የትንቢት ስጦታን ለመጠቀም መመሪያዎቹ ምን ምን ናቸው?

በ1ኛ ቆሮ. 12-14 ከተመለከትነው አንጻር የአዲስ ኪዳን አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት በአሁኑ ጊዜ ካሉን የቤተ ክርስቲያን ፕርግራሞቻችን በጣም የተለዩ ናቸው። በዚያ ዘመን በአምልኮ ፕሮግራሞች ሰዎች ሁሉ ይሳተፉ ነበር። የተለያዩ ጸሎቶችና መዝሙሮች፥ በድንገት እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚሰጣቸው መልእክቶችና የሚለውጠውን የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት የመስሚያ ጊዜያት ነበሩ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከነበሩ መንፈሳዊ ስጦታዎች አንዱ የትንቢት ስጦታ ነበር። ነገር ቀን እንደማንኛውም ስጦታ ይህ ስጦታም ያለ አግባብ በተግባር ላይ ሊውል ይችል ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ስልሳናት ለመናገር ስጦታ እንዳደረገው ትንቢት ስለመናገር ስጦታም መመሪያን ሰጠ። የሚከተሉትን በእዚህ ቁጥሮች ስለቀረበው ትንቢት ከተሰጡት እውነቶች ጥቂቶቹ ናቸው። 

1. ትንቢት የሚመጣው በመገለጥ ነው። መገለጡ እንደ ሕልምና ድምፅ ባሱ ልዩ ተአምራዊ መንገዶች ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ብዙ ጊዜ የሚገለጸው የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን ፍላጐቶች በሚያሟላ መልኩ ልዩ እውነተችን ከመጽሐፍ ቅዱስ በአዲስ መንገድ በመረዳት ነው። እነዚህ ትንቢቶች ሁልጊዜ የሚመጡት ትንቢት ተናጋሪው እራሱን በሚቆጣጠርበት ሁኔታ እንጂ ፈጽሞ እራሱን ስቶ በሰመመን ውስጥ ባለበት ሁኔታ አይደለም። ትንቢት ተናጋሪው እራሱን ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠርበት ሁኔታ ሳይሆን ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ የሚናገር ከሆነ የትንቢቱን እውነተኛነት በጥርጣሬ ልንመለከተው ይገባል። 

2. የቤተ ክርስቲያን ፕሮግራም በሚካሄድበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ ለብዙ ሰዎች መልእክት ከሰጠ ሁሉም በአንድ ጊዜ ለመናገር መሞከር የላባቸውም። ነገር ግን ተራ በተራ በሥርዓት ሊናገሩ ይገባል። 

3. የትንቢት መልእክት , በሚመጣበት በማንኛውም ጊዜ መልእክቱ መመዘን እላበት። ጳውሎስ እነዚህን መልእክቶች መመዘን ያለበት ጉባኤው ይሁን ወይም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለይቶ አይናገርም። ለማንኛውም የመጨረሻው ኃላፊነት የሚወድቀው በቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ላይ ነው። አንዳንዶቹ ትንቢቶች እውነት ሌሎች ደግሞ ሐሰት ሊሆኑ ይችላሉ። 

ወይም አንዳንዶቹ ዋጋ ያላቸው ሌሎቹ ደግሞ የሌላቸው ይሆናሉ። ክርስቲያኖችን ለማነጽ ምንም ዋጋ የሌላቸው ትንቢቶች ተቀባይነት ማግኘት የለባቸውም። ስለዚህ የትኛው የመልእክቱ ክፍል እግዚአብሔር ለእነርሱ የሰጠው እንደሆነና የትኛው ደሞ እንዳልሆነ ሕዝቡ እንዲያውቅ ማድረግና መልእክትን መመዘን የቤተ ክርስቲያን በተለይም ደግሞ የመሪዎች ኃላፊነት ነው። 

4. ትንቢቶች መመዘናቸውና እውነት የሆኑት ካልሆኑት የመለየታቸው እውነታ ትንቢቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል «ሥልጣን» እንደሌላቸው ያሳየናል። በእርግጥ በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን አማካኝነት ልዩ የሆኑ ነቢያትና ሐዋርያት የጻፉት መጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሚለይበት መመዘኛ መሆን ይገባዋል። 

5. በአንድ ስብሰባ ትንቢት እንዲናገሩ የተፈቀደላቸው ሰዎች ቁጥር የተወሰነ ነበር። ይህ የሚያመለክተው ነቢያት ስብሰባውን በሚያቀነባብሩና በሚመሩ ሰዎች ቁጥጥር ሥር መሆናቸውን ነው። ሥርዓት አልበኝነትና ግራ የሚያጋቡት ሁኔታዎች ከእግዚአብሔር ባሕርይ በተቃራኒ የሚሄዱ ስለሆኑ እርሱን ለማምለክ ትክክለኛና ተገቢም አዝማሚያ አይደለም። 

6. እማኞች ሁሉ ከእግዚአብሔር መገለጥን ሲያገኙ ትንቢት የመናገር መብት ቢኖራቸውም ይህ መንፈሳዊ ስጦታ ግን ሁሉም ሰው አይኖረውም። 

7. በመጽሐፍ ቅዱስና በዚህ ስፍራ በተገላጣው የትንቢት ስጦታ መካከል የብቃት ልዩነት መኖሩን ብንረዳም ቅሉ ይህ ስጦታ እዲስ ኪዳን ተጽፎ ካለቀበት ጊዜ ጀምሮ አይሠራም ለማለት ምንም አመልካች ማስረጃ አናገኝም። ይህ ስጦታ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላላመኖሩ ምንም አመልካች ማስረጃ የለም። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደዚህ ዓይነቱን ስጦታ እንዳያግዱ መጠንቀቅ አለባቸው። ሆኖም ግን የተነገረውን ትንቢት የመመዘንና ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር አብረው የማይሄዱ ስሕተቶች ያሉበትን አካባቢ ለሕዝቡ የማሳወቅ ኃላፊነት አለባቸው። 

8. ያልተፈተነ ትንቢት ለቤተ ክርስቲያን አደገኛ ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህ እንዲደረግ ከፈቀዱ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በቀጥታ ይቃረናሉ። ይህ የማይተረጐም ልሳን የመናገርን ያህል ለሕተት ነው። 

ጥያቄ፡- በዚህ ቀን ትምህርቶች መጀመሪያ ላይ የተመለከትናቸውን ሁኔታዎች ከልስ። ከላይ ከተጠቀሱት መመሪያዎች አንጻር በጸሎት ስብሰባ ላይ የምትገኝ የቤተ ክርስቲያን መሪ ብትሆን ኖሮ በዚያ ሁኔታ ውስጥ እግዚእብሔር ምን እንድታደርግ የሚፈልግ ይመስልሃል? 

ባደረግሁት ጥናት በትንቢት ስጦታ ከሚያምንና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይህን ስጦታ ከሚለማመድ አንድ ሰው የሚከተሉትን አሳቦች አግኝቻለሁ። 

1 እግዚአብሔር የትንቢት ቃል ስለሌላ ሰው ከሰጠህ፥ በተለይ ደግሞ ያን ሰው የመጉዳት ኃይል ካለው እግዚአብሔር መልእክቱን እንድትነግረው በግልጽ እስኪያሳውቅህና እስኪፈቅድልህ ድረስ ፈጽሞ አትንገረው። እግዚአብሔር ያንን መልእክት የሰጠህ ያንን ከርስቲያን እንድትጐጻው ሳይሆን እንድትጸልይለት ሊሆን ይችላል። አንዳንድ መገለጦች የሚሰጡህ ለሌሎች እንድታካፍል ሳይሆን በአንተና በእግዚአብሔር መካክል ብቻ እንዲቀሩ ነው (ለምሳሌ 2ኛ ቆሮ. 12፡4፤ መዝ. (25)፡1-4) 

2. እንድ መገለጥ በመቀበልና ያላ ስሕተት ተርጉሞ በሥራ ላይ በማዋል መካከል ልዩነት አለ። ትርጉምህና አጠቃቀምህ ያለ ስሕተት ለመሆኑ እርግጠኛ ሁን። የትንቢት ቃልህን ይህ እግዚአብሔር የሰጠኝ መልእክት እንደ ሆነ አምናለሁ በማለት በፍጹም ትሕትና ተናገር። «እግዚአብሔር እንደዚህ ይላል» በማለት ኃይለ ቃል ከመጠቀም ተጠንቀቅ። ይልቅ እግዚአብሔር እንደዚህ እንደሚል አስባለሁ… በሚል የአነጋገር ዘይቤ ተጠቀም። 

3. የትንቢትን ቃል አንድን ሰው በግልጽ ለመኮነን አትጠቀምበት። አንድን ሰው መገጽ እንዳለብህ እግዚአብሔር ካመለከተህ በማቴ. 18፡6 17 የተሰጠውን በመጠቀም በግሉ ቀርበህ ለመገሠጽ እርግጠኛ ሁን። 

4. የተቀበልከውን መልእክት ካካፈልህ በኋላ ስለ ውጤቱ ኃላፊነቱን በእግዚአብሔር ላይ ጣል። አንተ እግዚአብሔር ፈቃዱን ለመግለጥ የሚጠቀምብህ መሣሪያ ብቻ ነህ። ያቀረብከውን መልእክት መመዘንና እግዚአብሔር እንደተናገራቸው ያመኑበትን ክፍል መታዘዝ መልእክቱ የመጣለት ግለሰብ ወይም ቡድን ኃላፊነት ነው። አንተ እግዚአብሔር እንዳሳየህ የምታምነውን ነገር ሰዎች ባያምኑ ወይም ባይከተሉ አትመረር። በዚህ ምክንያት መራራ ከሆንክ፥ መጥፎ አመለካከት ካደረብህ ወይም እራስህን የመጥላት ስሜት የተሞላህ የትንቢቱን መልእክት ያመጣኽው ሰዎችን እንጂ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እይደለም ማለት ነው። በዚህ ፈንታ ትንቢቱን የተቀበሉት ሰዎች እነርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ጸልይላቸው። በመጨረሻ መንፈስ ቅዱስን በልባቸው አድምጠው ለመታዘዝ እግዚአብሔር ፊት ኃላፊነት አለባቸው። እግዚአብሔር በኃላፊነት የሚጠይቃቸው ለሚያደርጉአቸው ውሳኔዎች እንጂ አንተ ትክክል ነው ብለህ ላመንክበት ነገር አይደለም። 

5. በሰው ሕይወት ውስጥ ያለን ኃጢአት የመግለጥ ትንቢት እግዚአብሔር ቢያሳይህ ትንቢቱን እንዴት እንደምትጠቀምበት ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርግ። 

ሀ) ስለዚያ ትንቢት ከማንም ጋር አትነጋገር። ይህ የሐሜት ኃጢአት ነው። ከተሳሳትክ እንድ ሰው ስለ ኃጢአት በሐሰት ከሰለህ ማለት ነው። ይህ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን ማድረግ ነው። 

ለ) መልእክቱን ከመናገርህ በፊት እግዚአብሔር ፊት ለፊት ሄደህ በመናገር ትገሥጸው ዘንድ ይፈልግ እንደሆነ እርግጠኛ ሁን። እግዚአብሔር ስለዚያ ኃጢአት እንድታውቅ ያደረገህ እንድትጸልይ ብቻ ሊሆን እንደሚችልም አስታውስ። ሰውዩውን ከነኃጢእቱ በግልጽ የሚገናኝበት ሌላ ዕቅድ ሊኖረው ይችላልና። 

ሐ) ለሰውዬው ኃጢአቱን ፊት ለፊት ትነግረው ዘንድ እግዚአብሔር ካሳሰበህ ለባለጉዳዩ ብቻ በጥበብና በትሕትና ንገረው። 

መ) በተቀበልከው መገለጥ ላይ ብቻ ተመሥርተህ አንድን ሰው ስለ ኃጢአቱ በኃይል ልትገልጸው አትቅረብ። አስቀድመህ በእርግጠኛነት ማጣራት አለብህ። በተለይ ደግሞ መሪ የሆነን ሰው ስለ ኃጢአት ለመገሰጽ ልዩ ጥንቃቄ አድርጎ (1ኛ ጢሞ. 5፡19 ተመልከት)። 

6. ስለተጣላኽው ወይም ስለምትቀርበው ሰው የምታገኘውን መገለጥ አትመን። እነዚህ መገለጦች ብዙ ጊዜ የሰይጣን እንጂ የእግዚአብሔር አይደሉም። 

7. ታዋቂ «ነቢይ” የመሆን ፍላጐት እንዳይኖርህ እራስህን በመመርመር ጥንቃቄ አድርግ። መልእክት የምታመጣው ለግለሰቦች ወይም ጥቂት ሰዎች ላሉበት ቡድን፡ ወይም ለበርካታ ሰዎች መሆኑን የሚወስን እዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር እንድታደርገው ለነገረህ ነገር ብቻ ታማኝ ለመሆን ጥረት በማድረግ ውጤቱን ለእርሱ ተው። በተጨማሪ ስለ ችሎታህ፥ ስላየኸውና ስላደረግኸው ነገር በትምክህት አትናገር። 

8. ትንቢትን ለግል ጥቅምህ ፈጽሞ አታውል። እንደ ነቢይ በመታወቅ ምክንያት ደመወዝህ ክሌመረ ተጠንቀቅ። ይህ ወጥመድ ነው። ነቢዩ እግዚአብሔርን ለማገልገል ሳይሆን ለግል ጥቅሙና ለስግብግብ ዓላማዎቹ መኖር ይጀምራል። እንክብካቤ ለሚያደርጉላቸው መልካም መልእክትን፥ ለማያደርጉላቸው ደግሞ መጥፎ (ክፉ) መልእክትን የሚያመጡ ነቢያት ሰውን ደለ በማሰኘት ወጥመድ የተያዙ ስለሆነ እግዚአብሔርን አያከብሩም። 

9. የትንቢት ስጦታህን «እግዚአብሔር ይህን እንድነግርህ ነግሮኛል በሚል ሥልጣን በሞላበት መንገድ ፈጽሞ አትጠቀም። ይህ ዓይነቱ አጠቃቀም በሰውዬው ላይ ፈራጅና የበላይ ተቆጣጣሪ ወደ መሆን እንድታዘነብል ስለሚያደርግ በቀላሉ ከአግባብ ውጭ ወደ መጠቀም ያደርስሃል። እግዚአብሔር ትንቢትን የሚሰጣው ሰዎችን ለማነጽ+ ላመገሠጽ፥ ለማበረታታት፥ ለመምከርና ለማጠንከር እንጂ ሕይወታቸውን በበላይነት ለመቆጣጠር አይደለም። ነቢያት ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያረጋግጡ የሚያግዙ ቢሆንም እንድን ሰው ወይም ቡድን ለመቆጣጠር ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን ቃል ሊጠቀሙበት አይገባም። የአዲስ ኪዳን ነቢያት አንድ ሰው ማንን ማግባት እንዳለበት ለመናገር ወይም አንድን ነገር እንዲያደርግ የሥልጣን ትእዛዝ ሲያስተላልፉ ፈጽሞ እንመለከትም። 

10. ነቢያት ሁልጊዜ በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሥር ናቸው። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ሦስት ዓይነት መሪዎችን ሰጥቶ ነበር። እነዚህም ነገሥታት፥ ካህናትና ነቢያት ናቸው። እግዚአብሔር እያንዳንዱ መሪ ለተሰጠው ኃላፊነት በእርሱ ዘንድ ተጠያቂ እንደሆነ ግልጽ መመሪያ ሰጥቶ ነበር። ለመምራት የተሾሙት ነገሥታት እንጂ ነቢያት አልነበሩም ወዘተ…። በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት ኃላፊነት የተሰጣቸው የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንጂ ነቢያት አልነበሩም (1ኛ ጢሞ 5፡17)። ነቢያት ለሽማግሌዎች ሊዙ እንጂ ትንቢታቸውን የሽማግሌዎችን ሥልጣን ለማቃለል መጠቀም አልነበረባቸውም። ለሽማግሌዎች ሥልጣን የማይገዙ ለእግዚአብሔር የማይዙ ናቸውና በቤተ ክርስቲያን እንዲያገለግሉ ሊፈቀድላቸው አይገባም። 

11. እየተዘዋወሩ የሚያገለግሉ ነቢያት (ወይም አስተማሪዎች፥ ወንጌላውያን) በሽማግሌዎች አገልግሎታቸው እስኪመዘን ድረስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በግልጽ እንዲናገሩ ሊፈቀድላቸው አይገባም። በቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ ለሚተላለፈው መልእክት እግዚአብሔር ኃላፊነት የሰጠው ለሽማግሌዎች ነው። የስሕተት ትምህርት ቢያስተላልፉ የሽማግሌዎች ጥፋት ነው። እየተዘዋወሩ የሚያገለግሉ ነቢያት ብዙ ጊዜ በአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ቀጥተኛ ሥልጣን ሥር ስላልሆኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን የጥፋት ትምህርቶችን ለማምጣት ለሰይጣን አሠራር የተጋለጡ ናቸው (2ኛ ጢሞ. 3፡6)። ሁሉም ነቢያት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጉባኤው ፊት አገልግሎት እስክመስጣት የሚያበቃ ስጦታ ያላቸው አይደሉም። ትናንሽ ቡድኖች ውስጥ ወይም ግለስቦችን ብቻ ማገልገል ይገባቸዋል። 

12. አንድ የቤተ ክርስቲያን አባል የሆነ ሰው የትንቢት ቃል ለጉባኤው ለማካፈል ቢፈልግ ሊመዘን ይገባዋል። ከሁሉ የተሻለው መንገድ ግለሰቡ መገለጡን ለሽማግሌዎች ማካፈሉ ነው። ሽማግሌዎችም ሀ) የመጣው መልእክት በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ መሠረት እንደሆነ ለ) ቃሉን የቤተ ክርስቲያን ምእመናን በሙሉ መስማታቸው የሚጠቅም ወይም የሚረባ እንደሆነ ያረጋግጣሉ። ብዙ በማኅበር የሚነገሩ የትንቢት መልእክቶች የእግዚአብሔርን ቃል የማይጻረሩ ቢሆኑም እንኳ ለጉባኤው የሚሰጡት ጥቅም እጅግ አነስተኛ በመሆኑ በጉባኤ መነገራቸው አስፈላጊ አይደለም። እንዲህ ዓይነት መልእክት የሚያመጡ ሰዎች መልእክታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድናቸው ወይም ለአነስተኛ የጸሎት ስብሰባዎች እንዲያካፍሉ አበረታቷቸው። 

13. መንፈስ ቅዱስ፥ ኢየሱስን የሚገልጥበትና ለእኛም የሚናገርበት እጅግ የተላመደው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጋጥሙንን ተግባራትና ሁኔታዎች እንድንረዳ ይረዳናል። መንፈስ ቅዱስ የሚናገረን በመጽሐፍ ቅዱስ እርሱ ለገለጣቸው ነገሮች ስንታዘዝ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን የበለጠ ባወቅን ቁጥር ሕይወታችን የበለጠ የተረጋጋ ይሆንና የትንቢት አተረጓጐማችንም ትክክለኛነት እያደገ ይመጣል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተቀበልነው ኃላፊነት እየጨመረ በመጣ ቁጥር ሕይወታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መመሥረቱን የበለጠ እያረጋገጥን መምጣት አለብን። 

መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ ግን ምስጢሩን በመገላለጥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ እንችላለን በሚል አመለካከት በአእምሮ እውቀት እንዳንቀርብ መጠንቀቅ አለብን። እግዚአብሔር ለትዕቢተኞች፥ በእውቀታቸው ለሚመኩ አይናገርም። የእግዚአብሔርን ቃል እያጠኑ የእግዚአብሔርን ድምፅ አለመስማት የሚቻል ነገር ነው (ዮሐ 5፡37-40)። ይልቁኑ መንፈስ ቅዱስ ፈቃዱን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገልጥልን ዘንድ እንደ ሕፃናት በፍጹም ትሕትና ልንቀርብና እግዚአብሔር እንዲናገረን ልንጠይቅ ይገባል። መንፈስ ቅዱስ እራሱን ለእኛ ካልገለጠልን በቀር እኛ በራሳችን ልናደርገው አንችልም። 

14. በትንቢት ስጦታ ላይ ሳይሆን የእግዚአብሔር ጥብቅ ወዳጅ በመሆን ላይ አትኩሮትህን አድርግ። ይህን ካደረግህ ምን እንድታውቅ እንደሚፈልግና በእርሱ ስፍራ ሆነህ እንዴት ማገልገል እንዳለብህ ይገልጽልሃል። ይህ ነገር ሌሎችን ለማበረታታት የሚጠቅም ልዩ ተአምራዊ ቃሎችን የሚጨምር ከሆነም መልካም ነው። እግዚአብሔር አንተን በዚህ መንገድ ካልቀረበህ አትጨነቅ ወይም በሌሎችም አትቅና።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: