መጽሐፈ ነገሥት ከአዲስ ኪዳን ጋር ያለው ግንኙነት

ከመጸሐፍ ነገሥት የተጠቀሱ በርካታ ጥቅሶች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ባይኖሩም በ1ኛና በ2ኛ ነገሥት የተፈጸሙ ድርጊቶችን የመረዳት ጉዳይ ግን በአዲስ ኪዳን በአጠቃላይ እናገኛለን። በአዲስ ኪዳን ሰሎሞን በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። ማቴ. 1፡1-17 ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ኢየሱስ ያለውን የጌታን የዘር ግንድ ያሳየናል። በእነዚህ ጥቅሶች በመጽሐፈ ነገሥት የተጠቀሱት አብዛኞቹ ነገሥታት ተዘርዝረዋል። የሰሎሞን ጥበብና ሀብት አንዳንድ ጊዜ ተጠቅሷል (ለምሳሌ፡- ማቴ. 12፡42፤ ሉቃስ 12፡27)።

የ1ኛና የ2ኛ ነገሥት ታሪኮች በቀጥታ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ባያመላክቱም፥ ከቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ጠቃሚ እውነቶችን ማየት እንችላለን። በብሉይ ኪዳን የድነት (የደኅንነት) ግንድ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን የትንቢት መስመር እናገኛለን። ይህ ትንቢት የጀመረው የሰይጣንን ራስ እንደሚቀጠቅጥ የተነገረለት የሴቲቱ ዘር ጉዳይ ከተጠቀሰበት ከኦሪት ዘፍጥረት ነው (ዘፍ. 3፡15)። ይህ መስመር ከዚያ እስከ አብርሃም፥ ቀጥሎም እስከ ዳዊት፥ ከዚያም በይሁዳ ነገሥታት በኩል ያለፈ ነው።

ሰይጣን የአብርሃምና የይሁዳ የዘር ግንድ ልዩ እንደ ነበረና መሢሑ ከዚያ እንደሚመጣ ያውቅ ነበር። ስለዚህ በታሪክ መጻሕፍት በተደጋጋሚ ሰይጣን ይህንን የዘር ግንድ እንዴት ሊያጠፋ እንደሞከረ የሚያሳየውን የተደበቀ እውነት እናያለን። በዘፍጥረት ሰይጣን የግብፅን ንጉሥ በመጠቀም ሣራን እንደ ሚስቱ እንዲወስድና የአብርሃም የዘር ግንድ እንዲቋረጥ ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ሰይጣን ድርቅና ራብን በመጠቀም የእስራኤልን ቤተሰብ ለማጥፋት ቢሞክርም፥ እግዚአብሔር በዮሴፍ ተጠቅሞ እንዴት ከራብ እንዳዳናቸው እይተናል።

በ2ኛ ሳሙኤል ለዳዊት ዘር የተሰጠውን የዘላለም ዙፋን ተስፋ ተመልክተናል። በመጽሐፈ ነገሥት በአጠቃላይ የምናየው፥ ለዘላለም ዙፋን የተሰጠው ቃል ኪዳን ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ እንዴት እስከ ምርኮ ታሪክ ድረስ እንደመጣ ነው። ጎተልያ የተባለችው ክፉ ንግሥት ታሪክ የሚያሳየው፥ የዳዊትን ዝርያ እንዳለ በማጥፋት ሰይጣን የእግዚአብሔርን ዕቅድ ለማበላሸት እንዴት እንደሞከረ ነው። የዳዊት ንጉሣዊ ቤተሰብ በሙሉ የጠፋና ከእርሱ የዘር ግንድ አንድ ሰው ብቻ የቀረ ይመስላል። ሰይጣን ያንን የቀረውን ሰው ማስገደልና መስመሩ እንዲቋረጥ ማድረግ ቢችል ኖሮ መሢሑ በዳዊት ዘር በኩል መምጣቱን ሊያስቀር ይችል ነበር። እግዚአብሔር ግን አንድ ሰው እንዲቀርና የዳዊት የዘር ግንድም እንዲጠበቅ አደረገ። ኢየሱስ በቤተልሔም ትንሽ ሕፃን በነበረ ጊዜ ሄሮድስ ሊያስገድለው መሞከሩ በሰይጣንና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የዚያው ጦርነት ክፍል ነበር። 

ሰይጣን እግዚአብሔርን ለማሸነፍ የቱንም ያህል ቢጥርም ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ይሸነፋል። ሰይጣን ምንም ያህል ተግቶ ቢሠራም፥ እግዚአብሔር ለእኛና ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ዕቅድ ሊደመሰስ አይችልም። 

የውውይት ጥያቄ፥ በስደት፥ በሐሰት ትምህርት፥ ወዘተ በምንጠቃበትና የተሸነፍን በሚመስለን ሰዓት ይህ እውነት እንዴት ያበረታታናል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

2ኛ ነገሥት 18-25

ለእግዚአብሔር ሕዝቦች በጣም ጥሩ መምህራን ከሆኑት ነገሮች አንዱ ታሪክ መሆን አለበት። ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ነገሮች ብዙ ጊዜ ወደፊትም ይደገማሉ። ከዚህ ቀደም በነበረው ዘመን የእግዚአብሔር ሰዎች ችግር ገጥሟቸው ከነበረ ወደፊትም ተመሳሳይ ችግር እንደሚገጥማቸው ጥርጥር የለውም። የሐሰት ትምህርቶችን በምሳሌነት ውሰድ። ዛሬ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስቸግሩ የሐሰት ትምህርቶችን፥ በአብዛኛው ከዚህ ቀደም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያስቸግሩ የነበሩ ናቸው። ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ቀደም የሐሰት ትምህርቶችን ያስተናገደችበት መንገድ፥ ዛሬ የሐሰት ትምህርቶችን በሚመለከት ትምህርት ሊሆንን ይገባል። የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ማጥናት አስፈላጊ የሆነበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። እንደዚሁም በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑትን የአይሁድ ታሪክ ልናጠና አስፈላጊ የሆነበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። እንደዚሁም እነርሱም ልክ እንደ እኛ ሰዎች ስለነበሩ፥ የገጠሟቸው ችግሮችና ፈተናዎች እኛንም ይገጥሙናል። እነርሱን በአስቸገሯቸው ተመሳሳይ ኃጢአቶች የመውደቅ ዝንባሌ በእኛም ላይ ይታያል ማለት ነው (1ኛ ቆሮ. 10፡11 ተመልከት)። 

የይሁዳ ሕዝብ ከታሪክ ለመማር አልቻለም። ወገኖቻቸው የሆኑ እስራኤላውያን ወደ ምርኮ የተወሰዱት ለእግዚአብሔር መታዘዝና እርሱን ምምለክ እምቢ ስላሉ ነበር። ከዚህ ተምረው ወደ እግዚአብሔር ከመመለስ ይልቅ፥ ልክ በሰሜኑ መንግሥት እንደነበሩት እስራኤላውያን ተማርከው እስኪሄዱ ድረስ በኃጢአታቸው ቀጠሉ። ታሪክ ራሱን በመድገም፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደ ወገኖቻቸው እስኪማረኩ ድረስ የወገኖቻቸውን ኃጢአት አደረጉ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የቀድሞ አባቶቻችን በወደቁበት ተመሳሳይ በሆነ ኃጢአትና ችግር ስለ መውደቅ ዝንባሌ ከዚህ ምን እንማራለን? ለ) የራስህን ቤተ ክርስቲያንና በዘመናት ሁሉ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናትን ታሪክ ማጥናት እጅግ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ስለ ታሪካችሁ በቤተ ክርስቲያንህ የሚገኙ ሌሎች መሪዎችን ማስተማር የምትችሉት እንዴት ነው? መ) ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ልታቀርብ ስለምትችላቸው ነገሮች አሳብ ስጥ።

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ነገሥት 18-25 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ዓመታት በይሁዳ የነገሡትን ነገሥታት ዘርዝር። ለ) የእያንዳንዳቸው ባሕርይ ምን ይመስል ነበር? ሐ) የእነዚህ ነገሥታት ዘመናት ዋና ዋና ተግባራት ምን ነበር? መ) የይሁዳን ውድቀትና ሕዝቡ ለምን ወደ ምርኮ እንደተወሰዱ ግለጥ።

እስራኤል በምርኮ የተወሰደችው በ722 ዓ.ዓ. ነበር። እስራኤላውያን በሕዝብነት ወደ አገራቸው ጨርሶ አልተመለሱም። ይልቁንም በዓለም ሁሉ ባሉ ሕዝቦች መካከል ተበተኑ። ይህ ሕዝብ ምን እንደደረሰባቸው ስለማይታወቅና ወደ አገራቸው ጨርሶ ስላልተመለሱ፥ አንዳንድ ሰዎች «የጠፉት አሥሩ የእስራኤል ነገዶች» በማለት ጠርተዋቸዋል። እግዚአብሔር ወደፊት አንድ ቀን ወደ አገራቸው እንደሚመልሳቸው ተስፋ ሰጥቶአቸዋል (ኢሳ. 11፡11-16)። ዘመናዊው የእስራኤል መንግሥት በ1948 ዓ.ም. መመሥረቱ የዚህ ቃል ኪዳን ከፊል ፍጻሜ ነው።

ይሁዳ የተባለው የእስራኤላውያን ደቡባዊ መንግሥት፥ አገራቸውን ለ136 ዓመታት ለማቆየት ችሉ ነበር። የይሁዳ መንግሥት ወደ ምርኮ የተወሰደው በ586 ዓ.ዓ. ነበር። በእግዚአብሔር ጸጋ ምክንያት ግን የዚህ ሕዝብ ቅሬታዎች ከ50 ዓመታት በኋላ በ539 ዓ.ዓ. ወደ አገራቸው ለመመለስ ችለዋል። ይህንን ጉዳይ በይበልጥ በመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ውስጥ እናጠናለን። 

 1. የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ፡- (716-687 ዓ.ዓ.) 

ሕዝቅያስ ወጣት በነበረ ጊዜ፥ የእስራኤልን ሕዝብ ውድቀትና እንዴት ወደ ምርኮ እንደ ተወሰዱ በዓይኑ ተመልክቷል። ይህ ነገር ሕይወቱን በጣም ሳይነካው አልቀረም፤ ስለዚህ ወደ ንጉሥነት ሥልጣኑ በመጣ ጊዜ እንደ አባቱ እንደ አካዝ ሳይሆን፥ እግዚአብሔርን ፈራ። ሕዝቅያስ ታላቅ ሃማኖታዊ መሪ ነበር። የይሁዳን ሕዝብ እግዚአብሔርን ወደ ማምለክ ለመመለስ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል። ከዳዊት ቀጥሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ከሁሉ የተሻለ በመሆኑ የሚጠቀስ ታላቅ መሪ ሕዝቅያስ ነው።

ሕዝቅያስ በአሦር መንግሥት ቁጥጥር ሥር ቢሆንም፥ የሕዝቡን ሃይማኖታዊ ሕይወት ለመለወጥ የሚሠራበት ነፃነት ነበረው። እስራኤላውያን ወደ ምርኮ የተወሰዱት እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ላደረገው ቃል ኪዳን ባለመታዘዛቸው እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር፡ ስለዚህ ሕዝቅያስ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ አጥብቆ ጣረ። ለረጅም ጊዜያት ተዘግቶ የነበረውን ቤተመቅደስ በመክፈት እና በመጠገን ለአምልኮ የሚመች መልካም ስፍራ አደረገው። በእስራኤል ቀርተው የነበሩ አይሁዳውያንን ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም በመምጣት እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ጋበዛቸው። የሐሰተኛ አምልኮ መሣሪያ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ለማጥፋት ጣረ። ሙሴ ከብዙ ዓመታት በፊት ሠርቶት የነበረውንና በኋላ እስራኤላውያን የአምልኮ መሣሪያ አድርገውት የነበረውን የነሐስ እባብ አጠፋ (ዘኁ. 21፡4-9 ተመልከት)። የቤተ መቅደሱ አምልኮ በሥርዓት እንዲካሄድ ሕዝቅያስ የሌዋውያንን አገልግሎትና አሥራትን የመሰብሰቢያ ዘዴዎችን በሚገባ አደራጀ። ሕዝቅያስ በዚያን ዘመን ከነበረው ከኢሳይያስ ጋር በቅርበት ሳይሠራ አልቀረም። 

ሕዝቅያስ በመጨረሻ ከአሦራውያን ጋር እንደሚዋጋ ያውቅ ነበር፣ ስለዚህ የይሁዳን ብሔር ለመከላከል በከተሞች ምሽግ ሠራ። አሦራውያንንም ለማረጋጋትና ለማስደሰት ከቤተ መቅደስ ወርቅ አውጥቶ ሰጣቸው፤ ሆኖም በ701 ዓ.ዓ. አሦራውያን ወረሩትና ከኢየሩሳሌም ከተማ በቀር የይሁዳን መንግሥት በጠቅላላ ወሰዱ። በግንቦች የታጠሩ አርባ ስምንት ከተሞች ተደመሰሱና 200000 አይሁድም በምርኮ ተወለዱ። ሕዝቅያስ ግን በእግዚአብሔር ስለታመነ፥ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከጥፋት አዳነ። የአሦር ንጉሠ ነገሥት ግዛት አንዱ ክፍለ ሀገር በነበረው በባቢሎን በተነሣው ዓመፅ የአሦር ጦር ወደ አገሩ ለመመለስ ግድ ሆነበት። 

በኋላም ሕዝቅያስ በጠና ታመመ። በእግዚአብሔር ምሕረት ግን 15 ዓመታት በዕድሜው ላይ ተጨመረለት። በዚህ ጊዜም ልጁ ምናሴ አብሮት መግዛት ጀመረ። ከበሽታው በማገገሙ ደስታቸውን ሊገልጹለት ለመጡት ለባቢሎን ልዑካን ባለማስተዋል ሀብቱን በሙሉ አስጎበኛቸው። ባቢሎናውያን አንድ ቀን ኢየሩሳሌምን እንደሚያጠፉና ወርቁን እንደሚወስዱበት ለመገንዘብ አልቻለም ነበር። 

 1. የይሁዳ ንጉሥ ምናሌ፡- (692-642 ዓ.ዓ.)

