“ክርስቲያኖች ሦስት አማልክትን ያመልካሉ፡፡”

ሙስሊሞች በክርስትና ላይ ከሚያነሱት መከራከሪያዎች መካከል የተለመደውና ጠንካራው፣ ክርስቲያኖች ሦስት አማልክት ያመልካሉ የሚለው ነው፡፡ ‹‹ስላሴ›› ስለሚለው ቃል ሙስሊሞች የተሳሳተ ግንዛቤ አላቸው፡፡ ሙስሊሞች ይህ ቃል ጥቅም ላይ ውሎ ሲመለከቱ፣ ክርስቲያኖች አንድ አምላክን ሳይሆን ሦስት አማልክትን እንደሚያምኑ እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ እግዚአብሔር አንድ እንደሆነ ከእርሱም በቀር ሌላ አማልክት እንደሌሉ ለተማረ አንድ ሙስሊም ይህ ጉዳይ ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው ነው! ከዚህ ከአንዱ አምላክ በቀር ሌላ ማምለክ የከፋውን ኃጢአት መፈፀም ነውና፡፡

በሚያሳዝን ሁኔታ፣ በሙሐመድ ዘመን፣ በአረቢያ ምድር ይገኝ የነበረ ራሱን እንደ አንድ ‹‹የክርስቲያን ሃይማኖት›› ክፍል (denomination) ይቆጥር የነበረና የኑፋቄ ትምህርትን ያስተምር የነበረ ሃይማኖት፣ ከኢየሱስ በተጨማሪ፣ ማርያምም መለኮታዊት እንደሆነች ያስተምር ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች በስላሴ አምሳል እግዚአብሔር አብን፣ ኢየሱስ ወልድን እና ማሪያም እናቱን ያመልኩ ነበር፡፡ ይህ አይነቱ የስላሴ አሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አንጻር፣ በእርግጥም ያፈነገጠ ነው፡፡ ልብ ልንለው የሚገባን ነገር ቢኖር ቁርአኑ የሚቃወመው ይህንን የተሳሳተ የስላሴ አሳብ መሆኑን ነው፡-

 • አላህም፡- የመርየም ልጅ ዒሳ [ኢየሱስ] ሆይ አንተ ለሰዎቹ፡- እኔንና [ኢየሱስ ራሱንና] እናቴን [ማሪያምን] ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለሃልን በሚለዉ ጊዜ (አስታዉስ)፤ ጥራት ይገባህ፤ ለኔ ተገቢዬ ያልኾነን ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም፤ ብዬዉ እንደ ኾነም በእርግጥ ዐዉቀኸዋል፤ በነፍሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ታውቃለህ፤ ግን አንተ ዘንድ ያለውን አላውቅም፤ አንተ ሩቆችን ሁሉ በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህና ይላል፡፡

ሱረቱ አል-ማኢዳህ (5)፡116

And behold! God will say: “O Jesus the son of Mary, didst thou say unto men, ‘worship me and my mother as gods in derogation of God?”’

 • እነዚያ አላህ የሦስት ሦስተኛ ነዉ ያሉ በእርግጥ ካዱ፣ ከአምላክም አንድ አምላክ እንጅ ሌላ የለም፣ ከሚሉትም ነገር ባይከለከሉ፣ ከነሱ እነዚያን የካዱትን አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ ይነካቸዋል፡፡

ሱረቱ አል-ማኢዳህ (5)፡73

They do blasphem who say God is one of three in a trinity; for there is no god except on God.

ሙስሊሞች እውነተኛ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የስላሴ አሳብ በተሳሳተ መንገድ በመረዳታቸውና ከአንድ በላይ አምላክ ስለማምለክ ጉዳይ በሚያሳዩት ስሜታዊነት ምክንያት፣ ‹‹ስላሴ›› የሚለውን ቃል አለመጠቀም የተሻለ ነው፡፡ ሙስሊም ወዳጅህ፣ እንደ ክርስቲያን አንተም የምታመልከው አንድ አምላክ እንጂ ሦስት የተነጣጠሉ አማልክት አለመሆናቸውን ስትነግረው በግልፅ እንደተረዳህ እርግጠኛ ልትሆን ይገባል፡፡ በዘዳግም 4፡35፣ 6፡4 እና ማርቆስ 12፡29 ላይ የተገለፀውን የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ በመግለጽ እግዚአብሔር አንድ መሆኑን አካፍለው፡፡ 

 • እግዚአብሔርም አምላክ እንደ ሆነ ታውቅ ዘንድ ይህ ለአንተ ተገለጠ፤ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም።

ዘዳግም 4፡35

 • እሥራኤል ሆይ፣ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤

ዘዳግም 6፡4

 • ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ። እሥራኤል ሆይ፣ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፣

ማርቆስ 12፡29

ነገር ግን ይህ አንዱ አምላክ ፈቃድ እንዳለው፣ ይህም ፈቃድ በመንፈሱ ኃይል አማካኝነት በቃሉ እንደሚገለጥ፣ ይህም ማለት እግዚአብሔር ባለበት ቦታ ሁሉ ቃሉና ምንፈሱ እንዳሉ እንዲያውቅ እርዳው፡፡ ይህ እውነታ በዘፍጥረት ታሪክ እግዚአብሔር፣ ቃል ሲናገርና በመንፈሱም ኃይል፣ ፍጥረትን ካለመኖር ወደ መኖር ሲያመጣ በግልጥ ታይቷል! 

 • በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። ምድርም ባዶ ነበረች፣ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር። እግዚአብሔርም። ብርሃን ይሁን አለ፤ ብርሃንም ሆነ። 

ዘፍጥረት 1፡1-3

 • በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፣ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፤

መዝሙር 33፡6

 • አቤቱ፣ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፣ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች። … መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም፣ የምድርንም ፊት ታድሳለህ።

መዝሙር 104፡24፣30

የእግዚአብሔር ቃልና መንፈሱ ከእግዚአብሔር የማይነጠሉ መሆናቸውን እንደምታምን ለሙስሊም ወዳጅህ አብራራለት፡፡ እግዚአብሔር በኖረበት ዘመን ሁሉ ቃሉና መንፈሱም ነበሩ፤ አልተፈጠሩም፤ አይሞቱምም፡፡ ይህም እውነታ የሚያስገነዝበን ነገር ቢኖር መለኮታዊ መሆናቸውን ነው!

በሚያስገርም ሁኔታ፣ በብዙ ሙስሊሞች ዘንድ የታወቀ ባይሆንም፣ ቁርአኑም ቢሆን መለኮታዊ ስለሆኑት ስለእነዚህ ሦስት ነገሮች ያወራል፡፡ እርግጥ ነው የመጀመሪያው ያው እግዚአብሔር ነው፡፡ ነገር ግን ቁርአን ከዚህ በተጨማሪ ስለ እግዚአብሔር ቃል ያወራል፡፡ ይህም፣ ቃል ወይም ትእዛዝ ይሰኛል፡፡

 • ለማንኛዉም ነገር (መኾኑን) በሻነዉ ጊዜ ቃላችን ለርሱ ኹን ማለት ብቻ ነው፤ ወዲያውም ይኾናል፡፡

ሱረቱ አል-ነሕል (16)፡40

For to anything which We have willed, We but say the Word, “Be,” and it is.

 • ነገሩም አንዳችን በሻ ጊዜ ኹን ማለት ነው፣ ወዲያዉ ይኾናልም፡፡ 

ሱረቱ ያሲን (36)፡82

Verily when He (God) intends a thing, His Command is “Be,” and is!

ከላይ በ 36፡82 የሰፈረውን ጥቅስ በተመለከተ ቅዱስ ቁርአን፡- ትርጉምና ማብራሪያ፣ (በ ኤ. ዩሱፍ አሊ)፣ የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 4028 ስለ እግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፡- ‹‹እርሱ (እግዚአብሔር) አንድን ነገር በሻ (በፈለገ) በዚያች ሰአት፣ ያ ፈቃድ የእርሱ ቃልና ትዕዛዝ ይሆናል፣ ያም ነገር ወዲያውኑ ወደ መኖር ይመጣል፡፡›› መጽሐፍ ቅዱሳዊውም እውነታ የሚያስረዳን ነገር ቢኖር ነገሮች ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠሩ ነው፡፡ እንግዳውስ ፍጥረት በእግዚአብሔር ቃል ከፀና፣ ቃሉ ራሱ ሊፈጠር እንደማይቻል በግልፅ መረዳት ይቻላል፤ እርሱ ራሱ የፍጥረት መገኛ ምክንያት ነውና፡፡ በዚህ ምክንያት በርካቶቹ የሙስሊም ምሁራን ‹የእግዚአብሔር ቃል የተፈጠረ አይደለም› በሚለው አሳብ ይስማማሉ፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሕር ቃል ያልተፈጠረና ዘላለማዊ ከሆነ እንግዳውስ መለኮታዊ ማንነት (ባሕሪ) አለው ማለት ነዋ፡፡ ከዚህ ምክንያታዊነት በመነሳት መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ቁርአን ኢየሱስን የእግዚአብሔር ቃል ብለው ስለሚጠሩት፣ ኢየሱስ የሰው ማንነት የያዘ ብቻ ሳይሆን፣ መለኮታዊ ማንነትም እንዳለው ለሙስሊም ወዳጆቻችን ልናብራራላቸው ይገባል፡፡ 

ቁርአን የሚያወራለት ሦስተኛው ጉዳይ ደግሞ ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ወይም ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ መንፈስ ነው፡፡

 • አላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑትን ሕዝቦች አላህንና መልክተኛውን የሚከራከሩትን ሰዎች፣ አባቶቻቸው ወይም ልጆቻቸው፣ ወይም ወንድሞቻቸው ወይም ዘመዶቻቸው ቢኾኑም እንኳ የሚወዳጁ ኾነው አታገኛቸውም፤ እነዚያም በልቦቻቸው ውስጥ እምነትን ጽፏል፤ ከርሱም በኾነ መንፈስ ደግፏቸዋል፤ ከሥሮቻቸውም ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ ያገባቸዋል፤ አላህ ከነርሱ ወዷል፡፡ ከርሱም ወደዋል፤ እነዚያ የአላህ ሕዘቦች ናቸዉ፤ ንቁ የአላህ ሕዝቦች እነሱ ምኞታቸውን የሚያገኙ ናቸው፡፡ 

ሱረቱ አል-ሙጃደላህ (58)፡22

For such He (God) has written Faith in their hearts and strengthened them with a spirit from Himself.

በቅዱስ ቁርአን፡- ትርጉምና ማብራሪያ (በ ኤ. ዩሱፍ አሊ)፣ የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 5365 ‹‹ከእርሱ በሆነ መንፈስ›› የሚለውን ሲያብራራ፣ ‹‹በሰው ቋንቋ የአላህን ማንነትና ባሕርይ በበቂ ሁኔታ ለመበየን እንደማንችለው አይነት መለኮታዊ መንፈስ›› ማለት ነው ይለዋል፡፡ 

እንግዳው፣ በቁርአኑ ውስጥም እያንዳንዳቸው ለየቅል የሆኑ፣ ነገር ግን የማይነጣጠሉ – እግዚአብሔር፣ የእግዚአብሔር ቃል፣ እና የእግዚአብሔር መንፈስ የተሰኙ፣ አንድ አይነት መለኮታዊ ባህሪ ያላቸው መንፈሳዊ አካላት የመኖራቸውን ማስረጃ እናገኛለን፡፡

በመጨረሻም፣ ሙስሊም ወዳጅህ እንተ ሦስት አማልክት እንደምታመልክ እንዲመስለው ሊያደርጉት የሚችሉትን እንደ ‹‹ስላሴ›› ወይም ሌሎች ተመሳሳይ ስያሜዎችን አትጠቀም፡፡ አስተውል፣ ሙስሊም ወዳጅህ ሊረዳ የሚችለው ስለ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ስለ አንድ አምላክ ብቻ! በቃሉና (ኢየሱስ) በመንፈሱ አማካኝነት ስለ አንዱ አምላክ ለመግለጥ/ለማስረዳት ሞክር፡፡ የአብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስን ታላቅ ምስጢር ለመፍታት ፈፅሞ አትሞክር፡፡ እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር ብቻ ይሁን! ፈቃዱን በመለኮታዊ ቃሉና በመለኮታዊ መንፈሱ የሚገልጠውን አንድ አምላክ እንደምታምን ግለጥለት፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: