የጳውሎስ የግል ምስክርነት፣ ዕቅዶችና ሰላምታ (ሮሜ 15፡14-16፡27)

፩. የጳውሎስ የግል ምስክርነትና ዕቅዶች (ሮሜ 15፡14-33)

የውይይት ጥያቄ፡- ሮሜ 15፡14-33 አንብብ። ሀ) ጳውሎስ ስለ ራሱ የሰጠው መግለጫ ለሮሜ ሰዎች መልእክት የጻፈበትን ሁኔታ የሚያስረዳው እንዴት ነው? ለ) ጳውሎስ ስለ ወደፊት አገልግሎቱ ምን አለ?

ሰዎችንና አሳባቸውን በተሳሳተ መንገድ መረዳቱ ቀላል ነው። ብዙዎቻችን ከሰዎች ቃላት በስተጀርባ የተደበቁትን ፍላጎቶችን እየፈለግን በተሳሳተ መንገድ እንተረጉማለን። ከዚህም የተነሣ በማያስፈልግ መቀያየም ውስጥ እንገባለን። ጳውሎስ በአካል የማያውቁት የሮሜ ምእመናን ትምህርቱን በተሳሳተ መንገድ እንዳይረዱት ሰግቶ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በግልጽና ራሱን ዝቅ አድርጎ አሳቡን ይነግራቸዋል።

ሀ. ጳውሎስ የሮሜን ክርስቲያኖች ድነት (ደኅንነት) ማግኘትና በመንፈሳዊ ባሕርያት የታጀበ ሕይወት መምራታቸውን እንደማይጠራጠር ገልጾአል። መልእክቱን የጻፈላቸው እንደ «የአሕዛብ ሐዋርያነቱ» ኃላፊነቱን ለመወጣት ነበር። ጳውሎስ አሕዛብ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ስለማግኘታቸው ጉዳይ በግልጽ የጻፈው አሳብ የአይሁድ ክርስቲያኖችን ሊያስቀይም እንደሚችል በመገንዘቡ፥ ያስተማረውን ነገር በግልጽ ሊነግራቸው ፈለገ። እግዚአብሔር ለአሕዛብ መልካሙን የምሥራች የማካፈልን ልዩ አገልግሎት ሰጥቶታል። ጳውሎስም የአሕዛብ አማኞችን እንደ ቅዱስ መሥዋዕት በማቅረብ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ፈለገ።

ለ. የጳውሎስ ሸክም በቀዳሚነት ለአሕዛብ የክርስቶስን ወንጌል መስበክ ነበር። በቀዳሚነት ለማገልገል የፈለገው ደግሞ ከዚህ በፊት ወንጌል ባልተሰበከባቸው አካባቢዎች ነበር። ለዚህም ነበር ጳውሎስ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ወደ ሮም ለአገልግሎት ያልሄደው። እግዚአብሔር ጳውሎስ ወንጌሉን ከኢየሩሳሌም ወደ ኤልሪቆም (በሰሜን መቄዶንያ ውስጥ የምትገኝና አሁን በአልባኒያና ዩጎዝላቪያ ውስጥ ያለች ከተማ) በመውሰድ ጥሪውን ከፍጻሜ እንዲያደርስ ረድቶታል። እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተአምራትን እንዲሠራ በማድረግ የጳውሎስን አገልግሎት አጽድቋል።

ሐ. ወንጌሉ ባልተሰበከባቸው አካባቢዎች የማገልገል ጥሪው ከሮም ወደ ምዕራባዊ ጫፍ (ስፔይን) እየወሰደው ነበር። ይህን አገልግሎት በሚያካሂድበት ጊዜ እግረ መንገዱን የሮሜ ክርስቲያኖችን ለማየት ሲወጥን የነበረውን የረዥም ጊዜ ፍላጎቱን ለማሟላት አሰበ። ጳውሎስ በሮሜ ለተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ ክርስቲያኖቹ ወንጌሉን በማሰራጨቱ ረገድ አብረውት እንደሚሠሩ ተስፋ አደረገ። ይህም ለምሥራቃዊ የሮም ክፍል ወንጌሉን በመስበኩ በኩል የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ያበረከተችውን አስተዋጽኦ የሚመስል ነበር (ፊልጵ. 4፡10-18)።

መ. ጳውሎስ ወደ ሮሜ ከመሄዱ በፊት የመቄዶንያ (ሰሜን ግሪክ) እና አካይያ (ደቡብ ግሪክ) አሕዛብ ክርስቲያኖች ለድሀ የአይሁድ ክርስቲያኖች ያወጡትን ስጦታ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዞ ነበር። በአካል ባንተዋወቅም እንኳን የክርስቶስ አካል ክፍሎች የሆንን ሁሉ እርስ በርሳችን ልንረዳዳ ይገባናል። የአይሁድ ክርስቲያኖች ለአሕዛብ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ በረከትን ስላመጡ፥ በአሕዛብ ክርስቲያኖች የገንዘብ ችግር ለደረሰባቸው አይሁዳውያን ድሆች እርዳታ መሰጠቱ ተገቢ ነበር።

ሠ. ጳውሎስ የሮሜ ክርስቲያኖች እንዲጸልዩለት ጠየቀ። ለሌሎች መጻለይ በአገልግሎታቸው ውስጥ ከምንሳተፍባቸው መንገዶች አንዱ መንገድ ነው። የጳውሎስ ጭንቀት ምን ነበር? በመጀመሪያ፥ በኢየሩሳሌም ሊያጠፉት ስለሚፈልጉ የማያምኑ አይሁዶች ያስብ ነበር። ሁለተኛ፥ በኢየሩሳሌም የሚገኙ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በአሕዛብ ክርስቲያኖች ላይ መጥፎ ስሜት ይዘው የሚያመጣላቸውን ስጦታ ላለመቀበል እንዳይወስኑ ሰግቶ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሮሜ 16ን አንብብ። በዚህ የሰላምታ ምዕራፍ ውስጥ የሚገኙትን ለየት ያሉ ነገሮች ዘርዝር።

፪. ጳውሎስ በሮሜ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚያውቃቸው ሰዎች ያቀረበው ሰላምታ (ሮሜ 16)

ጳውሎስ በሮሜ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚያውቃቸው ሰዎች ሰላምታ በማቅረብ መልእክቱን ይደመድማል። እንዲህ ዓይነት ረዥም የሰላምታ ዝርዝር በጳውሎስ ጽሑፎች ውስጥ ያልተለመደ በመሆኑ፥ ምሁራን ጳውሎስ በአካል ባይጎበኛቸውም የሮሜን ክርስቲያኖች እንደሚያውቃቸው ለማሳየት እየሞከረ ነበር ይላሉ። ነገር ግን በሮሜ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከነበሩት ብዙ ሰዎች ጋር ጥልቅ ግላዊ ወዳጅነት ነበረው።

ሀ. ፌቤን ከቆሮንቶስ ከተማ 8 ኪሎ ሜትሮች ያህል ወጣ ብላ በምትገኝ የክንክራኦስ ከተማ የምትኖር ክርስቲያን ነበረች። የጳውሎስን መልእክት ወደ ሮም ያደረሰችው እርሷው ነበረች። ጳውሎስ እንደ ዲያቆንና ልዩ የክርስቶስ አገልጋይ እንዲቀበሏት ጠይቋቸዋል።

ለ. ጳውሎስ ለሚከተሉት ወገኖችም ልዩ ሰላምታ ልኮላቸዋል (ሮሜ 16፡1-16)።

 1. ወደ ሮም ለተመለሱት ጵርስቅላና አቂላ፡- እነዚህ ልዩ የጳውሎስ ወዳጆች ሕይወታቸውን ከአደጋ ላይ እየጣሉ ሁልጊዜም ከጳውሎስ ጎን የቆሙ ሲሆን፥ ለግሪክና ለትንሹ እስያ አብያተ ክርስቲያናት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። እንደ ጳውሎስ ያሉት ታላላቅ ወንጌላውያን ተግባራቸውን የሚወጡት ብቻቸውን አልነበረም። እግዚአብሔር ሁልጊዜም ወንጌላውያንን የሚረዱ ሰዎችን ያመጣል። ያለ እነዚህ ወገኖች እገዛ ቤተ ክርስቲያን ልታድግ አትችልም። ወንጌሉን በማሰራጨቱ ረገድ እግዚአብሔር አቂላና ጵርስቅላን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቅሞባቸዋል። አሁንም እንኳ እግዚአብሔር እየተጠቀመባቸው ነበር። ምንም እንኳ የሙሉ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ያልነበሩ በድንኳን ሰፊነት የሚተዳደሩ ቢሆኑም፥ እግዚአብሔር መንግሥቱን ለማስፋፋት ተጠቅሞባቸዋል። በሮም በቤታቸው ውስጥ የቤተ ክርስቲያን አምልኮ ይካሄድ ነበር።
 2. አጤኔጦን ኤፌሶን በምትገኝበት የእስያ አውራጃ የመጀመሪያው አማኝ ነበር። ማርያ ለሮሜ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ዕድገት ተግታ ትሠራ ነበር።
 3. አንዲራኒቆንና ዩልያን ምናልባትም የጳውሎስ ዘመዶች የሆኑ ባልና ሚስት ሳይሆኑ አይቀሩም። ከጳውሎስ ጋር ታስረው የነበሩ ሲሆኑ፥ ሐዋርያት ተብለው ተጠርተዋል። ምሁራን ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ምን ማለቱ እንደሆነ ይከራከራሉ። እነዚህ ሁለት ሰዎች «ዘመዶቹ» የሆኑት አይሁዶች በመሆናቸው ነው ወይስ የጳውሎስ የሩቅ ዘመዶች ይሆኑ? ከጳውሎስ ጋር አብረውት የታሰሩት የት ነበር? ስማቸው በሐዋርያት ሥራ ውስጥ አልተጠቀሰም። ጳውሎስ ሐዋርያት ብሎ ሲጠራቸው ምን ማለቱ ነው? ምናልባትም ጳውሎስ የቃሉን ሰፊ ትርጉም በመውሰድ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ምሥረታ እንደተጠቀመባቸው መግለጹ ይሆናል። እነዚህ ሁለቱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይህንን ስጦታ ተቀብለው ነበር (ሴቷ ዩልያ «ሐዋርያ» እንደተባለች ልብ በል)
 4. ኢሩባኖን፥ ጵልያጦን፥ ስንጣክን፥ ኤጤሌን የሚሉት ስሞች ሁሉ በሮም ቤተ መንግሥት ውስጥ የታወቁ የባሪያዎች ስሞች ነበሩ። ይህም ወንጌሉ በኔሮ ቤተ መንግሥት እንዴት ሥር ሰድዶ እንደገባ ሊያሳይ ይችላል። ጳውሎስ በኋላ ታስሮ ሳለ ለኔሮ የግል ጠባቂዎች መስክሮላቸዋል (ፊልጵ. 1፡13)።
 5. አርስጣባሉስ ምናልባትም የታላቁ የሄሮድስ የልጅ ልጅና የሄሮድስ አግሪጳ ቀዳማዊ ወንድም ሳይሆን አይቀርም። ይህም ወንጌሉ ወደ ቤተ መንግሥቱ ባለሥልጣናትም እንደደረሰ ያሳያል።
 6. ፕሮፊሞና፥ ጢሮፊሞሳ (ምናልባትም እኅትማማቾች) እና ጠርሲዳ ለጌታ ባበረከቱት አገልግሎት የሚታወቁ ሴቶች ነበሩ።)

ሐ. ጳውሎስ እነዚህ ክርስቲያኖች የሐሰት ትምህርትን እንዳያምኑ ያስጠነቅቃል (ሮሜ 16፡17-20)። ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍል ትምህርት ከሚያስተምሩ ሰዎች መራቅ ያስፈልጋቸው ነበር። ይህ ዛሬ ለእኛም ጥሩ ማስጠንቀቂያ ነው። በጳውሎስ ዘመን የሐሰት አስተማሪዎች እንደነበሩ ሁሉ፥ በዘመናችንም አሉ። የሐሰት አስተማሪዎችን እንዴት ለይተን እናውቃለን? ቀዳሚው መለያ ክብሩን ማን እንደሚወስድ ማጤን ነው። አንዳንድ ሰዎች አንደበተ ርቱዕ ሆነው በመቅረብ ብዙዎችን ቢያታልሉም፥ ራሳቸውን እንጂ ክርስቶስን አያከብሩም። አንዳንድ ጊዜ አስተማሪዎች በሌሎች ኪሳራ ባለጸጋ ይሆናሉ። ክርስቲያኖች ራሳቸውን መጠበቅ ያለባቸው እንዴት ነው? ከእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ጋር ግንኙነት ወይም ኅብረትን ባለመፍጠር ነው። ጳውሎስ በክርስቲያናዊ አንድነት ላይ አጽንኦት ሰጥቷል። ነገር ግን አንድነትና ኅብረት ሊያደርጉ የሚገባቸው እግዚአብሔርን ለማክበር የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። ክርስቲያኖች ነን እያሉ አንድነትን የሚያሰናክሉና የሐሰት ትምህርትን የሚያስፋፉ ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት ውጭ መሆን አለባቸው። አለበለዚያ ከእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ጋር ኅብረት ማድረጉ ለእነርሱ የተሳሳተ ሃሳብ ረዳት መሆን ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ቤተ ክርስቲያንህን የሚያስቸግሩትን አንዳንድ የሐሰት አስተማሪዎች ዘርዝር። ለ) ሌሎች ክርስቲያኖችና ሽማግሌዎች እንዴት እየተቀበሏቸው ነው? ሐ) ጳውሎስ እነዚህን የሐሰት አስተማሪዎች እንዴት እንድንቀበላቸው የሚፈልግ ይመስልሃል? መ) ዛሬ ያንን ለማድረግ የማንፈልገው ለምንድን ነው?

