የመጀመሪያው የመንፈስ ቅዱስ ዋና ሥራ፡- ዘላለማዊው አምላክ በውስጣችን መኖሩ

በመንፈስ ቅዱስ ላይ ያደረግነው ጥናት ሰፊ የነበረ ሲሆን ብዙ የተለያዩ አወዛጋቢ ርእሶችንም ተመልክተናል። በዚህ ሂደት ስለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ መማር ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር ባላችሁ ኅብረትሦ እንዳደጋችሁ እምነቴ ነው። በመንፈስ ቅዱስ ርእሰ ጉዳይ ላይ በሚደረግ እንደዚህ ዓይነት ዝርዝር ጥናት መካከል ስለ መንፈስ ቅዱስ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ትምህርቶችን የመዘንጋት ዕድሉ የቀለለ ነው። ስለዚህ የዚህ ትምህርት ዓላማ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ የእምነት ትምህርቶችን መከለስ ነው። 

ጥያቄ፡– ከሁሉ የላቁ ሥራዎች በሚል ለመመደብ ሁለት የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎችን መምረጥ ቢያስፈልግ የትኞቹን ትመርጥ ነበር? ለምን? 

ጥያቄ፡- ሀ) በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተፈጸመ ኃይለኛ ለውጥ ምንድን ነው? ለ) በሕይወትህ የተፈጸመ ወይም የተላማመድከው ዕፁብ ድንቅ ለውጥ ምንድን ነው? 

በሩሲያ ኮሙኒዝም የወደቀበትን ዕፁብ ድንቅ ለውጥ ማን ሊዘነጋ ይችላል? ወይም በጀርመን የበርሊን ግንብ መፍረስና በምሥራቅ ጀርመን የኮሙኒዝምን ማክተም ማን ሊዘነጋ ይችላል? ወይም በኢትዮጵያ የኃይለ ሥላሴ መንግሥትና በኋላም የኮሙኒዝም አገዛዝ የወደቁበትን ሁኔታ ማን ሊዘነጋ ይችላል? እነዚህ ዕፁብ ድንቅ ለውጦች በዓለም ታሪክ ላይ ተጽዕኖ አድርገዋል። 

በቀላሉ የሚታይ ሳይሆንም እንኳ በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን መካከል ያላው ለውጥ የበለጠ አስደናቂ ነው። በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ ውስጥ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሞተበት፥ ከሞት የተነሣበት፥ መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ላይ የወረደበት ዓመት ዓለም ከተፈጠረ ጀምር ከነበሩ ዓመታት ሁሉ የላቀ ነው። ነገር ግን በክርስቲያን ቤተሰብ ላደግንና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ደጋግመን ለሰማን ለብዙዎቻችን፥ ብዙዎች እራሳችውን ክርስቲያን ብለው በሚጠሩ ሕዝቦች መካከል ለምንኖር ለውጡ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነና እነዚህ ሦስት ክስተቶች በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ምን ያህል ታላቅ ስፍራ እንዳላቸው ዘንግተናል። ታሪኩን በጣም ከመልመዳችን የተነሣ እግዚአብሔር የሠራሳቸውን መንገዶች ማድነቅ ቀርቷል። በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላነበሩ ክርስቲያኖች ግን እንደዚህ አልነበረም። አንድ አስደናቂ ነገር እንደሆነ ያውቁ ነበር። በዓለም ሁኔታዎች ውጪአዊ ገጽታ ነገሮች ወዲያውኑ ብዙ ሳይለወጡም፥ ደቀ መዛሙርት ዓለም እንደ ድርዋ እንደማትሆን እስከሚገነዘቡ ድረስ ዕፁብ ድንቅ ነገር ተከናውኗል። 

አዳምና ሔዋን በኃጢአት ክወደቁበት ከፍጥረት ጀምሮ ኢየሱስ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ እግዚአብሔር ኃጢአት በዓለም ያመጣቸውን ውጤቶች ድል ለማድረግ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲሠራ ቆይቷል። የእስራኤልን ሕዝብ በመምረጥ በዚህ ሕዝብ አማካይነት የዓለም ሕዝብ በሙሉ ወደ እርሱ ቀርቦ በመንፈስና በእውነት እንዲያመልከው ለማድረግ ጥሯል። ነገር ግን የመረጠውና በመካከሉ የኖረበት ሕዝብ እንኳ በኃጢአት በመውደቁ መቀጣት ነበረበት። እግዚአብሔር የተመረጠውን ሕዝብ ለመቅጣት ወደ ምርኮ ከመላኩ በፊት በነቢያቱ በኩል ስለሚመጣው አዲስ ዘመን ለሕዝቡ ተናገረ። በዚያ አዲስ ዘመን የቀድሞው ኪዳን ለሰዎች ሊያደርግ ያልቻላቸው ነገሮች ሁሉ እንደሚፈጸሙና ሕዝቡም ከልባቸው እግዚአብሔርን እንደሚያመልኩ ነበር (ሕዝ 36፡26-27)። 

በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ከእግዚአብሔር ዘንድ በሆነ የጸጥታ ጊዜ ሕዝቡ ከታወክ በኋላ በድንገት መሢሑ ኢየሱስ ክርስቶስ መጣ። ሕዝቡ አሁን አስደናቂው የእግዚአብሔር መንግሥት ይጀመራል ብሎ አሰበ። በዚያ ምትክ ቀን የጠበቁት መሢሕ እነርሱ እንዳሰቡት ሳይሆን ቀረ። ምድራዊ መንግሥት አልተመሠረተም። በዚህ ፈንታ መሢሑ በመስቀል ላይ ሞተ። ነገር ግን በሁላት ክስተቶች እግዚአብሔር ነገሮች የነበራቸውን አካሄድ ካፈራረሰ በኋላ አዲስ ነገርን መሠረተ። የመጀመሪያው የኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣትና ወደ ሰማይ ዐርጐ በአባቱ ዙፋን ቀኝ መቀመጥ ነው። ይህ ድርጊት ሰይጣንና ሞት በአማኞች ላይ የነበራቸውን ሥልጣን መደምሰስ ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑንም አሳየ። ስለ አዲስ ኪዳን የተናገራቸው ነገሮች በሙሉሰዎች ኃጢአታቸው በመስቀል ላይ በፈሰሰው በኢየሱስ ደም ተሸፍኖ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት አዲስ መንገድ መፈጠሩ እውነት መሆኑን አረጋገጠ። 

በአስደናቂ ሁኔታ ዓለምን የለወጠው ሁለተኛ ድርጊት የተፈጸመው በበዓለ ኃምሣ ቀን በአማኞች ላይ መንፈስ ቅዱስ ሲወርድ ነበር። የብሉይ ኪዳን ተላሩዎች በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ተፈጸሙ። ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ከልቡ በራሱ ጥረት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንዲታዘዝ እደረገ። 

ነገር ግን እግዚአብሔር ይህን አዲስ ዘመን ያመጣው ሕዝቡ በጠበቀው መንገድ አልነበረም። ብሉይ ኪዳን መሢሑ በመጣ ጊዜ ክፋትን ሁሉ የሚያስወግድ አዲስ ዘመን እንደሚጀመር የሚናገር ይመስላል። የዓለም ክፉ ሕዝቦች ጠፍተው የእግዚአብሔር ሕዝብ በቅድስና አምላኩን የሚያመልክበት ጊዜ እንደሚሆን ይመስል ነበር። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ቃል የገባበትን «አዲስ ዘመን» በጀመረበት ጊዜ ግን በአዳምና ሔዋን ኃጢአት የተጀመረውን አሮጌውን ዘመን አላስወገደም። በአዲስ ኪዳን የሚጀመረው አዲስ ዘመንና በእግዚአብሔር ላይ ዓመፃን የሚያሳየው የቀድሞው ዘመን በአንድነት ጐን ለጐን መኖራቸውን ቀጠሉ። እግዚአብሔር መንግሥቱን በሕዝቡ መካከል ቢመሠርት ኃጢአትና በሽታው ቀን አልጠፋም ነበር። ሰይጣን፥ ኃጢአትና በሽታ ጠፍተው የቀድሞው ዘመን ሙሉ በሙሉ የሚወገደው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገና ሲመለስ ነው። 

እግዚአብሔር ተስፋ በሰጠበት በአዲስ ዘመን የመኖራችን ዋና ምልክት መንፈስ ቅዱስ ነው። ኃጢአትን እንዲያሸንፍና ሁል ጊዜ እርሱ በሚፈቅደው መንገድ እንዲያመልኩት እያስቻላ መንፈስ ቅዱስ በሰው ውስጥ ለማደር ባለው ኃይል አማካኝነት እግዚአብሔር ራሱ በሰው ውስጥ ይኖራል። 

እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠው አዲሱ ዘመን የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ተስፋዎች ሁሉ እየተለማመድን፥ በሥጋት ከዚህ ከአሮጌው ዘመንና ከሰብአዊ ድካማችን ጋር እየታገልንም እንኳ ቢሆን አሁን በመለኮታዊ ኃይል እንድንኖር የሚረዳን መንፈስ ቅዱስ ነው። 

አሁንም የምንኖረው በወደቀው ዓለም ውስጥ ነው። የእግዚአብሔርን ፍላጐቶች የምንፈልገውን ያህል አንታዘዝም። ብዙ ጊዜ የኃጢአታዊ ተፈጥሮአችንን ፍላጐቶች በማሟላት በአሮጌው ዘመን እንደሚኖሩ ሰዎች እንመላለሳለን። ይህ አሮጌው ዘመን ያለማቋረጥ በዙሪያችን ነው። በሽታና ሞት አሁንም አሉ። ስደትም እንደቀጠለ ነው። ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ የሰጣቸውን ኃይል እንኳ ስሙላት እየተላማመዱት እይደለም። ቤተ ክርስቲያን መሆን የሚገባትን ያህል የተቀዳጀች አይደለችም። ነገር ግን በምድር ላይ ያለ ሕይወት አሳዛኝ ቢሆንም እንኳ መንፈስ ቅዱስ በልባችን ስላለ መኖር የተጀመረውን የዘላለማዊ መንግሥት ጉዳይ ወደ ፍጻሜ እንደሚያመጣው ሙሉ እምነት አለን። እግዚአብሔር ስለ አዲሱ ዘመን የገባቸው ቃል ኪዳኖች አንድ ቀን ሙሉ በሙሉ የራሳችን እንደሚሆኑ እርሱ ዋስትናችን፥ ቀብዳችንና መያዣችን ነው (ኤፌ 1፡13-14)። 

ጥያቄ፡– የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት። ሕዝ. 36፡26-28 37፡14} ኤር. 31፡31-34። ሀ) እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ለመኖር ስላለው ፍላጐት ምን ያስተምሩፃል? ለ) በአዲሱ ኪዳን እግዚአብሔርና ሰው ስላሚኖራቸው ግንኙነት የተሰጡት ተስፋዎች ምንድን ናቸው? 

በብሉይ ኪዳን ተዘውትረው ከተጠቀሱት ዋና አሳቦች አንዱ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ለማደር መፈለጉ ነው። ይህ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል የማደሩ ጉዳይ በሁለት መንገዶች ይታያል። በመጀመሪያ፥ መደበኛ በሆነ ሁኔታ የእግዚአብሔር በሰዎች መካከል ማደሩ ነው። እስራኤላውያን በምድረ በጻ በኖሩበት ወቅት እግዚአብሔር በመካከላቸው ያድር ዘንድ የመገናኛ ድንኳን እንዲያዘጋጁ አዘዛቸው። የመገናኛው ድንኳን የሚያሳየው እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ለማደር መፈለጉን ቢሆንም እንኳ በተራው ሰውና የእግዚአብሔር ማደሪያ በሆነው በቅድስተ ቅዱሳን መካከል ሁልጊዜ ግድግዳ ነበር። ወደ እግዚአብሔር እንዲቀርቡ የሚፈቀድላቸው ሁልጊዜ ካህናቱ ብቻ ነበሩ። የእግዚአብሔር ሕዝብ ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ኅብረት እንዳይኖራቸው ያገደው ኃጢአት ለመሆኑ የዘወትር አስታዋሽ ነበር። ኋላ በሰለሞን ዘመን እግዚአብሔር ሕዝቡ መካከል የኖረው ሰለሞን በሠራው ቤተ መቅደስ ውስጥ ነበር። ሆኖም ግን ወደ እግዚአብሔር እንዳንቀርብ የሚያግዱት ግድግዳዎች እንዳሉ ቀጠሉ። 

ሁለተኛው፥ መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ የእግዚአብሔር በሰዎች መካከል መገኘት ነው። ፈርዖን ፊት በሚሆንበት ወቅት ከእርሱ ጋር እንደሚሆን እግዚአብሔር ለሙሴ ቃል ገብቶላት ነበር (ዘፀአ 3፡12፣ 33፡14-17)። እግዚአብሔር ኢያሱና ሕዝቡ የተስፋዪቱን ምድር ከከነዓናውያን እጅ ድል ባደረጉ ጊዜ አብሮአቸው እንደሚሆን ቃል ገብቶላቸው ነበር (ኢያሱ 5፥ 9)። ሕዝቡ በምርኮ በነበሩበት ወቅት ደግሞ በስደት ማዕበል ውስጥ ቢሆኑም እንኳ እግዚአብሔር አብሮአቸው እንደሚሆን ቃል ገብቶላቸው ነበር (ኢሳ. 43፡2)። እነዚህ ግን እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ልዩ በሆነ መንገድ የሚገኝባቸው ጊዜያዊ ወቅቶች ነበሩ። ችግሮቻቸውን ሁሉ ለመርታት እንዳይችሉ ዘላቂ የእግዚአብሔር ህልውና ከሕዝቡ ጋር አልነበረም። 

ነገሮች በሦስት ዐበይት መንገዶች የሚለወጡበትን ጊዜ እግዚአብሔር በነቢያት በኩል አስቀድሞ ተናገረ። 

ሀ. የእግዚአብሔር ሕዝብ አዲስ ልብ እንደሚኖራቸው (ኤር. 31፡31-33)። በእስራኤላውያን እንደሆነው ከእግዚአብሔር ርቀው ከመባዘን ይልቅ እግዚአብሔርን የሚታዘዝ ልብ ይኖራቸዋል። 

ለ. አዲሱ ልብ እግዚአብሔር ለሕዝቡ «እዲስ መንፈስ» የመስጠቱ ውጤት ነው (ሕዝ. 36፡26)። ይህ አዲስ መንፈስ አዲስ መንፈሳዊ ሕይወት፥ አዲስ ተፈጥሮ ነው። ይህ በሰው ውስጥ የሚሆነው አዲስ መንፈስ የሚገኘው የእዚአብሔር ሕዝብ ትእዛዛቱን እንዲጠብቁ ከሚያስችለውና ሰዎችን ማደሪያው ካደረገው የመንፈስ ቅዱስ ህልውና ነው (ሕዝ. 36፡27)። 

ሐ. የእግዚአብሔር መንፈስ በሰው ሕይወት ውስጥ ይኖራል። ይህ ማለት ዘላለማዊ የሆነው እግዚአብሔር በሕዝቡ ልብ ውስጥ ይኖራል ማለት ነው (ሕዝ. 37፡14)። 

በብሉይ ኪዳን ተስፋ የተሰጠው አዲስ ኪዳን በሁለት መንገዶች ፍጻሜውን አግኝቷል። በመጀመሪያ፥ የመሢሑ፥ የአማኑኤል፥ ከሕዝቡ ጋር የሚኖር አምላክ መወለድ ነበር (ማቴ. 1፡23)። ኢየሱስ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ በሰጠው የተስፋ ቃል እንደተናገረው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእነርሱ ጋር እንደሚሆን ነው (ማቴ. 28፡20)። በኢየሱስ በኩል (የሰውን ሥጋ የለበሰው አምላክ) እግዚአብሔር ሁልጊዜ ከእማኞች ሁሉ ጋር ይሆናል። በሁለተኛ ደረጃ ፥ መንፈስ ቅዱስ በሰው ልብ ውስጥ በማደር በህልውናው አማካኝነት እግዚአብሔር በልጆቹ ሁሉ ውስጥና በመካከላቸውም ይኖራል። 

ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ። 1ኛ ተሰ 4፡8፤ 1ኛ ቆሮ. 6፡19፤ (ኤፌ. 5፡18፤ 2ኛ ቆሮ. 1፡22፤ 3፡3፤ 6፡16፤ ገላ. 4፡6፤ ሮሜ 8፡9-11፤ ኤፌ. 2፡22። እነዚህ ጥቅሶች በመንፈስ ቅዱስ፥ በእግዚአብሔር ሕልውናና በአማኞች መካከል ስላለው ግንኙነት ምን ይናገራሉ? 

