በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ማረጋገጫዎች

ጥያቄ፡– የማያቋርጥ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ያለበትን ሕይወት የሚኖር ሰውን አስብ። የመንፈስ ቅዱስ ሙላት አለው ብለህ እንድታስብ የሚያደርግ ምን ተግባር ይፈጸማል? 

መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ እንዴት እንደምንሞላ እይናገርም። ይልቁኑ መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ ከመሞላት የሚያግዱንን ነገሮች የሚጠቁሙ አራት ትእዛዛት ይሰጠናል። መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ክርስቲያኖች መሙላት ይፈልጋል። የእግዚአብሔር ዕቅድ እንደዚያ ነው። 

እያንዳንዱ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ይችላል። ነገር ግን የሚያሳዝነው ያላማቋረጥ በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ሕይወትን የሚኖሩ ሰዎች ጥቂቶች መሆናቸው ነው። ወይም ደግሞ ምናልባት በመንፈስ ቅዱስ የመሞላትን ማረጋገጥ አሳስተን እናቀርባለን። አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ መሞላቱን እንዴት እናውቃለን? ቀጥሎ ለመንፈስ ቅዱስ ሙላት ማረጋገጥ የሚሆኑ እውነቶችን በዝርዝር እናቀርባለን። 

1. የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ 

ጥያቄ፡- ገላ. 5፡16-26 አንብብ። ሀ) «በመንፈስ ስንመላለስ» ምን ይፈጸማል? ለ) በኃጢአታዊ ተፈጥሮና በመንፈሳዊ ተፈጥሮ መካከል ያለው ግንኙነት የተገለጠው እንዴት ነው? ሐህ ኃጢአታዊው ተፈጥሮ እንዴት ተገልጿል? መ) የመንፈሳዊ ተፈጥሮ ባሕርያት ምንድን ናቸው? ሀ) ክመንፈስ ቅዱስ ጋር እርምጃ ችንን ጠብቀን የምንኖረው እንዴት ይመስልሃል? ሠ) ገላ. 5፡22-23 ያለውን በቃልህ ለማጥናት ጊዜ ውሰድ። እዚህ «የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ» ተብለው የተጠቀሱት ባሕርያት የሕይወትህና! ከሌሉች ጋር ያለህ ግንኙነት ዋና ክፍል የሚሆኑበትን መንገድ እንዲያሳይህ እግዚአብሔርን በጸሎትህ ጠይቀው። 

መጽሐፍ ቅዱስ በዓለማችን ላይ ሦስት ዓይነት ሰዎች እንዳሉ ያስተምረናል። በመጀመሪያ፥ ያልዳኑ ሰዎች አሉ። በዚህ ውስጥ የሚካተቱት በኢየሱስ ክርስቶስ ያላመኑ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታቸው ኖሮ የማያውቅ ለዘላለም ፍርድ የተጠበቁ ሁሉ ናቸው። በኃጢአታቸው የሞቱ ሰዎች ሁሉ በዚህ ውስጥ ይካተታሉ። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ በመሆናቸው ምክንያት ታላላቅ ነገሮችን ለማድረግ ቢችሉም እንኳ ሕይወታቸውን የሚኖሩት ከእግዚአብሔር ውጭ ስለሆነ ከሚያደርጓቸው ነገሮች የትኞቹም ድነት (ደኅንነት)ን ሊያስገኙላቸው አይችሉም። ጽድቃቸው ሁሉ እንደ «መርገም ጨርቅ» ነው (ኢሳ. 64፡6)። 

በሁለተኛው ዓይነት የሚፈረጁት ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ክርስቲያኖች ናቸው። ሕይወታቸውን ለኢየሱስ የሰጡና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚኖሩ ናቸው። ባሕርያቸውና ሕይወታቸው የተለወጡ ናቸው። በመንፈስ ቅዱስ ስለተሞሉ ክርስቲያኖች ወደፊት የበላጣ እናጠናለን። 

በሦስተኛ ዓይነት የሚፈረጁት ሰዎች ሥጋዊ ክርስቲያኖች ናቸው። እነዚህ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል የወሰኑ ክርስቲያኖች ናቸው። የሚኖሩት ግን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አይደለም። ነገር ግን በራሳቸው ኃይል ይመላለሳሉ። ስለዚህ ሕይወታቸው የማያምን ሰው ሕይወትን ይመስላል። «የኃጢአታዊው ተፈጥሮን ተግባራትን» መፈጸማቸውን አያቆሙም። ደግሞም እግዚአብሔርን በማያስከብር ሕይወት ይመላለሳሉ። ጳውሎስ ክርስቲያን ነን እያሉ ነገር ግን ያለሟቋረጥ በኃጢአታዊ ተፈጥሮ የሚኖሩትን በጥብቅ ያስጠነቅቃል። ያለማቋረጥ በኃጢአታዊ ተፈጥሮአቸው , የሚኖሩ ሰዎች «የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም» ይላል። የእግዚአብሔር ልጆች የመሆናችን ማረጋገጥ በአፋችን የምንለው ነገር ሳይሆን በየዕለቱ የምንኖረው ሕይወት ነው። በተወሰነ የጊዜ ክልል ውስጥ «የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ» በሕይወታችን ካልታየ አስቀድሞም ቢሆን መንፈሳዊ ሕይወት ኖሮን እንዴሆነ መጠየቅ እጅግ ተገቢ ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) ከራስህ ሕይወት ሦስቱንም ዓይነት ሰው እንዴት እንደነበርክና እንደሆንክ ግለጽ። ለ) አሁን ያለህበትን ሕይወት ከሦስቱ በላቀ ሁኔታ የሚገልጸው የትኛው ነው? 

በመንፈስ የተሞላን ክርስቲያኖች ከሆንን ነገሮች የተለዩ ይሆናሉ። ከኃጢአታዊ ተፈጥሮ ጋር ያለንን ትግል የምንቀጥል ቢሆንም እንኳ በይበልጥ ያለማቋረጥ በመንፈሳዊ ተፈጥሮአችን እንኖራለን። የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ውጫዊ ተግባራችንን ይለውጣል። ሆኖም ግን የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ይበልጥ በተለያዩ ውስጣዊ ባሕርያት ይረጋገጣል። ያላ መንፈስ ቅዱስ አንዳንድ ውግዊ ለውጦችን ማሳየት እንችላለን (ለምሳሌ የአልኮል መጠጥ ማቆም፥ ከአንድ በላይ የነበሩን ሚስቶቻችንን መተው፥ ወዘተ)። እነዚህ በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ማረጋገጣ ላይሆኑ ይችላሉ። የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ማረጋገጫ ሙሉ በሙሉ የመለወጥ ባሕርይ ነው። ጳውሎስ እነዚህን ለውጦች «የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ» በማለት ይጠራቸዋል። 

ጳውሎስ ለክርስቲያኖች በመንፈስ የተሞላ ሕይወት ማረጋገጫን ሲነግራቸው በፈለገ ጊዜ በክርስቶስ አካል ውስጥ ከሌሎች ጋር ያሏቸውን ግንኙነቶች የሚነካውን ጉዳይ ለማሳየት ወደ ልቦናዎቻቸውና ወደ ዝንባሌዎቻቸው አመለከተ። በልሳናት የመናገር ፥ተአምራትን የማድረግ :የመተንበይ ወይም ሌሎች የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን ጉዳይ አልተናገረም። ይልቁኑ ውስጣዊ ስለሆነ፥ ለተፈጥሮአዊው ሰው ፈጽሞ ስለ ማይቻል ነገር ነው የተናገረው። የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ላመንፈስ ቅዱስ ሙላት ከሁሉ የላቀ ማስረጃ ነው። 

የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ኢየሱስ በምድር ላይ በተመላለሰበት ወቅት የነበረው ባሕርይ ግልጽ መግላጫ ነው። የመንፈስ ቅዱስ ዋና ግቡ ኢየሱስን እንድንመስል ማድረግ በመሆኑ በመንፈስ የተሞሉ ክርስቲያኖች ምን እንደሚመስሉም ያሳየናል። በእነዚህ ቁጥሮች የሚከተሉትን እጅግ አስፈላጊ እውነቶች መመልከት እንችላለን። 

1. ዘጠኙ ባሕርያት የመንፈስ ቅዱስ «ፍሬ» በመባል ይታወቃሉ። የመንፈስ ቅዱስ «ፍሬዎች» እይደሉም። አንዱን እያደረግን ሌላውን ላለማድረግ እንችልም። አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ በሚሞላበት ጊዜ እነዚህ ባሕርያት በተለያየ ደረጃ በሕይወቱ ይኖራሉ። 

2. «የመንፈስ ቅዱስ» ፍሬ በመባል ይጠራሉ። የሰው ሥራ አይደሉም። ይልቁኑ መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚሠራው ሥራ ውጤት ናቸው። ብዙ ሰዎች በጣም በሞከርን ቁጥር የበለጠ ፍቅር ይኖረናል፤ የበለጠ ደስተኛ እንሆናለን፥ ወዘተ… ይላሉ። የሰው ጥረት ግን ይህንን ፍሬ አያመጣም። በሰው ሕይወት ውስጥ በሚሠራ መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሚመጣ ውጤት ነው። ስለዚህ ይህ ፍሬ በሕይወታችን እንዲረጋገጥ ከፈለግን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ባለን ትክክለኛ ግንኙነት መሥራት መቻል አለብን። 

3. የተጠቀሱት ዘጠኝ ባሕርያት ከሰው ልብ በመውጣት በተግባር የሚታዩ ይሆናሉ። በተቀጻሚ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነቶች የሚረጋገጡ ውስጣዊ ባሕርያት ናቸው። 

ጥያቄ፡- ሀ) በሥጋ ሥራዎች (ገላ. 5፡19-2) የተሞላ ሕይወትና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን አወዳድር። ለ) በሥጋ ፈቃድ እየተመላለስክ እንደሆነ የሚያሳዩ በሕይወትህ የሚፈጸሙ የተለያዩ ድርጊቶችን በምሳሌነት ጥቀስ። ሐ) በመንፈስ ቅዱስ መሞላት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬን እንዴት እንደሚያመጣ ከግል ሕይወትህ የተለያዩ ምሳሌዎችን ስጥ። 

2. መንፈሳዊ ስጦታዎች ለመንፈሳዊ አገልግሎት 

መንፈሳዊ ስጦታዎች በሰው ሕይወት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ የመኖሩ ውጤቶች ናቸው። እነዚህ መንፈሳዊ ስጦታዎች አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ባይሞላም እንኳ ሊኖሩት ይችላሉ። ለምሳሌ በልባችን መንፈሳዊ ትዕቢት እያላ እንኳ በልሳን መናገር እንችላለን። ስለዚህ መንፈሳዊ ስጦታዎችን መለማመድ ብቻ በራሱ በመንፈስ ቅዱስ ላመሞላታችን ማረጋገጥ አይደላም። ሆኖም ግን እነዚህን መንፈሳዊ ስጦታዎች ያለማቋረጥ በተገቢ ሁኔታ ለእግዚአብሔር ክብርን የሚያመጣና የክርስቲያንን ኅብረት በሚነባ መንገድ መጠቀም የሚቻለው በመንፈስ ቅዱስ በመሞላት ብቻ ነው። መንፈሳዊ ስጦታዎቻችንን ስንጠቀም በመንፈስ ቅዱስ ካልተሞላን ግን ብዙም ሳይቆይ ሰዎች የተሳሳቱ ነገርች ከሕይወታችን ማውጣት ይጀምራሉ። ውስጣዊ አመለካከታችን ንጹሕ ስለማይሆን በክርስቶስ አካል መካከል ፀብንና መከፋፈልን እናመጣለን። በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሰው በመንፈስ ቅዱስ መሞላቱን ሌሎችን በትሕትና በማገልገሉና የክርስቶስን አካል አንድነት በመጠበቁ ይገልጻል። 

3. በመንፈስ ቅዱስ መማር 

ሰዎች በአእምሮ እውቀት ችሎታቸው ሊገነዘቡ የሚችሉት የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ደረጃ አለ። ሆኖም ግን ጥልቅ የሆነ መረዳት፥ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር የመረዳትና በሕይወት ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው በመንፈስ ቅዱስ ላተሞሉ ሰዎች ብቻ ነው። ጥልቅ፥ ሕይወትን የሚለውጡ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሚገላጡት እርሱ ሕይወቱን በሚሞላበት ሰው ዘንድ ብቻ ነው (1ኛቆሮ. 2፡12፡3፡1፥ 2፤ 1ኛ ዮሐ 2፡20፥ 26-27)። አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ለማንበብና ለመረዳት ቢችልም እንኳ መንፈስ ቅዱስ በሚናገርበት ወቅት በጥሞና ካላደመጠ እውነቱ ወደ ልቡ ጠልቶ አይገባም። ላሕይወቱ ግልጽ የሆነ መመሪያን አይቀበልም። በሌላ በኩል ግን አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ከተሞላና እርሱን የሚያደምጥ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ ከሚገኙ ነገሮች ሁሉ ጣፋጭና ውድ ይሆንለታል። መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ለመገኘት፥ ለእኛ ላመናገርና እኛን ለመምራት የሚጠቀምበት ዋና መሣሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ይሆናል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመንፈስ ቅዱስ እማካይነት ጥብቅ የሆነ ግንኙነት የሚኖረን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ጊዜ የምንወስድ ከሆነ ነው። ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ቃል በማንበብ ሐሜት የማያደርጉና መንፈስ ቅዱስ እነርሱን ይናገርና ሕይወታቸውን ይለውጥ ዘንድ የማይጠቀምበት ከሆነ ምክንያቱ በመንፈስ ቅዱስ ያላመሞላታቸው ይሆናል። 

የመንፈስ ቅዱስ ህልውና ወይም ሙላት ራሱን የሚያረጋግጥባቸው ሌሎች በርካታ መንገዶች አሉ። በመንፈስ ቅዱስ በምንሞላበት ጊዜ እምልኮአችንና ለእግዚአብሔር የምንሰጠው ክብር ይለወጣል (ኤፌ. 5፡18 20)። በስግብግብነት የተሞላው ፍላጐታችን በሕይወታችን ገዥ ስለማይሆን አንዳችን ለሌላችን እራሳችንን ለማስገዛት አስተሳሰባችን ይለወጣል (ኤፈ. 5፡21)። በመንፈስ ቅዱስ በምንሞላበት ጊዜ እግዚአብሔር ለሕይወታችን ወዳለው ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ እንመራለን። 

ጥያቄ፡- ሀ) ከላይ በተመለከትናቸው መንገዶች የተገለጠው የመንፈስ ቅዱስ ሙላት በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ እጅግ አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት ምንድን ነው? ላ) ብዙ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ቢሆኑና በሕይወታቸው እዚህን ሦስት ማረጋገጫዎች የሚያሳዩ ቢሆኑ ኖሮ 1ቤተ ክርስቲያንህ በምን ዓይነት መንገድ ትለወጥ ነበር?

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: