ዘጸአት 25-40

ከዘጸአት 25-40 ባሉት ክፍሎች ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ቀርበዋል። 1) እግዚአብሔርን የማምለኪያ ስፍራ የሆነው የመገናኛው ድንኳን እንዴት መሠራት እንዳለበት የሚናገረው መመሪያ ሰፊውን ክፍል ይዟል። ቀጥሎም የእስራኤል ሕዝብ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ተቀብለው እግዚአብሔር የሚኖርበትን የመገናኛ ድንኳን እንዴት እንደሠሩ ይናገራል። 2) በሁለተኛ ደረጃ የካህናትና የሊቀ ካህኑ አልባሳት እንዴት እንደተሠሩ የሚናገር ክፍል እናገኛለን። 3) ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ የጥጃን ምስል ሠርተው እንዴት እንዳመለኩ የሚናገር ክፍል እናገኛለን።

የውይይት ጥያቄ፥ ዕብ. 8፡1-6፤ 9፡1-14 አንብብ። የዕብራውያን ጸሐፊ የቀድሞውን የመገናኛ ድንኳን ከክርስቶስ ሥራ ጋር በማወዳደር ያቀረበው እንዴት ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 25-40 አንብብ። ሀ) በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ ዕቃዎች ዝርዝር። ለ) ለመገናኛው ድንኳን የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ የሰጠው ማን ነበር? ሐ) እግዚአብሔር የመገናኛው ድንኳን እንዲሠራ ያዘዘበትን የተለያዩ ምክንያቶች ዘርዝር። መ) ሙሴ በተራራው ላይ በቆየበት ጊዜ እስራኤላውያን ምን ኃጢአት ሠሩ? ሠ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የሙሴ ታላቅ መንፈሳዊ መሪነት የተገለጠው እንዴት ነው? 

፩. የመገናኛው ድንኳን

እስከዚህ ጊዜ ድረስ እስራኤላውያን በመሠዊያ ላይ ያመልኩ ነበር። የየቤተሰቡ ኃላፊም ለቤተሰቡ እንደ ካህን ያገለግል ነበር። መሠዊያ ሠርቶ፥ በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር የሚሆን እንስሳ ይሠዋ ነበር። በምድሪቱ ውስጥ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ፥ ሌሎች መሠዊያዎችን ይሠራ ነበር። አሁን ግን እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ስለ መረጠና ለሕዝቡ የሚሆን ሕግ ስለ ሰጠ፥ የአምልኮ መንገዳቸውን ለወጠው። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር እርሱን የሚያመልኩበት የመገናኛ ድንኳን እንዲሠሩ አዘዛቸው። ሁለተኛ፥ አምልኮውን ይመሩ ዘንድ ካህናትን ለዚህ ሥራ ለየ። በዚህ በዘጸአት ባለው የተወሰነ ክፍልና በኦሪት ዘሌዋውያን ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለማምለክ እንዴት መቅረብ እንዳለባቸው የተጻፉ ትእዛዛት አሉ።

የእስራኤል ንጉሥ በሆነው በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን ከተደረገና የእግዚአብሔር አገልጋዮችም ካጸኑት በኋላ፥ ሕዝቡ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት የመገናኛ ስፍራ ይሆን ዘንድ የመገናኛ ድንኳንን እንዲሠሩ አዘዘ። የመገናኛው ድንኳን እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን ለሕዝቡ የሚገልጥበትም ስፍራ ነበር። እግዚአብሔር እንዳለው «በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ» (ዘጸ. 25፡8)። የመገናኛው ድንኳን ዛሬ እንዳሉት ቤተ ክርስቲያኖቻችን ቋሚ ሕንጻ አልነበረም። እስራኤላውያን በሚሄዱበት ስፍራ ሁሉ በውስጡ ካሉት ዕቃዎች ጋር ይዘው ለመሄድ እንዲችሉ ተደርጎ የተሠራ ነበር። ቤተ መቅደሱ ቋሚ የማምለኪያ ስፍራ ተደርጎ በሰሎሞን የተሠራው ከ400 ዓመታት በኋላ ነበር።

ስለ መገናኛው ድንኳን የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-

 1. የመገናኛው ድንኳን አንድ ብቻ ነበር እንጂ እንደ አሕዛብ የማምለኪያ ስፍራ ብዙ አልነበረም። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በመገናኛው ድንኳን ብቻ እንዲያመልኩ አዘዛቸው። ይህም እስራኤላውያንን ከመኮብለልና ሐሰተኞች አማልክትን ከማምለክ ለመጠበቅ ነበር።
 2. የእስራኤል ሕዝብ የመገናኛውን ድንኳን ለመሥራት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን የመስጠት ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር። የእስራኤል ሕዝብ የመገናኛውን ድንኳን ለመሥራት ምን ያህል ከፍተኛ ጉጉት እንደነበራቸው የምናየው ለመሥሪያ ከሚያስፈልጉ ነገሮች በላይ በመስጠታቸው ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ሙሴ ሕዝቡን ከመስጠት እንዲቆጠቡ ይነግራቸው ነበር (ዘጸ. 36፡2-7)።
 3. የመገናኛው ድንኳን የሚገኘው በእስራኤላውያን ሠፈር መሐል ነበር። ይህም እግዚአብሔርን ማምለክ በሕይወታቸው ከሁሉ በላይ አስፈላጊ ነገር መሆኑን የሚያሳይ ነበር (ዘኁል. 2፡17)።
 4. የእግዚአብሔር መገኘት የተቀደሰ መሆኑንና ከኃጢአትም መለየቱን ለማመልከት፥ ከሕዝቡ በሐር መጋረጃ ተለይቶ ነበር።

ለመገናኛው ድንኳን አራት የተለያዩ ክፍሎች ነበሩት። የመጀመሪያው፥ ከመገናኛው ድንኳን ውጭ ያለው ስፍራ ነው። ሰዎች እግዚአብሔርን ስለማምለክ አንዳችም ትኩረት ሳያደርጉ ሊመላለሱና ሊሠሩ የሚችሉበት ስፍራ ነው። ይህም ሕዝቡ የሚኖሩበት ስፍራ ነው። ሕዝቡን ከመገናኛው ድንኳን የሚለየው መጋረጃ ነበር። የመገናኛው ድንኳን እግዚአብሔር የሚያድርበትና እርሱ ሊመለክበት የሚገባ ስፍራ መሆኑ በግልጽ ታውቆ መከበር የሚገባው ነበር። 

በሁለተኛ ደረጃ፥ ውጫዊው ክፍል ወይም «አምልኮ የሚፈጽሙ ሰዎች ያሉበት ክፍል» የሚባል ስፍራ ነበር። በዚህ ክልል ለአምልኮ የሚያገልግሉ ሁለት ዋና ዋና ዕቃዎች ነበሩ። እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡

1) የነሐስ መሠዊያ፡- መሠዊያው 2.5 ካሬ ሜትር ስፋትና 1 ሜትር ከፍታ ነበረው። እርሱም መሥዋዕቶች ሁሉ የሚቀርቡበት ትልቅ መሠዊያ ነበር። ማንኛውም ተራ ሰው ወደ እግዚአብሔር በመምጣት አምልኮ ለመፈጸም የሚችልበት ስፍራ ነበር። ከዚህ የበለጠ ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ ግን አይችልም ነበር። ከዚህ የበለጠ በመቅረብና ወደ መገናኛው ድንኳን ውስጥ በመግባት ለማምለክ የሚችሉት ካህናት ብቻ ነበሩ። 

2) የነሐስ መታጠቢያ፡- ይህም የተሠራው ከነሐስ ሲሆን፥ በውስጡ ውኃ ይደረግበት ነበር። ካህናት ወደ ቅድስት በመግባት እግዚአብሔርን ከማምላካቸውና ከማገልገላቸው በፊት፥ ንጽሕና ከጎደላቸው ከማናቸውም ነገሮች መንጻታቸውን ለማሳየት፥ እግሮቻቸውን የሚታጠቡት በዚህ ውኃ ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ይኸው መንፈሳዊ መንጻት በዚህ ዘመን ላሉ መሪዎች የሚያስፈልገው እንዴት ነው? 

በሦስተኛ ደረጃ፥ የሚገኘው ስፍራ ቅድስት ተብሎ የሚጠራው ነው። በዚያ በሰፊው የመገናኛ ድንኳን ክልል ውስጥ አነስተኛ ድንኳን ነበር። ይህ ድንኳን ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፥ ሰፊው ክፍል ቅድስት ይባል ነበር። ቅድስት የተባለው ስፍራ እግዚአብሔር ለማገልገል ኃላፊነት ያለባቸው ካህናት በየዕለቱ አገልግሎታቸውን የሚፈጽሙበት ስፍራ ነበር። ቅድስት በተባለው ስፍራ ሦስት የአምልኮ ዕቃዎች ነበሩ።

1) በስተሰሜን በኩል የኅብስቱ መቀመጫ ወርቃማ ጠረጴዛ ነበር። የተሠራው ከግራር እንጨት ሲሆን በወርቅ ተለብጦ ነበር። በጠረጴዛው ላይ እያንዳንዳቸው አንዳንድ የእስራኤል ነገድ የሚወክሉ እርሾ የሌለባቸው አሥራ ሁለት ቂጣዎች ነበሩ። እነዚህ በየሳምንቱ እየተቀየሩ ካህናቱ ይበሏቸው ነበር።

2) በደቡብ የቅድስት ክፍል ደግሞ የወርቅ መቅረዝ ነበር። መቅረዙ ሰባት ቅርንጫፎች ነበሩት። በየጠዋቱና በየምሽቱ የሚሆነውን ነገር ለማድረግ ካህናቱ ይከታተሉ ነበር። መቅረዞቹም ሌሊቱን በሙሉ ሲበሩ ያድሩ ነበር።

3) በምዕራብ በኩል ቅድስትን ከተከታዩ ክፍል ከሚለየው መጋረጃ አጠገብ፥ ከወርቅ የተሠራ የዕጣን መሠዊያ ነበር። ይህ መሠዊያ ከነሐስ መሠዊያው የሚያንስ ሲሆን፥ 1.2 ካሬ ሜትር ቁመት ነበረው። በዕጣን መሠዊያው ላይ ካህናቱ በየቀኑ ጥዋትና ማታ ዕጣን ያጥኑበት ነበር። 

በአራተኛ ደረጃ፥ ቅድስተ ቅዱሳን የሚባል ስፍራ ነበር። ይህ አነስተኛ ክፍል ሲሆን፥ የያዘውም ታቦት ብለን የምንጠራውን አንድ የአምልኮ ዕቃ ብቻ ነበር። ይህ የእግዚአብሔር ዙፋን ስለነበር፥ ከመገናኛው ድንኳን ዕቃዎች ሁሉ የሚበልጥና የተቀደሰ ነበር። ታቦቱም ከግራር እንጨት የተሠራ ሆኖ በወርቅ የተለበጠ ነበር። ከ1 ሜትር ትንሽ የሚበልጥ ርዝመት ሲኖረው፥ 0.75 ሜትር ቁመትና ጎን ነበረው። ታቦቱ ክዳን ያለው ሳጥን ይመስል ነበር። በክዳኑ ጫፍና ጫፍ ላይ ክንፎቻቸው የሚያንዣብቡ የሚመስሉ ከወርቅ የተሠሩ የሁለት ኪሩቦች ምስል ነበረበት። ከሁለቱ ኪሩቦች ክንፎች በታች ያለው የክዳኑ ክፍል «የሥርየት መክደኛ» በመባል ይታወቅ ነበር። ምክንያቱም በዓመት አንድ ጊዜ እግዚአብሔር የሕዝቡን ኃጢአት ይቅር ይል ዘንድ ደም የሚረጨው በዚህ ስፍራ ላይ ስለነበር ነው። የእግዚአብሔር ክብር የሚያድረውም በሥርየት መክደኛው ላይ ነበር። ይህም ዙፋኑ ነበር። ከቅድስተ ቅዱሳን ንጉሥ ሆኖ እስራኤልን ያስተዳድር ነበር። ይህ የመገናኛው ድንኳን ክፍል እጅግ የተቀደሰ ስፍራ ስለነበር በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ወደ እርሱ የመግባት ሥልጣን ያለው ሊቀ ካህኑ ነበር።

በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ዓሥርቱ ትእዛዛት የተጻፈበት ጽላት (ዘጸ. 25፡21)፥ መና ያለበት ማድጋ (ዘጸ. 16፡32-34) እና ያቆጠቆጠች የአሮን በትር (ዘኁል. 17፡10) ነበሩበት። ኋላም የእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈበት መጽሐፍ በታቦቱ አጠገብ እንዲቀመጥ ተደረገ (ዘዳ. 31፡26)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የመገናኛውን ድንኳን በመሥራት ረገድ ከምናየው ከፍተኛ ጥንቃቄና ሰፊ ተግባር ውስጥ የምንማራቸው አንዳንድ መንፈሳዊ መመሪያዎች ምንድን ናቸው? ለ) ከአራቱ ክፍሎች ውስጥ እግዚአብሔርን ስለ ማምለክ የምንማረው ነገር ምንድን ነው? 

አንዳንድ ክርስቲያኖች እነዚህ የአምልኮ ዕቃዎች ወደ ክርስቶስ ያመለክታሉ ይላሉ። ለምሳሌ፡-

ሀ) የነሐስ መሠዊያው፥ ክርስቶስ በእኛ ምትክ መሥዋዕት የመሆኑ ምልክት ነው (ሮሜ 5፡8)። 

ለ) የነሐስ መታጠቢያው፥ ክርስቶስ ከኃጢአታችን እንደሚያነጻን ያመለክታል (1ኛ ዮሐ. 1፡9)። 

ሐ) የኅብስቱ ጠረጴዛ፥ ክርስቶስ የሕይወት እንጀራ መሆኑን ያመለክታል (ዮሐ. 6፡51)። 

መ) የወርቅ መቅረዙ፥ ክርስቶስ የዓለም ብርሃን የመሆኑ ምልክት ነው (ዮሐ. 8፡12)። 

ሠ) የዕጣን መሠዊያው፥ ክርስቶስ አማላጃችን መሆኑን ያመለክታል (ዕብ. 7፡25)። 

ረ) የቃል ኪዳኑ ታቦት ክርስቶስ ንጉሣችን መሆኑን ያመለክታል (ራእ. 19፤ 16)።

ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ለመረዳት «ክርስቶስ በማደሪያው ድንኳን» የሚለውን መጽሐፍ ማጥናት ትችላለህ። 

 1. የመገናኛውን ድንኳን ለመሥራት እግዚአብሔር ሁለት ሰዎችን መርጦ ኃይል አስታጠቃቸው። እነዚህ ሰዎች ባስልኤልና ኤልያብ ይባሉ ነበር፤ (ዘጸ. 31፡1-11)። እግዚአብሔር የስብከትና ወንጌልን የማስተማር ሥራ እንደሚያከብር ሁሉ፥ የእጅ ሙያንም ያከብራል።

ችሎታዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር የተሰጡ ስጦታዎች ናቸው። 

 1. የመገናኛው ድንኳን ሥራ በተጠናቀቀ ጊዜ፥ እግዚአብሔር የክብር ደመናውን በማውረድ ሥራቸውን ሁሉ እንደተቀበለ አረጋገጠ። ሕዝቡን ሲመራቸው የነበረው ደመና በመገናኛው ድንኳን ላይ ወረደና ሞላው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር ክብር ከመገናኛው ድንኳ በሚነሣበት ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን ለመከተል ይንቀሳቀሱ ነበር (ዘጸ. 40፡34-38)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዮሐ. 1፡14ን አንብብ። «በእኛ አደረ» ማለት «በእኛ መካከል የመገናኛው ድንኳን ሆነ» ማለት መሆኑን አስተውል። ሀ) ይህ ጥቅስ፥ በዘጸ. 40 ከተጠቀሰው ታሪክ ጋር የሚነጻጸረው እንዴት ነው? ለ) ይህ ስለ ክርስቶስ ምን ያስተምረናል? 

. የካህናት አልባሳት

ከዚህ ቀደም፥ ከሙሴ ዘመን በፊት የቤተሰቡ ካህን የቤተሰብ ኃላፊ የሆነው ሰው እንደነበረ ተመልከተናል። ለእግዚአብሔር መሥዋዕትና ለመሠዋት ኃላፊነት የተሸከመው ሰው እርሱ ነበር። አሁን ግን እግዚአብሔር ያንን አሠራር ለወጠው። እርሱን ያገለግለው ዘንድ አንድ የእስራኤል ነገድ ለየ። ያም የተለየ ነገድ የሌዋውያን ነገድ ነበር። በብሉይ ኪዳን ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን እንዲሠሩ የተፈቀደላቸው ሌዋውያን ብቻ ነበሩ። በተጨማሪ የተመረጡ መንፈሳዊ መሪዎች እንዲሆኑ ከሌዋውያን መካከል እግዚአብሔር አንድ ቤተሰብን ለየ። እነርሱም አሮንና ልጆቹ ናቸው። የአሮን ዝርያዎች ካህናት ሆኑ። ለመገናኛው ድንኳን አጠቃላይ አገልግሎት ኃላፊነት የነበራቸው ሌዋውያን ሲሆኑ፥ ካህናቱ ደግሞ እግዚአብሔርን የማምለክ ፕሮግራም ይመሩ ነበር። በብሉይ ኪዳን ዘመን ካህናት ለሚከተሉት ነገሮች ኃላፊነት ነበረባቸው፡-

 1. ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን በመሠዋትና ለሕዝቡ የኃጢአት ይቅርታን በማስገኘት፥ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል መካከለኛ ሆኖ የማስታረቅን ተግባር መፈጸም ዋና ሥራቸው ነበር (ዘጸ. 28፡29-30፥43)። 
 2. ብዙ ጊዜ ኢሪምና ቱሚም በመጠቀም ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይለዩ ነበር (ዘኁል. 27፡21)። 
 3. ቅዱሳት መጻሕፍትን የመገልበጥና ጠብቆ የማቆየት ኃላፊነት በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል የማስተማር ኃላፊነት ነበረባቸው። 
 4. በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚፈጸሙ ዕለታዊ ተግባራትን ማከናወንና በኃላፊነት መቆጣጠር ነበረባቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህ ኃላፊነቶች ዛሬ የቤተ ክርስቲያን መሪዎቻችን ካለባቸው ኃላፊነቶች ጋር የሚመሳሰሉት ወይም የሚለያዩት እንዴት ነው? 

ካህናት ምን ዓይነት ሰዎች መሆንና በማደሪያው ድንኳን እንዴት ማገልገል እንዳለባቸው እግዚአብሔር ዝርዝር መመሪያዎችን ስለሰጠ፥ ቆይተን እርሱን እንመለከታለን። እንዲሁም ካህናት እንዴት መሥራት እንዳለባቸው መመሪያዎችን ሰጥቷል። 

ካህናት መንፈሳውያን መሪዎች ስለሆኑ፥ ለእግዚአብሔር ራሳቸውን በቅድስና መጠበቅ ነበረባቸው። በእግዚአብሔር ፊት ላላቸው ልዩ ስፍራ መለያና ከመቀደሳቸው አስፈላጊነት አንጻር፥ እግዚአብሔር ልዩ የሆኑ ልብሶችን ሰጣቸው።

 1. በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናት ልብሶች፡- አገልጋዮች እንደ መሆናቸው ካህን መልበስ ያለበት አራት ዓይነት ልብሶች፡- 

ሀ. ረጅምና ያልተሰፋ፥ እስከ እግር ድረስ የሚወርድ እጅጌ ያለው ኮት፥ 

ለ. በሰማያዊ፥ በሐምራዊና በቀይ ጨርቆች የተሠራ የወገብ መታጠቂያ፡ 

ሐ. በራስ ላይ የሚደፋ ቆብ፥ 

መ. ከኮት ሥር የሚለበስ በፍታ የሆነ ዝንጉርጉር የውስጥ ልብስ ነበሩ። 

 1. የሊቀ ካህኑ ልብሶች በጣም የተለዩና ከሌሎች ካህናት ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርጉት ነበሩ። እነዚህን ልብሶች የሚለብሰውም በመገናኛው ድንኳን በሚያገለግልበት ጊዜ ብቻ ነበር።

ሀ. ረጅም መጎናጸፊያ፡- ይህ ከአንገት ጀምሮ እስከ ጉልበት በታች ድረስ የሚደርስ ልብስ ነው። መልኩ ሰማያዊ ሲሆን፥ ሮማኖችና የወርቅ ሻኩራዎች (ቃጭሎች) ነበሩበት። ሻኩራ ለሁለት ምክንያት ጠቃሚዎች ነበሩ፡- አንደኛ፥ ሊቀ ካህኑ በመገናኛው ድንኳን በሚያገለግልበት ጊዜ፥ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በመግባት ላይ መሆኑን ማስጠንቀቂያ ነበሩ (ዘጸ. 28፡35)። ሁለተኛ፥ ሊቀ ካህኑ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ሲገባ፥ እንቅስቃሴ በማሰማት በሕይወት እንዳለና ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር እንዳልቀሠፈው ሕዝቡ እንዲያውቁ ነበር። 

ለ. ኤፉድ፡- ከተልባ እግር የተሠራ (በፍታ)፥ ሁለት ጨርቆች የያዘና በሊቀ ካህኑ ትከሻ የሚያርፍ ነበር። መልኩም በወርቅ፥ በሰማያዊ፥ በሐምራዊና በቀይ ግምጃ የተፈተለ ነበር። ለሁለቱ ጫፎች እያንዳንዳቸው ስድስት ስድስት የእስራኤል ነገዶች ስሞች የተጻፉባቸው መረግድ (የከበረ ድንጋይ) ነበረባቸው። ይህም የሚያመለክተው፥ ሊቀ ካህኑ የእስራኤልን ነገዶች እንደሚወክልና በጌታ ፊት ሸክማቸውን እንደሚያቀርብ ነበር። 

ሐ. የደረት ኪሱ 25 ካሬ ሳንቲሜትር የሆነ ጠፍጣፋ ነገር፥ በብዙ ኅብረ ቀለም ያሸበረቀ ነው፤ ሁለት ዓላማዎችም ነበሩት። የመጀመሪያ፥ በእያንዳንዳቸው ላይ የእስራኤል ነገዶች ስም የተጻፉባቸው አሥራ ሁለት ዕንቁዎች ተሰፍተውበት ነበር። እነዚህም ድንጋዮች ሊቀ ካህኑ እግዚአብሔር ፊት እንዴት ሕዝቡን እንደሚወክል የሚያሳዩ ነበሩ። በደረቱ (በልቡ) ላይ መሆናቸው፥ በፍቅርና በርኅራኄ አሥራ ሁለቱን የእስራኤል ነገዶች ማገልገል እንዳለበት የሚያሳዩ ሊሆኑ ይችላሉ። በሁለተኛ ደረጃ፡ በደረቱ ላይ ባለው ጠፍጣፋ ነገር ሁለት ኪሶች ነበሩ። በሁለቱ ኪሶች ውስጥ ኡሪምና ቱሚም የሚባሉ ሁለት ልዩ ድንጋዮች ነበሩ። እነዚህ ሁለት ድንጋዮች ምን እንደሆኑ በእርግጥ የምናውቀው ነገር የለም። የስማቸው ትርጉም «ብርሃንና» «ፍጹምነት» የሚል ነው። የምናውቀው ነገር የጌታን ፈቃድ ለመወሰን አገልግሎት ላይ መዋላቸውን ነው (ዘኁል. 27፡21)።

መ. ሊቀ ካህኑ በቅጠል ቅርፅ በወርቅ የተሠራና በግንባር ላይ የሚንጠለጠል ነገርም ያደርግ ነበር። በላዩ ላይ «ቅድስና ለእግዚአብሔር» የሚል ጽሑፍም ነበረበት። ይህም የሚያመልኩት አምላክ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሆነ የሚያስታውስ ነበር፤ ስለዚህ ወደ እርሱ ሊቀርቡ የሚገባቸው በተቀደሰ ሕይወት ነበር። በተጨማሪም ሊቀ ካህኑ ለኃጢአት መሥዋዕትን በማቅረብ፥ ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎችን በእግዚአብሔር ፊት እንዴት የተቀደሱ እንደሚያደርጋቸው የሚያመለክት ነበር። 

ካህናቱን ለአምልኮ ሥራ ለመለየት ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ ነበር። ለኃጢአታቸው የሚሆኑ መሥዋዕቶችም ነበሩ። ለተለየ አገልግሎት በእግዚአብሔር መለየታቸውን የሚያሳይ ዘይት የመቀባት ሥርዓትም ነበራቸው። በቀኝ አውራ ጣታቸው ላይ፥ በጆሮአቸውና በትልቁ የእግር ጣታቸው ላይ የደም መረጨት ሥርዓትም ይካሄድ ነበር። ይህም የእግዚአብሔርን ቃል መስማት፥ የጌታን ሥራ መሥራትና፥ በእግዚአብሔር መንገድ መሄድ እንዳለባቸው የሚያሳይ ለመሆኑ አንዳችም ጥርጥር የለውም። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር ካህናትን በማንጻትና ለአገልግሎት በማዘጋጀት ይህን ያህል ጥንቃቄ ያደረገው ለምን ይመስልሃል? ለ) ስለ ቤተ ክርስቲያን አመራር ከዚህ የምንማረው ምን ይመስልሃል? 

፫. የጥጃ ምስል በማምለክ ሕዝቡ የሠሩት ኃጢአት 

ስለ እስራኤል ሕዝብ ታሪክ የሚያስደንቅ ነገር፥ እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር በተገናኘበት ተራራ ጫፍ ላይ እንኳ ቆመው፥ ከእግዚአብሔር ፊታቸውን መልሰው ኃጢአት መሥራታቸው ነበር። ወደ ተራራው በመመልከት የእግዚአብሔርን ሕልውና በደመናው ውስጥ ማየት ይችሉ ነበር። ኃያል የሆነውን እግዚአብሔር በመብረቅ፥ በነጎድጓድና በመሬት መንቀጥቀጥ ውስጥ ካዩና ሲናገራቸው ኃያል ድምፁን ከሰሙ ገና ጥቂት ጊዜ አልፎ ነበር። ይህም ቢሆን እንኳ ሙሴ እስኪመለስ ለ40 ቀናት መቆየት አልቻሉም። ሙሴ ሞቷል ብለው በመገመት እግዚአብሔርን ትተው፥ ጣዖትን ወደ ማምለክ ዞር አሉ። እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር አውጥቶአቸው ነበር፤ ነገር ግን በግብፅ ምድር የነበረው የጣዖት አምልኮ ከልባቸው አልወጣም ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን ትተው ከግብፅ ያወጣን አምላካችን ነው በማለት ከግብፅ አማልክት መካከል አንዱ የሆነውን ጥጃን ያመልኩ ጀመር (ዘጸ. 32፡4)። 

እግዚአብሔር ይህንን ባየ ጊዜ የሰጠው ምላሽ ከባድ ነበር። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በሙሉ በማጥፋት በሙሴ በኩል አዲስ ሕዝብን ለማስነሣት ወሰነ። ሙሴ ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዳያጠፋ ለመነ። በዚህ ስፍራ ሙሴ ያለውን ነገር አስተውሉ መመልከት ጠቃሚ ነው (ዘጸ. 32፡11-14)። በመጀመሪያ፥ ለእግዚአብሔር ስምና ክብር የሰጠውን ትኩረት እንመለከታለን። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ካጠፋ፥ የእግዚአብሔርን ኃይል የመሰከሩት ሕዝቦች ይህንን ተግባር በተሳሳተ መንገድ ይተረጉሙታል። የሙሴ ትኩረት እግዚአብሔር የሚገባውን ክብር በመቀበሉ ላይ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ፥ እግዚአብሔር በአብርሃም በይስሐቅና በእስራኤል በኩል ለራሱ ልዩ ሕዝብ እንደሚያስቀር ቃል የገባውን እንዲያስታውስ ይጠይቀዋል። እግዚአብሔር ከእስራኤል ፍርዱን ይመልስ ዘንድ የሙሴን የአስታራቂነት አገልግሎት ተቀበለ።

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) ከዚህ ታሪክ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ የምንማረው ነገር ምንድን ነው? ለ) ከዚህ ክፍል ስለ ሙሴ ባሕርይ የምንማረውስ ነገር ምንድን ነው?

ነገር ግን ሙሴ የሕዝቡን ኃጢአት በተመለከተ ጊዜ፥ የወሰደውን እርምጃ መመልከት አስፈላጊ ነው። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር በገዛ እጁ ቀርፆ ዓሥርቱን ትእዛዛት የጻፈበትን የድንጋይ ጽላት በቁጣ ሰባበረው። በሁለተኛ ደረጃ፥ ከወርቅ የተሠራውን የጥጃ ምስል ሰባብሮ ፈጨና በውኃ ተበጥብጦ ሕዝቡ እንዲጠጡት አደረገ። በሦስተኛ ደረጃ፥ ሕዝቡ ውሳኔ እንዲያደርጉ ጥሪ አደረገላቸው። ከጌታ ወገን የሆኑ በእርሱ በኩል እንዲሆኑ አደረገ። ሌዋውያን ወደ እርሱ ሲመጡ፥ የእግዚአብሔር የፍርዱ መሣሪያ እንደሆኑ ገልጾላቸው፥ ወንድሞቻቸው የሆኑትን እስራኤላውያን እንዲገድሉ አዘዘ። ሌዋውያኑም የሙሴን ትእዛዝ በመከተል በዚያን ቀን ብቻ ሦስት ሺህ እስራኤላውያንን ገደሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ) ይህን ትእዛዝ ለመፈጸም አስቸጋሪ የሆነው ለምን ነበር? ለ) ይህ ነገር ስለ ኃጢአት አስቸጋሪነት (አስጨናቂነት) እና በጽኑ ሊፈረድበት እንደሚገባም ምን ያስተምረናል?

ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ በመሄድ ለሕዝቡ መለመን ጀመረ። እንደገና የሙሴን የአመራር ብቃትና ታላቅነት እንመለከታለን። የተጨነቀው ለእግዚአብሔር፥ ለክቡሩና ለቃል ኪዳኑ ላለው ታማኝነት ብቻ ሳይሆን፥ ለእግዚአብሔር ሕዝብም ነበር። ሙሴ ሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት የሠሩትን ታላቅ ክፋት አምኖ ተቀበለ። ከዚያም ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን ለመነ። እግዚአብሔር ይቅር ሊላቸው ፈቃደኛ ካልሆነ፥ በሕዝቡ ፈንታ የራሱን የዘላለም ሕይወትን ሊሰጥ ዝግጁ መሆኑን ተናገረ። ከሕይወት መጽሐፍ ስሙን እንዲደመስስ እግዚአብሔርን ለመነ፤ (ዘጸ. 32፡32)።

ሙሴ በመሪነቱ ልዩና ታላቅ እንደነበር የሚያሳዩ ሌሎች ሁለት ታሪኮች አሉ። የመጀመሪያው፥ የመገናኛው ድንኳን ተሠርቶ ከመጠናቀቁ በፊት እንኳ ሙሴ ከሰፈር ውጪ ድንኳን ተክሎ እንደነበር የሚናገረው ታሪክ ነው። ይህ ድንኳን እስራኤላውያን የሚገናኙበት ነበር። ደግሞም ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝበት ስፍራ ነበር። ለእግዚአብሔር ቅርብ ከመሆኑ የተነሣ፥ የእግዚአብሔር ክብር ከፊቱ ያንጸባርቅ ነበርና ሕዝቡ ሊያዩት ባለመቻላቸው ሙሴ ፊቱን ይሸፍን ነበር። ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ተገናኝቶ ሲያበቃ ድንኳኑን በሚለቅበት ጊዜ፥ ኢያሱ ግን እዚያው ይቆይ እንደነበር መመልከቱ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ (ዘጸ. 33፡11)። 

ሁለተኛው ነገር፥ ሙሴ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያለማቋረጥ መምራት ይችል ዘንድ የእግዚአብሔር መገኘት ሁልጊዜ ያስፈልገው እንደ ነበር መገንዘቡ ነው፤ ስለዚህ እንዳይተወው እግዚአብሔርን ለመነ። ክብሩንም እንዲያሳየው ለምኖታል። እግዚአብሔር በቸርነቱ ለዚህ ልመናው መልስ ሰጠውና በሙሴ ፊት ክብሩን አሳለፈ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 32-33 እንደገና አንብብ። ሀ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ሙሴ እግዚአብሔርን የሚፈራ ታላቅ መሪ መሆኑን የሚያሳዩትን ነገሮች ዘርዝር። ለ) እነዚህን እውነቶች ዛሬ በቤተ ክርስቲያን አመራር ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ልናደርጋቸው እንችላለን?

በኦሪት ዘጸአት ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና ትምህርቶች፡-

 1. እግዚአብሔር፡- የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ዓላማ ለሕዝቡ ያለውን የእግዚአብሔር ባሕርይና ሥራ መግለጥ ነው፤ ስለዚህ በዘጸአት ውስጥ ስለ እግዚአብሔር የምናያቸው በርካታ እውነቶች አሉ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 3፡13-15 አንብብ። እግዚአብሔር በሚቃጠለው ቁጥቋጦ ውስጥ ራሱን በገለጸ ጊዜ ለሙሴ የተሰጠው ስም ማን ነበር?

ሀ. ያህዌ የእግዚአብሔር ልዩ ስሙ ነው፡- በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ በእግዚአብሔር የተሰጡ የተለያዩ ስሞችን ተመልክተናል። በጣም በብዛት ያየናቸው ግን ኤሎሄምና አዶናይ የሚሉትን ስሞች ነበር። እንደምታስታውሰው፥ የእግዚአብሔር «ስም» በዕብራውያን ባሕል የእግዚአብሔር ባሕርይ የሚገልጥ ነው። በኦሪት ዘጸአት እግዚአብሔር ሙሴን በተገናኘው ጊዜ ልዩ የሆነ ባሕርይውን ለሙሴ የሚገልጥበትን ያህዌ ያለውን የራሱን አዲስ ስም ስጠው። ይህ ስም «እኔ፥ እኔ ነኝ» የሚል ነበር። በዕብራይስጥ ይህ ሐረግ «ጄሆቫ» ወይም «ያህዌ» የሚል ነው። በኋላ አይሁድ ይህ ስም ከሁሉም በላይ የተቀደሰው የእግዚአብሔር ስም ነበር ብለዋል። 

የእግዚአብሔር ስም ጄሆቫ ወይም ያህዌ የተባለው ለምንድን ነው? የዕብራይስጥ ቋንቋ የሚጻፈው ምንም አናባቢ በሌለው ፊደላት ብቻ ነበር። ስለዚህ ይህ ስም በዕብራይስጡ ያለ አናባቢ ሲጻፍ ይሆናል። አይሁድ በምርኮ ወደ ባቢሎን ከተወሰዱና ከምርኮም ከተመለሱ በኋላ ይህን ይህውህ በሚለው የእግዚአብሔር ስም መጠቀም አቆሙ። ምክንያቱም ይህ ስም ለማንበብ በጣም የተቀደሰ ነው ብለው ስላመኑ ነበር። ስለዚህ እንደ ኤሉሂምና አዶናይ ያሉትን ሌሎች ስሞች ወይም ደግሞ «ቅዱሱ» ወይም የመሳሰሉትን ስሞች ብቻ መጠቀም ቀጠሉ። ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አይሁድ የአጻጻፍ ስልታቸውን ለወጡና ሰዎች ዕብራይስጥን ለማንበብ ማስታወስ ይችሉ ዘንድ አናባቢዎችን ማከል ጀመሩ፤ ስለዚህ ወደ ይህውህ ሲደርሱ፥ አዶናይ የሚለውን ስም ያስገኙትን አናባቢዎች እዚህም ላይ አከሉበት። (እነርሱም በላቲን ፊደል አ፡ኦ፡አ የሚሉት ሲሆኑ በሚጻፍበት ጊዜ ያህዌ የሚል ሆነ።) ይህንን ያደረጉበት ዋና ምክንያት ሰዎች ይህውህ ብለው ከማንበብ ይልቅ፥ አዶናይ እንዲሉ ነበር። በ1520 ዓ.ም. አካባቢ ግን ይህ የእግዚአብሔር ስም በትክክል ሥርዓት እንዲይዝ ተደረገና ጄሆቫ (ያህዌ) ተባለ። ይህንን ስም በቀላሉ የምታስታውሰው፥ የይሖዋ ምስክሮች ተብሎ የሚጠራ የሐሰት ትምህርትን የሚከተሉ ክፍል በመኖሩ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ግን እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው የመጀመሪያው ስም መነበብ ያለበት ያህዌ ወይም ጃሄዌ ተብሉ እንጂ ጄሆቫ (ይሖዋ) ተብሎ አይደለም ብለው ያምናሉ።

ይህውህ የሚለው ቃል በዕብራይስጥ «እኔ ነኝ»፥ ወይም «እርሱ ነው»፥ ወይም «እርሱ ይሆናል» የሚል ትርጉም ከሚሰጠው ግሥ ጋር አንድ ዓይነት ነው። ይህም እስራኤላውያን ስለ እርሱ ባሕርይ እንዲያስታውሱ እግዚአብሔር የፈለገው ልዩ ስም ነው። እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ለእነርሱ ለመግለጥ የተጠቀመበት የቃል ኪዳን ስም ነው። ይህ ስም ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ «እኔ ነኝ» እያለ የተናገራቸው ዐረፍተ ነገሮች ሁሉ የተመሠረቱበት ስም ነው። ለምሳሌ፡- «እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ»፤ «እኔ የሕይወት ውኃ ነኝ»፤ «እኔ ትንሣኤና ሕይወት ነኝ» ወዘተ. እያለ በዮሐንስ ወንጌል የሰጣቸው መግለጫዎች ማለት ነው።

እግዚአብሔር ይህንን ስም በርካታ መንፈሳዊ እውነቶችን ለመግለጥ የተጠቀመበት ይመስላል። በመጀመሪያ፥ ዘላለማዊ የሆነውን የእግዚአብሔርን ባሕርይ በመግለጥ፥ እርሱ መጀመሪያና መጨረሻ እንደሌለው ያሳየናል። እርሱ ምንጊዜም ነበር። እግዚአብሔር ለሙሴ ሊያሳየው የፈለገው ነገር እርሱ ከዓለም መፈጠር መጀመሪያ የነበረው፥ ደግሞም ከእስራኤል ሕዝብ አባቶች ጋር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን ያደረገው አምላክ መሆኑን ነው። በሁለተኛ ደረጃ፥ ደግሞ ይህ ስም እግዚአብሔር ራሱ የሕይወት ኃይል እንዳለውና ስለ ሕያውነቱ በማንም ወይም በምንም ነገር ላይ ያለመደገፉን ያሳያል። በሦስተኛ ደረጃ፥ ደግሞ እግዚአብሔር የማይታወቅ አምላክ እንዳልሆነ፥ የሩቅ አምላክም እንዳልሆነ ይልቁንም ለሚወዱትና በእርሱ ለሚያምኑ ቅርብ መሆኑን ያስተምረናል። አራተኛ፥ ይህ ስም እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ የሆነ፥ ብቃት ያለው በመሆኑ ሕዝቡ በምንም ሁኔታ ውስጥ ይሁኑ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን ያሳያል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ለሙሴ ይህንን ስም መግለጥ ያስፈለገው ለምን ይመስልሃል? ለ) የዚህን ስም ትርጉም ማወቅ ለእኛ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ሐ) የእግዚአብሔርን ስምና ባሕርይ ማወቅ ዛሬ እኛን እንዴት ያበረታታናል?

ለ. እግዚአብሔር ራሱን ለሰዎች የገለጠባቸው የተለያዩ መንገዶች፡-

በኦሪት ዘጸአት ውስጥ የምናገኘው አንድ አስደናቂ እውቀት እግዚአብሔር ራሱን ለእስራኤል ሕዝብ የገለጠባቸው በርካታ መንገዶች ናቸው። እግዚአብሔር በአንድ መንገድ ብቻ ለመሥራት ራሱን አልወሰነም። ራሱን ለመግለጥ የተጠቀመው በተጻፈ ቃል፥ በፍጥረት፥ በሕልም ወዘተ. ብቻ አይደለም። በታሪክ ውስጥ ራሱን ለሕዝቡ የገለጠባቸው በርካታ የተለያዩ መንገዶች አሉ። ኦሪት ዘጸአትን በምታነብበት ጊዜ እግዚአብሔር ራሱን የገለጠባቸውን የሚከተሉትን መንገዶች አስተውል፡-

 1. «በጌታ መልአክ» በኩል (ዘጸ. 3፡2፤ 14፡19) ከኦሪት ዘፍጥረት ጥናታችን ውስጥ እንደምታስታውሰው፥ ይህ መልአክ እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራ ልዩ መልአክ ነው። ይህ መልአክ በቤተልሔም ከመወለዱ በፊት የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ሳይሆን አይቀርም። 
 2. በሌሎች መላእክት (ዘጸ. 23፡20፤ 33፡2)
 3. በተአምራት (ዘጸ. 8፡ 16-19) 
 4. በሚቃጠል ቁጥቋጦ (ዘጸ. 3፡2) 
 5. በእሳት፥ በጢስና፥ በመብረቅ (ዘጸ. 19፡18-20) 
 6. በሚሰማ ድምፅ (ዘጸ. 24፡1) 
 7. በደመና ክብር (ዘጸ. 16፡10) 
 8. በደመናና በእሳት ዓምድ (ዘጸ. 40፡34-38) 
 9. ከሙሴ ጋር ፊት ለፊት በመገናኘት (ዘጸ. 33፡11)

የውይይት ጥያቄ ሀ) ዛሬ እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ የሚገልጥባቸው የተለመዱ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ለእግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን አልፎ አልፎ ባልተለመዱ መንገዶችስ የሚገልጥባቸው የትኞቹ ናቸው?

ሐ. በኦሪት ዘጸአት ውስጥ ስለ እግዚአብሔር የተገለጡ ሰባት እውነቶች፡-

 1. እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ሁልጊዜ ይጠብቃል፤ ተስፋ የሰጠውን የቃል ኪዳን ግዴታም ይፈጽማል (ዘጸ. 2፡24)። 
 2. እግዚአብሔር በክፉዎች ላይ ይፈርዳል፤ ሕዝቡንም ከመከራቸውና ከችግራቸው ያድናቸዋል (ዘጸ. 12፡27)። 
 3. እግዚአብሔር ከሁሉም ነገር የሚበልጥና የበላይ ነው፤ ነገር ግን ለሚወዳቸው ደግሞ ቅርብ ነው (ዘጸ. 19፡10-15፥ 13-18)። 
 4. እግዚአብሔር ለመረጠው ለራሱ ሕዝብ ጥቅም ሲል አሕዛብን ሁሉ የሚገዛና የሚቆጣጠር ነው (ዘጸ. 15፡4-6፤13-18)። 
 5. እግዚአብሔር ቅዱስ ነው። ቅዱስ የሚለው ስም መሠረታዊ ትርጉም «መለየት» ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቅዱስ የሚለው ቃል ሁለት የተሰወሩ ትርጉሞች አሉት። በመጀመሪያ፥ መለየት ወይም ልዩ ማለት ነው። እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም። ከእግዚአብሔር ጋር የሚወዳደር ወይም እርሱን የሚመስለው ማንም የለም። አቻ፥ አምሳያ የለውም። እጅግ ከፍ ያለና ሕልውና ካላቸው ነገሮች ሁሉ በላይ ነው (ዘጸ. 15፡11፤ 18፡10-12)። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፥ ከኃጢአት የተለየ ማለት ነው። እግዚአብሔር በኃጢአት የተበላሸ አይደለም። በአጠገቡ ኃጢአት እንዲኖር አይፈልግም። ጻድቅ ከሆነው ባሕርይ ጋር የሚቃረን፥ ኃጢአት የሆነ ማንኛውንም ነገር ሊያደርግ ወይም ሊያስብ ጨርሶ አይችልም። 
 6. እግዚአብሔር ለሕዝቡ ጸጋንና ምሕረትን የተሞላ ነው። ቅጣት በሚገባቸው ሰዓት እንኳ በንስሐ ሲመለሱ ይቅር ይላቸዋል። ቅጣት በሚገባቸው ጊዜ እንኳ ለጸሎታቸው መልስን ይሰጣል (ዘጸ. 32፡11-14)።
 7. እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚያድን አምላክ ነው። እርሱ ከእስራት ይቤዣቸዋል፤ ከባርነት ይታደጋቸዋል፤ እንዲያገለግሉት፥ እንዲያመልኩትና እንዲታዘዙት ነፃ ያወጣቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ህ) ስለ እግዚአብሔር እነዚህን እውነቶች ማስታወስ ያለብን ለምንድን ነው? ለ) እነዚህ እውነቶች ዛሬ ለክርስቲያኖች | መጽናኛ የሚሆኑት እንዴት ነው?

 1. እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚመሩ ልዩ መሪዎችን ይመርጣል። እነዚህ መሪዎች ልዩ የሆኑት በችሎታቸው ሳይሆን እግዚአብሔር ስለመረጣቸው ነው። ሙሴን የእስራኤል ሕዝብ መሪ አድርጎ እግዚአብሔር የመረጠው ገና ከመወለዱ አስቀድሞ ነው። ሆኖም ግን እግዚአብሔር ሙሴን የተጠቀመበት በመንፈሳዊ አንፃር ሕዝቡን ለመምራት ዝግጁ በሆነበት ጊዜ ነው። በኦሪት ዘጸአት ስለ መሪነት የምናያቸውን የሚከተሉትን ነገሮች ልብ በል፡-

ሀ. መሪዎችን የሚመርጥ እግዚአብሔር እንጂ ሰዎች አይደሉም። ምርጫውም የሚሆነው በሰውዬው ግላዊ ፍላጎት አይደለም።

ለ. እግዚአብሔር ምድራዊ የሆነ የኃይልና የአመራር እውቀት አይማርከውም። ይልቁንም መሪነትን የሚመለከት የዚህ ዓለም አስተሳሰብ (ለምሳሌ፡- ትምህርት፥ ሥልጣን፥ ከአባቶች የተወረሰ ማዕረግ እግዚአብሔር ከሚፈልገው ዓይነት አመራር ጋር በተቃራኒ የሚሄዱ ናቸው። ሙሴ በግብፅ ጥበብ ሁሉ ተኮትኩቶ አድጎ ነበር፤ ስለዚህ እስራኤልን የመምራት መብት እንዳለውና በራሱ ብርታት እስራኤልን ለመምራት እንደሚችል አሰበ። ይህ ግን አልሠራም። እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ በአንድ መሪ ከመገልገሉ በፊት፥ አስቀድሞ ያንን ሰው ዝቅ ያደርገዋል። እግዚአብሔር ይህንን የሚያደርገው፥ መሪው በእግዚአብሔር ብርታት እንጂ በራሱ መደገፍ እንደሌለበት እንዲማር ነው። በዚህ መንገድ ሰውዬው ክብር ከመውሰድ ፈንታ፥ እግዚአብሔር ክብሩን ለራሱ ይወስዳል። ሙሴ የእግዚአብሔር መገልገያ ለመሆን ከመዘጋጀቱ አስቀድሞ በምድረ በዳ በበግ እረኝነት ዓመታትን አሳልፏል። 

ሐ. እግዚአብሔር ከየትኛውም የመሪ ባሕርይ ይልቅ ትሕትናንና በእርሱ ላይ ያለውን መደገፍ ያከብራል። እግዚአብሔር ሙሴን በራሱ ለመናገርም ሆነ ሕዝቡን ለመምራት እንደማይችል ዋስትና እስኪያጣ ድረስ ትሑት አደረገው። 

መ. የእግዚአብሔር ሕዝብ መሪዎች ራሳቸውን ሳይሆን ሕዝቡን ማገልገል ይኖርባቸዋል። ሙሴ መሪነትን የተማረው «በጎችን» በማገልገል ነበር። ከዚያ በኋላ ብቻ ነበር ከእግዚአብሔር የሆኑ መሪዎች የሚመሩት በኃይልና በሥልጣን ሳይሆን በማገልገል ላይ የሚሆነው (ማር. 10፡45 ተመልከት)። 

ሠ. ከእግዚአብሔር የሆኑ መሪዎች የሕዝቡን ጥቅም ከራሳቸው ጥቅም ያስቀድማሉ። እስራኤላውያን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ፈለገ፤ ሙሴ ግን እነርሱ ከሚጠፉ ይልቅ ራሱ እንዲጠፋና እነዚያ በሕይወት እንዲኖሩ ማለደ (ዘጸ. 32፡ 12)።

ረ. የእግዚአብሔር መሪዎች ሸክም የሆነባቸው ስለ ራሳቸው ክብርና ደህንነት እምብዛም ሳይጨነቁ ስለ እግዚአብሔር ክብርና ሰለ ስሙ ክብር ነበር። እስራኤላውያን ኃጢአት ባደረጉና እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው በተነሣ ጊዜ፥ ሙሴ ስለ እግዚአብሔር ስም ገዶትና ይህ ስም በአሕዛብ መካከል ሊኖረው ስለሚችለው ምስክርነት ተጨንቆ ጸለየ (ዘጸ. 32፡12)።

ሰ. ከእግዚአብሔር የሆኑ መሪዎች የመሪነትን ሸክም ከሌሎች ጋር ይካፈላሉ። ሙሴ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚመራው እርሱ ብቻ እንዳልሆነ መማር ነበረበት። ኃላፊነቱን በሥራው ሊረዱት ከሚችሉ ሰባ ሽማግሌዎች ጋር መካፈል ነበረበት (ዘጸ. 18)። 

ሸ. ከእግዚአብሔር የሆኑ መሪዎች በጸሎትና በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት ይኖራቸዋል። የእግዚአብሔርን ቃል በቅጽበት ይሰማሉ፤ ሙሉ በሙሉም ይታዘዛሉ። በኦሪት ዘጸአት ውስጥ፥ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት ሳይቀር በተደጋጋሚ ይገናኝ እንደነበር እናነባለን። በሙሴና በአመራሩ ውስጥ የምናየው የኃይል ምንጭ ይህ ነበር (ዘጸ. 33፡7)።

እነዚህ ከኦሪት ዘጸአት ውስጥ ስለመሪነት ከምናገኛቸው በርካታ መመሪያዎች ጥቂቶቹ ናቸው። የቤተ ክርስቲያን መሪ ከሆንክ ኦሪት ዘጸአትን በሙሉ በጥንቃቄ በማንበብ እግዚአብሔር ሙሴን ለመሪነት እንዴት እንዳዘጋጀውና እርሱም የተዋጣለት የእግዚአብሔር ሕዝብ መሪ እንዴት እንደሆነ መመልከት ጠቃሚ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከላይ የጠቀስናቸው የመሪነት መመሪያዎች ዛሬም ላሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በጣም ጠቃሚ የሆኑት ለምንድን ነው? ለ) ከእነዚህ መመሪያዎች መካከል ብዙ ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን ያልተጠቀሱትና ያልተገለጹት የትኞቹ ናቸው? ለምን? ሐ) ከእነዚህ መመሪያዎች መካከል ብዙ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ሥራ ላይ ያልዋሉትስ የትኞቹ ናቸው? ለምን? መ) ከምታውቃቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መካከል ከሁሉ ይሻላል የምትለውን ሰው አስብ። በአመራሩ ከእነዚህ መመሪያዎች ውስጥ በምን ያህሉ ይጠቀማል? 

 1. የእግዚአብሔር ሕዝብ ባሕርይ፡- በተለይ በኦሪት ዘጸአት ውስጥ ከምናገኘው የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ፥ ዛሬም ያለው የእግዚአብሔር ሕዝብ ባሕሪያዊ ዝንባሌ ምን እንደሆነ ለማየት እንችላለን። የእስራኤልን ሕዝብ እግዚአብሔር ያዳናቸው እጅግ በሚያስደንቅ መንገድ ነበር። የእግዚአብሔርን ኃይል ሲያድናቸው አይተዋል። ከግብፃውያን እጅ በታደጋቸው ጊዜ እግዚአብሔርን በማምለክ ሐሴት አድርገዋል። ለእግዚአብሔር መገናኛ ድንኳን መሥሪያ የሚያስፈልገውን ነገር እንዲሰጡ በጠየቃቸው ጊዜ፥ ሙሴ በቃ አቁሙ እስኪል ድረስ በከፍተኛ ልግሥና ሰጥተዋል (ዘጸ. 35፡20-29፤ 36፡37)፤ ዳሩ ግን ልክ እንደ እኛ እስራኤላውያን ብዙ ጊዜ በኃጢአት ይወድቁ ነበር። በእግዚአብሔርና በመሪዎቹ ላይ ያጉረመርሙና ያማርሩ ነበር (ዘጸ. 16፡2-3)። እምነታቸው በጣም ደካማ ስለነበር፥ ነገሮች በማይስተካከሉበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ፊታቸውን ይመልሱ ወይም እግዚአብሔርን ይጠራጠሩ ነበር። የእግዚአብሔርን ክብር ያዩ ቢሆንም፥ ወደ ኃጢአት ያዘነበሉ ነበሩ። ከእግዚአብሔር ዞር ብለው ጣዖትን ያመልኩና ያመነዝሩ ነበር (ዘጸ. 32)። የተሻለ ሕይወት ይሰጠናል ብለው የሚያስቡት ዓለም ባርነት ቢሆንም እንኳ ያለማቋረጥ ወደዚያ ለመመለስ ይፈልጉ ነበር። ልክ በአብርሃም ውስጥ የኃጢአት ባሕርይ እንደታየ ሁሉ ያው ባሕርይ ወደ ልጆቹ ሁሉ ተላለፈ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ የኃጢአት ዝንባሌ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የሚታየው እንዴት ነው? ለ) የእግዚአብሔር ሰዎች እንደዚህ የሆኑት ለምን ይመስልሃል? ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደመሆናችሁ መጠን አባሎቻችሁ ኃጢአትን ድል አድርገው ይኖሩ ዘንድ ልታደርጉ የምትችሉት ነገር ምንድን ነው? 

 1. በኦሪት ዘጸአት ውስጥ ወደ ክርስቶስ የሚያመለክቱ በርካታ ነገሮች አሉ።

ሀ. ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ከባርነት ነፃ ያወጣ በመሆኑ፥ ከኃጢአት ባርነት ነፃ አውጥቶ የሚመራን የክርስቶስ ምሳሌ ነው (ሮሜ 6፡6፥17-18)። 

ለ. የፋሲካ በዓል የእግዚአብሔር ሕዝብ ከግብፅ ባርነት ነፃ የወጡበት በዓል እንደሆነ ሁሉ፥ ክርስቶስም ከኃጢአት ባርነት ነፃ ስላደረገን ፋሲካችን እርሱ ነው። ሞትን እንዳንሞት ደሙን ያፈሰሰልን የፋሲካ በግ ነው (1ኛ ቆሮ. 5፡7)። 

ሐ. የሕዝቡን የሥጋዊ ምግብ ፍላጎት ለማርካት እግዚአብሔር በምድረ በዳ መናን እንደሰጣቸው፥ ክርስቶስም የሰዎችን መንፈሳዊ መሻት ሁሉ የሚያሟላ የሕይወት እንጀራ ነው (ዮሐ. 6፡35፥ 48)።

መ. እግዚአብሔር ከዓለት ውስጥ ለሕዝቡ ውኃን እንደሰጠ፥ ኢየሱስ የሕይወት ውኃ ነው። ውኃ የሚሰጥ ዓለት ነው (1ኛ ቆሮ. 10፡2-4)።

ሠ. የመገናኛው ድንኳንና የአምልኮ ሥርዓቱ በርካታ የክርስቶስ ተምሳሌቶችን ያመለክታሉ። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ስለሚገኙ የተለያዩ የክርስቶስ ተምሳሌቶች ዝርዝር ከዛሬው ትምህርት ተመልከት።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ዘጸአት 19-24

ምናልባት ከእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ከሁሉም ላቅ ያለ ስፍራ ሊሰጠው የሚገባው ሕዝቡ በሲና ተራራ የቆዩበት የአንድ ዓመት ጊዜ ነው። እግዚአብሔር ራሱን በታላቅ ክብር ለሕዝቡ የገለጠው በዚያ ነበር። እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ግንኙነት የሚያደርግበትን የሥነ-ምግባርና የመንፈሳዊ ሕይወት መሠረት የሰጣቸው በዚያ ነበር። በእግዚአብሔር ሕዝብና በዓለም ሕዝብ መካከል የሚገኙ ዋና ዋና ልዩነቶች የተገለጡት በዚያ ነበር። ክርስቲያኖች ለሆንን ሁሉ ከእነዚህ መመሪያዎች አብዛኛዎቹ ዛሬም የሚሠሩ ናቸው። እኛም ለእግዚአብሔር የተለየን ሕዝብ መሆን አለብን። በዙሪያችን ካሉ ሕዝቦች ሁሉ የተለየ ኑሮ መኖር አለብን።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸአት 19፡3-6 አንብብ። ሀ) ስለ እስራኤል ሕዝብና ስለ ዓላማቸው በእነዚህ ጥቅሶች የተጠቀሱ የተለያዩ ነገሮችን ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ስለነበረው ግንኙነት ምን ልንማር እንችላለን? ሐ) ለእግዚአብሔር ሊኖራቸው የሚገባው ምላሽ ምን መሆን ነበረበት? መ) እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በሚመለከት የተናገረውን ነገር በአዲስ ኪዳን ስለ ቤተ ክርስቲያን ከተነገረው ጋር አወዳድር። እኛ በዚህ አንፃር ከእስራኤላውያን ጋር የምንመሳሰልባቸው ወይም የምንለያይባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? (1ኛ ጴጥ. 2፡9 ተመልከት)።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 19-24 ተመልከት። ሀ) እግዚአብሔር ተፈጥሮውንና ኃይሉን ለእስራኤል ሕዝብ የገለጠባቸውን የተለያዩ መንገዶች ዘርዝር። ለ) የእግዚአብሔር ቅዱስነትና እርሱ ከሕዝቡ የሚፈልገው ቅድስና በእነዚህ ቁጥሮች የታየው እንዴት ነው? ሐ) ዓሥርቱን ትእዛዛት ዘርዝር። መ) እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ትእዛዛት ለመሰሎቻቸው ያለባቸውን ኃላፊነት የሚያሳዩት እንዴት ነው?

እግዚአብሔር ከሕዝቡ (ከእስራኤል) ጋር በሲና ተራራ ያደረገው ግንኙነት፥ በሁሉም ዕድሜ ያሉ የእግዚአብሔር ሰዎች ከእርሱ ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባ ግንኙነት መሠረት የተጣለበት ነው። በርካታ ሕግጋትና ሃይማኖታዊ ልምምዶች ሊለወጡ ይችላሉ። ዋናው መመሪያ ግን አሁንም ይሠራል። ዘጸአት 19-24 የሲና ተራራ ቃል ኪዳን የተመሠረተበት ነው። በእነዚህ ምዕራፎች በእርሱና በሕዝቡ (በእስራኤል) መካከል ልዩ የሆነው ግንኙነት እንዲቀጥል ከእስራኤል ሕዝብ የሚጠበቁትን የቃል ኪዳኑን ግዴታዎች እግዚአብሔር ገልጧል። በሲና ተራራ ስለተገባው ቃል ኪዳን የሚከተሉትን ነገሮች ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡-

 1. በምንም ቅድመ ሁኔታ ላይ ሳይመሠረት እግዚአብሔር ከአብርሃምና ከዳዊት ጋር ከገባላቸው ሌሎች በርካታ ቃል ኪዳኖች በተቃራኒ በሲና ተራራ የተደረገው ቃል ኪዳን በቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ነው። ማለትም ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነው በረከትና የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል እንዲፈጸም እስራኤላውያን በቃል ኪዳኑ ውስጥ ለተጠቀሱት ትእዛዛት ታዛዦች መሆን ነበረባቸው። እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዳዊት በሰጣቸው ሌሉች ቃል ኪዳኖች፥ እንዲሁም በአዲሱ ቃል ኪዳን (ኤር. 31፡31) በመታዘዝ ቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር። የተስፋው ፍጻሜ የተመሠረተው ሰው በሚሰጠው ምላሽ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ተስፋ ላይ ብቻ ነበር።
 2. በሲና ተራራ የተሰጠው ቃል ኪዳን በዚያን ጊዜ በነበረው ባሕል ላይ የተመሠረተ ነበር። «የሱዜሪያን-ቫዛል» ቃል ኪዳን ተብሎ ተሰይሟል። እንዲህ ዓይነቱ ቃል ኪዳን በቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ነበር። ይኸውም በገዢ ንጉሥና በእርሱ አገዛዝ ሥር ከወደቁት ሌሎች ነገሥታት መካከል ከአንዱ ጋር የሚደረግ ቃል ኪዳን ዓይነት ነበር። በእንደዚህ ዓይነቱ ቃል ኪዳን ገዥው ንጉሥ በሥሩ ባለው ንጉሥ ላይ ፍጹም የሆነ መብትና ሥልጣን እንዳለው ይናገራል። በሥሩ ካለው ንጉሥ ፍጹም ታማኝነትና አገልግሎት ይጠብቃል። ይህ ንጉሥ ታማኝና ታዛዥ ከሆነ ከጠላቶቹ ሁሉ ሊታደገው ገዥው ንጉሥ ቃል ይገባለታል። ልክ እንደዚሁ፥ እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ላይ ፍጹም ንጉሥ ነበር፤ ስለዚህ እስራኤላውያን የሚጠብቁትን ሕግ ሰጣቸው። እነርሱ ለእርሱ ታማኞችና ታዛዦች መሆን ነበረባቸው። ለታማኝነታቸውና ለታዛዥነታቸው እግዚአብሔር ሊባርካቸውና ሊጠብቃቸው ቃል ገባ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ነገር ዛሬ እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ካለን ግንኙነት ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) እንዴትስ ይለያያል?

 1. በሲና ተራራ የተገባው ቃል ኪዳን በደም መፍሰስ ጸንቶአል (ዘጸ. 24፡3-8 ተመልከት)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ማር. 14፡24 ተመልከት። የአዲስ ኪዳን አጀማመር ከብሉይ ኪዳን አጀማመር ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ከዘጸ. 19-24 ባለው ጥናትህ ውስጥ የሚከትሉትን 6 ነገሮች ልብ ማለት ጠቃሚ ነው፡፡

 1. እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ቃል ኪዳንን ከመስጠቱ በፊት ኃይሉንና ታላቅነቱን ገለጠ። ይህ የእግዚአብሔር ኃይልና ቅድስና (መለየት) በተለያዩ ብዙ መንገዶች ይታያል። ማንም ሰው ወደተቀደሰው ተራራ እንዳይቀርብ ወይም እንዳይነካው በሚለው ትእዛዝ ውስጥ ይታያል (ዘጸ. 19፡12-13)። እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው በተሰጠው ጥብቅ ትእዛዝ ውስጥ ትኩረት ተሰጥቶታል፤ (ዘጸ. 19፡10-11)። እግዚአብሔር እጅግ ታላቅ የሆነው ኃይሉን በሚገልጥ ከተራራው ላይ በተገለጠ ነጎድጓድ፥ መብረቅ፥ ከባድ ደመና፥ እጅግ በሚያስተጋባ የቀንደ መለከት ድምፅ፥ የእሳትና የመሬት መንቀጥቀጥ ወዘተ. አሳይቷል (ዘጸ. 19፡ 16-19)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳን ከመግባቱ በፊት ክብሩንና ኃይሉን የገለጠላቸው ለምን ይመስልሃል? ለ) እግዚአብሔር ዛሬስ ኃይሉን የሚያሳየው እንዴት ነው? ሐ) ዛሬ የእግዚአብሔርን ኃይልና ታላቅነት መረዳታችን አምልኮአችንን እንዴት ይለውጠዋል? 

በጊዜያችን ካሉት ችግሮች አንዱ፥ ክርስቲያኖች ስለ እግዚአብሔር ኃይልና ቅድስና ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ መሆን ነው። ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን አይፈሩም። የእግዚአብሔርን ኃይልና ክብር ይበልጥ በተረዳን ቁጥር፥ የሚገባውን ያህል ልናመልከውና ልናከብረው እንችላለን። በመከራና በስደት ውስጥ ሳለን እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ ያለውን ኃይልና ሥልጣን ደግሞም የበላይ ተቆጣጣሪነት ስናስታውስ በእግዚአብሔር ላይ ለመታመን ብርታት እናገኛለን። ለእግዚአብሔር ያለን ፍርሃት ሁልጊዜ እርሱ ለእያንዳንዳችን ካለው ጥልቅ ፍቅር ጋር መስተካከል አለበት። ይህ ፍቅር እግዚአብሔር «አባ አባት» (ሮሜ 8:15) ብለን የምንጠራበትን ድፍረት ይሰጠናል። አምልኮአችን ፍቅርና ፍርሃት ደግሞም አክብሮትና ቅርበት የሚታይበት መሆን አለበት።

 1. እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን የማድረጉ ዓላማ እነርሱን ለራሱ የተለየ ርስት፥ የተለየ ሕዝብ፥ የንጉሥ ካህናት መንግሥትና የተቀደሰ ሕዝብ ለማድረግ ነበር (ዘጸ. 19፡5-6)። በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ዓላማ አንድ የተለየን ሕዝብ መምረጥ ነበር። በእስራኤላውያን ማንነት በኩል ምንም የተለየ ነገር አልነበረም። በቁጥር ብዙዎች ወይም ኃያላን የተማሩ ወይም የሠለጠኑ አልነበሩም። የተለዩ ወይም ልዩ ያደረጋቸው እግዚአብሔር በምሕረቱ ስለመረጣቸው ብቻ ነው። ስለዚህ የተለዩ ነበሩ። 

ዛሬ እግዚአብሔር ሰዎችን የሚመርጠው ከተለየ የዘር ሐረግ ስለተገኙ አይደለም። ይልቁንም እርሱ ወንዶችንና ሴቶችን በዓለም ላይ ከሚገኙ ሕዝቦች ሁሉ የተለየ ዓይነት ሕዝብ ወይም ዘር እንዲሆኑለት ይመርጣል። ያ ሕዝብ ቤተ ክርስቲያን ናት። የዚህ ሕዝብ አካል የመሆን መመዘኛ እንደ ብሉይ ኪዳን ዘመን በሥጋ መወለድ አይደለም። ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኝ መንፈሳዊ ልደት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ እውነታ በተለያዩ ነገዶችና ጎሣዎች መካከል ያለውን እኔ ከሌላው እሻላለሁ የሚለውን አዝማሚያ እንዴት ያስወግደዋል?

እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ የመረጠበት ምክንያት በሁለት ሐረጎች ተገልጾአል። በመጀመሪያ፥ «የንጉሥ ካህናት» እንዲሆኑ ነበር። ካህን መካከለኛ ነው። እግዚአብሔርንና ሰውን ወደ አንድነት በማምጣት ተግባር ውስጥ ለእግዚአብሔር ይሠራል፤ ስለዚህ እስራኤል፡ የካህናት ሕዝብ እንደመሆንዋ መጠን ልትፈጽማቸው የሚገባት ሁለት ተግባራት ነበሩዋት። 1) እግዚአብሔርን ማገልገል ነበረባቸው። 2) አሕዛብን በሙሉ ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብና ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ለማድረግ መሣሪያ መሆን ነበረባቸው (ኢሳ. 49፡6)።

ሁለተኛው ሐረግ እስራኤል «ቅዱስ ሕዝብ» መሆን እንዳለባት ይናገራል። ይህም ማለት ሕዝብዋ ከአሕዛብ የተለየ ኑሮ መኖር ነበረባቸው ማለት ነው። ከዘጸአት-ዘዳግም ያሉት አብዛኛዎቹ ትእዛዛት እስራኤል ቅድስት መሆን እንዳለባትና የተቀደሰ ሕይወት መኖር እንደሚጠበቅባት በመግለጥ ይህን እውነት አንፀባርቀዋል።

 1. ከእስራኤል ጋር የተደረገው ቃል ኪዳን የተመሠረተው በዓሥርቱ ትእዛዛት ላይ ነበር። እነርሱም እግዚአብሔር ራሱ የጻፋቸው ስለሆነ (ዘጸ. 20፡22) ዋና ወይም መሠረታዊ የቃል ኪዳን ሕግጋት ነበሩ። እነዚህ ትእዛዛት የመጡት ከሰማይ እንጂ ከሲና ተራራ አልነበረም። የእግዚአብሔርን ዓለም አቀፋዊ ሕግጋት ስለሚያሳዩ፥ በየዘመኑ በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ መጠበቅ አለባቸው።

ዓሥርቱ ትእዛዛት በሁለት ክፍሎች ተከፍለዋል። እነርሱም፡-

 1. አራቱ ትእዛዛት ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖረው በሚገባ ግንኙነት ላይ ያተኩራሉ። 

ሀ. «ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ።» እስራኤላውያን በዚያን ጊዜ በነበራቸው እውቀት እውነተኛው አምላክ አንድ ብቻ እንደሆነና ሌሉቹ ጣዖታት እንጂ አምላክ እንዳልሆኑ አያውቁም ነበር። እግዚአብሔር ግን የመጀመሪያና ፍጹም የሆነ ታማኝነት ፈለገ። እርሱን ብቻ ማክበርና መፍራት ነበረባቸው። አይሁድ እርሱን ብቻ ማምለክ ተገቢያቸው ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬ ለእኛ እንደ «አማልክት» ሊሆኑብን የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ለ. «የተቀረጸ ምስል ለአንተ አታድርግ።» ይህ ትእዛዝ ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሌሎች አማልክት ማንኛውንም ዓይነት ቅርፅ ወይም ምስል ማድረግን ይከለክላል። ዛፎችን ማምለክ፥ ወይም እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል እነርሱ በሚያስቡት መንገድ ቅርፁን ወይም ምስሉን ማበጀት አይገባቸውም ነበር። 

ሐ. «የእግዚእብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ።» ለእግዚአብሔር ክብርን የመስጠት አንዱ ክፍል ስሙን ማክበር እንደሆነ ተመልክተናል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ስም በየጊዜው እንደፈለግን የምንናገረው ወይም የምንጠራው መሆን የለበትም። ይህ ትእዛዝ ብዙ ጊዜ በሁለት መንገድ ይጣሳል፡- በመጀመሪያ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች የእግዚአብሔርን ወይም የኢየሱስን ስም ለእርግማን ዓላማ መጠቀማቸው ነው። በሁለተኛ ደረጃ ክርስቲያኖች የሆኑ ሳይቀሩ፥ ምንም ሳያስቡት ወይም ትርጉም በማይሰጥ መልኩ የእግዚአብሔርን ስም መጠቀማቸው ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ስም ያለአግባብ መጠቀማቸውን እንዴት አየኸው? ለ) ሰዎች የእግዚአብሔርን ወይም የኢየሱስ ክርስቶስን ስም እንዲያከብሩ ለማስተማር ቤተ ክርስቲያንህ ምን እያደረገች ነው?

መ. «የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ።» በብሉይ ኪዳን፥ እግዚአብሔር የሳምንቱን የመጨረሻ ቀን፥ ማለት ቅዳሜን ለእረፍትና ለአምልኮ ለየው። በአዲስ ኪዳን ክርስቶስ ከሞት የተነሣበትን ቀን ለማክበር፥ ክርስቲያኖች የአምልኮን ቀን ወደ እሑድ ለወጡት። ክርስቲያኖች ከዓሥርቱ ትእዛዛት መካከል እንዳለ ቃል በቃል ተቀብለው የማይታዘዙት ብቸኛ ትእዛዝ ይኸኛው ነው (ቆላ. 2፡16-17)፤ ነገር ግን የዚህ ትእዛዝ መንፈስ መጠበቅ አለበት። ለማረፍና እግዚአብሔርን ለማክበር በሳምንት አንድ ቀን ለጌታ መለየት አለብን። በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች ይህ ቀን እሑድ እንዲሆን መርጠዋል። በኦሪት ዘጸአትና ዘሌዋውያን የሚገኙ በርካታ ትእዛዛት አይሁድ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸና እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንዳለባቸው የሚናገሩ ናቸው። እነርሱም ይህንኑ መሠረት አጠናከሩት። 

 1. ስድስቱ ትእዛዛት ሰዎች ከሌሉች ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። የሚቀጥሉት ስድስት ትእዛዛት እርስ በርሳችን፥ በተለይም ደግሞ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል ከሆኑት ሰዎች ጋር ሊኖረን ስለሚገባ ግንኙነት ይናገራሉ።

ሠ. «አባትህንና እናትህን አክብር።» እግዚአብሔር ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩ፥ ለወላጆቻቸው እንዲጠነቀቁና፥ እንዲታዘዙ ሕዝቡን አዘዘ። ይህን ካላደረጉ በረከትን እንደማያገኙ ነገራቸው። እግዚአብሔር ለዚህ ትእዛዝ ምንም ቅድመ ሁኔታ አላኖረም። ወላጆቻችንን ማክበር ያለብን ቸርና መልካም ሰዎች ሲሆኑ ብቻ አይደለም። የተማሩ ስለሆኑ ወይም ገንዘብ ስለሚሰጡንም ወዘተ. አይደለም። ሰዎች ወላጆቻቸውን ላለመታዘዝ የሚችሉበት አንድ ወቅት ብቻ አለ። ይኸውም ወላጆቻቸው እግዚአብሔር በግልጥ አታድርግ ያለውን እንዲያደርጉ፥ ወይም አድርግ ያለውን እንዳያደርጉ ሲጠይቁአቸው ብቻ ነው። በዚህ ጊዜ ከወላጆቻቸው ይልቅ ለእግዚአብሔር መታዘዝ አለባቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ በዚህ ዘመን ብዙ ወጣቶች፥ ክርስቲያኖችም ሳይቀሩ ይህንን ትእዛዝ የማይከተሉት እንዴት ነው? 

ረ. «አትግደል።» ይህ ማለት ጨርሶ መግደል የለብንም ማለት አይደለም። እግዚአብሔር ይህንን የእርሱን ትእዛዝ በግድ የለሽነት የሚጥሱትን፥ በተለይ ደግሞ ሆን ብለው የሰዎችን ሕይወት የሚያጠፉትን ሰዎች በሞት እንዲቀጡ ለመንግሥታት መብት ሰጥቶአቸዋል (ሮሜ 13፡4 ተመልከት)። አንዳንዶች እንደሚያስተምሩት ይህ ሕግ ወደ ጦርነት መሄድን ጨርሶ የሚከለክል አይደለም፤ ይልቁንም ሕይወትን በግዴለሽነት ስለማጥፋት የሚናገር እንጂ።

ሲ. «አታመንዝር።» ይህ ትእዛዝ ሁለት ዓይነት ኃጢአቶችን ያጠቃልላል። የመጀመሪያው፥ በባልና ሚስት መካከል በግብረ ሥጋ ግንኙነት ረገድ ታማኝ ያለመሆን ኃጢአት ነው። ባልየውም ሆነ ሚስትየዋ ከሌላ ከማንኛውም ሰዎች ጋር የግብረ ሥጋ ኅብረት እንዲኖራቸው አልተፈቀደላቸውም። ሁለተኛው ደግሞ፥ ያላገቡ ሰዎች የሚፈጽሙት ማንኛውም የግብረ ሥጋ ግንኙነት ተግባር ነው። እግዚአብሔር እንዳዘዘው ግብረ ሥጋ መፈጸም ያለበት በጋብቻ በተጣመሩ ባልና ሚስት መካከል ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል በርካታ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ኃጢአት የሚከሰተው ለምንድ ነው? ለ) አንዳንድ ሰዎች ማመንዘር ከወንድ ይልቅ ለሴት የከፋ እንደሆነ የሚያስተምሩት ለምንድን ነው? ትክክል ናቸውን? መልስህን አብራራ። ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ «አታመንዝር» የሚለውን ሕግ እንዲያከብሩ ያገቡ የትዳር ጓደኛሞችንም ሆነ ያላገቡትን አባላትዋን እንዴት ማበረታታት ትችላለች?

ሸ. «አትስረቅ።» ይህ ማለት ስሕተት መሆኑን እያወቅህ፥ የራስህ ያልሆነውን ነገር ከሰው ላይ መውሰድ ለራስህ ማድረግ ስህተት ነው። ይህም ገንዘብ ወይም ቁሳቁሳዊ ነገር መሆን ይችላል። ወይም በትምህርት ቤት ከሌላ ሰው ወረቀት ላይ የፈተና መልስ መቅዳት ወይም መኮረጅ ሊሆን ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬ ሰዎች (ክርስቲያኖች ሳይቀሩ) የሚሰርቁባቸውን የተለያዩ መንገዶች ግለጽ።

ቀ. «በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።» ይህ ትእዛዝ ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን ያንፀባርቃል። የመጀመሪያው በዳኛ ፊት ወይም ለአንድ ነገር ምስክርነት መስጠት በሚያስፈልግበት ሰዓት አንዳችም ነገር ሳንቀንስና ሳንጨምር እውነቱን በሙሉ እንዳለ የመናገር ኃላፊነት ነው። እውነትን መሸሽግ ወይም እውነትን በከፊል ብቻ መናገር ውሸትና ስሕተት ነው። ሁለተኛ ስላደረግነውና ስላየነው ነገር እውነትን ብቻ የመናገር ኃላፊነት አለብን። ይህ ትእዛዝ ሐሜትንና የመሳሰሉትን ይቃወማል። 

በ. «የባልንጀራህን ቤት አትመኝ …።» መመኘት የብዙ ኃጢአት ምንጭ እንደሆነ ክርስቶስም፥ ጳውሎስም ተናግረዋል (ማቴ. 5፡20፤ ሮሜ 7፡7)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ማቴ. 22፡34-40 ሀ) ኢየሱስ ታላላቅ ያላቸው ሁለቱ ትእዛዛት ምንድን ናቸው? ለ) እነዚህ ሁለት ትእዛዛት ዓሥርቱን ትእዛዛት የሚጠቀልሉበት እንዴት ነው?

በብሉይ ኪዳን ከሚገኙ ሌሎች ሕጎች አብዛኛዎቹ እግዚአብሔርን እናከብር ዘንድ ከሚፈልጋቸው ከሁላቱ ኅብረቶች በአንዱ ላይ ማተኮር አለባቸው። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔርን የሚያከብሩና እርሱንም ስለማምለክ የሚናገሩ ሕጎች አሉ። ለምሳሌ፡- እስራኤላውያን እንዴት ማምለክ እንዳለባቸው (ዘጸ. 20፡22-26) እና ሊጠብቁዋቸው ስለሚገባቸው ሃይማኖታዊ በዓላት (ዘጸ. 23፡14-19) የተነገሩ ሕግጋት አሉ።

ሁለተኛ፡ እስራኤላውያን ከጎረቤቶቻቸው ጋር እንዴት መኖር እንዳለባቸው በግልጽ የሚናገሩ ሕግጋት አሉ። ምናልባት እነዚህን ሕግጋት ሁሉ ዛሬ መጠበቅ አስፈላጊ ባይሆንም እንኳ፥ እነርሱን በሚመለከት እርስ በርስ ሊኖረን ስለሚገባ ግንኙነት የምናወጣቸው በርካታ መመሪያዎች አሉ። አይሁድ አገልጋዮቻቸው የሆኑትን ሌሉች አይሁድ እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የሚናገሩ ሕግጋት ነበሩ (ዘጸ. 21፡2-11)። አንድ ሰው ወይም እንስሳ በሌላ ሰው ወይም እንስሳ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ጉዳት ሲደርስበት ሁኔታውን እንዴት መያዝ እንደሚገባ የሚናገሩ ሕግጋት ነበሩ (ዘጸ. 21፡12-36)። አንድ ሰው ንብረት ሲሰርቅ፥ ወይም ሲያበላሽ ሁኔታውን እንዴት መያዝ እንደሚያስፈልግ የሚናገሩ ሕግጋትም ነበሩ (ዘጸ. 22፡1-15)። በጋብቻ ውስጥ አለመተማመን በሚፈጠርበት ጊዜ ሁኔታውን እንዴት መያዝ እንደሚገባ የሚናገሩ ሕግጋት አሉ። ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር አሳብ ሰዎች ሁሉ በሰላምና በፍትሕ ተባብረው እንዲኖሩ ነበር (ዘጸ. 23፡1-9)። 

 1. እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግጋት ሰዎች ለሚሳተፉባቸው የተለያዩ ግንኙነቶች የሚጠቅሙ ትእዛዛት የሚገኙባቸው ናቸው። ከእነዚህ ሕጎች አብዛኛዎቹ በቀጥታ ተግባራዊ መሆን አለባቸው ማለት አይደለም። ነገር ግን እስራኤላውያን እርስ በርስ እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚያሳዩ ምሳሌዎች ነበሩ። የተቀደሱ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደመሆናቸው መጠን በዚህ በክፋት በተሞላ ዓለም ውስጥ እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚያሳዩ መመሪያዎች ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው። 

እነዚህን ሕጎች በምናጠናበት ጊዜ፥ ዛሬ ከሕይወታችን ጋር እንዴት እንደምናዛምዳቸው በጣም መጠንቀቅ አለብን። በመጀመሪያ ቋሚና ጊዜያዊ የሆኑ ሕግጋትን ለይተን ማወቅ አለብን፤ (ዘሌዋ. 17፤ ዘዳ. 12፡20-24 የጊዜያዊ ሕጎች ምሳሌዎች ናቸው)። አንድ ሕግ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ መሆኑን ለመለየት በጣም ጥሩው መንገድ፥ በአዲስ ኪዳን እንደ ሕጉ እንደገና ተደግሞ እንደ ሆነና እንዳልሆነ ማየት ነው። በሁለተኛ ደረጃ፥ ደግሞ እግዚአብሔር ሕጉን በሚሰጥበት ጊዜ የነበረውን ዓላማ ወይም ምክንያት ማየት ነው። እነዚህ የተለያዩ ሕጎች በተናጠል በዚህ ዘመን የማይሠሩ ቢሆኑም እንኳ በውስጣቸው ያለው መመሪያ ግን አሁንም ዋጋ ያለው ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 23፡1-9 አንብብ። እነዚህን ሕግጋት በሁለት ከፋፍለህ ተመልከታቸው። ሀ) በመጀመሪያ፥ ዛሬም ልንጠብቃቸው የሚገባን ቋሚ የሆኑ ሕግጋት የትኞቹ ናቸው? ለ) ሁለተኛ፥ ጊዜያዊ የሆኑ በተናጠል ለአንድ ሁኔታ ብቻ የሚጠቅሙ ሕግጋት የትኞቹ ናቸው? ሐ) ከእነዚህ ሕግጋት የምናገኛቸው ዛሬ ለሕይወታችን የሚጠቅሙን መመሪያዎች የትኞቹ ናቸው? መ) ከእነዚህ ሕግጋት መካከል ዛሬ በክርስቲያኖች ላይ ችግር የሚፈጥሩ የትኞቹ ናቸው?

በዘጸ. 24 የእስራኤል ሕዝብ በቃል ኪዳኑ ቅድመ ሁኔታዎች ሁሉ እንዴት እንደተስማሙ ያሳያል። በስምምነታቸውና በፈሰሰው ደም ቃል ኪዳኑን አጸኑት።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ዘጸአት 13-18

አንድ ሰው የመንፈሳዊ ሕይወት ጉዞውን በመልካም ሁኔታ ጀመረ ማለት ያለማቋረጥ በእምነት ይጓዛል ማለት አይደለም። እግዚአብሔር አይሁዳውያንን ከግብፅ ባርነት በታላቅ ኃይል አወጣቸው። አይሁድ በታላቅ ደስታ ከምርኮኛነት ተላቀቁ፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ መጠራጠር፥ ማጉረምረም ማማረር ጀመሩ። ከዚህም አልፈው ወደ ግብፅ ለመመለስ ከጀሉ። መንፈሳዊ አረማመዳቸው ልክ እንደ እኛው የድልና የሽንፈት ጊዜያትን ያካተተ ነበር። የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ያሳለፉት ሕይወት በመንፈሳዊ ሕይወታችን ተጠንቅቀን እንድንኖር ለሁላችንም ማስጠንቀቂያ ሊሆን ይገባል። ተግባራችን እንደ እነርሱ እንዳይሆንና በአለማመን እንዳንወድቅ፥ ከስሕትታቸው መማር አለብን።

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ቆሮ. 10፡1-13 አንብብ። ከእስራኤላውያን የምድረ በዳ ኑሮ መማር እንዳለብን ጳውሎስ የሚናገረው ምንድን ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 13-18 አንብብ። ሀ) እስራኤላውያን ወደ ሲና ተራራ በሚጓዙበት ጊዜ የሠፈሩባቸውን ቦታዎች ሁሉ ዘርዝር። ለ) በእያንዳንዱ ስፍራ ስለተፈጸመው ነገር አጫጭር ገለጻ አድርግ። ሐ) ከዚህኛው የእስራኤላውያን ጉዞ የምትማራቸው መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር። መ) የአንተና የቤተ ክርስቲያንህ ሕይወት ከእስራኤላውያን ጉዞ ጋር የሚመሳሰልበትን ነገር ዘርዝር።

እስራኤላውያን ከግብፅ ወደ ሲና ተራራ ያደረጉት ጉዞ ሦስት ወር ገደማ ፈጀባቸው። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን እንዲህ በሚያስደንቅ ጅማሬ ከግብፅ ባርነት ካወጣቸው በኋላ፥ ፍጹም በሆን እምነትና መታዘዝ ይጓዛሉ ብለን መጠበቃችን አይቀርም። በእስራኤላውያን ሕይወት የተፈጸመው ግን ይህ አልነበረም። ከግብፅ ወደ ሲና ያደረጉት ጉዞ በጣም አስቸጋሪ ነበር። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በእግዚአብሔር ከመታመን ይልቅ እርሱን ወደማማረርና በእርሱም ላይ ወደ ማጉረምረም አዘነበሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ እኛ ክርስቲያኖችም ችግር በሚያጋጥመን ጊዜ የምናጉረመርመውና የምናማርረው እንዴት ነው? ለምን?

እስራኤላውያን ወደ ሲና ተራራ በሚጓዙበት ጊዜ ያለፉባቸው ቦታዎች ከዚህ እንደሚከተለው ተተንትነዋል። 

1) አብዛኛዎቹ እስራኤላውያን በግብፅ በነበሩበት ጊዜ ከኖሩበት ከራምሴ ተነሥተው ግብፅን ለመልቀቅ ወደ ተዘጋጁበት ወደ ሱኮት ሄዱ (ዘጸ. 12:37-13፡19)። በዚህ ስፍራ ሁለት ዋና ዋና ድርጊቶችን ፈጸሙ። በመጀመሪያ፥ በቂጣ በዓል ምን መደረግ እንዳለበት የወሰኑት በሱኮት ነበር። በሁለተኛ ደረጃ፥ የእስራኤልን በኵር ሁሉ ለእግዚአብሔር የመቀደስ ተግባር የተከናወነው በሱኮት ነበር (ዘጸ. 13:1-16)።

በኩራትን የመቀደስ ተግባር እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር አሥራትን ከሰጡባቸው መንገዶች አንዱ ነበር። እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ያስጀመረው መመሪያ በአይሁድ ዘንድ ከሰውም ሆነ ከእንስሳ ለእግዚአብሔር አሳልፎ የመስጠት ተግባር ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ ከምርታቸው ወይም ከእንስሶቻቸው መካከል ለእግዚአብሔር መስጠት ያለባቸው የመጀመሪያውን እንጂ የመጨረሻውን አልነበረም።

ስለ በኩር በተሰጠው ትምህርት ውስጥ የተካተቱት ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ። በቅድሚያ በኩር ስለሆኑት ሰዎች የተሰጠ ትምህርት እናገኛለን። ) የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ አንድ ሕዝብ እንደ መሆኑ መጠን በኩር ነበር። ይህም የሚያንፀባርቀው እግዚአብሔር ያዕቆብን ወይም እስራኤልን የተስፋው ልጅ የኪዳን ወራሽ አድርጎ በመምረጥ የበኩሩን ልጅ መብት እንደሰጠው ነው፤ ስለዚህ የያዕቆብ ልጆች የሆኑ እስራኤላውያን ሙሉ እንደ እግዚአብሔር ልዩ ልጅ ተቆጥረው የእርሱ በኩር ሆኑ (ዘጸ. 4፡22)።

2) ነገር ግን የበኩር ትምህርት የእስራኤላውያን የመጀመሪያ ልጆች የሆኑትንም ሁሉ የሚመለከት ነው። እያንዳንዱ በኩር ልጅ የእግዚአብሔር ነበረ። ምክንያቱም እግዚአብሔር የግብፃውያንን በኩር በመቅሠፍት ባጠፋ ጊዜ የእስራኤላውያንን በኩር ትቶ ነበር (ዘጸ. 12፡12-13)፤ ስለዚህ የበኩሩ ልጅ ወላጆች ገንዘብ ከፍለው ልጁን እንዲያስመልሱ ወይም «እንዲዋጁ» እግዚአብሔር ይፈልግ ነበር። ገንዘብ መከፈል ነበረባቸው (ዘኁል. 18፡15-16)።

በእስራኤላውያን በኩሮች ምትክ መላው የሌዊ ነገድ ለእግዚአብሔር ተሰጥቶ ነበር፤ (ዘኁል. 3፡41-5)። 

ሁለተኛ፥ የእንስሳትን በኩር እናገኛለን። እንስሳትን በሚመለከት ሁለት ዓይነት ሕግጋት ነበሩ።

ሀ. «ንጹሕ» እንስሳት የሚባሉና ለመሥዋዕትነት የተፈቀዱ እንስሳት ነበሩ። የተባዕት እንስሳ በኩር የእግዚአብሔር ስለሆነ መሥዋዕት ሆኖ በመሠዊያ ላይ ይቀርብና ይሰዋ ነበር። ሥጋውም ለካህናት ይሰጥ ነበር (ዘኍል. 18፡14-19)። 2) ለመሥዋዕት ይቀርቡ ዘንድ ያልተፈቀዱ «ንጹሐን ያልሆኑ» እንስሳትም ነበሩ። ንጹሕ ባልሆነው እንስሳ ምትክ እስራኤላውያን ጠቦት መስጠት ነበረባቸው። ጠቦቱንም በመሠዊያ ላይ አቅርቦ በመሠዋት ለእግዚአብሔር መስጠት ተገቢ ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ለእግዚአብሔር አሥራት በምንሰጥበት ጊዜ የሁሉን ነገር በኩር ለእግዚአብሔር መስጠት መልካም መመሪያ የሆነው ለምንድን ነው? ለ) በአሁኑ ጊዜ ብዙ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ከመተ ከአሥር እጅ (10%) በታች የሚሰጡት ለምንድን ነው? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች ከገንዘባቸውም ሆነ ከምርታቸው የተረፈውን ለእግዚአብሔር የሚሰጡት ለምንድ ነው? መ) ይህ መመሪያ ዛሬ አሥራትን ስለመክፈል የሚያስተምረን ነገር ምን ይመስልሃል? 

የውይይት ጥያቄ፥ ሉቃ. 2፡7፤ ሮሜ 8፡29፤ ቆላ. 1፡15፥ 18 አንብብ። ሀ) በዚህ ስፍራ ለክርስተስ የተሰጠው ማዕረግ ምንድን ነው? ለ) ይህ ማለት ምን ማለት ነው? 

ለ. ሕዝቡ ከሱኮት ወደ ኤታም አመሩ (ዘጸ. 13፡20-22)። ከሱኮት ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚወስዱ ሁለት የተለያዩ መንገዶች ነበሩ። አንደኛው በሜዲትራኒያን ባሕር አጠገብ በፍልስጥኤማውያን ምድር ወደ ሰሜን የሚወስደው ሲሆን፥ የተለመደ የንግድ መስመር ነበር። ይህ መንገድ አጭር ስለሆነ፥ እስራኤላውያን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከነዓን ይደርሱ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በዚህ መንገድ አልመራቸውም። ረጅምና አስቸጋሪ በሆነው ወደ ሲና በረሀ በሚወስደው መንገድ መራቸው። እግዚአብሔር ይህን ያደረገው ለምን እንደሆነ አናውቅም። ምናልባት በምድረ በዳው ልምምድና በሲና ተራራ ላይ ባሳለፉት ጊዜ የተመረጡ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደመሆናቸው መጠን እንዴት መኖር እንዳለባቸው ሊያስተምራችው የፈለገ ይመስላል። የጉዞው አስቸጋሪነት በእግዚአብሔር ላይ እንዲታመኑ ለማስተማር የታቀደ ነበረ።

የውይይት ጥያቄ፥ በእርሱ ላይ ያለህን እምነት ለማነፅ እግዚአብሔር በሕይወትህ የሚከሰቱ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዴት ይጠቀምባቸዋል?

በኤታም በጣም አስፈላጊ የሆነ አንድ ነገር ተፈጸመ። እግዚአብሔር ቀን በደመና ዓምድ ሌሊት ደግሞ በእሳት ዓምድ በመምራት ከእነርሱ ጋር መኖሩን አሳያቸው። በሚቀጥሉት 40 ዓመታት እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በምድረ በዳ የመራቸው የእርሱን መኖር በሚገልጹት በእነዚህ ሁለት ምልክቶች ነበር። በኋላም የእግዚአብሔር ክብር ደመና የማደሪያውን ድንኳንና ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። አይሁድ ይህን የእግዚአብሔር መኖር ደመና «የሽካይናህ ክብር» ብለው ይጠሩታል። 

3) ከኤታም ተነሥተው ወደ ፊሀሒሮት በመምጣት ቀይ ባሕርን ተሻገሩ (ዘጸ. 14፡1-15፡21)። ፊሀሒሮት የት እንደሆነ እርግጠኞች ሳንሆንም፥ በትልቅ የውኃ አካል ጠርዝ ላይ ያለ ስፍራ ነበር። እግዚአብሔር ውኃውን በከፈለላቸው ጊዜ እስራኤላውያን በትክክል የተሻገሩት የትኛውን የውኃ አካል እንደሆነ በማሰብ ምሁራን ብዙ ጊዜ መደነቅ ይዞአቸዋል። ያቋረጡት ባሕር መጠሪያ ስሙ «የሸምበቆ ባሕር» የሚል እንጂ ቀይ ባሕር አልነበረም። ያቋረጡት ያሁኑን ቀይ ባሕር ነው ማለት ትክክል አይመስልም። ብዙ ምሁራን እንደሚሉት እግዚአብሔር በተአምር ለሁለት ክፍሎች ያቋረጡት ውኃ በቀይ ባሕርና በሜዲትራኒያን ባሕር መካከል የነበረ አንድ ትልቅ ውኃማ አካል ነው።

እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የመጀመሪያውን ፈተና በዚህ ስፍራ ሰጣቸው። ከፊት ለፊታቸው ታላቅ ውኃ፥ ከኋላቸው ደግሞ የፈርዖን ሠራዊት ነበር። ከጥቂት ቀናት በፊት 10 መቅሠፍቶችን በግብፅ ላይ በማውረድ ከፈርዖን ብርቱ እጅ ባዳናቸው እግዚአብሔር ላይ ታምነው ይሆን? የለም፤ በእግዚአብሔር አላመኑም ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ውኃውን ለሁለት ከፈለው። እስራኤላውያን በደረቅ ምድር ሲሻገሩ፥ የግብፅ ሠራዊት ግን በውኃው ውስጥ ሰጥሞ ቀረ።

የውይይት ጥያቄ፥ በእግዚአብሔር ጠላቶችም ሆነ በሌሎች ችግሮች ልንሸነፍ የተቃረብን በሚመስለን ጊዜ እግዚአብሔርን ባለማመን ሊኖረን ስለሚችል ዝንባሌ ይህ ምን ያስተምረናል?

4) ከሸምበቆ ባሕር ወደ ማራ (ዘጸ. 15፡22-26)፡- በማራ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በሌላ ነገር ፈተናቸው። ይህም ፈተና የሚጠጡትን ውኃ እንደሚሰጣቸው በእግዚአብሔር ይታመኑ እንደሆነ ለመለየት የተደረገ ነበር። የነበረው ውኃ መራራ ስለ ነበር ሰው ሊጠጣው አይችልም ነበር፤ ስለዚህ ከግብፅ ባወጣቸው አምላክ ላይ በመደገፍ ወደ እርሱ በመጸለይ ፈንታ፥ በሙሴ ላይ ያጉረመርሙ ጀመር። ሙሴ በእግዚአብሔር የተመረጠ መሪ ስለነበር፥ ያጉረመረሙት በእግዚአብሔርም በሙሴም ላይ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወይም በክልል ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ላይ በምናጉረመርምበት ጊዜ ምን እያደረግን እንደሆነ ምን ያስተምረናል? ለ) በዚህ ረገድ ከእስራኤላውያን ጋር የምንመሳሰለው እንዴት ነው?

እግዚአብሔር በእኛ ላይ በኃላፊነትና በሥልጣን ባስቀመጣቸው ሰዎች ላይ በምናጉረመርምበት ጊዜ የሚሆነው ነገር ተመሳሳይ ነው። ያጉረመረምነው በእነርሱ ላይ ብቻ እንደሆነ ሊመስለን ይችላል፤ ዳሩ ግን የሚመሩት በእግዚአብሔር ተመርጠው ስለሆነ፥ የምናጉረመርመው በእግዚአብሔርም ላይ ጭምር ነው። እግዚአብሔር በጸጋው እንደገና ሙሴን በመጠቀም በተአምር ንጹሕ ውኃን ሰጣቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሕዝቡ በማራ ያሳለፉት ይህ ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ የማጉረምረማቸው ምሳሌ ተደርጎ ይታያል (መዝ. 95፡7-11፤ ዕብ. 3፡7-19)። 

5) ከማራ ወደ ኤሊም፥ ከዚያም ወደ ሲን ምድረበዳ መጡ (ዘጸ. 15፡27-16፡36)። ኤሊም ብዙ ውኃ ያለበት ስፍራ ነበር። ከዚያም የሲን በረሀ ተብሎ ወደሚጠራው ምድረ በዳ ሄዱ። አሁን እስራኤላውያን ግብፅን ከለቀቁ ልክ አንድ ወር ስለሆናቸው፥ በጉዞው መሰላቸት ጀምረው ነበር። የሚበሉትን ምግብ አጡ። ስለዚህ እንደገና በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ። ምቹ ነው ብለው ወደጠሩት ወደ ግብፅ ኑሮ መመለስም ተመኙ። ነፃ ሆኖ ከመራብ፥ ባሪያ ሆኖ መጥገብ ይሻለናል የሚሉ ይመስላሉ። አሁንም እግዚአብሔር እንደገና በምሕረቱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሰጣቸው። «የሰማይ እንጀራ»፥ «መናን» ሰጣቸው (ዘጸ. 16፡4)። የድርጭትንም ሥጋ ላከላቸው። «መና» ማለት በዕብራይስጥ «ይህ ምንድን ነው?» ማለት ነው። እንዲህ የተባለበት ምክንያት እግዚአብሔር በመጀመሪያ ለእስራኤላውያን እንደሰጣቸው ምንነቱን ስላላወቁ ነበር። እግዚአብሔር የፈቀደላቸው ለየዕለቱ የሚሆነውን መና እንዲሰበስቡ ብቻ ነበር። እስራኤላውያን ለዕለት እንጀራቸው በእርሱ እንዲታመኑ ማድረጉ ነበር (ማቴ. 6፡11)። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን አንድ ማድጋ ጎሞር ሙሉ መና ወስደው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ባለው ታቦት ሥር እንዲያስቀምጡ አዘዛቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዮሐ. 6፡32-51 አንብብ። ሀ) እነዚህ ጥቅሶች እውነተኛ «የሕይወት እንጀራ» የሚሉት ማንን ነው? ለ) ይህስ ለአንተ እውነትነቱ እንዴት ነው?

6) ከሲን ምድረ በዳ ወደ ራፍቃ፥ ከራፍቃ ወደ ኤሉስ፥ ከኤሉስም ተጉዘው በራፊዲም ሠፈሩ (ዘኁል. 33፡12-13፤ ዘጸ. 17-18) እስራኤላውያን ወደ ሲና ተራራ የሚወስደውን የደቡብ ጉዞአችውን ቀጠሉ። ወደ ራፊዲም በደረሱ ጊዜም ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ተፈጸሙ።

 1. ውኃ ስላልነበራቸው እንደገና በሙሴ ላይ አጉረመረሙ። ዓለቱን በበትሩ እንዲመታ እግዚአብሔር ሙሴን አዘዘው። በመታውም ጊዜ ከዓለቱ ውኃ ወጣ። በመጽሐፍ ቅዱስ ይህ ድርጊት የእግዚአብሔር ሕዝብ እግዚአብሔርን የተፈታተነበት ምሳሌ ሆኖ ቀርቧል። እግዚአብሔር እንደሚሰጣቸው በማመን እርሱን ከመጠበቅ ይልቅ «እግዚአብሔር በመካከላችን ነውን ወይስ አይደለም?» በማለት ፈተኑት (ዘጸ. 17፡7)። እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ ፍላጎታቸውን እንደሚያሟላላቸው ከመተማመን ይልቅ፥ በራሳቸው ጊዜ እግዚአብሔር እንዲያደርግላቸው ግፊት አደረጉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም እግዚአብሔርን በተመሳሳይ መንገድ እንዴት ልንፈታተነው እንችላለን? ለ) ይህም በእግዚአብሔር ላይ እምነት ማጣት መሆኑን የሚያሳየን ለምንድን ነው?

 1. እስራኤላውያን ከአማሌቃውያን ጋር ተዋግተው አሸነፏቸው። እግዚአብሔር በሙሴ የተዘረጉ እጆች ላይ ድል እንዲመሠርት ማድረጉ የሚያስደንቅ ነው። የሙሴ እጆች ወደ እግዚእብሔር ጸሎት በተዘረጉ ጊዜ እስራኤላውያን ያሸንፉ ነበር። እጆቹን ባወረደ ጊዜ ግን አማሌቃውያን ያሸንፉ ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ለጸሎት አስፈላጊነት እንዴት ጥሩ መግለጫ ይሆናል? 

 1. ዮቶር፥ የሙሴ አማት የእግዚአብሔርን ሕዝብ በመምራት ሥራ ውስጥ ይረዱት ዘንድ ሽማግሌዎችን ወይም የተለያየ ደረጃ ያላቸውን ሰዎች እንዲሾም ሙሴን መከረው። ሙሴ ሁሉንም ሰው ለመምራት ከሞከረበት ጊዜ ይልቅ፥ ይህን እንዳደረገ የእስራኤል ሕዝብ የበለጠ ስኬታማ በሆነ መንገድ ለመተዳደር ችሏል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ አሠራር ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው አመራር ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) ይህ አሠራር ቤተ ክርስቲያንህ እንዴት እንደሚደረግ ወይም እንደማይደረግ ምሳሌዎችን ስጥ።

7) ከራፊዲም ወደ ሲና ተራራ (ዘጸ. 19)፡- እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ከሦስት ወራት በኋላ ወደ ሲና ተራራ ደረሱ። በዚያ ስፍራም እግዚአብሔር ለእርሱ የተቀደሱ ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ እያዘጋጃቸው ለአንድ ዓመት ቆዩ። የቀሩት የኦሪት ዘጸአት፥ ዘሌዋውያንና ዘኁልቁ ምዕራፍ1-10 ታሪክ የተፈጸምው በብሉይ ኪዳን የኮሬብ ተራራ በተባለው በዚህ በሲና ተራራ ላይ ነው (ዘጸ. 33፡6)። 

የውይይት ጥያቄ፥ የእስራኤል ሕዝብ ወደ ሲና ተራራ ካደረገው ጉዞ ስለ ራሳችን የእምነት ጉዞ የምንማራቸው ጠቃሚ ትምህርቶች ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የእግዚአብሔር ሕዝብ ነጻነት (ዘጸ. 5-12) 

በዚያን ጊዜ ግብፅ በምድር ላይ ካሉ መንግሥታት ሁሉ በላይ የሆነ ኃያል መንግሥት ነበር። ነገር ግን የሰዎች ሁሉ ፈጣሪ ከሆነው ከእግዚአብሔር የሚበልጥ ታላቅነት ነበረውን? እነዚህ ምዕራፎች እግዚአብሔርን ወክሎ በሚናገረው በሙሴና በግብፅ መሪ በነበረው በፈርዖን መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ያመለክታሉ። ምናልባት ሙሴ ከዚህ የግብፅ ንጉሥ ጋር በቂ ትውውቅ ያለውና አብረው ያደጉም ሳይሆኑ አይቀሩም። (ማስታወሻ፡- ፈርዖን የሚለው ቃል የአንድ የግብፅ ንጉሥ ስም አይደለም። የግብፅ መሪ የሚጠራበት የሥልጣን ስም ነው። «ንጉሥ» ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው) በመጀመሪያ ፈርዖን ታላቅ ኃይል ነበረው። ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ እንዲለቅ ሲጠይቀው ፈርዖን እንዲህ ሲል መለሰ፡- «ቃሉን እሰማ ዘንድ፥ እስራኤልን እለቅቅ ዘንድ እግዚአብሔር ማን ነው? እግዚአብሔርን አላውቅም፥ እስራኤልንም ደግሞ አልለቅም» (ዘጸ. 5፡2)። ይህ ጥያቄ ከቀረበለት በኋላ ፈርዖን በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ቀንበርን ጨመረ።

ከዚያም እግዚአብሔር በግብፅ ላይ አሥር መቅሠፍቶችን ላከ። በአሥሩ መቅሠፍቶች ታሪክ ውስጥ የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-

ሀ. የግብፅ አስማተኞች ሊሠሩ የቻሉት ሙሴ ከሠራቸው ተአምራት ከፊሎቹን ብቻ ነበር። ሰይጣን ብዙ ኃይል ስላለው፥ ተአምራትን ማድረግ ይችላል። የሙሴ ተአምር፥ የግብፅ አስማተኞች በመጨረሻ ይህንን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው እስኪሉ ድረስ፥ ከእነርሱ ተአምር የሚበልጥ ነበር (ዘጸ. 8፡19 ተመልከት)። በመጀመሪያዎቹ ሁለት መቅሠፍቶች የግብፅ አስማተኞች የሙሴን ተአምራት አስመስለው አሳዩ፡ በሦስተኛው መቅሠፍት ላይ ግን ማስመሰል አልቻሉም። ከአራተኛው መቅሠፍት ጀምሮ ችግሩ የደረሰው በግብፃውያን ላይ ብቻ ነበር። እግዚአብሔር ስለጠበቃቸው በእስራኤላውያን ላይ የመቅሠፍቱ ችግር አይደርስም ነበር።

ለ. ፈርዖን ከእግዚአብሔር ዘንድ ተጨማሪ ፍርድን ያስከተለበትና በመጨረሻም በበኩር ልጁ ላይ ሞትን ያመጣው የልብ ድንዳኔ ቀስ በቀስ በሕይወቱ እየጨመረ ሄደ። መጽሐፍ ቅዱሳችን የሚናገረውን ነገር በትክክል ከተመለከትን፥ የሚከተሉትን ነገሮች እናገኛለን፡- 1) ፈርዖን በሕዝቡ ላይ የደረሱትን አምስት መቅሠፍቶች አስቀድሞ ቢመለከትም፥ ልቡን አደነደነ፤ (ዘጸ. 8:15፥32)። ፈርዖን እያወቀ እውነትን አልተቀበለም። 2) ከዚያም እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ የበለጠ አደነደነው (ዘጸ. 9፡12፤ 10:1፥ 27)። 

ከዚህ ታሪክ ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነ መንፈሳዊ እውነት ለማየት እንችላለን። እግዚአብሔር በመጀመሪያ የሰውን ልብ በማደንደን ፍርድን በሰው ሕይወት ላይ አያመጣም፤ ነገር ግን በንስሐ ለመመለስ ወይም እግዚአብሔርን ለመታዘዝ እምቢ በማለት ልቡን ማደንደን የሚጀምረው ግለሰቡ ራሱ ነው። ያ ግለሰብ ባለመታዘዝና በፍርድ ለመኖር ሲወስን፥ እግዚአብሔር ሰውዬውን በጀመረው የልብ ድንዳኔ እንዲገፋበት ያደርገዋል። እግዚአብሔር ልቡን ይበልጥ እያደነደነው ሲሄድ፥ ሰውዬው ማመን ወደማይችልበት ደረጃ ላይ ያደርሳል። (በሮሜ 1፡24-28 ልባቸውን ያደነደኑና በእግዚአብሔር የተፈረደባቸው ሰዎች ለምሳሌ ታገኛለህና ተመልከት)።

የውይይት ጥያቄ፥ በዚህ ሁኔታ ልባቸው የደነደነባቸውን ሰዎች አስተውለህ ታውቃለህን? ምሳሌ ስጥ።

ሐ. መቅሠፍቶቹ ለፈርዖን፥ ለግብፃውያንና ለእስራኤላውያን የእግዚአብሔር ኃይል ምልክቶች ነበሩ።

መ. እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ፍርድን ለማምጣት ተፈጥሮአዊ መቅሰፍቶችን ተጠቀመ። እግዚአብሔር ተፈጥሮአዊ የሆኑ የአካባቢያችን ነገሮች ሁሉ ተቆጣጣሪ ነው፡፡ እንደ እንቁራሪት፥ ውኃ፥ ድርቅ፥ በሽታ ወዘተ.።

ሠ. መቅሠፍቶቹ በሙሉ ፊታቸውን ያዞሩት በፈርዖን ላይ ብቻ ሳይሆን፥ በግብፅ አማልክትም ላይ ነበር። ግብፃውያን የዓባይን ወንዝ ከብቶችን፥ ወዘተ ያመልኩ ነበር። ግብፃውያን የተደገፉባቸውና ያለማቋረጥ ያመለኩአቸው የነበሩ አማልክት የማይጠቅሙና ዋጋ የሌላቸው ነበሩ። ፈርዖንም እንደ አምላክ የሚታይበት ሁኔታ ነበር። ሆኖም ልጁ በተገደለበት ጊዜ ኃይል የሌለው መሪ መሆኑ ታወቀ። እግዚአብሔር ከግብፅ አማልክት ሁሉ በላይ ኃያል ስለሆነ፥ እስራኤላውያን የግብፅን አማልክት ለማምለክ መፈተን እንደሌለባቸው ሊያስተምራቸው ፈለገ።

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር በመቅሠፍቶች አማካይነት ካሳየው ኃይል የምናገኛቸውን መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር።

** በራእይ 6-17፥ በመጨረሻው ዘመን በሰው ልጆች ላይ የሚመጡ ፍርዶች በግብፅ ላይ ከወረዱት መቅሠፍቶች ጋር ተመሳሳይ መሆናቸው የሚያስገርም ነው።

የፋሲካ በዓል አከባበር (ዘጸ. 12)።

የፋሲካ በዓል በእርግጥ ሁለት በዓላትን ያካተተ ነበር። ከፋሲካ በዓል ቀጥሉ የቂጣ በዓል ይከበራል።

የመጀመሪያው በዓል፥ ፋሲካ ስያሜውን ያገኘው የእግዚአብሔር መልአክ የግብፃውያንን ቤት በኩራት በሙሉ ሲገድል፥ በመዝጊያ መቃኖቻቸው ላይ ደም ያደረጉትን የእስራኤልን ቤት «ከማለፍ» አንፃር ነው። ይህ የአንድ ቀን በዓል ነበር። በመጀመሪያው የማለፉ (የፋሲካ) በዓል፥ እያንዳንዱ ቤተሰብ ምንም ጉድለት የሌለበትን አንዳንድ ጠቦት ያርድ ነበር። ከዚያም የጠቦቱ ደም መቃንና በቤቱ በር ጎበን ላይ ይቀባ ነበር። የቀረው የጠቦቱ ሥጋ ደግሞ ተጠብሶ ማታ ይበላ ነበር።

ከእስራኤላውያን እጅግ የታወቁ በዓላት አንዱ ይህ የፋሲካ በዓል ነበር። ይህም ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሠራው ሥራ ምልክት ነበር። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለሞተ፥ የእግዚአብሔር ፍርድ እኛን አለፈ። ክርስቶስ የፋሲካ በግ የተባለበት ምክንያት ይህ ነው (1ኛ ቆሮ. 5፡7፤ ዮሐ. 1፡29 ተመልከት)። ብዙ ክርስቲያኖች አይሁድ ደሙን በበሩ መቃንና ጎበን ላይ ማድረጋቸው የመስቀሉ ምልክት ነው ብለው ያምናሉ። እኛ በመታሰቢያነት የምናከብረው የጌታ እራት የተመሠረተው በፋሲካ በዓል ላይ ነው።

ከፋሲካ በዓል ቀጥሉ የቂጣ በዓል ይከበራል። አንድ ሳምንት የሚፈጅ በዓል ነው። አይሁድ እግዚአብሔርን ለማምለክ ራሳቸውን ያዘጋጁ ነበር። በመጀመሪያ በቤታቸው ያለውን ማንኛውንም እርሾ ያስወግዳሉ። እርሾ ያለበት ማንኛውም ነገር ወደ ውጭ ይጣላል። እርሾ የክፋት ምልክት ስለሆነ፥ ይህንን ሲያደርጉ በመንፈሳዊ ነገር ራሳቸውን ከክፋት ሁሉ ማንጻታቸው ነው። ቀጥሉ እርሾ የሌለበትን ቂጣ ይጋግራሉ። ይህም እግዚአብሔር ከግብፃውያን እንዴት ነፃ እንዳወጣቸውና እንዴት ግብፅን በጥድፊያ ትተው መውጣት እንደነበረባቸው ለትውልዶች ሁሉ ማስታወሻ ነበር፤ (ዘጸ. 12፡11 ተመልከት)።

እርሾ የሌለበት የቂጣ በዓል እኛም ደግሞ ያለማቋረጥ ከኃጢአት ራሳችንን በማንጻት ለእግዚአብሔር የተቀደስን ሆነን እግዚአብሔር በእኛ ውስጥና በእኛ በኩል እንዲሠራ መዘጋጀት እንዳለብን የሚያሳይ ምልክት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- አሁን ልብህን ለመመርመር ጊዜ ይኑርህ። የኃጢአትን እርሾ ከሕይወትህ አስወግደሃልን? ካላስወገድክ ኃጢአትህን ለእግዚአብሔር ተናዘዝ። የፋሲካው በግ ደምም ከኃጢአት ያነጻሃል፥ (1ኛ ዮሐ. 1፡9 ተመልከት)።

ፈርዖን የበኩር ልጁ ከሞተ በኋላ እስራኤላዊያን እንዲሄዱ ፈቀደ። ግብፃውያን በጣም ተጨንቀው ስለነበር አይሁዳውያን ይሄዱላቸው ዘንድ ወርቃቸውን፡ ብራቸውንና ሌሎች ውድ ነገሮቻቸውን ሁሉ ሰጡአቸው። በዚህም አይሁድ ምንም ኃይል ሳይጠቀሙ ግብፃውያንን በዘበዙአቸው። (ይህም በዘፍ. 15፡14 ለተጻፈው ትንቢት መፈጸም ምክንያት ሆነ) ይህንን ጥቅስ አንብብ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የእግዚአብሔር ሕዝብ በባርነት ቀንበር ሥር መሆን እና እግዚአብሔር ሕዝቡን ከባርነት ለማውጣት መሪ መጥራቱ (ዘጸአት 1-4)

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአሁኑ ጊዜ አንተም ሆንክ በኢትዮጵያ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖች የምትጋፈጧቸው የመንፈሳዊ ውጊያ ክፍል የሆኑ ነገሮችን ዘርዝር። ለ) ብዙ ክርስቲያኖች እየተሸነፉ ያሉት እንዴት ነው? ሐ) እግዚአብሔር ለአንተና ለቤተ ክርስቲያንህ በእነዚህ ነገሮች ላይ ድልን ሲሰጥ ያየኸው እንዴት ነው?

ክርስቲያን በመንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ይህ ውጊያ በመጨረሻ በእግዚአብሔርና በሰይጣን መካከል በከፍተኛ ደረጃ የሚጧጧፍ ነው። ውጊያው ሰይጣንና የእግዚአብሔር ሕዝቦችንም ያሳትፋል። ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ለመጨቆን ብዙ የተለያዩ ነገሮችን ይጠቀማል። ሰዎች የሌሎች ባሪያዎች እንዲሆኑ በማድረግ ሥጋዊ እስራትን ሊያመጣ ይችላል። ሰዎችን የሚጨቁንና ወንጌልን የሚቃወም መንግሥትንም መሣሪያ ሊያደርግ ይችላል። የእግዚአብሔር ሕዝብ ከእውነት ዞር እንዲሉ ለማድረግ የሚፈልጉ ሐሰተኛ ሃይማኖቶችንም መጠቀም ይችላል። ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች ይህን በመሰለ መንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ ሲገቡ እግዚአብሔር የተዋቸውና የሚሸነፉም ይመስላቸዋል፤ ይህ ግን እውነት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ አሸናፊው ሁልጊዜ እግዚአብሔር እንደሆነ ይናገራል። እርሱ መንግሥታትን፥ መሪዎችን፥ ሐሰተኛ ሃይማኖቶችን፥ ሰይጣንና አጋንንትን ሁሉ የሚቆጣጠር ነው። አምላካችን ገዥ ነው። እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ ኃይሉን በጠላቶቹ ሁሉ ላይ ይገልጻል። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር አንዳዶችን ሲያነሣና ሌሉችን ሲጥል በሕይወት ዘመናችን ኃይሉን እናያለን። በሌላ ጊዜ ደግሞ የእግዚአብሔር ኃይል ጠላቶቹን ሁሉ እስከሚጥልበት፥ እስከመጨረሻው ጊዜ ድረስ ተሰውሮ ይቆያል። 

ይህ የኦሪት ዘጸአት የመጀመሪያ ክፍል ታሪክ እግዚአብሔር ሰይጣንን ለማሸነፍ እንዴት እንደሠራ ይነግረናል። እግዚአብሔር የተመረጡትን ሕዝቦቹን ከባርነት ነፃ ለማድረግ የሠራውን ሥራ ይተርክልናል። እግዚአብሔር ዓላማውን ለመፈጸም ተፈጥሮንና መሪዎችን በመቆጣጠር ረገድ በሕዝቡ ሠርቷል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 1-12 አንብብ። ሀ) የእግዚአብሔር ሕዝብ የነበሩበት ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? ለ) እግዚአብሔር ሙሴን ለመሪነት ለማዘጋጀት እንዴት ሠራ? ሐ) የተመረጠ መሪ መሆኑን ለማረጋገጥ እግዚአብሔር ለሙሴ ያሳያቸው ሦስት ተአምራት ምንድን ናቸው? መ) ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ከባርነት ነፃ ለማውጣት በሚሞክርበት ጊዜ ያገኘው የመጀመሪያ ውጤት ምን ነበር? ) እግዚአብሔር ግብፃውያን፥ ሕዝቡን (እስራኤላውያንን) ይለቁ ዘንድ ያመጣባቸው አሥር መቅሠፍቶችን ዘርዝር። ረ) እነዚህ መቅሠፍቶች በግብፅ ላይ በወረዱ ጊዜ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለእስራኤል ያለውን እንክብካቤ እንዴት ገለጠ? ሰ) የፋሲካ በዓል ዓላማ ምን ነበር? ቀ) ከእነዚህ ቁጥሮች ስለ እግዚአብሔር የምንማራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ሸ) እስራኤላውያን ግብፃውያንን «የበዘበዙት» በምን መንገድ ነበር?

፩. ዘጸአት 1. የእግዚአብሔር ሕዝብ በባርነት ቀንበር ሥር መሆን 

ሀ. እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ስለባረካቸው ተባዙ (ዘጸ. 1፡1-7)

ኦሪት ዘጸአት የሚጀምረው የዘፍጥረትን የመጨረሻ ታሪክ በክለሳ መልክ አጠቃልሉ በማቅረብ ነው። ዘጸአት ፔንታቱክ ተብሎ የሚታወቀው መጽሐፍ ትልቅ ክፍል መሆኑን አስታውስ።

የእስራኤል ሕዝብ ወደ ግብፅ የወረዱት ለምንድ ነው? በባርነትስ የወደቁት እንዴት ነበር? እነዚህ የዘጸአት ምዕራፍ 1 ሁለት ዋና ዋና ጥያቄዎች ናቸው። እስራኤላውያን ወደ ግብፅ የወረዱበት ምክንያት የያዕቆብ ዝርያዎች፥ የአሥራ ሁለቱ ነገድ መሪዎች በሆኑት አሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች መሪነት በዚያ ለመኖር መሆኑን ሙሴ ያስታውሰናል። መጀመሪያ ወደ ግብፅ በደረሱ ጊዜ 70 ሰዎች ብቻ ነበሩ። እግዚአብሔር ግን ለአብርሃም የገባውን የተስፋ ቃል አስቦና አክብሮ ታላቅና የተፈራ ሕዝብ አድርጎ አበዛቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘፍ. 12፡2 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ ምን ነበር? ለ) ይህ ተስፋ በዘጸ. 1 የተፈጸመው እንዴት ነው? ሐ) ስለ እግዚአብሔርና ስለ ተስፋ ቃሉቹ ይህ ምን ያስተምረናል? – በዘጸ. 1፡6 ና 1፡7 መካከል በመቶ የሚቆጠሩ ዓመታት ልዩነት አለ። እስራኤላውያን በሙሴ መሪነት ከግብፅ ለመውጣት በተንቀሳቀሱበት ጊዜ ቁጥራቸው ከሚሊዮን በላይ ይሆን እንደነበር ምሁራን ይገምታሉ። (በዘጸ. 12፡37 ሴቶችና ልጆች ሳይቆጠሩ ቁጥራቸው ስድስት መቶ ሺህ እንደነበር ተጽፏል። 

ለ. እስራኤላውያን በባርነት ቀንበር ሥር የወደቁና የተጨቆኑ ነበሩ (ዘጻ.1፡8-22)

በዘጸ. 1፡8 እንደምናነበው፥ ዮሴፍን የማያውቅ አዲስ ንጉሥ ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ሕዝብ መጨቆን ጀመረ። ይህ ነገር የሆነው በግምት ዮሴፍ ከሞተ ከ200 ዓመታት በኋላ ነበር። በዚህ ጊዜ ግብፃውያን ሐይክሶላውያንን አሸንፈው አገራቸውን እንደገና ማስተዳደር ጀምረው ነበር። የውጭ ዜጎች በአገልግሎት ሥልጣን እንዳይኖራቸው በመደረጉ፥ አይሁዶች በባርነት ቀንበር ተያዙ። ምሁራን ይህ ጭቆና የተጀመረው በ1550 ዓ.ዓ. ነው ይላሉ። ይህም ማለት አይሁድ ከባርነት ነፃ እስከ ወጡበት 1450 ዓ.ዓ. ድረስ፥ ለ100 ዓመታት በባርነት ቀንበር ሥር ቆይተዋል ማለት ነው።

ግብፆች አይሁዳውያንን ከማባረር ይልቅ ከተሞችን ለመገንባት ሊጠቀሙባቸው መረጡ። ስለዚህ ግብፃውያን አይሁዳውያንን ባሪያዎች አደረጉአቸው። አይሁዳውያን በግብፅ ውስጥ የሚገኙትን ከባድ ሥራዎች ሁሉ ለመሥራት ተገደዱ። ነገር ግን ቁጥራቸው እጅግ እንዳይበዛና ግብፃውያንን ሥጋት ላይ እንዳይጥሉአቸው የግብፅ ንጉሥ እስራኤላዊ የሆነ ወንድ በሚወለድበት ጊዜ እንዲገደል አዋላጆችን አዘዘ። አዋላጆች ግን ይህንን ከማድረግ ተቆጠቡ።

በባርነት ቀንበር ሥር በነበሩበት ጊዜ እንኳ የእግዚአብሔር እጅ አልተለያቸውም ነበር። እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ስለባረከ የግብፃውያን ጥረት ሁሉ ከንቱ ሆኖ ቀረ። (ቁጥራቸው እጅግ እየጨመረ ሄደ፤)

የውይይት ጥያቄ፥ በዚህ ውስጥ ስለታየው የእግዚአብሔር ኃይል ምን እንማራለን?

፪. እግዚአብሔር ሕዝቡን ከግብፅ ለማውጣት አንድ መሪን ጠራ (ዘጸ. 2-4)። 

የሙሴ ሕይወት በሦስት ዘመናት ሊከፈል ይችላል፡- ሀ) ሙሴ እንደ አንድ ግብፃዊ ለ40 ዓመታት ሠልጥኗል። ለ) እግዚአብሔር ሙሴን በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት አሠለጠነው። ሐ) ሙሴ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለ40 ዓመታት መርቷል።

ሀ. ሙሴ እንደ አንድ ግብፃዊ ሠልጥኗል (ዘጸ. 2፡1-10)።

ስለ ሙሴ የመጀመሪያ 40 ዓመታት የተጻፈው ነገር በጣም ጥቂት ነው። በሕፃንነቱ በግብፃውያን እጅ ከመገደል እግዚአብሔር በተአምር የጠበቀው ሰው ነው። ወላጆቹ ገና ከመወለዱ ጀምሮ ልዩ ልጅ እንደነበር የተረዱ ይመስላል። ምክንያቱም ያማረ ሕፃን፥ ወይም ተራ ያልሆነ ልጅ ተብሎ ተጠርቷል፤ (ዕብ. 11፡23 ተመልከት)። የሙሴ ወላጆች አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ከሸሽጉት በኋላ፥ ሊደብቁት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ሲደርሱ፥ ይጠብቀው ዘንድ ለእግዚአብሔር አሳልፈው ሰጡት፤ በእግዚአብሔርም ታመኑ። በቅርጫት አድርገው በዓባይ ወንዝ ላይ አኖሩት። የእግዚአብሔር ጥበቃ በዚህ ሰው ላይ ምን ያህልና እንዴት እንደነበረ አስተውል፡

 1. እግዚአብሔር ሁኔታዎችን ስለተቆጣጠረ፥ የፈርዖን ሴት ልጅ በቅርጫት ተደርጎ በተቀመጠበት ወንዝ ዳር ሙሴን አገኘችውና እንደ ልጇ ልታሳድገው ወደ ቤቷ ወሰደችው፡፡
 2. የሙሴ እናትና እኅት በአስተዳደጉ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ እግዚአብሔር ሁኔታዎችን አመቻቸ። ሙሴ ዕብራዊ መሆኑን የተማረው ከየት ነበር? ስለ እግዚአብሔር የተማረውስ የት ነው? ከእናቱና ከእኅቱ እንደሆነ አይጠረጠርም። 

የውይይት ጥያቄ፥ ወንጌልን ለልጆቻችን ስለማስተማር አስፈላጊነት ይህ ምን ያስተምረናል?

ሙሴ በግብፅ ያሳለፈው አብዛኛው ነገር አልተገለጸም። የምናውቀው ነገር ቢኖር በግብፅ ትምህርትና ጥበብ ሁሉ ማደጉን ነው (የሐዋ. 7፡22፤ ዕብ. 11፡24-27 ተመልከት)። ከግብፃውያን ትምህርት ቤቶች ከሁሉ በተሻለው ውስጥ ከንጉሣውያን ቤተሰብ ልጆች ጋር ሳይማር አልቀረም። አንዳንድ ምሁራን የግብፅ ንጉሥ ለመሆን በሚችልበት መስመር ላይ ነበር ይላሉ።

ሙሴ በግብፅ የተማረው ትምህርት በኋላ ፔንታቱክን ለመጻፍ ተግባሩ ጠቅሞታል።

ለ. ሙሴን በምድረ በዳ ውስጥ እግዚአብሔር አሠለጠነው።

ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ እንዲመራ እግዚአብሔር እንደፈለገው ሳያውቅ አልቀረም። ነገር ግን እግዚአብሔር እስኪሠራ መጠበቅ ሲገባው የራሱን እርምጃ በመውሰድ፥ አንዱን እስራኤላዊ ለመርዳት ሲሞክር አንድ ግብፃዊን ገደለ። ከዚያም በምድያን ወዳለው ምድረ በዳ ሄዶ በኋላ ልጁን የዳረለትን ዮቶርን በእረኝነት በማገልገል 40 ዓመታት አሳለፈ። ሙሴ በነፃነት ወደ ግብፅ ለመመለስ የቻለው በእርሱ ጊዜ የነበረው ንጉሥ ከሞተ በኋላ ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ነፃ ለማውጣት ያን ያህል ረጅም ጊዜ የቆየው ለምን ይመስልሃል? ለ) ሙሴ ከመምረጡ በፊት ለ40 ዓመታት የቆየውስ ለምንድን ነው? ሐ) የሙሴ ታሪክ ስለ መንፈሳዊ መሪነት ምን ያስተምረናል?

ሙሴ በምድረ በዳ የተማረውን ነገር በኋላ እግዚአብሔር ተጠቅሞበታል። ሙሴ የተዘጋጀው በመንፈሳዊ ሕይወቱ ብቻ ሳይሆን፥ በሥጋዊ ረገድም በምድረ በዳ መኖር እንዴት እንደሚቻል ተምሯል።

ስለዚህ በምድረ በዳ ስለመኖር አንዳችም እውቀት የሌላቸው አይሁዳውያን ወገኖቹን ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ ለመምራት በቅቷል።

፫. የእስራኤል ሕዝብ መሪ እንዲሆን እግዚአብሔር ሙሴን ጠራው (ዘጸአት 3-4)።

እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሙሴን የተገናኘበት መንገድ አስገራሚ ትዕይንት የታየበት ነበር። እሳት እየነደደበት ነገር ግን ተቃጥሎ የማያልቅ ቁጥቋጦ ባለበት ስፍራ ተገናኘው። እግዚአብሔር ለሙሴ ኃይሉን ሊያሳየው ፈልጎ ነበር። ደግሞም እሳት ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ሕልውና ምልክት ነው፤ (ሕዝ. 1፡4-5፥ 27 ተመልከት)። የእግዚአብሔር ቅድስናም ምልክት ነበር። በፊቱ በቆመ ጊዜ በአይሁድ ልማድ መሠረት ጫማውን በማውለቅ አክብሮቱን እንዲገልጥ እግዚአብሔር ለሙሴ ነገረው።

በሙሴ ጥሪ ውስጥ የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-

1) እግዚአብሔር ሙሴን መረጠውና እስራኤልን ከባርነት ነፃ ለማውጣት መሪ እንደሚሆን ነገረው። 

2) እግዚአብሔር ለሙሴ «እኔ እኔ ነኝ» ወይም ያህዌ በማለት ልዩ ስሙን ነገረው። ይህ ስም የእግዚአብሔርን ኃይልና በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ያለውን የበላይ ተቆጣጣሪነት የሚገልጽ ነው። 

3) ሙሴ በእግዚአብሔር የተመረጠ መሪ መሆኑን ያውቁ ዘንድ ለእስራኤላውያን እንዲያሳያቸው ሦስት ምልክቶችን ሰጠው፡

ሀ) እግዚአብሔር የሙሴን በትር ወደ እባብ፥ እባቡን ደግሞ መልሶ ወደ በትር ለወጠው። 

ለ) እግዚአብሔር የሙሴን እጅ በለምጽ መታውና ወዲያው ደግሞ ወደ ተለመደው መልኩ መለሰው። 

ሐ) እግዚአብሔር ለሙሴ፥ «አንተ በእኔ የተመረጥክ መሪ መሆንህን እስራኤላውያን ካላመኑ ከዓባይ ወንዝ ውኃን ውሰድና ወደ ደምነት ለውጠው» አለው።

4) ሙሴ በ40 ዓመታት የምድረ በዳ ቆይታው ጊዜ በጣም ተለውጦ ነበር በራሱ ብርታት መቆሙና መተማመኑ አብቅቶ ነበር። ስለዚህ አሁን ፈራና እኔ መናገር አልችልም ብሎ ለእግዚአብሔር መልስ ሰጠ። ይህም ሙሴ በእግዚአብሔር ለመታመን ፈቃደኛ አለመሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነበር። እግዚአብሔር ለሙሴ ጥያቄዎች በሙሉ በትዕግሥት መልስ ሰጠና ለመታዘዝ ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲያይ ተቆጣ። እኛም ብንሆን ያልገባንን ነገር ከእግዚአብሔር የመጠየቅ መብት አለን። ነገር ግን እግዚአብሔርን ለመታዘዝ እንድንችል ሁልጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ከዚያም ወንድሙ አሮን ከእርሱ ጋር እንደሚሠራና አፈቀላጤው እንደሚሆን እግዚአብሔር ለሙሴ ነገረው። 

5) ሙሴ ሊነጻና እግዚአብሔርን የመታዘዝ አስፈላጊነትን ሊማር ይገባው ነበር።

ወንዶች ልጆች ሁሉ እንዲገረዙ እግዚአብሔር ያዘዘ ቢሆንም (ዘፍጥ. 17 ተመልከት) ሙሴ ግን አልታዘዘም ነበር። ወንዶች ልጆቹ አልተገረዙም ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ሊፈርድበት ተዘጋጀ። እግዚአብሔር ሙሴን በአንድ ዓይነት በሽታ የመታው ይመስላል። የሙሴ ሚስት የወሰደችው ፈጣን እርምጃ ሙሴን ከሞት አዳነው። ልጇን ገረዘች። «አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ» ብላ የተናገረችውን ቃል ምንነት መረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። አንዳንድ ምሁራን እንዲህ ይላሉ፡- ሲፓራ አይሁዳዊት ስላልነበረች ይህ የግዝረት ባሕል ለእርሷ እንግዳ ነበር፤ ስለዚህ ሙሴ ልጆቹን እንዲገርዝ ሳትፈቅድ ቀረች። ነገር ግን ሙሴን ለማዳን ስትል ግትርነትዋን ተወችና ልጇን ገረዘች። ይህንን በማድረጓ በመጀመሪያ ለሙሴ የገባችውን ቃል ኪዳን በማደስ እንደ አዲስ ሙሽራ ቆጠረችው። ይህንን ያረጋገጠው በመገረዙ ምክንያት ከልጇ የፈሰሰው ደም ነው። ሆኖም የዚህ ሐረግ ትርጉም ግልጽ አይደለም። የታሪኩ ትርጉም ግን ግልጽ ነው። በታሪኩ ውስጥ ሁለት ዋና ዋና ነገሮች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡-

ሀ) ሙሴ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሪ ይሆን ዘንድ መሆን ቤተሰቡም መንጻትና እግዚአብሔርን ለማገልገል የተዘጋጀ ነበረበት። ግዝረት እግዚአብሔር ደስ የማያሰኙ ነገሮችን ሁሉ ከሕይወት የማስወገድና ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን አልፎ የመሰጠት ምልክት ነው። ለ) ምንም ያህል ትንሽና ኢምንት ቢመስሉም እንኳ ለእግዚአብሔር ትእዛዛት ሙሉ ለሙሉ መታዘዝ አስፈላጊ እንደሆነ ሙሴን ማስተማር አስፈላጊ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህን ሁለት እውነቶች ማወቅ ለሙሴ ለምን ያስፈልገው ነበር? ለ) ዛሬም ቢሆን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እነዚህን እውነቶች ማስታወስ ለምን ይጠቅማቸዋል? ሐ) በዚህ ዘመን ያሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እግዚአብሔርን በከፊል ብቻ የሚታዘዙባቸውን ሁኔታዎች ግለጽ። መ) ይህ ነገር በአመራራቸው ላይ እንዴት ተጽዕኖ ያደርጋል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኦሪት ዘጸአት አስተዋጽኦ እና ዓላማ

፩. የኦሪት ዘጸአት አስተዋጽኦ

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ኦሪት ዘጸአት ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። እዚያ የሚገኘውን አስተዋጽኦ ገልብጥ። በሚቀጥሉት ገጾች የሚገኘውን አስተዋጽኦም አጥና።

በአጠቃላይ የኦሪት ዘጸአት ታሪክ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል፡

 1. እስራኤላውያን በግብፅ ምድር (ዘጸ. 1-12፡36)

በዚህ የመጀመሪያ ክፍል ውስጥ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ተጠቅሰዋል። በመጀመሪያ የምናየው፥ የሙሴን ታሪክ ሲሆን ስለ ልደቱ፥ በምድረ በዳ ስላሳለፈው ጊዜና እግዚአብሔር እንዴት ለመሪነት እንደመረጠው እንመለከታለን።

በሁለተኛ ደረጃ፥ ስለ አሥሩ መቅሠፍቶች፥ እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ለመፍረድና ሕዝቡን ከባርነት ቀንበር ነፃ ለማውጣት እነዚህን መቅሠፍቶች እንዴት እንደተጠቀመባቸው እንመለከታለን።

በሦስተኛ ደረጃ፥ በፋሲካ በዓል ታሪክ አማካይነት እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ከባርነት ቀንበር ነፃ በማውጣት እንዴት እንደመራቸው የሚያሳየውን ታሪክ እንመለከታለን። 

 1. ከግብፅ ወደ ሲና ተራራ የተደረገ ጉዞ (ዘጸ. 12፡37- ምዕ. 18) 

እስራኤላውያን ወደ ሲና ተራራ ለመድረስ ያደረጉት ጉዞ ሦስት ወራት ፈጀባቸው። እግረ መንገዱንም የሚከተሉት ዋና ዋና ድርጊቶች ተፈጸሙ፡-

አንደኛ፥ እግዚአብሔር እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን እንዲሻገሩ አስቻላቸው፥ ፈርዖንና ሠራዊቱን ግን አሰጠማቸው።

ሁለተኛ፥ እስራኤላውያን በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች በእግዚአብሔር ላይ አጉረመረሙ። ስለ መራራው ውኃ አጉረመረሙና ሙሴ፥ በእግዚአብሔር ኃይል ወደ ጣፋጭነት ለወጠው። እግዚአብሔር ለሕዝቡ መናንና ድርጭቶችን ለምግብነት ሰጣቸው። ሕዝቡ እግዚአብሔር ከዓለት ውኃ እስኪሰጣቸው ድረስ አጉረመረሙ።

ሦስተኛ፥ ከአማሌቃውያን ጋር ጦርነት ተካሄደ። እግዚአብሔርም ለእስራኤል ሕዝብ ድልን ሰጠ።

አራተኛ፥ የእስራኤልን ሕዝብ በመምራት ሥራ ሙሴን ይረዱት ዘንድ የሰባ ሽማግሌዎች ምርጫ ተካሄደ። 

 1. በሲና ተራራ የቃል ኪዳኑ መሰጠት (ዘጸ. 19-40)

የእስራኤል ሕዝብ በሲና ተራራ ላይ ለአንድ ዓመት ያህል ቆዩ። ኦሪት ዘጸአትና ዘሌዋውያንም ሕዝቡ በሲና ተራራ ላይ ስለነበሩበት ጊዜ ይናገራሉ። በሲና ተራራ የተደረጉ አራት ዋና ዋና ድርጊቶች በኦሪት ዘጸአት ውስጥ ተገልጸዋል።

አንደኛ፡- እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በጽላት ላይ የጻፋቸውን ዓሠርቱን ትእዛዛት ሰጣቸው።

ሁለተኛ፥ የተቀደሱ ሕዝቦች ይሆኑ ዘንድ መጠበቅ ያለባቸውን የቃል ኪዳን መመዘኛዎች እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ሰጣቸው።

ሦስተኛ፥ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን የሚያመልኩበትን የመገናኛ ድንኳን አሠራር የሚያመላክት ትእዛዝ ተቀበሉ። በተጨማሪ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ካህናትን ለአገልግሎት የመመደብንም ትእዛዝ ሰጣቸው። በሲና ተራራ ላይ እያሉ እነዚህን ትእዛዛት ፈጸሙ።

አራተኛ፥ እስራኤላውያን የጥጃ ምስል ሠርተው በማምለክ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት አደረጉ፤ የማመንዘር ኃጢአትንም ፈጸሙ፤ እግዚአብሔርም በብርቱ ቀጣቸው።

ከዚህ በታች የኦሪት ዘጸአትን ታሪክ በሚገባ ለማስታወስ የሚረዳ ዝርዝር አስተዋጽኦ ቀርቦአል፡-

 1. እግዚአብሔር ሕዝቡን – እስራኤልን ከግብፅ አዳነ (ዘጸ. 1-18)

ሀ. እግዚአብሔር እስራኤልን እንደሚያበዛ የገባውን ቃል ኪዳን ፈጸመ (ዘጸ. 1) 

ለ. እግዚአብሔር ሙሴን ለመሪነት መርጦ አዘጋጀው (ዘጸ. 2-6)፣ 

ሐ. እግዚአብሔር ግብፅን በአሥር መቅሠፍቶች መታ (ዘጸ. 7-11)፤ 

መ. እግዚአብሔር የፋሲካን በዓል ለእስራኤል ሕዝብ ሰጠ (ዘጸ. 12፡1-28)፤ 

ሠ. እስራኤላውያን ከግብፅ ወጡ (ዘጸ. 12፡29-51)፤ 

ረ. በግብፅ የተወለዱት የእስራኤላውያን በኩራት በሙሉ ተቀደሱ (ዘጸ. 13፡ 1-16)፤

ሰ. እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን ተሻገሩ (ዘጸ. 13፡17-15፡21)፤ 

ሸ. እስራኤላውያን ወደ ሲና ተራራ ተጓዙ (ዘጸ. 15፡22-18፡27)። 

 1. እግዚአብሔር በሲና ተራራ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ (ዘጸ. 19-24)

ሀ. አይሁድ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘትና ቃል ኪዳን ለመቀበል ተዘጋጁ (ዘጸ. 19)፤ 

ለ. እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ዓሠርቱን ትእዛዛት ሰጣቸው (ዘጸ. 20፡1-17)፤ 

ሐ. እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ስለተቀደሰ አንዋንዋር መመሪያ ሰጣቸው (ዘጸ. 20፡18-23፤ 33)፤ 

መ. እስራኤላውያን በቃል ኪዳኑ ተስማሙ፤ ቃል ኪዳኑም ተረጋገጠ (ዘጸ. 24፡1-8)። 

 1. እግዚአብሔር የሚመለክበትን የመገናኛ ድንኳን አሠራር የሚመለከት ትእዛዝ ሰጠ (ዘጸ. 25-40)

ሀ. የመገናኛውን ድንኳን ለመሥራት ዝግጅት ተደረገ (ዘጸ. 24፡9-31፡18)፤ 

ለ. እስራኤላውያን ጣዖትን በማምለክ ኃጢአት ላይ ወደቁ፤ ተፈረደባቸውም (ዘጸ. 32-34)፤

ሐ. የማደሪያው ድንኳን ተሠራና እግዚአብሔር አደረበት (ሕልውናውን ገለጠበት) (ዘጸ. 35-40)። 

፪. የኦሪት ዘጸአት ዓላማ

ዮፔንታቱክ መጻሕፍት ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትን ይጥላሉ። የኦሪት ዘፍጥረት ተቀዳሚ ተግባር በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የነበሩትን የአይሁድን አጀማመር መግለጥ እንደነበር አይተናል። የኦሪት ዘፍጥረት መጨረሻ የሚያሳየው የእስራኤል ሕዝብ ከተስፋይቱ ምድር ውጭ በግብፅ እንዴት እንደተገኙ ነው። ኦሪት ዘጸአት እስራኤላውያን ወደ ታላቅ ሕዝብነት እንዴት እንዳደጉና ግብፅን ትተው ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ ከነዓን ለመመለስ እንዴት ጉዞ እንደጀመሩ ያሳየናል። ይህ መጽሐፍ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን እንዴት ትልቅ ሕዝብ እንዳደረጋቸው፥ የተመረጡ ሕዝብ እንደ መሆናቸው መጠንም ከእርሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያስረዳውን ቃል ኪዳን እንዴት እንደገባ ይነግረናል።

ኦሪት ዘጸአት አራት ዋና ዋና ዓላማዎች አሉት። እነርሱም :

 1. እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከባርነት እንዴት ነፃ እንዳደረጋቸው መናገር ነው። 

ይህ ታሪክ የመዋጀት ታሪክ ነው። «መዋጀት» የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚያስችል ቁልፍ ቃል ነው። «መዋጀት» የሚለው ቃል የሚናገረው ተገቢውን ዋጋ በመክፈል ሰውን ከባርነት ነፃ ስለ ማውጣት ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ በኢየሱስ ደም ከኃጢአት ባርነት ተዋጅተናል (ማር. 10፡45)። በብሉይ ኪዳን ግን የመዋጀትን ግልጥ ሥዕል የምንመለከተው እግዚአብሔር የአይሁድን ሕዝብ ከግብፅ ባርነት ለመዋጀት በሠራው ሥራ ውስጥ ነው (ዘጸ. 6፡6፤ ዘዳ. 15፡15 ተመልከት)።

እስራኤላውያን በትውልዶች ሁሉ እግዚአብሔር በግብፅ ከነበሩበት ባርነት እንዴት ነፃ እንዳወጣቸው ማስታወስ ነበረባቸው። ይህም እግዚአብሔር ከምንም ዓይነት ባርነት ነፃ እንዳወጣቸው ለማመን መሠረት ሆናቸው። በተጨማሪም የሌሎች አሕዛብን አማልክት ሳይከተሉ፥ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት እንዲጠብቁ ረድቶአቸዋል። 

 1. የእስራኤል ሕዝብ ልዩ ወይም የተለዩ እንደሆኑ ለማስታወስ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 19፡3-6 አንብብ። ሀ) እስራኤላውያን በእነዚህ ቁጥሮች የተገለጡት እንዴት ነው? ለ) እነዚህን ቁጥሮች ከ1ኛ ጴጥ. 2፡5-9 ጋር አወዳድር። ቤተ ክርስቲያን ከእስራኤል ጋር የምትመሳሰለው እንዴት ነው? ሐ) የአንተ ቤተ ክርስቲያን ይህን ጥሪ እንዴት እየፈጸመች ነው?

እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በዚህ ምድር ከሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ ለይቶ የተለዩ ቅዱስ ሕዝብ እንዲሆኑ መረጣቸው። ከሌሉች ሕዝቦች ሁሉ የተለዩ ነበሩ። የእግዚአብሔር የግል ገንዘቡ ነበሩ። የእግዚአብሔር ካህናት የሆኑ ሕዝብ ነበሩ። እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን የሕዝቡን ልዩ መሆን አጠናከረው። ከሌላው ሕዝብ ጋር ጨርሶ ባልተገናኘበት መንገድ ከዚህ ሕዝብ ጋር ተገናኘ፡፡ እግዚአብሔር ለነዚህ ሕዝብ፥ በቃል ኪዳኑና በሲና ተራራ በሰጣቸው ትእዛዛት መሠረት በታዛዥነት ከተራመዱና ከኖሩ ብቻ፥ ከዓለም የተለዩ እንደሚሆኑ ሊያሳያቸው ፈልጎ ነበር። ይህ ሲሆን ብቻ ነው የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ሕዝብ ሊሆኑ የሚችሉት (ዘጸ. 19፡5-6)።

በሲና ተራራ ላይ የተፈጸመው ቃል ኪዳን፥ በእግዚአብሔርና በእስራኤል ሕዝብ መካከል ሊኖር የሚገባውን ይህን ልዩ ግንኙነት አሳይቷል። እርሱን ብቻ ሊያመልኩ ይገባ ነበር። በእግዚአብሔር ፊት በመታዘዝና በቅድስና ሊኖሩ፥ በቅድስናቸውም እርሱን ሊመስሉ ይገባ ነበር፤ (ዘጸ. 22፡31)። በእርሱ በኩል እግዚአብሔር ለእነርሱ በተለየ መንገድ ኅብረት ያደርግ ነበር። በአእምሮአቸው ውስጥ የሚኖረው ክብሩን ሊያንፀባርቅ በሚችል የደመና ክብር እንጂ፥ በተቀረፀ ምስል ክብር አልነበረም። እግዚአብሔር «እርሱ የሚያድርበትን የመገናኛ ድንኳን» እንዲሠሩ አዘዛቸው (ዘጸ. 40፡33-38 ተመልከት)።

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ቆሮ. 3፡16-17፤ 6፡19 አንብብ። ሀ) በአዲስ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ምንድነው? ለ) በብሉይ ኪዳን ከነበረው ከመገናኛው ድንኳን ዓላማ ጋር እንዴት ይመሳሰላል?

 1. እስራኤላውያን ልዩ የሆኑት በሕዝብነታቸው ታላቅነት ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ምሕረትና ሉዓላዊ ምርጫ መሆኑን እንዲያስቡት ለማድረግ ነው። 

እነርሱ እግዚአብሔርን አልመረጡትም፤ እርሱ መረጣቸው እንጂ። ሆኖም ይህ ልዩ መብት እግዚአብሔር በሲና ተራራ ከእነርሱ ጋር ባደረገው ቃል ኪዳን ውስጥ ለሚገኙት ቅድመ-ሁኔታዎች እስራኤላውያን ባላቸው መታዘዝ ላይ መመሥረት ነበረበት። እስራኤላውያን ካልታዘዙ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኙት አንዳችም በረከት አይኖርም።

 1. ለእስራኤላውያን የእግዚአብሔርን ታላቅነት ለማሳየት ነው። 

ብዙ ጊዜ እግዚአብሔርን ሊረዳቸው እንደማይችል እንደ አንድ ደካማ ምስል አድርገው ያስቡት ነበር። የአብርሃምን፥ የይስሐቅንና የያዕቆብን ታሪክ የሰሙ ቢሆንም እንኳ በግል እግዚአብሔርን አልተዋወቁትም ነበር። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው ግንኙነት መጀመሪያ ታላቅነቱን ለእነርሱ ገለጠላቸው። እግዚአብሔር ታላቅነቱን የገለጠላቸው በተለያዩ መንገዶች ነው። በመጀመሪያ ታላቅነቱንና ኃይሉን የበለጠ ሊገልጥ የሚችለውን የራሱን አዲስ ስም ሰጣቸው። ያ ስም «ጂሆቫ» ወይም «ያህዌ» የሚል ነበር፤ (ዘጸ. 3፡13-15 ተመልከት)። ሁለተኛ፥ በፍጥረታት ሁሉና በምድር ከሁሉም ይበልጥ ገናና በነበረው መሪ ላይ እንኳ 10 መቅሰፍቶችን በመላክ ኃይሉን ገለጠ። ሦስተኛ፥ ቅድስናውንና ኃይሉን በሲና ተራራ በነጎድጓድ በታጀበ ታላቅ ድምፅ ገለጠላቸው (ዘጸ. 19፡15-19 ተመልከት)። አራተኛ፥ እግዚአብሔር ታማኝ መሆኑን ለአብርሃምና ለቀሩት የእስራኤል ሕዝብ አባቶች የገባላቸውን ተስፋ በመፈጸም አሳየ። እግዚአብሔር ለመረጣቸው ሰዎች ሁልጊዜ ታማኝ ነው። የገባውንም የተስፋ ቃል ዘወትር ይጠብቃል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔር ፍላጎት ራሱን ለእኛ መግለጥ ስለሆነ በኦሪት ዘጸአት ያለው ከሁሉም የሚበልጥ ዓላማ ይህ ሳይሆን አይቀርም። እግዚአብሔር አምላካችንን የምናውቅ ሕዝብ መሆን አለብን። በተለይ ጥርጥር በተስፋፋበት በዚህ ዘመን የእግዚአብሔርን ባሕርይ ባወቅንና በተረዳን መጠን በእርግጠኛነትና በእምነት ዋስትና መኖራችን ይቀጥላል። 

የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህ አራት ዓላማዎች ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚንፀባረቁት እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

በዘጸአት ጊዜ የነበረው የግብፅ ታሪክ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ በዓለም ከሚፈጸመው ታሪክ ጋር በቅርብ የተቆራኘ እንደሆነ ሁሉ፥ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክም ከጥንቱ ዓለም ጋር የተቆራኘ ነበር። ይህ ደግሞ በተለይ በዚያን ጊዜ ከሁሉም በላይ ገናና የነበረችውን ግብፅን በሚመለከት የበለጠ እውነትነት አለው።

የውይይት ጥያቄ፥ መዝ. 2፤ ኢሳ. 40፡ 15-25 አንብብ። ሀ) እነዚህ ቁጥሮች እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ ስላለው አገዛዝ ምን ያስተምሩናል? ለ) እነዚህ ቁጥሮች በአሁኑ ጊዜ እንዴት ያበረታቱናል?

እግዚአብሔር መንግሥታትን ሁሉ ይቆጣጠራል፤ ታሪካቸውንም ይወስናል። ደካሞች ይሁኑ ብርቱዎች ድንበራቸው የት ድረስ እንደሚሆን ሁሉ የሚወስን እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ወደ ግብፅ በማምጣት በእነርሱ ውስጥ የሠራው ከራብ ሊያድናቸው ብሎ ነው። እንደምታስታውሰው፥ እግዚአብሔር ይህንን ያደረገው የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ባደረገው በዮሴፍ መሪነት ነው። ነገር ግን በግብፅ በተፈጸሙት ክስተቶች ስሙ ይከበር ዘንድ በግብፅ ሕዝብ መካከልም ሠርቷል።

የውይይት ጥያቄ፥ ኢያ. 2፡8-11 አንብብ። በግብፅ የተፈጸሙት ታሪካዊ (ድርጊቶች በዚያን ጊዜ ለነበሩት የአሕዛብ መንግሥታት ሁሉ ምን አስተማራቸው?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብፅ ታሪክ ብዙ አይነግረንም። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል ትኩረት ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤል፥ እንዲሁም በእነርሱ በኩልና በእነርሱም አማካይነት እንዴት እንደሠራ መናገር ነው፤ ዳሩ ግን በዚያ ጊዜ ስለነበረው ስለ ግብፅ መንግሥት ከዓለም ታሪክ ብዙ ለመማር እንችላለን። የኦሪት ዘጸአት ታሪክ የተፈጸመው አዲሱ የመንግሥት ዘመን በመባል ይታወቅ በነበረው የግብፅ ታሪክ ጊዜ ነበር በማለት ብዙ ምሁራን ያምናሉ።

የኢትዮጵያ ታሪክ በተለያዩ ጊዜያት ሊከፋፈል እንደሚችል ሁሉ፥ የግብፅ ታሪክም በተለያዩ ጊዜያት ሊከፋፈል ይችላል። በ1800 ዓ.ዓ. ግብፃውያን መካከለኛው መንግሥት እየተባለ በሚጠራው መንግሥታቸው ይኖሩ ነበር። በዚህ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የግብፅ መንግሥት በጣም ተዳከመ። በ1700 ዓ.ዓ. አካባቢ ከእስያ የመጣ ሐይክሶስ የተባለ የሴም ዘር ሕዝብ ግብፅን በመውረር ሥልጣን ጨበጠ። እነዚህ ሕዝቦች ከአይሁድ ጋር የሚዛመዱና እንደ እነርሱም መጻተኞች ስለነበሩ አይሁድ ከሐይክሶሳውያን ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበራቸው፤ ዳሩ ግን በ1550 አካባቢ ግብፆች ሐይኪሶሳውያንን አባረሩና መንግሥታቸውን እንደገና ተቆጣጠሩ። ይህ ዘመን ከ1546-1085 ዓ.ዓ. ድረስ የቆየ ሲሆን የአዲሱ መንግሥት ዘመን በመባል ይታወቅ ነበር። ይህም በግብፅ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ጥንካሬና እድገት የታየበት ጊዜ ነበር።

ግብፃውያን በባዕዳን ተገዝተው ስለነበር በምድራቸው በሚኖሩ የውጭ ዜጎች ሕዝቦች ሁሉ ላይ ተቃውሞ አካሄዱና እንደ ሐይኪሶስ ያሉትን አንዳንዶቹን አባረሩ። እንደ አይሁድ ያሉትን ደግሞ ባሪያዎች አደረጉ። ኦሪት ዘጸአት 1-12 ግብፆች አይሁድን ባሪያ ያደረጉበትን ይህን ጊዜ ያንፀባርቃል። ግብፃውያን አይሁድ በኃይል እያደጉ እንዳይሄዱ የፈሩበትን ምክንያት ያስረዳል። ሐይኪሶሶች እንዳደረጉት አይሁድም ምድራቸውን እንዳይወስዱባቸውና እንዳይዙአቸው ይሠጉ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ቤተ ክርስቲያን ጠንክራ እንዳታድግ በሚፈልጉ በአንዳንድ በማያምኑ ሰዎች ላይ ይህ ተመሳሳይ ፍርሃት እንዴት ይታያል? 

የግብፃውያን ሃይማኖት 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸአት 32:1-8 አንብብ። እስራኤላውያን እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ምን ነገር አደረጉ?

እስራኤላውያን ከግብፃውያን ጋር ለ400 ዓመታት ኖረዋል። በዚህ ቆይታቸው ለእግዚአብሔር ባላቸው አምልኮ በንጽሕና መቆየት አልቻሉም። ይልቁንም የግብፃውያንን አማልክት ማምለክ ጀመሩ። በዘጸአት 32 እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ላይ ሲያምፁና በጥጃ የሚመሰለውን የግብፃውያን አምላክ ሲያመልኩ እንመለከታለን።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም ክርስቲያኖች ራሳችውን ለእግዚአብሔር ንጹሐን አድርገው ከመጠበቅ ይልቅ በዙሪያቸው ያሉትን ሕዝቦች አስተሳሰብና ልማድን መከተል የሚቀላቸው እንዴት ነው? አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ። ለ) ቤተ ክርስቲያንህ አባሎችዋ ዓለምን እንደማይመስሉና በእግዚአብሔር ፊት በንጽሕና እንዳሉ ለማረጋገጥ በየጊዜው ምን ታደርጋለች? ሐ) ቤተ ክርስቲያን አባሎችዋን ከዓለም አሉታዊ ተጽዕኖ ለመጠበቅ ምን የተሻለ ነገር ማድረግ ትችላለች?

ግብፃውያን በርካታ የተለያዩ አማልክትን ያመልኩ ነበር። ከእነዚህ አማልክት መካከል አብዛኛዎቹ በተፈጠረው ዓለም ውስጥ ያሉ ነገሮች ይመስሉ ነበር። ለምሳሌ፡- የፀሐይ አምላክን፥ የጨረቃ ሴት አምላክን፥ ወፎችን፥ እንደ ወይፈን ያሉ እንስሳትን ወዘተ. ያመልኩ ነበር። በአገራቸው በአጠቃላይ እነዚህን አማልክት የሚያመልኩባቸውን በርካታ ቤተ መቅደሶች ሠርተው ነበር። ግብፃውያን በበርካታ አማልክት ያምኑ ስለነበር፥ የሌሎች ሕዝቦችን አማልክት በቀላሉ ማምለክ ይችሉ ነበር። እስራኤላውያንም እነዚህን አማልክት ለምደው ነበርና እነርሱን ለማምለክ ተመሳሳይ የሆኑ ምስሎችን መሥራት ጀመሩ። እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የመጀመሪያዎቹን ሁለት ትእዛዛት የሰጠው የእነዚህን በርካታ አማልክት አምልኮን በመቃወም ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 20፡ 1-6 አንብብ። ሀ) በዚህ ስፍራ የምናገኛቸው ሁለት ትእዛዛት ምንድን ናቸው? ለ) ስለ እስራኤል ሕዝብ ታሪክ ባለህ ግንዛቤ መሠረት ብዙ ጊዜ እነዚህን ትእዛዛት የሚጥሱት እንዴት ነበር?

በሲና ተራራ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ የሰጣቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ትእዛዛት በግብፃውያን ዘንድ በጣም ተለምዶ የነበረውንና እስራኤላውያን በግብፅ በቆዩበት ጊዜ የተለማመዱትን የጣዖት አምልኮ የሚያመለክቱ ነበሩ። እንደ አጋጣሚ እስራኤላውያን በታሪካቸው ሁሉ ከጣዖት አምልኮ ጋር ይታገሉ ነበር።

በመጀመሪያው ትእዛዝ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የነገራቸው እውነተኛ አምላክ የሆነውን እርሱን ብቻ እንጂ ሌሎች አማልክትን እንዳያመልኩ ነበር። ሁለተኛው ትእዛዝ የሚናገረው ደግሞ በጊዜው በጣም የተለመደውን የተቀረፀ ምስልን ወይም እግዚአብሔርን የሚወክል ነገር ማድረግን የሚመለከት ነበር። አማልክቶቻቸው በጥጃ ወይም በእባብ ወዘተ. የተመሰሉ ነበሩ። እነዚህንም ምስሎች ያመልኩ ነበር። እግዚአብሔር እርሱን የሚመስሉበትን አንዳችም ነገር እንዳያደርጉ አይሁድን በጥብቅ አዝዞአቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ሰዎች እርሱን የሚመስሉበትን አንዳችም ምስል ወይም ቅርፅ እንዳያደርጉ የፈለገበት ምክንያት ምን ይመስልሃል?ለ) ሰዎች በቤታቸው ወይም በቤተ ክርስቲያናቸው የሚያንጠለጥሉት የኢየሱስ ሥዕልስ ጉዳይ እንዴት ነው? እነዚህ የእግዚአብሔር ምስሎች ናቸውን? መልስህን አብራራ። ሐ) ክርስቲያኖች የኢየሱስን ሥዕል በቤታቸው መስቀል አለባቸውን? መልስህን አብራራ።

እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ በመሆኑም ማንኛውንም የተፈጠረ ነገር አይመስልም። ሰው እግዚአብሔርን በአንድ ዓይነት ቅርፅ ወይም ምስል ለመመሰል የሚያደርገው ሙከራ እርሱን ማክበር ሳይሆን ማዋረድ ነው። ሰው የእግዚአብሔርን ኃይልና ክብር ሙላት ለማወቅም ሆነ ለመገመት አይችልም፤ ስለዚህ እንዲህ ላለው ታላቅ አምላክ ክብርን የሚሰጥ ነገር ማዘጋጀት አንችልም።

ክርስቲያኖች በቤትም ሆነ በቤተ ክርስቲያን የኢየሱስን ሥዕል ስለ መስቀል የተለያየ አመለካከት አላቸው። ሙስሊሞች በቤታቸውም ሆነ መስጊዳቸው ማንኛውንም ዓይነት የእግዚአብሔር ምስል ላለማድረግ ይጠነቀቃሉ። ስለ ክርስቲያኖች የሚነቅፉት ነገር ቢኖር ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን፥ የኢየሱስን ወይም የመላእክትን ሥዕል በቤተ ክርስቲያናቸው ወይም በቤታቸው ያደርጋሉ ብለው ነው። ይህ ነገር እግዚአብሔርን የማያስከብርና ትእዛዙንም የሚቃረን ነው ብለው ያምናሉ።

ክርስቲያኖች ማንኛውንም የኢየሱስን ሥዕል በቤተ ክርስቲያናቸውም ሆነ በቤታቸው ስለ መስቀል እጅግ መጠንቀቅ አለባቸው። ለዚህም አራት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ፡

 1. በዘጸ. 20፡4-6 የሚገኘው ሁለተኛው ትእዛዝ፥ ይህ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል እንዳልሆነ በግልጥ የሚያሳይ ይመስላል። 
 2. ሥዕሎቹ ኢየሱስን አያስከብሩም። እንዴት ኢየሱስን በትክክል ወይም ብቃት ባለው መንገድ መግለጥ ወይም መሣል ይቻላል? መጀመሪያ፥ በአሁኑ ጊዜ ከሚኖሩ ሰዎች ኢየሱስን ያየ ስለሌለ ምን እንደሚመስል አናውቅም። ሥዕሉን መሥራት የምንችለው ባሕላዊ አስተሳሰባችንን መሠረት በማድረግ ብቻ ነው። ሁለተኛ፥ ኢየሱስ ከሰው ብልጫ ያለው ነው። እርሱ አምላክ ነው። እንደ አምላክነቱ ክብሩን፥ ኃይሉን፥ ችሉታውን፥ ግርማ ሞገሱን፥ ቅድስናውንና ፍቅሩን ወዘተ. በሚገባ ልንገልጥ አንችልም። 
 3. ሥዕሎች ለክርስቲያኖች በቀላሉ የማሰናከያ ዓለት ሊሆኑ ይችላሉ፤ በመጀመሪያ፥ የኢየሱስን ሥዕል ስንሰቅል መጥፎ ነገር ሆኖ ላይሰማን ይችላል። ስለ ኢየሱስ «እንድናስብና» ሕልውናው «እንዲሰማን» ብቻ ያደርጋል እንላለን። ወዲያውኑ ግን ወደ ኢየሱስ ምስል መጸለይ እንጀምራለን፤ በአእምሮአችንም ውስጥ ያ ሥዕል ይቀረፃል። እንግዲህ የምንጸልየው ለምስሉ እንጂ ለኢየሱስ አይደለም ማለት ነው። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሁሉ የሚታየው የክርስቲያኖች ዝንባሌ ሥዕሎችን ወደሚመለክ ነገር መለወጥ ነው። ይህ ደግሞ በተለይ በካቶሊክና በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ይታያል።

የውይይት ጥያቄ፥ አንዳንድ የኦርቶዶክስ አማኞች ሥዕሎችን ወይም ሐውልቶችን ሲያመልኩ እንዴት እንዳየህ ግለጥ። ይህ እግዚአብሔርን የሚያስከብር ነው ወይስ የሚያዋርድ? 

 1. ሥዕሎች መጥፎ ምስክርነትን የሚያሳዩ ናቸው። በተለይ ሥዕል የምናመልክ ለሚመስላቸው ሙስሊሞችና አንዳንድ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች መጥፎ ምስክርነት ይሆናሉ። ሥዕሎች በእምነታችንና በምስክርነታችን ላይ የሚያመጡት አደጋ ሊሰጡን ከሚችሉት ከማንኛውም ዓይነት ጥቅም ይልቅ የሚያመዝን ነው። ስለዚህ እነዚህን ሥዕሎች በቤተ ክርቲያንም ሆነ በቤታችን አለመስቀል የሚመረጥ ይመስላል።

እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ የወጡበት ጊዜ

እስራኤላውያን ግብፅን ለቀው ወደ ከነዓን መጓዝ ስለ ጀመሩበት ጊዜ ምሁራን ያለማቋረጥ ይከራከራሉ። ሁሉም ምሁራን የሚስማሙት ይህ ነጻ የመውጣት ተግባር የተፈጸመው ከ1450-1200 ዓ.ዓ. ባለ ጊዜ እንደ ሆነ ነው። ምሁራን የሚቀበሉዋቸው ሁለት ዋና ዋና ጊዜያት አሉ። በመጀመሪያ፥ የኋለኛ ጊዜያትን የሚቀበሉትን እናገኛለን። እነዚህ ምሁራን የዘጸአት ታሪክ የተፈጸመው ልክ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈው አይደለም ይላሉ። ጊዜን በሚመለከትም ኦሪት ዘጸአት ሕዝቡ ከግብፅ የወጡበትን ትክክለኛ ቀን አልዘገበም በማለት የሚተማመኑትና ምክንያት የሚያቀርቡትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ በከርሰ-ምድር ጥናትና በታሪካዊ መረጃዎች ላይ በመመሥረት ነው። ስለዚህ ከግብፅ የመውጣት ታሪክ የተፈጸመው በ1321-1205 ዓ.ዓ. አካባቢ እንደሆነ ይናገራሉ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የሚያምኑ ምሁራን ከግብፅ የመውጣት ታሪክ የተፈጸመው ቀደም ብሎ ነው በማለት ቀኑን ወደ 1450 ዓ.ዓ. ይወስዱታል። ይህንን ቀን የመረጡበት ምክንያት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ጥቅሶች ሳቢያ ነው፤ እነርሱም፡- መሳ. 11፡26 እና 1ኛ ነገሥ. 6፡1 ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ መሳ. 11፡26ና 1ኛ ነገ. 6፡1 አንብብ። እነዚህ ቁጥሮች እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ ምን ያህል ጊዜ አልፎአል ይላሉ? 

በመሳ. 11፡26 እስራኤላውያን አንዳንድ ከተሞችን ለ300 ዓመታት ይዘው እንደነበር ይናገራል። ስለዚህ ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ ስናየው እስራኤል ከነዓንን በኢያሱ አማካይነት ከወረሱ 300 ዓመታት አልፈዋል ማለት ነው። ይሁን እንጂ በመሳፍንት ያለውን ጊዜ ጥርት አድርጎ ለመግለጽ አስቸጋሪ ስለሆነ፥ እስራኤላውያን ከግብፅ የወጡበትን ቀን ለመወሰን አይረዳንም።

በ1ኛ ነገሥ. 6፡1 ደግሞ ከግብፅ የመውጣት ታሪክ ከተፈጸመ 480 ዓመታት ማለፋቸውን ይናገራል። ይህም ቀን እስራኤላውያን ከግብፅ የወጡበትን ጊዜ በበለጠ ቅርበት ለመወሰን ይረዳናል። ምሁራን ከተለያዩ መረጃዎች በመነሣት የሰሎሞን መንግሥት አራተኛው ዓመት 966 ዓ.ዓ. እንደሆነ አረጋግጠዋል። ስለዚህ ከግብፅ የመውጣት ታሪክ የተከናወነው ከ480 ዓመታት በፊት ከሆነ የተፈጸመው በ1446 ዓ.ዓ. አካባቢ ነው ማለት ነው። ይህም እስራኤላውያን ከግብፅ የወጡበት ጊዜ እንደሆነ ልንጠራጠር የምንችልበት ምክንያት የለም። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኦሪት ዘጸአት መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከሁሉም በላይ አስፈላጊ የሆነና በሕይወትህ የተፈጸመ መንፈሳዊ ክስተት ምንድን ነው? ለ) ይህ ለአንተ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ስለዚህ ጉዳይ እግዚአብሔርን በጸሎትና በመዝሙር ምን ያህል ጊዜ ታመሰግነዋለህ?

ብዙዎቻችን በሕይወታችን የተፈጸመውና ከሁሉ በላይ አስፈላጊ የሆነው መንፈሳዊ ክስተት  ድነታችን (ደኅንነታችን) ነው በማለት ነው ለላይኛው ጥያቄ መልስ የምንሰጠው። ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናስብ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል የወሰነበትን ጊዜ እናስታውሳለን። ብዙዎቻችን ስለ ድነታችን በጸሎታችን ወይም በመዝሙር እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን።

አይሁድ፥ በታሪካቸው ከሁሉም አብልጠው የሚያስታውሱት አንድ ድርጊት ነበር። ያም ድርጊት እግዚአብሔር ከባርነት ነፃ አውጥቶአቸው በምድረ በዳ ወደ ሲና ተራራ፥ ከዚያም ወደ ከነዓን የመራበት ነበር። ይህ ታሪክ በኦሪት ዘጸአት ውስጥ ይገኛል። በመዝሙረ ዳዊትና በነቢያት መጻሕፍት ጸሐፊዎቹ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ከባርነት ነፃ አውጥቶ ወደ ከነዓን ስለ መራበት ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለው ይጠቅሳሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- መዝ. 78ን ተመልከት። ይህ ምዕራፍ የሚናገረው ስለየትኛው ታሪካዊ ድርጊት ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) «መቤዠት» የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? ለ) «መቤዠት» የሚለውን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልከት። ሐ) እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ነፃ ስላወጣበት ድርጊት ይህ ቃል ለምን ተጠቀሰ? መ) ይህ ቃል ስለ ክርስቲያኖች ድነት (ደኅንነት) ለመናገርስ ለምን አገለገለ?

ኦሪት ዘፍጥረትና ሌሎች የታሪክ መጻሕፍት ያካተቱት የብዙ ዓመታትን ታሪክ ሲሆን፥ ከኦሪት ዘጸአት እስከ ኦሪት ዘዳግም ያለው ታሪክ ግን በ50 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተፈጸመ ነው። እንዲያውም ከዘጸአት እስከ ዘዳግም ባሉት ክፍሎች ውስጥ ከተፈጸመው ታሪክ አብዛኛው የአንድ ዓመት ታሪክ ነው። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከባርነት እንዴት ነፃ እንዳወጣቸው በመናገር ይጀምርና በሲና ተራራ ከእስራኤላውያን ጋር እንዴት ቃል ኪዳን እንደገባ ይተነትናል። ከጠቅላላው የብሉይ ኪዳን ታሪክ አንድ ስድስተኛው (1/6ኛው) በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ስላለፈው ስለዚህ ጊዜ የሚናገር ነው። እስራኤል በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ስላላት ልዩ ስፍራ ለመረዳት ከፈለግን፥ ሕዝቡ ስለሆነው ስለ እስራኤል የሚናገረውን ነገርና አጀማመራቸውም እንዴት እንደነበረ መረዳት የግድ ያስፈልገናል።

እግዚአብሔር እስራኤልን ከባርነት እንዴት ነፃ እንዳወጣና፥ ከዚያም በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት እንዴት እንደተንከራተቱ የሚናገረው ታሪክ በአራት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ተጽፎ እናገኘዋለን፤ ኦሪት ዘጸአት ዘሌዋውያን፥ ዘኁልቁና ዘዳግም። ይህ ታሪክ በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ሊከፈል ይችላል፡-

 1. የእስራኤል ሕዝብ ነፃ መውጣትና ወደ ሲና ተራራ መጓዝ፥ (ዘጸ. 1-18) 
 2. በሲና ተራራ የሕግ መሰጠት፥ (ዘዳ. 19-ዘኁ. 10፡10) 
 3. 40 ዓመታት በምድረ በዳ መንከራተታቸው (ዘኁ. 10፡11 -ምዕራፍ 21) 
 4. የእስራኤል ሕዝብ ወደ ከነዓን ከመግባታቸው በፊት በዮርዳኖስ ወንዝ ዙሪያ ያደረጉት ቆይታ፥ (ዘኁል. 22 – ዘዳ. 34)

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ኦሪት ዘጸአት ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልከት። ስለ ኦሪት ዘጸአት ካነበብካቸው ነገሮች መካከል ዋና ዋና እውነቶች የትኞቹ ናቸው?

የመጽሐፉ ስም 

የውይይት ጥያቄ፥ በአማርኛ «ዘጸአት» ማለት ምን ማለት ነው?

ዕብራውያን (አይሁድ) የፔንታቱክን ሁለተኛ መጽሐፍ በመጀመሪያው ዐረፍተ ነገር «የ … ስሞች እነዚህ ናቸው» ብለው ሰይመውታል። ይህም ስያሜ የተገኘው ከመጽሐፉ የመጀመሪያ ዐረፍተ ነገር ነው። የግሪኩ ሴፕትዋጀንት መጽሐፍ ቅዱስ ግን የመጽሐፉን ርእስ «ዘጸአት» ብሎታል። ለእንግሊዝኛውም ሆነ ለአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ርእስ መሠረት የሆነው ይህ የግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ርእስ ነው። ዘጸአት ማለት «መውጣት» ወይም «መለየት» ማለት ነው። ለሁለተኛው የፔንታቱክ መጽሐፍ ይህ ርእስ የተሰጠበት ምክንያት በውስጡ የሚገኘው ዋናው ታሪክ የሚናገረው እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ በግብፃውያን ባርነት ሥር ከነበሩበት ሁኔታ እንዴት ነፃ እንዳወጣቸውና ከግብፅ ተለይተው ወደ ተስፋይቱ ምድር መጓዝ ስለ መጀመራቸው የሚናገር በመሆኑ ነው። 

ጸሐፊው

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ኦሪት ዘጸአትን እንደጻፈ የሚታመነው ሰው ማን ነው? ለ) ዘጸ. 17፡14፤ 24፡4 አንብብ። እግዚአብሔር ሙሴን ምን እንዲያደርግ አዘዘው? ሙሴስ ምን አደረገ?

ከጥንት ዘመን ጀምሮ አይሁድም ሆኑ ክርስቲያኖች የኦሪት ዘጸአት ጸሐፊ ሙሴ እንደሆነ ይስማሙ ነበር። የእግዚአብሔር ቃል ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ የማያምኑ ምሁራን መጠራጠር የጀመሩት ባለፉት 200 ዓመታት ብቻ ነው።

ስለ ኦሪት ዘጸአት ጸሐፊ ሰዎች ሦስት ዋና ዋና አሳቦች ይሰነዝራሉ።

 1. አንዳንድ ሰዎች የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ኢያሱ ወይም በኢያሱ ጊዜ ሊቀ ካህን የነበረው ኤሊዔዘር ነው ብለው ያስባሉ። ኦሪት ዘጸአትን የጻፈውም ከሙሴና ከአሮን በሰማው አፈ-ታሪክ መሠረት ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ይህን አስተሳሰብ ለመደገፍ ያለው ማረጋገጫ በጣም ጥቂት ነው። 
 2. ጄ.ኢ.ፒ.ዲ. የሚለውን ንድፈ ሐሳብ የሚከተሉ ሰዎች ኦሪት ዘጸአት የተጻፈው በሦስት ዋና ዋና ጸሐፊዎች ነው ይላሉ። እነዚህም «ጄ» ጄሆቫ፥ «ኢ» ኤሎሂም፥ «ፒ» ፕሪስት (ካህን) ተብለው የተሰየሙ ናቸው። የኦሪት ዘጸአት የመጨረሻ ቅጅ የተዘጋጀው ከ600-400 ዓ.ዓ. ከነበረው ጊዜ በፊት አልነበሩም ብለው ያስተምራሉ። ይህ አመለካከት በጣም ጥቂት መረጃ ያለው ሲሆን በርካታ የዘመኑ ምሁራንም አይቀበሉትም።
 3. ሙሴ የኦሪት ዘጸአት የመጀመሪያ ጸሐፊ ነው። ስለዚህ መጽሐፉ የተጻፈው በ1400 ዓ.ዓ. አካባቢ ነው። ሆኖም ሙሴ ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሌሉች አዘጋጆች የኦሪት ዘጸአት ታሪክ ከተፈጸመ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ማንበብ ለሚችሉ አይሁድ የበለጠ ግልጽና በቀላሉ የሚረዱት ለማድረግ አንዳንድ ነገሮችን አክለውበታል። ይህም በሚከተሉት ምክንያቶች ከሁሉ የተሻለው አመለካከት ነው፡-

ሀ. ሙሴ እንዲጽፍ በእግዚአብሔር ታዘዘ። ደግሞም እርሱ እንደጻፈ በግልጥ ተጠቅሷል፤ (ዘጸ. 17፡14፤ 34፡1-5 ተመልከት)። 

ለ. የኦሪት ዘጸአት ጸሐፊ ሙሴ መሆኑን ኢየሱስ በግልጥ ተናግሯል፤ (ማር. 7፡10 ተመልከት)። 

ሐ. ሙሴ በቂ እውቀት ስለነበረውና ስለተፈጸሙት ድርጊቶች ሁሉ ደግሞ የዓይን ምስክር ስለነበር ሊጽፉት ከሚችሉት ሰዎች ዋነኛው እርሱ ነው። 

መ. ከአንዳንድ ክፍሎች በግልጥ እንደምንመለከተው ኦሪት ዘጸአት በኋላ የተነሣ አዘጋጅ እንደገና አቀናብሮታል። የሚከተሉትን ተመልከት፡-

 1. አብዛኛው ታሪክ የሚያወራው ስለ ሙሴ ሲሆን በሙሴ በራሱ የተጻፈ ግን አይመስልም፤ (ምሳሌ፡- ዘጸ. 6፡13፤ 11፡3)። 2. ከሙሴ ሞት በኋላ የተጨመሩ የሚመስሉ መግለጫዎች በበርካታ ስፍራዎች አሉ፤ (ለምሳሌ፡- ዘጸ. 16፡31-36)።

የጸሐፊው የሙሴ ሕይወት

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዘጸ. 2-3 አንብብ። እነዚህ ምዕራፎች ስለ ሙሴ የመጀመሪያዎቹ 80 ዓመታት የሚናገሩትን ዘርዝር። ለ) ስለ ሙሴ በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት የተጻፈውን አንብብ። በጻፍከው ዝርዝር ላይ ስለ ሙሴ ያገኘኸውን ተጨማሪ ነገር ጻፍ።

የኦሪት ዘጸአት ታሪክ የጊዜ ርዝመት 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 1-2፡10 አንብብ። የዘጸአት ታሪክ የሚጀምረው ከምንድን ነው?

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 19 አንብብ። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የእስራኤል ሕዝብ ያለው የት ነው?

የኦሪት ዘጸአት ታሪክ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት እስራኤላውያን በግብፅ ለመኖር እንዴት እንደመጡ አጭር መግለጫ ከሰጠን በኋላ፥ የሙሴን ልደት ታሪክ ይጀምራል። ከዘጸአት እስከ ዘዳግም ባሉት መጻሕፍት ውስጥ ከሁሉም የላቀው ሰብዓዊ ገጸ ባሕርይ ሙሴ ነው። ኦሪት ዘጸአት የሚደመደመው እስራኤላውያን ወደ ሲና ተራራ ደርሰው ሲሰፍሩ ነው። እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን የገባው በዚህ ስፍራ ነው።

የእስራኤል ሕዝብ በሲና ተራራ የሰፈሩት ለአንድ ዓመት ያህል ነው። በዚያም እግዚአብሔር እነርሱን በአስደናቂ ኃይል ተገናኛቸው። የእርሱ ቅዱስ ሕዝብ ሆነው እንዴት እንደሚኖሩ የሚያስረዱ ሕግጋትን ሰጣቸው። ከእርሱ ጋር የሚገናኙበትን የማደሪያውን ድንኳን እንዴት እንደሚሠሩም ነገራቸው። አብዛኛው የዘጸአትና የሌዋውያን ታሪክ የተፈጸመው በሲና ተራራ ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)