መጽሐፍ ቅዱስ በውትድርና ሙያ ስለሚያገለግል ክርስቲያን ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ በውትድርና ሙያ ስለማገልገል ብዙ መረጃዎች ቢይዝም አንድ ክርስቲያን በውትድርና ውስጥ ማገልገል እንዳለበት ወይም እንደሌለበት በቀጥታ አይገልጽም። ያም ሆኖ ግን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የተገለጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎችን ስንመረምር፣ የውትድርና ሙያ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በጣም የተከበረ ሙያ እንደሆነ እና እንዲህ ያለው አገልግሎት ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው የዓለም አተያይ (biblical worldview) ጋር የማይጣረስ መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የመጀመርያው የውትድርና አገልግሎት ተጠቅሶ የምናነበው በብሉይ ኪዳን (ዘፍጥረት 14) ሲሆን በዚህ ስፍራ የአብርሃም የወንድም ልጅ የሆነው ሎጥ በኤላም ንጉሥ በኮሎዶጎምር እና በተባባሪዎቹ በተያዘበት ጊዜ፣ አብርሃም 318 የሰለጠኑ የቤተሰቡን ሰዎች ሰብስቦ ኤላማውያንን በመውጋት ሎጥን ለመርዳት በዘመተበት ጊዜ ነው። በዚህ ጦርነት ውስጥ የታጠቁ ሃይሎች ንፁሀንን የማዳን እና የመጠበቅ ስራ ሲሰሩ እናያለን።

እስራኤላውያን መደበኛ የጦር ሰራዊት ማደራጀት የጀመሩት እጅግ ዘግይተው ነበር፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ “እግዚአብሔር ተዋጊያችን ነው፤ ያለ ጠንካራ ሰራዊታችን እርሱ ከጠላቶቻችን ይጠብቀናል” የሚል እምነታቸው ሊሆን እንደሚችል ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንን ያስማማል፡፡ በእስራኤል ውስጥ መደበኛ ሰራዊት መፈጠር የጀመረው፣ ጠንካራ የተማከለ የፖለቲካ ስርዓት ከዘረጋ በኋላ በሳኦል፣ በዳዊት እና በሰሎሞን  ዘመን ነው። የመጀመሪያውን መደበኛና ቋሚ ሰራዊት የመሰረተው ንጉሥ ሳኦል ነበር (1ሳሙ.13፡2፤ 24፡2፤ 26፡2)።

ሳኦል የጀመረውን ዳዊት ቀጠለ። ዳዊት ለእርሱ ብቻ ታማኝ የሆኑ ወታደሮችን በመቅጠር የሠራዊቱን ቁጥር ጨመረ (2ሳሙ 15፡19-22)፤ የሠራዊቱንም ቀጥተኛ አመራር ለዋና አዛዥ ለኢዮአብ ሰጠ። የሰሎሞን የንግስና ዘመን ምንም እንኳ ሰላማዊ የነበረ ቢሆንም፣ ሠራዊቱን ለማስፋትና ለማጠናከር ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ይጨመር እንደነበር በ1 ነገ 10፡26 ውስጥ ተጠቅሷል። ይህ መደበኛ ጦር የሰሎሞንን ሞት ተከትሎ እስራኤል ለሁለት ስትከፈል ቢከፈልም እስከ 586 ዓ.ዓ.ማለትም እስራኤል (ይሁዳ) እንደ ፖለቲካ አካል ሕልውናዋ እስካቆመበት ጊዜ ድረስ ቆይቶ ነበር።

ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ (በማቴዎስ 8፡5-13) ላይ በተጠቀሰው ታሪክ ውስጥ አንድ ሮማዊ የመቶ አለቃ ከኢየሱስ ጋር ባደረገው ንግግር፣ ወታደሩ ስለ ስልጣን ተዋረድ ያለውን ግልጽ ግንዛቤ እና በኢየሱስ ላይ የነበረውን እምነት እናነባለን። በዚህ ታሪክ ውስጥ ኢየሱስ የመቶ አለቃውን የውትድርና ሙያ ሲነቅፍም ሆነ ሲያወግዝ አንመለከትም። ከዚህ በተጨማሪ፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሱ ብዙ ክርስቲያን የመቶ አለቆች- ፈሪሃ አምላክ ያላቸው እና መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች በሚል ተወድሰው እናነባለን (ማቴዎስ 8:5፤ 27:54፤ ማር. 15:39-45፤ ሉቃስ 7:2፤ 23:47፤ የሐዋርያት ሥራ 10፡1፤ 21:32፤ 28:16)፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የውትድርና ሙያ ስነልቦና እና የጦር መሣሪያዎቹ ለመንፈሳዊ መርሆች ማብራሪያ በመሆን ሙያው ክቡር ስለመሆኑ እናነባለን  (ፊልጵስዩስ 2፡25፣ ኤፌሶን 6፡10-20)፡፡ 

እናም፣ አገራቸውን በመልካም ሥነ ምግባር፣ በቁርጠኝነት እና በክብር የሚያገለግሉ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች የሚያከናውኑት የዜግነት ግዴታ በሉዓላዊው አምላካችን የተከበረና የተወደሰ ስለ መሆኑን እርግጠኛ ሆነን መናገር እንችላለን። በመሆኑም፣ ውትድርናን ጨምሮ በሌሎች የጸጥታና ደህንነት መዋቅሮች ውስጥ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ዜጎችን ከስርኣተ-አልበኝነት (ሮሜ 13፡1-4፣ 1ኛ ጴጥሮስ 2፡13-15)፣ ከዝርፊያ፣ ከአስገድዶ መደፈር፣ ከስደት፣ ከወረራ ወዘተ ለሚጠብቁ ወታደሮች ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል።

አዳነው ዲሮ ዳባ

2 thoughts on “መጽሐፍ ቅዱስ በውትድርና ሙያ ስለሚያገለግል ክርስቲያን ምን ይላል?”

  1. በጣም ደስ የሚል አገላለጽ ነው።እግዚአብሔር ይባርካችሁ ። t.me/aleazermelese ይህ መንፈሳዊ የቴሌግራም ቻናሌ
    ነው።ትምህርቶቻችሁን ሼር አደርጋለሁ ።ተባረኩ።

  2. በጣም እናመሰግናለን፤ እግዚአብሔር ይባርካችሁ፡፡ ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ አንድ ሰዉ ራሱን ከወንበደዎች እየተከላከለ ድንገት ሰዉ ነፍስ ቢያጠፋ ስለዚህ ሰዉ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል; ሰዉን ሆን ብሎ አይደለም ለመግደል ያሰበዉ፣ግን እራሱን ስከላከል ነዉ የገደለዉ፡፡ ስለዚህ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ካላችሁ መልሱልኝ፡፡ በተረፈ ተባረኩ፡፡ መሰል የሆኑ ለሰዉ ልጅ ጥያቄ የሚፈጥሩ ሃሳቦች ላይ በትኩረት መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ ትምህርት አቅርቡልን፡፡ ተባረኩ፡፡ ግን የእግዚአብሔር ሰዉ ኖትና በስራ ቦታ ምቾት የሚነሳኝ ነገር አለና ጸልዩልኝ፤ እግዚአብሔር መልስ እንዳለዉ አምናለሁ፡፡

Leave a Reply to Abraham SamuelCancel reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading