የብሉይ ኪዳን ተአምራትና አዲሱን ዘመን በተስፋ መመልከት

2ኛ ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት። ዘጸአ 14፡5-22፤ ኢያሱ 10፡11-14 1ኛ ሳሙ. 12፡18፤ 1ኛ ነገ 18፡30-38፤ 2ኛ ነገ. 4፡32-35። የእግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ሰዎች አማካኝነት የሠራቸውን ተአምራት ዘርዝር። 

በብሉይ ኪዳን የተዘረዘሩ ተአምራት በርካታ ናቸው። ከብሉይ ኪዳን የምንማረው ነገር ቢኖር እግዚአብሔር ታላቅና ኃያል፥ ተአምራትን ማድረግ የሚችል ለሕዝቡም ይህንን በተደጋጋሚ ያደረገ መሆኑን ነው። ቀይ ባሕርን መክፈል፥ የኢያሪኮን ግንብ መጣል በሽተኞችን መፈወስ፥ ሙታንን ማስነሣት እነዚህ ሁሉ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን የፈጸማቸው ተአምራት ናቸው።  

ነገር ግን የብሉይ ኪዳን ተአምራት አስገራሚ የሆነ የአፈጻጸም ሂደት አላቸው። ተአምራቱ ደረጃ በደረጃ የሚፈጸሙ ይመስላሉ። እግዚአብሔር በርካታ ተአምራት ያደረገባቸው ጊዜያት ነበሩ። እጅግ በጣም ጥቂት ተአምራት የፈፀመባቸው ረጅም ጊዜያትም ነበሩ። እግዚአብሔር ምንም ተአምራት ያላደረገበት ወቅት የሕዝቡን መንፈሳዊ ሕይወት እጅግ ዝቅተኛ የነበረበት ወቅት እንደሆነ ልናስብ እንችላለን። ነገር ግን እንደዚያ አልነበረም። የእስራኤል ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት ከፍተኛ የነበረበት የዳዊት አመራር ዘመን አንዳችም ተአምራት አልተደረገም ለማለት የሚያስችል ነበር። 

የብሉይ ኪዳን ታሪክ እንደሚያመላክተን ተአምራት እጅግ ቶሎ ይፈጸሙ የነበሩበት ዘመን የነበረ ቢሆንም የእስራኤል ሕዝብ አብዛኛው ታሪከ ግን በቁጥር እጅግ አነስተኛ ተአምራት የተፈጸመበት ጊዜ ነበር። ተአምራት የተዘወተረባቸው ሦስት ዘመናት ነበሩ። 

1. እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ በሠራበት የፍጥረት ዘመን። 

2. እግዚአብሔር እስራኤላውያን ከባርነት ነፃ በማውጣት በምድረ በዳ ውስጥ መርቶ በተስፋይቱ ምድር ያሳረፋቸው ዘመን። 

3. ኤልያስና ኤልሳዕ ነቢያት የነበሩበት ዘመን። 

ይህ ማለት እግዚአብሔር በሌሎች ዘመናት ተአምራትን አላደረገም ማለት አይደለም። ወይም ደግሞ እግዚአብሔር በሁሉም ዘመናት ተአምራትን ሊያደርግ አይችልም ማለት አይደለም። ይልቁኑ ይህ የሚያሳየው በእግዚአብሔር አሠራር ውስጥ እግዚአብሔር ለአንድ በግልጽ ተለይቶ ለታወቀ ዓላማ ተአምራትን ለመሥራት የሚፈልግበትና ብዙ ተአምራትን ለመሥራት የማይመርጥበት ጊዜ መኖሩን ነው። 

ከብሉይ ኪዳን የምንመለከተው ሌላው አስገራሚ ነገር ተአምራት በሚፈጸሙበት ወቅት ተአምራቱ ለእግዚአብሔር ስም ክብርን የሚያመጡ በሰዎች ዘንድ ፈሪሃ እግዚአብሔርን የሚያሳድሩ ቢሆንም እንኳ ብዙ ጊዜ ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው እምነት እንዲጨምር አያደርጉም ነበር። በሙሴና በኢያሱ ዘመን እግዚአብሔር በርካታ ተአምራት ቢያደርግም እንኳ የእስራኤል ሕዝብ እምነት አልነበራቸውም፥ ያጉረመርሙ ነበር፡ ስለሆነም እግዚአብሔር አብዛኛዎቹን አጠፋቸው። በተመሳሳይ መንገድ በኤልያስና በኤልሳዕ ዘመን በርካታ ተአምራት የነበሩ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር የበዓልን ነቢያት ለማሸነፍ በርካታ ተአምራት ቢያሳይም (1ኛ ነገ. 18፡30-38)፥ እስራኤላውያን ሕይወታቸውን ለውጠው በእውነተኛ ልብ እግዚአብሔርን አልተከተሉም ነበር። በተቃራኒው እጅግ ጥቂት ተአምራት ብቻ በተደረገባቸው በዳዊትና በሰለሞን ዘመናት ሕዝቡ ጤነኛ መንፈሳዊ ሕይወት ነበራቸው። 

ስለዚህ ከብሉይ ኪዳን ታሪኮች ልንገነዘባቸው የሚገቡ ሦስት ዋና ትምህርቶች 

ሀ) እግዚአብሔር ለሕዝቡ ተአምራትን የሚያደርግ ኃይል የተሞላ አምላክ መሆኑን 

ለ) እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ ተአምራት የሚያደርግበት ድግግሞሽ በየጊዜያቱ እኩል ያለመሆኑንና 

ሐ) ተአምራት በራሳቸው የእግዚአብሔርን ኃይል የሚገልጡ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ግን የእግዚአብሔርን ሕዝብ መንፈሳዊ ብስለት ሲጨምሩ አለመታየታቸው ናቸው። 

ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር ልዩ የሆነ ተአምር አድርጐልህ ለማየት ተመኝተህ ታውቃለህ? ምን ዓይነት ተአምራት እንዲያደርግልህ ነበር የፈለግኸው? ለ) እግዚአብሔር ይህን ተአምር እንዲያደርግልህ የፈለግኸው ለምን ነበር? ሐ) ይህ ነገር ስለ እምነት ምን ያሳያል? እምነትህ ደካማ ወይስ ብርቱ ነበር? መ) እግዚአብሔር ተአምራት እንዲያደርግ ሁልጊዜ የሚጠብቁ ሰዎች እምነት ምን ዓይነት ነው ብለህ ታምናለህ? ብርቱ ወይስ ደካማ? ይህን ለምን አልክ? 

ብሉይ ኪዳን ወደ መጠቃለል በቀረበበት ወቅት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ልዩ የሆነ ግንኙነት የሚያደርግበት አስደናቂ አዲስ ዘመን እንደሚመጣ በነቢያቱ በኩል መናገር ጀመረ። በአዲሱ ዘመን መሢሑና መንፈስ ቅዱስ ልዩ ስፍራ ይኖራቸዋል። ከዚህ ቀደም ትንቢትን የመናገር ስጦታ ለብዙዎች እንደሚሰጥ በኢዩኤል መጽሐፍ ተመልክተናል። ነገር ግን እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንደገና ተአምራትን የሚያደርግበትን ዘመን እንደሚያመጣና መሢሑን እንደሚያስነሣ የሚያመላክት ነገር አለ። መሢሑ ለታሠሩ መፈታትን፥ ለታወሩት ብርሃንን ያወጣል (ኢሳ.6፡1-2)። እንዲሁም ሕዝቡን ከበሽታቸው ይፈውሳቸዋል (ኢሳ. 3፡5)። 

ኢሳ 53፡5 በክርስቲያኖች መካከል ከፍተኛ ውዝግብን የፈጠረ ክፍል ነው። እግዚአብሔር፥ ኢየሱስ በሽታዎቻችንን «ሁሉ» እንደሚፈውስ ቃል መግባቱ ነበርን? እንደዚያ ከሆነ ብዙ ክርስቲያኖች ለምን ይታመማሉ? ኃጢአት በሕይወታቸው ስላለ ወይም በቂ እምነት ስለሌላቸው ነው? ብዙ ሰዎች ለክርስቲያኖች ሕመም የሚሰጡት ምክንያት ይህ ነው። ለነገሩ እግዚአብሔር ኃያል አምላክ ነውና ሁሉንም መፈወስ ይችላል። አፍቃሪ ስለሆነ ልጆቹ ሲሰቃዩ ማየት አይፈቅድም፤ እግዚአብሔር ከማንኛውም በሽታ እንደሚፈውሰን ቃል ገብቶልናል። ስለዚህ ካልተፈወስን በኃጢአት ወይም በቂ እምነት በማጣት ምክንያት ነው ይላሉ። 

ጥያቄ፡- በክርስቲያኖች መካከል እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ሲንጸባረቅ ሰምተህ ታውቃለህን? ከሰማህ ምን ምላሽ ትሰጣቸዋለህ? 

የሚያሳዝነው ነገር ይህ ዓይነት መረዳት ኢሳ. 53፡5 በተሳሳተ መንገድ በመተርጐሙ የመጣ መሆኑ ነው። ይህ ጥቅስ የሚናገረው በእርግጥ ስላ ሥጋዊ ፈውስ ነውን? በአይሁዳውያን አስተሳሰብ “ፈውስ” የሚለው ቃል ምሉዕነትን ያመለክታል። ብዙ ጊዜ የሥጋዊ አካል ምሉዕነትን ቢያመለክትም ቅሉ መንፈሳዊ ምሉዕነትንም ያመለክታል። አንድ ሰው ከኃጢአቱ በሚድንበት ጊዜ ይፈወሳል። ኢየሱስ የሚለውንና «እዳኝ» የሚል ትርጓሜ ያለውን ስም ያገኘነው ከዚህ ነው። ምሉዕ የሚያደርገን እርሱ ነው። ስለዚህ በኢሳ. 53፡5 የምናገኘው «ተፈወሳችሁ» የሚለው ቃል የግድ ሥጋዊ ሕመምን የሚያመለክት አይደለም። በዙሪያው ያሉትን አሳቦች ስንመላክት እግዚአብሔር በዚህ ቦታ የሚያመለክተው በተቀዳሚ ሥጋዊ ምሉዕነትን ሳይሆን መንፈሳዊ ምሉዕነትን ነው። ሌሎች ጥቅሶች የሚናገሩት ለለ መተላለፍ፥ ስለ በደልና፥ ስለ ሰላም ወዘተ… ነው። ስለዚህ በዚህ ጥቅስ አሳብ ላይ መሢሑ ፈውስን እንደሚያመጣ (በማቴ. 8፡16-17 የተተረጐመው በዚህ መንገድ ነው) የሚያመላክት አሳብ ሊገኝ ቢችልም ተቀዳሚ መረዳታችን ሊሆን የሚገባው ኢየሱስ ከኃጢአታችን እንደሚያድነን የሚናገር ስለመሆኑ ነው። የአዲስ ኪዳንን አጠቃላይ አሳብ በቅርብ በምንመረምርበት ወቅት እግዚአብሔር ለክርስቲያኖች ሁሉ ሙሉ የሆነ አካላዊ ፈውስን አልሰጠም። ጳውሎስ ይሰቃይ ነበር፥ ከእርሱ ጋር ይሠራ የነበረው አፍሮዲጡ አብሮት ሳለ እስከ ሞት ድረስ ታሞ ነበር (ገላ. 4፡13-14፤ ፊልጵ. 2፡27)። በሺህ የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ሌሎችን ለመፈወስ የሚጠቀምባቸው እንኳ ይታመማሉ። ስለዚህ እነዚህን ጥቅሶች ሰው ከሥጋዊ በሽታዎቹ ሁል ጊዜ ይፈወሳል ለማለት ልንጠቀምባቸው አንችልም።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.