የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች ክለሳ

ጥያቄ፡- ሀ) ስለ መንፈስ ቅዱስ ስዚህ ኮርስ የተመላክትናቸውን እውነቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህ አገልግሎቶች እያንዳንዳቸው ሕይወትህን የሚነኩት እንዴት ነው? ሐህ እነዚህን አገልግሎቶች እያንዳንዳቸውን ማጥናት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? 

መንፈስ ቅዱስ ማን እንደሆነና ምን እንደሚያደርግ ለመረዳት በጥናታችን ያደረግነው ጉዞ ረጅም ነበር። ዛሬ ቤተ ክርስቲያን በሚከፋፍሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ምክንያት አለመግባባቱን የሚያመጡ ርእሰ ጉዳዮችን ለመመልከት ሰፊ ጊዜ ወስደናል። ይህን በማድረጋችን ብዙ ክርስቲያኖች የሚስማሙበትን ስለ መንፈስ ቅዱስ ያላውን ሰፊ ትምህርት በመዘንጋት አደጋ ውስጥ እንወድቃለን። ቀጥሎ ስለ መንፈስ ቅዱስ የተመለከትናቸው አንዳንድ ዐበይት እውነቶች ተሰጥተዋል። 

1) መንፈስ ቅዱስ ማን እንደሆነና ምን እንደሚያደርግ በተቀዳሚ ልንማር የምንችልበት ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ ማን እንደሆነና ከእግዚአብሔር አብና ከወልድ ጋር ስላለው ግንኙነት እግዚአብሔር ካልገለጠልን ልናውቅ አንችልም። በሦስት አካላዊ ህልውና የተገለጠ አንድ አምላክን የማምላካችንን እውነት ልንረዳው የምንችለው በሰብአዊ አእምሮ ሥራ ሳይሆን በእምነት ብቻ ነው። መንፈስ ቅዱስ ማን እንደሆነ ግልጽ የሆነ መረዳት ከፈለግን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መመላስ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ የገለጠውን ለመመርመር በጥናት መጽሐፋችን ላይ እጅግ ብዙ ጊዜ ያጠፋነው ለዚህ ነው። 

2. መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ ሦስተኛ አካል ነው። 

ሀ. ስሙ እራሱ «ቅዱስ» የተለየ ከማንኛውም ተራና ኃጢአታዊ ነገር የተላየ መሆኑን ያመለክተናል። ደግሞም «መንፈስ» ስለሆነ እንደ እኛ ሥጋዊ አካል የለውም። 

ለ. መንፈስ ቅዱስ የራሱ የሆነ አካላዊ ህልውና አለው። መንፈስ ቅዱስ ሕይወት እንደሌላቸው እንደ ነፋስና እሳት ሳይሆን ሕይወት ያለው ኑባሬ ነው። አንድ ነገር አካላዊ ኑባሬ ያለው መሆኑን የሚያመለክቱ ነገሮች ሁሉ (ለማሰብ የሚችል ስሜት ያለው፥ ለመወሰን የሚችል፥ የሚያዝን፥ ወዘተ…) ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም እውነት ናቸው። ይህ ልናስታውሳቸው ከሚገቡን እጅግ ጠቃሚ እውነቶች አንዱ ነው። ስለዚህ ብዙ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ልንቆጣጠረው የምንችለው፥ የራሱ አካላዊ ህልውና የሌለው ኃይል አድርገን እንቆጥራለን። ይህም ብዙ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች አንድ የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት እስማታዊ ኃይልን እንደሚጠቀሙበት ዓይነት ነው። 

