የመጽሐፈ መሳፍንት ዋና ዋና ትምህርቶች

የውይይት ጥያቄ፥ ከመጽሐፈ መሳፍንት እንዳነበብነው በውስጡ የሚገኙ፥ ከሕይወትህና ከቤተ ክርስቲያንህ ጋር ልታዛምጻቸው የምትችለውን ዋና ዋና እውነቶች ናቸው ብለህ የምታስባቸውን ዘርዝር።

 1. መጽሐፈ መሳፍንት ለእግዚአብሔር በከፊል የመታዘዝ ውጤት ምን እንደሆነ ያሳየናል። እግዚአብሔር ከነዓናውያንን በሙሉ እንዲያጠፉ የሰጠውን ትእዛዝ አይሁድ በከፊል ብቻ ስለታዘዙት፥ ወደ ባሰ ኃጢአት የመውደቅን ሂደት ጀመሩ። ለእግዚአብሔር በከፊል መታዘዝ ብዙም ሳይቆይ፥ ለእርሱ በግልጽ ወዳለመታዘዝ ተለውጧል። የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ነገር በክርስቲያን ሕይወትም ይፈጸማል። ማንም ሰው በድንገት በኃጢአት ፈጥኖ አይወድቅም። ይልቁንም ይህ በሂደት የሚፈጸም ነው። በመጀመሪያ መጠነኛ ጅማሬ ይኖረዋል። ይህ ጅማሬ በከፊል መታዘዝ ነው። በአብዛኛው የሕይወት ክፍላችን ለእግዚአብሔር እንታዘዛለን፤ ነገር ግን ያልተናዘዝናቸው ኃጢአቶች በሕይወታችን እንዲቆዩ እንፈቅዳለን። እነዚህ ኃጢአቶች፥ ኩራት፥ ትዕቢት፥ ቁጣ፥ ወይም ቅንዓት ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ብዙ ሳይቆዩ እነዚህ ኃጢአቶች አድገው ሕይወታችንን በመቆጣጠር ለእግዚአብሔር በግልጽ ወዳለመታዘዝ ያደርሱናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህንን እውነት በራስህ ወይም በሌላው ክርስቲያን ሕይወት እንዴት አየኸው?

 1. መጽሐፈ መሳፍንት ዓለም በክርስቲያን ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ያላትን ኃይልና እንዴት ወደ ኃጢአት እንደምትመራ ያሳየናል። በኢያሱ መሪነት እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ለመከተልና እርሱን ብቻ ለማምለክ ቃል ኪዳን አደረጉ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጠላቶች የሆኑት ከነዓናውያን በመካከላቸው እንዲኖሩ ስለፈቀዱ፥ የከነዓናውያን ልምምድ ብዙም ሳይቆይ ችግር ያመጣባቸው ጀመር። ወዲያውኑ እንደከነዓናውያን ማሰብና ማምለክ ጀመሩ፤ በመጨረሻም እንደ ከነዓናውያን መኖር ጀመሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ራሳችንን ከዓለምና ከልምምዷ እንድንለይ፥ እርሷንም ከመምሰል እንድንጠነቀቅ ያስተምረናል።

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ቆሮ. 6፡14-18 እና 1ኛ ዮሐ. 2፡15-17 አንብብ። ከዓለም ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት በዚህ ክፍል የተሰጠን ትእዛዝ ምንድን ነው?

ክርስቲያኖች ሁሉ ከዓለም ጋር ያለንን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንድናቋርጥ መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምረንም። ኢየሱስም የጸለየው፥ በዓለም እንድንኖር እንጂ፥ ከዓለም እንድንወጣ አይደለም (ዮሐ. 17፡14-19)። እግዚአብሔርን የማያምኑ ሰዎችን ጓደኛ እንድናደርግ፥ ወንጌልን እንድናካፍላቸው፥ በሚያስፈልጋቸው ነገር እንድንረዳቸው፥ ከጎናቸው ሆነን እንድንሠራ፥ ወዘተ. ይፈልጋል። ኢየሱስ ራሱ «የኃጢአተኞች ወዳጅ» ተብሉአል (ማቴ. 11፡19)። ከማያምኑ ጋር ያለንን ማንኛውንም ኅብረት ማቆም አለብን የሚሉ ሰዎች ተሳስተዋል። ከእነርሱ ጋር ካልኖርን፣ ካላወቅናቸውና ፍቅርን ካላሳየናቸው በቀር፥ የዓለም ብርሃንና ጨው እንዴት መሆን እንችላለን? እንድንጠነቀቅ የተነገረን ነገር ቢኖር፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ ዓለማዊ ተጽዕኖ እንዳይኖር ነው። እንደ እግዚአብሔር ልጆች የዓለም ፍልስፍና በሕይወታችን ላይ የማያስፈልግ ተጽዕኖ እንዳያደርግ መጠንቀቅ አለብን። ለምሳሌ፡ የገንዘብና የሥልጣን ፍቅር፥ ለራሳችን፥ ለቤተሰባችን ወይም ለጎሣችን በራስ ወዳድነት የተለየ ጥንቃቄ ለማድረግ መመኘት የለብንም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያን በዓለም ፍልስፍና ተጽዕኖ ሊደረግበት የሚችለው እንዴት ነው? ለ) ክርስቲያን ከማያምኑ ሰዎች ጋር እየኖረ በዓለም ፍልስፍና ተጽዕኖ የማይደረግበት እንዴት ነው?

 1. እግዚአብሔር አማኞች ዓለምን እየመሰሉ ሲሄዱ፥ ያነጻቸው ዘንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ይጠቀማል። ይህ ማለት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሁሉ ስለ ኃጢአት ፍርድ ናቸው ማለት አይደለም፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ናቸው። አንዳንዶች በችግር ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ኃጢአተኞች ስለሆኑ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ናቸው በማለት እንዳንፈርድ መጠንቀቅ አለብን። የእግዚአብሔር ሕዝብ በኃጢአት ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲያልፉ የሚያደርግበት መንፈሳዊ መመሪያ አለ። ይህም በሽታ፥ የወዳጅ ሞት፥ ወይም በአገር ላይ የሚመጣ ችግር ሊሆን ይችላል። በዚህ ዓይነት ጊዜ የሚመጣው ችግር ዓላማ ሕዝቡ ንስሐ ገብተው ከክፉ መንገዳቸው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ለማድረግ ነው። እውነተኛ ንስሐ ሰውን ጠባዩን እንዲለውጥ ያደርገዋል። እስራኤላውያን ግን በእውነት ንስሐ ገብተው እንደሆነ የሚያሳይ ምንም መረጃ የለም። ከጠላቶቻቸው ነፃ እንደወጡ ብዙም ሳይቆዩ፥ ወደ ቀድሞ ክፉ ተግባራቸው ይመለሱ ነበር። የእግዚአብሔር ፍላጎት ግን ንስሐ እንድንገባና መንገዳችንን እንድንለውጥ ነው። ወደ በረከት ስፍራ የሚመልሰን በዚያን ጊዜ ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ በግል ሕይወትህና በቤተ ክርስቲያንህ እግዚአብሔር ከኃጢአት ያነጻችሁ ዘንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዴት እንደተጠቀመ ተጨባጭ ምሳሌዎችን ስጥ።

 1. የእግዚአብሔር ሕዝብ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር ታላቅ መሪን በማስነሣት በእርሱ አማካይነት ነጻነትን ይሰጣቸዋል። እስራኤላውያን በጠላቶቻቸው በሚጨቆኑበት ጊዜ፥ የሕዝቡን ጸሎት በመስማት መሳፍንትን አስነሣላቸው። በመጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ የምናያቸው መሳፍንት ተቀዳሚ ተግባራቸው ወታደራዊ መሪነት ሆኖ ሕዝቡን ከባርነት ነፃ አውጥተዋል። እግዚአብሔር እነዚህን ሰዎች የመረጠው በመንፈሳዊነታቸው ለመሆኑ ምንም መረጃ የለንም። እንዲያውም አብዛኛዎቹ መሳፍንት በጣም መንፈሳዊ አልነበሩም። ሶምሶን ዘማዊ ነበር። ዮፍታሔ ልጁን ሠውቷል። ጌዴዎን ሕዝቡን ወደ ኤፉድ አምልኮ መርቷል። አብዛኛዎቹ መሳፍንት ልንከተለው የሚገባ መንፈሳዊ ምሳሌነት አልተዉልንም። ቢሆንም እግዚአብሔር ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት ሰውን ከመንፈሳዊነቱ ውጭ እንዴት ሊጠቀምበት እንደሚችል የእነርሱ ታሪክ ያሳየናል።

ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር የሚሠራው በተመሳሳይ መንገድ ነው። እግዚአሔር ሕዝቡን ከባርነት ነፃ ለማውጣት መሠረታዊ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለውን ሰው የመንፈሳዊ ሕይወት ደረጃውን ሳይመለከት ሊጠቀምበት ይችላል። ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር፥ አማኝ ያልሆነን የፖለቲካ መሪን በማስነሣት፥ ለአማኞች እንዲራራና ከችግሮቻቸው ነፃ እንዲያወጣቸው ሊያደርግ ይችላል።

ነገር ግን እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ መሪዎች የተቀደሰ ሕይወት እንዲኖራቸው ይፈልጋል። የእስራኤል ልጆች በተደጋጋሚ በኃጢአት የወደቁበት ምክንያት፥ ምናልባት እነዚህ መሳፍንት ለሕዝቡ መልካም መንፈሳዊ ምሳሌ ስላልሆኑ ይሆናል። የሰዎች ሥነ-ምግባርና መንፈሳዊ ሕይወት ብዙ ጊዜ የሚወሰነው በመሪዎቻቸው መንፈሳዊ ሕይወት ላይ መሆኑ ከቅዱሳት መጻሕፍት መመሪያዎች አንዱ ነው። መሪዎች እግዚአብሔርን ሲወዱና በቅድስና ሲያገለግሉት፥ ሕዝቡም እንዲሁ ያደርጋሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ) ይህ በቤተ ክርስቲያንህ እውነት ሲሆን ያየኸው እንዴት ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምርጫ መመሥረት ያለበት፥ በትምህርት፥ በዘር፥ ወይም በቤተሰብ ውርስ፥ ወዘተ. ሳይሆን በመንፈሳዊ መመዘኛ መሆን እንዳለበት ይህ ምን ያስተምረናል?

