የመፈወስና ተአምራትን የማድረግ ስጦታዎች

ጉባኤው እጅግ ታላቅ ነበር። እርሱን ለመስማት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰብስበው ነበር። ያን ያህል ቁጥር ያለው ሰው የተሰበሰበት ዋና ምክንያት ግን ተአምራት ለማየት ነው። ይህ ሰው የፈውስ ስጦታ እንዳለው ይነገር ነበር። በስብከቱ መጨረሻ ላይ የታመሙ ሰዎች ሁሉ እንዲቆሙ ጠየቀ። ከአንድ በላይ በሽታ ያለባቸው ቢሆንም ፈውስን እንደሚያገኙ ነገራቸው። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ይፈወሱ ዘንድ ቆሙ። ከዚህ በኋላ እንደ ተፈወሱ አወጀ። በጉባኤው መካክል ከአዲስ አበባ የመጣች በጠና የታመመች ሌት ነበረች። እንደ ተፈወሰች አምና ወደ ቤቷ ተመለሰች። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ሞተች። 

እግዚአብሔር፥ ፈዋሽ እምላክ ነው። ነገር ቀን እግዚአብሔር የሚፈውሰው ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ነውን? ሰዎች መፈወሳቸው ከተነገራቸው በኋላ ባይፈወሱ ምንድን ነው የሚሆነው? ጥፋቱ የማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል። 

ጥያቄ፡- ማቴ. 12፡ 25-28፤ ሉቃስ 1፡21 ጀምሮ፤ ዮሐ 12፡31፤ ራእይ 21፡4። እነዚህ ጥቅሶች በኢየሱስ ዘመን የተአምራት ሚና ምን እንደነበር ያሳያሉ? 

እግዚአብሔር ተአምራትን የሚሠራ አምላክ ነው። ተአምራትን ሲሠራ ነበር። ወደፊትም ተአምራትን መሥራት ይቀጥላል። እግዚአብሔር ተአምራትን ማድረጉን አቁሟል የሚሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ቢኖሩም እንኳ ለዚህ አባባላቸው ምንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ የላቸውም። ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ የምንመለከታቸው መረጃዎች የሚያሳዩን እግዚአብሔር ተአምራት ማድረጉን እንደቀጠለ ነው። ስለዚህ ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር ተአምራትን ያደርግ ዘንድ፥ ይፈውስ ዘንድ፥ ሰዎችን ከአጋንንት ነፃ ያወጣ ዘንድ፥ ወዘተ… ልንጠብቅ እንችላለን። 

ነገር ግን እግዚአብሔር ተአምራትን በብሉይ ኪዳንና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ባደረገው ዓይነት በተዘወተረ ሁኔታ እንደሚያደርግ ማመንና መጠበቅ ትክክል አይደለም። በተጨማሪ ተአምራት ማንኛውም ክርስቲያን በፈለገው ጊዜ ሊያደርገው የሚችለው ነገር እንደሆነ ማሰብም ስሕተት ነው። ተአምራትን የማድረግ ኃይል ፈጽሞ በሰው ላይ የሚመሠረት አይደለም። የተአምራት መሠረት እግዚአብሔር ነው። ተአምራትን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔርን ሊያዝዘው የሚችል ማንም የለም። አንድ ሰው ሊያደርግ የሚችለው ነገር የእግዚአብሔር ተአምራት ይፈጸም ዘንድ መጠቀሚያ መሣሪያ ለመሆን እራሱን አዘጋጅተ መቅረብ ነው። ይህ ነገር ደግሞ ደረጃ በደረጃ ሊፈጸም ይገባል። ሰዎች ዛሬ በተአምራት ላይ ያላቸው በጥልቅ የመወሰድ ሁኔታ አደገኛ ነው። ለማመን ምልክትን እንደሚጠይቁ አይሁዶች ሆነናል። ኢየሱስ ከሞት የመነሣቱ እውነት ምልክት የሆነውን የዮናስን ምልክት ለማመን እምቢ እንላለን (ማቴ. 12፡39-4)። 

እግዚአብሔር በዚህ ዘመን ምንም ተአምራትን አያደርግም የሚሉትና እግዚአብሔር በእኛ ትእዛዝ ሁልጊዜ ተአምራትን ያደርጋል የሚሉ ሁለቱም አቋሞች ስሕተት ናቸው። እውነቱ ያለው በሁለቱ መካከል ነው። በልሳናት እንደ መናገርና እንደ ትንቢት ስጦታዎች የፈውስና ተአምራትን የማድረግ ስጦታዎችም ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የጋላ ክርክር የሚካሄድባቸው ናቸው። በሌሎች ስጦታዎች እንደሆነው ሁሉ የከረሩ አቋሞችና ከአግባብ ውጭ የሆኑ አጠቃቀሞች ሰዎች ከሚገባ በላይ እንዲሄዱ አድርገዋቸዋል። 

ጥያቄ፡- ሀ) ተአምራትን እንዴት ትተረጉመዋለህ? ለ) መለኮታዊ ፈውስን እንዴት ትተረጉመዋለህ? 

አንድ አስደናቂ ነገር ሲፈጸምልን «ተአምር ነው» እንላለን። ሕመም ሲሰማንና መድኃኒት በመውሰድ ሊሻለን እግዚአብሔር ፈወሰን እንላለን። በአንድ አንጻር ስናየው በሕይወታችን የሚፈጸሙ ነገሮች በሙሉ ተአምራት ናቸው። አካላዊ ሕይወታችን ራሱ ተአምር ነው። ሰውነታችን ከበሽታ ባገገመ ጊዜ ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚገኝ ፈውስ ተቀበልን ማለት ነው። 

እግዚአብሔር ተአምራትን አደረገ ወይም በተአምር ፈውስን ሰጠ ስንል በእርግጥ ምን ማለታችን ነው? ተአምር የምንለው እግዚአብሔር ዓለም ትተዳደርባቸው ዘንድ የደነገጋቸውን ተፈጥሮአዊ ሕግጋት ያለፈ ነገር ሲፈጽም ነው። ይህም ማለት እግዚአብሔር በተፈጥሮአዊ መንገድ ፈጽሞ የማይቻለውን ነገር ሲያደርግ ነው። መለኮታዊ ፈውስ ማለት እግዚአብሔር በሰው ሰውነት የሚካሄደውን ተፈጥሮአዊ የእርጅናና የበሽታ ሂደት ያለፈ ነገር ሲያደርግ ነው። እግዚአብሔር በተፈጥሮአዊ መንገድ በሰውነት ውስጥ ፈውስ ሲያካሂድ በሽታውን በቅጽበት በማንሣት ሙሉ ጤንነትን ይመልሳል። ይህ የሚሆነው በሽታን ለማስወገድ እግዚአብሔር በተፈጥሮ ከሰጠው የመድኃኒት ውጤት የተለየ ነው። 

ለማያምኑም ሆነ ለሚያምኑ ሰዎች ያልተለመዱ ነገሮች ይደረጋሉ። ነገር ግን ሁልጊዜ እንደ ልዕለ-ተፈጥሮአዊ ተአምራት መታየት የለባቸውም። እግዚአብሔር የሥጋ ፈውስን የሚሰጥበት የተለመደ መንገድ በተፈጥሮአዊ ሕግጋትና ለሰው ልጆች በሰጠው ተፈጥሮአዊ ፈዋሽ መድኃኒቶች አማካኝነት ነው። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላለው ተአምራትና ፈውስ ስንነጋገር እግዚአብሔር ፍጥረታትን ለማስተዳደርና ለመምራት ከደነገጋቸው ተፈጥሮአዊ ሕግጋት ባሻገር (እግዚአብሔር) ጣልቃ ገብቶ ካላደረገው በስተቀር ፈጽሞ ሊሆን የማይችለውን ነገር ነው።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.