የመጽሐፈ ዕዝራ ዋና ዋና ትምህርቶች 

 1. መጽሐፈ ዕዝራ እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን በመጠበቅ ረገድ ታማኝ እንደሆነ ያስተምረናል። 

እግዚአብሔር የአይሁድን ሕዝብ ከማስማረኩ በፊት፥ እንደሚመልሳቸው ተስፋ ሰጥቶአቸው ነበር (ኢሳ. 43፡1-7፤ ኤር. 29፡10 ተመለክት)። ኢየሩሳሌም ከተደመሰሰች ከ50 ዓመታት በኋላ እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ለመፈጸም በአንድ አረማዊ ንጉሥ ተጠቀመ። እግዚአብሔር ሕዝቡ ታማኝ ባልነበሩበት ሰዓት እንኳ ታማኝ ነበረና፥ ዛሪም በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ብንሠራም እንኳ፥ ሙሉ ለሙሉ እንደማይጥለን ዋስትና ሊኖረን ይችላል። እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን ለእኛ በመፈጸም እጅግ የዘገየ ቢመስልም፥ ሰራሱ ጊዜና ፍቅር በተሞላ መንገድ እንደሚፈጽምልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ነገር ግን እግዚአብሔር ሊባርካቸው የሚፈቅደው፥ ወደ እርሱ በንስሐ ለመመለስ የሚፈቅዱትን ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ ከኃጢአታቸው ተመልሰው ንስሐ በሚገቡበት ጊዜ እግዚአብሔር ለእነርሱ ሊሰጣቸው የሚፈልገውን በረከት ይመልስላቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የእግዚአብሔርን ታማኝነት በሕይወትህ የተለማመድከው እንዴት ነው? ምሳሌዎችን ጥቀስ። ለ) ስለዚህ ጉዳይ እርሱን ለማመስገን ጊዜ ወስን። 

 1. እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የፈረሱትን ነገሮች እንደገና ለማነጽና ለማደስ እንዴት እንደሚሠራ መጽሐፈ ዕዝራ ያስተምረናል። መጽሐፈ ዕዝራ ስለ ቤተ መቅደሱና ስለ እግዚአብሔር ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት እንደገና መታነጽ ያስተምረናል። የእግዚአብሔር ሕዝብ በመታዘዝ ለመኖር እግዚአብሔር በኃይል እንዲጠቀምባቸው በሚፈልግበት ጊዜ ሰይጣን ይህንን ነገር የማስቆም ሙከራ ለማድረግ ሁለት ነገሮችን ይጠቀማል። የመጀመሪያው፥ ተቃውሞ ወይም ስደት ነው። ሰይጣን የቤተ መቅደሱን ሥራ ለ20 ዓመታት ለማስተጓጎል የሰማርያ ሰዎችን ተቃውሞ ተጠቀመ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁልጊዜ ታማኝ ከሆኑ፥ በሚቃወሟቸው ሁሉ ላይ ድልን ይቀዳጃሉ። ሁለተኛ፥ ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሥራ ለማስቆም የእግዚአብሔር ሰዎች ለእርሱ ያላቸውን ፍቅር እንዲያጡና ባለመታዘዝ እንዲኖሩ ለማድረግ ይጥራል። ሰይጣን የእግዚአብሔር ሕዝብ ከእርሱ ተለይተው በኃጢአት እንዲወድቁ የሚያደርገው፥ ጥረት ከፍተኛ ነው። እግዚአብሔር ለሥራው ያልነጹ ዕቃዎችን አይጠቀምም። ይልቁንም ኃጢአት የእግዚአብሔርን ፍርድ ያመጣል። የመጽሐፈ ዕዝራ ጸሐፊ በሁለት ነገሮች ላይ አትኩሯል። የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ሕዝብ አለመታዘዝ ሌላ ምርኮ እንዳያመጣባቸው ከመሥጋቱ ላይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የማያምኑ ሰዎችን በማግባትና እንደ ዓለም በመኖር የራሳቸውን ማንነት የማጣታቸው ነገር ያሳስበዋል። ዛሬም ቢሆን እነዚህን ሁለት አደጋዎች ፊት ለፊት እንጋፈጣለን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ ትምህርቶች ዛሬ ለክርስቲያኖች የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ለ) መጽሐፈ ዕዝራን ለቤተ ክርስቲያንህ የምታስተምርባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

መጽሐፈ ዕዝራ ከአዲስ ኪዳን ጋር ያለው ግንኙነት በአዲስ ኪዳን ፈሪሳውያንና ጸሐፍት የሚባሉ የሕግ መምህራንና የሃይማኖት መሪዎች ቡድን እናያለን። እነዚህ የጌታ ኢየሱስ ዋና ጠላቶች የነበሩና በመስቀል ላይ እንዲሞትም ያደረጉ ናቸው። ለወጋቸው ከሚገባ በላይ ትኩረት በመስጠት የእግዚአብሔርን ሕግ ስለጣሱ፥ ኢየሱስ ግብዞች ናችሁ በማለት ብዙ ጊዜ ሲወቅሳቸው እንመለከታለን (ማቴ. 15፡1-9 እና 23፡13-35 ተመልከት)። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ከየት መጡ? ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የአዲስ ኪዳን ፈሪሳውያን ወይም የሕግ መምህራን ይህን በሚመለከት የመጀመሪያው ጸሐፊ የነበረውን የዕዝራን ባሕል የተከተሉ ናቸው ብለው ያስባሉ፤ ነገር ግን ዕዝራ ከእነርሱ በተለየ ሁኔታ ለእግዚአብሔር ሕግ ባለው ታዛዥነት፥ ራሱን ዝቅ በማድረግ፥ በትሕትናው፥ ደግሞም ለውስጥ ንጽሕና በሚሰጠው ትኩረት የታወቀ ነበር። ሆኖም በመጽሐፈ ዕዝራ ውስጥ እነዚህ ፈሪሳውያንና የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች የሆኑ ሰዎች ኢየሱስ በምድር ከኖረበት ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የነበረውን ሥረ መሠረታቸውን እንመለከታለን። በመጽሐፈ ዕዝራ የሚከተሉትን ነገሮች መመልከት እንጀምራለን፡-

 1. የሕዝቡ ዋና መሪዎች:- የፖለቲካ አመራሩን የያዙት ነገሥታት ወይም ገዥዎችና አስተዳዳሪዎች ሳይሆኑ፥ መንፈሳዊ መሪዎች ነበሩ። እነርሱም ካህናትና ሌዋውያን ነበሩ። ካህናቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኃይላቸውና ተሰሚነታቸው እየጨመረ ስለመጣ፥ በኋላ የፖለቲካ አመራሩንም ጠቅልለው ያዙ፤ ስለዚህም ካህናቱ ከመንፈሳዊ ነገር ይልቅ፥ በፖለቲካ ጉዳዮች ማተኰር ጀመሩ። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ የአይሁዳ መሪዎች የሃይማኖት መሪዎች ሲሆኑ፥ የአይሁድ ሕዝብ ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነው የካህናት አለቆች ሸንጎ አባላት ነበሩ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ እጅግ ጠለቅ ብለው በሚገቡበት ጊዜ ችግር የሚመጣው ለምንድን ነው? 

 1. የእግዚአብሔርን ሕግ ማጥናትና መተርጎም ብቸኛ ኃላፊነታቸው የሆነ ጸሐፍት የሚባሉ ባለሙያዎች አገልግሎት መጀመር (ዕዝራ 7፡10):- እንደነዚህ ዓይነት መሪዎች ተፈላጊ ነበሩ፤ ነገር ግን አደገኛም ሊሆኑ ይችላሉ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ አባላት በታወቁ መሪዎች ትምህርት ላይ ብቻ ከተደገፉና የእግዚአብሔርን ቃል ለራሳቸው ማጥናት ካቆሙ እነርሱም ሆኑ ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት እየደከሙ ይሄዳሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ እጅግ አስፈላጊ ትምህርቶች አንዱ ክርስቲያኖች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ካህናት ስለሆኑ (1ኛ ጴጥ. 2፡9)፣ እኛ ሁላችን የእግዚአብሔርን ቃል የማጥናትና የመተርጎም ኃላፊነት አለብን የሚል ነው።
 2. ለእግዚአብሔር ቃል ሙሉ በሙሉ በመታዘዝ ጉዳይ ላይ በማተኮር፡- እነዚህ በሙያው የተካኑ ጸሐፍት ወዲያውኑ ወደ ክፋት የተለወጠ አንድ ነገር ማድረግ ጀመሩ። ግን ሕዝቡ መታዘዝ እንዳለባቸው አድርገው ተጨማሪ ሕግጋትን መስጠት ጀመሩ። ግን ይህንን ያደረጉት ለመልካም ነበር? የታወቁ የእግዚአብሔር ሕግጋትን እንዳይጥሱ ተጨማሪ ጥበቃ ማድረጋቸውስ አስፈላጊ ነበር? ለመሆኑ እግዚአብሔር ሕዝቡን ያስማረከው የእግዚአብሔርን ሕግ ስለ ጣሱ አይደለምን? እነርሱ ግን ተጨማሪ ሕግጋት ቢያወጡ ሕዝቡ በጽሑፍ ያለውን የእግዚአብሔርን ሕግ ለመጣስ ብዙ ዕድል አይኖረውም ብለው አሰቡ። ብዙም ሳይቆዩ ከእግዚአብሔር ሕግ ይልቅ በዚህ መልክ በተሰጡ ሕጎች (ወግና ልማዶች) ላይ ማተኮር ጀመሩ፥ (ማለትም፡- ምሕረት፥ ቅን ፍርድና፥ እምነትን ለመሳሰለው) ከሁሉ ይልቅ አስፈላጊ ለሆነው ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዛቸውን ከማረጋገጥ ይልቅ፥ ሕዝቡ እነርሱ ላወጡት ሕግ መታዘዝ አለመታዘዛቸውን በማጣራት ላይ ትኩረት አደረጉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ተመሳሳይ ነገር በአብያተ ክርስቲያኖቻችን እንዴት ሊፈጸም ይችላል? ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጨመሩ ቤተ ክርስቲያንህ የምታስተምራቸው ሕጎች የትኞቹ ናቸው? ሐ) እነዚህ ሕግጋት ለክርስቲያን የማሰናከያ ዓለት የሆኑት እንዴት ነው? 

አንዲት ቤተ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ሕግጋት ላይ ሌሎች ተጨማሪ ሕግጋትን ስትጨምር፥ አንድ አደገኛ ነገር መከሰት ይጀምራል። ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ይልቅ የሰዎችን ሕግ መከተል ይጀምራሉ። (ማቴ. 23፡23፤ ማር. 7፡1-9)። ወዲያውኑ የሰዎችን ሕግ ከጠበቁ መንፈሳዊ እንደሆኑ ያስባሉ። በመቀጠልም አምልኮአቸው እግዚአብሔርን ከልብ ከማምለክ ይልቅ ሕግን መጠበቅ ወደ መሞከር ይለወጣል። የግል እምነት አስፈላጊነት ለመዳን ሕግን መጠበቅ ያሻል በሚለው ተተክቶአል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሕጋዊነት ብሎ ሲጠራው፥ ሐዋርያው ጳውሎስ የሮሜንና የገላትያን መልእክቶች የጻፈው ይህንን አቋም በሚፃረር መንገድ ነው። 

 1. ከዓለም የመለየት አስፈላጊነት:- ወዲያውኑ አይሁድ የዓለምን ሕዝብ እንዲጠሉና ከአሕዛብ ጋር ምንም ግንኙነት ሊያደርጉ እንደማይገባ እንዲወስኑ አደረጋቸው። ዕዝራና ነህምያ በግልጥ እንዳስተማሩት የእግዚአብሔር ሕዝብ ከአሕዛብ ጋር የጋብቻ ኅብረት ማድረግ የለባቸውም። ነገር ግን ከአሕዛብ ጋር ከሚደረግ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንዲርቁ አላስተማሩም። በኋላ የተነሡት የአይሁድ መሪዎች ግን ከአሕዛብ ጋር ከሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ግንኙነት መራቅ እንዳለባቸው ሕዝቡን አስተማሩ። መሪዎቹ በንጽሕና በመቆየት ላይ ትኩረት ስላደረጉ ከአሕዛብ ጋር መብላት ወይም ኅብረት ማድረግ እንደሚያረክሳቸው ገመቱ። እግዚአብሔር እነርሱን የመረጠበት አንዱ ምክንያት ለአሕዛብ ብርሃን እንዲሆኑ መሆኑን ረሱ (ኢሳ. 42፡6 ተመልከት)። 

የውይይት ጥያቄ፥ የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ነገር ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ሊፈጸም የሚችለው እንዴት ነው?

ብዙ ጊዜ በአብያተ ክርስቲያኖቻችን ከሚፈጸሙት አሳዛኝ ነገሮች አንዱ፥ ክርስቲያን ካልሆኑ ሰዎች ጋር ያለንን ማንኛውንም ግንኙነት ቀስ በቀስ ማቋረጣችን ነው። በዓለም ተጽዕኖ እንዳይደረግብን ከሚገባ በላይ በመሥጋት ክርስቲያን ያልሆኑ ጓደኞች እንዲኖሩን እንኳ አንፈቅድም። ከክርስቲያኖች ጋር ብቻ እንኖራለን፤ ቢመቸን ጊዜያችንን ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማሳለፍ እንሞክራለን ወዘተ። እግዚአብሔር ግን ለዓለም ብርሃንና ጨው እንድንሆን ጠርቶናል (ማቴ. 5፡13-16)። ይህንን ነገር መፈጸም የምንችለው ከማያምኑ ሰዎች ጋር ኅብረት ሲኖረን ብቻ ነው። ኢየሱስ የጸለየው ከዓለም ክፉ ነገሮች እንድንጠበቅ እንጂ፥ ከዓለም እንድንወጣ አይደለም (ዮሐ. 17፡9-16፥18 ተመልከት)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አባሎቻቸው ክርስቲያን ካልሆኑ ሰዎች ጋር ግንኙነት በማድረግ ወንጌልን እንዲያካፍሏቸው ለማበረታታት ምን ማድረግ ይችላሉ? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አባሎቻቸው ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ከሚገባ በላይ አዘውትረው ጊዜያቸውን በማሳለፍ ለማያምኑ ሰዎች ሊመሰክሩ እስከማይችሉ ድረስ እንዳይሆኑ ምን ማድረግ ይችላሉ? ሐ) የምትገናኛቸው ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች እነማን እንደሆኑ ዘርዝር። መ) ስለ ኢየሱስ የመሰከርክላቸው መቼ ነበር? ሠ) በዚህ ሳምንት ለምታውቀው ለአንድ ለማያምን ሰው ፍቅር በተሞላው መንገድ ስለ ክርስቶስ ልትነግረው ቀጠሮ ያዝ። (ለምሳሌ፡- ሻይ ወይም ምሳ ጋብዘው)። ይህን ለማድረግ የምታውቀው ክርስቲያን ያልሆነ ሰው ከሌለ፥ እግዚአብሔር አንድ ሰው እንዲሰጥህና በዚህ ሳምንት ልትመሰክርለት እንድትችል ጸልይ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ዕዝራ 7-10

ውጫዊ የሆነው የአምልኮ ስፍራ የሚደመሰስበት ጊዜ ቢኖርም እንኳ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያጋጥማቸው ከዚህ የባሰ ከፍተኛ ችግር አለ። ይህም የእግዚአብሔር ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት እንደገና መሠራት የሚያሻው ሆኖ ሲገኝ ነው። ተፈጥሮአዊ የሆነው ዝንባሌ የእግዚአብሔር ሕዝብ የመጀመሪያ ፍቅራቸውን በመተው ከእምነታቸው ፈቀቅ ማለታቸው ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አባላቱ በእግዚአብሔር ፊት በቅድስና የመመላለስ ፍላጎታቸው ቀስ በቀስ እየጠፋ ይሄዳል፤ እንዲሁም ለማያምኑ ሰዎች ጠንካራ ምስክሮች መሆናቸው ይቀራል። አምልኮ ልማዳዊ ብቻ ሊሆን ይችላል፥ በኋላም በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት ይተዋሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህን ዝንባሌ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ እንዴት ነው ያየኸው? ለ) መሪ እንደመሆንህ መጠን በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉ ሰዎች ፍቅራቸውን እንዳይተዉ፥ ንጽሕናቸውን እንዳያጓድሉና እግዚአብሔርን የማምለክ ፍላጎታቸው እንዳይቀንስ ልታደርጋቸው የምትችልባቸውን ነገሮች ዝርዝር።

የመጽሐፈ ዕዝራ የመጨረሻው ክፍል አጋማሽ የሚነግረን፥ የሕዝባችንን መንፈሳዊ ሕይወት ንጹሕና ለእግዚአብሔር ታዛዥ እንዲሆን አድርገን እንዴት እንደምናድሰው ነው። የካህኑ ዕዝራ ታሪክ ኃጢአትን የሚጠላና ሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት በቅድስና እንዲኖሩ የሚፈልግ መሪ ጥሩ ምሳሌ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዕዝራ 7-10 አንብብ። ሀ) ወደ ይሁዳ እንዲመለስ ለዕዝራ የፈቀደለት ንጉሥ የትኛው ነው? ለ) ዕዝራ በምዕ. 7፡6፥10 የተገለጸው እንዴት ነው? ዛሬም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይከተሉት ዘንድ ይህ መልካም ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው? ሐ) ከዕዝራ ጋር የተመለሱት ሰዎች ብዛት ምን ያህል ነበር? መ) ዕዝራ ሕዝቡ ከአሕዛብ ጋር በጋብቻ የመጣመርን ኃጢአት እንደሠሩ ሲሰማ ምን አደረገ? ሠ) በእግዚአብሔር ፊት ሕዝቡን ወደ ተቀደሰ አካሄድ ለመመለስ ዕዝራ ምን አደረገ? ረ) በእነዚህ ምዕራፎች «የእግዚአብሔር ሕግ» የሚለው ቃል የተጠቀሰው ስንት ጊዜ ነው?

በመጽሐፈ ዕዝራ ምዕራፍ 6 እና 7 በምናገኛቸው ክስተቶች መካከል የብዙ ዓመታት ልዩነት አለ። የመጽሐፈ አስቴር ጠቅላላ ታሪክ የተፈጸመው በዚህ ጊዜ ነው። የምዕ. 6 ታሪክ የተፈጸመው በ516 ዓ.ዓ. ሲሆን፥ ከዕዝራ 7-10 ያለው ታሪክ የተፈጸመው ደግሞ በ458 ዓ.ዓ. በአንድ ዓመት ውስጥ ነበር። ይህም ማለት በምዕ. 6 ና 7 መካከል 57 ዓመታት አሉ ማለት ነው።

ዕዝራ የዘር ግንዱ ከአሮን ወገን የሆነ ካህን ነበር። ወላጆቹ ከዘሩባቤል ጋር ከምርኮ ስላልተመለሱ፥ የተወለደው በምርኮ ምድር ነበር፤ ነገር ግን ዕዝራ ለእግዚአብሔርና ለቃሉ ከፍተኛ ፍቅርን አጎለበተ። ዕዝራ በአይሁድ ዘንድ የታወቀና በፋርስ መንግሥት በምርኮ ላይ ሳሉ እንኳ ሳይወክላቸው አልቀረም። ዕዝራ የእግዚአብሔርን ቃል ያውቅ ነበር። ያለማቋረጥ ያጠናው፥ ትምህርቱን ሁሉ ይከተልና በውስጡ ያለውን እውነት በሙሉ ለሕዝቡ ለማስተማር በሚገባ ይተጋ ነበር (ዕዝራ 7፡6፥ 10)። የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ሥራ ምን እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገባ ከሚገልጹት ክፍሎች አንዱ ይህ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ እግዚአብሔርን ማወቅ አለበት። እግዚአብሔርን ማወቅ ማለት ቃሉን ማወቅ ማለት ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ለማወቅ የብዙ ዓመታት ጥናት ይጠይቃል። አስተማሪ የተጻፈውን የእግዚአብሔርን ቃል ማወቅ ብቻ ሳይሆን፥ በውስጡ ያሉትን እውነቶች ለሌሎች ማስተማርና በመታዘዝም መመላለስ ይገባዋል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናት በጣም ጥቂት ጊዜ ብቻ የሚሰጡት ለምንድን ነው? ) ስለ እግዚአብሔር ቃል እውቀታቸውና ለቃሉ ባላቸው መታዘዝ የታወቁ የቤተ ክርስቲያንህ ሰዎችን ስም ዘርዝር። ሐ) እነዚህ ሰዎች ሌሎችን ለማስተማር እግዚአብሔር የተጠቀመባቸው እንዴት ነው?

ዕዝራ ወደ ይሁዳ ለመመለስ ስለፈለገ ንጉሥ አርጤክስስን ፈቃድ ጠየቀው። እግዚአብሔርም የአርጤክስስን ልብ ከፈተና ለዕዝራ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን ገንዘብም እንዲሰጠው አደረገ፡፡ ዕዝራም ወደ ይሁዳ ለመመለስ የሚፈልጉ አይሁዳውያንን ሰበሰበ። ከእነዚህ መካከል ግን የእግዚአብሔርን ቃል ለማወቅና ሌሎችን ለማስተማር፥ ለእግዚአብሔር የሚደረገውን አምልኮ መምራት የሚጠበቅባቸው ሌዋውያን ጥቂት መሆናቸውን አየ። ስለዚህ አብረውት እንዲሄዱ በተለይ ሌዋውያንን ጠየቃቸው። በመጨረሻም 1800 ወንዶችና ቤተሰቦቻቸውም ከዕዝራ ጋር ከምርኮ ተመለሱ። ይህም ከምርኮ፤ የተመለሰው ሁለተኛው ቡድን ነበር። ጉዞው ከ1400 ኪሉ ሜትር በላይ ስለነበር፥ ዕዝራና ሕዝቡ 3 ወር ተኩል ፈጀባቸው። 

ዕዝራ ወደ ይሁዳ በደረሰ ጊዜ በቀጥታ ከሕዝቡ ኃጢአት ጋር ተፋጠጠ። ሕዝቡ በይሁዳ ለ80 ዓመታት የቆዩ ሲሆን፥ ለእግዚአብሔር የነበራቸው ፍቅር እየቀዘቀዘ ሄዶ ነበር። ኃጢአትም ወደ አምልኮአቸው ገብቷል። በትንቢተ ሚልክያስ ውስጥ የሕዝቡ መንፈሳዊ ችግር ምን እንደሆነ እንመለከታለን፤ ነገር ግን ዕዝራ የተዋጋው ኃጢአት በአይሁዳና በአሕዛብ መካከል የተደረገ ቅይጥ ጋብቻ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ነገር ዕዝራን በጣም ያሳሰበው ይመስልሃል? ለ) አንድ ክርስቲያን የማታምን ሴት ሲያገባ መንፈሳዊ ሕይወቱ እየቀዘቀዘ ሲሄድ ያየኸው እንዴት ነው? 

ሰሎሞን ወደ ኃጢአት ካመራባቸው መንገዶች አንዱ ከአሕዛብ ሴቶች ጋር ጋብቻ መመሥረቱ እንደሆነ ዕዝራ ከመጽሐፍ ቅዱስ፥ በተለይ ደግሞ ከሰሎሞን ታሪክ ያውቅ ነበር። ባዕዳን የሆኑት የሰሎሞን ሚስቶች ሰሎሞን እውነተኛውን አምላክ ትቶ የተሳሳቱ አማልክትን እንዲያመልክ አደረጉት። ይህ ነገር በአይሁድም ላይ እንዳይፈጸም ዕዝራ ሰግቶ ነበር። ዛሬ በርካታ ክርስቲያኖች የማያምን ሰው በማግባት ይህንን ሰው በኋላ አማኝ አደርገዋለሁ ይላሉ፤ ይህ ግን ብዙ ጊዜ አይሆንም። ይልቁንም ቀስ በቀስ ወደ ዓለም በመግባት ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅርና ለሌሎች የነበራቸውን ምስክርነት ያጣሉ።

ስለዚህ ዕዝራ ይህን ኃጢአት በሚመለከት ፈጣን ምላሽ ሰጠ። በሕዝቡ መካከል ልብሱን ቀደደ፤ አመድ በራሱ ላይ ነሰነሰ፤ ጠጉሩን ነጨ፤ በመሬት ላይ ተቀምጦ በእግዚአብሔር ፊት ያለቅስ ጀመር። ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ከእግዚአብሔር ዘንድ በግልጽ ይቅርታን ጠየቀ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዕዝራ ስለ አይሁድ ሕዝብ ኃጢአት ከሰጠው ምላሽ በኃጢአት ላይ የነበረውን ጥላቻ እንዴት እናያለን? ለ) በቤተ ክርስቲያን መሪነታችን በእግዚአብሔር ሕዝብ ዘንድ ኃጢአት ስናይ ማድረግ ስላለብን ነገር ከዕዝራ ምላሽ ምን እንማራለን?

ሕዝቡ ዕዝራ ያደረጋቸውን ነገሮች በተመለከቱ ጊዜ፥ አንድ ስሕተት እንዳለ ወዲያውኑ አወቁ። በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኝነታቸውን በማወቅ ንስሐ መግባት ጀመሩ። ከዚያም ዕዝራ ለእግዚአብሔር ሕግ ለመታዘዝና አይሁድ ካልሆኑ ሰዎች ጋር ጋብቻን ላለመፈጸም ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡ አደረገ። ሕዝቡም ይህንን ነገር በመታዘዝ ባዕዳን ሚስቶቻቸውን አሰናበቱ። ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ ቃል ኪዳን ገቡ። የሚያሳዝነው ግን ይህ ቃል ኪዳን ለረጅም ጊዜ አለመቆየቱ ነው፤ ምክንያቱም በነህምያ ዘመን ሕዝቡ በተመሳሳይ ኃጢአት ወድቀው እናገኛቸዋለን።

ኃጢአት ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ሲገባ መሪዎች ወዲያውኑ እርምጃ መውሰድ አለባቸው። በእግዚአብሔር ፊት ራሳቸውን ትሑታን ሊያደርጉና ስለ ሕዝቡም ሆነ ስለ ራሳቸው ኃጢአት ንስሐ ሊገቡ ያስፈልጋል። ሕዝቡንም ስለ ኃጢአታቸው በመውቀስ ንስሐ እንዲገቡ ንጹሕ ሕይወትን በእግዚአብሔር ፊት እንዲኖሩ ለማድረግ መቻል አለባቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ አሁን የራስህንና የቤተ ክርስቲያንህን ሕይወት መርምር። ሀ) አንተና ሌሎች ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት የምትመላለሱት በንጽሕና ነውን? ለ) በአንተና በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ችግር የፈጠሩ አንዳንድ ኃጢአቶችን ጥቀስ። ሐ) አሁን እግዚአብሔር አንተንና ቤተ ክርስቲያህን ንጹሕ እንዲያደርግ ለመለመን የጸሎት ጊዜ ይኑርህ። መ) ስለ ኃጢአታቸው በፍቅር ልትወቅሳቸውና ወደ ንስሐ እንዲመጡ ልታደርጋቸው የምትችላቸው ሰዎች ካሉ፥ በዚህ ሳምንት አነጋግራቸው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ዕዝራ 1-6

የውይይት ጥያቄ፥ ኤር. 25፡7-12፤ 29፡10፤ ኢሳ. 43፡1-7 አንብብ። ወደ ምርኮ ከመሄዳቸው በፊት፥ እግዚአብሔር ለይሁዳ ሕዝብ የሰጣቸውን ቃል ኪዳኖች ጥቀስ።

የክርስቲያን ሕይወት ተስፋ የተመሠረተው በእግዚአብሔር ላይ ባለ ጠንካራ እምነት ነው። ልንሞት በተቃረብንበት ሰዓት ወይም በከፍተኛ ስደት ውስጥ እንኳ ተስፋ ያለን፥ እግዚአብሔር ቃሉን እንደሚያከብርና የተስፋ ቃሉን እንደሚጠብቅ ስለምናምን ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬም ቢሆን አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታዎች ውስጥ ልንጨብጣቸው የምንችል አንዳንድ የተስፋ ቃሎችን ጥቀስ።

የይሁዳ ሕዝብ ተማርከው ከመሄዳቸው በፊት፥ ከ70 ዓመታት ምርኮ በኋላ እንዲመለሱ እግዚአብሔር ነግሮአቸው ነበር። ከምርኮ እንዲመለሱ ያደርግ ዘንድ የሚጠቀምበትን ንጉሥ ስም እንኳ በኢሳይያስ በኩል ነግሮአቸው ነበር። የዚህ ንጉሥ ስም ቂሮስ ነበር (ኢሳ. 45፡1)። አይሁድ ለ70 ዓመታት የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ጠበቁ። ወዲያውኑ የፋርስ ንጉሥ የነበረው ቂሮስ ሜዶንን መውጋት ጀመረና የባቢሎንን ከተማ ወሰደ። አይሁዶች ቂሮስ የባቢሎንን ከተማ መማረኩን በተመለከቱ ጊዜ በመካከላቸው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን እየተፈጸመ እንደሆነ በማሰብ እንዴት ደስ እንደተሰኙ መገመት ትችላለህ።

የክርስትና መሠረት በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ማመን ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ብናምን በተሰጠን የተስፋ ቃል መሰረት የዘላለም ሕይወት ይኖረናል። የማይገቡንን ነገሮች እንኳ ለመልካም እንደሚያደርግልን (ሮሜ 8፡28) በሰጠን የተስፋ ቃል ላይ እንተማመናለን። እንዲሁም እግዚአብሔር ከሙታን እንደሚያስነሣንና ከእርሱም ጋር ለዘላለም በሕይወት እንደሚያኖረን በተሰጠን የቃል ኪዳን ተስፋ እናምናለን (1ኛ ቆሮ. 15)። የእነዚህን ተስፋዎች አንዳንድ ውጤቶች በምድር እንለማመዳለን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከሰጠን የተስፋ ቃሉች አብዛኛዎቹን በሙላት የምንለማመዳቸው ወደ መንግሥተ ሰማያት ከደረስን በኋላ ነው። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ለነበሩ አይሁድ የገባውን የተስፋ ቃል አስደናቂ በሆነ መንገድ ማክበሩ በማይዋሸውና ቃል ኪዳኑን ሁልጊዜ በሚፈጽመው አምላክ ላይ እምነታችንን እንድንጥል ያበረታታናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ እውነት ዛሬም ክርስቲያኖችን የሚያበረታታው እንዴት ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ዕዝራ 1-6 አንብብ። ሀ) ቂሮስ ያሟላው ትንቢት ምንድን ነው? ለ) እግዚአብሔር ፈቃዱን ለመፈጸም ቂሮስን የተጠቀመበት እንዴት ነው? ሐ) ወደ ይሁዳ የተመለሱት ሕዝብ ቁጥር በአጠቃላይ ስንት ነው? መ) ሌላስ የተመለሰ ነገር ምንድን ነው? (ዕዝራ 1፡7)። ሠ) ሕዝቡ ወደ ኢየሩሳሌም እንደደረሱ በቅድሚያ የሠሩት ነገር ምን ነበር? ረ) የቤተ መቅደሱን ሥራ የተቃወመው ማን ነበር? ሰ) ቤተ መቅደሱ በመጨረሻ የተሠራው በማን ዘመነ መንግሥት ነበር?

በዕዝራ 1-6 የተፈጸሙ ድርጊቶች የተጀመሩት በ538 ዓ.ዓ. ነበር። ቂሮስ ባቢሎንን በወጋና በባቢሎን ተማርከው በግዞት የመጡ የተለያዩ ሕዝቦች ወደ የአገራቸው እንዲመለሱ በፈቀደ ጊዜ፥ ከእነዚህ ሕዝቦች አንደኛው ከይሁዳ የመጡ የአይሁድ ሕዝብ ነበሩ። በቅድሚያ ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁድ ግን በአጠቃላይ 50000 ያህል ብቻ ነበሩ፤ የቀሩት ግን በባቢሎን የነበራቸው ሕይወት ተመችቶአቸው ስለነበር በዚያ ቆዩ። በዚህ በመጽሐፈ ዕዝራ የመጀመሪያ ክፍል መጨረሻ ላይ የተጠቀሰው ድርጊት ከ20 ዓመታት በኋላ በ516 ዓ.ዓ. የተፈጸመው የቤተ መቅደሱ ሥራ ነበር።

እግዚአብሔር የአሕዛብ ንጉሥ በሆነው በቂሮስ ልብ ውስጥ በመሥራት፥ ከእርሱ ቀደም የነበሩትን የአሦርንና የባቢሎንን ነገሥታት መመሪያ እንዲቀይር ማድረጉ፥ ጸሐፊውን እንዳስደነቀው እንመለከታለን። እንዲያውም ጸሐፊው አይሁድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የታዘዙትን ሕጋዊ ሰነድ ሁለት ጊዜ ጠቅሶታል። በመጀመሪያ፥ በምዕ. 1፡2-4 ሕጋዊ የሆነው የፈቃድ ትእዛዝ በዕብራይስጥ ቋንቋ ተተርጉሞ እንመለከተዋለን። ይህም ለአይሁድ የተደረገ የትርጉም ቅጂ ሳይሆን አይቀርም። ጸሐፊው የመንግሥቱ የመግባቢያ ቋንቋ በነበረው በአራማይክ ቋንቋ የቀረበውን ጽሑፍ በምዕ. 6፡3-5 እንደገና አቅርቦታል። ቂሮስ አይሁድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መፍቀድ ብቻ ሳይሆን ባቢሎናውያን ከቤተ መቅደሳቸው የወሰዱባቸውን የአምልኮ ዕቃዎቻቸውንም መለሰላቸው።

ሕዝቡ ወደ ኢየሩሳሌም በሚመለስበት ጊዜ የመጀመሪያውን ቡድን የመራው ሰው የይሁዳ አለቃ የነበረው ሼሽባደር ነበር፤ ስለዚህ ሰው ማንነት ምሁራን የተለያዩ አሳቦች አሏቸው። በዚህ አንጻር ሁለት ዋና ዋና አመለካከቶች ይቀርባሉ፡- በመጀመሪያ፥ አንዳንዶች ሼሽባደር ሺናአሰር በመባል የሚታወቅ ወደ ግዛት ተወስደው ከነበሩት የኢዮአኪን ልጆች አንዱ ነበር ይላሉ (1ኛ ዜና 3፡18)፡፡ ይህ ሰው ሽማግሌ ቢሆንም፥ አይሁድ በሚመለሱበት ጊዜ ሕጋዊ የሆነና የታወቀ መሪ ነበር። ምናልባትም በሰማርያ ከሰማርያ ገዢ በታች ሆኖ ይሁዳን ያስተዳድር የነበረ ሰው ሳይሆን አይቀርም ይላሉ። የቤተ መቅደሱን ግንባታ ሥራ የጀመረ ቢሆንም፥ ስለ ሞተ ወይም ሥራውን ለመምራት እስከማይችል ድረስ ስለ ሸመገለ አመራሩን ዘሩባቤል ከእርሱ ተረከበ። ይህንን አመለካከት ከተቀበልን፥ ዘሩባቤል የሼሽባደር የወንድም ልጅ ነው ማለት ነው። ሕጋዊ የሆነውን የታወቀው መሪ ሼሽባደር ሲሆን፥ ዝነኛ የሆነና ከሕዝቡ ጋር ግንኙነት የነበረው መሪ ግን ዘሩባቤል ነው ይላሉ።

ሁለተኛ፥ ሌሎች ምሁራን ደግሞ ሼሽባደር የዘሩባቤል ሌላው ስም ነው ይላሉ። እነዚህ ሁለት ሰዎች ስለ አንድ ሰው የተነገሩ እንደሆኑ ያስባሉ። ሼሽባደር የዘሩባቤል ባቢሎናዊ ስሙ ነው ይላሉ። ሁለቱም ሰዎች አለቆች ወይም ሹማምንት ነበሩ (ዕዝራ 5፡14፤ ሐጌ 1፡1)፤ ሁለቱም የቤተ መቅደሱን መሠረት ጥለዋል (ዕዝራ 3፡2-8፤ 5፡16፤ ሐጌ 1፡14-15)። ሌሉችም የታሪክ መጻሕፍት ሁለቱ ስሞች የአንድ ሰው ናቸው ይላሉ፤ ስለዚህ ሼሽባዳርና ዘሩባቤል የአንድ ሰው ሁለት ስሞች ሳይሆኑ አይቀሩም።

አይሁድ ከ4 ወራት ጉዞ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርሱ፥ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት የሚያቀርቡበት መሠዊያ መሥራት፡ ቅድሚያ የሰጡት ተግባር ነው። አይሁድ በምርኮ በነበሩባቸው 70 ዓመታት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ማቅረብ አልቻሉም ነበር፡፡ የዳስ በዓል በማክበርም እግዚአብሔርን አመለኩ።

ለ50 ዓመታት ያህል ቤተ መቅደሱ የተበላሸና ለአምልኮ አገልግሎት ያልዋለ ነበር (586-538 ዓ.ዓ.)፤ ስለዚህ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ሕዝብ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበትን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመሩ። ገና መሠረቱን እንደጣሉ ተቃውሞ ገጠማቸው። በሰሜን እስራኤል ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም በመምጣት የቤተ መቅደሱን ሥራ ለማገዝ ፈለጉ። የአሕዛብና የአይሁድ ቅይጥ እንጂ ሙሉ ለሙሉ አይሁድ ስላልነበሩ፥ የብሉይ ኪዳን ሕግም አሕዛብ ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲገቡ ስለማይፈቅድ፥ ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩና ከእነርሱ ጋር እንዲያመልኩ ለማድረግ አይሁድ ሳይፈቅዱ ቀሩ። የእግዚአብሔር አምልኮ ይበላሽና እንደገና የእግዚአብሔር ፍርድ ያጋጥመናል ብለው ፈሩ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የማያምኑ ሰዎች ለእግዚአብሔር ያለንን ንጹሕ አምልኮና የተቀደሰ አኗኗራችንን እንዲያበላሹ የምንፈቅድባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያንህ ሲፈጸም ያየኸው እንዴት ነው? የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የእግዚአብሔር አምልኮ ንጽሕና እንዲጠበቅና ሌሎችም በአኗኗራቸው ዓለምን እንዳይመስሉ ለማበረታታት ምን ማድረግ ይችላሉ?

ሳምራውያን የቤተ መቅደሱን ሥራ ማገዝ እንደማይችሉ ሲነገራቸው፥ አይሁድ የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲያቆሙ እንዲያደርግ የፋርስን መንግሥት ጠየቁ። አይሁድ የቤተ መቅደሱን ሥራ እንደገና በ538 ዓ.ዓ ጀመሩ፤ ነገር ግን ሥራውን እንዲያቆሙ ስለተገደዱ እስከ 520 ዓ.ዓ. ድረስ እንደገና ሊጀምሩ አልቻሉም። ይኸውም ከ18 ዓመታት በኋላ ማለት ነው።

ዕዝራ 4 አይሁድ በሰማርያ ሕዝብ አማካይነት የደረሰባቸውን የተለያየ የቤተ መቀደስ ሥራ ማደናቀፊያ መንገድ የተገለጠበት ክፍል ነው። የተቃውሞው ዓይነት የተዘረዘረው በጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ቀጥሉ አይሁድ የደረሱባቸውን ሦስት የተለያዩ ዓይነት ተቃውሞዎች እንመለከታለን።

አንደኛ፣ ቤተ መቅደሱን የመሥራት ተግባር እንደቆመና እስከ ዳርዮስ ዘመን ድረስ ሊቀጥል እንዳልቻለ እንመለከታለን (ዕዝራ 4፡5)።

ሁለተኛ፥ በኋላ የአስቴር ባል በነበረው በንጉሥ አርጤክስስ ዘመነ መንግሥት በአይሁድ ላይ ስለ ቀረበው ክስ እንመለከታለን። ይህም የሆነው ከ485-465 ዓ.ዓ. በነበረው ጊዜ ነው።

ሦስተኛ፥ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንደገና በመሥራት ረገድ ስለ ደረሰው ተቃውሞ እንመለከታለን (ዕዝራ 4፡7-23)። አርጤክስስ የነገሠው በ464 ዓ.ዓ. ስለነበር፥ ይህ ክስ የቀረበው እርሱ በነገሠበት ዘመን አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። በኋላ ዕዝራና ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱና የኢየሩሳሌም ቅጥሮችም እንዲሠሩ የፈቀደው እርሱ ነበር። ይህ ክፍል የሚናገረው ስለ ቤተ መቅደሱ ሥራ ስለ ከተማይቱ መሠራት ነው፤ ምክንያቱም በዚህ ጊዜ የቤተ መቅደሱ ሥራ ተጠናቅቆ ነበር።

የዕዝራ 5 ና 6 ታሪክ በ520 ዓ.ዓ. ወደ ተፈጸመው የዳርዮስ ዘመን ይመልሰናል። ሐጌና ዘካርያስ የተባሉት ነቢያት ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን ይሠሩ ዘንድ እንዴት እንዳበረታቱ የሚናገር ነው። ቤተ መቅደሱን መሥራት በጀመሩበት ጊዜ የሰማርያው ገዢ አይሁድ ይህን ነገር ለማድረግ ፈቃድ አላቸው ወይ? ብሎ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለፋርስ መንግሥት ጻፈ። ይህንንም ለማረጋገጥ በተደረገው ፍለጋ፥ አይሁድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩ የተፈቀደበት ሰነድ ቅጂ ተገኘ። አይሁድ ሥራቸውን ቀጠሉ። ቤተ መቅደሱን ሠርተው ለማጠናቀቅ አራት ዓመታት ፈጀባቸው። የቤተ መቅደሱም ሥራ በ516 ዓ.ዓ. ተጠናቀቀ። ኢየሱስ ከመወለዱ ጥቂት፥ ቀደም ብሎ የሄሮድስ ቤተ መቅደስ እስኪሠራ ድረስ ለአይሁድ ዋናው የአምልኮ ማዕከላቸው ይህ ቤተ መቅደስ ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የእግዚአብሔር ሰዎች ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለማድረግ በሚሠሩበት ጊዜ ሁሉ፥ በአብዛኛው ተቃውሞ የሚኖረው ለምን ይመስልሃል? ለ) ይህንን ነገር በቤተ ክርስቲያንህ ያየኸው እንዴት ነው? ሐ) ዮሐ. 15፡18-21፤ 17፡11-16 አንብብ። ዓለምን እየመሰሉ ለማይኖሩ ክርስቲያኖች የተሰጠው ተስፋ ምንድን ነው? መ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሕዝባቸው ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕይወት ለመኖር የሚፈልግ ከሆነ ለተቃውሞ እንዴት ሊያዘጋጁት ይገባል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመጽሐፈ ዕዝራ አስተዋጽኦ እና አላማ

የመጽሐፈ ዕዝራ አስተዋጽኦ

 1. የመጀመሪያው የአይሁድ ቡድን ከምርኮ መመለስና የቤተ መቅደሱ እንደገና መሠራት (ዕዝራ 1-6)፡-

ሀ. የምርኮኞቹ መመለስ (1) 

ለ. ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች ዝርዝር (2) 

ሐ. የመሠዊያው መሠራትና የቤተ መቅደሱ ሥራ መጀመር (3)

መ. በቤተ መቅደሱ ሥራ ላይ የደረሰው ተቃውሞና በአይሁድ ላይ የደረሱ ሌሎች ተቃውሞዎች (4፡1-23)

ሠ. የቤተ መቅደሱ ሥራ መፈጸም (4፡24-6፡22)። 

 1. ሁለተኛው የአይሁድ ቡድን በዕዝራ መሪነት ከምርኮ መመለሱና መንፈሳዊው ተሐድሶ (7-10) 

ሀ. ለመመለስ የሚያስችል ፈቃድ (7) 

ለ. የተመለሱት ሰዎች ስም ዝርዝር (8)

ሐ. ዕዝራ በኢየሩሳሌም የቀሰቀሰው ተሐድሶ (9-10) 

የመጽሐፈ ዕዝራ ዋና ዋና ዓላማዎች

መጽሐፈ ዕዝራ የተጻፈባቸው ሁለት ዐበይት ምክንያቶች አሉ፡- 

 1. አይሁድ ከምርኮ ተመልሰው እንደገና በይሁዳ መኖር እንዴት እንደ ጀመሩ ለመናገር ነው። በሁለት ክፍለ ጊዜያት የተከፈለ ሲሆን አንዱ በዘሩባቤል፥ ሌላው ደግሞ በዕዝራ መሪነት ከምርኮ ስለተመለሱት አይሁድ ይናገራል። ይህ ታሪክ ከ538-456 ዓ.ዓ. የተፈጸመው ነገር ባጭሩ የቀረበበት ነው።
 2. የዕዝራ መልእክት የተጻፈው በይሁዳ ይኖሩ ለነበሩት አይሁዳዊያን ጭምር ሲሆን፥ እግዚአብሔር ሊሠራ የጀመረውን ነገር እንደተወና እንደረሳቸው ተሰምቶአቸው እጅግ ተስፋ ቆርጠው ስለነበር፥ እነርሱን ለማበረታታት ነበር። ጸሐፊው እግዚአብሔር በነቢያት በኩል የተናገረውን ትንቢት ለመፈጸም ታማኝ እንደሆን ሊያሳያቸው ፈልጎ ነበር (ለምሳሌ፡- ኢሳ. 43፡1-7)። ይህም ትንቢት አንድ ቀን እግዚአብሔር ሕዝቡን ከምርኮ እንደሚመልስ የሚናገር ነበር። እግዚአብሔር እስካሁንም ድረስ በአይሁድ ታሪክ እየሠራ ነበር። የቤተ መቅደሱ ሥራ እግዚአብሔር በመካከላቸው እንደሚሠራ የሚያሳይ አንዱ ምልክት ነበር። ጸሐፊው የዚህን ዘመን ታሪክ በመጠቀም፥ ሕዝቡ የእግዚአብሔርን በረከት ለመለማመድና የይሁዳ መንግሥትም ቀድሞ ወደነበረው ታላቅነት እንዲመጣ ከፈለጉ፥ የቃል ኪዳኑ ሕዝብ እንደመሆናቸው መጠን ለእግዚአብሔር በመታዘዝ መኖር እንደነበረባቸው ለማስጠንቀቅ ፈልጎአል። የንጽሕና ሕይወት መኖር አለባቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በግል ሕይወታችን፥ በቤተ ክርስቲያናችንና በኅብረተሰባችን ውስጥ የምናገኘው በረከት ለእግዚአብሔር ቃል ከመታዘዛችን ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? ለ) ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ በሕይወትህ ውስጥ ልትለውጣቸው ከሚገቡ ነገሮች አንዳንዶቹን ጥቀስ። ሐ) በተሻለ ሁኔታ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ልታደርጋቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮችን ጥቀስ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

አይሁድ በምርኮ ምድር

አይሁድ በ586 ዓ.ዓ. ከተማርኩበት ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ ከምርኮ እንዲመለሱ እስከተፈቀደበት እስከ 538 ዓ.ዓ. ድረስ ስለነበረው ሁኔታ የሚናገር የታሪክ መጽሐፍ የለም። በእነዚህ አምሳ ዓመታት ሁለት ዋና ዋና ነቢያት ነበሩ። አንዱ በባቢሎን መንግሥት ውስጥ የኖረውና የሠራው ዳንኤል ሲሆን፥ ሌላው በምርኮ ከነበሩት ወገኖቹ ጋር በባቢሎን የኖረው ሕዝቅኤል ነበር። በባቢሎን ስለኖሩባቸው ስለ እነዚህ 50 ዓመታት የምናውቀው ብዙ ነገር የለም። በባቢሎንና በመካከለኛው ምሥራቅ ተበትነው የኖሩ ይመስላሉ። ነገር ግን ይሁዳ ከተደመሰሰችበት ከ586 ዓ.ዓ. በኋላ ሕዝቡ በምርኮ ምድር ማረስና የንግድ ሥራ መሥራት ጀመሩ። በባቢሎናውያንም እጅ ክፉ ነገር አይደርስባቸውም ነበር። 

የባቢሎን መንግሥት 

ከአሦር መንግሥት መውደቅ በኋላ፥ የባቢሎን መንግሥት ዓለምን መምራት ጀመረ። ኃይላቸው እጅግ ታላቅ የነበረ ቢሆንም፥ መንግሥታቸው የቆየው ግን በሜዶንና በፋርስ እስኪተካ ድረስ ከ70 ዓመታት ጥቂት ለሚበልጥ ጊዜ ነበር። የባቢሎን መንግሥት ዋና ዋና መሪዎች የነበሩት ከዚህ እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡-

 1. ናቦኋላሳር (626-605 ዓ.ዓ.) በባቢሎን መንግሥት የመጀመሪያ ንጉሥ የናቡከደነፆር አባት የነበረው ናቦቁላሳር ነበር። በአሦር ላይ የተደረገውን ዓመፅ በመምራት፥ የባቢሎንን ከተማ በ626 ዓ.ዓ. ያዘና ንጉሥ ሆነ። የአሦርን መንግሥት ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የቻለው በ609 ዓ.ዓ. ነበር። 
 2. ናቡከደነፆር (605-562 ዓ.ዓ.) በባቢሎን መንግሥት ውስጥ እጅግ ታላቅ የነበረው መሪ ናቡከደነፆር ነበር። አባቱ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት፣ በከነዓን ላይ የተደረገውን ጦርነት በመምራት ይሁዳ ለባቢሎን መንግሥት እጅ እድትሰጥ አድርጎ ነበር። ናቡከደነፆር ራሱ እስከነበረበት ዘመን ድረስ ከነበሩ መንግሥታት ሁሉ የላቀ እጅግ ገናና መንግሥትን ያቋቋመው ታላቅ ጦረኛ ስለነበረ ብቻ ሳይሆን፥ ታላቅ ከተማና ሕንጻ ገንቢም ስለነበረ ነው። የባቢሎንን ከተማ በጠላት እንደማትደፈር አድርጎ ገነባት። ከጥንቱ ዓለም ሰባት አስደናቂ ነገሮች አንዱ የተባለውን የአትክልት ስፍራ ለሚስቱ ሠራላት። እርሱ ከሞተ በኋላ የባቢሎን መንግሥት ኃይል እየተዳከመ ሄደ። 
 3. ከናቡከደነፆር በኋላ ሌሎች አራት ነገሥታት ይኖሩ ነበር። በመጀመሪያው የነገሠው አቤል ሙርዱክ ወይም ኢቭል ሜሮዳክ በመባል የሚታወቀው ሰው (562-560 ዓ.ዓ.) ሲሆን፥ ሁለተኛ ኔርግሊሳር (560-556 ዓ.ዓ.) ቀጥሎም ናቦኒዱስ (556-539 ዓ.ዓ.) ነገሠ። ይህ ሰው ከፖለቲካ አመራር ይልቅ ትኩረቱ በሃይማኖታዊ ጉዳይ ላይ ነበር። ብሔራዊ እምነት የነበረውን የማርዱክን አምልኮ የሚያስፈጽሙትን ቀሳውስት ባስቀየመ ጊዜ ሕዝቡ ከሥልጣን አወረዱትና ልጁን ብልጣሶርን በምትኩ አነገሡበት። ናቦኒዱስም ለመኖር በዐረቢያ ወዳለ ቤተ መንግሥት ሄደ፡፡ የፋርስ ወታደሮች በ539 መጥተው የባቢሎንን መንግሥት ባሸነፉበት ጊዜ በሥልጣን ላይ የነበረው መሪ ብልጣሶር ነበር። እግዚአብሔር መንግሥትህ ተደምስሳለች ብሎ በግድግዳ ላይ በጻፈና ዳንኤልም በዚያ ምሽት መንግሥቱ እንደምትከፈል በተናገረ ጊዜ በሥልጣን ላይ ያለው መሪ ብልጣሶር ነበር (ዳን. 5)።

ሜዶንና ፋርስ 

የሜዶንና የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ግዛት ከ539 አንስቶ የግሪክ ንጉሥ በነበረው ታላቁ እስክንድር እስከ ተሸነፈበት እስከ 331 ዓ.ዓ. ድረስ በገናንነት ቆይቷል። የመጽሐፍ ቅድስ ታሪክ ግን የፋርስ መንግሥት ከ539 – 400 ዓ.ዓ. የቆየበትን ዘመን ብቻ የሚሸፍን ነው። የፋርስ ዘመነ መንግሥት በዓለም ውስጥ ካሉት መንግሥታት ይልቅ በዚያን ጊዜ ላቅ ያለና ገናና ገዢ እንደ ነበረ የዓለም ታሪክ ይመሰክራል። ከዚህ በመቀጠል በፋርስ ዘመን መንግሥት እስከ 400 ዓመተ ዓለም ድረስ ይገዙ የነበሩት የንጉሦች ስም ተዘርዝረዋል። 

 1. ታላቁ ቂሮስ፡- (559-530 ዓ.ዓ.)፡- ፋርስን እስከዚያ ዘመን ድረስ ከነበሩ መንግሥታት ሁሉ የላቀች እጅግ ታዋቂ ያደረጋት የቂሮስ ወታደራዊ አመራር ነበር። ቂሮስ በሜዶን ቁጥጥር ሥር የሚኖር ንጉሥ ነበር፤ ነገር ግን በሜዶን መንግሥት ላይ ዓመፀ። በኋላም የሜዶንን ሕዝብ ከእርሱ ጋር እንዲተባበሩ አስገደዳቸውና የሜዶንና የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ግዛት የተባለውን መንግሥት አቋቋመ። በጥምሩ ውስጥ ዋናውን ቦታ የያዘው የፋርስ መንግሥት ነበር፣ ስለዚህ ብዙ ጊዜ ይህ መንግሥት የፋርስ መንግሥት ይባል ነበር። የቂሮስ የንጉሠ ነገሥት ግዛት ከሜዶን ወደ ባቢሎን፥ እስከ ሕንድ ወሰን፥ እንዲያውም እስከ ግብፅ ድረስ ሰፋ።

አሦራውያንና ባቢሎናውያን ከተጠቀሙበት መንገድ በተለየ ሁኔታ፥ ቂሮስ በጎነትንና ርኅራኄን በማሳየት ሕዝቡ እንዲከተሉት አደረገ። አሦራውያንና ባቢሎናውያን ዋና የሆኑ ሰዎችን ማርኮ የመውሰድና በግዛታቸው ሁሉ ውስጥ የማሰራጨት ፖሊሲ (መመሪያ) ነበራቸው፤ ስለዚህ አሦር ከእስራኤል፥ ባቢሎን ደግሞ ከይሁዳ የወሰዷቸውን ሕዝቦች መንግሥታቸው ሁሉ ውስጥ አሰራጭተዋቸው ነበር። ፋርስ ግን በምርኮ ተይዘው የመጡትን እነዚህን ሰዎች ሁሉ ወደ አገራቸው እንዲመለሱና የአምልኮ ስፍራቸውንም እንደገና እንዲገነቡ ፈቀዱላቸው። ይህ ነገር የተፈቀደው ለአይሁድ ብቻ ባይሆንም፥ በመጽሐፈ ዕዝራ አይሁድ ይህንን ዕድል እንዴት እንደተጠቀሙበትና ወደ እስራኤል ተመልሰው ቤተ መቅደሳቸውን እንደሠሩ እንመለከታለን። – 

የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳ. 45፡1፥ 13 አንብብ። ይህ ለኢሳያስ ትንቢት ፍጻሜ የሆነው እንዴት ነው? 

 1. ካምቢኤስ (530-522 ዓ.ዓ.)። ይህ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም፤ ነገር ግን አይሁድ በቂሮስ ዘመነ መንግሥት ሊሠሩ የጀመሩትን ቤተ መቅደስ እንዳይሠሩ በዚህ ሰው ዘመን መንግሥት ተከልክለው ነበር። 
 2. ቀዳማዊ ዳርዮስ (522-486 ዓ.ዓ.)፡- ይህ ንጉሥ ታላቁ ዳርዮስ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፥ አይሁድ ቤተ መቅደሳቸውን እንዲሠሩ እንደገና የፈቀደ ሰው ነው (ዕዝ. 6፡1-12፤ ሐጌ 1፡1)። የቤተ መቅደሱ ሥራ በ516 ዓ.ዓ. ተጠናቀቀ። ዳርዮስ ታላላቅ ከሚባሉት የፋርስ የጦር መሪዎች አንዱ ሲሆን፥ የፋርስን መንግሥት እስከ ግሪክ ድረስ ያስፋፋ ሰው ነበር። በሥሩ ላሉ መንግሥታት ሁሉ አንድ ዓይነት ሕግ ለመስጠት ስለሞከረ «ሕግ ሰጪ» በመባል ይታወቃል።
 3. ቀዳማዊ አርጤክስስ (486-425 ዓ.ዓ.)። ይህ ሰው በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ አህሳዊሮስ በመባል ይታወቃል። በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ግን አህሳዊሮስን ከአርጤክስስ በኋላ ከነገሠው ከአርጤክስስ ጋር የሚምታታ የተሳሳተ አተረጓጎም አለ። አርጤክስስ ወይም አህሳዊሮስ ብለን የምንጠራው አስቴርን ያገባው ንጉሥ ነው። በተጨማሪ በዕዝራ 4፡6 ተጠቅሷል። (ማስታወሻ፡- በዕዝራ 4፡7 ላይ የተጠቀሰው ግን የሚቀጥለው ንጉሥ አርጤክስስ ነው)። በዓለም ታሪክ የአርጤክስስ ዝና ካሸነፉት ከግሪኮች ጋር ባደረገው ጦርነት የታወቀ ነው። በተጨማሪ ትልልቅ ከተሞችን በመሥራት ችሎታው ይታወቃል። 
 4. ቀዳማዊ አርጤክስስ (464-425 ዓ.ዓ.)፡- አርጤክስስ በመጽሐፍ ቅዱሳችን የተጠቀሰው የመጨረሻው የፋርስ ንጉሥ ነው። በመጀመሪያ ዕዝራ፥ ቀጥሉም ነህምያ ወደ ይሁዳ እንዲመለሱ የተፈቀደላቸው በእርሱ ዘመነ መንግሥት ነበር።

የመጽሐፈ ዕዝራ፥ ነህምያና አስቴር ቅደም ተከተል

የመጽሐፈ ዕዝራ፥ ነህምያና አስቴር ታሪክ አፈጻጸም በጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት አልቀረበም። በመቀጠል የእነዚህ መጻሕፍት ቅደም ተከተላቸውን እናያለን።

 1. የመጀመሪያዎቹ አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ፡- ዕዝራ 1-6 (539-515 ዓ.ዓ.) 
 2. የአስቴር ታሪክ፡- አስቴር 1-10 (በ480 ዓ.ዓ.ገደማ) 
 3. የተሐድሶው መሪ ዕዝራና ሁለተኛው የአይሁድ ቡድን ከምርኮ መመለስ፡- ዕዝራ 7-10 (457 ዓ.ዓ.) 
 4. የአስተዳዳሪው ነህምያና የሦስተኛው የአይሁድ ቡድን ከምርኮ መመለስ፡- ነህ. 1-13 (444-430 ዓ.ዓ.)

(ማስታወሻ፡- አንዳንድ ምሁራን ዕዝራ 7፡8ን በሚመለከት የአጻጻፍ ስሕተት አለ ይላሉ፤ ይኸውም በአርጤክስስ በሰባተኛው ዓመት የሚለው ቃል በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት መሆን አለበት ብለው ያስባሉ። ይህም የዕዝራን መመለስ ወደ 428 ዓ.ዓ. በማራዘም ከነህምያ በኋላ ያደርገዋል። ይህንን ለማመን ግን በቂ ምክንያት የለም።)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ 

ልክ እንደ መጽሐፈ ሳሙኤል፥ ነገሥትና ዜና መዋዕል መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያም በዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን አንድ መጽሐፍ ነበሩ። ዕዝራና ነህምያ በጊዚያቸው የተፈጸመውን ድርጊት እየተከታተሉ ራሳቸው የመዘገቡት ቢመስልም፥ ብዙ ምሁራን የሚስማሙት ጽሑፎቹን የሰበሰባቸውና ወደ አንድ መጽሐፍ በማጠቃለል ያቃናቸው ሌላ ሰው እንደሆነ ነው።

የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ በኋላ ወደ ግሪክ ቋንቋ ሲተረጎም፥ ተርጓሚዎቹ አንድ የነበረውን መጽሐፍ ለሁለት ከፈሉት። በግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሁለት መጻሕፍት 1ኛና 2ኛ ዕዝራ በመባል ይታወቃሉ። በኋላ የእነዚህ መጻሕፍት ርዕስ የመጀመሪያው ዕዝራ፥ ሁለተኛው ደግሞ ነህምያ ተብሎ ተሰየመ። እነዚህን ስያሜዎች ያገኙት በመጻሕፍቱ ውስጥ ባሉት ዋና ገጸ ባሕርያት በዕዝራና በነህምያ ነው።

የመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ጸሐፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ በማን እንደተጻፉና እንዴት እንደተጻፉ ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው። የአብዛኛዎቹ አስተሳሰብ ዕዝራና ነህምያን የጻፈው ዜና መዋዕልን የጻፈው ሰው ነው የሚል ነው። ይህንንም ያሉበት ምክንያት የመጽሐፈ ዜና መዋዕል አጨራረስና የመጽሐፈ ዕዝራ አጀማመር ተመሳሳይ በመሆኑ ነው። በተጨማሪ በአጻጻፍ ስልቱም ተመሳሳይነት እናገኛለን።

ሌሎች ምሁራን ደግሞ መጻሕፍቱ ብዙ ተመሳሳይነት ቢኖራቸውም፥ የተጻፉት ግን በተለያዩ ጸሐፊዎች ለመሆኑ የሚያሳምኑ በቂ ልዩነቶች እናገኛለን ይላሉ።

ምሁራን መጽሐፈ ዕዝራንና ነህምያን ያቀናበረው ሰው የተጠቀመባቸው ሦስት የተለያዩ ምንጮች አሉ ይላሉ። በመጀመሪያ፣ ዕዝራ በእርሱ ዘመን ስለተፈጸሙት ክስተቶች ዘግቧል። ሁለተኛ፥ ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እንዴት እንደሠራ ዘግቧል። ሦስተኛ ደግሞ፥ በሼሺባዛር (ዘሩባቤል) መሪነት አይሁዶች በመጀመሪያ እንዴት ወደ ኢየሩሳሌም እንደተመለሱ የሚናገር የተለየ ዘገባ ነበር። መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያን በአንድ ላይ እንዲሆኑ ያደረገው ሰው ከሦስት የታሪክ ምንጮች በማሰባሰብ በአንድ መጽሐፍ እንዲጠቃለል አድርጓል።

ጸሐፊው ዕዝራ በእርሱ ስም የተሰየመውን የመጀመሪያ መጽሐፍ ጽፎ ሊሆን ይችላል። በፋርስ መንግሥት ውስጥ ሥልጣን የነበረው ሰው ስለነበር፥ አይሁድ ወደ ይሁዳ እንዲመለሱ የተፈቀደበትን ማዘዣ ቅጂና ሌሎች የቤተ መንግሥት መዛግብት ቅጂዎች ኖረውት ሊሆን ይችላል። ከዚህም የተነሣ አይሁድ እንዴት ወደ ምድራቸው እንደተመለሱና ዕዝራ ከስንት ዓመታት በኋላ በምድሪቱ መንፈሳዊ መነቃቃትን እንደመራ አጭር መግለጫ ጽፎ ሊሆን ይችላል። መጽሐፈ ነህምያ የተጻፈው በነህምያ ሊሆን ይችላል። መጻሕፍቱ ባላቸው ተመሳሳይነት ምክንያት፥ የመጨረሻው ሰው መጠነኛ ለውጦችን አድርጎ ወደ አንድ መጽሐፍ አዋሕዶአቸው ሊሆን ይችላል። መጽሐፈ ዕዝራ ከሌዊ ነገድ በሆነ፥ ከምርኮ በኋላ በእስራኤላውያን ታሪክ ውስጥ ታላቅ ሚና በተጫወተና ትልቅ ስፍራ በነበረው ዕዝራ በተባለ ጸሐፊ ስም ተሰይሟል። ዕዝራ የተወለደው በምርኮ ምድር ነበር። ያደገውም በባቢሎን ነበር። ለዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ ስላስተማሩት፥ ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ዕዝራ በባቢሎን ምድር እስራኤላውያንንና የብሉይ ኪዳን ሕግን የሚያውቅ ዝነኛ ሰው እየሆነ እንደመጣ ይመስላል። አንዳንድ ምሁራን ዕዝራ በፋርስ መንግሥት ውስጥ የአይሁድ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ እንደተሾመ ይገምታሉ። የፋርስ ንጉሥ ከነበረው ከአርጤክስስ ጋር ግንኙነት የነበረውም ለዚህ ነበር። በ538 ዓ.ዓ. ሕዝቡ በዘሩባቤል መሪነት ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ ዕዝራ ያልተመለሰበትን ምክንያት አናውቅም። ምናልባት በጣም ወጣት ስለነበረ ይሆናል። በ458 ዓ.ዓ. ግን ዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ ከፋርስ ንጉሥ ፈቃድ አገኘ። ንጉሡ ከቤተ መንግሥቱ ገንዘብ እንዲጠቀም ለዕዝራ ፈቃድ ሰጠው። ዕዝራ አንዳንድ ሌዋውያን ከእርሱ ጋር እንዲመለሱ በማሳመን፥ በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚደረገውን አምልኮ በመምራት ይረዱት ዘንድ አደረገ።

ዕዝራ ወደ እስራኤል ከተመለሰ በኋላ በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ሚናን ተጫወተ። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር ዕዝራን ሁለት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ለመምራት ተጠቀመበት (ዕዝራ 9-10፤ ነህ. 8-9)። ሁለተኛ፥ ዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ በጥንቃቄ በማጥናት የታወቀ ሰው ነበር። ለዚህ ነው አይሁድ በሕግ ሥራና እውቀት «የተካኑ» የሃይማኖት መሪዎች አባት አድርገው የሚቆጥሩት። በአዲስ ኪዳን የተጠቀሱት የፈሪሳውያንና የጸሐፍት አባት ነበር። በዕዝራ ዘመን ከምርኮ የተመለሱ አብዛኛዎቹ አይሁዳውያን የራሳቸው የሆነውንና መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን የዕብራይስጥን ቋንቋ ስለማያውቁ ዕዝራና ሌሎች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለእነርሱ ለመተርጎም ተገድደው ነበር። አብዛኛዎቹ አይሁድ የባቢሎንና የፋርስ የንግድ ቋንቋ የነበረውን አራማይክን ብቻ ያውቁ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የመጠቁ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉ፥ በዚህ ሁኔታ በሚገባ የሠለጠኑ ሰዎችን ስም ዝርዝር።

መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ የተጻፉበት ጊዜ 

የመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ጸሐፊ ማን እንደሆነ ስለማናውቅ የተጻፉበትንም ጊዜ በእርግጠኝነት ማወቅ አንችልም። በመጽሐፉ ውስጥ የተገለጡ ድርጊቶች የተፈጸሙት ከ538-420 ዓ.ዓ. ባለው ዘመን ነበር፤ ስለዚህ መጽሐፉ በ400 ዓ.ዓ. አካባቢ ተጠናቅቆ ሳይጻፍ እንዳልቀረ መገመት ይቻላል።

የመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ሥረ – መሠረት 

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ዜና 36፡15-19 አንብብ። ሀ) የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስና ቅጥሮች ምን ሆኑ? ለ) የይሁዳ ሕዝብና ንጉሡስ ምን ሆኑ?

እንደምታስታውሰው በ2ኛ ነገሥትና በ2ኛ ዜና መጨረሻ ላይ የይሁዳ ሕዝብ በባቢሎናውያን መማረካቸውን ተመልክተናል። ቤተ መቅደሱና የኢየሩሳሌም ከተማም ተደምስሰዋል። ንጉሡም ተገድሉ ሕዝቡ ተማረኩ። ይህ ሁሉ የሆነው በ586 ዓ.ዓ. ነበር። ዋና ዋና የሆኑ ምርኮዎች የተፈጸሙት ሦስት ጊዜ ብቻ ቢሆንም፥ የባቢሎን ንጉሥ አይሁዳውያንን በምርኮ የወሰደው አራት ጊዜ ይመስላል። በመጀመሪያ፥ ዳንኤልና ሌሎች በምርኮ የተጋዙት በ605 ዓ.ዓ. ሲሆን፥ ሁለተኛ፥ ሕዝቅኤልና ንጉሡ ኢዮአኪን የተጋዙት በ597 ዓ.ዓ. ነበር። ሦስተኛ፥ በ586 ዓ.ዓ. ቤተ መቅደሱ የፈረሰበትና አብዛኛውን ሕዝብ የሚመለከት ዋናው ምርኮ ተፈጸመ፤ ነገር ግን ሌላ አራተኛ መማረክም በ582 የነበረ ይመስላል (ኤር. 52፡30)። የቀሩት አንዳንድ እስራኤላውያን ወደ ግብፅ ሸሽተው ሄዱ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመጽሐፈ ዕዝራ መግቢያ

ብዙ ጊዜ ከመገንባት ይልቅ የሚቀለው ማፍረሱ ነው። የሐሰት ትምህርቶች በጥቂት ሳምንታት ወይም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊገቡና የብዙ ሰዎችን ሕይወት በቀላሉ ሊያጠፉ ይችላሉ፤ ዳሩ ግን አንዲት ቤተ ክርስቲያን በሐሰት ትምህርት ወይም በመለያየት ከፈረሰች በኋላ እንደገና እርስዋን መገንባት ብዙ ዓመታትንና እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ ሥራዎችን ይጠይቃል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ቤተ ክርስቲያን ወይም የክርስቲያኖች ሕይወት ሊጠፋ የሚችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የፈረሰውን ነገር የሚገነቡባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ሐ) በዚህ መንገድ ቤተ ክርስቲያንህ የፈረሰችበትና እንደገና የተሠራችበት ሁኔታ ካለ ምሳሌዎችን ዘርዝር።

መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ የፈረሰው ነገር እንዴት እንደተገነባ የሚናገሩ ናቸው። ከመጽሐፈ ዕዝራ በፊት በነበሩ የታሪክ መጻሕፍት እንደተገለጸው፥ እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ዓመፅና ኃጢአት ምክንያት፥ ባቢሎናውያን የኢየሩሳሌምን ከተማና የክብር ደመናው እንዲቀመጥበት ያዘዘውን ቤተ መቅደስ እንዲያጠፉ መፍቀዱን ተመልክተናል። አብዛኛዎቹ የይሁዳ ሰዎች በኃጢአታቸው ምክንያት በምርኮ ተወሰዱ። በመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ እንዴት ተመልሰው ለመቋቋምና ቤተ መቅዱሱን እንደገና መሥራት እንደጀመሩ እናያለን። የአይሁድ ሕዝብ ቅሬታዎች ከምርኮ ወደ ይሁዳ ተመለሱ። ቤተ መቅደሱ፥ በመጨረሞም የኢየሩሳሌም ቅጥሮች ተሠሩ። ከሁሉ በላይ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ግን የእግዚአብሔርን ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት መሥራት ነበር። ይህም ቤተ መቅደሱንና ቅጥሮቹን ከመሥራት እጅግ የከበደና ረጅም ጊዜ የወሰደ ነበር።

እስካሁን ድረስ የተመለከትናቸው የታሪክ መጻሕፍት፥ አይሁድ ወደ ምርኮ ከመሄዳቸው በፊት በነበራቸው ታሪክ ላይ የሚያተኩሩ ነበሩ። እነዚህም ከመጽሐፈ ኢያሱ እስከ 2ኛ ዜና መዋዕል ያሉት ናቸው። አይሁድ ከምድራቸው ተግዘው ወደ ምርኮ ከሄዱ በኋላ ስላለው ታሪከ የሚናገሩ ሦስት መጻሕፍት አሉ። እነዚህ ሦስት የመጨረሻ መጻሕፍት ዕዝራ፥ ነህምያና አስቴር ናቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ መጽሐፈ ዕዝራ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ከዚያም በዚህ ስፍራ ስለ መጽሐፈ ዕዝራ የተጠቀሱ ጠቃሚ እውነቶችን ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)