 1. መጽሐፈ መሳፍንት የሚያተኩረው በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ላይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ከመጽሐፈ መሳፍንት የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ፡- መሳ. 3፡10፤ 6፡34፤ 11፡29፤ 14፡6፥ 19፤ 15፡14፤ 16፡20። ይህ በዚያን ዘመን ስለነበረው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ምን ያስተምረናል?

ከመጽሐፈ መሳፍንት ልዩ ገጽታዎች መካከል አንዱ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የተደረገ ትኩረት ነው። ከዚህ መጽሐፍ በፊት ስለ መንፈስ ቅዱስ አገልግሎት የተነገረው በጣም ጥቂት ነገር ነው። በመጽሐፈ መሳፍንት ግን የጌታ መንፈስ ወይም መንፈስ ቅዱስ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። ከላይ የተሰጡትን ጥቅሶች በሚገባ ካጠናን የሚከተሉትን ነገሮች እንመለከታለን፡-

ሀ. አንድ የተለየ ተግባር ለመፈጸም በተጠሩ ውሱን መሪዎች ላይ መንፈስ ቅዱስ ይወርድ ነበር። የመንፈስ ቅዱስ በሰዎች ላይ መውረድ የተለመደ ነገር አልነበረም፤ ሆኖም እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመምራት ወይም ነፃ ለማውጣት ይችሉ ዘንድ ለመረጣቸው ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው ነበር። በዚህ ዓይነት እነዚህ መሳፍንት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከባርነ ያወጡት በራሳቸው ኃይል ሳይሆን፥ እግዚአብሔር መንፈሱን ስለ ሰጣቸው እንደሆነ ግልጥ መሆን ነበረበት። እውነተኛው የእስራኤል ነፃ አውጭ እግዚአብሔር እንጂ መስፍኑ አልነበረም።

ለ. መንፈስ ቅዱስ ሰዎች የእርሱን ልዩ ኃይል በሚፈልጉበት ጊዜ በተደጋጋሚ ይመጣ ነበር። በመጀመሪያ አካባቢ ሶምሶን ከጠላቶቹ ጋር በሚገናኝበት ጊዜ ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ በላዩ ላይ ይወርድ ነበር።

ሐ. መንፈስ ቅዱስ በሰው ደስ በማይሰኝበት ጊዜ ከዚያ ሰው ተለይቶ ይሄድ ነበር። ይህን እውነት እግዚአብሔር ከሶምሶን ተለየ ከሚለው ቃል መመልከት እንችላለን። በንጉሥ ሳኦል ታሪክ መንፈስ ቅዱስ ተወው የሚል ቃል ስናነብ (1ኛ ሳሙ. 16፡14)፥ ይህ ነገር ግልጽ ይሆንልናል። ለጸሎቱ መልስን በመስጠት መንፈስ ቅዱስ ወደ ሶምሶን እንደተመለሰ ደግሞ የዳጎንን ቤተመቅደስ በመደርመሱ እንረዳለን፤ (መሳ. 16፡28-30)።

ልናስታውሰው የሚገባን አንድ በጣም አስፈላጊ እውነት አለ። እግዚአብሔር እውነቱን ሁሉ በአንድ ጊዜ አልገለጠም። ነገር ግን ስለ እርሱ የሚናገር ተጨማሪ እውነትን በየጊዜው በዘመናት ሁሉ በዝግታ ይገልጥ ነበር። ይህ «እየጨመረ የሚሄድ መገለጥ» በመባል ይታወቃል። አይሁድ እግዚአብሔር አምላክ አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ ማለት ሥላሴ መሆኑን አያውቁም ነበር፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን መንፈስ የእግዚአብሔር ተቀጥያ፥ ወይም የእግዚአብሔር ኃይልና ሥልጣን፥ የመኖሩ ማረጋገጫ አድርገው ያስቡት ነበር። መንፈስ ቅዱስን ከሥላሴ አንዱ አድርገን የምንመለከተው በአዲስ ኪዳን ብቻ ነው፤ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ነው፥ ሆኖም ከእግዚአብሔር የተለየ ነው።

ይህም ማለት ስለ መንፈስ ቅዱስ ያለንን መረዳት በብሉይ ኪዳን ላይ ብቻ ከመመሥረት መጠንቀቅ አለብን ማለት ነው። በኢዩኤል 2፡28 እግዚአብሔር በመጨረሻው ቀን መንፈሱን በሰዎች ሁሉ ላይ እንደሚያፈስ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። የዚህ ትንቢት ፍጻሜ የጀመረው በጰንጠቆስጤ ቀን ነው፤ በዚያን ጊዜ ሕዝቡ በላይኛው ክፍል ሳሉ መንፈስ ቅዱስ በሁሉም ላይ ወርዶባቸው ነበር (የሐዋ. 2)። በአዲስ ኪዳን በሚገኙ የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች የሚከተሉት እውነቶች ግልጽ ናቸው።

ሀ. መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር በጸጋው በሚያምኑበት ጊዜ ለልጆቹ በሙሉ የሚሰጠው እንጂ ለተወሰኑ የተመረጡ ሰዎች የሚሰጥ ብቻ አይደለም። በሮሜ 8፡9 ጳውሎስ ማንም መንፈስ ቅዱስ የሌለው የክርስቶስ አይደለም ይላል። በሌላ አነጋገር፥ ይህ ማለት አማኝ አይደለም ማለት ነው። መንፈስ ቅዱስ ወደ እኛ የመጣው ባመንበትና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች በሆንበት ጊዜ ስለሆነ አሁን ወደ እኛ እንዲመጣ መጸለይ ስሕተት ነው፤ የእግዚአብሔርን መንፈስ ያለማቋረጥ እንድንሞላ መጸለይ ግን ተገቢ ነው፤ (ኤፌ. 5፡18)። መንፈስ ቅዱስን እንዳናጠፋው ኃጢአታችንን መናዘዝ አለብን (1ኛ ተሰ. 5፡19)።

ለ. እግዚአብሔር የመንፈስ ቅዱስን ሕልውና ከልጆቹ ላይ አይወስድም። ክርስቲያኖች ኃጢአት በሚያደርጉበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ሊወሰድባቸውና ደግሞ ተመልሶ ሊመጣ አይችልም። ኃጢአት የሚያደርግ ክርስቲያን እንኳ መንፈስ ቅዱስ አለው። እርስ በርሳቸው ይጋጩ የነበሩ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያኖች እንኳ መንፈስ ቅዱስ እንደነበራቸው ከ1ኛ ቆሮ. 1፡7 በግልጽ እንመለከታለን፤ ነገር ግን ኃጢአት በምናደርግበት ጊዜ በእኛ ውስጥ የሚሠራውን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል እናጣለን።

ሐ. የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ቤተ ክርስቲያንን ያገለግሉበት ዘንድ እግዚአብሔር እንደፈለገ ለክርስቲያኖች ሁሉ ተሰጥተዋል (1ኛ ቆሮ. 12፡11)። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ዓላማቸው ለግል ጥቅም፥ መንፈሳዊነታችንን ለመግለጥ አይደለም፤ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይ በመንፈሳዊ ብስለትና እግዚአብሔርን በማገልገል እንድታድግ እርስ በርሳችን ማገልገል እንድንችል ለማድረግ ነው (1ኛ ቆሮ. 14፡26)።

መ. የአንድ ሰው መንፈሳዊነት የሚመዘነው፥ በመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች እንጂ (ገላ. 3፡22-23)፥ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን በመቀበል አይደለም።

ይህ ትምህርት ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ከሚያስተምሩት የተለየ ቢሆንም፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ሁሉ በጥንቃቄ በመመርመር ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚናገሩትን ነገር ማወቅ አስፈላጊ ነው። በመጽሐፈ መሳፍንት ወይም በሐዋርያት ሥራ ውስጥ በሚገኝ አንድ ክስተት ላይ የሥነ-መለኮት ትምህርት መሥርተን፥ መንፈስ ቅዱስ የሚሠራበት መንገድ ምን ጊዜም ይኸው ነው ልንል አንችልም። በመንፈስ ቅዱስ ላይ ያለንን እምነት ከሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተገኘ እውነት እንጂ በእነዚህ ጥቂት ጥቅሶች ላይ ብቻ በተገኘ እውነት ላይ መመሥረት የለብንም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከላይ የተመለከትናቸው ጥቅሶች አንዳንድ ክርስቲያኖች ስለ መንፈስ ቅዱስ ከሚያስተምሩት ትምህርት ጋር እንዴት ይጋጫሉ? ለ) ሕይወትህን መርምር። የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በሕይወትህ እንዳይሠራ የከለከሉህ ኃጢአቶች አሉን?

ሐ) የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በሕይወትህ እንዳሉ ማረጋገጫ የሚሆኑ ነገሮችን በምሳሌነት ጥቀስ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መሳፍንት 17-21 

የውይይት ጥያቄ፥ የሰው ልጅ ልብ በመሠረቱ መልካም ነው ወይስ ክፉ? ለምሳሌ፥ ሕግ እንዲሁም ሕግን የሚያስፈጽም የፖሊስ ኃይል ባይኖር ኖሮ የሰዎች ዝንባሌ መልካም ይሆን ነበር ወይስ ክፉ? መልስህን አብራራ።

የመጽሐፈ መሳፍንት የመጀመሪያ ዋና ክፍል (ከምዕ. 1-16 ያለው) በእነዚያ ዓመታት የነበሩ የአይሁዳውያን ዋና የፖለቲካ ችግሮችን ግልጽ በሆነ መንገድ ያሳየናል። ትኩረታቸውም ሕዝቡን ከውጭ ኃይል ወይም ከጠላት ቀንበር ነፃ ለማውጣት እግዚአብሔር ባስነሣቸው መሳፍንትነት አመራር ላይ ነው።

የመጽሐፈ መሳፍንት የመጨረሻው ክፍል (መሳፍንት 17-21) በመሳፍንት ዘመን የነበረውን ሃይማኖታዊና የሥነ-ምግባር ጉድለት የሚያንጸባርቅ ነው። የሰው ልብ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር እስካልሆነ ድረስ ሊኖር የሚችለውን ግልጽ ሥዕል ያሳያል። ሰው «በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን» (መሳ. 21፡25) ማድረግ ሲጀምር፥ ክፉ መሆኑ ወዲያውኑ ይረጋገጣል። ሕግ ወይም ሕግ አስፈጻሚ አካል በሌለበት ለሕገወጥነት መከሰት ጊዜ አይወስድበትም። ሕግና ሕግን የሚያስፈጽሙ የሕዝብ መሪዎች የሰው ኃጢአት በተወሰነ ቁጥጥር ሥር እንዲሆን ያደርጋሉ። እነዚህ ተከላካዮች ሲነሡ፥ የሰው ኃጢአተኝነት ወዲያውኑ ገሐድ ይወጣል።

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) አንተስ ይህ ነገር ሲፈጸም ያየኸው እንዴት ነው? ለ) ይህ ስለ ሰው ክፉ ባሕርይ የሚያስተምርህ ምንድን ነው? 

የውይይት ጥያቄ፡ መሳ. 17-21 አንብብ። በእነዚህ ምዕራፎች የሰው ልጅ ክፋት የታየው እንዴት ነው?

በመጽሐፈ መሳፍንት ምዕ. 17-21 የሚገኙት ታሪኮች የተፈጸሙበትን ጊዜ ማወቅ የማይቻል ነው። የዳን ነገዶች ገና ርስት በመፈለግ ላይ ስለሚገኙና የአሮን ልጅ ፊንሐስ ሊቀ ካህን በመሆኑ፥ ታሪኮቹ የተፈጸሙት በመጀመሪያዎቹ የመጽሐፈ መሳፍንት ዘመን ሳይሆን አይቀርም (መሳ. 18፡1፤ 20፡27-28)። የእነዚህ ታሪኮች ዓላማ በዘመነ መሳፍንት የነበረውን አጠቃላይ የሥነ-ምግባር መመሪያ መጥፋት ለማሳየት ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ሊያውቁና ሌሎችን ማስተማር ይገባቸው ለነበሩ ሌዋውያን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶአል። ከቀሩት እስራኤላውያን ሁሉ በላይ፥ ለእግዚአብሔር ሕግ በመታዘዝ እንዲኖሩ የሚጠበቅባቸው ሌዋውያን ነበሩ። እነርሱም እንደቀረው ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት አደረጉ። በኃጢአታቸውም ምክንያት የቀሩት ሕዝብ ወደ ክሕደትና ጣዖት አምልኮ ሄዱ። የእነርሱም ተግባር ሕዝቡን ወደ እርስ በርስ ጦርነት መራው። 

 1. የሌዋውያን ካህናትና የዳን ነገድ ታሪክ (መሳ. 17-18)

የእግዚአብሔር ሕዝብን ኃጢአተኝነት የሚያመለክተው የመጀመሪያው ታሪክ፥ ስለ አይሁድ ሃይማኖት መበላሸት ይናገራል። ይህ ብልሽት የተጀመረው ከኤፍሬም ነገድ የሆነች አንዲት ሴትና ልጇ ከብር የተሠራ ምስል ሠርተው በቤታቸው ባስቀመጡ ጊዜ ነው።

ወደ ደቡብ ብዙ ኪሎ ሜትር ራቅ ብሉ አንድ ሌዋዊ ነበር። እንደምታስታውሰው፥ ሌዋውያን የእስራኤላውያን ሃይማኖታዊ መሪዎች እንዲሆኑ በእግዚአብሔር የተመረጡ ነበሩ። ደግሞም ይኖሩባቸውም ዘንድ እግዚአብሔር 48 ከተሞችን ሰጥቷቸው እንደነበረ ታስታውሳለህ። ቤተልሔም ከእነዚህ አንዷ አልነበረችም። ይህም የሚያሳየው በሙሴና በኢያሱ ዘመን ተጀምሮ የነበረው የአኗኗር ዘይቤ እየተጣሰ መሆኑን ነው። ሌዋዊ ቤተልሔምን ትቶ ስለ መሄዱ የተነገረው እውነት፥ ጨርሶ ሊገኝባት የማይገባው ከተማ ስለነበረች፥ ሥራ አግኝቶ ወደሌላ ስፍራ መሄዱ ሊሆን ይችላል። ይህም እግዚአብሔር ያዋቀረው የአኗኗር ስልት እየተጣሰ መሆኑን ያሳያል። ሌዋውያን እስራኤላውያን ለጌታ ከሚሰጡት አሥራት በሚገኘው ገቢ ኑሮአቸውን መምራት ነበረባቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የእግዚአብሔር ሕዝቦች አሥራታቸውን በማይሰጡበት ጊዜ ይህ የእግዚአብሔርን ሥራ እንዴት ይጎዳል? ለ) ይህ የአንተ ቤተ ክርስቲያንም ችግር ነውን? ከሆነስ ለምን? 

ሌዋዊው ሥራ ፍለጋ ወደ ሰሜን ተጓዘና ወደ ሚካ ቤት መጣ። ሚካም ላሠራው ጣዖት ካህን ሆኖ እንዲያገለግል ቀጠረው። ሚካ ቤቱን የአምልኮ ስፍራ ለማድረግ ፈልጎ ነበር። ይህንን ያደረገው ለእውነተኛው የእግዚአብሔር አምልኮ በኃላፊነት ማገልገል የነበረበትን አንዱን ሌዋዊ በመቅጠር ነበር። ሌዋዊው ስለ ግል ሕይወቱ እንጂ ለእግዚአብሔር ስለሚደረግ አምልኮ ግድ ስላልነበረው የተሳሳተውን አምልኮ ለመምራት ፈቃደኛ ሆነ። እውነተኛ አምልኮን ሳይሆን ገንዘብን ብቻ ፈለገ።

ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ የዳን ነገድ አባሎች የሚኖሩበትን ስፍራ እየፈለጉ ወደዚህ ስፍራ ደረሱ። የዳን ነገዶች በሜዲትራኒያን ባሕረሠላጤ አጠገብ መሬት ተሰጥቶአቸው ነበር። መሬቱ በዚያ ስፍራ እጅግ ለም ቢሆንም፥ በከነዓናውያን ተይዞ ነበር፤ ስለዚህ የዳን ነገዶች ሌላ ስፍራ ይፈልጉ ዘንድ አምስት ወታደሮችን ላኩ። ወደ ሚካ ቤት በደረሱ ጊዜ ሌዋዊው ከደቡብ የእስራኤል ክፍል እንደመጣ ተገነዘቡ። በዚያ ስፍራ የሚካሄድ የጣዖት አምልኮ አለቃ መሆኑንም አወቁ። ከዚያ በኋላ አምስቱ ሰዎች ወደ ሰሜን 240 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ሌሳ ወደምትባል ስፍራ ደረሱ። የወደፊት ቤታቸውም በዚያ እንዲሆን ወሰኑ። የቀሩት የዳን ነገዶች ወደ ሌሳ መጥተው ምድሪቱን ሲወሩ፥ አምስቱ ሰዎች ወደ ሚካ ቤት በመሄድ ሌዋዊውንና የሚካን ጣዖት ወደ ሌሳ ይዘው ሄዱ። ለብዙ ዓመታት ይህ ሌዋዊና ቤተሰቡ የዚህ ጣዖት ካህናት ሆነው ቀሩ። ሌሳ በኋላ «ዳን» ተብላ የተጠራች የእስራኤል የሩቅ ሰሜን ድንበር ናት።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን ስለ እግዚአብሔር የነበራቸውን ደካማ አስተሳሰብ በሚመለከት ምን እንማራለን? ለ) የአይሁዳውያን ሃይማኖት በከነዓናውያን ሃይማኖት በፍጥነት የተበከለው ለምንድን ነው? ሐ) ሃይማኖታችን በዓለማዊ ልምምድ ስለመበከሉ አደገኛነት ምን እንማራለን?

ከዚህ ትምህርት የምናገኛቸው በርካታ እውነቶች አሉ። በመጀመሪያ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የከነዓናውያንን ባሕልና ሃይማኖት እንዴት በፍጥነት እንደለመዱ ማየት እንችላለን። ሁለተኛ፥ ሕዝቡ የእግዚአብሔር አምልኮ ከጣዖት አምልኮ ጋር ሊቀላቀል እንደሚችል እንዴት እንዳሰበ ማየት እንችላለን። እግዚአብሔር ወደ ጣዖት ሊለወጥና ለራሳቸው ዓላማ ማስፈጸሚያና መጠቀሚያ ሊያደርጉት እንደሚችሉ አሰቡ። ሦስተኛ፥ የጣዖት አምልኮን ዋጋ ቢስነት እናያለን። ጣዖት ራሱን ከመሰረቅ ለማዳን አለመቻሉና፥ ኃይል እንደሌለው ያሳየናል። 

 1. ሌዋዊውና ቁባቱ (መሳ. 19-21)

ከዘመነ መሳፍንት የምናገኘው ሁለተኛው ታሪክ የሕዝቡን የሥነ ምግባር ብልሹነት ያሳየናል። እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎቹ ድካምና ኃጢአት እንዳየለባቸው ለሁለተኛ ጊዜ እንመለከታለን። የመጀመሪያው ሌዋዊ ከቤተልሔም ተነሥቶ ወደ ኤፍሬም እንደሄደ፥ ሁለተኛው ሌዋዊ ደግሞ ወደ ቤተሰቦችዋ የተመለሰችውን ቁባቱን ፍለጋ ከኤፍሬም ወደ ቤተልሔም መጣ። ከቤተልሔም ቁባቱን ይዞ ወደ ኤፍሬም በሚመለስበት ጊዜ እግረ መንገዱን ጊብዓ በምትባል በብንያማውያን ከተማ መሸበትና አደረ። ልክ እንደ ሰዶምና ገሞራ ሰዎች፥ እስራኤላውያን እጅግ አስጸያፊ ተግባር ፈጸሙ። ለራሳቸው ሰዎች መስተንግዶ ማድረግ አልቻሉም። ግብረ ሰዶም ለመፈጸም ፈልገው ሰውዩውን ካደረበት ቤት ለማስወጣት ሞከሩ። ሌዋዊውን ያሳደረው ሰው ግን የገዛ ሴት ልጁንና የሌዋዊውን ቁባት አውጥቶ ሰጣቸው። ቁባቱም እስክትሞት ድረስ በመፈራረቅ ሌሊቱን ሙሉ አመነዘሩባት።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ታሪክ የሌዋዊንና የእስራኤልን ሕዝብ ሃይማኖታዊና ሥነ- ምግባራዊ ክፋት እንዴት ያሳየናል?

ሌዋዊው የቁባቱን ሬሳ 12 ቦታ ቆራረጠና ለእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ አንዳንዱን ቁራጭ ላከ። ይህም ነገር የ12ቱን ነገዶች ቁጣ ቀሰቀሰና ምን እንደተፈጸመ ለማየት መጡ። ታሪኩን በሰሙ ጊዜ፥ ይህንን ኃጢአት የፈጸሙትን ሰዎች አሳልፈው እንዲሰጧቸው የብንያም ነገዶችን ጠየቁ። ብንያማውያን ግን ስለተቃወሙ፥ የእርስ በእርስ ጦርነት ተነሣ። በጦርነቱም 40000 እስራኤላውያንና 25100 ብንያማውያን ሞቱ። የብንያማውያን ሴቶችና ልጆች በሙሉ ተገደሉ። ከብንያም ነገድ በሙሉ የተረፉት 600 ሰዎች ብቻ ነበሩ።

ሌሎች እስራኤላውያን፥ ከእስራኤል ነገዶች አንዱ የሆነው የብንያም ነገድ ሊጠፉ እንደሆነ ተገነዘቡ፤ ስለዚህ ለእነዚህ 600 ብንያማውያን 600 ሚስቶች የሚገኙበትን ዘዴ ፈጠሩ። በዚህም የብንያምን ነገድ ጨርሶ ከመጥፋት አዳኑት።

ሰዎች ራሳቸው የሚፈልጉትን ነገር ብቻ ሲያደርጉ፥ ኃጢአታቸው አድጎ በርካታ ሰዎችን እንደሚነካና እንደሚያጠፋ አይገነዘቡም። የጊብዓ ሰዎች ኃጢአት በሺህ የሚቆጠሩ የበርካታ እስራኤላውያንን ሞትና የብንያም ነገድን ወደ ውድመት የሚያደርስ ጥፋት አስከትሉ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ ቁጥሮች ኃጢአት ስለሚስፋፋበት መንገድና በምድሪቱ ስለ ሕግና ሥርዓት አስፈላጊነት ምን ያስተምሩናል? ለ) ከዚህ ታሪክ ለቤተ ክርስቲያኖቻችን የሚጠቅሙና ልናዛምዳቸው የምንችል አንዳንድ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መሳፍንት 1-16

ብዙ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ችግር በእግዚአብሔር ላይ የሚደረግ ግልጥ ዓመፅ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ሙሉ ለሙሉ አለመታዘዝ ነው። እግዚአብሔርን ሙሉ ለሙሉ አላመልክም ማለት ሳይሆን፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ፈቃድ በከፊል ብቻ መታዘዝ የእግዚአብሔር ሕዝብ ችግር ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ በቤተ ክርስቲያን ወይም በራስህ ሕይወት ውስጥ ይህ ነገር እውነት መሆኑን ያየኸው እንዴት ነው? ምሳሌዎችን ስጥ። 

ለእግዚአብሔር በከፊል መታዘዝ፥ ቆይቶ ወዳለመታዘዝ ያመራል። እግዚአብሔር ልንከተለው የሚገባንን ትእዛዝ ወይም ልናደርገው የሚያስፈልግ ነገር ሲሰጠንና ያንንም በከፊል ብቻ ስንከተል መንፈሳዊ ውድቀት በሕይወታችን ይጀምራል። በቤተ ክርስቲያንም ተመሳሳይ ነገር ይከሰታል። በከፊል መታዘዝ ከዓለም ጋር ጓደኝነት ወደ መፍጠር ነው የሚመራው። ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ክርስቲያን በግሉ ዓለምን መምሰል ይጀምራል፤ ክርስቲያን ወይም ቤተ ክርስቲያን የሥነ ምግባር ንጽሕናቸውንና ልዩ መሆናቸውን እያጡ ይሄዳሉ። ይህም ነገር ወዲያውኑ ዓለምንና ቤተ ክርስቲያንን ወደ ቅልቅል አምልኮ ይመራል። በመጨረሻም እግዚአብሔርን ሙሉ ለሙሉ ወደ መካድና ወንጌልን ወደ መቃወም ያደርሳል።

መጽሐፈ መሳፍንት እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር እንዴት ሙሉ በሙሉ እንዳልታዘዙና እርሱ እንዳዘዘውም ከነዓናውያንን እንዳላባረሩ ያሳየናል። ስለሆነም እግዚአብሔርን የመቃወም ሂደታቸው ተጀመረ። በመጀመሪያው እንደ ከነዓናውያን ማምለክ ጀመሩ። ይህም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ወደ ከፍተኛ የሥነ-ምግባር ድቀት መራቸው። ወዲያውኑ ከነዓናውያን ይጨቁኗቸው ጀመር። እግዚአብሔር የእርሱ ወደሆነው ንጹሕ አምልኮ ሊመራቸው ጠላቶቻቸውን ድል ይነሣ ዘንድ ፈቀደ። ይህ ነገር ለጊዜው የሠራ ቢሆንም እንኳ እያንዳንዱ ተከታታይ ትውልድ እግዚአብሔርን በመተዉ እግዚአብሔር የሥነ-ሥርዓት እርምጃ ይወስድበት ጀመር።

የውይይት ጥያቄ፥ ምሳ. 1-16 አንብብ። ሀ) እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ያልታዘዙት እንዴት ነው? ለ) ሕዝቡ ባለመታዘዛቸው ምክንያት የጌታ መልአክ ያዘዘባቸው ፍርድ ምን ነበር፤ ሐ) በመሳ. 2፡10-19 የምታየውን የክሕደትን ዑደት፥ ፍርድና ነጻ መውጣት ግለጥ። መ) ከመሳፍንት 1-16 የእስራኤልን ሕዝብ ያሸንፉ ጠላቶችና በእነዚህ ጠላቶች ላይ ድልን ይሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር ያስነሣቸውን መሳፍንት ዘርዝር። ሰ) መንፈስ ወረደባቸው ተብሎ የተጻፈላቸውን ሰዎች ዘርዝር።

 1. የዘመነ መሳፍንት መግቢያ (መሳ. 1-3፡6)። 

ሀ. እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በጠላታቸው ሁሉ ላይ ድልን እንዴት እንደሰጣቸው ለማሳየት የቀረቡ ምሳሌዎች (መሳ.

1፡1-18)

አይሁዳውያን ጠላቶቻቸውን ለማሸነፍና ከምድሪቱ ለማባረር ያልቻሉበት ምክንያት ምንድን ነው? ኃይል ስላነሳቸው ነውን? ወይስ በጌታ ርዳታ ሊያባርሩአቸው ስላልሞከሩ ነው? ወይስ የጌታን ትእዛዝ በከፊል ብቻ በመታዘዝ ስለበደሉ? ወይስ እግዚአብሔር በከነዓናውያን ላይ ድልን እንደሚሰጣቸው የገባውን ተስፋ ስላጠፈ ነው?

በዚህ ክፍል የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ ሊያሳየን የፈለገው፥ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ስለ ነበር አይሁድን ለመቋቋቋም የቻለ ማንም ሰው እንዳልነበረ ነው። በይሁዳና በከነዓናውያን መካከል የተደረገውን ጦርነት በምሳሌነት በማቅረብ፥ አይሁድ በቀላሉ እንዴት ሊያጠፏቸው እንደቻሉ ያሳየናል። እንዲሁም አንድ ሰው በእግዚአብሔር እርዳታ አንድን ከተማ እንዴት እንዳሸነፈ አሳይቷል። የካሌብ ልጅ የሆነው የናትናኤል ታሪክ እግዚአብሔር ጠላቶቻቸውን ሁሉ ያሸንፉ ዘንድ ለማድረግ ፈቃደኛ እንደ ነበር የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው።

ለ. አይሁድ ከነዓናውያንን ለማሸነፍና ለማጥፋት አልቻሉም ነበር (መሳ. 1፡18-36) አይሁድ ከነዓናውያንን ሊያሸንፉ ያልቻሉበትን ምክንያት በእግዚአብሔር ላይ ከማሳበብ ይልቅ እራሳቸው እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝ አለመቻላቸው እንደሆነ መገንዘብ ነበረባቸው። ከእስራኤል ነገዶች ማናቸውም ቢሆኑ ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝ አልቻሉም ነበር፤ ስለዚህ በእያንዳንዱ ነገድ አካባቢ ያልተሸነፉና ያልጠፉ የከነዓናውያን ከተሞች ነበሩ።

ሐ. ሕዝቡ ሙሉ በሙሉ ባለመታዘዛቸው ምክንያት እግዚአብሔር ያመጣው ፍርድ (መሳ. 1፡1-5) አንድ ቀን እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ ለመፍረድ ተነሣ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ የሚታመነው የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ ባለመታዘዛቸው ምክንያት ከነዓናውያንን ከእንግዲህ ማሸነፍ እንደማይችሉ ነገራቸው። ከነዓናውያንንና የአምልኮ ስፍራቸውን በሙሉ ስላላጠፉ፥ ከእንግዲህ እግዚአብሔር በከነዓናውያን ላይ ሙሉ ድልን እንደማይሰጣቸው ነገራቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ መታዘዝ እንዳለብን ይህ ነገር ብርቱ ማስጠንቀቂያ እንዴት ይሆነናል?

ለእግዚአብሔር በከፊል መታዘዝ ሙሉ በሙሉ አለመታዘዝ ነው። ያልታዘዝናቸው አንዳንድ ነገሮች መኖራቸውን እያወቅን፥ ለእግዚአብሔር በታዘዝንባቸው ነገሮች መመካት አንዳችም ረብ የለውም። በከፊል መታዘዝ አለመታዘዝ ስለሆነ፥ በእኛ ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ያመጣል።

መ. የክሕደት፥ የፍርድና ነፃ የመውጣት ዑደት (መሳ. 2፡6-3፡6)

በመሳፍንት 3፡1-6 ከነዓናውያን ሙሉ በሙሉ እንዲጠፉ እግዚአብሔር ያልፈቀደበትን ሌላ ምክንያት እናገኛለን። እግዚአብሔር የሚቀጥለው የእስራኤል ትውልድ ለቃል ኪዳኑ ይታዘዝና ይከተለው ወይም አይከተለው እንደሆነ ለመፈተን ይህንን ሕዝብ ሊጠቀምበት ፈለገ። የሚያሳዝነው፥ እያንዳንዱ ትውልድ ዓለምን (ከነዓናውያንን) ወደ መምሰል አዘነበለ፤ በአምልኮውና በሥነ ምግባሩም የተበላሸ ሆነ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም እግዚአብሔር ለእርሱ ያለንን ፍቅር የሚመዝንባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ያ ብዙ ክርስቲያኖች በዚህ ፈተና የሚወድቁት ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል፥ የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ በዚህ ዘመን ውስጥ የእስራኤል ሕዝብ ያለፈበትን የታሪክ ዑደት ያሳየናል። በመጀመሪያ፥ አይሁድ ሌሎች አማልክትን በማምለክ በእግዚአብሔር ላይ ዓመጹ። በሁለተኛ ደረጃ፥ እግዚአብሔር ሊቀጣቸውና ለእርሱ ወደሆነ አምልኮ ሊመልሳቸው ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ሰጣቸው። ሦስተኛ፥ እስራኤላውያን ከጠላቶቻቸው ነፃ ያወጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ። አራተኛ ከጠላቶቻቸው የጭቆና አገዛዝ ነፃ የሚያወጡአቸውን መሳፍንት አስነሣላቸው። አምስተኛ፥ እስራኤላውያን በሰላም ጊዜ ደስ እያላቸው ኖሩ። በዚህ የሰላም ጊዜ ነበር እስራኤላውያን እንደገና በእግዚአብሔር ላይ ያመፁትና እርሱም ለጠላቶቻቸው ቀንበር አሳልፎ በመስጠት ይቀጣቸው።

 1. ዘመነ መሳፍንት (መሳ. 3፡7-16) 

ስማቸው ተጠቅሶ የምናገኘው 12 መሳፍንት ቢሆኑም፥ የተለየ ትኩረት የተሰጣቸው ስድስቱ ብቻ ናቸው።

 1. ጎቶንያል፡- የካሌብ ልጅ ሲሆን በቅድሚያ የተጠቀሰ ነው። የሌሎች መሳፍንት ተግባር የተመሠረተው በዚህ ሰው ምሳሌነት ላይ ነው። በጎቶንያል ታሪክ የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ የሚተርከው የኃጢአት፥ የፍርድ፥ የንስሐና ነፃ የመውጣት ዑደትን ነው። ይህ ዑደት በመጽሐፈ መሳፍንት ሌላ ክፍል አምስት ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። 
 2. ናዖድ፡- የዚህ ሰው ታሪክ በዝርዝር ተዘግቧል። እስራኤልን ነፃ ማውጣቱን ልዩ የሚያደርገው ሞዓባውያንን ለማሸነፍ ራሱ የሠራው ሥራ በመኖሩ ነው። ሌላው መለያው እጀ ግራኝ መሆኑ ነው፡፡
 3. የዲቦራና የባርቅን ታሪክ ልዩ የሚያደርገው ሴቶች በድሉ ውስጥ በተጫወቱት ልዩ ሚና ነው። ዲቦራ የእስራኤል መንፈሳዊ መሪ የነበረች ነቢይት ናት። ኢያዔል ደግሞ የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስን በመግደል የዚህ ድል ተሳታፊ ነበረች።
 4. በመጽሐፈ መሳፍንት ማዕከላዊ ታሪክ ላይ የጌዴዎንና የልጁን የአቤሜሌክን ታሪክ እናገኛለን። በዚህም ቦታ የጌታ መልአክ የተባለው (ክርስቶስ) ጌዴዎንን በመጥራትና በኃይል በማስታጠቅ ተግባር የተጫወተውን ሚና እንመለከታለን። በጌዴዎን ታሪክ ውስጥ ትኩረት የተሰጠው የእስራኤላውያንን ጦርነት እግዚአብሔር እንዴት እንዳሸነፈላቸው መናገር ነበር። ባደረጉት ነገር እንዳይመኩ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ጦርን ለማሸነፍ 400 ሰዎችን ብቻ ተጠቀመ።

አይሁድ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድን ሰው ንጉሥ ለማድረግ እንደሞከሩ እናያለን። ጌዴዎንን ንጉሣቸው እንዲሆን ጠየቁት፤ እርሱ ግን እምቢ አለ። ይህንን ያደረገው የሕዝቡ ንጉሥ መሆን ያለበት እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነና እርሱም ሆነ ሕዝቡ፥ ሰብዓዊ ንጉሥ ከመፈለግ ይልቅ ለእግዚአብሔር ሥልጣን መገዛት እንዳለባቸው ያውቅ ስለነበረ ነው (መሳ. 8፡22-23)።

በጌዴዎን ታሪክ ውስጥ ሦስት የሚያሳዝኑ ነገሮች ተፈጽመዋል፡-

ሀ. መጀመሪያ፥ ጌዴዎን ከጠላቶቼ በተዋጋሁ ጊዜ አልረዳችሁኝም ብሉ የሱኮትን ከተማ ሲቀጣ እናያለን።

ለ. ሁለተኛው ጌዴዎን የወርቅ ኤፉድ መሥራቱ ነበር። ኤፉድ ካህናት የሚለብሱት በተለያየ ሕብር ያሸበረቀ ልብስ ነበር። ኤፉድ ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ የሚያገለግል መሣሪያ ነበር፤ (1ኛ ሳሙ. 23፡6-12)። ጌዴዎን ኤፉድ ለምን እንደሠራ ግልጽ አይደለም። ምናልባት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ተጠቅሞበት ይሆናል። በምንም መንገድ ይሁን ብቻ ወዲያውኑ ወደ አምልኮ ዕቃነት ተለወጠ። የእግዚአብሔር አምሳል ተደርጎ ተመልኳል፤ ወይም አንዳንድ ምሁራን እንደሚያስቡት፥ ኤፉድ በአንድ ጣዖት ላይ ይደረግና ሰዎች ወደዚያ በመምጣት ኤፉዱ የአማልክቶቻቸውን ፈቃድ እንደሚወስንላቸው ያምኑ ነበር።

እግዚአብሔር ጌዴዎንን በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቀመበት ቢሆንም ይህ ነገር ለእርሱና ለቤተሰቡ የማሰናከያ ዓለት ሆነባቸው።

ሐ. የጌዴዎን ልጅ የሆነው አቤሜሌክ ራሱን አነገሠ። ይህም በእስራኤል ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት አስነሣ። አቤሜሌክንም አንዲት ሴት የወፍጮ ድንጋይ በራሱ ላይ ለቃ ገደለችው።

 1. ዮፍታሔ፡- በኅብረተሰቡ ተንቆና ተጠልቶ የነበረ ሰው ሲሆን የሚቀጥለው ዋና መስፍን ሆነ። በእርሱም ጊዜ ሁለት የሚያሳዝኑ ነገሮች ሆኑ። በመጀመሪያ፥ ከጦርነት አሸንፎ በሚመጣበት ጊዜ የሚያገኘውን የመጀመሪያውን ነገር ለእግዚአብሔር ለመሠዋት አደገኛ ስእለት ተሳለ። ጦርነቱን አሸንፎ በመጣ ጊዜ ያገኘው የመጀመሪያ ነገር ሴት ልጁ ስለነበረች፥ ስእለቱን መፈጸም ነበረበት። በዮፍታሔ ሴት ልጅ ላይ ስለተፈጸመው ትክክለኛ ነገር ምሁራን ይከራከራሉ። አንዳንዶች ዮፍታሔ ልጁን ለእግዚአብሔር ስለሰጠ፥ ድንግል ሆና በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የምታገለግል ሆነች ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ዮፍታሔ ልጁን ለእግዚአብሔር ሠውቶ መሥዋዕት አቅርቧል ይላሉ። ሰውን በመሥዋዕትነት ማቅረብ በብሉይ ኪዳን የተከለከለ ቢሆንም (ዘሌ. 18፡21፤ ዘዳ. 18፡10-12)፥ ዮፍታሔ በልጁ ላይ ያደረገው ይህን ሳይሆን አይቀርም።

ሁለተኛ፡በዮፍታሔና በኤፍሬም ነገዶች መካከል ጦርነት ተቀሰቀሰ። በዚህም ከኤፍሬም ነገድ 42000 ሰዎች ሞቱ።

 1. በመጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ የምናገኘው የመጨረሻው ትልቅ መስፍን ሶምሶን ነው። ሶምሶን ናዝራዊ ሆኖ እንደሚወለድ እግዚአብሔር ለወላጆቹ ስለነገራቸው ልደቱ ልዩ ነበር። ናዝራዊ ለተወሰነ ጊዜ ራሱን ለእግዚአብሔር አገልግሉት የለየ ሰው መሆኑን ታስታውሳለህ። የሶምሶን ናዝራዊነት ልዩ የሆነው የዕድሜ ልክ በመሆኑ ነው። ናዝራዊ በመሆኑም የወይን ፍሬ ውጤት የሆነ ማንኛውንም ነገር የማይበላ፥ ምንም ዓይነት ሬሳ የማይነካና ጠጉሩን የማይቆረጥ ነበር፤ (ዘኁ. 6፡1-21 ተመልከት)። የሚያሳዝነው ግን ሶምሶን እነዚህን ትእዛዝት ሁሉ አፍርሷል። ከፍልስጥኤማውያን ጋር ወይንን ሳይጠጣ አልቀረም፤ የሞተ አንበሳ ሬሳ ነክቷል።ጠጉሩን በተቆረጠ ጊዜ ግን እግዚአብሔር የሰጠው ኃይል ከእርሱ ተወሰደ። ሶምሶን መንፈስ ቅዱስና ታላቅ ኃይል የነበረው ቢሆንም፥ የሥነ ምግባር ሕይወቱ ግን በጣም የተበላሸ ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እስራኤልን ለማዳን በሶምሶን ለመጠቀም ያሰበውን ያህል አልተጠቀመበትም። ለዚህ ነው ሶምሶን በእስራኤል ሕዝብ ላይ የነበረው መሪነት ፍልስጥኤማውያንን ማሸነፍና እንደገና በእነርሱ እጅ መውደቅና መገዛት የተደጋገመበት። ፍልስጥኤማውያን በእስራኤል ላይ የነበራቸው የበላይነት እስከ ዳዊት ዘመን ድረስ ቀጥሎአል።

የውይይት ጥያቄ፥ የእግዚአብሔርን ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ መሪዎች ራሳቸውን በእግዚአብሔር ፊት በንጽሕና መጠበቃቸው አስፈላጊ እንደሆነ የሶምሶን ታሪክ እንዴት ያስጠነቅቀናል? 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከተለያዩ መሳፍንት የምናገኛቸው አንዳንድ መንፈሳዊ ትምህርቶች ምንድን ናቸው? ለ) በእነዚህ ምዕራፎች ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ የምንማረው ነገር ምንድን ነው? 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመጽሐፈ መሳፍንት ዓላማ

እስራኤል በጠላቶችዋ ለምን ተሸነፈች? ያለማቋረጥ በባርነት ውስጥ የሆነችውስ ለምንድን ነው? እስራኤላውያን እግዚአብሔር የሰጣቸውን የተስፋ ቃል ኪዳን በረከት ያልተለማመዱት ለምንድን ነው? እግዚአብሔር ሊያድናቸው ስላልቻለ ነውን? የከነዓናውያንና የአሕዛብ አማልክት ብርቱ ስለሆኑ ነውን?

የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ ለመመለስ የሚሞከራቸው ጥያቄዎች እነዚህ ናቸው። የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ እስራኤላውያን ያ ሁሉ ሥቃይ የደረሰባቸው ለምን እንደሆነ ሊገልጥላቸው ይፈልግ ነበር። በመጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ እስራኤላውያን ለምን እንደተሸነፉና በመከራ ውስጥ እንደተዘፈቁ የሚያሳዩ ሁለት ምክንያቶች ተሰውረው እናገኛለን፡

 1. እስራኤላውያን ብዙ መከራና ችግር የደረሰባቸው ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን በታዛዥነት ስላልኖሩ ነው። እግዚአብሔር እንዳልተጠነቀቀላቸው በማሰብ እርሱን ከመውቀስ ይልቅ፥ እስራኤላውያን ለወደቁበት አስጊ ሁኔታ ራሳቸውን ብቻ መውቀስ ነበረባቸው። እውነተኛ ንጉሣቸውን እግዚአብሔርን ትተው፥ የከነዓናውያንን አማልክት፥ ሥነ-ምግባራት፥ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችና የአኗኗር ዘይቤዎች ስለተከተሉ እግዚአብሔር እየቀጣቸው ነበር። በኦሪት ዘዳግም እንደተጠቀሰው፥ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድን አስከተለባቸው። በመጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ በተደጋጋሚ እንደምናነበው «የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረጉ» (መሳ. 2፡11፤ 3፡7፥ 12፤ 4፡1 ወዘተ.)። በመጽሐፈ መሳፍንት የሚገኙት የመጨረሻዎቹ ሁለት ታሪኮች የሚያሳዩት የእግዚአብሔር ሰዎች ምን ያህል ከፍተው እንደነበር ነው።

የሚያሳዝነው የእግዚአብሔር ሕዝብ በታሪክ ሁሉ በፊቱ የተቀደሰ ኑሮ ከመኖር ወደኋላ ማለታቸው ነው። በዚህ ፈንታ ዓለምን መሰሉ። ውጤቱም በራሳቸው ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ማስከተል ሆነ። እግዚአብሔር በረከቱን ከእነርሱ ወሰደ። ወደ እግዚአብሔር መመለስን እምቢ ሲሉ፥ እግዚአብሔር ለምርኮ አሳልፎ ይሰጣቸውና በዓለም እንዲሸነፉ ያደርግ ነበር። ይህም ሆኖ ሳይመለሱ ሲቀሩ፥ እግዚአብሔር ይተዋቸው ነበር። በትንቢተ ሕዝቅኤል የእግዚአብሔር ክብር ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱን እንዴት እንደተወ እናነባለን (ሕዝ. 10፡ 11፡23)። በአዲስ ኪዳን በጳውሎስ ከተጀመሩት አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ቅድስናቸውን ስላጡ በመጨረሻ ተደመሰሱ ወይም ወደ መስጊድነት ተለወጡ፤ ስለዚህ አሁንም ቢሆን ያለማቋረጥ እርሱን ከተውንና እንደ ዓለም መኖር ከጀመርን እግዚአብሔር እኛንም ይተወናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም ቢሆን ዓለምን የመምሰል አዝማሚያ በአብያተ ክርስቲያኖቻችን ውስጥ የሚታየው እንዴት ነው? ለ) በዘመነ መሳፍንት ከነበረው የእስራኤላውያን ታሪክ እንደ ማስጠንቀቂያ ልንወስደው የሚገባን ነገር ምንድን ነው? ሐ) እኛ ክርስቲያኖች ዓለምን መምሰል እንደሌለብን ለማስተማር መጽሐፈ መሳፍንትን እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን?

 1. እስራኤላውያን ከፍተኛ መከራና ችግር የደረሰባቸው ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ቃል ኪዳን ይጠብቁ ዘንድ የሚያስችላቸው ብቁ መሪ ስላላገኙ ነው። በመጽሐፈ መሳፍንት ኋለኛ ክፍል እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን፡- «በዚያም ዘመን ከእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር» (መሳ. 21፡25)። እንደ ጸሐፊው አመለካከት፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የተሸነፉበትና በኃጢአት የወደቁበት አንዱ ምክንያት ጠንካራ መሪ ወይም የሚመራቸው ንጉሥ ስላልነበራቸው ነው። ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን የቃል ኪዳን ግንኙነት ለመጠበቅ የነገድ አመራር በቂ አልነበረም።

መጽሐፈ መሳፍንት የተጻፈው ምናልባት በዳዊት ጊዜ ስለሆነ ጸሐፊው እግዚአብሔርን የሚፈራ ጠንካራ መሪ፥ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ ይኖር ዘንድ የሚጫወተውን ከፍተኛ ሚናና የሚሰጠውን ጥቅም ታላቅነት ተመልክቶ ይሆናል። ከኋለኛው ታሪክ እንደምንገነዘበው፥ ንጉሥ እግዚአብሔርን የሚፈራ ካልሆነ ሕዝቡ ወዲያውኑ እግዚአብሔርን ይተዋሉ። መጽሐፈ ነገሥት የሚያሳየን እስራኤል ነገሥታትን ማግኘቷ ብቻ ቃል ኪዳንን ለመጠበቅና ከእግዚአብሔር ፍርድ ለማምለጥ በቂ እንዳልሆነ ነው።

የእስራኤል ዋና ችግር ለሰማያዊ ንጉሥዋ አለመታዘዝዋ ነው። ምድራዊው ንጉሥ እግዚአብሔርን የሚፈራ ከሆነ፥ ሕዝቡ ለቃል ኪዳኑ ታዛዥ ሆኖ እንዲኖር ይረዳል። ንጉሡ ታዛዥ ባይሆንም እንኳ፥ እስራኤላውያን ለሰማያዊ ንጉሣቸው መታዘዛቸውን መቀጠል ነበረባቸው፤ ነገር ግን ልክ በመሳፍንት ዘመን እንደ ነበረው ፈጥነው በኃጢአት ይወድቁ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) ሕዝቡ ለእግዚአብሔር እየታዘዙ እንዲኖሩ እግዚአብሔርን ስለሚፈራ መሪ አስፈላጊነት ይህ ምን ያስተምረናል? ለ) መሪው ወደየትኛውም አቅጣጫ ቢመራ፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን ግን የግል ግንኙነቱን ከእግዚአብሔር ጋር መጠበቅ እንዳለበት ይህ ምን ያስተምረናል?

መጽሐፈ መሳፍንት የሚያስተምረን የእግዚአብሔር ሰዎች በትእዛዙ በማይመላለሱበት ጊዜ፥ ፍርድን ብቻ ሳይሆን፥ ጥፋትንም ጭምር በራሳቸው ላይ እንደሚያመጡ ነው። ከመሳፍንት 17-21 ያለው ክፍል ዋና ትምህርት ለቃል ኪዳኑ አለመታዘዝ በሚኖርበት ጊዜ ሕዝቡ እግዚአብሔርን በመተው ሐሰተኛ አማልክትን እንደሚያመልኩ ነው። እግዚአብሔርን በሚተዉበት ጊዜ የቅን ፍርድ ጉድለትና የእርስ በርስ መጠፋፋት ይከሰታል። ፈሪሀ እግዚአብሔር በማይኖርበት ስፍራ፥ ፍትሐዊ ሕግጋት አይኖሩም፤ ውጤቱም የሕዝቡ ሁሉ መሠቃየት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በሕጎቻቸው ውስጥ እንዲሠሩ ያልፈቀዱ ሕዝቦች ያጋጠሟቸው መቅሠፍት፥ የፍርድ መዛባት፥ ጉቦኝነት፥ ጦርነትና የመሳሰሉት ነገሮች ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ በኢትዮጵያ እውነት መሆኑን እንዴት አየህ?

በመጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ ሁለት ዋና ዋና የእግዚአብሔር ሥዕላዊ ሁኔታ እናያለን። የመጀመሪያው፥ የእግዚአብሔር የሥነ – ሥርዓት እርምጃ ነው። ሕዝቡ በኃጢአት በሚወድቁበት ጊዜ እግዚአብሔር አስቸጋሪ ነገሮችን ወደ ሕይወታቸው በማምጣት ሥነ ሥርዓትን (ዲስፕሊንን) ያስተምራቸው ነበር። የእግዚአብሔር ፍላጎት ሊያጠፋቸው አልነበረም፤ ነገር ግን ሕዝቡ ከኃጢአት እንዲርቁና እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ለሕዝቡ ሁሉ የሚጠቅም ኑሮ እንዲኖሩ ነበር፤ (ዕብ. 12፡4-11 ተመልከት)።

በሁለተኛ ደረጃ በምሕረት የተሞላውን የታጋሹን የእግዚአብሔር ሥዕላዊ ሁኔታ እናያለን። እግዚአብሔር ሕዝቡ በሚተዉት ጊዜ በጽድቅ በመፍረድ ወዲያውኑ ሊቀጣቸው ይችል ነበር። ይህንንም ቢያደርግ ፍጹም ትክክል ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ለብዙ መቶ ዓመታት በትዕግሥት በመሥራት ይቅርታውንና በሕይወታቸው ላይ የሚደርሰውን ችግር ልባቸውን ወደ እርሱ ለመመለስ ይጠቀሙበት ዘንድ ሞክሮ ነበር። እግዚአብሔር ሕዝቡ ታማኝ ባልሆኑበት ጊዜ እንኳ ለእነርሱ ታማኝ ነበር። ወደ እርሱ በጮኹ ጊዜ ጸሎታቸውን በመመለስ፥ እነርሱን ከባርነት ነፃ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ያደርግ ነበር። እግዚአብሔር በምሕረቱ ነቢያትን እየላከ ያስጠነቅቃቸውና ለማውጣት መሳፍንትን ያስነሣላቸው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር በአሁኑ ዘመንም ምሕረቱንና ትዕግሥቱን እያሳየን ያለው እንዴት ነው? ለ) የእግዚአብሔር ምሕረት በሕይወትህ የታየው እንዴት ነው? ሐ) ለአንተ ስላለው ትዕግሥት፥ ምሕረትና ጸጋ እግዚአብሔርን አመስግነው። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመጽሐፈ መሳፍንት መግቢያ

የመጽሐፈ ኢያሱ ታሪክ የደስታና የድል ታሪክ ነው። የእግዚአብሔር ሰዎች በእርሱ ርዳታ በቃል ኪዳኑ ተስፋ መሠረት ጠላቶቻቸውን አሸንፈው የከነዓንን ምድር ወርሰዋል። እስራኤላውያን በእነርሱና በእግዚአብሔር መካከል ለተገባው ቃል ኪዳን ለመታዘዝ የሰጡትን ቃል እንደገና አደሱ። የሚገርመው ግን የዚህ ሕዝብ ታሪክ በድል አልተደመደመም። ታሪኩ በመጽሐፈ መሳፍንት ይቀጥላል።

የመጽሐፈ መሳፍንት ታሪክ የኃዘንና የሽንፈት ታሪክ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ ለእርሱ ለመታዘዝ እምቢ አሉ። ቃል ኪዳኑንም አላከበሩም፤ ስለዚህ ለቃል ኪዳኑ መታዘዝ እንዳለባቸው ለማስተማር እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው እንዲሸነፉ ፈቀደ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማስተማርና ለማስጠንቀቅ ችግርንና ሽንፈትን በመሣሪያነት ተጠቀመ። ይህም ሆኖ ግን ሕዝቡ ለእግዚአብሔር መታዘዝን አልተማሩም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የእግዚአብሔር ሕዝብ እግዚአብሔርን ለማክበርና ለእርሱም ለመታዘዝ የገቡትን ቃል ለመጠበቅ የሚከብዳቸው ለምንድን ነው? ለ) ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች ለኢየሱስ ያላቸውን የመጀመሪያ ፍቅራቸውን የሚተዉትና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እየቀዘቀዙ የሚሄዱት ለምንድን ነው? ) ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅርና መታዘዝ ሕያውና ጠንካራ አድርገው እንዲጠብቁ ቤተ ክርስቲያን ምን ማድረግ ትችላለች

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ መጽሐፈ መሳፍንት በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ አንብብ። ሀ) ጸሐፊው ማን ነው? ለ) የመጽሐፉ ዓላማ ምንድን ነው? ሐ) የመጽሐፉ አስተዋጽኦስ ምንድን ነው? 

የመጽሐፈ መሳፍንት ርእስ

የዚህ መጽሐፍ ርእስ የተገኘው ከኢያሱ ሞት ጀምሮ እስከ መጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ እስከ ሳኦል ድረስ የነበሩ ጊዜያዊ የአገሪቱ መሪዎች በነበሩ ሰዎች የሥልጣን ስም ነው። እነዚህ መሪዎች መሳፍንት (ፈራጆች) ተብለው የሚጠሩ ሲሆን፥ ከአስተዳዳሪነት ወይም ከፈራጅነት ይልቅ ሥራቸው ወደ ጦር መሪነት ያደላ ነበር። ለእስራኤላውያን ነፃነትን ለማምጣት እግዚአብሔር በግል የሚመርጣቸውና ኃይልን የሚያስታጥቃቸው ሰዎች ነበሩ። መሳፍንት የእስራኤልን ሕዝብ ከሚያስጨንቁአቸው ጠላቶቻቸው ነፃ ካወጡዋቸው በኋላ በነገዶቻቸው ላይ መጠነኛ የሆነ ሥልጣን ይኖራቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ መሳፍንት ወይም ነፃ አውጪዎች በበርካታ ነገዶች ላይ ሥልጣን የነበራቸው ቢሆንም፥ ብዙ ጊዜ ግን በተወሰኑ ነዶች ላይ ብቻ ሥልጣን የነበራቸው የአካባቢ መሪዎች ነበሩ።

እግዚአብሔር በሕዝቡ ሁሉ ላይ ገዥ የሚሆን መሪን ያላስነሣው ሆን ብሎ ነበር፤ ይኸውም እግዚአብሔር ራሱ ንጉሣቸው ነበርና ነው (መሳ. 8፡23)። የተለያዩት ነገዶች በእግዚአብሔር የሚገዙና በቃል ኪዳኑ ውስጥ የሚገኙ ሕግጋትን በመታዘዝ ሊኖሩ ይገባ ነበር። እግዚአብሔር ንጉሣቸው ስለነበር ንጉሥ አያስፈልጋቸውም ነበር። በኋላ በመጽሐፈ ሳሙኤል ውስጥ እንደምንመለከተው፥ እስራኤላውያን እንደ አሕዛብ ንጉሥ እንዲኖራቸው በጠየቁ ጊዜ ድርጊታቸው በእግዚአብሔር ላይ እንደሚፈጸም ዓመፅ ተቆጥሮባቸው ነበር (1ኛ ሳሙ. 8፡5-8)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ከእግዚአብሔርና ከመንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ከሚኖረን ግንኙነት ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) የሚለየውስ እንዴት ነው?

የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ 

የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ ማን እንደሆነና እነዚህ የተለያዩ ተግባራትን አሰባስቦ በአንድ ላይ ያቀናበራቸው ማን እንደሆነ የሚያመለክት ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። ዓለማውያን ምሁራን መጽሐፉ የተጻፈበትን ጊዜ በማዘግየት በዚህ መልክ የጻፈው ኦሪት ዘዳግምን የጻፈውና ከኢያሱ እስከ 2ኛ ነገሥት ያለውን የታሪክ ዘገባ ያቀናበረው ሰው ነው ይላሉ። ሆኖም ለዚህ ሁሉ አንዳችም ማረጋገጫ የለም።

አይሁድ ጸሐፊው ሳሙኤል ነው ብለው ያምናሉ። ይሁን እንጂ ይህን በሚመለከት ማረጋገጫ የለንም። በዘመነ መሳፍንት የተለያዩ መሳፍንትን በሚመለከት አጫጭር ታሪኮች ሳይጻፉ አልቀሩም። በኋላ አንድ ጸሐፊ፥ ምናልባትም ሳሙኤል እነዚህን ታሪኮች ሰብስቦ በአንድ መጽሐፍ አቀነባብሮአቸው ይሆናል። 1ኛ ዜና 29፡29 እንደሚናገረው ሳሙኤል፥ ናታንና ጋድ የተባሉት ነቢያት የተለያዩ ታሪኮችን ዘግበዋል። ከብሉይ ኪዳን ጥናት እንደምንረዳው በዚሁ ጊዜ የተጻፉ ሌሎች መጻሕፍትም ነበሩ። ለምሳሌ፥ የያሻር መጽሐፍ (ኢያሱ 10፡13)፥ የእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ (2ኛ ነገ. 15፡31) እና የይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ (2ኛ ነገ. 16፡19) ይገኛሉ። እንደዚሁም በመሳፍንት መጻሕፍት ውስጥ ንጉሥ አልነበረም የሚለው ቃል ተደጋግሞ መጠቀስ የሚያመለክተን መጽሐፈ መሳፍንት ተቀናብሮ በተጻፈበት ጊዜ በእርግጥም በእስራኤል ላይ የነገሡ ነገሥታት መኖራቸው ነው።

መጽሐፈ መሳፍንትን ማን እንደጻፈው ለመናገር አስቸጋሪ ቢሆንም የተጻፈው ግን በ1000 ዓ.ዓ. ገደማ በዳዊት ዘመን እንደነበር መገመት ይቻላል። የመጽሐፈ መሳፍንት ታሪካዊ ሥረ – መሠረት ባለፈው ሳምነት የጸለስጢና ምድር የተለያዩ ትላልቅ መንግሥታት የጦርነት ሜዳ እንደነበረች ተመልክተናል። የከነዓን ምድር ከእነዚህ ትላልቅ መንግሥታት ጋር ከሚተባበሩ ከተለያዩ የከተማ መንግሥታት የተዋቀረች ነበረች። በደቡብ በኩል የሚገኘው ትልቁ መንግሥት ግብፅ ነበር። በሰሜን በኩል በኢያሱና በመሳፍንት ዘመን የነበረው ትልቅ መንግሥት የኬጢያውያን መንግሥት ነበር። እነዚህ ትላልቅ መንግሥታት በጳለስጢና ውስጥ ብዙ ጊዜ ጦርነት ይገጥሙ የነበሩ ቢሆንም፥ ይህ ጦርነት እስራኤላውያንን በከፍተኛ ሁኔታ መንካቱ አጠራጣሪ ነው። እስራኤላውያን የሚኖሩት በተራራማዎቹ ስፍራዎች ነበር እንጂ ከዋናዎቹ የንግድ መተላለፊያዎች አጠገብ አልነበረም። በአብዛኛው መሳፍንት ግብፃውያንም ሆኑ ኬጢያውያን አንዱ ሌላውን ለማሸነፍ አልቻሉም ነበር፤ ስለዚህ ከነዓን በየትኛውም መንግሥት ቀጥተኛ በበላይ ተቆጣጣሪነት ሥር አልነበረችም። በዚህም ምክንያት ብዙ ትናንሽ መንግሥታት ከነዓንን ለመቆጣጠር ወይም ለመውረርና አደጋ ለመጣል ይሞክሩ ነበር። ይህ በከነዓን ምድር ላይ የተደረገ ጦርነት በውጤቱ የተለያዩ ሕዝቦች እስራኤላውያንን ለመቆጣጠርና ለመግዛት እንደቻሉ በሚያንፀባርቅ መንገድ በመጽሐፈ መሳፍንት ተገልጧል። ከኢያሱ ሞት ጀምሮ ሳኦል እስከ ነገሠበት ጊዜ ድረስ የነበረው ሁኔታ የተለያዩ መንግሥታት እስራኤልን ያጠቁበትና የጨቆኑበት ዘመን ነበር። በእነዚህ ዓመታት ነበር የባሕር ሕዝቦች ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ፍልስጥኤማውያን በመባል የሚታወቁ አዲስ ነገዶች ወደ ከነዓን የባሕር ዳርቻ ተሰደው የመጡት። ወዲያውኑ አብዛኛውን የከነዓንን ምድር ተቆጣጠሩና ለብዙ ዓመታት የአይሁድ ሕዝብ ዋና ጠላት ሆኑ።

የእስራኤል ሕዝብ የተለያዩ ነገዶች በየራሳቸው ክልል መኖር ከጀመሩ ወዲህ የሕዝቡ አንድነት እየቀነሰ መጣ። በአንድነት እንዲቆዩ የሚያደርግ እንደ ሙሴ ወይም እንደ ኢያሱ ያለ ጠንካራ መሪ አልተገኘም፤ ስለዚህ ጎሰኝነት ወይም የዘር ልዩነት እየጠነከረ መጣና ነገዶቹ በየራሳቸው ሽማግሌዎች ወይም የነገድ አለቆች መተዳደር ጀመሩ። 12ቱን ነገዶች እጅግ በላላ መንገድ (ፈዴራላዊ አስተዳደር) እንዲቆዩ ያደረጉ ሁለት ነገሮች ነበሩ። የመጀመሪያው፥ ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት የጋራ የሆነ አምልኮአቸው ነበር። የከነዓናውያንን አማልክት ሳይሆን እግዚአብሔርን እስካመለኩ ድረስ የተባበሩ ነበሩ። የእውነተኛውን አምላክ አምልኮ በሚተዉበት ጊዜ የጋራ የሆነ ሃይማኖት አይኖራቸውም ነበር። ሁለተኛው፥ ሁሉም የያዕቆብ ልጆች መሆናቸውና ይኸውም የጋራ ውርስ መያዛቸው ነበር፤ ስለሆነም አንድ ነገድ በውጫዊ ጠላት በሚጠቃበት ጊዜ ሌሎቹ ነገዶች ለእርዳታ መድረሳቸው የተለመደ ነበር፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ይህንን አንድነት በሚረሱበት ጊዜ በ12ቱ ነገዶች መካከል የሚደረግ ጦርነትም የተለመደ ነበር።

የመጽሐፈ መሳፍንት ጸሐፊ ስለ ዘመነ መሳፍንት ዝርዝር የሆነ መግለጫ የመስጠት አሳብ አልነበረውም። ለምሳሌ፡- በግብፃውያንና በኬጢያውያን መካከል ስለተደረገ ጦርነት የሚጠቅሰው አንዳችም ነገር የለም። የጸሐፊው ዋና አሳብ በዚህ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን ላይ ለደረሰው ከፍተኛ ችግር የሥነ – መለኮታዊ ትምህርት ትንተና መስጠት ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ትኩረት በቀድሞ ዘመናት ሁኔታ ላይ ሰፊ ገለጻ መስጠት ሳይሆን የአይሁድ መጨቆን ለምን እንደሆነ መናገር ነበር። 

የዘመነ መሳፍንት የጊዜ ቅደም ተከተል

የመጽሐፈ መሳፍትን የጊዜ ቅደም ተከተልን በተመለከተ ብዙ ክርክርና ጥርጣሬ አለ። ይህም በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው፥ የእስራኤል ሕዝብ ነፃ የወጡበትና ከነዓንን የወረሱበት ጊዜ ጉዳይ በሊቃውንቱ ዘንድ አከራካሪ መሆኑ ነው። ይህ ነገር የሆነው በ15ኛው ክፍለ ዘመን (1400 ዓ.ዓ.)? ነው ወይስ በ13ኛው ክፍል ዘመን (በ1280 ዓ.ዓ.)? ወግ አጥባቂ የሆኑ ምሁራን፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መረጃ የሚስማማው ለ15ኛው ክፍለ ዘመን ቀረብ ላለው ጊዜ ነው ወደ ማለት ያዘነብላሉ።

ሁለተኛው ጥያቄ፥ መሳፍንት የገዙት በአንድ ጊዜ ነው ወይስ በተከታታይ? የሚለው ነው። እያንዳንዱ መስፍን የገዛበትን ጊዜ በተናጠል ወስደን ከደመርነው አጠቃላዩ 410 ዓመታት ይመጣል። ሁሉም ምሁራን እንደሚስማሙበት ከሆነ ይህ ጊዜ ለዘመነ መሳፍንት እጅግ ብዙ ነው፤ ስለዚህ እነዚህ የመሳፍንትን ዘመን የምናይባቸው ሁለት አማራጮች አሉን። የመጀመሪያው፥ የእስራኤል ሕዝብ የወጡበትና ሰዎች ማስታወስ ይችሉ ዘንድ ቀላል ለማድረግ የተሰጠ አጠቃላይ ጊዜ ተደርጎ የተሰጠ ነው የሚል ሲሆን፥ ሁለተኛው ግን፥ አንዳንዶቹ መሳፍንት ሌሎቹ መሳፍንት በሌላ ስፍራ በገዙበት ጊዜ የነበሩ የአንድ የተወሰነ ክልል ገዥዎች ነበሩ የሚል ነው። ለምሳሌ፡- ሶሜጋር፥ ቶላ፥ ኦጢር፥ ኢብሃን፥ ኤሉንና አብዶን ሌሎች መሳፍንት በሚገዙበት ጊዜ የተነሡ የአንድ ክልል መሪዎች ነበሩ፤ ስለዚህ የመሳፍንት የጊዜ ቅደም ተከተል በቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ካለው የጊዜ ቅደም ተከተል ጋር የሚስማማ ነው።

ዘመነ መሳፍንት ከ (1380-1050) ዓ.ዓ. ድረስ 300 ዓመታት ያህል የፈጀ ሳይሆን አይቀርም።

ቀጥሎ ለዘመነ መሳፍንት የተሰጠ የጊዜ ቅደም ተከተል እናገኛለን፡፡ 

1, ኢያሱ 1406-1376 ዓ.ዓ. 

 1. የሽማግሌዎች አገዛዝ 1376-1366 ዓ.ዓ
 2. የመስጴጦምያ የጭቆና ዘመን 1366-1358 ዓ.ዓ. 
 3. የጎቶንያል አገዛዝ የ40 ዓመት ሰላም 1358-1318 ዓ.ዓ. 
 4. በሞዓብ የመጨቆን ዘመን 1318-1301 ዓ.ዓ. 
 5. የናዖድ አገዛዝና የ80 ዓመት ሰላም 1301-1221 ዓ.ዓ. 
 6. በከነዓናውያን የመጨቆን ዘመን 1221-1201 ዓ.ዓ. 
 7. የዲቦራና የባርቅ አገዛዝ የ40 ዓመት ሰላም 1201-1161 ዓ.ዓ.
 8. በምድያን የመጨቆን ዘመን 1161-1154 ዓ.ዓ. 
 9. የጌዴዎን አገዛዝና የ40 ዓመት ሰላም 1154-1114 ዓ.ዓ. 
 10. የአቤሜሌክ- የ3 ዓመታት ንጉሥ 1114-1111 ዓ.ዓ. 
 11. የዮፍታሔ አገዛዝ -6 ዓመት 1111-1105 ዓ.ዓ.

      የሶምሶን አገዛዝ – 20 ዓመት 

 1. የዔሊ አገዛዝ 1066-1046 ዓ.ዓ. 
 2. የሳሙኤል አገዛዝ 1046-1026 ዓ.ዓ. 
 3. የሳኦል አገዛዝ 1026-1011 ዓ.ዓ. 

** እነዚህ ጊዜያት በጣም ያልተረጋገጡ እንደሆኑና የተለያዩ ምሁራን መሳፍንት የገዙበት ዘመን ብለው የሚሰጡት ጊዜ የተለያየ መሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው።

የመጽሐፈ መሳፍንት አወቃቀርና አስተዋጽኦ 

መጽሐፈ መሳፍንት ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት፡-

 1. የዘመነ መሳፍንት መግቢያ (1፡1-3፡6)
 2. የገዙ የተለያዩ መሳፍንት (3፡7-16፡31)
 3. የዘመነ መሳፍንት አጠቃላይ የሥነ – ምግባር ባሕርያት (17-21)

የሚከተለው ጠለቅ ተደርጎ የተዘረዘረ የመጽሐፈ መሳፍንት አስተዋጽኦ ነው፡-

 1. የመጽሐፈ መሳፍንት መግቢያ(1፡1-3፡6)

ሀ. የእስራኤላውያን ከነዓናውያንን የማስወጣት ተግባራቸውን በሚገባ አለማከናወን (1፡1-2፡5) 

ለ. የእስራኤል የክሕደት ዑደት መግቢያ (2፡6-3፡6) 

 1. ስድስቱ የእስራኤላውያን የክሕደት ዑደቶች «የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደገና ክፉ ሥራ ሠሩ» (3፡7-16፡31)። 

ሀ. ጎቶንያል (3፡7-11) 

ለ. ናዖድ (3፡12-31) 

ሐ. ዲቦራና ባርቅ (4-5) 

መ. ጌዴዎን (6-8)

1)አቤሜሌክ (9)

2) ቶላዕና ኢያዕር (10፡1-5) 

ሠ. ዮፍታሔ (10፡6-12፡7)

1) ኢብጻን (12፡8-10) 

2) ኤሎም (12፡11-12)

3) ዓብዶን (12፡13-15) 

ረ. ሶምሶን (13-16) 

 1. እስራኤላውያን በዘመነ መሳፍንት ያሳዩት የሥዓ-ምግባር ብልሹነት፡- «ሰውም ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር» (17-21)። 

ሀ. የዳን ነገድ ታሪክ (17-18) 

ለ. የብንያም ነገድ ታሪክ (19-21) 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)