በይሁዳ ላይ ከነገሡ ነገሥታት ሁሉ ረጅም ዘመን የነገሠው ምናሴ ነው። ለ55 ዓመታት በሥልጣን ላይ ቆይቷል። ይህ ዘመን ከሕዝቅያስ ጋር አብሮ የገዛበትን ጊዜንም ይጨምራል።

ምናሴ ሕዝቅያስ ከሞተና ብቻውን ንጉሥ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በእግዚአብሔር ላይ ፊቱን በማዞር ጀርባውን ሰጠው። ሕዝቅያስ በይሁዳ ያደረጋቸውን ተሐድሶዎች በሙሉ ለማበላሸት አሰበ። ሕዝቡን ወደ ጣዖት አምልኮ መራ። ትላልቅ የአምልኮ ስፍራዎችንና የጣዖታት መሠዊያዎችን ለበአልና የአሞናውያን አምላክ ለሆነው ለሞሎክ አሠራ። ከኢየሩሳሌም ከተማ ውጭ ለሞሎክ ጣዖት ልጆቹን ሳይቀር ሰዋ። በቤተ መቅደሱ ውስጥ የጣዖት አምልኮን አቆመ። እግዚአብሔርን ለማምለክ የፈለጉትን እጅግ ብዙ ሰዎችን ገደለ። እንዲያውም የአይሁድ አፈ ታሪክ ኢሳይያስ የሞተው በምናሴ ትእዛዝ በመጋዝ ለሁለት ተሰንጥቆ ነው ይባላል። በምናሴ ዘመነ መንግሥት የእግዚአብሔር ሕዝብ የሥነ-ምግባር ሕይወት ተበላሸ። እንዲያውም አብረዋቸው ከነበሩት ከነዓናውያን የባሰ ተበላሹ።

በምናሴ ዘመነ መንግሥት ይሁዳ ለአሦር መንግሥት እንደ ባሪያ ነበር፤ ነገር ግን ባቢሎን በአሦር ላይ በምታምፅበት ጊዜ ምናሴም በአሦር ላይ ለማመፅ ሞከረ። ሆኖም ወደ አሦር በምርኮ ተወሰደና በኋላ ተለቀቀ (2ኛ ዜና 33፡10-13 ተመልከት)። ምናሴ በምርኮ ላይ በነበረበት ጊዜ ከክፉ ተግባሩ ሁሉ የተመለሰ ይመስላል። ወደ ይሁዳ በተመለሰ ጊዜም ሕዝቡ እግዚአብሔርን ወደ ማምለክ እንዲመለሱ አበረታታ፤ ነገር ግን በዚህ ተግባሩ ብዙ ውጤታማ መሆን አልቻለም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የአንድ ሰው መንፈሳዊ እምነት ወደ ልጆቹ ሊተላለፍ እንደማይችል፥ የምናሴ ሕይወት ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው? ለ) ወላጆች ልጆቻቸውን የእግዚአብሔርን መንገድ ሊያስተምሯቸው የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? 

 1. የይሁዳ ንጉሥ አሞን፡- (643-641 ዓ.ዓ.)

ስለ አሞን አገዛዝ ብዙ የምናውቀው ነገር የለም፤ ነገር ግን እንደ አባቱ እንደ ምናሴ የመጨረሻ የሕይወት ዘመን ሳይሆን፥ ምናሴ ሕዝቡን ወደ ጣኦት አምልኮ እንደመራባቸው እንደ መጀመሪያው ዘመን ኖረ። አሞን በይሁዳ ሰዎች ተገደለና ልጁ ኢዮስያስ በእርሱ ፈንታ ነገሠ። 

 1. የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ (641-609 ዓ.ዓ.) 

ኢዮስያስ በይሁዳ ላይ በነገሠ ጊዜ የ8 ዓመታት ልጅ ነበር። በይሁዳ ላይ ከነገሡና እግዚአብሔርን ይፈሩ ከነበሩ መሪዎች ኢዮስያስ የመጨረሻው ነበር። ከኢዮስያስ ሞት በኋላ፥ በባቢሎናውያን ወደ ምርኮ እስኪወሰድ ድረስ የይሁዳ ብሔር በጣም ፈጣን በሆነ ሁኔታ እየተዳከመ ሄደ።

ኢዮሳያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሦር መንግሥት መውደቅ ጀምሮ ነበር። ይህም ኢዮሳያስ የእስራኤል ግዛት የነበረውን አንዳንድ ምድር ለመውሰድ እስኪችል ድረስ ግዛቱን ለማስፋፋት ረዳው። በዘመነ መንግሥቱ መጨረሻ አካባቢ፥ በ612 ዓ.ዓ. የአሦር ዋና ከተማ የሆነችው ነነዌ በባቢሎናውያን እጅ ወደቀች።

ኢዮስያስ ከነገሠ ከ10 ዓመታት በኋላ አንድ ነገር ልቡን ለወጠውና እግዚአብሔርን እንዲከተል አደረገው። ኢዮስያስ እግዚአብሔርን መፈለግና የሕዝቡን ልብ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ መሥራት ጀመረ። ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን በመሥራት ላይ ሳሉ፥ ከስምንት ዓመታት በኋላ ፔንታቱክ ብለን የምንጠራቸው የሙሴ ሕግጋት በቤተ መቅደሱ ተገኙ። ለብዙ ዓመታት ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብ ያልቻሉ ይመስላሉ። ይልቁንም የእግዚአብሔር ቃል በምናሴ ዘመነ መነግሥት በቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ሳይሸሸግና ሳይጣል፥ ሳይረሳም አልቀረም።

የእግዚአብሔር ቃል ተገኝቶ በዘዳግም 27-28 የተጻፉት መርገምቶች ሁሉ በተነበቡ ጊዜ፥ በይሁዳ ሕዝብ ላይ ፍርዱ በደጅ እንደ ቀረበ ኢዮስያስ አወቀ። እግዚአብሔርም ነቢያትን ወደ ኢዮስያስ ላከና የኢየሩሳሌም ጥፋት የማይቀር እንደሆነና እርሱ እግዚአብሔርን ስለፈራ ግን በእርሱ ዘመነ መንግሥት ይህ እንደማይፈጸም አስታወቀው። ኢዮስያስም ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ለመመለስና ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ቃል ኪዳን ለማደስ ተግቶ ሠራ። ለጣዖት አምልኮ የሆኑ መሣሪያዎችን በሙሉ አጠፋ። እስከ ቤቴል ድረስ ሳይቀር ሄዶ ቀዳማዊ ኢዮርብዓም ከ300 ዓመታት በፊት ያቆማቸውን ጣዖታት አፈራረሰ። ይህንንም በማድረጉ አንድ ያልታወቀ ነቢይ የተነበየውን ትንቢት ከፍጻሜ አደረሰው፤ (1ኛ ነገሥት 13 ተመልከት)። ኢዮስያስ ለጣዖት አምልኮ የሚያገለግሉ ውጫዊ ነገሮችን ሊያጠፋ ቢችልም፥ በሰዎቹ ውስጣዊ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ማድረጉ ግን እጅግ አጠራጣሪ ነው። ምክንያቱም ኢዮስያስ እንደሞተ ሕዝቡ ወደ ጣዖት አምልኮ ተመልሰዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የሐሰተኛ አምልኮ አካሄድን ወይም የሰዎችን ውስጣዊ ልብን መለወጥ ከውጫዊ ነገሮች ይልቅ የበለጠ አስቸጋሪና ከባድ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ለማያምኑ ሰዎች በምንመሰክርበት ጊዜ ወይም የቤተ ክርስቲያን ሰዎችን በምናስተምርበት ጊዜ በውጫዊ ለውጥ ላይ ከማተኮር ይልቅ በውስጣዊ ለውጥ ላይ የማተኮር አስፈላጊነት ይህ ምን ያስተምረናል?

በኢዮስያስ ዘመን ያገለግል የነበረው ዋና ነቢይ ኤርምያስ ነበር።

በ609 ዓ.ዓ. ኢዮስያስ ብልህነት የጎደለው ስሕተት ፈጸመ። የግብፅ ንጉሥ ከአሦር ጋር በመተባበር አዲሱን ኃያል መንግሥት ባቢሎንን ለመውጋት ወደ ሰሜን በሚጓዝበት ጊዜ በይሁዳ በኩል ያልፍ ነበር። ኢዮስያስ ከግብፅ ንጉሥ ምንም ዓይነት ጠብ አጫሪነት ሳይኖር የግብፅን ንጉሥ ለመውጋት ሄደ፤ በጦርነቱም ቆሰለና ቆይቶ ሞተ።

 1. የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአሐዝ (ሻሉም) (609 ዓ.ዓ.)

ኢዮስያስ በሞተ ጊዜ፥ በእርሱ ምትክ ልጁ ኢዮአሐዝ ነገሠ፤ ነገር ግን በሥልጣን ላይ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ አልቻለም። ከሦስት ወራት በኋላ ግብፃውያን ከባቢሉን ጦርነት ሲመለሱ፥ ኢዮአሐዝ ቆይቶ ወደ ሞተበት ወደ ግብፅ ማርከው ይዘውት ሄዱ። 

 1. የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም (609-598 ዓ.ዓ.)

ግብፃውያን ኢዮአሐዝን ማርከው ሲወስዱ፥ ኢዮአቄም የተባለውን ወንድሙን በዙፋኑ ላይ አስቀመጡት። በዚያን ጊዜ ስሙን ወደ ኢዮአቄም ለወጡት። ግብፃውያን በተጨማሪ የይሁዳ መንግሥት ከባድ ቀረጥ እንዲከፍል አደረጉት።

በ605 ዓ.ዓ. የባቢሎን ንጉሥ የሆነው ናቡከደነፆር ብዙም ሳይቆይ ኢየሩሳሌምን አጠቃ። ኢዮአቄም ለእርሱ ራሱን ማስገዛት ግድ ሆነበት። በዚህ ጊዜ ናቡከደነፆር የይሁዳ ዋና ዋና ሰዎችን ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደ፡፡ ከእነዚህም መካከል ዳንኤል፥ ሐናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ይገኙበታል። ይህ በይሁዳ ላይ ከደረሰው ምርኮኝነት የመጀመሪያው ነበር።

ኤርምያስ በንጉሡ ኢዮአቄም ዘመንም አገልግሎአል። ኢዮአቄም ግን የኤርምያስን ቃል መስማት እምቢ አለና የጻፈውን የተቀደሰ ጽሑፍ አቃጠለ። ኢዮአቄም የጣዖት አምልኮን ከማበረታታቱም ሌላ አባቱ እንዳደረገው የእግዚአብሔርን መንገድ ሳይከተል ቀረ። ከዚህ የተነሣ እግዚአብሔር በኢዮአቄም ላይ ፈረደና ተገቢ የሆነው የንጉሣውያን ቤተሰብ የቀብር ወግ ሳያገኝ ቀረ። አንዳንድ ምሁራን በ598 ዓ.ዓ. ባቢሎንን ለመውጋት በተደረገ ጦርነት እንደሞተ ያስባሉ። 

 1. የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን (597 ዓ.ዓ.)

የኢዮአቄም ልጅ የሆነው ዮአኪን በሥልጣን ላይ የቆየው ለሦስት ወራት ብቻ ነበር፡፡ እርሱ የመንግሥት ሥልጣን በያዘ ጊዜ ይሁዳ ከባቢሎን ጋር በጦርነት ላይ ነበረች። ዮአኪን እጁን ለባቢሎን ሰጠ። ናቡከደነፆር በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበሩ የከበሩ ነገሮችን ሁሉ ዘረፈ። ዮአኪንና ሌሎች የይሁዳ ትላላቅ ሰዎችን በምርኮ አጋዛቸው። ሕዝቅኤል ተማርኮ የሄደው በዚህ ጊዜ ነበር። ዮአኪን በባቢሎን መልካም እንክብካቤ ተደረገለት። ከናቡከደነፆር ሞት በኋላ ከታሠረበት ከመለቀቁም በቤተ መንግሥት በእንክብካቤ ተያዘ። ወደ እስራኤልም ጨርሶ ሳይመለስ ቀረ። 

 1. የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ (ማታንያህ) (597-586 ዓ.ዓ.) 

ሴዴቅያስ የኢዮአሐዝ የመጨረሻ ልጁ ነበር። በሥልጣን ላይ ያስቀመጠው የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሲሆን፥ ማስተዳደር የሚችለውም በባቢሎን መንግሥት ሥልጣን ሥር ነበር። ለጊዜው ሴዴቅያስ ለባቢሎን መንግሥት ታማኝ ነበር፤ ነገር ግን ግብፅ በ588 ዓ.ዓ. በባቢሎን ላይ ስታምፅ ሴዴቅያስም ዓመፀ። ይህም በእርሱና በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ የባቢሎንን ሙሉ ቁጣ አስከተለ። በ586 ዓ.ዓ. ኢየሩሳሌም ተሸነፈች። የሴዴቅያስ ልጆችም በእርሱ ፊት ተገደሉ። ለዴቅያስንም ዓይኑን አውጥተው ወደ ባቢሎን በምርኮ ወሰዱት። ሌሎች ብዙ ሰዎችም ተማርከው ተወሰዱ። የኢየሩሳሌም ቅጥር፥ የሰሎሞን ቤተ መቅደስና አብዛኛው የከተማይቱ ክፍል ተደመሰሰ፡፡

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ኤርምያስ ለንጉሥ ሴዴቅያስ ምክር ሊሰጠው ቢሞክርም ሴዴቅያስ ኤርምያስን መስማት እምቢ አለና ኤርምያስን አሳደደው። 

 1. የይሁዳ ገዥ ገዳልያ 

ኢየሩሳሌም ከተደመሰሰች በኋላ ናቡከደነፆር ገዳልያን የይሁዳ ገዥ አደረገው፤ ይሁን እንጂ እስማኤል የተባለው የንጉሣውያን ቤተሰብ ዝርያ የነበረ ሰው ሥልጣኑን ስለፈለገ ገዳልያን ገደለው። በዚህ ምክንያት ሊመጣ ያለውን የባቢሎናውያንን ቁጣ በመፍራት፥ አብዛኛዎቹ አይሁዳውያን ወደ ግብፅ ሸሽተው ሄዱ። ኤርምያስንም ከእነርሱ ጋር እንዲሄድ አስገደዱት። እርሱም በዚያው በግብፅ ሞተ።

በ2ኛ ነገሥት የተጻፈው ታሪክ እጅግ አሳዛኝ ታሪክ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ ያለማቋረጥ ልባቸውን እንዳደነደኑና እውነተኛውን አምላክ ከማምለክ ይልቅ ሐሰተኛ አማልክትን እንዴት እንዳመለኩ ይናገራል፤ በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር የሰሜኑም ሆነ የደቡቡ መንግሥታት ወደ ምርኮ እንዲሄዱ አደረገ። ለደቡብ መንግሥት ግን ፍርዱ ጊዜያዊ ነበር። የኢየሩሳሌም ቅጥር ከፈረሰ ከ50 ዓመታት በኋላ እግዚአብሔር በአሕዛብ መንግሥታት ልብ ውስጥ በመሥራት፥ የራሱ ሕዝብ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ አደረገ። የሚያሳዝነው ግን አብዛኛዎቹ አይሁድ በምርኮ በነበሩበት ስፍራ ኑሮአቸው የሚያረካ ስለሆንላቸው ለመመለስ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ። እግዚአብሔር በሰጣቸው ምድር በድኅነት ከመኖር ይልቅ የዓለምን ምቾት መረጡ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከ2ኛ ነገሥት የተማርካቸውን መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህ ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያንህ አባላት መንፈሳዊ ዕድገት ውስጥ እንዴት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ? ሐ) እነዚህን ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ለሚገኙ ሌሎች ሰዎች የምታስተምርባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

2ኛ ነገሥት 13-17

ሕይወትንና ቤተ ክርስቲያንን በሚመለከት አንዱ አስደናቂ ነገር የሰው ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ ከሕይወት ወደ ሞት መሆኑ ነው። በሰው አነጋገር፣ እኛ የምንጓዘው ከሕይወት ወደ ሞት ነው። ቤተ ክርስቲያንም እንዲሁ ከሕይወት ወደ ሞት ለማዝገም ትሻለች። ለመከላከል አስቸጋሪ የሆነ የመፈራረስ ሂደት አለ። በመንፈሳዊ አባባል ደግሞ ይህ ሂደት ለእግዚአብሔር ካለን ፍቅር ወደ ሥርዓታዊ የሃይማኖት ልማድ፥ በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያን ሙት ወደምትሆንበት ሁኔታ ያደርሳል። ይህ ሂደት ብዙ ዓመታት የሚወስድ ቢሆንም እንኳ ለማቆም ግን አስቸጋሪ ነው። ይህ ዝንባሌ ያለማቋረጥ ልንዋጋውና ልንታገለው እንደሚገባ ኃይለኛ የስበት ኃይል እንዳለው ማግኔት ነው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ለእግዚአብሔር የነበረንን የመጀመሪያ ግላዊ ፍቅር ልንጠብቅና እንደ ቤተ ክርስቲያን ያለማቋረጥ ልናድግ እና ለእግዚአብሔር ክብር ልሠራ የምንችለው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በሕይወትህ ይህንን ወደ መንፈሳዊ ሞት የሚወስደውን ዝንባሌ እንዴት ተመለከትከው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ይህን ዝንባሌ የምታየው እንዴት ነው?

የእስራኤልና የይሁዳ ነገሥታትን በምንመለከትበት ጥናታችን፥ በመበላሸትና በመፈራረስ ወደ መንፈሳዊ ሞት የሚወስደውን ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ መመልከት እንችላለን። ምንም እንኳ እግዚአብሔርን የሚፈሩ መሪዎች ሕዝቡን ወደተገቢውና በእግዚአብሔር ላይ ወዳለው ትክክለኛ አምልኮ ለመምራት ቢሞክሩም፥ ሕዝቡ ወደ ጣዖት አምልኮ ለመመለስ ብዙ ጊዜ አይወስድባቸውም ነበር። በኃጢአት መውደቅና ከጌታ መራቅ ቀላል ነገር ነው። መንፈሳዊ መሠረታችንን እንደገና መገንባት ግን ብዙ ጊዜ በጣም አስቸጋሪ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ነገሥት 13-17 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ቁጥሮች የተጠቀሱትን ነገሥታት ዘርዝር። ለ) ስለ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ሥዕላዊ መግለጫ ስጥ። ሐ) በነገሡበት ዘመን ሰለተፈጸሙ ዋና ዋና ነገሮች ጥቀስ። መ) እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ በመፍረድ አይሁድን ወደ ምርኮ እንዲሄዱ ያደረገበት ምክንያት ምንድን ነው? 

 1. የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአካዝ፡- (814-798 ዓ.ዓ.)

የኢዮአካዝ ዘመን ለእስራኤል በጣም አስቸጋሪ ነበር። አዛሄል የተባለው የሶርያ ንጉሥ ያለማቋረጥ እነርሱን የጨቆነበትና በሰሜኑ መንግሥት ክልል ውስጥ ከፊሉን መሬት የወረረበት ጊዜ ነበር። እንደ ኤዶም፥ አሞንና ፍልስጥኤም ያሉ ሕዝቦች እስራኤልን ያጠቁበትም ጊዜ ነበር።

በመጨረሻም ኢዮአካዝ እጅግ ተስፋ ቆርጦ ፊቱን ወደ እግዚአብሔር መለሰና ከእርሱ እርዳታን ጠየቀ። እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ረዳውና የእስራኤልን ምድር በእንግዳ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ ከመወሰድ ጠበቀው።

ኢዮአካዝ እግዚአብሔር ቢረዳውም እንኳ ሙሉ ለሙሉ እርሱን አልተከተለም። ይልቁንም ከብዙ ዓመታት በፊት በቀዳማዊ ኢዮርብዓም የተጀመረውን የጣዖት አምልኮ ቀጠለ። 

 1. የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ፡- (798-782 ዓ.ዓ.) 

በዮአስ ዘመነ መንግሥት፥ የሶርያ ንጉሥ የነበረው አዛሄል ስለ ሞተ፥ እስራኤላውያን ከሶርያውያን ይደርስባቸው የነበረው ጭቆና ቀነሰ። ኤልሳዕ ብርቱ ደዌ ታሞ ከሞት አፋፍ ላይ ደርሶ በነበረበት ጊዜ ዮአስ ወደ እርሱ መጣ። ንጉሥ ዮአስ እግዚአብሔርን የማይከተል መሪ ቢሆንም እንኳ፥ የእግዚአብሔር ኃይላት በሙሉ ከእርሱ ጎን እንደሆኑና ኤልሳዕ የእግዚአብሔር ሰው እንደሆነ የተገነዘበ መሪ ነበር። ለዚህ ነው ኤልሳዕን «የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞች» ብሎ የጠራው። እውነተኛው የእስራኤል ጦር እግዚአብሔር ነበር እንጂ ሌላ ሥጋዊ ጦር አልነበረም። ኤልሳዕ የሶርያን ጦር ሽንፈት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። እስራኤልም ሶርያን ለማሽንፍና ከሰሜኑ የእስራኤል ክፍል የወሰደችውን ግዛት ሁሉ ለማስመለስ ችላ ነበር፤ በተጨማሪ ዮአስ ኤዶምንም ለማሸነፍ ችሉ ነበር።

በዮአስ ዘመነ መንግሥት በይሁዳ ንጉሥ ከነበረው ከአሜስያስ ጋር ጦርነት ተደርጎ ነበር። የእስራኤል ጦር ይሁዳን ለማሸነፍና የኢየሩሳሌምን ቅጥር የተወሰነ ክፍል ለመደምሰስ ችሎ ነበር።

ዮአስ እንደቀሩት የእስራኤል ነገሥታት ሁሉ የጣዖት አምልኮውን ቀጠለ። እግዚአብሔርን ለመፍራትና ለእርሱ ለመታዘዝም አልቻለም።

 1. የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ (796-767 ዓ.ዓ.)

አሜስያስ በይሁዳ ላይ ለብዙ ዓመታት የነገሠ ቢሆንም፥ አብዛኛውን የሥልጣን ዘመኑን ያጠፋው ከልጁ ከታዝያን ጋር ነበር። በአሜስያስ ዘመነ መንግሥት ይሁዳ በጣም ብርቱ ነበረች። ኤዶምንም ለማሸነፍ ችለው ነበር። ኤዶምን ካሸነፉ በኋላ ግን አሜስያስ ከኤዶም ጣዖትን አስመጣና በኢየሩሳሌም በማቆም አመለከው። ስላገኘው ድል ለእግዚአብሔር ክብርን ከመስጠት ይልቅ ጣዖትን አከበረ።

ቆይቶም አሜስያስ ባለማስተዋል ከእስራኤል ጋር ጦርነት ጀመረና ተሸነፈ (791-790 ዓ.ዓ.)። በዚህ ጊዜ አሜስያስ እስረኛ የነበረና የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዮአስ እስኪሞት ድረስ እንደገና ወደ ሥልጣኑ ለመመለስ ያልቻለ ይመስላል። በእርሱ ምትክ ግን ልጁ ዖዝያን ነግሦ ነበር። በኋላ ግን አሜስያስ ከእስሩ ተለቀቀና ወደ ይሁዳ ተመለሰ። ሕዝቡ ግን ጠልተውት ስለ ነበር ሊገድሉት አሴሩበት። አሜስያስ በዚህ ምክንያት ሸሽቶ ወደ ላኪሽ ከተማ ቢሄድም፥ ያሴሩበት ሰዎች ተከታትለው ገደሉት።

አሜስያስ የጣዖት አምልኮን የሚከተል ክፉ ንጉሥ ነበር። 

 1. የእስራኤል ንጉሥ ዳግማዊ ኢዮርብዓም (793-753 ዓ.ዓ.)

ከዓለም ታሪክ አመለካከት፥ ዳግማዊ ኢዮርብዓም በሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ከነበሩት ታላላቅ ነገሥታት አንዱ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን ስለ እርሱ የተነገረው ነገር በጣም ጥቂት ነው። ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ፍላጎት መንፈሳዊ ታላቅነትን መግለጽ እንጂ የፖለቲካ ዝናን ወይም ችሎታን ማሳወቅ አይደለም። ዳግማዊ ኢዮርብዓም የእግዚአብሔር ሰው ስላልነበረ፥ መጽሐፍ ቅዱስ አያመሰግነውም። በእስራኤል ላይ ለመንገሥ የመጀመሪያው በነበረው በቀዳማዊ ኢዮርብዓም የተጀመረውን የጣዖት አምልኮ ማካሄዱን ቀጠለ።

ከዳዊትና ከሰሎሞን ዘመነ መንግሥት በኋላ እጅግ ሰላምና ብልጽግና የሞላበት፥ ለእስራኤል መልካም የነበረ ጊዜ የዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ነበር። በሰሜን በኩል አንዳችም ኃያል መንግሥት ስላልነበረ ኢዮርብዓም ፖለቲካዊ ተጽዕኖውን እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ለማስፋፋት ችሎ ነበር። እስራኤልም እጅግ ባለጠጋ መንግሥት ሆና ነበር። ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ ያለውን የሶርያን ምድርም ወሰደች።

ሆሴዕና አሞጽ የተባሉት ነቢያት ያገለገሉት በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ነበር። በምድሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ብልጽግና የነበረ ቢሆንም፥ በሀብታምና በድሀ መካከል ከፍተኛ የሆነ የፍርድ አድልዎ ነበር። የሕዝቡ ሥነ-ምግባርም በእጅጉ ድቀት ይታይበት ነበር። ለእግዚአብሔር ባላቸው አምልኮም ግድ የለሾች ነበሩ።

የውይይት ጥያቄ፥ ብልጽግና፥ ወደ ፍርድ መዛባት፥ ወደ ሥነ-ምግባር ድቀት በእግዚአብሔር ላይ ወዳለ የአምልኮ ግድየለሽነት የሚያመራው እንዴት ነው?

 1. የይሁዳ ንጉሥ አዛርያ (ዖዝያን) (791-740 ዓ.ዓ.) 

ከዳዊትና ከሰሎሞን ዘመነ መንግሥት በኋላ፥ በይሁዳ ከነገሡ ታላላቅ ነገሥታት አንዱ ዖዝያን ወይም አዛርያ ነው። ጥሩ የፖለቲካ መሪ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔርን የሚፈራና የሚያመልክም ነበር። ዖዝያን በትረ መንግሥቱን በጨበጠ ጊዜ፥ የይሁዳ መንግሥት – በጣም ደካማ ነበር። ለእስራኤልና ለሶርያ አገልጋይ ነበር። ከዮአስ ሞት በኋላ ግን ይሁዳ ከእስራኤል ጋር መልካም ግንኙነት ነበራት። ዖዝያን የይሁዳን ጦር እንደገና መመሥረት ችሎ ነበር። እንደዚሁም ፍልስጥኤማውያን፥ ዓረቦችንና አሞናውያንን ለማሸነፍም ችሎ ነበር። ከዚህ ቀደም በሰሎሞን ጊዜ ብቻ እንደሆነው፥ ሕዝቡን ባለጸጋና በዚህም ተደስተው የሚኖሩ አደረጋቸው።

በዘመነ መንግሥቱ መጀመሪያ አካባቢ ዖዝያን እግዚአብሔርን አጥብቆ ተከተለ። እጅግ ባለጸጋ የሆነውም እግዚአብሔርን ስለተከተለና የእርሱን ትእዛዛት ስለ ጠበቀ ነበር (2ኛ ዜና 26፡5-7)።

በሥልጣንና በዝና እጅግ ከፍ ባለ ጊዜ ግን ታበየ። ካህናቱ ቢከለክሉትም እንኳ እምቢ ብሎ ወደ ቤተ መቅደስ በመግባት፥ ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን ዕጣን በመሠዊያው ላይ የማጠን ሥርዓትን ፈጸመ። ይህ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ የማመፅና ትዕቢትን የማሳየት ግልጥ ድርጊት ነበር። የእግዚአብሔር ፍርድ በዚህ ድርጊቱ ምክንያት ፈጣንና ኃይለኛ ቅጣትን መላክ ነበር። ዖዝያን ወዲያውኑ በለምጽ ተመታ። ይህም በሕይወቱ ላይ ዐበይት ውጤቶችን አስከተለ። ሞትን ባይሞትም እንኳ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር እንዳይገናኝ ተገለለ። በቤተ መንግሥቱ ውስጥም ለመኖር አይችልም ነበር። ወደ ቤተ መቅደሱ ለአምልኮ እንደገና መሄድ ጨርሶ አይችልም ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ልጁ ኢዮአታም በይሁዳ ላይ ተባባሪ ገዥ የሆነው። በዖዝያን ዘመነ መንግሥት መጨረሻ አካባቢ የአሦር መንግሥት በኃይሉ እጅግ ገናና እየሆነ ሄደ። ከአሦር ጋር ለመዋጋትና ለማሸነፍ ቢሞክርም አልሆነለትም። ተሸነፈ። ከዖዝያን ሞት በኋላም የይሁዳ መንግሥት ብርታት በፍጥነት እየቀነሰ መጣ። 

ዖዝያን ለ52 ዓመታት የነገሠ ቢሆንም፥ ብቻውን በንጉሥነት ሥልጣን ላይ የቆየው ግን ለ17 ዓመታት ብቻ ነበር። ከዚህ ቀጥሎ ከይሁዳ ታላላቅ ነገሥታት አንዱ የነበረው የዖዝያን ዘመነ- መንግሥት ዋና ዋና ዓመታት ተጠቅሰዋል፡-

797 ዓ.ዓ. አሜስያስ መንገሥ ጀመረ።

791 ዓ.ዓ. ፆዝያን ከአሜስያስ ጋር ይገዛ ጀመር። 

768 ዓ.ዓ. ዖዝያን ለብቻው መንገሥ ጀመረ። 

750 ዓ.ዓ. ዖዝያን በለምጽ ስለተመታ ኢዮአታም ከእርሱ ጋር መንገሥ ጀመረ። 

740 ዓ.ዓ. ዖዝያን ሞተ።

የውይይት ጥያቄ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሚሰምርላቸው ጊዜ በትዕቢት የመውደቅ አደጋ ከፊታቸው እንዳለ፥ ከዖዝያን ሕይወት ምን ለመማር እንችላለን? 

 1. የእስራኤል ንጉሥ ዘካርያስ (753 ዓ.ዓ.)

ዘካርያስ በእስራኤል ላይ ለረጅም ጊዜ ለመንገሥ አልቻለም። ለስድስት ወራት ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ በሻሎም ተገደለ። 

 1. የእስራኤል ንጉሥ ሻሎም (752 ዓ.ዓ.)

የዳግማዊ ኢዮርብዓም ልጅ የነበረውን ዘካርያስን ገድሉ በሥልጣን ላይ ከወጣ ከአንድ ወር በኋላ በምናሔም ተገደለ። 

 1. የእስራኤል ንጉሥ ምናሔም (752-741 ዓ.ዓ.)

ምናሔም በእስራኤል ላይ ለ10 ዓመታት ለመንገሥ ቢችልም፥ ዘመነ መንግሥቱ በጣም አስቸጋሪ ከነበሩት ጊዜያት አንዱ ነው። በዚህ ጊዜ የአሦር ኃይል ስለ ጨመረ፥ ጥቃት እንዳይደርስበት ከፈለገ ለአሦር ንጉሥ ቀረጥ የመክፈል ግዴታ ነበረበት።

 1. የእስራኤል ንጉሥ ፈቃሕያ (741-739 ዓ.ዓ.)

የምናሔም ልጅ የነበረው ፈቃሕያ የመንግሥት ሥልጣን በያዘ ጊዜ፥ የእስራኤል መንግሥት በአሦር መንግሥት ቁጥጥር ሥር ሆኖ አገልጋዩ ነበር። ስለዚህ ፈቃሕያ ብዙ ኃይል አልነበረውም። በእነዚህ ጊዜያት በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ በአሦር መንግሥት ቁጥጥር መሆናቸውን አይወዱትም ነበር። ከእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች አንዱ ፋቁሔ እንደነበር የማያጠራጥር ነው። ፋቁሔ ፈቃሕያን ገደለና የሚቀጥለው የእስራኤል ንጉሥ ሆነ። 

 1. የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ (739-731 ዓ.ዓ.)

በፋቁሔ ዘመነ መንግሥት ሶርያ ዋናዋ ኃያል መንግሥትና ለእስራኤል መንግሥት ፈተና ነበረች። የሶርያ ኃያል መሆን ለፋቁሔ የፀረ አሦር አቋም ትልቅ እርዳታ ሆኖት ነበር። ረአሶን የተባለው የሶርያ ንጉሥም አሦርን ለመውጋት ከእስራኤልና ከይሁዳ ሕዝቦች ጋር የጦር ቃል ኪዳን ትብብር ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ይሁዳ ይህን ትብብር (ፌዴሬሽን) ለመቀበል ሳትፈቅድ ስትቀር፥ ሶርያና እስራኤል በመተባበር ይሁዳን ወጉ። በዚህም ጦርነት ከኢየሩሳሌም በቀር ሌላው የይሁዳ ግዛት በሙሉ በእነርሱ እጅ ወደቀ። በመጨረሻም አካዝ የአሦርን እርዳታ በጠየቀ ጊዜ የሶርያና የእስራኤል ኃይሉች ወደ ግዛታቸው መመለስ ግድ ሆነባቸው።

ኢየሩሳሌም ሙሉ በሙሉ ያልተጠቃችበት ሁለት ምክንያቶች ነበሩ፡- 

 1. እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እንደሚፈርድ አንድ ነቢይ የእስራኤልን ንጉሥ አስጠነቀቀው።
 2. የይሁዳ ንጉሥ የነበረው አካዝ የአሦርን እርዳታ ለመነ፤ ስለዚህ የአሦር ንጉሥ የነበረው ቴልጌልቴልፌልሶር ሶርያን አጠቃ። በ732 ዓ.ዓ. የሶርያ ዋና ከተማ የነበረችው ደማስቆ ተደመሰሰችና አሥር ሶርያን ተቆጣጠረች።

በዚህ ጊዜ የአሦር መንግሥት እስከ እስራኤል ድንበር ድረስ ምድሪቱን ስለ ተቆጣጠረና የእስራኤልን መንግሥት ለማጥቃት የተዘጋጀ ስለ መሰለ፥ በመንግሥቱም ውስጥ የፀረ አሦር አስተዳደር ማካሄድ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም ነበር። ስለዚህ ፋቁሑ በሆሴዕ መሪነት ተገደለ።

እስራኤል የምትጠፋበት ጊዜ የቀረበ ቢሆንም የእግዚአብሔር ሕዝብ ግን ወደ እርሱ አልተመለሱም ነበር፤ ይልቁንም እስከመጨረሻው ድረስ የጣዖት አምልኮአቸውን ቀጠሉ።

 1. የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ኢዮአታም (750-732 ዓ.ዓ.)

ኢዮአታም መንገሥ የጀመረው ከአባቱ ጋር በአንድነት ሲሆን፥ ጠቅላላ አመራሩን ለብቻው የወሰደው ግን በ740 ዓ.ዓ. ነበር። ኢዮአታም የአባቱን የዖዝያንን የአመራር ፈለጎች (ፖሊሲዎች) የተከተለ ቢሆንም ለብቻው ለመግዛት የቻለው ግን ለ4 ዓመታት ብቻ ነበር። በቤተ መቅደስ ይካሄድ የነበረውን አምልኮ ደገፈ። ቀደም ሲል በይሁዳ የነበሩትን ጣዖታት ለማጥፋት ግን ቆራጥ አልነበረም።

ኢዮአታም አሦርን ለመደገፍ አልፈለገም። የይሁዳ መሪዎች ግን የአሦርን ኃይል መዳበር እየፈሩ ሲመጡ፥ ከአሶር ጋር በሰላም ለመኖር ፈለጉና ልጁን አካዝን የኢዮአታም ተባባሪ መሪ አደረጉት። በዘመነ መንግሥቱ መጨረሻ አካባቢም ከእስራኤልና ከሶርያ በኩል ችግር ገጥሞት ነበር። 

 1. የይሁዳ ንጉሥ አካዝ (735-716 ዓ.ዓ.)

አካዝ አባቱ በሥልጣን ላይ በነበረ ጊዜ እርሱም ወደ መንግሥት ሥልጣን የመጣው የአሦር ደጋፊ ስለነበረ ነው። አሦርን ለመውጋት ሶርያና እስራኤል እንዲተባበራቸው በጠየቁት ጊዜ እምቢ በማለቱ፥ እስራኤልና ሶርያ ይሁዳን አጠቁና ከይሁዳ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ምርኮ ወሰዱ። ስለዚህ እርዳታ ለመጠየቅ ተወካዮን ወደ አሦር ላከ። አሦርም ሶርያን አጠቃችና ደማስቆን አጠፋች። እስራኤላውያንም ከይሁዳ እንዲወጡ አደረጉ። አካዝም ለአሦር መንግሥት ለመገበር ተገደደ።

አካዝ የአባቱን መመሪያዎች ተቃረነ። ጣዖት አምላኪና በይሁዳ ከነገሡት እጅግ ክፉ ነገሥታት አንዱ ነበር። አካዝ ልጁን እንኳ ለጣዖት አምልኮ የሠዋ ሰው እንደሆነ ተጽፏል። አካዝ የአሦርን ንጉሥ ለመገናኘት ወደ ደማስቆ ሄደ። እዚያ እያለ አንድ ትልቅ የጣዖት መሠዊያ ያያል። የዚህን የጣዖት መሠዊያ ተመሳሳይ ያሠራና በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ ያኖረዋል። ከዚህ በኋላም ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለሌሎች የውሸት አማልክት በዚህ መሠዊያ ላይ መሥዋዕትን ያቀርቡ ዘንድ ሕዝቡን ያበረታታቸዋል።

የሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ወደ ምርኮ የተወሰደው አካዝ በይሁዳ ላይ ሥልጣን በነበረው ጊዜ ነበር። አካዝ እግዚአብሔርን ብቻ ያመልክ ዘንድ ለእርሱም ይታዘዝ ዘንድ ከእስራኤል ውድቀት አልተማረም። ነቢዩ ኢሳይያስ ያገለገለውና በእግዚአብሔር ላይ ይታመን ዘንድ አካዝን ለማበረታታት የሞከረው በዚህ ሰው ዘመነ መንግሥት ነበር። አንዳንዶቹ ትላልቅ የኢሳይያስ ትንቢቶች የተሰጡትም በዚህ ዘመን ነበር (ለምሳሌ፡- ኢሳ. 7፡14፤ 9፡6-7)። 

 1. የእስራኤል ንጉሥ ሆሴዕ (731-722 ዓ.ዓ.) 

ሆሴዕ ሥልጣን የያዘው የእስራኤል ንጉሥ የነበረውን ፋቁሑን በመግደል ነበር። ሆሴዕ ሥልጣን በያዘ ጊዜ ደማስቆ በአሥር እጅ የወደቀች ሲሆን፥ እስራኤልም የአሦር አገልጋይ ሆና ነበር። ከጥቂት የእስራኤል ግዛት በስተቀር አብዛኛው የእስራኤል ግዛት በአሦር ቁጥጥር ሥር ሆኖ ነበር። 

በ727 ዓ.ዓ. የአሦር ንጉሥ ሞተ። ይህንንም ሆሴዕ፥ የአሦር መንግሥት በእስራኤል ላይ የነበረውን የበላይነት ለማስወገድ ጥሩ ዕድል አድርጎ ቆጠረው፤ ስለዚህም ከግብፅ መንግሥት ጋር ተባበረ። በ725 ዓ.ዓ. ግን የአሦር መንግሥት የእስራኤል ዋና ከተማ የነበረችውን ሰማርያን አጠቃች። ለሦስት ዓመታት ከተማዋን ለመከላከል ቢችሉም፥ በ722 ዓ.ዓ. ግን የሰማርያ ከተማ ተደመሰሰች። ከ28000 የሚበልጡ ሰዎች ተገደሉ። የቀሩት እስራኤላውያንም በምርኮ ተግዘው በአሦር ግዛት በሙሉ፥ በተለይም በፋርስ ተበተኑ። በባቢሎን የነበሩ ሌሎች ሕዝቦች ደግሞ ወደ እስራኤል እንዲመጡና እንዲኖሩ ተደረገ። የሰሜኑ የእስራኤል ሕዝብ ከሌሎች ጋር በጋብቻ የተሳሰሩትና የተቀላቀሉት በዚህ ጊዜ ነበር። ስለዚህም እውነተኛ እስራኤላውያንም ሆነ ሙሉ አሕዛብ መሆናቸው ቀረ። እምነታቸውም ሙሉ በሙሉ ጣዖትን ማምለክ ወይም እውነተኛውን እግዚአብሔርን ማምለክ አልነበረም። ይልቁንም የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን አምልኮ ከአሕዛብ አምልኮ ጋር ቀላቀሉት። ዝርያዎቻቸውም በአዲስ ኪዳን ዘመን ሳምራውያን በመባል ይታወቁ የነበሩት ሲሆኑ፥ በአይሁዶችም የተጠሉትም የእግዚአብሔርን እውነተኛ አምልኮ ስላበላሹ ነበር።

እግዚአብሔር ሕዝቡ ወደ ምርኮ እንዲሄዱ የፈቀደው ለምን ነበር? የመጽሐፉ ጸሐፊ በ2ኛ ነገ. 17፡7-23 ለመመለስ የሚሞክረው ይህንን ጥያቄ ነው። እነዚህ ጥቅሶች እስራኤል በነገሥታት ዘመን የነበራትን ታሪክ በአጭሩ የሚያቀርቡና ከእግዚአብሔር ጋር የነበራትን ግንኙነት የሚናገሩ ናቸው። በአጭሩ የመጽሐፈ ነገሥት ጸሐፊ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ፥ አይሁድ በማያቋርጥ ሁኔታ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዙ እግዚአብሔር ቀጣቸው የሚል ነው። ትኩረት የተደገረበት ዋናው ኃጢአትም የጣዖት አምልኮና የውሸት አምልኮ ነው።

በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ያለውን የእስራኤልን የውድቀት ማሽቆልቆል መገንዘብ በጣም የሚያስገርም ነው። በመጀመሪያ፡- ጸሐፊው በሕዝቡ የተሳሳተ አምልኮ ላይ ያተኩራል። ጣዖታትን ያለማቋረጥ አመለኩ። 

ሁለተኛ፡- ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ፈቃደኞች አልነበሩም። እግዚአብሔር ሕዝቡን ያለማቋረጥ ወደ እርሱ መመለስ እንዳለባቸው ወይም ፍርዱን እንደሚቀበሉ በነቢያት ያስጠነቅቃቸው ነበር። ሦስተኛ፡- በአምልኮ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር፥ አይሁድ በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ መሰሉ። ልጆችን እንደ መሥዋዕት ይሠዉ ጀመር። በሥነ – ምግባር የወደቁና ጣዖት አምላኪ ሆኑ። አራተኛ፡- እግዚአብሔር ወደ ራሱ ሊመልሳቸው ይችል ዘንድ ጊዚያዊ ቅጣትን ቀጣቸው። ጭቆና ይደርስባቸው ዘንድ ለተለያዩ ሕዝቦች አሳልፎ ሰጣቸው። ይህም ሆኖ ግን ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር አልተመለሱም። አምስተኛ፡- እግዚአብሔር ወደ ምርኮ ይጓዙ ዘንድ ተዋቸው። 

እግዚአብሔር በነገሥታት ዘመን ያደረገውን ተመሳሳይ ሂደት ዛሬም ይጠቀማል። ሕዝቡ ከእውነት እየራቁ ሲሄዱ፥ አምላክነቱን ሲገፋና አምልኮአቸውን ሲያበላሹ፥ በመጀመሪያ እግዚአብሔር የተመረጡ ሰዎችን ወደ እነርሱ በመላክ በግልጥ እንዲያስጠነቅቋቸውና ይህ እውነተኛ አምልኮ እንዳልሆነ፥ በእግዚአብሔር ፊትም ተቀባይነት እንደሌለው እንዲነግሯቸው ያደርጋል። ሕዝቡም ካልተመለሱ እግዚአብሔር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲያልፉ ያደርጋል። ይህም ራብ፥ ስደት፥ ወይም ሌሎች ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። የእግዚአብሔር ሕዝቦች በዚህም ሁኔታ ሊመለሱ ካልፈቀዱ፥ እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ እንዲጠፉ ይተዋቸዋል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ክፍል በዘመናችን ላሉ አብያተ ክርስቲያናትም ጠንካራ ማስጠንቀቂያ የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) ይህ ነገር ባለፈው ጊዜ እንዴት እንደተፈጸመ ምሳሌዎችን ጥቀስ። ሐ) እኛ በግላችንም ሆነ አብያተ ክርስቲያኖቻችን ይህንን ወደ ጥፋትና ምርኮ የሚወስደውን ማሽቆልቆል አለመጀመራችንን ለማረጋገጥ ምን ማድረግ እንችላለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

2ኛ ነገሥት 8፡16-12፡21

አንድ የተሳሳተ ውሳኔ፥ ወይም ዓለምን ለማስደሰት ሲባል የሚወስድ እርምጃ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጥፋትን ሊያመጣ ይችላል። ኢዮሳፍጥ በልጁና የእስራኤል ንጉሥ በነበረው በአክዓብ ሴት ልጅ መካከል ጋብቻ እንዲፈጸም በማድረግ፥ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ሰላምን ብቻ የፈጠረ መስሉት ነበር። ይህ ተግባር በእስራኤል ያደረጋቸውን ሃይማኖታዊ ተሐድሶዎች በሙሉ እንደሚያጠፋ አልተረዳም ነበር። ልጆቹን ሁሉ ለምት የሚዳርግ ነገር እንደሆነ አላስተዋለም ነበር። የዳዊትን ዘር በሙሉ ሊያጠፋ የሚችል ነገር እንደነበረም አላወቀም። 

የውይይት ጥያቄ፥ በዚህም ዘመን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያደርጉት ተመሳሳይ ውሳኔ እንዴት በከፍተኛ ሁኔታ የቤተ ክርስቲያን መፍረስን ሊያስከትል እንደሚችል ምሳሌዎችን ጥቀስ።

ምንም እንኳ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች፥ ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የማያስከትሉ ቢሆንም፥ ሆኖም ግን በርካታ መልካም ነገሮችን ወይም ጉዳቶችን ሊያመጡ ይችላሉ። ለምሳሌ፡- አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የዓለም አቀፍ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ተብሎ በሚጠራው ኅብረት ውስጥ፥ ለክርስትና አንድነት ስንል መግባት አለብን ብለው ይወስናሉ። ቤተ ክርስቲያናቸው ምስክርነቷንና መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ የተቀበለችውን እምነት እንድታጣ ያደርጋሉ። ይህን መሰሉ እርምጃ ብዙ ክርስቲያኖች ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያደርሱ መንገዶች በርካታ ናቸው፤ በኢየሱስ ላይ ያለ እምነት ብቻ አይደለም ወደሚል እምነት እንዲያመሩ አድርጎአቸዋል። ይህም ማለት ዛሬ ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ኢየሱስን የማያውቁና ያልዳኑ ሰዎች ናቸው። አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከትርፍ ገንዘብ ለራሳቸው ጥቅምን ያገኙ ዘንድ የልማት ሥራን ለመጀመር ፈጥነው መወሰናቸው፥ ወደ ቤተ ክርስቲያን ክፍፍል፥ የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ምን እንደሆነ ወደ አለመረዳት፥ በአንዳንድ ሁኔታዎች ለእግዚአብሒር ያላቸውን ፍቅር ሁሉ ወደ መቀነስ አድርሶአቸዋል። የልማት ሥራ ወንጌልን ለማስፋፋት መሣሪያ ሊሆን ቢችልም፥ በሚገባ ካልተያዘ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ፥ ወይም የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ኃላፊነቷ ከሆነው ከወንጌል ሥራና ከማስተማር አገልግሎት ፈቀቅ እንድትል ዋና የሰይጣን መሣሪያ ሊሆን ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ነገ. 8፡16-12:21 አንብብ። ሀ) በዚህ ክፍል የተጠቀሱ የተለያዩ ነገሥታትን ዘርዝር። ለ) የእያንዳንዱን ንጉሥ ባሕርይ ዘርዝር። ሐ) እያንዳንዱ ንጉሥ በነገሠበት ጊዜ ስለ ተፈጸሙት ዋና ዋና ጉዳዮች ግለጥ። መ) የኢዮሳፍጥ ውሳኔ የይሁዳን መንግሥት ሊያጠፋ የነበረው እንዴት ነው? 

 1. ኢዮራም፡- የይሁዳ ንጉሥ (848-841 ዓ.ዓ.)

ኢዮራም ከአባቱ ከኢዮሳፍጥ ጋር ተባባሪ መሪ ሆኖ የሠራ ቢሆንም፥ ሥልጣን ሙሉ ለሙሉ ለመጨበጥ የበቃው ግን አባቱ ከሞተ በኋላ ነው። ኢዮሳፍጥ ሲሞት፥ ኢዮራም ከአባቱ የመንግሥት አስተዳደር መመሪያ ዞር በማለትና ስድስት ወንድሞቹን በመግደል መንግሥቱን ደም በማፍሰስ ጀምሯል። ሕዝቡም ወደ ጣዖት አምልኮ እንዲመለሱ አድርጓል። እንደምታስታውሰው፥ ይህ ሰው ያገባው የበአልን አምልኮ ወደ እስራኤል ያመጡትን የአክዓብንና የኤልዛቤልን ሴት ልጅ ነበር። በሚስቱ በጎቶልያና በአባቱ በአክዓብ ተጽዕኖ የበአልን አምልኮ ወደ ይሁዳ አስገባ፤ እንዲሁም በይሁዳ ከተሞች ዙሪያ የነበሩትን የጣዖት ማምለኪያ ስፍራዎች አደሰ።

በኢዮራም ዘመነ መንግሥት፥ የይሁዳ መንግሥት መዳከም ጀመረ። ኤዶማውያን በይሁዳ ላይ ዓመፁ። ፍልስጥኤማውያንና ዓረቦችም ኢየሩሳሌምን በማጥቃት ብዙ ብዝበዛ ከማድረጋቸውም በላይ በርካታ የንጉሣውያን ቤተሰብ አባሎችን ማርከው ወሰዱ። ኢዮራም በክፉ ደዌ ተመትቶ ሞተ። ሕዝቡ ግን እጅግ ስለጠላው፥ በይሁዳ ነገሥታት መቃብር አልተቀበረም። 

 1. የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ (841 ዓ.ዓ.) 

ከማንኛውም የይሁዳ ንጉሥ ያነሰ አጭር ጊዜ የገዛው አካዝያስ ነበር። በሥልጣን ላይ የቆየው ለአንድ ዓመት ብቻ ነበር። በእናቱ በጎቶልያ ተጽዕኖ አባቱ በጀመረው መንገድ የጣዖትና የበአልን አምልኮ ለማካሄድ ሳይገደድ አልቀረም። እንዲሁም የእስራኤል ንጉሥ በነበረው በአጎቱ በኢዮራም ማበረታቻና ምክር ሶርያን ለመውጋት ከእስራኤል ጋር ተባበረ። አካዝያስ ኢዮራምን ለመጎብኘትና ከእርሱ ጋር በመተባበር ለመዋጋት ሊሄድ፥ ኤልዛቤልንም ሆነ ኢዮራምን በመግደል ሥልጣን ከያዘው ከኢዩ ጋር ተገናኙ። ኢዩም አካዝያስንና በርካታ የይሁዳ ገዥዎችን ገደለ (2ኛ ዜና 22፡7-9)።

 1. የእስራኤል ንጉሥ ኢዩ (841-753 ዓ.ዓ.)

በሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ለረጅም ጊዜ የቆየው፥ የኢዩ ሥርወ መንግሥት ነበር። ኢዩ ሥልጣንን በያዘ ጊዜ፥ የእስራኤል መንግሥት በጣም የተዳከመ ቢሆንም በከፊል እንደገና ሊያጠናክረው ችሎ ነበር። ኢዩ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንደሚሆንና የአክዓብን ቤት እንደሚያጠፋ በነቢዩ ኤልሳዕ ተነግሮት ነበር። ኢዩ የጦሩ አዛዥ ስለ ነበር፥ ኢዮራምንና ኤልዛቤልን ከሥልጣናቸው ለማስወገድ ቻለ። ይህ ሰው በጣም ደም የተጠማ ሰው ነበር። የአክዓብን 70 ልጆች ገድሏል። የእስራኤል ንጉሥ የነበረውን ኢዮራምን፥ የእስራኤልን ንግሥት ኤልዛቤልና የይሁዳን ንጉሥ አካዝያስን ገደለ። ይህን በማድረጉ የኤልሳዕ ትንቢት እንዲፈጸም አደረገ። በተጨማሪ የበአል ነቢያትንም ገደለ። ከብዙዎቹ የእስራኤል ነገሥታት የተሻለ ቢሆንም እንኳ በእስራኤል ምድር የነበረውን የጣዖት አምልኮ ስላላጠፋ፥ እርሱም ክፉ መሪ ነበር። 

በኢዩ ዘመነ መንግሥት በአሦርና በሶርያ መካከል ጦርነት ነበር። ኢዩ ለአሦር ግብር ሰጠ። በኋላ ግን ሶርያ በአሦር ላይ የበላይነቱን ልታገኝና አንዳንዱን የእስራኤል ምድር ወርራ ለመያዝ ችላ ነበር። 

 1. የይሁዳ ንግሥት የነበረችው ጎተልያ (841-835 ዓ.ዓ.) 

በእስራኤልም ሆነ በይሁዳ ለመግዛት የቻለች ብቸኛ ሴት ንግሥት ጎቶልያ ነበረች። እርሷ የአክዓብና የኤልዛቤል ልጅ ነበረች። አካዝያስ በኢዩ እጅ በተገደለ ጊዜ የይሁዳን መንግሥት ለማስተዳደር የቀሩ ንጉሣውያን ቤተሰቦች በጣም ጥቂት ነበሩ፤ ስለዚህ ጎተልያ ዙፋኑን ወረሰችና ለ6 ዓመታት ገዛች። የእርሷ አስተዳደር ብዙ ደም የፈሰሰበት ነበር። በይሁዳ ዙፋኑ ይገባኛል የሚል ማንኛውንም ሰው በመግደል የዳዊትን ዝርያዎውን ለማጥፋት ሞከረች። በኢዮሳፍጥ የተደረገውን ተሐድሶ የተመለከተው ካህኑ ዮዳሄ ግን የአካዝያስን ከሁሉም ታናሽ የሆነውን ልጅ ኢዮአስን በቤተ መቅደስ ሸሸገው። ስድስት ዓመት ከሸሽገው በኋላም የጦሩን አዛዥ ጠርቶ ገና የሰባት ዓመት ልጅ ቢሆንም እንኳ በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆኖአል ብለው በአንድነት አወጁ። ጎቶልያ በሕዝቡ ዘንድ የተጠላች ስለነበረች የጦሩ አዛዦች ኢዮአስ ንጉሥ እንዲሆን በመስማማት ጎቶልያን ገደሏት። 

 1. የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ (835-796 ዓ.ዓ.)

ኢዮአስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ ገና የሰባት ዓመት ልጅ ነበር። ኢዮአስን በቤተ መቅደስ ያሳደገው ሊቀ ካህኑ ዮዳሄ የቅርብ አማካሪው ነበር፤ ስለዚህ ኢዮአስ ከይሁዳ ምድር የበአል አምልኮንና ሌሎች የጣዖት አምልኮዎችን ሁሉ እንዲያስወግድ ዮዳሄ አበረታታው። በአብዛኛው የሥልጣን ዘመኑ ኢዮአስ እግዚአብሔርን ተከተለ። 

በዮዳሄ አመራር የይሁዳ ሕዝብ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ ያላቸውን ፈቃደኝነት አረጋገጡ። ቃል ኪዳንቸውንም ከእግዚአብሔር ጋር አደሱ። ኢዮአስ ቤተ መቅደሱንም ማደስ ጀመረ። እግዚአብሔርን በማይፈሩ መሪዎች ዘመን ለመጠገን አስቸጋሪ እስኪሆን ድረስ ፈራርሶ የነበረው ቤተ መቅደስ እንዲሠራ ሕዝቡ ገንዘብ ማዋጣት ጀመሩ። 

ሆኖም ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ባደሱት ቃል ኪዳን ብዙ አልቆዩም። የሚያሳዝነው ነገር ኢዮአስ ለመንፈሳዊ አመራር በዮዳሄ ላይ ተደገፈ እንጂ፥ እርሱ ራሱ በእምነቱ ጠንካራ አልነበረም፤ ስለዚህ ዮዳሄ እንደሞተ ወዲያውኑ ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ ዓመፁና ወደ ጣኦት አምልኮ ተመለሱ። ኢዮአስ ራሱም ጣዖት ማምለክ ጀመረ። በቤተ መቅደስ ኢዮአስን ያሳደገው የካህኑ የዮዳሄ ልጅ የነበረው ዘካርያስም፥ ኢዮአስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መተላለፍ መልካም እንደማይሆን በማመልከት እንደገና አስጠነቀቃቸው። ኢዮአስ ግን በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ተወግሮ እንዲገደል አስደረገ (2ኛ ዜና 24፡17-22)።

ኢዮአስ እግዚአብሔርን ስለተወ፥ በሕይወቱ ላይ መከራን አመጣ። ለሶርያ መንግሥት ግብር ለመክፈል ተገደደ። በኋላም ግብሩን መክፈል ሊያቆም፡ የሶርያ ኃይል በጉልበት ወደ ኢየሩሳሌም በመግባት ከኢዮአስ ጋር ተዋጋ። ኢዮአስ በውጊያው ቆስሉ በተኛ ጊዜም የገዛ አገልጋዮች ተማምለውበት በአልጋው ላይ ሳለ ገደሉት። ይህም በዘካርያስ ላይ የፈጸመውን በደል ለመበቀል ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚኖር መንፈሳዊ መሪነት ከእነዚህ ቁጥሮች ምን እንማራለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

2ኛ ነገ. 1፡1-8፡15

 1. የነቢዩ ኤልያስ የመጨረሻ ሥራና ከዚህ ዓለም መሄዱ (2ኛ ነገ. 1-2፡18)

በ1ኛ ነገሥት መጨረሻ ላይ አካዝያስ ስለሚባል የእስራኤል ንጉሥ ተመልክተናል። አካዝያስ የነገሠው ለሁለት ዓመታት ብቻ ሲሆን፥ ከፍተኛ ውድቀት ስላጋጠመው ታመመ፤ ስለዚህ ስለ መሞቱና በሕይወት ሰለመኖሩ ለማወቅ ወደ ኤልያስ ላከ። የእግዚአብሔር ነቢይ መከበር ያለበት መሆኑንና እንደማንኛውም አገልጋይ መልእክት ተልኮበት መታዘዝ እንደሌለበት ለማሳየት፥ ኤልያስ ከሰማይ እሳት አወረደና ወደ ንጉሡ ሊወስዱት የመጡትን ሰዎች እንድትበላ አደረገ። በመጨረሻም ኤልያስ ወደ ንጉሡ ዘንድ በሄደ ጊዜ እንደሚሞት ነገረው። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ንጉሥ አካዝያስ ሞተ።

ታማኝ የሆነውን ነቢዩ ኤልያስን እግዚአብሔር አከበረው። ሄኖክ ሞትን እንዳላየ ሁሉ ኤልያስም አልሞተም። እግዚአብሔር ሰማያዊ ሰረገሎችን ልኮ ኤልያስን ወደ መንግሥተ ሰማያት አስወሰደው። 

በብሉይ ኪዳን መጨረሻ፥ እግዚአብሔር መሢሑ ከመምጣቱ በፊት ኤልያስ እንደሚመለስ የተስፋ ቃል ሰጥቶ ነበር (ሚል.4፡5 ተመልከት)። ይህ ትንቢት በመጥምቁ ዮሐንስ ተፈጽሟል(ማቴ. 11፡14)። በአዲስ ኪዳን ኤልያስ የብሉይ ኪዳን ነቢያትን በመወከል፥ በተራራ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስን ተገናኝቶታል (ማቴ. 17፡2-8)። 

 1. የነቢዩ የኤልሳዕ አገልግሎት (2ኛ ነገ. 2-8፡15) 

ከብዙ ዓመታት በፊት እግዚአብሔር፥ ኤልሳዕን ለነቢይነት እንዲጠራው ለኤልያስ ነግሮት ነበር። ኤልሳዕ ሀብታም ቤተሰቦቹን ትቶ (አባቱ ብዙ ጥማድ በሬዎችና አገልጋዮች እንደነበሩት አስተውል) ከኤልያስ ጋር ተጓዘ። ከኤልያስ ጋር በነበረበት ጊዜ ጌታን መውደድ ተማረ። ኤልሳዕ ልምድ ካለው ነቢይ ጋር አብሮ በመሥራት ለነቢይነት ሠለጠነ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን በማሠልጠን ሥራ ውስጥ፥ አዳዲስ መሪዎችን ልምድ ካላቸው መሪዎች ጋር ቀላቅሎ ማሠልጠን እንዴት ጥሩ መንገድ ሊሆን ይችላል? ለ) የቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች ለመሪነት የሚሠለጥኑት እንዴት ነው? ሐ) ይህ ዓይነት የማሠልጠኛ ዘዴ ተግባራዊ ሊሆን የሚችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር። 

ከኤልሳዕ ታሪክ የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-

 1. ኤልያስ ሞትን ሳያይ ወደ ሰማይ በሚወሰድበት ጊዜ በማየት፥ በመጎናጸፊያው የተመሰለውን የኤልያስን ኃይልና ሥልጣን ተቀበለ። ኤልያስ ከሄኖክ ቀጥሉ ሞትን ሳያይ ወደ ሰማይ የተወሰደ ሁለተኛ ሰው ነው (ዘፍ. 5፡24)። 
 2. ኤልሳዕ በርካታ ተአምራትን አደረገ፡-

ሀ. መራራ ውኃን አገልግሎት ላይ ሊውል ወደሚችል ንጹሕ ውኃ ለወጠ። 

ለ. በመላጣነቱ ለመቀለድ የሞከሩ ልጆችን ድብ እንዲበላቸው አደረገ። 

ሐ. የእስራኤል ነገሥታት ለነበሩት ለኢዮሳፍጥና ለኢዮራም ከሞዓባውያን ጋር ሲዋጉ ረዳቸው። 

መ. የመበለቲቱን ዘይት በመባረክ እንዳትራብ አደረገ። 

ሠ. የሱነማይቱን ልጅ ከሞት አስነሣ። 

ረ. የተመረዘ ምግብን ሊበላ ወደሚችል ንጹሕ ምግብነት ለወጠ። 

ሰ. በ20 ዳቦ 100 ሰዎችን መገበ። 

ሸ. የሶርያ ጀኔራል የነበረውን ንዕማንን ከለምጹ አነጻው። 

ቀ. ጠፍቶ የነበረው የመጥረቢያ ዛፍ በውኃ ላይ እንዲንሳፈፍ አደረገ። 

በ. ሊይዙት የመጡትን የሶርያ የጦር ኃይላትን አሳውሮ ለእስራኤል ንጉሥ አሳልፎ ሰጣቸው። 

ተ. የሶርያ ጦር ኃይል የሰማርያን ከተማ ከመክበብ እንደሚመለሱ አመለከተ። 

ቸ. ቤንሃጻድ የሚባለው የሶርያ (አራም) መሪ እንደሚሞትና በምትኩ አዛሄል የሚባለው ሰው እንደሚነግሥ አመለከተ። ራቅ ብሎ በሚገኘው የሶርያ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች እንኳ፥ ኤልሳዕ የእግዚአብሔር ነቢይ እንደሆነ አውቀው ነበር። ሶርያ (አዛሄል) በእስራኤል ላይ ስለምታገኘው ድልም አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከኤልሳዕ ታሪክ ስለ ቤተ ክርስቲያን አመራር የምናገኛቸውን መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) ከኤልሳዕ አገልጋይ ክፉ ምኞት የምንማረው ነገር ምንድን ነው? ሐ) ስለ መንፈሳዊ ዓይን ከኤልሳዕ፥ ከአገልጋዩና ከሶርያ የጦር ኃይል የምንማረው ነገር ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ2ኛ ነገሥት አስተዋጽኦ እና ዓላማዎች

የ2ኛ ነገሥት አስተዋጽኦ

 1. የመጨረሻው የኤልያስ አገልግሉትና ወደ ሰማይ መወሰዱ (2ኛ ነገ. 1-2፡18) 
 2. የጌታ ነቢይ የሆነው የኤልሳዕ አገልግሎት (2ኛ ነገ. 2፡19-8፡15) 
 3. የእስራኤልና የይሁዳ ነገሥታት እስከ እስራኤል ምርኮ ድረስ (2ኛ ነገ. 8፡16-17፡41) 

ሀ. የይሁዳ ንጉሥ ኢዮራም (8፡16-24) 

ለ. የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ (8፡25-29) 

ሐ. የእስራኤል ንጉሥ ኢዩ (9-10) 

መ. የይሁዳ ንግሥት ጎቶልያ (11) 

ሠ. የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ (12) 

ረ. የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአካዝ (13፡1-9) 

ሰ. የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ (13፡10-25) 

ሸ. የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ (14፡1-22)

ቀ. የእስራኤል ንጉሥ ዳግማዊ ኢዮርብዓም (14፡23-29) 

በ. የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን (15፡1-7) 

ተ. የእስራኤል ንጉሥ ዘካርያስ (15፡8-12) 

ች. የእስራኤል ንጉሥ ሻሎም (15፡13-16) 

ኀ. የእስራኤል ንጉሥ ምናሔም (15፡17-22) 

ነ. የእስራኤል ንጉሥ ፋቂስያስ (15፡23-26) 

ኘ. የእስራኤል ንጉሥ ፋግፈ(15፡27-31) 

አ. የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአታም (15፡32-38) 

ከ. የይሁዳ ንጉሥ አካዝ (16)

ኸ. የእስራኤል ንጉሥ ሆሴዕ (17፡1-6)

ወ. የእስራኤል መማረክ (17፡7-41) 

 1. ከሕዝቅያስ ጀምሮ ይሁዳ እስከተማረከች ድረስ የነበሩ የይሁዳ ነገሥታት (2ኛ ነገ. 18-25) 

ሀ. ሕዝቅያስ (18-20) 

ለ. ምናሴ (21፡1-18) 

ሐ. አሞን (21፡19-26)

መ. ኢዮስያስ (22፡23-30) 

ሠ. የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአሐዝ (23፡31-35) 

ረ. የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም፡- የመጀመሪያው የባቢሎን ምርኮ (23፡36-24፡7) 

ሰ. የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን፡- ሁለተኛው የባቢሎን ምርኮ (24፡8-17) 

ሸ. የሴዴቅያስ በምርኮ ወደ ባቢሎን መወሰድ (24፡18-25፡21)

ቀ. በምርኮ ጊዜ የተፈጸሙ ድርጊቶች (25፡22-30) 

2ኛ ነገሥት የተጻፈባቸው ዓላማዎች 

 1. ከ853 ዓ.ዓ. ጀምሮ የእስራኤልና የይሁዳ መንግሥታት ወደ ምርኮ እስከ ተወሰዱበት ጊዜ ድረስ በእስራኤልና በይሁዳ የነገሡ ነገሥታትን ታሪክ በአጭሩ ለመተረክ ነው። 
 2. የእስራኤልና የይሁዳ መንግሥታት ወደ ምርኮ የተወሰዱበትን ምክንያት ለመግለጥ ነው። ይህ መጽሐፍ በግልጽ የሚያሳየው እስራኤልና ይሁዳ የጠፉት አሦርና ባቢሎን ታላቅ ስለ ነበሩ አለመሆኑን ነው። እንዲሁም አጋጣሚ ወይም ተፈጥሮአዊ የሆነ የታሪክ ክስተትም አይደለም። እስራኤልና ይሁዳ የጠፉት ትእዛዛቱን ስላልጠበቁ፥ እግዚአብሔር በቀጥታ ባመጣባቸው ፍርድ ነው። በእግዚአብሔር ላይ ዓመፁና በዚያ ፈንታ ሌሎች አማልክትን አመለኩ። 

የ2ኛ ነገሥት ታሪክ እግዚአብሔር በታሪክ ሁሉ ውስጥ ያለውን አመለካከት ያሳየናል። ታሪክ የነገሮች ተፈጥሮአዊ አፈጻጸም ብቻ አይደለም። አንድ ሕዝብ ሌላውን የሚወጋበት፥ አንድ ንጉሥም ሌላውን የሚገዛበት ታሪክ ብቻ አይደለም። ተፈጥሮአዊ የሆነ የድርቅ፥ የበሽታና የሞት ታሪክም አይደለም። ይህኛው ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች ታሪክን የሚመለከቱበት መንገድ ነው። እግዚአብሔር ግን ታሪክን የሚመራ ነው። ራንና በሽታን የሚልክ እርሱ ነው። ጦርነቶችንና አሕዛብን ሁሉ የሚቆጣጠር እርሱ ነው። ሕዝቡ በምርኮ እንዲወሰዱ የሚፈቅድ እርሱ ነው። ክርስቲያኖች ግን በጎም ሆኑ ክፉ ነገሮችን ሁሉ ያያሉ። እንዲሁም የእግዚአብሔር እጅ በሥራ ላይ ሆኖ ማየት ይቻላል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች በታሪክ ላይ ይህን አመለካከት ማስታወስ የሚያስፈልጋቸው ለምንድ ነው? ለ) መንግሥት በትምህርት ቤቶች ካስተማረን ታሪክ እዚህ ያለው አመለካከት እንዴት ሊለያይ ቻለ? 

 1. ከምርኮ በኋላ የሚኖሩ እስራኤላውያንና ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ቅጣት እንዳያገኛቸው ለእርሱ በመታዘዝ መኖር እንዳለባቸው ለማስጠንቀቅ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች የ2ኛ ነገሥትን እውነት ማወቃቸው በጣም አስፈላጊ የሚሆነው ለምን ይመስልሃል? ለ) የእግዚአብሔር ፍርድ ሳይመጣባቸው በቅድስና ይኖሩ ዘንድ ይህንን መልእክት ለቤተ ክርስቲያንህ አባሉች ለማስተማር የምትችለው እንዴት ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ነገሥት 1-8፡15 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ዓመታት የተጠቀሱትን የተለያዩ ነገሥታት ዘርዝር። ለ) ባሕርያቸው ምን ይመስል ነበር? ሐ) ኤልሳዕ የሠራቸውን የተለያዩ ተአምራት ዘርዝር።

እንደምታስታውሰው፥ የ1ኛ ነገሥት መጨረሻና የ2ኛ ነገሥት መጀመሪያ የሚያተኩሩት ኤልያስና ኤልሳዕ በተባሉ ሁለት ነቢያት ላይ ነው። እነዚህ ሁለት ነቢያት በእስራኤል የሠሩና ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ የጣሩ ነበሩ። የኤልያስ ታሪክ በአብዛኛው የሚገኘው በ1ኛ ነገሥት ውስጥ ነው። የሕይወቱ የመጨረሻ ታሪክ በ2ኛ ነገሥት 1-2 ውስጥ ይገኛል። 2ኛ ነገሥት 2-8 የሚያተኩረው ደግሞ በኤልሳዕ ታሪክ ላይ ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

በ2ኛ ነገሥት የታሪክ ዘመን የነበሩ ዋና ዋና ኃይላት

የ2ኛ ነገሥት የታሪክ ዘመናት በዋና ዋና የዓለም መንግሥታት ዘንድ ከፍተኛ ትግል የተካሄደባቸው ጊዜያት እንደነበሩ 2ኛ ነገሥት ይነግረናል። የጳለስጢና ምድር በዚህ ትግል መሀል ተይዛ ጦርነትን አሳልፋለች። እስራኤላውያን የትኛውን ወገን መደገፍ እንዳለባቸው ለመወሰን የተቸገሩበት ጊዜ ነበር፤ ስለዚህ ነገሥታቱ ከአንድ ኃያል መንግሥት ጋር የነበራቸውን ስምምነት እርሱን በሚጥለው ሌላ ኃያል መንግሥት ሲቀይሩና ሲዋዥቁ እንመለከታለን። በእነዚህ ዓመታት በእስራኤልና በይሁዳ መንግሥታት ታሪክ ውስጥ ታላቅ ሚና የተጫወቱ ሦስት ዋና ዋና መንግሥታት ነበሩ።

 1. ግብፅ፡- በእነዚህ ዓመታት ግብፅ እስከዚህም ብርቱ የሆነችበት ጊዜ ጨርሶ አልነበረም። ነገር ግን ወደ ቀድሞ ስፍራዋ ለመመለስና የመካከለኛው ምሥራቅ ዋና መንግሥት የመሆን ሕልም ሁልጊዜ ነበራት፤ ስለዚህ ግብፅ ብዙ ጊዜ እንደ አሦርና ባቢሎን ካሉት ሌሎች ኃያላን መንግሥታት ጋር ግጭት በመፍጠር ጦርነትን ታካሂድ ነበር። ይህም ጦርነት ብዙ ጊዜ የሚደረገው በከነዓን ምድር ነበር። በተጨማሪ ብዙ ጊዜ ግብፅ በመሰጴጦሚያ የሚገኙ ሌሎች ግዛቶችንና መንግሥታትን ለመውጋት የእስራኤልንና የይሁዳ መንግሥታትን ድጋፍ ለማግኘት ትሞክር ነበር። ግብፅ በአሦርና በባቢሎን የተሸነፈች ብትሆንም፥ የምትገኘው እጅግ ርቃ ስለ ነበር፥ እነርሱ ሊቆጣጠሯት አልቻሉም ነበር።

በ2ኛ ነገሥት ያለው ታሪክ በተፈጸመበት ዘመን፥ ግብፅ በሁለት ዋና ዋና መንገዶች በጳለስጢና ላይ ተጽዕኖ አድርጋበት ነበር። በመጀመሪያ፥ በ609 ዓ.ዓ. ኢዮስያስ ብልህነት በጎደለው መንገድ ከግብፅ ጋር ተዋግቶ በጦርነቱ ተገደለ። ልጁም ኢዮአካዝ ወደ ግብፅ በምርኮ ተወሰደ። የግብፅ ንጉሥ በእርሱ ምትክ ኢዮአቄም የተባለውን ወንድሙን አነገሠው። 

ሁለተኛ፥ በ586 ዓ.ዓ. ኢየሩሳሌም ከተደመሰሰች በኋላ፥ ብዙ አይሁድ ተሰድደው ወደ ግብፅ ሄዱ። ነቢዩ ኤርምያስንም አስገድደው ከእነርሱ ጋር ወሰዱት። በዚያም በርካታ የሆነ የአይሁድ ኅብረተሰብ ሰፈረና ለብዙ መቶ ዓመታት በዚያ ኖረ። ሴፕቱዋጀንት የሚባለው የግሪክ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በ70 ዓ.ዓ. አካባቢ በግብፅ ነበር።

 1. አሦር፡- ባለፈው ሳምንት የአሦር መንግሥት በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የተጫወተውን ከፍተኛ ሚና ተመልክተናል፤ ሆኖም እስከ 853 ዓ.ዓ. ለእስራኤል መንግሥት ዋና ፈተና የነበረች ሶርያ ናት። በ745 ዓ.ዓ. በአሦር ቴልጌልቴልፌልሶር የተባለ ታላቅ ንጉሥ በሥልጣን ወንበር ላይ ተቀመጠ። የአሦርንም ግዛት ማስፋፋት ጀመረ። ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ አገር ወርረው የሚይዙ ሕዝቦች በተወረረችው ከተማ ላይ ያደርጉት ስለ ነበረው ነገር ያስተዳደር መመሪያ ለውጥ አመጣ። ይህም ያስተዳደር መመሪያ በተወረረው አገር የሚኖሩ የሚጠቅሙ ዜጎችን የተማሩ፥ ንጉሣዊ ቤተሰብ የሆኑ፥ የሥነ-ጥበብ ሰዎች ወዘተ.) መውሰድና በግዛቷ ሁሉ ውስጥ መበተን ነበር። ሉሎች የተወረሩ ሕዝቦችን ደግሞ ወደ ሌላ የተወረረ ከተማ አምጥተው ማስፈር ነበር። ይህም ያ ሕዝብ እንደገና እንዳያንሰራራና እንዳይዋጋ የማድረጊያ ዘዴ ነበር። አሦር እስራኤልን ባሸነፈች ጊዜ ሕዝቡን ወደ ምርኮ የወሰደችውና በግዛቱ ሁሉ ውስጥ የበተነችው ለዚህ ነበር። ሕዝቡ ወደ እስራኤል እንደገና ለመመለስ ጨርሶ አልቻለም። ይህንን ልምድ አሦራውያን ብቻ ሳይሆኑ፥ ባቢሎናውያንም አደረጉት። ይሁዳን ባሸነፉ ጊዜ፥ ሕዝቡን ወደ ምርኮ ወሰዱና በባቢሎን ግዛት ሁሉ ውስጥ በተኑአቸው። የባቢሎን መንግሥት በፋርስ መንግሥት በተሸነፈና በወደቀ ጊዜ፥ ወደ እስራኤል ለመመለስ የቻሉ አይሁድ በጣም ጥቂትና የተወሰኑ ብቻ ነበሩ።

የቴልገልቴልፌልሶር ልጅ ስልምናሶር 5ኛ ከ727-722 ዓ.ዓ. የገዛ ንጉሥ ሲሆን፥ የእስራኤልን መንግሥትና የሰማርያን ከተማ የከበባትና አሸንፎ የያዛት እርሱ ነበር። አጠቃልሉ ይህን ከማድረጉ በፊት ግን ዳግማዊ ሳርጎን በተባለው የጦር ጄኔራሉ ተገደለ። ዳግማዊ ሳርጎን የሰሜኑን መንግሥት የማረከና ወደ ግዛቱም የደባለቀ ሰው ነው። 

የሳርጎን ልጅ የሆነው ሰናክሬም (704-681 ዓ.ዓ.) በኋላ በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ይሁዳን ወግቶ ወደ 200000 የሚደርሱ ሰዎች ወደ ምርኮ ቢወስድም፥ ኢየሩሳሌምን ግን ለመውጋትና አሸንፎ ለመያዝ አልቻለም፡ ኢየሩሳሌም ከመውደቋ በፊት በራሱ ሁለት ልጆቹ ተገደለ የሚቀጥለው የአሦር ንጉሥ፥ አስራዶን ይባል ነበር። የይሁዳ ንጉሥ የነበረውን ምናሴን በምርኮ ወደ ባቢሎን የወሰደ እርሱ ነበር (2ኛ ዜና 33፡10-13)። የመጨረሻው ታላቁ የአሦር ንጉሥ አሱርባኒፓል (668.630 ዓ.ዓ.) የሚባለው ሲሆን፥ እርሱም መንግሥቱን እስከ ግብፅ ድረስ አስፋፍቷል። እርሱ ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፥ የአሦር መንግሥት መዳከም ጀመረና በመጨረሻ በ605 ዓ.ዓ. በባቢሎናውያን ተደመሰሰ። 

 1. ባቢሎን፡- የ2ኛ ነገሥት ታሪክ በተፈጸመበት ዘመን በእስራኤል መንግሥት ላይ ተጽዕኖ ያደረገ ሦስተኛው ታላቅ መንግሥት የባቢሎን መንግሥት ነበር። የባቢሎን መንግሥት ከ626-539 ዓ.ዓ. ድረስ ጠንካራ ነበር። በአሥር እጅ በነበረችም ጊዜ የባቢሎን ምድር በጣም ታዋቂ ክፍለ አገር ነበረች። ከአሱርባኒፓል ሞት በኋላ በ633 ዓ.ዓ. የባቢሎን ከተማ በአሦር ላይ ማመፅ ጀመረ። ከ626-605 ዓ.ዓ. የባቢሎን ንጉሥ በነበረው በናቦፖላሳር አመራር የባቢሎን መንግሥት ብቅ አለና የአሦርን መንግሥት ለመጣል ቻለ። በ612 ዓ.ዓ. የአሦር ዋና ከተማ የነበረችው ነነዌ ተደመሰሰች። በ609 ዓ.ዓ. የአሦር ጦር ተደመሰሰ። ናቦፖላሳር የይሁዳን መንግሥት ጦር ማጥቃት ቢጀምርም ሊያሸንፍ ግን አልቻለም ነበር።

ከናቦፖላሳር በኋላ፥ በባቢሎን መንግሥት ውስጥ በታላቅነቱ አቻ የማይገኝለት ናቡከደነፆር ነገሠ። እርሱም ከ605-562 ዓ.ዓ. በሥልጣን ላይ ቆየ። የይሁዳ መንግሥት ሦስት ጊዜ የተጠቃውና በመጨረሻም በምርኮ የተወሰደ በእርሱ ዘመነ መንግሥት ነበር።

 1. አብዛኛው ንጉሣዊ ቤተሰብና ጠቃሚ የሆኑ ዜጎች የተወሰዱት በ605 ዓ.ዓ. ነበር። ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ አብዛኛው ሀብት ወደ ባቢሎን የተወሰደውና ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ወደ ምርኮ የተወሰዱት በዚህ ጊዜ ነበር (ዳን. 1፡1)። የይሁዳ መንግሥት የባቢሎን መንግሥት አገልጋይ የሆነውም ያኔ ነበር፡፡ 
 2. በ597 ዓ.ዓ. የሆነው ምርኮ፡- ኢዮአቄም ከግብፅ ጋር አብሮ በባቢሎን ላይ ባመፀ ጊዜ፥ ባቢሎን ኢየሩሳሌምን አጥቅታ ወረረቻት። በዚህ ጊዜ የንጉሣዊው ቤተሰብ ሌላ አባሎች የሆኑት ንጉሥ ዮአኪንና እጅግ ታዋቂ ከሆኑት 10000 ያህል የኢየሩሳሌም ዜጎች እንደነ ሕዝቅኤል ያሉት ጭምር ወደ ባቢሎን ተወሰዱ።
 3. በ586 ዓ.ዓ. የሆነው ምርኮ፡- የመጨረሻው የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በባቢሎን ላይ ባመፀ ጊዜ ናቡከደነፆር ትዕግሥቱን አጣ። በ588 ዓ.ዓ. ከኢየሩሳሌም ጋር መዋጋት ጀመረ። ከግብፅ ጋር ለመዋጋት ሲል ከኢየሩሳሌም ጋር የጀመረውን ውጊያ አቆመ። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ግን በ586 ዓ.ዓ. ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰና ከረጅም ውጊያ በኋላ በወረራ ኢየሩሳሌምን ያዘ። የሴዴቅያስ ልጆች ተገደሉ። እርሱንም ዓይኑን አሳውረው ወደ ምርኮ ወሰዱት። የኢየሩሳሌም ቅጥር፥ እንዲሁም ከብዙ ዓመታት በፊት የተሠራው የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ተደመሰሱ። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አይሁድ በምርኮ ተወሰዱ። ድሀ የሆኑ ሰዎች ብቻ በምድሪቱ ላይ ቀሩ። ናቡከደነፆር ጎዶልያስን በይሁዳ ላይ ሾመው፤ ነገር ግን በእስማኤል ተገደለ። የቀሩትም አብዛኛዎቹ ሰዎች ወደ ግብፅ ሸሹ።

ከናቡከደነፆር ሞት በኋላ፥ የባቢሎን መንግሥት ኃይል ፈጥኖ በመቀነሱ በ539 ዓ.ዓ. በሜዶንና በፋርስ የተባበረ ኃይል ከሥልጣን ተወገደ። አይሁድን ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ የፈቀደ በብሉይ ኪዳን የተጠቀሰ የመጨረሻ ኃያል መንግሥት የሜዶንና የፋርስ መንግሥት ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ2ኛ ነገሥት መግቢያ

በመጀመሪያ 1ኛና 2ኛ ነገሥት አንድ መጽሐፍ እንደነበሩ ታስታውሳለህ። በኋላ ወደ ሁለት መጻሕፍት የተከፈሉት መጽሐፉ እጅግ በመርዘሙ ምክንያት ነበር። የነገሥት መጽሐፍ ርዕስ የተገኘው በ1ኛና 2ኛ ነገሥት ከሰሎሞን ጀምሮ እስከ ሴዴቅያስ ድረስ በእስራኤልና በይሁዳ የነገሡ ነገሥታት አጫጭር ታሪኮች የሚገኝበት መጽሐፍ ከመሆኑ አንፃር ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ነገሥት 17፡7-23 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር እስራኤልንና ይሁዳን ያጠፋው ለምንድን ነው? ለ) በዚህ ክፍል የተሰጡትን የተለያዩ ምክንያቶችን ዘርዝር።

እስራኤላውያን በእግዚአብሔር የተመረጡት ለእርሱ የተለዩ ሕዝብ እንዲሆኑ ነበር። በአብርሃም በኩል ከእግዚአብሔር ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን ነበራቸው። በሲና ተራራ እግዚአብሔር በታላቅ መንገድ ተገናኛቸውና ትእዛዛቱን ሰጣቸው። እስራኤላውያን ለምን ጠፉ? ወደ ምርኮ የሄዱት ለምንድን ነው? ራብ፥ በሽታ፥ ሞት፣ ጦርነትና ምርኮ በእነርሱ ላይ የመጣው ለምንድን ነው?

የ1ኛና 2ኛ ነገሥት መጻሕፍት ሊመልሱት የሚሞክሩት ጥያቄ ይህ ነው። አዎን፥ የእስራኤል ሕዝብ የተለዩ ነበሩ። አዎን፥ እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ከአብርሃም፥ ከእስራኤላውያንና ከዳዊት ጋር አድርጎ ነበር። የእግዚአብሔር ሕዝብ የጠፉበት ምክንያት ግን በእግዚአብሔር ሳይሆን በራሳቸው ጥፋትና ስሕተት ነበር። የእግዚአብሔር ቃል ነበራቸው፤ ስለዚህ ቃሉን ማወቅ ይጠበቅባቸው ነበር። ነገር ግን እያወቁ በግትርነት በእግዚአብሔር ላይ ዓመፁ። ቅዱሱ እግዚአብሔር ኃጢአታቸውን ሳይቆጣ ሊያልፋቸው ስላልቻለ አስቀድሞ በተደጋጋሚ ባስጠነቀቃቸው መሠረት አስማረካቸው።

ዛሬም እግዚአብሔር ተመሳሳይ ነገር በቤተ ክርስቲያኑ ሊያደርግ ይችላልን? በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ራብ፥ በሽታና ጥፋት እንዲመጣ መፍቀድ ይችላልን? እግዚአብሔር እኛን ለምርኮ ማለትም ለሌላው ሃይማኖት ቁጥጥር አልፈን እንድንሰጥ ሊያደርግ ይችላልን? ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልሱ አዎን የሚል ነው። እኛም ልክ እንደ እስራኤላውያን ከሆንን፥ የእግዚአብሔርን ቃል ካላወቅንና ካልታዘዝን እንጠፋለን። የ2ኛ ነገሥት መልእክት ለእግዚአብሔር ካልታዘዝን፥ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ እንደፈረደ፥ በእኛም ላይ እንደሚፈርድ የሚያመለክት ማስጠንቀቂያ ነው። ጉዳዩ እግዚአብሔር ባለፈው ዘመን እንዴት ተጠቀመብን የሚለው አይደለም። ቁም ነገሩ እግዚአብሔርን አሁንና ወደፊት እንዴት እንደምናገለግለውና ከእርሱም ጋር እንዴት እንደምንራመድ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ዜና 7፡14 አንብብ። ሀ) በዚህ ቁጥር እግዚአብሔር የገባቸው የተስፋ ቃሎች ምንድን ናቸው? ለ) ለዚህ የተስፋ ቃል የተሰጠው ቅድመ ሁኔታ ምንድን ነው? ሐ) አንተና ቤተ ክርስቲያንህ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች እያሟላችሁ ያላችሁት እንዴት ነው? ይህንን ጥቅስ በቃልህ አጥና፡፡ 

የ2ኛ ነገሥት ታሪክ የተፈጸመበት የዘመን ርዝመት 

በ1ኛ ነገሥት የተጻፈው ታሪክ ከዳዊት ሞት ከ971 ዓ.ዓ. ጀምሮ እስከ 853 ዓ.ዓ. ድረስ በነበረው ጊዜ መፈጸሙን ተመልክተናል። በ1ኛ ነገሥት ታሪክ ጊዜ የሰሎሞንን መንግሥትና ቀጥሉም እስራኤል በሰሜን፥ ይሁዳ ደግሞ በደቡብ ሆኖ ለሁለት የተከፈለውን መንግሥት ተመልክተናል።

2ኛ ነገሥት የተከፈለውን የእስራኤል መንግሥት ታሪክ ይቀጥላል። የሚናገረውም ከ853-586 ዓ.ዓ. ስላለው ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከተፈጸሙ ድርጊቶች በጣም አስፈላጊዎቹ በ722ዓ.ዓ. የተፈጸመው የሰሜኑ መንግሥት ጥፋትና ከብዙ ዓመታት በኋላ በ586ዓ.ዓ የተከናወነው የደቡብ መንግሥት ጥፋት ነው። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)