ይህ ችግር በሁለት የተለያዩ መንገዶች ሊፈጸም ይችላል። በመጀመሪያ። ብዙ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን በጥብቅ ለመከተል ካላቸው ፍላጎት አንጻር እንደ አስማታዊ መጽሐፍ ይቆጥሩታል። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በቂ እውነቶች ካወቁ ሊያደርጉ የፈለጉትን ነገሮች እንዳከናወኑ ይቆጥራሉ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያለን እውቀት ከጉዳት ይጠብቀናል። መንፈሳዊ ያደርገናል። እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ኑሮ እንኖር ዘንድ ኃይል ይሰጠናል። ስለዚህ ሊጣና፥ በቃል ሊያዝና በጥብቅ ሰዎች ሊክተሉት ይገባል። ሆኖም ግን መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ዓላማችን መጽሐፍ ቅዱስን የበለጠ ለማወቅ መሆን የለበትም። ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠውን እግዚአብሔርን የበለጠ ለማወቅ እንድንችል ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናደርገው አትኩሮት ከመጠን አልፎ ሄዶ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቀዳሚ ዓላማ በውስጡ ያለውን ሕያው እግዚአብሔር ለመገናኘት መሆኑን ከዘነጋን አስማታዊ ኃይል እንዳለው መጽሐፍ መቁጠር ጀምረናል ማለት ነው። 

ሕያው ቃል ከሆነውና አብን ከሚያሳየን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የምንገናኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። መንፈስ ቅዱስ ከአብ ጋር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በቃሉ ውስጥ እንድንገናኝ ይፈልጋል። እርሱ የራሱ የሆነ አካላዊ ህልውና ስላለው ከእኛ ጋር የግል ግንኙነት ለማድረግ ይፈልጋል። እርሱ ሊረዳን ከጎናችን ያላ አጽናኛችን ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችንን በማጥናት ስለ መንፈስ ቅዱስ በማወቃችን ብቻ መንፈስ ቅዱስን እናውቃለን ማለት አይደለም። መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ኑባሬ ነው። ከእርሱ ጋር ያለን ግንኙነት ሊያድግና ድምፁን አውቀን የቅርብ ወዳጆች ልንሆን ይገባል። 

ሁለተኛው፥ አደጋ የቅጽበታዊ ኃይል ምንጭ መሆኑን ለማየት አስማታዊ ኃይል አድርገው መቁጠራቸው ነው። ለእነርሱ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ለማድረግ ነው እርሱ በዚያ ያለው። ስለዚህ በሚታመሙበት ጊዜ መፈወስ ግዴታው እንደሆነ አድርገው ይጸልያሉ። ምንም ዓይነት ችግር ቢገጥማቸው ከዚያ ችግር እንዲያወጣቸው መንፈስ ቅዱስን ያዛሉ። መንፈስ ቅዱስን እንደ መልካም ዕድል እድራጊ በመቁጠር የሚፈልጉትን እንዲያደርግ ያዙታል። መንፈስ ቅዱስ የምንቆጣጠረው ነገር አይደለም። እንደ ወዳጅ የማያቋረጥ ግንኙነት ከእርሱ ጋር ለማድረግ የምንችለው ዘላለማዊና አካላዊ አምላክ ነው። ልናውቀውና በጊዜ ሂደት ዘላለማዊ የሆነ የቅርብ ግንኙነት ከእርሱ ጋር ልናደርግ ይገባል። እንደ ልዩ ወዳጃችን ከሁሉ በላቀ ሁኔታ ሊረዳን እብሮን አለ። አንዳንድ ጊዜ ከበሽታና ከችግሮች በመታደግ ሊሆን ይችላል። በሌላ ጊዜ ደግሞ በችግሮች ውስጥ ድል እየሰጠ በእርሱ ላይ በመደገፍና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል እንድናድግ ያደርጋል። 

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን አካላዊ ኑባሬ እንደሌለው እስማታዊ ኃይል መቁጠር በፍጹም፥ በፍጹም፥ በፍጹም የሚገባ ነገር አይደለም። ከእርሱ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ለማድረግና ግንኙነትህንም ለማሳደግ የምትችልበት የራሱ አካላዊ ኑባሬ እንዳለው አድርገህ ተመልክተው። 