መ. ጳውሎስ ሰላምታ ያስተላልፋል (ሮሜ 16፡21-24)።

 1. ጢሞቴዎስ ወንጌሉን በማሰራጨቱ በኩል የጳውሎስ ረዳትና የሥራ ባልደረባ።
 2. ሉቂዮስ፥ ኢያሶን፥ ሱሲጴጥሮስ- ምናልባትም የቆሮንቶስና የመቄዶኒያ አብያተ ክርስቲያናት ዐበይት መሪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም (የሐዋ. 17፡5-9፤ 20፡4)።
 3. ጤርጥዮስ፥ የጳውሎስን መልእክት ጸሐፊ።
 4. የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መሪና ብዙውን ጊዜ ታይተስ ጆስትስ በመባል የሚታወቀው ጋይዮስ (የሐዋ. 18፡7፤ 1ኛ ቆሮ. 1፡14)።
 5. በቆሮንቶስ መንገዶች ጨምሮ ብዙ ጉዳዮችን የሚያስፈጽም ቁልፍ የፖለቲካ መሪ የሆነው ኤርስጦስ። ኤርስጦስ አማኝ መሆኑ አያጠራጥርም።

ሠ. ጳውሎስ መልእክቱን በቡራኬ ይደመድማል (ሮሜ 16፡25-27)። የሮሜ መልእክት በወንጌል ላይ ያማከለ መጽሐፍ ነው። የወንጌሉም አሳብ በዚህ የማጠቃለያ ቡራኬ ላይ ያማክላል። ክርስቶስ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ ከሰዎች በምሥጢርነት ተሰውሮ የነበረው ወንጌል አሁን ተገልጧል። የእግዚአብሔር ፍላጎት ሰዎች በክርስቶስ አምነው የታዛዥነትን ሕይወት እንዲመሩ ነበር። የሮሜን ክርስቲያኖች በዚህ ወንጌል የሚመሠርታቸው ደግሞ እግዚአብሔር ነበር። የጳውሎስ ትልቁ ፍላጎት የእግዚአብሔር ለዘላለም መክበር ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ እግዚአብሔርን የምናስከብርባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) ይህ እንዴት የሕይወታችን ዋነኛ ዓላማ መሆን እንዳለበት ግለጽ። ሐ) በምታደርገው ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብርን እያመጣህለት እንደሆነ በጸሎት ጠይቀው። ዛሬ ለእርሱ ክብር ለመኖር ራስህን እንደገና አሳልፈህ ስጥ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ክርስቲያኖች የተለየ አመለካከት ያላቸውን ክርስቲያኖች የሚያስቀይም ነገር ባለማድረግ ፍቅራቸውን ያሳያሉ (ሮሜ 13፡14-15፡13)

ሰላማዊት በአጥባቂ ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ክርስቲያን ነበረች። ጥሩ ክርስቲያኖች ጌጣጌጥ እንደማይጠቀሙ፥ ከንፈራቸውንም ሆነ ጥፍራቸውን ቀለም እንደማይቀቡ፥ ፊልም ቤት እንደማይሄዱ፥ ፋሽን ልብስ እንደማይለብሱ፥ በቤተ ክርስቲያን ስካርፎችን እንደማይለብሱ፥ ወዘተ… ገና በትንሽነቷ ተምራለች። ፍቅርተ ደግሞ ክርስቲያን ባልሆኑ ሀብታም ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ሴት ነበረች። ሁልጊዜም ሕይወቷ በፋሽን ልብሶች፥ ጌጣጌጦች፥ ፊልሞች፥ የፀጉር ስታይሎች፥ ወዘተ… የታጀበ ነበር። ፍቅርተ ክርስቲያን ስትሆን፥ እነዚህ ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ስላልተከለከሉ መተው አለብኝ ብላ አላሰበችም። አንድ ቀን የአንድ ቤተ ክርስቲያን መእመናን የነበሩት ሰላማዊትና ፍቅርተ መነጋገር ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ሰላማዊት ለፍቅርተ፥ «ከአለባበስሽ እንደምረዳው፥ አንቺ ጥሩ ክርስቲያን አይደለሽም አለቻት።

ይህ ወደ ትልቅ ፀብ በመለወጡ፥ ሰላማዊትና ፍቅርተ ከመነጋገርና በጸሎት ከመተጋገዝ ታቀቡ። ይባስ ብለውም በጓደኞቻቸው መካከል አንዳቸው ስለሌላቸው መጥፎ ወሬዎችን ያዛምቱ ጀመር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጥሩ ክርስቲያን ሊያደርግ በሚችላቸውና በማይችላቸው ነገሮች ላይ የሚከሰተው የአሳብ ልዩነት ክፍፍልን ሲፈጥር የተመለከትከው እንዴት ነው? ለ) ጳውሎስ በሮሜ 14፡1–15፡13 ባስተማረው አሳብ መሠረት፥ ለሰላማዊትና ፍቅርተ ምን ምክር ትሰጣለህ? ሐ) ክርስቲያኖች በአሳብ የሚለያዩባቸውን ሌሎች ልምምዶች ዘርዝር።

ሁልጊዜም ክርስቲያኖች የትኞቹን ልምምዶች ሊያደርጉ እንደሚገባቸው ወይም እንደማይገባቸው በአሳብ መለያየታቸው የማይቀር ነው። በተለይም ልምምዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ካልተብራሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ዝሙት ኃጢአት እንደሆነ በግልጽ ስለሚያስተምር ብዙ ክርስቲያኖች በዚህ ጉዳይ ላይ አይከራከሩም። ነገር ግን ሌሎች ሰላማዊትና ፍቅርተ ያነሡዋቸው ዓይነት ጉዳዮች ቤተ ክርስቲያንን እስከ መከፋፈል ድረስ ይደርሳሉ። ለምሳሌ፥ አንዳንድ ክርስቲያኖች ምንም ዓይነት የአልኮል መጠጥ መጠጣት የለብንም ሲሉ፥ ሌሎች ደግሞ አልኮል መጠጣት ኃጢአት እንዳልሆነ ያስረዳሉ። በክርስቲያኖች መካከል መከፋፈልን የሚፈጥሩትን ጉዳዮች እንዴት ልናስተናግዳቸው ይገባል?

በሮሜ 14፡1-15፡13፥ ጳውሎስ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያልጠቀሳቸው ነገሮች የአሳብ ልዩነቶችን በሚያስከትሉበት ጊዜ ክርስቲያኖች እንዴት አንድነታችንን ጠብቀን ልናቆይ እንደምንችል አብራርቷል። በሮምና ከፍልስጥኤም ውጭ ባሉት አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አይሁዶችና አሕዛብ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያመልኩ ነበር። ሁልጊዜም በሁለቱ ወገኖች መካከል የአሳብ ልዩነቶችን የሚያስከትሉ ባሕላዊ ልምዶች ነበሩ። ከእነዚህ ጉዳዮች አንዱ ክርስቲያኖች በገቢያ ውስጥ የሚሸጥ ሥጋ መብላት ይችላሉ ወይ? የሚል ነበር። በገበያ ውስጥ ከሚሸጥ ሥጋ አብዛኛው በሚታረድበት ጊዜ ለጣዖት የተሠዋና ከፊሉ ለጣዖት አምልኮ ያገለገለ ነበር። የተቀረው ገበያ ውስጥ ይሸጣል። የአይሁድ ክርስቲያኖችና አንዳንድ አሕዛብ ክርስቲያኖች ይህን ለአረማዊ ጣዖት የተሠዋ ሥጋ መብላት ትክክል አይደለም የሚል አሳብ አቀረቡ። ለእነርሱ ሥጋውን መብላት በጣዖት አምልኮ እንደ መካፈል ቆጠሩት። ብዙ ክርስቲያኖች ደግሞ ሥጋውን መብላት ምንም ስሕተት መስሎ አልታያቸውም። «ሥጋ ሥጋ ነው። ጣዖታትን በፈቃዳችን እስካላመለክን ድረስ ሥጋውን ልንበላ እንችላለን። ሥጋውን በላን ማለት ጣዖት አመለክን ማለት አይደለም» ሲሉ አስተማሩ። ይህ በገበያ ላይ የሚሸጠውን ሥጋ ስለመብላት የቀረበው ሁለት ዓይነት አመለካከት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍልን አስከተለ። (ይህ በደቡብ ኢትዮጵያ የመስቀል በዓል ምግብ ስለመብላት ከሚነሣው ክርክር ጋር ተመሳሳይ ነው።) ቅዳሜ ወይስ እሑድ ልናመልክ ይገባል? የሚሉ ዓይነት ሌሎች ጉዳዮችም ክፍፍል አስከትለዋል።

ስለሆነም፥ ጳውሎስ የሮሜ ክርስቲያኖች ችግሩን ማስገናገድ እንደሚገባቸው ለሮሜ ክርስቲያኖች ጽፎላቸዋል። (ጳውሎስ ቀደም ሲል ለጣዖት የተሠዋን ምግብ ስለመብላት በ1ኛ ቆሮንቶስ 8-10 ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን አብራርቷል። በሮም የተከሰተው ችግር ደግሞ ከሥጋ በተጨማሪ የአምልኮ ቀንንም ያካትት ነበር።)

ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች ያስተማራቸውን መርሆች መረዳት ጠቃሚ ነው። ሁልጊዜም ጥሩ ክርስቲያኖች ሊያደርጉ በሚገቧቸውና በማይገቧቸው ጉዳዮች ላይ የአመለካከት ልዩነቶች መከሰታቸው የማይቀር ነው። ጳውሎስ የጠቀሳቸውን መሮሆች ካላወቅን በቤተ ክርስቲያናችን ወይም በክርስቲያኖች መካከል ክፍፍል በመፍጠር፥ ከሌሎች ክርስቲያኖች የተሻልን ነን የሚል የትዕቢት አመለካከት በመያዝ፥ ወይም የጥሩ ክርስቲያንነት ማረጋገጫዎች ናቸው የምንላቸውን የ«አድርጉ/አታድርጉ» ትእዛዛት በመዘርዘር ችግሮችን ልንጋብዝ እንችላለን። ሁልጊዜም መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊነት የልብ ጉዳይ እንጂ የውጫዊ ተግባራችን መግለጫ አለመሆኑን ያስረዳል። በቀዳሚነት ክርስቲያንነታችንን የምናሳየው በምናደርገው ወይም በማናደርጋቸው ነገሮች ሳይሆን፥ በሮሜ 12-13 እንደተገለጸው ከሌሎች ሰዎች ጋር በምንዛመድበት ሁኔታና በልባችን ዝንባሌዎች ነው።

ከዚህ በታች ጳውሎስ ያስተማራቸው ስምንት ዐበይት እውነቶች ቀርበዋል።

ሀ. ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ባላስተማረው ጉዳይ ላይ በአሳብ በሚለያዩበት ጊዜ፥ ሁልጊዜም «ደካማ» እና «ጠንካራ» ክርስቲያኖች ይኖራሉ። ደካማና ጠንካራ የሚሉት ቃላት አንዱ ከሌላኛው የበለጠ መንፈሳዊ መሆኑን አያሳዩም። ጳውሎስ እንደሚለው፥ «ደካማ» ክርስቲያኖች መልካም ክርስቲያኖች የተወሰኑ ነገሮችን ማድረግ የለባቸውም የሚል አቋም ሲይዙ፥ «ጠንካሮች» ክርስቲያኖች እነዚህን ነገሮች ለማድረግ እንደተፈቀደላቸው ያምናሉ።

ለ. መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ በማያስተምራቸው ጉዳዮች ላይ የአሳብ ልዩነት በሚከሰትበት ጊዜ፥ ሁለቱም ወገኖች ከእነርሱ በአሳብ የተለየውን ወገን ከመተቸትና መንፈሳዊ አይደለም ከማለት መቆጠብ አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ባላስተማራቸው ጉዳዮች ላይ ክርስቲያኖች ነጻነት አላቸው። ያለማድረግ (አትክልት ብቻ የመመገብ) ወይም የማድረግ (ሥጋ የመብላት) ነጻነት አለን።

ሐ. ግልጽ ባልሆኑት ጉዳዮች ላይ ተመሥርተን የአንድን ሰው መንፈሳዊ ሁኔታ ከመመዘን የምንጠነቀቅባቸው ሁለት ምክንያቶች አሉ። ሀ) የሰውን ልብና አመለካከት ለመለካት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለሆነም፥ እውነተኛ መንፈሳዊነት የሚገኝበት ልቡን ስለማናውቅ፥ በአከራካሪ ጉዳዮች ላይ ተመሥርተን ግለሰቡን ልንጠራጠር አይገባም። ለ) የኋላ ኋላ፥ ሁሉም ክርስቲያን የእግዚአብሔር ባሪያ ስለሆነ ተጠያቂነቱ ለእርሱ ነው። አንድ አማኝ በእንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ላይ አቋም እንዲይዝ መምራቱ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ወይም የሌሎች ክርስቲያኖች ሳይሆን የእግዚአብሔር ኃላፊነት ነው። ፈራጅ ክርስቶስ እንጂ እኛ አይደለንም።

መ. ክርስቲያኖች በአንድ ልምምድ ላይ በሃሳብ በሚለያዩበት ጊዜ፥ በሁለቱም ወገን የሚገኙ ሰዎች በሚያደርጉት ነገር እግዚአብሔርን እያከበሩ ለመሆናቸው እርግጠኞች መሆን አለባቸው። ቢራ መጠጣት ትክክል ነው ብለው ቢያስቡና ቢራ የሚጠጡትን ክርስቲያኖች ምሳሌነት መከተል ቢጀምሩ፥ ዳሩ ግን ልባቸው ውስጥ ጥርጣሬ ካለ ኃጢአትን ሠርተዋል ማለት ነው። ኃጢአትን የሠሩት ቢራ በመጠጣታቸው ሳይሆን ትክክል ስላልሆነውና ስለሆነው ጉዳይ አቋም ባለመውሰዳቸው ነው። ያለ እምነት የምናደርገው ነገር ሁሉ ኃጢአት ነው።

ሠ. የክርስቲያኖች ሁሉ ትልቁ ፍላጎት «እግዚአብሔርን ማስደሰት» ሊሆን ይገባል። ከእሑድ ቀጥሎ ባለው ቀን አምልኮ ለማካሄድ፥ የተወሰነ ምግብ (ለምሳሌ የእስላም ሥጋ፥ የርኩስ እንስሳት ሥጋ) ለመብላት፥ ወይም የተወሰነ ልብስ ለመልበስ ብንፈልግ፥ «በማደርገው ነገር ለእኔ ሲል የሞተውን ክርስቶስን እያስደሰትሁት ነው?» ብለን ልንጠይቅ ይገባል።

ረ. ክርስቲያኖች ሁሉ ለምናካሂዳቸው ልምምዶችና የእኛን ዓይነት እምነት ለማይከተሉ ክርስቲያኖች ለምንይዛቸው አመለካከቶች ተጠያቂዎች እንደምንሆን መገንዘብ አለብን። ሁላችንም በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት ስለምንቆም፥ ለተግባራችንና ለአስተሳሰባችን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።

ሰ. ለክርስቲያኖች አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ፍቅርና ለሌሎች መስጠት ስለሆነ፥ ተግባራችን ሌሎች ክርስቲያኖችን በመጉዳት ወደ ኃጢአት እየመራቸው አለመሆኑን ማረጋገጥ አለብን። በፍቅር መኖር፥ በእምነት ለማደግ መደጋገፍና አንድነትን መፍጠር ከነጻነቶቻችን፥ ከግል መብቶቻችንና እምነቶቻችን በላይ ጠቃሚዎች ናቸው። ቀዳሚው ምስክርነታችንና ክርስቶስን የምናስከብርበት መንገድ የሚገለጸው የግል እምነቶቻችንና መብቶቻችንን በማሳየት ሳይሆን፥ በፍቅራችንና በአንድነታችን ነው።

ሸ. ከየትኛውም ጎሳ ብንመጣ (ለምሳሌ አይሁዳዊ፥ አሕዛብ፥ አማራ፥ ኦሮሞ) ወይም በተለያዩ ልምምዶች ላይ የትኛውንም አቋም ብንይዝ፥ ክርስቶስ ሁለቱንም አቋማት ለሚይዙ ክርስቲያኖች ስለ ሞተ፥ አንድነታችንን ልናጠብቅ ይገባል። የአይሁድ ክርስቲያኖች እነርሱ የማይቀበሏቸውን ነገሮች ስለሚያደርጉ ከአሕዛብ ክርስቲያኖች መለየት አልነበረባቸውም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቅርቡ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የተከሰተውን ዐቢይ ክፍፍል ግለጽ። ለ) እነዚህን እውነቶች ተግባራዊ ማድረግ ያንን ክፍፍል በመቀነስ አንድነትን ሊያመጣ የሚችለው እንዴት ነው? ሐ) የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ወይም ክርስቲያኖች የሚከራከሩባቸውን ልምምዶች ዘርዝር። ጳውሎስ ባስተማራቸው በእነዚህ እውነቶች መሠረት ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ምላሽ ሊሰጡ ይገባል? በእነዚህ ትምህርቶች ምክንያት በሰዎች እምነቶችና ተግባራት ላይ ምን ምን ለውጦች ይከሰታሉ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

