ዘኁልቁ 22-36

እግዚአብሔር አንድን ሰው ለመባረክ ከወሰነ፥ ያንን ሰው መርገም አንዳች ፋይዳ ይኖረዋልን? የበለዓምና የሞዓብ ንጉሥ ታሪክ እግዚአብሔር የሚወዳቸውን ሰዎች፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶች በምንም ዓይነት ብርታት ሊረግሟቸው ቢሞክሩም፥ እርግማናቸውን እግዚአብሔር እንደሚያከሽፍ ያሳያል፤ ሙከራቸውም ከንቱ ልፋት ብቻ ይሆናል። በተጨማሪ ይህ የበለዓምና የሞዓብ ንጉሥ ታሪክ የሚያስተምረን የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚያጠፋቸው ውጫዊ ስደት ሳይሆን፥ ከዓለም ጋር ጓደኝነት መግጠማቸውና ዓለምን መምሰላቸው እንደሆነ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የማያምኑ ሰዎች አንተንም ሆነ ቤተ ክርስቲያንን ለመርገም ወይም የሚጎዳ ነገር በማድረግ በእናንተ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚያደርጓቸውን የከንቱ ሙከራ መንገዶች ዘርዝር። ለ) ክርስቲያን ዓለምን በመምሰል ሽንፈትን ሊከናነብ የሚችልባችውን መንገዶች ዘርዝር። 

የውይይት ጥያቄ፡- ዘኁ.22-36 አንብብ። ሀ) በለዓም እስራኤልን ይረግም ዘንድ እግዚአብሔር ያልፈቀደው እንዴት ነው? ለ) እስራኤላውያንን ለማሸነፍ በለዓም የተጠቀመበት ምክር ምንድን ነው? (ዘኁ.31፡8፥16 ተመልከት)። ሐ) 2ኛ ጴጥ.2፡14-16 እና ይሁዳ 11 ተመልከት። ስለ በለዓም ምን ያስተምራሉ? መ) በሁለተኛው ቆጠራ ወቅት የተገኘውን የእስራኤልን ሕዝብና የተዋጊውን ኃይል ቁጥር በየነገዱ ጻፍ። ሠ) ወንጀልን ለሠሩ ሰዎች መሸሸጊያና የስደት ከተሞች ይሆኑ ዘንድ የተለዩትን የስድስት ከተሞች ስም በዝርዝር ጻፍ።

 1. ነቢዩ በለዓም (ዘኁ.22-25)

የሞዓብ ንጉሥ እስራኤላውያን የአሞንንና የባሳንን ነገሥታት እንዳሸነፉ በሰማ ጊዜ ፈራ፤ ስለዚህ ከምድያማውያን ጋር በመተባበር፥ እስራኤላውያንን በጦርነት ከማሸነፉ ይልቅ በመለኮት ኃይል በመርገም ሊያሸንፋቸው ሞከረ። በሰሜን መስጴጦምያ ብዙ ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ በጊዜው የታወቀ በለዓም የሚባል ምዋርተኛ ወይም ጠንቋይ ነበር፤ ስለዚህ የሞዓብ ንጉሥ በለዓምን ለመቅጠር ሞከረ። ቀጥሎ የምንመለከተው ነገር በበለዓምና የእስራኤል ጌታ በሆነው በእግዚአብሔር መካከል የተደረገውን ጦርነት ነው። በለዓም አማኝ ነበር ማለት በጣም አስቸጋሪና የማይመስል ነገር ነው። ሰዎችን በመርገም ባሳየው ስኬታማነት ታዋቂ የነበረ ጠንቋይ ለመሆኑ አንዳችም ጥርጥር የለውም፤ እግዚአብሔር ግን ከዚህ ክፉ ጠንቋይ ጋር ይነጋገር ዘንድ የማያስችለውን ሁኔታ አልፎ በቀጥታ ተናገረው፤ ስለዚህ በመጀመሪያ እግዚአብሔር የእስራኤል ሕዝብ በእርሱ የተባረከ ስለሆነ፥ ሊረግመው እንደማይችል የተናገረውን ቃል በመስማት የሞዓብን ንጉሥ በመርዳት እስራኤልን ከመርገም ተቆጠበ። በለዓም ግን ስስታምነቱ አሸነፈውና ወደ ሞዓብ ሄደ። እግዚአብሔር ኃይሉን ይገልጥ ዘንድ ወደ ሞዓብ እንዲሄድ በለዓምን የተወው ቢሆንም፥ በለዓም ያሰበው ግን በመስገብገብ ጥቅምን ማግኘት ነበር፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር መልአክ በመንገድ ላይ ተገናኘው። የሚያስገርመው ነገር ከበለዓም በፊት መልአኩን ያየችው አህያይቱ መሆኗ ነበር። እንዲያውም እግዚአብሔር አህያይቱ ለበለዓም እንድትናገር አስችሉአት ነበር። ከዚህ ታሪክ በግልጽ የምንረዳው በለዓም ወደ ሞዓብ ምድር የሚሄደው በተሳሳተ ፍላጎት እንደነበር ነው። በለዓም ሦስት ጊዜ እስራኤላውያንን ለመርገም ሞከረ ዳሩ ግን ሦስቱም ጊዜ እርግማኑ ወደ ምርቃት (በረከት) ተለወጠበት፤ ስለዚህ የሞዓብ ንጉሥ በለዓምን አባረረው። በለዓምም ከመሄዱ በፊት ስለ እስራኤል ሕዝብ ሁለት ተጨማሪ ዐረፍተ ነገሮችን ተናገረ።

በእዚህ የመጨረሻ ንግግሮቹ ውስጥ ሁለት ዋና ዋና ትንቢቶች ነበሩ።

ሀ) ሞዓብ «ከያዕቆብ በሚወጣ ኮከብ» ይሸነፋል፤ ይህም ሞዓባውያንን እንደሚያሸንፉ በዳዊት የተነገረ ትንቢት ለመሆኑ ጥርጥር የለውም (ዘኁ.24፡17)፤ ነገር ግን ብዙ ክርስቲያኖች ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ስለመንገሡ የተነገረ ትንቢት ነው ይላሉ። 

ለ) እንደ አማሌቃውያን ያሉ ሌሎች ሕዝቦችም በእስራኤላውያን መሸነፍ ነበረባቸው። 

ይሁን እንጂ ዘኁ.25 የሚናገረው የሞዓብ ንጉሥ እስራኤልን ለማሸነፍ ተቃርቦ እንደነበር ነው። 

በሞዓብ ምድር ቆንጆ የተባሉትን ሴቶች በሙሉ ወደ እስራኤላውያን ሰፈር በመላክ ከእስራኤል ወንዶች ጋር እንዲዳሩ አደረጉ። እነዚህ የቤተ መቅደስ ጋለሞታዎች ሳይሆኑ ስለማይቀሩ፥ እስራኤላውያን ማመንዘር ብቻ ሳይሆን ጣዖትም ያመልኩ ነበር። ከመጽሐፍ ቅዱሳችን በግልጥ እንደምንመለከተው በለዓም ከሞዓብ ምድር አልተመለሰም ነበር፥ (ለምሳሌ፡- ዘኁ.31፡8፥16)። ለገንዘቡ እጅግ ይሳሳ ነበር ስለዚህ እስራኤላውያንን በምንዝርናና በጣዖት አምልኮ ይጥሉአቸው ዘንድ፥ በዚህም የእግዚአብሔር ቁጣ እንዲመጣባቸው ሞዓባውያንን የመከራቸው በለዓም ነበር። እግዚአብሔር ቅዱስ አምላክ መሆኑንና በኃጢአታቸው ሕዝቡን እንደሚያጠፋ ያውቅ ነበር። በኋላም እስራኤል ምድያማውያንን በጦርነት ባሸነፉ ጊዜ በለዓምን እንደ ገደሉ እናውቃለን፤ (ዘኁ.31፡8፤ ኢያ.13፡22 ተመልከት)።

እስራኤላውያን በዝሙትና ጣዖትን በማምለክ ኃጢአት ውስጥ ስለወደቁ፥ የእግዚአብሔር ቁጣ በላያቸው ላይ ነደደና 24000 ሰዎች ሞቱ። እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የጀመረው ይህ ፍርድ የቆመው፥ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ የሆነው ፊንሐስ በጽድቅ ተቆጥቶ ምንዝርና ሲፈጽሙ የተገኙ ወንድና ሴት ከገደለ በኋላ ነበር።

እግዚአብሔር የፊንሐስን ቅንዓት አከበረ። ሁልጊዜ የክህነት መብቱን እንደሚጠብቅለት እግዚአብሔር ለፊንሐስ ቃል ኪዳን ገባለት። ዔሊ በክህነት ካገለገለበት ከጥቂት ጊዜያት በስተቀር፣ ቤተ መቅደሱ እስከተደመሰሰበት እስከ 70 ዓ.ም. ድረስ የፊንሐስ ዘር የሊቀ ካህንነቱን አገልግሎት እንደያዘ ዘልቆአል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በኃጢአት ላይ ቅንአትና ቁጣችንን ማሳየት ትክክል የሚሆነው መቼ ነው? ምሳሌዎችን ጥቀስ። ለ) በኃጢአት ላይ የምንቆጣው አንዳንድ ጊዜ ብቻ የሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ይህስ ራሳችንን ከፊንሐስ ጋር ስናወዳድር ምን ያሳየናል?

 1. ሁለተኛው የሕዝብ ቆጠራ (ዘኁ.26)

እስራኤላውያን ከ38 ዓመታት በፊት በሲና ተራራ በነበሩበት ወቅት ሙሴ ዕድሜያቸው ከ 20 ዓመት በላይ የሆኑ እስራኤላውያን ወንዶችን ሁሉ ቆጥሮ ነበር። ቁጥራቸውም 603550 ነበር። ከ38 ዓመታት በኋላ የከነዓንን ምድር ለመውረስ ተዘጋጅተው ባሉበት ወቅት በተደረገው ቆጠራ የወንዶቹ ቁጥር 601730 ሆነ። 

 1. የተለያዩ ትእዛዛት (ዘኁ.27-30) 

በዚህ ስፍራ ልንመለከተው የሚገባ የተለየ ነጥብ እግዚአብሔር ኢያሱን ተከታዩ መሪ አድርጎ እንዲሾም ሙሴን ማዘዙ ነው። በተጨማሪ በቤት ውስጥ ወንዶች ልጆች ከሌሉ ርስትን የማውረስ ጉዳይ ለሴት ልጆች እንደሚተላለፍ፥ በተቀደሱ ቀናት ለእግዚአብሔር ስለሚቀርቡ መሥዋዕቶች፥ ለእግዚአብሔር የተገቡ ስእለቶች ምን መደረግ እንዳለባቸው የተሰጡ ሕግጋት እናገኛለን።

 1. ምድያማውያን ተቀጡ (ዘኁ.31)

ምድያማውያን ብዙ እስራኤላውያንን ስላጠፉ እግዚአብሔር ቀጣቸው። እስራኤላውያን ተዋግተው አሸነፏቸው። በለዓምም በዚህ ጦርነት ተገደለ። እግዚአብሔር ከምድያማውያን አብዛኛዎቹ እንዲገደሉ አዘዘ። ከምርኮውም እስራኤላውያን የተወሰነውን እንዲወስዱና የቀረውን ግን ወደ ጌታ እንዲያመጡ ታዘዙ። 

 1. ስለ ከነዓን ምድር የተሰጡ ትእዛዛት (ዘኁ. 32-36)

በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የተካተቱ ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን እናያለን። የመጀመሪያው፥ ሙሴ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ ያለውን ስፍራ ለሦስት ነገዶች ርስት ይሆን ዘንድ ስለመስጠቱ ነው። ከፊሉ የተሰጠው ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ነው። (ለቀሪው የምናሴ ነገድ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ የሚገኝ ክፍል ተሰጥቶታል)። ይህንን ክፍል ያገኙት ሁለቱ የጋድና የሮቤል ነገዶች ሲሆኑ እነርሱም የቀሩት ወንድሞቻቸው በሙሉ የተሰጣቸውን የከነዓንን ምድር እስኪወርሱ ድረስ የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር አብረዋቸው ሊዋጉ ቃል ገብተው ነበር። ሙሴ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ የሚገኘውንና ከከነዓናውያን በጦርነት የሚወሰደውን ምድር በሙሉ 9 1/2 ለሆኑት ለቀሩት የእስራኤል ነገዶች አከፋፈለ።

ሁለተኛው ነገር ደግሞ፥ ሙሴ የተወሰኑ ከተሞችን ለሌዋውያን መለየቱ ነበር። እንደምታስታውሰው፥ እግዚአብሔር የካህናት ዘር ለሆኑት ለሌዋውያን የሰጣቸው ምድር አልነበረም። ይልቁንም በከነዓን ምድር ሁሉ የተሰራጩ በአጠቃላይ 48 ከተሞች ለእነርሱ ተሰጥተው ነበር። የዚህን ተስፋ መፈጸም ለመረዳት (ኢያሱ 21ን ተመልከት)። ሙሴ በተጨማሪ ሦስት በስተምሥራቅ፥ ሦስት በዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ፣ በአጠቃላይ ስድስት ከተሞችን «የስደተኞች ከተሞች» አድርጎ ለያቸው። እነዚህ ከተሞች በድንገት ሰውን ለገደለ ለማንኛውም ሰው መሸሸጊያ ወይም መጠጊያ በመሆን ያገለግሉ ነበር። ይህ በዘመኑ ከተለመደው በሟቹ ቤተሰብ ወይም ቤተ ዘመድ ከሚሰነዘር የደም በቀል የሚጠብቀው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በኦሪት ዘኁልቁ ስለ እግዚአብሔር፥ በእምነት ስለ መራመድና ኃጢአት ስለሚያስከትለው ፍርድ ምን ተማርክ? ለ) የእስራኤላውያን ታሪከ ዛሬ በምድር ከሚኖሩ ከብዙ ክርስቲያኖች ታሪክ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

ኦሪት ዘኁልቁ የሚያበቃው፥ እስራኤላውያን ከ400 ዓመታት በፊት እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋ የሰጠውን ምድር ለመውረስ የዮርዳኖስን ወንዝ ሊሻገሩ ተዘጋጅተው በነበሩበት ሁኔታ ነው። ወደ ከነዓን ምድር ከመግባታቸው አስቀድሞ ግን እግዚአብሔር ከ39 ዓመታት በፊት በሲና ተራራ የሰጣቸውን ሕግ ሙሴ ሊያስታውሳቸው ፈለገ። ኦሪት ዘዳግም የሕጉን በዚህ መልክ መደገም የሚያሳይ ነው።

ኦሪት ዘኁልቁ የእግዚአብሔር ሕዝብ ብዙ ጊዜ ከመታዘዝ ይልቅ ባለመታዘዝ እንደሚኖር የሚናገር አሳዛኝ ታሪክ ነው፤ (ሮሜ 7፡7-25 ተመልከት)። በራሳችን ላይ ፍርድን የምናመጣው እኛው እራሳችን ነን። እግዚአብሔር ቅዱስና ኃጢአትን የሚቀጣ መሆኑን እናያለን፤ ደግሞም ሕዝቡ ምንም እንኳ ደጋግመው ቢያጠፉም እንዳያጠፋቸው ይጠነቀቅላቸው እንደ ነበር እንመለከታለን። እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችንም ጸጋ የተሞላ አምላክ ነው። እንደ ጳውሎስ ሁላችንም የባስን ኃጢአተኞች መሆናችንን መናገር እንችላለን (1ኛ ጢሞ.1፡15-16 ተመልከት)። እግዚአብሔር በጽድቅ ቢፈርድ ኖሮ ሊደርስብን ይችል የነበረው ቅጣት አልደረሰብንም፤ ግን ኢየሱስ ቅጣታችንን በመስቀል ላይ ተሸከመ። አሁን እግዚአብሔር፥ በኃጢአት ላይ በድል የምንራመድበትን፥ እርሱን በመታዘዝና በማክበር ለመኖር የምንችልበትን ኃይል ይሰጠናል። እንግዲህ ሌሎች ሰዎች ዓለማዊ በሆነ መንገድ ቢሄዱም እንኳ አንተ በቅድስናና በመታዘዝ ለመኖር ወስነሃልን) እንደ ፊንሐስ፥ ኢያሱና ካሌብ ለመሆን ፈቃደኛ ህን?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ያለማቋረጥ ኃጢአት ብታደርግም እንኳ እግዚአብሔር እስከ ዛሬ ድረስ ስላሳየህ ትዕግሥት እርሱን ለማመስገን ጊዜ ይኑርህ። ለ) በእግዚአብሔር ፊት በንጽሕናና በድል ለእርሱ ክብርን በሚያመጣ መንገድ ለመኖር ትችል ዘንድ ዕለት ዕለት ብርታትና ኃይል እንዲሰጥህ ለምነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ዘኍልቁ 13-21

በሕይወታችን የምናደርገው ምርጫ ለሚያጋጥመን በጎም ይሁን ክፉ ነገር ሁሉ ወሳኝ ሚና አለው። በኢየሱስ ማመንን በመረጥን ጊዜ፥ የወደፊት ሁኔታችን ሁሉ ይለወጣል። ኢያሱና ካሌብ በእግዚአብሖር ለመታመንና ከነዓናውያንን ለመውጋት ሲወስኑ፥ ከዚያ ትውልድ መካከል ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚገቡ ብቸኛዎቹ ሰዎች እነርሱ መሆናቸውን አላወቁም ነበር። የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ላለመከተል በምንወስንበት ጊዜ፥ ለጊዜው የቱንም ያህል ትንሽ ቢመስለንም፥ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ የሚታይ መጥፎ ውጤት ሊኖረው ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) መልካም ምርጫዎቻችን ለሕይወታችን በጎ ውጤት እንዴት እንደሚያመጡ አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ ለ) ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛችን እርሱ ይቅር ሊለን ቢችልም እንኳ ውጤታቸው በሕይወታችን ዘመን ሁሉ ሊከተሉን ለሚችሉ ነገሮች ምሳሌዎችን ጥቀስ።

ሳኦል ለእግዚአብሔር ሙሉ ለሙሉ ለመታዘዝ ባለመወሰኑ መንግሥቱ ከእርሱ እንዲወሰድ አደረገ (1ኛ ሳሙ.15፡2-3፡ 13-30)። ዳዊት ዝሙት በፈጸመና ከወዳጆቹ አንዱን ባስገደለ ጊዜ ቀሪው የሕይወት ዘመኑ በሙሉ በዚህ እንደሚነካ፥ በመንግሥቱና በቤተሰቡም ሰላም እንደሚጠፋ አላወቀም ነበር (2ኛ ሳሙ.12፡1-14 ተመልከቱ)። እግዚአብሔር ይቅር ካለው በኋላ እንኳ የኃጢአቱ ውጤቶች ዳዊትን ይከተሉት ነበር። አንዲት ልጃገረድ ካላገባችው ወንድ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ኃጢአት ፈጽማ በምትናዘዝበት ጊዜ እግዚአብሔር ይቅር ይላታል፤ ነገር ግን ክብረ ንጽሕናዋን የማጣት ኃፍረቷን፥ ምናልባትም የማርገዝንና ሌላ ለማግባት ያለመቻልዋን፥ ወይም በኤድስ የመያዝን ኃፍረት ሊያስወግድላት አይችልም።

ወደ ከነዓን ጉዞ ከሚጀምሩበት ካለፈው አንድ ዓመት እንሥቶ እግዚአብሔር ኃይሉንና በጸጋ የተሞላ ቸርነቱን ለአይሁድ ሲገልጥ ቆይቶአል፤ ነገር ግን በቃዴስ በርኔ እንዲታመኑበትና ወደ ከነዓን ምድር በእምነት እንዲገቡ እግዚአብሔር ሲጠይቃቸው እስራኤላውያን እምቢ አሉ። በዚህ ውሳኔአቸው ምክንያት አይሁድ በሚከተሉት 38 ዓመታት በምድረ በዳ ተንከራተቱ። ከ20 ዓመት ዕድሜ በላይ የሆኑት በግምት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በሙሉ አለቁ። ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ በጭራሽ ያልገመቱትን ፍርድ አስከተለባቸው። ስሕተታቸውን ለማረም እንኳ ቢሞክሩ ጨርሶ የማይቻል ሆነባቸው። የኦሪት ዘኁልቁ ክፍል የሆነው የዚህ ክፍል ታሪክ እግዚአብሔር ከግብፅ ባርነት በጸጋው ነፃ ያወጣቸው የእስራኤላውያን አለመታዘዝና ያስከትለው ውጤት ታሪክ ነው።

የውይይት ጥያቄ፦ ዘኁልቁ 13-21 አንብብ ሀ) ሰላዮችን ወደ ከነዓን የመላኩ ዓላማ ምን ነበር? ለ) ) የአሥሩንና የሁለቱን ሰላዮች የተለያዩ ምላሾች አወዳድር። 2) ስለ ምድሪቱ የነበራቸው መረዳት አንድ የሆነው እንዴት ነው? 3) ስለ እግዚአብሔር የነበራቸው መረዳት የተለያየው እንዴት ነው? 4. ከዚህ የምንማረው ነገር ምንድን ነው?ሐ) ከኦሪት ዘኁልቁ ይህን ክፍል አለፍ አለፍ እያልክ ተመልከት፡፡ እስራኤላውያን የሄዱባቸውን ስፍራዎችና በየደረሱባቸው ስፍራዎች የተፈጸሙትን ነገሮች ዝርዝር። መ) የሙሴን ኃጢአት ግለጥ። እግዚአብሔር ክፉኛ የፈረደበትና የቀጣው ለምን ይመስልሃል? ሠ) እስራኤላውያን የከነዓንን ምድር መውጋት በጀመሩ ጊዜ ያሸነፏቸውን ሕዝቦች ዘርዝር፡፡

12ቱ ሰላዮች (ዘኁ.13-14)

እስራኤላውያን የከነዓንን ምድር ካዩ ከ400 ዓመታት በላይ ሆኖአል። አሁን የከነዓን ደቡባዊ ጫፍ በሆነው በቃዴስ በርኔ ሰፍረዋል። ይህም እግዚአብሔር ሊሰጣቸው ያለች ምድር ምን ያህል መልካምና ፍሬያማ እንደሆነች ለማየት እንጂ፥ የጠላቶቻቸውን ብርታት ለማየት አላስቻላቸውም። 12ቱ ሰዎች ወደ ከነዓን ምድር በመሄድ ለ40 ቀናት ምድሪቱን ሲሰልሉ ቆይተው የየራሳቸውን ዘገባ ይዘው ተመለሱ።

አሥሩ ሰላዮች በመጀመሪያ ዘገባቸውን አቀረቡ። ምድሪቱ ምን ያህል ፍሬያማ እንደሆነች ተናገሩ፡፡ እንዲያውም ምድሪቱ ከምታፈራቸው ነገሮች ለናሙና የሚሆን ነገርም አምጥተው ነበር። ዘገባቸው ግን በጠላቶቻቸው ብዛትና ታላቅነት ላይ የሚያተኩር ሆነ! ስለዚህ ወደ ከነዓን እንዳይሄዱ ሕዝቡን ተስፋ አስቆረጡአቸው። ካሌብና ኢያሱ የተባሉት ሁለት ሰላዮችም ተመሳሳይ ዘገባ አቀረቡ። ስላዩአቸው ታላላቅ ነገሮች ተናገሩ፤ ነገር ግን ጠላቶቻቸው ምንም ያህል በቁጥር የበዙና ታላላቅ ቢሆኑም፥ በጠላቶቻቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ፥ ሊያጠፋቸው በሚችለው በእግዚአብሔር ኃይል ላይ አተኮሩ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአሥሩና በሁለቱ ሰላዮች መካከል የነበረው የአመለካከት ልዩነት ለሕዝቡ በሰጡት ምክር ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ምንድን ነው? ለ) ዛሬ ጠላቶቻችንንም ሆነ ችግሮቻችንን ስለ መጋፈጥ ከዚህ ነገር ምን እንማራለን?

የሚያሳዝነው ሕዝቡ 2ቱን ሳይሆን 10ሩን ሰላዮች ተከተሉ። ዓይኖቻቸውን ከጠላቶቻቸው ሁሉ በላይ ከሆነው ከእግዚአብሔር ላይ አነሡና በችግራቸውና በራሳቸው ላይ አደረጉ። ሌሊቱን በሙሉ ሲያጉረመርሙ አድረው፥ ጠዋት የባርነት ምድር ወደሆነችው ወደ ግብፅ ለመመለስ ወሰኑ። እግዚአብሔር በቁጣው እስራኤላውያንን በሙሉ እንዳያጠፋቸው የሚከለክለው የሙሴ የማማለድ አገልግሎት ነበር። ሆኖም እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ ፍርድን አመጣባቸው። የሚከተሉትን ነገሮች ልብ በል፡-

 1. እግዚአብሔር አሥሩን ሰላዮች ወዲያውኑ ገደላቸው። 
 2. ከ20 ዓመት በላይ የሆኑ ማለትም የእግዚአብሔርን ክብር ያዩና የተአምራቱ ምስክሮች የሆኑ ሰዎች በሙሉ የተስፋይቱን ምድር ሳይወርሱ በምድረ በዳ ማለቅ ነበረባቸው። 

iii. እስራኤላውያን በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት ተንከራተቱ። ሰላዮቹ ለአንድ ዓመት ሙሉ በየቀኑ በከነዓን ነበሩ። በኋላ ግን ከከነዓን ውጭ ሞቱ። 

 1. ከዚያ ትውልድ መካከል ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ካሌብና ኢያሱ ብቻ ነበሩ።

እስራኤላውያን ካለማመን ኃጢአታቸው ንስሐ ለመግባት ቢሞክሩም እንኳ እግዚአብሔር ከተናገረው ፍርድ ወደ ኋላ አላለም። ያለ እግዚአብሔርና ያለ ታቦቱ ሕልውና እስራኤላውያን በራሳቸው ኃይል ከጠላቶቻቸው ጋር ለመዋጋት ሞከሩ፤ ነገር ግን የተረፋቸው ሽንፈት ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ይህ ጠላቶቻችንን በራሳችን ኃይል ለመዋጋት ብንሞክር፥ ስለሚደርስብን ነገር ምን ያስተምረናል?

(ማስታወሻ፡- ሕዝቡ 40 ዓመታት በምድረ በዳ ነበሩ ስንል፥ ከግብፅ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ያሳለፉትን አንድ ዓመት ከሁለት ወር ጨምሮ ነው)

38 ዓመታት በምድረ በዳ በተንከራተቱ ጊዜ የተፈጸሙ ነገሮች (ዘኁ.15-19)

ዘኁ. 15-19 በእነዚህ 38 ዓመታት የምድረ በዳ ኑሮ ስለነበሩት ሁኔታዎችና ስለተፈጸሙት ሁኔታዎች አንዳንድ ነገሮችን ይነግረናል። ቢሆንም በከነዓን በስተደቡብ ባለው ምድረ በዳ በመንከራተት ሰላሳለፉት ጊዜ የምናውቀው ነገር በጣም ጥቂት ነው። ቆይታ ያደረጉባቸውን አብዛኛዎቹን ስፍራዎች አናውቃቸውም። የምናውቀው ነገር ቢኖር፥ ከፍተኛ ኃዘን የነበረባቸው ዓመታት መሆናቸውን ነው። ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ሞቱ። በእነዚህ ምዕራፎች የሚከተሉት ነገሮች ተተንትነዋል፡

 1. ሕዝቡ ከነዓን በደረሱ ጊዜ ምን ዓይነት መሥዋዕት ማቅረብ እንዳለባቸው እግዚአብሔር ለሙሴ ነገረው፤ (15፡1-31)። 
 2. የሰንበት ዕረፍት ትእዛዝን እያወቀ የጣሰ ሰው በድንጋይ ተደብድቦ እንዲገደል ታዘዘ፤ (15፡32-36)። 

ይህ ቀላል ስሕተት አይደለም፤ ይልቁንም በእግዚአብሔር ላይ የተፈጸመ ግልጥ ዓመፅ ይመስላል። በእግዚአብሔርና በትእዛዛቱ ላይ ሆን ተብሎ ለሚሠራ ዓመፅ ይቅርታ የለም፤ ስለዚህ ሕጉን የተላለፈው ሰው በድንጋይ ተውግሮ እንዲገደል ይደረግ ነበር። 

 1. ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ያስታውሱ ዘንድ በልብሶቻቸው ዘርፍ ላይ ቋጥረው እንዲያስሩት እግዚአብሔር ሙሴን አዘዘው (15፡37-40)። 

እግዚአብሔር ሕዝቡ ትእዛዛቱን በቀላሉ ለማስታወስ እንዲችሉ ለማድረግ ሞክሯል፤ ስለዚህ ቀኑን ሙሉ በማስታወስ ይታዘዙት ዘንድ ውጫዊ የሆኑ ምልክቶችን እንዲያበጁ ነገራቸው። ሌሎች ማስታወሻዎችን (ዘዳ.6፡4-9 ተመልከት)

 1. የተለያዩ የእስራኤል መሪዎች በሙሴና በአሮን ሥልጣን ላይ ዓምፀዋል (ዘኁ.6-17)። 

የዓመፁ መሪዎች ቆሬ፥ ዳታን፥ አቤሮንና ኦን ሳይሆኑ አይቀሩም፤ ሆኖም በሙሴና በአሮን ሥልጣን ላይ ያመፁ ሌሎች 250 ዋና ዋና የእስራኤል መሪዎች ነበሩ። የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመምራት ሙሴና አሮን የነበራቸውን ሥልጣን ተፈታተኑ። ሙሴ የፖለቲካ መሪ ሲሆን፡ አሮን ሊቀ ካህን ወይም ሃይማኖታዊ መሪ ነበር። ሙሴና አሮን እርሱ የመረጣቸው መሪዎች እንደሆኑ እግዚአብሔር ለሁሉም ሰው አሳየ፡፡

ሀ. የዓመፁ መሪ የነበሩት፥ ቆሬ፥ ዳታን፥ አቤሮንና ኦን ከነቤተሰቦቻቸው ከእስራኤል ሕዝብ ተለዩና መሬት ተከፍታ እነርሱና ቤተሰቦቻቸውን፥ እንዲሁም ንብረቶቻቸውን በሙሉ ዋጠች። 

ለ. ቆሬ ሌዋዊ ነበር፤ ስለዚህ የእርሱ ዓመፅ በተለይ አሮን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በነበረው ስፍራ ላይ ነበር! ስለዚህ እግዚአብሔር እርሱንና የተከተሉትን ሰዎች በሙሉ (በአጠቃላይ 250 ነበሩ) ጥናዎችን ወስደው እሳት እንዲያደርጉባቸውና ዕጣን እንዲጨምሩባቸው በመገናኛው ድንኳንም በእግዚአብሔር ፊት እንዲያቀርቡት አዘዘ። ይህንንም በሚያደርጉበት ጊዜ ከመገናኛው ድንኳን የወጣች እሳት ቆሬን፥ ዳታንን አቤሮንንና ኦንን የተከተሉትን 250 ሰዎች በላች። የዕጣን ማቅረቢያቸው በእሳት ተበልቶ ጠፍጣፋ ሆነና እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንደመረጠ እነርሱም ትክክለኛዎቹ የእስራኤል ሕዝብ መሪዎች እንደሆኑ ቋሚ መታሰቢያ ሆኖ ቀረ። 

ሐ. እነዚህ ዓመፀኛ መሪዎች ከሞቱ በኋላ፥ ሕዝቡ መሪዎቻችንን ገደልክብን ብለው በሙሴ ላይ አጉረመረሙ። እግዚአብሔርም ተቆጣና ከመካከላቸው 14700 ሰዎችን ገደለ። አሮን፥ የመሠዊያውን ጥና እሳትን በማድረግና እጣን በመጨመር ለሕዝቡ ባይማልድ ኖሮ፥ የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ይጠፉ ነበር። ብዙ ክርስቲያኖች ዕጣንን በጥና ላይ ማጠን የጸሎት ምልክት ነው ይላሉ። አሮንና ሙሴ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል አማላጅ ሆነው ሕዝቡን አዳኑ።

መ. ሊቀ ካህኑ አሮን ብቻ እንደሆነ እግዚአብሐር በሕዝቡ ሁሉ ፊት አረጋገጠ። እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ሙሴ በእያንዳንዳቸው ላይ የአንድ ነገድ ስም የተጻፈባቸውን አሥራ ሁለት በትሮች ወሰደ። በአንድ ሌሊትም የአሮን በትር አቆጥቁጣ፥ ቅጠሎች አውጥታና ፍሬ አፍርታ አደረች። ሊቀ ካህን የመሆኑ መብት ቋሚ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ የአሮን በትር በቅድስተ ቅዱሳን በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ተቀመጠች።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ ያሉ ሰዎች፥ በስፍራው የተቀመጡት በእግዚአብሔር ምርጫ ስለሆነ ሊከበሩ እንደሚገባ ማወቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ለ) ይህ ታሪክ መሪዎች በእግዚአብሔር ፊት ስለ ሕዝቡ መማለድ ስላላቸው ሥልጣንና ሚና የሚያስተምረን ነገር ምንድን ነው?

 1. ሕዝቡ ለካህናት ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔርን አምልኮ መምራት ይችሉ ዘንድ መሥዋዕት እንዴት እንደሚሠዉና በእግዚአብሔር ፊት ንጽሕናቸውን እንዴት እንደሚጠብቁ የተሰጡ ትእዛዛት (ዘኁ.18)። 
 2. የቀይ ጊደር መሥዋዕትና የሚያነጻ ውኃ ሥርዓት (ዘኁ.19)

ኃጢአት ምን ያህል ኃይለኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እግዚአብሔር ሌላ ግልጥ የሆነ ምልክትን ሰጠ፡- በመጀመሪያ፥ ቀይ ጊደር ከእስራኤላውያን ሰፈር ውጭ ተመስዳ ትታረድና ሙሉ በሙሉ ትቃጠላለች። ከዚያም አመዷ ተወስዶ ከውኃ ጋር ይቀላቀላል። ይህ ውኃ የሞተን ሰው በድን በመንካት የረከሰውን ሰው የሚነጻበትን ሥርዓት የሚያመለክት ነበር። ውኃ ራሱ

አያነጻም ነበር፤ ዳሩ ግን ውስጣዊ መንጻት አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየት እግዚአብሔር የሰጠው ውጫዊ ምልክት ነበር።

 1. ሙሴ ከዓለት ውስጥ ውኃ በማውጣት በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት በመሥራቱ ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ ከነዓን እንዳይገባ ተከለከለ (ዘኁ.20፡1-13)።

ዘኁ. 20 እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ በወጡ በ40ኛው ዓመት የተፈጸመ ይመስላል። ይህም ማለት የመጀመሪያዎቹ የእስራኤል ትውልድ በሙሉ ስለሞቱ፥ ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተዘጋጅተው ነበር ማለት ነው። እስራኤላውያን ወደ ቃዴስ በርኔ በመመለስ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተዘጋጅተው ነበር። በዚህ ስፍራ ሁለት ዋና ዋና ነገሮች ተፈጸሙ፡-

ሀ. የሙሴ እኅት ማርያም ሞተች።

ለ. ሙሴ ለእግዚአብሔር ሳይታዘዝ ቀረ። እስራኤላውያን (አዲሱ ትውልድ) ልክ እንደ አባቶቻቸው በእግዚአብሔር መታመንን ገና አልተማሩም ነበር። የሚጠጣ ውኃ ስላልነበራቸው፥ በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ። ከ40 ዓመታት በፊት እግዚአብሔር ሙሴ ዓለቱን በመምታት ለሕዝቡ ውኃ እንዲያወጣ አድርጎ ነበር (ዘጸ.17፡5-6)፤ አሁን ግን እግዚአብሔር ሙሴን ለዓለቱ ተናገር ውኃም ይወጣል አለው። ሙሴ ባለመታዘዝና በቁጣ ዓለቱን ሁለት ጊዜ መታው፤ ከዓለቱ ውኃ ወጣና ሕዝቡን አረካ፤ ነገር ግን ሙሴ በዚህ መልክ ኃጢአት በመሥራቱ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ተከለከለ። 

የሙሴ ኃጢአት ምን ነበር? እግዚአብሔር ሙሴን በዚህ ዓይነት ከባድ ቅጣት ለምን ቀጣው? የሙሴ ዋና ስሕተት አለመታዘዝ ብቻ አልነበረም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ከመደገፍ ለእርሱ ያለውን ታዛዥነት ከመግለጥ ፈንታ በንግግሩ ኃይሉን እንደራሱ ኃይል አድርጎ አቀረበ። «በውኑ ከዚህ ድንጋይ ውኃ እናወጣላችኋለን?» በማለት ትአምራቱን የሠራው እግዚአብሔር ሳይሆን እርሱና አሮን እንደሆኑ አድርጎ አቀረበ። ለእግዚአብሔር ብቻ ሊሰጥ የሚገባውን ክብር ለራሳቸው ወሰዱ። እንዲሁም ሙሴ በእግዚአብሔር ላይ እምነት እንደጎደለው የሚያሳይ ነገር አደረገ፤ ምክንያቱም ዓለቱን ሳይመታው፥ በመናገር ብቻ ውኃ ሊወጣ ይችላል ብሎ በእግዚአብሔር አልታመነም።

ይህ ታሪክ አስፈላጊ የሆነ መንፈሳዊ መመሪያን ያስተምረናል። ለእግዚአብሔር የሚሆነውን ከብር ለራስ ማድረግ እጅግ በጣም ክፉ ነገር ነው። በምንዘምርበት፣ በምንሰብክበት፣ በምንመሰክርበትና ሰዎች በሚድኑበት ጊዜ ማንኛውም ኃይል ከእኛ የሚመጣ አይደለም፤ ስለዚህ ከክብሩ የትኛውንም ክፍል መውሰድ አይገባንም፤ ነገር ግን በእኛ ውስጥ ለሚሠራው ለእግዚአብሔር ብቻ ክብር ልንሰጥ ይገባናል። በተጨማሪም፥ እግዚአብሔር አንድን ሰው ወደ ሥልጣን ወይም ወደ መሪነት ኃላፊነት ሲያመጣው፥ ከተራው ምእመን ይልቅ በሥራው ወደሚጠየቅበት ወደ ከፍተኛ ደረጃ የመጣ መሆኑን እንረዳለን፤ ምክንያቱም አንድ መሪ እግዚአብሔርን ባያከብርና ኃጢአትን ቢሠራ፥ ሌሎች በርካታ ሰዎች ኃጢአትን እንዲሠሩ ምክንያት ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ. ሀ) እግዚአብሔር በሙሴ ላይ ከባድ ፍርድ ያስተላለፈው ለምን ይመስልሃል? ለ) ከዚህ ነገር ስለ መንፈሳዊ

መሪነት ምን እንማራለን?

 1. እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ባደረጉት ጉዞ ኤዶማውያን አገራቸውን አቋርጠው እንዳያልፉ ከለከሉዋቸው (ዘኁ.20፡14-21) 

ስለዚህ እስራኤላውያን በኤዶም ምድር ዙሪያ አድርገው ወደ ሞዓብ ምድር ረጅም መንገድ በመሄድ ወደ ከነዓን መጓዝ ነበረባቸው። 

 1. ሊቀ ካህኑ አሮን በሖር ተራራ ሞተ (ዘኁ.22-29)

የሊቀ ካህንነት መብቱም ወደ ልጁ ወደ አልዓዛር ተላለፈ።

 1. ዓራድ ከተባለው ንጉሥ ጋር የተደረገ ጦርነት (ዘኅ. 21፡1-3)

እስራኤላውያን በ40 ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያ ጦርነት ያደረጉት ከከነዓን በስተደቡብ ከምትገኝ ዓራድ ከተባለች ከተማ ንጉሥ ጋር ነበር። የዓራድ ንጉሥ በድንገት አደጋ ጥሎ ያለ አንዳች ማስጠንቀቂያ የገጠማቸው ይመስላል። በውጤቱ እስራኤላውያን ተበቀሉዋቸውና እነርሱንና ከተሞቻቸውን በሙሉ አጠፉ። «ፈጽመው ደመሰሱ» የሚለው ቃል የዕብራይስጥ ትርጉም፥ አንድን ነገር ወይም ሰው ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ከመስጠት ጋር የተያያዘ ነው። አንዳንድ ጊዜ ይህ ቃል ከ «ተለዩ» ወይም ከ «ተቀደሱ» በኋላ ለእግዚአብሔር ስለሚሠዉት እንስሳ ለመግለጽ የሚያገለግል ቃል ነው። ይህ ቃል በጦርነት ዓውድ ስንጠቀምበት በዚያ ከተማ ውስጥ ያሉ እንስሳትንና ሰዎችን በሙሉ ስለማጥፋት ይናገራል። በዚያ ከተማ ያሉ እንስሳትና ሰዎች ሁሉ ለእግዚአብሔር እንደሆኑ ያህል ነው። እንስሳት ለእርሱ በብዛት የመሠዋታቸውን ያህል፥ ሰዎችም የእግዚአብሔር ፍርድና ጥፋት ዒላማ ሆኑ።

 1. በእስራኤል ሕዝብ ላይ ለፍርድ የተላኩት መርዘኛ እባቦች (ዘኁ.21፡4-9)

ኤዶማውያን የእስራኤል ሕዝብ በምድራቸው እንዲያልፉ ስላልፈቀዱላቸው፥ ወደ ሰሜን ከመጓዛቸው በፊት ወደ ደቡብ ረጅም ጉዞን ማድረግ ነበረባቸው። ምናልባት ይህ ነገር ከጠየቀው ረጅም ጉዞ የተነሣ፥ ሕዝቡ በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ ማጉረምረም ጀመሩ። የእግዚአብሔርን መና አንበላም በማለታቸው፥ ለእነርሱ ባሳየው ቸርነት ጸጋውን እምቢ ማለታቸው ነበረ። ስለዚህ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ፈረደባቸው። መርዛማ እባቦችን ልኮ ብዙ እስራኤላውያን ተነድፈው እንዲሞቱ አደረገ። 

ሕዝቡ ኃጢአታቸውን በተናዘዙ ጊዜ፥ የነሐስ እባብ እንዲሠራ እግዚአብሔር ሙሴን አዘዘው። ሕዝቡ ወደ ነሐሱ እባብ በእምነት በተመለከቱ ጊዜ ይፈወሱ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዮሐ.3፡14-15 ተመልከት። ይህ ታሪክ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ተምሳሌት የሆነው እንዴት ነው? ለ) እስራኤላውያን የዳኑበትና እኛም ድነት (ደኅንነት)ን የምናገኝበት መንገድ ተመሳሳይ የሆነው እንዴት ነው?

የነሐሱ እባብ ታሪክ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆነ። ወደ ተሰቀለው የነሐስ እባብ በእምነት የተመለከቱ ሁሉ በሥጋቸው ፈውስ እንዳገኙ ሁሉ፥ ወደ ተሰቀለው ክርስቶስ በእምነት የሚመለከቱም መንፈሳዊ ፈውስን ያገኛሉ። እጅግ የሚያሳዝነው ነገር ግን ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን የነሐስ እባቡን ማምለክ መጀመራቸው ነው (2ኛ ነገ.18፡4 ተመልከት)። ሰይጣን ሁልጊዜ ለሕይወታችን መልካም የሆነን ነገር ይወስድና ወደ ማሰናከያ ዓለትነት ይቀይረዋል።

 1. ወደ ሞዓብ ሜዳዎች የተደረገ ጉዞ (ዘኁ.21፡10-35)

ሕዝቡ ከምድረ በዳ ተነሥተው ወደ ሰሜን በመጓዝ፥ በሞአብ ምድር ላይ ሰፈሩ። ሊሰፍሩ ወደሚችሉበት ወደ እስራኤላውያን በአሞን ምድር ለማለፍ ፈቃድ በጠየቁ ጊዜ የአሞን ንጉሥ ሊወጋቸው ሞከረ። እስራኤላውያን ግን አሸነፉትና የአሞንን ምድር ወሰዱ። የባሳን ንጉሥ ዐግ ደግሞ እስራኤላውያንን ሊወጋ ሞከረ፤ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ተሸነፈ። እነዚህ ስፍራዎች የምናሴና የጋድ ነገዶች የወረሷቸው ስፍራዎች ናቸው። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ዘኍልቁ 1-12

የእግዚአብሔርን ሕዝብ በጥሩ ሁኔታ ለመምራት ጥሩ አደረጃጀት ያስፈልጋል። ጥሩ አደረጃጀት ከሌለ መምራት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፤ ሕዝቡም ስለሚምታታበት፥ የእግዚአብሔር ሥራ እንደሚጠበቀው ስኬታማ አይሆንም። ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ የሲና ተራራን ለቆ ወደ ቃዴስ በርኔ፥ ከዚያም ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመሄዱ በፊት ሕዝቡን ለማደራጀት ይረዳው ዘንድ እግዚአብሔር ግልጥ ትእዛዛትን ሰጠ። ይህም ግራ መጋባትንና ውጤት አልባነትን ተከላከለ።

የውይይት ጥያቄ ሀ) ደካማ አደረጃጀት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት ግራ መጋባትን እንደሚፈጥር አይተህ ታውቃለህ? ለ) የእግዚአብሔር ሥራ በሚገባ ከግብ እንዲደርስ መልካም አደረጃጀት የሚጫወተውን ሚና ጥቀስ ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ እንዴት እንደተደራጀች ግለጥ። ) ከዚህ በተሻለ ሁኔታ እንዴት ልትደራጅ እንደምትችል አብራራ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘኁልቁ 1-12 አንብብ ሀ) እግዚአብሔር ሕዝቡ ይቆጠር ዘንድ ሙሴን ያዘዘው ለምን ነበር? ለ) የእያንዳንዱ ነገድ ሕዝብ ብዛት ምን ያህል እንደነበር ግለጥ። ሐ) ሕዝቡ በአጠቃላይ ምን ያህል ነበር? መ) ይህንን ዝርዝር በዘኁልቁ ምዕራፍ 26 ከሚገኘው ቁጥር ጋር አወዳድር። ሠ) በዘኁልቁ 26 ያለው ጠቅላላ ቁጥራቸውስ ምን ያህል ነበር?

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የእስራኤላውያን አሰፋፈር እንዴት ሊሆን እንደሚገባ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት አደረጃጀቱን የሚገልጥ ሥዕላዊ መግለጫ አቅርብ። ለ) የመገናኛው ድንኳን አቀማመጥና የእያንዳንዱ ነገድ አሰፋፈር እንዴት ነበር? ሐ) የተለያዩት የሌዋውያን ብድኖች ኃላፊነት ምን ነበር? መ) እስራኤላውያን ወደ ቃዴስ በርኔ በሚጓዙበት ጊዜ ያለፉባቸውን የተለያዩ ቦታዎችና በእያንዳንዱም ቦታ ምን እንደተፈጸመ ተናገር። ሠ) አሮንና ማርያም እግዚአብሔርን ያሳዘነ ምን ነገር ፈጸሙ? 

 1. እስራኤላውያን በሲና ተራራ ሰፈሩ (ዘኅ. 1-10)

ሀ. የእስርኤላውያን መቆጠር (ዘኁ. 1) 

እንደምናስታውሰው፥ አራተኛው የፔንታቱክ መጽሐፍ ርዕስ በአማርኛ «ዘኁልቁ» የሚል ነው። ዘኁ. ምዕ. 1ና 26 የእስራኤል ሕዝብ ሁለት ጊዜ መቆጠራቸውን ያሳያሉ። ዘኁ. 1 የመጀመሪያው የእስራኤል ትውልድ ወደ ተስፋይቱ ምድር ጉዞ ከመጀመራቸው ጥቂት ቀደም ብሉ የተደረገውን ቆጠራ የሚያሳይ ሲሆን ዘኁ. 26 ደግሞ ሁለተኛው የእስራኤል ትውልድ ወደ ከነዓን ከመግባታቸው በፊት የተደረገ ቆጠራ ነው።

የቆጠራው ዓላማ ምን ነበር? አራት ዋና ዋና ምክንያቶች ነበሩ? 1) ለመዋጋት የሚችሉ ስንት ወንዶች እንዳሉ ለማዋወቅ (ዘኁ. 1፡3 ተመልከት)፤ 2) የተለያዩ ተግባራት እንዲያከናውኑ ለማድረግ ስንት ሰዎች እንዳሉ ለማወቅ (ዘኁ. 3፡4፤ 3) የእግዚአብሔር ሕዝብ ለሥራው አስራት እንዲሰጡ ለማድረግ (ዘጸ. 30፡11-16)፤ 4) የከነዓንን ምድር እንደየነገዱ ብዛት ለመከፋፈል (ዘኁ. 26፡53)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንተ ባለህበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስንት ክርስቲያኖች እንዳሉ ማወቅ መልካም የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያንህን አባሎች ጠቅላላ ቁጥር አግኝ። 2ኛ ሳሙ.24፡1-10 አንብብ። በዚህ ስፍራ የዳዊት ሕዝቡን መቁጠር ስሕተት የሆነው ለምንድነው? መ) የቤተ ክርስቲያናችንን አባሎች ስለ መቁጠር ይህ ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል?

በቤተ ክርስቲያንህ ያሉትን ሰዎች ብዛት መቁጠር ስሕተት አይደለም። የዚህ ዓይነት እውነታዎችን ማወቅ እንዲያውም ብዙ ጊዜ ጠቃሚ ነው። በዚህ መንገድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ደካማ የሆኑትን የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዩ ልዩ አካባቢዎች ለመርዳት ያስችላቸዋል። በአንድ አካባቢ ችግሮች እንዳሉ ለማወቅም ይረዳቸዋል። ለምሳሌ፥ የቤተ ክርስቲያን አባሎች ቁጥር እየቀነሰ ከሄደ፥ በዚያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድ ችግር እንዳለ ግልጥ ይሆንልናል። በሌላ አንጻር አባሎችን የምንቆጥረው ብዛታችንን ለማወቅ ከሆነ፣ በቤተ ክርስቲያን አባሎቻችን ብዛት ወደ መታበይ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ በእነርሱ ቁጥር ወደ መመካት፥ ወዘተ ይመራናል። እግዚአብሔር ዳዊትን ባካሄደው ቆጠራ የቀጣው ባለው የተዋጊ ኃይል ለመመካት በመፈለጉ ብቻ ነበር። ድልን የሚሰጠው እግዚአብሔር መሆኑን ረስቶ በእርሱ ተዋጊ ኃይል ብዛት ተደገፈ።

በዘኁ.1 ና 26 ከተደረገው የእስራኤል ሕዝብ ቆጠራ፥ የሚከተሉትን ነገሮች መመልከት እንችላለን፡-

 1. በሲና ተራራ በተካሄደው ቆጠራ ከ20 ዓመት በላይ የነበሩ ወንዶች ብዛት 603550 ሲሆን ከ38 ዓመታት በኋላ ደግሞ ከዚሁ ከ20 ዓመት በላይ የነበሩ ወንዶች ቁጥር 601730 ብቻ ነበር። ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ብለን ስንጠብቅ፥ መቀነሱ አስገራሚ ነገር ነው። በ38 ዓመት ውስጥ ቁጥራቸው ዕጥፍ ይሆናል ተብሎ ነበር የተጠበቀው፤ ነገር ግን መጀመሪያ ከነበሩት እስራኤላውያን ከ38 ዓመታት በኋላ ሲቆጠሩ እጅግ አንሰው የተገኙ ሆኑ። ይህም እግዚአብሔር በአይሁዶች ላይ ያመጣው ፍርድ ውጤትና ምልክት ነው። 
 2. 20 ና ከዚያም በላይ ዕድሜ የነበራቸው ወንዶች ብቻ ተቆጠሩ። ይህም የሆነበት ምክንያት የቆጠራው ዋና ዓላማ ሊጋጠሟቸው ከሚችሉት ጠላቶቻቸው ጋር ሊዋጋ የሚችል ምን ያህል ኃይል እንደነበር ለማወቅ ነው። በምድረ በዳ የነበረው የእስራኤል ሕዝብ ብዛት ከ 2-3 ሚሊዮን እንደሚደርስ ምሁራን ይገምታሉ።

ይህ ከፍተኛ ቁጥር አንዳንዶች እውነተኛነቱን እንዲጠራጠሩ አድርጎአቸዋል። እነዚህ ሁሉ በምድረ በዳ እንዴት ለመኖር ቻሉ? ይህን ያህል ብዙዎች ከነበሩ፥ ከእነርሱ ጋር ሲነጻጸሩ በቁጥር እጅግ ጥቂቶች የነበሩትን ከነዓናውያን ፈጽመው ለማጥፋት ለምን አልቻሉልም? (መሳ.1 ተመልከት)። ከዚህ የተነሣ አንዳንድ ሰዎች የዚህን ቁጥር ትክክለኛነት ይጠራጠራሉ። የሕዝቡን ብዛት ለመቀየር የተሰጡ ሁለት አሳቦች ነበሩ፡- የመጀመሪያው፥ እግዚአብሔር ምን ያህል ሕዝብ ነፃ እንዳወጣ ለማሳየት የቀረበ ምሳሌ ብቻ ነው እንጂ ቁጥሩ ትክክለኛ ቁጥር አይደለም የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ፡ «አንድ ሺህ» የሚለው የዕብራይስጥ ቃል «ነገድ»፥ «ጎሣ»፥ «ክፍል» እንደሚል ተደርጎ መተርጎም አለበት የሚል ነው፤ ስለዚህ አንዳንድ ሰዎች ይህ ቁጥር በእስራኤል ውስጥ የነበረው ክፍል ቁጥር እንጂ የህዝቡ ብዛት አይደለም ይላሉ። ስለዚህ እንደ ቃሉ አተረጓጎም ከ18000-100000 ተዋጊ ኃይላት እንዲሁም በአጠቃላይ ከ72000-400000 የሚደርሱ እስራኤላውያን ነበሩ። ሆኖም ግን ይህን ለሚያህል ሕዝብ እግዚአብሔር ሊጠነቀቅና የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ሊሰጥ እንደሚችል ለመጠራጠር ምንም በቂ ምክንያት የለም፤ ስለዚህ ቀደም ብሎ ከላይ የተጠቀሰው ቁጥራቸው ትክክል እንደሆነ በመቀበል፥ በእስራኤል ምን ያህል ሕዝብ እንደ ነበር የሚያሳይ መሆኑን ማመን ተገቢ ነው። 

 1. በ38 ዓመታት ውስጥ በተካሄዱት ሁለት ቆጠራዎች የአብዛኛዎቹ ነገዶች ቁጥር በግምት እንደ መጀመሪያው ሆኖ የቆየ ሲሆን፥ ሁለት ነገዶች ብቻ ከፍተኛ ለውጥ አሳይተዋል። የምናሴ ነገድ በ20500 የጨመረ ሲሆን፥ የስምዖን ነገድ ግን በ37100 ቀንሷል። በእነዚህ ሁለት ነገዶች ውስጥ ይህ ከፍተኛ ለውጥ የታየው ለምን እንደሆነ አናውቅም። 
 2. ሌዋውያን በሕዝብ ቆጠራ ውስጥ አልገቡም ነበር፤ ምክንያቱም ወደ ጦርነት መሄድ አይጠበቅባቸውም ነበር፤ የእነርሱ ኃላፊነት በቤተ መቅደስ ውስጥ ማገልገል ነበር። 

ለ. የእስራኤላውያንን ሰፈር ማደራጀት (ዘኁ. 2)

ምናልባት ቁጥራቸው ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጋው የእስራኤል ሕዝብ እያንዳንዱ ሰውና እያንዳንዱ ቤተሰብ የት መሆንና ድንኳኑን የት መትከል እንዳለበት በሚገልጥ መንገድ መደራጀት ነበረባቸው። የመገናኛው ድንኳን ያለው በእስራኤላውያን መሀል እንደ ነበረ አስተውል። ልክ እንደዚሁ፥ እግዚአብሔር የሕይወታችን፣ የአምልኮአችንና የፍላጎታችን ሁሉ፥ ወዘተ. እምብርት ነው (ማቴ.6፡33፣ ሉቃ.10፡27)።

ሐ. የሌዋውያን አሰፋፈርና ተግባር (ዘኍ.3-4)

እግዚአብሔር የሌዋውያንን ልዩ ልዩ ጎሣዎች በመገናኛው ድንኳን አካባቢ አሰፈራቸው። በምሥራቅ አሮን፥ ልጆቹና የእርሱ ዝርያዎች ነበሩ። እነርሱ ካህናት ስለ ነበሩ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚካሄደውን አምልኮ በበላይነት የመምራት ኃላፊነት ነበረባቸው። ሌዋውያን ከዚህ በተጨማሪ በሦስት ይከፈሉ ነበር፤ በደቡብ በኩል ቀዓታውያን ነበሩ። የመገናኛው ድንኳን በሚንቀሳቀስበት ጊዜ በውስጡ ባሉት የተለያዩ ዕቃዎች ላይ ኃላፊነት ነበረባቸው። በምዕራብ ደግሞ ጌርሶናውያን ነበሩ፡፡ እነርሱም የመገናኛው ድንኳን፥ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ የመገናኛው ድንኳን አልባሳትንና መጋረጃውን የማንቀሳቀስ ኃላፊነት ነበረባቸው። በሰሜን በኩል ደግሞ ሜራሪዓውያን ነበሩ። የመገናኛውን ድንኳን ምሰሶዎችና ግድግዳዎች የማንቀሳቀስ ኃላፊነት የእነርሱ ነበረ።

መ. የሰፈሩን ንጽሕና መጠበቅ (ዘኁ.5)

በዚህ ምዕራፍ እስራኤላውያን የሰፈሩበትን ቦታ ስለ መጠበቅ በርካታ ትእዛዛት ተሰጥተዋል። አንደኛ፥ እስራኤላውያን ቅርብ ለቅርብ ሆነው በአንድነት ይኖሩ ነበር። ስለዚህ በሽታ በቀላሉ ይዛመት ነበር፤ በመሆኑም ያልተለመዱ በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች እስኪፈወሱ ድረስ በሰፈሩ ውጪ እንዲቆዩ እግዚአብሔር አዘዘ።

ሁለተኛ፥ ሕዝቡ የሚኖረው ተቀራርቦ ስለ ነበር፥ ክርክርና ጠብ ሊነሣ ይችል ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በጎረቤቶቻቸው ላይ የማይገባ ነገር ቢያደርጉ፥ ይቅርታ መጠየቅና በወሰዱት ወይም ባጠፉት ነገር ላይ ከአምስት አንድ እጅ ጨምረው ካሣ እንዲከፍሉ አዘዛቸው። 

ሦስተኛ፥ እግዚአብሐር የኃጢአት መስፋፋት እንዴት መገታት እንዳለበት መመሪያዎችን ሰጠ። አንዲት ሴት በዝሙት ኃጢአት ተጠያቂ መሆን አለመሆኗን ለመወሰን የሚያስችል ያልተለመደ አደራረግ ተዘርዝሮአል። ይህ አደራረግ በብሉይ ኪዳን ውስጥ በየትኛውም ስፍራ በተግባር ሲውል አለመታየቱ፥ እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ ብቻ እንዲጠቀሙበት የተሰጠ ጊዜያዊ ትእዛዝ ይመስላል። እግዚአብሔር ሰው በአመንዝራነት ተጠያቂ መሆኑን ለመወሰን እርሱ ራሱ ዳኛ የሚሆንበትንና የሚወስንበት መንገድ ለእስራኤላውያን ሰጣቸው። ጥፋተኛ ያልሆነው ሰው «በመራራ ውኃ» እንዳይሞት የሚጠብቅና ጥፋተኛ የሆነውን ደግሞ እንዲሞት የሚያደርግ እርሱ ብቻ ነበር። 

ሠ. የናዝራዊነት ስእለት (ዘኁ.6፡1-2)

ራሱን ለተወሰነ ጊዜ ለእግዚአብሔር ለመስጠት ለሚፈልግ ሰው፥ እግዚአብሔር ልዩ መመሪያዎችን ሰጠ። ራሱን ለእግዚአብሔር የለየ ሰው «የናዝራዊነትን ስእለት» ፈጽሟል ይባል ነበር። ሰው ለእግዚአብሔር የገባውን ስእለት ለመፈጸምና ከእግዚአብሔር ልዩ ጥበቃ እንዲሁም በረከት ለማግኘት ራሱን የመስጠት ጊዜ ይኖረዋል። የናዝራዊነትን ስእለት የሚያደርግ ሰው ሦስት ነገሮችን ማሟላት አለበት፡-

ሀ) የወይን ተክል ውጤት የሆነውን ማንኛውንም መብላት አይችልም ነበር። በእስራኤል ምድር የሚገኝ ዋነኛው ፍራፍሬና መጠጥም የወይን ፍሬ ውጤት ነው።

ለ) በናዝራዊነት ስእለት ሥር መሆኑን የሚያሳይበት ውጫዊ መንገድ ጸጉሩን ማሳደግ ነበር። 

ሐ) ማንኛውንም አስከሬን መንካት አይፈቅድለትም ነበር። 

ይህ አደራረግ በፍጹም ፈቃደኝነት የሚፈጸም መሆኑን ማስተዋል ጠቃሚ ነው። በእግዚእብሔር ግፊት ሳይሆን፥ በሰውዬው ፈቃደኝነት የሚፈጸም ነው። ደግሞም ጊዜያዊና ሰውዬው ለስእለቱ እስከተለየ ድረስ ብቻ የሚቆይ ነው።

ሳምሶን በናዝራዊነት ስእለት ሥር ለነበሩ ሰዎች ጥሩ ምሳሌ ነው። የእርሱ ስእለት ቋሚ በመሆኑ፥ ጉዳዩን የተለየ ያደርገዋል። አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ የናዝሬቱ ኢየሱስ ተብሎ ስለሚጠራ፥ በዚህ ስእለት ሥር ነበረ ይላሉ። ይህ ግን ሊሆን እንደማይችል የምናየው ኢየሱስ ወይን እንደጠጣ የተገለጠ ነገር ስላለ ነው (ሉቃ.1፡33-34)። ይልቁንም ናዝራዊ የተባለው እርሱ ከናዝሬት ከተማ ስለነበረ ነው።

ረ. በመገናኘው ድንኳን ስለሚደረግ አምልኮ የተሰጡ ልዩ መመሪያዎች (ዘኁ.6፡22-8፡26) 

ሰ. እስራኤላውያን ሊመሩበት የሚገባ መንገድ (ዘኁ. 9፡15-10፡10) 

በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመምራት ሁለት ዋና ዋና መሣሪያዎችን ሰጥቷቸው ነበር፡፡ የመጀመሪያው፥ የእግዚአብሔር የደመና ክብር ነበር። ይህ ደመና የእግዚአብሔር ሕልውና ምልክት ነበር። በቀን ደመና፥ በማታ ደግሞ እሳት ይሆን ነበር። ደመናው የመገናኛውን ድንኳን ለቆ በሰማይ ላይ በሚሆንበት ጊዜ፥ ሕዝቡ የነበሩበትን ስፍራ ለቀው፥ ደመናውን እየተከተሉ በመሄድ የሚቀጥለውን የሰፈራ ስፍራ እስኪያገኙ ድረስ መንቀሳቀስ፥ ደመናው ከመገናኘው ድንኳን ላይ እስካልተነሣ ድረስ ግን በዚያው መቆየት እንዳለባቸው ያውቁ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር እንመራበት ዘንድ ለእኛ የሰጠን ምንድን ነው? ለ) እግዚአብሔር አንድን ጉዳይ በሚመለከት ግልጽ የሆነ መመሪያ ለአንተ የሰጠበትን ጊዜ ጥቀስ። ሐ) ምን ዓይነት የአመራር መንገድ በመስጠት ነበር የተጠቀመው?

ሁለት ልዩ መለከቶችን ሠርቶ ለካህናቱ እንዲሰጥ እግዚአብሔር ሙሴን አዝዞት ነበር። ሁለቱም መለከቶች በሚነፉበት ጊዜ ሕዝቡ ሙሴ ወደሚገኝበት ወደ መገናኛው ድንኳን ይመጣል። አንዱ መለከት ብቻ ሲነፋ፥ ወደ ሙሴ የሚመጡት መሪዎች ብቻ ነበሩ። እነዚህ መለከቶች ጉዞ ለመጀመር ምልክት ለመስጠትና በተጨማሪ ጠላቶች ካሉ ለውጊያ ለማዘጋጀት ይጠቀሙ ነበር፤ እንዲሁም ለተለዩ ሃይማኖታዊ በዓላት ምልክት በመሆንም ያገለግሉ ነበር። 

 1. እስራኤል ከሲና ተራራ ተነሥተው ወደ ቃዴስ በርኔ እንደተጓዙ (10፡11-12፡16)

ሕዝቡ በሲና ተራራ 11 ወራት ከቆዩ በኋላ፥ ወደ ከነዓን ለመሄድ ጉዞ ጀመሩ። ይህ ጉዞ ጥቂት ወራት ብቻ የሚፈጅ ነበር። ነገር ግን 38 ዓመታት ፈጀ። እስራኤላውያን ከሲና ተራራ የከነዓን ምድር ደቡባዊ ጫፍ ወደ ሆነችው ወደ ቃዴስ በርኔ ለመድረስ የፈጀባቸው 11 ቀናት ብቻ ነበር። ነገር ግን እነዚህ 11 ቀናት በኃዘንና በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ የተሞሉ ነበሩ። እስራኤላውያን ወደ ቃዴስ በሚጓዙበት ጊዜ ስለተፈጸሙት ነገሮች የሚከተሉትን አስተውል፡-

ሀ. የሲና ተራራ፡- ሰፈሩ ከተደራጀና የጉዞ ትእዛዝ ከተላለፈ በኋላ፥ የእግዚአብሔር ደመና ከመገናኘው ድንኳን ላይ ተነሥቶ ሕዝቡ ለጉዞ ተዘጋጀ። ሙሴም ሕዝቡን ወደ ከነዓን እንዲመራ የአማቱን የራጉኤልን ልጅ ኦቦብን ጠየቀው። (ማስታወሻ፡- ራጉኤል የዮቶር ሌላው ስም ነው) (ዘጸ.2፡18፤ 3፡)። 

ለ. ተቤራ ወይም የምኞት መቃብር (ዘኁ.10፡33-11፡35)፣ በዚህ ስፍራ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ተፈጸሙ፡-

 1. ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ ስላጉረመረሙ ከሰማይ የመጣ የእግዚአብሔር እሳት አንዳንዶቹን ገደለ። 
 2. ሕዝቡ ከመና ሌላ የሚበላ ነገር ስለፈለጉ በእግዚአብሔር ላይ አጉረመረሙ። የእግዚአብሔር የቸርነት ስጦታ የሆነውን መና እምቢ በማለታቸው እግዚአብሔር ይበሉ ዘንድ ድርጭትን ላከላቸው፤ ነገር ግን «ከግብፅ ለምን ወጣን» በማለት ጌታን ስላልፈለጉ ብዙዎቹ ሞቱ።

iii. ሙሴ ሕዝቡን በመምራት ይረዱት ዘንድ ሰባ ሰዎችን መረጠ። የተመረጡት በሙሴ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር መሆኑን ለማረጋገጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ወረደባቸው። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከእነዚህ ቁጥሮች ስለ እግዚአብሔር የምንማረው ነገር ምንድን ነው? ) እኛም ራሳችን አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔርን የጸጋ ስጦታዎች በመቃወም ጥፋተኞች የምንሆነው እንዴት ነው?

 1. ሐዴሮት (12፡1-16)

በሐዴሮት አንድ ያልታሰበ ነገር ተፈጸመ። የእስራኤልን ሕዝብ ለመምራት እግዚአብሔር በሙሴ ስለ ተጠቀመ፣ ወንድሙ አሮንና እኅቱ ማርያም ቀኑበት። በከፊል የቀኑበት ምክንያት ኢትዮጵያዊ በማግባቱ ነበር። አንዳንድ ምሁራን ሙሴ ኢትዮጵያዊቱን (ኩሻዊቱን) ያገባው የመጀመሪያ ሚስቱ ስለሞተችበት ነው ይላሉ። (ማስታወሻ፡- በብሉይ ኪዳን ኢትዮጵያ (ኩሽ) የተባለው ስፍራ ዛሬ የምናውቀው የኢትዮጵያ ክፍል ሳይሆን በደቡብ ግብፅ የሚገኝ ክፍል ነው።) በተጨማሪም ክብሩን ሁሉ ሙሴ ማግኝቱ ትክክል አይደለም ብለው አሰቡ። እግዚአብሔር ከእነርሱም ጋር ተነጋግሯልና!

የእግዚአብሔር ምላሽ ጠንከር ያለ ነበር። ወደ መገናኛው ድንኳን ጠራቸውና በሙሴ ላይ ለመናገር መብት እንደሌላቸው ነገራቸው። ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት በመነጋገር የተለየ ዕድል ነበረው። ስለዚህ በሙሴ ላይ ለተፈጸመው ዓመፅ አነሣሽ እንደሆነች የምንጠራጠራትን ማርያምን እግዚአብሔር ቀጣት። ማርያምም ለምፃም ሆነችና እስራእላውያን ከሰፈሩበት ሰፈር ውጭ ለ7 ቀናት እንድትቆይ ሆነ፡፡ ሙሴም ስለ ጸለየላት እግዚአብሔር በምሕረቱ ፈወሳት።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በመሪዎች መካከል ስለሚሆነው መቀናናት ከዚህ ታሪክ የምንማረው ነገር ምንድን ነው? ) አንዳንድ መሪዎች በሌሎች ላይ የሚቀኑት ለምንድን ነው? ሐ) በአመራር ስፍራ ላይ በምንሆንበት ጊዜ ክብርን ለራሳችን የምንፈልገው ለምንድን ነው? መ) ቅንዓት ክፉ ለለመሆኑ ከዚህ ታሪክ ምን መማር እንችላለን?

መ.በፋራን ምድረ በዳ የሚገኘው ቃዴስ በርኔ (ዘኁ.12፡16) 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኦሪት ዘኁልቁ ዓላማና መልእክት

፩. በመሠረቱ የኦሪት ዘኁልቁ ታሪክ፥ የእስራኤል ሕዝብ ከሲና ተራራ ጀምሮ እስከ ከነዓን ምድር ያደረገውን ጉዞ በአጭሩ የሚያቀርብ ነው። እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ባለማመናቸው ምክንያት ወደ ከነዓን ምድር ለመግባት አለመቻላቸውንና በእነርሱ ላይ ስለ ተሠጠው የእግዚአብሔር ፍርድ የሚናገር ታሪክ ነው። በኦሪት ዘፍጥረት ተጀምሮ በዘጸአትና በዘሌዋውያንም የቀጠለው የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ አካል ነው።

፪. እንደቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ኦሪት ዘኁልቁም ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ በግልጽ ያስተምረናል። መጽሐፉን በምታጠናበት ጊዜ፥ የሚከተሉትን የእግዚአብሔር ባሕርያት አስተውል፡-

ሀ) እግዚአብሔር ሕዝቡ በማይታዘዘው ጊዜም ቢሆን ታጋሽ ነበር። ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ ጨርሶ አያጠፋቸውም። ነገር ግን ፈጥኖ ይቅር ይላቸዋል። ጸሎታቸውን ከመመለስና ፍላጎታቸውን ሁሉ ከማሟላት አይዘገይም። 

ለ) እግዚአብሔር “ቀናተኛና” ቅዱስ አምላክ ነው። ለእርሱ የሚገባውን ክብሩን ለመጠበቅ ቀናተኛ ነው። እርሱ ቅዱስ ነው፤ ማለትም ኃጢአት በሚፈጸምበት ጊዜ ተገቢውን ፍርድ ይሰጣል። 

ሐ) እግዚአብሔር ሕዝቡን «ለመፈተን» አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተጠቅሟል (ዘዳ. 8፡1-2 ተመልከት)። የአዳምን (ዘፍ. 2፡15-17)፥ የአብርሃምን (ዘፍ. 22፡1-14)፥ የዮሴፍን (ዘፍ. 22፡1-17) እምነት ለመፈተን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተጠቀመ። እግዚአብሔር ፈተናን ወደ ሕዝቡ የሚልከው ሊያጠፋቸው ወይም ኃጢአት እንዲሠሩ ለማድረግ ሳይሆን፥ እምነታቸውን ለማጠንከር ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ያዕ. 1፡2-4 እና ሮሜ 5፡3-5 አንብብ። ሀ) ፈተና በሕይወታችን ውስጥ የሚቀርጻቸውንና የሚገነባችውን ባሕርያት ዘርዝር። ለ) ይህ በሕይወትህ እንዴት ሲፈጸም አየህ? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ላይ ፈተና በሚደርስበት ጊዜ የሚያጉረመርሙት ለምንድን ነው? (1ኛ ዜና 29፡17፤ ኤር. 11፡20፤ መዝ. (139)፡23፤ ኢሳ. 48፡10-11 ተመልከት)።

እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ የፈተነው ለምንድን ነው? ምናልባት ለዚህ ሦስት ምክንያቶችን መጥቀስ እንችላለን።

1) የእስራኤልን ሕዝብ ትሑት ለማድረግና የቃል ኪዳኑን ቅድመ ሁኔታዎች ለሟሟላት፥ በእግዚአብሔር ብቻ መታመን እንዳለባቸው ለማስተማር ነበር። የብርታታቸው ምንጭ እርሱ እንደሆነ እግዚአብሔር ሊያስተምራቸው ይፈልግ ነበር። 

2) እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን በረከት ለመቀበል ለእርሱ በጥንቃቄ መታዘዝና በእርሱ ላይ መደገፍ እንዳለባቸው ለማስተማር ነበር። እግዚአብሔር የሚፈልገው ከፊል መታዘዝን ሳይሆን ፍጹም የሆነ መታዘዝን ነው። እግዚአብሔርን በከፊል ብቻ ስንታዘው ዓመጽ ስለሆነ፥ ሕዝቡን ከኃጢአት ለማንጻት ፍርድን ያመጣል። 

3) የእስራኤላውያንን ውስጣዊ የልብ ሁኔታ በግልጽ ለማሳየት ነበር። ነገሮች ሁሉ በተመቻቹ ጊዜ በእግዚአብሔር መደገፍ እጅግ ቀላል ነው፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ በእርግጥ እንደምንደገፍ የሚያሳዩን አስቸጋሪ ጊዜያት ናቸው (ዕብ. 3፡16-4፡2)። የሚያሳዝነው ግን እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በፈተናችው ጊዜ፥ በፈተናው ወደቁ። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብፅ አውጥቶአቸዋል። ዳሩ ግን አሁንም የግብፅ አለማመንና ውሸት በልባቸው ስለቀረ የተቀደሰ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነው ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት መንጻት ነበረባቸው። ስለዚህ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ መታመንና ለእርሱ መታዘዝን ለማስተማር 38 ዓመታት በምድረ በዳ እንዲንከራተቱ ማድረግ ነበረበት።

የውይይት ጥያቄ ሀ) እነዚህ ትምህርቶች ለዛሬስ የሚያስፈልጉን እንዴት ነው? ለ) በአሁኑ ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ምላሽ በምድረ በዳ ከነበሩት አይሁድ ምላሽ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ሕይወታችንን ከኃጢአት ፍላጎትና ዓለምን ከመምሰል ለማንጻት የምንቸገረው ለምንድን ነው?

መ) እግዚአብሔር ለእስራኤልና ለአብርሃም የገባውን ቃል ኪዳን ጠበቀ፡- አብዛኛዎቹ እስራኤላውያን ባለማመናቸው እግዚአብሔር ቢፈርድባቸውም፥ በትዕግሥት እርሱን ሊያከብሩ የሚችሉ ሕዝብ ያደርጋቸው ዘንድ የተለያዩ ተግባራትን ፈጸመ እንጂ፥ ሕዝቡን አላጠፋም። እግዚአብሔር ባሪያ የነበሩትን ሕዝቦችን ወሰደና አንድ ነጻ ሕዝብ በማድረግ ከእነርሱ ጋር በሲና ተራራ የገባውን ቃል ኪዳን ለመፈጸም ይችሉ ዘንድ አዘጋቸው።

ሠ) እግዚአብሔር ተከታዩ የእስራኤል ትውልድ በእርሱ ማመንና ለእርሱ መታዘዝ እንደሚገባቸው ለማስጠንቀቅ ፈልጎ ነበር። አለበለዚያ፥ አባታቸው በምድረ በዳ ያጋጠማቸው ዓይነት ፍርድ ያገኛቸዋል።

ረ) እግዚአብሔር ባለማመንና በዓመፅ ላይ ፈረደ፡፡ በብዙ ረገድ የኦሪት ዘኁልቁ ታሪክ ያለማመን፥ ያለመታዘዝና በዚህም ምክንያት በሕዝቡ ላይ የመጣው ፍርድ ታሪክ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ በኃጢአታቸው ምክንያት ስላገኛቸው ፍርድና ሞት የተዘገበ ታሪክ ነው። ግልጽ የሆነው የኃጢአት ባሕርይ በእግዚአብሔር ላይ ፃመፅ መሆኑን ያሳያል። ኃጢአት ድንገተኛ ስሕተት ወይም ያልታሰበ ክስተት አይደለም። ሆን ብሎ በእግዚአብሔር ላይ በግልጽ ማመፅ ነው።

በመንፈሳዊ ረገድ ኦሪት ዘኁልቁ የሚናገረው፥ ስለ እምነት እርምጃ፥ ይልቁንም ያለማመን ውጤቶችን በሚመለከት ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ፥ በእምነትና በመታዘዝ ከመኖር ይልቅ፥ ባለመታዘዝና ባለማመን የመመላለስ ዝንባሌ ነበራቸው። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ያለማቋረጥ በመንፈሳዊ ብስለት ያድጉ ዘንድ አባሎቻቸውን ሊያበረታቱ ይገባል። እኛ ወይ እያደግን ነው፥ አልያም አለማመንና አለመታዘዝ ወዳለበት ሥጋዊ ሕይወት እየተንሸራተትን ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ቤተ ክርስቲያን ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ሞገስዋን ትታ፥ እግዚአብሔርን በግማሽ ልብ ማምለክ እንዳትጀምር መጠንቀቅ አለባቸው። አምልኮ ሥነ-ሥርዓት ብቻ ከሆነና በቤተ ክርስቲያን አባሎች ሕይወት ውስጥ ዕለታዊ መታዘዝ እንዲኖር የማያደርግ ከሆነ፡ በመጨረሻ ያቺ ቤተ ክርስቲያን ትሞታላች።

የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህን የኦሪት ዘኁልቁ መሠረታዊ ትምህርቶች ስትመለከት፥ ክርስቲያን ይህን መጽሐፍ ማጥናት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው ብለህ ታስባለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኦሪት ዘኁልቁ መግቢያ

እስካሁን ድረስ ከፔንታቱክ መጻሕፍት መካከል የመጀመሪያዎቹ ሦስቱን ማለት ዘፍጥረት፥ ዘጸአትና ዘሌዋውያንን አጥንተናል። በዘፍጥረት እግዚአብሔር፥ አይሁድ የራሱ የተለዩ ሕዝብ እንዲሆኑና እንዲያገለግሉት እንዴት እንደመረጣቸው ተመልክተናል። በዘጸአት ደግሞ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከባርነት እንዴት እንደተቤዣቸው አይተናል። ዘሌዋውያን የተዋጁ የእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ሆነው መኖር ይችሉ ዘንድ፥ እግዚአብሔር ለአይሁድ ሕዝብ ስለሰጣቸው ሕግጋት ይናገራል። ዛሬ ደግሞ የእስራኤል ሕዝብ እምነትን በማጣቱ ምክንያት በእግዚአብሔር ተቀጥቶ በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት እንደተንከራተተ የሚናገረውን ኦሪት ዘኍልቁን እናጠናለን።

የውይይት ጥያቄ ሀ) የክርስቲያን ሕይወት እንደጉዞ የሚቆጠረው እንዴት ነው? ለ) የክርስቲያን የሕይወት ጉዞ ጅማሬ ምንድን ነው? ሐ) የጉዞው መጨረሻስ ምንድን ነው? መ) የራስህን ጉዞ የጀመርከው መቼ ነው?

የክርስቲያን መንፈሳዊ አካሄድ በጉዞ መልክ በጥሩ ሁኔታ ተገልጿል። የክርስቲያን ሕይወት ዕድሜ ልክ የሚጠይቅ ረጅም ጉዞ ነው። አንዳንዶች ይህ ጉዞ «የመናኝ» ጉዞ ነው ይሉታል። ለክርስቲያኖች ይህ ጉዞ የተጀመረው በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን በዳኑበት ጊዜ ነው። ጉዞውንም የምናጠቃልለው መንግሥተ ሰማያት ስንደርስ ነው። በጣም አስፈላጊ ነገር የጉዞው መጀመሪያ ሳይሆን፥ መንግሥተ ሰማያት እስክንደርስ ድረስ ጉዞውን እንዴት እንደምንጓዝ ነው። የድልና የመንፈሳዊ እድገት መንገድ ልንጓዝ፥ እንችላለን። ወይም ደግሞ የመንፈሳዊ ሕይወት ሽንፈትና የእምነት ጉድለት ጉዞ ልንጓዝ እንችላለን። የእምነት ጉድለትና አለመታዘዝ የሚታይበት ሕይወት ለመኖር ከመረጥን በግል የምንከፍላቸው በርካታ ዕዳዎች ይኖራሉ።

እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፅ ባርነት ነጻ ካወጣቸው በኋላ ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚያደርጉትን ጉዞ ጀመሩ። ከሦስት ወራት በኋላ በሲና ተራራ ራሱን ከገለጠላቸውና የእርሱ ሕዝብ በመሆናቸው የተለዩ የሚያደርጋቸውን ግልጽ ትእዛዛት ከሰጣቸው ከእግዚአብሔር ጋር ተገናኙ። በኦሪት ዘኁልቁ ወደ ከነዓን የሚደረገው ጉዞ ቀጥሉ እንመለከታለን። ከነዓን ለመድረስ ጥቂት ሳምንታት ብቻ ይፈጅ የነበረው ጉዞ 40 ዓመታት ወሰደ። ለምን? ምክንያቱም የእስራኤል ሕዝብ አለማመንና አለመታዘዝ ነበር። ኦሪት ዘኁልቁ በመንፈሳዊ ሕይወት ጉዞአችን እንዴት መራመድ እንደሌለብን የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎችን፥ አለማመንና አለመታዘዝ የሚያስከትለውን ክፉ ፍሬ ያሳየናል። ስለዚህ ከእነዚህ ትምህርቶች በመጠቀም በመንፈሳዊ ሕይወታችን እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝና ለታይታ ሳይሆን በእምነት ለመራመድ መወሰን አለብን።

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) ባለማመንና ባለመታዘዝ የተጓዝክባቸው ጊዜያት የትኞቹ ናቸው? በዚያን ጊዜ ምን ሆነ? ለ) ለእግዚአብሔር በመታዘዝና በእርሱ በማመን የኖርክባቸው ጊዜያት የትኞቹ ናቸው? ሐ) እምነትን በማጣት ከተራመድክባቸው ጊዜያት እነዚህ በምን ይለያሉ?

ኦሪት ዘኍልቁ ከኦሪት ዘጸአትና ዘሌዋውያን የሚቀጥል ታሪክ ነው። እስራኤላውያን ከሲና ተራራ ተነሥተው በከነዓን ምድር መግቢያ ድረስ ያደረጉትን ጉዞ ይገልጻል። በኦሪት ዘኁልቁ ታሪክ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በምድረ በዳ እንዴት እንደፈተናቸው በእግዚአብሔር ላይ ያለማቋረጥ እንዴት እንዳመፁ እንመለከታለን። ሕዝቡ ባለመታዘዛቸው ምክንያት ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገቡ እግዚአብሔር ከመፍቀዱ በፊት፥ እንዴት አንድ ትውልድ በሙሉ እንዲጠፋ እንዳደረገ እንመለከታለን።

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ኦሪት ዘኁልቁ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ሀ) የኦሪት ዘኁልቁ ዋና ታሪክ ምንድን ነው? ለ) በመዝገበ ቃላት ውስጥ የሚገኘውን የመጽሐፉን አስተዋጽኦ ገልብጥ። ሐ) «ዘኁልቁ» የሚለው ቃል በአማርኛ ምን ማለት ነው? ትርጉሙን የማታውቅ ከሆነ ግዕዝ የሚያውቅ ሰው ፈልገህ ትርጉሙን ለመረዳት ሞክር (የኦርቶዶክስ ቀሳውስት በዚህ ሊተባበሩህ ይችላሉ)።

የመጽሐፉ ርእስ

ከፔንታቱክ መጻሕፍት ውስጥ የአራተኛው መጽሐፍ ርእስ በአማርኛ «ዘኁልቁ» የሚል ሲሆን ትርጉሙም «መቁጠር» ማለት ነው። ይህ ርእስ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ አይሁዳውያን ሁለት ጊዜ የመቆጠራቸውን ታሪክ ያመለክታል (ዘኁል.1 እና 26)። የዚህ ርእስ ምንጭ ሴፕቱዋጀንት የተባለው የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። 

በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን የዚህ መጽሐፍ ርእስ “በምድረ በዳ ውስጥ” የሚል ነው። ይህ ቃል የተገኘው በመጽሐፉ ውስጥ ከሚገኘው የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር ከተወሰዱት ቃላት ነው። ይህ ርእስ በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ርእሶች በብዙ ረገድ የተሻለ ነው። ምክንያቱም የኦሪት ዘኍልቁ ቃና ታሪክ እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ባለማመናቸው ምክንያት ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ እንደተንከራተቱ ስለሚናገር ነው።

ጸሐፊው

እንደቀሩት የፔንታቱክ መጻሕፍት ሁሉ የዘኁልቁ ጸሐፊ ማንነት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የሚያከራክር ሀኖ ቆይቶአል። ክርስቲያኖችም ሆኑ አይሁድ የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ሙሴ በመሆኑ ላይ አጥብቀው ይስማሉ። ስለዚህ ዋናው የዘኁልቁ ጸሐፊ ሙሴ መሆኑን ማመን የተሻለ ነው (ዘኁል. 33፡2)። ሙሴ በዘኁልቁ ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ ነገሮች በቀጥታ ከእግዚአብሔር ተቀብሏል። ዘኍልቁ የተፈጸሙትን አብዛኛዎቹን ነገሮች በግል ተለማምዶአቸዋል። በጊዜው የነበሩትንም ሌሎች መጻሕፍት ተጠቅሞባቸዋል። ለምሳሌ ሙሴ፥ ምሁራን «የበለዓም መዝሙራት» (ዘኁል. 22-24)፥ «የሐሴቦን መዝሙር» (ዘኁል. 21፡27-30) እና «የጌታ ጦርነት መጽሐፍ» ብለው የሚጠሯቸውን መጻሕፍት ኦሪት ዘኁልቁን ለመጻፍ ተጠቅሞባቸዋል (ዘኁል. 21፡14-18 ተመልከት)። በመጽሐፉ ውስጥ ሙሴ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው እንደ ሦስተኛ ሰው በመሆኑና (ዘኁል. 12፡3፤ 15፡22-23) እንዲሁም አንዳንድ የተጻፉ አስተያየቶችም መጽሐፉን በሌላ አቀናባሪ የተዘጋጀ ስለሚያስመስሉት (ምሳሌ፡- ዘኁል. 13፡11፤ 27፡14፤ 31፡53) ሙሴ ከጻፈው ከብዙ ዓመታት በኋላ፥ ሌላ ሰው አቀናብሮት ይሆናል። 

የኦሪት ዘኁልቁ ታሪካዊ ማጠቃለያ

የኦሪት ዘኁልቁ ታሪክ 38 ዓመታት ከ9 ወር የፈጀ ታሪክ ነው። · ይህ መጽሐፍ የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ስለመንከራተታቸው ይናገራል። ታሪኩ በሦስት ዋና ዋና ክፍለ-ጊዜያት ይከፈላል፡-

 1. በሲና ተራራ (ይህ የመገናኛው ድንኳን ተሠርቶ ካለቀበት ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር የክብር ደመና ሕዝቡን መምራት እስከ ጀመረበት ድረስ ያለው የ20 ቀናት ጊዜ ነው) (ዘኁል. 1-10፡11)። 
 2. በምድረ በዳ መንከራተት (ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ በማመፃቸው የተንከራተቱበት የ38 ዓመታት ጊዜ) (ዘኍል. 10፡11-20፡13)።
 3. ከቃዴስ እስከሞዓብ ምድር ድረስ የተደረገ ጉዞ (6 ወራት) (ዘኁል. 20፡14-36፡13)። 

የኦሪት ዘኁልቁ አስተዋጽኦ 

 1. እስራኤላውያን በሲና ተራራ (1፡1-10፡11) 
 2. ከሲና ተራራ እስከ ቃዴስ በርኔ የተደረገ ጉዞ (10፡11-13፡25)
 3. የእስራኤላውያን በቃዴስ መስፈርና ያ ትውልድ ሁሉ እስኪያልቅ ድረስ በምድረ በዳ መንከራተታቸው (13፡26-20፡21)። 
 4. ተተኪው የእስራኤል ትውልድ ከቃዴስ እስከሞዓብ ምድር ያደረገው ጉዞ (20፡22-21፡35) 
 5. የእስራኤላውያን በሞአብ ምድር መስፈር (22-36) 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)