“የአሳማ ሥጋ መብላት ተገቢ አይደለም፡፡”

ክርስቲያኖች የአሳማ ሥጋ በነፃነት ሲበሉ ሲመለከቱ፣ ሙስሊሞች ይደነግጣሉ፡፡ አይሁድ በሙሴ ሕግ ሥር በነበሩበት ወቅት ይከተሉት የነበሩት አሳማን ያለመብላት ሥርአት አሁን ድረስ በተለወጡ በርካታ አይሁዳዊያን ክርስቲያኖች ሕይወት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ ነው፡፡ ሙስሊሞችም አሳማን ሲመለከቱ ተመሳሳይ ጥላቻቸውን በግልጽ ያሳያሉ፡፡ እርግጥ ነው በብሉይ ኪዳን የአሳማ ሥጋ እንዳይበላ ተከልክሏል፡-

  • እርያም ሰኮናው ተሰንጥቋል፣ ነገር ግን ስለማያመሰኳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። የእነዚህን ሥጋ አትበሉም፣ በድናቸውንም አትነኩም፤ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው። 

ዘሌዋዊያን 11፡7፣8

ተመሳሳይ ክልከላ በቁርአኑ ውስጥም አለ፡-

  • በናንተ ላይ እርም ያደረገው በክትንና ደምን የእሪያ ሥጋንም በርሱም (ማረድ) ከአላህ ስም ሌላ የተነሳበትን ነገር ብቻ ነው፤ ሺፍታና ወሰን አላፊ ሳይኾን (ለመብላት) የተገደደ ሰውም በርሱ ላይ ኃጢአት የለበትም አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡

ሱረቱ አል-በቀራህ (2)፡173

He hath only forbidden you dead meat, and blood, and the flesh of swine, and that on which any other name hath been invoked besides that of God.

የአሳማ ሥጋ መብላት በእስልምና በጥብቅ የተከለከለ በመሆኑ፣ ሥጋውን መብላት በሙስሊሞች ዘንድ የእርኩስነት ምልክት ነው፤ በፈጣሪም ዘንድ እንዲህ ያለው ተግባር አፀያፊ እንደሆነ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ቅዱስ የሆነውን ነቢይ ኢየሱስን፣ እንከተላለን የሚሉት ክርስቲያኖች የአሳማ ሥጋ መብላታቸውን ሙስሊሞች ሲመለከቱ ትልቅ ጥያቄ ይነሳባቸዋል፡፡

እዚህ ላይ የሙሴን ሕግ ባሕሪ እና ለእስራኤላውያን ያለውን የተለየ ፋይዳ ለሙስሊሙ ማብራራት ጠቃሚ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ሕግ የሥነ-ምግባር ሕግንና ማህበራዊ ሕግን ያካተተ ሕግ ነው፡፡ የሥነ-ምግባር ሕጉ ከሕይወት ስርዐት ጋር በብርቱ የተዛመደ ሲሆን አላማውም በውስጣዊ ቅድስና መመዘኛ፣ የእሥራኤልን ሕዝብ ከቀሪው ሕዝብ መለየት ነበር፡፡ ይህ ታላቅ የሥነ-ምግባር ሕግ የእሥራኤልን ሕዝብ ወደላቀ የቅድስና መለኪያ ከፍታ ማምጣትና ለተቀረው የምድራችን ሕዝቦች ሁሉ ምሳሌ የማድረግ አላማን ያነገበ ነበር፡፡ ለአብነት፣ አስርቱ ትዕዛዛት ሰዎች በእግዚአብሐርና በሰው ፊት ስላላቸው ሃላፊነትና ተጠያቂነት የሚያስገነዝቡ የሥነ-ምግባር ሕጎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሕጎች በአካባቢያዊ ሁኔታ ለውጥ ተፅእኖ ውስጥ አይገቡም፡፡ ምንም ነገር ቢለወጥ እነርሱ እንዳሉ ይቆያሉ፡፡

ማኀበራዊ ሕጉ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ለዕለት ተዕለት ኑሮ የሚበጁ ሥርዐቶችንና ደንቦችን ያካተተ ነው፡፡ እነዚህ ሥርዐቶች በአካባቢያዊ ሁኔታዎችም ሆነ እግዚአብሔርን በማያመልኩ አጎራባች ኗሪዎች ልማድና ባህል ተፅእኖ ውስጥ ሊወድቁ ይችሉ ነበር፡፡ እነዚህ ደንቦች መንጻትን፣ አመጋገብን፣ ጤንነትን አለባበስን፣ እና የበአል ስርአቶችን ይመለከታሉ፡፡ የእነዚህ አላማ ደግሞ በውጫዊ የቅድስና ስርአት መመዘኛ የእሥራኤልን ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ መለየት ነበር፡፡ እስራኤላውያን በዙርያቸው የሚመለኩትን የጣኦት አምልኮ ስርአቶች የሚቃወሙና አንዱን አምላክ ብቻ የሚያመልኩ ሕዝቦች በመሆናቸው በሌሎች የዓለም ሕዝቦች አይን ልዩ መሆናቸው መታየት ነበረበት፡፡

ከእነዚህ ማኅበራዊ ሕጎች መካከል የአሳማ ሥጋን መብላት የሚከለክለው ሕግ አንዱ ነበር፡፡ የአሳማን ሥጋ ለጣኦቶቻቸው በመሥዋዕትነት ማቅረብ በወቅቱ በዙሪያቸው የነበሩ የኢ-አማኒያን ሕዝቦች ልማድ ነበር፡፡ በተጨማሪም፣ በወቅቱ በዚያ ስፍራ፣ አሳማ ውዳቂና የሞተ አካል ሥጋን የሚመገብ አጻያፊ እንስሳ ስለነበር የአሳማ ሥጋ መብላት ሕብረተሰቡን የሚጎዳና የአስከፊ በሽታ መስፋፊያ ምክንያትም ነበር፡፡ እስራኤላውያን ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ ከዚህ አይነቱ የኢ-አማኒያን ተፅእኖና አፀያፊ ተግባር መለየት ነበረባቸው፡፡

የእሥራኤል ሕዝብ፣ ለአብርሃም፣ ይስሃቅና ያዕቆብ አንዱና እዉነተኛ አምላክ እንዲገዛ የተመረጠ ቅዱስ ሕዝብ መሆኑን ሙስሊሙ ሊረዳ ይገባል፡፡ ይህ ሕዝብ ለተለየ አላማ፣ ከሌሎች ሕዝቦች መካከል፣ ለተቀረው የዓለም ህዝብ የማይጠፋ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ በእግዚአብሔር የተመረጠ ነው፡፡ ይህንን ሃቅ ቁርአኑም ቢሆን ይመሰክረዋል፡-

  • ባሮቻችንንም ኢብራሂምን [አብርሃምን]፣ ኢስሐቅንና [ይስሃቅንና] ያዕቆብንም [ያዕቆብንም] የኀይልና የማስተዋል ባለ ቤቶች የኾኑትን አውሳላቸዉ፡፡ እኛ ጥሩ በኾነች ጠባ መረጥናቸዉ [እኛ ለተለየ አላማ መረጥናቸው]፤ (እርሷም) የመጨረሻይቱን አገር ማስታወስ ናት፡፡

 ሱረቱ ሷድ (38)፡45-46

And commemorate our servants Abraham, Isaac, and Jacob, possessors of power and vision. Verily We did choose them for a special (purpose)-proclaiming the message of the hereafter.

  • የእሥራኤል ልጆች ሆይ! ያችን በናንተ ላይ የለገስኳትን ጸጋየንና እኔም በዓለማት ላይ ያበለጥኳችሁ መኾኔን አስታውሱ፡፡

ሱረቱ አል-በቀራህ (2)፡47

O Children of Israel, call to mind the (special) favor which I bestowed upon you, and that I preferred you to all others (for My Message).

ለሙስሊም ወዳጅህ የእሥራኤል ልጆች ለምን የተለየ ሕዝብ እደሆኑና ለምን አላማ እግዚአብሔር እንደ መረጣቸው አብራራለት፡፡ የአለሙ ሁሉ አዳኝ የሆነው፣ መሲሁ ኢየሱስ፣ የሰው ልጆች ቤዛ ይሆን ዘንድ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከው ቅዱሱ፣ ከዚህ የተመረጠ ሕዝብ መካከል እንዲመጣ እግዚአብሔር ወዷል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሆነው ኢየሱስ የሰውን ሥጋ ለብሶ ከድንግል ማሪያም ተወለደ፡፡ ይህ ቅዱስ ከአብርሃም፣ ይስሃቅና ያዕቆብ ዘር ሊወለድ ተገባው፡፡ በዚህ ምክንያት ከሌላው ሕዝብ ተለይተው ቅዱስና የተለዩ ሕዝቦች መባላቸው የሚያስገርም አይሆንም፡፡

በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረው የአገልግሎት ዘመን፣ ከእሥራኤል ሕዝቦች መካከል በርካታዎቹ የዚህን ማኅበራዊ ሕግ አላማ ዘንግተውት ነበር፡፡ የልብን መንጻት በእጅ መንጻት ቀይረው የዕለት ተዕለት ስርአትና ደንብ ለሆነው ማኅበራዊ ሕግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተውት ነበር፡፡ እንደውም የሃይማኖት መሪዎች የነበሩት የልብ ንፅህናን ወደጎን በመተው የራሳቸው የሆነ ተጨማሪ ስርአትና ደንብ በመጨመር ደንቦቻቸውን የቅድስና ትክክለኛ መመዘኛዎች ናቸው ለማለትም ደፍረው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት በበርካታዎቹ ህዝቦች ሕይወት ውስጥ፣ እውነተኛው የእምነት አስተሳሰብ እየላሸቀ ሕይወት በሌላቸው ሌሎች ሃይማኖታዊ ስርአቶችና ግብዝነት ተተካ፡፡ የሃይማኖት መሪዎች ከላይ ሲታዩ ፀሎታቸውን ይደግማሉ፣ እጆቻቸውን ያነፃሉ፣ ያልተፈቀዱ ምግቦችንም ከመመገብ ይቆጠቡ ነበር፡፡ በውስጣቸው ግን፣ ልባቸው በጥላቻ፣ በስስት፣ በምኞት እና በቅንአት ተመርዞ ነበር፡፡ የራሳቸውን ጽድቅ ሊያቆሙ የእግዚአብሔርን ሕግ አለአግባብ ተጠቀሙ!

ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር በሰጠው ስልጣን በመጠቀም፣ ሰው አለአግባብ ለራሱ ጥቅም በቀየጠው በዚህ ማኀበራዊ ሕግ ላይ እርምጃ ወሰደ፡፡ ይህንን ግብዝነት ለማጥፋትና እውነተኛ ቅድስና የልብ ጉዳይ መሆኑን አፅንኦት ለመስጠት ሁሉም ምግቦች ንፁህ ናቸው ሲል አወጀ፡፡ በውጤቱም፣ ለኢየሱስ ተከታዮች ሁሉ ማንኛውንም ምግብ መመገብ ሕጋዊ ሆነ፡-

  • ከተዉራትም ከኔ በፊት ያልለውን ያረጋገጥሁ ስኾን የዚያንም በናንተ ላይ እርም የተደረገውን ከፊል ለናንተ እፈቅድ ዘንድ (መጣኋችሁ) ከጌታችሁም በኾነ ታምር መጣሁዋችሁ፡፡ አላህንም ፍሩ፣ ታዘዙኝም፡፡

ሱረቱ አሊ-ዒምራን (3)፡50

“(I have come to you), to attest the Law which was before me, and to make lawful to you part of what was (before) forbidden to you…”’ 

ኢየሱስ ክርስቶስ በአዲስ ኪዳን ስለ ቅድስና ካስተማረው ትምህርቶች መካከል የሚከተለው አንዱ ነው፡-

  • እርሱም፡- እናንተ ደግሞ እንደዚህ የማታስተውሉ ናችሁን? ከውጭ ወደ ሰው የሚገባ ሊያረክሰው ምንም እንዳይችል አትመለከቱምን? ወደ ሆድ ገብቶ ወደ እዳሪ ይወጣል እንጂ ወደ ልብ አይገባምና፤ መብልን ሁሉ እያጠራ አላቸው። እርሱም አለ፡- ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው። ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ መጐምጀት፣ ክፋት፣ ተንኰል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስድብ፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ናቸውና፤ ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውን ያረክሰዋል። 

ማርቆስ 7፡18-23

ኢየሱስ ሁሉንም የዓለም ሕዝብ አንድ በማድረግ፣ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ታላቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን የሥነ-ምግባር ሕግ በእግዚአብሔር የቅድስና መለኪያ ልክ ሊኖሩት እንዲችሉ ኃይልን (ጸጋን) ሊሰጣቸው እንደመጣ እናውቃለን፡፡ የዓለም ህብረተሰብ በተለያዩ አካባቢዎችና መልክአ ምድሮች ውስጥ ባደገና በሰፋ መጠን አኗኗሩ በሚፈጥረው ልዩነት የተነሳ ሁሉን በአንድ ሊዳኝ የሚችል ማኅበራዊ ሕግ ሊኖር አይችልም፡፡ ሆኖም ግን፣ ታላቁ የኢየሱስ የሥነ-ምግባር አስተምህሮዎች በማንኛውም ሁኔታና ቦታ ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ለእግዚአብሔር ታላቅ ክብርን የሚያመጣው ከምግብ መቆጠባችን ሳይሆን ለእርሱና ለተከታዮቹ ሁሉ በምናሳየው እውነተኛ ፍቅር ነው! ይህ ሕግ በማንኛውም ሰው እና በየትኛውም የዓለም ክፍል ተግባራዊ ሊሆን ይችላል!

የሙሴ ማሕበራዊ ሕጎች ለእሥራኤል ልጆች መሆኑ መታወቅ አለበት፣ በርካታዎቹ ክርስቲያኖች ከእሰራኤል የዘር ግንድ ስላልሆኑ በእሥራኤላውያን ማኅበራዊ ሕጎችና ልማዶች የግድ መገዛት አይኖርባቸውም፡፡

አንዳንዴ ግን በአካባቢያቸው ያሉ አሳማዎች፣ ውዳቂና የሞተ አካል ሥጋን የሚመገቡ መሆናቸውን ካወቁ ስለ ጤንነታቸው ሲሉ የአሳማን ሥጋ ከመመገብ መቆጠብ እንዳለባቸው ክርስቲያኖች ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ስለ ሰውነታችን መጠንቀቅ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነውና፡፡ አንዳንድ ክርስቲያኖች ደግሞ ለሙስሊም ወዳጆቻቸውና ጎረቤቶቻቸው የክርስቶስን አዳኝነት ለመመስከር እንቅፋት ሆኖ ካገኙት የአሳማ ሥጋ ከመብላት ሊቆጠቡ ይችላሉ፡፡ የአሳማ ሥጋ በቤትህ እንዳይኖር ብታደርግ ሙስሊሞች እንዲጎበኙህ፣ እንዲያዋሩህ፣ አብረውህ እንዲመገቡ ከማድረጉ አልፎ ታላቁን የወንጌል ዜና ለማስተላለፍ እድል ይከፍትልሃል፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: