የሚያንገጫግጭ መንገድ

ሰዎች፣ ሕይወት አስቸጋሪ እንደሆነች ሲነግሩኝ ሁልጊዜ የምመልሰው ‹‹በእርግጥ አስቸጋሪ ናት፡፡›› በማለት ነው፡፡ ልሰጥ ከምችላቸው ምላሾች በላይ ይህ መልስ ያረካኛል፡፡ ፀሐፊ ቻርለስ ዊሊያምስ በአንድ ወቅት እንዲህ አለ፣ ‹‹አለም በሁሉም ረገድ ስቃይ አለባት፤ ይህን ስቃይ መውደድ ይኖርብናል የሚለውን ሃሳብ መስማት ደግሞ ሊሸከሙት የማይችሉት ዜና ነው፡፡››

እግዚአብሔር እኛን ይዞን የሚጓዝበት መንገድ ብዙውን ጊዜ እኛ ለራሳችን ካየነው ጥሩ መንገድ አንጻር በተቃራኒው ሊመስል ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዴ እየተጓዝንበት ያለንበት የእግዚአብሔር መንገድ ትክክለኛ ያልሆነ ይመስለናል፡፡ ለዚህ ነው ብዙዎቻችን፣ በትክክለኛው መንገድ ላይ ብሆን ኖሮ፣ የእግዚአብሔር መልካምነት፣ ሁል ጊዜ ከችግር ነፃ በሆነ የሕይወት ጎዳና ይመራኝ ነበር ብለን የምናስበው፡፡
ይህ ሃሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሃሳብ የወጣና ሊሰራ የማይችል ሕልም ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ምድራዊ ምቾት በሌለበት ጎዳና ሊመራን ይችላል፡፡ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፣ ‹‹… ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም›› (ፊል. 1፡29)፡፡ ስንጓዝበት ከነበረው የመከራ ጉዟችን ስንወጣ እያንዳንዱን ሁኔታ እግዚአብሔር ለዘለቄታዊ ጥቅማችን ሲል የፈቀደው እንደነበረ ይገባናል፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ የሆነው ኤፍ ቢ ሜየር እንዲህ አለ፣ ‹‹ካለፍንበት መንገድ የተሻለ ተስማሚ ወይም ደህና መንገድ የለም፤›› ‹‹አንድን መንገድ ልንመረጠው የምንችለው እግዚአብሔር እንደሚያየው፣ እኛም ማየት ስንችል ብቻ ነው፡፡›› ዴቪድ ሮፐር ይህን አስመልክቶ ሲናገር ደግሞ እንዲህ ይላል፣ «እግዚአብሔር መከራዎቻችንን የፈቀደበት ምክንያት አውቀነው ቢሆን ኖሮ የትኛውም መከራ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንድንገባ ባላደረገን ነበር፡፡››

ወንጌል በድረ ገጽ አገልግሎት፤ https://ethiopiansite.com/
Our daily Bread – (መጋቢት 21, 2005) – የሚያንገጫግጭ መንገድ
ትርጉም፣ አዳነው ዲሮ

በወንጌል በድረገጽ ላይ ያሉ ጽሁፎችን በ PDF ፋይል ፎርማት ለማስቀመጥ (save) ለማድረግ

ሰላም፣

በወንጌል በድረገጽ ላይ ያሉ ጽሁፎችን በ PDF ፋይል ፎርማት በግሎ ማህደር ለማስቀረት (save) የሚሹ ከሆነ የሚከተሉትን ቅደም ተከተሎች ተግባራዊ ያድርጉ፦
 1. የሚፈልጉትን ጽሑፍ ከዌብ ሳይቱ (https://ethiopiansite.com/) ላይ ከከፈቱ በኋላ የጽሁፉ መጨረሻ (ግርጌ) ላይ ይሂዱ፤
 2. በጽሁፉ መጨረሻ (ግርጌ) ላይ የሚከተሉትን አማራጮች ያገኛሉ (Press This, Twitter, Facebook, More)፣ ከእነዚህ አማራጮች መካከል (More) የሚለውን ይጫኑ (ክሊክ) ያድርጉ፤
 3. (More) የሚለውን ሲጫኑ የሚመጣውን (Print) የሚል አይከን ይጫኑ፤
 4. በሚከፈተው የ Print ዊንዶ ውስጥ (Destination) በሚለው ትይዩ ያለውን ድሮፕ ዳውን (የተዘቀዘቀ ቀስት የሚመስል ምልክት) በመክፈት (Save as PDF) የሚለውን ይምረጡ፤ ከዛም (Save) ያድርጉት፡፡ አበቃ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስዎን በማጥናት መንፈሳዊ ሕይወትዎን ያሳድጉ (https://ethiopiansite.com/)

የኢየሱስ መፈተን (ማቴ. 4፡1-11)

ተስፋዬ ክርስቲያን ነጋዴ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ንግዱን በሚያካሄድበት መንገድ ሊከብር እንደሚፈልግ ያውቃል። ነገር ግን ጉቦ ካልከፈለ ባለሥልጣናቱ የንግድ ፈቃዱን እንደማያድሱለት ይገነዘባል። «ጉቦ ብሰጣቸው ምን አለበት?» ሲል አሰበ። ስለሆነም ተስፋዬ ጉቦ በመስጠት የንግድ ፈቃዱን ኣሳደሰ። ሰዎች ጉቦ መስጠቱን ሲገነዘቡ፥ ወዲያው እውነተኛ ሰው አለመሆኑን አወቁ። ጌታሁን ወደ አሜሪካ ሄዶ ለመማርና እዚያው ለመኖር የሚፈልግ ብሩኅ አእምሮ ያለው ተማሪ ነበር። በታማኝነት እዚያው ለመኖር እንደሚፈልግ ለኤምባሲው ኃላፊዎች ሲናገር ቪዛ እንደማይሰጠው ያውቃል። ስለሆነም ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ ተመልሶ እንደሚመጣ ቃል ገባላቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች የሚፈልጓቸውን ነገሮች ለመፈጸም ሲሉ የተሳሳቱ ነገሮችን ለማከናወን እንደሚፈተኑ የሚያሳዩ ሌሎች ምሳሌዎችን ስጥ። ለ) ፈተናቸው ምን ነበር? ሐ) እግዚኣብሔር ተግባሮቻቸውን እንዲያከናውኑ የሚፈልገው እንዴት ይመስልሃል? መ) የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት ስንል የተሳሳቱ ዘዴዎችን የምንጠቀም ከሆነ፥ በእግዚአብሔር ላይ ስላለን እምነት ምን እያሳየን ነው? ሀ) በቅርቡ የምትፈልገውን ነገር ለማግኘት ስትል ምን ለማድረግ ተፈትነህ ነበር?

ሁላችንም ሰይጣን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን። እርሱና ረዳቶቹ የሆኑት ኣጋንንት የእግዚአብሔር ሕዝብ ኃጢኣትን እንዲፈጽም ባለማቋረጥ ይፈትናሉ። ከፈተኑን በኋላ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ይከሱናል። (ሰዕብራይስጡ «ሰይጣን» እና በግሪኩ «ዲያብሎስ› ማለት ከሳሽ ማለት ነው። ይህም ሰይጣን አማኞች ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ እንደሚከሳቸው ያሳያል።) አንድ የተሳሳተ ተግባር ለመፈጸም በምንነሣበት ጊዜ እንፈተናለን። ነገሩ መልካም ወይም አስደሳች ይመስላል። የምንፈልገውን ነገር የምናገኝበት አቋራጭ መንገድ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ይህ ሁልጊዜም እግዚአብሔር ለእኛ ከሚፈልገው መንገድ ውጭ ነው። ሔዋን እንደ እግዚአብሔር ለመሆን ስለ ፈለገች፥ መልካሙንና ክፉውን የምታስታውቀውን ፍሬ በላች። ወሲባዊ እርካታን ስለምንፈልግ፥ የጋብቻችን ጊዜ ሳይደርስ አሁኑኑ በአቋራጭ መንገድ ለመፈጸም እንሻለን። ወይም ቁሳዊ ሀብቶችን እንፈልግና እግዚአብሔር በጊዜው እንዲባርከን ከመጠበቅ ይልቅ አንድን ነገር ለማግኘት እንዋሻለን፤ ስለዚህ ጉቦ እንሰጣለን።

ስለ ክርስቶስ ከሚያስደንቁን ነገሮች አንዱ፥ እግዚአብሔር ልጁም እንደኛ እንዲፈተን መፍቀዱ ነው። በዕብ 2፡17-18፤ 4፡15 ላይ ከኃጢአት በስተቀር በሁሉም ነገር እንደኛ የተፈተነ ሊቀ ካህናት እንዳለን ተገልጾአል። ፈተና ሲያጋጥመን እንድናሸንፍ የሚረዳን ስለዚህ ነው።

ልጁ ለአገልግሎት በሚዘጋጅበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ሆን ብሎ ልጁ እንዲፈተን አድርጓል። እንዲያውም በምድረ በዳ በዲያብሎስ እንዲፈተን ያደረገው መንፈስ ቅዱስ ነበር። ክርስቶስ ለ40 ቀናት ያለምግብ በቆየባቸው ጊዜያት በተለያዩ መንገዶች ተፈትኗል። ዋንኛው ፈተና የተከሰተው ግን፥ ያለ ምግብ በቆየባቸው 40 ቀናት መጨረሻ ላይ ነበር። መሢሑ አካላዊ ድካም በተጫጫነው ሰዓት፥ ሰይጣን እርሱን ለማጥመድ የሚችልበት አጋጣሚ እንደደረሰ አሰበ። ሰይጣን ሁልጊዜ የሚፈትነን ደካማ በምንሆንበት ነገር ነው። በክርስቶስም ላይ ያደረገው ይህንኑ ነበር ። ፈተናዎቹ ክርስቶስ እንደ መሢሕ ከሚያጋጥሙት ነገሮች ጋር የሚዛመዱ ነበሩ።

ማቴዎስ ይህንን ታሪክ የሚገልጸው ሰይጣን እያንዳንዳችንን እንዴት እንደሚፈትነንና ፈተናውን እንዴት እንደምንቋቋም ለማሳየት ነው። ክርስቶስ የተፈተነው በሦስት የሕይወት ፈርጆች ሲሆን፥ እነዚህም የሥጋ ምኞት፥ የሕይወት ትምክሕትና የዐይን አምሮት ናቸው (1ኛ ዮሐ. 2፡16)። አንዳንድ ምሑራን የዚህ ፈተና ውጤት የኣዳምና ሔዋን ፈተና ውጤት ተቃራኒ መሆኑን ይናገራሉ። የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጅ ወላጆች በፈተናው ወድቀው ሞትን ሲያመጡ፥ «ሁለተኛው አዳም» ፈተናውን ተቋቁሞ የሰውን ልጅ ሊታደግ ችሏል (ሮሜ 5፡12-19)። ሌሎች ምሑራን የክርስቶስን ፈተና ከአይሁዶች በምድረ በዳ መቅበዝበዝ ጋር ያመሳስላሉ። ኣይሁዶች ለ40 ዓመት በምድረ በዳ እንደ ተቅበዘበዙ ሁሉ፥ ክርስቶስም ለ40 ቀናት በምድረ በዳ ውስጥ ቆይቷል። በምድረ እስራኤል ውስጥ በመቅበዝበዟ እንደ አገር የምትደራጅበትን ሁኔታ እንዳዘጋጀ ሁሉ (ዘዳግ. 8፡2-3)፥ የክርስቶስም ፈተና የእስራኤል መሢሕ እንዲሆን አዘጋጅቶታል። ኢየሱስ፥ እግዚአብሔር ከዚህ በፊት ከእስራኤል የፈለገውን ታዛዥነትና በመከራ ውስጥ በእርሱ የመታመን ምሳሌ ሆነ።

የውይይት ጥያቄ፡- ዕብ 2፡15-18፤ 5፡ 7-8 ኣንብብ። ሀ) የክርስቶስ መፈተንና መሠቃየት ያስፈለገው ለምንድን ነው? ለ) ክርስቶስ እንደ እኛ መፈተኑ በምን መንገዶች ሊያበረታታን ይችላል?

የመጀመሪያው ፈተና ድንጋይን ወደ ዳቦ መለወጥ ነበር። ክርስቶስ ለ40 ቀናት ከጾመ በኋላ በረሃብ ደክሞ ነበር። ድንጋይን ወደ ዳቦ መለወጡ ምን ችግር አለው? ክርስቶስ እንጀራ አብዝቶ ሰዎችን መግቦ የለ! በተራበበት በዚያ ሰዓት ለምን ኃይሉን ተጠቅሞ ድንጋዩን ዳቦ አላደረገውም? ፈተናው ሥልጣኑን ለራሱ ጥቅም ሳይሆን ለእግዚአብሔር ክብር ማዋሉ ነበር። እግዚአብሔር የፈቀደው ክርስቶስ ኃይሉን ለሌሎች ጥቅምና ለእግዚአብሔር ክብር እንዲያውል ነበር። ተኣምራትን የማድረግ ኃይሉ ለግል ጥቅሙ አልነበረም። በተጨማሪም ኢየሱስ ኃይሉን ይጠቀም የነበረው በእግዚአብሔር ሲፈቀድለት ብቻ ነበር። በኋላም ክርስቶስ አብ የነገረውን ብቻ እንደሚያደርግ ገልጾአል (ዮሐ 5፡19-20)። ሰይጣን ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እንዲጠራጠር ለማድረግ አልሞከረም። ሰይጣንም ሆነ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነቱን ያውቁ ነበር። ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቶስ፥ ሥልጣኑን እግዚኣብሔር ባልፈቀደው መንገድ እንዲጠቀም እየፈተነው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙውን ጊዜ ክርስቲያን መሪዎች ሥልጣናቸውን ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ጥቅም የሚያውሉት እንዴት ነው? ለ) ይህ ስሕተት የሚሆነው እንዴት ነው?

በፊልጵ. 2፡5-8 ላይ ክርስቶስ ወደ ምድር በመምጣቱ መለኮታዊ ባሕርያቱን «ባዶ» እንዳደረገ ተገልጾአል። ምንም እንኳ ክርስቶስ አምላክነቱን ባያጣም፥ በምድር ላይ ሳለ እውነተኛ ሰው መሆኑ ይታወቅ ዘንድ እግዚአብሔር እስካልፈቀደለት ድረስ መለኮታዊ ኃይሉን ሳይጠቀም ቀርቷል። ክርስቶስ ድንጋዩን ወደ ዳቦ ለመለወጥ ወይም የግል ጥቅሞችን ለማሟላት በኃይሉ ቢጠቀም ኖሮ፥ እውነተኛ ሰው አይሆንም ነበር። በእግዚአብሔር ዕቅድ ክርስቶስ በመከራ አማካይነት መታዘዝን መማር ነበረበት (ዕብ. 5፡7-8)። ለሥጋዊ ፍላጎቶች ቅድሚያ ከሰጡት እስራኤላውያን ባሻገር፥ ፍጹም ሰው የሆነው ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔርን ቃል ለመታዘዝ ራሱን አስገዝቷል።

እዚህ ላይ ክርስቶስ ሰይጣንን እንዴት እንዳሸነፈ ማጤኑ ጠቃሚ ነው። ሔዋን እንዳደረገችው ከሰይጣን ጋር አልተሟገተም። ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቃል ተጠቅሞ እግዚአብሔርን መታዘዝ ከምግብና ከግል ጥቅም እንደሚልቅ ገለጸለት። ያንን ሁሉ ሥልጣን የያዘው ክርስቶስ፥ ሰይጣንን ለማሸነፍ ይጠቀምበት ዘንድ የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት ካስፈለገው፥ እኛስ ሰይጣን በሚፈትነን ጊዜ እናሸንፈው ዘንድ የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት ምን ያህል እጅግ ያስፈልገን ይሆን?

ለሁለተኛው ፈተና ሰይጣን ክርስቶስን በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው የቤተ መቅደስ ጫፍ ወስደው። ይህ ፈተና የተሰጠው በአይሁድ ሕዝብ ፊትና በሃይማኖት ማዕከል ውስጥ ነበር። ይህ የሆነው ክርስቶስ በአካል በተገኘበት ስፍራ ይሁን በመንፈስ አልተገለጸም። (ለምሳሌ፥ ጳውሎስ ወደ ሦስተኛው ሰማይ የተወሰደው በአካል ይሁን በመንፈስ እንዳላወቀ ተናግሯል። 2ኛ ቆሮ.12፡24።) የሄሮድስ ቤተ መቅደስ ከጥንቱ ዓለም አስደናቂ ሥራዎች አንዱ ነበር። በዚህ ጊዜ ለ50 ዓመት ያህል በመገንባት ላይ ነበር። ከአንደኛው የቤተ መቅደሱ ጣሪያ ጫፍ፥ ኢየሱስ አሽቆልቁሎ የኢየሩሳሌምን ከተማ ለመመልከት ይችል ነበር።

ሰይጣን ኢየሱስ ያደረገውን በማስመሰል ለሁለተኛው ፈተና መጽሐፍ ቅዱስን ጠቅሷል። ክርስቶስ ከቤተ መቅደሱ ወደ ታች ራሱን እንዲወረውር ነገረው። ለዚህም አሳቡ፥ እግዚኣብሔር ክርስቶስን ለማዳን መላእክቱን እንደሚልክ የእግዚአብሔርን ቃል ጠቀሰለት [መዝ. (91)፡11-12]። ሰይጣን ይህን ሲል መጽሐፍ ቅዱስን ለራሱ ጥቅም በተሳሳተ መንገድ እየጠቀሰ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ሰዎች ውሸትን እንዲያምኑ ለማድረግ ሰይጣን መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ የሚጠቀመው እንዴት ነው? አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ። ለ) የእግዚአብሔር ቃል በተሳሳተ መንገድ መተርጎሙን ወይም አለመተርጎሙን ለማረጋገጥ ምን ልናደርግ እንችላለን?

ይህ ሁለተኛው ፈተና ምን ነበር? አንዳንድ ሰዎች ይህ ክርስቶስ አስደናቂ ተአምራትን በመሥራት ሰዎች በራሱ እንዲያምኑ የሚረዳ እንደ ነበር ይናገራሉ። እነዚህ ወገኖች ክርስቶስ ራሱን ከቤተ መቅደሱ ቢወረውርና መላእክት ቢይዙት፥ ብዙ ሰዎች በክርስቶስ ሊያምኑ እንደሚችሉ ይናገራሉ። ነገር ግን ክርስቶስ በአስደናቂ ተአምራት ምክንያት ሰዎች እንዲያምኑበት አይሞከርም።

የውይይት ጥያቄ፡- አንዳንድ ሰዎች ፈተናን በትክክለኛ ምክንያት ሳይሆን፥ መንፈሳዊነታቸውን ወይም ኃይላቸውን ለማሳየት የሚጠቀሙበት እንዴት ነው?

ሰይጣን ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት እንዲፈትን እየጠየቀው ሳይሆን አይቀርም። «አንተ የእርሱ ልጅ ነህ። እግዚአብሔርን ፈትነውና ካንተ ጋር ያለውን ልዩ ግንኙነት እንዲያሳይ አድርግ። ራስህን ወደ ታች ወርውርና እንዲያድንህ አስገድደው» ማለቱ ነው።

ይህ ፈተና ሁለት በጣም ጠቃሚ ትምህርቶችን ያስተምረናል። በመጀመሪያ፥ ሰይጣን ኃጢአት እንድንሠራ ለማድረግ መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ እንደሚጠቀም ያሳየናል። መዝ 90፡11-12 እግዚአብሔር ልጆቹ በታዛዥነት በሚመላለሱበት ጊዜ እንደሚጠብቃቸው ይናገራል። ይህ እግዚአብሔር እንዲጠብቀን የምናስገድድበት አይደለም። ለዚህ ነው እግዚአብሔር በቃሉ የሚናገረውን በትክክል መተርጎም የሚያስፈልገን። ቃሉን ከጠመዘዝነው እኛ የፈለግነውን ሁሉ እንዲልልን ማድረግ እንችላለን። የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል መጠቀማችንን ለማረጋገጥ የምንችልበት አንድ ጠቃሚ መንገድ፥ ጠቅላላውን የመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ ማወቅና አንዱን እውነት ከሌላው ጋር ማነጻጸር ነው። እግዚአብሔር ከራሱ ጋር ስለማይቃረን፥ የትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ወይም አሳብ ከሌላው ክፍል ጋር እንደማይቃረን እርግጠኛች ልንሆን እንችላለን፡፡ ክርስቶስ ይህንን ስለሚያውቅ፥ እግዚአብሔር እንዲጠብቀን ለማስገደድ መፈተን እንደማይገባን ቃሉ በትክክል እንደሚያሳይ አመልክቷል።

ሁለተኛው፥ በእግዚአብሔር ላይ እምነት መጣል ምን ማለት እንደሆነ ያስተምረናል። ብዙዎቻችን በእግዚአብሔር ማመናችን ከእግዚአብሔር አንድን ነገር የመጠየቅና እርሱን የመፈተን መብት ይሰጠናል ብለን እናስባለን። «እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ መፈወስ ትችላለህ። ስለሆነም፥ ይህን ግለሰብ እንድትፈውሰው እፈልጋለሁ» እንላለን። ከዚያም በቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ፊት ግለሰቡን ጠርተን ፈውስን እናውጃለን። «እግዚአብሔር እንዲፈውሰን ከነገርነውና በተለይም ኃይሉን በተአምራዊ መንገድ ለማሳየት በምንፈልግበት ጊዜ አይፈውስ ይሆን?» ብለን እናስባለን። ወይም ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት እንፈልጋለን። ምንም እንኳ የቤተ ክርስቲያኒቱ የገንዘብ አቅም ከዕቅዳችን ጋር ባይጣጣምም፥ በእግዚአብሔር «በማመን» ሥራውን እንጀምራለን። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዐይነቱ ተግባር እኛን ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርንም ስም በማኅበረሰቡ ዘንድ ያሳንሳል። እግዚአብሔር አንድን ሰው እንደሚፈውስ ወይም አንድን ሕንጻ እንደሚገነባ በግልጽ እስካልተናገረን ድረስ፥ እግዚአብሔር ለአስገዳጅ እምነታችን ምላሽ እንዲሰጥ መሞከሩ እርሱን መፈተን ነው። ይህም ሰይጣን ክርስቶስን የፈተነውን ዓይነት ኃጢኣት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች እግዚአብሔር የሚፈልጉትን ነገር እንዲፈጽምላቸው በማስገደድ እንዴት ሊፈታተኑት እንደሚችሉ ሌሎች ምሳሌዎችን ዘርዝር። ለ) እግዚኣብሔርን የሚፈትን አስገዳጅ እምነት ከእውነተኛው እምነት እንዴት ይለያል?

አሁንም ክርስቶስ ከሰይጣን ጋር አልተከራከረም። ሰይጣን ለምን እንደሚፈትነው ተረድቶ ነበር። ጉዳዩ የራስ ወዳድነት ምክንያት መሆኑን ስለተገነዘበ፥ ወደ ዘዳግም 6፡16 በመሄድ ማንም ሁኔታዎችን በመጠቀም እግዚአብሔርን ለአንዳች ተግባር ሊያስገድደው እንደማይችል ነገረው። ማንም እግዚአብሔርን መፈተን አይገባውም።

ክርስቶስ ድርሻው በየዕለቱ እግዚአብሔር አብ ያዘዘውን መፈጸም እንደሆነ ያውቅ ነበር። ተአምራት የማድረግ ኃይሉም ሆነ የእግዚአብሔር ጥበቃ የሚመጣለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሚያደርግበት ጊዜ እንደሆነ አልጠፋውም። በኋላ እግዚኣብሔር ክርስቶስን በድንጋይ ከመወገር፥ ከመታሰርና ያለጊዜው ከመገደል ጠብቆታል። እርሱን እየታዘዝን በምንመላለስበት ጊዜ እግዚአብሔር እንደሚጠብቀን እሙን ነው። ካስፈለገም መላእክቱን በመላክ ይታደገናል። ይህ ግን እግዚአብሔር መቼ ተኣምር መፈጸም እንዳለበት ወይም እንዴት እኛን መጠበቅ እንዳለበት ለማዘዝ መብት አይሰጠንም። ከራሳችን ግዴለሽነት የተነሣ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ወድቀን እግዚአብሔር እንዲረዳን ለማድረግ መብት አይሰጠንም።

ሦስተኛው ፈተና የተከሰተው ሰይጣን ክርስቶስን ወደ ረጅም ተራራ በወሰደው ጊዜ ነበር። አሁንም ሰይጣን ክርስቶስን የወሰደው በሥጋ ይሁን በመንፈስ አናውቅም። ተራራው የት እንደሚገኝም አናውቅም። ተራራው የሚገኘው በሊባኖስ ወይም ከሲና ተራራ በታች ሊሆን ይችላል። ስፍራው የትም ይሁን የት ሰይጣን ለክርስቶስ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በራእይ አሳየው። ከዚያም እነዚህን መንግሥታት እሰጥሃለሁ አለው።

ክርስቶስ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ነው። በብሉይ ኪዳን በዓለም ሁሉ ላይ እንደሚነግሥ የሚገልጹ ብዙ የተስፋ ቃሎች ተሰጥተውታል። ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጅ የኃጢአትን ቅጣት ለመክፈልና ለራሱ ቅዱስ ሕዝብ ለመሰብሰብ በመስቀል ላይ መሞት ነበረበት። ይህም ክርስቶስ በዓለም ላይ የሚነግሥበትን ጊዜ በብዙ መቶ ምእተ ዓመታት ያርቅበታል (ፊልጵ. 2፡91)። አሁን ሰይጣን ለክርስቶስ አቋራጭ መንገድ በማቅረብ በመስቀል ላይ ሳይሞት የምድርን መንግሥት ሊጨብጥ እንደሚችል ገለጸለት። ሰይጣን የዚህች ዓለም ጊዜያዊ ገዥ መሆኑን ክርስቶስ ያውቅ ነበር (ዮሐ 12፡3)። ስለሆነም ሰይጣን በጊዜያዊው የዓለም መንግሥት ላይ ለክርስቶስ ሥልጣን መስጠት ይችል ነበር። ነገር ግን ለሰይጣን ቢሰግድ ኖሮ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ላይ የሚካሄድ የሰይጣን ዐመፅ ተሳታፊ ይሆን ነበር። ሰይጣን የወደቀው እንደ እግዚአብሔር ለመሆንና ለመመለክ በመፈለጉ ምክንያት ነበር (ኢሳ. 14፡12-15)። ክርስቶስ ሰይጣንን ማምለክ ለእግዚኣብሔር ብቻ የሚገባውን አምልኮ መንሳት እንደሆነ ያውቅ ነበር። አይሁዶች፥ ክርስቲያኖችም ሆኑ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ውጭ ምንም ነገር ወይም ማንንም ሰው እንዲያመልኩ ኣልተፈቀደላቸውም። ስለሆነም ክርስቶስ ዘዳግም 6፡13ን በመጥቀስ ከእግዚአብሔር ውጭ ማንንም ለማምለክ እንደማይፈልግ ለሰይጣን ነገረው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር የሚሰጠንን አንድ ነገር በአቋራጭ ለመቀበል ክርስቲያኖች ልንፈጽማቸው የምንችላቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ስንል በለይጣን ወጥመድ ተይዘን እርሱን ልናመልክ የምንችልባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? ሐ) ብዙውን ጊዜ ሥቃይ ያለበትንና ረዥም ጊዜ የሚወስደውን የእግዚአብሔርን መንግድ ትተን በፍጥነት የሚመጣውን የሰይጣንን በረከት በሁከት በምንከተልበት ጊዜ፥ ለእግዚአብሔር ስለ መገዛታችን የምናስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው?

ክርስቶስ የኋላ ኋላ የእርሱ የሚሆነውን በረከት ለማግኘት ሲል አቋራጭ መንገድ ለመከተልና እምነቱን ለማመቻመች አልፈለገም። እግዚአብሔር የዓለምን መንግሥት ሁሉ እንደሚሰጠውና ሁሉም እንደሚንበረከክለት ያውቅ ነበር። ነገር ግን የእግዚአብሔርን መንገድ በመስቀሉ በኩል ማለፍ እንዳለበት ያውቃል። ጊዜያዊ በረከት እግዚአብሔርን ላለመታዘዝ ማመኻኛ ሊሆነን አይችልም።

ሰይጣን ክርስቶስ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ከጠቀሰለት በኋላ፥ በእግዚአብሔር ልጅነት ሥልጣኑ ከእርሱ እንዲርቅ አዘዘ። ሰይጣንም ታዘዘ። ነገር ግን በቀረው የክርስቶስ የአገልግሎት ዘመንና በተለይም በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ፥ ሰይጣን ክርስቶስን በኃጢአት ለመጣል ፈትኖታል። ማቴዎስ ከዚያ በኋላ መላእክት ቀርበው እንዳገለገሉት ገልጾአል። ሰይጣን ክርስቶስ፥ እግዚአብሔርን መላእክትን እንዲልክለት እንዲያስገድደው ቢፈልግም፥ ክርስቶስ ለፈቃዱ ራሱን ካስገዛ በኋላ እግዚአብሔር መላእክት ልኮለታል።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ክርስቶስን ለይፋዊ አገልግሎቱ ካዘጋጀበት መንገድ ምን እንማራለን? እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ መሪዎችን ለኣገልግሎት የሚያዘጋጅበትን አንዳንድ ምሳሌዎች ዘርዝር።

አብዛኛውን ጊዜ ወደ መሪነት ሥልጣን ለመውጣት እንቸኩላለን። የተወሰነ ትምህርት ካገኘን በኋላ የመሪነት ሥልጣን መያዝ እንደሚገባን እናስባለን። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ሥልጣን ማግኘታችን ለአመራር ኃላፊነት ብቁ አያደርገንም። ብዙ መሪዎች ለመሪነት ዝግጁ ባለመሆናቸው ሥልጣኑን በሚረከቡበት ጊዜ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ጉዳት ያስከትላሉ ። እግዚኣብሔር እንደኛ አይቸኩልም። ኢየሱስ በመሪነት ስፍራ ላይ የተቀመጠው 30 ዓመት ሲሞላው ነበር። እግዚአብሔር የበለጠ ትኩረት ያደረገው ልጁን ወደፊት ለሚጠብቁት ኃላፊነቶች ማዘጋጀቱ ላይ ነበር። ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ግንኙነትና በባሕርዩ መዘጋጀት ያስፈልገው ነበር። ከዝግጅቱ መካከል ኣንዱ የእግዚአብሔርን ዕቅዶች የጊዜ ሰሌዳ ማወቅ ነበር። በገጠሪቱ ገሊላ ለእግዚአብሔር በታማኝነት ካገለገለ በኋላ፥ የእግዚኣብሔር ጊዜ በመድረሱ ክርስቶስ ይፋዊ አገልግሎቱን ጀመረ። ክርስቶስ ለይፋዊ አገልግሎቱ የተዘጋጀው መከራን በመቀበልና በመፈተን ነበር። እግዚአብሔር ሰዎችን ለመሪነት ለማዘጋጀት ከሚጠቀምባቸው ዐበይት መሣሪያዎች መካከል ሦስቱ ዝምታ፥ ኣለመታወቅና መከራ ናቸው። የእግዚአብሔርን ጊዜ ለመጠበቅ ዝግጁ ነን? ከእግዚአብሔር በቀር ማንም በማያውቀን ጊዜ እንኳ በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነን? መከራን ለመቀበል ዝግጁ ነን? እግዚአብሔር መሪዎችን ለማዘጋጀት የሚጠቀምበትን መንገድ በትክክል ብንረዳ፥ ብዙ የመሪነት ችግሮች ይቀረፋሉ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

የኢየሱስ መጠመቅ (ማቴ. 3፡13-17)

የኢየሱስ ሕይወት ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር አመራር ሥር ነበር። ይፋዊ አገልግሎቱ እስኪደርስ ድረስ በትዕግሥት በናዝሬት ከተማ ውስጥ ሲጠብቅ ቆየ። በዚያን ጊዜ የመጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎት በስፋት ይታወቅ ነበር። አንድ ቀን ኢየሱስ ከናዝሬት ተነሥቶ ዮሐንስ ወደሚያጠምቅበት ዮርዳኖስ ወንዝ (ይሁዳ ውስጥ) መጣ። መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስ መሢሕ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ብዙውን ጊዜ ትልቁ ትንሹን ስለሚያጠምቅ፥ መጀመሪያ ዮሐንስ ክርስቶስን ለማጥመቅ አልፈለገም ነበር። አንዳንድ ምሑራን ዮሐንስ ከእርሱ የውኃ ጥምቀት የሚበልጠውን የክርስቶስን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ፈልጎ ነበር ይላሉ።

ክርስቶስ ግን ጽድቅን ሁሉ ለመፈጸም ዮሐንስ ሊያጠምቀው እንደሚገባ ገለጸ። ምናልባትም ክርስቶስ ይህን ሲል በእግዚአብሔር የታቀደለት እንደሆነና ዮሐንስ ሊያጠምቀው እንደሚገባ መግለጹ ይሆናል። ይህ የታዛዥነትና የጽድቅ መንገድ ነበር። ምሑራን ክርስቶስ ለምን እንደ ተጠመቀ ይከራከራሉ። ክርስቶስ ከኃጢአት የጠራ ስለሆነ (ዮሐ 8፡46፤ ዕብ. 4፡15)፤ የእርሱ ጥምቀት ከኃጢአት ንስሐ መግባትንና የሕይወት ለውጥን የሚያመለክት አልነበረም። ምክንያቱ ግን ሌላ ነው። አዘውትረው ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።

1) ክርስቶስ ከመጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎት ጋር እንዲተባበር ለማድረግ። ክርስቶስ መጥምቁ ዮሐንስ እንዲያጠምቀው በመጠየቁ፥ ከዮሐንስ የንስሐና የጥምቀት መልእክት ጋር መስማማቱን ለሕዝቡ እያሳየ ነበር። እንዲያውም ራሱ ክርስቶስም ተመሳሳይ መልእክት ሰብኳል (ማቴ. 4፡17)።

2) ክርስቶስ አማኞች ሁሉ ሊከተሉት የሚገባውን ምሳሌ እያዘጋጀ ነበር። ጥምቀት ለአማኞች ከሚያስፈልጉ ዐበይት መመዘኛዎች አንዱ ነው። [መጽሐፍ ቅዱስ አማኞች ሁሉ እንዲጠመቁ ያዝዛል(ማቴ. 28፡19-20)።] ስለሆነም፥ ክርስቶስ ለሌሎች አርአያ ለመሆን ሲል ተጠምቋል።

3) ይህ የክርስቶስ ይፋዊ አገልግሎት ጅማሬ ነበር። እስከዚህ ጊዜ ድረስ ክርስቶስ በናዝሬት ይፋዊ ያልሆነ ሕይወት ሲመራ የቆየ ሲሆን፥ ካሁን በኋላ ግን የመሢሕነት አገልግሎቱ አደባባይ ይወጣል።

4) ክርስቶስ ኃጢአት ሠርቶ ባያውቅም፥ ራሱን ከኃጢአተኞች ጋር እያስተባበረ ነበር። ከአገልግሎቱ አንዱ የሆነው የሊቀ ካህንነት ተግባሩ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጥምቀት ለክርስቶስ አስፈላጊ ከነበረና ክርስቲያኖችም እንዲጠመቁ ከታዘዙ፡ ብዙ ክርስቲያኖች ያልተጠመቁት ለምንድን ነው? ለ) ጥምቀት ለክርስቲያኖች ምንድን ነው? (ሮሜ 6፡1-14፤ ቲቶ 3፡5 የሐዋ. 2፡38 አንብቡ።)

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሦስቱ የሥላሴ አካላት አብረው የሠሩበት አንዱ ግልጽ ምሳሌ የክርስቶስ ጥምቀት ነው።

የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ በምድር ላይ በዮሐንስ እጅ የተጠመቀው ነበር።

መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በክርስቶስ ላይ ወረደ። ምንም እንኳ አምላክ እንደ መሆኑ መጠን፥ በራሱ ሥልጣን ሊሠራና ሊያስተምር ቢችልም፥ ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ለአማኞች ምሳሌ በመሆን ለመንፈስ ቅዱስ ራሱን አስገዝቷል። መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ መውረዱ መሢሕ ሆኖ ለመቀባቱ ምልክት ነበር (ኢሳ. 11፡2)። መንፈስ ቅዱስ የርግብን አምሳል የመረጠው ለምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ርግብ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሆና ተጠቅሳለች። በፍጥረት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ (እንድ ርግብ) ሰፍፎ እንደ ነበር ተገልጾአል (ዘፍጥ. 1፡2)። ለአይሁዶች፥ ርግብ ገርና ሰላማዊ ኣገልግሎትን ታመለክታለች። ምንም እንኳ አይሁዶችና ዮሐንስ ጠላትን እያወደመና የጽድቅን መንግሥት እየመሠረተ በኃይል እንዲገለጥ ቢፈልጉም፥ ክርስቶስ የመጣው በትሕትናና በገርነት መንፈስ ነበር (ማቴ. 11፡29)።

እግዚአብሔር አብም በሥራው ውስጥ ተሳትፎአል። ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ እግዚአብሔር ልዩ ልጁ እንደሆነ በይፋ መስክሯል። (ይህ የእግዚአብሔር ቃል መዝ. 2፡7ን እና ኢሳ 42፡1ን ያንጸባርቃል። እነዚህም ስለ መሢሑ መምጣት የሚናገሩት ትንቢቶች ናቸው።) እግዚአብሔር በክርስቶስ ባሕርይና ተግባራት ሙሉ በሙሉ ደስ ተሰኝቶ ነበር። ክርስቶስ ሁሉም ሊከተሉት የሚገባ ፍጹም ሰው ነበር። ይህ እግዚአብሔር በክርስቶስ ደስ መሰኘቱን በይፋ ከመሰከረባቸው ሦስት አጋጣሚዎች አንዱ ነው (ማቴ. 17፡5 ዮሐ 12፡28)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ማቴ. 3፡16-7 እግዚአብሔር በሦስት አካላት (አብ፥ ወልድና መንፈስ ቅዱስ) እንደሚገለጥ የሚያሳየው እንዴት ነው? ለ) በሥላሴ ውስጥ ሦስት አካላት እንደሌሉና፥ ኣንዱ ኣምላክ ኣንዳንድ ጊዜ ኣብ፥ ሌላ ጊዜ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እየሆነ እንደሚገለጥ የሚያስተምረው «የኢየሱስ ብቻ» (Only Jesus) ተከታይ፣ ከሳተበት ለመመለስ ማቴ. 3፡16-17ን እንዴት ልትጠቀም ትችላለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት (ማቴ. 3፡1-12)

ማቴዎስ የክርስቶስን ታሪክ የቀጠለው ከሠላሳ ዓመት በኋላ ነበር። ማቴዎስ የክርስቶስን ይፋዊ አገልግሎት የጀመረው፥ ከክርስቶስ በፊት መጥቶ ሰዎችን ለእምነት ስለሚያዘጋጀው ነቢይ በአጭሩ በመግለጽ ነበር። ከዚያም ክርስቶስ የእግዚአብሔር አዳኝና ሊቀ ካህናት እንዲሆን ያዘጋጁትን ሁለት ክስተቶች ገልጾአል።

በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ከመሢሑ በፊት መንገድ ጠራጊ ነቢይ እንደሚላክ ለአይሁዶች ነግሯቸው ነበር። የብሉይ ኪዳን የመጨረሻው የእግዚአብሔር ነቢይ የሆነው ሚልክያስ ይህን ነቢይ «ኤልያስ» ብሎታል። ይህም ነቢዩ ከኤልያስ ጋር በሚመሳሰል መንገድ እንደሚመጣ ያሳያል። ከሚልክያስ እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ ለ400 ዓመት እግዚኣብሔር ለሕዝቡ አልተናገረም ነበር። እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ የተመራ ምንም ዓይነት ነቢይ አልላከም ነበር። ከረጅሙ ዝምታ በኋላ ግን አንድ ዐይን የማይገባ ልብስ የለበሰ ግለሰብ ከበረሃ ወደ ምሥራቅ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ዝምታው አበቃ [መጥምቁ ዮሐንስ ቆዳ የለበሰውና አንበጣ የበላው የአይሁዶች ነቢያት ምሳሌ የሆነውን ኤልያስን ለመምሰል ነበር (2ኛ ነገ. 1፡8)።] ስሙ ዮሐንስ ሲሆን፥ ልዩ ስሙ «መጥምቁ» የሚል ነበር። ይህም ሰዎች ሕይወታቸውን ለመለወጥና ለመሢሑ በተዘጋጀ ሁኔታ ለመኖር መወሰናቸውን ለማመልከት እንዲጠመቁ መጥራቱን ለማሳየት ነበር። እነዚህን ዐበይት እውነቶች ልብ አድርግ።

1. መጥምቁ ዮሐንስ ያስተላለፈው «የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» የሚል ቀላል መልእክት ነበር። ብዙውን ጊዜ ንስሐ መግባት ማለት ለፈጸምነው በደል መጸጸት ብቻ ይመስለናል። ነገር ግን የግሪኩ ቃል፥ ከዚያ የጠለቀና አያሌ ነጥቦችን ያካተተ ነው።

ሀ. የፈጸምናቸውን ዝርዝር ኃጢአቶችና እግዚአብሔርንም ያልታዘዝናቸውን ነገሮች አምነን እንቀበላለን። ኣብዛኛውን ጊዜ ይቅርታ ስንጠይቅ ኣንድን ሰው መበደላችንን እየገለጽን ነው። ኃጢኣታችን በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸም ዐመፅ መሆኑን እምብዛም ኣናጤንም። በዚህም ነው ብዙውን ጊዜ መጸጸታችንን ገልጸን ይቅርታ ብንጠይቅም፥ ተግባራችንን ግን የማንለውጠው።

የውይይት ጥያቄ፡- 1) ባለፈው ሳምንት የፈጸምኸውን ኃጢአት ጥቀስ። ይህ ኃጢአት የምትጸጸትበት ስሕተት ብቻ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ፊት የዐመፅ ተግባር የሚሆነው እንዴት ነው? 2) እያንዳንዱ ኃጢኣት በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸም ኃጢአት እንደሆነ ብንገነዘብ፥ ይህ በኃጢአት ላይ ያለንን አመለካከት እንዴት ይለውጠዋል?

ለ. እውነተኛ ንስሐ የፈጸምነውን ድርጊት ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ አኗኗራችንን የሚለውጥ ቁርጥ ውሳኔ የሚያካትት ነው። የግሪኩ ቃል ስለ ንስሐ የሚሰጠን አሳብ፥ ወደ አንድ አቅጣጫ ይሄድ የነበረ ሰው፥ ፊቱን አዙሮ በተቃራኒው አቅጣጫ መጓዙን ያሳያል። ጠቅላላ የተግባር ለውጥ የሌለበት ንስሐ ሊባል አይችልም። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ባሕርያቸውን ሳይለውጡ ውጫዊ የንስሐ ተግባር ለመፈጸም በመፈለጋቸው፥ መጥምቁ ዮሐንስ ወቅሷቸዋል። «የእፉኝት ልጆች» ብሎ በመጥራት፥ ሃይማኖታውያን ለመምሰል ቢሞክሩም፥ ጠቅላላ አኗኗራቸውን ሊለውጡና ፍጹም የተለየ አኗኗር ሊከተሉ እንደሚገባ ነግሯቸዋል። ሃይማኖተኛ መሆን ወይም ከትክክለኛው ነገድ ወገን (የአብርሃም ልጆች) መሆን ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንዲኖራቸው አላደረገም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ የንስሐ አሳብ ብዙውን ጊዜ ለማመን ወይም የቤተ ክርስቲያን ኣባል ለመሆን ለሚፈልጉ ሰዎች ከምንነግራቸው የሚለየው እንዴት ነው? ለ) የደኅንነት (የድነት) ወይም የይቅርታ ትምህርታችን፥ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ንስሐ የሚናገረውን ያንጸባርቅ ዘንድ እንዴት ሊለወጥ ይገባል?

ሐ ዮሐንስ ከልባቸው ለመለወጥና ለመሢሑ መምጣት የሚያዘጋጅ ሕይወት ለመኖር የወሰኑት ሰዎች እንዲጠመቁ ነገራቸው። ምሁራን የጥምቀትን አሳብ ከየት እንዳመጣ ይከራከራሉ። ጥምቀት በአይሁድ ታሪክ የተለመደ ነገር ነበር። በመጀመሪያ፥ አንድ አሕዛብ አይሁዳዊ ለመሆን በሚፈልግበት ጊዜ ይጠመቅ ነበር። ሁለተኛው፥ የኤሴናውያን ማኅበረሰብ አባል የሚሆን ሰው ሁሉ ይጠመቅ ነበር።

ጥምቀት ሁለት ዐበይት ዐላማዎች አሉት። በመጀመሪያ፥ አንድ ሰው አኗኗሩን ለመለወጥና እግዚአብሔርን ለመከተል የሚፈልግ ማኅበረሰብ አባል ለመሆን መፈለጉን ያሳያል። ግለሰቡ በውስጣዊ ሕይወቱ ለመለወጥ መፈለጉን የሚያሳይ ይፋዊ ምስክርነት ነበር። ሁለተኛው፥ የግለሰቡን ውስጣዊ ንጽሕና የሚያመለክት ውጫዊ ምሳሌ ነበር። ውኃ መንፈሳዊ ቆሻሻንና ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደማይችል አልጠፋቸውም ነበር። በብሉይ ኪዳን ካህናት እግዚአብሔርን ከማገልገላቸው በፊት በውኃ መታጠብ ያስፈልጋቸው ነበር። ይህም ኃጢአታቸውን በመናዘዝ መዘጋጀታቸውን የሚያመለክት ነበር። በተመሳሳይ መንገድ፥ ዮሐንስ የሚያጠምቃቸው ሰዎች ኃጢአታቸውን እንደ ተናዘዙና ሕይወታቸውን በእግዚአብሔር ፊት እንዳስተካከሉ ለማሳየት በውኃ ይታጠቡ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- የአይሁዶች የጥምቀት ግንዛቤ፥ ከክርስቲያኖች ጋር የሚመሳሰለው ወይም የሚለያየው እንዴት ነው?

ቤተ ክርስቲያን በተመሠረተችበት ወቅት፥ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ትእዛዝ ተከትለው ጥምቀትን ያካሂዱ ጀመር። በተጨማሪም ጥምቀት ክርስቲያኖች ክርስቶስን እንደ መሢሓቸው ለመከተል ሕይወታቸውን እንደ ሰውት የሚያመለክት ይፋዊ እርምጃ ነበር። ሕይወታቸው ከኃጢአት እንደ ነጻ ያሳዩ ነበር። እንዲሁም አማኞቹ የክርስቲያኖች ማኅበር አካል መሆናቸውንና የቤተ ክርስቲያን ሙሉ አባላት ለመሆን መፍቀዳቸውን እያሳዩ ነበር። ጥምቀት ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር መተባበራቸውንም የሚያሳይ ተግባር ነበር። ለአርጌ ኃጢኣታቸው ሞተው፥ ለአዲሱ ሕይወት ተነሥተዋል።

2. መጥምቁ ዮሐንስ «መንግሥተ ሰማይ» እንደ ቀረበች አውጇል። ከማቴዎስ ቁልፍ ሐረጎች አንዱ «መንግሥተ ሰማይ» የሚለው ነው። በመጽሐፉ ውስጥ 33 ጊዜ ያህል ጠቅሶታል። ይህ ሐረግ ማቴዎስ መጽሐፉን ለኣይሁዶች እንደ ጻፈ ያመለክታል። ሌሎቹ ወንጌላት ትርጉሙን ለአሕዛብ ይበልጥ ግልጽ የሚያደርገውን «የእግዚአብሔር መንግሥት» የሚለውን ሐረግ ተጠቅመዋል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፥ «መንግሥት» በአይሁዶችና በክርስቲያኖች ግንዛቤ መልክአ ምድራዊ አካባቢን ኣያመለክትም። ነገር ግን በአንድ ነገር ላይ ኃይልና ሥልጣን መቀዳጀትን ያመለክታል። ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔር መንግሥት ነው። እግዚአብሔር በኣንድ ሰው ልብ ውስጥ የሚገዛ ከሆነ፥ ያ የእርሱ መንግሥት ነው። [ለዚህ ነው ክርስቶስ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ (በውስጣችሁ) ነች ያለው (ማቴ. 17፡21)።] ወይም ደግሞ ይህ ክርስቶስ በቤተ ክርስቲያን ላይ መግዛቱን ሊያመለክት ይችላል። መንግሥት የሚለው ቃል አካባቢን ሊያመለክት የሚችለው ክርስቶስ በምድር ላይ የሚመሠረተውን የመጨረሻ መንግሥት በሚጠቅስበት ጊዜ ብቻ ነው።

ማቴዎስ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰማይ የሚለውን ስም የተጠቀመው አይሁዶች «እግዚአብሔር» (ጀሆቫ) የሚለውን ስም በቀጥታ ለመጥራት ስለሚፈሩ ነበር። በዘጸ 20፡7 መሠረት፥ ስሙን መጥራት እግዚአብሔርን እንዳላከበሩ ወይም እንዳቀለሉ ይሰማቸው ነበር። በተለይ በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል በነበረው ጊዜ፥ አይሁዶች እግዚአብሔር ስሙን ካቃለልን ይፈርድብናል ብለው ስለሚፈሩ፥ ይህ እውነት በጣም አስፈላጊ ሊሆን በቅቷል። ስለሆነም የእግዚአብሔርን ስም ለመጥራት «የሰማይ አምላክ» የሚሉትን ዐይነት ሌሎች አገላለጾች ይጠቀሙ ነበር (ነህ. 1፡4)። ለአይሁዶች «ሰማይ» የሚለው ቃል የእግዚአብሔር ምትክ ነበር። ስለሆነም ማቴዎስ «ሰማይ» ሲል እግዚአብሔር ማለቱ ነበር። ይህም መንግሥተ ሰማይ እና የእግዚአብሔር መንግሥት አንድ ዐይነት መሆናቸውን ያመለክታል።

3. መጥምቁ ዮሐንስ ስለ እግዚአብሔር የጊዜ ሰሌዳ ሙሉ ግንዛቤ አልነበረውም። በኋላ ኢየሱስ ዮሐንስ ባልጠበቀው መንገድ በመሥራቱ፥ መሢሑ አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ? ብሎ ሲጠይቅ እንመለከታለን (ማቴ. 11፡2-6)። ዮሐንስ የጠበቀው መሢሑ የሚገዛበትን ምድራዊ መንግሥት ሲሆን፥ ክርስቶስ መጀመሪያ የመጣው እንደ መንፈሳዊ ንጉሥ ነበር፡፡ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ ሲመጣ ንጉሣዊ አገዛዙ ይጀመራል። የእግዚአብሔር የፍርድ ጊዜ መድረሱ የዮሐንስ መልእክት አካል ነበር። ከልባቸው ንስሐ ገብተው ሕይወታቸውን ለመለወጥ የማይፈልጉ ሰዎች ለእግዚአብሔር ፈጣን ፍርድ ይጋለጣሉ። ይህ በመጨረሻው ዘመን ይፈጸማል።

4. መጥምቁ ዮሐንስ ሰዎችን ለማዘጋጀት እንደ ተጠራና ይህንንም በትክክል እንደ ፈጸመ ተረድቷል። ሰዎችን ወደ ራሱ ለመሳብ በመሞከር ራሱንና ድርሻውን ከፍ ከፍ ከማድረግ ይልቅ፥ ዮሐንስ ከእርሱ ለሚበልጥ ሌላ አገልጋይ መንገድ እያዘጋጀ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። ስለሆነም መሢሑ ከእርሱ በኋላ እንደሚመጣ ለሕዝቡ አበሠረ። መጥምቁ ዮሐንስ ወደ መሢሑ በማመልከት ሁለት ዐበይት አገልግሎቶቹን ጠቅሷል።

በመጀመሪያ፥ መንፈስ ቅዱስን በመስጠት አገልግሎቱን እንደሚጀምር ገልጾአል። ኣይሁዶችና የጥንት ክርስቲያኖች ከመሢሕ መምጣት ዐበይት ምልክቶች አንዱ የመንፈስ ቅዱስ በሰዎች ሁሉ ላይ መውረድ እንደሆነ ያውቁ ነበር (ኢዩ. 28-29 አንብብ።) በብሉይ ኪዳን ዘመን መንፈስ ቅዱስ አገልግሎታቸውን ለማጽናት ሲል አንዳንድ ጊዜ ወደ ኣንዳንድ መሪዎች ይመጣ ነበር (መሳ. 6፡34)። አሁን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሙሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበላሉ። በሐዋ. 2 ላይ እንደምናነበው መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ሲወርድ፥ ይህ የኢዩኤል ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ ተገነዘቡ። ይህም የመጥምቁ ዮሐንስ የተስፋ ቃል ፍጻሜ ነበር።

ሁለተኛው፥ መሢሑ ተከታዮቹን በእሳት «ያጠምቃቸዋል»። አንዳንድ ክርስቲያኖች፥ ይህ በሐዋርያት ሥራ 2 ላይ በደቀ መዛሙርቱ ራሶች ላይ የተቀመጡትን የእሳት ልሳናት እንደሚያመለክት ያስባሉ። ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እሳት ከእግዚአብሔር ጋር ተያይዞ ስለተጠቀሰ (ለምሳሌ፥ ዘጸ. 3፡2-4)፥ እነዚህ ክርስቲያኖች እሳትን የእግዚአብሔር መገኘት ተምሳሌት አድርገው ይወስዱታል። ይሁንና የእሳት ጥምቀት መሢሑ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ በማይፈልጉ ሰዎች ላይ የሚያመጣውን የፍርድ ጥምቀት የሚያመለክት ይመስላል። መጥምቁ ዮሐንስ መሢሑ ንስሓ በማይገቡት ሰዎች ሁሉ ላይ ፍርድን እንደሚያመጣ እያስጠነቀቀ ነበር። ስንዴ ንስሐ ገብተው እግዚአብሔርን ለመታዘዝ የሚወስኑትን ሲያመለከት፥ የሚቃጠለው እንክርዳድ ደግሞ እግዚኣብሔር በሕይወታቸው ላይ እንዳይገዛ የሚያምፁትን ያመለክታል። መጥምቁ ዮሐንስ ይህ የእሳት ጥምቀት እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽኣት ድረስ እንደሚዘገይ አላወቀም ነበር (ራእይ 19፡11-21፤ 20፡7-8)።

የውይይት ጥያቄ፡- የመጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎትና መልእክት ለዛሬው አገልግሎታችን ምሳሌ የሚሆነው በምን መንገድ ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

የንጉሡ የኢየሱስ ልደት (ማቴ. 1፡18-2፡23)

የክርስቶስን ልደት የሚገልጹ ወንጌላት ሁለት ብቻ ናቸው። ከእነዚህ ሁለቱ መካከል፥ ሉቃስ ስለ ክርስቶስ ልደት ሰፊ ምርምር ኣካሂዷል። ሉቃስ የክርስቶስን ልደት ከማርያም እይታ አንጻር ሲመለከት፥ ማቴዎስ ግን ከዮሴፍ እይታ አንጻር ይመለከታል።

የክርስቶስ ልደት የሆነው ዮሴፍና ማርያም ተጫጭተው ባሉበት ወቅት ነበር። እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ፥ የአይሁድ መተጫጨት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ስለ ነበሩ፥ መቋረጥ የሚችሉት በፍች ነበር። በሚተጫጩበት ወቅት ማርያም «በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች» (ማቴ. 1፡18)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እጮኛህ ያረገዝሁት ከሌላ ወንድ ሳይሆን ከመንፈስ ቅዱስ ነው ብትልህ ምን ትላታለህ? ለ) ለዮሴፍ ማርያምን ማመኑ ምን ያህል ከባድ ነበር?

ማርያም ስለሆነው ነገር ለዮሴፍ ገልጻለት ይሆናል። ስለዚህ የተጠቀሰ ነገር የለም። ነገር ግን ዮሴፍ በሆነ መንገድ ደርሶበታል። ነገር ግን ዮሴፍ የዋህ ሰው ስለ ነበር፥ ከሌላ ወንድ ለማርገዟ በይፋ ሊወቅሳት አልፈለገም። ስለሆነም ለእርሷ ሳይነግራት በስውር ሊተዋት አሰበ። እግዚአብሔር ግን ማርያም በትክክል ከመንፈስ ቅዱስ እንደፀነሰች ለዮሴፍ ለመንገር መልአኩን ላከ። ማርያም ከሌላ ሰው ጋር አላመነዘረችም ነበር። ምንም እንኳ ማርያም በማርግዟ ቢቀልዱባትም፥ ዮሴፍ እግዚአብሔርን ታዝዞ ማርያምን ወሰዳት።

እግዚአብሔር በዚህ መሢሑን ወደ ዓለም በመላኩ ሂደት ማርያምን ብቻ ሳይሆን ዮሴፍንም አክብሯል። እንደ ባልና የቤት ራስ ሁሉ፥ እግዚአብሔር ዮሴፍ ለልጁ ስም እንዲያወጣ መብት ሰጠው። ለክርስቶስ ስም በማውጣቱ፥ ዮሴፍ ሕጋዊ ኣባትነቱን እያረጋገጠ ነበር። እግዚአብሔር ዮሴፍ ልጁን «ኢያሱ» (ዕብራዊ ስም) ወይም «ኢየሱስ» (ግሪካዊ ስም) ብሎ እንዲጠራ ነገረው። የሁለቱም ስሞች ፍች «እግዚእብሔር ደኅንነት ነው» የሚል ነው። ይህም የመሢሑ ቀዳሚ ተግባር ድል ነሺ ንጉሥ መሆን ሳይሆን፥ አዳኝ እንደሆነ የሚያመለክት ነው። ክርስቶስ «ሕዝቡን ከኃጢአታቸው የሚያድን» መንፈሳዊ አዳኝ እንጂ ፖለቲካዊ ነፃ አውጪ እንዳልሆነ ማቴዎስ ገልጾአል።

ማቴዎስ፥ የድንግሊቱ መውለድና የክርስቶስ ልደት ዝርዝር ጉዳዮች ሁሉ፥ በእግዚአብሔር በጥንቃቄ እንደታቀዱና በብሉይ ኪዳን እንደተተነበዩ አስረድቷል። ማርያም በሚያስደንቅ መንገድ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ስለ ወለደች፥ ኢየሱስ ሰውም አምላክም ሆኗል። ይህም እርሱ ብቻ «አማኑኤል» ማለትም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆኖኣል (ኢሳ. 7፡14)። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር የክብር ደመናውን በሰዎች መካከል ያኖረ ሲሆን፥ አሁን ግን እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በሰዎች መካከል አድሯል። ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከመመለሱ በፊት፥ ለደቀ መዛሙርቱ አሁንም አማኑኤል እንደሚሆን፥ ማለትም እስከ መጨረሻው አብሯቸው እንደሚሆን ገልጾአል (ማቴ. 28፡1820 አንብብ።) ማቴዎስ ክርስቶስ የብሉይ ኪዳንን ትንቢት በመፈጸም በቤተልሔም እንደ ተወለደ ተናግሯል።

ለአይሁዶች እግዚአብሔር ለአሕዛብም ዕቅድ እንዳለው ማቴዎስ አመልክቷል። እንዲሁም መጀመሪያ ክርስቶስን ያከበሩትና ያመለኩት ሰብዓ ሰገል መሆናቸውን ገልጾአል። ማቴዎስ እነዚህ ሰብዓ ሰገል ከየት እንደ መጡ ወይም ስንት እንደሆኑ አልጠቀሰም። በክርስትና ትውፊት ሦስት ሰዎች እንደሆኑ የሚታመነው ካበረከቱት ስጦታ በመነሣት ነው። ለእነዚህ ሰዎች የተሰጠው የግሪክ ስያሜ «ማጂ» (magi) የሚል ነው። ማጂ የልዩ ሃይማኖታዊ ሰዎች ቡድን ሲሆን፥ ብዙ ምሑራን ከፋርስ ወይም ከሳውዲ ዓረቢያ እንደ መጡ ያምናሉ። እነዚህ ሰዎች በከዋክብት ጥናት ይካኑ እንጂ፥ ስለ እግዚአብሔርም በቂ ግንዛቤ የነበራቸው ይመስላል። ያዩት አዲስ ኮከብ ለአይሁዶች ልዩ ንጉሥ እንደ ተወለደ የሚያመለክት መሆኑን የተረዱ ይመስላል። ለመስገድ መፈለጋቸው ደግሞ ይህ ንጉሥ ከተራ ንጉሥ በላይ መሆኑን እንደ ተገነዘቡ ያሳያል። የአይሁዶች መዲና ወደሆነችው ኢየሩሳሌም እስኪደርሱ ድረስ ለብዙ ወራት ኮከቡን ተከትለው ተጓዙ። ንጉሡ በቤተ መንግሥት ይወለዳል ብለው ስለ ገመቱ፥ ወደ ንጉሥ ሄሮድስ ሄደው ኣዲስ ስለ ተወለደው ንጉሥ ጠየቁ።

ቀደም ሲል ዙፋኔን ይነጥቁብኛል በሚል ስጋት ከቤተሰቡ አባላት መካከል ብዙ ሰዎችን የፈጀው ንጉሥ ሄሮድስ፥ ይህን ሲሰማ ደነገጠ። በመጀመሪያ፥ የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎችን ሰብስቦ ጠየቃቸው። እነዚህ ሰዎች በብሉይ ኪዳን እንደተነገረው መሢሑ ከኢየሩሳሌም ሰባት ኪሎ ሜትር ወጣ ብላ በምትገኘው በቤተልሔም እንደሚወለድ ያውቁ ነበር። ሄሮድስ ያለበትን ስፍራ አይተው እንዲነግሩት በማዘዝ ሰብዓ ሰገልን ወደ ቤተልሔም ላካቸው። ምንም እንኳ ሄሮድስ ሕጻኑን ንጉሥ ለማክበር እንደፈለገ ቢነግራቸውም፥ እውነተኛ ፍላጎቱ ግን ሕጻኑን መግደል ነበር። ኮከቡ እንደገና ለሰብዓ ሰገል ተገልጦ፥ ኢየሱስ ወደነበረበት ወደ ቤተልሔም መራቸው።

ማቴዎስን ከሉቃስ ትረካ ጋር በማነጻጸር እንደምንገነዘበው፥ ኢየሱስ ከተወለደ የተወሰነ ጊዜ አልፎ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ከተወለደበት ግርግም ወደ ቤት ተዛውሮ ነበር። ይህም የዘመድ ቤት ወይም እነዮሴፍ የተከራዩት ቤት ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ ከተወለደ ምን ያህል ጊዜ እንዳለፈ አናውቅም። ሄሮድስ ከሰብዓ ሰገል ኮከቡ መጀመሪያ የታየበትን ጊዜ ተረድቶ እስከ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ሕጻናት ሁሉ ስለ ገደለ፥ ኢየሱስ ከተወለደ ሁለት ዓመታት ሳይሞላው ኣይቀርም ተብሎ ይገመታል። ሰብዓ ሰገል ስጦታዎችን በመስጠትና እንደ አምላክ በማምለክ ክርስቶስን አክብረውታል።

እግዚአብሔርም ለሰብዓ ሰገል ያዩትን ለሄሮድስ ሳይናገሩ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አድርጓል። በዚህ ታሪክ ማቴዎስ እግዚአብሔር የአይሁዶች ብቻ አምላክ እንዳልሆነና አሕዛብም የዕቅዱ አካል መሆናቸውን አመልክቷል። ክርስቶስ መሢሕ እንደሆነ በመጀመሪያ ከተገነዘቡት ሰዎች አንዳንዶቹ አሕዛብ ነበሩ። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ክርስቶስን አንቀበለውም ቢሉም፥ የአሕዛብ ሃይማኖት መሪዎች ግን ሰግደውለታል። ዓለም ስለ እነርሱ ምንም ዐይነት አመለካከት ቢኖረውም ወንጌሉን ብዙውን ጊዜ እናውቃለን ከሚሉት የተሰወረው እውነት ልባቸውን ለከፈቱት ተገልጧል።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ ዓለም የሚንቃቸውን እየመረጠ፥ ታላላቆች ነን ብለው በማሰብ በዕውቀታቸው ወይም በሥልጣናቸው የሚኩራሩትን ሰዎች እንዴት እንደሚንቅ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

ከመሢሑ ታሪክ በስተጀርባ መንፈሳዊ ውጊያ አለ፡፡ ሰይጣን መሢሑን ለማጥፋት ፈልጎ ነበር። ይህንንም ያደረገው በዓለም ላይ ያለውን ኃይሉን እንደሚሽርበት ስለ ተገነዘበ ነበር። እግዚአብሔር ግን ልጁ ዕቅዶቹን ፈጽሞ፥ በመስቀል ላይ እንዲሞት ወስኖ ነበር። ስለዚህ ሰይጣን ኢየሱስን ለመግደል በሄሮድስ ልብ ውስጥ ያሴር እንደነበረ እግዚአብሔር በመገንዘብ፥ ዮሴፍ በመጀመሪያ ወደ ግብፅ ይዞት እንዲወርድ ከዚያም ወደ ናዝሬት ይዞት እንዲመለስ አዘዘው። ከዚያም ሄሮድስ ወደ ቤተልሔም ተጉዞ እስከ ሁለት ዓመት ዕድሜ የሆናቸውን ሕጻናት ሁሉ አስገደለ። ይህም ሰብዓ ሰገል ኢየሱስን ለማየት የመጡት ቢያንስ ከኣንድ ዓመት ተኩል እስከ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ ሳይሆን አይቀርም ወደሚል ድምዳሚ ይመራናል።

በክርስቶስ ልደት ዙሪያ በተከናወኑት በእነዚህ ክስተቶች ሁሉ፥ የእግዚአብሔር እጅ እንደ ነበረበት ማቴዎስ ያውቅ ነበር። የሕጻናቱ መገደል፥ የክርስቶስ ከግብፅና በኋላም ከናዝሬት መምጣት፥ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ተተንብዮአል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከእነዚህ ታሪኮች፥ የታሪክ ጌታ ስለሆነው ልዑል አምላክ ምን መማር እንችላለን? ለ) እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ነገሮችን ሁሉ መቆጣጠሩ እንዴት ሊያበረታታን ይገባል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

የዳዊት ልጅ፥ የክርስቶስ የዘር ሐረግ (ማቴ. 1፡1-17)

የቅድመ አያቶችህን ስም ወደ ኋላ ተመልሰህ ምን ያህል ልትቆጥር ትችላለህ? አምስት ወይስ? ሰባት ትውልዶች? በኢትዮጵያ ብዙ ሰዎች የዘር ግንዳቸውን ቢያንስ እስከ ሰባት የዘር ሐረግ ይቆጥራሉ። ለኢትዮጵያውያን የዘር ሐረግ መቁጠር አስፈላጊ ቢሆንም፥ ለአይሁዶች ግን ከዚያ የበለጠ አስፈላጊ ነበር። አንድ አይሁዳዊ የዘር ሐረጉን የአይሁዶች ኣባት እስከሆነው አብርሃም ድረስ መቁጠር መቻል አለበት። በተለይም አንድ አይሁዳዊ የተስፋ ቃል የተገባለትን ነቢይ ያህል ታላቅ ሥልጣን ለመያዝ ከፈለገ፥ ይህንን ማድረጉ ወሳኝ ነው። በብሉይ ኪዳን በተለይም አስፈላጊ ግለሰቦችና የቤተሰብ መስመሮች በሚመሠረቱበት ጊዜ፥ የዘር ሐረጎችን በተደጋጋሚ እናገኛለን። በዘፍጥረት መጽሐፍ፥ ከአዳም እስከ ኖኅ ልጆች ድረስ የአይሁዶች የዘር ሐረግ በጥንቃቄ ተዘርዝሯል (ዘፍጥ. 5)። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ የሊቀ ካህናቱ የአሮን የዘር ሐረግ ተዘርዝሯል (ዘኁል. 3፡1-4)። በኋላም፥ የንጉሥ ዳዊት የዘር ሐረግ ተገልጾአል (ሩት 4፡13-2)።

ስለሆነም ማቴዎስ ክርስቶስ እውነተኛ አይሁዳዊ ብቻ ሳይሆን፥ የንጉሥ ዳዊት ሕጋዊ የዘር ሐረግ መሆኑንም ጭምር በመግለጽ ወንጌሉን ይጀምራል። ይህም ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን ትንቢት የተነገረለት መሢሕ ለመሆን ከሚያስፈልጉ ዐበይት መመዘኛዎች አንዱን እንዳሟላ ያሳያል። እርሱ የዳዊት የዘር ሐረግ የሆነ አይሁዳዊ ነበር። ከዚህ የዘር ሐረግ የሚከተሉትን ነጥቦች ልንመለከት እንችላለን።

1. ማቴዎስ የዘር ሐረጉን የጀመረው የአይሁዶች አባት ከሆነው ከአብርሃም ነው። ይህም ክርስቶስ ንጹሕ አይሁዳዊ እንደሆነ ያሳያል። ሉቃስ ፍጹም ሰው በሆነው ክርስቶስ ላይ በማተኮር፥ የዘር ሐረጉን ከአዳም ይጀምራል።

2. በመጀመሪያው ወንጌል ውስጥ የቀረቡት የዘር ሐረጎች በሦስት የ14 ትውልዶች ተመድበው ተከፍለዋል። ከንጉሥ ዳዊት በፊት 14 የዘር ሐረጎች ሲዘረዘሩ፥ ከዳዊት እስከ ባቢሎን ምርኮ 14፥ እንዲሁም ከምርኮው እስከ ክርስቶስ ድረስ 14 ትውልዶች ተዘርዝረዋል (ማቴ. 1፡17 አንብብ)። ማቴዎስ በመሢሕነቱ ላይ በማተኮር፥ ኢየሱስን ለማመልከት «ክርስቶስ» የሚለውን ስም ብቻ ይጠቀማል።)

3. «አባት» የሚለው ቃል ወሳኝ ባልሆነ መንገድ ገብቶአል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ቃሉ «የዘር ሐረግ» የሚል ፍች ነበረው። ምክንያቱም ማቴዎስ በዝርዝሩ ውስጥ አያሌ ትውልዶችን ዘሏል። ለምሳሌ፥ ማቴዎስ ኢዮራም ዖዝያን እንደ ወለደ ገልጾአል። በ2ኛ ዜና 21፡4-26፡23 ግን ከኢዮራም በኋላ ኣሃዚያ፥ ኢዮአስ፥ አሜስያስና ዖዝያን እንደሚመጡ እንመለከታለን።)

4. ማቴዎስ በዳዊት የዘር ሐረግ ውስጥ የገቡትን አራት የተለዩ ሴቶች ዘርዝሯል። የመጀመሪያዋ ይሁዳን የወለደችው ትዕማር የምትባል ከነዓናዊት ናት። ሁለተኛይቱ በኢያሪኮ ከተማ ውስጥ ሰላዮችን የሸሸገችው ረዓብ ናት። ሦስተኛዋ ቦዔዝን አግብታ የንጉሡ ዳዊት አያት ለመሆን የቻለችው ሞዓባዊቷ ሩት ናት። የመጨረሻዋ፥ ዳዊት ዝሙት የፈጸመባት የኦሪዮን ሚስት ናት። ማቴዎስ እነዚህን አራት ሴቶች ብቻ የጠቀሰው ለምንድን ነው? ማቴዎስ የእግዚአብሔር በረከት በጸጋ እንጂ፥ አንድ ሰው የትክክለኛ ቤተሰብ አባል ስለሆነ ብቻ የሚያገኘው ነገር እንዳልሆነ ለማመልከት ፈልጎ ይሆን? ምናልባትም ደግሞ ይህ እግዚአብሔር አሕዛብን ወደ ቤተሰቡ ለመቀላቀል ፈቃደኛ መሆኑን የሚያመለክት ይሆናል፡፡ ማቴዎስ ከሚያስተምረን ነገሮች አንዱ፥ እግዚአብሔር ለአሕዛብም ለአይሁዶችም እኩል ዕቅድ እንዳለው ነው።

5. የማቴዎስ የዘር ሐረግ የዮሴፍን አቅጣጫ ሲከተል፥ የሉቃስ ግን የማርያምን ይከተላል። ማቴዎስ ክርስቶስ ከዮሴፍ ጋር የነበረውን ግንኙነት የገለጸው በጥንቃቄ ነበር። ዮሴፍ የማርያም ባል ነበር። ነገር ግን የክርስቶስ አባት አልነበረም። ምንም እንኳ በሚገባ የማያውቁት ሰዎች እባቱ እንደሆነ ቢያስቡም። ዮሴፍ የክርስቶስ ሕጋዊ አባት እንጂ ሥጋዊ አባቱ አልነበረም። በአይሁድ ባህል፣ ሕጋዊ መብቶች የሚተላለፉት በወንዱ እንጂ በሴቷ የዘር ሐረግ አልነበረም። ይህ ግለሰቡ ሥጋዊ አባት ባይሆንም እውነት ነበር። ስለሆነም በሕጋዊ ገጽታው ዳዊታዊ መብቶች ወደ ክርስቶስ የሚተላለፉት በዮሴፍ እንጂ በማርያም በኩል አልነበረም። እንግዲህ ክርስቶስ የዮሴፍ ሕጋዊ ልጁ ባይሆን ወይም ዮሴፍ የዳዊት የዘር ሐረግ ባይሆን ኖሮ፥ እንደ ዳዊት ልጅ ወደ ዳዊት ዙፋን ለመውጣት መብት ኣይኖረውም፤ ደግሞም መሢሕ ለመሆን አይችልም ነበር። ማርያም ከዳዊት ወገን መሆኗ ብቻ በቂ ኣልነበረም።

6. የማቴዎስ ወንጌል የዳዊትን የዘር ሐረግ በሰሎሞንና በገዥ ነገሥታት በኩል ይዘረዝራል። ሉቃስ የዳዊትን የዘር ሐረግ የተከተለው ካልነገሡት የዳዊት ልጆች አንዱ በሆነው በናታን በኩል ነበር። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አንዳንድ ምሑራን ክርስቶስ ሁሉም የመሢሕነቱን መመዘኛዎች እንዳሟላ የሚያስረዱ በመሆናቸው፥ ሁለቱም የዘር ሐረጎች አስፈላጊዎች መሆናቸውን ይናገራሉ። በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር የኢዮአቄም ዘሮች በእስራኤል ላይ እንዳይነግሡ ረግሟቸው ነበር (ኤር. 22፡24-30)። ማቴዎስ የክርስቶስን የዘር ሐረግ በኢዮአቄም በኩል ዘርዝሯል (ኢኮንያን ማቴ. 1፡11)። ስለሆነም፥ ምንም እንኳ ክርስቶስ ከኢዮአቄም የሚወስደው ሕጋዊ የመግዛት መብት ቢኖረውም፥ የእግዚአብሔር ርግማን የኢዮአቄም ቀጥተኛ ትውልዶች በመሢሕነት እንዳይገዙ ይክለክል ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ ከኢዮአቄም የተቀበለው ሕጋዊ የመግዛት መብትን ብቻ ሲሆን፥ የኢዮአቄም ቀጥተኛ ትውልድ አልነበረም። ከድንግል በመወለዱ ምክንያት ክርስቶስ ከናታን ትውልድ ወገን ነበር። ይህም ክርስቶስ በእርግማኑ ሥር ሳይደመር በመሢሕነት የማገልገል መብት አግኝቷል።

1ኛ የውይይት ጥያቄ፡– ይህ እግዚአብሔር ለዳዊት ልጅ ለመሢሑ የወጠናቸው ዕቅዶች በሙሉ መሟላታቸውን እንዴት ያሳየናል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

ወንጌላትን እንዴት መረዳትና መተርጎም ይቻላል?

የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ዐይነቶች በተለያዩ መንገዶች ይተረጎማሉ። ለምሳሌ፥ ተምሳሌታዊ ቋንቋን የሚከተል ግጥም በተራ ቃላት ከሚጻፍ ደብዳቤ ጋር ተመሳሳይ አይደለም። ከአንድ ጓደኛችን ደብዳቤ ቢደርሰን «ሰምና ወርቁን» መለየት ሳያስፈልገን ከጓደኛችን ጋር አፍ ለአፍ እንደምንነጋገር ሁሉ በቀላሉ ልናነበው እንችላለን። ቅኔን እንደ ደብዳቤ ካነበብን ጥልቅ ምሥጢሩን እናጣዋለን። ስለሆነም የመጽሐፉን መልእክት በቅጡ ለመረዳት፥ የጽሑፉን ዐይነት ለይቶ ማወቅና የዚያን ዐይነት ሥነ ጽሑፍ ለመረዳት የሚቻልበትን መንገድ መገንዘብ ይኖርብናል።

የመጽሐፍ ቅዱስም ሁኔታ እንደዚሁ ነው። ምንም እንኳ መንፈስ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሕተቶች እንዳይከሰቱ ቢቆጣጠርም፥ ጸሐፊዎቹ የእግዚአብሔርን ቃል ለመግለጽ የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ስልቶችን እንዲጠቀሙ ፈቅዶላቸዋል። ጳውሎስ የጻፋቸው መልእክቶች ደብዳቤዎች ናቸው። ምሑራን የሐዋርያው ዮሐንስን ራእይ «አቡቀለምሲሳዊ ሥነ ጽሑፍ» ብለው ይጠሩታል። በኋላ ስለዚህ ዐይነቱ ሥነ ጽሑፍ በሰፊው እናጠናለን።

ለመሆኑ አራቱ ወንጌላት ምን ዐይነት ሥነ ጽሑፍ ናቸው። ምናልባት ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሆነው አራቱ ወንጌላት ትምህርተ ታሪክ ናቸው የሚለው ይሆናል። ወንጌላትን በምናጠናበት ጊዜ ልናጤናቸው የሚገቡ ሁለት ነገሮች አሉ።

በመጀመሪያ፥ ወንጌላት ታሪክ መሆናቸውን ማስታወስ ኣለብን። ማቴዎስ፥ ማርቆስ፥ ሉቃስና ዮሐንስ ታሪክን አልጀመሩም፤ እውነተኛ ታሪካዊ ሁኔታዎችን ነው የዘገቡት። ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ ያለ ሥራ አልኖረም። ተአምራትን ሠራ። በወንጌላቱ ውስጥ የተጠቀሱትን ነገሮች አስተማረ። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በተአምራት የማያምኑ ምሁራን፥ ኣራቱ ወንጌላት ልብ ወለድ ፈጠራዎች እንደሆኑ ይናገራሉ። ነገር ግን እኛ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነና በውስጡም የሚገኘው አሳብ ሁሉ እውነት መሆኑን የማይቀበል ኣሳብ ማስተናገድ የለብንም።

1ኛ የውይይት ጥያቄ፡- አራቱ ወንጌላት እውነተኛ ታሪኮች መሆናቸውን አጥብቆ ማመን ለምን ያስፈልጋል?

ሁለተኛው፥ ጸሐፊዎቹ ሰዎችን በታሪኮች አማካይነት ለማስተማር እየሞከሩ ነበር። በሌላ አነጋገር፥ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከምናጠናቸው የታሪክ መጻሕፍት በተቃራኒ፥ የተመረጡት ታሪኮችና የቀረቡበት ሁኔታ ያዘጋጀው ሰዎች እንዴት ከክርስቶስ ጋር እንደሚቀራረቡ ለማስተማር ነበር። በአጠቃላይ የወንጌል ጸሐፊዎች ሁለት ነገሮችን ለማከናወኑ ይፈልጉ ነበር።

ሀ) ወንጌላት የክርስቶስን ማንነት ለማብራራት ሞክረዋል። ክርስቶስ ተራ የታሪክ ተዋናይ ሳይሆን፥ ለዓለም ኃጢአት የሞተ አምላክ ነው። እርሱ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የተለየ ነበር። እርሱ ለሰው ኃጢኣት በመሠዋቱ፥ የወንጌሉ ጸሐፊዎች የሆኑ ሰዎች ክርስቶስን ማወቅና ማመን እንዳለባቸው ተገንዝበው ነበር።

ለ) የመጀመሪያዎቹ አራት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት፥ ለክርስቲያኖች የክርስቶስ ተከታይ መሆን ማለት ምን እንደሆነ ያስተምራሉ። ክርስቶስ ሞቶ ተነሥቷል። ስለሆነም አሁን ሕያው ነው። በአምላክነቱ ተሰግዶለታል። ክርስቶስ እንደተናገረው፥ እርሱ ለዘላለም ከእኛ ጋር ነው። ስለሆነም የክርስቶስ ተከታይ ነኝ ማለት እርሱ በሥጋ የተገለጠና ለኃጢአታችን የሞተ አምላክ መሆኑን መቀበል ነው። በተጨማሪም ከእርሱ ጋር ግንኙነት መመሥረት ማለት ነው። ለማቴዎስና ለሌሎች ደቀ መዛሙርት እንደታየው ለእኛ አሁን በአካል ላይታየን ይችላል። ይሁንና እርሱ አሁንም አዳኛችንና ወዳጃችን ሆኖ አብሮን ይኖራል። የክርስቶስ ተከታይ ማለት ያስተማረንን በሥራ ላይ ለማዋል መወሰን ማለት ነው። የክርስቶስ ተከታይ የሆነ ሰው የእርሱን ዐይነት ባሕርይና ተግባር ሊያሳይና ስለ ክርስቶስ ለሌሎች ሊመሰክር ይገባዋል።

2ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከላይ በ«ሀ» እና በ«ለ» ሥር የቀረቡት እሳቦች ለክርስቲያኖች ጠቃሚ የሚሆኑት ለምንድን ነው? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ እነዚህን እውነቶች ለምእመኖቿ፥ በተለይም ለአዳዲስ ክርስቲያኖች የምታስተምረው እንዴት ነው?

3ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 1-2 ኣንብብ። ሀ) ማቴዎስ የክርስቶስ የዘር ሐረግ በመዘርዘር ለማስተላለፍ የፈለገው ትምህርት ምንድን ነው? ለ) በክርስቶስ ሕይወት ውስጥ ለማቴዎስ አስፈላጊ ዓመታት የትኞቹ ነበሩ? ሐ) በማቴ. 1፡1-17 የተጠቀሰውን የክርስቶስ የትውልድ ሐረግ በሉቃስ 3፡23-38 ከቀረበው ገለጻ ጋር በማነጻጸር ልዩነቱን አስረዳ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

የማቴዎስ ወንጌል መዋቅር እና አስተዋጽኦ

መጽሐፍ ቅዱስን የመጻፉ ተግባር እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስና ሰዎች በጋራ ያከናወኑት መሆኑን ቀደም ብለን ተመልክተናል። መንፈስ ቅዱስ ቃል በቃል እየተናገረ አላጻፋቸውም። ነገር ግን ደራሲያኑ ቃላት እየመረጡ መንፈስ ቅዱስ በልባቸው ውስጥ ያስቀመጠውን ዐላማ ለማሳካት እንዲጽፉ መርቷቸዋል። እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ደራስያኑ መጽሐፎቻቸውን በልዩ መንገድ እንዲያደረጁ ፈቅዷል። ይህም ሆኖ መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ ስልቶችን እየተጠቀሙ፥ በሁሉም ዘመን የሚኖሩ ሰዎች እንደ እግዚአብሔር ቃል የሚጠቀሙባቸውን እውነቶች እንዲያስተላልፉ ተቆጣጥሯቸዋል።

ማቴዎስ ቁጭ ብሎ ስለ ክርስቶስ የቻለውን ያህል ታሪክ ለመጻፍ አልሞከረም። ነገር ግን ክርስቲያኖችና ክርስቲያን ያልሆኑ ወገኖች ሊያውቋቸው የሚገቧቸውን ታሪኮች በጥንቃቄ መርጧል። እነዚህን ታሪኮች ያዋቀረው ደግሞ በጊዜ ቅደም ተከተላቸው ሳይሆን፥ በተለየ መንገድ ነበር። ብዙ ምሑራን ማቴዎስ አይሁዶች እጅግ የተቀደሱ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች አድርገው የሚመለከቷቸውን የሙሴን መጻሕፍት ተከትሎ፥ መጽሐፉን በአምስት ክፍሎች እንዳደራጀ ያምናሉ። ማቴዎስ በአምስት የተለያዩ የማስተማሪያ ክፍሎች፥ ላይ አተኩሯል (ማቴ. 5-7፥ 10፥13፥ 18፥ 24-25)። እነዚህ አምስት የትምህርት ክፍሎች «ክርስቶስ ይህን በፈጸመ ጊዜ» በሚሉ ቃላት ይጠቃለላሉ (ማቴ. 7፡28፤ 11፡1፤ 13፡53፣ 19፡1፤ 26፡)። የክርስቶስ ታሪኮች የተደራጁት የክርስቶስን ትምህርት ለማስተዋወቅ ነው።

የማቴዎስን ወንጌል አስተዋጽኦ ማዘጋጀት የሚቻልባቸው የተለያዩ መንገዶች ሲኖሩ፥ ከእነዚህ መካከል አንዱ ክርስቶስ ያገለገለባቸውን አገሮች መከተል ነው።

 1. የክርስቶስ መወለድና ለአገልግሎት መዘጋጀት (ማቴ. 1፡1-4፡16)
 2. የክርስቶስ አገልግሎት በገሊላ (ማቴ. 4፡17-14፡12)
 3. የክርስቶስ አገልግሎት ከገሊላ ውጭ (ማቴ. 14፡13-17፡20)
 4. የክርስቶስ የመጨረሻ አገልግሎት በገሊላ (ማቴ. 17፡21-18፡35)
 5. የክርስቶስ አገልግሎት በይሁዳና ጴሪያ (ማቴ. 19-20)
 6. ክርስቶስ ከመሰቀሉ በፊት የፈጸመው የመጨረሻው ሳምንት አገልግሎት (ማቴ. 21-27)
 7. የክርስቶስ ትንሣኤ (ማቴ. 28)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

የማቴዎስ ወንጌል ዐላማ

ከሉቃስና ከዮሐንስ በተቃራኒ፥ ማቴዎስ ወንጌሉን ለምን እንደ ጻፈው ምክንያቱን አይገልጽም (ሉቃስ 1፡1-4፤ ዮሐ 20፡30-3)። ስለሆነም የማቴዎስን ዓላማ የምንረዳው ወንጌሉን በመገንዘብ ነው። ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈባቸው ብዙ ምክንያቶች እንደሚኖሩ ባይጠራጠርም፤ ጥቂቶቹን እንደሚከተለው ዘርዝረናል።

1 ማቴዎስ ክርስቶስ ለዓለም በተለይም ለአይሁዶች የእግዚአብሔር ዐላማ ፍጻሜ እንደሆነ ያሳያል።

1ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 1፡2-232፡5፥ 17-18 4፡14-16፤ 27፡9-10 አንብብ። ሀ) እነዚህ ሁሉ ክርስቶስ የፈጸማቸው የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ምን ያሳያሉ፤ ለ) ለአይሁዶች እነዚህን ሁሉ እውነቶች ማመን አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ማቴ. 1፡1 9፡27 22፡41-45 አንብብ። እነዚህ ምንባቦች በየትኛው የክርስቶስ የሕይወት ገጽታ ላይ ያተኩራሉ?

ማቴዎስ ሕዝቡ ለሆኑት አይሁዶች በጣም ያስብ ነበር። አይሁዶች የብሉይን ኪዳን ሕዝብና የእግዚአብሔር ምርጦች ነበሩ። ነገር ግን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ቢኖሯቸውም እንኳ፥ ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን ለአይሁዶች የሰጣቸው ትንቢቶች ፍጻሜ መሆኑን ለመረዳት ተቸግረው ነበር። ስለሆነም ሲጠብቁት የነበረው መሢሕ መሆኑን አይሁዶችን ለማሳመን ሲል ወንጌሉን ጻፈ። ማቴዎስ ይህንን ያደረገው እንዴት ነበር?

ሀ. ከየትኛውም ወንጌል በላይ ማቴዎስ ክርስቶስ እንዴት ብሉይ ኪዳን ስለ መሢሑ የተነበየውን ቃል እንደ ፈጸመ ያሳያል። ማቴዎስ ከብሉይ ኪዳን ቢያንስ 60 ጥቅሶችን ወስዷል። እያንዳንዱ የክርስቶስ ሕይወት የጥንቱን ትንቢት እንዴት እንደ ፈጸመ ያሳያል። ክርስቶስ በቤተልሔም መወለዱ፥ ወደ ግብፅ መሸሹ፥ በገሊላና በናዝሬት ማደጉ፥ በምሳሌ ማስተማሩ ሁሉ በብሉይ ኪዳን ተተንብዮ ነበር። ማቴዎስ እያንዳንዱ የክርስቶስ ሕይወት ክፍል እግዚአብሔር ትንቢትን ለማሟላት በተጠቀመበት መንገድ እንደ ተጓዘ አብራርቷል።

ለ. ኢየሱስ «የዳዊት ልጅ» በመሆኑ፥ መሢሕ ለመሆን ይችላል። ማቴዎስ የክርስቶስ የዘር ሐረግ ከዳዊት መምጣቱን አሳይቷል። ማቴዎስ ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ብቻ ሳይሆን በሕጋዊ የንግሥና የዘር ሐረግ የዳዊት ልጅ መሆኑን ለማመልከት፥ የዮሴፍ ሕጋዊ ልጅ የሆነው ክርስቶስ የአይሁዶች ንጉሥ ማለትም መሢሕ ለመሆን የሚያበቁትን መመዘኛዎች ሁሉ እንዴት እንዳሟላ አሳይቷል።

ሐ. ማቴዎስ ክርስቶስ ምን ዐይነት መንግሥትን እንደ ሰበከ በወንጌሉ ገልጾአል። አይሁዶች ምድራዊና ፖለቲካዊ መንግሥት ይፈልጉ ነበር። እንዲያውም ማቴዎስ ወንጌሉን በሚጽፍበት ጊዜ አይሁዶች በሮም መንግሥት ላይ ትግል ማካሄድ ጀምረው ነበር። እንደ መቃብያን፥ ዳዊትና ሰለሞን ዘመን የራሳቸውን አገር የሚቆጣጠሩበትን ፖለቲካዊ ነጻነት ይሹ ነበር። አይሁዶች በክርስቶስ ለማመን ከተቸገሩበት ምክንያት አንዱ፥ ከብሉይ ኪዳን ትንቢቶች የተረዱትን የፖለቲካዊ ነፃ አውጪነትን ተግባር አለማከናወኑ ነበር። ሮማውያን በቀላሉ ይዘው የሰቀሉት ሰው እንዴት መሢሕ እንደሚሆን ሊከሰትላቸው አልቻለም።

2ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 5፡3፥ 10፥ 19፥ 20፣ 1፡11-12፤ 13፡1-52፣ 18፡1-4፤ 19፡14-30፣ 25፡1-46 እንብብ። ማቴዎስ ያተኮረባቸው የመንግሥተ ሰማይ ባሕርያት ምንድን ናቸው?

ማቴዎስ ክርስቶስ ፖለቲካዊ ሳይሆን መንፈሳዊ መንግሥት ማምጣቱን ለማመልከት ሲል፥ ለክርስቶስ መንግሥት «የሰማይ መንግሥት» የሚል ስያሜ ሰጥቷል። ማቴዎስ «የሰማይ መንግሥት» በማለቱ፥ ክርስቶስ በአይሁዶች ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔርን አገዛዝ የሚያሳይ መንግሥት እንደሚመሠርት እያመለከተ ነበር። የእርሱ መንግሥት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በመከተሉ ላይ ያተኩር ነበር። ይህም በኣንድ ሰው ልብ ውስጥ የሚቀመጥና ባሕርዩን የሚለውጥ መንግሥት ነበር (ማቴ. 5-7። በዚህ ታሪካዊ ወቅት እግዚአብሔር ክርስቶስ ይህንን መንፈሳዊ መንግሥት እንዲጀምር ልኮታል። ነገር ግን ክርስቶስ በሙሉ ክብሩ ተመልሶ የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎች ሁሉ የሚፈጸሙበትን ምድራዊ መንግሥት ይመሠርታል። ወደዚያ መንግሥት የሚገቡት ግን፥ ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ መንግሥት ሕይወታቸውን የሚያስገዙ አይሁዶች ወይም ኣሕዛብ ብቻ ይሆናሉ።

3ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ክርስቶስ በግል ሕይወታችንና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ባለው መንፈሳዊ አገዛዝ እንድናተኩር የሚፈልገው እንዴት ነው? ለ) ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በሕይወታቸው ውስጥ እንዲገዛ ከፈቀዱ፥ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ለውጦችን ገልጾአል። ማቴዎስ 5፡1-16 አንብብ። ከእነዚህ ለውጦች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? በሕይወትህ ውስጥ እነዚህን ለውጦች በመፈጸም ንጉሡ ክርስቶስን እንዴት ልታከብር እንደምትሻ ግለጽ።

 1. የማቴዎስ ወንጌል የሚጀምረው «የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ» በማለት ነው (ማቴ. 1፡1)። ይህም ማቴዎስ ወንጌሉ የዳዊት ልጅና ትክክለኛ የእስራኤል ንጉሥ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደሚያተኩር ያሳያል። ክርስቶስ ስለ መሢሑ የተነገሩት ትንቢቶች ሁሉ ፍጻሜ ነው። እነዚህም የዳዊት ልጅ በእስራኤልና በዓለም ሁሉ እንደሚነግሥ የሚያመለክቱ ትንቢቶች ነበሩ (ለምሳሌ፥ ኢሳ 11፡1-16)። በተጨማሪም ማቴዎስ ክርስቶስ የአብርሃም ልጅ መሆኑን ገልጾአል። ይህም ክርስቶስ አይሁዳዊ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፥ የአብርሃም ቃል ኪዳን ፍጻሜ መሆኑንም ያስረዳል።

4ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ዘፍጥ. 12፡1-3 አንብብ። ሀ) እግዚእብሔር ከአብርሃም ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ምንድን ነው? ለ) ክርስቶስ የአብርሃምን ቃል ኪዳን የፈጸመው እንዴት ነው?

በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ለአብርሃም ብዙ የተስፋ ቃሎችን ሰጥቶታል። አብዛኞቹ የተስፋ ቃሎች ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የተያያዙ ናቸው። ስለሆነም ማቴዎስ ክርስቶስ ፍጹም እስራኤላዊና እግዚአብሔር ለአይሁዶች የሰጣቸውን ተስፋዎች ሁሉ የሚፈጽም መሆኑን ያሳያል (ገላ. 3፡16 አንብብ።) በተጨማሪም እግዚአብሔር ለአብርሃም በእርሱ አማካይነት የዓለም ሕዝቦች ሁሉ እንደሚባረኩ ተናግሯል። ይህ የተስፋ ቃል የተፈጸመበት ዋንኛው መንገድ የአብርሃም ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ነበር። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞቱ ለሰዎች ሁሉ ይቅርታን አስገኝቶላቸዋል። በክርስቶስ በማመን ሰዎች ሁሉ የአብርሃም መንፈሳዊ ልጆች ይሆናሉ (ገላ. 3፡7-9)። ጳውሎስ እንዳለው፥ እነዚህ ወደ እግዚአብሔር ቤተሰብ ተቀላቅለዋል (ሮሜ 11፡11-24)።

 1. ማቴዎስ አዳዲስ ክርስቲያኖችን ለማስተማር በማሰብ ወንጌሉን እንደ ጻፈ የሚያስቡ ምሑራን አሉ። ብዙዎች በክርስቶስ ቢያምኑም (ሮሜ 10፡9-10)፥ ስለ ክርስቶስ የሚያውቁት ብዙ ነገር አልነበራቸውም። ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያት በአካል እየተገኙ በሚያስተምሩበት ስፍራ ብቻ ሳይሆን፥ በሌሎችም አካባቢዎች ተስፋፍታ ነበር፤ እነርሱም ስለ ክርስቶስ መሢሕነት ለእያንዳንዱ አማኝ ያስተምሩ ነበር። ይሁን እንጂ ሐዋርያትና ክርስቶስን በአካል የሚያውቁት የነበሩ ሰዎች እያረጁ በመሄድ ላይ ይገኙ ነበር። ሌሎቹም ተሠውተው ነበር። ስለዚህም ማቴዎስ የክርስቶስን ታሪክ ለመጻፍ ፈለገ። ማቴዎስ አዳዲስ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ማንነትና በመስቀል ላይ በመሞት ስላከናወነው ተግባር ግልጽ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ፈለገ። ማቴዎስ «በክርስቶስ አምናለሁ» የሚለው አጠቃላይ አሳብ ብቻ ለክርስቲያኖች በቂ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። ስለ ክርስቶስ ማንነት፥ ምን እንዳደረገ፥ ስለ ሞቱና ትንሣኤው፥ እንዲሁም እከተልሃለሁ ከሚሉት ሰዎች ምን እንደሚፈልግ ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር። ማቴዎስ ክርስቶስ ተከታዮች ስለመሆን ያስተማረውን ዘግቧል። አጠቃላይ የሕይወት ለውጥ ያስፈልግ ነበር። ከእንግዲህ በውጫዊ ደንቦችና ሕጎች ላይ ሳይሆን፥ በውስጣዊ ባሕርይና አመለካከት ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል (ማቴ. 5-7)። አይሁዶች ከሌሎች ጎላዎች እንደሚበልጡ በማሰብ በብሔራዊ ውርሳቸው መኩራራት እንደሌለባቸውና የአሕዛብና የአይሁዶች ንጉሥ የሆነውን ክርስቶስን መከተል እንዳለባቸው ገልጾአል። እውነትም ወንጌሉና የእግዚአብሔር በረከት ለሰዎች ሁሉ የተሰጠ እንጂ ለአንድ ጎሳ ብቻ አልነበረም።

5ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለኣዳዲስ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ባሕርይ ግልጽ ግንዛቤ መጨበጡ ለምን የሚያስፈልግ ይመስልሃል? ለ) ለአዳዲስ ክርስቲያኖች ክርስቶስ ከተከታዮቹ ሕይወት ለማየት ስለሚፈልጋቸው ነገሮች ግልጽ ግንዛቤ ማግኘቱ ለምን ያስፈልጋል? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሳድጉ የምታደርግባቸውን መንገዶች አብራራ። መ) ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ክርስቶስን የበለጠ እንዲያውቁ ለማገዝ ልታደርጋቸው የሚገባቸው ተጨማሪ ነገሮች ምንድን ናቸው?

 1. የማቴዎስ ወንጌል እግዚአብሔር ለአሕዛብ ልዩ ዕቅድ እንዳለው ያሳያል። በማቴዎስ ዘመን የነበሩት አብዛኞቹ አይሁዶች አሕዛብን ስለሚጠሉ፥ እግዚአብሔርም አሕዛብን እንደሚጠላ ያስቡ ነበር። አንዳንድ አይሁዶች እግዚአብሔር አሕዛብን የፈጠረው መልሶ ሊያጠፋቸው እንደሆነ ያስተምሩ ነበር። ማቴዎስ ግን በመጽሐፉ ውስጥ ለአሕዛብ ልዩ ትኩረት ይሰጣል። ክርስቶስ የኣይሁድ ንጉሥ መሆኑን መጀመሪያ ጊዜ የተገነዘቡት ከኣሕዛብ ወገን የሆኑት ሰብዓ ሰገል ነበሩ (ማቴ. 2)። ንጉሥ ሄሮድስ ኢየሱስን ሊገድለው በፈለገ ጊዜ በቤቷ የተቀበለችው አሕዛባዊቷ ምድር ግብፅ ነበረች (ማቴ. 2፡13-15)። ከአሕዛብ ወገን የነበረው የመቶ አለቃ በብዙ አይሁዶች መካከል ያልነበረውን የእምነት ምሳሌነት አሳይቷል (ማቴ. 8፡10)። ክርስቶስ አሕዛብ ከእግዚአብሔር ቤተሰብ ጋር ስለሚቀላቀሉበት ጊዜ ተንብዮአል (ማቴ. 8፡11-12)። በመጨረሻም፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ወንጌሉን ለተለያዩ የኣሕዛብ አገሮች እንዲያደርሱ እዝዟቸዋል (ማቴ. 28፡1920)።
 1. የመጀመሪያው ወንጌል ክርስቶስ ሰው ብቻ ሳይሆን፥ በነገሮች ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው አምላክም እንደሆነ ያሳያል። ማቴዎስ ክርስቶስ በበሽታ (ማቴ. 9፡22፤ 14፡35-36)፥ በተፈጥሮ (ማቴ. 8፡23-27)፤ በኃጢአት (ማቴ. 9፡2)፥ በክፉ መናፍስት (ማቴ. 8፡31-32)፥ በሰዎች ዘላለማዊ ሕይወት ዕጣ ፈንታ (ማቴ. 7፡21-23፤ 24፡29-31)፥ እንዲሁም በራሱ ሕይወት ላይ (ማቴ. 16፡21፣ 20፡7-19) ሥልጣን እንዳለው አሳይቷል። ክርስቶስ ኃያል በመሆኑ፥ ሰዎች አምልከውታል (ማቴ. 8፡2፤ 14፡33)። ኢየሱስ አምላክ በመሆኑ ለሰዎች የራቀና ስለ ሰዎችም ግድ የሌለው ኣምላክ አልነበረም። ሁልጊዜ ለሰዎች ይራራ ነበር (ማቴ. 9፡36፤ 14፡14)። ሰዎች የሚፈልጉትን ዘላለማዊና መንፈሳዊ ዕረፍት የሚያገኙት በእርሱ ነው (ማቴ. 11፡28-30)።
 1. ማቴዎስ፥ አይሁዶች በክርስቶስ መሢሕነት ላይ ለሚያነሡዋቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንደፈለገ የሚገልጹ ምሑራን አሉ። ለምሳሌ፥ ኣይሁዶች ክርስቶስ የዮሴፍ (የሥጋ ተፈጥሯዊ) ልጅ እንዳልሆነ ያውቁ ነበር። ኢየሱስ ዲቃላ ነው ብለው ያስቡ ስለነበር (ዮሐ 8፡4)፤ ማቴዎስ ስለ ልደቱ በጥንቃቄ ያብራራል። ሌሎች ኢየሱስ በቤተልሔም እንዳልተወለደና ብሉይ ኪዳን ስለ መሢሑ የተነበየውን አሳብ እንደማያሟላ ይናገሩ ነበር። ማቴዎስ፥ ኢየሱስ በቤተልሔም እንደ ተወለደና የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎችን እንደ ፈጸመ ኣሳይቷል። ክርስቶስ ከወቅቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ የተነሣ ወደ ግብፅና ናዝሬት ተጉዟል። ይህም በበኩሉ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች እንደ ተፈጸሙ የሚያሳይ ነበር። ሌላው ምሳሌ፥ ማቴዎስ ከክርስቶስ ትንሣኤ ጋር የተገናኘውን የጠባቂዎቹን ታሪክ ለማፍረስ መፈለጉ ነው (ማቴ. 28፡1115)። ማቴዎስ ጠባቂዎቹ ለምን እንደ ዋሹ ለማሳየት ወደደ።

ሌላም በሮም ግዛት የነበሩ ሰዎች ሁሉ፥ በተለይም አይሁዶች የሚያነሡት ጥያቄ ነበር። «ክርስቶስ መሢሕ ከነበረ እንዴት ይሰቀላል? የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች በእርሱ ከተፈጸሙ በኋላ የሃይማኖት መሪዎች ለምን አልተቀበሉትም?» ስለሆነም ማቴዎስ፥ አይሁዶች፥ በተለይም የሃይማኖት መሪዎች ለምን ክርስቶስን እንዳልተቀበሉ ያብራራል። ይህ የሆነው ክርስቶስ መሢሕ ስላልሆነ፥ ተኣምራትን ስላላደረገ፥ ወዘተ. . አይደለም። ክርስቶስን ያልተቀበሉት በተወዳጅነቱ ስለ ቀኑበትና ለሰው ሥርዓቶች ባለመገዛቱ ስለ ተበሳጩበት ነበር።

ልዩ ገጽታዎች

1 ስለ ቤተ ክርስቲያን በቀጥታ የተናገረው የማቴዎስ ወንጌል ብቻ ነው (ማቴ. 16፡18-19፤ 18፡17)። ማቴዎስ የቤተ ክርስቲያን ዕድገት የሰው ሳይሆን የክርስቶስ ሥራ እንደሆነ ያሳያል። ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን ስለሚገነባ፥ የትኛውም መንግሥት ክርስቲያኖችን ለማጥፋት የሚያደርገው ጥረት ሊሳካና የቤተ ክርስቲያንም ዕድገት ሊገታ አይችልም። ክርስቲያኖች ለቤተ ክርስቲያን ንጽሕናና ኣንድነት ተግተው ሊሠሩ ይገባል። በተጨማሪም፥ ዐመፀኝነትንና ኃጢአትን ለማስወገድ መትጋት አለብን። ስለሆነም ሰዎች ሕይወታቸውን ለክርስቶስ ሥልጣን እንዲያስገዙ ካደረግን በኋላ፥ ንጉሥ ለሆነው ክርስቶስ ለመገዛት የማይፈልጉትን እንድናስወግድ ታዝዘናል (ማቴ. 18፡5-17)።

 1. ኢየሱስ በሠራው ሥራ ላይ ካተኮሩት ከሌሎች ተመሳሳይ ወንጌላት ይልቅ፥ ማቴዎስ ለክርስቶስ ትምህርት አጽንኦት ሰጥቷል። እንዲያውም ክርስቶስ ካስተማራቸው ነገሮች ውስጥ ረጅሙ ክፍል በማቴዎስ 5-7 ውስጥ ይገኛል። ይህም ክርስቶስ ያስተማራቸው የተለያዩ ትምህርቶች ማጠቃለያ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ምንባብ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ የሚፈልጋቸውን ውስጣዊ ባሕርያት ያሳያል። ክርስቶስ ስለ ወንጌል ስርጭት የሰጠው ትምህርት (ማቴ. 10)፥ ምሳሌዎቹ (ማቴ. 13)፥ የይቅርታ ትምህርቱ (ማቴ. 18)፥ እንዲሁም የመጨረሻ ዘመን ትምህርቱ (ማቴ. 24-25) በተለያዩ ክፍሎች ቀርቧል።
 1. ማቴዎስ የክርስቶስን ታሪክ ሲዘግብ፥ የደቀ መዛሙርቱ መጠራት በቤተ ክርስቲያ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ እያስከተለ መሆኑን አመልክቷል። ክርስቶስ በምድር ላይ እንደኖረ፥ እንዳስተማረና ተአምራትን እንዳደረገ፥ ክርስቶስ ለዓለም ኃጢአት በመሞት በትንሣኤው አምላክነቱን እንዳረጋገጠ፥ እንዲሁም በተቀረው ታሪክ ሁሉ ከተከታዮቹ ጋር ለመኖር ቃል መግባቱን ከማቴዎስ ዘገባ እንረዳለን (ማቴ. 28፡20)። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ፥ ማዕበሉን ፀጥ ያሰኘው ጌታ፥ ዛሬም ኃይል እንዳለውና የሕይወታችንን ማዕበል እንደሚቆጣጠር መገንዘብ አለብን።

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በማንኛውም ዘመን ለሚኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች ምሳሌ ናቸው። ዋጋው ምንም ያህል ታላቅ ቢሆንም፥ ክርስቶስን ከመከተል ወደ ኋላ እንዳይመለሱ ተጠርተዋል። ወንጌሉን ወደ ዓለም ሁሉ ማድረስ ነበረባቸው። የክርስቶስን ቃል በመናገር የሚያምኑ ሰዎች የኃጢአትን ይቅርታ እንደሚያገኙና የማያምኑት ግን ዘላለማዊ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው የማወጅ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል (ማቴ. 16፡18-19)። የክርስቶስን ትእዛዛት ለመፈጸም እስከሚያዳግታቸው ድረስ በቁሳዊ ነገሮች መጨነቅ አያስፈልጋቸውም ነበር (ማቴ. 10፡9-10)። ችግሮች በሚኖሩበት ጊዜ ክርስቶስ ሸክማቸውን እንደሚያግዝ ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር (ማቴ. 1፡28-30)።

 1. ማቴዎስ በሕግ ላይ ትኩረት ሰጥቷል። የአይሁዶች የሃይማኖት ግንዛቤ የመነጨው ከሙሴ ሕግ ነበር። ለሕጉ መታዘዝ መልካም አይሁዶች መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን፥ ለእግዚአብሔር ሊያደርጉት የሚገባቸውን ግዴታ እየተወጡ መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ ያስቡ ነበር። አንድ ሰው የሚከተላቸው ሕግጋት እየበዙ ሲሄዱ፥ መንፈሳዊነት እየጠነከረ እንደሚሄድ ይታሰብ ነበር። ማቴዎስ ስለ እግዚአብሔር ሕግ ጠቃሚ ነገሮችን አስተምሯል።

ሀ. ማቴዎስ የእግዚአብሔር ሕግ ዘላለማዊ እንደሆነ ገልጾአል። ከሕግ አንዲት ነጥብ እንኳ ከእግዚአብሔር ቃል ውስጥ አትወድቅም (ማቴ. 5፡18)። ይህም ክርስትና የብሉይ ኪዳንን ሕግ እንዳላስወገደ፥ ዳሩ ግን እንደፈጸመው ያሳያል።

ለ ላይ ላዩን ለሕግ ከመታዘዝ ይልቅ፥ እግዚአብሔር ሕጉን የሰጠበትን ምክንያት ማወቅና የሕጉን መንፈስ መታዘዝ እንደሚልቅ ከማቴዎስ ወንጌል መረዳት ይቻላል። ስለሆነም ምንም እንኳ ዝሙትን አለመፈጸሙ አስፈላጊ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ለመከላከል የፈለገው የዝሙትን ተግባርን ብቻ ሳይሆን፥ ወደ ዝሙት የሚመራውን የልብ ምኞት ጭምር ነበር።

ሔ ማቴዎስ አይሁዶች የሃይማኖት ማዕከል አድርገው የሚመለከቱትን ሕግን መጠበቅ አስመልክቶ፥ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የክርስቶስ ቀንደኛ ጠላቶች የነበሩት በብሉይ ኪዳን ላይ ሕግ እየጨመሩ ሰዎች እንዲጠብቁ የሚያስገድዱ ወገኖች ነበሩ። ከማቴዎስ ልዩ ገጽታዎች መካከል አንዱ ስለ ሃይማኖትና ሕግ ከፈሪሳውያን ጋር የሚያካሂደው የማያቋርጥ ጦርነት ነበር።

መ. አምላክ በመሆኑ ክርስቶስ ክብሉይ ኪዳን ሕግ ጋር እኩል ነበር። እግዚአብሔር ነፍስ ግድያ፥ ዝሙት ወይም ሰንበትን ማክበር ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ የበየነው እርሱ ነበር። ቃሉቹ እንደ ብሉይ ኪዳን ሕግ ዘላለማዊ ነበሩ (ማቴ. 24፡35)።

6ኛ የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) እኛም መንፈሳዊነትን ሕግን በመጠበቅ እንደምንናገር የሚያሳዩ የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ደንቦችን እየጠቀስህ አብራራ። ለ) ይህ ጠቃሚ የሚሆነው እንዴት ነው? ጎጂስ የሚሆነው? ሐ) ሰዎች ከሚደነግጓቸው አንዳንድ ሕግጋት ይልቅ ከኃጢአት በስተ ጀርባ ያሉትን እመላካከቶችና ምክንያቶች የማናጤነው ለምንድን ነው? አንድ ምሳሌ ስጥ። ይህንን የምናደርገው እንዴት ነው?

(ማብራሪያዎቹ ሁሉ የተወሰዱት በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)