እግዚአብሔር ፈውስን የሚሰጥባቸው የተለያዩ አሠራሮች

ጥያቄ፡- ያዕ. 5፡14–15 አንብብ። ሀ) በዚህ ክፍል በምታገኘው መሠረት የፈውስን ቅደም ተከተሎች አስፍር። ለ) ይህ የፈውስ አሠራር ለመፈወስ ኃይል እንዳላቸው ከሚናገሩት ሰዎች አሠራር ጋር እንዴት ይሄዳል? 

እግዚአብሔር አሁንም ይፈውሳልን? አዎን። እግዚአብሔር በቀደሙት ዘመናት ተአምራትን እንዳደረገ ዛሬም ፈውስን የሚያካትቱ ተአምራትን ያደርጋል። እግዚአብሔር የፈውስ ሥራውን አቁሟል ማለት ስሕተት ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር ሁልጊዜ ይፈውሳል ማለትም ስሕተት ነው። ኢየሱስ በከነዓን የነበሩትን በሙሉ እንዳልፈወሰና ደቀ መዛሙርትም በአገልግሎታቸው የፈወሱት ያገኙትን ሰው ሁሉ እንዳልሆነ ዛሬም እግዚአብሔር ሰውን ሁሉ እንደሚፈውስ ማስረጃ ማቅረብ እንችልም። 

ታዲያ እግዚአብሔር ዛሬ ፈውስን የሚያደርግበት ተለምዶአዊ መንገድ ምንድን ነው? ስንታመም ወይም የምንወደው ሰው ሲታመም ወይም በቤተ ክርስቲያን ያለ አንድ ሰው ሲታመም ምን ማድረግ አለብን? አዲስ ኪዳን የሚከተሉትን ነገሮች ያስተምራል። 

1. በመጀመሪያ ስትታመም እግዚአብሔር ይፈውስህ ዘንድ ጸልይ። እግዚአብሔር እየቀጣህ ያለው ያልተናዘዝኸው ኃጢአት እንዳለ እራስህን መርምር። ፈውስን እስኪሰጥህ ድረስ በትዕግሥት በመጠበቅ እግዚአብሔር በዚህ በሽታ ውስጥ ሊያስተምርህ የሚፈልገው ነገር ምን እንደሆነ ጠይቀው። በሽታ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ልጆቹን ለማስተማር የሚጠቀምበት መሣሪያ ነው። 

2. ወደ ሐኪም ወይም በሕክምና ሙያ ወደ ሠለጠነ ሰው በመሄድ ምርመራ አድርግ። እግዚአብሔር ያለ ምንም መድኃኒት ሊፈውሰን ቢችልም እንኳ አእምሮአችንን በመጠቀም ውሳኔ ልናደርግና ተገቢውን የሕክምና እርዳታ ሊሰጠን ወደሚችል ሰው ልንሄድ ይገባናል። ለሕክምና ባለሙያዎች ችሎታንና ሥልጣናን የሰጠ እግዚአብሔር መሆኑን አስታውስ። እግዚአብሔር ፈውስን ለማምጣት መሣሪያው አድርጐ ሊጠቀምባቸው ይችላል። ነገር ግን እምነታችን በመድኃኒት ወይም በሰዎች ሳይሆን ፈውስን ለማምጣት በሰዎች በሚሠራ በእግዚአብሔር እንደሆነ መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ 

3. የሕክምና እርዳታ ፈውስን ሊያመጣ ካልቻላ ስያዕ. 5 ላይ ያለውን መመሪያ ተከተል። የመፈወስ ስጦታ አለን ወደሚሉ ሰዎች አትሂድ። በምንታመምበት ወቅት እግዚእብሔር በቀጥታ ያላመለከተውን መንገድ ከመከተል መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን መከተል ይሻላል። 

ሀ. የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ጥራ። 

ለ. ከሽማግሌዎች ጋር በመሆን በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ ትሆን ዘንድ ራስህን መርምር። ብዙ በሽታዎች በቀጥታ የኃጢአት ውጤት ባይሆኑም እግዚአብሔር ያለመታዘዛችንን ለመቅጣት በሽታዎችን አንዳንድ ጊዜ ወደ ሕይወታችን ያመጣል። ኃጢአትን ካደረግን እግዚአብሔር ይፈውሰን ዘንድ ከመጠየቃችን በፊት ተናዝዘን ንስሐ መግባት አለብን። 

(ማስታወሻ፡–በሽታ ሁሉ የኃጢአት ውጤት ነው ከማለት እጅግ ተጠንቀቅ። ብዙ ጊዜ አይደለም። እግዚአብሔር ክፉዎችን የሚቀጣበት ጊዜ ቢኖርም እንኳ ብዙ ጊዜ እስከ መጨረሻው የፍርድ ቀን ድረስ ሳይቀጡ ይቆያሉ። ደግሞም እግዚአብሔር ኃጢአትን የሚያደርጉ ክርስቲያኖች አንዳንድ ጊዜ ቢቀጣም እንኳ ሁልጊዜ አይቀጣም (መዝ. [73]፡1-17)። እግዚአብሔር ልዩ በሆነ መገለጥ ችግሩን ካልጠቆመ በስተቀር በሰው ሕይወት ውስጥ ንስሐ ያልተገባበት ኃጢአት እንዳለ የሚያውቁት ግለሰቡና እግዚአብሔር ብቻ ናቸው። 

ሐ. ኃጢአትህን ከተናዘዝክ ወይም ሽማግሌዎች ነፃ መሆንህን ካረጋገጡልህ በኋላ ሽማግሌዎች ዘይት ቀብተው ይጸልዩልህ። ለምን ዘይት መቀባት አስፈለገ? ብዙ ክርስቲያኖች በዘይት ውስጥ የተለየ ነገር እንዳለ ስለሚያስቡ ዘይት መኖር አለበት፤ በዘይቱና እርሱ በሚወክለው ነገር አማካኝነት ፈውስ ያመጣል ያላሉ። ይህ ግን ሊሆን የሚችል ነገር አይደለም። በጥንት ጊዜያት ከሁሉ የተሻለና የታወቀ መድኃኒት ዘይት ነበር። በመዝ 23 ላይ እግዚአብሔር ራሳችንን በዘይት የሚቀባ እረኛ መሆኑ የተነገረው ለዚህ ነው። መቀባቱ ፈውስን ለማምጣት የታለመ ነበር። ዘይት መጠቀም ስሕተት ባይሆንም እንኳ ያዕቆብ የሚናገረው ጸሎትን ለበሽታው ተስማሚ ከሆነ መድኃኒት ጋር የማቀናጀት ጉዳይ እንደሆነ አምናለሁ። 

መ. ሽማግሌዎች ዘይት ከመቀባት ጋር ሊጸልዩልህ ይገባል። ጸሎት ከመድኃኒት ወይም ከዘይት ጋር ሲቀናጅ እግዚአብሔር ይፈውሳል። ነገር ግን የሚፈውሰው ምንድን ነው? ፈውስን የሚያመጣው ዘይቱ ወይም መድኃኒቱ ብቻ ሳይሆን ጸሎቱም ጭምር ነው። ፈውስን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው። 

ሠ. እግዚአብሔር እንደሚያደርግልህ ማመን አለብህ። የእምነት ጉድለት እግዚአብሔር እንዳይነካህና ፈውስን እንዳታገኝ ሊያደርግ ይችላል። 

እግዚአብሔር ልዕለ-ተፈጥሮአዊ ፈውስ የሚሰጥበት መንገድ በቤተ ክርስቲያን ጸሎትና ለታመመው ሰው በሚሰጠው መድኃኒት ነው። 

4. አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ለአንዳንድ ሰዎች የታመመ ሰው መፈወሱን የሚያውጁበት ወይም የሚያሳውቁበት ችሎታ ይሰጣቸዋል። ይህ የፈውስ መንፈሳዊ ስጦታ በመባል ተገልጿል። 

በ1ኛ ቆሮ. 12፡9-10 ጳውሎስ ሁለት ተአምራዊ የሆኑ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ጠቅሷል። የመጀመሪያው ተአምራት የማድረግ ሌላው ደግሞ የፈውስ ስጦታ ነበር። ከሌሎች መንፈሳዊ ስጦታዎች በተለየ ሁኔታ ለእነዚህ ሁለት ስጦታዎች ጳውሎስ የተጠቀመው የብዙ ቁጥር ማለትዎ የፈውሶችና ተአምራትን የማድረግ ስጦታዎች እያለ ነው። እንዲህ ያደረገው ለምን ነበር? እነዚህ መንፈሳዊ ስጦታዎች በሚሰጠው ሰው ላይ በተደጋጋሚ የመስጠቱንና እንደገና ተመልሶ የመወሰዱን ጉዳይ የሚያመለክት ይመስላል። አትኩሮቱ ሰው ላይ አይደለም። ይህ ስጦታዎች ተብሎ በብዙ የመጠቀሱ ጉዳይ የሚያመለክተው እግዚአብሔር አንድን ሰው ለመፈወስ ሲፈልግ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላለ ሰው ያንን የታመመ ሰው ለመፈወስ ፈቃዱ እንደሆነ በመግለጥ የታመመው ሰው እንደሚፈወስ እንዲናገር ማድረጉን ነው። ይህ ስጦታ የተሰጠው ሰው ከተናገረ በኋላ ሰውዬው ይፈወሳል። ይህ የፈውስ ስጦታ ግን ከሰውዬው ሊወሰድ ይችላል። በሌላ ሰው ላይ ፈውስ እንዲያውጅ እግዚአብሔር እንደሚናገረው እስኪሰማው ድረስ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። 

በቤተ ክርስቲያን ያሉ የታመሙ ሰዎች ሁሉ እንደሚፈወሱ ለመናገር ችሎታ የለውም። ይልቁኑ ይህ ሰው የፈውስን ጉዳይ በተናጠል ሊመለከት ይገባዋል። በእያንዳንዱ ወቅት እግዚአብሔር አንድን ሰው እንደሚፈውስ እንዲናገር መንፈሱን ሊያነሣሣለት ይገባል። እግዚአብሔር ፈውስን ያመጣ ዘንድ በሚፈልግበት ጊዜ ሁሉ በአንድ ሰው እንደሚጠቀም ምንም ዋስትና የለም። ይህን ሊያደርግ ይችላል። ነገር ግን የፈውስ መልእክት ለማምጣት በሌላ ሰውም በቀላሉ መጠቀም ይችላል። ስጦታው የሚሰጠው ለቤተ ክርስቲያን እንጂ ለግለሰቦች አይደለም። (ማስታወሻ፡- የፈውስ መልእክት በአንድ ሰው በኩል መምጣቱ ከሰውየው ማንነት ወይም መንፈሳዊ ታላቅነት አድርገን መመልከት እንደሌለብን ማስታወስ እጅግ አስፈላጊ ግዴታ ነው። የሚፈውሰው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ሰውዬው እግዚአብሔር የሚያደርገውን ለሕዝቡ ለማሳወቅ የሚጠቀምበት መሣሪያ ብቻ ነው። የመፈወስ ስጦታ ያለው ሰውዩው ነው ብለን ካሰብን እግዚአብሔርን ሳይሆን ሰውዬውን ማክበር ጀምረናል ማለት ነው። 

እግዚአብሔር ፈውስን ካልሰጠስ? እራሳችንን መርምረን የመንፈስ ቅዱስን ሥራ የሚያግድ ኃጢአት እንደሌለ ካረጋገጥን በኋላ እንኳ ፈውስ ባይመጣልንስ? እግዚአብሔር እንደሚፈውስ በልባችን ፈጽሞ እያመንን እንኳ እግዚአብሔር ካልሠራና ፈውስን ካላመጣስ? መጽሐፍ ቅዱስ እንደምንፈወስ የሚሰጠን ዋስትና የለም። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በተሰወረ ፈቃዱ በሽታና ሞት እንዲሆኑ ይፈቅዳል። የእግዚአብሔር ዓላማዎች ሁልጊዜ የምንረዳቸው አይደሉም። ነገር ግን ሁለት እውነቶችን እናውቃለን። በመጀመሪያ እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ ይቆጣጣራል። ስለዚህ በሽታዎች እግዚአብሔር ሳያውቅ ድንገት የሚሆኑ አይደሉም። ሁለተኛ በሽታና ሐዘን እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያስተምርባቸው ሁለት ትላልቅ መሣሪያዎች ናቸው። እግዚአብሔር ጳውሎስን የእግዚአብሔር ጸጋ በድካም ጊዜ በቂ እንደሆነ እስተምሮታል (2ኛ ቆሮ. 12፡7-10)። ስለሆነም በሽታ እግዚአብሔር እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ለእኛ የሚያስተምርበት መሣሪያ ነው። 

ደግሞ በጸሎት መትጋት አለብን። እግዚአብሔር ጸሎታችንን እስኪመልስ ወይም ጥያቄያችንን እንደማይመልስ ነገር ግን በዚያ ሁኔታ ውስጥ እንኖር ዘንድ ችሎታን እንደሚሰጠንና ለክብሩ እንደሚጠቀምበት ዋስትና እስክናገኝ ድረስ ጸሎታችንን መቀጠል አለብን።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.