ለሙስሊም ወዳጆቻችን ጥያቄዎች የተሰጠ ምላሽ፣ መግቢያ

ከክርስትና ውጪ፣ ሃይማኖቱን በሚሽን/በተልዕኮ በዓለም ላይ ለማስፋፋት ጥረት የሚያደርግ ብቸኛ ሃይማኖት እስልምና ነው፡፡ የእስልምና እምነት አስፋፊዎች የመጨረሻ ግብ ዓለምን በእስልምና መሸፈን መሆኑ ምስጢር አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሙስሊም፣ ሙስሊም ያልሆኑ ሌሎች ሰዎችን ወደ እምነቱ ከመጥራት ሃላፊነት በተጨማሪ የሙሐመድ አስተምህሮዎችንና የሃይማኖቱን መሠረታዊ መመሪያዎች የመፈፀም ግዳጅ አለበት፡፡ ይህ፣ ከሃይማኖቱ ውጪ ያሉ ሰዎችን ወደ እምነቱ የመጋበዝ ሥራ ዳዋ (dawah) በመባል ይታወቃል፡፡

ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ አንዳንድ ሙስሊሞች በዚህ የመነቃቃት ወኔ በመነዳት ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ የሃይማኖታቸውን ታላቅነት ለማሳየት በክርስትናና በአስተምህሮቱ ላይ በጭካኔ የተሞላ ጥቃት እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ ማንም ሊገነዘበው እንደሚችል እንደዚህ አይነቱ ከሃይማኖቱ ውጪ ያሉ ሰዎችን ወደ እምነቱ የመጥራት አካሄድ ሰውን በማክበርና በትህትና ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ በሌላው ሰው የተቀደሰ እምነት እና ልማዶች ላይ የሚካሄድ እንዲህ አይነቱ በጭካኔ የተሞላ አቀራረብ ጥላቻና አለመረጋጋትን ከመፍጠር የዘለለ ምንም ፋይዳ ሊኖረውም አይችልም፡፡ አንዳንድ ስሜታዊ ክርስቲያኖችም የዚህ ችግር አካሎች እንደነበሩ መደበቅ አስፈላጊ መስሎ አይታየንም፡፡ የክርስቶስን ትምህርት በአግባቡ ያልተገነዘቡ እንደ እነዚህ አይነቶቹ ሰዎች፣ የእስልምናን ነብይ ስም አንጓጠዋል፣ በእስልምና ባሕልና ልማዶች ላይም የስድብ ቃል ሰንዝረዋል፡፡ ይህ ተግባር በሙስሊሙ ማህበረሰብ ታሪክ ውስጥ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በሙሐመድ ዘመን እንኳን በእስልምና እምነት ላይ ያላግጡ የነበሩና ራሳቸውን ‘ክርስቲያን’ እያሉ የሚጠሩ ሰዎች እንደነበሩ ቁርአን ይናገራል፡፡ በእነዚህ ላይ ቁርአን እንዲህ ሲል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ያስተላልፋል፡-

  • እናንት ያመናችሁ ሆይ! [ሙስሊሞች ሆይ!] ይሁዶችና ክርስቲያኖችን ረዳቶች [ወዳጆች] አድርጋችሁ አትያዙ፣ ከፊላቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፣ ከእናንተም ውስጥ ረዳቶች የሚያደርጋቸው ሰው እርሱ በእነርሱ ነው፣ አላህ አመጸኞችን ሕዝቦች አያቀናም፡፡ … እናንት ያመናችሁ ሆይ! ከነዚያ ከበፊታችሁ መጽሐፍን ከተሰጡት [ይሁዶችና ክርስቲያኖችን] እነዚያን ኃይማኖታችሁን ማላገጫና መጫወቻ አድርገው የያዙትን ከሃዲዎችንም ረዳቶች አድርጋችሁ አትያዙ፣ ምእመናንም እንደሆናችሁ አላህን ፍሩ፡፡ 

ሱረቱ አል-ማኢዳህ (5)፡51፣57

O ye who believe! Take not the Jews and the Christians for your friends and protectors … take not for friends and protectors those who take your religion for a mockery or sport. 

በዚያ ዘመን የነበሩትንና እንዲህ አይነቶቹን አይሁድና ክርስቲያኖች ከሚያስጠነቅቀው ከፍ ብሎ ከተገለጸው ጥቅስ በተቃራኒው፣ ቁርአን ስለ ክርስቲያኖች የሚናገረው በርካታ አዎንታዊና ገንቢ ጥቅሶች አሉት፡፡ እነዚህ ጥቅሶች የስም ክርስቲያኖችን ሳይሆን እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮችን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ እስቲ ከዚህ በታች የተገለፁትን የቁርአን ጥቅሶች ለአብነት እንመልከት፡-

  • ይሁዶችንና እነዚያን ያጋሩትን ለነዚያ ለአመኑት [ሙስሊሞች] በጠላትነት ከሰዎች ሁሉ ይበልጥ የበረቱ ኾነው በእርግጥ ታገኛለህ፣ እነዚያንም እኛ ክርስቲያኖች ነን ያሉትን ለነዚያ ለአመኑት [ለሙስሊሞች] በወዳጅነት በእርግጥ ይበልጥ የቀረቧቸው ሆነው ታገኛለህ፤ ይህ ከነሱ ውስጥ ቀሳውስትና መነኮሳት በመኖራቸውና እነሱም የማይኮሩ በመሆናቸው ነው፡፡

 ሱረቱ አል-ማኢዳህ (5)፡82

nearest among them in love to the believers (Muslims) wilt thou find those who say, “We are Christians” because amongst these are men devoted to learning and men who have renounced the world, and they are not arrogant.

 ይህ ጥቅስ ስለ ኢትዮጵያ ነጋሢ ልኡካን የተነገረ ነው ይባላል (ከቅዱስ ቁርአን የግርጌ ማስታወሻ የተወሰደ)፡፡

  • ዒሳ [ኢየሱስ] ከእነርሱ ክህደት በተስማው ጊዜ፡- ወደ አላህ (ተጨምረው) ረዳቶቼ እነማን ናቸው አለ፣ ሐዋሪያት፡- እኛ የአላህ ረዳቶች ነን፣ በአላህ አምነናል፣ እኛም ትክክለኛ ታዛዦች መሆናችንን፣ መስክር አሉ፡፡ ጌታችን ሆይ! ባወረድኸው አመንን፣ መልዕክተኛውንም ተከተልን፣ ከመስካሪዎችም ጋር መዝግበን (አሉ)፡፡

 ሱረቱ አሊ-ዓምራን (3)፡52፣53 

When Jesus found unbelief on their part, he said, “Who will be my helpers to (the work of) God?” Said the disciples: “We are God’s helpers; we believe in God, and do thou bear witness that we are Muslims (those who bow to God’s will). Our Lord! We believe in what Thou hast revealed, and we follow the Apostle (Jesus): then write us down among those who bear witness.”

  • እናንተ ያመናችሁ ሆይ [ሙስሊሞች] የመርየም [የማርያም] ልጅ ዒሳ [ኢየሱስ] ለሐዋሪያቶቹ ወደ አላህ ረዳቴ ማነው እንዳለ ሐዋሪያቶቹም እኛ የአላህ ረዳቶች ነን እንዳሉት፣ የአላህ ረዳቶች ሁኑ፣ ከእሥራኤልም ልጆች አንደኛዋ ጭፍራ አመነች፣ ሌላይቱም ጭፍራ ካደች፣ እነዚያን ያመኑትንም በጠላታቸው ላይ አበረታናቸው፣ አሸናፊዎችም ሆኑ፡፡ 

 ሱረቱ ኣል-ሶፍ (61)፡14

Said the Disciples (of Jesus), “We are God’s helpers!” Then a portion of the Children of Israel believed (became followers of Jesus), and a portion disbelieved. But We gave power to those who believed against their enemies, and they became the ones that prevailed.

  • አላህም ባለ ጊዜ (አስታውስ)፤ ዒሳ [ኢየሱስ] ሆይ! እኔ ወሳጅህ ወደ እኔም አንሺህ ነኝ፤ ከነዚያም ከካዱት ሰዎች አጥሪህ ነኝ፣ አነዚያንም የተከተሉህን፣ እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ፣ ከነዚያ ከካዱት በላይ አድራጊ ነኝ፤ ከዚያም መመለሻችሁ ወደኔ ነው፤ በእርሱ ትለያዩበትም በነበራችሁት ነገር በመካከላችሁ እፈርዳለሁ፡፡

 ሱረቱ አሊ-ዒምራን (3)፡55

Behold! God said: “O Jesus! I will take thee and raise thee to Myself and clear thee (of the falsehoods) of those who blaspheme. I will make those who follow thee superior to those who reject faith to the Day of Resurrection”

  • ከዚያም በዱካዎቻቸው ላይ መልዕክተኞቻችንን አስከታተልን የመርየምን [የማርያምን] ልጅ ዒሳንም [ኢየሱስንም] አስከተልን፤ ኢንጂልንም [ወንጌልንም] ሰጠነው፤ በነዚያም በተከተሉት (ሰዎች) ልቦች ውስጥ መለዘብንና እዝነትን፣ አዲስ የፈጠሩዎትንም ምንኩስና አደረግን… 

 ሱረቱ አል-ሐዲድ (57)፡27

We sent after them (the prophets) Jesus the son of Mary, and bestowed on him the Gospel; and We ordained in the hearts of those who followed him Compassion and Mercy.

ከሙስሊሞች ጋር በሚኖርህ ግንኙነት ወቅት፣ ሆን ብለውም ሆነ ባለማወቅ ሃይማኖታቸውንና ነቢያቸውን ስለተሳደቡ ክርስቲያኖች ይቅርታ ለመጠየቅ ወደኋላ አትበል፡፡ የቁርአን አስተምህሮዎችን የማትቀበል ቢሆንም እንኳ፣ አንተ ሙስሞችን ከሚወዱና ቁርአን ከሚያወድሳቸው ከእውነተኞቹ የኢየሱስ ተከታዮች መካከል እንደሆንክ ራስህን ልታስመሰክር ይገባል፡፡ ቃልህና ተግባርህ በአንዱ – በአብርሃም፣ በይስሃቅና በያዕቆብ አምላክ የምታምንና ለእርሱም ፈቃድ የምትገዛ መሆንህን ለሙስሊም ወዳጅህ ሊመሰክሩለት ይገባል፡፡ ሁል ጊዜ ለመማር የተዘጋጀህ፣ ከዓለማዊ እሥራቶች የተፈታህ፣ ትሁት፣ እግዚአብሔርን የምታገለግል፣ በጠላት ላይ የእግዚአብሔርን ኃይል የምትለማመድ፣ እስከ መጨረሻው የምትፀናና የምትበረታ በተጨማሪም ለሰው ልጆች ሁሉ ርህራሄና ምህረት ያለህ መሆንህን በፍቅር የምትገልጥለት ሁን፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ራስህን የምትገልጥ ከሆንህ የእስልምና እምነት ተከታዮችን የልብ በር ለማግኘትና ለማገልገል ያለጥርጥር ተሳካልህ ማለት ነው፡፡

ከዚህ ጋር አያይዘን፣ ይህ መጽሐፍ የሙስሊሞችን አስተምህሮ በማጥቃት ወይም የጥቃት ምላሽ በመስጠት መንፈስ አለመቅረቡን በአፅንኦት ልንገልጽ እንወዳለን፡፡ ይህ መጽሐፍ እንደ ክርክር ማጣቀሻ ጽሑፍ ተደርጎ በሚነበብበት አቅጣጫም አልተጻፈም፡፡ አስተውል፣ እንደ እውነተኛ የጌታ ኢየሱስ ተከታይ ለሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ማሳሰቢያ ልብህን ልትሰጥ ይገባል፡-

  • ነገር ግን ጠብን እንዲያመጣ አውቀህ ከሰነፎችና ካልተማሩ ምርመራ ራቅ፤ የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም። ደግሞም ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሐን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው፣ ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ።

 2ጢሞቴዎስ 2፡23-26 

  • ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ፣ ማንንም የማይሰድቡ፣ የማይከራከሩ፣ ገሮች፣ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ አሳስባቸው።

ቲቶ 3፡1-2 

ይህ መጽሐፍ፣ በተለያየ መንገድ የቀረቡ የተለያዩ ጸሐፊዎች ጭምቅ አሳብና ከ 15 ዓመታት በላይ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ በመኖር ያካበትኩት የግል ልምዴ ውሁድ ውጤት ነው፡፡ በቀጣዮቹ ገጾች ውስጥ ያሉ ፍሬ አሳቦች በክርስቲያኑ ማህበረሰብ መካከል ጥርጥርና ግራ መጋባት ለመፍጠር፣ በክርክር አዋቂ ሙስሊም ሊቃናት ያለማቋረጥ በሚደረገው ዘመቻ ለሚደናገሩ አማኞች መረጃ በማቅረብ ረገድ የራሱ የሆነ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው እምነታችን ነው፡፡ 

ክርስቲያኖች፣ ጥብቅና የሚቆሙለትን እውነት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለሌሎች ለመመስከር የሚያስችላቸው ብቸኛው መንገድ፣ የሚናገሩትን እውነት በሕይወት ኖሮ በማሳየት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል! በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ መከባበርን ማስፈንና ወዳጅ መሆን ከማንኛውም እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ የሚጠበቅ ሥነ-ምግባር ነው፡፡ የቃላት ጥቃትና መልሶ ማጥቃት መጨረሻው፣ ሽንፈት ብቻ ነው፡፡ የዚህም ነገር የሩቅ ጊዜ ውጤት፣ ቅሬታና ብስጭት ከመፍጠር የዘለለ አይሆንም፡፡ በትህትና እየኖሩ በየዕለቱ የሰውን ጠንካራ ልብ ሊያሸንፍ የሚችለውን የክርስቶስን ፍቅር በተግባር እየገለጡ ከመኖር በቀር፣ ሙስሊም ወዳጆችን ለማፍራት ምን የተሻለ መንገድ ሊኖረን ይችል ብለው ያስባሉ? 

በዚህ መጽሐፍ ስር የቀረቡ መረጃዎች፣ በወዳጅነት እና በጋር መከባበር ላይ በተመሠረተ አቀራረብ ጥቅም ላይ እስከዋሉ ድረስ፣ በቅንነት እውነትን ለማወቅ ለሚሹ ሙስሊም ጠያቂዎች መልስ ለመስጠት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ እምነታችን ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ በግልፅ፣ እምነትን የመነጋገር ልምድ ሙስሊም ወዳጅዎ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥልቅ እውነቶች ለመመርመር እንዲነሳሳ ያግዘዋል፡፡ የዚህ ፍጻሜው ደግሞ በመሲሁ ኢየሱስ የሚገኘውን ድነት/መዳን የማወቅ እድል መፍጠር ይሆናል፡፡
እውነተኛዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች በታሪክ በመሳሪያም ሆነ በቃል ጦርነት ውስጥ አልተባበሩም፡፡ በእዚህ ፈንታ ዓለማዊ ግቦቻቸውን ወደጎን በማድረግ ወንጌልን ለሰው ልጆች ሁሉ ለማድረስ ራሳቸውን ሰጡ እንጂ፡፡ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ታማኝ በመሆን የክርስቶስን ፍቅር መግለጥ፣ በስሙም የሚገኘውን ድነት/መዳን እና የኃጢአት ስርየት መስበክ ዋነኛ ተልዕኮአቸው ነበር፡፡ ማንንም አልኮነኑም፣ አይኮንኑምም፡፡ ከእዚህ ይልቅ እንደ ክርስቶስ አምባሳደሮች፣ ሰዎች እርስ በእርሳቸው እና ከእግዚአብሔር ጋር እንዲተራረቁ የማስታረቅን አገልግሎትን ሊያውጁ ተገባቸው! ይህንን ክቡር ተጋድሎ እግዚአብሔር ይባርክ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: