የመንፈስ ቅዱስ ሁለተኛ ዋና ተግባሩ፡- ወደ ኢየሱስ ማመልከትና እርሱን እንድንመስል ማድረግ።

ሁሴን እስላም ነበር። አንድ ቀን ታዋቂ ክርስቲያን የሆነ ሰባኪ ሰው እንደመጣና የፈውስ ፕሮግራም እንደሚያካሂድ ሰማ። ሁኔታውን ለማጣራት ስለጓጓ ወደ ሥፍራው ሄደ። ለብዙ ዓመታት ታምሞ የነበረ ሰው ሊፈወስ ተመለከተ። ሁሴን የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ኃይል ስለተመለከተ በኢየሱስ አመነ። ያመነበት ምክንያት ኃጢአተኛ መሆኑን ኢየሱስ ከኃጢአቱ እንዲያነጻው እንደሚያስፈልግ በመገንዘብ አልነበረም። ነገር ግን ለዚያ ኃይል ቅርብ ለመሆን በመፈለግ ነው። በየሳምንቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን መመላለስ ጀመረ። እግዚአብሔር ሰውን ሁሉ እንደማይፈውስ በተገነዘበ ጊዜ ቀን ተስፋ ቆረጠ። ሁሴን እግዚአብሔር ሰዎችን የፈወሰባቸውን ጊዜያት በተጨማሪ ተመልክቷል። ይህ ቀን ለእርሱ የሚያስደንቅ መሆኑ ቀረ። እግዚአብሔር በየጊዜው የተሻሉና ትላልቅ ተአምራትን እንዲያደርግ ፈለገ። ይህ ያልሆነው ምናልባት በዚያ ቤተ ክርስቲያን የነበሩ ሰዎች እምነት ጉድለት ሊሆን ይችላል። ትላልቅ ተአምራት የሚደረግበት ሌላ ቤተ ክርስቲያን እንዳለ ሰማ። በዚያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተአምራትን የሚያደርግ ሰው ነበር። ኃይሉ ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ ሰዎች በየመድረኩ ራሳቸውን ስተው እስከሚወድቁ ይደርሱ ነበር። ሁሴን መጀመሪያ የነበረበትን ቤተ ክርስቲያን ትቶ ወደዚያች ቤተ ክርስቲያን ሄደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በዚህ ቤተ ክርስቲያንም እርካታ እጥቶ ከዚያ የላቀ ተአምራት እንደሚደረግ ወደ ሰማበት ሌላ ቤተ ክርስቲያን ሄደ። ሁሴን የሚፈልገው ነገር ቢኖር የተአምራት መስካሪና እድናቂ መሆን ነበር። በእግዚአብሔር እውቀትና በቃሉ ላማደግ የነበረው አትኩሮት ዝቅተኛ ነበር። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በባሕርይ ለመምሰል የሚያደርገው ጥረት አልነበረም። አንድ ቀን ሚስቱ ታማ ሞተች። ቢጸልይላትም፥ ተአምራትን ሠሪዎች ወደ እርሱ በማምጣት እንዲጸልዩላት ቢያደርግም አልተሳካላቸውም። ከሞተች በኋላ እምነቱን በመካድ ወደ መጀመሪያ ቅርሱ ወደ እስልምናው ተመለሰ። 

ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚማረኩትና ተአምራትንና ሌሎች ትላልቅ ነገሮችን ለማየት የሚፈልጉት ለምን ይመስልሃል? ለ) መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ሕይወት ውስጥ በየዕለቱ ቀስ በቀለ በሚያመጣው ጸጥተኛ የለውጥ አሠራር ብዙ ሰዎች የማይነኩት ለምንድን ነው? ሐ) በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ላይ ከሚገባ በላይ አትኩሮት መስጠት ወደ ስሕተት ትምህርቶች እንዴት ሊመራ እንደሚችል ምሳሌዎችን ስጥ። መ) በእውቀት በጥልቀት ባለማደጋቸው ምክንያት ክእምነት ስተው የወደቁ እንደ ሁሴን ያሉ ሰዎችን ምሳሌዎች ጥቀስ።  

ሰዎች ሊያሸንፉት ወይም ሊያመልኩት በሚከብዳቸው ኃይል ላይ የመደናቀፍ ነገር አላቸው። ሰዎች በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ መሪዎች ለመሆን የሚፈልጉበት አንድ ምክንያት ሌሎችን ለመቆጣጠር ኃይል ለማግኘት ስለሚፈልጉ ነው። ሰዎች በተጨማሪ ኃይልን የሚገልጽ ማለትም የመንፈስ ቅዱስን ኃይል የሚገልጽ የሚማርኩ አስደናቂ ተአምራትን ማየት ይወዳሉ። ካልተጠነቀቅን በስተቀር እንዲህ ዓይነቱ ለአስደናቂ ነገሮች የመሳብ አዝማሚያ፥ ሱስ እንደሚያሲዙ መድኃኒቶች የሚሠራ በመሆኑ ይበልጥ ታላላቅ ኃይል ያላቸውን ተአምራት ለማየት እንድንጓጓ ያደርገናል። የእሳት እራት ወደ ሻማ ብርሃን እጅግ እየተሳበች በነበልባሉ ተቃጥላ እንደምትጠፋ ሁሉ ተአምራትን ብቻ ለማየት ብለን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከተሳብን ሚዛናዊነት ልናጣና ሕይወታችን የተበላሸ ሊሆን ይችላል። የመንፈስ ቅዱስን ኃይልና አገልግሎት በሚገባ ስፍራ ሰጥተን ማክበር ሲኖርብንም እንኳ የመንፈስ ቅዱስን አገልግሎት መመልከት ያለብን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው መሠረት አኳያ እንጂ አድናቆትን ከሚፈጥሩ የመንፈስ ቅዱስ እገልሎተች አኳያ መሆን የለበትም። 

የመንፈስ ቅዱስ ዋና ሥራ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተንጸባረቁ በርካታ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ። አንዳንዶች መንፈስ ቅዱስ ከኃጢአት እኛን ለማንጻት ባለው ፍላጎት ላይ በማተኮር የመንፈስ ቅዱስ ተቀዳሚ አገልግሎት ሰውን መቀደስ ነው ይላሉ። ሌሎች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ላይ በማተኮር የመንፈስ ቅዱስ ተቀዳሚ አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን ውስጥና በቤተ ክርስቲያን በኩል ተአምራትን ማድረግ ነው ይላሉ። እነዚህ ተአምራት መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን እንደሚኖር ያረጋግጣሉ ይላሉ። 

ነገር ግን ወደ ጥያቄው እንመለስና «መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ተቀዳሚ አገልግሎት ምን ያስተምረናል?» መንፈስ ቅዱስ ማን እንደሆነና በሕይወታችን ምን ለማድረግ እንደሚፈልግ ለመወሰን የምንጠቀምባቸው ሌሎች መንገዶች ሁሉ አደገኛ ናቸው። አመለካከታቸውና ተግባሮቻቸው በእግዚአብሔር ቃል ላይ ይመዘኑ ዘንድ የማይፈቅዱ እንዳንድ ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች ፍጹም እውነት የለም ከሚሉ ጋር በሚናወጥ መሠረት ላይ የቆሙ ናቸው። «የተሰማን ነገር በሙሉ፥ በልባችን የምናምነው ነገር ሁሉ ትክክል ነው» በማለት ያስተምራሉ። ስለዚህ እውነትን የሚመዝኑት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ባለ ፍጹም መመዘኛ ሳይሆን በስሜታቸው ነው። ይህ አመለካከት ዛሬ በስሩት በተለመደው «መንገዶች ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ያደርሳሉ» ከሚለው የሐሰት ትምህርት ጋር ተመሳሳይ ነው። «ቅንና እውነተኛ እስከሆንን ድረስ ሙስሊም፥ ቡድሂስት፡ ኦርቶዶክስ ወይም ዛፍ እምላኪ እንኳ ብንሆን ሁሉም ቅንነት የሞላባቸው ስለሆኑ ትክክል ናቸው» ይላሉ። ይህ የሰይጣን ውሸት የአዲስ ዘመን እንቅስቃሴ፥ የዓለም አቀፍ አብያተ ክርስቲያናት እንቅስቃሴና በዘመናችን ያሉ በርካታ የሐሰት ሃይማኖቶች እምብርት ነው። አንድ እርጠኛ የማይነቃነቅ የእውነት ምንጭ ብቻ አለ። እርሱም መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የሚያስተምራቸውን እውነቶች ልናምንባቸውና ልንቆምላቸው ይገባል። ግልጽ ትምህርት ያልተሰጠባቸው እውነቶች ወይም አመላካክቶችን ሁሉ እግዚአብሔር ቃል ጋር ለመስማማት ጥረት እስካደረጉ ድረስ ያላቸውን መብት ልንጠብቅላቸው ይገባል። 

ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች አመላካከቶቻቸው ወይም ትምህርቶቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ሚዛን መመዘናቸውን የሚፈሩት ለምንድን ነው? ለ) አመለካከቶቻችን በእግዚአብሔር ቃል ያላመመዘናቸው አደጋ ምንድን ነው? 

የእግዚአብሔር ተቀዳሚ ዓላማ በዓለም ውስጥ። 

ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት። ቈላ. 5-23፤ 2ኛ ቆሮ. 5፡18-20፤ ሮሜ 8፡29። ስለ እግዚአብሔር ዓላማዎችና በዘመናችን እያደረጋቸው ስላሉ ነገሮች ምን ያስተምራሉ? 

የመንፈስ ቅዱስን አገልግሎት ለመረዳት የእግዚአብሔርን ተቀጓሚ ዓላማ መረዳት ያስፈልገናል። የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅዶች ዋና ማዕክል ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የብሉይ ኪዳን ትምህርቶችና ተስፋዎች በሙሉ ወደ እርሱ ያመለክታሉ። አዲስ ኪዳን በሞላ የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ዕቅድ የሚፈጽም እርሱ እንደሆነም ያመላክታል። ስለ ኢየሱስ የተነገሩትን የሚከተሉትን ነገሮች ልብ በል። 

1 ኢየሱስ እግዚአብሔር አብን በሙላት የሚወክል ነው። ወደ ምድር የመጣው እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል ለሰው ልጆች በግልጽ ለማሳየት ነው። ስለዚህ ኢየሱስን ያየ አብን አይቷል ተብሎ ተነግሮናል (ዕብ 1፡3፤ ቈላ. ፡9)። 

2. ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስሙላት ለሌሎች የሚገልጥ የእግዚአብሔር ቃል ነው (ዮሐ 1፡1-5፤ ዕብ. 1፡1-2)። 

3 ኢየሱስ ዓለምን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ የመጣ ነው። በኢየሱስ በሰማይና በምድር ያሉ ነገሮች በሙሉ ወደ ፍጹም አንድነት ይጠቀላላሉ። ኢየሱስ ታሪክን በሙሉ ነገሮችንም ሁሉ ለእግዚአብሔር ወደ መታዘዝ እንደገና መልሶአቸዋል (ኤፌ. 1፡10፤ ቆላ. 1፡20)። 

4. ኢየሱስ በእርሱ ውስጥና በእርሱ በኩል እግዚአብሔር አብ የሚመለክበት አዲስ አካልን ይኽውም ቤተ ክርስቲያንን የሚነሳ ነው (ኤፌ. 20-23)። 

ስለዚህ የአዲስ ኪዳን ዋና ነጥብ መንፈስ ቅዱስ ሳይሆን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ (ዕብ 12፡2) ማዕከልና መሠረት ነው። የቤተ ክርስቲያን ዋና ትምህርትና ዋና አምልኮ ሁልጊዜ ማመልክት ያለበት ወደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱም በኩል ወደ እዚአብሔር አብ ነው። ከዚህ የምንመለከተው ማንኛውም የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በጥብቅ መቆራኘት እንዳለበት ነው። የእግዚአብሔር ዕቅድ «ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ይንበረክክ ዘንድ» (ፊልጵ. 29=ህ ከሆነ የመንፈስ ቅዱስ ተቀዳሚ ሥራ ከዚህ ጋር የሚስማማና ይህ እንዲከናወንም የሚፈልግ መሆን እንዳለበት እንጠብቃለን። 

መንፈስ ቅዱስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለው ግንኙነት 

ጥያቄ፡- የሚክተሉትን ጥቅሶች ተመልከት። ዮሐ 14፡2818፡26-27 16፡12-15። እነዚህ ጥቅሶች መንፈስ ቅዱስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዴት ያሳያሉ? 

በመላው አዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ ከኢየሱስ ጋር ተቆራኝቶ ከመቅረቡ የተነሣ «የኢየሱስ መንፈስ» ተብሎ ተጠርቷል። በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ያለማቋረጥ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነው ኢየሱስ ያንኑ መንፈስ ቅዱስ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ሁሉ ሰጠ። መንፈስ ቅዱስ ወደ አማኙ ልብ ከመግባቱ ጋር ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ ወደ ሕይወቱ ይመጣል (ሮሜ 8፡9-11)። በአዲስ ኪዳን በሞላ ኢየሱስ ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ እጅግ ተቆራኝተው ስለቀረቡ አንዱን ማግኘት ሌላውንም ማግኘት ነው (2ኛ ቆሮ. 3፡17-18)። 

ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ ስለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ አስተማራቸው። ኢየሱስ፥ ላደቀ መዛሙርቱ ስለ መንፈስ ቅዱስ በሚያስተምራቸው ወቅት ስለ መንፈስ ቅዱስ ኃይል፥ ስለ ሚሠራቸው ተአምራት፥ በልሳናት ስለ መናገር፥ ስለ ፈውሶች፥ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች፥ ወዘተ… አልጠቀሰም። ይልቁኑ መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ ጋር ስለ ሚኖረው ቀንኙነት ደቀ መዛሙርት እንዲረዱ ፈለገ። መንፈስ ቅዱስ የሚያደርጋቸው ነገሮች በሙሉ በኢየሱስ ላይ ያተኮሩና እርሱን የሚያከብሩ እንደሚሆኑ የታቀዱ ነበሩ (ዮሐ 16፡14)። መንፈስ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ያለውን እውነት ለደቀ መዛሙርት የሚያቀብል የኢየሱስ አፈቀላጤ እንደሚሆን ነበር። ኢየሱስ እግዚአብሔር እንደሆነ ደግሞም አዳናቸው፥ እረኛቸው፥ ንጉሣቸው እንደሆነ ለደቀ መዛሙርት ማረጋገጥ የመንፈስ ቅዱስ ኃላፊነት ነበር። መንፈስ ቅዱስ፥ ኢየሱስ ከእብ ጋር አንድ እንደሆነና እብ እንደ ተከበረ እርሱም ሊከበር እንደሚገባ ለደቀ መዛሙርት ያስተምራቸው ነበር (ዮሐ 5፡3)። 

ስለ መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ አገልግሎቶች የሚናገሩ በርካታ ጥቅሶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ። በአብዛኛዎቻቸው የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ከኢየሱስ ጋር ተያይዞ የተጠቀሰ ነው። ሆኖም ግን መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርት ላይ ለምን እንደሚወርድ ግልጽ የሆነ ማብራሪያ የምናገኘው በዮሐንስ ወንጌል ላይ ነው። ቀጥሎ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተያያዙ የኢየሱስ ክርስቶስን አገልግሎቶችን እንመለከታለን። 

1. ሌላው «አጽናኝ» በመባል ብዙ ጊዜ የሚታወቀው መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ ጠያቂነት አብ የሚላክ ነበር (ዮሐ 14፡6፥ 26)። ኢየሱስ የእብ ወኪል እንደነበረ ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ደግሞ የእርሱ ወኪል አድርጎ ላከው (ዮሐ 6፡26፥ 16፡7)። 

2. መንፈስ ቅዱስ የተላከው በኢየሱስ ስም ነበር። በሌላ አባባል መንፈስ ቅቶስ ኢየሱስን ወክሎ በእርሱ ስምና ሥልጣን ይሠራ ዘንድ እንደ ነበር ነው (ዮሐ 1426)። 

3. መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ለመኖር ሲመጣ ወደ ክርስቲያኑ ሕይወት ለመኖር የመጣው ኢየሱስ እራሱ ነው እንደ ማለት ነው (ዮሐ 14፡18-23)። 

4. መንፈስ ቅዱስ ሰዎችን ሁሉ ወደ ኢየሱስ በማመልከት የበለጠ እንዲወዱት፥ እንዲታዘዙት፥ እንዲያመልኩትና ከፍ ከፍ እንዲያደርጉት፥ ሕይወታቸውንም ለእርሱ አሳልፈው እንዲሰጡ ያደርጋቸዋል። 

5. እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር ወልድ በእያንዳንዱ አማኝ ሕይወት ውስጥ ማደሪያ የማድረጋቸውን እውነታ መግለጽ ብቻ ሳይሆን እንዲለማመዱት ማድረግም የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው (ዮሐ. 14፡21-23)። በመንፈስ ቅዱስ በኩል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር በልጆቹ ውስጥ በመኖር ከእነርሱ ጋር ኅብረት ያደርጋል። መንፈስ ቅዱስ በሰው ልብ ውስጥ የማደሩ ተቀዳሚ ዓላማ ከኢየሱስ ጋር ቅርብ የሆነ ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረግ ነው። 

6. ለሦስት ዓመታት ያስተማራቸውን ኢየሱስን በመተካት መንፈስ ቅዱስ ደቀ መዛሙርትን እንደሚያስተምራቸው ነበር (ዮሐ 14፡26፥ 16፡13)። 

7. መንፈስ ቅዱስ ለዓለም ስለ ኢየሱስ ይመሰክራል። ኢየሱስ ማን እንደሆነ ለኃጢአታቸው ይቅርታ ያገኙ ዘንድ በእርሱ ማመን እንዳለባቸው በኢየሱስ ካላመኑ እግዚአብሔር እንደሚፈርድባቸው ያስተምራቸው ነበር (ዮሐ 16፡8፤ 17፡20)። 

መንፈስ ቅዱስ በእያንዳንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ሕይወት ውስጥ በሚገባ ይሳተፋል። አገልግሎቱን የሚጀምረው ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያምን የሰውን ልብ በማነሣሣት ነው። አንድ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ያመነው ሰው ከጌታው ጋር ኅብረት እንዲያደርግና ጌታውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲመስል እንደ ዋና የሥራው መሪ ሆኖ መንቀሳቀስ ይጀምራል። ያመነው ሰው እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ መንገድ እንዲኖርና እንዲሠራ ኃይልን ያስታጥቀዋል። ይህን በሚያደርግበት ጊዜ በፍጻሜው ኢየሱስ እንዲታወቅ፥ እንዲወደድ፥ እንዲታመን፥ እንዲከበርና እንዲመሰገን ነው። 

እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስን ሰጥቷል። በተጨማሪ የእግዚአብሔር ልጆች ኢየሱስ ክርስቶስን ለማምለክ በሚሰበስቡት ወቅት መንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜ በመካከላቸው ይገኛል። መንፈስ ቅዱስ በዚህ ወቅት ያለው ተቀዳሚ ዓላማ ምንድን ነው? 

ሀ. መንፈስ ቅዱስ ለተሰበሰቡት ሁሉ የኢየሱስን መገኘት እውን ያደርጋል። 

ሊ መንፈስ ቅዱስ፥ ኢየሱስን በእውነትና በመንፈስ እንድናመልከው ይረዳናል። 

ሒ መንፈስ ቅዱስ፥ በተሰበሰብንበት ስፍራ ቃሉን ና አንዳችን ለሌላችን የምንናገረውን በመጠቀም ይናገረናል። 

መ. መንፈስ ቅዱስ እምነታችንን ለመገንባት አንዳችን ለሌላችን እንድናገለግልና እንድንተናነጽ ይረዳናል። 

ሠ. መንፈስ ቅዱስ፥ ወደ ዓለም እንድንወጣና ኢየሱስን ወክለንና የእርሱ አፈቀላጤ ሆነን እንድንናገር ያዘጋጀናል። 

አዲስ ኪዳን ስለ መንፈስ ቅዱስና ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር ለላላው ግንኙነት የሚናገረውን ሁሉ በአጭሩ ማቅረብ ቢያስፈልግ የመንፈስ ቅዱስ ተቀዳሚ አገልግሎት ለእያንዳንዱ ክርስቲያንና ለእያንዳንዱ የአማኞች ኅብረት ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላቸው ለላ መኖሩ ማሳወቅ እንደሆነ ድምጻሜ ላይ እንደርሳለን። በመካከላቸው መኖር ብቻ ሳይሆን እጅግ የቀረበ የግል ግንኙነት ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲያደርጉ ልባቸውን ያነሣሣባቸዋል። 

ጥያቄ፡ መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስን ህልውና በሕይወትህና በቤተ ክርስቲያንህ ባለ የአምልኮ ጊዜ እውን ሲያደርግ ያየኽው እንዴት ነው? 

መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ላይ እንድናተኩር የሚያደርግባቸው መንገዶች 

በአገልግሎቶቹ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስ ክርስቶስን ህልውና ለእግዚአብሔር ልጆች እውን በማድረግ ከኢየሱስ ጋር ዘላቂ የሆነ ጥብቅ ወዳጅነት እንዲፈጥሩ ያስችላል። ይህ በሦስት መንገድ ይሆናል። 

በመጀመሪያ፥ መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዱ አማኝ ክኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የግል ግንኙነት እንዲጀምር ይረዳል። የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት በሥጋ ከኢየሱስ ጋር ኖረዋል፥ ተመላልሰዋል፥ ሁልጊዜ ኢየሱስ ከጎናቸው ነበር። ኢየሱስ ዛሬ በዚህ ዓይነት መንገድ ከእኛ ጋር የለም። ነገር ግን ያለው በመንፈስ ነው። ዛሬ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ ሁልጊዜ በልባችን እንደሚኖር እኛን ተከታዮቹን ለማሳሰብ ይሠራል። መንፈስ ቅዱስ ሰልባችን የሚኖረው ከኢየሱስ ጋር ኅብረት እንድናደርግ፥ እንድንወደው፥ እንድንታዘዘውና በሕይወታችን ህልውናው እንዲሰማን ላማድረግ ነው። 

ጥያቄ፡– መንፈስ ቅዱስ ይህን በልብህ የሚያደርገው እንዴት ነው? አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ። 

በሁለተኛ ደረጃ ፥ መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዱ ሰው ክርስቶስን እንዲመስል ለመለወጥ ይፈልጋል። በኢየሱላ በምናምንበት ወቅት ድነት (ደኅንነት)ን ማግኘት ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ወንዶችና ሴቶች ልጆች ሆነናል (ዮሐ 1፡2)። የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን እግዚአብሔር አብ እርሱን እንድንመስል ይፈልጋል። በተለይ ደግሞ አንድያ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንመስል ይፈልጋል። የመጀመሪያ አባታችን የነበረውን ሰይጣንን ከመምሰል ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ መምሰል እኛን የመለወጡ ኃላፊነት የመንፈስ ቅዱስ ነው። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? መንፈስ ቅዱስ አትኩሮታችንን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመልሰዋል። ኢየሱስ ክርስቶስን የበለጠ እያወቅነው ነው ፍቅሩን፥ ኃይሉን፥ ለሚጠፉት ነፍሳት ያላውን ርኅራሄ+ ወዘተ… የበለጠ እየተረዳን ስንሄድ ስተራችን እኛም ኢየሱስን መምሰል እንጀምራለን። ኢየሱስን እንድናመልክእንድናወድሰውና ሕይወታችንን ለእርሱ እንድናስረክብ መንፈስ ቅዱስ በረዳን መጠን ኢየሱስን ማምለክ እንጀምራለን። አስተሳሰባችንና ዝንባሌያችን ይለወጣል። በተጨማሪ ውስጣዊ ፍላጎታችንና ተግባራችን ይለወጣል። 

ጥያቄ፡– መንፈስ ቅዱስ ይህንን በሕይወትህ ያደረገው እንዴት ነው? አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ። 

በሦስተኛ ደረጃ ፥ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት መሆናችንን ለልባችን ይመሰክርልናል። በእግዚአብሔር የተወደድን መሆናችንን፥ በእግዚአብሔር ጸጋ ከኃጢአታችን በሙሉ መዋጀታችንን በእግዚአብሔር ቤተሰብ ልጆች እንድንሆን መደረጋችንን ያላማቋረጥ ያሳስበናል (ሮሜ 8፡17)። የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን አንዳንድ ጊዜ የምንጠራጠርበት ሁኔታ ቢገጥመንም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እነዚህን ጥርጣሬዎቻችንን ለማሸነፍ እንችላለን። የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞችና እህቶች እንደሆንን እኛን የማሳሰብ አገልግሎትና የዋስትና ስሜት ይሰጠናል። ለእግዚአብሔር አብና ለአዳኛችን ለኢየሱስ በጥልቅ ፍቅር ልባችን ሐሤት እንዲያደርግ ይረዳናል። 

ጥያቄ፡- በሕይወትህ እጅግ ተስፋ የቆረጥክበትን ጊዜ ግላጽ። እግዚአብሔር በእውነት ይወድህ እንደሆነና በእርግጥ ልጁ እንደሆንክ በመገረም ጠይቀህ ይሆናል። በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ያጽናናህ እንዴት ነበር? 

ስለዚህ በአጭሩ የመንፈስ ቅዱስ ተቀዳሚ እገልግሎት የእግዚአብሔር ልጆች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲወዱና ከፍ አድርገው እንዲያመልኩት ማድረግ ነው። ለአማኞች ያለው ዓላማ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው ሕይወት ማደሩን እንዲለማመዱ ወይም እውነታውን እንዲጨብጡ ማድረግ ነው። በአሳብ፥ በባሕርይና በተግባር ኢየሱስ ክርስቶስን ይመስል ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አማኙን በኃይል ያስታጥቀዋል። 

የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶችና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸው ግንኙነት ማጠቃለያ 

ሁሉንም የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች መጥቀስ ቢያስፈልግ በሚከተለው መንገድ መዘርዘር ይቻላል። 

1. ኢየሱስን ለሰዎች ማስተዋወቅና ለደኅንነታቸው ወደ እርሱ የመመለሳቸውን አስፈላጊነት የማሳወቅ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት። 

2. ሰዎች ከሰይጣን ልጅነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት እንዲለወጡና ዕለት በዕለት የእግዚአብሔር ልጅ የሆነውን ኢየሱስን እየመሰሉ እንዲሄዱ የማድረግ አገልግሎት። በባሕርይና በተግባር ኢየሱስን እንመስል ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ኃይልን ይሰጠናል። 

3. ክርስቲያን ኢየሱስን በአክብሮትና በፍቅር እንዲያመልክ የመርዳት የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት። 

4. መንፈስ ቅዱስ፥ አማኞች እንዱ ሌላውን እንዲያገለግል፥ ኢየሱስን ወክለው ደግሞ እንደ ኢየሱስ አካል ዓለምንም ጭምር እንዲያገለግሉ የሚረዳበት አገልግሎት። 

ጥያቄ፡- ከላይ በተሰጡት እራት ርእሰ ጉዳዮች የመንፈስ ቅዱስን አገልግሎት የምትመድብበት ሠንጠረዥ አዘጋጅ። እስካሁን ያጠናናቸውን እያንዳንዳቸውን የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች ከአራቱ በአንዱ ክፍል ለይተህ አስቀምጣቸው።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.