መንፈሳዊ ስጦታ (1ኛ ቆሮንቶስ 13)

አንድ ሰው እንዲህ ይላል «በልሳናት የመናገር ስጦታ አለኝ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በምፈልገው መንገድ እጠቀምበት ዘንድ እንድትተውኝ እፈልጋለሁ። የመንፈስ ቅዱስ ሥራን እንዴት ልትቆጣጠሩ ትችላላችሁ? ሌላው ሰው ደግሞ «እኔ የዚህ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ነኝ። ልሳን ሁከት ፈጣሪ ነው የተማርነውም እንደዚህ ስላልነበረ በልሳናት እንድትናገር ልፈቅድልህ አልችልም» ይላል። ስለዚህ በልሳናት መናገር በአምልኮ ስብሰባ አንዱ ክፍል እንዲሆን በሚፈልጉና ሊቆጣጠሩት በሚፈልጉ መካከል ክርክሩ ይቀጥላል። ሁለቱም ከፊል እውነት አላቸው። ነገር ግን የየራሳቸውን መንገድ ብቻ ከፈለጉ ቤተ ክርስቲያን በዓመታት ውስጥ እንደሆነችው ትከፋፈላለች። 

በካሪዝማቲክና ካሪዝማቲክ ባልሆኑ ክርስቲያኖች በሚደረጉ ክርክሮች ከስጦታዎች ሁሉ በላይ የሆነ ብዙ ጊዜ የሚጐድል አንድ ነገር አለ። ይህ የጐደለ ነገር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላለ አንድነት ሲባል የራስን ፍላጐትና አመለካከት በፈቃድ የሚያስተው ፍቅር ነው። 

ጥያቄ፡- ስለ መንፈስ ቅዱስ ወይም ስለ አምልኮ አይነት የአሳብ ልዩነት በሚያሳዩ ክርስቲያኖች መካከል የፍቅር ጉድለት መኖሩን የምትመሰክርባቸውን ምሳሌዎችን ጥቀስ። ለ) ያለ መግባባት የሚያስከትላቸውን ውጤቶች የፍቅር አመለካከት እንዴት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊለውጥ ይችል እንደነበር ግለጽ። 

ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 13 አንብብ። ሀ) ያለ ፍቅር ከንቱ መሆናቸው የተነገረላቸውን የተለያዩ መንፈሳዊ ስጦታዎች ዘርዝር። ከቁ 4-7 የተገለጸው የፍቅር ባሕርይ መንፈሳዊ ስጦታዎችን በመሳሰሉ ነገሮች ያለመግባባት ሲኖር የሚጠቅመው እንዴት ነው? ሐ) እንደሚያልፉ የተጻፈላቸው ነገሮች ምን ምን ናቸው? ጳውሎስ ይህን ያለው ለምን ይመስልሃል? መ) ጳውሎስ በ 1 ና 2 ላይ እውነትን የሚያውቀው በከፊል ብቻ እንደሆን በገለጸበት ወቅት የነበረው ዝንባሌ ምንድን ነው? ይህ ዝንባሌ በሌላ ሰው ላይ የተለየ አመለካክት ሲኖረን የሚጠቅመው ለምንድን ነው? 

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ እጅግ ውብ ምዕራፎች አንዱ 1ኛ ቆር. 13 ነው። ብዙ ጊዜ በሠርግ በዓል ላይ ይጠቀሳል። ነገር ግን በዚህ ምዕራፍ ላይ የተጠቀሰው በመንፈሳዊ ስጦታዎች ላይ በተለይም በልሳን በመናገር ስለሚፈጠር ያለመግባባት ነው። ይህንን ምዕራፍ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላሉ ልዩነቶች ተግባራዊ ብናደርገው በቤተ ክርስቲያን ባሉ ሰዎች መካከል ያለው አብዛኛው መከፋፈል ወደ ፍጻሜ ይመጣ ነበር። ስለዚህ ምዕራፍ ብዙ ነገሮችን ማለት እንችላለን። ነገር ግን በመንፈሳዊ ስጦታዎች አንጻር ስናየው የሚከተሉትን እውነቶች መማር እንችላለን። 

1. መንፈሳዊ ስጦታ ምንም ያህል ታላቅና አስደናቂ ቢሆንም በፍቅር መንፈስ የሚደረግና በአማኞች መካከል ፍቅርን የሚጠብቅ ካልሆነ በስተቀር በእግዚአብሔር ዓይን ምንም ዋጋ የለውም። ያለ ፍቅር ልሳናት የመላእክት ቋንቋ ቢሆኑም እንኳ የማይጠቅም ባዶ ጩኽት ናቸው። ጳውሎስ በልሳናት የጀመረው የቆርንቶስ ክርስቲያኖች ችግር ያለው በዚህ ጉዳይ ላይ ስለነበር ሳይሆን አይቀርም። ትንቢትና ተአምራት ሰዎችን ምንም ያህል የሚያስገርሙ ቢሆኑም እንኳ ያለ ፍቅር በእግዚአብሔር ዓይን ፊት ዋጋ የላቸውም። በሕይወታችን ከሁሉ የላቀውን ነገር ብንሰጥና ሕይወታችንን መሥዋዕት እስከማድረግ ለወንጌል ብንሞት እንኳ የፍቅር ሕይወት ካልኖርን በእግዚአብሔር ዓይን አንዳችም ክብር የለውም። መንፈሳዊ ስጦታዎቻችንን በፍቅር ካልተጠቀምንባቸው ብንጠቀምባቸውም እንኳ የተሰጡበትን ዓላማ ስተናል ማለት ነው። የክርስቶስን አካል በመገንባት ይልቅ አፍርሰነዋል ማለት ነው። ይህ በሌላ አባባል በገላ. 5፡22-23 የምናገኘው የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ከወመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች የላቀ ነው ማለት ነው። 

2. ጳውሎስ የሚናገረው መንፈሳዊ ስጦታዎችን ያለ ፍቅር መጠቀም ስጦታዎች የሚያስገኙትን ጥቅም ስለማስቀረቱ ብቻ ሳይሆን ለጦታውን በተሳሳተ መንገድ የሚጠቀመውን ሰው በአሉታዊ መንገድ እንደሚጐዱ ነው። ያላ ፍቅር የሆነ ልሳን ባለ ስጦታውን እንደሚንሿሿ ባዶ ጸናጽል ያደርገዋል። ትንቢት፥ ተአምራትን ማድረግ ወይም መሥዋዕት ሆኖ ማለፍ ያለ ፍቅር ሰውን ወደ ባዶ ቀፎነት ይለውጣል። ጳውሎስ የሚለው በልሳናት በመናገር ችሎታችን ክብር ብናገኝ፥ እውነትን ብናውቅ፥ ተአምራትን ብናደርግ መንፈሳዊ የሚያደርገን ይህ ነው ብለን ካሰብን ሙሉ ለሙሉ የተሳሳትን እንደምንሆን ነው። መንፈሳዊ ስጦታዎች በራሳቸው ስለ ሰው መንፈሳዊ ሕይወት አንዳችም ነገር አይናገሩም። አንድ ሰው በእውነት መንፈሳዊ የመሆኑ ማስረጃ ፍቅር ብቻ ነው። መንፈሳዊ ስጦታዎች የክርስቶስን አካልም ሆን የግለሰብ ክርስቲያን ሕይወትን እንዲጠቅሙ ከተፈለገ በፍቅር መዋሃድ አለባቸው። 

3. ፍቅር ለሚለው ትርጉም የግሪኩ ቃል «ኦጋፔ» ነው። ጳውሎስ ስላ ፍቅር የሚሰጠውን ስናነብ መንፈስ ቅዱስ ለክርስቲያኖች የሚሰጠው ፍቅር እንጂ ተፈጥሮአዊ ፍቅር እንዳይደላ በቀላሉ እንረዳለን። የመንፈስ ፍሬ የተባለውም ለዚህ ነው። ይህ ፍቅር ከራስ ወዳድነት ተላቅቆ ለሌሎች ድነት (ደኅንነት) እራስን መስጠት ነው። ፍቅር በመሠረቱ ስሜት ሳይሆን በገዛ ፈቃድ እራስን ለሌላው መስጠት ነው። ፍቅር የሚወደደው ሰው መልካምና ተፈቃሪ እንዲሆን አይጠብቅም። ነገር ግን የኢየሱስ ትእዛዝ ስለሆነ ሌላን ሰው ለመውደድ መወሰን ነው። ኢየሱስ ለእያንዳንዳችን ኃጢአት በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ያሳየው አይነት ፍቅር ነው (ዮሐ 13፡34-35/ 1ኛ ዮሐ 3፡16)። 

4. ጳውሎስ ፍቅርን በሚገልጥበት ወቅት ፍቅር ባለአለመግባባት መካከል እራሱን እንዴት እንደሚገልጥ ለማሳየት ትኩረት አድርጓል። የእግዚአብሔር መንፈስ ያልተግባባነውን ሰው ወደ ብስለት እስኪያመጣ ድረስ የሚታገሥ ነው። የበለጠ የሚታይና የሚደነቅ ስጦታ ባላቸው ሰዎች አይቀናም። የእርሱ ስጦታ ከሌሎች እንዴት የላቀ እንደሆነ በማሰብ አይመካም። ሰዎች ሳይረዱትና ከእርሱ ጋር ሳይግባቡ ሲቀሩ አይቆጣም። በአለመስማማት መካከል ያለአግባብ ቢከሰስና ወይም የሚያስቆጣ ንግግር ቢደረግበትም አይበሳጭም። ፍቅር ያልተግባባናቸው ሰዎች ንጹሕ ውስጣዊ መነሻ አሳብ እንዳላቸውና ልክ እንደ እኛ እግዚአብሔርን ለመከተል ፈልገው እንዳደረጉት በመረዳት ላለመግባባት ስፍራ ይነሳል። 

5. መንፈሳዊ ስጦታዎች ጊዜያዊ ሲሆኑ ፍቅር ግን ዘላለማዊ ነው። ሊቃውንት በ1ኛ ቆሮ. 13፡8-11 ባለው አጠቃላይ አሳብ ላይ ይስማሙበታል። ትንቢት በልሳናት መናገርና እውቀት የሚቆሙበት ጊዜ ይመጣል። ግን የሚቆሙት መቼ ነው? ጳውሎስ «ፍጹም የሆኑና፡ «ፍጹም ያልሆኑ» የሚላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ስለዚህ ጉዳይ የተለያዩ አሳቦች አሉ። 

በመጀመሪያ ካሪዝማቲክ ያልሆኑ ብዙ ክርስቲያኖች እንደሚያምኑት ፍጹም ያልሆነው የሚለው ቃል የሚያመላክተው የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን መልክ የያዘችባቸውን ጊዜያት ነው። ጳውሎለ ቤተ ክርስቲያን ወደተሳሰረ እንድነት እየገባች እንደሆነ ያውቅ ነበር። የአመራርና የመሠረተ እምነት ትምህርት ይዞታም ገና እያደገ ነበር። ከሁሉም በላይ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ገና አልተጠናቀቁም ነበር። ፍጹም የሆነችውና የበሰለች ቤተ ክርስቲያን የተገኘችው ከብሉይ ኪዳን ወደ አዲስ ኪዳን የተደረገው ሽግር ከተፈጸመ በኋላ እና አዲስ ኪዳን ከተጻፈ በኋላ ነበር። ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈውን ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ካገኙበት ጊዜ ጀምሮ በልሳናት የመናገር፥ የትንቢትና የእውቀት ስጦታዎች አያስፈልጋቸውም ይላሉ። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እነዚህን ስጦታዎች አዲስ ኪዳን ተጠናቆ ከተጻፈበት ከ100 ዓ.ም ጀምሮ መሰጠቱን አቁሟል ይላሉ። አዲስ ኪዳን ተጠናቅቆ ከተጻፈበት ጊዜ ጀምሮ እነዚህ ስጦታዎች አያስፈልጉንም፤ ምክንያቱም የሚያስፈልጉን ትንቢቶችና እውቀቶች በሙሉ በእጃችን ባለው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ ይላሉ። 

መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ያለቀበትን ጊዜ የፍጹምነት ጊዜ አድርገው የሚቆጥሩት ለምንድን ነው? ካሪዝማቲክ ያልሆኑ ክርስቲያኖች ከካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች ጋር ካሏቸው ልዩነቶች አንዱ ትንቢትን የሚረዱበት መንገድ ነው። የትንቢት ስጦታ እስካሁን እየሰራ ነው ብለን ካመንና ይህ ትንቢት በኢሳይያስ በኤርምያስ፥ ወይም በጳውሎስ እንደነበረው ዓይነት ሥልጣን አለው ካልን መጽሐፍ ቅዱስ ገና አልተጠናቀቀም ማለታችን ነው። የትንቢት ስጦታ ያላቸው ሰዎች እያንዳንዳቸው አዲስ መጻሕፍትን መጻፋቸውን መቀጠል አለባቸው ማለት ነው። ይህ ደግሞ መናፍቃን የሚያደርጉት ነው (ለምሳሌ—የይሖዋ ምስክሮች፥ ሞርሞናውያን፥ የባሃኢ ተከታዮች)። ስለዚህ ይህ ስጦታ ቢያንስ በመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ጸሐፊዎች ዘንድ እንደነበረው ዓይነት መንፈስ ቅዱስ ያረፈበት የትንቢት ስጦታ አክትሟል ብለው ያስተምራሉ። ያሳሰባቸው ነገር ትልቅ ዋጋ ያለው ቢሆንም በዚህ ዘመን የሚነገሩት ትንቢቶች የተጻፈውን የእግዚአብሔርን ቃል ያህል ሥልጣን እንደሌላቸው ግልጽና እንዲያውም በእግዚአብሔር ቃል የመፈተናቸው አስፈላጊነት የማያወላዳ ቢሆንም ጳውሎስ የተናገረው ፍጹምነት ግን ይህ አይደለም። 

በሁለተኛ ደረጃ፣ ጳውሎስ የሚናገርለት ፍጹምነት ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ከተመለሰ በኋላ የሚሆን ሳይሆን አይቀርም። እስከዚያ ድረስ መንፈስ ቅዱስ ምንም ያህል የእውቀት ስጦታን፥ የትንቢት ስጦታ፥ ወይም በልሳናት የመናገር ስጦታን ቢሰጠንም እንኳ እውቀታችን የተወሰነ መሆኑ አይቀሬ ነው። ያለን እውቀት ከፊል ብቻ ይሆናል። በመረዳታችን ወደ ፍጹም ሙላት የሚመጣው ኢየሱስን ፊት ለፊት ስናየው ብቻ ነው። በዚያን ጊዜ የእውቀት፥ የትንቢትና ወይም በልሳናት የመናገር ስጦታ አያስፈልጉንም። ፍጹምነት የሚያመላክተው ለለመጨረሻው ጊዜያት ነው ብለን ካመንን ልናስታውሳቸው የሚገቡ ሁላት እውነቶች ይኖራሉ። የመጀመሪያው፥ የእውቀት፥ የትንቢትና በልሳናት የመናገር ስጦታዎች እንዳለፉ የሚያመለክት ግልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክንያት አናገኝም። ጳውሎስ እነዚህ ስጦታዎች ከቤተ ክርስቲያን ይወሰዳሉ የሚል አመልካች አሳብ አልተናገረም። ያተኮረበት ነገር እነዚህ ስጦታዎች መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጠው ከብዙዎቹ ስጦታዎች መካከል የሚገኙ እንጂ ብቸኛ ስጦታዎች እነርሱ ብቻ አይደሉም በሚለው አሳብ ነው። እነዚህ ስጦታዎች ሁሉን ነገር ለማወቅ የሚያስችሉን አለመሆናቸውን አበክሮ ተናግሯል። 

በሦስተኛ ደረጃ፥ ጳውሎስ እውቀታችን በከፊል ነው ስላለ የትሕትና መንፈስ ሊኖረን ይገባል። ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ለምሳሌ ካሪዝማቲክ በሆኑትና ባልሆኑት መካከል በተላይ መሠረታዊ የእምነት ትምህርትን አስመልክቶ እንዳለው ዓይነት ያለመግባባት ሊኖረን ይችላል። በዚህ ጊዜ በጉዳዩ ላይ ያለን እውቀት ከፊል መሆኑን ከተረዳን ሌላው ወገን የሚናገረውን ለማድመጥ ፈቃደኞች ልንሆንና የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን እንዴት እንደሚመለከት ለመረዳት ጥረት ልናደርግ ይገባል። ይህም ቤተ ክርስቲያን ሳትለያይ የተለያዩ የሥነ-መለኮት ትምህርቶችንና የተለያዩ አሳቦችን እንድታስተናግድ ይረዳታል። በዚህ ዓይነት ሰዎች ግጭት ሳይፈጥሩና ሳይጣሉ የፍቅር ግንኙነትን ጠብቀው ለመኖር ይችላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ነገሮችን በምንረዳበት መንገድ አለመስማማት ስሕተት አይደለም። ከእኛ በአሳብ ለሚለዩት ሰዎች ፍቅርና አክብሮት ከሌላን ግን ስሕተት ነው። ይህንን በምንልበት ጊዜ ግን ትምህርቶችን ሁሉ መፈተንና መጽሐፍ ቅዱስ ከሚለው ውጭ ያሉትን ትምህርቶች በግልጽ መቃወም እንዳለብን የተጻፈውን ትእዛዝ የማክበር ሚዛንን መጠበቅ እንዳለብን ሳይዘነጋ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ትእዛዝ ውጪ ያሉ ትምህርቶች እንዳይሰጡ መከላከል አለብን። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ባልተብራሩ መሠረታዊ የእምነት ትምህርቶች ላይ ከእኛ ጋር የማይስማሙትን መታገሥ አለብን። 

ሕይወት ስትጠቃለልና ስንሞት ወይም ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ ሲመጣልን የሚቀጥሉት ሦስት ነገሮች አሉ። የእግዚአብሔር ልጆች ያደረገን እምነት፥ እግዚአብሔር ተስፋ የገባልንን እንድንቀበል ዋስትና የሚሆንልን ተስፋና በእኛና በእግዚአብሔር፥ እንደገና እርስ በርሳችን በክርስቶስ እንዳሉ ወንድሞችና እህቶች ሆነን በቋሚ ግንኙነት እንድንተሳሰር የሚያደርገን ፍቅር ናቸው። ከሁሉ የሚበልጠው ቀን ለዘላለም ቋሚ ሆኖ የሚኖረው ይህ የፍቅር ግንኙነት ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ በቆሮንቶስ 13 ስለ ፍቅር ያስተማረውን ተግባራዊ ብናደርግ በቤተ ክርስቲያኖቻንና በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ካሉ ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት እንዴት ይሆን ነበር? ለ) ፍቅር ከመንፈሳዊ ስጦታዎች ሁሉ የላቀ መሆኑን በራስህ ቋንቋ በአጭሩ ግለጽ።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: