የመጽሐፈ ነህምያ ዋና ዋና ትምህርቶች

ከመጽሐፈ ነህምያ ልንማራቸው የምንችለው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም፥ ሦስቱ ግን በጣም አስፈላጊና ከሌሉቹ የላቁ ናቸው።

 1. አንዲት ቤተ ክርስቲያን ልትገነባና ጤነኛ ልትሆን ከተፈለገ ተገቢ የሆኑ መሪዎች ያስፈልጓታል። እነዚህ መሪዎች ከሁሉ በፊት ተገቢ መንፈሳዊ መመዘኛዎችን ማሟላት አለባቸው። እግዚአብሔርን መውደድ አለባቸው፤ ለእግዚአብሔር ሕግ ሊገዳቸው ያስፈልጋል፤ ኃጢአትን ሊጠሉና የጸሎት ሰዎች ሊሆኑም ይገባል። 
 2. መሪዎች እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የሰጣትን ሥራ እንዲሠሩና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲፈጽሙ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሊያደራጁትና ሊያቅዱ ይገባል። ቤተ ክርስቲያን በሚገባ መደራጀት አለባት። እንዲሁም እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን አባል የተሰጠውን መንፈሳዊ ስጦታ አካሉን ለማነጽ እንዲያውለው በተናጠል የተለየ ኃላፊነት ሊሰጠው ይገባል።
 3. ቤተ ክርስቲያን ለእግዚአብሔር ልታደርግ የገባችውን ግዴታ ዘወትር ልታድስ ያስፈልጋታል። አይሁድ ኃጢአታቸውን በግልጥ እንደተናዘዙ እኛም ኃጢአታችንን በመናዘዝ ራሳችንን በግልና በቡድን ማንጻት አለብን። ለእግዚአብሔርም በመታዘዝ ግልጽ ቃል ኪዳን ማድረግ አለብን። ወደ ኃጢአት ላለመመለስም ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ለእግዚአብሔር የገባነውንም ግዴታ ያለማቋረጥ ልናድሰው ያስፈልጋል። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በተለይ የሕዝባቸውን የሕይወት ንጽሕና ለመጠበቅ ጠንቃቆች መሆን አለባቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እነዚህን ሦስት እውነቶች ማወቅና ከሕይወታቸው ጋር ማዛመድ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ የእዚህን ሦስት እውነቶች መኖር ወይም አለመኖር የምታየው እንዴት ነው? ሐ) በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያንህ ከእነዚህ ሦስት እውነቶች በጣም አስፈላጊ የሆነውና የሚፈለገው የትኛው ነው? መ) ይህን ያልክበት ምክንያት ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ነህምያ 11-13

ሕዝቡ ስለ ኃጢአታቸው ሕዝባዊ ኑዛዜ በማድረጋቸውና ለእግዚአብሔር ሕግጋት ለመታዘዝ በግልጽ ቃል ኪዳን በመግባታቸው ብቻ ይህ ውሳኔ ለረጅም ጊዜ ይቆያል ማለት አይደለም። ቤተ ክርስቲያንን በሚመለከት የሚያሳዝነው ነገር እግዚአብሔርን ለመከተልና ለእርሱም ለመታዘዝ ብዙ ጊዜ በርካታ ቃል ኪዳን ብንገባም፥ ወዲያውኑ ባለመታዘዝ መመላለሳችን ወይም ቤተ ክርስቲያን ብዙውን ጊዜ መልሳ በኃጢአት ስለምትወድቅ፥ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ከመግባታቸው በፊት በነበሩበት ሁኔታ መኖር መጀመራቸው ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ሰዎች ለእግዚአብሔር የሚያደርጓቸውን አንዳንድ የተስፋ ቃሎች ዘርዝር። ለ) ከእነዚህ ተስፋዎች አብዛኛዎቹ ሳይፈጸሙ የሚቀሩት እንዴት ነው? ሐ) ለእግዚአብሔር የገባሃቸው አንዳንድ የተስፋ ቃሉችን ጥቀስ። መ) ከገባሃቸው የተስፋ ቃሎች መካከል የፈጸምሃቸው የትኞቹ ናቸው? ሀ) ያልፈጸምሃቸውስ የትኞቹ ናቸው? ረ) ልትፈጽማቸው ያልቻልክበት ምክንያት ምንድን ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ነህምያ 11-13 አንብብ። ሀ) ነህምያ ኢየሩሳሌምን እንደገና በሕዝብ ለመሙላት ምን አደረገ? ለ) የኢየሩሳሌም ቅጥር ለእግዚአብሔር አልፎ የተሰጠበትን ሥርዓት ግለጥ። ሐ) ነህምያ ከፋርስ ከተመለሰ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸውን የተለያዩ መንፈሳዊ መነቃቃቶች ዘርዝር።

አሁን የኢየሩሳሌም ቅጥር ተሠርቶ ስላለቀ ነህምያ ሌሉች ሁለት ዓላማዎች ነበሩት። በመጀመሪያ፥ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ በርካታ ሰዎችን መፈለግ ሲሆን፥ ይህም ከተማይቱ ባዶ እንዳትሆን ለማድረግ ነበር፤ ስለዚህ ነህምያ ሕዝቡ ዕጣ እንዲጥሉና ከየአሥሩ ሰው አንድ ሰው በኢየሩሳሌም እንዲኖር ወሰነ።

ሁለተኛ፥ ነህምያ የቅጥሩን መሠራት ምክንያት በማድረግ በሚኖረው መንፈሳዊ በዓል ላይ የሚያገለግሉ መዘምራንና የሃይማኖት መሪዎችን አደራጀ። ቅጥሩን ለመጨረስ የቻሉት በእግዚአብሔር እርዳታ መሆኑን ተገንዝበው ስለ ነበር ምርጫውን ለእግዚአብሔር አሳልፈው ሰጡት። ነህምያ ሕዝቡንና መዘምራኑን በሁለት ቡድን በማደራጀቱ ከቅጥሩ ጫፍ አንሥቶ በኢየሩሳሌም ቅጥር ዙሪያ እየዘመሩ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር። ለሕዝቡ ሁሉ ይህ ታላቅ በዓል ነበር።

ነህምያ የይሁዳ ገዢ ሆኖ ለ12 ዓመታት ከሠራ በኋላ ወደ ፋርስ በመመለስ ከንጉሥ ጋር መሥራት ጀመረ። በዚያ የቆየው ስንት ጊዜ እንደነበር ባናውቅም፥ በመጨረሻ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ እንዲኖር ተፈቀደለት። የሕዝቡ መንፈሳዊ ሕይወት በከፍተኛ ሁኔታ ስለቀነሰና በኃጢአት ስለ ወደቁ፥ ነህምያ ለተወሰነ ጊዜ ከእነርሱ ርቆ እንደ ነበር በግልጥ ያሳየናል።

ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሰ ጊዜ ሕዝቡ በኃጢአት ወድቀው አገኛቸው። ነህምያ በፈሪሀ እግዚአብሔር ላይ የተመሠረተ የኃጢአት ጥላቻ ነበረው። ሕዝቡ በቅድስና መኖር እንዳለባቸው የወሰነ ሰው ነበር፤ ስለዚህ ወዲያውኑ እርምጃ ወሰደ፡፡ በመጀመሪያ፥ እንግዶች (ባዕዳን) የሆኑ ሰዎች በሙሉ ወደ ቤተ መቅደስ እንዳይመጡ አገለላቸው (ነህ. 13፡1-3)።

ሁለተኛ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላት የነበረውንና ካህኑ ኤልያሴብ በቤተ መቅደሱ አጠገብ አንደኛው ክፍል ውስጥ እንዲኖር የፈቀደለትን ጦቢያን አባረረ። ነህምያ የጦቢያ ክፋት ሕዝቡን እንዲበክል አልፈለገም፤ ስለዚህ የጦቢያ የሆኑትን ንብረቶች ሁሉ አውጥቶ በመንገድ ላይ በተናቸው። 

ሦስተኛ፥ ነህምያ ሕዝቡ አሥራት ለሌዋውያን መስጠት ማቆማቸውና በዚህም ምክንያት ሌዋውያን የአምልኮ ፕሮግራም የመምራት አገልግሎታቸውን አቋርጠው፥ ሥራ ፍለጋ በይሁዳ ሁሉ ለመበተን እንደተገደዱ ተገነዘበ። ነህምያ ሕዝቡ አሥራት እንዲሰጡና ሌዋውያንም አምልኮ ወደ መምራት አገልግሎታቸው እንዲመለሱ አደረገ።

አራተኛ፥ ነህምያ ሕዝቡ አናደርግም ብለው ቃል ከገቡት ነገሮች መካከል፥ በሰንበት የመሸጥና የመግዛት ነገር ሲለማመዱ ተመለከተ፤ ስለዚህ የከተማይቱ በሮች ዓርብ ማምሻውን ተዘግተው ሰንበት (ቅዳሜ) ካለቀ በኋላ ብቻ እንዲከፈቱ አዘዘ። ነጋዴዎቹንም ከእንግዲህ በሰንበት ቀን ቢመጡ እንደሚቀጡ በመንገር አስጠነቀቃቸው።(ማስታወሻ፡- ለአይሁድ ሰንበት የሚጀምረው ዓርብ ማምሻውን ከ12 ሰዓት በኋላ ሲሆን፥ የሚያበቃው ቅዳሜ ከ12 ሰዓት በኋላ ወደ ማታ ነው።)

አምስተኛ፥ ሕዝቡ ከአሕዛብ ጋር መጋባት ጀምረው ነበር። እንደምታስታውሰው፥ ይህንን አናደርግም ብለው ቃል ከገቡ ብዙ ዓመታት አላለፉም ነበር (ዕዝራ 10፡2፥ 10-14)። ነህምያ በታላቅ ቁጣ ሕዝቡን ተራገመ፤ ጠጉራቸውን ነጨ፤ ባዕዳን ሚስቶቻቸውንም እንዲያባርሩ አደረገ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምናደርጋቸውንና ከእነርሱ መንጻት የሚገባንን ተመሳሳይ ነገሮች ዘርዝር። ለ) የነህምያን ምሳሌነት በመከተል ቤተ ክርስቲያንህን እንዴት ልታነጻ ትችላለህ? ሐ) ከነህምያ ሕይወትና ለኃጢአት ከነበረው ጥላቻ የምንማረው ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ነህምያ 5-10

ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን መሪ በተጋለጠ ስፍራ ላይ ያለ ነው። ሰይጣን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኘውን ማንኛውንም አባል የሚያጠቃ ቢሆንም፥ በተለይ በቀጥታ የሚያነጣጥረው በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ላይ ነው። ጥቃቱን የሚያደርገው በሦስት ዋና ዋና ፈተናዎች ነው። አንደኛ፥ በትዕቢት ይፈትናቸዋል። ሰይጣን መሪዎችን በኃይላቸው፥ በችሎታቸውና በውጤታማነታቸው እንዲታበዩ ይፈትናቸዋል፤ በዚህ ዓይነት በእግዚአብሔር ላይ መታመናቸውን ስለሚያቆሙ ያለ ውጤት ይቀራሉ። በሁለተኛ ደረጃ የገንዘብ ፍቅር ያጠቃቸዋል። በዚህም ሕዝቡ በአደራ የሰጡአቸውን ገንዘብ ያለ አግባብ ይጠቀሙበታል። በሦስተኛ ደረጃ፥ መሪዎች በፍትወተ ሥጋ እንዲወድቁ ያደርጋል።

የውይይት ጥያቄ፥ መሪዎች በእነዚህ ሦስት ፈተናዎች ሲወድቁ ያየኸው እንዴት ነው?

ሰይጣን ሕዝቡን ተስፋ በማስቆረጥ፥ በስደትና በማስፈራራት ሊያሸንፋቸው ስላልቻለ፥ እስራኤላውያንን በሌላ መንገድ ማጥቃት ጀመረ። ጥቃቱንም በተለይ የሕዝቡ መሪ በነበረው በነህምያ ላይ አነጣጠረ።

የውይይት ጥያቄ፥ ነህምያ 5-10 አንብብ። ሀ) ሰይጣን በእስራኤላውያን መካከል የአሳብ መከፋፈል እንዲመጣ ያደረገው እንዴት ነበር? ለ) ሰይጣን ነህምያን ለማጥፋት የሞከረው እንዴት ነበር? ሐ) የኢየሩሳሌምን ቅጥር ለመሥራት የፈጀው ጊዜ ምን ያህል ነበር? መ) የእግዚአብሔርን ቃል የማንበብ ውጤትስ ምን ነበር?

የእግዚአብሔር ሕዝብ በዓላማቸው አንድ ሲሆኑ፥ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ሲኖሩና ለእርሱ ለመሥራትም ሲስማሙ ሰይጣን ይፈራል። አንድ ሰው ለብቻው ተነጥሉ መሥራቱ አያስፈራውም። ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የታጠቁ ክርስቲያኖች በአንድነት ሆነው በቡድን የእግዚአሔርን ሥራ ከፍጻሜ ለማድረስ መሥራት ሲጀምሩ ይፈራል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን እንድትሠራ የጠየቃትንና በግል ከሚሠሩ ይልቅ በቡድን ቢከናወኑ የበለጠ በጥሩ ሁኔታ ሊሠሩ የሚችሉ ነገሮችን ዘርዝር። ለ) በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ የሚሳተፉት የቤተ ክርስቲያናችን አባሎች ጥቂቶች የሆኑት ለምንድን ነው? ሐ) ብዙ አባላትን ማሳተፍ የምንችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር (ኤፌ. 4፡11-13 ተመልከት)።

ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥር የሚሠሩ ሰዎችን ሲያደራጅ ተቃውሞ ተነሣበት። በቅድሚያ ተቃውሞው የመጣው የእግዚአብሔርን ሕዝብ ተስፋ ለማስቆረጥና ስደትን እንዲፈሩ በማድረግ ነበር። ይህ ዘዴ ውጤት ሳያስገኝ ሲቀር፥ ሰይጣን ሌሎች መንገዶችን ሞከረ።

በመጀመሪያ፥ ሰይጣን በአይሁድ መካከል መከፋፈልን ሊያመጣ ሞከረ (ነህ. 5)። በነህምያ ዘመን በእስራኤል ምድር ራብ ነበር። በተጨማሪ የፋርስ መንግሥት የሚጠይቀው ግብር ለሕዝቡ ሸክም ሆነ፤ ስለዚህ አንዳንድ ሰዎች ግብር ለመከፈልና የሚበሉትን ለማግኘት ሲሉ መሬታቸውን ለሀብታሞች መሽጥ ነበረባቸው። ሌሎች ደግሞ ልጆቻቸውን ለባርነት አሳልፈው መስጠት ነበረባቸው። የሚያሳዝነው ነገር ሀብታም የሆኑ አይሁድ ይህን አጋጣሚ ለመጠቀም መሞከራቸው ነው። ገንዘባቸውን ከድሆች አይሁዳውያን ላይ በርካሽ ዋጋ መሬት ለመግዛት ተጠቀሙበት፤ እንዲሁም የገዛ ሕዝባቸውንም በባርነት ያዙ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም በኢትዮጵያ ይህ እንዴት ሊፈጸም ይችላል? ለ) በእንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ጊዜያት ሀብታም ክርስቲያኖች ማድረግ ያለባቸው ነገር ምንድን ነው? ሐ) መዝ. (35)፡10፤ (140)፡12 አንብብ። እግዚአብሔር ወደ ድሆች የሚመለከተው እንዴት ነው?

ነህምያ የአይሁድን መሪዎች በተለይም ገንዘባቸውን ያለ አግባብ በመጠቀማቸውና ለወንድሞቻቸው ምሕረት ባለማሳየታቸው ሀብታሞቹን ገሠጻቸው። ይህ ጉዳይ መከፋፈልን ሊያመጣና የተጀመረው ሥራ እንዲቆም ሊያደርግ ይችል ነበር፤ ነገር ግን ነህምያ በፍጥነት ስብሰባ በመጥራቱና ለችግሩ መፍትሔ በመፈለጉ፥ የመከፋፈል ነገር ቀረና የቅጥሩ ሥራ ቀጠለ።

ሁለተኛ፥ ጦቢያና ሰንባላጥ ነህምያን ማጥቃት በመጀመር ሥራውን እንዲተው ለማድረግ ሞከሩ። እነዚህ ሰዎች መሪው ከሥራው ከተለየ ሥራው እንደሚቆም ያውቁ ነበር። መሪው በቅርቡ የማይከታተለው ከሆነ ወይም ብዙ ጊዜ በሥራው ላይ ከሌለ ሥራው ሊሠራ አይችልም። ጦቢያና ሰንባላጥ ለነህምያ መልካም የሚመስለውን አሳባቸውን አቀረቡለት። ስለ አሳባቸው ለመመካከርና ሰላምን በአንድነት ለማምጣት ስለሚቻልበት መንገድ በመሰባሰብ እንዲወያዩበት አሳብ አቀረቡለት። ኦኖ ከኢየሩሳሌም 30 ኪሎ ሜትር ርቆ በይሁዳ ጫፍ የሚገኝ ስፍራ ነበር። ነህምያ ግን ሥራውን ትቶ ወደዚያ መሄድ እምቢ አለ። እግዚአብሔር ቅጥሩን ይሠራ ዘንድ እንደጠራው ያውቅ ነበር፤ ስለዚህ ሥራው እስኪጠናቀቅ ድረስ በዚያ ሥራ ላይ መቆየትን መረጠ። 

የውይይት ጥያቄ፥ አንድ መሪ እግዚአብሔር ከሰጠው ሥራዎች እጅግ ሊርቅ የሚችልበትንና በዚህ ምክንያት ሥራው እየተዳከመ ሊሄድ የሚችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

ሦስተኛ፥ ጠላቶቻቸው በሕዝቡ ፊት የነህምያን መልካም ምስክርነት ለማበላሸት ሞከሩ። ለነህምያ ግልጽ ደብዳቤ ላኩለት። የደብዳቤው አሳብ በንጉሡ ላይ ለማመፅ መሞከርህ ተሰምቶአልና ይህንን ማረጋገጫ ወደ ንጉሡ ከመላካችን በፊት ናና እንማከር የሚል ነበር።

ለአንድ መሪ ምስክርነቱን መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ሕዝቡ መሪውን የማያምነው ከሆነ፥ ወይም መጥፎ ምስክርነት ካለው ወዲያውኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት እርሱን መከተል ያቆማሉ። የነህምያ ምላሽ ግን የሚያስፋፉት ወሬ ውሸት መሆኑን በሕዝቡ ሁሉ ፊት ማሳወቅ ነበር። ነህምያ በእነዚህ ሁሉ ተቃውሞዎች ውስጥ ሥራውን እንዲቀጥል ከእግዚአብሔር ዘንድ ብርታትን ጠየቀ። አንድን መሪ እጅግ ተስፋ ሊያስቆርጡት ከሚችሉት ነገሮች አንዱ፥ የሚፈጽመውን ተግባር ሌሉች ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ሲረዱትና በሐሰት ሲወነጅሉት ነው። ሕዝቡ ሁሉ እውነትን ያውቁና ይረዱ ዘንድ የተፈጸሙትን ተግባራት ለመግለጥ መሞከር አስፈላጊ ቢሆንም፥ መሪዎች በእንደዚህ ዓይነት የሐሰት ውንጀላ ሊረቱ አይገባም።

አራተኛ፥ ጠላቶች ነህምያ ስለ ሕይወቱ እንዲሠጋና ሕይወቱን ለማዳን ወደ ቤተ መቅደስ ሸሽቶ ካልተሸሸገ እንደሚገደል በመናገር አስፈራሩት። ይህም የነህምያን ምስክርነት ለማበላሸት የተደረገ ሙከራ ነበር። ነህምያ በጣም ቢፈራና ሕይወቱን ለማዳን ብሎ ቢደበቅ ኖሮ፥ ሕዝቡም ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚያስፈልጋቸው አውቀው ሥራውን ሊያቆሙ ይችሉ ነበር። መሪዎች ከሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባላት ሁሉ በተሻለና በበለጠ ሁኔታ በስደት ጊዜ ራሳቸውን ለመሸሽግና ለመከላከል መሞከር ጨርሶ የለባቸውም። ስደትን ለመጋፈጥ፥ አስፈላጊ ከሆነ ለወንጌል ለመሞት እንኳ፥ የመጀመሪያዎቹ መሆን አለባቸው። መሪዎች ደፋሮች ሲሆኑና ተቃውሞን ሲጋፈጡ፥ ሕዝቡ ድፍረትን ያገኛሉ። መሪዎች ግን ሕይወታቸውን ለመጠበቅና ለመሸሸግ ከሞከሩ፥ ሕዝቡም ለወንጌል ከመኖር ይልቅ ሕይወታቸውን በመጠበቅ ላይ ያተኩራሉ።

ነህምያና ሕዝቡ በጠላቶቻቸው ሙከራ ለመሸነፍ ፈቃደኞች ባለመሆናቸውና በአንድ አሳብ አብረው ስለሠሩ የቅጥሩ ሥራ በ52 ቀናት ውስጥ ተጠናቀቀ።

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ቤተ ክርስቲያን አመራር ከነህምያ ሕይወትና ከቅጥሩ መሠራት ምን ለመማር እንችላለን?

የውይይት ጥያቄ፥ በነህምያ 8-10 እንደተጻፈው በሕዝቡ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል እውቀት ምን ድርሻ ነበረው?

በምዕ. 7 ከምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱ ሰዎች ስም ከተዘረዘረ በኋላ፥ በዕዝራና በነህምያ መሪነት በእስራኤል ስለ ተካሄደው መንፈሳዊ መነቃቃት (ተሐድሶ) እናነባለን። አንዳንድ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቁሳቁሳዊ የሆኑ ሌሎች ነገሮችን መገንባት በጣም ቀላል ነው፤ ነገር ግን የሰዎችን መንፈሳዊ ሕይወት መገንባት በጣም አስቸጋሪ ነው። ነህ. 8-10 በእስራኤል የቅጥሩ ሥራ ከተፈጸመ በኋላ ስለተካሄደው መንፈሳዊ መነቃቃት ይገልጣል። ስለ መንፈሳዊ መነቃቃት የሚከተሉትን ነገሮች ተመልከት፡

 1. መንፈሳዊ መነቃቃት የተጀመረው ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብና ማጥናት በጀመሩበት ጊዜ ነው፤ (ነህ. 8፡4-9)። ዕዝራ ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል በሚያነብበት ጊዜ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ቃል እየታዘዙ እንዳልኖሩ ተገነዘበ። ብዙ ሰዎች የዕብራይስጥን ቋንቋ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የተጻፈበትን ቋንቋ የማይረዱ ስለነበሩ፥ ነህምያ ሕዝቡ መልእክቱን እንዲረዱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ወደ አራማይክ ቋንቋ በቃል ይተረጉምላቸው ነበር። 
 2. የእግዚአብሔር ቃል በእንባ የተረጋገጠ የግል ንስሐን ወደ ሰዎቹ ሕይወት አመጣ፤ (ነህ. 8፡9)። ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል በሰሙ ጊዜ እያንዳንዱ ሰው በኃጢአት እንደሚኖር ተገነዘበ። ይህም ጥልቅ ኀዘን፥ ልቅሶና በእግዚአብሔር ፊት የግል ንስሐን አስከተለ። 
 3. የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብና መረዳት ሕዝቡን ለእግዚአብሔር ወደ መታዘዝ መራቸው። ሕዝቡ ከ800 ዓመታት በፊት ከኢያሱ ዘመን ወዲህ ከተከበሩት በዓላት ሁሉ በላቀ ሁኔታ የዳስ በዓል አከበሩ።
 4. የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብ በሕዝብ ፊት በግልጽ መናዘዝንና ንስሐን አመጣ። ሕዝቡ በግል ስለ ኃጢአታቸው ማወቅ ብቻ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔር ጉባኤ እንደ መሆናቸው መጠን ስለ ኃጢአታቸው በአንድነት በግልጽ ከተናዘዙ በኋላ ንስሐ ገቡ።
 5. . ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ መወሰናቸውን ለማሳየት በመሪዎቻቸው በኩል ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ቃል ኪዳን አደሱ። እንዲሁም ለሙሴ ሕግጋት እንደሚታዘዙ በጽሑፍ ለእግዚአብሔር ቃል ሰጡ። በተለይ ከአሕዛብ ጋር ላለመጋባት መወሰናቸውን፥ በሰንበት መግዛትና መሽጥ እንደሚያቆሙ፥ አሥራትና ምጽዋት በመስጠት የቤተ መቅደሱን አገልግሉትና የአምልኮ መሪዎች የሆኑትን ሌዋውያኑን እንደሚደግፉ ቃል መግባታቸው ተገልጿል።  

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) መንፈሳዊ መነቃቃት (ተሐድሶ) በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ስለሚያስከትለው ውጤት፥ በእስራኤል ሁሉ ላይ በኃይልና በፍጥነት ከተስፋፋው ከዚህ መንፈሳዊ መነቃቃት ምን እንማራለን? ለ) የዚህ ዓይነቱ መንፈሳዊ መነቃቃት ለቤተ ክርስቲያናችን ያስፈልጋል ብለህ ታስባለህን? ምክንያትህን ግለጥ። ሐ) የዚህ ዓይነቱ መንፈሳዊ መነቃቃት እንዲኖር የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሊያደርጉት የሚገባ ነው ብለህ የምታስበውን ነገር ተናገር። መ) የዚህ ዓይነት መንፈሳዊ መነቃቃት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈጥኖ እንዲመጣ ጸልይ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ነህምያ 1-4

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ለአንድ የተዋጣለት የቤተ ክርስቲያን መሪ በጣም አስፈላጊ ባሕርይ ምን ይመስልሃል? መሪው ምን መሆን አለበት? ምንስ ማድረግ አለበት? ወዘተ. ለ) በኢትዮጵያ ውስጥ የተዋጣላቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ናቸው ብለህ የምታስባቸውን አንዳንድ ሰዎች በምሳሌነት ጥቀስ። ሐ) ውጤታማ ያደረጋቸው ነገር ምንድን ነው?

በመሪነት እግዚአብሔር የሚጠቀምበት ሰው ምን ዓይነት ነው? የፈረሱ መንፈሳዊ ቅጥሮችን እንደገና በመሥራት ጠንካራ ቤተ ክርስቲያንን መመሥረት በሚያስችል መንገድ የእግዚአብሔርን ሕዝብ መምራት የሚችል ምን ዓይነት ሰው ነው? መጽሐፈ ነህምያ ስለ እንደዚህ ዓይነት ሰው ይነግረናል። ይህ ሰው ነህምያ ነበር። ነህምያ ውጫዊና የሚታይ የነበረውን የኢየሩሳሌምን ቅጥር ለማሠራት ኃላፊነት የነበረበት ፖለቲካዊ መሪ ቢሆንም፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የፈረሱ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ቅጥሮችን እንደገና ሊሠሩ በሚችሉበት መንገድ እንዴት መምራት እንደሚቻል በርካታ ነገሮችን ከእርሱ እንማራለን። በነህምያ ጥናታችን እግዚአብሔር ነህምያን ሊጠቀምበት የቻለው በእግዚአብሔር ፊት በነበረው መንፈሳዊ ሕይወትና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመምራት በነበረው የአስተዳደር ችሉታ እንደነበረ እንመለከታለን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ነህምያ 1-4 አንብብ። ሀ) ስለ ነህምያ ግለጥ። ስለ ነህምያ መንፈሳዊ ሕይወት ከእነዚህ ቁጥሮች የምንማረው ነገር ምንድን ነው? ለ) ከእነዚህ ቁጥሮች ስለ ነህምያ የማቀድና የመምራት ችሎታ ምን እንማራለን? ሐ) የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እንደገና ለመሥራት በሞከረ ጊዜ፥ ነህምያን ያጋጠሙትን የተለያዩ ችግሮችና ትግሉች ጥቀስ።

የንጉሥ አርጤክስስ ጠጅ አሳላፊና አማካሪ የነበረው ነህምያ የሚኖረው በፋርስ መንግሥት ዋና ከተማ በሱሳ ባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ ነበር። አንዳንድ ዘመዶቹና ሌሎች አይሁዶች ከኢየሩሳሌም ወደ ፋርስ ነህምያን ለመጎብኘት መጡና የኢየሩሳሌም ከተማ የነበረችበትን ሁኔታና የእግዚአብሔር ሕዝብም በዚያ እንዴት እንደሚኖሩ ነገሩት።

ነህምያ እግዚአብሔርን የሚፈራ ታላቅ መሪ ያደረጉትን የሚከተሉትን ነገሮች ተመልከት፡-

 1. ነህምያ የእግዚአብሔር ሕዝብ ስለ ነበሩበት ሁኔታ የሚገደው ሰው ነበር። የሚኖረው በኢየሩሳሌም አካባቢ ባይሆንም ጉዳዩ ያሳስበው ስለ ነበር ሕዝቡን በሚመለከት ወደ እርሱ የመጡትን አይሁድ ጠየቀ። ነህምያ ሕዝቡ ስለ ነበሩበት አሳዛኝ ሁኔታ ሲሰማ አለቀሰ። እንዲሁም በእግዚአብሔር ፊት ጾመና ጸለየ። 
 2. ነህምያ የጸሎት ሰው ነበር። በመጽሐፈ ነህምያ በአጠቃላይ ሁኔታዎች አስቸጋሪ በሚሆኑበት ጊዜ ነህምያ ፊቱን ወደ እግዚአብሔር ሲመልስ እንመለከተዋለን።

የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፡- ነህ. 1፡4፤ 2፡4፤4፡9፤6፡9 ሀ) በእነዚህ ጥቅሶች ነህምያ የጸለየባቸውን ጊዜያትና ስለምን እንደጸለየ ዘርዝር። ለ) ከእነዚህ ጥቅሶች ስለ ጸሎት የምንማረው ነገር ምንድን ነው? 

 1. ነህምያ የእግዚአብሔርን ቃል ያውቅ ነበር። በምዕራፍ 1 የተጻፈውን የነህምያን ጸሎት ስንመለከት፥ ነህምያ የይሁዳን ታሪክ እንደሚያውቅ ማለትም የሙሴን ሕግ፥ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የገባውን ቃል ኪዳንና እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደገና ለማደስና ለማነጽ የሰጠውን ተስፋ በሚገባ ማወቁን እንመለከታለን።
 2. ነህምያ ኃጢአቱንና የአባቶቹን ኃጢአት የሚናዘዝ መሪም ነበር። ነህምያ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ኅብረት የሚያበላሽና የሚያጠፋ፥ እግዚአብሔር ለጸሎቱ ሊሰጠው ያለውን መልስ የሚያግድ አንዳችም ነገር እንዳይኖር የሚፈልግ ሰው ነበር። ኃጢአት ይህንን ሊያደርግ እንደሚችል ያውቅ ሰለ ነበረ ኃጢአቱን ተናዘዘ። 
 3. ነህምያ ሥራው ውስጥ ለመግባት ራሱን በማዘጋጀት፥ ሕዝቡን እንደገና ለመሥራት እንዲጠቀምበት እግዚአብሔርን ለመነ። እግዚአብሔርን ሌላ ሰው እንዲያስነሣ አልጠየቀውም፤ ግን ለእግዚአብሔር ምን መሥራት እንደሚችልና ያንን ለማድረግ ምን እንደሚጠበቅበት ጠየቀ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ አምስት መንፈሳዊ መመዘኛዎች ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ለ) በሕይወትህ ውስጥ የሚኖሩትስ እንዴት ነው? ሐ) በእነዚህ አምስት የሕይወትህ አቅጣጫዎች ለማደግ የምትችለው እንዴት ነው?

ነህምያ 2-3 የነህምያን የአስተዳደር ብቃቶች ይነግሩናል። በመጨረሻም ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመልሰውና የፈረሰውን ቅጥር እንደገና የመሥራት ሥራውን ሊያከናውን የሚችለው እግዚአብሔር እንደሆነ ቢያውቅም፥ እግዚአብሔር በሰዎች መገልገል ደስ እንደሚለውም ያውቅ ነበር፤ ስለዚህ ነህምያ ጸለየና ዕቅድ አወጣ። ነህምያ መጸለይ በጀመረበት በኪስሊቭ፥ በኅዳር ወርና ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፈቃድ በጠየቀበት በኒሳን፥ በመጋቢት ወር መካከል የአራት ወራት ልዩነት አለ። እግዚአብሔር የንጉሡን ልብ ሲከፍት፥ ነህምያ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ነበር።

ነህምያ እግዚአብሔር ጸሎቱን እንደሚመልስ ስላመነ፥ በኢየሩሳሌም ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይና ሥራውን ለመሥራት ምን እንደሚያስፈልገው፥ ሄዶም ምን እንደሚሠራ ለንጉሡ ለመናገር ተዘጋጅቶ ነበር። ነህምያ የዕቅዱን ምንነት በሚመለከት ንጉሡ እስኪጠይቀው ድረስ አልጠበቀም፤ ነገር ግን በእምነት አስቀድሞ ዐቀደ። እግዚአብሔር በሮችን እስከሚከፍትለት ድረስም ጠበቀ። ጥሩ የቤተ ክርስቲያን መሪ ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ሥራ እንዴት እንደሚሠራ የሚያቅድ፥ ሥራውን ለማሻሻል ምን መደረግ እንዳለበትና እንዴት ማደረግ እንዳለበት የሚወስን የተግባር ሰው ነው። 

ቅጥሮቹን እንደገና ለመሥራት ምን እንደሚያስፈልግ ለማወቅ የፈረሱትን የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እየዞረ በመጎብኘቱ የነህምያን የአስተዳደር ብቃት እንመለከታለን። ከዚያም ሕዝቡን በሥራው ውስጥ እንዲሳተፉ ጠየቃቸው። አንድ ጥሩ መሪ ሁልጊዜ እንደሚያደርገው፥ ነህምያ ሥራውን ብቻውን ለመሥራት ጥረት አላደረገም፤ ነገር ግን በርካታ ሰዎች በሥራው እንዲሳተፉ የተቻለውን አደረገ። ነህምያ እያንዳንዱ ሰው አንድ የተወሰነ ኃላፊነት እንዲወስድ ሥራውን ከፋፈለ። በነህምያ ምዕራፍ 3 በቅጥሩ ሥራ ላይ የተሰማሩትን ሰዎች ስም ዝርዝር እናገኛለን። ሥራውን የሠሩት ሰዎች ምን ዓይነት እንደነበሩ መመልከት መልካም ነው። የከተማ ሹማምንት፥ ነጋዴዎች፥ ድሆች፥ የሃይማኖት መሪዎች፥ ወንዶች፥ ሴቶች ወዘተ ነበሩ። ሥራውን አንሠራም ያሉ የቴቁሔ መኳንንት ብቻ ነበሩ (ህ. 3፡5)። እነርሱ ትዕቢተኞች ነበሩ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ መሠራት ካለባቸው ሥራዎች አንዱን ጥቀስ። ለ) ይህ ሥራ ከፍጻሜ እንዲደርስ መወሰድ ያለበት እርምጃ ምንድን ነው? ሐ) ይህ ሥራ በሚገባ ወደ ፍጻሜ እንዲደርስ ለተለያዩ ሰዎች ሥራዎችን ለማከፋፈል የሚቻለው እንዴት ነው? መ) በዚህ ሥራ ውስጥ ለመሳተፍ ትችል ዘንድ እግዚአብሔር በሩን እንዲከፍትልህ በጸሎት ጠይቀው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ኤፌ. 4፡11-13 አንብብ። ሀ) እነዚህ ቁጥሮች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለአባላት ማድረግ ስላለባቸው ነገሮች የሚናገሩት ምንድን ነው? ለ) ይህ በቤተ ክርስቲያንህ የተፈጸመው እንዴት ነው?

በነህምያ ምዕራፍ 4 ቅጥሩ መሠራት ከተጀመረ ወዲህ ስለ ተፈጠረው የመጀመሪያ ተቃውሞ እንመለከታለን። ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር ለመሥራት ሲጀምርና የእግዚአብሔር ሕዝብም ለመሥራት ሲደራጁ፣ ሥራውን ለማቆም ተቃውሞ መፈጠር ይጀምራል። ይህ ተቃውሞ በቤተ ክርስቲያን ክልል ውስጥ በሚገኙ፥ ወይም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ከሚገኙ ሰዎች ሊመጣ ይችላል። መሪዎች ማረጋገጥ ያለባቸው ነገር የእግዚአብሔር ሥራ በተቃውሞ ውስጥ ሁሉ የሚቀጥል መሆኑን ነው። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ስለተቃውሞ የሚከተሉትን ነገሮች ተመልከት፡-

 1. በመጀመሪያ፥ ተቃውሞ የመጣው ፌዝ በተቀላቀለበት ንግግር መልክ ነበር። የአይሁድ ሕዝብ ጠላቶች የነበሩት ጦቢያና ሰንባላጥ ሌሎችም፥ ሕዝቡ በሚሠሩት ሥራ ላይ በመቀለድ ተስፋ ቆርጠው ሥራውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ሞከሩ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰዎች ሌሎች ስለ እነርሱ የሚሉትን ነገር በሚመለከት የሚገዳቸውና በሚቀልዱባቸውም ጊዜ ተስፋ ቆርጠው የጀመሩትን ሥራ የሚያቆሙት ለምንድን ነው? ለ) የዚህ ዓይነት ተቃውሞ በክርስቲያኖች ላይ ሲሠራ ያየኸውን ምሳሌ ስጥ። 

 1. ሁለተኛ፥ ተቃውሞው በሕዝቡ ላይ ችግር የማድረስ ወይም ጥቃት የማምጣት መልክ ያዘ። በእርግጥ ጠላቶቻቸው በዚህ ስፍራ የማጥቃት ዛቻ ብቻ ነው ያሰሙት። ብዙ ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን የሚከብደው በቀጥታ የሚመጣው ስደት ሳይሆን የጥቃትና የስደት ዛቻ ነው። ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን ይገኝ የነበረው የሰማርያ ገዥ ሰንባላጥና ሌሎችም ግብረ አበሮቹ ሠራተኞቹን ባልጠበቁት ሰዓት ሊያጠቋቸው አስፈራሯቸው። የነህምያ መልስ ግን የሚያስገርም ነበር። በመጀመሪያ፥ ሊጠብቃቸው የሚችል እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ የተገነዘበበትን ጸሎት ነህምያ ጸለየ። ሁለተኛ፥ ነህምያ ሕዝቡ ሊደርስ ከሚችል ጥቃት ለመከላከል በተጠንቀቅ እንዲቆሙ አደረገ። ሦስተኛ፥ ነህምያ የሕዝቡን ትኩረት ይጠብቀናል ወዳለው ወደ እግዚአብሔር መለሰ። አራተኛ፥ ሕዝቡ ሥራውን መቀጠላቸውን አረጋገጠ። ሕዝቡ ራሳቸውን ለመጠበቅ ብለው፥ ሥራቸውን ከማቆም ይልቅ ሥራውን እንዲቀጥሉ አደፋፈረ። ነህምያ ሰይጣን ሥራውን ለማስቆም እንደሚጥር ያውቅ ስለ ነበር፥ ሕዝቡ ሥራውን እንዲቀጥሉ አበረታታቸው።

እነዚህ ሁለት ዘዴዎች ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሥራ ለማስቆም ብዙ ጊዜ የሚጠቀምባቸው መንገዶች ናቸው። ሁለቱም ዘዴዎች ያነጣጠሩት በእግዚአብሔር ሕዝብ እንጂ በመሪው ላይ አልነበረም። በሚቀጥለው ጥናታችን ደግሞ ሰይጣን ሥራውን ለማስቆም መሪውን ነህምያን እንዴት እንዳጠቃ እንመለከታለን።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ቤተ ክርስቲያንህን ስለ መምራት ከእነዚህ ምዕራፎች የተማርካቸውን ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህ እውነቶች በሕይወትህ በተግባር ላይ የሚውሉባቸውን መንገዶች ዘርዝር። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመጽሐፈ ነህምያ መግቢያ

እንደ ዕዝራ ሁሉ ነህምያም የእግዚአብሔርን ሕዝብ እንደገና ስለ ማነጽ የሚናገር ታሪክ ነው። ምናልባት ስለ መልካም የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ እጅግ ግልጽ ከሆኑ ምሳሌዎች አንዱ ይህ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ እርሱ የሰጣቸውን ሥራ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲያከናውኑ እንዴት ማደራጀት እንደሚቻል ያሳያል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ሕዝቡ እንዲሠሯቸው የሚፈልጋቸውን ነገሮች ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመሥራት ይቻል ዘንድ ጥሩ አደረጃጀት የሚጠይቁ ሥራዎችን ዘርዝር። ለ) በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዘንድ ጥሩ የሆነ አደረጃጀት ወይም አስተዳደር ባለመኖሩ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ በሚገባ ያልተሠሩ ሥራዎች የትኞቹ ናቸው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ነህምያን ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልከት። ስለ መጽሐፈ ነህምያ የተጠቀሱ አንዳንድ ጠቃሚ ነገሮችን ጥቀስ። 

መጽሐፍ ቅዱስን በቅደም ተከተል እያጠናህ ከሆነ ከዚህ ቀደም ብለን የመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ የመጀመሪያ ዘገባዎች የተጻፉት በዕዝራና በነህምያ እንደሆነ ተመልክተናል። እነዚህ ዘገባዎች ተጠናቅረውና ወደ ይሁዳ ስለተመለሱት ምርኮኞች የሚናገረው ታሪክ ታከሉባቸው ዕዝራ-ነህምያ ወደሚል አንድ መጽሐፍ ተጠቃለሉ። የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ግሪክ ቋንቋ በተተረጎመበት ጊዜ ግን ይህ መጽሐፍ በሁለት ክፍል ተከፈለ።

መጽሐፈ ህምያ ስያሜውን ያገኘው የመጽሐፉ ዋና ገጸ ባሕርይ ከሆነው ከነህምያ ነው። እርሱም የይሁዳ ገዥ በመሆን የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እንደገና በበላይነት ይቆጣጠር ነበር። 

የነህምያ ዘመን

ነህምያ በምርኮ ዘመን በምርኮ አገር የተወለደ አይሁዳዊ ነው። እግዚአብሔር በፋርስ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን እንዲያገኝ አደረገው። ነህምያ የንጉሡ ጠጅ አሳላፊ ነበር። ይህ ከፍተኛ የሥልጣን ስፍራ ባይመስልም፥ ጠጅ አሳላፊነት በጥንት ዘመን የንጉሡ ወዳጅ ለሆነና በከፍተኛ ደረጃ ታማኝነት ላለው ሰው የሚሰጥ ሥራ ነበር። ጠጅ አሳላፊ ታማኝ መሆን የነበረበት ሰዎች ንጉሡን የመግደል ሙከራ የሚያደርጉበት አንዱ መንገድ በሚበላው ወይም በሚጠጣው ነገር ላይ መርዝ በመጨመር ስለ ነበር ነው፤ ስለዚህ ይህ ማለት ነህምያ የፋርስ ንጉሥ የቅርብ አማካሪ ከሆኑት ሰዎች አንዱ ነበር ማለት ነው። ነህምያ በመንግሥት ዘንድ በጣም ጥሩ ሥራ ያለውና ጥሩ ኑሮን የሚኖር ቢሆንም፥ ወገኖቹንና ጨርሶ አይቷት የማያውቃትን ኢየሩሳሌምን አልረሳም። ነህምያ እግዚአብሔርን የሚወድ፥ ስለ እግዚአብሔር ክብርና ስለ ሕዝቡ በጣም የሚገደው ሰው ነበር። የኢየሩሳሌም ቅጥር ባለመሠራቱ የእግዚአብሔር ስም ተነቅፍ ስለ ነበረና ሕዝቡም ለጠላት ጥቃት ተጋልጠው ስለ ነበር ነህምያ ስለ ደኅንነታቸው ገደደውና የኢየሩሳሌምን ቅጥር በመሥራት እርሱን ይጠቀምበት ዘንድ እግዚአብሔርን ለመነ።

ነህምያ አብሮት ይሠራ የነበረው የፋርስ ንጉሥ አርጤክስስ በመባል ይታወቃል። በሥልጣን ላይ የቆየው ከ464-425 ዓ.ዓ. ነበር። አርጤክስስ በዘመነ መንግሥቱ መጀመሪያ ላይ አይሁድን ስደት እንዲደርስባቸው ያደረገ ቢሆንም፥ ለዕዝራ ግን የተለየ ርኅራኄ በማሳየት በ458 ዓ.ዓ. ዕዝራንና አንዳንድ አይሁድን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አድርጓል። ከ13 ዓመታት በኋላ ደግሞ ነህምያ ሌላ ቡድን እየመራ ወደ አገሩ እንዲሄድ አርጤክስስ ፈቅዶለታል። ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም አገሩ ከተመለሰ በኋላ ለ12 ዓመታት (444-432 ዓ.ዓ.) የይሁዳ ገዥ በመሆን አገልግሏል። ከ12 ዓመታት በኋላ ግን ወደ ፋርስ በመመለስ በአርጤክስስ መንግሥት ውስጥ እንደገና አገልግሏል። ከዚያ በኋላ በፋርስ ምን ያህል እንደቆየ ባናውቅም፥ በመጨረሻ ወደ ኢየሩሳሌም በመመለስ የይሁዳ ገዥ እንደሆነ እንመለከታለን። ለሁለተኛ ጊዜ ገዥ የሆነበት ዘመን ምን ያህል እንደሆነ አናውቅም።

ነህምያ ገዥ ሆኖ ስለሠራበት ጊዜ ብዙ የምናውቀው ነገር የለም። ከነህምያ 1-12 የሚገኘው ታሪክ በአብዛኛው የተፈጸመው ነህምያ በኢየሩሳሌም ባገለገለባቸው በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ነው።

የነህምያ የመጀመሪያ አገልግሎት የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንደገና መሥራት ነበር። ይህ ነገር በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው፥ በጥንት ዘመን ሕዝቦች ድንገት ከሚመጣ የጠላት ጦርና ከሚዘርፍ ወራሪ የሚከላከሉበት ዋናው መንገድ የከተማ መከለያ ቅጥር ነበር፤ ስለዚህ በኢየሩሳሌም ከተማ ዙሪያ ቅጥር እስከሌለ ድረስ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሰላም ሊኖራቸውና የደኅንነት ዋስትና ሊያገኙ አይችሉም ነበር። ይልቁንም በማያቋርጥ ፍርሃት መኖር ዕጣ ፈንታቸው ነበር። ልክ ቅጥሩ እንደተሠራ ሕዝቡ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ላይ በማተኮር የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማትና ለመታዘዝ የነበራቸውን ፈቃደኝነት ማየት የሚያስገርም ነው።

ሁለተኛ፡- የኢየሩሳሌም ቅጥሮች የእግዚአብሔር ሕዝብ ያሉበት መንፈሳዊ ሁኔታ ምልክት ነበሩ። ቅጥሮቹ እስካልተሠሩ ድረስ እግዚአብሔር ስሙን ሊያኖርባትና ሊመለክባት ተስፋ ለሰጣት ለዚህች ከተማ በቂ ትኩረት እንደሌለ የሚያሳይ ነበር። እግዚአብሔር ሊመለክበት ባለው ስፍራ ስሙን ለማኖር ቃል ገብቶ ነበር። የእግዚአብሔር ከተማ የነበረችው የኢየሩሳሌም ውጫዊ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የልብ መንፈሳዊ አቋም የሚያንጸባርቅ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ የአብያተ ክርስቲያናቶቻችን ውጫዊ ሁኔታ ብዙ ጊዜ መንፈሳዊ ሁኔታቸውን የሚያመለክተው እንዴት ነው?

የነህምያ አስተዋጽኦ

 1. የነህምያ የመጀመሪያ አስተዳደር(1-12)

ሀ. ነህምያ ስለ ኢየሩሳሌም ሰማ (1) 

ለ. ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ (2)

ሐ. በኢየሩሳሌም ቅጥር ይሠሩ የነበሩ ሰዎች ዝርዝር (3) 

መ. የኢየሩሳሌም ቅጥር ሥራ የገጠመው ተቃውሞ (4) 

ሠ. የኢየሩሳሌም ቅጥር ሥራን ያስቆሙ ውስጣዊ ችግሮች (5) 

ረ. የቅጥሩ ሥራ ተፈጸመ (6) 

ሰ. ወደ ይሁዳ የተመለሱ ምርኮኞች ዝርዝር (7) 

ሸ. በዕዝራ አመራር ሥራ የተነሣ መንፈሣዊ መነቃቃት (ተሐድሶ)(8-10) 

ቀ. በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎች ተመረጡ (11) 

በ. የካህናት ዝርዝርና የቅጥሩ መመረቅ (12) 

 1. የነህምያ ሁለተኛ አስተዳደር፥ መንፈሳዊ ተሐድሶ (13) 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ 

ልክ እንደ መጽሐፈ ሳሙኤል፥ ነገሥትና ዜና መዋዕል መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያም በዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን አንድ መጽሐፍ ነበሩ። ዕዝራና ነህምያ በጊዚያቸው የተፈጸመውን ድርጊት እየተከታተሉ ራሳቸው የመዘገቡት ቢመስልም፥ ብዙ ምሁራን የሚስማሙት ጽሑፎቹን የሰበሰባቸውና ወደ አንድ መጽሐፍ በማጠቃለል ያቃናቸው ሌላ ሰው እንደሆነ ነው።

የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ በኋላ ወደ ግሪክ ቋንቋ ሲተረጎም፥ ተርጓሚዎቹ አንድ የነበረውን መጽሐፍ ለሁለት ከፈሉት። በግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሁለት መጻሕፍት 1ኛና 2ኛ ዕዝራ በመባል ይታወቃሉ። በኋላ የእነዚህ መጻሕፍት ርዕስ የመጀመሪያው ዕዝራ፥ ሁለተኛው ደግሞ ነህምያ ተብሎ ተሰየመ። እነዚህን ስያሜዎች ያገኙት በመጻሕፍቱ ውስጥ ባሉት ዋና ገጸ ባሕርያት በዕዝራና በነህምያ ነው።

የመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ጸሐፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ በማን እንደተጻፉና እንዴት እንደተጻፉ ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው። የአብዛኛዎቹ አስተሳሰብ ዕዝራና ነህምያን የጻፈው ዜና መዋዕልን የጻፈው ሰው ነው የሚል ነው። ይህንንም ያሉበት ምክንያት የመጽሐፈ ዜና መዋዕል አጨራረስና የመጽሐፈ ዕዝራ አጀማመር ተመሳሳይ በመሆኑ ነው። በተጨማሪ በአጻጻፍ ስልቱም ተመሳሳይነት እናገኛለን።

ሌሎች ምሁራን ደግሞ መጻሕፍቱ ብዙ ተመሳሳይነት ቢኖራቸውም፥ የተጻፉት ግን በተለያዩ ጸሐፊዎች ለመሆኑ የሚያሳምኑ በቂ ልዩነቶች እናገኛለን ይላሉ።

ምሁራን መጽሐፈ ዕዝራንና ነህምያን ያቀናበረው ሰው የተጠቀመባቸው ሦስት የተለያዩ ምንጮች አሉ ይላሉ። በመጀመሪያ፣ ዕዝራ በእርሱ ዘመን ስለተፈጸሙት ክስተቶች ዘግቧል። ሁለተኛ፥ ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እንዴት እንደሠራ ዘግቧል። ሦስተኛ ደግሞ፥ በሼሺባዛር (ዘሩባቤል) መሪነት አይሁዶች በመጀመሪያ እንዴት ወደ ኢየሩሳሌም እንደተመለሱ የሚናገር የተለየ ዘገባ ነበር። መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያን በአንድ ላይ እንዲሆኑ ያደረገው ሰው ከሦስት የታሪክ ምንጮች በማሰባሰብ በአንድ መጽሐፍ እንዲጠቃለል አድርጓል።

ጸሐፊው ዕዝራ በእርሱ ስም የተሰየመውን የመጀመሪያ መጽሐፍ ጽፎ ሊሆን ይችላል። በፋርስ መንግሥት ውስጥ ሥልጣን የነበረው ሰው ስለነበር፥ አይሁድ ወደ ይሁዳ እንዲመለሱ የተፈቀደበትን ማዘዣ ቅጂና ሌሎች የቤተ መንግሥት መዛግብት ቅጂዎች ኖረውት ሊሆን ይችላል። ከዚህም የተነሣ አይሁድ እንዴት ወደ ምድራቸው እንደተመለሱና ዕዝራ ከስንት ዓመታት በኋላ በምድሪቱ መንፈሳዊ መነቃቃትን እንደመራ አጭር መግለጫ ጽፎ ሊሆን ይችላል። መጽሐፈ ነህምያ የተጻፈው በነህምያ ሊሆን ይችላል። መጻሕፍቱ ባላቸው ተመሳሳይነት ምክንያት፥ የመጨረሻው ሰው መጠነኛ ለውጦችን አድርጎ ወደ አንድ መጽሐፍ አዋሕዶአቸው ሊሆን ይችላል። መጽሐፈ ዕዝራ ከሌዊ ነገድ በሆነ፥ ከምርኮ በኋላ በእስራኤላውያን ታሪክ ውስጥ ታላቅ ሚና በተጫወተና ትልቅ ስፍራ በነበረው ዕዝራ በተባለ ጸሐፊ ስም ተሰይሟል። ዕዝራ የተወለደው በምርኮ ምድር ነበር። ያደገውም በባቢሎን ነበር። ለዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ ስላስተማሩት፥ ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ዕዝራ በባቢሎን ምድር እስራኤላውያንንና የብሉይ ኪዳን ሕግን የሚያውቅ ዝነኛ ሰው እየሆነ እንደመጣ ይመስላል። አንዳንድ ምሁራን ዕዝራ በፋርስ መንግሥት ውስጥ የአይሁድ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ እንደተሾመ ይገምታሉ። የፋርስ ንጉሥ ከነበረው ከአርጤክስስ ጋር ግንኙነት የነበረውም ለዚህ ነበር። በ538 ዓ.ዓ. ሕዝቡ በዘሩባቤል መሪነት ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ ዕዝራ ያልተመለሰበትን ምክንያት አናውቅም። ምናልባት በጣም ወጣት ስለነበረ ይሆናል። በ458 ዓ.ዓ. ግን ዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ ከፋርስ ንጉሥ ፈቃድ አገኘ። ንጉሡ ከቤተ መንግሥቱ ገንዘብ እንዲጠቀም ለዕዝራ ፈቃድ ሰጠው። ዕዝራ አንዳንድ ሌዋውያን ከእርሱ ጋር እንዲመለሱ በማሳመን፥ በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚደረገውን አምልኮ በመምራት ይረዱት ዘንድ አደረገ።

ዕዝራ ወደ እስራኤል ከተመለሰ በኋላ በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ሚናን ተጫወተ። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር ዕዝራን ሁለት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ለመምራት ተጠቀመበት (ዕዝራ 9-10፤ ነህ. 8-9)። ሁለተኛ፥ ዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ በጥንቃቄ በማጥናት የታወቀ ሰው ነበር። ለዚህ ነው አይሁድ በሕግ ሥራና እውቀት «የተካኑ» የሃይማኖት መሪዎች አባት አድርገው የሚቆጥሩት። በአዲስ ኪዳን የተጠቀሱት የፈሪሳውያንና የጸሐፍት አባት ነበር። በዕዝራ ዘመን ከምርኮ የተመለሱ አብዛኛዎቹ አይሁዳውያን የራሳቸው የሆነውንና መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን የዕብራይስጥን ቋንቋ ስለማያውቁ ዕዝራና ሌሎች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለእነርሱ ለመተርጎም ተገድደው ነበር። አብዛኛዎቹ አይሁድ የባቢሎንና የፋርስ የንግድ ቋንቋ የነበረውን አራማይክን ብቻ ያውቁ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የመጠቁ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉ፥ በዚህ ሁኔታ በሚገባ የሠለጠኑ ሰዎችን ስም ዝርዝር።

መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ የተጻፉበት ጊዜ 

የመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ጸሐፊ ማን እንደሆነ ስለማናውቅ የተጻፉበትንም ጊዜ በእርግጠኝነት ማወቅ አንችልም። በመጽሐፉ ውስጥ የተገለጡ ድርጊቶች የተፈጸሙት ከ538-420 ዓ.ዓ. ባለው ዘመን ነበር፤ ስለዚህ መጽሐፉ በ400 ዓ.ዓ. አካባቢ ተጠናቅቆ ሳይጻፍ እንዳልቀረ መገመት ይቻላል።

የመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ሥረ – መሠረት 

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ዜና 36፡15-19 አንብብ። ሀ) የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስና ቅጥሮች ምን ሆኑ? ለ) የይሁዳ ሕዝብና ንጉሡስ ምን ሆኑ?

እንደምታስታውሰው በ2ኛ ነገሥትና በ2ኛ ዜና መጨረሻ ላይ የይሁዳ ሕዝብ በባቢሎናውያን መማረካቸውን ተመልክተናል። ቤተ መቅደሱና የኢየሩሳሌም ከተማም ተደምስሰዋል። ንጉሡም ተገድሉ ሕዝቡ ተማረኩ። ይህ ሁሉ የሆነው በ586 ዓ.ዓ. ነበር። ዋና ዋና የሆኑ ምርኮዎች የተፈጸሙት ሦስት ጊዜ ብቻ ቢሆንም፥ የባቢሎን ንጉሥ አይሁዳውያንን በምርኮ የወሰደው አራት ጊዜ ይመስላል። በመጀመሪያ፥ ዳንኤልና ሌሎች በምርኮ የተጋዙት በ605 ዓ.ዓ. ሲሆን፥ ሁለተኛ፥ ሕዝቅኤልና ንጉሡ ኢዮአኪን የተጋዙት በ597 ዓ.ዓ. ነበር። ሦስተኛ፥ በ586 ዓ.ዓ. ቤተ መቅደሱ የፈረሰበትና አብዛኛውን ሕዝብ የሚመለከት ዋናው ምርኮ ተፈጸመ፤ ነገር ግን ሌላ አራተኛ መማረክም በ582 የነበረ ይመስላል (ኤር. 52፡30)። የቀሩት አንዳንድ እስራኤላውያን ወደ ግብፅ ሸሽተው ሄዱ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)