በአዲስ ኪዳን በሞላ መንፈስ ቅዱስ በእግዚአብሔር ሕዝቦች ውስጥ እንደሚያድርና በእግዚአብሔር ሕዝቦች መካከል እንደሚኖር ተጽፏል። ዛሬም ቢሆን መንፈስ ቅዱስ በሕዝቡ ውስጥ የሚያድርባቸው ሁለት መንገዶች አሉ። በመጀመሪያ፥ የእያንዳንዱን አማኝ ልብ ማደሪያው በማድረግ በውስጡ ይኖራል (2ኛ ቆሮ. 6፡16)። እያንዳንዱ ክርስቲያን ዘላለማዊ አምላክ በውስጡ ይኖራል። በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር በመገናኛው ድንኳንና በቤተ መቅደስ ውስጥ እንዳደረ ሁሉ፥ አንድ ሰው እንዳመነ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ በልቡ ውስጥ ማደር ይጀምራል። በሁለተኛ ደረጃ ፥ መንፈስ ቅዱስ የክርስቶስ አካል በሆነችው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያድራል (1ኛ ቆሮ. 3፡16)። እሁን መንፈስ ቅዱስ በሚታይ ሰው ሠራሽ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሳይሆን በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ስለሚያድር የእግዚአብሔር ሕዝቦች ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ይሆናሉ። ይህ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ማደሪያ ይሆን ዘንድ ያለማቋረጥ ይገነባል (ኤፌ. 2፡22)። 

በሕዝቅኤል መጽሐፍ በክብር ደመና የታየው የእግዚአብሔር ህልውና የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ትቶ እንደሄደ እንመለከታለን (ሕዝ. 10፡1-19፤ 11፡22-23)። አሁን ደግሞ የእግዚአብሔር ሕልውና ወደ ሕዝቡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመለስ እንመለከታለን። በዚህ ጊዜ በሚታይ የክብር ደመና ሳይሆን በማይታይ እውነተኛ ህልውና ባለው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው። የእግዚአብሔር ክብር ደመና እስራኤላውያንን በምድረ በዳ እንደመራ (ዘፀአ 13፡2) አሁን ደግሞ በዘላለማዊ የእግዚአብሔር መንፈስ ውስጣዊ ህልውና አማካኝነት የእግዚአብሔር ሕዝቦች በመንፈስ ቅዱስ ይመራሉ (ገላ5፡16፥ 5)። 

የእግዚአብሔር ማደሪያ አሁን የሚታይ ሕንፃ አይደለም። የምናመልክበት የቤተ ክርስቲያን ሕንፃም አይደለም። የእግዚአብሔር ማደሪያ የእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብና በዓለም ውስጥ በማንኛውም ስፍራ የሚኖሩ የክርስቲያኖች ኅብረት ነው። ብዙ ጊዜ እንደማንኛውም ክርስቲያን ስለ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ አንድ ልዩ ነገር ይሰማናል። እግዚአብሔር ማደሪያውን ያደረገው በዚያ ሕንህ ውስጥ እንደሆነ እናስባለን። ይህ አስተሳሰብ በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል የተከናወነውን አስደናቂ ለውጥ ፈጽሞ ያላገናዘበ ነው። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ማደሪያውን የሚያደርግበት እንደ ቤተ መቅደስ ያለ ልዩ ስፍራ ነበረው። በአዲስ ኪዳን ግን የእግዚአብሔር ሰዎች ለሕንፃ የተለየ ክብር አይሰጡም። ምክንያቱም እግዚአብሔር በሕንፃ ውስጥ መኖሩን አቁሟልና። ይልቁኑ እግዚአብሔር በሙሉ ኃይሉና ክብሩ በእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብ ውስጥ ይኖራል። በኅብረት ባሉ ክርስቲያኖች መካከል ያድራል። የቤተ ከርስቲያን ሕንን ልዩ የሚያደርገው ቦታው ወይም ሕንፃው ሳይሆን የእግዚአብሔር ሕዝብ መሰብሰብ ነው። የእግዚአብሔር ሰዎች በሚሰበሰቡበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ በመካከላቸው ስላሚሆን ቤተ መቅደስ ይሆናሉ። ኢየሱስ ሁለት ወይም ሦስት ሆናችሁ በስሜ በተሰበሰባችሁበት በመካከላችሁ እገኛለሁ ያለው ለዚህ ነው (ማቴ. 18፡20)። ኢየሱስ በሕዝቡ መካከል ይገኛል። ይህ እውን የሚሆነው በመንፈስ ቅዱስ በሕዝቡ ውስጥ የማደር አገልግሎት ነበር። 

ጥያቄ፡- ሀ) በምታደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር መሆኑን አውቀህ ብትሆን ይህ እውነት እንዴት ያበረታህ ነበር? ለ) እግዚአብሔር ሁልጊዜ ከአንተ ጋር መሆኑን አውቀህ ቢሆን ኖሮ በኋላ የሚያሳፍሩህን ነገሮች ከማድረግ እንዴት ልትቆጠብ ትችል ነበር? 

ዘላለማዊው እግዚአብሔር ከሰው ልጅ ጋር ለመኖር መጥቷል። አሐዱ ሥሉስ የሆነው አምላክ በመንፈስ ቅዱስ ህልውና መጥቷል። እዚአብሔር አብ የበረከቶች ሁሉ አመንጪ ሲሆን እዚህን በረከቶች ለእኛ እንዲኖሩ ያደረገ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የእግዚአብሔር በረከተች በሙሉ ለእኛ እውን የሚደረጉበት መሣሪያ ነው። ድነት (ደኅንነት)ን እንቀበል ዘንድ ልባችንን ያነሣሣው እርሱ ነው (2ኛ ተሰ. 2፡3)። ደስታን የሚሰጠን፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚገልጥልን ቃሉን ለሌሎች እንድናካፍል የሚያስችለን እርሱ ነው (1ኛ ቆሮ. 2፡10፤ 1ኛ ተሰ. 5-6)። በልባችን ዘላለማዊው እግዚአብሔር ሲኖር ነገሮች ይለወጣሉ። ከሌሎች ጋር በምንካፈልበት ወቅት እግዚአብሔር ካለ በኃይል በመሥራቱ ምክንያት መንፈስ ቅዱስ አእምሮአቸውን ይከፍትና እንዲያምኑ ያስችላቸዋል (1ኛ ቆሮ. 2፡6-16፤ 2ኛ ተሰ. 2፡13)። የተሰበከውን የእግዚአብሔር ቃል ተከትሎ መንፈስ ቅዱስ በአገልጋዮቹ አማካይነት በመሥራት እንደ ተአምራትና ፈውስ የመሳሰሉ ኃይላኛ ድርጊቶችን ያከናውናል (ሮሜ. 15፡18-19)። መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዱን ክርስቲያን በሕይወት ዘመኑ በሙሉ ይናገረዋል፤ ይመራዋል። የግለሰቡ እያንዳንዱ የሕይወት ክፍል ማለትም አእምሮው አመለካከቱና ተግባሩ ሁሉ ይለካል። መንፈስ ቅዱስ ሕይወታችንን የሚያንፀባርቁ ባሕርያትን ያዘለ ፍሬ ያፈራል። መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ኑሮ እንኖር ዘንድ የሚያስችለን የመንፈሳዊነታችን ምንጭ ነው። 

የመንፈስ ቅዱስ ህልውና የእግዚአብሔርን ማኅበረሰብ ተግባራት በከፍተኛ ደረጃ የሚነካ ነው። አምልኮአችን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተሞላ ነው። እንደ አምልኮአችን አንዱ አካል መንፈስ ቅዱስ የህልውናውን እውነታ የሚያሳዩና የክርስቶስን አካል የሚያገለግሉ የተላያዩ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ይሰጣል። 

ጥያቄ፡- ሀ) ዘላለማዊ እግዚአብሔር የሆነው መንፈስ ቅዱስ በልብህ በመኖሩ ምክንያት የተለወጡ የሕይወትህን ጉዳዮች ዘርዝር። ለ) ስለ መንፈስ ቅዱስ ከምንማራቸው እውነቶች ምናልባት ይህ ከሁሉ የላቀ የሚሆነው በምን መንገድ ነው? 

ዘላለማዊ የሆነው እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜ በውስጣችን ይኖራል ማለት ምን ማለት ይመስልሃል? ይህ ምን ዓይነት አስደናቂ እውነት መሆኑን ለማሳየት አንዳንድ ሁኔታዎችን ከዕለታዊ የሕይወታችን ጉዳዮች እንውሰድ። 

1. እራሳችን ወይም እጅግ ከምንወዳቸው ሰዎች እንዳቸው እስከ ሞት ድረስ ብንታመም። ለእንድ ሰው እጅግ የሚወደው ሰው ልጅ ሚስቱ ወይም ወላጆቹ ወደ ሞት ሲያዘግሙ ክማየት የባሰ ከባድ ፈተና የለም። በዚህ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ዘላለማዊው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አለ። በአንድ በኩል ተአምራዊ በሆነ ኃይል ፈውስን በማምጣት ቅጽበታዊ መፍትሔ ለመስጠት የሚችል እርሱ ነው። ወይም እግዚአብሔር ያ ሰው በሞት ጥላ መካከል እንዲሄድ ቢፈቅድ በዚህ ሁኔታ ውስጥ አብሮ በመሆን የሚያጽናና የመለያየትን ሐዘን ለመሸከም እንዲቻል የሚረዳ መንፈስ ቅዱስ ነው። እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ብርታትን የሚለግስ እርሱ ነው። 

2. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰብዓዊ የሆነ መፍትሔ የሌላቸው ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን። የተላያዩ ክርስቲያኖች ሲጋጩ ይታያሉ፥ በሰላም ለመኖርና ላመሥራት ፈጽሞ የሚችሉ አይመስሉም፤ ቤተ ክርስቲያን የገንዘብ ችግሮች ስላሉባት ለወንጌላውያን የሚሆን ደመወዝ እንኳ መክፈል አልተቻለም እንበል። ያላንባቸው እነዚህን ሁኔታዎች በሙላት የሚያውቀው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አብሮን ስላለ መልሶቹን እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ሌላው ቀርቶ ስሕተቶቻችንን እንኳ በመውሰድ ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርን ለማምጣት ሊጠቀምባቸው እንደሚችል እርግጠኞች መሆን እንችላለን። 

3. ከቤተሰባችን፥ ከማኅበረሰባችን ወይም ከመንግሥት ስደት በተነሣብን ወቅት። ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብድናጐም በሚነድ የእቶን እሳት ውስጥ በተጣሉ ጊዜ የሰውን ልጆች የሚመስል አራተኛ ሰው እንዴት አብሮአቸው እንደነበር አስታውስ። በዚያ ታሪክ ሁላችንም እንደነቃለን። ያ ምናልባት ኢየሱስ ክርስቶስ ሳይሆን አይቀርም ከእነርሱ ጋር ሁልጊዜ ለመሆን በዚያ አልቀረም። ከእቶኑ እሳት እንደወጡ ወዲያውኑ ተለያቸው። እኛ ግን ከዚህ የሚበልጥ ነገር አለን። የመንፈስ ቅዱስ ቋሚ ህልውና አብሮን አለ። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርት በመንግሥት ባለሥልጣን ፊት ቢሆኑ እንዳይፈሩ መናገሩ የሚያስደንቅ አይደለም (ማቴ. 10፡17-20)። ኃይልን ሁሉ የተሞላው መንፈስ ቅዱስ በልባቸው ላለሚኖር ምን እንደሚናገሩ የሚሰጡት ምላሽ ምን እንደሚሆን ያውቅ ነበር። ጳውሎስ ክርስቲያን ቢጣልም እንኳ እንደማይጠፋ ተናግሯል (2ኛ ቆሮ. 2፡7-9)። ለምን? ምክንያቱም የትንሣኤው ኃይል የእርሱ ስለሆነና መንፈስ ቅዱስ ስልቡ እንደሚኖር ስለሚያውቅ ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) የዘላለማዊ እግዚአብሔር በቋሚነት በልብህ ወይም በቤተ ክርስቲያንህ መገኘት ታላቅ መበረታታትን ሊያመጣ የሚችልባቸውን ሌሎች ሁኔታዎች ዘርዝር። ለ) መንፈስ ቅዱስ አማኑኤል ስለመሆኑ ማለትም ሁልጊዜ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ከእኛ ጋር የሚሆን አምላክ ስለመሆኑ ታመሰግነው ዘንድ ጊዘ ወሰድ።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: