የመጽሐፈ ኢያሱ ዋና ትምህርቶች

የውይይት ጥያቄ፥ ከመጽሐፈ ኢያሱ ጥናት ከሕይወትህ ጋር ልታዛምድና በቤተ ክርስቲያንህ ላሉ ሰዎች ልታስተምር የምትችላቸውን መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር።

 1. የከነዓንን ምድር ለአብርሃምና ለዘሩ ለመስጠት ቃል ኪዳን የገባው እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል ኪዳን ፈጸመ፤ (ዘፍ. 12፡7፤ 15፡7፥ 18-21)። እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በከነዓን ምድር በሚኖሩ ሰዎች ላይ ድልንና የከነዓንን ምድር ርስት አድርጎ ሰጣቸው። እኛ አይሁድ ስላልሆንን እነርሱ ለከነዓን ምድር የነበራቸውን በስሜት የተሞላ ቅርበት ልንረዳ አንችልም። የተስፋይቱ ምድር እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ደግሞም በሲና ተራራ ከገባው ቃል ኪዳን ጋር በቅርብ የተያያዘች ናት። እንዲያውም እስራኤል ከምድሪቱ ጋር ያላት ግንኙነት ለቃል ኪዳኑ ምን ያህል ታዛዥ ናት በሚለው ነገር ላይ የተመሠረተ ነበር። ለቃል ኪዳኑ አለመታዘዝ ማለት በነገሥታት ዘመን እንደሆንው ከምድሪቱ ተባርረው ይወጣሉ ማለት ነው። በንስሐ መመለስና ለቃል ኪዳኑ መታዘዝ ማለት እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው የተስፋ ምድር ይመለሳሉ ማለት ነው። አይሁድ በ1948 ዓ.ም. ወደ ከነዓን የመመለሳቸው ነገር እግዚአብሔር እስካሁንም ድረስ ለአይሁድ ቃል ኪዳኑን እየጠበቀ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነው።

የክርስቲያን ርስት ከሚታይ መሬት ርስት ወይም ምድራዊ ተስፋ ጋር የተያያዘ አይደለም። የእኛ የተስፋ ምድር መንግሥተ ሰማያት ነው። እኛ የሰማያዊ አገር ዜጎች ነን። ቤታችን በዚያ ነው፤ የምንጓዘውም ወደዚያው ነው። አንድ ክርስቲያን ስለምድራዊ መሬት ወይም በምድር ስላለው ቤት ከሚገባ በላይ ትኩረት ሲሰጥ፥ በምድር ላይ የሚኖረው ለጊዜው እንደሆነና እውነተኛ ቤቱ በሰማይ እንዳለ ረስቷል ማለት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት። ስለ ዘላለማዊ ቤታችን የሚናገሩት ነገር ምንድን ነው? ዮሐ. 14፡1-4፤ ዕብ. 11፡10፥ 16፤ ፊል. 3፡20።

 1. የእምነት ሕይወት የጦርነት ሕይወት ነው። ድል መንሣት ያለባቸው በርካታ ጠላቶች አሉ። ለአይሁድ ጠላቶቻቸው በአካል የሚታዩ አገሮች ወይም ነገዶች ሲሆኑ፥ ሊሸነፉ ያስፈልግ ነበር። ለክርስቲያን ሦስት ጠላቶች አሉት፤ እነርሱም፡- ሰይጣን፥ የዓለም ክፉ ሥርዓትና በሁላችንም ዘንድ ያለው የቀድሞው (አሮጌው) የኃጢአት ባሕርይ ናቸው። እነዚህን ጠላቶች የምናሸንፍበት ብቸኛው መንገድ የእግዚአብሔር ኃይል ነው። ይህንን ኃይል የምናገኘው በውስጣችን እንደሚሠራ ስናምን፥ ለእግዚአብሔር ሕግጋት ስንታዘዝና በቅድስና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ስንራመድ ነው።

እግዚአብሔር ለአይሁድ የሠራዊታቸውና የሰማይ ሠራዊትም አዛዥ እንደሆነ አስተምሮአቸዋል። ለሕዝቡ ለመዋጋት እንደተዘጋጀ መለኮታዊ ተዋጊ ሆኖ እንመለከተዋለን፤ (ኢያሱ 10፡14)። በነቢያትና በቅኔ መጻሕፍት ውስጥ ሁሉ እግዚአብሔር ታላቅ ተዋጊ ሆኖ እናየዋለን። እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ያካሄዱት ማንኛውም ዓይነት ጦርነት ቅዱስ ጦርነት ነበር።

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በአካል የሚታይ ሥጋዊ ጦርነት የለብንም። ክርስቲያኖች መብታቸውን ለማግኘት ኃይልን መጠቀም ስሕተት ነው። ጦርነታችን መንፈሳዊ ነው፤ (ኤፈ. 6፡12)። ክርስቶስ እኛ ያለንበት መንፈሳዊ ጦር መሪ ነው፤ ስለዚህ ለእርሱ ትእዛዝ መገዛት አለብን። ለእርሱ በመታዘዝ በእርሱ ርዳታ ብቻ የሚያጋጥሙንን መንፈሳዊ ጠላቶች ለማሸነፍ እንደምንችል መገንዘብ አለብን።

የውይይት ጥያቄ፥ ኤፌ. 6፡12። ሀ) ጳውሎስ የሚናገረው ስለማን ነው? ለ) እነዚህን ጠላቶቻችንን የምንዋጋውና የምናሸንፈው እንዴት ነው? ሐ) ለጦርነቱ ማረጋገጫ የሚሆኑ አንዳንድ ነገሮች ከሕይወትህ ጥቀስ።

 1. ድል ለማግኘት በሚኖረን ብቃት ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል ዕከላዊ ነው። በመጽሐፈ ኢያሱ ውስጥ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል። የእግዚአብሔርን ቃል፥ በቃል ልናጠና፥ ልንረዳውና ልንታዘዘው ያስፈልጋል፤ (ኢያሱ 1፡7-8፤ 23፡6 ተመልከት)።
 2. በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ድል፥ በሦስት ነገሮች ላይ የተመረኮዘ ነው፡- 

ሀ. ነገሮችን በራሳችን ጥበብና ብርታት ከማድረግ ይልቅ ኃይል እንዲሰጠን በጌታ ላይ መታመን አለብን። 

ለ. የእግዚአብሔርን ቃል ልንረዳውና ልንታዘዘው ያስፈልጋል።

ሐ. በእግዚአብሔር ፊት የተቀደሰ ሕይወት መኖር አለብን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ከእነዚህ ሦስት ነገሮች ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ የማይጠብቋቸውና በዚህም ምክንያት በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የሚሸነፉባቸው የትኞቹ ናቸው?

 1. እግዚአብሔር ከሁሉ የባሱ ኃጢአተኞችን ይቅር ይላል። ከዚያም በእርሱ ዕቅድ ውስጥ እጅግ ጠቃሚ ሚና እንዲጫወቱ ያደርጋል። ምንም ስፍራ የለውም የምንለው ሰው እንኳ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ እጅግ ጠቃሚ ቦታ አለው። ረዓብ ጋለሞታና አሕዛብ ነበረች። ምንም ተስፋ የሌላት ሴት ነበረች። በእግዚአብሔር ከጥፋት ዳነች። ከይሁዳ ቤት የሆነውን ሰው አገባችና በሥጋ ኢየሱስ ከመጣበት ከዳዊት የዘር ሐረግ ውስጥ ተቆጠረች። ከአዳም ጀምሮ በአብርሃም፥ በዳዊት፥ ከዚያም በኢየሱስ ክርስቶስ የተዘረጋው የድነት (ደኅንነት) መስመር ውስጥ ገባች።
 2. የጌታ ሠራዊት አዛዥ የነበረው ያለምንም ጥርጥር ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። እርሱ የነገሥታት ንጉሥ የጌቶችም ጌታ ነው። አንድ ቀን ከሰማይ ሠራዊት ሁሉ ጋር ይገለጥና የእግዚአብሔርን ጠላቶች ሁሉ ያሸንፋል፤ ራእይ 19፡11-21 ተመልከት)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) መጽሐፈ ኢያሱ በድል ስለመመላለስ ለማስተማር ክርስቲያኖችን እንዴት ይጠቅማቸዋል? ለ) ለቤተ ክርስቲያንህ አባሉች ይህን መጽሐፍ እንዴት እንደምታስተምር ዕቅድ አውጣ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢያሱ 13-24

ክርስቲያን በሕይወቱ ከሚያጋጥሙት አደገኛ ነገሮች አንዱ ሰላምና በረከትን በሚያገኝ ጊዜ እግዚአብሔርን መርሳት ነው። ሙሴ ስለዚህ ጉዳይ በዘዳ. 8፡7-20 ባለው ክፍል እስራኤላውያንን አስጠንቅቆአቸዋል። የከነዓን ምድር በሙሉ ለእስራኤላውያን (ለአሥራ ሁለቱም ነገዶች) ከተከፋፈለ በኋላ እያንዳንዱ ሰው በተሰጠው ምድር አርፎ ሲኖር ሕዝቡ በዕለታዊ ተግባራቸው እየተጠመዱ በመፈተናቸው እግዚአብሔርን የመርሳት ከፍተኛ ዝንባሌ ታይቶባቸው ነበር፤ ስለዚህ ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ ወደ ሴኬም ጠራና ቃል ኪዳኑን አደሰ። እግዚአብሔርን ወይም ሌላን ነገር እንዲመርጡ፥ በቃል ኪዳኑ ስምምነት እንዲኖሩ ወይም በእግዚአብሔር ላይ እንዲያምፁ ምርጫ ማድረግ እንዳለባቸው አስገነዘባቸው። እኛም ልክ እንደ እስራኤላውያን ሁሉ ራሳችንን ለእግዚአብሔር ለመስጠት የገባነው ቃል ኪዳን ያለማቋረጥ መታደስ አለበት። በመጀመሪያ እንዳመንን ወይም ራሳችንን ለእግዚአብሔር እንደሰጠን የገባነው ቃል ኪዳን ያለማቋረጥ መታደስ አለበት፤ አለበለዚያ መንፈሳዊ ሕይወታችን እየቀዘቀዘ ይሄድና እግዚአብሔርን እንረሳለን።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰላምና በረከት በሞላበት ጊዜ እግዚአብሔርን መርሳት በጣም ቀላል የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ስለ ራስህ ሕይወት አስብ። በሙሉ ልብህ እግዚአብሔርን እንደምትወደውና እንደምትከተለው የገባኸውን ቃል ኪዳን ለመጨረሻ ጊዜ ያደስከው መቼ ነው? ሐ) እግዚአብሔር ስለ ሰጠህ በረከት ሁሉ እስቲ ለጥቂት ጊዜ አስብ። መ) ስለ እነዚህ ጉዳዮች ለአንድ አፍታ እርሱን አመስግን። ሠ) እግዚአብሔርን ለመከተል፥ እርሱን ሁልጊዜ ለማገልገል፥ በፊቱ በፍጹም ንጽሕና ለመመላለስ ወዘተ. የገባኸውን ቃል ኪዳን አድስ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ኢያሱ 13-24 አንብብ። ሀ) ለካሌብ የተሰጠው ምን ነበር? ለ) የስድስቱ መማፀኛ ከተሞች ዓላማ ምን ነበር? ሐ) ለሌዋውያን ስንት ከተሞች ተሰጡአቸው? መ) የጎሣ ጦርነት ሊያስከትል የነበረ በምሥራቅ በሚገኙ ጎሣዎች የተፈጸመ ተግባር ምን ነበር? ሠ) ኢያሱ ከመሞቱ በፊት ለእስራኤላውያን የሰጠው ማስጠንቀቂያ ምን ነበር?

 1. የከነዓን ምድር ለእስራኤላውያን መደልደል (ኢያሱ 13-21)። አብዛኛው የከነዓን ምድር እንደተያዘ፥ እግዚአብሔር ለኢያሱ ምድሪቱን ለ12 ነገዶች እንዲያከፋፍል አዘዘው። እስካሁን ድረስ ያልተወረሩና ያልተያዙ ከተሞች በምድሪቱ ክፍል እንዲወርሱ የተደለደሉ ነገዶች የማስለቀቅ ኃላፊነት ነበረባቸው።

ሀ. ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የሚገኙ ነገዶች፡- እንደምታስታውሰው፥ ሙሴ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ የሚገኘውን ስፍራ ለሮቤል ለጋድ ነገዶችና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጥቶ ነበር። አሁን ክልላቸው ተወስኗል።

ለ. ከዮርዳኖስ በስተምዕራብ የተደለደሉ ነገዶች፡- ለቀሩት ዘጠኝ ተኩል (9 የ2) ነገዶች ከዮርዳኖስ በስተምዕራብ የሚገኘው ክፍል ተሰጣቸው። በእግዚአብሔር ላይ ለነበረው እምነትና ጥንካሬ የይሁዳ መሪ ለነበረው ለካሌብ ልዩ ትኩረት ተሰጠውና የኬብሮንን ምድር አገኘ። ኢያሱ ለነገዶቹ ሁሉ የሚሆነውን ምድር ደለደለ፤ ክልላቸውን ወሰነ፤ በክልላቸው ውስጥ ያሉትንም ከተሞች ነገራቸው። ከዚህ በኋላ በክልላቸው ውስጥ የሚገኙትን ከተሞች ሁሉ የመያዝ ኃላፊነት የእነርሱ ነበር። እያንዳንዱ ነገድ ገና ወርሮና አሸንፎ የሚይዘው ክልል ነበረው። ከአሥራ ሁለቱ ነገዶች ዋና ዋና ለሆኑት፥ ለይሁዳ፥ ለኤፍሬምና ለምናሴ ነገዶች ስለተሰጠው ምድር ሰፊና ጥልቀት ያለው ትንተና ቀርቦአል።

ሐ. የመማፀኛ ከተሞች፡- በዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ሦስት፡- በስተምዕራብ ሦስት፥ በአጠቃላይ ስድስት ከተሞችን እግዚአብሔር የስደተኛች ከተሞች ይሆኑ ዘንድ ለየ። የእነዚህ ከተሞች ዋና ዓላማ አንድን ሰው በስሕተት ለገደለ ሰው የጥበቃ ስፍራ ለመስጠት ነበር። ከሟቹ ሰው ዘመዶች ሊደርስበት ከሚችል ብቀላ ለመዳን ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ መሸሽ ነበረበት። የዚህ ዓይነቱ የፍትሕ ሥርዓት በእስራኤል ነገዶች መካከል በቤተሰባቸው ውስጥ በሞተ ሰው ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን በቀልና የእርስ በርስ ግጭት ለመከላከል ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ መንገድ በምድሪቱ ሰላምን ለማስፈን መልካም የሆነው ለምንድን ነው? ለ) በቀል ፍለጋ ወደበለጠ ጦርነትና ጥፋት የሚመራው እንዴት ነው? ሐ ሮሜ 12፡17-21 አንብብ። ብዙ ክርስቲያኖች ይህንን ትእዛዝ የማይከተሉት ለምንድን ነው? መ) ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ እርስ በርስ በቀልን የሚፈላለጉት እንዴት እንደሆነ ምሳሌዎችን ስጥ። ሠ) ለእግዚአብሔር ቤተሰቦች ይህንን የማድረግ ውጤት ምንድን ነው?

መ. ምንም ምድር ያልተሰጣቸው ሌዋዊያን በ12 ነገዶች የመሬት ድልድል ውስጥ ተሰራጭተው ያሉ 48 ከተሞች ተሰጧቸው። በተጨማሪ ከተሞቹን የሚከቡ ለሰብልና ለከብቶቻቸው ግጦሽ የሚሆን መሬት ተሰጣቸው። 

 1. ምሥራቃዊ ነገዶች ወደ አገራቸው ተመለሱ (ኢያሱ 22)። ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ የሚገኘውን ሥፍራ የወረሱት ነገዶች በስተምዕራብ የሚገኘውን ምድር ለመውረስ ያሉትን 9 ½ ነገዶች ለመርዳት፥ እንደ እነርሱ ምድራቸውን እስኪወርሱ ድረስ ለመዋጋት ቃል ገብተው ነበር። ቃላቸውንም ጠብቀዋል። አብዛኛው የጦርነቱ ክፍል ተጠናቆ ስለነበር፥ ወደ ምድራቸው ለመመለስ ፈቃድ አገኙ። ወደ ስፍራቸውም ለመመለስ፥ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በደረሱ ጊዜ የምሥራቁና የምዕራቡ ክልል ድንበር በሆነው ስፍራ ላይ ትልቅ መሠዊያን ሠሩ። የቀሩት እስራኤላውያን ግን፡- ይህን መሠዊያ የሠሩት 2 1/2 ነገዶች ጣዖታትን ለማምለክ ሲሉ ነው ብለው ገመቱ። ስለዚህ ቅዱስ በሆነ ቁጣ ወንድሞቻቸውን ለመውጋት ተነሡ። የትኛውም ነገድ ለዚህ ቃል ኪዳን የማይታዘዝ ቢሆን ፍርዱ የሚመጣው በሁላቸውም ላይ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። ነገር ግን የተሠራው መሠዊያ ዋናው ዓላማ፡- እነዚህ 2 1/2 የሚሆኑ ነገዶች የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል ለመሆናቸው የቀሩቱ 9 1/2 ነገዶች፥ እንዲያውቁላቸው፥ ለማስታወሻ የተሠራ እንጂ ለጣዖት አምልኮ እንዳልሆነ ገለጡላቸው። እዚህ 2 1/2 ነገዶች በዮርዳኖስ ወንዝ አማካይነት ከሌሎቹ ነገዶች የተለያዩ ስለነበሩ እስራኤላውያን እንደ መሆናቸው መጠን ወደ እስራኤል ገብተው እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ፥ እንደ ባዕዳን እንዳይቆጠሩ ቋሚ የሆነ ምልክት እንዲኖር ለማድረግ በመፈለጋቸው ነበር መሠዊያውን የሠሩት።

የውይይት ጥያቄ፥ እስራኤላውያን የተሳሳተ አምልኮ ወደ መካከላቸው እንዳይገባ ከነበራቸው ፍላጎት ምን እንማራለን?

 1. ኢያሱ ለእስራኤላውያን ያደረገው የስንብት ንግግር (ኢያሱ 23-24) ኢያሱ የመሞቻው ጊዜ እንደተቃረበ በማወቁ፥ ቃል ኪዳናቸውን እንዲያድሱ የእስራኤልን ነገዶች በሙሉ በአንድነት ጠራቸው። ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዝ እንዳለባቸው ለሕዝቡ ለማስታወስ ፈልጎ ነበር። ሕዝቡም ቃል ኪዳናቸውን በሴሎ አደሱ። ይህ ስፍራ እስከ ዳዊት ዘመን ድረስ የእስራኤል ሕዝብ ሃይማኖታዊ ማዕከል ሆነ። የመገናኛው ድንኳን ያረፈውና እስራኤላውያን ለአምልኮ ይመጡ የነበረው ወደዚህ ስፍራ ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢያሱ 1-12

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሽንፈት የሚደርስባቸው ለምንድን ነው? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ያለማቋረጥ በኃጢአት የሚወድቁትና ጨርሶ ድል የማያገኙ የሚመስሉት ለምንድን ነው? ሐ) እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ይህን ይመስልሃልን? ግለጥ።

እግዚአብሔር ለሕዝቡ ድልን ለመስጠት ቃል ገብቷል። ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች ሲጽፍ፦ «በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን» ብሉአል (ሮሜ 8፡37)። በተጨማሪ 1ኛ ቆሮ. 15፡57፤ 1ኛ ዮሐ. 2፡13፤ 4፡4 ተመልከት። ይህ ድል ግን እንዲሁ በቀላሉ የሚገኝ ነገር አይደለም። ለዚህ ድል ዝግጅት ማድረግ ያሻናል። እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል። ድል የሚገኘው ከእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን ጥረት እንዳልሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። በኃጢአት ላይ የድል ነሺነት ሕይወት በመኖር፥ የተቀደስን ልንሆን ያስፈልጋል። ለእግዚአብሔር ታዛዦች መሆን አለብን። የመጽሐፈ ኢያሱ የመጀመሪያ ክፍል እስራኤላውያን ከነዓንን ድል አድርገው በወረሱት ልምምድ በኩል እነዚህን አስፈላጊ መንፈሳዊ እውነቶችን ይገልጣል።

የውይይት ጥያቄ. ኢያሱ 1-12 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ኢያሱን ለመሪነት ያዘጋጀው እንዴት ነው? ለ) እግዚአብሔር በጠላቶች ላይ ስላዘጋጀው የድል መንገድ ሁለቱ ሰላዮች የተማሩት ነገር ምን ነበር? ሐ) ቀይ ባሕርን መሻገር ለእስራኤላውያን የሚያሳየው ነገር ምንድን ነው? (ኢያ. 3፡10-13)። መ) ለመታሰቢያ ይሆን ዘንድ በዮርዳኖስ ምዕራባዊ ክፍል እስራኤላውያን የገነቡት ነገር ምን ነበር? ለምን? ) በጌልጌላ ምን ተደረገ? ረ) ኢያሱ የተገናኘው የእግዚአብሔር ሠራዊት አዛዥ ማን ነበር? ለ) በኢያሪኮ ላይ እግዚአብሔር ለአይሁዳውያን ድልን የሰጠው እንዴት ነበር? ) እስራኤላውያን ጋይን ያላሸነፉት ለምንድን ነው? ቀ) እስራኤላውያን በኢባል ተራራ ምን አደረጉ? በ) አይሁድ እንዳያጠፏቸው የገባዖን ሰዎች ያደረጉት ምን ነበር? ተ) በእስራኤላውያን የተደመሰሱትን የተለያዩ ሕዝቦች ዘርዝር።

እስራኤላውያን ዮርዳኖስን በመሻገር ወደ ከነዓን ገቡ፤ (ኢያሱ 1-5)።

እስራኤላውያን በዮርዳኖስ ወንዝ ምሥራቃዊ ክፍል ሰፍረው ነበር። ከ40 ዓመታት በፊት የቀይ ባሕርን እንዲሻገሩ የረዳቸው እዚአብሔር፥ ከሙሴ ሞት በኋላ ደግሞ የዮርዳኖስን ወንዝ እንዲሻገሩ አዘጋጃቸው።

ሀ. በመጀመሪያ ግን እግዚአብሔር የእስራኤል ሕዝብ መሪ እንደ መሆኑ ኢያሱን ወደ ፊት ለሚጠብቀው አዲስ ኃላፊነት ለማዘጋጀት ፈለገ (ኢያሱ 1)። ስለዚህም እግዚአብሔር ለኢያሱ አንዳንድ ትእዛዛትን ሲሰጠው እንመለከታለን፡- 1) ከሙሴ ጋር እንደነበረ ከኢያሱም ጋር እንደሚሆንና በጠላቶቹ ሁሉ ላይ ድልን እንደሚሰጠው ቃል ገባለት። 2) እግዚአብሔር ለኢያሱ እንዲበረታና እንዲጠነክር፥ እምነቱንም በእርሱ ላይ እንዲያደርግ ነገረው። 3) እግዚአብሔር ኢያሱን ከቃል ኪዳኑ ወይም በሙሴ በኩል ከሰጠው ሕግጋት እንዳይለይ አስጠነቀቀው። ይልቁንም እነዚህን ሕግጋት በሕይወቱ በመኖር ሊያሳይና በልቡ ሊሰውር ይገባው ነበር። እግዚአብሔር ለኢያሱ እንዲከናወንለት የሚያደርገው እርሱን ካወቀና ቃሉን ከታዘዘ ብቻ ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህን ሦስት ነገሮች በዚህ ዘመን ያሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ማስታወስ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

ለ. እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ በመጀመሪያ ወደምትገኘዋ ከተማ ወደ ኢያሪኮ ኢያሱ ሁለት ሰላዮችን ላከ (ኢያሱ 2)። እነዚህ ሁለት ሰላዮች ረዓብን አገኙአት። ረዓብም በከነዓናውያን ልብ እግዚአብሔር ፍርሃትን እንዳደረገና እያንዳንዱ ሰው እግዚአብሔር ከአይሁድ ጋር ስለሆን በእነርሱ መሸነፋችን የማይቀር ነው የሚል ግምት እንዳደረበት ነገረቻቸው። ረዓብ ምን ዓይነት ሴት እንደነበረች ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ሴተኛ አዳሪ የነበረች ሴት ትመስላለች፤ (ኢያ. 2፡1)። ነገር ግን ይህ ስለማንነቷ የሚገልጠው ቃል የሆቴል ቤት ዓይነት መኝታ ክፍሉችንም የምታከራይ ሴት እንደሆነችም ሊያመለክት ይችላል። ሁለቱ ሰላዮችም ወደ እርሷ ቤት የገቡት ለዚህ ሊሆን ስለሚችል፥ በዚህ መልኩ ልንተረጉመው እንችላለን። ረዓብ ሰላዮቹን በመሸሸግ በእግዚአብሔር ላይ ያላትን እምነት ስለገለጠች፥ እርሱ አከበራት። በአዲስ ኪዳን የእምነት ምሳሌ ሆና ቀርባለች (ዕብ. 11፡31፤ ያዕ. 5፡25)። በኋላም ከይሁዳ ነገድ የሆነ ሰው ስላገባች፥ መሢሑ ክርስቶስ የመጣበት ዘር አካል ሆናለች፤ (ማቴ. 1፡5)። የዳነችው በእምነትና በመታዘዝ ቀይ ፈትልን በመስኮቷ በኩል ስላንጠለጠለች ነው። ብዙዎች ይህ እኛን ያዳነ የክርስቶስ ደም ምሳሌ ነው ይላሉ።

ሐ. እስራኤላውያን የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ (ኢያሱ 3)።

እስራኤላውያን የዮርዳኖስን ወንዝ በተሻገሩ ጊዜ እጅግ ሞልቶ እንደ ነበረ እናነባለን። ለመሻገርም የማያስችል ነበር። እግዚአብሔር ግን ተአምር ሠራ። ምናልባት በሚንሸራተት ጭቃ ወይም በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት [መዝ. (114)፡3-4] በስተሰሜን 25 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝና እስራኤላውያን በተሻገሩት አዳም በሚባል ከተማ ውኃው ተገድቦ ይሆናል። በምንም መንገድ ይሁን፥ እግዚአብሔር ምንም ነገር ይጠቀም፥ ተአምር ነበር። 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የዮርዳኖስን ወንዝ በየብስ ተሻገሩ። ይህ ተአምር ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች ነበሩት። የመጀመሪያው፥ ሙሴ ሕዝቡን ቀይ ባሕርን እንዳሻገራቸው ሁሉ፥ ኢያሱም እውነተኛ መሪ መሆኑን ለማሳየት ነበር። ሁለተኛ፥ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንደሆነና በጠላቶቻቸው ላይ ድልን እንደሰጣቸው የሚያሳይ ነበር።

መ. እስራኤላውያን በዮርዳኖስ ምዕራባዊ ክፍል መታሰቢያን አቆሙ (ኢያሱ 4)። ኢያሱ በመጽሐፉ ውስጥ እስራኤላውያን ከእነርሱ በኋላ ለሚመጣ ትውልድ ቋሚ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር በዚህ ዘመን ለእነርሱ ያደረገላቸውን እንዲያውቁ፥ በርካታ ጊዜያት መታሰቢያ ያቀሙ ነበር። ለእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ አንድ አንድ ድንጋይ የቆመለትና በአጠቃላይ 12 ድንጋዮች በመታሰቢያነት የቆሙት እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ወንዝ እንዲሻገሩ እስራኤላውያንን እንዴት እንደረዳቸው በመታሰቢያነት ለማሳየት ነበር።

ሠ. በጌልገላ የአይሁድ መገረዝ (ኢያሱ 5)። አይሁድ 40 ዓመታት እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ ኖረዋል። ወንዶች ልጆቻቸውን አልገረዙም ነበር። ግዝረት አይሁድ በቃል ኪዳኑ ውስጥ ለመኖራቸው ውጫዊ ምልክት ነበር፤ በተጨማሪ ራሳቸውን ከኃጢአት የመለየታቸው ምልክት ነበር። በግብፅ ሊኖሩ የነበረባቸው የኃጢአት ነውር አልለቀቃቸውም ነበር፤ (ኢያሱ 5፡9)። ስለዚህ እግዚአብሔር አይሁድ ምድሪቱን እንዲወርሱ ከማድረጉ በፊት በመንፈሳዊ ሁኔታ ሊያዘጋጃቸው ያስፈልግ ነበር። በግዝረት የሕመም ስሜት ውስጥ ማለፋቸው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን የማክበራቸውን አስፈላጊነት የሚያሳስብ ነበር። በዚያ ቀን በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት የተመገቡት መና አበቃና የከነዓንን ምድር ፍሬ መብላት ጀመሩ። በዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ለመጀመሪያ ጊዜ አይሁድ በሰፈሩበት በጌልገላ የተፈጸመ አንድ ሌላ በጣም አስፈላጊ ነገር ነበር። ጌልጌላ የእስራኤል ሕዝብ ጊዘያዊ ዋና ማዕከል ሆነች። በዚህ ስፍራ ኢያሱ «የእግዚአብሔር ሠራዊት አዛዥ» የሆነውን ተገናኘው። መዋጋት ከመጀመሩ በፊት፥ የእስራኤልን ጦር የሚመራው እርሱ እንጂ ኢያሱ እንዳልሆን እግዚአብሔር ሊያስታውሰው ፈለገ። በመጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ «የሠራዊት ጌታ» በመባል ይታወቃል። ብዙ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ «የሠራዊት ጌታ» የተባለው እግዚአብሔር የእስራኤል ማለት የሕዝቡ ሠራዊት እውነተኛ መሪ ነበር። ኢያሱ በእርሱ ትእዛዝ ሥር ነበር። ብዙ ሰዎች የጌታ ጦር አዛዥ የነበረው ይህ አለቃ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብለው ያስባሉ።

የውይይት ጥያቄ ሀ) ለኢያሱ ይህንን እውነት የመረዳት አስፈላጊነቱ ምን ነበር? ለ) ዛሬ ይህንን እውነት ከሕይወታችን ጋር እንዴት ልናዛምደው እንችላለን?

ረ. እስራኤላውያን ኢያሪኮን ያለ ውጊያ ያዙ (ኢያሱ 6)። እስራኤላውያንን የገጠመቻቸው የመጀመሪያዋ ከተማ ጠንካራዋ ኢያሪኮ ነበረች። ዙሪያዋን በትልቅ ግንብ የታጠረች፥ በምሽት የሚዘጋ ትልቅ መዝጊያ የነበራት ስለሆነ፥ እርስዋን ማጥቃት ፈጽሞ አስቸጋሪ ነበር። ይህችን ከተማ ያለ አንዳች ጦርነት እንዲይዙዋት በማድረግ ድልን የሚሰጥ እግዚአብሔር እንጂ እነርሱ እንዳይደሉ አሳየ። እስራኤላውያን በኢያሪኮ ግንብ ዙሪያ በእምነት ስለዞሩ ቅጥሩ በሰባተኛው ቀን ወደቀ። በከነዓን ምድር በመጀመሪያ ልትጠፋ ያለችው ከተማ ኢያሪኮ ስትሆን በርሷም ውስጥ ያሉት ነገሮችን በሙሉ እንዲያጠፉ ወይም ለእርሱ ጥቅም ብቻ እንዲያውሉ እግዚአብሔር አዘዘ። ከጦርነቱ ምርኮ የሚገኝ ማንኛውም ነገር ቢሆን ለግል ጥቅም እንዳይውል ተከለከለ። በተጨማሪ ኢያሱ ይህችን ከተማ እንደገና ለመገንባት የሚሞክር ሰው ሁሉ በልጆቹ ሞት መከራ ያገኘው ዘንድ ከተማይቱን ረገመ (በ1ኛ ነገሥት 16፡34 የዚህን ጥቅስ ፍጻሜ እናገኛለን)።

ሰ. እስራኤላውያን በኃጢአታቸው ምክንያት በጋይ ተሸነፉ (ኢያሱ 7-8)። እግዚአብሔር በጋይ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሁለት ትምህርቶችን ለእስራኤላውያን ማስተማር ነበረበት። በመጀመሪያ፥ ድል ለማግኘት መደገፍ ያለባቸው በእግዚአብሔር እንጂ በራሳቸው ኃይል እንዳልነበረ ነው። እስራኤላውያን ትንሿን የጋይ ከተማ ያለ እግዚአብሔር ርዳታ በራሳቸው ኃይል እንደሚያሸንፉ ገመቱ፤ ነገር ግን ተሸነፉ። ሁለተኛው ነገር ደግሞ፥ እግዚአብሔር ለእነርሱ የሚሠራውን ሥራ በመካከላቸው እንዳይሠራ የሚከለክለው ኃጢአት እንደሆነ ማሳየት ነበረበት። አካን እግዚአብሔርን ስላልታዘዘና ከኢያሪኮ ከተማረከው ነገር ለራሱ የሚሆነውን ስላስቀረ እስራኤላውያን እንዲሸነፉ አደረገ። እስራኤላውያን በተሠራው ኃጢአት ከፈረዱና ከመካከላቸው ካስወገዱ በኋላ ብቻ እግዚአብሔር በጋይ ምድር ላይ ድልን ሰጣቸው። እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ ያለውን ጥላቻ ለመግለጥና የእግዚአብሔርን ማኅበረሰብ ኃጢአት እንዴት ችግር ላይ ሊጥለው እንደሚችል ለማሳየት፥ ይህ ታሪክ፥ እግዚአብሔር አካንና ቤተሰቡ ሁሉ እንዲገደሉ መስማማቱን ያሳየናል። በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል የሚፈጸም ኃጢአት በዚያ ሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚሆን ግላዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በአጠቃላይ የሚመለከት ነው። በአክአብና በቤተሰቡ በተቃጠለ አካል ላይ የተከመረው ድንጋይ ኃጢአት እንዴት ሰዎችን እንደሚጎዳ የሚያሳይ የመታሰቢያ ሐውልት ሆኖ የሚያገለግል ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ድል ለማድረግ ባለን ችሎታ ላይ ኃጢአት ስለሚያመጣው ችግር ምን መማር እንችላለን? ለ) ስለ እግዚአብሔር ባሕርይና ኃጢአትን በከባድ ሁኔታ እንዴት እንደሚመለከተው ከዚህ ታሪክ ምን መማር እንችላለን? ሐ) ብዙ ጊዜ ኃጢአትን እንደ ቀላል ነገር የምንመለከተው እንዴት ነው? መ) በኃጢአት ላይ ስላለን አመለካከት ይህ ምን ይላል? ሠ) ኃጢአትን በቀላል ሁኔታ መመልከት በአጭር ጊዜ ውስጥ በቤተ ክርስቲያን እንዲስፋፋ የሚያደርገው እንዴት ነው?

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጋይን ካሸነፉ በኋላ ወደ ሴኬም ተጓዙ። ሴኬም የሚገኘው በጌባል ተራራ ግርጌ ነበር። በጌባልና በገሪዛን ተራራ ላይ በእግዚአብሔርና በእስራኤላውያን መካከል የተደረገው ቃል ኪዳን ታደሰ። በጌባል ተራራ ላይ የእግዚአብሔርን ሕግ ቢጠብቁ ስለሚያገኙት በረከት ከፊሎቹ እስራኤላውያን አነበቡ። የቀሩት ደግሞ በገሪዛን ተራራ ላይ ሆነው የእግዚአብሔርን ሕግ ባይጠብቁ ስለሚገጥሟቸው ርግማኖች የተጻፉትን አነበቡ። ከዚያም በአንድነት ቃል ኪዳናቸውን አደሱ።

ሸ. የገባዖን ሰዎች እስራኤላውያንን አታለሉ (ኢያሱ 9)። ከትላልቅና ከተገነቡ ከተሞች ብዙ ኪሎ ሜትር ሳያርቁ የሚገኙት የገባዖን ሰዎች በኢያሪኮና በጋይ የነበረቱን ከነዓናውያንን በማሸነፍ ሙሉ በሙሉ እንዴት እንዳጠፏቸው ሰሙ። ስለዚህ ከሩቅ ቦታ የመጡና ከእስራኤላውያን ጋር ለመተባበር የፈለጉ በመምሰል ሊያታልሏቸው ወሰኑ። አይሁድም በጉዳዩ እግዚአብሔርን ሳይጠይቁ ከሰዎቹ ጋር ስምምነት አደረጉ። እግዚአብሔር ከከነዓናውያን ጋር ምንም ዓይነት ስምምነት እንዳያደርጉ አግዶአቸው ነበር፤ (ዘጸ. 34፡ 12፥ 15)። ስለዚህ ጉዳይ ንጉሣቸው የሆነውን እግዚአብሔርን ስላልጠየቁ ተታለሉ። ለገባዖን ሰዎች ቃላቸውን ሰጥተው ስለ ነበር ምንም ነገር ያደርጉባቸው ዘንድ እግዚአብሔር አልፈቀድም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደምናየው እግዚአብሔር ሕዝቡ የገቡትን ቃል እንዲጠብቁ ከፍተኛ ትኩረት ያደርግ ነበር (ዘሌ. 19፡12-13)፤ ነገር ግን የገባኦንን ሰዎች ባሪያዎች አደረጉአቸው። 

ቀ. ከደቡብ ከነዓን ነገሥታት ጋር የተደረገ ጦርነት (ኢያሱ 10)። የደቡብ ከነዓን ነገሥታት የገባዖን ሰዎች ከእስራኤላውያን ጋር መተባበራቸውን በሰሙ ጊዜ ገባዖንን ወጉ። እስራኤላውያንም ከገባዖን ሰዎች ጋር ባደረጉት ስምምነት የተነሣ የገባኦንን ሰዎች በዚህ ጦርነት መርዳት ግዴታቸው ነበር፤ ስለዚህ እስራኤላውያን አምስቱን የከነዓን ነገሥታት ወግተው አሸነፏቸው። እግዚአብሔር አሁንም ለእስራኤል ሲል ተአምር አደረገ። የእነዚህን አምስት ነገሥታት ሠራዊት ፈጽመው ይመቱ ዘንድ ፀሐይን እንድትቆም አደረገ። የእስራኤል ጦር ከገደላቸው ይልቅ እግዚአብሔር ከሰማይ በላከው፥ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት ቁጥር ይበልጥ ነበር። ከዚህ በኋላ ኢያሱ ወደፊት በመገስገስ በደቡብ ከነዓን የሚገኙትን ሌሎች ዋና ዋና ከተሞች አሸነፈ። 

** እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን መዋጋቱን የሚገልጸውን የዚህን ምዕራፍ ትኩረት አስተውል (ኢያ. 10፡14፥ 42)። ጠላቶቻቸውን እንዲያሸንፉ ያደረጋቸው የራሳቸው ብርታት ሳይሆን ስለ እነርሱ ሲል የተዋጋው የእግዚአብሔር ኃይል ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ በሕይወታችን ለሚያጋጥመን ለማንኛውም ድል ይህ ነገር እውን የሆነው እንዴት ነው?

በ) የሰሜን መንግሥታት ተሸነፉ (ኢያሱ 11)። እስራኤላውያን በኢያሱ መሪነት በመካከለኛይቱ ከነዓን የሚገኙትን ዋና ዋና ነገሥታት (ኢያሪኮና ጋይ) እና እንደዚሁም የደቡብ ከነዓን ነገሥታትን ካሸነፉ በኋላ ወደ ሰሜን ከነዓን ከተሞች ዘመቱ (ኢያሱ. 11፡18)። ይህ ጦርነት ረጅም ጊዜ የወሰደ ቢሆንም (ኢያሱ 11፡18)፥ ሆኖም በሰሜኑም የሚገኙት ዋና ዋና ከተሞች በሙሉ ተሸነፉና እስራኤላውያን ተቆጣጠሩአቸው። 

አሁን እያንዳንዱ ነገድ በምድሪቱ የቀሩትን ከነዓናውያን የማጥፋት ኃላፊነት ነበረበት። ነገር ግን ለእግዚአብሔር በመታዘዝ እንደማጥፋት ከቀሩት ከነዓናውያን ጋር በሰላም መኖርን መረጡ። በዚህም ምክንያት ወደ ፊት እንደምናየው፥ ከነዓናውያን ኃጢአትን ለእስራኤል ሕዝብ በማስለመድና እነርሱን ወደ ኃጢአት በመምራት የእግዚአብሔር ቁጣ በእስራኤላውያን ላይ እንዲመጣ አደረጉ።

ተ) በእስራኤል የተሸነፉ የ31 ነገሥታት ዝርዝር (ኢያሱ 12)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በእግዚአብሔር ጠላቶች ላይ ድል ለመቀዳጀት የሚጠቅሙትን መመሪያዎች ከእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ዘርዝር። ለ) ድል አድራጊ ክርስቲያን እንድትሆን እነዚህን መሠረታዊ የሥነ ምግባር ሕግጋት ከሕይወትህ ጋር እንዴት እንደምታዛምድ ግለጽ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመጽሐፈ ኢያሱ ዋና ዓላማ

መጽሐፉ የተሰየመው፥ በመጽሐፉ ውስጥ በሚገኘው ዋና ተዋናይ በኢያሱ ቢሆንም፥ ትኩረቱ ግን በእርሱ ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ መሪ የሆነውና የእስራኤልን ጦር በመምራት ድልን ያስገኘው እግዚአብሔር ነው። ኢያሱ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሥር ያለ ሰብአዊ መሪ በመሆኑ ትእዛዙን በቀጥታ ይፈጽም ነበር።

ከሌሎች መጻሕፍት (መጽሐፈ መሳፍንት፥ ሳሙኤልና ነገሥት) ጋር በአንድነት ሆኖ የመጽሐፈ ኢያሱ ዋና ዓላማ እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ ከእስራኤል ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እንዴት እንደፈጸመ ማሣየት ነው። መጽሐፈ ኢያሱ የሚያሳየው፥ እስራኤላውያንን ወደ ከነዓን ምድር በማምጣትና ለአብርሃም ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የገባውን ቃል ኪዳን በመፈጸም፥ የቃል ኪዳን ተስፋዎቹን በታማኝነት እንዴት እንደጠበቀ ነው (ዘፍ. 15፡18-2)። የእግዚአብሔር ሕዝብ ምንም ያህል አስቸጋሪ ሆኖ ቢታይም፥ እግዚአብሔር ለሰጠው ተስፋ ታማኝ መሆኑን አሳየ።

መጽሐፈ ኢያሱ በጠላቶች ላይ ድል የሚገኘው በእግዚአብሔር ኃይልና አመራር ብቻ መሆኑን ያሳያል። ሕዝቡ በእርሱ ላይ በእምነት በሚደገፉበትና ሙሉ ለሙሉ እርሱን በሚታዘዙበት ጊዜ ብቻ ይፈጸማል። ኃጢአት የእግዚአብሔርን ሥራ የሚከለክል ሲሆን፥ እምነት ግን በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል የእግዚአብሔር ኃይል እንዲገለጥ ያደርጋል። ድል የሚገኘው በመታመንና በመታዘዝ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የመጽሐፈ ኢያሱ ዓላማ በመንፈሳዊ ሕይወት ጠላቶቻችን ላይ ድልን የማግኛ ምሥጢር ምን እንደሆነ የሚያስተምረን እንዴት ነው? ለ) ይህ በሕይወትህ ሲፈጸም ያየኸው እንዴት ነው? ሐ) እግዚአብሔር በሕይወትህ ስለሠራው ሥራ እርሱን ለማመስገን አሁኑኑ ጊዜ ይኑርህ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመጽሐፈ ኢያሱ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ መዝ. (91)፡1-16 አንብብ። ሀ) በጠላቶቻችን ላይ ስለምንቀዳጀው ድል በዚህ ስፍራ የተሰጡ ተስፋዎች ምንድን ናቸው? ለ) እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ድል የሰጠህን አንዳንድ ጠላቶች ጥቀስ። ሐ) እግዚአብሔር፥ ቤተ ክርስቲያንህ በእነርሱ ላይ ድል እንድትጎናጸፍ ያደረጋትን አንዳንድ ችግሮችንና ጠላቶችን ጥቀስ።

መጽሐፈ ኢያሱ በእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶች ላይ ስለተገኘ ድል የሚናገር መጽሐፍ ነው። ዛሬም እኛ ድልን እንዴት እንደምናገኝ የሚያስተምረን መጽሐፍ ነው። ድልን የምናገኘው ለእግዚአብሔር ስንታዘዝ፥ በተቀደሰ ሕይወትና በእግዚአብሔር ላይ ባለን እምነት ስንመላለስ ብቻ ነው። ይህ መጽሐፍ ዛሬም ለእኛ የሚሆን በጣም አስፈላጊ መልእክት አለው። እግዚአብሔር እያንዳንዳችን ኃጢአትን፥ ሰይጣንን ወዘተ. ድል በማድረግ እንድንኖር ይፈልጋል። ቤተ ክርስቲያን እንደ መሆናችንም እግዚአብሔር በድል እንድንኖር ይፈልጋል። መጽሐፈ ኢያሱ በግልም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ደረጃ በድል እንዴት እንደምንመላለስና የእግዚአብሔርን ጠላቶች ሁሉ እንደምናሸንፍ ሊያስተምረን ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ መጽሐፈ ኢያሱና ስለ ኢያሱ ሕይወት ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ሀ) ስለ ኢያሱ ማንነት የተጠቀሱትን ነገሮች በሙሉ ዘርዝር። ለ) የመጽሐፈ ኢያሱ ጸሐፊ ማን ነው?

የመጽሐፈ ኢያሱ ጸሐፊና የተጻፈበት ጊዜ

መጽሐፈ ኢያሱን የጻፈው ማን ነው? የሚለው ጥያቄ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንን አከራክሮአል። መጽሐፉን የጻፈው ማን ነው? የሚለውን ጥያቄ በሚመለከት ሦስት የተለያዩ አሳቦች አሉ፡- 

 1. አንዳንዶች መጽሐፈ ኢያሱ የተጻፈው በታሪኩ ውስጥ የሚገኙ ድርጊቶች ከተፈጸሙ ከ800 ዓመታት በኋላ ነው፤ የተጻፈውም ኦሪት ዘዳግምንና እስከ 2ኛ ነገሥት ያሉትን ሌሎች የታሪክ መጻሕፍትን በጻፈው ሰው ነው ይላሉ። ሆኖም በመጽሐፈ ኢያሱ ውስጥ የተሰጡትን ታሪካዊ ዘገባዎች ከተመለከትን መጽሐፈ ኢያሱ የተጻፈው ከዳዊት በፊት እንደሆነ ግልጥ ነው። ለምሳሌ፡- ኢየሩሳለም አልተወረረችም ነበር። 
 2. አንዳንዶች መጽሐፉን የጻፈው ኢያሱ ነው ይላሉ፤ ይህም ስለ ሞቱ ከሚናገረው ክፍል በቀር መጽሐፉን በሙሉ የጻፈው ኢያሱ ነው የሚለው የአይሁድ አመለካከት ነው። ከመጽሐፈ ኢያሱ 18:8 ና 24፡25-26 እንደምንመለከተው፥ ኢያሱ አንዳንድ ነገሮችን ጽፎአል። ስለ ጦርነቶቹና ስለ ተካሄደባቸው ስፍራዎች ከሚሰጠው ገለጻ አንፃር፥ ጸሐፊው ድርጊቱ ሲፈጸም በዓይኑ ያየ ሰው ይመስላል። ይሁን እንጂ ጸሐፊው ኢያሱ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አይናገርም። መጽሐፉን የጻፈው ኢያሱ እንደሆነ የሚናገር ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም።
 3. ከኢያሱ ዘመን በኋላ፥ ምናልባትም በሳሙኤል ጊዜ መጽሐፈ ኢያሱ ተጽፎ፥ ወይም ተቀናብሮ ይሆናል። በመጽሐፈ ኢያሱ ውስጥ የመጽሐፉ የመጨረሻ ቅንብር የተከናወነው ኢያሱ ከሞተ ከብዙ ጊዜ በኋላ መሆኑን የሚጠቁም፥ «እስከዚህ ቀን ድረስም» የሚል ቃል ከ12 ጊዜ በላይ ተጠቅሶአል።

ስለዚህ የመጽሐፈ ኢያሱ ጸሐፊ አይታወቅም፥ ነገር ግን የመጸሐፉ ሥራ የተጠናቀቀው በዳዊት ጊዜ በ1000 ዓ.ዓ. ነው ማለቱ ይሻላል።

ከነዓንን የመውረር ታሪካዊ ሥረ – መሠረት 

 1. ከነዓንን ለመቆጣጠር የተደረገ ጦርነት ከፔንታቱክ መጽሐፍ ጥናታችን እንዳየነው፥ የከነዓን ምድር ተፎካካሪ የሆኑ መንግሥታት ጦር ሜዳ ነበረች። ከ2000 – 1780 ዓ.ዓ. በአብርሃም ጊዜ ከነዓን በግብፅ ግዛት ሥር ነበረች። የግብፅ ኃይል በደከመና በቀነሰ ጊዜ በሐይክሶሳውያን ተውግታ ድል ሆነችና ከ1780-1550 ዓ.ዓ. በቁጥጥራቸው ሥር ሆነች። ግብፃውያን ሐይክሶሳውያንን አስወጥተው እንደገና ገናና መንግሥት ሆኑና አይሁድን በባርነት ገዟቸው። በ1440 ዓ.ዓ. አካባቢ የግብፃውያን ኃይል ቀነሰና እግዚአብሔር አይሁዳውያንን ከግብፅ ኃይል ነጻ አደረጋቸው። በዚህ ጊዜ ግብፃውያን በከነዓን ላይ የነበራቸውን የበላይነት አጡ።

በ1460 ዓ.ዓ. ከጳለስጢና በስተሰሜን እጅግ ራቅ ብሎ (በአሁኑ ዘመን ቱርክ በሚባለው ስፍራ) ሌላ ሕዝብ ተነሣ። ይህ ሕዝብ ኬጢያዊ ይባል ነበር። ይህ ሕዝብ ግብፅን አሸነፈና በሰሜን ከነዓን ላይ ጊዜያዊ የሆነ የበላይነት አገኘ። በዚሁ ጊዜ የአሦር መንግሥት ተነሣ ይህችን የተስፋ ምድር ለመውረስ የሚዋጉ ሦስት ትላልቅ መንግሥታት ስለነበሩ፥ በከነዓን ውስጥ የሚደረጉ በርካታ ጦርነቶች ቢኖሩም፥ ከነዓንን የተቆጣጠረ አንድም መንግሥት አልነበረም። ይህ ጦርነት ኬጢያውያን ከተደመሰሱ በኋላ ግብፅ በከነዓን ላይ እንደገና የበላይነትን እስከተቀዳጀችበት እስከ 1280 ዓ.ዓ. ድረስ ቀጠለ።

ይህም ማለት እግዚአብሔር እስራኤልን ነፃ ለማውጣትና ለአብርሃም በገባው ቃል መሠረት፥ የከነዓንን ምድር ለመስጠት በተዘጋጀበት ጊዜ፥ ግብፅ በኃይሏ እንድትዳከም ሁኔታዎችን አመቻችቶ ነበር። በኋላም በ1300 ዓ.ዓ. በመሳፍንት ዘመን በመጽሐፉ ውስጥ ባይጠቀስም እንኳ ግብፅ እንደገና ኃያል አገር በመሆን ከነዓንን ተቆጣጥራ ነበር።

የዓለምን ታሪክ በምናጠናበትና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በምናወዳድርበት ጊዜ እግዚአብሔር በታሪክ ሁሉ አይሁዳውያን ከምርኮ ነፃ የሚወጡበትን መንገድ ለማዘጋጀትና ከነዓንን እንዲወርሱ ለማድረግ እንደሠራ በመገንዘብ እንደነቃለን። አይሁዳውያን ከባርነት ነፃ ለመውጣት የቻሉት ግብፃውያን በዚያን ጊዜ ደክመው ስለነበር ነው። ሦስት መንግሥታት ከነዓንን ለመውረስ በመታገል ላይ ስለነበሩ አንድ ታላቅና የታወቀ ኃይል የከነዓንን ምድር ለመቆጣጠር አልቻለም፤ ስለዚህ እስራኤላውያን እንደ ግብፅ፥ ኬጢያውያንና አሶራውያን ያሉ ታላላቅ መንግሥታት ጣልቃ ሳይገቡ ወረራ በማካሄድና ድል በማድረግ የከነዓንን ምድር ለመውረስ በቅተዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር በሕዝብ ሁሉ ላይ ተቆጣጣሪ እንደሆነና ይህንም በማድረጉ ለሕዝቡ ያለውን ዓላማ ለመፈጸም እንደሚሠራ ይህ ክፍል ምን ያስተምረናል? ለ) ይህንን መረዳት ዛሬ ለእኛ የሚሰጠው መጽናናት ምንድን ነው?

የከነዓናውያን የፖለቲካ መዋቅር

ከነዓን በአንድ ንጉሥ ሥር ተጠቃልላ የምትተዳደር ምድር አልነበረችም። ይህም ራሱ ምድሪቱን ለመውረር ቀላል አድርጎታል። ከነዓን የምትተዳደረው «የከተማ ግዛቶች» በመባል ይታወቁ በነበሩ ትናንሽ መንግሥታት ነበር። ይህም ማለት በአካባቢው ያለው መሬት በአንዲት ሰፊና ትልቅ ከተማ ሥር ሆኖ በንጉሥ ይገዛ ነበር ማለት ነው። በመሆኑም የንጉሡ ሥልጣን በአካባቢያቸው ላለው ምድር ብቻ ነበር። እነዚህ ከተሞች በጠላቶቻቸውና በወራሪ ዘላኖች እንዳይደፈሩ በትላልቅ ቅጥሮች የተከበቡ ነበሩ። እነዚህ የከተማ ግዛቶች ብዙ ጊዜ በውጭ ኃይል ቁጥጥር ሥር የሆኑና ለእነዚህ ኃይላት የሚገብሩ ነበሩ። እነዚህ ትናንሽ የከተማ ግዛቶች ጠላቶች ሊያጠቋቸው በሚመጡበት ጊዜ፥ በቃል ኪዳን ይተባበሩና የጠላቶቻቸውን ጥቃት ለመመከት ይታገሉ ነበር። ይህ ሁሉ በመጽሐፈ ኢያሱ ውስጥ ተንጸባርቆአል። የከነዓን ምድር አቀማመጥ አገሪቱ አንድ ሆና በአንድ ንጉሥ እንድትተዳደር የማያስችላት ስለነበረና ብዙ ጊዜ እንደ ግብፅ ባሉ ውጫዊ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ስለነበረች ለተፈጸመው ታሪካዊ ሁኔታ በዚህ መልክ ተደራጅታ ነበር።

በዚህ ሳይቀር የእግዚአብሔርን እጅ እናያለን። አንድ የሆነና የተባበረ መንግሥት ስላልነበረ ለኢያሱና ለእግዚአብሔር ሕዝብ ትናንሽ ከተሞችን ወይም የትናንሽ ከተሞችን ኅብረት ለማጥቃት ቀላል ነበር። በመጽሐፈ ኢያሱ ጥናታችን፥ ኢያሱ ምድሪቱን በአጠቃላይ ለመውረስ ሦስት ዋና ዋና የከተማ ግዛት ፌዴራላዊ ኅብረቶችን ብቻ ማሸነፍ እንደነበረበት እናያለን። 

ከነዓን ለዓለም የነበራት አስፈላጊነት

የከነዓን ምድር ብዙ ሕዝብ ያልነበረባት ብትሆንም ለቀረው ዓለም በጣም ተፈላጊ ነበረች። አስፈላጊነቷ በነበራት ሀብት አልነበረም። አስፈላጊነቷ የሦስት ክፍለ ዓለማት፡- የአውሮፓ፥ የአፍሪካና የእስያ መገናኛ ስለነበረች ነው። ስለዚህ የበርካታ ንግዶች መተላለፊያ ነበረች። የዚህ ዓይነት የንግድ መተላለፊያ ስለነበረችና ጠቃሚ የወደብ አገልግሎት ስለ ነበራት ለመካከለኛው ምሥራቅ ኢኮኖሚ ካላት ጠቀሜታ አንፃር፥ ትላልቅ መንግሥታት እርሷን ለመቆጣጠር ይዋጉ ነበር።

የከነዓናውያን ሃይማኖት

የውይይት ጥያቄ፥ ዘፍ. 15፡16 አንብብ። በዚህ ስፍራ እግዚአብሔር የአሞራውያን ኃጢአት ምንድን ነው ይላል? (አሞራውያን የሚለው ስም የከነዓናውያን ሌላ ስም ነው)።

በቅርብ ዓመታት የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች ስለ ከነዓናውያን ጥንታዊ ማምለኪያ ስፍራዎች በርካታ ነገሮችን አግኝተዋል። የከነዓናውያን ሃይማኖት እጅግ የተበላሸ በመሆኑ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት እንደነበር አረጋግጠዋል። ሃይማኖታቸው በርካታ አማልክት ያሉት ብቻ ሳይሆን በብዙ የፍትወተ ሥጋ ኃጢአት ላይ የተመሠረተ፥ ወንዶችና ሴቶች በማምለኪያ ስፍራዎች በግልሙትና የተጠመዱበት፣ ፍትወተ ሥጋ ከእንስሳት ጋር ሁሉ የሚፈጸምበት ሃይማኖት ነበር። ልጆቻቸውንም ለጣዖቶቻቸው ይሠዉ ነበር።

ከነዓናውያን ከ70 የሚበልጡ የተለያዩ ተባዕትና እንስት አማልክት እንደነበሩ ያምኑ ነበር። እነዚህ ሁሉ የሁለት ዋና ዋና አማልክት – ኤል እና አሼራህ የሚባሉ ልጆች እንደሆኑ ያምኑ ነበር። ኤል ዋና አለቃ የሆነው አምላክ ሲሆን፥ ስሙ አይሁድ የእግዚአብሔር ስም አድርገው ይጠቀሙበት ለነበረው ኤሎሂም መሠረት ነው። ይህን አምላክ ብዙ ጊዜ ከኮርማ ወይም በሬ ምስል ጋር ያያይዙት ነበር። የሚስቱ ስም አሴራ ነበር፤ (2ኛ ነገሥት 21፡7 አዲሱን የአማርኛ ትርጉም ተመልከት)። ከልጆቻቸው ዋና ከነበሩት መካከል አንዱ በአል ሲሆን የስሙ ትርጉምም ጌታ ማለት ነው። እርሱ የሌሎቹ አማልክት ሁሉ ጌታ ሲሆን ሰማይና ምድርን፥ ዝናብን፥ ወዘተ ይቆጣጠር ነበር። ሁለት ሚስቶች አግብቶ ነበር። አንደኛዋ የጦርነት አምላክ የነበረችው «እኅቱ» አናት ነበረች። ሁለተኛዋ ሚስቱ ደግሞ «አሽቶሪዝ» ተብላ የምትጠራው የምሽት ኮከብ አምላክ የነበረችዋ ናት። «ሞት» የተባለው የሞት አምላክ ሲሆን፥ የበአል ጠላት ነበር። «ዮምም» የባሕር አምላክ የነበረና ከበአል ጋር ተጣልቶ የተሸነፈ ነው። «ሞሌክ» የአሞን አምላክ ሲሆን ብዙ ጊዜ ሰውን ከመሠዋት ጋር ይያያዝ ነበር። እነዚህ ከነዓናውያን ያመልኩአቸው ከነበሩ አማልክት ጥቂቶቹ ናቸው።

እግዚአብሔር አንድ ቀን የአሞራውያን ወይም የከነዓናውያን የኃጢአት ጽዋ ሲሞላ የሚፈርድበት ጊዜ እንደሚመጣ ለአብርሃም ተናግሮ ነበር። ያ የፍርድ ጊዜ እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ለመግባት ወረራ ባካሄዱ ጊዜ ተፈጸመ።

አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔር ከነዓናውያንን ሙሉ በሙሉ እንዲያጠፉ እስራኤላውያንን አዝዞአቸው ነበር የሚለውን ትእዛዝ ለመቀበል ይቸገራሉ (ዘዳ. 7፡16፤ 20፡17-18 ተመልከት)። ይህ ቅን ፍርድ አይደለም ብለው ያስባሉ። ነገር ግን አራት ነገሮችን በቀጥታ ማስታወስ ይገባናል፡-

1) እግዚአብሔር በፈለገው መንገድ በኃጢአትና በኃጢአተኞች ላይ የመፍረድ መብት አለው። በበሽታ ወይም በሞት ሊቀጣ ይችላል። ደግሞም ሌሎች ሰዎችን በመቅጫ መሣሪያነት ሊጠቀም ይችላል። እግዚአብሔር በምሕረቱ ለከነዓናውያን ከኃጢአታቸው ንስሐ ገብተው እንዲመለሱ 400 ዓመታት ሰጥቶአቸው ነበር። ይህንን ዕድል ለመጠቀም ስላልፈቀዱ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን የፍርድ መሣሪያው አድርጎ ተጠቀመባቸውና የከነዓናውያንን ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆቻቸውን ሁሉ እንዲያጠፉ አዘዛቸው።

2) ከነዓናውያን ይህንን ፍርድ በራሳቸው ላይ ያመጡት፣ በእግዚአብሔርና እርሱ በልባቸው ባኖረላቸው ሕግጋት ላይ በግልጽ ስላመፁ ነው። ልባቸውን በእግዚአብሔር ላይ አደነደኑ (ኢያ. 11፡18-20)።

3) እግዚአብሔር፥ ከነዓናውያንን በሙሉ እንዲያጠፏቸው እስራኤላውያንን ያዘዘው አይሁድን ወደ ጣዖት አምልኮ እንዳይመልሱ ነበር፤ (ዘዳግ. 20፡16-17)። ይህንን ባለማድረጋቸው፥ ወዲያውኑ ከነዓናውያን እስራኤላውያንን ሲያስኮበልሉና የብልሹ ምግባሮቻቸው ሰለባዎች ሊያደርጉአቸው እንመለከታለን። እንዲያውም በመጨረሻ እስራኤላውያን ከእነርሱ ብሰው በመገኘታቸው እግዚአብሔር እንደፈረደባቸው እንመለከታለን፤ (2ኛ ነገሥት 21፡9)።

4) የከነዓን ምድር የእግዚአብሔር እንጂ የከነዓናውያን አይደለም። ስለዚህ እግዚአብሔር ለፈለገው ሰው ሊሰጠው መብቱ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ነገሥት 17፡7-23፤ 21፡9ን አንብብ። ሀ) እስራኤላውያን የሠሩትን ኃጢአትና የተፈረደባቸውን ፍርድ ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር ኃጢአትን ስለ መጥላቱ ይህ ነገር ምን ያስተምረናል? ሐ) ኃጢአትን እንዴት መጥላት እንዳለብንና በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እንዳይስፋፋ እንዴት መጠበቅ እንዳለብን ከዚህ ምን እንማራለን? መ) ኃጢአት እንዳይስፋፋ ቤተ ክርስቲያንህ ልታደርግ ትችላለች ብለህ የምታስባቸውን ነገሮች ዘርዝር።

ምሁራን የመጽሐፈ ኢያሱ ታሪክ እጅግ አከራክሮአቸዋል። በተለይ ደግሞ የታሪኩን በትክክል መመዝገብ የሚጠራጠሩ አሉ። የሚከራከሩባቸውም ዋና ዋና ሐሳቦች ሦስት ናቸው፡

 1. የእስራኤል ሕዝብ ከነዓንን መቼ እንደወረሩ፡- መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያሳየው የእስራኤል ሕዝብ ወደ ከነዓን የገቡት በ1400 ዓ.ዓ. ነበር። ሐሳባቸውን በከርሰ ምድር (አርኪዮሎጂ) ጥናት ላይ የመሠረቱ አዋቂዎች እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ምድር የገቡት ብዙ ቆይተው ወደ 1250 ዓ.ዓ. ገደማ ነው ይላሉ።
 2. የእስራኤል ሕዝብ ከነዓንን ወርረው ምድሪቱን በአጠቃላይ የያዙት ምንኛ ፈጥነው ነው፡- ሌሎች ምሁራን ከነዓንን የመውረርና የመያዝ ነገር ቀስ በቀስ በብዙ ክፍለ-ዘመናት የተፈጸመ ስለሆነ እስራኤላውያንም ምድሪቱን የወረሱት ቀስ በቀስ ነው ይላሉ። ጥቂት ምሁራን ደግሞ እስራኤላውያን 600000 ተዋጊ ሰዎች ቢኖሯቸው ኖሮ ማንም ሊቋቋማቸው እስከማይችል ድረስ በአጭር ጊዜ ምድሪቱን ሊወርሱ ይችሉ ነበር ይላሉ። ሌሎቹ ደግሞ እስራኤላውያን ምድሪቱን ለመውረስ ችግር ገጥሟቸው ነበርና፥ ይህን ያህል ተዋጊ ኃይል አልነበራቸውም፤ በማለት ከነዓንን ለመያዝ በቁጥርና በኃይል እስኪያድጉ ድረስ ብዙ ዓመታት ፈጅቶባቸዋል ይላሉ።

ከነዓንን በጦርነት የመውረርና የመያዝ ተግባር ልክ በመጽሐፈ ኢያሱ እንደተጻፈው በአጭር ጊዜ በ1400 ዓ.ዓ. የተፈጸመ ነው የሚለውን አቋም መያዝ ከሁሉም የተሻለ ነው።

 1. በጣም የተለያዩና እርስ በርስ የሚጋጩ ሆነው የሚታዩ ቢመስሉም፥ መጽሐፈ ኢያሱና መሳፍንት እርስ በርስ የተያያዙት እንዴት ነው? አንዳንድ ምሁራን መጽሐፈ ኢያሱና መሳፍንት እርስ በርስ የሚቃረኑ ናቸው ይላሉ። መጽሐፈ ኢያሱ የሚያስተምረው፡- እስራኤላውያን ከነዓንን እንደወረሩና እንደተቆጣጠሩ ነው፤ መጽሐፈ መሳፍንት ግን ምድሪቱን ለመቆጣጠር እንዳልቻሉ ያሳያል ይላሉ።

ነገር ግን እነዚህን መጻሕፍት በጥልቀት ስናጠና በመካከላቸው ምንም ቅራኔ እንደሌለ እንገነዘባለን። መጽሐፈ ኢያሱ አብዛኛው የከነዓን ምድር እንደተወረረና እንደተያዘ ቢናገርም (ኢያ. 11፡23፤ 21፡43-45)፣ አንዳንድ የምድሪቱ ክፍሎች አለመያዛቸውንም አይሸሽግም፤ (ኢያ. 13፡1-6፤ 23፡4-5፥ 13)። ሁለቱ መጻሕፍት ሁለት የተለያዩ ዓላማዎች አሏቸው። መጽሐፈ ኢያሱ የሚናገረው፣ እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን እንዴት እንደፈጸመና ለእስራኤላውያን በጠላቶቻቸው ላይ እንዴት ድል እንደሰጣቸው ነው። በኢያሱ ዘመን መጨረሻ ምድሪቱ በሙሉ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ሆና ነበር፤ ዋና ዋና የተባሉ ጠላቶችም ተሸንፈው ነበር። ነገር ግን በምድሪቱ የነበሩት ጠላቶቻቸውን ሁሉ ለማስወጣት ሳያቋርጡ መታገልና መዋጋት የእስራኤላውያን ኃላፊነት ነበር። መጽሐፈ መሳፍንት የሚያሳየው ግን እግዚአብሔር እስራኤላውያን በጠላቶቻቸው ሁሉ ላይ ድል የሰጣቸው ቢሆንም፥ መዋጋታቸውን አቁመው ምድሪቱ ላይ ሰፍረው ቁጭ እንዳሉ ነው። ምድሪቱን ሁሉ ለመያዝ ሙከራ ባለማድረጋቸው፥ እግዚአብሔር የድል ክንዱን ከእነርሱ ላይ አነሣ። ስለዚህ በጠላቶቻቸው ላይ ድልን ለማግኘት አልቻሉም። አይሁድ በቀረው ታሪካቸው በሙሉ ባገኙት ድል ለመቀጠል ባለመዋጋታቸውና እግዚአብሔር በመራቸው መሠረት ጠላቶቻቸውን በሙሉ ባለማጥፋታቸው ችግር ውስጥ ገብተው እናያቸዋለን።

የውይይት ጥያቄ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በከፊል ስለ መታዘዝ ከዚህ የምናገኘው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው?

የመጽሐፈ ኢያሱ አስተዋጽኦ 

የሚከተለውን የመጽሐፈ ኢያሱን አስተዋጽኦ አጥና፡-

 1. የእስራኤላውያን ወደ ከነዓን መግባት (ኢያሱ 1-4)
 2. እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን እንደ አሸነፉ (ኢያሱ 5-12)

ሀ. ጠላቶቻቸውን ለማሸነፍ ያደረጉት ዝግጅት (ኢያሱ 5) 

ለ. በከነዓን መካከለኛ ክፍል ባሉ ጠላቶች ላይ የተደረገ ዘመቻ (ኢያሱ 6-8) 

ሐ. በደቡብ ከነዓን በሚገኙ ጠላቶች ላይ የተደረገ ዘመቻ (ኢያሱ 9-10) 

መ. በሰሜን ከነዓን በሚገኙ ጠላቶች ላይ የተደረገ ዘመቻ (ኢያሱ 11) 

ሠ. በእስራኤላውያን የተሸነፉ ጠላቶች ዝርዝር ማጠቃለያ (ኢያሱ 12) 

 1. የምድሪቱ ለልዩ ልዩ የእስራኤል ነገዶች መከፋፈል (ኢያሱ 13-21) 
 2. ኢያሱ ለተለያዩ ነገዶች ያደረገው የስንብት ንግግር (ኢያሱ 22-24)

ኢያሱ የእስራኤል ሕዝብ መሪ 

በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙ ታላላቅ የእምነት ሰዎችን ያህል ስለ ኢያሱ የተነገረ ባይሆንም፥ ኢያሱ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ነበር። ኢያሱ ከኤፍሬም ነገድ ሲሆን የመጀመሪያ ስሙ አውሴ ነበር፤ ትርጉሙም «ድነት (ደኅንነት)» ማለት ነው፤ (ዘኁ. 13፡8)። በኋላ ሙሴ ስሙን ኢያሱ አለው፤ ትርጉሙም «ጌታ ያድናል» ማለት ነው።

ማስታወሻ፡- «ኢየሱስ» የሚለው ስም ኢያሱ (ጆሽዋ) ከሚለው የተወሰደ የግሪክ ስም ነው፤ ስለዚህ ኢየሱስ በአራማይክ ቋንቋ ኢያሱ ተባለ።

ኢያሱ በግብፅ፥ በባርነት ያደገ ሰው ነው። እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ከወጡ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የእስራኤል ጦር አዛዥ ስለሆነ፥ አንዳንድ ሰዎች የአንድ የግብፅ የጦር መሪ ባሪያ የነበረ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ፤ (ዘጸ. 17፡8-13)። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ሲያወጣ የተመለከተ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በእግዚአብሔር ላይ ዓምዖ አያውቅም። በ40 ዓመታቱ የምድረ በዳ ጉዞም የሙሴ ረዳት እንዲሆን ተመርጦ ነበር። ከሙሴ ጋር ወደ ሲና ተራራ ወጥቶ ነበር። ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ካየ ወዲህ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አብሮት የነበረው ኢያሱ ለእግዚአብሔር ያለውን ታላቅ ፍቅር ለማሳየት በእግዚአብሔር ፊት ቆየ፤ (ዘጸ. 33፡11)። ከ12 ነገዶች የተመረጡ ምድሪቱን እንዲሰልሉ በተላኩ ጊዜ፥ ኢያሱ የኤፍሬምን ነገድ ወክሎ ሄደ፤ ከካሌብም ጋር በመሆን የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ማመንና ወደ ምድሪቱ መግባት እንዳለባቸው ተናገረ፤ በውጤቱም እግዚአብሔር እምነቱን አከበረና ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደሚገባ ነገረው። እግዚአብሔር ሙሴን፥ ከእርሱ ቀጥሎ የሚመጣ መሪ አድርጎ ኢያሱን እንዲመርጠው ተናገረ። በኃይልም አስታጠቀው፤ (ዘዳ. 31፡14)። በኢያሱ መሪነት እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ወደ ከነዓን ምድር መራቸው። በከነዓናውያን ላይም ድልን ሰጣቸው። ኢያሱ የእስራኤልን ሕዝብ የመራው ከ25-30 ዓመታት ለሚደርስ ጊዜ ሲሆን፥ በመጨረሻም ሲሞት በኤፍሬም ምድር ተቀበረ። ኢያሱ ከመሞቱ በፊት በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የነበረውን ቃል ኪዳን አደሰ። ለእግዚአብሔር የነበረው ፍቅር ለእስራኤላውያን ባቀረበው ምርጫ ታውቋል፡- «የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን» አላቸው (ኢያ. 24፡15)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደመሆናችን፥ ዛሬ እግዚአብሔር ከእኛ ስለሚፈልገው ነገር የኢያሱ ሕይወት መልካም ምሳሌ የሆነው እንዴት ነው? ለ) ከኢያሱ ሕይወት ውስጥ ከምታየው ባሕርይ በሕይወትህ ልታያቸው የምትፈልጋቸውን ነገሮች ዘርዝር።

የመጽሐፈ ኢያሱ ርእሰ 

መጽሐፉ፥ መጽሐፈ ኢያሱ ወልደነዌ የሚለውን ስም ያገኘው በውስጡ ዋና ገጸ ባሕርይ ሆኖ ከቀረበውና የእስራኤል ሕዝብ መሪ ከሆነው ከኢያሱ ነው። ከሙሴ ሞት በኋላ፥ እግዚአብሔር ኢያሱን መረጠውና የከነዓንን ምድር ድል በመንሣት የእስራኤልን ሕዝብ እንዲመራ በኃይል አስታጠቀው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ታሪካዊ መጻሕፍትን እንዴት እንደምንተረጉማቸው?

ብዙ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪካዊ መጻሕፍት እንዴት እንደሚተረጉሙና በተለይም ከሕይወታቸው ጋር እንዴት እንደሚያዛምዱ ባለማወቅ ይቸገራሉ። ከእኛ ባሕል ጨርሶ ልዩ በሆነ ባሕል ውስጥ ብዙ ያልተለመዱ ስሞች፥ ቦታዎችና ክስተቶች ይኖራሉ። ስለዚህ ብዙ ጊዜ በቀላሉ ከሕይወታችን ጋር ልናዛምዳቸው የምንችላቸውን ታሪኮች የመምረጥና የቀረውን የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ መለኮት ትምህርት ቸል የማለት ዝንባሌ ይታይብናል።

እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ ሰዎችን ሲመራ፥ ከሁሉም በላይ የተጠቀመበት የተለመደው መንገድ (የሥነ ጽሑፍ ዓይነት) ታሪክ ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ራሱን የሚገልጥበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ይህ ከሆነ፥ እነዚህ ታሪኮች ዛሬም ለሕይወታችን ጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው። የታሪክ መጻሕፍትን በምታጠናበትና ከሕይወትህ ጋር ለማዛመድ በምትሞክርበት ጊዜ ልትከተላቸው የሚገቡ መመሪያዎች ከዚህ በታች ቀርበዋል፡-

 1. የቅዱሳት መጻሕፍት (የታሪክን መጻሕፍት ጨምሮ) ዓላማ የእግዚአብሔርን ዓላማዎችና ባሕርያት ለእኛ መግለጥ ነው። በእያንዳንዱ ታሪክ ውስጥ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ስለ እግዚአብሔር ወይም ከሰዎች ጋር ስላለው ግንኙነት አንድ ነገር እንማራለን። የቀድሞ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዴት ደስ እንዳሰኙት በማየት እግዚአብሔርን እንዴት ደስ እንደምናሰኝ እንማራለን። ኃጢአት የቀድሞ ሰዎችን እንዴት እንዳጠፋቸውና እግዚአብሔር ኃጢአተኛን እንዴት እንደቀጣ በመመልከት ኃጢአት ስለሚያመጣው ነገር እንማራለን።
 2. በታሪክ መጻሕፍት ውስጥ በተናጠል ሊታዩ የሚችሉ የተለያዩ በርካታ ታሪኮች ቢኖሩም፥ እነዚህ ታሪኮች በመጽሐፍ ቅዱስ ወይም በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ የአንድ ትልቅ ዓላማ አካል መሆናቸውን መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ፡- 2ኛ ሳሙኤል የተጻፈው የዳዊትን ታሪክ ለመናገር ብቻ አይደለም። ነገር ግን ስለ ዳዊት ታሪክ በምናነብበት ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር፥ ስለ ኃጢአትና እግዚአብሔር፥ ስለ ሕዝቡ ዓላማ በርካታ ታላላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እንድንማር ነው። የታሪክ መጻሕፍትን በምታነብበት ጊዜ፥ እያንዳንዱ ታሪክ በሦስት ደረጃ የሚታዩ እውነቶችን እንደሚያስተምር አስታውስ፤ እነዚህም፡-

ሀ. በጣም አስፈላጊው (በከፍተኛው ደረጃ)፡- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ታሪኮች እያንዳንዳቸው መጽሐፉ እግዚአብሔርንና አጠቃላይ ዕቅዱን የሚገልጥባቸው አካል ናቸው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ጊዜ ልንወስደው የሚገባ የመጀመሪያ እርምጃ፡- ያ የምናጠናው ታሪክ እግዚአብሔር በድነት (ደኅንነት) ውስጥ ባለው ዓላማ፥ የእግዚአብሔርን ባሕርይ በመግለጥ ረገድ ባለን ግንዛቤ፣ እርሱ ከሰዎች ጋር ስላለው ግንኙነት ባለን መረዳት ወዘተ. ላይ የሚጨምረው ነገር ምን እንደሆነ መመልከት ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ መጽሐፈ ኢያሱ 6ን ተመልከት። ይህ ታሪክ በዘመናት ሁሉ ያለውን የእግዚአብሔርን ባሕርይና ዓላማ ለመረዳት እንዴት ይጠቅማል?

ለ. የታሪኩ መካከለኛ ደረጃ የመጽሐፍ ቅዱስን ዋና ዋና አሳቦችን ያመለክታል። ለምሳሌ፡- ይህ መካከለኛ ደረጃ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ እነማን እንደነበሩና (እስራኤላውያን) የእግዚአብሔር ዓላማ ለእነርሱ ምን እንደነበረ ይናገራል። አዲስ ኪዳን ደግሞ ስለ ቤተ ክርስቲያንና እግዚአብሔር ለእርስዋ ስላለው ዓላማ ይናገራል። የአብርሃም ጥሪ፥ ቀይ ባሕርን መሻገር፥ የጰንጠቆስጤ ቀን ወዘተ.፥ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ግንዛቤ እንዲኖረን ደግሞም እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ዓላማና እያደረገላቸው ያለውን ነገር ለመረዳት በጣም ይረዳናል። ስለዚህ በሁለተኛ ደረጃ አንድን ታሪክ በምንተረጉምበት ጊዜ፥ መወሰን ያለብን እነዚህ ታሪኮች ለእነዚህ ዋና ዋና አሳቦች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ምን እንደሆነ ነው፤ (ለምሳሌ፡- ድነት (ደኅንነት)፥ የሰው ልጅ ኃጢአት፥ ኃጢአት በዓለም ላይ ስላመጣው ነገርና የመታዘዝ በረከት ወዘተ. ናቸው)። 

የውይይት ጥያቄ፥ መጽሐፈ መሳፍንትን አንብብ። ይህ ታሪክ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ስላለው ዓላማ ባለን ግንዛቤ ላይ የሚጨምረው ነገር ምንድን ነው?

ሐ. ዝቅተኛው የታሪክ ደረጃ የሚያመለክተው በተለይ በእያንዳንዱ ታሪክ ውስጥ ያለውን ትምህርት ነው፤ ለምሳሌ፡- በሳምሶን ታሪክ ውስጥ የእግዚአብሔርን ሥራ በምንሠራበት ጊዜ ስለ ቅድስና አስፈላጊነት ጸሐፊው ሊያስተምረን የፈለገው ነገር ምን እንደሆነ ወዘተ.።

የውይይት ጥያቄ፥ መጽሐፈ ሩት ምዕ. 2ን አንብብ። ይህ ታሪክ ሊያስተምረን የሚሞክረው ነገር ምንድን ነው?

በታሪኩ ውስጥ በተናጠል የምናገኘውን ትምህርት (መመሪያ) መፈለግ ያለብን ታሪኩ የሚያስተምራቸውን ታላላቅ እውነቶች አስቀድመን ከተረዳን በኋላ መሆን አለበት። ታሪካዊ መጻሕፍትን በተገቢ ሁኔታ ለመተርጎም ከፍተኛውን፥ መካከለኛውንና የመጨረሻውን የታሪክ ደረጃ ትርጉም መረዳታችንን ማረጋገጥ አለብን። 

ታሪካዊ መጻሕፍትና ታሪኮች በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተጨመሩበት የራሳቸው የሆነ ልዩ ዓላማ አላቸው። ዓላማቸው በተናጠል ታሪኮቹን እንድናውቅ ብቻ አይደለም። ይልቁንም እነዚህ ታሪኮች እያንዳንዳቸው ትላልቅ እውነቶችን እንድንረዳ ሊያደርጉን የታሰቡ ናቸው። ስለዚህ ታሪካዊ መጻሕፍትን በምናጠናበት ጊዜ በታሪኮች ውስጥ በተደጋጋሚ የሚመጡትን ዋና ዋና ሐሳቦች ወይም እውነቶች መፈለግ አለብን። ይህ ሲሆን ብቻ ነው የታሪኩን ዓላማ ለመረዳት የምንችለው።

 1. እያንዳንዱ የብሉይ ኪዳን ታሪክ ለአንድ ለተለየ ዓላማ የተመረጠና ስለ እግዚአብሔርና ስለ ብሉይ ኪዳን ታሪክ ባለን መረዳት ላይ ልዩ የሆነ ሚና የሚጫወት ወይም ተጨማሪ ነገርን የሚያክል ነው። የቅዱሳት መጻሕፍት ጸሐፊዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሊያካትቱት የሚችሉዋቸው በርካታ ታሪኮች ቢኖሯቸውም እነዚህን ተጨማሪ ታሪኮችን ዘልለዋቸዋል። ለምን? ምክንያቱ ሌሉቹ ታሪኮች፥ ለአጠቃላዩ የሥነ መለኮት ትምህርት ዓላማ፥ ለመጽሐፉ የሚያበርክቱት አስተዋጽኦ ስላልነበራቸው ነው። ጸሐፊዎቹ ሁሉ እያንዳንዱን ታሪክ በከፍተኛ ጥንቃቄ መረጡ፤ ስለዚህ በእያንዳንዱ ታሪክ ውስጥ ያለው ይህ ልዩ ዓላማ ምን እንደሆነ ለመረዳት መሞከር አለብን። አንዳንዶቹ ታሪኮች ለመረዳት አስቸጋሪ ቢሆኑም እንኳ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱበትን ምክንያት ከተረዳን እግዚአብሔርን የበለጠ እንረዳዋለን።
 2. የታሪክ መጻሕፍት ዓላማ እንደ ሰምና ወርቅ ያሉ የተደበቁ እውነተችን ለማስተማር አይደለም። ነገር ግን መንፈሳዊ እውነተችን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ለመግለጥ ነው። ስለዚህ መፈለግ ያለብን የተደበቁ ምሥጢሮችን ሳይሆን፥ በታሪኩ ውስጥ የሚገኙ ግልጥ የሆኑ ጠቅላላ መንፈሳዊ የሥነ – ምግባር ሕግጋትን ወይም እምነቶችን ነው። እግዚአብሔር እነዚህን ጠቅላላ የሥነ ምግባር ሕግጋት ወይም እምነቶች በቀጥታ ከመስጠት ይልቅ በግለሰቦች ተግባራዊ ሕይወት ውስጥ መግለጥ እንደሚሻል ያውቅ ነበር። ይህ መንገድ እነዚህ መንፈሳዊ የሥነ – ምግባር ሕግጋት ወይም እምነቶች አኗኗራችንን እንዴት እንደሚለውጡት ለማወቅ የሚረዳ ነው።
 3. ታሪኮችን በምንተረጉምበት ጊዜ ታሪኩ የሚያስተምረን በአዎንታዊ ወይም በአሉታዊ ምሳሌነት እንደሆነ አስቀድመን መወሰን አለብን። አንዳንዶቹ ታሪኮች በእምነት እንዴት መኖር እንደሚቻል ምሳሌዎችን ይሰጣሉ፤ ስለዚህ በሕይወታችን ልናካትተው የሚገባ አዎንታዊ ምሳሌ ነው። ሌሎች ምሳሌዎች ለምሳሌ በመጽሐፈ መሳፍንት 19 ስለ አንድ ሌዋዊና ቁባቱ የተጻፈው ነገር የሚያስተምረን በአሉታዊ ምሳሌነቱ ነው። በታሪኩ ውስጥ እግዚአብሔር የሰዎቹን ተግባር በምንም ዓይነት እየደገፈ አይደለም። ይልቁንም እግዚአብሔር የተፈጸመውን ተግባር በግልጥ ይናገራል። የተፈጸመውን ታሪክ ምሳሌነት መከተል እንዳለብንና እንደሌለብን የምንወስነው ከተግባሩ ውጤት ነው። 
 4. በታሪክ መጻሕፍት ውስጥ የምናገኛቸው ታሪኮች የቀረቡት በአጭሩ ነው። ስለ ተፈጸሙት ድርጊቶች የሚኖረንን ጥያቄ ሁሉ ለመመለስ የቀረቡ አይደሉም፤ ጠቃሚ ትምህርቶችን ለማቅረብ ብቻ የተጻፉ ናቸው። በታሪኩ ውስጥ በግልጥ ስላልተነገሩ ነገሮች አትጨነቅ (ለምሳሌ፡- ቃየል ሚስት ያገኘው ከየት ነው?) ይልቁንም፥ አስፈላጊ የሆነው ነገር በታሪኩ ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና ትምህርቶች መረዳትና ከሕይወት ጋር ማዛመድ ነው።
 5. አብዛኛዎቹ የብሉይ ኪዳን ታሪኮች ለእኛ ያልተለመዱ ባሕላዊ ነገሮችን ያካተቱ ስለሆኑ ታሪኩን ለመረዳት በምናደርገው ሙከራ፥ ለእኛ ያልተለመዱ ባሕላዊ ነገሮችን መረዳታችንን ማረጋገጡ አስፈላጊ ነው (ለምሳሌ፡- ሩት ቦኤዝን «ልብስህን በባሪያህ ላይ ዘርጋ» [ሩት 3፡9] ስትለው ምን ማለቷ እንደ ነበር …)። በተጨማሪ ከራሳችን ባሕል ጋር ተመሳሳይ የሆነ፥ በዕብራውያን ባሕል ግን የተለየ ትርጉም ያለውን ነገር መረዳታችንን ማረጋገጥ አለብን፤ (ለምሳሌ፡- ለአይሁድ የእረኝነት ሥራ የተከበረ ነው፤ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ግን ያልተማሩ ሰዎች ወይም የልጆች ኃላፊነት እንደሆነ ስለሚቆጠር ይህን ያህል የተከበረ አይደለም)።

ታሪካዊ መጻሕፍትን በምታነብበትም ሆነ በምትተረጉምበት፥ ደግሞም ከመጻሕፍቱ በምታስተምርበት ጊዜ እነዚህን መመሪያዎች ተጠቀም፡- እግዚአብሔር እነዚህን የታሪክ መጻሕፍት ሲሰጥ ምን ሊያስተምረን እንደሆነ በመጀመሪያ ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን አስታውስ። ይህ ሲሆን ብቻ ትርጉማችን የእግዚአብሔር ቃል መሆኑንና ስናስተምረውም የእግዚአብሔር ሥልጣን እንዳለው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። 

የውይይት ጥያቄ፤ ሀ) የእግዚአብሔር ቃል በተገቢው መንገድ መተርጎም የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ለ) አንድን ታሪክ በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም በርካታ ስሕተቶችና ሐሰተኛ ትምህርቶች ሊጀምሩ የሚችሉት እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የታሪካዊ መጻሕፍት መግቢያ

በዚህ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት መክፈቻ ጥናታችን እስካሁን ድረስ የመጀመሪያውን ክፍል ፔንታቱክን ተመልክተናል። ፔንታቱክ፡- ዘፍጥረት፥ ዘጸአት፥ ዘሌዋውያን ዘኁልቁና ዘዳግም የሚባሉ አምስት መጻሕፍትን ይዞአል። ከታሪካቸው አንጻር፥ እነዚህ መጻሕፍት የሚናገሩት ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት እስከተዘጋጁበት ጊዜ ድረስ ያለውን ሁኔታ ነው። የፍጥረት መጀመሪያ መቼ እንደነበር ምንም የምናውቀው ነገር ባይኖርም፥ የፔንታቱክ ታሪክ ግን በ1400 ዓ.ዓ. ገደማ ያበቃል።

አይሁድ እነዚህን የብሉይ ኪዳን የመጀመሪያ አምስት መጻሕፍት ልዩና በታሪካቸው ውስጥ ለተሰጡት የእግዚአብሔር መገለጦች ሁሉ መሠረታዊ እንደሆኑ ያምናሉ። ስለዚህ ከሌሎቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ አብልጠው፥ እነዚህን አምስት መጻሕፍት ያከብራሉ።

የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁለተኛ ዋና ክፍል «ታሪካዊ መጻሕፍት» በመባል የሚታወቁ ሲሆን፥ እነዚህም ከመጽሐፈ ኢያሱ ጀምሮ እስከ መጽሐፈ አስቴር ያሉት 12 መጻሕፍት ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- አሥራ ሁለቱን የታሪክ መጻሕፍት በዝርዝር አቅርበ።

እነዚህ የታሪክ መጻሕፍት ከሙሴ ሞት ጀምሮ እስከ አስቴር ድረስ ያለውን የእስራኤል ታሪክ የሚናገሩ ናቸው። ስለዚህ ከ1400 ዓ.ዓ. – 430 ዓ.ዓ. ያለውን የ1000 ዓመታት ጊዜ ያካትታሉ። እነዚህ 12 መጻሕፍት የቀሩትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ታሪክ በሙሉ የሚያካትቱ ናቸው። የቀሩት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ማለትም የግጥምና የቅኔ እንዲሁም የትንቢት መጻሕፍት በእነዚህ 12 መጻሕፍት የታሪክ ዘመን ውስጥ የሚጠቃለሉ ናቸው። የተጻፉትም በእነዚህ ታሪካዊ ወቅቶች ነው፡፡

አይሁድ የታሪክ መጻሕፍትን በሁለት የተለያዩ ዓበይት ክፍሎች ይከፍሉአቸዋል። ከመጽሐፈ ኢያሱ እስከ 2ኛ ነገሥት ያሉ መጻሕፍትን «የቀድሞ ነቢያት» መጻሕፍት ብለው ይጠሯቸው ነበር። ይህም የሚያመለክተው አይሁድ እነዚህን መጻሕፍት የሚያዩአቸው እንደ ታሪክ መጻሕፍት ብቻ ሳይሆን፥ የቀድሞዎቹ ነቢያት የሠሩበት ጊዜም እንደሆነ ጭምር ነው። ከመጽሐፈ ሩት ጀምሮ እስከ መጽሐፈ አስቴር ድረስ ያሉትን መጻሕፍት ደግሞ «ጽሑፎች» ብለው የሚጠሩአቸው የአንድ ትልቅ ክፍል አካል አድርገው በመቁጠር ነው።

እነዚህ አሥራ ሁለት የታሪክ መጻሕፍት በሊቃውንት መካከል ከፍተኛ የሆኑ አወዛጋቢና አከራካሪ ነገሮችን ፈጥረዋል። አንዳንድ ምሁራን እነዚህ መጻሕፍት በእስራኤል ታሪክ ውስጥ እጅግ ዘግይተው የተጻፉ ናቸው ብለው ያስባሉ። ከመጽሐፈ ኢያሱ እስከ 2ኛ ነገሥት ያሉት መጻሕፍት የተጻፉት እንዲያውም ከኦሪት ዘዳግም ጋር በአንድነት ስለሆነ፥ «የዘዳግም ታሪክ» በመባል ይታወቃሉ ይላሉ። ከመጽሐፈ ኢያሱ እስከ 2ኛ ነገሥት ያሉት መጻሕፍት ዋና ዓላማ በኦሪት ዘዳግም እስራኤላውያን ባለማመናቸው ምክንያት ፍርድ እንደሚጠብቃቸው የተነገረው ትንቢት በአይሁድ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ፍጻሜ ግግኘቱን ለማሳየት ነው ብለው ያምናሉ።

የታሪክ መጻሕፍት በሙሉ የተጻፉት በአንድ ጸሐፊ መሆኑን መገመት በጣም አጠራጣሪ ቢሆንም፥ በጥልቀት ስንመለከታቸው ግን የታሪክ መጻሕፍቱ የእስራኤልን ታሪክ የተመለከቱት እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ በሲና ተራራ ከሰጠው ቃል ኪዳን አንጻር ለመሆኑ ግልጥ ይሆናል። የታሪክ መጻሕፍትን የጻፉት የተለያዩ ጸሐፊዎች፥ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ እግዚአብሔር በኦሪት ዘዳግም የሰጠውን ተስፋና ቃል ኪዳን እንዴት እንደፈጸመ የሚናገር ታሪክ መሆኑን ተገንዝበው ነበር። የእግዚአብሔር ሕዝብ ለቃል ኪዳኑ በሚታዘዙበት ጊዜ እግዚአብሔር ያከብራቸውና ይባርካቸው እንደ ነበር ያሳያሉ፤ ነገር ግን እስራኤላውያን በታሪካቸው ሁሉ ያጋጠሟቸው ችግሮች ቃል ኪዳኑን ለመታዘዝ ፈቃደኞች ያለመሆናቸው ውጤቶች እንደነበሩም ያመለክታሉ። የታሪክ መጻሕፍት ጸሐፊዎች ሊያሳዩን የፈለጉት ነገር እስራኤላውያን በርካታ ችግሮች እንደገጠሟቸውና በመጨረሻም የጠፉትና ወደ ምርኮ የተወሰዱት ለምን እንደሆነ ነው። ይህ የሆነው እግዚአብሔር ሕዝቡን መጠበቅ አቅቶት ሳይሆን፥ የኃጢአት ውጤት መሆኑን ለመግለጽ በመፈለጋቸው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ጊዜ፥ የበረከት እጦት በኃጢአት ላይ የተሰጠ ፍርድ ውጤት መሆኑን መረዳት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) አማኞች በእግዚአብሔር ፊት የተቀደሰ ሕይወት ለመኖር እንዲጠነቀቁ ለማድረግ ይህ እንዴት ይረዳል?

የታሪካዊ መጻሕፍት ጸሐፊዎች 

በታሪክ መጻሕፍት ሁሉ የሚታዩ የጋራ የሆኑ ዋና ሐሳቦች ቢኖሩም እንኳ መጻሕፍቱ በተለያዩ ሰዎች ተጽፈው በኋላ የተቀናበሩ ሳይሆኑ አይቀሩም። መጽሐፈ ኢያሱ፥ መሳፍንትና ሩት የተጻፉት የእስራኤል መንግሥት በተባበረ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። 1ኛ ና 2ኛ ሳሙኤል የተጻፉት ደግሞ በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት፥ ወይም የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ከተከፈለ በኋላ ሳይሆን አይቀርም። ከ1ኛ ነገሥት እስከ መጽሐፈ ዕዝራ ድረስ ያሉ መጻሕፍት ደግሞ አይሁድ ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ የተጻፉ ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት በተጻፉ ጊዜ ጸሐፊዎቹ ያኔ በነበሩት ሌሎች ታሪካዊ መጻሕፍት ተጠቅመው እንደጻፉ ይታመናል። እነዚያ መጻሕፍት ግን የእግዚአብሔር ቃል ስላልሆኑ፥ አንዳቸውም እስካሁን ድረስ አልቆዩም።

የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ዐበይት ክፍሎች 

የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ በሚከተሉት ዋና ዋና ጊዜያት ሊከፈል ይችላል፡-

 1. የእስራኤል ሕዝብ መመሥረት (ዘፍጥረት 12 – ዘዳግም መጨረሻ)፡- ይህ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ የሚናገረው፥ ጅማሬያቸው እንዴት እንደሆነና የተስፋይቱን ምድር ወርረው ለመውረስ እስከተዘጋጁበት ጊዜ ድረስ ታላቅ ሕዝብ ወደ መሆን እንዳደጉ ነው። ዘመኑም ከ2100 ዓ.ዓ. እስከ 1400 ዓ.ዓ. ያለውን ጊዜ የሚያካትት ሲሆን፥ የእነዚህን ዓመታት ታሪክ በዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ስድስት ምዕራፎች ውስጥ አጥንተነዋል።
 2. የተስፋይቱን ምድር መውረርና መውረስ (ኢያሱ)፡- የዚህ ዘመን ታሪክ የሚያሳየን የእስራኤል ሕዝብ የተስፋይቱን ምድር እንዴት እንደወረሩና ድል በማድረግ እንደወረሱ ነው፤ ዘመኑም ከ1400-1375 ዓ.ዓ. ነው።
 3. ዘመነ መሳፍንት (ከመጽሐፈ መሳፍንት – 1ኛ ሳሙኤል 8)፡- ይህ ዘመን ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው በተደጋጋሚ በተለያዩ ጠላቶች ስለ መሽነፋቸው በሚተርክ ዘገባ የተሞላ ከመሆኑ በስተቀር፥ ስለ ዘመኑ እምብዛም የምናውቀው ነገር የለም። መሳፍንት፥ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ከጠላቶቻቸው ያርፉ ዘንድ የሚያስነሣቸው ጊዚያዊ መሪዎች ነበሩ። ዘመነ መሳፍንት ከ1375 – 1050 ዓ.ዓ. ማለትም ሳኦል ንጉሥ እስከሆነበት ድረስ ያለው ጊዜ ነው። 
 4. የተባበረው የእስራኤል መንግሥት ዘመን (1ኛ ሳሙኤል 9 – 1ኛ ነገሥት 11፣ 1ኛ ዜና – 2ኛ ዜና 9)፡- ይህ ዘመን የእስራኤል ሕዝብ እንደ ታላቅ ሕዝብ የነበሩበት ዘመን ነው። ይህ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ሦስት የእስራኤል ነገሥታት- ሳኦል፥ ዳዊትና፥ ሰሎሞን እያንዳንዳቸው 40 ዓመታት እስራኤልን የገዙበት ዘመን ነበር። በዚህ ክፍለ ዘመን ዋናው ትኩረት የነበረው በዳዊት ላይ ነው። በሙሉ ልቡ እግዚአብሔርን በመውደድና በእስራኤል ጠላቶች ላይ ድል በማድረግ ብዙ ነገሥታትን ለማንበርከክ እግዚአብሔር የተጠቀመበት ሰው፥ እንደ ዳዊት ያለ ታላቅ ንጉሥ እስራኤላውያን አይተው አያውቁም። ይህ የተባበረው የእስራኤል መንግሥት ዘመን ከ1050 – 930 ዓ.ዓ. ማለትም ከሰሎሞን ሞት በኋላ ሕዝቡ እስከተከፈለበት ድረስ የሚዘልቅ ነበር።
 5. የተከፋፈለው መንግሥት ዘመን (1ኛ ነገሥት 12 – 2ኛ ነገሥት 25፤ 2ኛ ዜና 10-36)፡- ከሰሎሞን ሞት በኋላ የእስራኤል ሕዝብ በሁለት መንግሥታት ተከፈለ። የሰሜኑ መንግሥት እስራኤል ተብሎ የተጠራ ሲሆን፥ የቆየውም ከ930 – 722 ዓ.ዓ ማለትም መንግሥቱ በአሦራውያን እጅ ወድቆ ሕዝቡ ወደ ምርኮ እስከተወሰዱበት ድረስ ነበር። የደቡቡ መንግሥት ደግሞ ይሁዳ ተብሎ የተጠራ ሲሆን፥ ከ930 – 586 ዓ.ዓ. ማለትም መንግሥቱ ፈርሶ በባቢሎናውያን ወደ ምርኮ እስከተወሰደበት ድረስ ቆይቷል።
 6. የምርኮ ዘመን (ሕዝቅኤልና ዳንኤል)፡- መጽሐፍ ቅዱስ ስለ 70ው ዓመት የምርኮ ዘመን የሚናገረው በጣም ጥቂት ነገር ነው፤ (586-536 ዓ.ዓ.)። እንደ እውነቱ ከሆነ፥ የይሁዳ ሕዝብ በምርኮ የቆየው ለ50 ዓመታት ብቻ ነው። ሰባው ዓመት የሚያመለክተው የመጀመሪያዎቹ የይሁዳ ሕዝብ ወደ ምርኮ ከሄዱበት ከ606 – 539 ዓ.ዓ. ማለት አይሁድ ወደ ከነዓን እስከተመለሱበት ድረስ ያለውን ጊዜ፤ ወይም ቤተ መቅደሱ ከፈረሰበት ከ 586 ዓ.ዓ ጀምሮ እንደገና እስከታደሰበት እስከ 516 ዓ.ዓ ድረስ ነው። 
 7. የይሁዳ መንግሥት ሕዝብ ከምርኮ መመለስ (ዕዝራና አስቴር)፡- በ536 ዓ.ዓ. የፋርስ መንግሥት የእስራኤልን ሕዝብ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ፈቀደ። የይሁዳ ሕዝብ በዘሩባቤል፥ በዕዝራና በነህምያ መሪነት እንደገና የራሳቸውን አስተዳደር መሠረቱ እንጂ የነበራቸውን ሉዓላዊነት ግን መልሰው አላገኙትም። በፋርስ ታላቅ መንግሥት ውስጥ እንደ አንድ ጠቅላይ ግዛት ነበሩ። ይህ ዘመን ከ536-400 ዓ.ዓ. ድረስ ቆይቷል። ከ400 ዓ.ዓ. በኋላ ያለውን ታሪክ ከብሉይ ኪዳን ውስጥ አናገኘውም። የብሉይ ኪዳን ታሪክ በሙሉ የሚናገረው እስከዚህ ዘመን ድረስ ስላለው ሁኔታ ብቻ ነው። በአዲስ ኪዳን መጀመሪያ ላይ የምናገኘው መጥምቁ ዮሐንስ እስኪመጣ ድረስ የእግዚአብሔርን ቃል የተናገረ የመጨረሻው ነቢይ ሚልክያስ

ነበር።

 1. 400 የጸጥታ ዓመታት፡- ከ400 ዓ.ዓ. ጀምሮ ክርስቶስ እስከመጣበት እስከ 4 ዓ.ዓ. ድረስ ስለነበረው ዘመን የሚናገር የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የለም። አንዳንዶቹ የአዋልድ መጻሕፍት በዚህ ጊዜ ስለተፈጸሙት አንዳንድ ጉዳዮች ይናገራሉ። እነዚህ ዓመታት በመለኮታዊ መንገድ፥ በእግዚአብሔር መንፈስ በመመራት ቃሉን ያስተላለፈ አንድም ነቢይ ስለ ሌለ፥ 400 የጸጥታ ዓመታት በመባል ይታወቃሉ።

መጽሐፍ ቅዱሳዊ የታሪክ አመለካከት

ታሪክን ስለምንረዳበት መንገድ የተለያዩ ባሕሎችና የተለያዩ አመለካከቶች አሉ። ታሪክን የምንረዳበት መንገድ ዛሬ በዘመናችንና በዙሪያችን የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ለመረዳትና ለመተርጎም ወሳኝ ነው። ቀጥሉ ሰዎች ታሪክን የሚረዱባቸውን ሦስት ዋና ዋና መንገዶች እንመለከታለን፡-

 1. ጣዖት አምላኪዎች ታሪክን የሚመለከቱበት መንገድ፡- በጥንት ዘመንም ሆነ ዛሬ በአብዛኛው የዓለም ክፍል (አፍሪካ፥ እስያ፥ ደቡብ አሜሪካ) ሰዎች ታሪክን የሚረዱት ሰው ሊቆጣጠረው የማይችል፥ የማያቋርጥ ክስተት ሂደት እንደሆነ አድርገው ነው። ይህ አመለካከት በዓለም ላይ ለሚፈጸሙ ድርጊቶች ምክንያቶቹ ልንታመንባቸው የማንችል ጣዖታት ናቸው የሚል ዝንባሌ አለው። አንድ ጊዜ በረከትን በሌላ ጊዜ ደግሞ ጥፋትን ያመጣሉ። ይህንን የሚያደርጉበት ግልጽ የሆነ መንገድ የለም፡፡ ይልቁንም እኛ ሰዎች እንደመሆናችን በእነርሱ ምሕረት ሥር እንገኛለን። ስለዚህ ለጉዳዩ ከመገዛትና እንደ ሙስሊሞች «አላህ ከፈቀደ» ከማለት በስተቀር ምንም ምርጫ የለንም። ልናደርግ የምንችለው ብቸኛው ነገር፥ አማልክትን ደስ የሚያሰኛቸውን መልካም ተግባራት ለመፈጸም መሞከር ነው። እኛ ለእነርሱ መልካም ከሆንን እነርሱም መልካም ሊሆኑልን ይችላሉ ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። በዚህ አመለካከት ታሪክን መጻፍ፥ ሰዎች ስለ ስኬታማነታቸው እንዲመኩ ከማድረግ ሌላ የሚፈይደው ነገር በጣም ትንሽ ነው። ታሪክ በሥልጣን ላይ ላሉ ሰዎች መግዛት መብታቸው መሆኑን የማረጋገጥ መሣሪያ ይሆናል ወዘተ።
 2. ዓለማዊው የምዕራባውያን አመለካከት፡- ዛሬ በትምህርት ቤት የምንማረው ታሪክ የተመሠረተው በሌላ ዓይነት የታሪክ አመለካከት ላይ ነው። ይህ አመለካከት በተለይ በአውሮጳና በሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ያለው ሲሆን፥ ታሪክ በምድር ላይ የሚፈጸሙ ክስተቶች ዘገባ ነው ይላል። እንደዚህ አመለካከት፥ ታሪክ የሚወሰነው በእግዚአብሔር ሳይሆን በሰው ብቻ ነው። ታሪክን የምናጠናው፥ ሰው የሠራውን ስሕተት በማየትና ባለፈው ጊዜ ከተፈጸሙ ድርጊቶች ልምድ በመውሰድ በምድር ላይ ለራሳችን የተሻለ ሕይወት ለመኖር ነው። ይህ የታሪክ አመለካከት፥ ለተአምራትም ሆነ ለእግዚአብሔር ቦታ የለውም። በምድር ላይ የሚፈጸሙ ነገሮች፥ ጥፋቶችም ሆኑ ጦርነቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት ለመፈጸማቸው አንዳችም መረጃ የለም፤ በተፈጥሮ የሚሆኑ ናቸው ይላሉ። በዚህ የታሪክ አመለካከት፥ ምን እንደተፈጸመ መመዝገብና ማስቀመጥ ከሁሉ የበለጠ አስፈላጊ ነገር ነው። ከዚያም ታሪክ አዋቂዎች ክስተቱ የተፈጸመው በምን ምክንያት እንደሆነ ይመረምራሉ። 
 3. መጽሐፍ ቅዱስ ታሪክን የሚመለከትበት መንገድ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እግዚአብሔር በሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚሠራው ሥራ ውጤት ነው በማለት ያስተምረናል። በምድር ላይ የሚፈጸሙ ነገሮች ሁሉ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር ያሉ ናቸው። ከመጀመሪያው አመለካከት በተቃራኒ፥ እግዚአብሔር ግልጽ የሆነ ዕቅድ እንዳለውና በምድር ላይ የሚፈጸሙ ነገሮች ሁሉ የዚያ ዕቅድ አካል ናቸው በማለት ያስተምረናል። የእግዚአብሔር ዕቅድ መጀመሪያ የነበረው (የፍጥረታት መፈጠር ታሪክ) እና ወደ መጨረሻውም (የዘላለማዊ መንግሥት) እያዘገመ ያለው ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በምድር ላይ የሚፈጸሙ ነገሮች በሙሉ በእግዚአብሒር ቁጥጥር ሥር እንደሆነ ያምኑ ነበር። ስለዚህ ታሪክን በሚጽፉበት ጊዜ፥ ያተኮሩት በክስተቶች ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ ነበር። የታሪክ መጻሕፍት ዓላማ እግዚአብሔር የገባውን ቃል ኪዳን ለመፈጸም በታሪክ ውስጥ እንዴት እንደሚሠራ ማሳየት ነው። ጸሐፊዎቹ ጽሑፎቻቸውን የሚያነቡ ሰዎች እግዚአብሔር የፈጸመውን ድርጊት ለምን በዚያ መልክ እንደፈጸመውና በሕዝብ ላይ ለምን እንደፈረደ እንዲረዱላቸው ይፈልጉ ነበር። እግዚአብሔር ታሪክን ወደ አንድ ትልቅ ዓላማ በመምራት ላይ እንደሆነ ግልጽ ቢሆንም፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ ተግባር እርሱ የሚሰጣቸውን ምላሽ የሚወስን እንደነበር አስተምረዋል። ድርቅ፥ የመሬት መንቀጥቀጥ፥ ሕዝብና መሪዎች በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር መሆናቸው በግልጽ ሰፍሮአል፡፡ እግዚአብሔር ታሪክን እየመራና እየሠራ የታሪክ የመጨረሻ ማጠቃለያ ወደሆነው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መመሥረት እያቃረበው ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ ሦስት የታሪክ አመለካከቶች ተግባራዊ ሆነው ያየህባቸውን ምሳሌዎች ጥቀስ። ለ) እነዚህ የታሪክ አመለካከቶች እያንዳንዳቸው ዛሬ በዓለም ላይ ባለን አመለካከት ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ግለጽ። ሐ) በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በምናልፍበት ጊዜ፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊው የታሪክ አመለካከት የሚያበረታታን እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)