አማኞች ባለሥልጣንት የሚታዘዙና በፍቅር የሚመላለሱ ናቸው (ሮሜ 13፡1-13)

፩. አማኞች ለሰብአዊ መንግሥታቸው ይጸልያሉ፥ ይታዘዛሉ (ሮሜ 13፡1-7)

እንደ ወንጌላዊያን ክርስቲያኖች ከመንግሥትና ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የቀረበ ግንኙነት የለንም። በቀደመው ሥርዓት የስደት ምንጮች ሆነው እሠቃይተውናል። አሁን ድምፅ የመስጠት ዕድል ሲሰጠን ደግሞ ብዙ አማኞች ድምፅ ለመስጠት ፈቃደኞች አይደሉም። ለአገልግሎት ሲጠይቁንም አዎንታዊ ምላሽ አንሰጥም። ከመንግሥት በመራቃችን ደስ የምንሰኝ ይመስላል።

ጳውሎስ ግን ከመንግሥት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ሊኖረን እንደሚገባ ይመክራል። ጳውሎስ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ብዙ ጊዜ ስደት እንደደረሰበት አስታውስ። በሮሜ መንግሥት ለአራት ዓመታት ታስሮ ወደ ሚቆይበት የወኅኒ ቤት ይገባ ነበር። ጳውሎስ የሮሜን መልእክት ከጻፈ ከአሥር ዓመታት ያህል በኋላ የሮም ንጉሥ የሞት ቅጣት ፈርዶበታል። ይህም ሆኖ፥ ጳውሎስ ክርስቲያኖች ለመንግሥት መልካም አመለካከት እንዲኖራቸው አስተምሯል። ለምን? ምክንያቱም ኮሚኒስትም ይሁን እንደ የኔሮ ዓይነት ክፉ መንግሥት ይሁን ወይም ጥሩ መንግሥት የትኛውም መንግሥት በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር ነው። ስለሆነም መንግሥትን መቃወም ማለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ መቃወም ማለት ነው። እንግዲህ፥ ክርስቲያኖች ከመንግሥት ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል? ጳውሎስ አያሌ ነገሮችን ጠቃቅሷል።

ሀ. ለመንግሥት ባለሥልጣናት መገዛት አለብን። እነዚህ ባለሥልጣናት መጽሐፍ ቅዱስን በቀጥታ እስካልተቃወሙ ድረስ (የሐዋ. 5፡27-29ን አንብብ።)፥ ሕግጋቱን ባንወዳቸውም እንኳ መፈጸም አለብን። መንግሥት እግዚአብሔር ሕግንና ሥርዓትን ለማስከበር፥ የማኅበረሰቡ እንቅስቃሴ እንዳይደናቀፍ ለማገዝና የክፋትን ስርጭት ለመቋቋም ሲል የመሠረተው ተቋም ነው። ለመንግሥት አለመታዘዝ ማኅበረሰቡን ወደ ሁከት፥ ውድመትና ክፋት ይመራል።

ለ. ቀረጥ መክፈል አለብን። ብዙ ክርስቲያን ነጋዴዎች ለመንግሥት ቀረጥ አይከፍሉም። ጳውሎስ ግን ይህ ስሕተት እንደሆነ ያስረዳል። ሁላችንም መንግሥት የሚያሠራቸውን መንገዶች፥ ትምህርት ቤቶች፥ ሆስፒታሎች፥ ወዘተ… ስለምንጠቀም፥ ለእነዚህ ወጭዎች መሸፈኛ የሚያግዝ ቀረጥ መክፈል አለብን።

ሐ. ክርስቲያኖች መሪዎቻቸውን ማክበር አለባቸው። ጳውሎስ የሚናገረው ስለ ክርስቲያን የመንግሥት መሪዎች ወይም ስለ ጥሩ መሪዎች አይደለም። እርሱ የሚናገረው ብዙውን ጊዜ የራስ ወዳድነት አመለካከት ስላላቸው ክርስቲያን ያልሆኑ መሪዎች ነው። ጳውሎስ ሰዎቹ ጥሩ ናቸው ብለን በማሰባችን ሳይሆን እግዚአብሔር ለመሪነት እንዳስነሣቸው በመገንዘባችን ሁልጊዜም ልናከብራቸው እንደሚገባን ያብራራል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ ለመንግሥት መሪዎች ያለውን አመለካከት ከእኛ አመለካከት ጋር አነጻጽር። ለ) በ1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡1-2 ለባለሥልጣናት እንድንጸልይ ተነግሮናል። ቤተ ክርስቲያንህ ይህንን የምታደርገውና ክርስቲያኖች በቀዳሚነት ለመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲጸልዩ የምታበረታታው እንዴት ነው? ሐ) በቀበሌህ፡ በወረዳህ፥ በክልልህና በፌዴራል ደረጃ ሥልጣን ላይ ያሉትን መሪዎች ስም ዘርዝር። አሁን ጊዜ ወስደህ ለእነዚህ ሰዎች ጸልይላቸው።

፪. የአማኙ ሕይወት በቅርብ በሚሆነው የኢየሱስ መመለስ ብርሃን ሊታይ (ሮሜ 13፡8-13)

ድነት (ደኅንነት) በምናገኘበት ጊዜ የሕይወታችን ክፍሎች በሙሉ መለወጥ አለባቸው። ጳውሎስ የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን ምክንያት የሚለወጡትን ነገሮች ዘርዝሯል።

ሀ. ክርስቲያኖች የተበደሩትን ገንዘብ ሁሉ ሊክፍሉና በተቻለ መጠን ከብድር የጸዳ ሕይወት መምራት አለባቸው። ከሰው ገንዘብም ሆነ ሌላ ነገር ተበድሮ ለመክፈል እየቻሉ ቸል ማለቱ የክርስቲያናዊ ፍቅር ምልክት አይደለም። ይህ ዓለም በሰዎች ትከሻ ላይ ሆኖ ለመጠቀም የምትከተለው አሠራር ነው።

ለ. ከሕግጋት ዝርዝሮች ይልቅ በአመለካከታችን ላይ ልናተኩር ይገባል። አመለካከቶቻችንም አጠቃላይ ግንኙነቶቻችንን፥ ማለትም ባልንጀራን መውደድ (ክርስቲያኖችንም ሆነ ክርስቲያኖች ያልሆኑትን)፥ ለራሳችን የምናደርገውን ያህልና ሌሎችም እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን ጥንቃቄ ለእነዚህ ወገኖች ማድረግ፥ ወዘተ… ያጠቃልላሉ።

ሐ. ክርስቲያኖች ክርስቶስ ዛሬ እንደሚመለስ እያሰቡ ይኖራሉ። ስለሆነም፥ ሕይወታችን ክርስቶስ ሊያጠፋው የመጣበትን የዓለምን ክፋት ከሚያንጸባርቁ ነገሮች ሁሉ ተለይቶ በንጽሕና ሊያዝ ይገባል። ጳውሎስ ክርስቶስን እንድንለብስ አዞናል። ጳውሎስ ይህን ሲል በአመለካከታችንም ሆነ በተግባራችን ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንድናደርጋቸው የሚፈልገውን ነገሮች ብቻ እንድናደርግ መጠየቁ ነው። አሁንም ጳውሎስ የምናስባቸውን ነገሮች እንድንቆጣጠር ማሳሰቡን አስተውል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ እንደ አማኝ ስለመመላለስ ባስተማረው መሠረት፥ አዳዲስ ክርስቲያኖችን ማስተማር የሚያስፈልገው ስለ ምንድን ነው? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ለአዳዲስ አማኞች የምታስተምረው ምንድን ነው? ይህንን ጳውሎስ ካስተማረው ጋር አነጻጽር። ጳውሎስ ለክርስቲያን ሕይወት አስፈላጊ ነው ብሎ ያስተማረውን ሃሳብ ለመከተል ይቻል ዘንድ የቤተ ክርስቲያንህን ትምህርት ለመለወጥ ምን ሊደረግ ይገባል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ወንጌሉ የአማኞችን አኗኗር ይለውጣል (ሮሜ 12፡1-21)

ጥሩነሽ በቅርቡ በክርስቶስ አምናለች። መንፈስ ቅዱስ ኃጢአተኛ እንደሆነችና ይቅርታ ልታገኝ የምትችልበት ብቸኛው መንገድ ለኃጢአት በሞተው በክርስቶስ በማመን መሆኑን ለልቧ መስክሮላታል። ጥሩነሽም በኃጢአተኝነት ስሜት ተሞልታና እግዚአብሔር ለእርሷ ስላለው ፍቅር ተደንቃ ክርስቶስ ለኃጢአቷ የሞተ አዳኝዋና ጌታዋ እንደሆነ አመነች። በዚህ ጊዜ ሰላም ልቧን ሞላው። የእግዚአብሔር ልጅ ሆነች።

ነገር ግን ከዚህ በኋላ ማድረግ ያለባት ነገር ምንድን ነው? አሁን ልጁ ከሆነች በኋላ እግዚአብሔር ምን እንድታደርግ ይፈልጋል? ሕይወቷ እንዴት ሊለወጥ ይገባል? ክርስቲያኖችን ስትጠይቅ ሁሉም ከመጠጥ፥ ከሲጋራ፥ ከጫት፥ ከዘፈን ወደ ፊልም ቤት ከመሄድ፥ ወዘተ… መታቀብ እንዳለባት ይነግሯታል። ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ ዋናው መዳኗ እንደሆነ በመግለጽ ደስ ያላትን ሁሉ ልታደርግ እንደምትችል ይነግሯታል። በእነዚህ የአሳብ ግጭቶች ግራ የተጋባችው ጥሩነሽ ብዙም ሳይቆይ ለእግዚአብሔር የነበራትን ፍቅር አጣች።

የወንጌሉ ተግባራዊ አካል የሆነውን ጉዳይ ብዙውን ጊዜ አናነሣውም። ይህም አዳዲስ ክርስቲያኖች እንደ እግዚአሔር ልጆች እንዴት መመላለስ እንዳለባቸው አለማብራራታችን ነው። ክርስቶስ እርሱን ለመከተል ከመወሰናችን በፊት የደቀ መዝሙርነትን ዋጋ መተመን እንዳለብን ተናግሯል (ሉቃስ 14፡25-33)። ነገር ግን እኛ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በክርስቶስ ለማመን የሚፈልጉ ሰዎች ካመኑ በኋላ ምን እንደሚጠበቅባቸው አናብራራላቸውም። ምናልባትም ብዙዎቹ አማኞቻችን ፈጥነው ወደ ዓለም ከሚመለሱባቸው ምክንያቶች አንዱ ይሄ ሳይሆን አይቀርም።

ጳውሎስ የሮም ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ቁጣ ለመዳን ወይም መንግሥተ ሰማይ በሚደርሱበት ጊዜ የኋላ ኋላ ድነትን (ደኅንነትን) እንደሚጎናጸፉ የተስፋ ቃል ለማግኘት ብቻ ሳይሆን፥ የዳኑት እግዚአብሔርን ለማገልገል እንደሆነ ገልጾአል። ሮሜ 12-16 በሮሜ ውስጥ ያለውን ሁለተኛ አጠቃላይ ክፍል ይይዛል፡፡ ሮሜ 1-11 የድነት ምንነት ያብራራል። ከሮሜ 12-16 ጳውሎስ ድነት የአንድን ሰው አጠቃላይ ሕይወት እንዴት እንደሚለውጥና ተግባራዊ ለውጦችንም እንደሚያስከትል ያብራራል። ክርስቶስን የሕይወታችን ሁሉ ጌታ ማድረግ ማለት ምን ማለት ነው?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አማኝ ከሆንህበት ጊዜ ጀምሮ ሕይወትህ የተለወጠው እንዴት ነው? ለ) ሮሜ 12-13 እንብብ። ክርስቶስ የሕይወታችን ጌታ በሚሆንበት ጊዜ የሚለወጡትን ዐበይት የሕይወታችንን ክፍሎች ዘርዝር። ሐ) ሮሜ 12፡1-2ን በቃልህ አጥና። የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን በኋላ የሕይወታችን ዓላማ ምን እንደሚሆን እብራራ።

 1. አማኞች ሙሉ ሕይወታቸውን እንደ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀርባሉ (ሮሜ 12፡1-2)

ጳውሎስ ይህን የሮሜ መልእክት ሁለተኛ ክፍል የሚጀምረው «እንግዲህ» በማለት ነው። «እንግዲህ» የሚለው ቃል ቀደም ሲል በተነገረው አሳብ ላይ ተመሥርቶ ድምዳሜ የሚሰጥ ስለሆነ፥ ይህን ቃል በምንመለከትበት ጊዜ ሁሉ ምንን እንደሚያመለክት ለመረዳት መሞከር አለብን። በዚህ ስፍራ ጳውሎስ ከሮሜ 1-11 ያቀረበውን ትምህርት ለማመልከት የሚፈልግ ይመስላል። እግዚአብሔር በምሕረቱ ልጁ ለኃጢአታችን እንዲሞት በማድረግ፥ ከኃጢአት ኃይል ነፃ በማውጣት፥ የኋላ ኋላ ደኅንነታችንን በማረጋገጥ፥ እንዲሁም ምንም ነገር ከእርሱ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል የተስፋ ቃል በመስጠት በሚያስደንቅ መንገድ ስላዳነን፥ ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት መለወጥ አለበት። አኗኗራችንም መለወጥ አለበት። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ክርስቲያኖች ሊያደርጓቸው ስለሚገቧቸው ወይም ስለማይገቧቸው ነገሮች ብዙ መመሪያ አለመስጠቱ አስገራሚ ነው። ጳውሎስ ስለ መጠጥ፥ ዕጽ፥ ወዘተ… አይጠቅስም። ለእግዚአብሔር ስለሚኖሩን አመለካከቶችና በክርስቲያኖች መካከል የሚታዩትን ግንኙነቶች በመሳሰሉት ጥልቅ ጉዳዮች ላይ ነበር ትኩረት የሰጠው። ሕይወታችን የሚለወጠው እንዴት ነው? ጳውሎስ ልናደርጋቸው የሚገቡንን አያሌ ነገሮች ይጠቃቅሳል።

ሀ. ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው፥ ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። እግዚአብሔር ልጁን እንደ መሥዋዕት ለእኛ ሰጥቶናል። እኛ ደግሞ ራሳችንን ለእግዚአብሔር መልስን እንሰጠዋለን። በብሉይ ኪዳን የሚቃጠል መሥዋዕትንና የኃጢአት መሥዋዕትን የመሳሰሉ ብዙ የመሥዋዕት ዓይነቶች ነበሩ። ጳውሎስ ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ የመሰጠትን አሳብ ለማመልከት እንስሳው ሙሉ በሙሉ ስለሚቃጠልበት የሚቃጠል መሥዋዕት ነበር የሚናገረው። ጳውሎስ ሁለንተናችንን ለእግዚአብሔር መልሰን መስጠት እንዳለብን ያስረዳል። ነገር ግን ለእግዚአብሔር የምናቀርበው መሥዋዕት ከኃጢአት የተለየ ቅዱስ መሆን አለበት። እግዚአብሔርን የምናስደስተው በዚህ መልኩ ነው። ለእግዚአብሔር የምናቀርበውን የመጨረሻ አምልኮ የምንገልጸው እንደዚህ ነው። ብዙውን ጊዜ ስለ አምልኮ ስናስብ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለምንዘምራቸው መዝሙሮች፥ የቃለ እግዚአብሔር ስብከት፥ ወዘተ እናስባለን። ስሜታችንን በብዛት ካንጸባረቅን ፍሬያማ አምልኮ ያካሄድን ይመስለናል። ጳውሎስ ግን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አምልኮ የሚጀምረው ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ በመስጠት እንደሆነ ያስተምራል። ለእግዚአብሔር ክብር የተቀደሰ ሕይወት መኖር አለብን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔርን በትክክል አምልኬአለሁ ብለህ ያሰብከው መቼ ነው? የዚያን ጊዜ አምልኮ ለአንተ ልዩ የሆነው በምን ምክንያት ነው? ለ) ለእግዚአብሔር የተሰጠና የተቀደሰ ሕይወት መምራት ለእውነተኛ አምልኮ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመምጣታቸው በፊት ስለዚህ በአምልኮ ውስጥ የመጀመሪያው እርምጃ ስለሆነው ጉዳይ የማያስቡት ለምንድን ነው? መ) ብዙ ክርስቲያኖች በዕለተ ሰንበት ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር አሳልፈው ሳይሰጡ ለማምለክ የሚፈልጉ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ።

ለ. በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ጳውሎስ እነዚህ ክርስቲያኖች ማንን መምሰል እንዳለባቸው ጥብቅ ውሳኔ እንዲያደርጉ ያዝዛቸዋል። በአንዱ በኩል ዓለም አለች። ዓለም ደግሞ የገንዘብን ዋስትና፥ ክብርን፥ ተወዳጅነትን፥ ለግል ጥቅም የሚውልን ትምህርት፥ ወዘተ… ትፈልጋለች። በሌላ በኩል፥ በሙሉ ልባቸው እግዚአብሔርን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። ይህ መንገድ ደግሞ ራስን የማዋረድ፥ እግዚአብሔርን የመታዘዝ፥ ሌሎችን የመውደድ፥ የመመስከር፥ ወዘተ… አቅጣጫ ነው። ጳውሎስ በየቀኑ አስተሳሰባችንን የተቆጣጠረው የዓለም መንገድ እንዲገዛን ከመፍቀዱ ይልቅ የእግዚአብሔርን መንገድ ልንመርጥ እንደሚገባ ገልጾአል። ሐዋርያው ዮሐንስም የዓለም አሳብ እንዲገዛን መፍቀድ እንደሌለብን አስተምሯል (1ኛ ዮሐ 2፡15-17)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከዓለም የሚመጡትንና ክርስቲያኖች ሊለውጧቸው የሚገባቸውን ነገሮች፥ በተለይም ዓለማዊ አመለካከቶች ዘርዝር። ለ) ቤተ ክርስቲያንህ አዳዲስ አማኞች እነዚህን አመለካከቶች እንዲቀይሩ የምታስተምረው እንዴት ነው?

ነገር ግን እነዚህን ከዓለም የወረስናቸውን አመለካከቶች ልንለውጥ የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ለውጡ የሚመጣው በጸሎት ወይም ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ብቻ እንዳልሆነ አመልክቷል። እነዚህ ነገሮች አስፈላጊዎች ቢሆኑም በዋናነት ለውጥ የሚመጣው አእምሯችንን በማደስ ነው። በአሳባችን ውስጥ ያለው ጉዳይ አስፈላጊ ነው ብለን ያሰብነው ነው። በሕይወታችን ተግባራዊ የምናደርገውም ይህንኑ የምናስበውን ጉዳይ ነው። ስለሆነም፥ አስተሳሰባችንን ብንለውጥና ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጋር ብናዛምድ፥ ተግባራችንም እንደሚለወጥ ጳውሎስ አብራርቷል።

ራሳችንን ለእግዚአብሔር ክብርና አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ስንሰጥና ወደ ተግባር የሚመራን አስተሳሰባችንን ስንለውጥ፥ ይህ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ወደ ማወቅ እንደሚመራን ጳውሎስ ገልጾአል። ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች፥ በተለይም ወጣቶች ለሕይወታቸው የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ያስባሉ። ማንን ሊያገቡ፥ ምን ዓይነት ትምህርት ሊማሩ፥ ምን ዓይነት ሥራ ሊይዙ፥ የት አካባቢ ሊኖሩ፥ ወዘተ. እንደሚገባቸው ያብሰለስላሉ። እነዚህ ጠቃሚ ጥያቄዎች ቢሆኑም፥ ጳውሎስ ወደ ሁለተኛ ደረጃነት ዝቅ ያደርጋቸዋል። ከሁሉም የሚበልጠው ጥያቄና ለሁላችንም ግልጽ ሊሆን የሚገባው እጅግ ጠቃሚው የእግዚአብሔር ፈቃድ አካል፥ «ሕይወታችንን የምንመራው ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ተሰጥተን ነው ወይ?» የሚለው ሊሆን ይገባል። ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር ራሳችንን ሰጥተን ስንኖር፥ ፍላጎቶቻችንና እሴቶቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጹት ጋር አንድ ዓይነት ሲሆኑ፥ አእምሯችን፥ የምናስባቸው ነገሮችና ጠቃሚ ነው ብለን የምናስበው ሁሉ እግዚአብሔር ከሚፈልገው ነገር ጋር ሲጣጣሙ፥ ሌሎች የሚያሳስቡን ነገሮች ሁሉ ግልጽ ይሆኑልናል። ለእግዚአብሔር ክብር የሚኖር ሰው በእግዚአብሔር እየተመራ በሚያልፍበት ሁኔታ ውስጥ ሁሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ መልካም፥ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም መሆኑን ይገነዘባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ የሚቸገሩባቸውን አንዳንድ ነገሮች ዝርዝር። ለ) ሰውነታችንን መሥዋዕት ማድረግ የእዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ የሚረዳን እንዴት ነው? ሐ) ለእግዚአብሔር ራስን ሙሉ በሙሉ አሳልፎ መስጠት የትዳር ጓደኛን መምረጥ የመሳሰሉትን ነገሮች በሕይወታችን ቀላል የሚያደርገው እንዴት ነው?

 1. እማኞች እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያገለግላሉ (ሮሜ 12፡3-8)

ዛሬ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ከሚያጋጥማት ችግሮች አንዱ እግዚአብሔር በቀዳሚነት በእኛ ግለሰባዊ ሁኔታ ደስ ይሰኛል የሚል የራስ ወዳድነት ክርስትና ነው። በግል ደኅንነታችን፥ በጸጋ ስጦታዎቻችን፥ በአምልኮ ባርኮታችን፥ ወዘተ ላይ እናተኩራለን። ጳውሎስ ግን ክርስቲያን በዋናነት ሊያተኩር የሚገባው በግል ጉዳይ ላይ ሳይሆን የክርስቶስ አካል በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊሆን እንደሚገባ አብራርቷል። ጳውሎስ የሚያስተምራቸው አብዛኞቹ ተግባራዊ ነገሮች እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዴት አብረን ልንኖር እንደሚገባን የሚያሳዩ ናቸው። በዚህ ክፍል ጳውሎስ እያንዳንዱ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለማገልገል ሊያስታውሳቸው የሚገባቸውን አራት መሠረታዊ ነገሮች ጠቃቅሷል።

ሀ. ከሌሎች ጋር መዛመድ ማለት የራሳችንን ትክክለኛ ማንነት መገንዘብ ማለት ነው። ከዓለም ከምንማራቸው ነገሮች አንዱ ራሳችንን ከሌሎች ጋር የማወዳደር ዝንባሌ ነው። ስለሆነም ራሳችንን እንደተሻልን የበለጠ የተማርን፥ የበለጠ ስጦታ ያለን አድርገን እንመለከታለን። የዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ከእግዚአብሔር ሳይሆን ዓለማዊ ነው። ጳውሎስ ማንነታችንንና ግንኙነታችንን እግዚአብሔር በሚያየን መንገድ መገንዘብ እንዳለብን ገልጾአል። በአንድ በኩል ይህ ማለት እግዚአብሔር ምን ያህል እንደወደደን፥ ለእርሱ ምን ያህል አስፈላጊዎች እንደሆንን፥ ከእርሱ ስጦታዎችን እንዳገኘንና ለእርሱ እንደምንጠቅም መገንዘብ ማለት ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክርስቲያኖች፥ በተለይም ያልተማሩ ወይም ሴቶች፥ «ለምንም የማልረባ ስለሆንሁ እዚያ ቁጭ ብዬ ልስማ። ለእግዚአብሔር እንደ እገሌና እገሌ አስፈላጊ አይደለሁም» ሊሉ አይችሉም። እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ለሁላችንም እንዲሞት ልጁን ለላከው እግዚአብሔር ስድብ ነው። ሁላችንም ለእግዚአብሔር አስፈላጊዎች ነን። ይህ እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታዎችና ችሎታዎች አውቀን ለሌሎች ጥቅም መገልገል እንዳለብን ያሳያል። በሌላ በኩል፥ እኛ ከማንም እንደማንሻል መገንዘብ አለብን። የምንኩራራበት ምንም ምክንያት የለንም። ሰዎች ሁሉ፥ ያልተማሩና የተማሩ፥ ወንዶችና ሴቶች፥ ወጣቶችና አረጋውያን ሁሉ በመስቀሉ ሥር እኩል ናቸው። ሁላችንም በጸጋ የዳንን ኃጢአተኞች ነን።

ለ. እያንዳንዱ ክርስቲያን የአንድ አካል ክፍል መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል። ሁላችንም የቤተ ክርስቲያን አካሎች ነን። ዛሬ እንደ ግለሰብ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው የሚያመልኩ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ተመልሰው ተግባራቸውን ያከናውናሉ። የቤተ ክርስቲያን አካል ሆነው ለቤተ ክርስቲያን ሕይወት ምንም አስተዋጽኦ አያበረክቱም። ይህ ጳውሎስ ከሚያስተምረው አሳብ ተቃራኒ ነው። ጳውሎስ እያንዳንዱ ግለሰብ የቤተ ክርስቲያን አካል እንደሆነ ያስተምራል። እያንዳንዳችን መንፈስ ቅዱስ በሰጠን ስጦታ ወይም ስጦታዎች አማካኝነት ለአካሉ የምናበረክታቸው ድርሻዎች አሉን። ቤተ ክርስቲያን የሁሉም ክርስቲያን ነች። ሁሉም ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያን ሊሆን ይገባል። (መሪዎች ቤተ ክርስቲያንን ስለምናስተዳድር ወይም ስለምንመራ ንብረታችን ናት ብለን እንዳናስብ መጠንቀቅ አለብን። የቤተ ክርስቲያን ዋነኛው ባለቤት እግዚአብሔር ሲሆን፥ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሁሉ እኩል ድምፅ አላቸው።)

ሐ. አንዳችን ሌላውን እናገለግል ዘንድ እግዚአብሔር ለአማኞች ሁሉ የተለያዩ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ሰጥቷል። ሁሉም ስጦታዎች ያሉት ክርስቲያን የለም። ነገር ግን እያንዳንዱ ክርስቲያን ቢያንስ አንድ ስጦታ ተሰጥቶታል። መንፈሳዊ ስጦታ በቀዳሚነት ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት የሚውል ችሎታ ነው። በዛሬው ዓለም ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ስናስብ አእምሯችን በፍጥነት የሚወነጨፈው እንደ ልሳን፥ ፈውስ፥ ትንቢት፥ ወዘተ… ወዳሉት አስደናቂ ስጦታዎች ነው። ብዙውን ጊዜ እነዚህን መንፈሳዊ ስጦታዎች የምንፈልገው ለራስ ወዳድነት ዓላማ፥ ማለትም ሰዎች በመንፈሳዊነታችን እንዲደነቁ ለማድረግ ነው። ጳውሎስ ግን ብዙ ዓይነት ስጦታዎችና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማገልገል የሚቻልባቸው ብዙ መንገዶች እንዳሉ ይነግረናል። ሁሉም አስፈላጊዎች ናቸው።

መ. ዋናው ነገር እግዚአብሔር ለአንድ ክርስቲያን መንፈሳዊ ስጦታ መስጠቱ ወይም ግለሰቡ ስጦታውን መጠቀሙ ብቻ አይደለም። ጳውሎስ ስጦታውን ከምንጠቀምበት ሁኔታ በስተጀርባ ያለው አመለካከታችን አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳል። ስለሆነም፥ ትንቢትን በምንናገርበት ጊዜ ከመንፈሳዊ የእምነት ደረጃችን ጋር በተስተካከለ ሁኔታ መሆን አለበት። በችግር ላይ ላሉት በምንሰጥበት ጊዜ በልግስና ልናደርገው ይገባል። አመራራችንም በትጋት የሚካሄድ ሊሆን ይገባዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) መንፈሳዊ ስጦታዎችህ ምንድን ናቸው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ እንዴት እየተጠቀምህባቸው ነው? ሐ) አንድ መንፈሳዊ ስጦታ ጥቀስና ይህንኑ ስጦታ እንዴት በተሳሳተ አመለካከት መጠቀም እንደሚቻል ግለጽ። በትክክለኛ አመለካከት መጠቀም የሚቻለውስ እንዴት ነው? እግዚአብሔር ለእርሱ በምንሠራው ሥራ ላይ ብቻ ሳይሆን በሥራው ላይ በነበረን አመለካከት ላይም የሚገደው ለምን ይመስልሃል? መ) ብዙ ምእመናን በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደማገልገል ከቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን የሚዟዟሩት ለምን ይመስልሃል? ሠ) በቤተ ክርስቲያንህ ሰዎች መንፈሳዊ ስጦታዎቻቸውን ተግባራዊ ሊያደርጉ የሚችሉባቸውን የአገልግሎት ዓይነቶች ዘርዝር። ሰዎች የበለጠ በአገልግሎት ውስጥ እንዲሳተፉ ልታደርግ የምትችለው እንዴት ነው? ረ) በቤተ ክርስቲያንህ ከሌሎች አማኛች ጋር እኩል አይደለንም የሚል ስሜት ያላቸው ሰዎች አሉ? እነዚህ እነማን ናቸው? የእኩልነት ስሜት እንዲሰማቸው ምን ልታደርግ ትችላለህ?

 1. አማኞች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር የፍቅር ግንኙነት ያደርጋሉ (ሮሜ 12፡9-13)

በአማኞች ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በራስ ወዳድነት አንድን ነገር ከሌላው ለመውሰድ የሚፈልጉ ሳይሆኑ፥ እርስ በርሳቸው የሚዋደዱ መሆን አለባቸው። ፍቅር ከራሳችን በላይ ሌላውን ሰው እንድንረዳ ነው የሚፈልገው። እያንዳንዱ ክርስቲያንና ባጠቃላይም የአማኞች አካል ክፋትን በሚጠሉና በጎነትን በሚያስፋፉ፥ ትሑት በሆኑና ከራሳቸው በላይ ሌሎችን ለመጥቀም በሚፈልጉ፥ ወዘተ… ወገኖች የተገነባ እንዲሆን ይሻል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ በክርስቲያኖች መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት የገለጸውን ሃሳብ ከቤተ ክርስቲያንህ ሁኔታ ጋር አነጻጽር፡፡ የቤተ ክርስቲያንህ ጠንካራና ደካማ ጎኖች የትኞቹ ናቸው? ለቤተ ክርስቲያንህ ጳውሎስ በዚህ ክፍል የገለጸውን ባሕርይ እንድታንጸባርቅ ለመርዳት ምን ልታደርግ ትችላለህ?

 1. አማኞች ከክርስቲያኖችም ሆነ ክርስቲያኖች ካልሆኑ ሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ያደርጋሉ (ሮሜ 12፡14-21)።

ከሰዎች ጋር በሰላም ለመኖር ምንም ያህል ጥረት ብናደርግም፥ በግንኙነቶች ውስጥ ችግሮች ይከሰታሉ። ከአማኞችም ሆነ አማኞች ካልሆኑ ሰዎችም ጋር የግንኙነት ችግሮች ይከሰታሉ። ጳውሎስ ደኅንነታችንን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መልኩ ለመኖር ከፈለግን፥ ከማንስማማቸው ሰዎች ጋር ስለሚኖረን አመለካከት መጠንቀቅ እንዳለብን። ግንኙነታችንን የሚመለከቱ አያሌ ትእዛዛትን ሰጥቷል።

ሀ. ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖር ፈልጉ።

ለ. በኩራት ሌሎችን ላለመናቃችሁ እርግጠኞች ሁኑ። በሮም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩ ብዙ አማኞች ባሮች እንደነበሩ አትዘንጋ። ነገር ግን ጥቂት ባሪያ አሳዳሪዎችም ነበሩ። ጥቂት ምእመናን የተማሩ ሲሆኑ፥ አብዛኞቹ ግን ያልተማሩ ነበሩ። ይህ ልዩነታቸውም አንዳቸው ከሌላቸው እንደሚበልጡ እንዲያስቡ ሊገፋፋቸው ይችላል። ጳውሎስ አንዱ ሰው ለእግዚአብሔር ከሌላው የተሻለ እንዳልሆነ ገልጾአል። ስለሆነም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኩራት፥ ጎሰኝነት፣ ወዘተ ሊኖሩ አይገባቸውም።

ሐ. ሰዎች በሚቃወሙህ ጊዜ እነርሱን መጥላትና መበቀል እንደሌለብህ እርግጠኛ ሁን። ነገር ግን በጎነታቸውን በመሻት፥ እግዚአብሔር በሕይወታቸው እንዲሠራ በመጠየቅ ባርካቸው። ቅጣታቸውን ለእግዚአብሔር ተወው። የጥላቻንና የክፋትን ዑደት ማስወገድ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ መልካምን ለማድረግ በመወሰን ነው። አንድን ሰው ብንበቀል ራሳችንን፥ ቤተሰባችንን፥ ቤተ ክርስቲያናችንን፥ ማኅበረሰባችንንና አገራችንን የሚያጠፋ የክፋት ዑደት እንቀጥላለን፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- ብዙ ቤተ ክርስቲያኖቻችን በመክፋፈል የታወቁ ናቸው። ሀ) ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያን ወይም በቤተ እምነትህ ዐቢይ ክፍፍል ከፈጠሩት ነገሮች አንዱን ነቅሰህ አውጣ። ጳውሎስ ባስተማረው መሠረት፥ አለመግባባቶቹን ለማቆም ክርስቲያኖች እንዴት መመላለስ ይኖርባቸዋል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

አይሁድ፣ በዚህ ዘመን ቅሬታቸው ሲድኑ አንድ ቀን ደግሞ እንደ አንድ ሕዝብ ይድናሉ (ሮሜ 11፡1-36)

የውይይት ጥያቄ፡– ሮሜ 11ን አንብብ። ሀ) ጳውሎስ እግዚአብሔር ከአይሁዶች ጋር ስለሚያደርገው የአሁንና የወደፊት ግንኙነት ምን አለ? ለ) ጳውሎስ ለአሕዛብ ክርስቲያኖች የሰጣቸው ማስጠንቀቂያ ምን ነበር?

አይሁዶች እንደ ሕዝብ የእግዚአብሔርን የድነት (ደኅንነት) መንገድ ለመቀበል ስላለመፈለጋቸው ጳውሎስ የሚሰጠውን ትንታኔ የሚሰማ አይሁዳዊ ክርስቲያን፥ «ይህ ማለት እግዚአብሔር ከእንግዲህ ለአይሁዶች ልዩ ዕቅድ የለውም ማለት ነው?» የሚል ጥያቄ ማንሣቱ የማይቀር ነው። ጳውሎስ ለዚህ ጉዳይ በሦስት መንገዶች ምላሽ ሰጥቷል።

 1. በታሪክ ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ የሚያምኑ ቅሬታዎች አሉት (ሮሜ 1፡1-10)። ራሱ ጳውሎስና የአይሁድ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር አይሁዶችን ሙሉ ለሙሉ ላለመተዉ ማረጋገጫዎች ናቸው። እግዚአብሔር በጨለማው የእስራኤል ታሪክ እንዳሳየው፥ ኤልያስ ታማኝ የእግዚአብሔር ተከታይ እኔ ብቻ ነኝ በሚልበት ወቅት ሌሎች 7,000 ታማኝ ተከታዮች ነበሩት (1ኛ ነገ 19)። አብዛኞቹ አይሁዶች «የመንፈስ ድንዛዜ» ቢደርስባቸውም፥ ታማኝ ቅሬታዎች የእግዚአብሔርን የድነት (ደኅንነት) መንገድ ተከትለው በክርስቶስ አምነዋል። በአሁኑ ጊዜ አይሁዶች ክርስቲያኖች ወገኖቻቸውን በወንጌል ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ብዙ አይሁዶችም ክርስቶስን ለማመን እንደ መሲሐቸው አድርገው ለመከተል እየወሰኑ ነው።
 2. እግዚአብሔር «የአሕዛብን ዘመን» ዐቅዷል። ይህም ብዙ አሕዛብ በክርስቶስ የሚያምኑበትና ቀደም ሲል አይሁዶች ያገኙ የነበረውን በረከት የሚቀበሉበት ነው (ሮሜ 11፡11-24)። ጳውሎስ የአሕዛብ ክርስቲያኖች አሁን ከአይሁዶች ይልቅ እነርሱ የእግዚአብሔርን ሞገስ እንዳገኙ በማሰብ እንዳይታበዩ ሰግቶ ነበር። ስለሆነም፥ የእግዚአብሔርን ረዥም የድነት (ደኅንነት) ዕቅድ በሰፊው ያብራራል። ይህ ለአሕዛብ የተሰጠው ጸጋ ጊዜያዊ ይሆናል። ይህም እግዚአብሔር አይሁዶችን አስቆጥቶ ወደ ራሱ የሚመልስበት መንገድ ነበር። በእግዚአብሔር ዕቅድ፥ አይሁዶች የእግዚአብሔርን የድነት (ደኅንነት) መንገድ አለመቀበላቸው በአንድ ወቅት ከእግዚአብሔር ሕዝብ ተገልለው ለነበሩት አይሁዶች የድነትን መንገድ ከፍቷል። ጳውሎስ አንድ ቀን አይሁዶች እንደ ሕዝብ በክርስቶስ የሚያምኑ ሲሆን፥ ደኅንነታቸውም ለዓለም የበለጠ በረከትን ያመጣል በማለት ተስፋውን ተናግሯል።

ጳውሎስ እግዚአብሔር እያደረገ የነበረውን ተግባር ለማብራራት አያሌ ምሳሌዎችን ተጠቅሟል።

ሀ. አይሁዶች ከመጀመሪያው የመከር እህል ያዘጋጁትን ሊጥ ለእግዚአብሔር ስለሚሠዉበት ሁኔታ ይገልጻል። ይህም ለእግዚአብሔር የተሠዋውን እርሾ ብቻ ሳይሆን የተቀረውንም ሊጥ በመቀደስ (ስመለየት)፥ እግዚአብሔር የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንደሚያሟላላቸው ያመለክታል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ እግዚአብሔር የእምነት አባቶችን ልዩ ሕዝቡ አድርጎ ስለመረጣቸው፥ የተቀሩትም አይሁዶች ለእግዚአብሔር ልዩ ይሆናሉ። (በዚህ ክፍል «ቅዱስ» የሚለው ቃል ኃጢአት አልባነትን ሳይሆን «መለየት»ን ያሳያል።)

ለ. ጳውሎስ በተጨማሪም የአይሁዶችንና የአሕዛብን ግንኙነት ከወይራ ዛፍ ጋር ያነጻጽረዋል፡፡ አይሁዳውያን ካሏቸው ዋና ዋና ተክሎች መካከል አንዱ የወይራ ዛፍ ነው። ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ልጆች በወይራ ዛፍ መስሏቸው ነበር። ዋነኞቹ የወይራ ዛፍ በልዩ ሁኔታ የተመረጡት የብሉይ ኪዳን ሕዝቦች አይሁዶች ነበሩ። አሕዛብ ክርስቲያኖች በዚያው የወይራ ዛፍ ላይ የተተከሉ የበረሃ ቅርንጫፎች ናቸው። (ብዙውን ጊዜ ሰው ጥሩ ቅርንጫፎችን በበረሃ ዛፍ ላይ ለማዳቀል ያጣብቃል እንጂ የማይጠቅም የሚመስለውን የበረሃ ቅርንጫፍ በጥሩ ዛፍ ላይ አያጣብቅም። የእግዚአብሔር ጸጋ ግን ኃጢአተኛ አሕዛብን ወደ ትውፊታዊ የእግዚአብሔር ቤተሰብ በማምጣት በዚህ መንገድ ይሠራል።) ክርስቶስን የተዉት የአይሁድ ሕዝብ ፍሬያማ ባለመሆናቸው ምክንያት ከዛፍ እንደተቆረጡ ቅርንጫፎች ናቸው። ነገር ግን የአሕዛብ ክርስቲያኖች መመካት እንደሌለባቸው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ወደ እግዚአብሔር የበረከት ዛፍ ለመግባት የሚያበቃ ምንም ዓይነት ተግባር አላከናወኑም። ይህ የእግዚአብሔር ምሕረት ያስገኘላቸው በረከት ነበር። ጳውሎስ አሕዛብ እንዲጠነቀቁ ያሳስባል። ካልታዘዙ እነርሱም ከእግዚአብሔር በረከት ሊቆረጡና ሊወገዱ ይችላሉ። ጳውሎስ እግዚአብሔር አንድ ቀን ተፈጥሯዊ ቅርንጫፎቹ የሆኑትን አይሁዶች ወደ በረከት ዛፍ መልሶ እንደሚተክላቸው ገልጾአል።

 1. አንድ ቀን እግዚአብሔር አይሁዶችን እንደ አንድ ሕዝብ ያድናቸዋል (ሮሜ 11፡25-32)። በዚህ ጊዜ አይሁዶች የአሕዛብ ክርስቲያኖችን ቢያሳድዱም፥ ይህ ማለት እግዚአብሔር አይሁዶችን ሙሉ ለሙሉ ከዕቅዶቹ ሠርዟቸዋል ማለት አልነበረም። «የአሕዛብ ሙላት ከተፈጸመ በኋላ» እግዚአብሔር አይሁዶችን እንደገና በመጎብኘት ብዙዎቹን ያድናቸዋል።

ጳውሎስ ይህን እውነት «ምሥጢር» ብሎ ይጠራዋል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ምሥጢር ለሌላ ሰው የማይነገር አሳብ ማለት ሳይሆን፥ በብሉይ ኪዳን ተሰውሮ የነበረና በአዲስ ኪዳን ግን እግዚአብሔር ለሕዝቡ የገለጠው እውነት ነው።

የአሕዛብ ሙላት ማለት ምን ማለት ነው? «እስራኤል ሁሉ» በሚለው ውስጥ የተካተቱትስ እነማን ናቸው? በዚህ ጉዳይ ላይ የሚቀርቡ የተለያዩ አተረጓጎሞች ቢኖሩም፥ ጳውሎስ በዚህ የአሕዛብ ወይም የቤተ ክርስቲያን ዘመን እግዚአብሔር በአሕዛብ ድነት (ደኅንነት) ላይ ማተኮሩን ለማሳየት ይፈልጋል።

በቤተ ክርስቲያን ዘመን የተወሰነ ቁጥር ያላቸው አሕዛብና የተወሰነ የድነት (ደኅንነት) ጊዜ ስላለ፥ በዋናነት አሕዛብ ይድናሉ። የተመረጡት አሕዛብ በሙሉ ከዳኑ በኋላ፥ ታሪኩ አቅጣጫውን ይቀይራል። ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር በአይሁዶች መካከል በመሥራት በክርስቶስ እንዲያምኑ ያደርጋል። ይህ ማለት ግን እያንዳንዱ አይሁዳዊ ድነት ያገኛል ማለት አይደለም። ነገር ግን እንደ አንድ ሕዝብ ብዙ አይሁዶች በክርስቶስ አምነው ይድናሉ። ከእንግዲህ አይሁዶች በጥረታቸው ድነትን ለማግኘት መሞከራቸውን አቁመው እንደ አሕዛብ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ምሕረት ፊታቸውን ያዞራሉ። ጳውሎስ እግዚአብሔር በስጦታዎቹና በመጥራቱ አይጸጸትም ብሏል። በሌላ አገላለጽ፥ እግዚአብሔር ሊዋሽ ስለማይችል በብሉይ ኪዳን ለአብርሃምና ለአይሁዶች የሰጣቸው የተስፋ ቃሎች ይፈጸማሉ።

 1. ለእግዚአብሔር ታላቅ ጥበብ የቀረበ የምስጋና መዝሙር (ሮሜ 11፡33-36)። እግዚአብሔር የአይሁዶችን አለመታዘዝ ተጠቅሞ አሕዛብን ማዳኑና በኋላም አይሁዶች በአሕዛብ ድነት (ደኅንነት) ቀንተው ወደ እርሱ እንዲመለሱ ማድረጉ አስደናቂ ነገር አይደለምን? ጳውሎስ የእግዚአብሔር መንገድ ከሰዎች ማስተዋል ይልቅ ምሥጢራዊ መሆኑን የሚገልጽ መዝሙር ተቀኝቷል። የድነትና የበረከቶች ሁሉ ምንጭ እግዚአብሔር ነው። በረከቱን የሚያመጣልን እርሱ ሲሆን፥ ይህንንም ለክብሩ ይጠቀምበታል። ልናደርግ የምንችለው ነገር ቢኖር እርሱን ለዘላለም ማክበር ነው (ሮሜ 11፡33–36)።

ይህ የጳውሎስ መዝሙር እግዚአብሔር በአንድ ሁኔታ ውስጥ የሚያደርገውን ሁሉ እንገነዘባለን እንዳንል ሊያስጠነቅቀን ይገባል። «ኃጢአትን ስለሠራህ እግዚአብሔር እየፈረደብህ ነው። እግዚአብሔር ልጅ ያልሰጠህ የበለጠ እንድታምነው ነው። እግዚአብሔር በአገሪቱ ላይ ረሃብን ያመጣው ኃጢአተኞች ስለሆኑ ነው።» እነዚህ ሁሉ አሳቦች እግዚአብሔር በአንድ ሁኔታ ውስጥ ምን ዓላማ እንዳለው እናውቃለን ባይነታችንን ያሳያሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር የሚያደርገው ነገር በአብዛኛው ከእኛ የተሰወረ ምሥጢር ነው። ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር የሚሠራው እኛ ከምንጠብቀው መንገድ ውጭ ነው። እግዚአብሔር ክፉውን የኮሚዩኒዝም ዘመን ተጠቅሞ ቤተ ክርስቲያንን እንዲህ በፍጥነት ያሳድጋታል ብሎ ማን ያሰበ ነበር? ጳውሎስ እንደሚለው፥ የእግዚአብሔር መንገድ ከማስተዋል ያለፈ መሥጢራዊ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል። የእርሱ መንገዶች ሁልጊዜም አስደናቂዎች በመሆናቸው፥ ሁሉም ነገር ከእርሱ እንጂ ከአመክኒዮአችን (Logic)፥ ከትምህርታችን፥ ከዘዴያችን፥ ከመዋቅራችን፥ ወዘተ… እንደማይመጡ ልንገንዘብ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ያደረገውና ምሥጢር የሆነብህን ነገር ዘርዝር? ለ) እግዚአብሔር ሰዎች ከሚያደርጉት መንገድ ፍጹም በተለየ ሁኔታ ያከናወነውንና ለእግዚአብሔር ታላቅ ክብር ያስገኘውን አንድ ነገር ጥቀስ። ሐ) አሁን ጊዜ ውሰድና እግዚአብሔርን ስለ ታላቅ ጥበቡና እውቀቱ፥ በማትገነዘብበት ጊዜ እንኳ ነገሮችን ሁሉ ስለ መቆጣጠሩ አመስግነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ሮሜ 9፡30-10፡21

 1. ብዙ አይሁዶች እግዚአብሔር የማይቀበለውን የድነት (ደኅንነት) መንገድ በመከተላቸው ምክንያት አልዳኑም (ሮሜ 9፡30-33)።

«አይሁዶች በኢየሱስ የማያምኑት ለምንድን ነው? ይህ ክርስቶስ መሢሕ አለመሆኑን አያሳይምን?» በማለት ሰዎች ጳውሎስን ይጠይቁት ነበር። ጳውሎስ ላለማመናቸው ምክንያቱ የክርስቶስ መሢሕ አለመሆን ሳይሆን አይሁዶች ድነትን (ደኅንነትን) ወይም ጽድቅን በተሳሳተ መንገድ መፈለጋቸው እንደሆነ አብራርቷል። አይሁዶች ከእግዚአብሔር ዘንድ ድነት እና ማረጋገጫ ለመቀበል የፈለጉት በውርላሳቸው፥ በግርዛታቸውና በመልካም ሥራቸው አማካኝነት ነበር። እግዚአብሔር ያዘጋጀው የድነት መንገድ ግን ይሄ አልነበረም። በድንጋዩ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በመሰናከላቸው ምክንያት ድነት ሊያገኙ አልቻሉም። ታሪካዊ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንዳልሆኑና የእግዚአብሔርን ምሕረት ለመቀበል በክርስቶስ ሞት ማመን እንደሚያስፈልጋቸው የተገነዘቡት አሕዛብ ግን ድነትን አግኝተዋል። አሕዛብ የራሳቸውን ጽድቅ ከመመልከት ይልቅ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ተቀበሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- አማኞች ነን የሚሉትን ጨምሮ ሃይማኖተኛ ሰዎች እግዚአብሔር ከሚሰጠው ጽድቅ በላይ በራሳቸው ጽድቅ ላይ በማተኮራቸው ምክንያት ዛሬ የድነትን መንገድ ለማግኘት የሚቸገሩት እንዴት ነው?

ጳውሎስ አይሁዶች ስላልዳኑበት ሁኔታ ማብራራቱን ይቀጥላል። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በድነት ውስጥ እግዚአብሔር ከሚያበረክተው ድርሻ ይልቅ በሰዎች ድርሻ ላይ ያተኩራል።

 1. አይሁዶች የእግዚአብሔርን የድነት (የደኅንነት) ዕቅድ አልተገነዘቡም (ሮሜ 10፡1-4)። አይሁዶች የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን በቅንዓት ቢጠብቁም፥ ቅንዓታቸው ድነትን ሊያስገኝላቸው አልቻለም። ብዙ ጊዜ አንድ ሰው ቀናተኛና ሃይማኖተኛ ሆኖ እምነቱን የሚከተል ከሆነ እግዚአብሔር ይቀበለዋል ብለን እናስባለን። ነገር ግን ቡድሂስቶች፥ ሙስሊሞችም ሆኑ ሌሎች ሕዝቦች ለሃይማኖታቸው ቀናተኞች እንደሆኑ መገንዘብ ይኖርብናል። ቅንዓት አንድን ነገር ትክክል ሊያደርግ አይችልም። አንድ ሰው ስለ አንድ ነገር ቀናተኛ ሊሆንና የተሳሳተ ሊሆን ይችላል። ቅንዓት ከትክክለኛ እውቀት ጋር መዋሃድ አለበት። አይሁዶች ያላገኙትም የድነትን መንገድ ትክክለኛ ግንዛቤ ነበር። የእግዚአብሔር አቀባበሉ፥ ጽድቁ፥ «ጥፋተኛ አይደለህም። የሚለው እወጃው እንዴት በስጦታ መልክ እንደሚመጡ አላውቁም ነበር። ይህ በራሳቸው ጥረት የሚያገኙት ነገር አይደለም። መሢሐቸው ክርስቶስ በፖለቲካዊ ጠላቶቻቸው ላይ ድልን እንደሚነሣ ንጉሥ ላይሆን እንደ የኃጢአት መሥዋዕት መምጣቱን ሊገነዘቡ አልቻሉም።
 2. ድነት (ደኅንነት) ወይም «ጻድቅ ነህ» የሚል እወጃ የሚያምኑ ሰዎች ሁሉ የሚቀበሉት እንጂ የማይቻል ነገር አይደለም (ሮሜ 10፡5-13)። ጳውሎስ ሁለት የድነት (ደኅንነት) መንገዶችን ለማነጻጸር ሲል ብሉይ ኪዳንን ይጠቀማል። የመጀመሪያው፥ አይሁዶች ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት የሚያስችል በጎነት ለመቀዳጀት ያደረጉት ጥረት ነው። ዘሌዋውያን 18፡5 እንደሚለው፥ እግዚአብሔርን ለማስደሰት ሕግጋቱን ሙሉ በሙሉ መፈጸም ያስፈልጋቸው ነበር። ነገር ግን ይህ ለሁሉም ኃጢአት የሚሠራ አለመሆኑን ጳውሎስ ቀደም ብሎ አመልክቷል። ስለሆነም፥ መንፈሳዊ ሕይወት ሕግጋትን ከመከተል ሊገኝ አይችልም።

የእግዚአብሔር የሆነው ሁለተኛው የድነት መንገድ ግን ከፍተኛ ብርታትንና ተአምራትን አይጠይቅም። ወደ ቅዱስ ስፍራዎች የሚደረጉ ረዣዥም ጉዞዎች ለድነት ሚያበረከቱት አስተዋጽኦ አይኖርም። የእግዚአብሔር ድነት ሰዎች ሁሉ ይቀበሉት ዘንድ በአጠገባቸው አለ። ድነትን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ማመን እንደሚያስፈልግ ጳውሎስ አብራርቷል። ክርስቶስ የኃጢአታችንን ቅጣት የከፈለ የግል መሥዋዕታችን እንደሆነ ከልባችን ማመን አለብን። እንዲሁም ክርስቶስን እንደ ጌታችን ለመከተል ቆራጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። ይህ ውስጣዊ ተግባር በኃፍረት ተሸማቅቀን ከሰዎች የምንደብቀው ዓይነት ሳይሆን፥ በይፋ የሚታወጅ ነው። አንድ አይሁዳዊ ወይም አሕዛብ ይህን ቀላልና ነገር ግን ሕይወት ለዋጭ ውሳኔ በሚያደርግበት ጊዜ የእግዚአብሔር ጽድቅና በረከት ሕይወቱን ይሞላዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ብዙውን ጊዜ ወንጌላውያን ክርስቲያኖች አንድ ሰው ክርስቶስን እንደ ግል አዳኙ አድርጎ መቀበል እንዳለበት በሚያስረዳው እውነት ላይ ቢያተኩሩም፥ ግለሰቡ ክርስቶስን እንደ ጌታውም አድርጎ መቀበል እንዳለበት አያብራሩም። ሀ) ይህ ሚዛናዊ አስተምህሮ ይመስልሃል? ለ) አንድ ሰው ክርስቶስን እንደ ግል አዳኙ አድርጎ ለመቀበልና በጌትነቱ ሥር ለመኖር ቃል መግባት ያለበት ለምን እንደሆነ አብራራ? ሐ) ሮሜ 10፡9-10ን በቃልህ አጥና።

 1. ሰዎች ለማመን ወንጌሉን መስማት አለባቸው (ሮሜ 10፡14-15)። እግዚአብሔር ስለ ክርስቶስ ባልሰሙት ሰዎች ላይ አይፈርድም የሚሉ አንዳንድ ምዕራባውያን ክርስቲያኖች አሉ። ምንም እንኳ ጳውሎስ በዚህ ጉዳይ ላይ ባያተኩርም፥ ቀደም ሲል ወንጌልን ያልሰሙትን ጨምሮ አሕዛብ ሁሉ እግዚአብሔር በልባቸው ውስጥ ያስቀመጠውንና በተፈጥሮ የገለጣቸውን እውነቶች ሆነ ብለው ስላላከበሩ ኃጢአተኞች መሆናቸውን ገልጾአል። በክርስቶስ ላይ ያለ እምነት ሊፈጠር የሚችለው እንደ ጳውሎስ ብርቱ ትምህርት ሲሰማና ሊያምን ብቻ ነው። ለዚህም ነበር ምንም ወንጌል ወዳልተሰበከበት የስፔይን አገር ለመሄድ የፈለገው። እግዚአብሔር ሰዎችን ወደ ድነት (ደኅንነት) የሚያመጣበት መንገድ የእግዚአብሔር ልጆች የማመን ዕድል ያገኙ ዘንድ ወንጌሉን ላልሰሙት ሰዎች በሚሰብኩበት ጊዜ ነው። ጳውሎስ ይህ የሐዋርያ፥ የወንጌላዊ ወይም የሚሲዮናዊ ኃላፊነት ብቻ እንዳልሆነ አመልክቷል። ነገር ግን ጠቅላላይቱ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር መልእክተኞቹ እንዲሆኑ የመረጣቸውን ሰዎች የመላክ ኃላፊነት አለባት። ጳውሎስ የሮም ክርስቲያኖች በስፔይን ወንጌልን በመሰብክ ሥራው ላይ እንዲተባበሩት አበረታቷቸዋል።

ይህ በጣም አስፈላጊ አገልግሎት በመሆኑ፥ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ጥሪ ሰምተው ወንጌሉን ወዳልሰሙት ወገኖች የሚያደርሱ ሰዎች ያማረ እግር እንዳላቸው አመልክቷል። ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች ለመማርና ጥሩ ሥራ ለመያዝ ወይም የራሳቸውን «ቢዝነስ» ለመክፈት ይፈልጋሉ። ጳውሎስ ግን ሥራቸውን በእግዚአብሔር እይታ እንዲመለከቱ ያበረታታቸዋል። ሰዎች ወንጌልን መስበክ ጊዜ ማጥፋትና ላልተማሩትና ሌላ ሥራ ሊያገኙ ለማይችሉ ሰዎች ሥራ መፍጠሪያ ነው ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። በእግዚአብሔር ዓይኖች ግን ይህ እጅግ ውብ የሆነ ሥራ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በኢትዮጵያ ብዙ አማኞች የሌሉባቸውን ጎሳዎች ዘርዝር። ለ) አምነው ይድኑ ዘንድ ወንጌልን በማድረሱ በኩል እግዚአብሔር ከአንተና ከቤተ ከርስቲያንህ ምን የሚፈልግ ይመስልሃል? ሐ) ጥቂት ወጣቶች ለጠፉት ወንጌል መስበክን እንደተከበረ ሙያ የሚያዩት ለምን ይመስልሃል? በሕይወት ጠቃሚ ስለሆነው ነገር የእግዚአብሔርን እይታ በተሳሳተ መንገድ የተገነዘቡት እንዴት ነው?

 1. ጳውሎስ አይሁዶች የእግዚአብሔርን የድነት (የደኅንነት) ጥሪ እንዴት እንደተቃወሙ ያብራራል (ሮሜ 10፡ 16-21)። በጳውሎስ ዘመን፥ በቀድሞዪቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለውጦች ተካሂደዋል። እስከዚህ ጊዜ ድረስ፥ ቤተ ክርስቲያን በኢየሩሳሌም የተማከለች ስትሆን፥ ብዙ አይሁዶች ክርስቶስን እንደ መሢሐቸው ተቀብለውት ነበር። አሁን ግን ቤተ ክርስቲያን በአሕዛብ መካከል በፍጥነት በመስፋፋቷና በኢየሩሳሌም ብሔርተኝነት እያደገ በመምጣቱ፥ ብዙ አይሁዶች በክርስቶስ ላለማመን ወሰኑ። በዚህ ጊዜ በፍልስጥኤም በአሕዛብ ላይ ፖለቲካዊ ጠላትነት እያደገ ከመምጣቱም በላይ፥ የሮምም ጭቆና ተጠናክሮ ነበር። ከዚህም የተነሣ በክርስቶስ የሚያምኑ አይሁዶች በቁጥር እየቀነሱ ሄዱ። ቀደም ሲል ያመኑትም በክርስቶስ ላይ የነበራቸውን እምነት ትተው ወደ ቀደመው የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓት እንዲመለሱ ግፊት ተደረገባቸው። የዕብራውያን መጽሐፍ እምነታቸውን ለመተው በተፈተኑት በእነዚህ አይሁዶች ላይ ትኩረት ያደርጋል።

ጳውሎስ በክርስቶስ ያመኑ ብዙ አይሁዶች እንዳሉ ቢያምንም፥ አንዳንዶች በክርስቶስ ላይ የተቃዋሚነት አቋም ይዘው ነበር። ይህ ግን ጳውሎስን አላስደነቀውም። በብሉይ ኪዳን ውስጥ አይሁዶች የእግዚአብሔርን መልእክት እንደማይቀበሉ የሚገልጸውን ሰፊ ጭብጥ ተመለከተ። ኢሳይያስ ምንም እንኳ እግዚአብሔር እጆቹን ዘርግቶ ወደ እርሱ እንዲመለሱ ቢጠይቃቸውም፥ አይሁዶች በእግዚአብሔር መልእክት ለማመን አለመፈለጋቸውን መስክሯል። ነገር ግን ታሪካዊ የእግዚአብሔር ሕዝብ ያልነበሩት አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር በመመለስ ድነትን ያገኙ ነበር። ይህም ሙሴ እግዚአብሔር አንድ ቀን አይሁዶችን ለማስቆጣት ሲል አይሁዶች ባልሆኑት ሰዎች መካከል እንደሚሠራ የተነበየው ትንቢት ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ምርጫ (ሮሜ 9፡1-29)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ «ድነት (ደኅንነት)» የሚለው ቃል የሚያስተላልፋቸውን ፍቺዎች በሙሉ ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር አንተን ያደነባቸውን የተለያዩ መንገዶች ዘርዝር።

ድነት (ደኅንነት)፡- በሁሉም ቋንቋዎች ውስጥ ከሚገኙ ውድ ቃላት አንዱ ድነት (ደኅንነት) ነው። ቃሉ በብዙ የተለያዩ መንገዶች ያገለግላል። አንድ ሰው ከአደጋ በሚተርፍበት ጊዜ ድኗል እንላለን። አንዲት ሴት በጠና በታመመች ጊዜ የታዘዘላት መድኃኒት ካሻላት አድኖአታል ማለት ነው። ይህን ቃል ባለማቋረጥ ከምንጠቀምባቸው መንገዶች ጥቂቶቹ እነዚህ ሁለቱ ናቸው።

