በልሳናት ስለመናገር ተጨማሪ ጉዳዮች (ክፍል 1)

ጥያቄ፡- ሀ) በቆሮንቶስ የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ በዘመናችን ከሚገኙ አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ጋር አወዳድር። እንዴት ይመሳሰላሉ? ለ) ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከሰጣቸው ትምህርቶች የተማርካቸውን ጠቃሚ ነገሮች ጥቀስ። 

አንድ ድርጊት የሚያስከትለው አጸፋዊ ምላሽ አለ። ይህ ከሳይንስ ሕጐች አንዱ ነው። ይህ ስለ ሰብዓዊ ተፈጥሮም የሚሠራ እውነት ነው። አንድ ሚዛናዊ ያልሆነ ድርጊት ወደ ሌላ ሚዛናዊ ያልሆነ ድርጊት የሚወስድ አጸፋዊ ምላሽ አለው። አንዲት ቤተ ክርስቲያን ከሚገባ በላይ ወግ አጥባቂነትን የምትከተልና መንፈሳዊ ኃይል የሚጐድላት ከሆነ በመጨረሻ የምታመራው የማይታይ ድንቃ ድንቅ ነገሮችን ወደሚያሳድድ ጭልጥ ያለ ስሜታዊነት ነው። ይህ ደግሞ በበኩሉ ወግ አጥባቂ ከሆኑ ቤተ ክርስቲያኖች የሚሰነዘር፥ ሌላ ብርቱ የተቃውሞ አጸፋዊ ምላሽን ያስከትላል። ይህ ዑደት እየቀጠለ በመሄድ ክርስቲያኖች እየተፋጩ አብያተ ክርስቲያናት ይከፋፈላሉ። 

ይህን የድርጊቱን አጸፋዊ የድርጊት ዑደት በእውነት የሚሰብር ብቸኛው መንገድ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መመላለና ምን ማድረግ እንዳለብን እግዚአብሔርን መጠየቅ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ያልተሰጡ ትምህርቶችን ሰዎች ላይ እንዳንጭን ቁርጥ አቋም ሊኖረን ይገባል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ያልተከለከሉ ልምምዶችን እንዳያደርጉ ሰዎችን ከማሰናከልም መጠንቀቅ አለብን። እያንዳንዱ ሰው ስላ አቋሙ በእግዚአብሔር ፊት መልስ ይሰጣል። (2ኛ ቆሮ. 5፡10) ሌላው ክርስቲያን የእኛ ሳይሆን የሕያው እግዚአብሔር አገልጋይ ነው። 

ስለ መንፈስ ቅዱስ ባደረግነው ጥናት የመንፈስ ቅዱስን አጠቃላይ አገልግሎት ስትኩረት ውስጥ ማስገባት እንዳለብን አበክረን ተናግረናል። በመንፈስ ቅዱስ አንድ አገልግሎት ላይ በምናተኩርበትና ያንን አገልግሎት እንደ መንፈስ ቅዱስ ሥራ በምንቆጥርበት ማንኛውም ጊዜ ሚዛናዊነትን እናጣለን። ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች በተለይ ደግሞ በልሳናት ስላመናገርና ስለ ትንቢት በዝርዝር በማጥናታችን የትኩረት አድማሳችንን የመዘንጋት አደጋ አለብን። መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጣቸው በርካታ የተለያዩ አገልግሎቶች አንዱ ለእግዚአብሔር ልጆች መንፈሳዊ ስጦታዎችን መስጠቱ ነው። መንፈስ ቅዱስ ለክርስቲያኖች ከሚሰጣቸው በርካታ ስጦታዎች አንዱ በልሳናት መናገርን ነው። ስለዚህ በመንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳናት በመናገር ላይ ባተኮርን ቁጥር ሰፊውን ገጽታ እንዳንዘነጋ መጠንቀቅ አለብን። 

በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን እንደነበረው በዚህ ዘመን በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ስለ ትንቢት፥ በልሳናት ስለ መናገርና ስለ ፈውስ መንፈሳዊ ጦታዎች በርካታ ግራ የሚያጋቡ ውዥንብሮች አሉ። እነዚህ ውዥንብሮች ቤተ ክርስቲያንን እየከፋፈሉና የኢየሱስን ስም እያሰደቡ ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነዚህ ስጦታዎች የሚናገረው ምንድን ነው ብለን መጠየቅ አለብን። 

ዛሬ በልሳናት የመናገር መንፈሳዊ ስጦታ ላይ አተኩረናል። በሚቀጥለው ሳምንት የትንቢት የፈውስና ተአምራትን የማድረግ ስጦታዎችን እንመለከታለን። ለእነዚህ ትምህርቶች በየትኞቹም ጉዳዮች ለመረዳት የማያሻሙ መንገዶችን የሚያሳዩ ወሳኝ መልሶችን አላቀርብም። ይልቁኑ . ጥያቄዎችን በማንሣት ልዩነት የሚታይባቸው ትምህርቶች በተንሰራፉበት በዚህ ዘመን ልናስታውሳቸው የሚገቡ ጉዳዮችን እጠቁማለሁ። ከሁሉ በላይ የሚያስፈልገው ነገር መልሱ አለኝ ብሎ ማሰብ አለመሆኑን አስታውስ። እግዚአብሔርን የሚፈሩ ክርስቲያኖች በጉዳዮች ለረጅም ጊዜ ስለተከራከሩ ብቸኛው መልስ ያላው እኛጋ አለመሆኑን በቅንነት መቀበል አለብን። ሆኖም ግን እራሳችንን ከሁለቱም የከረረ አመለካከቶች መጠበቅ አለብን። በልሳናት መናገር ሁልጊዜ ከአጋንንት ነው የሚለው የከረሩ አመለካክት አደገኛ ነው። አዎን ሰይጣን በልሳናት መናገርን መክፋፈልን ለማምጣት አንዳንዶችንም ከቀንበሩ ሥር ለማድረግ ሊጠቀምበት ይችላል። ይህ ማለት ግን ልሳናት ሁሉ ከሰይጣን ናቸው ማለት አይደለም። በልሳናት መናገር ከሁሉ የላቀ ስጦታና ለመንፈስ ቅዱስ ህልውና ማስረጃ ነው የሚለው ሌላው ጽንፍም እንደ መጀመሪያው አደገኛ ነው። በሁለቱ ጽንፎች መካከል በነህነት ለመለማመድ ሰፊ ዕድል አለ። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች ፍቅርና መቻቻል ሊሠለጥኑባቸው ይገባል። ከእኛ የተለየ አመለካከት ያላቸውን ክርስቲያኖች ለንቃወም ክጠላታችን ክለይጣን ጋር ወግነን እንዳንገኝ መጠንቀቅ አለብን። እርስ በርስ እንደ ጠላት መተያየት የአንድ አገር አየር ኃይል ከጠላት ጋር በሚዋጋበት ጦርነት የራሱን ወገን ሠራዊት እንደ ጠላት የመቁጠሩን ያህል የከሩ ነው። 

የተለያዩ ቡድኖች አንዱ በሌላው አቋም ላይ ያለው ዋንኛው ሥጋት ምንድን ነው? 

ነገሮች፥ ከሚገባ በላይ በሆነ መንገድ ወይም ሚዛን ባጣ ሁኔታ ሊፈጸሙ ሰዎች አምርረው ይቃወማሉ። ለምሳሌ አብዛኛዎቹ መድኃኒቶች በበቂ መጠን ካልተወሰዱ የሚሰጡት ውጤት መናኛ ስለሚሆን ወሳጆቹ በሽታቸው ብዙ ሳይቆይ ይመለስባቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ከሚፈለገው መጠን በላይ ከተወሰዱ መርዛማነታቸው አይሎ እስከ መግደል ይደርሳሉ። ስለዚህ መድኃኒት የሚፈለገውን ውጤት ያስገኝ ዘንድ መጠኑ ተላከተ በትክክለኛው ጊዜ ለተፈቀደ የጊዜ ርዝመት ብቻ መወሰድ አለበት። መድኃኒትን በመጠኑ አስበልጦም ሆነ አሳንሶ መውሰድ ምንም መድኃኒት ካለመውሰድ የበለጠ አደገኛ ነው። የሚጠበቀው ውጤት ሳይጨበጥ ሲቀር መድኃኒቱን አሳንሶ ለመውሰድም ሆነ አብዝቶ ለመውሰድ የሞከረው የሚኖራቸው አጸፋዊ ምላሽ አንድ ዓይነት ነው። በትክክለኛው መጠን በመውሰድ ፈውስ ሊያመጣላቸው ይችል የነበረውን መድኃኒት ይጠራጠራሉ። 

በሚዛናዊነት እጦት የሚከሰተው ተመሳሳይ አጸፋዊ ድርጊት ካሪዝማቲክ የሆኑትንም ሆነ ያልሆኑትን እኩል ይጐዳል። የካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች የአንዳንድ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ትክክለኛነት የማይቀበሉ ወግ አጥባቂ ክርስቲያኖችን አምልኮና ሕይወት እንደዚሁም የአንዳንዶቻቸውን ዝቅተኛ ሕይወትና ኃይል ይመለከታሉ። በዚህ መንገድ አምልኮአቸውን የሚያካሄዱትን ሁሉ ሕይወትና ኃይል አልባ አድርገው ይቆጥሩአቸዋል። ካሪዝማቲክ ያልሆኑትና ከመንፈሳዊ ስጦታዎች አንዳንዶችን የሚጠራጠሩ ሁሉ የእግዚአብሔርን ሥራ እንደሚገድቡና የመንፈስ ቅዱስን ሥራ እንደሚያፍኑ ያስባሉ። በልሳናት መናገርና ትንቢት ምን ስሕተት አለው? ብለው ይጠይቃሉ። እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ከሰዎች ጋር ኅብረት ማድረግ አይችልምን? ይላሉ። ቅድመ-ግምታችን እግዚአብሔር በአንድ የተወሰነ መንገድ አይሠራም ወደሚል እምነት የሚመራን ከሆነ በሕይወታችን ባሉ የተወሰኑ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ እግዚአብሔር እንዳይመራን ራሳችንን እያራቅንና ከሚያንጹን ነገሮችም እየተገላልን ነው ማለት ነው። በአምልኮአችን ወቅት የእግዚአብሔርን ህልውና ማወቅ ይሳነናል ደግሞም መንፈስ በሕይወታችን ሊሠራ ያለውን በማጥፋት ሙት በሆነ አክራሪነት ውስጥ እንዘፈቃለን። ስለዚህ መንፈሳዊ መሆናችንን ለማሳየት፥ እራሳችንንም ከመንፈሳዊ ሙትነት ለመከላከል ሰዎች ሁሉ በልሳን እንዲናገሩ፥ በአምልኮ ጊዜ እጆቻቸውን ወደ ላይ በማንሣት እንዲያመልኩ፥ ሃሌሉያ እያሉ እንዲጮችና በመሰብሰቢያው መተላለፊያ መንገዶች ወድቀው በኃይለኛ ሳቅ እንዲንፈራፈሩ እንጠብቃለን። ሙት አምልኮን የመቋቋም ዝንባሌ ካሪዝማቲኮችን ቤተ ክርስቲያንን ወደ ሚከፋፈሉና የእግዚአብሔርን ክብር ወደሚያርቁት አክራሪ ልምምዶች ብዙ ጊዜ ይገፋፋቸዋል። 

ካሪዝማቲክ ያልሆኑትም ካሪዝማቲኮች በሚያሳዩት ሚዛን አጥነት ላይ አጸፋዊ ምላሽ ይሰነዝራሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰዎች ወድቀው ሲንፈራፈሩና እንደ ውሾች ሲያባርቁ የምናየው በየትኛው ቦታ ነው? ይላሉ። እንደዚህ ዓይነቱን ልምምድ በቴሊቪዥን ሲመለከቱ ካሪዝማቲኮች በሙሉ እንደዚህ ናቸው ብለው ያስባሉ። ካሪዝማቲክ ያልሆኑ ክርስቲያኖችን የሚያሳስባቸው ነገር ለልሳናትና ትንቢት ስጦታዎች ባለው ከፍተኛ ጉጉት በእነዚህ ስጦታዎች በኩል የሚመጣው የእግዚአብሔር መልእክት ከመደበኛው የእግዚአብሔር ቃል ጋር እኩል ተደርጐ ወደ መቆጠር ያመራል የሚል ነው። ከእግዚአብሔር ቃል ጋር እኩል ከሆኑ ደግሞ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚሰጣው ተጨማሪ መገለጥ እንደቀጠለ ነው ማለት ነው። ይህ ማለት መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር በተሰጠን መገለጥነቱ በቂ አይደለም ማለት ነውን? ለሕይወትና ለተቀዴሰ ኑሮ የሚበቃ ነገር እግዚአብሔር አልሰጠንምን? (2ኛ ጴጥ. 1፡3) መጽሐፍ ቅዱስ በቂ ከሆነ ተጨማሪ መገለጥን ከእግዚአብሔር ለምን እንፈልጋለን? ሰዎች ከእግዚአብሔር መገለጥ እንዳገኙ ሲናገሩ የሚናገሩትን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እኩል ማድረጋቸው አይደለምን? «የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲህ ይላል» በማለት ካሪዝማቲኮች መልእክት ሲያመጡ ይህንን ማለታቸው አይደለምን? የሚያመጡት ቃል በእርግጥ የእግዚአብሔር ቃል ከሆነ እንዳንጽፈውና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እኩል እንዳናደርገው የሚያግደን ምንድን ነው? ይህ ከሆነ ደግሞ የአንዳንድ መናፍቃንን ስሕተት መድገም አይሆንምን? የእዚህን መገለጦች ትክክለኛነት የምናረጋግጠው እንዴት ነው? በሰዎች ስሜታዊ ቁጥጥር ሥር እንዳንወድቅ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ማተኮር ብቻ አይሳላንም? ሰመጽሐፍ ቅዱስ መላኪያዎች ለመኖር በመወሰንና ትክክለኛ የመሠረታዊ እምነት ትምህርትን በመያዝ ከስሕተት ትምህርቶች ተጠብቆ ጤናማ መሆን የተሻለ አይደለምን? 

ጥያቄ፡– ሀ) እነዚህ ሁሉ ሥጋቶች ዋጋ ያላቸው የሚሆኑት በምን በምን መንገድ ነው? ለ) እነዚህ ሁለቱ ሥጋቶች የካሪዝማቲኮች ሆኑ ካሪዝማቲክ ያልሆኑት እምነት ከመሆን ይልቅ በጉዳዮቹ ላይ ከሚገባ በላይ ከሚሰነዘር አጸፋዊ ምላሽ የመነጩ የሚሆኑት በምን መንገድ ነው? 

በልሳናት ስለመናገር ክርስቲያኖች ያሏቸው የተለያዩ አቋሞች ምንድን ናቸው? 

እስካሁን ድረስ በጥናታችን የተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ በልሳናት ስለመናገርና ስለ ትንቢት ምን እንደሚያስተምር ነው። ሆኖም ግን፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሻሚ ነገሮች አሉ። እንደ እብዛኛዎቹ ነገሮች በልሳናት በመናገር ላይም በርካታ የተለያዩ አመላካክቶች አሉ። ነገር ግን በመሠረቱ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን የሚፈሩ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን የሚወዱ ክርስቲያኖች የበሰሉ ክርስቲያኖች ከሚከተሉት ሦስት እቋሞች እንቶን ይይዛሉ። 

1. በልሳናት የመናገር መንፈሳዊ ስጦታ ዘመኑ አልፏል ። እግዚአብሔር ይህንን ስጦታ በዛሬ ዘመን ላሉ ሰዎች አይሰጥም። እግዚአብሔር፥ በአዲስ ኪዳን ዘመን ይህን ስጦታ የሰጠበት ምክንያት መሢሐቸውን ኢየሱስን አንቀበልም ላሉት የእስራኤል ሕዝብ የፍርድ ምልክት እንዲሆን ነበር። እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን አዲስ ሕዝብ እንዳደረገና በመካከላቸው እንደሚኖር አይሁዶች ግን የኢየሱስን ወንጌል ካልተቀበሉ እንደሚፈርድባቸው የሚያሳይ ምልክት ነበር። ልሳን በተለይ በምልክትነት የሚያገለግለው ለእስራኤል ሕዝብ ነበር። ዛሬ ግን በምልክትነት አያስፈልግም። ይህ ስጦታ አያስፈልገንም። ስለዚህ እግዚአብሔር ዛሬ ላቤተ ክርስቲያን ይህን ስጦታ መስጠት አቁሟል። 

ይህ አመለካከት ያላቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች በልሳን የመናገር ስጦታ አሁን አይሠራም ብለው ለምን እንደሚያምኑ ሌሎች ምክንያቶችን ይጨምራሉ። በልሳናት መናገር ከሐዋርያት ሞት በኋላ አገልግሎቱ ከቤተ ክርስቲያን ወዲያውኑ ቆሟል ብለው ይናገራሉ። ከዚያ በኋላ የተለማመዱትን ሁሉ ቤተ ክርስቲያን መናፍቃን በማላት ፈርጃቸዋለች። እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ባለፉት 19 ክፍለ ዘመናት ትላልቅ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሰነበሩባቸው ዘመናት እንኳ የልሳናት ጉዳይ ትኩረት የተሰጠበት ጊዜ አልነበረም። ስለዚህ በልሳናት ለመናገር ይህ ሁሉ ጉጉት ዛሬ የተፈጠረበት ምክንያት ምንድን ነው? አንዳንዶች ደግሞ 1ኛ ቆሮ. 13፡8 እና 19 ሰማመልከት ፍጹም የሆነው ሲገለጥ ልሳናት ይቀራሉ ይላሉ። ፍጹም የሆነው የሚለው ቃል የሚያመለክተው ከሐዋርያት ሞት በኋላ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ተጽፈው መጠናቀቃቸውን እንደሆነ ያስባሉ። ሐዋርያት እንደሞቱ አዲስ ኪዳን ብሎም መጽሐፍ ቅዱስ ስለተጠናቀቀና ልዕለ-ተፈጥሮአዊ መገለጦች ስላላስፈለጉ ልሳናት አከተሙ። 

በእኔ አመለካከት ይህን አቋም ለመቀበል ያለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ እጅግ አነስተኛ ነው። በልሳናት የመናገርን አክራሪነት ለመቋቋም የሚሰነዝሩት አጸፋዊ ምላሻቸው ነው፥ ልሳናት ዛሬ አይሠሩም የሚለውን አመለካከታቸውን ለማረጋገጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምክንያታችን እንዲፈላልጉ የሚገፋፋው። 

2. በልሳናት መናገር እግዚአብሔር ለአንዳንድ ክርስቲያኖች ዛሬም ቢሆን የሚሰጠው መንፈሳዊ ስጦታ ነው። ሆኖም ቀን ከመንፈሳዊ ስጦታዎች አንዱ እንጂ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ምልክት አይደለም። ስለዚህ አመለካከት የተለያዩ ዓይነቶች አሉት። 

ሀ. አንዳንዶች እንደሚያምኑት የዚህ ዘመን በልሳናት የመናገር ልምምድ ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ልምምድ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ነው። እግዚአብሔር በሥራ ላይ የመሆኑ ምልክት ነው። ሰዎች በወንጌል እንዲያምኑ ከወንጌል ጋር የተቆራኘና የእግዚአብሔር ኃይልም የሚገለጽበት መሆን ይገባዋል። 

ለ. ሌሎች ደግሞ እግዚአብሔር የወንጌል ስርጭት እንዲሳካ ኃይሉን ለመግለጽ የሚጠቀምበት መሣሪያ ከመሆኑም በላይ እግዚአብሔር ቃሉን ለአንዲት አጥቢያ ቤተ-ክርስቲያን የሚገልጽበት አንድ መንገድ ነው ብለው ያምናሉ። 

ሐ. አሁንም ይህ እቋም ያላቸው ሌሎች ደግሞ በልሳናት መናገር ከላይ ለተጠቀሱት ዓላማዎች ተግባር ላይ እንደሚውል ባይክዱም እንካ ተቀዳሚ ዓላማው ቀን የጸሎት ቋንቋ መሆን ነው የሚሉ አሉ። ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ያመልኩ ዘንድ የሚያነሣሣ መሣሪያ ነው ይላሉ። በአምልኮ መሣሪያነቱ ሁሉም ክርስቲያኖች ሊፈልጉት የሚገባ ነው። 

3. በልሳናት መናገር የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ምልክት ሊሆን አንድ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ እንዳለው ማረጋገጫ ነው። ይህን አመለካከት የሚያራምዱት አካላት ከድነት (ከደኅንነት) ልምምድ በኋላ ልማዳዊ የክርስቲያኖችን ልምምድ ተከትሎ የሚመጣ ዳግመኛ መንፈሳዊ ልምምድ አለ ብለው ያስተምራሉ። ይህ ሁላተኛ ልምምድ «ዳግም በረክት» በመባል ይታወቃል። ይህ ክርስቲያን በሕይወቱ እንድ ጊዜ የሚለማመደው፥ ወደ ከፍተኛ መንፈሳዊ ልምምድ የሚሸጋገርበትና በረከትን የሚቀበሉ ሁሉ ደግሞ ስልሳን መናገርን የሚቀዳጁበት ልምምድ ነው። ይህ በልሳናት ስለ መናገር ዓይነተኛው የጰንጠቆስጤ ሥነ መለኮት ነው። በልሳናት የመናገር የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በሁለተኛው አመለካከት (ሀ፥ ላ፥ ሐህ ሥር በተጠቀሱት ሦስት መንገዶች፥ አገልግሎት ላይ እንደሚውል ይስማማል። ብዙ ጊዜ በሐዋ. 2 ና በ1ኛ ቆሮ. 12-14 በተጠቀሱት በልሳናት የመናገር ልምምዶች መካከል ልዩነት ያደርጋሉ። በሐዋ. 2 የምናገኘው በልሳናት መናገር የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ማረጋገጥና ክርስቲያኖች ሁሉ ሊሹት የሚገባ ሲሆን በ1ኛ ቆሮ. 12 በመንፈሳዊ ስጦታነት የተጣቀሰው በልሳናት መናገር ግን የራሱ ልዩ ዓላማ ያላውና ለአንዳንድ ክርስቲያኖች ብቻ የሚሰጥ ነው። 

እንደገና በእኔ አመለካክት ለዚህ እቋም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠን ድጋፍ በጣም አነስተኛ ነው። መንፈሳዊነታቸውን በልሳናት በመናገር ለማረጋገጥ የሚፈልጉ አስቀድመው የወሰኑትን አቋማቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር የበለጠ እንዲስማማ ከመቅረጽ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋገጥላቸው ዘንድ ለማስገደድ የሚሞክሩ ናቸው። 

ጥያቄ፡– ከእነዚህ አመለካከቶች የትኛውን ታምናለህ? ለምን?

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

1 thought on “በልሳናት ስለመናገር ተጨማሪ ጉዳዮች (ክፍል 1)”

Leave a Reply

%d bloggers like this: