መጽሐፍ ቅዱስ ከሶስተኛው የትርጉም አሳብ ይልቅ የመጀመሪያውን ወይም ሁለተኛውን እንደሚደግፍ አምናለሁ። 

የተለያዩ ሰዎች ትንቢት በሚናገሩበት ጊዜ የመጨረሻው ግብ ሰዎች ሁሉ መመሪያ እንዲያገኙና እንዲበረታቱ ነው። ትኩረታችን መንፈስ ቅዱስ ይናገርባቸው ዘንድ ሰዎችን የመጠቀሙ ጉዳይ አይደለም። ዋናው ጥያቄ ሊሆን የሚገባው «ሰዎች እየተማሩና በእምነታቸው እየተገነቡ ናቸው ወይ» የሚል ነው። 

ሰ. የትንቢት ቃል በሚናገረው ሰው ሙሉ ቁጥጥር ሥር ያለ ነው። ሰውዬው ከራሱ ቁጥጥር ውጭ ሆኖ እንደ ሰመመን የሚናገርበት ሁኔታ አይደለም። በተመሳሳይ መንገድ በልሳናት መናገርም ሰው ከራሱ ቁጥጥር ውጭ የሚሆንበት ሁኔታ አይደለም። 

ይህ ክፍል በመንፈስ ቅዱስ ሥራና መንፈስ ቅዱስ መጠቀሚያ አድርጐ መልእክቱን በሚያስተላልፍበት ሰው መካከል ያለውን አስገራሚ ውጥረት ያሳያል። በልሳናት የመናገርንና የመተንበይን ስጦታ የሚሰጡ አጋንንትም ሰውን ይቆጣጠራሉ። ስሜቶቹን በበላይነት ይቆጣጠራሉ። በበላይነትም ተጽዕኖ ያደርጋሉ። መንፈስ ቅዱስ ግን ከሰውዬው ጋር አብሮ ይሠራል። 

መንፈስ ቅዱስ በልሳናት የመናገርና የመተንበይ ስጦታ በሚሰጠው ወቅት ሰውዬው አእምሮውን መቆጣጠሩን አያቆምም። ስለዚህ ሰውዬው መንፈስ ቅዱስ የትንቢት ቃልን እንደሰጠው ቢሰማውም እንኳ እራሱን ተቆጣጥሮ በሥርዓት መልእክቱን ያስተላልፋል። ከዚያ በኋላም የተናገረው መልእክት ይመዘን ዘንድ ተራውን ለመጠበቅ ፈቃደኛ መሆን አለበት። 

ሸ. መንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜ የሚሠራው ከእግዚአብሔር ባሕርይ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው። እግዚአብሔር የሥርዓተ አልበኛነት አምላክ አይደለም። ፍጥረታት በፍጹም ሥርዓት መመራት እግዚአብሔር የሥርዓት አምላክ መሆኑን ያሳየናል። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በእውነት የተገኘበትና በሙላት የሚገለጥባቸው የአምልኮ ስብሰባዎች ፍጹም ሥርዓት የሞላባቸው ናቸው። ሥርዓተ አልበኛነት ካለ መንፈስ ቅዱስ በዚያ ስብሰባ የለም ማለት ነው። ስለዚህ በምናመልክበት ጊዜ የአምልኮ ስብሰባችን ሥርዓት የሞላበት መሆኑን ማረጋገጥ አለብን። 

ነገር ግን ሥርዓት ምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠት የሚችለው ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትገኝበት ባሕል ነው። ለምሳሌ በኮሪያ ሁሉ ሰው በአንድ ጊዜ በአንድ ላይ የመጸለዩ ነገር በቁጥጥር ሥር የተያዘና ሥርዓታዊ ተደርጐ ይቆጠራል። በሌላ ባሕል ግን ሁሉ ሰው በአንድ ጊዜ ቢጸልይ ሥርዓት እንደጠፋና የእግዚአብሔርን ሰም ማሰደብ እንደሆነ ተደርጐ ይቆጠራል። 

ጥያቄ፡- ሀ) አንድ ክርስቲያን የትንቢት ቃል አለኝ ብሎ ሲናገር የሰማህበትን ሁኔታ ግለጽ። ከላይ የተመለከትናቸው የትንቢት ቃል ማቅረቢያ መመሪያዎች የተከበሩት ወይም የተጣሱት እንዴት ነው? ለ) ቤተ ክርስቲያን ለእነዚህ መመሪያዎች የተገዛች መሆኗን ለማረጋገጥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ሚና መጫወት የሚገባቸው ይመስልሃል? 

ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ. 14 ላይ በኅብረት አምልኮ ላይ ተግባራዊ የሚሆኑ ሁለት ስጦታዎችን ማለትም በልሳናት መናገርንና ትንቢትን ያወዳድራል። የመጀመሪያው በልሳናት መናገር ሲሆን የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሲታገሉበት የነበረ መንፈሳዊ ስጦታ ነው። ሚዛናዊ ባልሆነ መንገድ በልሳናት በመናገር ስጦታ መማረካቸው መንፈሳዊነታቸውን ሳይሆን ሥጋዊነታቸውን ያረጋገጠ ነበር። ለምን? በተቀዳሚ ውስጣዊ ዓላማቸው የተሳሳተ ስለ ነበር ነው። ከስጦታው ለራሳቸው ክብርን ማግኘት ፍላጐታቸው ነበር። ለክርስቶስ አካል ግድ አልነበራቸውም። በስጦታው በማገልገል ሁሉንም የመገንባት ፍላጐት አልነበራቸውም። በመንፈሳዊ ሕይወት ያለመብሰል ተቀዳሚ ማስረጃ ስስታምነት ነው። 

ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የትንቢት ጉዳይ ነበር። ጳውሎስ ይህን መንፈሳዊ ስጦታ ከሁሉ የላቀ ስጦታ ምሳሌ አድርጐ አልተጠቀመበትም። የኅብረት አምልኮአችን አካል ሊሆኑ የሚገባቸው ሌሎች መንፈሳዊ ስጦታዎች የሉም ማለቱም አይደለም። የእውቀት፣ የጥበብ፡ የማስተማር ወዘተ… ስጦታዎች የኅብረት አምልኮአችን አካል ናቸው። ነገር ግን ትንቢት የተጠቀሰው በልሳናት ከመናገር ለምን እንደሚሻል ምሳሌ እንዲሆን ነው። ትንቢት ወደ ሌሎች ለመድረስ የተሻለ መሣሪያ የሆነው ያልዳነን ሰው ከኃጢአቶቹ ጋር በመጋፈጥ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣው ስለነበር ነው። ክርስቲያኖች የተባለውን ነገር ተረድተው በእምነታቸው ስለሚታነጹበት ትንቢት ለማነጽ የተሻለ መሣሪያ ነበር። ትንቢት የመጣው ግለሰብን ሳይሆን በአካሉ ውስጥ ያሉትን በሙሉ ለመገንባት ነበር። ስለዚህ ሌሎችን ለመገንባት የሚጥር ስለሆነ በልሳናት መናገር ሳይሆን ትንቢት ለመንፈሳዊ ብስለት የተሻላ አመልካች ነበር። 

ጳውሎስ አንድ ሌላ የሚያሳስበው ነገር ነበረው። በልሳናት መናገር ይሁን ትንቢት ይሁን ወይም ሌላ ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን ልምምድ በሥርዓት የመደረጉ ጉዳይ ነበር የሚያሳስበው። የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች የእግዚአብሔርን ባሕርይ የሚያንጸባርቁ መሆን አለባቸው። የእግዚአብሔርን ባሕርይ ሲያንጸባርቁ ለክርስቶስ ስም ክብርን ያመጣሉ። 

ጥያቄ፡– በዚህ ሳምንት ትምህርት የመጀመሪያው ቀን የተገለጸውን ሁኔታ ተመልከት። የቤተ ክርስቲያን መሪ ሆነህ በአንድ የቡድን ስብሰባ ላይ ሰዎች በልሳናት መናገር ሲጀምሩ ምን ታደርጋለህ? ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ማድረግ እንዳለብህ የሚያስተምረው ምንድን ነው ብለህ ታምናለህ? ለ) ቡድኑ ልምምዳቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንዲያጣጥሙ ለማድረግ ምን እርምጃ ትወስዳለህ? ሐ) በቡድኑ በልሳናት ስለመናገር ምን ምን ለየት ያሉ ነገሮችን ታስተምራለህ?

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.