ጥያቄ፡- ሀ) መንፈስ ቅዱስን እካላዊ ህልውና የሌላው ኃይል ብቻ እንደሆነና የራሳቸውን ፍላጎቶች ለማሟላት እንደሚፈልጉት የሚጠቀሙበት ነገር አድርገው የሚቆጥሩ ምን ያህል ክርስቲያኖች እንዳሉ ግለጽ። ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የግል ግንኙነት ከመመሥረት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችና ስለ መንፈስ ቅዱስ የተጻፉ እውነቶችን በማወቅ ላይ የሚያተኩሩት እንዴት ነው? ሐ) ይህ አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው? 

ሐ.መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው። የሥላሴ አንዱ አካል ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ግልጽ ነው። መንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር አብና ከእግዚአብሔር ወልድ ጋር አካል የሆነ ምሉዕ አምላክ ነው። የእግዚአብሔር ኃይል ያለውና እግዚአብሔር ብቻ ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን ተግባራት የሚያደርግ ነው። እግዚአብሔር በሦስት ውስጥ ያለ አንድ የመሆኑ ጉዳይ ፈጽሞ ልንረዳው የማንችላው ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር አንድ መሆኑን ደግሞም የተለያዩ ሦስት የሥላሴ አካላት ነገር ግን በባሕርይም እኩል የሆኑ አምላክ መሆናቸውን በግልጽ ስለሚያስተምር ይህን እውነት በእምነት መቀበል አለብን። 

3. ስለ መንፈስ ቅዱስ በብሉይ ኪዳንና በወንጌላት የተሰጡ እውነቶች። መንፈስ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በሙሉ የተገለጠ ቢሆንም በብሉይ ኪዳን የነበረውን አገልግሎት ለመረዳት የአዲስ ኪዳን መገለጥ ያስፈልገናል። 

ሀ. በብሉይ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ይሠራ ነበር። በመጀመሪያ፥ በመፍጠር ሥራ ይሳተፍ ነበር። በተለይ በመፍጠርና የተፈጠሩትን በሕይወት በማቆየት ሥራ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ: አንዳንድ መሪዎችን (መሳፍንት፥ ነገሥታት፥ ነቢያት) ኃይል በማስታጠቅ ይሠራ ነበር። ኃይል የሚያስታጥቃቸው የእግዚአብሔርን ሕዝብ በጥበብና በኃይል እንዲመሩ ነበር። መንፈስ ቅዱስ ኃይል የማስታጠቅ አገልግሎቱ ለአማኞች በሙሉ ሳይሆን ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ነበር። በተጨማሪ ይህ አገልግሎት የጊዜ ገደብም ነበረው፤ ማለትም ሥራው በሚጠናቀቅ ወይም ኃይሉን የተቀበለው ሰው ትልቅ ኃጢአት በሚያደርግበት ጊዜ ሰውዬውን ትቶ ይሄድ ነበር። 

በብሉይ ኪዳን መጨረሻ ነቢያት መንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ ጋር በጥልቀት አብሮ የሚሆንበት አዲስ ዘመን እንደሚመጣ እሻረው ተመለከቱ። ይህ ዘመን በመጣ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔርን እንዲታዘዙና እንዲያገለግሉ እንደሚያስችላቸው ነበር። 

ለ. በወንጌላት ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ተቀዳሚ አገልግሎት ግልጽ ሆነ። በመጀመሪያ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ውስጥ በቅርብ የሚኖረውን ሕይወት በምሳሌነት አሳየ። ኢየሱስ እግዚአብሔር አብ እንዲሠራው የፈለገውን ነገር ሁሉ የሠራው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው። 

በሁለተኛ ደረጃ፥ መንፈስ ቅዱስ ከኢየሱስ ጋር የነበረውን ዓይነት ኅብረት ከአማኞች ሁሉ ጋር የሚያደርግበት ጊዜ እንደሚመጣ ኢየሱስ ያመለክታል። ኢየሱስ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከተመለሰ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን አጽናኝ፥ መምህር፥ ጓደኛና ኃይል ሰጪ ይሆናል። 

4. መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ያለው አገልግሎት። ስለ መንፈስ ቅዱስ እያደገ በሚመጣ ሂደት በሐዋርያት ሥራና በመልእክቶች ውስጥ የተሰጡ ትምህርቶችን ከሰው ከመመልከት ይልቅ አሁን እየተሳተፈባቸው ያሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንመለከታለን። ቀጥሎ የእነዚህ አገልግሎቶች ማጠቃለያ ቀርቧል። 

ሀ. ኃጢአትና ውጤቶቹ በዓለም እንዳይስፋፉ በማድረግ አጠቃላይ እገልግሎት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ይሳተፋል። በዓለም ላይ መንፈስ ቅዱስ ባይኖር ኖሮ የሰው ልጅ ኃጢአት እሁን ካለበት በላይ እጅግ አድጎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሱኑ መልሶ ያጠፋው ነበር። 

ለ. መንፈስ ቅዱስ፥ የማያምን ሰው ኃጢአተኝነቱን ተረድቶ ለደኅንነቱ : በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን እንዳለበት በማሳወቅ ተግባር ይሳተፋል። መንፈስ ቅዱስ የግለሰቡን መንፈሳዊ ዓይኖች በመክፈት ኃጢአተኛነቱን እግዚአብሔር እንደሚያየው እንዲያይና ኢየሱስንም ከኃጢአትና ከሞት የማምለጫው ብቸኛ መንገድ አድርጎ እንዲመለከት ያስችላዋል። በዚህ ሁኔታ ሰውዬው ኢየሱስን እንደ ግል አዳኙ አድርጎ ይቀበላል። 

ሐ. መንፈስ ቅዱስ፥ አንድ ሰው ኢየሱስን በሚያምንበት ጊዜ ወዲያውኑ በልቡ ለመኖር ወደ ሰውየው ይመጣል። ይህን በሚያደርግበት ጊዜ በርካታ አስደናቂ ነገሮች ይፈጸማሉ። 

1. መንፈስ ቅዱስ ለአዲሱ ክርስቲያን አዲስ ተፈጥሮ ይሰጠዋል። በመንፈስ ዳግም ይወለዳል። ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ለማድረግና እግዚአብሔር የሚፈልገውን ነገር ለማድረግ ይችል ዘንድ መንፈሳዊ ተፈጥሮው ከሞት ይነሣል። 

2. መንፈስ ቅዱስ፥ የክርስቲያኑን ኃጢአት በሙሉ በማንጻት በእግዚአብሔር ፊት ቅዱስና ንጹሕ ሆኖ እንዲቆም ያደርገዋል። 

3. መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ማኅተም በአማኙ ልብ ላይ ያደርጋል። ይህ ማኅተም እማኙ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል መሆኑን የሚያመለክት ነው። በተጨማሪ አዲሱ የእግዚአብሔር ልጅ በሙላት የእግዚአብሔርን ተስፋዎች ወደ ሚቀበልበት ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ለማግኘቱ ዋስትናም ነው። 

4. መንፈስ ቅዱስ አዲሱን አማኝ ቤተ ክርስቲያን ወይም የክርስቶስ አካል ወደምንላው ትልቅ ቤተሰብ ያስገባዋል። የዘር፥ የጾታ፥ ወይም የማኅበረሰብ ደረጃ ልዩነት ሳያደርግ በክርስቶስ አካል ውስጥ እኩል ስፍራ ይሰጠዋል። በተጨማሪ እግዚአብሔርን የሚያገለግልበት ስፍራም ይሰጠዋል። 

መ) መንፈስ ቅዱስ በዳነው ሰው ሕይወት ቀሪ ዘመን ሁሉ የሚቀጥል አገልግሎት ይጀምራል። 

1. መንፈስ ቅዱስ፥ እማኙ የእግዚአብሔርን ድምፅ መስማት እንዲችል ያደርገዋል። በተቀጻሚ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ አማካይነት ለአዲስ ክርስቲያን ሲናገር መንፈስ ቅዱስ አማኙ መስማት እንዲችል ያደርገዋል። ነገር ግን አማኙ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲያውቅና እንዲያደርግ መንፈስ ቅዱስ በሌሎች በርካታ መንገዶች ይናገረዋል። 

2. መንፈስ ቅዱስ ለአዲሱ ክርስቲያን በክርስቶስ አካል ውስጥ የሚሳተፍበትን ልዩ ተግባር ይሰጠዋል። አዲስ ኪዳን እነዚህን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተሞሉ ልዩ ችሎታዎችን «መንፈሳዊ ስጦታዎች» በማለት ይጠራቸዋል። ለመላው ቤተ ክርስቲያን ጥቅም የሚሰጡት እነኚህ ስጦታዎች እማኙ በሚኖሩት ዋና ተግባራት የሚያተኩሩ ናቸው። 

በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔርን በግልና በኅብረት «በመንፈስና በእውነት» ለማምለክ እንዲችል ያደርጉታል። መንፈሳዊ ስጦታዎች ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን እንድታመሰግንና እግዚአብሔር በጋራ የሚሰጠውን መልእክት እንድታዳምጥ ያስችላታል። 

በሁለተኛ ደረጃ፥ መንፈሳዊ ስጦታዎች በቤተ ክርስቲያን ያሉ ምእመናን እንዳቸው ሌላውን እንዲያገለግሉ በእምነትም አንዱ ሌላውን እንዲያንጽ ያገለግላሉ። 

በሦስተኛ ደረጃ፥ መንፈሳዊ ስጦታዎች ቤተ ክርስቲያን ለምን እንድታገለግል፥ የማያምኑ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ለመምራትና እነርሱም አምነው የኢየሱስን ፍቅር ርኅራኄ እንዲያሳዩ ለማድረግ ያግዛል። 

በጥናታችን ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች አንዳንድ እጅግ ጠቃሚ እውነቶችን ተመልክተናል። 

ሀ. መንፈሳዊ ስጦታዎች ተፈጥሮአዊ ችሎታዎች ብቻ አይደሉም። ነገር ግን በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሚሰጡና ልዕለ-ተፈጥሮአዊ የሆኑ፥ እግዚአብሔር በክርስቲያኑ ውስጥ ሲሠራ የሚፈጸሙ ናቸው። 

ለ. እያንዳንዱ ክርስቲያን መንፈሳዊ ስጦታ ያለው ሲሆን አንዳንድ ክርስቲያኖች ከአንድ በላይ መንፈሳዊ ስጦታዎች አሏቸው። መንፈሳዊ ስጦታዎችን እንደ ፈለገ ለሰዎች የሚያከፋፍል መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈሳዊ ስጦታዎች በተቀዳሚ በግለሰቦች ጥያቄ ወይም ፍላጎት የሚሰጡ አይደሉም። 

ሐ. የመንፈሳዊ ስጦታዎች ዓላማ ቤተ ክርስቲያንን ሁሉ ለማገልገል እንጂ ላግለሰቦች ጥቅም አይደለም። 

መ. ከመንፈሳዊ ስጦታዎች ከራሳቸው ይልቅ በጣም ተፈላጊው የሚተገበሩበት ዝንባሌ ነው። መንፈሳዊ ስጦታዎች በትዕቢትና የሰዎችን አትኩሮት ክመሳብ ፍላጎት አኳያ የሚተገበሩ ከሆነ መጨረሻቸው የግለሰቡን መንፈሳዊ ሕይወትም ሆነ የቤተ ክርስቲያንን (የአካሉን) አንድነት ማጥፋት ነው። የእርስ በርስ ፍቅርና መተሳሰብ፥ እንዲሁም እግዚአብሔርን የማገልገል ፍላጎት ለመንፈሳዊ ስጦታዎች አጠቃቀማችን ማዕክላዊ መሆን አለባቸው። ይህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን የሚያንጽ ይሆናል። 

ሠ. በልሳናት የመናገር መንፈሳዊ ስጦታን ዛሬም ልንለማመደው እንችላለን። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያን ልብ ውስጥ የመኖሩ ተቀዳሚ ምልክት አይደለም። ወይም ደግሞ የላቀ መንፈሳዊነትን የሚያሳይ አይደለም። እንደ ትንቢት ካሉ የእግዚአብሔርን ቃል መልእክት በሚታወቅ ቋንቋ ከሚያመጡና ሌሎች ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ ከሚያደርጉ ለጦታዎች ያነሰ ጥቅም የሚሰጥ ነው። በልሳናት የመናገር ስጦታ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲተገበር ካስፈለገ በአንድ ስብሰባ ከሦስት የሚበልጡ ሰዎች መናገር የላባቸውም። እድማጮች ደግሞ መልእክቱ ይደርሳቸው ዘንድ ልሳኑ መተርጎም አለበት። 

ረ. ትንቢት የመናገር መንፈሳዊ ስጦታ ዛሬም ይሠራል። ሁልጊዜ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የሰጠው የመጨረሻ መመሪያና ቃል ከሆነው ከተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል በታች አድርገን ልንመለከተው ይገባል። ትንቢተች ቁጥጥር የሚያስፈልጋቸው፥ ተራ በተራ የሚነገሩ፥ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ ለመሆናቸውና መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ከሚያስተምረው ትምህርት ጋር የሚስማሙ ለመሆናቸው መገምገም አለባቸው። 

3. ባሕርዩ እንዲለወጥና የበለጠ ኢየሱስ ክርስቶስን እየመሰለ እንዲሄድ መንፈስ ቅዱስ በአማኙ ሕይወት ውስጥ ይሠራል። በሕይወቱ በኃጢአት ኃይል ላይ ድልን እንዲያገኝ ይረዳዋል። የመንፈስ ቅዱስ ፍሬን እያሳየ በጽድቅ እንዲኖር በሕይወቱ ይረዳዋል። 

4. መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ኃይል ከክርስቲያኑ ጋር እንዲሆን ያደርጋል። ይህ ኃይል በፈውሶችና በተአምራት ሊታይ ይችላል። በተጨማሪ ሰይጣን በክርስቲያን ላይ በሚከፍታቸው ጦርነቶች ድልን በማቀዳጀት ይታያል። 

5. መንፈስ ቅዱስ በተደጋጋሚ የክርስቲያኑን ሕይወት መሙላት ይቀጥላል። 

በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና ሙላት ርእሰ-ጉዳይ ላይ ጰንጠቆስጤ (ወይም ካሪዝማቲክ) በሆኑ ክርስቲያኖችና ባልሆኑት መካከል ያለውን የአመለካከት ልዩነት ለመመልከት ረጅም ጊዜ ወስደናል። ይህ ክርክር የአንድን ሰው የእግዚአብሔር ልጅነት አይለውጥም። ነገር ግን ክርስቲያን ተለምዶአዊውን ክርስቲያናዊ ልምምድ እንዴት እንደሚመለከተው ተጽዕኖ ያደርጋል። ሁለቱም ቡድኖች ክርስቲያኖች ሁሉ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ መንፈስ ቅዱስ እንዳላቸው ይስማማሉ። ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች ግን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት መንፈስ ቅዱስ ወደ ክርስቲያን ልብ ልዩ በሆነ መንገድ የሚመጣበት አንድ ጊዜ ብቻ የሚደረግ ልምምድ እንደሆነ ያምናሉ። ብዙ ጊዜ ይህ የአንድ ጊዜ ልምምድ የሚታወቀው በልሳናት በመናገር ነው ይላሉ። 

ካሪዝማቲክ ያልሆኑ ክርስቲያኖች እንደዚህ ዓይነቱን ልምምድ የመንፈስ ቅዱስ «ሙላት» ብለው ይጠሩታል። በእነርሱ አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ያለው አመለካከት አንድ ሰው በሚያምንበት ጊዜ በመጀመሪያ የሚጠናቀቅ ሥራ እንደሆነ ነው። መንፈስ ቅዱስ፥ በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ወቅት ወደ አማኙ ልብ መጥቶ ማደሪያ በማድረግ አማኙን ወደ ክርስቶስ አካል ይጨምረዋል። የመንፈስ ቅዱስ «ሙላት» የአንድ ጊዜ የአማኙ የሕይወት ልምምድ አይደለም። ይልቁኑ በክርስቲያን የሕይወት ዘመን በሙሉ መንፈስ ቅዱስ በአማኙ ላይ በተደጋጋሚ በመምጣት የማያምን ሰው ፈጽሞ ሊኖረው በማይችል መንገድ እንዲኖር ይረዳዋል። አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስን አሳብ በአመዛኙ የሚደግፈው ሁላተኛው አመለካከት ይመስላል። 

ቁም ነገሩ ስለ መንፈስ ቅዱስ እውቀት ያላን መሆናችን እይደለም፥ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ማወቃችን በራሱ ሕይወታችንን ሊለውጥ አይችልም። ሕይወታችንን የሚለውጠው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ማድረጋችን ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የቅርብ ወዳጃችን ሲሆን ከማንም በፊት የምንነጋገረው ከእርሱ ሲሆንና በተለያዩ መንገዶች በሚናገረን ጊዜ ከእርሱ መስማትን ስንማር የሕይወታችን ገጽታ በሙሉ ይለወጣል። እርሱ ከእኛ ጋር እንደሆነ ስለምናውቅ የሕይወትን ማዕበሉች መቋቋም እንችላለን። እርሱ እጃችንን ይዞ በጆሮአችን በቀስታ እየተናገረ በመንገዱ ሁሉ ይመራናል። ኢየሱስን ስናገለግል ስራሳችን ብርታት ክምንሠራበት ይልቅ መንፈስ ቅዱስ ተንቀሳቃሽ ኃይል በመሆን መናኛውን ጥረታችንን ተጠቅሞ የብዙዎችን ሕይወት ይለውጣል። ወደ መንፈስ ቅዱስ በተጠጋንና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ደግሞ ወደ ኢየሱስ በቀረብን መጠን ሕይወታችን እየነጻ ይሄዳል። ጣፋጭ ሽታ እንዳለው ነገር ሕይወታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይሸታል። ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ራስን መግዛት የሕይወታችን ባሕርያት ስለሚሆኑ ሰዎች ሕይወታችን ለምን የተለየ እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋሉ። ዘላለማዊ የሆነውን አምላክ እግዚአብሔር አብ፥ እግዚአብሔር ወልድ፥ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ከሁሉ የቀረበ ወዳጃችን ማድረግ እንማር ዘንድ እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን። 

ጥያቄ፡- ሀ) ስለ መንፈስ ቅዱስ በርካታ እውነቶችን ከማወቅ ይልቅ ክእርሱ ጋር ሕያው የሆነ ኅብረት ማድረግ የበለጠ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ለ) ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለህ ግንኙነት በዚህ ጥናት ውስጥ ያደገው እንዴት ነው? ሐህ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ወዳጅህ ስለሆነ በጸሎትህ አመስግነው። በዚህ ግንኙነትህ እያደግህ እንድትሄድ እንዲረዳህ ጠይቀው።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: