መክብብ 7-12

በሕይወት ውስጥ ሌሎች የሚሰጡንን ቀላል መልሶች ከመቀበል ይልቅ አስቸጋሪ የሆኑ ጉዳዮችን ማሰብ እጅግ አስፈላጊ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ። መጽሐፈ መክብብ አስቸጋሪ የሆኑ ጉዳዮችን ያነሣል። ጸሐፊው የሚያስተምረውን ነገር ለመረዳት በጥንቃቄ የተሞላ ጥናት ይጠይቃል። ግልጽ መልሶች ስለሌላቸው ጉዳዮች በጥልቀት ለማሰብ ፈቃደኞች ካልሆንን በስተቀር እምነታችንና መረዳታችን ሁል ጊዜ የላላ ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰዎች ቀላል መልሶች የሚሰጡባቸውን፥ በጣም የተወሳሰቡና በጥልቀት ማሰብ የሚጠይቁ ጉዳዮችን ዘርዝር። ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ በመመራትና በጥንቃቄ በማሰብ፥ የተወሳሰቡ ጉዳዮችን በመቀበልና ጥሩ መልሶችን በመስጠት ችሎታቸው የታወቁትን ኢትዮጵያውያን ጥቀስ። ሐ) እንደ መጽሐፈ መክብብ ጸሐፊ በጥልቀት ለማሰብ የሚፈልጉ ሰዎች እጅግ ጥቂት የሆኑት ለምንድን ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ መክብብ 7-12 አንብብ። ሀ) ጸሐፊው «ከንቱ» የሚላቸውን ነገሮች ዘርዝር። ለ) ጸሐፊው እነዚህ ነገሮች ከንቱዎች እንደሆኑ የሚናገረው ለምንድን ነው? ሐ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ፥ ከእግዚአብሔር ጋር በሚደረግ ግንኙነት ለሕይወት ትርጒም ማግኘት እንደሚቻል ለማንጸባረቅ፥ ጸሐፊው ስለ እግዚአብሔር የሚናገራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

1. መክብብ 7 የሰዎችን የተለመደ አስተሳሰብ የሚቃወሙ የአጫጭር ምሳሌዎች ስብስብ ነው። ሰዎች፡- ከሞት ቀን የልደት ቀን፥ ኃዘን ካለበት የቀብር ሥርዓት ላይ ከመገኘት ደስታ ባለበት በጋብቻ በዓል ላይ መገኘት ይሻላል ይላሉ። ጸሐፊው ግን ይህንን አሳብ ይቃረናል። ምናልባት ይህ የሆነው፥ በደስታ ከምንፈነጥዝበትና በሳቅ ከምናወካበት ጊዜ ይልቅ ወደ ሞት ስንጠጋ በይበልጥ ስለ ሕይወትና እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ መንገድ ስለ መጓዝ ስለምናስብ ይሆናል። ምንም እንኳ ሐሤት በምናደርግበት ጊዜ ደስ መሰኘት ቢኖርብንም፥ እግዚአብሔር ያስተምረን ዘንድ ክፉ ጊዜያትንም እንደሚሰጠን ማስታወስ ያስፈልጋል (መክብብ 7፡1-14)። 

2. ሕይወት ሚዛናዊና ቅን ፍርድ የሚገኝባት አይደለችም። ጻድቅ ዕድሜ ሳይጠግብ ይሞታል፤ ኃጢአተኛ ሰው ግን በክፋቱ እየቀጠለ፥ ረጅም ዕድሜ ይኖራል (መክብብ 7፡15)። ጻድቃን ብዙ ጊዜ ይቀጣሉ፤ ኃጢአተኞች ግን ቅጣት ሳያገኛቸው ይኖራሉ (መክብብ 8፡14)። 

3. ትምህርት ማብቂያ የለውም ጥበብንም ሁሉ ማወቅ አይቻልም። በኃጢአት ወጥመድ ውስጥ ከመውደቅ ይጠብቀን ዘንድ ጥበብ ያስፈልገናል (መክብብ 7፡19-8፡1)። 

4. የሰው ልብ በኃጢአትና በክፋት የተሞላ ነው (መክብብ 7፡20፤ 9፡3)።

5. ሞት የሀብታምና የድሀ፥ የመሪዎችና የተራ ሰዎች፥ በአጠቃላይም የሰው ልጅ ሁሉ መጨረሻ ነው፤ ዳሩ ግን በሕይወት ዘመንህ ሳለህ ደስ ይበልህ። እግዚአብሔር በሰጠህ ሚስት ደስ ይበልህ። በሥራህ ደስ ይበልህ፤ ሥራህንም በሙሉ ኃይልህ ሥራ። ሞት ይህንን ሁሉ ወደ ፍጻሜ እንደሚያመጣ በማስተዋል ኑር (መክብብ 9፡1-10)። 

6. ጥበብ ከሀብት ይበልጣል (መክብብ 9፡13-11፡6)። ጥበብ ሰውን ከጕዳት በመጠበቅ ረጅም ዕድሜን ያጐናጽፈዋል።

ደግሞም ጸሐፊው የሕይወትን ከንቱነት በማሳየት እግዚአብሔርን በሕይወት ዘመን ሁሉ ከማስታወስ አስፈላጊነት ጋር አወዳድሮ ሚዛናዊ ያደርገዋል። የሚከተሉትን አስተውል፡-

1. ጸሐፊው በሃይማኖት ስም ተገቢ ያልሆነ ቅንዓት እንደማያስፈልግ፥ ይልቁንም የሃይማኖትን ቅንዓት ከተግባራዊ ጥበብ ጋር ሚዛናዊ ማድረግ እንደሚገባ ይመክራል (መክብብ 7፡15-18)። በሌላ አባባል ሚዛናዊነት አትጣ ማለት ነው። የማይገባ የሃይማኖት ቅንዓት ከሌሉች ጋር ላለህ ግንኙነት ዕንቅፋት እንዲሆን ወይም በራስህ ላይ የማያስፈልግ ስደት እንዲያስከትል አታድርግ። 

የውይይት ጥያቄ፥ የማያስፈልግ የሃይማኖት ቅንዓት በሰው ላይ የሚያመጣቸው ተገቢ ያልሆኑ ችግሮች ምንድን ናቸው?

2. ወጣቶች በሕይወት ጣጣዎች ሊጐብጡ አይገባም። ነገር ግን መደሰት ያስፈልጋቸዋል። ዳሩ ግን በሕይወታቸው የሚያደርጉትን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንደሚያመጣው ሁልጊዜ ሊያስታውሱ ይገባል (መክብብ 11፡7-10፤ 12፡14)። 

3. ሰው እስከ ሽምግልና ዕድሜው ድረስ በመጠበቅ እግዚአብሔርን ሊያስብና እርሱን ሊያከብር ከመሞከር ይልቅ በወጣትነት ዕድሜው ሊያደርገው ይገባል። ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ለእግዚአብሔር ልንሠራ የምንችልበት ኃይላችን የሚከዳበት ጊዜ ይመጣል። ያኔ ለእግዚአብሔር ለመሥራት ጊዜው እጅግ እንደዘገየ እንረዳለን (መክብብ 12፡1-7)። 

4. ለሕይወት መሠረታዊውና ትርጒም የሚሰጠው ነገር ራስን ለእግዚአብሔር ማስገዛት ወይም እግዚአብሔርን በመፍራትና ትእዛዛቱን በመጠበቅ መኖር ነው (መክብብ 12፡13)፤ እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረበት ምክንያት ይህ ነው። ሕይወት ከንቱና ተስፋ አስቆራጭ በሆነ ነገር የተሞላች ብትመስልም በፈሪሀ-እግዚአብሔር በመኖር ደስታና እርካታ ለማግኘት ይቻላል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህን የመጽሐፈ መክብብ ምዕራፎች በመጠቀም፥ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉትን ወጣቶች እንዴት ትመክራቸዋለህ? ለ) በሕይወታቸው መጨረሻ፥ ጊዚያቸውን በከንቱ እንዳጠፉ እንዳይሰማቸው ማስታወስ የሚገባቸውን እጅግ አስፈላጊ ነገሮች ጥቀስ። ሐ) መጽሐፍ መክብብን በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችንና ነጋዴዎችን የምታስተምርባቸውን መንገዶች ዐቅድ። መ) ከዚህ መጽሐፍ ውስጥ ልታስተምራቸው የምትፈልጋቸውን እጅግ ጠቃሚ እውነቶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መክብብ 1-6

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች በተለይም ወጣቶች፡- ሀብታም፥ የተማረ፥ ጥሩ ኑሮ የሚኖርና ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ሰው ለመሆን የሚፈልጉት ለምንድን ነው? ለ) ይህ መልካም ነውን? መልስህን አብራራ። ሐ) ለእነዚህ ነገሮች ያለው አመለካከት ሚዛናዊነት ለጐደለውና ያለ እግዚአብሔር ከንቱና እርባናቢስ መሆናቸውን ላልተገነዘበው ሰው እንዴት ትመክረዋለህ? 

የውይይት ጥያቄ፥ መክብብ 1-6 አንብብ። ሀ) የመጽሐፈ መክብብ ጸሐፊ «ከንቱ» የሚላቸውን ነገሮች ዘርዝር። ለ) ጸሐፊው እነዚህ ነገሮች ከንቱ ናቸው የሚለው ለምንድን ነው? ሐ) ከእግዚአብሔር ጋር በሚደረግ ግንኙነት ሕይወት ትርጒም እንደምታገኝ ለማንጸባረቅ ጸሐፊው በእነዚህ ምዕራፎች ስለ እግዚአብሔር የሚናገረው ነገር ምንድን ነው?

1. አጠቃላይ አሳብ፡- ሕይወት ሁሉ ከንቱ ነው (1፡1-11)።

ጸሐፊው ከእግዚአብሔር የተለየን ሕይወት ሲመለከት ከንቱ ነው ከማለት በቀር ምንም ለመናገር አልቻለም። ሰው በከፍተኛ ድካም ይሠራል፤ ከዚያም ይሞታል። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሰዎች ይሞታሉ፤ ስማቸውን እንኳ የሚያስታውስ የለም። ሕይወት የከንቱ ድግግሞሽ የማያቋርጥ ዑደት ይመስላል። 

2. የዓለም ጥበብ ከንቱ ነው (መክብብ 2፡12-18)። ጸሐፊው ጥበብን ለመመርመር የተቻለውን ያህል ጥረት አድርጓል፤ ነገር ግን በተመራመረ ቊጥር፥ በምድር ላይ የሚያየው ነገር የበለጠ እያሳዘነው ሄደ። ጥበብ ከአላዋቂነት የሚሻል ቢሆንም፥ በመጨረሻ ግን ጥበበኛውም ሆነ ሞኙ ይሞታሉ። ከሞቱ በኋላ ሁለቱም ይረሳሉ፤ ስለዚህ አንዱ ከሌላው አይሻልም። 

