ዘሌዋውያን 23-27

ሰዎች እግዚአብሔርን የሚያመልኩባቸው የተለዩ ቀናት ከሌሏቸው በቀር፥ የሳምንቱን ቀናት በሙሉ በሥራ ወደ ማሳለፍ በማዘንበል፥ ስለ መንፈሳዊ ነገር ለማሰብና እግዚአብሔርን ለማምለክ ጊዜ ሊያጡ ይችላሉ። ለአይሁድ ከተለመደው ዕለታዊ ተግባራቸው ዞር የሚሉባቸውንና ስለ እግዚአብሔር በማሰብ እርሱን የሚያመልኩባቸው የተለያዩ ሃይማኖታዊ በዓላትን ሰጣቸው። አይሁድ ሳምንታዊ የአምልኮ ቀን፥ ወርኃዊ የአምልኮ ቀን፥ በየዓመቱ የሚደረጉ ሰባት የአምልኮ ቀናት፥ በየሰባት ዓመቱ የሚሆን የአምልኮ ዓመትና በየ50 ዓመቱ የሚፈጸም ልዩ የአምልኮ ጊዜ ነበራቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እኛ የምንጠቀምባቸው ዋና ዋና ሃይማኖታዊ በዓላት የትኞቹ ናቸው? ለ) ትኩረታችንን የበለጠ በእግዚአብሔር ላይ እንድናደርግ የሚረዱን እንዴት ነው?

የውይይት ጥያቄ፦ ዘሌ. 23-27 አንብብ። ሀ) የተለያዩ የአምልኮ ቀናትንና ዓላማቸውን ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔርን በመታዘዝ የሚገኙ በረከቶችና ባለመታዘዝ የሚመጡ ቅጣቶች ምንድን ናቸው? ለእግዚአብሔር የተገባ ስዕለትን ወይም ቃል ኪዳንን ስለመጠበቅ በዚህ ስፍራ የተሰጠው ትምህርት ምንድን ነው? 

 1. ሃይማኖታዊ በዓላት (ዘሌ. 23)

አይሁድ እርሱን ለማምለክ መለየት ስለሚገባቸው ቀናት እግዚአብሔር በግልጥ አዞአቸዋል። በመጀመሪያ፥ ሳምንታዊ የአምልኮ ቀን የሆነው ሰንበት ወይም ቅዳሜ ነው። እግዚአብሔር ከመፍጠር ሥራው ያረፈበትን የሰንበት ቀን ማንም ሰው በማክበር ማረፍና እግዚአብሔርን ማምለክ ስላለበት፥ በሰንበት እንዲሠራ አይፈቀድለትም ነበር።

ሁለተኛ፥ የወር መባቻ የተባለው ወርሐዊ የአምልኮ ቀን ነበር፤ (ዘኁል. 10፡10)። ይህ ቀን እግዚአብሔር ለአይሁዳውያን ሌላ ወር ስለሰጣቸው ለመታሰቢያ የሚያከብሩት ዕለት ነው።

ሦስተኛ፣ ዓመታዊ የአምልኮ ቀናት ነበሩ። 

ፋሲካ (ዘጸ. 12፡1-4፣ ዘሌ 23፡5፣ 1ቆሮ 5፡7)

ቀኑ፡- አንደኛ ወር (መጋቢትና ሚያዝያ) 

የበዓሉ አላማ፡- እስራኤላውያን ከግብጽ ነጻ የወጡበት ቀን መታሰቢያ (ለአንድ ቀን)  

በዓሉ የሚያመለክተው ትንቢት፡- ክርስቶስ የፋሲካው በግ መሆኑን ለማሳየት

የቂጣ በዓል (ዘጸ. 12፡15-20፣ ዘሌ ዘጸ. 23፡6-8)

ቀኑ፡- አንደኛ ወር ከፋሲካ ወር በኋላ ወዲያውኑ 

የበዓሉ አላማ፡- እግዚአብሔር ከግብጽ አቻኩሎ ነጻ እንዳወጣቸው (ለ1 ሣምንት)

በዓሉ የሚያመለክተው ትንቢት፡- ክርስቶስ ሃጢአት የሌለበት የእግዚአብሔር በግ መሆኑንና እኛም እንዴት ቅዱሳን መሆን እንዳለብን ለማሳየት (1ቆሮ 5፡6-8)

የበኩራት በዓል (ዘሌ. 23፡9-14)

ቀኑ፡- በቂጣ በዓል ጊዜ ውስጥ (1ኛ ወር)

የበዓሉ አላማ፡- ምርቱንና የሚያስፈልጋቸውን የሚሰጣቸው እግዚአብሔር እንደሆነ ለማሳሰብ (ለ1 ቀን)

በዓሉ የሚያመለክተው ትንቢት፡- የክርስቶስ ትንሣኤ የበኩራት መሆኑን ለማሳየት (1ቆሮ 15፡20-23)

በዓለ ኅምሣ (ዘሌ. 23፡9-14)

ቀኑ፡- ከፋሲካ በኋላ 50ኛ ቀናት (ግንቦት-ሰኔ)

የበዓሉ አላማ፡- የመከር መጨረሻንና የእግዚአብሔር የለጋስነት ስጦታን ለማክበር (ለ1ቀን)

በዓሉ የሚያመለክተው ትንቢት፡- የቤተ ክርስቲያን ጅማሬ (ሐዋ 2)

የመለኮት ድምጽ (ዘሌ. 23፡23-25)

ቀኑ፡- የሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን (መስከረም-ጥቅምት)

የበዓሉ አላማ፡- ከሁሉም በላይ የተቀደሰውን ሰባተኛ ወር ለመጀመር፣ ሃይማኖታዊ አዲስ አመት ለመጀመር፣ እስራኤልን ለእግዚአብሔር በጎነት ለማቅረብ (ለ1 ቀን) 

በዓሉ የሚያመለክተው ትንቢት፡- የወደፊቱን የእስራኤልን መሰብሰብ ለማመልከት

የስርየት ቀን (ዘሌ. 16፡23፣ 26-32)

ቀኑ፡- በሰባተኛው ወር (መስከረም-ጥቅምት)

የበዓሉ አላማ፡- ለሕዝቡ ሃጢአት መሥዋዕት ለማቅረብ፣ ቤተ መቅደሱን ለአምልኮ ለማንጻት

በዓሉ የሚያመለክተው ትንቢት፡- የክርስቶስን ሞት ለማመልከት (ሮሜ 3፡24-26) የወደፊቱን የእስራኤል ንስሐ ለማመልከት (ዘካ 12)

የዳስ በዓል (ዘሌ. 23-33-36)

ቀኑ፡-በሰባተኛው ወር (መስከረም-ጥቅምት)

የበዓሉ አላማ፡- ለምርቱ ምስጋናን ለማቅረብ፣ የአርባ አመት የምድረበዳ ኑሮን ለማስታወስ፣ (1ኛ ሳምንት)

በዓሉ የሚያመለክተው ትንቢት፡- የወደፊቱን የእስራኤል መንግሥት ለማመልከት

አንዳንዶቹ የበዓል ቀናት ክርስቶስን የሚያመለክቱ መሆናቸው ግልጥ የሆነው ከአዲስ ኪዳን ትምህርት ነው። ነገር ግን አንዳንዶቹ በዓላት ስለ ክርስቶስ የሚያሳዩ ናቸው የሚለውን ግምታዊ አስተሳሰብ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ሲስማሙባቸው በሌሎቹ ግን ተቀባይነትን አላገኙም።

አራተኛ፥ ዓመታዊ ሰንበት የሚባል በየሰባት ዓመቱ የሚመጣ አንድ ልዩ በዓል ነበር (ዘሌ. 25፡1-7)። በዚህ ዓመት ሊያርሱም ሆነ መከር ሊሰበስቡ አይችሉም ነበር። ይህ ለእስራኤላውያን የሚያስተምረው መከሩ የሚመጣው ከእግዚአብሔር እንደሆነና ለምግባቸውም መታመን ያለባቸው በእግዚአብሔር እንጂ በራሳቸው ሥራ አለመሆኑን ነው።

አምስተኛ፥ የኢዮቤልዩ ዓመት የሚባልም ነበር (ዘሌ. 25፡8-55)። ይህ አምሳኛው ዓመት ወይም እንደ አይሁድ አቆጣጠር፥ የዓመታት ሰንበት ሰባተኛ ዙር ነው። በዚህ ዓመት ከማምረትና መከርን ከመሰብሰብ ማረፍ ብቻ ሳይሆን፥ ባሪያዎች ሁሉ ነፃ ይሆናሉ። መሬት በሙሉ ለባለቤቱ ይመለሳል። ይህም እነርሱም ባሪያዎች እንደነበሩ በማሰብ ለባሮች መራራት እንዳለባቸው እስራኤላውያንን ለማስተማር ነበር። መሬትን ለቀድሞ ባለንብረቶች የመመለሱ ሥርዓትም፥ ሀብታሞች የበለጠ እየበለጸጉ እንዳይሄዱና ድሆችም ምድራቸውን ሁሉ በማጣት የበለጠ ድሆች እንዳይሆኑ የሚከላከል ነው። እንዲሁም መሬት የእግዚአብሔር እንጂ የራሳቸው እንዳልሆነ ተገንዝበው፥ ለረጅም ጊዜ ማከራየት እንጂ መሸጥ እንደሌለባቸው ለማሳሰብ ነው።

ስለ ሃይማኖታዊ ቀናት የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡- 1. በቁጥር 7 ላይ ትኩረት አለ። ሰባት በዓላት አሉ፤ አብዛኛዎቹ በዓላት ደግሞ በሰባተኛው ወር የሚከበሩ ናቸው። እያንዳንዱ ሰባተኛው ዓመትና የዓመታቱ ሰባት ሱባዔዎች በሙሉ የተቀደሱ ናቸው፤ ምክንያቱም በአይሁዳውያን አእምሮ ሰባት ፍጹምነትንና ብቃትን የሚያመለክት ልዩ ቁጥር ነው። 

 1. አይሁዳውያን ወንዶች ሁሉ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደው እንዲያከብሩ የሚፈለግባቸው ሦስት በዓላት ነበሩ። እነርሱም ፋሲካ፥ በዓለ ኃምሳና የዳስ በዓል ነበሩ።
 2. እነዚህ በዓላት ለአይሁዳውያን የማስተማሪያ መሣሪያዎች ነበሩ። እያንዳንዱ በዓል እግዚአብሔር ለልጆቻቸው ቀድሞ ምን እንዳደረገላቸው ለማስተማርና ራሳቸውንም ለማሳሰብ አመቺ ጊዜያት ነበሩ (ለምሳሌ፡- በግብፅ በባርነት የነበሩበትን ጊዜና እንዴት ነጻ እንደወጡ) ደግሞም ለየዕለቱ በሚያስፈልጋቸው ነገር በእግዚአብሔር ላይ ያለማቋረጥ እንዴት ይደገፉ እንደነበር የሚያሳስቧቸው ነበሩ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የእኛ የገናና (የልደት) የፋሲካ (የትንሣኤ) በዓላት ከእነዚህ በዓላት ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው? ለ) ቀድሞ እስራኤላውያን ያደርጉት ከነበረው አከባበር ስለእነዚህ በዓላት ዓላማ ምን ልንማር እንችላለን? 

 1. በመታዘዝ የሚገኝ በረከትና አለመታዘዝ የሚያስከትለው ቅጣት (ዘሌ. 26) 

በሲና ተራራ የተሰጠው ቃል ኪዳን በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነበር። እግዚአብሔር፥ ሕዝቡን ሊባርካቸው ቃል የገባላቸው፥ የሚታዘዙትና የሚከተሉት ከሆነ ብቻ ነበር። ከታዘዙት እግዚአብሔር ምድሪቱን በልግሥናው በሰብል እንደሚባርካት፥ ሰላምን እንደሚሰጣት፥ ለሕዝቡ በጠላቶቻቸው ላይ ድልን እንደሚያቀዳጃቸው፥ እነርሱንና ከብቶቻቸውንም ፍሬያማ እንደሚያደርጋቸው፥ ከሁሉም በላይ በመካከላቸው እንደሚሆንና በልዩ መንገድ እንደሚገናኛቸው ገለጠላቸው።

የማይታዘዙት ከሆነ ግን እነዚህን ነገሮች ሁሉ አያገኙም ነበር። በዘሌ. 26፡14-45 የተጠቀሱት ቅጣቶች፥ በኤርምያስ ዘመን በአይሁድ ላይ ስለደረሱት ነገሮች አስቀድመው የተነገሩ ትንቢቶች መሆናቸውን መመልከት የሚያስገርም ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ዜና 36፡20-21፤ ኤር. 26፡9-11 አንብብ። እነዚህ ጥቅሶች በዘሌ. 26 የተጠቀሱትን አንዳንድ ቅጣቶች የሚገልጹት እንዴት ነው?

መታዘዝ ከእግዚአብሔር ጋር ላለን ኅብረትና በረከቱን ለመቀበላችን መሠረት ነው። እግዚአብሔርን ከታዘዝን ይባርከናል። በከፍተኛ ሥጋዊ በረከት ሊባርከን ይችላል፤ የየዕለት ምግባችንን ይሰጠናል፤ ሰላምን በልባችን ያፈሳል፤ የእርሱ መሆናችንን ያረጋግጥልናል፤ ወዘተ። እርሱን ካልታዘዝነው ግን በአንድ ወቅት ሐሴት ስናደርግበት የነበረውን በረከት ከእኛ በመውሰድ ይቀጣናል። ውስጣዊ ሰላማችንና እርሱን የማወቃችንን ደስታ ይወስድብናል፤ ወዘተ። አንድ ጊዜ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፡- «እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ ከሚመላለስ ክርስቲያን የበለጠ ምስኪን በምድር ላይ የለም።»

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የዚህን ነገር እውነተኛነት በሕይወትህ ምን ያህል አይተሃል? ለ) በሕይወትህ ምን ዓይነት የተደበቀ ኃጢአት እንዳለ ለመረዳት አሁን ራስህን መርምር። እግዚአብሔር ይቅር እንዲልህና በረከቱን እንዲመልስልህ ጸልይ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ዘሌዋውያን 11-22

እግዚአብሔር ሕዝቡን የጠራው በፊቱ ቅዱሳን እንዲሆኑ ነው። ከዓለም የተለዩ መሆን አለባቸው። ይህ ልዩ መሆን በውስጣዊ ሕይወታችን ከሚኖር ለውጥ ይጀምራል። እኛ አዲስ ፍጥረት ነን (2ኛ ቆሮ. 5፡17)። ለውጥ ሁልጊዜ መጀመር ያለበት ከውስጥ (ከልብ) እንጂ ከድርጊት አይደለም። ይህም ማለት ልባችን በፍቅር፥ በደስታ፥ በሰላም፥ በትዕግሥት፥ ወዘተ. (ገላ. 5፡22-23) መሞላት አለበት ማለት ነው። የተለዩ ዝንባሌዎችና ዓላማዎች ሊኖሩን ይገባል። ደግሞም ይህ ልዩነት ውጫዊ በሆኑ ተግባራት ራሱን ይገልጣል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በጌታችን ባመንክ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ልብህን የለወጠባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? ለ) በጌታ ባመንክ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ተግባርህን የለወጠባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? (ሐ) አንዳንድ ክርስቲያኖች በውስጣዊ ሳይሆን በውጫዊ ለውጥ ላይ ብቻ የሚያተኩሩት ለምንድን ነው? ይህ ትክክል ነውን?

የእስራኤል ሕዝብ የተለዩ መሆን ነበረባቸው፤ ቅዱሳን መሆን ነበረባቸው። ስለዚህ ልዩ መሆናቸውን ለማጠናከር፥ እግዚአብሔር በርካታ ሕግጋት ሰጣቸው። ሆኖም እነዚህ ሕግጋት የተሰጧቸው እንዲያው በዘፈቀደ አልነበረም። አብዛኛዎቹ ለእስራኤል ሕዝብ ጥቅም የዋሉ ግልጽ የሆኑ ዓላማዎች ነበራቸው፡፡

የውይይት ጥያቄ፥ ዘሌ. 11-22 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ቁጥሮች የተጠቀሱ የተለያዩ የሕግ ዓይነቶችን ወይም ክፍሎችን ጥቀስ። ለ) የማስተስርያ ቀን በዓል ዓላማ ምን ነበር? ሐ) ዘሌ. 18፡1-5 አንብብ። እነዚህ ቁጥሮች የኦሪት ዘሌዋውያንን ትምህርት የሚያጠቃልሉት እንዴት ነው? መ) ከእነዚህ ምዕራፎች ስለተቀደሰ ኑሮ የምንማራቸው አንዳንድ መመሪያዎች ምንድን ናቸው?

ዘሌ. 11-22 የእስራኤላውያንን የሕይወት ክፍል ሁሉ የሚነኩ በርካታ የሆኑ የተለያዩ ዓይነት ሕግጋትን ይዟል። እነዚህ ሕግጋት ጊዜያዊ ነበሩ። በአዲስ ኪዳን ዘመን ለምንኖር ለእኛ ግዴታዎች አይደሉም (ማር. 7፡14-22 አንብብ)።

 1. ስለምግብ የተሰጡ ሕግጋት (ዘሌ. 11)፡- እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን እንዲበሉ የተፈቀዱላቸው ምግቦች ምን ዓይነት እንደሆኑ ነገራቸው። በመሬት ላይ የሚኖሩ፥ ሣር በልተው የሚያመሰኩትና ሸኮናቸው የተሰነጠቀ እንስሳት ብቻ ለምግብነት ተፈቅደው ነበር። እነዚህ እንስሳት ብቻ «ንጹሐን» ሲባሉ የቀሩት ግን «ርኩሳን» ተብለው ነበር። ከዓሣ ዓይነቶች ክንፍና ቅርፊት ያላቸው ብቻ ለምግብነት ተፈቅደው ነበር። ከበራሪ እንስሳትና ከወፎች እንዲበሉ የተፈቀዱት የተወሰኑት ብቻ ነበሩ።
 2. ሴቶች ከወለዱ በኋላ የሚጠብቁት የመንጻት ሥርዓት (ዘሉ. 12)፡- ሴት ከሰውነትዋ ደም በሚፈሳት በማንኛውም ጊዜ በሃይማኖታዊ ሥርዓት ያልነጻች (ርኩስ) ትሆናለች። ስለዚህ ደም ከሰውነትዋ የሚፈስባት ልጅ የመውለጃዋ ጊዜ ስለሆነ ከተጠቀሰው ጊዜ በኋላ መሥዋዕት በማቅረብ እስክትነጻ ድረስ የረከሰች ትሆን ነበር።
 3. ስለ ቆዳ በሽታ፥ በልብስ፥ ወይም በቤት ግድግዳ ላይ ስለሚታዩ ያልተለመዱ ምልክቶች የተሰጠ ሕግ (ዘሌ. 13-14)፡-

እንደምታስታውሰው፥ በአይሁዳውያን አስተሳሰብ ያልተለመደ ማንኛውም ዓይነት ነገር የኃጢአት ምልክት ወይም ምሳሌ ነው። ይህ በራሱ ኃጢአት ወይም የኃጢአት ውጤት አልነበረም። ያልተለመዱ የቆዳ በሽታዎችና በልብስ ወይም በቤት ግድግዳ ላይ የሚታዩ ምልከቶች ኃጢአትን የሚያመለክቱ ስለነበሩ፥ በተሰጠው ሕግ መሠረት የመንጻት ሥርዓቶች መፈጸም ነበረባቸው።

 1. ከሰውነት የሚወጣ ያልተለመደ ፈሳሽ (ዘሌ. 15)፡- ከወንድም ሆነ ከሴት የሚወጡ የፍትወት ፈሳሾች ያልተለመዱ ሆነው ስለሚቆጠሩ፥ ሰውየውን (ሴትዮዋን) ያረክሳሉ። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች የነካ ሰው ወይም በእነዚህ ሰዎች የተነካ ዕቃ መልሶ እስኪነጻ ድረስ የሚቆይበት የተወሰነ ጊዜ ነበር።
 2. የማስተስርያ ቀን በአይሁዳውያን የቀን መቁጠሪያ ከሁሉም የሚበልጥ ሃይማኖታዊ በዓል ነው (ዘሌ. 16)። ስለዚህ እንዴት ሊጠብቁት እንደሚገባ የተሰጡ በጥንቃቄ የተሞሉ ትእዛዛት ነበሩ። የማስተስርያ ቀን ዓላማ ሕዝቡንም ሆነ የመገናኛውን ድንኳን በየዓመቱ ውስጥ ከገጠማቸው ከማናቸውም ዓይነት ዕርኩሰት ማንጻት ነው። ያለፈውን ዓመት ኃጢአት በማንጻት ሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ የሆነ አዲስ የሃይማኖት ዓመት ይጀምሩ ዘንድ ነው። የማስተስርያ ቀን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ኃጢአት በእነርሱ ላይ ያመጣውን አጠቃላይ ተጽዕኖ በማሳሰብ በእግዚአብሔር ፊት ያለማቋረጥ መንጻታቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለአይሁድ የሚያሳይ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነበር። እግዚአብሔር በጸጋው ኃጢአታቸውን ይቅር እንዳለና ከእነርሱም እንዳራቀው ሕያው በሆነ መግለጫ ለእስራኤላውያን በማሳየት፥ ፍየልን ወደ በረሃ የመስደድ ሥርዓት ነበር። በቃል ኪዳኑ ታቦት የስርየት መክደኛ ላይ ደምን ይረጭ ዘንድ ሊቀ ካህኑ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚገባበት ብቸኛ ዓመታዊ ቀን ይህ የሥርዓት ቀን ነበር።
 3. እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ስለ እንስሳት ደም ግልጽ የሆነ መመሪያ ሰጣቸው። እንደምታስታውሰው ደም የእንስሳት ሕይወት ምልክት ነበር (ዘሌ. 17፡11)። ስለዚህ እንስሳትን በሚያርዱበት ጊዜ ደማቸውን ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲጠነቀቁ ግልጥ የሆነ ትእዛዝ ተሰጥቶአቸው ነበር።
 4. እግዚአብሔር፥ አንድ ሰው ማንን ማግባት እንዳለበትና ማንንስ ማግባት እንደሌለበት ግልጥ የሆነ ትእዛዝ ሰጥቷል (ዘሌ. 18)። በተጨማሪ ወንድና ሴት የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም የሌለባቸውን ጊዜያት በሚመለከት ትእዛዛት ተሰጥተዋል።
 5. እግዚአብሔር፥ ሕዝቡ ከእርሱ ጋርና እርስ በርስ ስለሚኖራቸው ግንኙነት ግልጥ የሆኑ ትእዛዛትን ሰጥቷል። የእግዚአብሔርን ሕግ በግልጥ የማይታዘዙ ሰዎች ሊደርስባቸው ስላለው ቅጣትም ተናግሯል (ዘሌ. 19-20)።
 6. በመጨረሻም እግዚአብሔር ለካህናት የሚሆኑ ግልጥ ትእዛዛትን ሰጠ። እነዚህ ትእዛዛት ማን ካህን ሊሆን እንደሚችል፥ ካህን ማንን ማግባት እንደሚችልና እግዚአብሔርን እንዴት ማገልገል እንዳለበት የሚገልጡ ነበሩ (ዘሌ. 21-22)። የተቀደሰውን አምልኮ በመምራት ረገድ ዋናው ኃላፊነታቸው መሥዋዕትን ማቅረብ ስለነበር፥ በተለይ ይህን በሚመለከት እግዚአብሔር ለካህናት ግልጥ የሆነ ትእዛዝን ሰጣቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ እግዚአብሔር፥ ስለ ኃጢአት፥ ከእግዚአብሔር ጋርና እርስ በርስ ሊኖረን ስለሚገባ ግንኙነት ከእነዚህ ምዕራፎች የምንማራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኦሪት ዘሌዋውያን 1-10

መሥዋዕቶችንና ዓላማቸውን በትክክል መረዳት እግዚአብሔር የኃጢአት ይቅርታ ያዘጋጀበትን መንገድ ለመረዳት ይጠቅማል። ኦሪት ዘሌዋውያን ኃጢአተኛ የሆነው የእስራኤል ሕዝብ የተቀደሰውን እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንዳለበት ዝርዝር መመሪያ ይሰጣል። እግዚአብሔር ቅዱስ ባይሆን ኖሮ፥ መሥዋዕት የሚባል ነገር ባላስፈለገም ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነና ኃጢአትን ሳይቀጣ ስለማያልፍ፥ እንዲሁም መሐሪ ስለሆነ፥ ለእስራኤላውያን ወደ እርሱ እንዴት እንደሚመጡና የኃጢአታቸውን ይቅርታ እንደሚያገኙ ዝርዝር መመሪያ ሰጣቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘሌ. 1-10 አንብብ። ሀ) አምስቱን ዋና ዋና የመሥዋዕት ዓይነቶች ዘርዝር። ለ) የእያንዳንዱ መሥዋዕት ዓላማ ምን ነበር? ሐ) ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ከመሥዋዕቶች የምንማረው ነገር ምንድን ነው? መ) መሥዋዕት ስለ ኃጢአት ክፉነት የሚያስተምሩት ምንድን ነው? ሠ) ከካህናት ለአገልግሎት መለየትና ከአሮን ልጆች ሞት የምንማረው ምንድን ነው? 

ዘሌ. 1-10 በሁለት የተለያዩ ርእሶች ያተኩራል። አጠቃላይ ክፍሉ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት እስራኤላውያን እንዴት እግዚአብሔርን ማምለክ እንደ ነበረባቸው የሚናገር ቢሆንም፥ ዘሌ. 1-7 እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ሊያመልኩ ስለሚችሉበት አምስት መሥዋዕተች ይናገራል። ዘሌ. 8-10 ደግሞ የአምልኮ መሪዎች የሆኑት ካህናት ቅዱስ እግዚአብሔር የሚመለክበትን የአምልኮ ፕሮግራም ለመምራት እንዴት በጥንቃቄ እንደሚዘጋጁ ይናገራል። 

 1. ይቅርታን ለማግኘትና እግዚአብሔርን ለማምለክ የሚያስፈልጉ መሥዋዕቶች (ዘሌ. 1-7)። 

በእነዚህ ዘሌዋውያን ምዕራፎች ለእግዚአብሔር ትክክለኛ የሆነ መሥዋዕትን በትከክለኛ መንገድ ስለ መሠዋት በርካታ ሕጎች ተሰጥተዋል። የሚከተሉት ሕግጋት መሥዋዕቶቹን ሁሉ ከሚመለከቱ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡-

ሀ. መሥዋዕቶቹ ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ በነሐስ መሠዊያው ላይ መቅረብ ነበረባቸው።

ለ. እንስሶቹ ከመሠዋታቸው በፊት፥ መሥዋዕቱን የሚያቀርበው ሰው በእንስሳው ራስ ላይ እጆቹን ይጭናል። ይህም የሚደረገው ለሁለት ዓላማ ነው፡፡ የመጀመሪያው፥ እንስሳው ራስ ላይ እጆቹን መጫኑ ምትክ መሆኑን ሰውዬው ተገንዝቧል ማለት ሲሆን፥ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሰውዬው በዚህ ጊዜ ኃጢአቱን በመናዘዝ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ኃጢአቱን ሁሉ በእንስሳው ላይ ያኖራል።

ሐ. ካህኑ እንስሳውን ያርዳል።

መ. የእንስሳው ደም በመሠዊያው ላይ ይረጫል።

ሠ. እንስሳው ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ይቃጠላል።

እስራኤላውያን በአምልኳቸው ለእግዚአብሔር የሚሠዏቸው የአምስት መስዋዕቶች ዝርዝር

 1. የሚቃጠል መሥዋዕት (ዘሌ 1)

የሚቃጠለው ክፍል፡- ሁሉም

የሚሰዋው እንስሳ፡- ተባዕት ሆኖ ነውር የሌለበት፣ መስዋዕቱን በሚያቀርበው ሰው አቅም

የሚሰዋበት ምክንያት፡- ለአጠቃላይ ሃጢአት፣ ለእግዚአብሔር መሰጠትን ያሳያል

 1. የእህል ቁርባን (ዘሌ 2)

የሚቃጠለው ክፍል፡- ከፊሉ፣ ሌሎች ክፍሎችን ካህናት ይበሉታል

የሚሰዋው እንስሳ፡- እርሾ የሌለበት ቂጣ፣ ጨው ያለበት የዳቦ ሙልሙል 

የሚሰዋበት ምክንያት፡- የበኩራት ፍሬን ለእግዚአብሔር በመስጠት ስለሰብሉ እግዚአብሔርን ማመስገን

 1. ስለደኅንነት (ዘሌ 3 እና 22፡18-30)
 • ሀ) የምስጋና መስዋዕት
 • ለ) የስዕለት መስዋዕት
 • ሐ) የበጎ ፈቃድ መስዋዕት

የሚቃጠለው ክፍል፡- ስቡ፣ ሌሎች ክፍሎች በካህናትና መስዋዕቱን ባቀረበው በሕብረት ይበላል

የሚሰዋው እንስሳ፡- ተባዕት ወይም እንስት እንደ አቅራቢው አቅም 

የሚሰዋበት ምክንያት፡- 

 • ሀ) ላልተጠበቀ በረከት ምስጋናን ለማቅረብ
 • ለ) ከችግር ስለመዳን ስዕለትን ለመክፈል
 • ሐ) በአጠቃላይ ምስጋናን ለመግለጥ
 1. የሃጢአት መሥዋዕት (ዘሌ 4)

የሚቃጠለው ክፍል፡- ስቡ፣ ሌሎች ክፍሎችን ካህናት ይበሉታል 

የሚሰዋው እንስሳ፡- 

 • ካህናት ወይም ሕዝቡ፡- በሬ
 • ንጉሡ፡- ወንድ ፍየል
 • ግለሰቦች፡- ሴት ፍየል   

የሚሰዋበት ምክንያት፡- አጠቃላይ መንጻት ሲያስፈልግና ለተለያዩ የግል ሃጢአቶች ይቀርባል 

 1. የበደል መሥዋዕት (ዘሌ 5፡1-6፡7)

የሚቃጠለው ክፍል፡- ስቡ፣ ሌሎች ክፍሎችን ካህናት ይበሉታል

የሚሰዋው እንስሳ፡- ነውር የሌለበት አውራ በግ 

የሚሰዋበት ምክንያት፡- እግዚአብሔርን ወይም ሰውን ሲበድል

ስለተለያዩ መሥዋዕቶች የሚከተሉትን እውነቶች አስተውል፡-

 1. የሚቃጠል መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ ሙሉ ለሙሉ ይቃጠላል። ብዙዎች ይህ ስለ ኃጢአታችን መስዋዕት ይሆን ዘንድ ራሱን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር የሰጠው የክርስቶስ ምሳሌ እንደሆነ ያስባሉ። በሮሜ 12፡1 ላይ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ሕያው መሥዋዕት አድርገው እንዲያቀርቡ ሲጠይቅ በጳውሎስ አእምሮ የነበረው መሥዋዕት ይህ ሳይሆን አይቀርም። 
 2. እንደ አቅራቢው ሰው ዓይነቱ ይለያያል። በሥልጣን ላይ ያሉ ከፍተኛ መሥዋዕት ያቀርባሉ። ሀብታም የሆኑ ሰዎችም ትልቅ መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። ድሀ ሰው ርግብ ወይም እህል ብቻ ቢሆን እንኳ እንዲያቀርብ እግዚአብሔር ፈቅዶ ነበር። ምሕረቱን ሰዎች ሁሉ ሊቀበሉት የሚችሉ እንዲሆን የይቅርታ ማግኛ መንገድ አደረገው።
 3. የበደል መሥዋዕት የሚቀርበው ካሣ ስለሚጠየቅባቸው ኃጢአቶች ነበር። ለምሳሌ፡- አንድ ሰው አሥራቱን ለእግዚአብሔር ካልከፈለ፥ የበደል መሥዋዕት እንዲያቀርብ ይጠበቅበት ነበር። ወይም አንድ ሰው የራሱ ያልሆነውን ነገር ከጎረቤቱ ሲወስድ፥ የበደል መሥዋዕት እንዲያቀርብ ይፈለግበት ነበር። ነገር ግን የበደሉን ይቅርታ ያገኝ ዘንድ፥ መሥዋዕቱን ከማቅረቡ በፊት፥ ዕዳውን ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሰው እንዲከፍል ይጠበቅበት ነበር። ዕዳውን ሲከፍል በዕዳው ላይ አንድ አምስተኛ እጅ መጨመር ነበረበት። ይህ በሌላ ሰው ላይ በደል በምንፈጽምበት ጊዜ ካሣ እንዴት መክፈል እንዳለብን የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው። ገንዘብ ሰርቀን እንደሆነ ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን፥ ገንዘቡን መመለስም አለብን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ጊዜ ክርስቲያን ገንዘብ ወይም ሌላ ነገር በሚሰርቅበትና ይቅርታ ለማግኘት በሚፈልግበት ጊዜ፥ የሰረቀውን ነገር ይመልሳል ወይስ ይቅርታ ብቻ ይጠይቃል? መልስህን አብራራ። ለ) የበደል መሥዋዕት ይቅርታ ከመጠየቅ በፊት ገንዘቡን ስለ መክፈል ምን ያስተምረናል? ሐ) የእግዚአብሔርን ይቅርታ ከማግኘት በፊት ከሌሎች ጋር ስለ መታረቅ ማቴ. 5፡23-24 ምን ይላል? 

 1. የካህናት ለእግዚአብሔር አገልግሎት መለየት (ዘሌ. 8-10)

በእግዚአብሔር ፊት ማገልገል በቀላሉ የምናየው ነገር አይደለም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመሪነት ማገልገል በርካታ ኃላፊነትንና ከእግዚአብሔር ዘንድ ከባድ ፍርድን የሚያመጣ ነው (ያዕ. 3፡1፤ ዕብ. 13፡17)፡፡፡ ስለዚህ አሮንና ልጆቹ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በተቀደሰ አምልኮ ለመምራት ሲዘጋጁ፥ እነርሱ ራሳቸውም ሆኑ የአምልኮ ዕቃዎቹ በሙሉ በጥንቃቄ እንዲነጹ ያስፈልግ ነበር። እነዚህ ምዕራፎች በአምልኮ ሰዓት እንዴት መጠንቀቅ እንዳለብንና የቤተ ክርስቲያን አመራር ምን ያህል ከፍተኛ ነገር እንደሆነ የሚያስገነዝበን ነው።

ቀጥሎ በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና ነገሮች ተጠቅሰዋል፡-

 1. ሙሴ የአምልኮ ሥርዓት ከመጀመሩ በፊት ካህናትንና የአምልኮ ዕቃዎችን በሙሉ ያነጻቸው ነበር። ከኃጢአት ያነጻቸው ዘንድ የሚቃጠልና ባለማወቅ ስለተፈጸመ በደል የሚቀርብ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር። ልዩ የሆነ አውራ በግ ያርድና በደሙ ቀኝ ጆሮን፥ የቀኝ እጅ አውራ ጣትና የቀኝ እግር አውራ ጣትን ለማስነካት ይጠቀም ነበር። ይህም እግዚአብሔርን ለመስማት፥ ሥራውን ለመሥራትና በመንገዱ ለመሄድ ዝግጁ መሆናቸውን ያመለክት ነበር። ከዚያም ሥራውን ከመጀመራቸውም በፊት ለአንድ ሳምንት ይቆዩ ነበር። አሮንና ልጆቹ በዝግጅት ለአንድ ሳምንት ከቆዩ በኋላ፥ ሁሉንም የመሥዋዕት ዓይነቶች በማቅረብ አገልግሎታቸውን ይጀምሩ ነበር። እግዚአብሔር ነሐስ መሠዊያ ላይ ያለውን መሥዋዕት የሚያቃጥል እሳት በመላክ አገልግሎታቸውንና አምልኮአቸውን መቀበሉን ያላይ ነበር።
 2. ሁለቱ የአሮን ልጆች በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አገልግሎት ጀምረው ብዙም ሳይቆዩ እግዚአብሔር በሞት ቀጣቸው። የተሰጠው ምክንያት በጌታ ፊት የማይገባ እሳት ይዘው መቅረባቸው ነው። የናዳብና የአብድዩ ኃጢአት ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። በተገደሉ ጊዜ ለዕጣን መሠዊያ የሚሆን ዕጣን ይዘው ወደ ቅድስት የገቡ ይመስላል። ፍርዱ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡- ሀ) እግዚአብሔር ያልፈቀደውን ከሰል ወይም ዕጣን ተጠቅመው ይሆናል። ለ) ለሊቀ ካህኑ ብቻ የተፈቀደውን ሥራ ሠርተው ሊሆን ይችላል። ) ያለ አሮንና ሙሴ ፈቃድ ዕጣን አጥነው ይሆናል። መ) ሰክረው ሊሆን ይችላል። ምናልባት ከእነዚህ ልጆች ሞት በኋላ፥ እግዚአብሔር ወዲያውኑ ለአሮንና ለካህናቱ በመገናኛው ድንኳን ከማገልገላቸው በፊት እንዳይጠጡ ያዘዛቸው ስለዚህ ይሆናል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር በእነዚህ ሰዎች ላይ ወዲያውኑ ከባድ ፍርድ የሰጠው ለምን ይመስልሃል? ለ) የእግዚአብሔርን ሕዝብ ስንመራ ልንወስደው ስለሚገባን ጥንቃቄ ይህ ምን ያስተምረናል?

በእስራኤላውያንም ሆነ በቤተ ክርስቲያን የአምልኮ መጀመሪያ፥ እግዚአብሔር ፍጹም የሆነ ቅድስናን እንደሚፈልግ በኃጢአት ላይ ከባድ ፍርድ በመፍረድ ገልጧል (የሐዋ. 5፡1-11)። እግዚአብሔር ለእስራኤላውያንና ለአሮን በተለይም ለሕዝቡ ምሳሌ ይሆኑ ዘንድ ለመሪዎች የቅድስናን አስፈላጊነት ለማስተማር ፈለገ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኦሪት ዘሌዋውያን ዓላማ እና ቁልፍ ሃሳቦች

የኦሪት ዘሌዋውያን ዓላማ

የኦሪት ዘሌዋውያን ዋና ዓላማ «ቅዱስ» በሚለው ቃል ተጠቃሏል። በመጽሐፉ ውስጥ ቅዱስ የሚለው ቃል ከ90 ጊዜ በላይ ተጠቅሶአል። ጌታ ራሱ ቅዱስ እንደሆነ ይገልጻል። ሕዝቡም በእርሱ ፊት ቅዱስ ይሆኑ ዘንድ ይነግራቸዋል። ቅድስና በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ የማይነካው ነገር የለም። እግዚአብሔርን ለእስራኤል ሕዝብ እንዴት የተቀደሱ ሕዝብ እንደሚሆኑና የማያቋርጥ በረከት እንደሚያገኙ ነግሮአቸዋል። ያ ቅድስናቸው የሚያተኩረው በሁለት ዋና ዋና ነገሮች ላይ ነበር። በመጀመሪያ፥ በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ባለው መንገድ እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንደሚቻል ይናገራል።

ዛሬ በዓለም ላይ በርካታ የሃይማኖት ሰዎች አሉ። እግዚአብሔር ግን አምልኮአቸውን አይቀበልም። ለምን? ምክንያቱም እግዚአብሔርን የሚያመልኩት፥ እርሱ በሚመራቸው መንገድ ስላልሆነ ነው። እርሱ በሚቀበለው መንገድ እንዴት ልናመልከው እንደምንችል ሊነግረን የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው። በብሉይ ኪዳን፥ ሰዎች መሥዋዕት በመሠዋት እንዴት እደሚያመልኩት ገልጾላቸዋል። በአዲስ ኪዳን ደግሞ ሰዎች እግዚአብሔርን ሊያመልኩ የሚችሉበት ብቸኛ መንገድ፥ በመጨረሻው መሥዋዕት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዮሐ. 14፡6 አንብብ። ሀ) ይህ ጥቅስ እግዚአብሔርን ስለምናመልክበት ብቸኛ መንገድ ምን ይነግረናል? ለ) ይህ ጥቅስ በዓለም ዙሪያ ስላሉና፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ስለማያምኑት ሰዎች ምን ያስተምረናል?

በሁለተኛ፥ ደረጃ የተቀደስን የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደመሆናችን መጠን በቅድስና እንዴት መኖር እንዳለብን ያሳያል። በኢየሱስ ላይ ያለን እምነት እውነተኛ ከሆነ፥ ወንጌል ሕይወታችንን መለወጥ አለበት። የሚለውጠው አምልኮአችንን ብቻ ሳይሆን፥ ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለንን አኗኗር፥ አሠራራችን ወዘተ. ሁሉንም ነው። ኦሪት ዘሌዋውያን የተሰጠው፥ ሕዝቡ የእግዚአብሐር ቅዱስ ሕዝብ ሆነው እንዴት መኖር እንዳለባቸው ዝርዝር የሕይወት ሁኔታዎችን ለማሳየት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያን ከሆንክ ጀምሮ ሕይወትህ እንዴት እየተለወጠ ነው? ለ) አንተና ሌሎች የቤተ ክርስቲያንህ አባሎች የተቀደሰ ሕይወት የምትኖሩት እንዴት ነው? ምሳሌዎችን ጥቀስ። 

በኦሪት ዘሌዋውያን ውስጥ የሚገኙ ቁልፍ አሳቦች

ኦሪት ዘሌዋውያን ከኦሪት ዘጸአት ቀጥሎ መምጣቱ በጣም ትክከለኛ ነው። በኦሪት ዘጸአት የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበትን የመገናኛውን ድንኳን እንዴት እንደሠሩ ተመልክተን ነበር። በተጨማሪም የአምልኮ መሪዎች የሆኑት ካህናትና ሊቀ ካህናት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በሚደረገው አምልኮ ስለሚኖራቸው ዝግጅትም ተነግሮናል። አሁን ደግሞ በኦሪት ዘሌዋውያን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ አምልኮው ስለሚፈጸምበት መንገድ የተሰጠ መግለግጫ እናገኛለን። ደግሞም ቅዱሱን እግዚአብሔር በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለማምለክ የተፈቀደላቸው ሰዎች መንፈሳዊ ሁኔታም ተገልጦ እናያለን። የሚከተሉት በኦሪት ዘሌዋውያን ውስጥ ከሚገኙ ዋና ዋና ትምህርቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡

 1. ቅድስና

ብዙ ክርስቲያኖች ምን ማለት እንደሆን ባያውቁም እንኳ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉ እጅግ በጣም አስፈላጊ ቃላት አንዱ «ቅድስና» ነው። ኦሪት ዘሌዋውያን እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘትና እርሱ በሕይወታችን ውስጥ ሳያቋርጥ በመገኘቱ ሐሴት እንድናደርግ ሁለት ነገሮችን ማድረግ አለብን ይላል። በመጀመሪያ፥ ተገቢ የሆነ ወይም የተቀደሰ አምልኮ መፈጸም ነው። ሁለተኛው ደግሞ፥ የተቀደሰ አኗኗር ነው። ስለዚህ ቅድስና ምን ማለት እንደሆነ መረዳት አስፈላጊ ነው።

«ቅድስና» የሚለው ቃል በመሠረቱ «መለየት» ማለት ነው። በብሉይ ኪዳን ቅድስና ስለ ሁለት ዓይነት መለየት ይናገራል። በመጀመሪያ፥ የእግዚአብሔር ካልሆነ ከማንኛውም ነገር መለየት ነው። እስራኤል «የተቀደሰ» ሕዝብ የተባለው ከአሕዛብ ተለይቶ፥ የእግዚአብሔር ስለሆነ ነው። እስራኤላውያን ከአሕዛብና ከተግባራቸው በመለየት በአኗኗራችው የተቀደሱ መሆን ነበረባቸው፤ ምክንያቱም አሕዛብ ለእግዚአብሔር የተለዩ አልነበሩምና። ለአምልኮ የተለዩ እንስሳት እንኳ የተቀደሱ ይባሉ ነበር። በኦሪት ዘሌዋውያን ውስጥ ትኩረት የተሰጠው አብዛኛው ነገር ከተለመዱ ነገሮች በመለየት ቅዱስ መሆንን የሚመለከት ነው። እግዚአብሔር ልዩ በመሆኑ ቅዱስ ነው። ከተፈጠሩ ነገሮች ሁሉ የተለየና የላቀ ነው። እንደ እርሱ ያለ ማንም የለም፤ እርሱን የሚመስል ማንም የለም።

ሁለተኛው፥ ከክፉ ሥነ-ምግባር መለየት ነው። የሥነ-ምግባር ቅድስና ከኃጢአት መራቅን የሚያመለክት ነው። እግዚአብሔር ኃጢአት ስለማያደርግና ሊያደርግም ስለማይችል ሥነ-ምግባር የተቀደሰ ነው። ኃጢአታችንን ስንናዘዝና የክርስቶስ ደም ከኃጢአታችን ሁሉ ሲያነጻን በሥነ-ምግባር የተቀደስን እንሆናለን። ለእግዚአብሔር ሕግ በታዛዥነት ስንኖርና ኃጢአት ሕይወታችንን እንዳይቆጣጠር ጸንተን ስንቃወም በሥነ-ምግባር የተቀደሰ ሕይወት እንኖራለን።

በአዲስ ኪዳን፥ እኛ ክርስቲያኖች በሁለቱም መንገዶች የተቀደስን ነን። እግዚአብሔር ስለመረጠንና ከዓለም ስለተለየን የተቀደስን ነን። ነገር ግን ኃጢአትን ድል የመንሣት ሕይወት በመኖር ደግሞ በቅድስና መመላለስ አለብን። በሕይወታችን የሚኖር ማንኛውም ኃጢአት በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ሲታጠብ በእግዚአብሔር ፊት ብቁ ሆኖ ወደሚገኘው ወደ ቅድስና ደረጃችን እንደገና ሊመልሰን ይችላል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሕይወትህን መርምር። ሀ) በመጀመሪያው መንገድ የተቀደስከው እንዴት ነው? ለ) በሁለተኛው መንገድስ የተቀደስከው እንዴት ነው? ሐ) በሕይወትህ ያልተቀደስህባቸው ክፍሎች ካሉ {አሁን ተናዘዝና ከእነዚህ ኃጢአቶች ተመለስ። 

 1. ንጹሕና እርኩስ

አብዛኛው የኦሪት ዘሌዋውያን ክፍል ንጹሕ ስለሆኑና ስላልሆኑ ነገሮች፥ እንዲሁም ሰውን ንጹሕ ስለሚያደርጉና ስለማያደርጉ ነገሮች ይናገራል። ይህ ለእኛ እንግዳ ስለሆነ ለብዙዎቻችን ይህንን ሐሳብ መረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። በኦሪት ዘሌዋውያን ውስጥ የሚገኙትን፥ አብዛኛዎቹን ሕግጋት ለመረዳት የእግዚአብሔርን ዓላማዎችና የአይሁዳውያንን አስተሳሰብ መረዳት ያስፈልጋል።

በብሉይ ኪዳን፥ እግዚአብሔር ውጫዊ የሆኑ የአካል ጉድለቶችን የኃጢአት ተጽዕኖዎች ገላጭ ማስተማሪያዎች አድርጎ ሲጠቀምባቸው እናያለን። የአካል ጉድለት በራሱ ኃጢአት አይደለም። ነገር ግን አካሉ ጎዶሎ መሆን ኃጢአተኝነትን ያመለክት ነበር። ለምሳሌ፡- በሥጋው ምንም ዓይነት ጉድለት ያለበትን፥ ወይም ጤናማ ያልሆነ ሰው በክህነት እንዳያገለግል እግዚአብሔር አግዶታል (ዘሌ. 21፡17-21)። ለምን? ያ ካህን ኃጢአተኛ ነውን? አይደለም። ነገር ግን ጤናማ አለሆኑ፥ በዓለም ላይ ኃጢአት መኖሩን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ ያለውን ጥላቻ ለእስራኤል ሕዝብ በግልጽ ለማሳየትና ከታወቀ ኃጢአት የመራቃቸውን አስፈላጊነት ለመግለጥ፥ አካለ-ጎዶሉ የሆን ካህን በተቀደሰው በእግዚአብሔር ፊት እንዲያገለግል አልፈቀደም። በዘሌዋውያን ውስጥ ላሉ አብዛኛዎቹ ሕግጋት ይህ መመሪያ የሚሠራ ነው። ጤነኛ ያልሆኑ፡- እንደ የሴት የወር አበባ ወይም በሽታ ያሉቱ የኃጢአት ውጫዊ ምልክቶች ነበሩ፤ ስለዚህ ለመንጻት መሥዋዕት ይፈልጉ ነበር።

አይሁድ ነገሮችን ሁሉ በሁለት ክፍሎች ይከፍሉ ነበር። የመጀመሪያው «ቅዱስ» ወይም የተለየ የሚባለው ክፍል ሲሆን፥ ሁለተኛው ደግሞ፥ «የተለመደ» የሚባለው ክፍል ነው። እንስሳትም ሆኑ ሰዎች ከሌሎች ተለይተው ለእግዚአብሔር ሲሰጡ ቅዱስ (የተለዩ) ይሆናሉ (ለምሳሌ፡- ዘሌ. 21፡7-8)። ቅዱስ የነበሩ ነገሮች በሰዎች ዘንድ በማይገባ መንገድ ለተለመዱ ነገሮች አገልግሎት ሲውሉ፥ ቅዱስ መሆናችው ይቀርና የተለመዱ ይሆናሉ። ለምሳሌ፡- አንድ ሰው ከመንጋዎቹ መካከል አንድን ጠቦት ለመሠዋት ቃል ቢገባ፥ ያ ጠቦት ቅዱስ ይሆናል። ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናል። ቅዱስ የሚሆነው በሥነ-ምግባር አልነበረም። ለእግዚአብሔር ተመርጦ በመለየቱ ብቻ ነው። ልክ እንደዚሁ፥ ሳምሶን በሥነ – ምግባር የወደቀ ወይም የተበላሸ ሕይወት ቢኖረውም፥ ለአንድ ለተለየ አገልግሎት በእግዚአብሔር በመመረጡ ብቻ የተቀደሰ ነበር። የተለመዱ (ተራ) የሆኑ ነገሮች፡ በሥነ ምግባር የሚፈተኑ አልነበሩም፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ዓላማ ተመርጠው የተለዩ ሊሆኑ ይችላሉ። 

«ንጹሕ የመሆንና ያለመሆን» አሳብ የሚጎለብተው ከዚህ ነው። በእግዚአብሔር ፊት ጤናማ የሆኑ ነገሮች ንጹሐን ናቸው። ሣር የሚበሉና ሸሆናቸው የተሰነጠቀ እንስሳት ጤናማ ስለሆኑ፥ ንጹሐን እንስሳት ናቸው። ምንም ዓይነት አካላዊ ጉድለትና በሽታ የሌለባቸው ሰዎች ጤናማና የተለመዱ ስለሆኑ፥ ንጹሐን ናቸው፤ ነገር ግን ከተለመደው ነገር ውጭ የሆነ ማንኛውም ነገር «ንጹሕ አይደለም»። ንጹሕ ያልሆነ ነገር ሁሉ የኃጢአት ምልክት ስለሆነ፥ ወደ እግዚአብሔር ፊት ሊቀርብ ወይም ለእግዚአብሔር ሊሰጥ አይገባም ነበር። ለምሳሌ፡- አንድን ጠቦት በመሥዋዕትነት ለእግዚአብሔር በመስጠት ቅዱስ ማድረግ ይቻላል፤ ነገር ግን አንድ አካሉ ጉድለት ካለው (አንድ ዓይኑ ዕውር ቢሆን፥ ወይም ሽባ ቢሆን፥ ወዘተ.) ንጹሕ ስላይደለ፥ ለእግዚአብሔር ሊሠዋ አይገባም ወይም አንድ ሰው ያልተለመደ በሽታ ካለው ርኩስ ነበር። ከበሽታው ለመፈወሱና ንጹሕም ለመሆኑ ሁለንተናውን በማጠብ ካሳየና መሥዋዕት ካቀረበ እንደገና እንደቀሩት እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ማምለክ ይችላል።

በኦሪት ዘሌዋውያን ውስጥ ያሉትን ሕግጋት በምታጠናበት ጊዜ የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-

 1. ቅዱስ ለመሆን፥ ሰው ወይም ሌላ ነገር ተቀባይነት ባለው መንገድ ለእግዚአብሔር ይለያል። ይህ ካልሆነ የተለመደ ወይም ተራ ነገር ነውና ለማንኛውም ተራ አገልግሎት ብቻ ይውል ነበር።
 2. አንድ ነገር ንጹሕ ለመሆን አካሉ ሙሉ መሆን ነበረበት። አካለ-ጎዶሎ የሆነ ነገር ንጹሕ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ጤናማ ያልሆነ ነገር የሚያመለክተው ኃጢአትን ነውና። 
 3. አካለ ጎዶሎ የሆነ ነገር ሁሉ እርኩስ ነበር። ኃጢአት ባይሆንም እንኳ ኃጢአትን ስለሚወከል እንደገና ንጹሕ ይሆን ዘንድ መሥዋዕት ሊቀርብለት ያስፈልግ ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ንጹሕ ስለ መሆንና አለመሆን የተሰጠው ትምህርት እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ ስላለው ጥላቻ ምን ያስተምረናል? ለ) ይህ ስለተገለጠው የኃጢአት ተጽዕኖ ምን ያስተምረናል? ሐ) በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ስለ ግላዊ ቅድስና አስፈላጊነት ይህ ምን ያስተምረናል?

በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ንጹሕ መሆንና አለመሆንን በሚመለከት በውጫዊ ነገሮች ላይ አላተኮረም። ይልቁንም ሰውን የሚያረክሱት ውስጣዊ የሆኑ ወይም በሰው ልብ ውስጥ የሚፈጸሙ ነገሮች ናቸው። ምክንያቱም ግልጽ የሆነ ክፋትና ኃጢአት የሚገለጠው በሚታዩ መንገዶች (በጥላቻ፥ በቁጣ፥ በመግደል፥ በምንዝር፥ ወዘተ.) ሲሆን የሚመነጨውም ከልብ ነው (ማቴ. 15፡8-20 ተመልከት)።

አዲስ ኪዳን እኛ የተወለድነው «በኃጢአት» ነው ይላል። ምክንያቱም ሁላችንም የአዳምን የኃጢአት ባሕርይ ወርሰናል (ሮሜ 5፡12-14)። የምንቀደሰው በመስቀል ላይ በተሰቀለው በኢየሱስ ሞትና ለድነት (ደኅንነት) በእርሱ ላይ በምንታመንበት ጊዜ ለልባችን እርሱ በሚሰጠን መንጻት ብቻ ነው (1ኛ ቆሮ. 6፡9-11)። 

 1. ንጉሡ እግዚአብሔር ስለ ሕይወታችን አቅጣጫ ሁሉ ይገደዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር የሚገደው በቤተ ክርስቲያን ስለምናደርገው ወይም በመንፈሳዊ ሕይወታችን ስለሚሆነው ነገር ብቻ እንደሆነ በማሰብ ይሳሳታሉ። ሥጋዊ ናቸው የምንላቸው ነገሮች እጅ ሥራን እንደ መሥራት፥ ከሰዎች ጋር መነጋገር፥ ትምህርት ቤት መሄድ፥ ወዘተ፥ እግዚአብሔርን ብዙ የሚያሳስበው አይደሉም ይላሉ፤ ዳሩ ግን እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ያስተማረው ስለ ማንኛውም የሕይወታቸው ክፍል ዝርዝር ጉዳይ ሁሉ እንደሚገደው ነው። ንጉሣቸው እንደመሆኑ መጠን እግዚአብሔር እስራኤላውያን እንዲታዘዙትና እንዲያከብሩት የሚፈልገው በሁሉም የሕይወታቸው አቅጣጫ ነው።

ስለዚህ በኦሪት ዘሌዋውያን ውስጥ ሁሉንም የሕይወት አቅጣጫ የሚነኩ ሕግጋትን እናገኛለን። እግዚአብሔርን እንደ ማምለክ ያሉ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች የሚመለከቱ ሕግጋት አሉ። ደግሞም እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደመሆናቸው መጠን እርስ በርሳቸው እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚናገሩ ሕግጋትም አሉ። ግላዊ ስለሆኑ ነገሮች (ለምሳሌ፡- በሽታ ወዘተ) የሚናገሩ ሕግጋት ደግም አሉ። እግዚአብሔር በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ላይ ያለውን ፍላጎትና ቁጥጥር ለማሳየት ትእዛዛትን ሰጠ።

የውይይት ጥያቄ ፥ 1ኛ ቆሮ. 10፡31 አንብብ። ሀ) ይህ ጥቅስ ይህንን እውነት የሚገልጸው እንዴት ነው? ለ) እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝባቸውንና እኛ የምናደርጋቸውን አንዳንድ የተለመዱ ነገሮች ጥቀስ። ሐ) እነዚህን ነገሮች ለእግዚአብሔር ክብር በማያመጣ መንገድ ልንጠቀምባችው የምንችለው እንዴት ነው? መ) እነዚህን ነገሮች ለእግዚአብሔር ክብር በሚያመጣ መንገድ ልንጠቀምባቸው የምንችለውስ እንዴት ነው? 

 1. መሥዋዕቶች

በብሉይ ኪዳን፥ ሰው እግዚአብሔርን የሚቀርበውና የሚያመልከው መሥዋዕትን በማቅረብ ነበር። በአጠቃላይ አምስት ዓይነት የተለያዩ መሥዋዕተች ነበሩ። የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህል ቁርባን፥ የድነት (ደኅንነት) መሥዋዕት፥ የበደል መሥዋዕትና የኃጢአት መሥዋዕት ናቸው። እነዚህ መሥዋዕቶች ሁሉ የየራሳቸው ዓላማ ያላቸው ቢሆንም የሚቀርቡበት ግን ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ፡

1) አንዳንድ መሥዋዕቶች ለእግዚአብሔር ምስጋናንና ክብርን ለመግለጥ የሚቀርቡ ናቸው።

2) ሌሎች መሥዋዕቶች ደግሞ ከእግዚአብሔር ዘንድ የኃጢአት ይቅርታን ለመቀበል የሚቀርቡ ናቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘሌ. 17፡ 11ና ዕብ. 9፡22 አንብብ። የመሥዋዕት ዓላማ መሠረታዊ ግንዛቤ ምን ነበር? አብዛኛዎቹ የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች የእንስሳት ደም የሚፈስባቸው ነበሩ። ስለመሥዋዕቶች ልናውቃቸው የሚገቡ በርካታ መሠረታዊና ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች አሉ።

 1. የእንስሳው ደም የእንስሳውን ሕይወት የሚወክል ነው። ስለዚህ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን የእንስሳት ደም የኃጢአት ስርየትን ያስገኛል ሲሉ፥ እርቅን የሚያስገኘው በደሙ የተወከለው የእንስሳው ሞት ነው ማለት ነው። እንደዚሁም እኛ ስለ ክርስቶስ ደምና ስላለውም ኃይል ስንናገር፥ ስለ ሞተና በእርሱም ስለተገኘው ውጤት መናገራችን ነው።
 2. የመሥዋዕት መሠረት ምትክ የመሆን ሐሳብ ነው። በብሉይ ኪዳን አንድ ሰው አንድን እንስሳ ለመሥዋዕት እንዲሆን ሲያቀርብ፥ በእንስሳው ራስ ላይ እጁን ይጭናል። ይህን ሲያደርግ ጥፋተኛ ስለሆነ ሞት ይገባዋል ብሎ ማወጁ ነበር። ነገር ግን የእንስሳው ሕይወት ለኃጢአተኛው ሕይወት ምትክ ሆኖ የቀረበ ነው። በአዲስ ኪዳንም እንደዚሁ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ለኃጢአተኛው ሕይወት ምትክ ሆኗል። የኃጢአትን ዕዳ ለመክፈል እያንዳንዳችን መሞት ሲገባን፥ በእኛ ፈንታ ኢየሱስ ሞተ።
 3. የመሥዋዕቱ ውጤት ኃጢአትን ማስተሰረይ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) «ማስተስረይ» የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተመልከት። ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ሙሉ ትርጉም ጻፍ። ለ) ይህ ቃል እግዚአብሔር በኢየሱስ የክርስቶስ በኩል ስላደረገልን ነገር የሚገልጸው እንዴት ነው?

«ማስተሰርይ» የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን በተደጋጋሚ ያገለገለ ሲሆን፥ በግሪኩ አዲስ ኪዳን ግን አንድ ጊዜ ብቻ እናገኘዋለን (ሮሜ 5፡11)። ማስትሰረይ እግዚአብሔር ለኃጢአተኛ ሰው ይቅርታን እንዲያገኝና ከራሱ ጋር እንዲታረቅ የሠራው ሥራ ነው። በብሉይ ኪዳን የቃሉ ትርጉም «ማጥፋት»፥ «መሸፈን»፥ «ማስወገድ»፥ ወይም «መጥረግ» ማለት ነው። ኃጢአተኛው በሚያቀርበው መሥዋዕት ከእግዚአብሔር ይቅርታን ለመግዛት አይሞከርም። ይልቁንም እግዚአብሔር ለኃጢአተኛው፥ በጸጋው ከእርሱ ጋር ሊታረቅ የሚችልበትን መንገድ ሰጠው። የእርቅ መሠረታዊ አሳብ፥ በሌላ እንስሳ መሠዋት እግዚአብሔር የኃጢአተኛው ኃጢአት እንዲሸፈን ያደርግ ነበር። ልክ እንደዚሁ፥ እግዚአብሔር ጻድቃን አድርጎ ይቀበለን ዘንድ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ኃጢአታችንን ይሸፍናል። 

 1. መሥዋዕቱ ራሱ ኃጢአተኛውን የሚያድን ወይም ይቅርታ የሚያስገኝለት አይደለም። መሥዋዕቱ ውጫዊ ማስረጃ ሲሆን የኃጢአተኛው ውስጣዊ ዝንባሌ ማለትም ንስሐ መግባቱንም የሚያሳይ ነበር። ንስሐ ለመግባት የተዘጋጀ ልብ ከሌለና ለእግዚአብሔር ታዛዥ ለመሆን ይችል ዘንድ የሰውየው ሕይወት ካልተለወጠ፥ መሥዋዕቱ አንዳችም ዋጋ የለውም ፤(1ኛ ሳሙ. 15፡22-23፤ መዝ. (50፡16-17፤ ሚክ. 6፡6-8 ተመልከት)። 

የውይይት ጥያቄ፥ በዚህ ዘመን ለሚኖረን አምልኮ የዚህ እውነትነት እንዴት ነው? 

 1. የመሥዋዕት ዓላማዎች የሚከተሉት ነበሩ፡

ሀ. የእግዚአብሔርን ቅድስናና እርሱ ኃጢአትን እንዴት እንደሚጠላ፥ ደግሞም ሁልጊዜ ኃጢአትን በሞት እንደሚቀጣ ለማስተማር ነው። በብሉይ ኪዳን በኃጢአተኛው ምትክ እንስሳ ይገደል ነበር። በአዲስ ኪዳን ደግሞ የኃጢአት ቅጣት የተከፈለው በኢየሱስ ሞት ነው። 

ለ. የሰውን ኃጢአተኛነት ለማስተማር ነው። ሰው መሥዋዕት ባቀረበ ቁጥር ኃጢአተኛ መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ደግሞም የኃጢአት ደመዎዝ የኃጢአተኛው ወይም የእንስሳው ሞት መሆኑንም ያሳያል፤ (ሮሜ 6፡23)። 

ሐ. ይቅርታ የሚገኘው የኃጢአተኛውን ኃጢአት ለመሸፈን በሚፈጸም የምትክ ሞት መሆኑን ለማሳየት ነው።

መ. አንድ ኃጢአተኛ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሕይወቱን በንጽሕና የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበትና ኃጢአት ከሠራም ለመንጻትና እንደገና ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ለማድረግ ንስሐ መግባት እንዳለበት ለማስተማር ነው። 

ሠ. የእግዚአብሔርን ምሕረትና ጸጋ ለማሳየት ነው። እግዚአብሔር እያንዳንዱ ኃጢአተኛ በግል ስለ ኃጢአቱ እንዲሞት መጠየቅ ይችል ነበር። ነገር ግን እርሱ እንደዚያ ቢያደርግ ኖሮ ሁላችንም ኃጢአተኞች ስለሆንን ማንም ሰው በሕይወት አይቀርም ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር፥ ኃጢአተኛን ሰው ከራሱ ጋር የሚያስታርቅበትንና ይቅርታ የሚሰጥበትን መንገድ ሁልጊዜ ማዘጋጀቱ ምሕረቱንና ጸጋውን ያሳያል። ቅዱስ ስለሆነ፥ ኃጢአትን ሳይቀጣ አይተውም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በኃጢአተኛ ምትክ የሌላን ሰው ወይም የሌላን ነገር ሞት ጠየቀ። ነገር ግን መሐሪ ስለሆን፥ ሰው ይቅርታ በመቀበል ከእግዚአብሔር ጋር የሚታረቅበትን መንገድ አዘጋጀ። 

 1. የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች እግዚአብሔር ለኃጢአተኞች የሠዋውን የእግዚአብሔር በግ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያመላክቱ ተምሳሌቶች ናቸው (ዮሐ. 1፡29-31፤ ሮሜ 5፡6-11፤ ዕብ. 10፡10-12 ተመልከት)።
 2. የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች ክርስቲያኖች ዛሬ ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡትን መሥዋዕት የሚያመላክቱ ናቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) 1ኛ ጴጥ. 2፡5፤ ፊልጵ. 4፡18፤ ዕብ. 13፡15-18፤ ራእ. 5፡8፤ ሮሜ 15፡16-17፤ ሮሜ 12፡1፤ ፊልጵ. 2:17፤ 2ጢሞ. 4፡6 አንብብ። ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ማቅረብ የሚገባቸውን መሥዋዕቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህን መሥዋዕቶች በሕይወትህ እንዴት እየሠራህ ነው? ምሳሌዎችን ስጥ። 

 1. በብሉይ ኪዳን ሳይታሰብ ለተሠሩ ኃጢአቶች የሚቀርቡ መሥዋዕቶች ብቻ ነበሩ። አንድ ሰው ግን አውቆ በእግዚአብሔር ላይ በሚያምፅበት ጊዜ ምንም መሥዋዕት ማቅረብና ይቅርታን መቀበል አይችልም ነበር። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኦሪት ዘሌዋውያን መግቢያ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልንረዳቸው በጣም አስፈላጊ ከሆኑት አሳቦች አንዱ «የቅድስና» አሳብ ነው። ይህም የእግዚአብሔር ባሕርይ መሠረት ነው። እግዚአብሔር በኦሪት ዘሌዋውያን ውስጥ ቅዱስ እንደሆነ በመደጋገም ይናገራል። የእግዚአብሔር ሕዝቦች ማንነትና እግዚአብሔር ሕዝቦቹን ሊሆኑ የሚገባቸውን የሚያስረዳ መሠረታዊ አሳብ የቅድስና አሳብ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደ መሆናችን መጠን እግዚአብሔርን መምሰል አለብን። ዘሌዋ. 11፡44፡- «እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና፤ ሰውነታችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ» ይላል።

የውይይት ጥያቄ፥ «ቅዱስ» እና «መቀደስ» የሚሉትን ቃላት ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እይ። የእነዚህን ቃላት ትርጉም ጻፍ። ሀ) እግዚአብሔር ቅዱስ የሆነው በምን መንገድ ነው? ለ) የእግዚአብሔር ሕዝብ ቅዱስ መሆን ያለብን በምን መንገድ ነው? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ ቅድስት ነችን? ግለጽ። መ) ብዙ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም ክርስቲያኖች ለመቀደስ ያለባችው ችግር ምንድን ነው? ሠ) ዘሌዋ. 11፡44ን በቃልህ አጥና።

ኦሪት ዘሌዋውያን ስለ ቅድስና የሚናገር መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ ለመረዳትና ለመተርጎም በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም፥ በእግዚአብሔር ቅድስና ላይ የሚያተኩር በመሆኑና መመለክም ያለበት በቅዱሳን ሰዎች መሆኑን ከተገነዘብን፥ የኦሪት ዘሌዋውያንን መልእክት የበለጠ እንረዳለን። 

የኦሪት ዘሌዋውያን ርእስ

እንደሌሎቹ የፔንታቱክ መጻሕፍት ርእሶች ሁሉ የኦሪት ዘሌዋውያን – የአማርኛው ርእስም የተገኘው በግሪክ ከተጻፈው የብሉይ ኪዳን ትርጉም ከሴፕቱዋጀንት ነው። «ዘሌዋውያን» ማለት «የሌዋውያን ጉዳይ» ወይም «ስለ ሌዋውያን የተነገረ» ማለት ነው። ከጥናታችን እንደምናስታውሰው ሌዋውያን ከእስራኤል ነገዶች አንዱ ነበሩ። ዋናው ኃላፊነታቸው በብሉይ ኪዳን ዘመን ሁሉ በቤተ መቅደስ ውስጥ እግዚአብሔርን ማገልገል ነበር። ከእነዚህ ተግባራት አብዛኛዎቹ የሌዋውያን አካል የሆኑት የአሮን ቤተሰቦች ቢሆኑም ሁሉም ሌዋውያን በቤተ መቅደስ ሥራ ውስጥ የማገልገልና የመርዳት ኃላፊነት ነበረባቸው፤ ስለዚህ ይህ ስም የሚያመለክተው፥ የዚህ መጽሐፍ አብዛኛው ክፍል የእግዚአብሔር ሕዝብ አምልኮ እንዴት እንደሚመሩ ለካህናት ትእዛዝንና መመሪያን ለመስጠት ትኩረት የሚያደርግ እንደሆነ ነው። ኦሪት ዘሌዋውያን የሚያተኩረው በአምልኮ ሕግጋትና ደንቦች ላይ ነው። 

አይሁድ ለፔንታቱክ ሦስተኛ መጽሐፍ የሰጡት ስም የተለየ ነው። እንደልማዳቸው የመጽሐፉን ርእስ «እርሱም ጠራ» በማለት ሰይመውታል (ዘሌ. 1፡1)። 

የኦሪት ዘሌዋውያን ጸሐፊ

በኦሪት ዘፍጥረትና በዘጸአት ጥናታችን እንደተመለከትነው፥ ምሁራን የፔንታቱክ ጸሐፊ ማን እንደሆነና የተጻፈበት ጊዜ መቼ እንደሆነ የተለያዩ አሳብ በመስጠት ይከራከራሉ። ስለዚህ በትምህርት ሦስት ስለ ፔንታቱክ ጸሐፊ የተሰጠውን ገለጻ ተመልከት። የኦሪት ዘሌዋውያን ጸሐፊ ሙሴ እንደሆነ መጽሐፉ ባይናገርም፥ ከ25 ጊዜ በላይ «እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው» የሚል ቃል አለ። ስለዚህ ጸሐፊው ሥጋ ለባሹ ሙሴ እንደሆነ መገመቱ ትክክል ነው። 

ኦሪት ዘሌዋውያን የተጻፈበት ጊዜ

ኦሪት ዘሌዋውያን የተጻፈበት ጊዜ፥ ሕዝቡ ከግብፅ የወጡበትን ጊዜ አርቀው በሚገምቱ (1440 ዓ.ዓ.) እና አቅርበው በሚገምቱ (1220 ዓ.ዓ.) መካከል ይለያያል። ሆኖም ከሁለቱ ጊዜያት 1440 ዓ.ዓ. ትክክል ይመስላል።

በኦሪት ዘሌዋውያን መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት ነገሮች ሁሉ የተፈጸሙት በሲና ተራራ ነው። ስለዚህ ሙሴ እስራኤላውያን በሲና ተራራ በነበሩበት ጊዜ ሕግጋትን በሙሉ ተቀብሎአል ብሎ መገመቱ ትክክል ነው። የጻፋቸውም በዚያው ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። 

የኦሪት ዘሌዋውያን አስተዋጽኦ

ኦሪት ዘሌዋውያን በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል። 

 1. የተቀደሰውን አምላክ እንዴት ማምለክ እንደሚቻል (ዘሌ. 1-10)፡- በዚህ ክፍል እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን፥ ምን ዓይነት መሥዋዕት፥ በምን ምክንያት ማቅረብ እንዳለባችው ይነግራቸዋል። በተጨማሪ እግዚአብሔርን ለማምለክ ብቁ ይሆኑ ዘንድ ቄሶች እንዴት እንደሚለዩም ተጽፏል።
 2. በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ቅዱስ ሕዝብ ሆኖ መኖር እንደሚቻልና የእግዚአብሔርን በረከት እንዴት መቀበል እንደሚቻል (ዘሌ. 11-27)፡- በዚህ ክፍል እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የተለያዩ ትእዛዛትን ይሰጣል። እነዚህም ትእዛዛት የእግዚአብሔር እንደመሆናቸው መጠን በእግዚአብሔር ፊት በቅድስና እንዴት መኖር እንደሚችሉ ይገልጽላቸዋል። 

የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህ ሁለት ዓበይት ነጥቦች በዚህ ዘመን ላሉ ክርስቲያኖች የሚያስፈልጉት እንዴት ነው? ከዚህ በታች የኦሪት 1 ዘሌዋውያን ዝርዝር አስተዋጽኦ ተሰጥቶአል? 

 1. በመሥዋዕቶች አማካይነት የተቀደሰውን አምላክ ማምለክ (ዘሌ. 1-7)

ሀ. የሚቃጠል መሥዋዕት (ዘሌ. 1)፥ 

ለ. የእህል ቁርባን (ዘሌ. 2)፥

ሐ. የድነት (ደኅንነት) መሥዋዕት (ዘሌ. 3)፥

መ. የኃጢአት መሥዋዕት (ዘሌ. 4)፥ 

ሠ. የበደል መሥዋዕት (ዘሌ. 5)፥ ረ. ስለ መሥዋዕቶች የቀረቡ ልዩ ልዩ ሕግጋት (ዘሌ. 6-) ናቸው።

 1. የተቀደሰውን የእግዚአብሔርን አምልኮ ለመምራት ካህናትን  መለየት (ዘሌ. 8-10)፡

ሀ. ካህናት ለአገልግሉት ተለዩ (ዘሌ. 8)፤ 

ለ. ካህናት አገልግሎታቸውን ጀመሩ (ዘሌ. 9)፤ 

ሐ. የአሮን ልጆች ናዳብና አቢዩድ ለፈጸሙት በደል ፍርድ ተሰጣቸው (ዘሌ. 10)።

 1. በተቀደሰው እግዚአብሔር ፊት የቅድስና አንዋኗር (ዘሌ. 11-27)፡

ሀ, በሃይማኖታዊ ሥርዓት ሰውን «ስለሚያነጹት» እና «ስለሚያረክሱት» ነገሮች የተደረጉ ሕግጋት (ዘሌ. 11-15)፥ 

ለ. በእግዚአብሔር ፊት በቅድስና ስለመኖር የተደነገጉ ሕግጋት (ዘሌ. 16-25)፥ 

ሐ. የእግዚአብሔርን ሕግ በመታዘዝ የሚገኝ በረከትና ባለመታዘዝ የሚመጣ መርገም (ዘሌ. 26)፥ 

መ. በእግዚአብሔር ፊት ስለትን ስለ መፈጸም የተደነገጉ ሕግጋት (ዘሌ. 27) ናቸው። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)