ከመጽሐፈ ኢዮብ የምናገኛቸው ልዩ ትምህርቶች

1. የሰይጣን ሥራ፡- ቀደም ሲል በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ ሰይጣን በእባብ ተመስሉ ሔዋንን እንዳታለላትና ወደ ኃጢአት እንደመራት የሚያሳየውን የሰይጣንን ሥራ ተመልክተናል፤ ዳሩ ግን በዚያ ታሪክ ውስጥ አይሁድ ከምርኮ እስኪመለሱ ድረስ ስለ ሰይጣን የተገለጠው ነገር እጅግ አነስተኛ ነበር። በዘካርያስ መጽሐፍ ውስጥ አይሁድ ስለ ሰይጣን አካላዊ ህልውና የነበራቸው እውቀት እያደገ መምጣቱን መመልከት እንጀምራለን። በኢሳይያስ 14ና በሕዝቅኤል 28 ስለ አንድ ታላቅ የክፋት ኃይል የሚናገር ፍንጭ እንመለከታለን፤ ዳሩ ግን እነዚህ ጥቅሶች በግልጽ ወደ ሰይጣን አያመለክቱም። በመጽሐፈ ኢዮብ የዚህ የክፋት ኃይል ማንነት ተገልጾልናል። ከዚያም በኋላ በከፍተኛ ደረጃ በሚታወቅበት «ሰይጣን» በተባለ ስሙ ተጠርቶ እናገኛለን። ሰይጣን ማለት «ባላጋራ» ማለት ነው። ሰይጣን የእግዚአብሔርና የልጆቹ ባላጋራ ነው። ሰይጣን ከእግዚአብሔርና ከዕቅዱ በተቃራኒ የሚሠራ ነው፥ በተለይ ቅዱሳንን በእግዚአብሔር ፊት የሚከስ ሆኖ ተገልጾአል። 

2. የእግዚአብሔር ልጆች ጠበቃ አላቸው (ኢዮብ 5፡1፤ 9፡33፤ 16፡19-21)። ኢዮብ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ባያውቅም እንኳ እግዚአብሔርን ግን ያውቅ ነበር። ስለ እግዚአብሔር የነበረው እውቀት እግዚአብሔር ጠበቃው እንደሚሆንለት ዋስትና ሰጠው። ኢዮብ በሰማይ ስላለ የፍርድ ቤት ችሎት ያስብ ነበር። በዘላለማዊው ፈራጅ ፊት ጠበቃ ሆኖ ከማንኛውም ጥፋት ነፃ በማድረግ ጻድቅ መሆኑን እንደሚያረጋግጥለት እርግጠኛ ነበር። በአዲስ ኪዳን እውነተኛው ጠበቃ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ግልጽ ሆኖአል (1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡5 ተመልከት)። ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ እንደመሆኑና የኃጢአታችንን ዋጋ በመስቀል ላይ በመሞት ሙሉ በሙሉ በመክፈሉ፥ ዘላለማዊ ዳኛ በሆነው በእግዚአብሔር ፊት ለመቆምና እኛን ለማጽደቅ የሚችል ኢየሱስ ብቻ ነው። እግዚአብሔር «በደለኞች አይደላችሁም» የሚለውን ቃል ስለ እኛ መናገሩ የሚረጋገጥልን ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሠራው ሥራ ብቻ ሳይሆን፥ ጠበቃችን እንደ መሆኑ መጠን ያለማቋረጥ በሚሠራው ሥራ ጭምር ነው። ኢዮብ ስለ ጠበቃ ያቀረበው ጩኸት በኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ተፈጽሟል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ኢየሱስ ክርስቶስ ጠበቃችን መሆኑን መገንዘባችን ማበረታቻ የሚሆነን እንዴት ነው? ለ) በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በምናልፍበት ጊዜ ኢዮብ በመከራ ውስጥ ሲያልፍ ካሳየው ዝንባሌ የምንማራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ኢዮብ ከፍተኛ ጽናትን አሳይቷል። እንደ እውነቱ ኃጢአት እንደሠራና በኃጢአቱ ምክንያትም እንደተቀጣ ለወዳጆቹ ቢናገር እጅግ ይቀለው ነበር፤ ነገር ግን ኢዮብ ንጹሕ እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ከወዳጆቹ ንትርክ ለመዳን ብሎ ለመዋሸት ፈቃደኛ አልሆነም። ዛሬም ቢሆን ራሳቸውን በሚገባ የሚያውቁ፡ በማንኛውም ሰው ፊት በማስመሰል የማይቆሙና እውነትን በግልጽ የሚናገሩ ወንዶችና ሴቶች ያስፈልጉናል።  

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመጽሐፈ ኢዮብ ዓላማ

በመከራና በክፋት መካከል ያለው ግንኙነት

መጽሐፈ ኢዮብ የተጻፈው፥ በዚህ ዓለም ላይ ያለውን መከራና ሥቃይ፥ በተለይም ደግሞ ቅዱሳን ወንዶችና ሴቶች ለምን መከራ እንደሚቀበሉ ለማስረዳት ነው። የምንኖረው መከራና ሥቃይ በሞላበት ዓለም ውስጥ ነው። መከራ የሚመጣው ከየት ነው? እግዚአብሔር ሉዓላዊና ጻድቅ ከሆነ፥ በምድር ላይ መከራና ሥቃይ የሚኖረው ለምድን ነው?

የውይይት ጥያቄ፥ ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር በምድር ላይ መከራ እንዲኖር ለምን እንደሚፈቅድ አንድ ሰው ቢጠይቅህ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር እንዴት ትመልስለታለህ?

የሰው ልጅ ባለፈበት የዓለም ታሪክ ውስጥ ሁሉ ከመከራና ከክፋት ጋር ሲታገል ኖሯል። መከራና ክፋት በብዙ ልዩ ልዩ ዓይነት መንገዶች ይመጣሉ። መከራና ሥቃይን የሚያመጡ እንደ ጐርፍና ድርቅ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች አሉ፤ በተጨማሪ በሽታም አለ። እንደ አስገድዶ ሴትን መድፈር፥ ነፍስ መግደል፥ ጦርነት፥ ወዘተ ያሉ ሰው-ሠራሽ መከራዎችና ሥቃዮችም አሉ። እነዚህ ነገሮች ሁሉ የሚመነጩት ከየት ነው? እግዚአብሔር እነዚህ ነገሮች ይቀጥሉ ዘንድ ለምን ፈቀደ? የተለያዩ ሰዎችና የሃይማኖት ክፍሎች ስለ መከራ ያላቸው አስተሳሰብ ወይም የሚሰጡት መልስ የተለያየ ነው።

1. አንዳንዶች፡- እግዚአብሔር መከራን ለመቆጣጠር ብቁ አይደለም፤ ይልቁንም የእግዚአብሔርን ያህል ኃይል ያለው፥ እንደ ዲያብሎስ ያለ የክፋት ኃይል አለ፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን በማሸነፍ ክፋትን ወደ ምድር ያመጣል ይላሉ። አብዛኛዎቹ የምሥራቅ ሃይማኖቶች (የሂንዱ፤ የቡድሀ ሃይማኖት) አስተሳሰብ የዚህ ዓይነት ነው። 

2. ሌሎች ደግሞ፡- እግዚአብሔር በእርግጥ ጻድቅ አምላክ አይደለም፤ ስለዚህ ያለ አንዳች ምክንያት ክፋትን ወደ ሕይወታችን ያመጣል ይላሉ። እግዚአብሔር በጣም ተለዋዋጭ አምላክ ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግ ይሆናል፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ያላንዳች ምክንያት ክፉ ነገርን ያመጣል። እኛ በምንፈጽመው ተግባርና እግዚአብሔር ወደ ሕይወታችን በሚያመጣው ነገር መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት የለም። የብዙ ሙስሊሞች አስተሳሰብ ይህ ነው። እግዚአብሔር ኃይል እንዳለው የሚያውቁት እነዚህ ሙስሊሞች መከራና ክፋትን የሚያመጣው እግዚአብሔር ራሱ እንደሆነና በዚህም ምክንያት ፍትሐዊ እንዳልሆነ ለመቀበል ተገድደዋል።

3. አንዳንድ ሰዎች ብዙ ዓይነት አማልክት ወይም መናፍስት እንዳሉ ይናገራሉ። ከነዚህም አንዳንዶቹ መልካም፥ ሌሎቹ ደግሞ ክፉዎች ናቸው። በእነዚህ ሁለት ዓይነት አማልክት መካከል የማያቋርጥ ትግል ይካሄዳል። ሰዎቹ ክፉ የሆኑት አማልክት እንዳይጐዱአቸው የእህልና የመጠጥ መሥዋዕት በማቅረብ ደስ ሊያሰኙአቸው ይገባል። ሰዎች ከአማልክት ችሮታን ለመግዛት ይፈልጋሉ። በመላው ዓለም ላይ የነገድ ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች የተለመደ አመለካከት ይህ ነው። 

4. አንዳንድ ሰዎች፡- እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረ በኋላ እንዲሁ እንደተዋት ያስተምራሉ፤ ስለዚህ ክፉ ነገሮች የየትኛውም የእግዚአብሔር ተግባር ውጤት አይደሉም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በማይቆጣጠርበት ወይም በኃላፊነት በማይጠየቅበት መንገድ ሰውና ተፈጥሮ ባደረጉት ተፈጥሮአዊ ግንኙነት የሚፈጸም ነው ይላሉ። የአብዛኛዎቹ ምዕራባውያን ምሁራን አመለካከት ይህ ነው።

5. እግዚአብሔር የለም የሚል እምነት ያላቸው (ኤቲስቶችና እግኖስቲኮች)፡ መከራ በተፈጥሮ ሥርዓት የሚከሠት እንደሆነ ለማመን ተገድደዋል። መከራ ምንም ዓላማ የለውም፤ ከእርሱም የማምለጥ መንገድ የለም። የእኛ ኃላፊነት የሚያደርስብንን ተጽዕኖ ውሱን ለማድረግ መጣር ብቻ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ስለ መከራ ከላይ ከተመለከትናቸው አመለካከቶች ውስጥ በአንዱ የሚያምኑ የምታውቃቸው ሰዎችን በምሳሌነት ጥቀስ። ለ) ስለዚህ አመለካከታቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ የምትሰጠው መልስ ምንድን ነው? ከአመለካከቶቹ አንዱን ውሰድና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መልስ ጻፍ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት ከፍ ሲል የተመለከትናቸው አምስቱ አመለካከቶች በሙሉ ስሕተት ናቸው። እግዚአብሔር ራሱ በሰጠው መገለጥ መሠረት አይሁድና ክርስቲያኖች የሚከተሉትን እውነተች ያምናሉ፡-

1. እግዚአብሔር የዓለም ፈጣሪና በውስጥዋ ላይ የሚገኙ ነገሮች ሁሉ ተቆጣጣሪ ነው። በእያንዳንዱ ሰው ሕይወትና በዓለም ክሥተቶች ውስጥ ራሱን የሚያገልል አምላክ አይደለም። ሕይወት እግዚአብሔር ወደ መልካም ፍጻሜ በሚመራው በጎ ዓላማ የተሞላ እንጂ ትርጕም የለሽ አይደለም። 

2. እግዚአብሔር ታላቅ ኃይል ያለው ነው፤ ስለዚህ ክፋትን ሁሉ ለመቈጣጠር ይችላል። ክፋት ግን እርሱን ሊቈጣጠረው አይችልም። ደግሞም እግዚአብሔር ጻድቅ ስለሆነ በባሕርይው ክፉ የሆነውን ነገር ሊያደርግ አይችልም። 

3. እግዚአብሔር በዓለማት ሁሉ «ሰው የሚዘራውን ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤» (ገላትያ 6፡7 ተመልከት) የሚል መመሪያ መሥርቷል። ይህ ማለት አንድ ሰው መልካም ሕይወትን ከኖረ ከእግዚአብሔር ሽልማቱን ይቀበላል፤ የኃጢአት ሕይወት ከኖረ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ቅጣትን ይቀበላል ማለት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ የመጨረሻ ሥነ-ምግባራዊ መመሪያ በሕይወት ውስጥ እውን የሆነው እንዴት ነው? ለ) የዚህን መመሪያ ተግባራዊነት ያየኸው እንዴት ነው? ምሳሌዎችን ጥቀስ። ከኦሪት ዘዳግም ጥናታችን እንደምታስታውሰው፥ ያኛው የሙሴ ሕግ ክፍል ለእግዚአብሔር ለሚታዘዙ በረከትን፥ ለማይታዘዙት ደግሞ መርገምን የሚያመጣ እንደሆነ የሚያሳይ ነበር።

አይሁድ በዚህ የሥነ-ምግባራዊ ሕግ መመሪያ ላይ ሌላ ከራሳቸው ጨመሩበት። እግዚአብሔር ሉዓላዊ ከሆነ፥ መከራና ሥቃይ የሚመጣው ከእርሱ ብቻ ነው በማለት አይሁድ ይከራከሩ ነበር። እንዲሁም እግዚአብሔር ጻድቅ ስለሆነ መከራና ሥቃይ ከርሱ ዘንድ የሚመጣ ቅጣት ነው። እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ጻድቅ ከሆነ፥ መከራውና ሥቃዩ ከሚቀበለው ሰው ኃጢአተኝነት ጋር ተመጣጣኝ መሆን እንዳለበት ያስቡ ነበር። አንድ ሰው ያለው ሀብትና በረከት የሰውዬውን ጻድቅነት የሚያረጋግጥ ነው። የሚደርስበት መከራና ሥቃይ ደግሞ የኃጢአተኝነቱ ማረጋገጫ ነው የሚል እምነት ነበራቸው። አንድ ሰው ሀብታም ከሆነ በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛ ነው ማለት ነው፤ ዳሩ ግን አንድ ሰው በሕመምና በደዌ የሚሠቃይ ከሆነ በኃጢአቱ ምክንያት እግዚአብሔር እየቀጣው ነው ማለት ነው፤ ዳሩ ግን ጻድቃን ሆነው መከራን የሚቀበሉ፥ ኃጥአን ሆነው መልካም ነገርን የሚለማመዱ ሰዎች ስላሉ፥ ይህኛው አቀራረባቸው ስሕተት ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ዮሐንስ 9፡1-3 አንብብ። ሀ) ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን በጠየቁት ጥያቄ ውስጥ ስለ መከራ የነበራቸው አስተሳስብ የዚህ ዓይነት መሆኑን እንዴት ታያለህ? ለ) የዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ዛሬም በበርካታ ክርስቲያኖች የሚደገፈው እንዴት ነው? 

4. በጎነት ሽልማትን፥ ከፋት ደግሞ ፍርድን ማምጣቱ ዓለም አቀፋዊ መመሪያ ቢሆንም፥ እግዚአብሒር ሽልማት ወይም ፍርድ መቼ እንደሚመጣ አይናገርም። አንዳንድ ጊዜ ወዲያውኑ ይሆናል። እግዚአብሔርንና ቤተ ክርስቲያንን በመቃወማቸው የተመቱ ሰዎች እንዳሉ ሁላችንም ምስክሮች ነን። ይሁን እንጂ፥ ሀብታሞች የሆኑ ብዙ ኃጥአን እንዳሉና ድሆች የሆኑ ብዙ ጻድቃን እንዳሉ ለሁላችንም ግልጽ ነው፤ ስለዚህ ኃጥአን ሁሉ ወዲያውኑ ይቀጣሉ ጻድቃንም ወዲያውኑ ሽልማታቸውን ያገኛሉ ማለት አንችልም። እግዚአብሔር የመጨረሻውን ሽልማት ወይም ቅጣት ለዘላለም ይሰጣል። ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን «እገሌ ሀብታም ነውና እግዚአብሔር ሸልሞታል፤ ወይም እገሌ ታሞአልና በሕይወቱ ኃጢአት አለ» ብለን ከመናገር መቆጠብ አለብን (መዝሙር (73) ተመልከት)። ክፉ ሰዎች ብዙ ጊዜ የክፋታቸውን ያህል አይቀጡም፤ መልካም ሰዎችም እንደ መልካምነታቸው አይሸለሙም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች የታመመ፥ ወይም ድሀና አካለ-ስንኩል የሆነ ክርስቲያን ሲያዩ፡- እንደዚህ የሆነው በሕይወቱ ኃጢአት ስላለ ነው ሲሉ ሰምተህ ታውቃለህን? ሁኔታውን ግለጽ። ለ) ይህ አባባል ትክክል ነውን? ሐ) ይህንን በምትሰማበት ጊዜ ለእነርሱ የምትሰጠው መልስ ምንድን ነው?

5. መከራ በብዙ ልዩ ልዩ ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል። ምክንያቶቹ ሁሉ ግን በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር ናቸው፤ ዳሩ ግን መከራ ሁሉ የኃጢአት ውጤት ነው ለማለት አንችልም። መከራ ሊመጣ የሚችልባቸውን የሚከተሉትን ሁኔታዎች ተመልከት፡-

ሀ. የተፈጥሮ አደጋዎች፡- አንዲት አገር በድርቅ ከተመታች እግዚአብሔር ቀጣት ማለት ነውን? አንዴትስ አገር ስትበለጽግ ከሌሎች የበለጠ ጻድቅ ነች ማለት ነውን? አይደለም። እንዲህ ብለን መናገር አንችልም። ድርቅ ወይም ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ሲኖሩ፥ አብዛኛዎቹ በአዳምና በሔዋን ኃጢአት የተነሣ በዓለም ላይ በደረሰው መርገም ምክንያት የመጡ ናቸው። እነዚህ ነገሮች ሰዎች ንስሐ መግባት እንዳለባቸው ለማስታወስ በምድር ላይ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔር የተፈቀዱ ቢሆኑም፥ ሁልጊዜ በአንድ አገር ውስጥ ካለ በጎነት ወይም ኃጢአት ጋር በቀጥታ የተዛመዱ አይደሉም። የሰው ልጅ የኃጢአት ውድቀት ውጤት ስለሆነው በሽታም ተመሳሳይ ነገር ማለት ይቻላል። ሁላችንም ብንሆን እንታመማለን ደግሞም እንሞታለን። ይህም ተፈጥሮአዊ ሂደት እንጂ በእኛ ዘንድ ካለ ኃጢአት ጋር ሁልጊዜ የሚያያዝ አይደለም።

ለ. በሰው ልጅ ክፋት ወይም መጥፎ ውሳኔ ምክንያት የሚከሠቱ የተፈጥሮ አደጋዎች፡- የመጨረሻ ምሳሌ የሆነው ጦርነት የሚመጣው በሰው ልጅ ራስ ወዳድነትና በኃጢአት ምክንያት እንጂ በእግዚአብሔር ሊመካኝ የሚችል አይደለም። ስለዚህ እኛም በሠራናቸው ስሕተቶች ወይም ባደረግናችው መጥፎ ውሳኔዎች ምክንያት ብዙ ጊዜ መከራን እንቀበላለን። በጥንቃቄ ሳንጓዝ ቀርተን የመኪና አደጋ ቢገጥመንና እግራችንን ብናጣ የእግዚአብሔር ጥፋት አይደለም፤ ግራና ቀኝን አይቶ በጥንቃቄ ያለማቋረጥ ወይም በኃላፊነት ያለማሽከርከር ውጤት ነው። 

ሐ. መከራና በሽታ ቀጥተኛ የኃጢአት ውጤት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፡- የሥነ-ምግባር ጕድለት አንድን ወጣት በኤድስና በሌሉች የአባለዘር በሽታዎች እንዲያዝ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፥ እነዚህን በሽታዎች ጥፋት ወደ ሌላት ሚስቱና ልጆቹ እንዲተላለፍ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ይህ የአንድ ሰው ኃጢአት ውጤት ቢሆንም፥ በዚህ ሰው ኃጢአት ምክንያት ጥፋተኛ ያልሆኑ ሰዎችም ሊሠቃዩ ይችላሉ። 

መ. መከራና በሽታ አንድ ሰው በኃጢአቱ ምክንያት በሕይወቱ ላይ የሚያመጣው ቀጥተኛ የእግዚአብሔር ቅጣት የሚሆንበት ወቅት አለ። ሰው ኃጢአት በሚሠራበት ጊዜ እግዚአብሔር በቀጥታ በሰውዬው ላይ የሚፈርድበት ጊዜ አለ። እግዚአብሔር በበሽታ ወይም በሞት እንኳ ሰውዬውን ወዲያውኑ የሚቀጣበት ወቅት አለ።

የውይይት ጥያቄ፥ በሰው ልጅ ሕይወት መከራና ሥቃይ ሊመጣባቸው ከሚችሉ ከእያንዳንዱ ክፍሎች ምሳሌዎችን ጥቀስ። 

6. የእግዚአብሔርና የልጆቹ ጠላት የሆነው ሰይጣን በሰው ልጆች ላይ በሚደርሰው መከራ ውስጥ ድርሻ አለው። የእግዚአብሔርን ልጆች እምነት ለማጥፋት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ሰይጣን የእግዚአብሔርን ልጆች ሊነካ አይችልም። በእግዚአብሔር ልጆች ላይ ሊያደርስ የሚችለው ነገር በእግዚአብሔር የተወሰነ ነው። ሰይጣን እንደፈለገው ሊሠራ አይችልም። 

7. መከራ የማንወደው ነገር ቢሆንም እንኳ እግዚአብሔርን የመምሰል ባሕርይ እንዲኖረን እግዚአብሔር እኛን ከሚያሳድግባቸው ዐበይት መንገዶች አንዱ ነው። መከራ ሰውን እንደ ወርቅ አንጥሮ የሚያወጣ ነው (ኢዮብ 23፡10)። መከራ ባሕርይን የሚቀርጽና የሚያሳድግ፥ መንፈሳዊ ብስለትንም የሚያመጣ ነው (ያዕቆብ 1፡2-4)። የምንቀበለው መከራ፥ ሌሎች በመከራ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ለማጽናናትና ለማበረታታት ያስችለናል (2ኛ ቆሮንቶስ 1፡3-7)። የተፈጥሮ ዝንባሌያችን ከመከራ መሸሽ ቢሆንም፥ መከራ በምንቀበልበት ጊዜ በክርስቶስ መከራ ስለምንካፈል ደስ እንድንሰኝ ተነግሮናል (ፊልጵስዩስ 3፡10፤ ቈላስይስ 1፡24)።

8. እግዚአብሔር በክፋት ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው የበላይ ተቈጣጣሪ ስለሆነ፤ አንድ ቀን ክፋትን ከምድረ-ገጽ ያጠፋል፤ ዳሩ ግን መጨረሻው እስኪደርስ ድረስ መከራና ክፋት በምድር ላይ ይኖራል። የትም ብንሄድ ልናመልጠው አንችልም፤ በየሄድንበት ይከተለናል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን መከራን ከመሸሽ ይልቅ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ዕድገት ልንጠቀምበት ያስፈልጋል። በመጽሐፈ ኢዮብ ውስጥ፥ ኢዮብ ስለተባለ አንድ ሰው ትግል እናነባለን። ይህ ሰው የነበረውን እጅግ ከፍተኛ ሀብትና ብልጽግና፥ ቤተሰቡን በሙሉ እንዳጣና ከፍተኛ ሕመምና ሥቃይ እንደደረሰበትም እንመለከታለን። በዚህ መከራ ውስጥ እያለ ሦስት ወዳጆቹ ሊያጽናኑት መጡ። በማጽናናት ፈንታ ግን፥ በሐሰት ኃጢአት ሠርቶአል ብለው በመክሰስ ሥቃዩንና ኃዘኑን እንዳባባሱ እንመለከታለን። እግዚአብሔር ኢዮብ ጻድቅ ሰው መሆኑን ያውቅ ነበር። ወዳጆቹ ግን በኃጢአተኝነት ከሰሱት። (ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን በመከራ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ኃጢአት ባይሠሩም እንኳ፥ ይህ የሆነው በኃጢአታቸው ምክንያት ነው እያልን በምንናገርበት ጊዜ መከራቸውንና ሥቃያችውን እናባብሳለን)። የኢዮብ ወዳጆች ንስሐ እንዲገባ ኢዮብን መከሩት። እነርሱ ያሉት ነገር ሁሉ ከመሠረታዊ ትምህርት አንጻር ስናየው ትክክል ነው። ዋናው አሳባቸው ፍርድ የሚመጣው በኃጢአት ምክንያት ነው የሚል ነበር፤ ዳሩ ግን በሰው ልጆች ላይ መከራ የሚደርሰው ግለሰቦች ራሳቸው በሚፈጽሙት ኃጢአት ምክንያት ነው ወደሚል አስተሳሰብ ርቀው ሄደው ነበር። የኢዮብ ወዳጆች የኢዮብን ጉዳይ ሳያውቁ የራሳቸውን አስተሳሰብ በማንጸባረቃቸው ንስሐ መግባት እንዳለባቸው እግዚአብሔር በመረጃ በግልጽ አሳውቆአቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ መከራ የደረሰባቸው በኃጢአት ምክንያት እንደሆነ አድርገን መከራ የሚቀበሉ ሰዎችን እንዳንከስ ከኢዮብ ታሪክ ምን እንማራለን?

መከራን በምንቀበልበት ጊዜ ብዙዎቻችን እንደምናደርገው፥ ጻድቅ የሆነው ኢዮብም እግዚአብሔር ያለ ኃጢአቱ ለምን ይህ ሁሉ መከራ እንዲደርስበት እንደፈቀደ በመገረም ይናገራል። በእግዚአብሔርና በሰይጣን መካከል በሰማይ ስለ ተደረገው ንግግር ኢዮብም ሆነ ወላጆቹ አያውቁም ነበር። ኢዮብ መከራ የሚቀበለው በኃጢአቱ ሳይሆን፥ በጽድቁ ምክንያት እንደሆነ ወዳጆቹ አልተገነዘቡም ነበር። መከራ የሚቀበለው ለምን እንደሆነ እግዚአብሔር ለኢዮብ ጨርሶ አልነገረውም ነበር። ኢዮብ ስለ እግዚአብሔር ለጠየቀው ጥያቄ ሁሉ እግዚአብሔር መልስ አልሰጠውም፤ ነገር ግን ኃይሉንና ታላቅ ጥበቡን አሳየው። ኢዮብ በመከራ ውስጥ እያለ ለጠየቀው ጥያቄ እግዚአብሔር የሰጠው መልስ፡- ትንሽ የሆነው ሰው የእግዚአብሔርን ጽድቅና ኃይል መጠየቅ አይችልም የሚል ነበር። የሰው ልጆች የእግዚአብሔርን ምክርና ዓላማ ለማወቅ ከቶ አይችሉም። እናውቃለን ብለን የቅድሚያ ግምት መውሰድ ወይም እግዚአብሔር የሚሠራው ሥራ ትክክል እንዳይደለና አድልዎ እንዳለበት ማሰብ ከእግዚአብሔር እበልጣለሁ እንደማለት ነው። ኢዮብና ወላጆቹ በእግዚአብሔር ላይ የሠሩት ኃጢአት ይህ ነበር። ኢዮብ የእግዚአብሔርን አእምሮ ለመረዳት የጥበብ ጉድለትና የችሎታ ማነስ እንዳለበት ለመቀበል ተገዶ ነበር። እግዚአብሔር ለኢዮብና ለእኛ ያስተማረን ነገር፡- መከራን ስንቀበል እርሱን በመጠየቅ ጊዜ ማጥፋት እንደሌለብንና አፍቃሪው እግዚአብሔር ለእኛ ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንደሚያደርግልን ማወቅንና በእምነት መራመድ እንዳለብን ነው። ጥያቄዎች ቢኖሩንም እንኳ ለእግዚአብሔር ታማኞች ልንሆን ያስፈልጋል፤ ኢዮብ ያደረገው ይህንን ነበር። በጥያቄዎቹ ሁሉ መካከል ኢዮብ ሁልጊዜ ወደኋላ በመመለስ አንድ ቀን በእግዚአብሔር ፊት ነፃ እንደሚሆን ያስብ ነበር።

እግዚአብሔር ልጆቹን መባረክ ደስ ይለዋል። ክፉዎችንም ይቀጣል። ዳሩ ግን ይህን መመሪያ በሚመለከት እጅግ ርቀን እንዳንሄድ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ይህንን መመሪያ እግዚአብሔር እኛንም ሆነ ሌሎችን በጽድቃችን መሠረት እንዲባርከን ወይም ኃጥአንን ወዲያውኑ እንዲቀጣቸው ለመጠየቅ ልንጠቀምበት አንችልም። በተጨማሪ መከራን በምናይበት ጊዜ የኃጢአት ውጤት ነው ብለን ለማሰብ አንችልም። ነገሮች ሁሉ ፈር በሚይዙበት ጊዜም ይህ የሆነው የተቀደሰ ሕይወት ስለኖርንና እግዚአብሔር ለዚህ ሕይወታችን የሰጠው ሽልማት እንደሆነ አድርገን ማሰብ አንችልም። ወይም አንድ ሰው መከራ የሚቀበለው በኃጢአቱ ምክንያት ነው ብለን በፍጹም ማሰብ የለብንም። እንደ ኢዮብና ወዳጆቹ ሁሉ የጉዳዮቹን ጭብጥ ሙሉ በሙሉ ስለማናውቅ ትልቅ ስሕተት ልንሠራ እንችላለን። እግዚአብሔር ከገለጠልን በላይ እንዳንናገር መጠንቀቅ አለብን። እኛም ሆንን ሌሉች መከራ የምንቀበለው ለምን እንደሆነ በግልጽ ለይተን ባናውቅም፥ መከራ ሁሉ የሚመጣው ጠቢብና አፍቃሪ በሆነው በእግዚአብሔር እጅ በኩል እንደሆነ በመገንዘብ ልንጽናና እንችላለን። ብዙ ጊዜ መከራና ሥቃይ የምንቀበለው በምን ምክንያት እንደሆነ የምንረዳው ከዓመታት በኋላ ነው። ከዚያ በኋላ እንድንቀበል ያደረገንን ነገር ብንጠላም እንኳ በመከራ ውስጥ ስላደረገው ነገር እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። 

ከሳሹ ሰይጣን 

ከኢዮብ 1-2 ባለው ክፍል የተጻፈ አንድ ሌላ አስፈላጊ ትምህርት አለ። ይኸውም የስሙ ትርጒም «ከሳሽ» የሆነው ሰይጣን፥ እግዚአብሔር ጻድቅ የሆነውን ሰው በመባረኩ ትክክል እንዳልሠራ አድርጎ ሲከስ እንመለከታለን። ሰይጣን፥ ኢዮብና ሌሎች ጻድቃን እግዚአብሔርን የተከተሉት ስለባረካቸው እንደሆነ ይናገራል። እግዚአብሔር ባይባርካቸው ኖሮ አይከተሉትም ነበር ይላል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ክስ ብዙውን ጊዜ እውነት የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) ብዙ ሰዎች ነገሮች ሁሉ በመልካም እስከተከናወኑላቸው፥ ሥራ እስካላቸው፥ ከኃጢአትና ከበሽታ እስከተፈወሱ ድረስ ብቻ በእግዚአብሔር የሚታመኑት እንዴት ነው?

አዎን፥ ከእርሱ የሚያገኙትን መልካም ነገር ብቻ ተስፋ አድርገው እግዚአብሔርን የሚከተሉ በርካታ ክርስቲያኖች አሉ። የዚህ ዓይነቱ እምነት እጅግ በጣም ደካማ ነው። ስደት፥ በሽታና ሞት የሚፈጸሙባቸው አስቸጋሪ ጊዜያት ሲመጡ፥ እምነታችን በሥጋ ከምናገኘው በረከት የበለጠ ጠልቆ መሄድ አለበት። በእግዚአብሔር ዘላለማዊ የተስፋ ቃሉ ላይ ማረፍ አለበት። አስተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን ማድረግ ያለብን አንድ ነገር፡- ክርስቲያኖች በምድር በሚቀበሏቸው በረከቶች ከመታመን ይልቅ የእግዚአብሔር ልጆችና የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት በመሆናቸው እንዲረኩ ማድረግ ነው። እግዚአብሔር አሁኑኑ ሊባርከን ወይም መከራን የማይጨምር በረከት ብቻ ይሰጠን ዘንድ አይገደድም።

ኢዮብን በሚመለከት ሰይጣን እንደተሳሳተ እግዚአብሔር ማረጋገጥ ፈለገ። እግዚአብሔር ከኢዮብ እጅ ላይ ንብረቱን ቀጥሎም ጤንነቱን እንዲወስድ ለሰይጣን ፈቀደለት። በዚህ ሁሉ ግን ኢዮብ በእግዚአብሔር ላይ በነበረው እምነቱ ጸና። ኢዮብ በመከራው ምክንያት በመንፈሳዊ ሕይወቱ አደገ። እግዚአብሔር ጻድቅ ሰውን እንደሚባርክ፥ ኢዮብ በመከራው ውስጥ ባሳየው ሁኔታ የእግዚአብሔርን ስም ከፍ ከፍ ማድረጉን በግልጽ አረጋግጦአል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመጽሐፈ ኢዮብ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያን አንዳንድ ጊዜ መከራ የሚቀበልባቸውን ምክንያቶች ጥቀስ። ለ) በክርስቲያን ላይ የሚደርሰው መከራ ሁልጊዜ የኃጢአት ውጤት ነውን? መልስህን አብራራ። ሐ) አንድ ክርስቲያን በበሽታ በሚሠቃይበት ወይም የሚወደው ሰው በሞት በሚለይበት ጊዜ የምትሰጠው ምክር ወይም ማበረታቻ ምንድን ነው?

የምንኖረው መከራና ሥቃይ በሞላበት ዓለም ውስጥ ነው። ትንንሽ ልጆች ራሳቸውን በሕይወት ለማቆየት የሚችሉበትን ዕድል ሙሉ በሙሉ በማጣት፥ በየቀኑ በበሽታና በራብ ይረግፋሉ። ወታደሮች ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ሰላማዊ ሰዎች የሚያልቁባቸው በርካታ ጦርነቶች በምድራችን ይካሄዳሉ። እግዚአብሔር በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀምባቸው ታላላቅና ታዋቂ ክርስቲያኖች ይታመማሉ ይሞታሉም። ይህ ሁሉ ክርስቲያኖችን «ለምን?» የሚል ጥያቄ እንዲሰነዝሩ ያስገድዳቸዋል። ለመረዳት በጣም አስቸጋሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ መከራን የመቀበል ጉዳይ ነው። እጅግ ጻድቅ የሚመስሉ ሰዎች መከራን የሚቀበሉት ለምንድን ነው? በሌላ አንጻር ደግሞ እጅግ ክፉ የሆኑ ሰዎች መልካም ሕይወትን የሚኖሩት ለምንድን ነው? ይህ ጉዳይ እንዴት ትክክል ሊሆን ይችላል? እግዚአብሔር ምንም ሳናደርግ በዚች ዓለምና በሕይወታችን ላይ ብዙ መከራ እንዲመጣ በማድረጉ ትክክል ነውን?

የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ከተፈጠረና በኃጢአት ከወደቀ ጀምሮ ይህ ጥያቄ ራስ ምታት ሆኖበታል። ጉዳዩ በጣም የተወሳሰበ ስለሆነ ሰዎችን ሁሉ የሚያረካ መልስ መስጠት እጅግ አዳጋች ነው። በተለይ ደግሞ መከራን ለሚቀበሉ ሰዎች ለዚህ ጉዳይ መልስ መስጠት ከባድ ነው።

እግዚአብሔር መጽሐፈ ኢዮብን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲጨመር ያደረገው ይህንን መከራ መቀበልን በሚመለከት የሚሰነዘር የምንጊዜም ጥያቄ ለመመለስ ይረዳ ዘንድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፥ ሰዎች በተለይ ደግሞ ጥፋተኛ ያልሆኑት መከራ ስለሚቀበሉበት ምክንያት ሁሉ መልስ ባይሰጥም፥ በመከራ ጊዜ በእምነታችን ጸንተን እንድንኖር የሚያደርጉንን የተወሰኑ መልሶች ይሰጠናል። መጽሐፈ ኢዮብ ስለ አንድ ጻድቅ ሰው መከራ መቀበል የሚናገር ነው። ይህ ሰው ሁሉን ነገር ቢያጣም እንኳ በእግዚአብሔር ላይ ስለነበረው ጽኑ እምነት እናነባለን። በተጣማሪም በመከራ ውስጥ ሳለ ስለ እግዚአብሔር የጽድቅ ፍርድ ቢገረምም በግሉ ስለ ፈጸመው ትግል እንመለከታለን። 

የመጽሐፈ ኢዮብ ጸሐፊ

በመጽሐፈ ኢዮብ ውስጥ የምናገኘው ታሪካዊ ዘገባ አነስተኛ በመሆኑ መቼ እንደተጻፈና ማን እንደጻፈው ለመናገር አንችልም። ልናደርግ የምንችለው የመመራመር ግምትን ማቅረብ ነው። የመጽሐፈ ኢዮብ አጻጻፍ በሁለት ደረጃዎች የተከናወነ ሳይሆን አይቀርም።

በመጀመሪያ፥ የመጽሐፈ ኢዮብን ታሪካዊ ድርጊት እናገኛለን። መጽሐፉን በጥንቃቄ በምንመለከትበት ጊዜ የምንረዳው ነገር፥ ኢዮብ እስራኤላዊ እንዳልሆነና በኤዶም ወይም በዓረብ ምድር የኖረ ሰው እንደሆነ ነው። ኢዮብ የኖረው የእስራኤል ሕዝብ አባቶች የሚባሉት አብርሃም፥ ይስሐቅና ያዕቆብ በኖሩበት ዘመን ይመስላል። ይህ ማለት መጽሐፈ ኢዮብ የተጻፈው ከ3000-2000 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር ማለት ነው። ብዙ ምሁራን ይህን አቋም የያዙባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፡- 

1) የኢዮብ ዕድሜ በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ ከምናያቸው የእስራኤል ሕዝብ አባቶች ዕድሜ ጋር ተቀራራቢ ነው። 

2) ኢዮብ ከብት አርቢ ነበርና ሀብቱም በከብቶቹ ላይ የተመሠረተ ነበር፤ ይህም ከአብርሃም ጋር ይመሳሰላል። 

3) ኢዮብ ቤተሰቡን እንደ ሊቀ ካህን የሚያገለግልና እንደ አብርሃም መሥዋዕት የሚያቀርብ ሰው ነበር። 

4) በመጽሐፈ ኢዮብ ውስጥ ስለ ሙሴ ሕግ፥ ስለ መገናኛው ድንኳን ወይም ስለ ቤተ መቅደሱ የሚናገር አንዳችም ነገር አልተጠቀሰም።

5) በነቢያት ዘመን እንደነበረው የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምሩ ስለነበሩ የአይሁድ ነቢያት የተጠቀሰ አንዳችም ነገር የለም፤ ስለዚህ ኢዮብ ይኖር የነበረው ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው ሺህ ዓመት ይመስላል። 

ሁለተኛው፥ መጽሐፈ ኢዮብ ከፍተኛ ትምህርትና ችሎታ በነበረው በአንድ ባልታወቀ ሰው የመጻፉ ነገር ነው። መጽሐፈ ኢዮብ በጥንታዊ ዓለም ከተገኙ ከፍተኛ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ወይም ግጥሞች ውስጥ አንዱ ነው። ጸሐፊው መልእክቱን ለማስተላለፍ የሚያስችለውን ግጥም ለመጻፍ ከፍተኛ ችሉታውን ተጠቅሟል። እንደ አንዳንዶቹ ግምት ደግሞ መጽሐፈ ኢዮብ የተጻፈው ከሙሴ እስከ ዕዝራ ባለው ዘመን (1440-450 ዓ.ዓ.) በማንኛውም ጊዜ ውስጥ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም አንዳንድ ምሁራን የመጽሐፉ ጸሐፊ ሙሴ እንደሆነ ቢናገሩም፥ ለዚህ አመለካከት ምንም ማስረጃ የለንም። ጸሐፊው ማን እንደሆነ አይታወቅም ማለቱ የተሻለ ነው። መጽሐፉ በአይሁድ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተካተተ ጸሐፊው እስራኤላዊ እንደሆነ መገመት እንችላለን። ጽሑፉንና የተጻፈበትን ቋንቋ ስንመለከት፥ ጸሐፊው በጣም የተማረ ሰው እንደነበረ እንገነዘባለን። ጸሐፊው ስለ መከራና እግዚአብሔርም ከመከራ ጋር ስላለው ግንኙነት የሚያስብ ፈላስፋ ነበር። እርግጠኞች መሆን ባንችልም፥ ጸሐፊው ይህንን ታሪክ በቃል ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣ ትውፊት ሰምቶታል ወይም የተጠቀመበት ሌላ መጽሐፍ አለ። ብዙ ምሁራን መጽሐፉ የተጻፈው ከንጉሥ ሰሎሞን በኋላ (970 ዓ.ዓ.) ከእስራኤል ምርኮ በፊት (586 ዓ.ዓ.) እንደሆነ ይመስላቸዋል። 

የመጽሐፉ ርእስ

መጽሐፈ ኢዮብ የተሰየመው በታሪኩ ዋና ገጸ ባሕርይ ስም ነው። መጽሐፉ የሚናገረው በመከራ ውስጥ ስላለፈው፥ ስለ ጻድቁ ሰው ስለ ኢዮብ ነው። ታሪኩ የሚያንጸባርቀው ኢዮብ በመከራ ውስጥ እያለ የጠየቃቸውን ጥያቄዎችና ሌሎች ሰዎች ስለ መከራ የሰጡዋቸውን የተለመዱ መልሶች ነው።

መጽሐፈ ኢዮብ በሥነ-ጽሑፍነቱ

መጽሐፈ ኢዮብ፡- በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ከሚገኙ እጅግ ምርጥ ከሆኑ የግጥም መጻሕፍት መካከል አንዱ ቢሆንም፥ ለመተርጐም እጅግ አስቸጋሪ ከሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አንዱ ነው። ምሁራን ስለ ትርጕማቸው እርግጠኞች ያልሆኑባቸው በርካታ ቃላትና ዐረፍተ ነገሮች የሚገኙበት መጽሐፍ ነው። ስለተለያዩ የመጽሐፈ ኢዮብ ትርጒሞች ያሰብን እንደሆነ በትርጕም ብዙ የሚለያዩበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።

መጽሐፈ ኢዮብ ባለሙያ በሆነ ጸሐፊ በጥንቃቄ ታቅዶ የተጻፈ መጽሐፍ ነው። ጽሑፉ በአብዛኛው በሕጋዊ የችሎት ክርክር መልክ የቀረበ ሲሆን፥ በዚህ ክርክር ጸሐፊው ኢዮብን ከሳሽ አድርጎ በማቅረብ የእግዚአብሔርን ቅን ፍርድ ያሳያል። መጽሐፈ ኢዮብን በምታነብበት ወቅት የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-

1. መጽሐፈ ኢዮብ የሚጀምረው የግጥም መልክ በሌለው የአጻጻፍ ስልት ሲሆን (ኢዮብ 1-2)። የሚጠቃለለውም በዚሁ ዓይነት ሥነ-ጽሑፍ ነው (ኢዮብ 42)፤ ዳሩ ግን በመካከል ያሉት ምዕራፎች በሙሉ በግጥም መልክ የቀረቡ ናቸው። 

2. በመጽሐፉ መጀመሪያ ላይ ኢዮብን የምናገኘው እጅግ ደስተኛና በረከት የበዛለት ሆኖ ሲሆን (ኢዮብ 1፡1-5)። በመጽሐፉም መጨረሻ የምናገኘው በዚሁ መልክ ነው (ኢዮብ 42፡7-17)። በመካከል ያሉት ምዕራፎች ግን ስለ ኢዮብ መከራ ይናገራሉ። 

የመጽሐፈ ኢዮብ አስተዋጽኦ

1. የታሪኩ መግቢያ (ኢዮብ 1-2) 

2. ኢዮብ ከሦስቱ ጓደኞቹ ጋር ያደረጋቸው ንግግሮች (ኢዮብ 3-31)

ሀ. የመጀመሪያው ውይይት ዑደት (ኢዮብ 4-14)

1. የኢዮብ እንጉርጉሮ መግቢያ (ኢዮብ 3) 

2. የኤልፋዝ ንግግር (ኢዮብ 4-5) 

3. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 6-7) 

4. የበልዳዶስ ንግግር (ኢዮብ 8) 

5. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 9-10)

6. የሶፋር ንግግር (ኢዮብ 11)

7. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 12-14) 

ለ. ሁለተኛው የውይይት ዑደት (ኢዮብ 15-21)

1. የኤልፋዝ ንግግር (ኢዮብ 15)

2. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 16-17) 

3. የበልዳዶስ ንግግር (ኢዮብ 18) 

4. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 19) 

5. የሶፋር ንግግር (ኢዮብ 20)

6. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 2) 

ሐ. ሦስተኛው የውይይት ዑደት (ኢዮብ 22-31)

1. የኤልፋዝ ንግግር (ኢዮብ 22) 

2. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 23-24) 

3. የበልዳዶስ ንግግር (ኢዮብ 25)

4. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 26-3) 

3. የኤሊሁ ንግግር (ኢዮብ 32-37) 

4. የእግዚአብሔር ንግግርና የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 38-41) 

5. ማጠቃለያ (ኢዮብ 42) 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የጥበብ ሥነ-ጽሑፎች

አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሥነ ግጥማዊ የአጻጻፍ ስልት መጻፉን ቀደም ሲል ተመልክተናል። ይህ በተለይ በመዝሙረ ዳዊት፥ በመኃልይ መኃልየ ዘሰሎሞን፥ እንዲሁም በአንዳንድ የትንቢት መጻሕፍት ውስጥ የምናየው እውነታ ነው። የጥበብ ጽሑፎች የሥነ- ግጥምና ቅኔ ጽሑፎች ክፍል ቢሆኑም፥ «የጥበብ» ጽሑፎች ብለን ልንጠራቸው የምንችለው ልዩ ዓይነት ግጥሞች ናቸው። ከመዝሙረ ዳዊት አንዳንድ ክፍሎችና እንደዚሁም አብዛኛዎቹ የመጽሐፈ መክብብና የመጽሐፈ ምሳሌ ክፍሎች የጥበብ ጽሑፎች የሚገኙባቸው ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአማርኛ ቋንቋ «ጥበብ» የምንለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? ለ) በኅብረተሰብህ ውስጥ እንደ ጠቢብ የሚቆጠር አንድ ሰው ጥቀስ። ሐ) ጠቢብ ያደረገው ምንድን ነው? መ) ከሌሎች ሰዎች የሚለየው እንዴት ነው?

ባለንበት ዘመን፥ ብዙዎቻችን ጥበብ የሚገኘው በትምህርት ቤት እንደሆነ አድርገን እናስባለን። ጥበብ የበርካታ እውነቶች ስብስብ እውቀት እንደሆነ እንቆጥራለን፤ ስለዚህ ጥበብ የሚገኘው ባልተማሩ ሳይሆን፥ በሚገባ በተማሩ ሰዎች ዘንድ እንደሆነ አድርገን እንገምታለን።

አይሁድ ግን «ጥበብ» ሲሉ ይህን ማለታቸው አይደለም። የብሉይ ኪዳን ጸሐፊዎች «ጥበብ» የሚለውን ቃል በተለያዩ መንገዶች ተጠቅመውበታል፡-

1. የተለየ ሙያ ወይም ችሎታ ስላላቸው ሰዎች ለመናገር አገልግሏል። ለምሳሌ የመገናኛውን ድንኳን የሠሩት ባስልኤልና ኤልያብ የተባሉት ሁለት ሰዎች «ጠቢባን» የተባሉት ድንኳኑን በመሥራት ረገድ ልዩ ችሎታ ስለነበራቸው ነው (ዘጸአት 31፡1-11)። 

2. አንዳንድ ጊዜ ይህ ቃል አገልግሎት ላይ ውሎ የምናየው ለጐበዞችና ጥሩ የአእምሮ ችሎታ ላላቸው ሰዎች ነው (ኢዮብ 38፡36)። 

3. ጥበብ የሚለው ቃል ጥሩ የተፈጥሮ እውቀት ላላቸውና አንድን ጉዳይ አመዛዝኖ በማቅረብ ችሎታቸው ጠቢባን ተብለው ለተጠሩ ሰዎች አገልግሉአል (ኢዮብ 32፡7)። 

4. ከሁሉ በላይ ግን፥ ጥበብ እውቀትን በትክክለኛ መንገድ የመጠቀም ችሎታ ነው (ምሳሌ 1፡5)። አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የተሳካ ኑሮ ለመኖር የሚችለው ጠንቃቃና ሚዛናዊ የመሆን ችሉታ ሲኖረው ነው። ይኸውም ትክክለኛና ሚዛናዊ የሆኑ ነገሮችን ማድረግ ሲችል ነው (ምሳሌ 3፡1-6)።

የውይይት ጥያቄ፥ መዝሙረ ዳዊት (11)፡10፤ ምሳሌ 1፡7፤ 2፡5-6፤ 19፡10፤ ያዕቆብ 1፡5፤ 3፡17 አንብብ። ሀ) የጥበብ መጀመሪያ ምንድን ነው? ለ) እውነተኛ ጥበብ የሚመጣው ከየት ነው? ሐ) የዚህ ዓይነቱ ጥበብ በሕይወትህ ለመኖሩ ማስረጃ የሚሆኑ መንገዶችን ግለጽ። 

ስለዚህ የጥበብ ሥነ-ጽሑፎች የምንላቸው ለሕይወታችን ጥቅም በሚያስገኙ መንገዶች እንዴት መኖር እንዳለብን የሚያስተምሩን የብሉይ ኪዳን ሥነ-ጽሑፎች ናቸው። የተመሠረቱትም ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት በማድረግ ሲሆን፥ ያለዚህ ግንኙነት ለእግዚአብሔር ፍርድ የተጋለጥንና እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ መንገድ ለመኖር የማንችል ነን። የጥበብ ሥነ-ጽሑፍ ሕይወታችንን ስለሚለውጥ፥ ተግባራዊ ነው። ለሕይወታችን ያለው ጠቀሜታ ከሁሉም የላቀ ነው። እውነተኛ እውቀትን ከሕይወታችን ጋር በማዛመድ እንዴት የተሻለ ሕይወት መኖር እንዳለብን ለመማር የሚያስችለን ነው። የጥበብ ሥነ-ጽሑፍ ዓላማ የአንድን ሰው ዝንባሌ፥ ባሕርይና አኗኗር በመለወጥ፥ በልቡ ውስጥ ሊኖር የሚገባውን ፈሪሀ እግዚአብሔር እንዲያንጸባርቅ የሚያደርግ ነው። ይህም ወደ በጎነት ሕይወት ይመራል (ምሳሌ 2፡20)።

ጥበብና እውቀት እንደ ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ካለው ግንኙነት ጋር በጥብቅ የተቆራኙ መሆናቸውን አይሁድ ተገንዝበው ነበር። እግዚአብሔር የጥበብ ሁሉ ምንጭ በመሆኑ ለእርሱና ለፈቃዱ ታዝዘው ለመኖር ለወሰኑ ሰዎች ሁሉ ጥበብን ለመስጠት ቃል ገብቶአል (ኢዮብ 12:13፤ ምሳሌ 2፡5-6)፤ ስለዚህ ማንኛውም ሰው ጥበብን ለማግኘት ወደ ትምህርት ቤት አልሄደም፤ ወይም ጥበበኞችን አላማከረም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር እንደፈቃዱ ተጓዘ። ስለዚህ ሰው በእውነት ጠቢብ ነው የሚባለው መሠረታዊ በሆነ ጉዳይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ጥበብ በትምህርት ቤት ከምንማረው «ጥበብ» የሚለየው እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስን ጥበብ ለመረዳት መሠረቱ፡- ሕይወት ሁለት ዋና ዋና መንገዶችን የያዘች መሆንዋን መገንዘብ ነው። ወደ ጽድቅ የሚያደርስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንገድ አለ፤ ወይም ወደ ጥፋት የሚያደርስ የኃጢአት መንገድ አለ (ማቴዎስ 7፡13-14)። አንደኛው መንገድ የጠቢብ (ምሳሌ 10፡8፥14)፥ የቅንና (ምሳሌ 11፡3) የጻድቅ መንገድ ነው (ምሳሌ 10፡16)። ሌላው የሞኞች ወይም የሰነፎች (ምሳሌ 10፡1፥8፥14)፤ የኃጥአንና (ምሳሌ 10፡3) ታማኝ ያልሆኑ ሰዎች ወይ የወስላቶች መንገድ ነው (ምሳሌ 11፡3)።

የጥበብ መጻሕፍትን በምንተረጕምበት ጊዜ ልናስታውሳቸው የሚገባን ሁለት ዓይነት የጥበብ ሥነ-ጽሑፎች አሉ። መጀመሪያ፥ ልንከተላቸው የሚገባን ተግባራዊ ጥበባትን የሚያስተምሩን ምሳሌዎችና አባባሎች አሉ። እነዚህ ጥሩ ልማዶችን፥ ጥሩ ሙያዎችንና መልካም ባሕርያትን የሚያስተዋውቁን ናቸው (ለምሳሌ፥ ምሳሌ 21፡23፤ 22፡3)።

ሁለተኛ፥ በዚያን ዘመን ይነገሩ የነበሩ ምርጥ አባባሎችን የሚያንጸባርቁ፥ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ግን ሊከተላቸው የማያስፈልጉ ምሳሌዎች አሉ፤ ወይም እነዚህ ከቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጋር የማይስማማ ፍልስፍና የሚያንጸባርቁ ናቸው። መጽሐፈ ኢዮብና መክብብ ከያዛቸው የጥበብ አነጋገሮች መካከል ትክክል ያልሆኑና ልንከተላቸው የማያስፈልጉ ዐረፍተ ነገሮች ይገኛሉ። የኢዮብ ወዳጆች ለኢዮብ ያካፈሉት ምክር በአብዛኛው ትክክለኛ አልነበረም። በመጽሐፈ መክብብ ውስጥ የምናገኛቸው የሰሎሞን አስተሳሰቦች ላይ ላዩን በምንመለከታቸው ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በትክክል የሚያንጸባርቁ አይደሉም። በውስጡ የሚገኘውን የጥበብ ትምህርት የምናስተውለው መጽሐፉን በተገቢው መንገድ ስንረዳ ነው።

የጥበብ ሥነ-ጽሑፎችን ብዙ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ የምንተረጉምበት አንዱ ምክንያት በውስጡ ያሉትን ልዩ ቃላት ካለመረዳታችን ነው። ቀጥለን በእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና ቃላት እንመለከታለን፡-

1. ጥበብ፡- ልዩ እውቀትን ማግኘት ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ያገኘነውን እውቀት እግዚአብሔርን ለማስከበር በሚያስችል ትክክለኛ መንገድ ለመኖር መጠቀም ማለት ነው። 

2. ጠቢብ ሰው:- በመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዛት መሠረት የሚኖር ሰው ማለት ነው። 

3. ሞኝ ወይም ሰነፍ፡- ያልሠለጠነና ማንም ሰው በቀላሉ ሊያሞኘው የሚችል (ምሳሌ 14፡15)፣ ሕይወቱን በብልሃት የማይመራ፥ ዓመፀኛና ያልተገራ፥ ተግሣጽን የማይቀበልና እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰው ነው። ሞኝ ወይም ሰነፍ በአእምሮው ደካማ የሆነ ሰው ማለት ሳይሆን እግዚአብሔርን በሕይወቱ የማያከብር ሰው ማለት ነው።

4. ኃጥእ፡- ሆን ብሉ እግዚአብሔርንና ቃሉን ያልተቀበለ፥ በእግዚአብሔር ትእዛዛት ላይ ያመፀና ሌሉችም ከእውነት እንዲርቁ የሚፈልግ ሰው ነው። 

5. ፌዘኛ ወይም ቀልደኛ፡- እውነትን በተጠራጣሪነት የሚጠይቅ፥ ተግሣጽንና ምክርን የሚጠላ ሰው ነው። የጥበብ ሥነ-ጽሑፎች ዓይነቶች የተለያዩ ናቸው። በመጀመሪያ፥ እንዴት መኖር እንዳለብን የሚያስረዱ «ተግባራዊ ጥበባት አሉ።» ይህ በተለይ የሚገኘው በመጽሐፈ ምሳሌ ነው። ሁለተኛው፥ የከንቱነት ጥበብ የምንለው ሲሆን፥ ትንሽ አዎንታዊ ትምህርት ኖሮት ነገር ግን የዚህን ዓለም ጥበብና ዘይቤ እንዳንከተል የሚያስጠነቅቀን ነው። ይህን የምናገኘው በመጽሐፈ መክብብ ውስጥ ነው። ሦስተኛ፣ «መከራ የሚኖረው ለምንድን ነው? መከራ ሁልጊዜ የኃጢአት ውጤት ነውን? » የሚሉትንና የመሳሰሉትን ዐበይት ጥያቄዎች የሚመረምር የፍልስፍና ጥበብ አለ። ይህም የሚገኘው በመጽሐፈ ኢዮብ ውስጥ ነው።

የተለያዩ የመዝሙር ዓይነቶች እንዳሉ ሁሉ፥ የጥበብ ጽሑፎችም በዓይነታቸው የተለያዩ ናቸው።

1. ምሳሌ፡- በጥበብ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ከሁሉም የላቀ አስፈላጊና የተለመደው መሣሪያ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው። ምሳሌ፥ ሰፊ የሆነ እውነትን በአጭር አነጋገር የሚገልጽ ነው። በምሳሌ ውስጥ ያለውን እውነት ሰዎች በቀላሉ ሊያስታውሱት በሚችሉት መንገድ በአጭሩ የቀረበ የቃላት ቅንብር ነው። የሕይወትን ሰፊ ክፍል በመውሰድ ዓለም አቀፋዊ በሆነ መመሪያ አሳጥሮ ለማቅረብ ይሞክራል። ብዙውን ጊዜ ምሳሌያዊ አነጋገርን ለመረዳት ቀላል ቢሆንም፥ እውነቱ ግን በጣም ጥልቅና በርካታ የሕይወት ተዛምዶዎችን ሊያካትት የሚችል ነው። ምሳሌያዊ አነጋገር ብዙ ጊዜ ነገሮችን በማነጻጸር ውይም በማመሳሰል ይቀርባል። ለምሳሌ፡- «እንቁላል ቀስ በቀስ በእግሩ ይሄዳል» በሚለው የተለመደ የአማርኛ ምሳሌያዊ አነጋገር ውስጥ እንቁላሉ በሕይወት ውስጥ ያለውን የተለመደ መሠረታዊ እውነታ ለመግለጥ የቀረበ ነው። ይህም መሠረታዊ እውነታ ነገሮች በመሆን ሂደት ውስጥ ለማለፍ ጊዜን ይጠይቃሉ ማለት ነው። ምሳሌዎች የሰውን ሕይወትና እውነት በአጭሩ ስለሚያቀርቡ መቶ በመቶ ትክክል ሊሆኑ አይችሉም። ይልቁንም አጠቃላይ የሆኑ መግለጫዎች ወይም የሕይወት ዝንባሌዎች ናቸው። ለምሳሌ፡- በፍጥነት የሚፈጸሙ ጉዳዮች አሉ። ሁሉም ነገር በዝግታ የሚፈጸም አይደለም፤ ይህም ማለት ከላይ የተመለከትነው ምሳሌ ሙሉ በሙሉ ትክክል ሊሆን አይችልም። 

የውይይት ጥያቄ ሀ) ከምታውቃቸው የኢትዮጵያ ምሳሌዎች አምስቱን ጥቀስ። ) ምሳሌነቱ ምንድን ነው? ሐ) ምሳሌው ሊገልጠው የሚፈልገው የሕይወት መሠረታዊ እውነታ ምንድን ነው?

ልዩ ልዩ ዓይነት ምሳሌያዊ አነጋገሮች አሉ። አንዳንዶቹ እንደሞኝ ወይም ሰነፍ ሰው በኃጢአት እንዳንወድቅ ልንጠነቀቅባቸው ስለሚገባን ነገሮች የሚያሳስቡ ናቸው (ምሳሌ 6፡20-35)። ሌላው ዓይነት ምሳሌ ሥልጣን ያለው እውነት ሆኖ የቀረበ ነው (ምሳሌ 3፡ 27)። በመጨረሻ ስለ ጥበብ መንገድ የሚናገሩ አጠቃላይ መግለጫዎች ደግሞ አሉ (ምሳሌ 18፡18፤ 20፡19)።

2. እንቆቅልሾች፡- የጥበብ ሥነ-ጽሑፎች በውስጣቸው የተሰወሩ ትርጕሞችን ያዘሉ፥ አእምሮን የሚያሠሩ ጥያቄዎች ሆነው የሚቀርቡበት ጊዜ አለ። ከእንደነዚህ ዓይነት ጽሑፎች እጅግ የታወቀው ሶምሶን ስለ አንበሳና ስለ ማር ያቀረበው እንቆቅልሽ ነው (መሳፍንት 14፡14)።

3. ተረቶች፡- ተረት ስለ እንስሳት ወይም አዝዕርት የሚናገርና በውስጡ ትምህርት ወይም እውነት የያዘ ታሪክ ነው(መሳፍንት 9፡7-20)። 

የምሳሌዎች አተረጓጐም

የምናነበውን ጽሑፍ በተገቢው መንገድ ለመረዳት ጽሑፉ በየትኛው የሥነ-ጽሑፍ ዓይነት ውስጥ እንደሚመደብ ማወቅ አስፈላጊ ነው። ምሳሌዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም የተለመዱ ስለሆኑ፥ ይህን ማድረግ ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ አይደለም። ምሳሌዎችንና የጥበብ ጽሑፎችን በምናነብበትና ለመረዳት በምንሞክርበት ጊዜ ልንከተላቸው የሚገቡን እንዳንድ መመሪያዎችን ቀጥለን እንመለከታለን፡-

1. በሕይወት ውስጥ የመከሠት ዝንባሌ ያላቸውን ነገሮች በሚገልጡና (ለምሳሌ መክብብ 8፡1)፥ በሕይወት ውስጥ ምን መሆን እንዳለበት (ምሳሌ 23፡4) በሚናገሩ ምሳሌዎች መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት ለማድረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርግ። ብዙ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምሳሌን ወይም ድርጊትን በመውሰድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጻፈ ብቻ ልንከተለው ይገባል ብለው ያስባሉ። ጉዳዩ ግን እንደዚያ አይደለም። 

2. ምሳሌዎች ሁልጊዜ መፈጸም ያለባቸው፥ ከእግዚአብሔር የተገኙ ቃል ኪዳኖች ወይም ዋስትናዎች አይደሉም። ይልቁንም የተለመዱ ዝንባሌዎች ወይም ባጠቃላይ የሚሆነውን ነገር የሚያንጸባርቁ ናቸው። በምሳሌ 15፡25 እግዚአብሔር የትዕቢተኞችን ቤት እንደሚነቅልና የባልቴትን ዳርቻ እንደሚያጸና ተጽፎአል፤ ዳሩ ግን በዚህ ምድር ላይ ትዕቢተኞችና ሀብታሞች መከራና ጉዳት እንደማይደርስባቸውና ድሆች ደግሞ ለኑሮአቸው የሚፈልጉትን ነገር እንደማያገኙ ሁላችንም እናውቃለን፤ ይህ ምሳሌ ግን እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን እንደሚቃወምና በመጨረሻም እንደሚፈርድባቸው የሚናገር አጠቃላይ መግለጫ ነው። ድሆችንም በማሰብ ይጠነቀቅላቸዋል። 

3. ማንኛውም ምሳሌ ራሱን ችሉ የሚቆም አይደለም፡፡ እውነትን በተሻለ መንገድ ለመረዳት አንድን ምሳሌ በሌላ ምሳሌና በአጠቃላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መመዘን ያሻናል። 

4. ምሳሌዎች በቀላሉ ልናስታውሳቸው እንችል ዘንድ አጠር ባለ ቅንብር የተጻፉ ናቸው፤ ስለዚህ ትክክል ሊሆኑ የማይችሉበትና የማይሠሩት ጊዜ አለ። ምሳሌዎች የመሆን ዝንባሌ ያላቸው አጠቃላይ እውነታዎች ናቸው።

5. አንዳንድ ምሳሌዎች ለባህላችን እንግዳ የሆኑ ማነጻጸሪያዎችን ይጠቀማሉ፤ ስለዚህ እነዚያ ማነጻጸሪያዎች ለአይሁድ ምን ማለት እንደሆኑ መረዳት ያስፈልገናል። ከዚህ በኋላ በራሳችን ባህል በታወቁ ማነጻጸሪያዎች ያንን እውነት እንገልጠዋለን። ለምሳሌ፥ በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በኋላ ንጉሥ ላይኖር ይችላል፤ ነገር ግን መሪዎች አሉ፤ ስለዚህ ስለ ነገሥታት የተጠቀሱ ነገሮች ለመሪዎችም ይሠራሉ (ለምሳሌ፡- ምሳሌ 22፡1)። 

6. ምሳሌዎችን ለመተርጐም በምንሞክርበት ጊዜ፥ በመጀመሪያ ማነጻጸሪያዎችን ወይም የተጻፉትን መግለጫዎች ለመረዳት መሞከር አለብን። በእነዚህ ማነጻጸሪያዎች መሠረት፥ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድና በተሻለ ሁኔታ ለመኖር የሚረዱ አጠቃላይ እውነተችን ፈልግ።

የውይይት ጥያቄ፥ ምሳሌ 20፡1-10 አንብብ። ሀ) በእያንዳንዱ ምሳሌ ውስጥ የሚገኙትን ማነጻጸሪያዎች ጥቀስ። ለ) በማነጻጸሪያዎች ውስጥ የሚገኙትን አጠቃላይ እውነቶች ጥቀስ። ሐ) እነዚህ ምሳሌዎች ከሕይወትህ ጋር ሊዛመዱ የሚችሉት እንዴት ነው?

የውይይት ጥያቄ፥ መዝሙረ ዳዊት 1 እና 121 አንብብ። እያንዳንዱን መዝሙር በሚመለከት ግጥሞችን ስለ መተርጐም በሁለተኛው ቀን ትምህርት ያየሃቸውን መመሪያዎች በመከተል፡- ሀ) በእያንዳንዱ ጥቅስ ውስጥ ምን ዓይነት ተነጻጻሪነት (ፓራለሊዝም) እንዳለ ግለጥ። ለ) በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ የሚታየው ስሜት ምንድን ነው? ሐ) [የተጠቀምክባቸውን ተምሳሌቶችን ዘርዝር። እያንዳንዳቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተመልከታቸው። መ) እነዚህ ተምሳሌታዊ መግለፃዎች ጸሐፊው ማስተማር የፈለገውን መንፈሳዊ እውነት የሚገልጹት እንዴት ነው? ሠ) እነዚህን መንፈሳዊ እውነቶች ለቤተ ክርስቲያንህ አባሎች እንዴት ታስተምራቸዋለህ? 

የውይይት ጥያቄ፥ መጽሐፈ ምሳሌ 10ን አንብብ። ሀ) ከምሳሌዎቹ ውስጥ ምን እንደተፈጸመ የሚናገሩትንና እንዴት መኖር አንዳለብን የሚናገሩትን ለይተህ ግለጽ። ለ) በምሳሌው ውስጥ ለመንፈሳዊ እውነት መሠረት በመሆን ያገለገለው ማነጻጸሪያ ምንድን ነው? ሐ) ማነጻጸሪያ መንፈሳዊ እውነቱን የሚገልጸው እንዴት ነው? መ) በእያንዳንዱ ምሳሌ ውስጥ የሚተላለፈው መንፈሳዊ እውነት ምንድን ነው? ሠ) ይህ መንፈሳዊ እውነት ከራስህ ሕይወት ወይም በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች ሕይወት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የግጥም መጻሕፍት መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) በራስህ ባህል ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የአጻጻፍ ወይም የአነጋገር ዓይነቶችን ዘርዝር። ለ) ከእነዚህ የአጻጻፍ ወይም የአነጋገር ስልቶች ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ምን ያህሎቹ ናቸው?

በእያንዳንዱ ባህል ውስጥ የተለያዩ የአጻጻፍ ወይም የአነጋገር ስልቶች ይገኛሉ። ለምሳሌ፥ ከጓደኞቻችን ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ የምንጠቀምበት የተለመደ የአነጋገር ዘይቤ አለ፤ ነገር ግን ለተናገርነው ጉዳይ አትኩሮት ለመስጠት ምሳሌያዊ አነጋገሮችን የምንጠቀምበትም ጊዜ አለ። ብዙዎቻችን በልጅነታችን የተለያዩ ተረቶችን ሰምተናል። በተለይ በኢትዮጵያ ብቻ የሚነገር የ«ሰምና ወርቅ» የአነጋገር ዘይቤ አለ። ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች፥ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚጽፉት፥ በንግግር የሚያቀርቡት ግጥም በመባል የሚታወቅ የአጻጻፍና አነጋገር ስልት አለ። በመጨረሻ መዝሙር በመባል የሚታወቁ በሙዚቃ ተቀናብረው የሚቀርቡ የተለዩ የግጥም ዓይነቶችም አሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህ ሁሉ የአነጋገር ዓይነቶች በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ እንዴት በጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ የሚያስረዱ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

ብሉይ ኪዳን በእነዚህ የአጻጻፍ ስልቶች በሙሉ ይጠቀማል። እስካሁን ድረስ ባካሄድነው የብሉይ ኪዳን ጥናታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ የተለያዩ የአጻጻፍ ስልቶች መኖራቸውን ተመልክተናል። እግዚአብሔር በሲና ተራራ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግጋት አሉ። በእስራኤል ሕዝብ ላይ የደረሰውን ታሪክ ቀጥተኛ በሆነ ቋንቋ የሚናገሩ ታሪኮችን እናገኛለን። ከዚያም በብዙ ሌሎች ቋንቋዎች ውስጥ የማይገኙ የነቢያት ጽሑፎች ብለን የምንጠራቸው፥ ለየት ባለ የአጻጻፍ ስልት የተጻፉ ጽሑፎች አሉ።

ከመጽሐፈ ኢዮብ እስከ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን የሚገኙትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የሚያካትተው ሦስተኛው ክፍል በአመዛኙ ሁለት ዓይነት የአጻጻፍ ስልቶችን ይጠቀማል። የመጀመሪያው፥ በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የምናገኘው ዓይነት የግጥም ምንባብ ሲሆን፥ ሁለተኛው ደግሞ፥ በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ የምናገኘውን ዓይነት የጥበብ ክፍል ያካተተ ነው።

ምንም እንኳ ብዙውን ጊዜ የጥበብ ጽሑፍ በመባል የሚጠራው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ባመዛኙ ግጥም፥ ቅኔና ምሳሌዎችን ያካተተ ቢሆንም፥ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ባሉት በእያንዳንዱ መጻሕፍት ውስጥ የተወሰኑ ግጥሞች፥ ቅኔዎችና ምሳሌዎች አይጠፉም። እንዲያውም የብሉይ ኪዳን አንድ ሦስተኛው ግጥም ነው። ይህ ግጥም፡- አጭር ምንባብ (ለምሳሌ ዘፍ. 4፡23-24) ወይም ሙሉ ምዕራፉ (ለምሳሌ ዘጻ.15፡1-18) ወይም (እንደ መዝሙረ ዳዊት) ሙሉ መጽሐፍ ሊሆን ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አብዛኛው የብሉይ ኪዳን ክፍል በግጥም አጻጻፍ ስልት የተጻፈው ለምን ይመስልሃል? ለ) ሰዎች እንደ ጌታችን የልደት በዓል ባሉት ልዩ ቀናት ግጥም ማንበብ የሚወዱት ለምንድን ነው? ሐ) ሰዎች በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የሚገኙ ግጥሞችን የሚወዱት ለምን ይመስልሃል?

እግዚአብሔር ከቃሉ አብዛኛውን ክፍል ለሰው ልጆች ያስተላለፈበት የሥነ ጽሑፍ መንገድ ግጥምና ቅኔ መሆኑን መገንዘብ የሚያስደንቅ ነገር ነው። ምናልባት ምክንያት ሊሆን የሚችለው ነገር ከተለመዱ ቀጥተኛ የአጻጻፍ ስልቶች ይልቅ የግጥምና የቅኔ የአጻጻፍ ስልቶች ልብን የሚያነቃቁ መሆናቸው ነው። በየትኛውም ባህል ውስጥ የሚገኙ የአብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች ተወዳጅ መጽሐፍ መዝሙረ ዳዊት የሆነው በዚህ ምክንያት ነው። የመዝሙረ ዳዊት ግጥም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም መጽሐፍ የበለጠ ስሜቶቻችንን ይገልጻል። ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅርና አክብሮት ይገልጻል፤ ሞት ወይም የተለያዩ ችግሮች በገጠሙን ጊዜ የሚሰማንን ኃዘን ይገልጻል፤ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ሊጠቀሙብን በሚሞከሩ ጊዜ የሚሰማንን የቁጣ ስሜት ይገልጻል።

ሆኖም ግን ችግሩ መዝሙረ ዳዊት ከግጥምና ከቅኔ መጻሕፍት የሚመደብና መተርጐምም ያለበት በዚሁ መልክ መሆኑን አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች መዘንጋታቸው ነው። ስለዚህ በርካታ ክርስቲያኖች በመዝሙረ ዳዊትና በሌሉች የቅዱሳት መጻሕፍት ሥነ-ግጥማዊና ቅኔያዊ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙትን ትምህርቶች በተሳሳተ መንገድ ይተረጒሙአቸዋል። በሥነ-ግጥምና በቅኔ የሚገለጹ ነገሮች ብዙ ጊዜ ምሳሌያዊ ወይም ሥዕላዊ መሆናቸውን በመዘንጋት በቀጥታ ሊተረጕሟቸው ይሞክራሉ።

ብዙ ምሁራን የግጥምና የቅኔ መጻሕፍትን በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፍሏቸዋል። የመጀመሪያው ክፍል፥ በባሕርያቸው ባመዛኙ ሥነ-ግጥማዊ የሆኑት ናቸው፤ ስለዚህ እነዚህን የግጥም መጻሕፍት ይሏቸዋል። መዝሙረ ዳዊትና መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን በአብዛኛው የግጥም መጻሕፍት ናቸው። በሁለተኛው ክፍል፥ የጥበብ መጻሕፍት የሚባሉት ናቸው፤ እዚህም የተጻፉት በግጥም ሥነጽሑፍ መልክ ቢሆንም፥ ትኩረት የሚያደርጉት ግን በጥበብና ብዙውን ጊዜ ደግሞ በምሳሌያዊ አነጋገሮች ላይ ነው። መጽሐፈ ምሳሌና መክብብ ለጥበብ መጻሕፍት ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው። 

የዕብራውያን ሥነ-ግጥምና ቅኔ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አጠር ያለ አንድ ግጥም ወይም ቅኔ ጻፍ። ለ) አንድ ደብዳቤ በመጻፍና አንድ ግጥም ወይም ቅኔ በመጻፍ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ሐ) ሰዎች ግጥምን ለመጻፍ የሚጠቀሙባቸውን የተለያዩ ሕግጋት ጥቀስ (ምሳሌ፡- በየስንኙ መጨረሻ ቤት የመምታት ጉዳይ)። 

እያንዳንዱ ባህል ስለ ግጥም ይዘት የራሱ የሆነ አመለካከት አለው። በብሉይ ኪዳን የምናገኘው የዕብራውያንን ግጥም ነው። የዕብራውያን የግጥም አጻጻፍ በእኛ ባህል ውስጥ ካለው የሥነ-ግጥም አጠቃቀም የተለየ ስለሆነ፤ የዕብራውያን የግጥም ይዘትና ሥን-ግጥማቸውን ለመቅረጽ አሳቦችንና ድምፆችን እንዴት እንደሚያቀናብሩ መረዳት አስፈላጊ ነው። የዕብራውያን የሥነ- ግጥም ቅንብር ከእኛ ባህል የሥነ-ግጥም ቅንብር የተለያየ ስለሆነ በቀጥታ ይዘቱን ሳይቀይር መተርጐም አስቸጋሪ ነው። የዕብራውያንን ሥነ ግጥም ትክክለኛና ተገቢ በሆነ መንገድ ለመተርጐም፤ አይሁድ ግጥማቸውን የሚጽፉባቸውን የተለየ መንገዶችና ከእኛ ግጥም እንዴት እንደሚለይ መረዳት አስፈላጊ ነው።

ሥነ-ግጥም ማለት የግጥም ጥበብ ማለት ነው።

አይሁድ የተለያዩ የጽሑፍ አደረጃጀቶችን በመጠቀም አስደናቂ የሆኑ ሥነ- ግጥሞችን ይጽፉ ነበር። እነዚህ የተለያዩ የአጻጻፍ መሣሪያዎች በትርጕም ሂደት ውስጥ ስለጠፉ በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ውስጥ ውበታቸውን ለማየት አለመቻላችን የሚያሳዝን ነው። ይህም ቢሆን እንኳ የዕብራውያን ግጥም በተለያዩ ሂደቶች ውስጥ አልፎ በእግዚአብሔር ፊት ስሜታችንን ይገልጻል፤ ይነካናልም። በመጀመሪያ ደረጃ የዕብራውያን ግጥም የተቀናበረው በተመሳሳይ ድምፆች ነበር። ይህ የእያንዳንዱን ስንኝ የመጨረሻ ቃል አንዱ ከሌላው ጋር በድምፅ እንዲስማማ ከሚያደርገው ከእኛ ግጥም ጋር ተመሳሳይ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ፥ አይሁድ በግጥሞቻቸው ውስጥ አሳቦች አንድ ዓይነት ሂደት እንዲኖራቸው አድርገው ያቀናብሯቸዋል። ይህ በጽሑፉ ውስጥ «ፓራላሊዝም» ተነጻጻሪነት በመባል ይታወቃል። ለምሳሌ፦ መዝሙር (103)፡10 በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈው በቀጥታ ብንተረጕመው የሚነበበው እንደሚከተለው ነው፡- «እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፤ እንደ በደላችን አልከፈለንም።» 

የዚህ መዝሙር ጸሐፊ አንድ ዓይነት ድምፅ ያላቸውን ቃላት ማቀናበር ብቻ ሳይሆን፥ የያዙትን አሳብ በማያያዝ እንዴት እንዳቀናጃቸው ልብ በል።

አይሁድ ግጥምን በሚጽፉበት ጊዜ አሳባቸውን የሚያቀርቡበት አራት መንገዶች አሉ፡-

 1. የመጀመሪያ ደረጃ፥ እጅግ የተለመደው መንገድ አንድን አሳብ በጣም ተቀራራቢ በሆኑ ቃላት መድገም ነው። ይህ «ሲኖኒመስ ፓራለሊዝም» (ተመሳሳይ የሆነ ተነጻጻሪነት) ሊባል ይችላል። ይህን ቅንብር በመዝሙር (103)፡10 እናገኛለን። በዚህ ስፍራ የግጥሙ ጸሐፊ ለአንድ አሳብ ሁለት የተለያዩ፥ ነገር ግን በእጅጉ የተያያዙ ቃላትን ይጠቀማል፤ እነዚህም ኃጢአትና በደል የሚሉ ናቸው። መዝሙረ ዳዊትን በምናነብበት ጊዜ ይህን ነገር በአትኩሮት መመልከት በጣም አስፈላጊ ነው። ጸሐፊው ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት አንድ ሆኖ ሳለ ብዙ ሰዎች ለእነዚህ ቃላት የተለያዩ ትርጕሞችን ይፈልጋሉ። ለምሳሌ፥ ጸሐፊው መዝሙር (103):3 የዚህ ዓይነቱን የግጥም ስልት ይጠቀማል፤ እዚህ ላይ «ኃጢአት» እና «ደዌ» የሚሉት ቃላትም አንድን አሳብ የሚገልጹ ናቸው። 
 2. በሁለተኛ ደረጃ፥ እጅግ የተለመደው መንገድ ሁለተኛው ስንኝ ከመጀመሪያው ስንኝ ተቃራኒ ወይም ተነጻጻሪ ሆኖ መቅረቡ ነው፡፡ (ይህ አንቲቴቲክ ፓራለሊዝም) ተቃራኒ የሆነ ተነጻጻሪነት ይባላል። ለዚህ ዓይነቱ ሥነ-ግጥም በጣም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው መዝሙረ ዳዊት 1፡6 ነው። በዚህ ስፍራ ጸሐፊው በመጀመሪያው ስንኝ የጻድቃንን መንገድ፣ በሁለተኛው ስንኝ ደግሞ የክፉዎችን መንገድ ያነጻጽራል። 
 3. በሦስተኛ ደረጃ፥ አንዳንድ ጊዜ ጸሐፊዎች በመጀመሪያው ስንኝ ምሳሌያዊ አነጋገር ወይም ተምሳሌት ይጠቀሙና በሁለተኛው ስንኝ ደግሞ ያንኑ አሳብ በቀጥተኛ ቋንቋ ይገልጹታል። ይህንንም «ሲምቦሊክ ፓራለሊዝም» ተምሳሌታዊ ተነጻጻሪነት ልንለው እንችላለን። ለምሳሌ መዝሙረ ዳዊት (42)፡1 ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ ስለ መናፈቁ በመጀመሪያው ስንኝ ይናገርና፤ በሁለተኛው ስንኝ ደግሞ ጸሐፊው ነፍሱ ወደ እግዚአብሔር እንደምትናፍቅ ይናገራል። 
 4. በአራተኛው ደረጃ፥ አንዳንድ ጊዜ ጸሐፊው የጻፈው እያንዳንዱ ስንኝ በመጀመሪያው መስመር ላይ ባለው አሳብ ላይ ጥቂት ነገርን ይጨምራል። (ኢንቴቲክ ፓራለሊዝም) ተጨማሪ የሆነ ተነጻጻሪነት ይባላል። በመዝሙረ ዳዊት (29)፡1-2 ለእግዚአብሔር ልንሰጠው ስለሚገባ ነገር በየስንኙ ጥቂት አሳቦችን ይጨምራል።

የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ግጥሞች ተመልከትና ጸሐፊው የተጠቀመባቸውን የቅንብር ዓይነቶች ጥቀስ፡- ኢሳይያስ 44፡22፤ ሆሴዕ 7፡14፤ ምሳሌ 15፡1፤ አብድዩ 21፤ ምሳሌ 4፡23፤ መዝሙረ ዳዊት (49)፡1፤ ኤርምያስ 17፡11።

አይሁድ ግጥምና ቅኔ በሚጽፉበት ጊዜ የተጠቀሙባቸው ሌሎች የአጻጻፍ ስልቶችም ነበሩ። መጀመሪያ፥ በአብዛኛው መዝሙራት ጸሐፊው በግጥሙ እያንዳንዱን ስንኝ ወይም ጥቅስ በተለያየ ፊደል ይጀምረዋል። በዕብራውያን ሆሄያት ውስጥ ሃያ ሁለት የተለያዩ የፊደል ቅርጾች ነበሩ። ለዚህ ዓይነቱ አጻጻፍ በጣም ጥሩ ምሳሌ መዝሙረ ዳዊት 119 ነው። ይህ መዝሙር በተለያዩ ክፍሎች መከፈሉን እንመለከታለን፡- የመጀመሪያው ክፍል አሌፍ፥ ሁለተኛው ክፍል ቤት ወዘተ ይላል። እነዚህ የዕብራይስጥ ፊደላት ስሞች ሲሆኑ ጸሐፊው በመዝሙሩ ውስጥ በእያንዳንዱ ስንኝ ላይ ተጠቅሞባቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ መዝሙረ ዳዊት (25) አንብብ። በዚህ መዝሙር ውስጥ ያሉት ጥቅሶች ስንት ናቸው?

ሁለተኛ ደረጃ፥ አይሁድ በመዝሙራቱ ሁሉ ቁልፍ የሆነን ስንኝ በተለየ መንገድ ይደግሙ ነበር። እነዚህ መዝሙራት በአሁኑ ጊዜ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እንደሚደረገው ይጠቀሙባቸው ነበር። በኢትዮጵያ ባህላዊ የሆነ መዝሙር ሲዘመር ሕዝቡ መሪውን እየተከተለ እንደሚዘምረው ዓይነት ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ መዝሙር 136 አንብብ። በዚህ መዝሙር ውስጥ በተደጋጋሚ የምናገኘው ሐረግ የትኛው ነው?

አይሁድ ሥነ-ግጥምና ቅኔን ለተለያዩ ሁኔታዎች ይጠቀሙባቸው ነበር። በብሉይ ኪዳን የነበሩ የሥነ-ግጥምና ቅኔ ዓይነቶች አንዳንዶቹ ቀጥሉ ተዘርዝረዋል፡

 1. ታሪካዊ ግጥሞች፥ ዘኁልቁ 21፡14፡ ኢያሱ 10፡12-13 
 2. በጠላቶች ላይ ስለተገኘ ድል የቀረቡ ግጥሞች፥ ዘጸአት 15፡1-8
 3. ሰዎችን የሚረግሙ ግጥሞች፥ ዘኁልቁ 21፡27-30 
 4. በቀብር ሥነ-ሥርዓት የሚቀርቡ ግጥሞች፥ 2ኛ ሳሙኤል 1፡17-27
 5. መለኮታዊ ጥበብን የሚገልጡ ግጥሞች፥ መዝሙር 1 (37) 
 6. ለነገሥታት የሚቀርቡ ግጥሞች፥ መዝሙር (20) 
 7. እግዚአብሔርን ለማምለክ የሚቀርቡ ግጥሞች፣ መዝሙር 8 
 8. በእግዚአብሔር ላይ መታመንን የሚገልጡ ግጥሞች፥ መዝሙር (1)
 9. እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ ግጥሞች፥ መዝሙር (18) 
 10. የኃዘን ግጥሞች፥ መዝሙር(27)፣ 28) 
 11. ንስሐ መግባትን የሚገልጡ ግጥሞች፣ መዝሙር (32) 
 12. ስለ ፍቅር የተገጠሙ ግጥሞች፣ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 4፡1-7 
 13. ስለ ጋብቻ የተገጠሙ ግጥሞች፥ መዝሙር (45) 
 14. የትንቢት ግጥሞች፥ ዘፍጥረት 49፡1-27። 

በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የሚገኙ ግጥሞች የሚነበቡ ብቻ አልነበሩም ነገር ግን መዝሙረ ዳዊት የአይሁድ የመዝሙር መጽሐፍ ነበር። እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ለማምለክ ይረዳቸው ዘንድ የተጻፈ ነበር፤ ስለሆነም አብዛኛዎቹ በጉባኤያቸው እንዲዘመሩ የተጻፉ ነበሩ። ሌሎቹ ደግሞ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት በሚያቀርቡበት ጊዜ የሚያገለግሉ ነበሩ። 

ግጥሞችን ለመተርጐም የሚረዱ መመሪያዎች 

 1. ግጥሞችና ቅኔዎች ታልመው የሚጻፉት ከአእምሮአችን ይልቅ ለስሜታችን ነው፤ ስለዚህ በሥነ-ግጥም አማካይነት ስሜታችን ጠልቆ እንዲሰማውና እንዲነካ መፍቀድ አለብን። እያንዳንዱን ቃልና አሳብ በአእምሮ እውቀት አስቀድመን ለመረዳት መሞከር የለብንም። ሥነ-ግጥምን በምናነብበት ጊዜ ጸሐፊው ግጥሙን በሚጽፍበት ወቅት የተሰማውን ስሜት እንዲሰማን ያስፈልጋል። ጽሑፉን በሚጽፍበት ጊዜ የነበረው ዝንባሌ ወይም ውስጣዊ ስሜት ምን እንደነበረ መረዳት ያስፈልገናል። በግጥሙ ውስጥ ሊገልጥ የፈለገው ስሜት ቁጣ፥ ፍቅር፥ አክብሮት፥ ምስጋና ወይም ኃዘን የመሳሰለውም መሆኑን ለመወሰን መሞከር አለብን። ይህም ግጥሙን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ያስችለናል።

የውይይት ጥያቄ፥ መዝሙር (102) አንብብ። ሀ) የዚህ መዝሙር ጸሐፊ ይህንን መዝሙር በሚጽፍበት ጊዜ የነበረው ስሜት ምን ይመስልሃል? ለ) ይህን ነገር አንዳንድ ጊዜ በተመሳሳይ መንገድ ተሰምተህ የሚያውቀው እንዴት ነው?

 1. ግጥሞች ብዙውን ጊዜ የሚጻፉት በተምሳሌት እንጂ በቀጥተኛ ቋንቋ አይደለም። በሕይወት ውስጥ ተምሳሌታዊ እውነቶችን የሚገልጡ በርካታ ነገሮችን ይጠቀማል። ለምሳሌ፥ በመዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 1 ውስጥ ጸሐፊው ስለ ዛፎች፥ የውኃ ፈሳሾች፥ ገለባና ፍርድቤት ይናገራል። የጸሐፊው ዋና ፍላጎት እነዚህን ነገሮች መግለጥ አይደለም፤ ነገር ግን ጸሐፊው አንባቢዎቹ እንዲያውቁትና እንዲሰማቸው ወደሚፈልገው መንፈሳዊ እውነቶች የሚጠቁሙ ምልክቶች ናቸው። በግጥም ውስጥ፥ ጸሐፊዎች የሚናገሩአቸውን ነጥቦች አጉልቶ ለማሳየት ሲባል አንዳንድ ጊዜ የተጋነኑ የንግግር ዘይቤዎችን ይጠቀማሉ። ጸሐፊው የሚጽፈው፥ ሰዎች አሳቡን በሙሉ ይቀበሉታል በማለት አልነበረም። ለምሳሌ፥ በመዝሙር (42)፡3 ጸሐፊው በእርግጥ እንባውን እንደተመገበ መናገሩ ሳይሆን በገጠመው ከፍተኛ ኃዘን ምክንያት ብዙ እንዳለቀሰ መግለጡ ነው።

በሌላ ጊዜ ደግሞ ጸሐፊዎች ሰብአዊ ያልሆኑ ነገሮችን ልክ ሰብአዊ እንደሆኑ አድርገው ይናገራሉ። ለምሳሌ፥ በመዝሙር (85)፡10 ምሕረትና እውነት እንደ ሁለት ጓደኛሞች ሲገናኙና፥ ጽድቅና ሰላም ሲስማሙ እንመለከታለን። በሌላ ቦታ ደግሞ ዛፎችና ድንጋዮች እንደዘመሩና በእጆቻቸው እንዳጨበጨቡ ተጽፎ እናነባለን። እነዚህን ሁሉ ማድረግ የሚቻለው በሥነ- ግጥም ብቻ ነው።

ይህም ማለት ሥነ-ግጥምን በተለየ ሁኔታ መተርጐም ይኖርብናል ማለት ነው። የምናተኩረውም ቀጥተኛ ትርጕሙን በማግኘቱ ላይ ሳይሆን፥ በተምሳሌታዊ ትርጕሙ ላይ ነው፤ ለዚህ ነው ስለ እግዚአብሔር በምናነብበት ጊዜ እጆች፥ ዓይኖችና አፍ እንዳሉት ሆኖ የምንመለከተው። እግዚአብሔር መንፈስ እንደሆነና ሥጋዊ አካል እንደሌለው እናውቃለን። በሥነ- ግጥም ውስጥ ግን እግዚአብሔር ከሰው ሥጋዊ አካል ጋር ተነጻጻሮ ቀርቧል። በተጨማሪም እግዚአብሔር እረኛ፥ አምባ፥ ዓለትና መሸሸጊያ ተብሉ ተጠርቷል።

ሥነ-ግጥማዊ ይዘት ያላቸውን ጽሑፎች በሚገባ ለመረዳት ተምሳሌታዊ መግለጫ ሆኖ የቀረበውን ጉዳይ በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። እግዚአብሒር ዓለት ነው፥ መጠለያ ነው፥ እረኛ ነው ማለት ምን ማለት ነው? እነዚህ ተምሳሌታዊ አባባሉች ለጸሐፊውና ለመጀመሪያዎቹ ጻሐፊዎች ምን ትርጕም እንደነበራቸው በሚገባ ጠይቀን መረዳት አለብን። ዛሬ ለእኛ የሚሆነውን ተምሳሌታዊ አባባል እውነተኛ ትርጉም ለመረዳት የምንችለው ከዚህ በኋላ ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር ዓለትና መሸሽጊያ ነው ማለት ምን ማለት ነው? መዝሙር (18)፡2፤ (31)፡2 ተመልከት። እነዚህን ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተመልከት።

 1. በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የሚገኙ መዝሙሮች ብዙ ጊዜ ስሜቶቻችንን ለመግለጽ የተጻፉ ሙዚቃዊ ግጥሞች ናቸው። በአእምሮአዊ እውቀት ላይ የተመሠረቱ እውነቶችን ለመግለጽ የተጻፉ አይደሉም፤ ስለዚህ የመሠረታዊ እምነት ትምህርታችንን በግጥም ወይም በመዝሙር ላይ ከመመሥረት መጠንቀቅ ይኖርብናል።
 2. በግጥም መልክ በተጻፈ አንድ ጥቅስ ላይ ብዙ ትኩረት ማድረግ የለብንም። አንድ ግጥም ሲጻፍ እውነተኛው የጸሐፊው ትርጕም የሚገኘው በጠቅላላው ግጥም ውስጥ እንጂ በአንድ ጥቅስ ላይ አይደለም። በአንድ ጥቅስ ላይ ብዙ ካተኮርን፥ ጸሐፊው እንድናስብ ከሚፈልገው በላይ በመሄድ የጽሑፉን ሃሳብ ልንስት እንችላለን።
 3. ቢቻል ጸሐፊው ያንን ግጥም እንዲጽፍ ያስገደደው ወይም ያነሣሣው ነገር ምን እንደሆነ ለመወሰን ሞክር። አንዳንድ ጊዜ በግጥሙ መጀመሪያ ግጥሙ መቼ እንደተጻፈ የሚያሳይ ፍንጭ እናገኛለን። ለምሳሌ፥ መዝሙረ ዳዊት (51) የተጻፈው ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ኃጢአት ካደረገ በኋላ ነው። ግጥሙ የተጻፈበትን ሁኔታ ማወቅ ግጥሙን የበለጠ ለመረዳት ይጠቅማል።
 4. አብዛኛዎቹ ሙዝሙራት በአምልኮና በእግዚአብሔር ላይ የሚያተኩሩ ስለሆኑ፥ በዚያ መዝሙር የቀረበው የእግዚአብሔር ሥዕላዊ ሁኔታ ምን እንደሆን ወስንና ለዚያ ባሕርይ ልብህ እግዚአብሔርን እንዲያመልክ ፍቀድለት።

ሥነግጥምን በትክክል ለመረዳት የሚከተሉትን አምስት ነገሮች ማድረግ ይጠቅማል፡- 

 1. በዚያ ግጥም ውስጥ ጸሐፊው ያለውን ስሜት ለመረዳት ሞክር። የግጥሙ ምሳሌ ሊያሳይ ወደሚሞክረው ስሜት ውስጥ ለመግባት ሞክር። በዓይነ ሕሊናህ ጸሐፊው የተመለከተውን ተመልከት፤ እርሱ የነካቸውን ነገሮች ለመንካትና የተሰማውን ስሜት ለማግኘት ሞክር።
 2. ጸሐፊው የተጠቀመባቸውን የተለያዩ ተምሳሌታዊ አባባሎች ለይተህ አውጣ። እነዚህን አባባሎች ዛሬ አንተ በተረዳኸው መንገድ ሳይሆን፥ ከእስራኤላውያን ግንዛቤ ጋር በሚዛመድ መልኩ ማወቅህን አረጋግጥ። ግልጽ ያልሆኑልህን ምሳሌዎች ለመረዳት የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ወይም ትርጓሜ ለመጠቀም ሞክር። 
 3. ከምሳሌያዊ ወይም ከተምሳሌታዊ አባባሎቹ መካከል ጸሐፊው ሊያተኩርበት የሚሞክረው ክፍል የትኛው እንደሆን ወስን። ለምሳሌ፥ ጸሐፊው እግዚአብሔር ዓለት ነው የሚል ከሆነ፥ በዚህ አባባሉ ለማመልከት የፈለገው ነገር ምንድን ነው? እግዚአብሔር የማይለወጥና በማንኛውም ጊዜ ልንታመንበት የምንችል አምላክ እንደሆነ ነው ወይስ ጠንካራና ወደ እርሱ ጠልቀን ልንገባ የማንችል እንደሆን ነው? ማንኛውም ተምሳሌታዊ አባባል የሚገለጠውን ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ሊወክል አይችልም፤ ስለዚህ ተምሳሌቱ የሚያመለክተውን ጉዳይ በመቀበል የማይመለከተውን ክፍል ግን መተውን ተማር።
 4. «ጸሐፊው ሌሎች ተምሳሌቶችን ትቶ ይህን የተጠቀመው ለምንድን ነው?» ብለህ ራስህን ጠይቅ፤ ይህ የተምሳሌቱን ትርጒም ለመረዳት ይጠቅምሃል።
 5. ተምሳሌቱን ከእውነተኛው ትምህርት ለመለየት መቻልህን አረጋግጥ። ተምሳሌቱን እንደ እውነተኛው ትምህርት ካየነው፥ መዝሙሩን በተሳሳተ መንገድ ልንተረጉመው እንችላለን። «ይህ ነገር ተምሳሌት ነው ወይስ እውነተኛው ጭብጥ?» ብለህ ራስህን ጠይቅ።

የውይይት ጥያቄ፥ መዝሙረ ዳዊት (42) አንብብ። ሀ) ጸሐፊው ይህንን መዝሙር በሚጽፍበት ጊዜ የነበረውን መሠረታዊ ስሜት ለመግለጽ አጭር ዐረፍተ ነገር ጻፍ። ለ) ጸሐፊው የፈለገው መሠረታዊ እውነት ምንድን ነው? 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የታሪክ መጻሕፍት

መጽሐፈ ኢያሱ፡- መጽሐፈ ኢየሱ በጠላት ላይ ስለሚገኝ ድል የሚናገር መጽሐፍ ነው። እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የከነዓንን ምድር ርስታቸው አድርጎ ሊሰጣቸው ቃል ኪዳን ገብቶላቸው ነበር፤ ነገር ግን በከነዓን ድል መነሣት የነበረባቸው በርካታ ጠላቶች ነበሩ። መጽሐፈ ኢያሱ ሕዝቡ ጠላቶቻቸውን እንዲያሸንፉና የተስፋይቱን ምድር እንዲወርሱ እግዚአብሔር እንዴት እንደረዳቸው ይገልጻል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ ክርስቲያን ሊያሸንፋቸው ወይም ድል ሊያደርጋቸው የሚገባው ጠላቶች እነማን ናቸው? (ኤፌሶን 6፡12 ተመልከት)። ለ) እነዚህን ጠላቶች ልናሸንፍ የምንችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

መጽሐፈ መሳፍንት፡- መጽሐፈ መሳፍንት የእግዚአብሔርን ሕዝብ አለመታዘዝ የሚያሳይ አሳዛኝ ታሪክ ነው። ይህ መጽሐፍ «ሰውም ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር» (መሳፍንት 17፡6) በሚለው ቃል ሊጠቃለል ይችላል። እግዚአብሔር መንገዳቸውን የለቀቁ ልጆቹን በጠላቶቻቸው እንዲሸነፉና በባርነት ቀንበር እንዲወድቁ በማድረግ፥ የሥነ-ሥርዓት ቅጣትን እንዴት እንደቀጣቸው የሚያሳይ ታሪክ ነው፤ ነገር ግን መሳፍንትን በመጠቀም እግዚአብሔር ከጠላቶቻቸው የባርነት ቀንበር እንዴት ነፃ እንዳወጣቸው የሚናገርም ታሪክ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ አንታዘዝም በምንልባቸው ጊዜያት እግዚአብሔር አንዳንዴ እንድንሸነፍ የሚፈቅደው እንዴት ነው?

መጽሐፈ ሩት፡- በዘመነ መሳፍንት የተፈጸመው የሩት ታሪክ ከፍተኛ የክፋት ሥራ በሞላበት ሁኔታ ውስጥ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው የሚኖሩ ሰዎች እንደሚገኙ የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው። ሩት የተባለችው ከአሕዛብ ወገን የሆነች ሴት እግዚአብሔርን በመከተልዋ የታላቁ የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት አያት የመሆን ሽልማት እንዳገኘች የሚናገር ታሪክ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ አብዛኛው ሕዝብ እግዚአብሔርን መከተል በተወበት ጊዜ እንኳ ለእግዚአብሔር ታማኞች መሆን ያለብን እንዴት ነው?

1ኛ ሳሙኤል (መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ)፡- መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ እስራኤል በአንድ ንጉሥ ሥር እስከቆየችበት፥ እስከተባበረው የእስራኤል መንግሥት ድረስ ያለውን የሽግግር ወቅት ታሪክ የሚሸፍን ነው። የመጨረሻው መስፍን የነበረው የሳሙኤልና የመጀመሪያው ንጉሥ የነበረው የሳኦልን ታሪክ የሚናገር ነው። የመጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ አብዛኛው ክፍል ሳኦልን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ይነግሥ ዘንድ ከተመረጠውና የመልካም ንጉሥ የላቀ ምሳሌ ከሆነው ከዳዊት ጋር ያወዳድረዋል። ሌሎች የእስራኤል ነገሥታት በሙሉ የሚመዘኑት ዳዊትን በመምሰላቸው ወይም ባለመምሰላቸው ነበር። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ የሚጠናቀቀው በሳኦል ሞት ነው።

2ኛ ሳሙኤል (መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ)፡- መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊና ካልዕ መጀመሪያ በታላቁ ንጉሥ በዳዊት ላይ የሚያተኩር አንድ መጽሐፍ ነበር። መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ ስለ ዳዊት መንገሥ የሚናገር መጽሐፍ ነው። ዳዊት በአሕዛብ ሁሉ ላይ ስላገኛቸው ታላላቅ ድሎችና የእስራኤልን ድንበር ከግብፅ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ እንዳሰፋ ይናገራል። የዳዊት ታሪክ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን በመግባቱ ሲሆን፥ በዚህ ቃል ኪዳን በእስራኤል ላይ ንጉሥ የመሆንን ሥልጣን ለዘሩ ሰጥቶአል። የመጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ ሁለተኛ ክፍል ግን ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር የፈጸመው ኃጢአት ያስከተላቸው ውጤቶች የተዘረዘሩበት ነው። ይህ ኃጢአት የቤርሳቤህ ባል የኦርዮንን ሞት አመጣ፤ በድጋሚም ከዳዊትና ከቤርሳቤህ የተወለደውን የመጀመሪያ ልጅ ቀሰፈ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዳዊት ቤት ላይ ችግር በዛ። የዳዊት ሴት ልጅ በግድ ተደፈረች፤ አቤሴሉም ወንድሙን ገደለ፤ ቀጥሉም በአባቱ በዳዊት ላይ ዓመፀ፤ ከዚያም አቤሴሎም ተገደለ። ዳዊት እንደ እግዚአብሔር ልብ የሆነ ሰው ነበር (የሐዋርያት ሥራ 13፡22)። ይህ ማለት እግዚአብሔርን በከፍተኛ ደረጃ የሚወድና በሙሉ ልቡ እርሱን ለመከተል የጣረ ሰው ነበር ማለት ነው እንጂ ዳዊት ፍጹም ነበር ማለት አይደለም።

የውይይት ጥያቄ፥ እንደ እግዚአብሔር ልብ መሆንን በሚመለከት ከዳዊት በሕይወት ውስጥ ከምንማራቸው ትምህርቶች አንዳንዶቹን ዘርዝር። 

1ኛና 2ኛ ነገሥት (መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊና ካልዕ)፡- እነዚህ ሁለት መጻሕፍት የእስራኤል ነገሥታትን ታሪክ ይናገራሉ። ለእግዚአብሔር ትልቅ ቤተ መቅደስ ስለሠራው ስለ ሰሎሞን ታሪክ ይናገራሉ፤ ነገር ግን የሚያሳዝነው ሰሎሞን ሐሰተኞች አማልክትን ማምለክ ጀመረ። ከሰሎሞን ሞት በኋላ እግዚአብሔር በመፍረዱ መንግሥቱ በሰሜን- እስራኤል፥ በደቡብ-ይሁዳ ተብሎ ለሁለት ተከፈለ፡ እነዚህ መጻሕፍት በሁለቱም መንግሥታት የነበሩትን ነገሥታት ታሪክ እግዚአብሔርን ይወድ ከነበረው ንጉሥ ከዳዊት ጋር በተናጠል በማወዳደር ያጠቃልላሉ። እነዚህ መጻሕፍት የእግዚአብሔር ሕዝብ የእግዚአብሔርን ሕግ ባለመቀበላቸውና ባለመታዘዛቸው ምክንያት የሰሜኑ መንግሥት በአሦር፥ የደቡቡ መንግሥት ደግሞ በባቢሎን ስለ መጥፋታቸው ይናገራሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ እግዚአብሔርን ስለ መተውና እርሱን ባለመታዘዝ ስለ መኖር የሚያስጠነቅቀን እንዴት ነው?

1ኛና 2ኛ ዜና መዋዕል (መጽሐፍ ዜና መዋዕል ቀዳማዊና ካልዕ)፡- እንደ ሳሙኤልና ነገሥት መጻሕፍት፥ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊና ካልዕም አንድ መጽሐፍ ነበሩ። እነዚህ መጻሕፍት የሳሙኤል ካልዕንና የነገሥት ቀዳማዊና ካልዕ መጽሐፍትን ታሪክ ይደግማሉ። የዳዊትን፥ የሰሎሞንና የይሁዳ ነገሥታትን ታሪክ በድጋሚ የሚናገሩ ናቸው። ይሁን እንጂ የዜና መዋዕል መጽሐፍ ታሪኩን የሚያቀርበው ከሃይማኖታዊ አመለካከት አንጻር ነው። በነገሥታቱ መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ያተኩራል። በመልካም ምሳሌነቱ ዋና ተጠቃሽ ለሆነው ለንጉሥ ዳዊት በእስራኤል ስለሰጠው መንፈሳዊ አመራር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶአል። በተጨማሪ የሰሎሞን ቤተ መቅደሱን የመገንባቱ ታሪክ ተጽፎአል። ከነገሥታት መጻሕፍት በተቃራኒ የይሁዳ ነገሥታትን ታሪክ እንጂ የእስራኤልን ነገሥታት ታሪክ አይናገርም።

ዕዝራ፡- የዕዝራ መጽሐፍ የሚናገረው ከባቢሎን ምርኮ ስለተመለሱ አይሁዶች ታሪክ ነው። አይሁዶች ቤተ መቅደሱን ለመሥራት ስለወሰዱት እርምጃ ፥ ስለገጠማቸው ተቃውሞና ስለ ቤተ መቅደሱ ሥራ መጠናቀቅ ይናገራል። በተጨማሪ በዕዝራ መሪነት ስለተካሄደው መንፈሳዊ መነቃቃት ይናገራል።

መጽሐፈ ነህምያ፡- ይህ መጽሐፍ አስቀድሞ ከመጽሐፈ ዕዝራ ጋር በአንድነት ተጠቃልሉ ይገኝ የነበረ ነው። አይሁድ ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ ስለነበረው ጊዜ ታሪክ መናገሩን ይቀጥላል። የመጽሐፈ ነህምያ ትኩረት በኢየሩሳሌም ቅጥር እንደገና መሠራትና በነህምያ መሪነት በኢየሩሳሌም በተካሄደው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ላይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአይሁድ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ፈሪሀ-እግዚአብሔር የተሞላበት አመራር የተጫወተው ሚና ምንድን ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ መንፈሳዊ መነቃቃትን ለማበረታታት የቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች ምን ማድረግ አለባቸው?

መጽሐፈ አስቴር፡- በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ የታሪክ መጻሕፍት የመጨረሻው መጽሐፈ አስቴር ነው። በአቀማመጥ ቅደም ተከተል የመጨረሻው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ቢሆንም፥ በብሉይ ኪዳን በእስራኤል ታሪክ ውስጥ የተፈጸመውን የመጨረሻ ክሥተት የሚናገር አይደለም። ይልቁንም የመጽሐፈ አስቴር ታሪክ የተፈጸመው በመጽሐፈ ዕዝራ ታሪክ መካከል ነበር። መጽሐፈ አስቴር አይሁዳውያን በፋርስ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከመደምሰሳቸው በፊት፥ እግዚአብሔር ፡ በአንዲት አይሁዳዊት ሴት በመጠቀም እንዴት እንዳዳናቸው ይናገራል። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመጠበቅ ኢምንት በሚመስሉ ድርጊቶች ውስጥ እንዴት እንደሚሠራ የሚያሳይ ታሪክ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ተራ በሚመስል ድርጊት ውስጥ የእግዚአብሔር እጅ ሕይወትህን ለመጠበቅ ሲሠራ ያየኸው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ፔንታቱክ፣ የብሉይ ኪዳን የክፍል አንድ ጥናት ክለሳ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተመደቡባቸውን አራት የተለያዩ ክፍሎች ጥቀስ። ለ) በእነዚህ አራት የተለያዩ ክፍሎች የሚመደቡትን መጻሕፍት ዘርዝር።

ሠላሳ ዘጠኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ ነው። የመጀመሪያው መጽሐፍ ኦሪት ዘፍጥረት በሙሴ በ1400 ዓ.ዓ. ተጻፈ። የመጨረሻው መጽሐፍ ትንቢተ ሚልክያስ ደግሞ በ400 ዓ.ዓ. አካባቢ ተጻፈ።

ብሉይ ኪዳን በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ሊከፈል ይችላል፡-

 1. ፔንታቱክ ወይም የሙሴ መጻሕፍት፡- ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ኦሪት ዘዳግም ያሉት የመጀመሪያ አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት በሙሴ ነው ተብሎ ይታመናል። አይሁድ እነዚህን አምስት መጻሕፍት እንደ አንድ ክፍል ያዩዋቸዋል። እነዚህ መጻሕፍት ለቀሪው የብሉይ ኪዳን ክፍል መሠረት ስለሚጥሉ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ የብሉይ ኪዳን መጻሕት መካከል ነበሩ፡
 2. የታሪክ መጻሕፍት፡- የሚቀጥሉት አሥራ ሁለቱ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ የደቡቡ የይሁዳ መንግሥት ከምርኮ በመመለስ ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እስከሠራበት ጊዜ ያለውን የእስራኤልን ታሪክ የሚናገሩ ናቸው (ኢያሱ – ዕዝራና ነህምያ)። በመጀመሪያው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ጥናታችን ውስጥ እነዚህን ሁለት ክፍሉች ተመልክተናል። 
 3. የግጥምና የቅኔ ወይም የጥበብ መጻሕፍት፡- ሦስተኛው የብሉይ ኪዳን ክፍል ሁለት ዐበይት መጠሪያዎች አሉት። አንዳንዶች የግጥምና የቅኔ መጻሕፍት ብለው ሲጠሩት፥ ሌሎች ደግሞ የጥበብ መጻሕፍት በማለት ይጠሩታል። ይህ ክፍል ከኢዮብ እስከ መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን ያሉትን አምስት መጻሕፍት ይይዛል። 
 4. ነቢያት፡- የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የመጨረሻ ዐቢይ ክፍል አሥራ ሰባት የነቢያት መጻሕፍትን ይዟል። እነዚህ አሥራ ሰባት የነቢያት መጻሕፍት በተጨማሪ በሁለት ክፍሎች ይከፈላሉ። የመጀመሪያው ክፍል አምስት ትልልቅ የነቢያት መጻሕፍትን የያዘ ሲሆን እነዚህ መጻሕፍት ከኢሳይያስ እስከ ዳንኤል ያሉት ናቸው። ትልልቅ የነቢያት መጻሕፍት የተባሉበት ምክንያት ረጃጅም ስለሆኑና መልእክታቸው ከሌሉች የነቢያት መጻሕፍት ይልቅ ጥልቀት ያለው ስለሆነ ነው። ሁለተኛው የነቢያት መጻሕፍት ክፍል ደግሞ ታናናሽ የነቢያት መጻሕፍት የሚባል ሲሆን፥ ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ ያሉ አሥራ ሁለት መጻሕፍትን የያዘ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የፔንታቱክን አምስት መጻሕፍት ዘርዝር። ለ) የእነዚህ መጻሕፍት ጸሐፊ ማን ነበር? ሐ) በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ዋና ታሪክ ወይም ትምህርት ምንድን ነው?

ፔንታቱክ 

ፔንታቱክ ወይም የመጀመሪያዎቹ አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት በሙሴ እንደሆነ ይታመናል። እነዚህ መጻሕፍት የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ ከመጀመሪያው ከአብርሃም አንሥቶ፥ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ፍጻሜ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት እስከተዘጋጁበት ጊዜ ድረስ ያለውን የሚያጠቃልሉ ናቸው።

ኦሪት ዘፍጥረት፡- ኦሪት ዘፍጥረት ስለ ነገሮች ጅማሬ የሚናገር መጽሐፍ ነው። ኦሪት ዘፍጥረት የአብዛኛዎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶች የሚያስተዋውቀን መጽሐፍ በመሆኑ፥ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረት የሚጥል መጽሐፍ ነው። ዓለም እንዴት በእግዚአብሔር እንደተፈጠረ፥ ኃጢአት ወደ ዓለም እንዴት እንደገባ፥ የተለያዩ ነገዶች የተገኙት እንዴት እንደሆነ ይገልጥልናል። ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር ምርጥ የሆነው የእስራኤል ሕዝብ ጅማሬ እንዴት እንደነበር ይገልጻል። የእስራኤል ሕዝብ አባትና የክርስቲያኖች መንፈሳዊ አባት ስለሆነው ስለ አብርሃም ይናገራል። እንዲሁም ስለ ሌሉቹ የእስራኤል ሕዝብ አባቶች ማለትም ስለ ይስሐቅና ያዕቆብ ይነግረናል። ያዕቆብ የአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች አባት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ ከሚገኙ ዐበይት መንፈሳዊ ትምህርቶች አንዳንዶቹን ጥቀስ።

ኦሪት ዘጸአት፡- የኦሪት ዘጸአት መጽሐፍ የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ሲናገር የቆየውን የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ ከ400 ዓመታት ልዩነት በኋላ በመቀጠል ይተርካል። በግብፅ ስለነበረባቸው የባርነት ቀንበር፥ እግዚአብሔር ከባርነት እንዴት ነፃ እንዳወጣቸውና በሲና ተራራ ከእነርሱ ጋር በመገናኘት ቃል ኪዳንን እንዳደረገ ይናገራል። የኦሪት ዘጸአት ታሪክ ለእስራኤላውያን እጅግ ጠቃሚ ነበር። ስለሆነም የግጥምና የቅኔ እንዲሁም የነቢያት መጻሕፍት ጸሐፊዎች በተደጋጋሚ ከኦሪት ዘጸአት ይጠቅሱ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ፥ እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት በእግዚአብሔር የመዋጀታቸው ታሪክ እግዚአብሔር እንዴት ሕዝቡን ያለማቋረጥ ከመከራቸው እንደሚያድናቸው ለአይሁድ የሚያሳይ ምሳሌ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት አሥር ተአምራትን የተጠቀመበት መንገድ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ አስደናቂ ተአምራትን በማድረግ ከጎናቸው እንደሚቆም ዋስትና ነበር። በሦስተኛ ደረጃ፥ እግዚአብሔር ታላቅነቱን ያሳየበትና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን የጀመረበት የሲና ተራራ ገጠመኝ፥ እስራኤላውያንን የእግዚአብሔር ልዩ ሕዝብ እንደሆኑ በማሳየት አበረታትቶቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ከላይ የተመለከትናቸው ሦስቱ እውነቶች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለክርስቲያኖች የሚታዩት እንዴት ነው?

ኦሪት ዘሌዋውያን፡- ኦሪት ዘሌዋውያን ስለ አምልኮና ስለተቀደሰ አኗኗር ሕግጋት የሚናገር ነው። የኦሪት ዘሌዋውያን አብዛኛው ክፍል የሕግጋትን ዝርዝር የያዘ ነው። እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ለማምለክ ማቅረብ ስለነበረባቸው የተለያዩ መሥዋዕቶች ይገልጻል። የአምልኮውን ሥርዓት ለመምራት ስለተመረጡት ካህናትና ሌዋውያን ይገልጻል። በመጨረሻም የእግዚአብሔር ሕዝብ በዙሪያው ከሚኖሩ ሕዝብ የሚለይባቸውን በርካታ የተለያዩ ሕግጋት ይሰጣል። እነዚህ ሕግጋት የእግዚአብሔርን ቅድስናና ሕዝቡም ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ እንደሚፈልግ ያሳያሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ጴጥሮስ 1፡15-16 ኣንብብ። ሀ) በዚህ ስፍራ ከኦሪት ዘሌዋውያን ትምህርት ጋር ተመሳሳይ ሆኖ የተሰጠው ትእዛዝ ምንድን ነው? ለ) በዚህ ዘመን ክርስቲያኖች ቅዱሳን እንደሆኑ የሚያሳዩባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

ኦሪት ዘኁልቁ፡- ኦሪት ዘኁልቁ እስራኤላውያን ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ መንከራተታቸውን ይገልጻል። የእስራኤልን ሕዝብ ዓመፀኛነት በሚያመለክቱ አሳዛኝ ታሪኮች የተሞላ ነው። እግዚአብሔር የሚቀጥለው የእስራኤል ትውልድ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገባ ከመፍቀዱ በፊት፥ የመጀመሪያው ትውልድ በሙሉ በምድረ-በዳ እንዳለቀ የሚናገር ታሪክ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ የክርስትና ሕይወትህ ብዙ ጊዜ የኦሪት ዘኁልቁን ታሪክ የሚመስለው እንዴት ነው?

ኦሪት ዘዳግም፡- ኦሪት ዘዳግም በሲና ተራራ ለአይሁዳውያን የተሰጣቸው ሕግ በክለሳ መልክ የቀረበበት ነው። ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ለተዘጋጀው ለአዲሱ ትውልድ ሕጉን ደግሞ ተናገረ። ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግ ካልታዘዙና እግዚአብሔርን ካላወቁት፥ እግዚአብሔር እንደሚቀጣቸውና የገባላቸውን የተስፋ ቃል እንደሚያጡ ሙሴ ያውቅ ስለነበር የእግዚአብሔርን ሕግ ማወቃቸውን ለማረጋገጥ ፈለገ።

የውይይት ጥያቄ፥ ክርስቲያኖችም እግዚአብሔርን ካልታዘዙ በረከትን ሊያጡ የሚችሉት እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)