3. ዓለማዊ ደስታ ከንቱ ነው፤ (መክብብ 2፡1-11)። ለመሆኑ ሳቅና ደስታ ምን ትርጕም አላቸው? ጸሐፊው ብዙ ወይን በመጠጣትና በመሳቅ በሕይወት ደስ ለመሰኘት ሞክሯል። በተጨማሪ ታላላቅ ሕንጻዎችን ከገነባ፥ መዝናኛዎችን ካቋቋመ። በርካታ አገልጋዮችና ቁሳቁስ ካለው፥ ደስተኛ እንደሚሆን አስቦ ነበር፤ ዳሩ ግን ከእነዚህ ነገሮች አንዳቸውም እውነተኛ ደስታን ወይም የሕይወት ዓላማ ሊያስጨብጡት አልቻሉም፤ ከንቱዎች ነበሩና። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሀብት አንድን ሰው ደስተኛ የሚያደርገው ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ለ) መልስህን የሚደግፉ ምስሌዎችን ከሰዎች ሕይወት ስጥ።

4. በትጋት መሥራት እርካታን አያስገኝም (መክብብ 2፡17-23)። ሰው እጅግ ጠንክሮና ተግቶ ሊሠራ ይችላል፤ በሚሞትበት ጊዜ ግን የድካሙ ፍሬ ሁሉ ለሌሎች ይሆናል። በዚያን ጊዜ የደከመበትን ነገር ሁሉ ስለሚያጣ በድካሙ ሁሉ ላይ የበላይ ተቆጣጣሪ ሊሆን አይችልም። ሞኝ ሰው የደከመበትን ሁሉ ሊያጠፋና ሊያበላሽ ይችላል፤ ስለዚህ ብዙ ሀብት ለማግኘት ጠንክሮና ተግቶ መሥራቱ ከንቱ ነው። ሰው ልክ እንደ እንስሳት ሞቶ ወደ ዐፈርና ወደ ትቢያ መመለሱ ስለማይቀር ከእንስሳት አይሻልም። 

5. ሕይወት በፍትሐዊነት የተሞላች ናት (መክብብ 5፡8-9)። በምድራዊ መንግሥታት ዘንድ ብዙ ጊዜ የፍርድ መዛባትን እናያለን። በምድር ላይ በክፋትና በኃጢአት ከመኖር ይልቅ የዚህ ዓይነቱን ክፋትና ኃጢአት ላለማየትና ላለመልመድ አለመወለድ ይሻል ነበር (መክብብ 2፡16፤ 4፡1-3)። በመንግሥት አመራር ውስጥ የተለያየ ደረጃ ባላቸው ሰዎች ዘንድ ራስ ወዳድነትን አስከትሏል። ባላቸው ሥልጣንና ሀብት ከቶ ስለማይረኩ ያለማቋረጥ ባላቸው ነገር ላይ ለመጨመር ይፈልጋሉ፤ ስለዚህም የበታቾቻቸውን ይጨቁናሉ። 

6. ሰዎች፥ ሀብት ደስታን ያስገኛል ብለው ቢያስቡም፥ ፍጹም አያስገኝላቸውም (መክብብ 5፡10-6፡12)። ሀብት ያላቸው ሰዎች ነጋ ጠባ በያዙት ላይ ለመጨመር ይጥራሉ እንጂ በፍጹም አይረኩም። ሰው በርካታ ሀብትና ቁሳቁስ ሲኖረው ሌቦች ይሰርቁብኛል ብሉ ይጨነቃል። ዳሩ ግን ሰው በሚሞትበት ጊዜ ሀብቱን ይዞ ሊሄድ አይችልም። ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ሰው ባለው ቢደሰት ይሻላል፡፡ ሰዎች ከሚፈልጓቸው ከንቱ ነገሮች በተቃራኒ፥ ጸሐፊው እውነተኛ ደስታና እርካታ የሚሰጡትን ነገሮች አመልክቷል። አንድ ሰው በሕይወቱ ትርጕም ያለው ኑሮ ሊኖር የሚችለው ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ሲኖረው ብቻ ነው። ጸሐፊው የሚሰጠውን የሚከተለውን ምክር አስተውል፡- 

1. ሰው ሕይወትን የተቀበለው ከእግዚአብሔር እጅ መሆኑን በመገንዘብ ደስ ሊለው ይገባል (መክብብ 2፡24)። እግዚአብሔር በሰው ልብ ውስጥ ዘላለማዊ አምላክ ከሆነው ከእርሱ ጋር ኅብረት የማድረግን ፍላጎት ወይም «ዘላለማዊነትን» ሰጠው። ሙላትና እርካታ ሊኖር የሚችለው በዚያ ግንኙነት ውስጥ ብቻ ነው (መክብብ 3፡1-14)። ሁልጊዜ የተሻለና የበለጠ ነገር ከመፈለግ ይልቅ እግዚአብሔር በሰጠን ነገር መመራትና መርካት አስፈላጊ ነው (መክብብ 5፡18-20)። 

2. እግዚአብሔር እውነተኛ ጥበብን የሚሰጠው፥ ሰው ከእርሱ ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ሲኖረው ብቻ ነው (መክብብ 2፡26)። 

3. ሰው በፈራጁ በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ መሆኑን ማስታወስ አለበት (መክብብ 3፡15)። 

4. ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን፥ ልባዊና በተግባርም የሚገለጥ መሆን አለበት (መክብብ 5፡1-7)። ሰው ወደ እግዚአብሔር ፊት መምጣት ያለበት መሥዋዕቶች በሚቀርቡበት ባዶ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ወይም በበርካታ ከንቱ ቃላት ሳይሆን፥ እርሱ የሚለውን በፍርሃትና በአክብሮት ለመስማት መሆን አለበት። ለእግዚአብሔር የሚነገሩ ቃላት ከእውነተኛ ልብ የመነጩ መሆን አለባቸው። በእግዚአብሔር ፊት የምናደርጋቸው ስእለቶች የቱንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍሉንም እንኳ መጠበቅ አለባቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ወጣት ክርስቲያኖች በሰው ሕይወት ውስጥ ከፍተኛና ከሁሉ የላቁ ነገሮች፡- ትምህርት (ጥበብ)፥ ሀብት፥ ቁሳዊ ነገሮች፥ ወዘተ. እንደሆነ በማሰብ በአጉል ወጥመድ ሊጠመዱ የሚችሉባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ከሌለው፥ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከንቱ መሆናቸውን እነዚህ ምዕራፎች የሚያሳዩት እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመጽሐፈ መክብብ ዓላማ እና ዋና ዋና ትምሕርቶች

የመጽሐፈ መክብብ ዓላማ

የምናጠናው የጥበብ መጻሕፍት በመባል የሚታወቁትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደሆነ ታስታውሳለህ። መጽሐፈ መክብብ ከጥበብ መጻሕፍት አንዱ ነው። የመጀመሪያው፥ የጥበብ መጽሐፍ የሆነው መጽሐፈ ኢዮብ ጻድቅ ለምን መከራ ይቀበላል? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ይሞክራል። መዝሙረ ዳዊት እግዚአብሔርን በማምለክ የሚገኘውን የጥበብ መሠረት ሲሰጠን፥ መጽሐፈ ምሳሌ ደግሞ በሕይወታችን እንዴት መኖር እንዳለብን የሚያሳዩ ተግባራዊ መልሶች በማቅረብ የጥበብን መሠረት ይሰጠናል። መጽሐፈ መክብብ በሕይወት ዓላማ ላይ በማተኮር፥ ያለ እግዚአብሔር ሕይወት ከንቱ እንደሆነ ያስተምረናል። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ደግሞ ጥበብ የሞላበት የጋብቻ ግንኙነት የሚመሠረተው በእውነተኛ ፍቅር ላይ እንደሆነ ያስተምረናል።

መጽሐፈ መክብብ የተጻፈው፥ «አንድ ሰው ደስታንና የዓላማን መከናወን በሕይወቱ ውስጥ እንዴት ሊያገኝ ይችላል?» (መክብብ 1፡3) ለሚል ዐቢይ የፍልስፍና ጥያቄ መልስ ለማስገኘት ነበር። «ከፀሐይ በታች» ባለ ነገር ውስጥ ሁሉ የሕይወትን ዓላማ ስለሚፈልግ ሰው የተጻፈ መጽሐፍ ነው። «ከፀሐይ በታች» የሚለው ሐረግ ከእግዚአብሔር ውጭ ላሉ ለማናቸውም ነገሮች የተሰጠ ስም ነው። በመሠረቱ ጸሐፊው «እግዚአብሔር ባይኖር ኖሮ ወይም እኔ የምኖረው እግዚአብሔር እንደሌለ ቆጥሬ ቢሆን ኖሮ፥ ምን እሆን ነበር? ሕይወት ትርጕም ይኖራት ነበርን? » በማለት ይናገራል። ስለዚህ ጸሐፊው በሕይወት ውስጥ ምናልባት ትርጉም ባገኝ ብሉ የተለያዩ ነገሮችን መመልከት ይጀምራል። ምናልባት ሕይወት ያለ እግዚአብሔር ትርጕም ይኖረው እንደሆነ በማለት የተለያዩ የታወቁ የዓለም ፍልስፍናዎችን መርምሯል ለማለት እንችላለን። ማጠቃለያው «ሁሉም ከንቱ ነው» የሚል ነው። (በመጽሐፉ ውስጥ ይህንን ዓረፍተ ነገር 25 ጊዜ ተደጋግሞ እናገኘዋለን)። 

1. ጸሐፊው ትኲረቱን ወደ ሳይንስ በማድረግ በምድር ላይ ያሉ ነገሮች ትርጕም ይኖራቸው እንደሆነ ለመረዳት ምርምር አድርጓል። ሳይንስ ማድረግ የሚችለው ችግሮችን ማየት እንጂ መፍትሔ መስጠት አይደለም (መክብብ 1፡4-10። 

የውይይት ጥያቄ፥ ለእግዚአብሔር ክብርን ሳይሰጥ ነገሮችን ሁሉ ለማብራራት በሚሞክረው ዘመናዊ ሳይንስ ላይ ከሚገባ በላይ እንዳንደገፍ ይህ እንዴት ሊያስጠነቅቀን ይገባል? 

2. ጸሐፊው ዓለማዊ ጥበብ፥ ፍልስፍናና ትምህርት ለሕይወት ትርጕም ይሰጡ እንደሆነ ለማየት ምርመራ አካሄደ፤ ነገር ግን ዓለማዊ ጥበብ እውነተኛ መልሶችን ለመስጠት አይችልም። ጥበበኛውም ሆነ ሞኙም ሳይቀር ሁሉንም ሰው ሞት ይጠባበቀዋል። ችግሮች በሁሉም ስፍራ አሉ። 

3. ጸሐፊው፥ ሰው ራሱን ለማስደሰት ሲል ብቻ በራስ ወዳድነት የሚገፋውን የምቾት ሕይወት ተመልክቷል፤ ነገር ግን ያም ደስታ በራሱ ከንቱ መሆኑን ለማየት ጊዜ አልወሰደበትም። 

4. ቀጥሎ ጸሐፊው፥ ሰዎች ለሕይወት ደስታና ትርጒም ይሰጣል ብለው የሚያስቡትን አንድ ነገር ይመለከታል። ይህም ሀብት ነው። ሀብት እርካታ ይሰጣልን? ጸሐፊው አይሰጥም ይላል፤ ምክንያቱም ሰው በሚሞትበት ጊዜ የአንድ ሰው ሀብት ወደ ሌላው ስለሚተላለፍ ሰውዬው በሙላት ደስታን አያገኝበትም። 

5. ጸሐፊው የሰውን ሕይወት መለወጥ ወደማይችል፥ ሆኖም እግዚአብሔርን የማምለክ ሥርዓት ወደሚታዩበት ሃይማኖት ሳይቀር ተመልክቶ ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር እውነተኛ ግንኙነት የሌለበት ሃይማኖትም ከንቱ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህን እውነቶች ክርስቲያኖች ያስታውሷቸው ዘንድ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? 

ጸሐፊው፥ የሰው ልጅ ዋጋ ያለው ነው ብሎ የሚቈጥረውን ነገር ሁሉ በመመርመር፥ የሚከተሉትን ማጠቃለያዎች ይሰጣል፡-

1. ሕይወት ትርጕም እንዲሰጥና ዓላማ እንዲኖረው፥ እግዚአብሔር የነገሮች ሁሉ ማዕከል መሆኑን በመገንዘብ መኖር ይገባናል። ሕይወት የራሱ የሆኑ ስንክሳራዊ ሁኔታዎችና ችግሮች ሲኖሩት የእግዚአብሔርን ዓላማ በማንረዳበት ጊዜ እንኳ እርሱ ዓላማውን በመፈጸም ላይ መሆኑን ማስታወስ ለእኛ ለክርስቲያኖች አስፈላጊ ነው። ያለ እግዚአብሔር፥ ማንኛውም ነገር ትርጕም የሌለው ከንቱ ነገር ነው።

2. የሕይወትን ትርጒም ለማወቅ መሠረታዊው ነገር በእግዚአብሔር መታመን ነው። ነገሮች ሁሉ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር መሆናቸውን ማመን አለብን (መክብብ 3፡1-15፤ 6፡1-2፤ 9፡1)።

3. ሕይወት በአብዛኛው ዓላማ ያለው ባይመስልም፥ አስተማማኝ በሆነ ትዕግሥት በእግዚአብሔር ላይ ተደግፈን፥ እርሱ በሰጠን መልካም ነገሮች ሁሉ ደስ እየተሰኘን ልንኖር ይገባል (መክብብ 2፡24-26፤ 11፡8)።

4. ሕይወት ትርጒም የሚኖረው፥ እግዚአብሔርን በመታዘዝና በምናደርገው ነገር ሁሉ እርሱ ፈራጅ እንደሆን በመገንዘብ የምንኖር ስንሆን ነው (መክብብ 8፡8-9፤ 12፡13)። እግዚአብሔር ደስታንና ዓላማን ይሰጣል። የእውነተኛ ጥበብ መሠረት እግዚአብሔርን መፍራት ነው (መክብብ 3፡14፤ 5፡7፤ 7፡18)። ክርስቲያን ባለው ነገር የሚረካ መሆን አለበት (መክብብ 2፡24-25፤ 3፡10-13)። 

መጽሐፈ መክብብ የተጻፈው በዓለም የሚኖሩ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲመረምሩና ከንቱ መሆኑን እንዲያዩ ለመገፋፋት ነው። ከዚያም ጸሐፊው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በእርሱ የሕይወትን ትርጒም እንዲሹ ይፈልግ ነበር። ያለ እግዚአብሔር፥ የሕይወት ትርጒምና እውነተኛ ደስታ የለም።

የውይይት ጥያቄ፥ ለእኛ እነዚህን እውነቶች ማስታወስ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? 

ዋና ዋና ትምህርቶች፡-

1. እንደ ሌሎቹ የጥበብ መጻሕፍት ሁሉ፥ መጽሐፈ መክብብ ጻድቅ እንደሚባረክና ኃጢአተኛ ሰው እንደሚቀጣ በሚናገረው መመሪያ ላይ ያተኲራል። መጽሐፈ መክብብ ይህንን እውነት የሚደግፍ ቢሆንም እንኳ ሰዎች የሌሎችን ጽድቅ ወይም ክፋት በዚህ መመሪያ በመመዘን እንዳይፈርዱ ያስጠነቅቃል። ጸሐፊው ጻድቃንም ሆኑ ኃጥአን እንደሚሞቱ ይናገራል። ብዙ ጊዜ ጻድቃን በግፍ የገደሉ፥ ድሆች፥ የተጨቆኑና ወዘተ. ናቸው። 

2. መጽሐፈ መክብብ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው መሠረት ዓለምን መመልከት አስፈላጊ እንደሆነ ያስተምራል። ከእግዚአብሔር ውጭ («ከፀሐይ በታች») ያለውን የዓለምን አመለካከት ያቀርባል። በትክክል ስንመዝናቸው ሁሉም ትርጕም አልባና ከንቱዎች ናቸው። ክርስቲያን ስለ ዓለም ያለው አመለካከት አንድን ሰው በእግዚአብሔር ምክንያት ደስ ወደሚሰኝበት ሕይወት እንደሚመራው ያስተምራል። እግዚአብሔር መልካም ነገሮችን ይሰጠናል። ለምናደርገው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂዎች ስለሆንን እርሱን በመፍራትና በመታዘዝ መኖር ይገባናል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ ሁለት ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ለ) ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ በዓለም አስተሳሰብ የሚሳቡባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? ሐ) እነዚህ እውነቶች ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ከመኖር ውጭ፥ የዓለም ነገሮች ሁሉ ጥቅም የሌላቸው ከንቱዎች እንደሆኑ እንዲያውቁ እንዴት ይረዷቸዋል? መ) እነዚህን እውነቶች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች እንዴት ልታስተምራቸው ትችላለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመጽሐፈ መክብብ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የማያምኑ ሰዎች በሕይወት ውስጥ ካላቸው ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል ጥቂቶቹ ምንድን ናቸው? እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከፍተኛ ጥረት የሚያደርገው ምን ለማግኘት ነው? እርካታ እንደሚሰጠው አድርጎ የሚገምተው ምንድን ነው? ለ) ብዙ ክርስቲያኖችም በሕይወት ውስጥ ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው እንዴት ነው? ሐ) ይህ ነገር መልካም ነው ወይስ ክፉ? መልስህን አብራራ።

ከእግዚአብሔር ጋር የግል ግንኙነት የሌላቸው ወይም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የማይስማማ ዓይነት ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች፥ በሰው ሕይወት ውስጥ እጅግ ከፍተኛውና የላቀው ነገር ምን ምንድን ነው ብለው ያስባሉ? ይህን በሚመለከት ልንጠቅሳቸው የምንችላቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ሀብት፥ ዝና፣ ሥልጣን፥ ትምህርት፡ ምቹ ኑሮ ናቸው። እነዚህ ነገሮች ሁሉ በራሳቸው አንዳችም ክፋት ባይኖርባቸውም እንኳ ለሰው ሕይወት እርካታን ለማስገኘት የሚችሉ ግን አይደሉም። የሕይወት ዓላማ ሊሆኑ የሚችሉ አይደሉም። የሚያሳዝነው ግን ልክ እንደ ዓለም ሰዎች የሚያስቡ በርካታ ክርስቲያኖች መኖራቸው ነው። ትምህርት ብቻ ካላቸው ደስተኞች የሚሆኑ ይመስላቸዋል። ሌሎች ደግሞ ብዙ ገንዘብ ኖሯቸው:- ቴሌቪዥን፥ ቪዲዮ፥ ቴፕና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ ባሉበት ትልቅ ዘመናዊ ቤት የተመቻቸ ሕይወት ለመኖር ያልማሉ። የሌሎች ግብ ደግሞ የአንድ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን መሪ መሆን ነው። በዚህ የሥልጣን ስፍራ በኩል ክብርና ዝናን ለማግኘት ይፈልጋሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህን የተለያዩ ነገሮች ለማግኘት የሚፈልጉ ክርስቲያኖችን በምሳሌነት ጥቀስ። ለ) እነዚህን ነገሮች መመኘት በአንድ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የሚያመጣው ችግር ምንድን ነው?

ይህ አዲስ ችግር አይደለም። በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ አይሁድም ተመሳሳይ ችግር ነበረባቸው። በዓለም አመለካከት ሀብትን፥ ጥበብን፥ ዝናን፥ ክብርን፥ ወዘተ. ይፈልጉ ነበር። መጽሐፈ መክብብ የሚያሳየው፡ አንድ ሰው እግዚአብሔርን መፈለግ ተቀዳሚ ተግባሩ ካላደረገ በስተቀር እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከንቱ መሆናቸውን ነው። ሕይወት ዋጋ የሚኖረውና እግዚአብሔር በሰጠው ነገር ሁሉ ሰው ደስተኛ ሊሆን የሚችለው፥ እግዚአብሔርን ደስ በማሰኘት ለመኖር በሚፈልግበትና በሚሞክርበት ጊዜ ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ማቴዎስ 6፡25-34 አንብብ። እግዚአብሔርንና መንግሥቱን ማስቀደምንና ለዚህ ዓለም ነገሮች አለመኖርን በተመለከት ረገድ እነዚህ ጥቅሶች ምን ያስተምሩናል?

እግዚአብሔር የለም የምንል ከሐድያን (ኤቲስቶች) ወይም እግዚአብሔር ቢኖርም እንኳ ልናውቀው አንችልም የምንል አግኖስቲኮች ወይም እግዚአብሔር እንደሌለ አድርገን የምንኖር ተግባራዊ አግኖስቲኮች ብንሆን ኖሮ፥ ሕይወት ምን ትርጒም ይሰጠን ነበር? ሰዎች ደስታን ይሰጣሉ የሚሉአቸው እንደ ሀብት፥ ዝና፥ ሥልጣንና ትምህርት ያሉ ነገሮች በእርግጥ ደስታን ይሰጣሉን? መጽሐፈ መክብብ እግዚአብሔር እንደሌለ ለሚቆጠሩ ሰዎች፥ ሕይወታቸው ትርጕም የሌለው እንደሆነ ለማረጋገጥ የተጻፈ ነው። ያለእግዚአብሔር ሰው ባዶና ሕይወቱም ትርጒም የሌለው «ከንቱ» ነው። ብዙ ጊዜ ክርስቲያን ወጣቶች የማያምኑ ሰዎች የሕይወት አኗኗርን ይመኛሉ። የማያምኑ ሰዎች ደስተኛ ሕይወት የሚኖሩ ይመስላሉ። ሀብታምና ነፃ ሆነው፥ ለሕይወት ደስታን የሚሰጥ ብዙ ነገር ያላቸው ይመስላሉ። ሰይጣን አኗኗራቸውን ታላቅ ደስታና ሐሤት ያለበት አስመስሎ ያቀርባል። መጽሐፈ መክብብ ይህ አስተሳሰብ ምን ያህል የተሳሳተ እንደሆነ ይናገራል። ሰው እግዚአብሔርን ለማክበር በመሻትና እንደሚፈርድበት ተገንዝቦ ካልኖረ በስተቀር፥ የልብ ሰላምና እውነተኛ የሕይወት ትርጕም ሊያገኝ አይችልም።

መጽሐፈ መክብብ ለመተርጐም እጅግ አስቸጋሪ ከሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አንዱ ነው። ከዚህም የተነሣ ብዙ ክርስቲያኖች መጽሐፈ መክብብን አያነቡም፤ ሊረዱትም አይሞክሩም። የመጽሐፈ መክብብን ዓላማ እስካልተረዳን ድረስ መጽሐፉን መረዳት አስቸጋሪ ነው። የመጽሐፈ መክብብን ዓላማ ከተረዳን ግን ያለንን ውስጣዊ አሳብ ለመመርመር ከሁሉም የላቀ መጽሐፍ ነው። የዚህን ዓለም ነገሮች ከንቱነት እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችን ከመከተል ጋር በማወዳደር ራሳችንን ለመመርመር ይረዳናል። 

የመጽሐፈ መክብብ ስያሜ 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) «መክብብ» ማለት ምን ማለት እንደሆነ አንድን የኦርተዶክስ ቄስ ጠይቅ። ለ) መጽሐፈ መክብብን በተሻለ ሁኔታ ሊገልጥ የሚችል ሌላ የአማርኛ ቃል ምንድን ነው?

በአይሁድ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ መጽሐፍ «የኮህሌዝ» ቃላት ወይም «ኮህሉዝ» በመባል ይታወቃል። ይህ ቃል የተገኘው ከመጽሐፈ መክብብ 1፡1 ሲሆን፥ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ «ሰባኪ» ተብሉ ተተርጕሟል። ኮህሌዝ የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን፥ ትርጕሙም አንድን ጉባኤ የሚሰበስብ ማለት ስለሆነ፥ ጉባኤን የሚያስተምር ሊባል ይችላል። ይህ ቃል የጸሐፊው ስም ወይም በጉባኤ ውስጥ እንደ አስተማሪ ሆኖ የማገልገል ተግባሩ ሊሆን ይችላል። ጸሐፊው ጥበበኛ ሰው እንደመሆኑ መጠን ሰዎችን በአንድነት ለመሰብሰብና ጥበብን ለማስተማር ኃላፊነት የነበረው ሰው ሊሆን ይችላል። «ኤክለሲያስተስ» የሚለው የእንግሊዝኛው ርእስ የተገኘው ከግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን፥ ትርጕሙም «ሰባኪ» ማለት ነው። መክብብ የሚለው የግዕዙ ቃል ትርጕምም «ሰባኪ ወይም አስተማሪ» ማለት ነው። 

የመጽሐፈ መክብብ ጸሐፊ 

የመጽሐፈ መክብብ ጸሐፊን ማንነት በሚመለከት ምሁራን ይከራከራሉ። ከመጽሐፉ በግልጽ እንደምንመለከተው ጸሐፊው ታላቅ ጥበብ ያለው ሆኖ፥ ነገር ግን የአይሁድ ሃይማኖታዊያን መሪዎች የሚሰጡትን ቀላል መልስ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልነበረ ሰው ነበር። በክፍሉ ውስጥ «የዳዊት ልጅ» እንደነበረ የሚናገር ሐረግ እናገኛለን። ይህም በቀጥታ የዳዊት ልጅ ወይም የዳዊት ዘር ነበር ማለት ሊሆን ይችላል። በኢየሩሳሌም የኖረ ንጉሥም ነበር። ስለ መጽሐፉ ጸሐፊ ሦስት ዐበይት አመለካከቶች አሉ፡-

1. መጽሐፉ በተለያዩ ጸሐፊዎች የተዘጋጀ ነው የሚል አስተሳሰብ ያላቸው አሉ። ይህ የማይመስልና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነትነት የሚያምኑ ብዙ ምሁራን የማይቀበሉት አሳብ ነው።

2. አንዳንዶች ደግሞ መጽሐፉን የጻፈው ሰሎሞን ነው ብለው ያምናሉ። ይህ በአይሁድና በክርስቲያኖች ሁሉ ዘንድ የሚታመንበት ታሪካዊ አመለካከት ነው። በመጽሐፉ ውስጥ የምናያቸውን መመዘኛዎች ሁሉ በተሻለ ሁኔታ የሚያሟላ ሰሎሞን ብቻ ነው ይላሉ። ሰለሞን የዳዊት ልጅና የእስራኤል ንጉሥ ነበር፤ ደግሞም ጥበበኛ ነበረ። ልቡ በባዕዳን ሴቶች ከእግዚአብሔር ርቆ የኮበለለበትና ዓለማዊ ጥበቡ በርካታ የሆኑ የሕይወት መሠረታዊ ነገሮችን እንዲጠይቅ ያደረገው ሰው ነበር። ይህን መጽሐፍ በሕይወቱ ፍጻሜ ለሕይወቱ ትርጒም በመሻት ያሳለፋቸውን ማብቂያ የሌላቸውን ነገሮችና የተጓዘባቸውን መንገዶች ወደኋላ ዞሮ በመመልከት የጻፈው ሊሆን ይችላል። ሰሎሞን በሕይወቱ እውነተኛ ትርጕም የሚኖረው በእግዚአብሔር በማመንና ለእርሱም በመታዘዝ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር።

3. አንዳንድ ምሁራን መጽሐፈ መክብብ ሁለት ምንጮች ያሉት ይመስላቸዋል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ካሉት አሳቦችና የጥበብ ንግግሮች አብዛኛዎቹ የሰሎሞን እንደሆኑ ጥርጥር የለውም ይላሉ፤ ነገር ግን ከሰሎሞን በኋላ ብዙ ዓመታት ቆይቶ ይኖር የነበረ አንድ ሌላ ሰው፥ ሰሎሞን ለሌሉች ያስተላለፈውን ጥበብ በመጠቀም፥ መጽሐፉን ጽፎት ይሆናል። ጸሐፊው «ኮህሌዝ» የሚለውን ቃል የተጠቀመው በሦስተኛ መደብ ነው፤ ይህም ማለት ከሰባኪው ወይም ከአስተማሪው በቀጥታ የተጠቀሰ ሳይሆን፥ ሌላ ሰው ስለ ሰባኪው የተናገረው ነው። ሰሎሞን መጽሐፉን ጽፎ ቢሆን ኖሮ የሚጠቀመው የራሱን ስም እንጂ ኮህሌዝ የሚለውን ቃል አልነበረም በማለት የማሳመኛ አሳብ ያቀርባሉ። በተጨማሪ መጽሐፈ መክብብ ከሰሎሞን በኋላ የተጻፉትን ሌሎች መጻሕፍት የሚመስል ነው። የተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ ይዘትም ከሰሎሞን በኋላ የነበረውን ጊዜ የሚያመለክት ነው በማለት ያረጋግጣሉ። እንደ ሌሉች የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ የመጽሐፈ መክብብ ጸሐፊ አይታወቅም ማለቱ የተሻለ ነው፤ ነገር ግን የሰሎሞንን ጥበብ የሚያንጸባርቅ ነው። መጽሐፉ አብዛኛውን የሕይወት ዘመኑን ከእግዚአብሔር ተለይቶ የኖረና ሕይወት ያለ እግዚአብሔር ትርጒም የለሽ መሆኑን የተገነዘበ አዛውንት ሁኔታን የሚያንጸባርቅ ነው። 

መጽሐፈ መክበብ የተጻፈበት ዘመን 

የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ማን እንደሆነ ስለማናውቅ የተጻፈበትንም ጊዜ አረጋግጠን መናገር አንችልም። አንዳንዶች ጊዜው ከ400-300 ዓ.ዓ. ነው ቢሉም፥ መጽሐፉ የተጻፈው ቀደም ብሎ ሳይሆን አይቀርም። ጸሐፊው ሰሎሞን ቢሆን ኖሮ፥ የተጻፈው በ940 ዓ.ዓ. ገደማ ይሆን ነበር። ከሰሎሞን በኋላ ይኖር በነበረ ሌላ ጸሐፊ ተጽፎ ቢሆን ኖሮ ደግሞ፥ ጊዜው ከ900-800 ዓ.ዓ. ይሆን ነበር። 

የመጽሐፈ መክብብ አስተዋጽኦ 

1. መግቢያ፡- ከእግዚአብሔር ተለይቶ በምድር ላይ መኖር ትርጕም የለውም(1፡11)።

2. በምድራዊ ሕይወት ጊዜያዊ ነገሮችን መመዘን (1፡12-3፡22)፡-

ሀ. የዓለም ጥበብ ከንቱ ነው (1፡12-28)፤ 

ለ. ምቾት ከንቱ ነው (2፡1-11)፣ 

ሐ. የዓለም ጥበብ ከንቱ ነው(2፡12-23)፤ 

መ. የእግዚአብሔር ጥበብና የእግዚአብሔርን ዓላማ መከተል ለሕይወት ትርጕም ይሰጣል (2፡24-3፡15)፤

ሠ. ሰው ላደረገው ነገር በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ መሆኑን ማስታወስ አለበት (3፡16-22)። 

3. የሰውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መመዘን (4፡1-8፡8)፡-

ሀ. የድህነትና የጭቆና ከንቱነት (4፡1-16)፤

ለ. ለእግዚአብሔር የሚቀርብ እውነተኛ አምልኮ ዋጋ አለው (5፡1-7)

ሐ. የሀብት ከንቱነት (5፡8-17)፤ 

መ. ሰው በእግዚአብሔር ደስ መሰኘት ሲጀምር ለሕይወቱ ትርጉም ያገኛል (5፡18-20)፤ 

ሠ. የሀብት ከንቱነት (6፡1-12)፤ 

ረ. ከእግዚአብሔር የሆነ ጥበብ ወደ ሚዛናዊ ሕይወት ይመራል (7፡1-8፡8)።

4. ዓለማዊ ጥበብን መመዘን (8፡9-12፡7)፡-

ሀ. ዓለማዊ ጥበብ በምድር ላይ በሚታዩ ነገሮች የተወሰነ ነው (8፡9-17)፤ 

ለ. ሰው ሁሉ ሟች ስለሆነ አሁን በሕይወት ሳለ ደስ ሊለው ይገባል (9፡1-12)፤ 

ሐ. በእግዚአብሔር ጥበብ መኖር ለሕይወት ጥቅምን ያስገኛል (9፡13-10፡20)፤

መ. ለወጣት የተሰጠ ምክር (11፡1-12፡7)። 

5. ማጠቃለያ፡- ሕይወት ትርጒም የሚኖረው እግዚአብሔርን ስንፈራና ስንታዘዘው ነው (12፡8-14)።

ማስታወሻ፡- መጽሐፈ መክብብን በአስተዋጽኦ ለመከፋፈል የሚያመች መጽሐፍ አይደለም። ከላይ የተመለከትነው አስተዋጽኦ መክብብ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን አብዛኛዎቹን ዐበይት ትምህርቶች ለማጠቃለል የሚሞክር ብቻ ነው። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)