1ኛ ዜና 1 እስከ 2ኛ ዜና መጨረሻ

በመጽሐፈ ዜና መዋዕል የሚገኙ አብዛኛዎቹ ታሪኮች ከመጽሐፈ ሳሙኤልና ከነገሥት ታሪክ የተደገሙ ስለሆኑ፥ ለሚቀጥሉት ሦስት ቀናት 1ኛና 2ኛ ዜና መዋዕልን በሙሉ በማንበብ ጥያቄዎችን ትመልሳለህ። እነዚህን ምዕራፎች በሚመለከት የሚሰጥ መግለጫ አይኖርም። 

1ኛ ቀን፡- 1ኛ ዜና 1 – 21

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ እግዚአብሔር የምንማራቸውን ነገሮች ዘርዝር። ለ) በእነዚህ ምዕራፎች እንደሚታየው፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኙ የተግባር ሰዎች ስለመሆን፥ ከዳዊት ሕይወት ምን መማር እንችላለን? ሐ) ከእነዚህ ጥቅሶች ስለ አምልኮ ልንማራቸው የምንችል አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

2ኛ ቀን፡- 1ኛ ዜና 22 – 2ኛ ዜና 9

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከሰሎሞንን ሕይወት እግዚአብሔርን ስለማገልገል የምንማራቸውን ነገሮች ዘርዝር። ለ) ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ አምልኮ ልንማራቸው የምንችል አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ሐ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ሕይወትህን የነኩትን መንፈሳዊ ትምህርቶችን ዘርዝር። 

3ኛ ቀን፡- 2ኛ ዜና 10-36

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ እግዚአብሔር ልንማራቸው የምንችል ነገሮችን ዘርዝር ለ) ለመንፈሳዊ መሪነት መልካም ምሳሌ የሚሆኑ የነገሥታትን ስም ዘርዝር። ከአመራራቸው የምንማረው ነገር ምንድን ነው? ሐ) ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ አምልኮ የምንማረው ነገር ምንድን ነው? መ) ከእነዚህ ጥቅሶች ስለ ንስሐ ልንማራቸው የምንችል አንዳንድ ነገሮችን ጥቀስ። 

የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ዋና ዋና ትምህርቶች

 1. ከመዝሙረ ዳዊት በቀር በብሉይ ኪዳን ከሚገኙ መጻሕፍት ሁሉ በላይ አይሁድ እግዚአብሔርን በብሉይ ኪዳን ዘመን እንዴት እንዳመለኩ በማሳየት፥ ዛሬም እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንዳለብን የሚያስተምር መጽሐፍ ዜና መዋዕል ነው። በመጽሐፈ ዜና መዋዕል በርካታ የግልና የኅብረት አምልኮ ምሳሌዎችን እናገኛለን (ለምሳሌ፥ 2ኛ ዜና 31፡20-21)። ዛሬም ቢሆን በርካታ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን በእውነት ማምለክ የምንችለው ልክ የብሉይ ኪዳን ዓይነት የአምልኮ መንገድ ወይም ውጫዊ ሁኔታ ከተከተልን ነው ይላሉ። በምንጸልይበት ወይም በምንዘምርበት ጊዜ እጆቻችንን ማንሣት አለብን ይላሉ፤ መጨፈርና እልልታ ማሰማት አለብን ይላሉ። ይህ ግን በጐችንና ኮርማዎች ጥጃዎችን መሠዋት አለብን ወይም በበገናና በጥንታዊ መሣሪያዎች ብቻ መጠቀም አለብን ወዘተ እንደማለት ነው። አምልኮ የምትኖርበትን ማንኛውንም ዓይነት ባሕል ቅርፅ ይይዛል። እግዚአብሔር የሚፈልገው ዋናው ነገር ውስጣዊ ልባችንን እንጂ ውጫዊ የአምልኮ ቅርፃችንን አይደለም። እግዚአብሔርን የሚያከብረው በምስጋናና በአምልኮ የተሞላ ልብ ነው። በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ውስጥ የሚገኙትን የአምልኮ ምሳሌዎች በሙሉ በጥንቃቄ ብናጠና ከሚከተሉት ነገሮች አንዳንዶቹን እንመለከታለን፡-

ሀ. የኅብረት አምልኮ ሥነ-ሥርዓት ያለውና አምልኮውን እንዲመሩ በተመረጡ ሰዎች የሚመራ እንዲሆን ብዙውን ጊዜ በቁጥጥር መካሄድ አለበት። በመጽሐፈ ዜና መዋዕል እንደምናየው፥ ሕዝቡ አምልኮ የሚፈጽሙት እንደፈለጉት ሳይሆን፥ ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔርን ሕዝብ አምልኮ በሚመሩት በካህናት መሪነት ነበር (ለምሳሌ፥ 2ኛ ዜና 35፡1-19)። 

ለ. አምልኮ እግዚአብሔር ለሚሠራው ታላቅ ሥራ ድንገተኛ ምላሽ የሚሆንባቸው ጊዜያትም አሉ። እነዚህ የተለመዱ ዓይነት የአምልኮ ጊዘያት አይደሉም። እግዚአብሔር ታላቅና ያልተለመዱ ነገሮች ሲያደርግልን የሚፈጸሙ ናቸው (ለምሳሌ፥ 1ኛ ዜና 16፡28-36)።

ሐ. አምልኮ ሥርዓት ሆኖ መፈጸም የለበትም፤ ወይም ልማድ ሆኖ፥ ወይም ሌሉች ስላደረጉት፥ ወይም መንፈሳዊ ለመምሰል ስለፈለግን የሚፈጸም ነገር አይደለም። ይልቁንም የአምልኮ ምንጩ ለእግዚአብሔር ያለን ፍርሃት ወይም ፍቅር ነው (ለምሳሌ፥ 2ኛ ዜና 6፡31፥ 33፤ 1ኛ ዜና 28፡9፤ 2ኛ ዜና 19፡9)።

መ. አምልኮ መዝሙር ከመዘመርና የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት በላይ ነው። ከምንፈጽማቸው ውጫዊ የሃይማኖት ሥርዓቶች በላይ ነው። ይልቁንም አምልኮ እግዚአብሔርን ከሚወድና እርሱንም ለማክበር ከተዘጋጀ ልብና አእምሮ የሚመነጭ ውስጣዊ ዝንባሌ ነው (ለምሳሌ፥ 1ኛ ዜና 16፡10-11፤ 28፡9፤ 2ኛ ዜና 15፡12፥ 15)።

ሠ. አምልኮ ዝም ብሎ መቀመጥ ሳይሆን፥ መላ ሰውነታችንን የሚያካትት ነው። ከሁሉም የሚሻል አንድ የተለየ ዓይነት አምልኮ የለም፤ ነገር ግን የተለያዩ ዓይነት የሰውነት አቋሞች፥ ተግባራትና እንቅስቃሴዎች ተጠቅሰዋል (ለምሳሌ፥- 2ኛ ዜና 20፡18፤ 29፡26-30፤ 31፡2፤ መዝ. 5፡7፤ 20፡5፤ (28)፡2፤ (47)፡1፤ (95)፡6 (123)፡1)። እነዚህ ሁሉ የሚያስተምሩት፥ እግዚአብሔርን ለማምለክ እኛነታችን ሁሉ አገልግሎት ላይ መዋል እንዳለበት ነው። በአምልኮ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ መሳተፍ አለብን እንጂ ዝም ብለን ልንቀመጥና ምስጋናውንና ዝማሬውን ሁሉ ሌሉች እንዲያደርጉልን መጠበቅ የለብንም። አምልኮ ዝም ብሎ ተቀምጦ የመመልከት ድርጊት አይደለም፡፡ ለምሳሌ፥ መዘምራን ሲዘምሩ ብቻ የማዳመጥ ሳይሆን መሳተፍ አለብን። (ለምሳሌ፥ በአንድነት መዘመርና እግዚአብሔርን ማመስገን ነው)። በአምልኮ ፕሮግራማችን ለሕዝቡ ሁሉ በቂ ጊዜ በመስጠት በአምልኮ እንዲሳተፉ ለማድረግ መጠንቀቅ እንጂ በመዘምራን እንዲስተናገዱ ብቻ ማድረግ የለብንም። 

ረ. አምልኮ ድብቅ በሆነው በልባችን ክፍል ሊፈጸም ቢችልም፥ ብዙ ጊዜ የሚገለጠው ግን በንግግር ነው፤ ስለዚህ በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ውስጥ ሕዝቡ በጉባኤ መሐላ ሲያደርግ፥ እግዚአብሔርን ሲያመሰግን፥ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይና ሲዘምር እንመለከታለን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው እውነቶች፥ በእግዚአብሔር ፊት እውነተኛ አምልኮ ምን እንደሆነ እንድንረዳ እንዴት ይረዱናል? ለ) በተለያዩ ክርስቲያኖች ላይ አንዳንድ ጊዜ ችግር የሚፈጥሩት የትኞቹ እውነቶች ናቸው? ለምን? ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪ እንደ መሆንህ መጠን በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያለውን የአምልኮ ብቃት በማሻሻል፥ አምልኮው የሚፈጸመው ከልማድ ሳይሆን፥ ከልብ እንዲሆን ምን ማድረግ ትችላለህ?

 1. በመጽሐፍ ቅዱስ በአጠቃላይ የምንመለከተው አንድ መንፈሳዊ መመሪያ አለ። መታዘዝ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ በረከትን ሲያመጣ፥ አለመታዘዝ ደግሞ የእግዚአብሔርን ፍርድ ወይም የሥነ-ሥርዓት እርምጃን ያመጣል። የእግዚአብሔር የሆኑት እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር በሚታዘዙ ጊዜ ይባረኩና ሰላምን ያገኙ ነበር። እንደዚሁ እግዚአብሔርን ስንታዘዝ እግዚአብሔር ዛሬም እኛን ይባርከናል፤ ነገር ግን በተመሳሳይ መንገድ፥ ለእግዚአብሔር በማንታዘዝበት ጊዜ በአንድ መንገድ የእግዚአብሔርን ፍርድና ቅጣት እንቀበላለን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ለእግዚአብሔር በታዘዝህ ጊዜ እግዚአብሔር እንዴት እንዳከበረህና እንደባረከህ ምሳሌዎችን ስጥ። ለ) ለእግዚአብሔር ባልታዘዝክ ጊዜ እግዚአብሔር እንዴት እንደ ቀጣህ ምሳሌዎችን ስጥ። 

 1. የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ጸሐፊ በእግዚአብሔር ፊት የእውነተኛ ንስሐ ባሕርይ ምን እንደሚመስል ሊያስተምረን ፈልጎ ነበር። እግዚአብሔር የሚቀጣና ያለአድሉ የሚፈርድ አምላክ ቢሆንም፥ የምሕረትና የፍቅር አምላክም ነው። በእግዚአብሔር ፊት ባለመታዘዝ ስንኖር፥ ፍርዱንና ቁጣውን እንቀበላለን። እግዚአብሔር ግን ይቅር ሊለንና ለሕዝቡ ምሕረትን ሊያሳይ ሁልጊዜ ፈቃደኛ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ በእውነት ንስሐ ሲገቡና ኃጢአት ከሞላበት ሕይወት ተመልሰው እግዚአብሔር በሰጣቸው የመታዘዝ መንገድ ሲኖሩ፥ እግዚአብሔር ይቅር ይላቸውና ከእርሱ ጋር ያላቸውን ኅብረት ያድስላቸዋል፤ ነገር ግን ንስሐ እናዝናለን ከማለትና ይቅርታን የመጠየቅ ዝንባሌ ከማሳየት የላቀ ነው። ንስሐ አቅጣጫን መለወጥ የኃጢአትን መንገድ መካድ እንጂ ለኃጢአት ተግባር ይቅርታን መጠየቅ ብቻ አይደለም። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እውነተኛና ሐሰተኛ ንስሐን አወዳድር። የሚለያዩት እንዴት ነው? ለ) እውነተኛ ንስሐን የሚመለከቱ ምሳሌዎችን ጥቀስ። ሐ) የሐሰተኛ ንስሐን ምሳሌዎች ጥቀስ። መ) በሕይወትህ ያሉ አሁን ንስሐ ልትገባባቸው የሚያስፈልጉ ነገሮች ምንድን ናቸው? የእግዚአብሔርን በረከት ለመቀበል አሁኑኑ አድርገው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መጽሐፈ ዜና መዋዕል የተጻፈባቸው ዓላማዎች

 1. መጽሐፍ ቅዱስ የሚያተኩረው በእግዚአብሔር ላይ ነው። እርሱ የፍጥረታትና የሁሉ ጌታ እንዲሁም ታሪክን የሚመራና የሚወስን ነው። የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ትኩረትም በእግዚአብሔር ላይ ነው። ጸሐፊው ከምርኮ የተመለሱ እስራኤላውያን አሁንም እግዚአብሔር ለእነርሱ እንዴት እንደሚሠራ እንዲያዩ ይፈልግ ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ያለውን ሚና በመናገር ላይ አተኮረ፡፡ እስራኤልን ከዓለም ሕዝብ ሁሉ መካከል የመረጠው እግዚአብሔር ነበር (1ኛ ዜና 16፡13)። እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን መካከል በታቦቱ ፊት የሚያገለግሉ ሰዎችን ማለት ሌዋውያንን መረጠ (1ኛ ዜና 15፡2)። ዳዊትን ለንጉሥነት መረጠው (1ኛ ዜና 28፡4)። ሰሎሞንን ቤተ መቅደሱን ለመሥራት መረጠው (1ኛ ዜና 28፡5-6)። እንደዚሁም ኢየሩሳሌምን የልዩ ክብሩ መኖሪያ እንድትሆን የመረጣትና (2ኛ ዜና 6፡6) ስሙንና ክብሩን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያኖረው እግዚአብሔር ነው (2ኛ ዜና 7፡12፥16)።

ጸሐፊው የነገሥታትን ዘመን ታሪክ የከለሰው፥ እግዚአብሔር ዓላማውን ከዚህ በፊት በነበሩት ዘመናት እንደ ፈጸመ ለእስራኤላውያን ያለውንም ዓላማ እንደሚፈጽም ለማስተማር ነበር። እግዚአብሔር አሁንም ቢሆን ዓላማና ዕቅድ አለው። እግዚአብሔር ሕዝቡን አልተወም፥ አልረሳምም (1ኛ ዜና 17፡16-27)። ለአይሁድ የመጽሐፈ ዜና መዋዕል መልእክት የተስፋ መልእክት ነበር። እግዚአብሔር ለዳዊትና ለሰሎሞን እንዳደረገ አንድ ቀን ለእስራኤላውያን ሁሉ ያደርጋል (ዘካ. 14፡12-21)። 

የውይይት ጥያቄ፡ ሮሜ 8፡29-30 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ በአንድነት እንደመረጠ፥ እኛንስ በግል የመረጠን እንዴት ነው? ለ) እግዚአብሔር በቀድሞ ዘመን የሠራቸውን ነገሮች ማወቅ ዛሬ እኛን እንዴት ያነቃቃናል? 

 1. ጸሐፊው ዳዊትና ሰሎሞን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ንጉሥ ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር የገባላቸው ቃል ኪዳን ትክክለኞች ወራሾች መሆናቸውን በማሳየት ላይ ሊያተኩር ፈልጓል። «እውነተኞች እስራኤላውያን» በይሁዳ የነበሩትና በተለይ ደግሞ ከምርኮ የተመለሱት ነበሩ። የይሁዳ ነገድ አንድነቱን መጠበቅ አስፈላጊው ነበር፤ ምክንያቱም አንድ ቀን እግዚአብሔር በይሁዳ ሕዝብ መካከል በኃይል ለመሥራት ስለሚፈልግ ይመለሳል፤ ነገር ግን ጸሐፊው በተጨማሪ ሊያስተምር የፈለገው የእስራኤልን አንድነት በተመለከተ ነበር፡፡ በዜና መዋዕል መጽሐፍ ብዙ ጊዜ በእሥራኤል ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን ወደ ይሁዳ በመምጣት እውነተኛውን እግዚአብሔርን ማምለክ እንዴት እንደቀጠሉ ተጽፏል። ከይሁዳ ነገድ የሆነው መሢሑ የዳዊት ልጅ ይመጣና ዳዊት ከዚህ ቀደም እንደነገሠው ይነግሣል። ዳዊትና ሰሎሞን በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ለሚነግሡ ሌሎች መሪዎች ሁሉ ምሳሌ ነበሩ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ከዳዊትና ከሰሎሞን ሕይወት ጥናትህ፥ ለቤተ ክርስቲያን አመራር መልካም ምሳሌዎች የሚሆኑ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

 1. ለእግዚአብሔር ንጹሕ የሆነ አምልኮ አስፈላጊ መሆኑን ለሕዝቡ ለማስታወስ ነበር። ከምርኮ የተመለሱት አይሁድ የቀድሞ አባቶቻቸው እንዳደረጉት የአሕዛብን የአኗኗር ዘይቤና አምልኮ የመልመድ ፈተና ደርሶባቸው ነበር። አሁን ያንን ወደ መሰለ ሁኔታ ውስጥ ለመግባት ተቃርበው ነበር፤ ስለዚህ ጸሐፊው ለሕዝቡ ስለ ንጹሕ አምልኮ ለማስተማር የቀድሞውን ነገር ተጠቀመበት። ትንሽና ኢምንት ቢመስላቸውም እንኳ በመካከላቸው ያለውን ቤተ መቅደስ ማክበር ነበረባቸው። አምልኮአቸውንም በቤተ መቅደስ ውስጥ ብቻ መፈጸም ነበረባቸው። ለእግዚአብሔር የሚሆነውን አምልኮ ለመምራት የተመረጡትን የካህናትና የሌዋውያንን ትምህርትም መታዘዝ ነበረባቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬስ የክርስቲያኖች አምልኮ ሊበላሽ የሚችለው እንዴት ነው? ለ) አምልኮአችን ንጹሕና እግዚአብሔርን የሚያከብር መሆኑን ለማረጋገጥ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዛሬም ማድረግ የሚችሉት ነገር ምንድን ነው? 

 1. በረከት እንዲኖር መታዘዝ መኖር እንዳለበት ለሕዝቡ ለማስታወስ ነበር። ሕዝቡ እግዚአብሔር ለሰጣቸው ሕግጋት መታዘዝ ነበረባቸው። የእግዚአብሔር መልእክተኞች የሆኑት ነቢያት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ወደ እነርሱ ይዘው ሲመጡ ሊታዘዙአቸው ይገባ ነበር። ጸሐፊው ኃጢአት በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንደሚያመጣ ሊያስታውሳቸው ይፈልግ ነበር (1ኛ ዜና 28፡9)። በተጨማሪ ደግሞ ንስሐ፥ ለእግዚአብሔር መታዘዝና በእርሱ መታመን ካለ፥ እግዚአብሔር ሰላምን፥ ድልንና ብልጽግናን እንደሚሰጣቸው ለመግለጽም ፈልጎ ነበር (2ኛ ዜና 7፡14)።

የውይይት ጥያቄ፥ ) ዛሬስ ይህ ትምህርት ለእኛ የሚያስፈልገው እንዴት ነው? ለ) አለመታዘዝ ፍርድን፥ መታዘዝ ደግሞ በረከትን ወደ ክርስቲያን ሕይወት እንዴት እንደሚያመጣ ምሳሌዎችን ዘርዝር። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የዜና መዋዕል አስተዋጽኦ እና አወቃቀር

የዜና መዋዕል አስተዋጽኦ

 1. ከፍጥረት ጀምሮ አይሁድ ከባቢሎን ምርኮ እስከ ተመለሱበት ጊዜ ድረስ ያለውን እምነት የሚመለከት የትውልዶች ታሪክ የዘር ሐረግ (1ኛ ዜና 1-9)
 2. የተባበረው የእስራኤል መንግሥት

ሀ. የዳዊት ታሪክ (1ኛ ዜና 10-29)

ለ. የሰሎሞን ታሪክ (2ኛ ዜና 1-9) 

 1. የይሁዳ መንግሥት ታሪክ (2ኛ ዜና 10-36፡16) 
 2. የይሁዳ መንግሥት መማረክ (2ኛ ዜና 36፡17-23)

የመጽሐፈ ዜና መዋዕል አወቃቀር 

1ኛ እና 2ኛ ዜና መዋዕልን በአራት ዋና ዋና ክፍሎች መክፈል ይቻላል። .

 1. የመጀመሪያው ክፍል በተለይ የሚያተኩረው የዘር ሐረግ (ትውልድ) ላይ ነው (1ኛ ዜና 1-9)። ይህ ዝርዝር የዘር ሐረግ ለእኛ ምንም የሚጠቅመን ባይመስለንም፥ ለአይሁድና ለመጽሐፈ ዜና መዋዕል በጣም አስፈላጊ ነበር። ጸሐፊው ከአዳም ጀምሮ እስከ ይሁዳ መታደስ ድረስ የዘለቀውን የዘር ሐረግ የጠቀሰበት ሦስት ታላላቅ ምክንያቶች ነበሩት፡- 

የመጀመሪያው፥ ጸሐፊው ከአዳም ጀምሮ ከምርኮ በኋላ እስካሉት አይሁድ ድረስ የነበረውን የእምነት መስመር (የዘር ሐረግ) ለመናገር ፈልጎ ነው። ይህ የእምነት መስመር አይሁድ ከእስራኤልም ሆነ ከይሁዳ ቢሆኑ አንድ ሕዝብ እንደሆኑ የሚያሳይ ነበር። የዘር ግንዳቸው ከአንድ አባት ከአብርሃምና ከአንድ ሰው ከአዳም እንደሆነ የሚያሳይ ነበር።

ሁለተኛው፥ የዘር ግንዱ (ሐረጉ) የሚያተኩረው በሌዊና በይሁዳ ነገድ ላይ ነበር። እነዚህ ሁለት ነገዶች የካህናትና የነገሥታት ነገዶች ስለሆኑ በጣም አስፈላጊዎች ነበሩ። ጸሐፊው እነዚህ ሁለት ነገዶች አሁንም ቢሆን የሕዝቡ ትክክለኛ መሪዎች እንደሆኑና የዘር ሐረጋቸውም እንዴት እንደ ቀጠለ ለማሳየት ፈልጎ ነበር። የሌዊ ነገዶች የሃይማኖት መሪዎች ነበሩ። በመጽሐፈ ነህምያ እንደምንመለከተው፥ የዘር ሐረጋቸው ዞሮ ዞሮ ወደ አሮን የማይደርስ በቤተ መቅደስ ውስጥ እንደ ካህናት ማገልገል አይችሉም ነበር (ነህ. 7፡64-65)። መጽሐፈ ዘና መዋዕል በተጻፈበት ጊዜ ነገሥታት ባይኖሩም፥ የይሁዳ ነገድ መኖር ብቻ እንኳን ከዳዊት ዘር የሆነ ንጉሥ እስራኤልን እንደሚገዛ እግዚአብሔር ለዳዊት የገባው ቃል ኪዳን ማረጋገጥ ነበር።

ሦስተኛ፥ ይህ የዘር ሐረግ ዝርዝር ሕጋዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለመስጠት የሚረዳ ነበር። ይህ የዘር ሐረግ በኩር የሆኑ የወንዶች ስም ስለሚዘረዝር፥ የቤተሰብ ውርስ፥ የፖለቲካ ሥልጣንና የመሬት ባለመብትነት መስመርን የሚያሳይ ነበር።

በዜና መዋዕል ያለውን የዘር ሐረግ ዝርዝር በኦሪት ዘፍጥረትና በማቴዎስ ወንጌል ካለው ጋር ስናወዳድር አንዳንድ ልዩነቶችን እንመለከታለን። ይህንን ልዩነት የምናብራራበት የተለመደው መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ብዙ ጊዜ የዘር ሐረጎችን ለማሳጠር ከመሀል አንዳንዶቹን ስሞች መተዋቸው ነው። በዕብራይስጥ «ልጅ» የሚለው ቃል «ዘር» ማለትም ስለሚሆን፥ በአንዳንድ ሁኔታዎች የዘሩን ሐረግ በማሳየት ረገድ በርካታ ትውልዶች ይዘለላሉ። 

 1. ዳዊትና የሰሎሞን ዘመነ መንግሥት፡- የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ጸሐፊ አብዛኛውን የ1ኛና የ2ኛ ሳሙኤል ክፍል እንደገና ቢተርክም፥ በዜና መዋዕል ውስጥ የተሰጠው ትኩረት ለየት ያለ ነው። የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ያተኮረው ዳዊት ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ልዩ ግንኙነት ከቃል ኪዳኑ ታቦትና ከቤተ መቅደሱ ጋር በነበረው ግንኙነት እንዴት እንደገለጠው በማሳየት ነው። የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦል የእግዚአብሔርን ታቦት ተወና እርሱንም እግዚአብሔር ንቆ ተወው። ዳዊት ግን የእግዚአብሔርን ታቦት አከበረና ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ዳዊትን ቤተ መቅደሱን ይሠራ ዘንድ ባይፈቅድለትም እንኳ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለመሥራት የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ አዘጋጀ፤ የቃል ኪዳኑ ታቦትም መኖር የነበረበት በዚያ ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት በጣም ያሳሰበውና ትኩረቱን በእርሱ ላይ ያደረገው ለምን ይመስልሃል?

አይሁድ እግዚአብሔር በሰማይ የሚኖርና ከሰማይ ሆኖ የሚገዛ መሆኑን የሚያውቁ ቢሆንም እንኳ የቃል ኪዳኑን ታቦት የእግዚአብሔር ሕልውና ቁሳዊ አምሳያ አድርገው ይመለከቱት ነበር። በእርግጥ እግዚአብሔርን በታቦቱ አይወስኑትም ነበር። ታቦቱ ግን የእግዚአብሔርን ሰማያዊ ዙፋን በምድር ላይ የሚወክል ምድራዊ ዙፋን ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በመካከላቸው ለመሆኑ ቁሳዊ የሆነ ተወካይ እንጂ የሚመለክ ነገር አልነበረም። በዳዊት ዓይን ይህን የእግዚአብሔር ሕልውና ምልክት የሆነው የእግዚአብሔር ታቦት ጊዜያዊ በሆነ ሕንጻ ወይም በድንኳን መኖሩ ትክክል አልነበረም። ዳዊት ለእግዚአብሔር ወይም ለታቦቱ የሚሆን ቤት ማለትም ቤተ መቅደስ ለመሥራት መፈለጉ ለእግዚአብሔር ያለው ፍቅር መግለጫ ነበር። ይህን እንዲያደርግ እግዚአብሔር ለዳዊት ባይፈቅድለትም እንኳ የዳዊት ልጅ የአባቱን ምኞት ፈጽሞአል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ለእግዚአብሖር ያለንን ፍቅር ለማረጋገጥ ዛሬ ልናደርጋቸው የምንችል አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) እግዚአብሔር ዛሬ የሚኖረው የት ነው? (1ኛ ቆሮ. 6፡19)። ሐ) ዳዊት በብሉይ ኪዳን ታቦቱንና ቤተ መቅደሱን ባከበረ ጊዜ ለእግዚአብሔር የሰጠውን ዓይነት ክብር እንዴት ለእግዚአብሔር መስጠት እንችላለን?

መጽሐፈ ዜና መዋዕል በሰሎሞን ላይም አተኩሮአል። ሰሎሞን ታላቅ የሆነው ስለ ጥበቡና ስለ ታላቁ ቤተ መንግሥቱ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር የሚመለክበት ትልቅ ቤተ መቅደስ በመሥራቱ ነበር።

የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ስለ ዳዊትም ሆነ ስለ ሰሎሞን አንዳችም ክፉ ነገር አለመጨመሩን ማየት የሚያስገርም ነው። ይህን ያላደረገው የእነዚህን ሁለት ሰዎች ኃጢአትና ችግር ባለማወቁ አልነበረም፤ ነገር ግን በዳዊትና ሰሎሞን ሕይወት ታሪክ ላይ ያተኮረው ሁለት ዓላማዎች ስለነበሩት ነው። በመጀመሪያ፥ ዳዊትንና ሰሎሞንን ሌሎች ነገሥታትና የእግዚአብሔር ሕዝብ መሪዎች ሁሉ ሊከተሏቸው የሚገቡ መልካም ምሳሌነት ያላቸው መሪዎች እንደሆኑ ለማመልከት ነበር። እግዚአብሔርን ስለሚወዱትና ስለሚያከብሩት እርሱም በተራው አከበራቸው። እንደ ጸሐፊው አመላካከት ፍጹም መሪዎች እንደመሆናቸው፥ ለመጨረሻው ታላቅ ንጉሥ ተምሳሌቶች ነበሩ፤ ያም ንጉሥ እንደ ዳዊት የሚነግሥ መሢሕ ሲሆን ከኃጢአት ግን የራቀ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ፣ ጸሐፊው ዳዊትና ሰሎሞን እንዴት የሙሴና የኢያሱ ምሳሌዎች እንደ ነበሩ አሳይቶአል። ዳዊት እንደ ሙሴ ነበር። ሁለቱም በእግዚአብሔር የተወደዱ ነበሩ። ሁለቱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ መሪዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ ሁለቱም የተመኙት ነገር አልሆነላቸውም፡፡ ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር መግባት አልቻለም፤ ዳዊት ደግሞ ቤተ መቅደሱን መሥራት አልቻለም። የሁለቱም ግብ በእነርሱ ቦታ በተተኩ ሰዎች ከፍጻሜ ሊደርስ ቻለ።

ሰሎሞን እንደ ኢያሱ ነበር። የእግዚአብሔርን ሕዝብ ወደ ዕረፍትና ወደ ብልጽግና ለማድረስ በሁለቱም እግዚአብሔር ተጠቅሞባቸዋል (1ኛ ዜና 22፡8-9 እና ኢያሱ 11፡23፤ 21፡44)። ዳዊትና እግዚአብሔር ለሰሎሞን የሰጡት የማበረታቻ ቃላት በአብዛኛው ለኢያሱ ከተሰጡት ጋር ተመሳሳይ ነበሩ። (1ኛ ዜና 22፡11-13፥ 16፤ 28፡7-10፥ 20፤ 2ኛ ዜና 1፡1ን ከዘጻ. 31፡5-8፥ 23፤ ኢያሱ 1፡5-9 ጋር አወዳድር)።

 1. የይሁዳ ነገሥታት፡- መጽሐፈ ዜና መዋዕል ሁሉንም የይሁዳ ነገሥታት ባይጠቅስም እንኳ «መልካም» ለሆኑና እግዚአብሔርን ለሚፈሩ መሪዎች ጸሐፊው በተለይ ትኩረት የሰጠው ነው። እንደ ዳዊትና ሰሎሞን በነበሩና ቤተ መቅደሱን በማንጻት፥ ንጹሕ የሆነ የእግዚአብሔር አምልኮ እንደገና በመጀመር፥ እንዲሁም የጣዖት አምልኮ በማጥፋት እግዚአብሔርን ባከበሩ መሪዎች ላይ አትኩሮአል።
 2. መጽሐፈ ዜና መዋዕል የሚደመደመው በምርኮ ነው። ጸሐፊው ትኩረት ያደረገው፥ ነቢያት ሕዝቡ ወደ ምርኮ እንደሚወሰዱና ይሁዳ እንደምትጠፋ፥ እንደምትታደስም በተናገሩት ላይ ነው። የእግዚአብሔርን ቅጣት ያስከተለው የእግዚአብሔር ሕዝብ ዓመፅ ነበር። ይህ ቅጣት የዳዊት ሥርወ መንግሥት መጥፋትንና የቤተ መቅደሱን መደምሰስ አስከተለ። የዳዊት ሥርወ መንግሥት ሊታደስ ባይችልም ቤተ መቅደሱ ግን እንደገና ተሠርቶአል። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የዜና መዋዕል ታሪካዊ ሥረ መሠረት 

የዜና መዋዕልን ዓላማ ለመረዳት መቼ እንደተጻፈና ለምን እንደተጻፈ መረዳት ያስፈልጋል። መጽሐፈ ዜና መዋዕል የተጻፈው የይሁዳ ሕዝብ በባቢሎን ከተደመሰሱ በኋላ ነበር። የይሁዳን ሕዝብ ታላቅና ልዩ ያደረጓቸው ያለፉ ነገሮች ሁሉ ጠፍተዋል። ቤተ መቅደሱ ተደምስሷል። የኢየሩሳሌም ቅጥርም ፈርሷል። ማንኛውም የዳዊት ዘር አሁን በዙፋን ላይ የለም። ከ70 ዓመታት በኋላ በ538 ዓ.ዓ. አንዳንድ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም ቢመለሱም፥ የይሁዳ ሕዝብ በቁጥር ጥቂትና በፖለቲካም ደካማ ነበሩ። ይሁዳ የፋርስ መንግሥት አንደ ክፍለ ሀገር ነበረች። ሕዝቡም ራሳቸውን የቻሉ ሕዝብ ሳይሆኑ በፋርስ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ነበሩ፡፡ ቤተ መቅደሱ የተሠራ ቢሆንም ከቀድሞው የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ጋር ሲወዳደር በጣም ትንሽና ከመኖር የሚቆጠር አልነበረም። የኢየሩሳሌም ቅጥሮች በነህምያ መሪነት እንደገና ቢሠሩም፥ የታላቁ የዳዊት መንግሥት ዋና ከተማ የነበረችው ኢየሩሳሌም ትንሽና ደካማ ነበረች። 

ከዚህም የተነሣ የይሁዳ ሕዝብ ተስፋ ቆረጡ። «እግዚአብሔር አሁንም ከእኛ ጋር ነውን?» ብለው ጠየቁ። ከባቢሎን መፍረስ በኋላ ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረን ግንኙነት ምንድን ነው? እግዚአብሔር ከአብርሃምና ከዳዊት ጋር የገባቸው ቃል ኪዳኖች አሁንም ይሠራሉ ወይስ ቀርተዋል? ከባቢሎን ውድቀት በኋላ ለብዙ ዓመታት ስለኖሩ እግዚአብሔር የመረጠን ሕዝብ ከሆንን የይሁዳ ሕዝብ እንዲጠፉ ለምን ፈቀደ? እግዚአብሔር ስሙንና ክብሩን ለማድረግ የመረጣት ከተማ ኢየሩሳሌም ለምን ጠፋች? እነዚህና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ስለነበሩዋቸው፥ የሕዝባቸውን ታሪክ መማር ነበረባቸው። እግዚአብሔር በዓለም ሕዝብ ሁሉ ላይና በይሁዳም ላይ ያለውን የሉዓላዊነት ቁጥጥር መማር ነበረባቸው። እግዚአብሔር ከአብርሃም፥ ከእስራኤልና ከዳዊት ጋር ለገባው ቃል ኪዳን በመታዘዝ ታማኝ የመሆናቸውን አስፈላጊነት መማር ነበረባቸው። የኃጢአት ውጤት ምን እንደሆነና የእግዚአብሔርን ፍርድ እንዴት እንደሚያመጣ መረዳት ነበረባቸው። እግዚአብሔር አንድ ቀን የእስራኤልን መንግሥት ለመመለስ ጻድቅ የሆነውን ንጉሥ እንደሚያስነሣ ሊነገራቸው ይገባ ነበር። መጽሐፈ ዜና መዋዕል የማስጠንቀቂያና የማበረታቻ መጽሐፍ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪክ መረዳት የሚያበረታታን እንዴት ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪክ መረዳት ከእውነት እንዳንርቅ የሚያስጠነቅቀን እንዴት ነው?

መጽሐፈ ዜና መዋዕል የታሪክ ዘገባውን የጀመረው ከፍጥረት መጀመሪያ ነው። ከአዳም ይጀምራል። የተለያዩ ሰዎችን የዘር ሐረግ በመመልከት፥ የእምነት መስመር ከአዳም ጀምሮ በተለያዩ የእምነት አባቶች ወደ ዳዊት እንዴት እንደደረሰ ያሳየናል። ጸሐፊው የዘር ሐረጎችን በመዘርዝር፥ የአመራር ሥልጣን ወደ ሌዋውያንና ካህናት፥ ደግሞም ወደ ዳዊትና ልጆቹ እንዴት እንደደረሰ ያሳየናል። 

በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ውስጥ የተተነተኑት ታሪኮች ግን ዳዊት ከነገሠበት ከ 1020 ዓ.ዓ. የባቢሎን ምርኮ እስከ ሆነበት እስከ 538 ዓ.ዓ. ጊዜ ያለውን የሚያካትቱ ናቸው። ይህም ማለት ሁለቱ መጻሕፍት ከ2ኛ ሳሙኤል እስከ 2ኛ ነገሥት መጨረሻ ድረስ ያለውን ጊዜ የሚያካትቱ ናቸው ማለት ነው። 

ጸሐፊው የሚገልጸው የእነዚህን ጊዜያት ታሪክ ቢሆንም የሚያተኩረው ግን በተለዩ እውነቶች ላይ መሆኑ ግልጽ ነው። የሚከተሉትን ነገሮች ልብ ብለህ ተመልከት፡-

 1. ጸሐፊው የእግዚአብሔርን ሕልውናና ቤተ መቅደሱን በሚያመለክተው በቃል ኪዳኑ ታቦት ላይ ያተኩራል። 
 2. ጸሐፊው በሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ላይ ከማተኮር ይልቅ፥ በይሁዳ ላይ በነገሡት በዳዊት ልጆች ላይ ያተኩራል። በተለይ ደግሞ የዳዊት መንፈሳዊ ልጆች በመሆን በይሁዳ ምድር ሃይማኖታዊ መነቃቃትን ባመጡ ሰዎች ላይ ያተኩራል (ምሳሌ፡- አሳ፥ ሕዝቅያስ፥ ኢዮስያስ ወዘተ)።

እነዚህ ሁለት እውነቶች በጣም ጠቃሚ የሆኑት ለምንድን ነው? መጽሐፈ ዜና መዋዕል የተጻፈው ኢየሩሳሌም ከፈረሰችና ባቢሎንም ከወደቀች በኋላ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል። በእርግጥ የተጻፈው አንዳንድ የአይሁድ ቅሬታዎች ለመኖር ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሱበት ጊዜ ነበር። ቤተ መቅደሱን ሲገነቡም እንኳ፥ ሰሎሞን የሠራው ዓይነት ቤተ መቅደስ አልነበረም። የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ሠርተዋል። በፖለቲካ አንጻር ግን አሕዛብ በሆነው በፋርስ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ነበሩ። በይሁዳ ሕዝብ የቀድሞ የፖለቲካ አመራር ታላቅነት ላይ ከማተኮር ይልቅ፥ የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ጸሐፊ የፖለቲካ ታላቅነት የመንፈሳዊ ታላቅነትን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆነ ሊያስገነዝባቸው ፈለገ። ዳዊትና ሰሎሞን ሌሉችም የቀድሞ ነገሥታት ዕቅዳቸው በከፍተኛ ደረጃ ሊከናወንላቸው የቻለው፥ በነበራቸው የግል ኃይልና ሥልጣን ሳይሆን ለእግዚአብሔርና ለሕጉ በነበራቸው ታዛዥነት ምክንያት ነበር። ስለዚህ ጸሐፊው የፖለቲካ ታላቅነት ከመንፈሳዊ ታላቅነት ቀጥሎ የሚመጣ ነገር መሆኑን ሊያሳያቸው ፈልጎ ነበር። ይሁዳ በፖለቲካ ወደ ታላቅነት ልትመጣ የምትችለው፥ በመንፈሳዊ ነገር ታላቅ ከሆነች በኋላ ብቻ ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ እውነት ዛሬም በዚህ ዘመን በመንፈሳዊ ነገር ታላቅ ሳይሆኑ፥ በቁጥር ሊበዙና በልማት ተግባር የታወቁ ለመሆን ለሚፈልጉ አብያተ ክርስቲያናት ጠቃሚ የሚሆነው እንዴት ነው? 

ከ500-300 ዓ.ዓ. የይሁዳ መንግሥት፥ በተለይ በስተሰሜን በኩል በሰማርያ የሐሰት ትምህርት መስፋፋት አጋጥሞት ነበር። በቀድሞው ሰሜናዊ እስራኤል ከነበሩ አይሁድና አሕዛብ የመጡ እነዚህ ድብልቅ ሳምራውያን፥ የራሳቸውን የተበላሸ አምልኮ ከመጀመራቸው እንዲያውም የረከሰ ቤተ መቅደስ በመሥራት አሁራ ማዝዳ የሚባለውን አምላካቸውን ማምለክ ጀምረው ነበር፤ ከዚያም በኋላ የግሪክ ሃይማኖት የመስፋፋት አደጋም ነበር። ስለዚህ የዜና መዋዕል ጸሐፊ፥ ለእግዚአብሔር ያላቸውን አምልኮ በንጽሕና የመጠበቅ አስፈላጊነትን ለአይሁድ ያስታውሳቸዋል። ጊዚያዊ የሆኑ ተሐድሶዎች በዕዝራና በነህምያ አልፎ አልፎ ሲደረጉም ለረጅም ጊዜ ግን አልቆዩም። ሕዝቡ ወዲያውኑ ወደ ጣዖት አምልኮ ይመለሰ ነበር፡፡

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) የእግዚአብሔር ሕዝብ ዓለምን መምሰል እንደሌለባቸውና የሐሰት ትምህርት ገብቶ እውነተኛ እምነታቸውን እንዲያጠፋ መፍቀድ እንደሌለባቸው ማስታወስ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ለ) የሐሰት ትምህርትን ቤተ ከርስቲያንህን እንዴት እንደ ጎዳት ምሳሌ ስጥ። ሐ) የቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች ሐሰተኛ ትምህርት ለመዋጋት ምን ያደርጋሉ? መ) የሐሰት ትምህርትን በተሻለ ሁኔታ ለመዋጋት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ማድረግ ይችላሉ? ሠ) የሐሰት ትምህርትን ለመዋጋት፥ ታሪክን በተሻለ ሁኔታ መረዳት ለምን ይጠቅማል?

አይሁድ ሌላ ንጉሥ በእነርሱ ላይ እንደሚነግሥ ተስፋ ቢያደርጉም ከዳዊት ዘር የሆን ንጉሥ ከዚያ በኋላ አልተነሳም። ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ተስፋ የተሰጣቸውን መሢሕ ሲጠብቁ ቢቆዩም ነጻ ሊያደርጋቸው ገና ወደ እነርሱ አልመጣም ነበር።

የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ሌላ ታሪክ እንዲጽፍ ያስፈለገበት ምክንያት ይህ ነበር። ሕዝቡን ሊያስታውስ የፈለገው አንድ ቀን እስራኤል ተመልሶ እንደሚቋቋም ነበር። እንደ ዳዊት ያለ እጅግ መልካም መሪ አንድ ቀን ሕዝቡን እንደገና ይመራል። በእርሱም መሪነት እውነተኛ ሃይማኖታዊ ተሐድሶ ይኖርና ሕዝቡ እግዚአብሔርን ይወዳሉ፤ ይታዘዙታልም። ይህ ሰው እስኪደርስ ድረስ ሕዝቡ ለእግዚአብሐር ታማኞች እንዲሆኑና በኃጢአታቸው ምክንያት የእግዚአብሔርን ፍርድ እንዳይቀምሱ ያስጠነቅቃቸዋል፤ ያበረታታቸዋልም።

መጽሐፈ ዜና መዋዕልን ከሌሎች መጻሕፍት ጋር ስናወዳድረው፥ ጸሐፊው በውስጡ ያቀረባቸውን ነገሮች በመምረጥና በማደራጀት ከሌሎቹ የተለየ ነው። በተጨማሪም በአንዳንዶቹ የዜና መዋዕል ታሪኮች ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ታሪኮችና ቁጥሮች በሌሉች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከሚገኙት የተለዩ ናቸው። የእነዚህ ልዩነቶች ምክንያቶች ምን እንደሆኑ ሙሉ በሙሉ ባናውቅም የሚከተሉት ነገሮች ለልዩነቶቹ መከሰት ምክንያት ከሆኑት አንዳንዶቹ ናቸው፡-

 1. በመጽሐፈ ሳሙኤልና ነገሥት ውስጥ ምን እንደተጻፈ ይህ ጸሐፊ ያውቅ ስለነበር በድጋሚ ሊጽፈው አልፈለገም፤ ነገር ግን ዜና መዋዕልን ለመጻፍ የተነሣበትን የሥነ-መለኮት ዓላማ ለመደገፍ የሚያስችሉትን ነገሮች ብቻ መረጠ። 

የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ክፍሎች አወዳድር። በዜና መዋዕልና በሌሎቹ ክፍሎች መካከል ያለውን የቁጥር ልዩነት ዘርዝር (2ኛ ሳሙ. 23፡8 እና 1ኛ ዜና 11፡11፤ 2ኛ ሳሙ. 24፡9 እና 1ኛ ዜና 21፡5)። 

 1. በመጽሐፈ ዜና መዋዕል፥ ሳሙኤልና ነገሥት መካከል ባሉ ተመሳሳይ ታሪኮች አንዳንድ የቁጥር ልዩነቶች አሉ። በተመሳሳይ ታሪክ ውስጥ ካሉ 213 ቁጥሮች፥ 19ኙ ልዩነት አላቸው። ይህንን አንዳንዶቹ ጸሐፊዎች በሚገለብጡበት ጊዜ የሠሩት ስሕተት ነው ለማለት እንችላለን። ሌሎቹ ደግሞ ቀጥተኛ ቁጥሮች ሳይሆኑ ግምታዊ ወይም የተጠጋጉ ናቸው።

ለእነዚህ ልዩነቶች ምክንያቶቹ ምን እንደሆኑ ሙሉ ለሙሉ ባናውቅም፥ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ስለ መሆኑና ስሕተትም እንደሌለበት ያለንን መረዳት አይለውጠውም። ቀደም ሲል እንደተማርነውና ክርስቲያኖችም እንደመሆናችን መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ ጽሑፎቹ ምንም ስሕተት እንደሌለበት ቢገኝበትም እንኳ በቅጂዎች ምክንያት ስሕተት እንደሚፈጥር እናምናለን። ለዚህ ልዩነት አሁን ግልጽ የሆነ ምክንያት ባይኖረንም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ሐቀኛና አንዳች ስሕተት የሌለበት ለመሆኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አንድ ቀን ያ ልዩነት ከምን እንደመጣ እንገነዘባለን።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ1ኛና 2ኛ ዜና መዋዕል መግቢያ

1ኛና 2ኛ ዜና፥ ከዳዊት ጊዜ ጀምሮ የይሁዳ መንግሥት በባቢሎን እጅ እስከ ወደቀበት ድረስ ያለውን የነገሥታትን ዘመን ታሪክ እንደገና ይናገራሉ። ብዙ ሰዎች እነዚህ ታሪኮች ለሁለተኛ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለምን እንደገቡ በማሰብ ይገረማሉ። ሁለት ሰዎች የመኪና አደጋን የመሰለ ክስተት ቢመለከቱ፥ የሚሰጡት ገለጣ አንድ ዓይነት እንደማይሆን ሁሉ መጽሐፈ ዜና መዋዕልም የብሉይ ኪዳን ነገሥታትን ታሪክ የጻፈበት የራሱ የሆነ የተለየ ዓላማ አለው። 1ኛና 2ኛ ዜናን በመረዳት ስለ ዳዊት፥ ስለ ሰሎሞንና ስለ ሌሎች የይሁዳ ነገሥታት ከፍተኛ ግንዛቤን እናገኛለን።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የአንድን ታሪክ የተለያዩ አመለካከቶች ማየት ጥሩ የሚሆነው ለምንድ ነው? ለ) ስለተፈጸመው ነገር እውነተኛውን ለመረዳት ይህ የሚጠቅመን እንዴት ነው?

ቀደም ሲል ከተመለከትነው ጥናታችን እንደምታስታውሰው፥ የሳሙኤልን፥ የነገሥታትንና የመሳሰሉትን የታሪክ መጻሕፍት የጻፉ ጸሐፊዎች ዓላማቸው በዚያ ዘመን የተፈጸሙትን ነገሮች ሁሉ መተንተን አልነበረም። ይልቁንም የጻፉት ነገር ሕዝቡ አባቶቻቸው በወደቁበት ተመሳሳይ ኃጢአት እንዳይወድቁ ለማስተግር ግልጥ ዓላማዎች ነበሯቸው። የ1ኛና 2ኛ ዜና መጻሕፍት ጸሐፊም የመጽሐፈ ነገሥት ታሪክ የያዘውን የነገሥታት ታሪክ የደገመበት ምክንያት ነበረ። ይህም ዓላማ ከምርኮ በኋላ የነበሩ አይሁዳውያን እግዚአብሔርን እንዴት እንደሚያመልኩና ለእርሱ እንዴት ታማኝ ሆነው ሊቆዩ እንደሚችሉ፥ በዚህም ዓይነት በእግዚአብሔር መባረክን ማግኘት እንደሚችሉ ለማስተማር ነበር።

የ1ኛና 2ኛ ዜና መጻሕፍት አብዛኛውን የ2ኛ ሳሙኤል፥ የ1ኛና 2ኛ ነገሥት ታሪክ ይደግሙታል። ከሳኦል ሞት በኋላ ስለ ነበረውና በሉዓላዊነቱ ስለ ቆየው የእስራኤል መንግሥት ይተርኩልናል። 1ኛ ዜና መዋዕል የእስራኤል ታላቅ ንጉሥ በነበረው በዳዊት ላይ ያተኩራል። አንድ መልካም የሆነ የአይሁድ ሕዝብ መሪ ምን እንደሚመስል በማሳየት፥ የአይሁድ ሕዝብ መሪዎችና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምሳሌነቱን ይከተሉ ዘንድ የዳዊትን ታሪክ እንደገና ይነግረናል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች አርዓያነቱን መከተል ይችሉ ዘንድ መልካም ምሳሌነት ያለው ሰው የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? 1ኛ 1ቆሮ 11፣1 ተመልከት። ለ) ጳውሎስ ለክርስቲያኖች የሰጠው ትእዛዝ ምንድን ነው? ሐ) ይህ ትእዛዝ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሙሉ ለአባሎቻቸው ሊናገሩት ከሚገባው ትእዛዝ የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

2ኛ ዜና መዋዕል በድጋሚ የሚናገረው የመጽሐፈ ነገሥት የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ታሪኮች ነው። ይህም ታሪክ በድጋሚ የሚያወሳው የንጉሥ ሰሎሞንና የይሁዳን ነገሥታት ታሪክ ነው። ታሪኩ የሚያበቃውም የይሁዳ ሕዝቦች ወደ ምርኮ እስከተወሰዱ ድረስ ያለውን በመናገር ነው። 

2ኛ ዜና የ2ኛ ሳሙኤል እንዲሁም የ1ኛና የ2ኛ ነገሥት ታሪክ በድጋሚ የቀረበበት ቢሆንም፥ የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ዓላማ ከመጽሐፈ ነገሥት ዓላማ የተለየ ነበር፤ ስለዚህ ጉዳይ በኋላ እናጠናለን። 

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛና 2ኛ ዜና መዋዕልን ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልከት። ስለ መጻሕፍቱ የተጠቀሱትን አስፈላጊ የሆኑ እውነቶች ዘርዝር።

1ኛና 2ኛ ዜና መዋዕል ርዕስ

እንደ 1ኛና 2ኛ ሳሙኤልና እንዲሁም እንደ 1ኛና 2ኛ ነገሥት ሁሉ፥ 1ኛና 2ኛ ዜና መዋዕል በመጀመሪያ አንድ መጽሐፍ ነበር። ልክ እንደ ሌሎቹ መጻሕፍት ሁሉ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ለሁለት የተከፈለው የዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን፥ ወደ ግሪክ ቋንቋ በተተረጎመበት ጊዜ ነው። በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ የዚህ መጽሐፍ ርዕስ ከመጽሐፉ መጀመሪያ ዐረፍተ ነገር ላይ የተገኘ ሲሆን፥ የነገሥታት «ዘመን ቃላት» ወይም «ድርጊቶች» የሚል ነው። «ዜና መዋዕል» የሚለው የእንግሊዝኛው ቃል ትርጉም «ዘገባ» ማለት ሲሆን፥ በነገሥታት ዘመን የነበረው መለኮታዊ ታሪክ ዘገባ ማለት ነው። በአማርኛ «ክስተቶች ወይም ታሪክ» ማለት ነው። 

የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ጸሐፊ 

መጽሐፍ ቅዱስ የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ማን እንደሆነ ጨርሶ ስለማይናገር፥ በበኩላችንም የምንሰጠው አስተያየት ግምታዊ ነው። የዕብራውያን ትውፊት የመጽሐፉ ጸሐፊ ታሪኩን በመጽሐፈ ዕዝራ ያነበብነው ካህን ዕዝራ ነው ይላል። መጽሐፈ ዕዝራ፥ ነህምያና ዜና መዋዕል በአንድ ጸሐፊ መጻፋቸውን የሚያመለክት በርካታ ተመሳሳይነት አለ በማለት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይስማማሉ፤ ነገር ግን ሌሎች ምሁራን ደግሞ በርካታ ልዩነትም ስላለ ጸሐፊው ዕዝራ አይደለም ይላሉ። 1ኛና 2ኛ ዜና የተጻፉት በአንድ ሰው ነው።

ጸሐፊው ማን እንደሆነ ባናውቅም ዳሩ ግን የታሪክ ሰው፥ የሥነ መለኮት ትምህርት አዋቂና ሃይማኖታዊ መምህር መሆኑን ከጻፈው መጽሐፉ እንገነዘባለን። ይህንን የምንመለከተው የጻፋቸውን ነገሮች በመረጠበት ሁኔታ ነው። በአንድ በኩል መጽሐፈ ዜና መዋዕል “ስብከት” እንደሆነ መመልከት እንችላለን፤ ምክንያቱም ጸሐፊው ለእግዚአብሔር በታማኝነት ስለ መቆምና እርሱን በቅድስና ስለማምለክ አንዳንድ እውነቶችን ለሕዝቡ ለማስተማር እንደተጠቀመበት ስለምናይ ነው። የብሉይ ኪዳን ታሪኮችን የማስተማርያ መሣሪያዎች አድርጎ ተጠቅሞባቸዋል።

መጽሐፈ ዜና መዋዕል የተጻፈበት ጊዜ

የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ታሪኮች ከዳዊት ዘመን ከ1020 ዓ.ዓ. ጀምሮ የይሁዳ ሕዝብ እስከተበተኑበት እስከ 538 ዓ.ዓ. ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል። ጸሐፊው ማን እንደሆነ ስላላወቅን፥ ይህ መጽሐፍ መቼ እንደተጻፈ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ከመጽሐፉ በግልጽ የምንመለከተው ግን፥ ባቢሎን ከወደቀች ከብዙ ዓመታት በኋላ የተጻፈ ሳይሆን እንደማይቀር ነው። ይህ የተጻፈው አይሁዶች ከስደት ወደ ይሁዳ በ538 ዓመተ ዓለም ከተመለሱ በኋላ ነው። ጸሐፊው ዕዝራ ከሆነ የተጻፈው በ450 ዓ.ዓ. ነው። አንዳንድ ምሁራን መጽሐፉ የተጻፈው በ300 ዓ.ዓ. ነው ብለው ቢያስቡም፥ ከዘሩባቤል በኋላ በ400 ዓ.ዓ. ሳይሆን አይቀርም (1ኛ ዜና 3፡17-21)። 

የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ጸሐፊ የተጠቀመባቸው ምንጮች 

የመጽሐፈ ዜና መዋዕልን ታሪክ የጻፈው አንድ ጸሐፊ ብቻ ቢሆንም መጽሐፉን ለመጻፍ ግን የተለያዩ ነገሮችን አልተጠቀመም ማለት አይደለም። በዚህ ዘመን ያሉ ምሁራን የተለያዩ መጻሕፍትን እንደሚያነቡና ሲጽፉም እንደሚጠቅሱ ሁሉ የዜና መዋዕል ጸሐፊም በተለያዩ መረጃዎች ተጠቅሞአል። የዜና መዋዕል ጸሐፊ ለዓላማው ምቹ ሆነው ያገኛቸውን የተለያዩ ታሪኮች ከተለያዩ መጻሕፍት በመጠቀም ሌሎቹን ታሪኮች ትቶአቸዋል። ለምሳሌ በ2ኛ ሳሙኤል የዳዊትንና የቤርሳቤህን የኃጢአት ታሪክ እናነባለን። የዜና መዋዕል ጸሐፊ ይህንን ታሪክ የሚያውቀው ቢሆንም የጻፈበትን ዓላማ ስለማያንጸባርቅ አላካተተውም። ቀጥሎ ጸሐፊው መጽሐፈ ዜና መዋዕልን ለመጻፍ ከተጠቀመባቸው ከምናውቃቸው መጻሕፍት አንዳንዶቹ ተዘርዝረዋል፡-

 1. የመጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ መጻሕፍት፥ እንደ ፔንታቱክ፥ ሳሙኤልና ነገሥት የመሳሰሉ 
 2. የተለያዩ የዘር ሐረግ የተተነተነባቸው ሌሎች መጻሕፍት (1ኛ ዜና 4፡33፤ 5፡17፤ 7፡9) 
 3. ደብዳቤዎችንና የታወቁ የመንግሥት መዛግብትን (1ኛ ዜና 28፡11-12፤ 2ኛ ዜና 32፡16-17) 
 4. በሌላ መዛግብት የተጻፉ ግጥሞችና ቅኔዎች፥ ጸሎቶች ንግግሮችና መዝሙሮች (1ኛ ዜና 16፡8-36፤ 29፡10-22፤ 2ኛ ዜና 29፡30፤ 35፡25) 
 5. እንደ እስራኤልና የይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ፥ የዳዊትንና የሰሎሞንን መመሪያዎች የያዙ ሌሎች የታሪክ መጻሕፍት (2ኛ ዜና 16፡11፤ 26፡22፤ 35፡4) 
 6. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኙ የነቢያት ጽሑፎች፥ ማለትም (የሳሙኤል፥ የናታንና፥ የጋድ ዜና መዋዕል፥ የአሐያና የአዶ ትንቢተች የሻማያ፥ የኢዩና የኢሳይያስ ዘገባዎች ናቸው፤ 1ኛ ዜና 29፡29፤ 2ኛ ዜና 9፡29፤ 12፡15፤ 20፡34፤ 32፡32)። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)