ነገር ግን ከሌሎች ሁሉ የበለጠ ጠቀሜታ ያለው አንድ የድነት (ደኅንነት) ዓይነት አለ። ይህም እግዚአብሔር እኛን ከኃጢአታችን የሚያድንበት ነው። (ጳውሎስ ዛሬ ብዙ ሰዎች አጽንኦት በሚሰጡበት ከበሽታ ወይም ከድህነት የመዳን ጉዳይ ላይ ምን ያህል አነስተኛ ትኩረት እንደሰጠ ተመልከት።) በሮሜ መጽሐፍ ውስጥ፥ ጳውሎስ ስለ ድነት ሲያብራራ ነበር። ጳውሎስ ድነት አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት በመግለጽ ነበር የጀመረው። ሰዎች፥ የየትኛውም ነገድ አባል ይሁኑ፥ ሃይማኖተኞች ይሁኑ ወይም አይሁኑ፥ ጥሩ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት ይኑራቸው ወይም አይኑራቸው፥ በቅዱስ አምላክ ፊት ኃጢአትን ስለፈጸሙ ጥፋተኛ ናቸው። ይህም ማለት ከእግዚአብሔር ቁጣ ሥር በመሆናቸው እግዚአብሔር በሞት ይቀጣቸዋል ማለት ነው። በኃጢአታችን ምክንያት የእግዚአብሔር የሞት ቅጣት እንደሚገባን እስካላወቅን ድረስ የድነትን ትርጉም እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ልንረዳው አንችልም።

ጳውሎስ ሰዎች ወደ ክርስቶስ ተመልሰው በመስቀል ላይ እንደሞተላቸው ሲያምኑ እግዚአብሔር ስለሚሰጣቸው ድነት አብራርቷል። ጳውሎስ ማብራሪያውን የጀመረው ከኃላፊ ጊዜ ነው። በሰው ልጆች ሁሉ ላይ የተወሰነው የኃጢአት ጥፋተኝነት «ጥፋተኛ አይደለህም» በሚል እንዲለውጥ እግዚአብሔር ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን የኃጢአት መሥዋዕት ወይም የቁጣው ማብረጃ አድርጎ መላኩ ብቻ በቂ አይሆንም። እያንዳንዱ ግለሰብ በክርስቶስ ለማመን የግል ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። ያንን የእምነት ውሳኔ ካደረገ በኋላ፥ ጻድቅ የሆነው አምላክ «ጥፋተኛ አይደለህም» ወይም «ጻድቅ ነህ» ሲል ወደ ቤተሰቡ ይቀበለዋል። ይህ የአንድ ጊዜ ውሳኔ ሰዎችን ከዘላለማዊ የሲዖል ፍርድ ያድናቸዋል።

ጳውሎስ በመቀጠል ስለ አሁኑ የድነት ገጽታ ያብራራል። ይህም ከኃጢአት ቁጥጥር ነፃ ወጥተን ክርስቶስን ለመምሰል በየቀኑ በቅድስና የምናድግበት ነው። የክርስቶስ መስቀል ከአማኞች ሕይወት የኃጢአትን ተፈጥሮ እጥፍቷል። በሕይወታችን ውስጥ ባለው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ምክንያት ከኃጢአት ርቀን ለእግዚአብሔር ሕግጋት ልንታዘዝ እንችላለን።

ከዚያም ጳውሎስ ስለ ወደፊቱ የድነት ገጽታ ያብራራል። ጳውሎስ እያንዳንዱ አማኝ ከክርስቶስ ጋር የሚከብርበትን የወደፊት ዘመን አሻግሮ ያያል። ሕይወት በምድር ላይ ብዙ ኀዘንና መከራ የሚበዛበት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ምንም ነገር ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ክርስቲያኖች ሊገነዘቡ ይገባል። ሁሉም ነገር ለልጆቹ ጥቅም ይውል ዘንድ እግዚአብሔር ወደ መንግሥተ ሰማይ ሊያደርሰንና ሙሉ ለሙሉ በሕይወታችን ዙሪያ የሚከሰቱትን ነገሮች ለመቆጣጠር ቆርጧል።

ጳውሎስ የወደፊቱን የድነት ገጽታ በሚመለከትበት ጊዜ እያንዳንዱ ክርስቲያን የሚያገኘውን ድነትና ክብር ብቻ አይጠቅስም። ነገር ግን ድነት ሌሎች ሁለት ዐበይት ነገሮችን እንደሚያጠቃልል ያስረዳል። በአዳምና ሔዋን ኃጢአት የተጀመረው ጥፋት (ረሃብ፥ በሽታ፥ የመሬት መንቀጥቀጥ፥ ድርቅ) ይወገድና ፍጥረት ሁሉ ይድናል። እግዚአብሔር መጀመሪያ ሲፈጥር የነበረውንም መልክ ይይዛል። የመጨረሻው ድነት የብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የነበሩትን አይሁዶችም ይነካል። በዚያን ጊዜ እነርሱም ድነትን ያገኛሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በዚህ የወደፊት ድነት (ደኅንነት) እግዚአብሔር ፍጥረትንና ዓለምን በሚያድንበት ጊዜ ይለወጣሉ የምትላቸው አንዳንድ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ለ) ዛሬ በኃጢአት በቆሸሸች ዓለም ውስጥ በምንሠቃይበት ጊዜ ወደፊት የሚለወጡትን ነገሮች በትክክል መገንዘባችን የሚያጽናናን እንዴት ነው?

የእስራኤላውያን ያለማመናቸው መሠረቱ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ከመቀበል ይልቅ በራሳቸው ጥረት ሊጸድቁ ስለፈለጉ ነው (ሮሜ 9-10)።

የውይይት ጥያቄ፡– ሮሜ 9-10 አንብብ። ሀ) ጳውሎስ አይሁዶች ወደ ክርስቶስ እንዲመለሱ የነበረውን ጥልቅ ፍላጎት የገለጸው እንዴት ነው? ለ) አይሁዶች የተቀበሏቸው በረከቶች ምን ምንድን ናቸው? ሐ) በእነዚህ በረከቶች አሁን የማይደሰቱበት ለምንድን ነው? መ) ጳውሎስ ከአይሁድ ዘር መወለድ በቂ እንዳልሆነና ሰዎች የአብርሃም መንፈሳዊ ልጆች ሆነው መወለድ እንዳለባቸው የሚያስረዳው እንዴት ነው? መ) ጳውሎስ አይሁዶችንና ያልዳኑበትን ምክንያት የገለጸው እንዴት ነው? ረ) ለሰዎች ሁሉ የተዘጋጀውን የድነት (ደኅንነት) መንገድ ጠቅለል አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው? ሰ) ሮሜ 10፡9-10ን በቃልህ አጥና። ይህ ክፍል ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑበትን መንገድ በአጭሩ የገለጸው እንዴት ነው?

የሥነ መለኮት ምሁራንን ከሚያስቸግራቸው ጥያቄዎች አንዱ የእግዚአብሔር ታሪካዊ ሕዝብ የሆኑት አይሁዶች ስፍራ ምን ይሆን? የሚለው ነው። አሁን በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ምን ድርሻ አላቸው? በብሉይ ኪዳን ዘመን በምድር ላይ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ መካከል እግዚአብሔር የራሱ ልዩ ሕዝብ አድርጎ መርጧቸው ነበር። ልዩ ቃል ኪዳኖችንና የተስፋ ቃሎችንም ሰጥቷቸዋል። የሰጣቸውን ሕግጋት በማይታዘዙበት ጊዜም ባለማቋረጥ ይቀጣቸው ነበር። እንግዲህ እግዚአብሔር ከአይሁዶች ጋር የነበረውን ግንኙነት አጠናቅቆ ወደ ቤተ ክርስቲያን ፊቱን መልሷል ማለት ነው? በሮም የነበሩት አይሁዳውያን ክርስቲያኖችም በዚህ አሳብ ግራ ሳይጋቡ አልቀሩም። አይሁዶችና አሕዛብ አሁን እኩል ከሆኑና ወደ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ቤተሰብ የሚመጡት በክርስቶስ በማመን ብቻ ከሆነ፥ አይሁዳዊ መሆን ምን ታሪካዊ ጥቅም አለው? የአይሁዶች የወደፊት ተስፋስ ምንድን ነው? እግዚአብሔር ለአይሁዶች የሰጣቸው የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎችስ? ከእንግዲህ በሥጋ አይሁዳውያን ለሆኑት ወገኖች አያገለግሉም ማለት ነው?

ብዙ ክርስቲያኖች ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልስ እግዚአብሔር ከእንግዲህ ወዲህ ለአይሁዶች የተለየ ትኩረት አይሰጥም የሚል ነው። አሁን የእግዚአብሔር ዕቅድ የአብርሃም መንፈሳዊ ዝርያዎች በሆኑት ክርስቲያኖች ላይ ነው፥ የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎችም በተምሳሌታዊ መልኩ በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸሙ እንጂ እግዚአብሔር በሆነ መንገድ ወደፊት ከአይሁዶች ጋር የሚካሄደውን ተግባር የሚያሳዩ አይደሉም ይላሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር ለእስራኤልና ለአይሁድ ሕዝብ አሁንም የተለየ ዕቅድ እንዳለው የሚያምኑ ክርስቲያኖች ደግሞ አሉ። እግዚአብሔር ለአይሁዶች የሰጣቸው የተስፋ ቃሎች በብሉይ ኪዳን ውስጥ በተጠቀሰው መልክ ይፈጸማሉ። በዮሐንስ ራእይ ጥናታችን፥ ለዚህ ጥያቄ በምንሰጠው መልስ የትንቢትና የመጨረሻው ዘመን ግንዛቤያችንን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚለውጥ እንመለከታለን።

በሮሜ 9-11፥ ጳውሎስ የአይሁድ ክርስቲያኖች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክሯል። ጳውሎስ ፀረ አይሁዳዊ ነው የሚል ክስ ቀርቦበት ነበር። ጳውሎስ ይህን መልእክት ጽፎ ከጨረሰ ከጥቂት ወራት በኋላ ኢየሩሳሌም ውስጥ ነበር። በዚያም የአይሁድ ክርስቲያኖች በሐዋርያት መሪነት ጳውሎስ ወደ ቤተ መቅደሱ ገብቶ አንዳንድ የአይሁድ የመንጻት ሥርዓቶችን በመፈጸም ፀረ-አይሁዳዊ አቋም እንደሌለው እንዲያረጋግጥ ጠይቀውታል። ጳውሎስ ራሱን ዝቅ አድርጎ የተጠየቀውን ሁሉ በመፈጸም ለአይሁዶች የነበረውን ፍቅር አሳይቷል (የሐዋ. 21፡21-26)። ከዚህም የተነሣ ወደ እስር ቤት ወርዶ ለአራት ዓመታት ማቅቋል። በሮሜ 9-11፥ ጳውሎስ የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎች በአይሁዶች መካከል ስላልተፈጸሙበት ምክንያት፥ በአሕዛብና አይሁዶች መካከል ስላለው ግንኙነትና እግዚአብሔር ለአይሁዶች ያለው የመጨረሻ ዕቅድ ምን እንደሚሆን በማብራራት ለእነርሱ የነበረውን ፍቅር ገልጧል።

 1. ጳውሎስ ለአይሁዶች የነበረውን ጥልቅ ፍቅር ገለጠ (ሮሜ 9፡1-3)። እጅግ የምንወዳቸው የቤተሰባችን አባላት በክርስቶስ ለማመን በማይፈልጉበት ጊዜ ምን ያህል እንደምንጨነቅ ሁላችንም እናውቃለን። ወደ ሲዖል እንደሚሄዱ ስለምናውቅ እንጨነቃለን። በሰማይ እናገኛቸው ዘንድ ዘመዶቻችን በክርስቶስ የሚያምኑበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠብቃለን። ጳውሎስም ወገኖቹ ስለሆኑት አይሁዶች ባሰበ ጊዜ እንዲህ ዓይነት የጭንቀት ስሜት ተሰምቶታል። ጳውሎስ የአይሁድን ሕዝብ ወደ ድነት (ደኅንነት) ለማምጣት የሚችል ቢሆን የራሱን ድነት (ደኅንነት) አጥቶ ስለ እነርሱ ወደ ሲዖል ቢወርድ ፈቃደኛ እንደሆነ ገልጾአል። ጳውሎስ አይሁዶችን በጣም ይወዳቸው ነበር እንጂ ፀረ-አይሁዳዊ አቋም አልነበረውም።
 2. ጳውሎስ አይሁዶች ያገኟቸውን ብዙ በረከቶች ይዘረዝራል (ሮሜ 9፡4-5)። እግዚአብሔር አይሁዶችንና አሕዛብን በእኩል ሁኔታ ነበር ያስተናገደው? ጳውሎስ እግዚአብሔር ከአይሁዶች ጋር ታሪካዊ ግንኙነት ስለነበረው፥ አሕዛብ ያላገኟቸውን በረከቶች እንዳገኙ አብራርቷል።

ሀ. አይሁዶች ከእግዚአብሔር ጋር የአባትና የልጅ ዓይነት ልዩ ግንኙነት ነበራቸው። (ዘዳግ. 4፡22-23 አንብብ።)

ለ. «መለኮታዊ ክብር» ነበራቸው። ጳውሎስ ይህን ሲል በምድረ በዳ የነበረውን የክብር ደመና ለመግለጽ ብቻ ሳይሆን በቤተ መቅደስ ውስጥ የተገለጠውንም ለማመልከት ነበር (ዘጸ. 16፡7፤ 1ኛ ነገ 8፡10-10።

ሐ. አይሁዶች ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ቃል ኪዳኖችን አድርገዋል። በሲና ተራራ ላይ ከተሰጣቸው ቃል ኪዳን በተጨማሪ፥ ለሌዊ፥ ለዳዊት፥ ወዘተ… የተሰጡት ቃል ኪዳኖች ነበሯቸው።

መ. በሲና ተራራ የእግዚአብሔርን ሕግ ተቀብለዋል። ይህም እግዚአብሔር እንዴት ሊኖሩና እርሱን ሊያክብሩ እንደሚገባቸው የገለጠበት መመሪያ ነበር። በዚህ መልኩ የእግዚአብሔርን ቃል የተቀበለ ሌላ ነገድ የለም።

ሠ. አይሁዶች በእግዚአብሔር የተሠራ የቤተ መቅደስ አምልኮ ያካሂዱ ነበር። ይህም በሰዎች አሳብ ሳይሆን በእግዚአብሔር የታቀደ ነበር።

ረ. እግዚአብሔር በቃሉ ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር። ከእነዚህ የተስፋ ቃሎች አብዛኛዎቹ በትንቢት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፥ ከአይሁዶች የወደፊት በረከቶች ጋር የሚያያዙ ነበሩ።

ሰ. እንደ አብርሃም፥ ያዕቆብና ይስሐቅ ያሉት የአይሁድ የእምነት አባቶች ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን፥ እግዚአብሔር በእነርሱ ተጠቅሞ ልዩ የሆነውን የአይሁድ ሕዝብ መሥርቷል።

ሸ. እግዚአብሔር መሢሑ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ዓለም ያመጣው በአይሁዶች በኩል ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ አይሁዳዊነት ከፍተኛ ታሪካዊ ጠቀሜታ እንደነበረው አስረድቷል። የቀድሞ ታሪካቸው ሊዘከር የሚገባው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- የሚያምኑ ሰዎች ያላገኟቸውንና አንተ እንደ እግዚአብሔር ልጅ የምትደሰትባቸውን አንዳንድ በረከቶች ዘርዝር። እግዚአብሔርን ስለ እነዚህ በረከቶች ለማመስገን ጥቂት ጊዜ ውሰድ።

 1. ጳውሎስ እግዚአብሔር አጽንኦት የሚሰጠው ከሥጋዊ አይሁዳዊነት ይልቅ ለመንፈሳዊ አይሁዳዊነት እንደሆነ ገልጾአል (ሮሜ 9፡6-29)።

በዚያን ጊዜ የአይሁድ ክርስቲያኖች ጳውሎስን የሚጠይቁት ሌላም ጥያቄ ነበራቸው። ክርስቶስ የአይሁዶችን የኃጢአት ችግር የሚቀርፍና የብሉይ ኪዳን ተስፋዎች ፍጻሜ የሆነው መሢሕ ከሆነ፥ ብዙ አይሁዶች ያላመኑበት ለምንድን ነው? ይህ ክርስቶስ መሢሕ አለመሆኑን አያረጋግጥም? ጳውሎስ ለዚህ ጥያቄ በሰጠው ምላሽ የሚከተሉትን አሳቦች ትኩረት ሰጥቶ አብራርቷል።

ሀ. በትውልድ አይሁዳዊ የሆነ ሁሉ እውነተኛ አይሁዳዊ አይደለም (ሮሜ 9፡6-13)። እስማኤልንና ሌሎችንም ጨምሮ አብርሃም ብዙ ልጆች ነበሩት (ዘፍጥ. 25፡1-4)። ከእነዚህ ልጆች መካከል የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚያመለክተውና የተስፋ ቃል ፍጻሜ የሆነው ይስሐቅ ብቻ ነበር። ርብቃ ሁለት ልጆች ወልዳለች። ዔሣው ታላቅ በመሆኑ፥ እንደ ደንቡ ከሆነ በአይሁዶችና በያዕቆብ የዘር ሐረግ ውስጥ መግባት ነበረበት። ነገር ግን አንዱ የተሻለ ወይም የከፋ በመሆኑ ሳይሆን እግዚአብሔር በሉዓላዊነቱ ስለመረጠው ያዕቆብ የተስፋ ልጅ ሆኗል። በተመሳሳይ መንገድ፥ ሥጋዊ አይሁዳዊ የሆነ ሁሉ መንፈሳዊ አይሁዳዊ አይደለም። ምክንያቱም የአብርሃምን ዓይነት መንፈሳዊ እምነት ያልያዙ አይሁዶች ሁሉ እውነተኛ አይሁዶች ስላይደሉ እነዚህ እንደ ይስሐቅና እንደ ያዕቆብ ላይሆኑ፥ እንደ እስማኤልና ዔሣው ነበሩ።

ለ. ድነት (ደኅንነት) የሚወሰነው በእግዚአብሔር ምርጫ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመረዳት እጅግ ከሚያስቸግሩ አሳቦች እንዱ እግዚአብሔር ለድነት (ደኅንነት) ሰውን በሚመርጥበትና ሰው እግዚአብሔርን በሚመርጥበት ተግባር መካከል ያለው ግንኙነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የሚድኑትን እንደሚመርጥ፥ የእግዚአብሔር የድነት (ደኅንነት) ስጦታ ለሰዎች ሁሉ ክፍት እንደሆነና ምላሽ የሚሰጡት እንደሚቀበሉ ያስተምራል። በሰብአዊ ደረጃ እነዚህ ሁለት እውነቶች እንዴት አብረው እንደሚሠሩ አናውቅም። በዚህ ስፍራ ጳውሎስ እግዚአብሔር የሚድኑትን እንደሚመርጥና እንደሚወስን ገልጾአል። ይህ እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል።

 1. እግዚአብሔር ሁለቱም ከመወለዳቸው በፊት ዔሳውን ሳይሆን ያዕቆብን መርጦታል።
 2. እግዚአብሔር ለወደደው ምሕረቱን እንደሚያሳይና በጠላው ላይ ደግሞ ፍርዱን እንደሚያወርድ ለሙሴ ነግሮታል።
 3. እግዚአብሔር ፈርዖንን ወደ ሥልጣን እንዳመጣውና አይሁዶችን ላለመልቀቅ እንዲወስን እንዳደረገው ገልጾአል። ይህንንም ያደረገው በአሥሩ መቅሠፍቶችና በአይሁዶች ነፃ መውጣት ክብሩ በዓለም ላይ እንዲገን በመፈለጉ ነበር።

ሐ. እግዚአብሔር አንዳንዶችን ለድነት (ደኅንነት) በመምረጡ አድልዎ አልፈጸምም (ሮሜ 9፡19-29)። እግዚአብሔር አንዳንዶችን ለድነት (ደኅንነት) መምረጡና ሌሎችን መተዉ ፍትሐዊ አይደለም ብለን ከማጉረምረማችን በፊት፥ ጳውሎስ በሮሜ 1-3 የገለጸውን አሳብ ማስታወስ አለብን። ይህ አንዳንድ ሰዎች ለመዳን ጥረት እያደረጉ ሳለ እግዚአብሔር በሰማይ ላይ ተቀምጦ ዕጣ እያወጣ «አትድንም» ሲል የከለከለበትን ሁኔታ የሚያሳይ አይደለም። ወይም ደግሞ አንዳንዶች ለመዳን ሳይፈልጉ እግዚአብሔር አስገድዶ እንዳሳመናቸው የሚያሳይ አይደለም። ይልቁንስ ጳውሎስ ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች ሆነው በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፁ አብራርቷል። ሰዎች ሊድኑ የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ በእግዚአብሔር ምሕረት አማካኝነት ነው። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር ለአንድ ሰው ምሕረትንና ድነትን (ደኅንነትን) ለመስጠት መምረጡና ይህንኑ ተመሳሳይ ተግባር ለሌላው ሰው አለመፈጸሙ አድልዎአዊ ነው አያስብለውም።

ጳውሎስ እግዚአብሔር አንድን ሰው እየመረጠ ሌላውን መተዉ ፍትሐዊ አይደለም ለሚሉ ሰዎች በሰጠው ምላሽ፥ የሚከተሉትን እውነቶች እንዲገነዘቡ ያሳስባቸዋል።

 1. እግዚአብሔር እግዚአብሔር ነው፥ እኛ ሰዎች ግን ማንን ሊመርጥ እንደሚችልና እንደማይችል የመናገር መብት የለንም። እንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ እግዚአብሔር ሊሆን የሚገባውንና የማይገባውን፥ ፍትሐዊ የሆነውንና ያልሆነውን የሚወስን የመጨረሻው ባለሥልጣን መሆኑን እንደዘነጋን ያሳያል።
 2. አንድ ሸክላ ሠሪ የተለያዩ ዓይነት የሸክላ ዕቃዎችን የመሥራት መብት አለው። አንዳንድ ዕቃዎች (ወጭቶች) ለምግብ ማቅረቢያ አምረው ሲሠሩ፥ ሌሎች ደግሞ ለውኃ ማምጫ ይውላሉ። እነዚህ ሸክላዎች የማጉረምረም መብት እንደሌላቸው ሁሉ፥ መለኮታዊ ሸክላ ሠሪ የፈጠራቸው ሰዎችም በእግዚአብሔር ውሳኔዎች ላይ የማጉረምረም መብት የላቸውም።
 3. ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ቁጣ የሚገባቸው ኃጢአተኞች ናቸው። የማናችንም ድነት (ደኅንነት) የእግዚአብሔርን ምሕረት እንጂ እኛ ከሌሎች ሰዎች የተሻልን መሆናችንን የሚያሳይ አይደለም። እግዚአብሔር ደግሞ አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ እንዲድኑና በመንግሥተ ሰማይ እንዲከብሩ መርጧቸዋል። የሰው ልጆች ማን እንደተመረጠና እንዳልተመረጠ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ እንደሌላቸው መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። አንድ ሰው «እኔ በክርስቶስ ለማመን ብፈልግም፥ እግዚአብሔር አልጠራኝም» ሊል አይችልም። ወይም ደግሞ «እገሌ ክርስቲያን ያልሆነው እግዚአብሔር ስላልመረጠው ነው» ልንል አንችልም። ልናውቅ የምንችለው ነገር ቢኖር፥ ሀ) የእግዚአብሔር የድነት (ደኅንነት) ስጦታ ለማመን ለሚፈልጉ ሁሉ ክፍት እንደሆነና «በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን ትድንማለህ» ብሎ የመስበክ ኃላፊነት ነው ያለብን። ለ) ከልባቸው የሚያምኑ ሰዎች በእግዚአብሔር እንደተመረጡ ነው። ይህ ግን የግል ውሳኔያቸው ብቻ አይደለም።
 4. በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር፥ ) በታሪክ ሕዝቡ ያልነበሩትን እንደሚመርጥ፥ ለ) የአይሁድን ቅሬታ ብቻ እንደሚያድንና በሌሎቹ ላይ እንደሚፈርድ፥ ሐ) እግዚአብሔር ከምሕረቱ የተነሣ ሁሉንም እንደ ሰዶምና ገሞራ ከማጥፋት ይልቅ አንዳንዶችን እንዳዳነ ተናግሯል።

የውይይት ጥያቄ፡- ጳውሎስ ድነት (ደኅንነት) የእግዚአብሔርም የሰውም ምርጫ እንደሆነ ያብራራበትን ሁኔታ በራስህ አገላለጽ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ሮሜ 8፡1-39

፩. እግዚአብሔር ልጆቹ የኃጢአትን ኃይል ያሸንፉ ዘንድ መንፈስ ቅዱስን ሰጥቷቸዋል (ሮሜ 8፡1-17)

የውይይት ጥያቄ፡- ሮሜ 8ን አንብብ። ) ክርስቲያን ሕግን ከመጠበቅ፥ በእግዚአብሔር ጻድቅ ከመደረግና ከኃጢአት ተፈጥሮ ኃይል ጋር ያለውን ግንኙነት ጠቅለል አድርገህ ግለጽ። 2) መንፈስ ቅዱስ ለአማኙ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ዘርዝር። 3) ጳውሎስ የክርስቲያኑን የወደፊት ተስፋ እንዴት ይገልጸዋል? 4) ጳውሎስ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት አስተማማኝ ለማድረግ እንዳከናወናቸው የሚገልጻቸውን ነገሮች ዘርዝር።

ሮሜ 6፡1-8፡17 በክርስትና አኗኗራችን እንዴት ቅዱሳን ልንሆን እንደምንችል የሚያስረዳ መሆኑን ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። ጳውሎስ የሚያብራራው እንዴት ክርስቲያን መሆን እንደሚቻል ሳይሆን ክርስቲያን ከሆንሁ በኋላ፥ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ለመፈጸም እየፈለግሁ የኃጢአት ባሕርይ ሲያሸንፈኝ ምን ተስፋ ይኖረኛል? የሚለውን ነው።

ጳውሎስ የሚከተሉትን ነጥቦች በማሳየት ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል።

 1. በክርስቶስ ካመንን በኋላ ምንም እንኳ ከኃጢአት ጋር ብንታገልና ለመታዘዝ የምንፈልጋቸውን የእግዚአብሔርን ሕግጋት ብንተላለፍም፥ የእግዚአብሔር ውሳኔ «ጥፋተኛ አይደላችሁም» የሚል ነው (ሮሜ 8፡1-4)። ከእግዚአብሔር ዘንድ ዘላለማዊ ኩነኔ እይጠብቀንም። የክርስቶስ ሞት ከመዳናችን በፊት፥ አሁንም በየዕለቱ፥ እንዲሁም እስክንሞት ድረስ የምንፈጽማቸውን ኃጢአቶች ሁሉ ቅጣት ከፍሏል። ስለሆነም፥ ኃጢአትን በምንፈጽምበት ጊዜ ወደ ሲዖል እንድንወርድ አይፈርድብንም። ጳውሎስ ሕይወታችን ሁሉ በክርስቶስ ውስጥ እንደተሰወረ ለማመልከት ክርስቲያን «በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ» መሆኑን አመልክቷል። ይህ ከክርስቶስ ጋር እስከተዛመድን ድረስ የክርስቶስን በረከቶች ሁሉ እንደምንቀበል ለማሳየት የሚጠቀምበት ተወዳጅ አገለላጽ ነው።

እንግዲህ፥ ኃጢአታችንን መናዘዝ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ኃጢአትን ስንፈጽም ምን ይከሰታል? ኃጢአት ኑዛዜና ዕርቅ እስክንፈጥር ድረስ ከሰማያዊ አባታችን ጋር ያለንን ግንኙነት ያደናቅፋል። ይህ ልጃችን ለመታዘዝ በማይፈልጉበት ጊዜ ከሚሆነው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። ልጅነቱ ባይፋቅም በተግባሩ ማዘናችን ግንኙነቱን ያበላሸዋል።

ጳውሎስ በዳንን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊ ሕይወት እንደሰጠን አብራርቷል። ይህም ሕይወት ከኃጢአት ኃይልና ይጠብቀን ከነበረው የሞት ፍርድ (ሲዖል) አድኖናል። ክርስቶስ «የኃጢአት መሥዋዕታችን» (ለፈጸምናቸው ኃጢአቶች የተከመረብንን ዕዳ የከፈለው) ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን አድርጎናል። ይህም በፍጹም ኃጢአት ሠርተን እንደማናውቅና የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን ሙሉ በሙሉ እንደጠበቅን ያህል በእግዚአብሔር ፊት የምንስተናገድበት መንገድ ነው።

 1. አማኞች በመሆናችን፥ የምንመላለሰው በኃጢአት ባሕርይ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው። በኃጢአት ተፈጥሮና በመንፈስ ቅዱስ በመመላለስ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? በሮሜ 8፡5-8 ጳውሎስ እነዚህን ሁለት ሁኔታዎች ያነጻጽራል።

ሀ. የኃጢአት ተፈጥሮ ቁጥጥር የሚጀምረው ከአእምሮ ነው። ይህም የራስወዳድነት አሳባችን፥ ራስን ለማስደሰት መፈለግንና ክፉ ባሕሪያችንን ያረካል ብለን የምናስበውን እርምጃ መውሰድን ያጠቃልላል። በአንጻሩ፥ በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር የሚኖር ሰው ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ያስባል። ይህም እግዚአብሔርን ማስደሰትን፥ ማክበርን፥ ለእርሱ መገዛትን፥ ማምለክን፥ ሌሎችን ማገልገልን፥ ወዘተ…. ያጠቃልላል። ጳውሎስ እንደሚለው፥ እግዚአብሔርን ወይም የኃጢአት ባሕሪያችንን የማስደሰቱ ጦርነት የሚጀምረው ከአሳባችን ነው። ክርስቲያኖች ለሚያነቡት፥ በቴሌቪዥን ወይም በቪዲዮ ለሚመለከቱት ወይም ከሰዎች ለሚሰሟቸው ነገሮች ጥንቃቄ ማድረግ ያለባቸው ለዚህ ነው። ክፉ አሳቦች አእምሯችንን ሲሞሉት ተግባራችንም ክፉ ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አስተሳሰብህ በባሕሪህ፥ እግዚአብሔርን ወይም የኃጢአት ባሕሪህን በመታዘዝህ ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ግለጽ። ለ) እግዚአብሔርን ስለሚያስከብሩ ነገሮች ታስብ ዘንድ የምትመለከተውንና የምትስማውን እንዴት እንደምትመርጥ ምሳሌዎችን በመስጠት አብራራ (ፊልጵ. 4፡8ን አንብብ።)

ለ. ባለማቋረጥ ስለ ክፉ ነገሮች የሚያስበው ሰው ሞትን ሲያጭድ፥ በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር የሚኖር አእምሮ ሕይወትን ያጭዳል። ሥጋውን ስለማስደሰት፥ የሚፈልገውን ብቻ ስለማድረግ የሚያስብ ሰው በመንፈሳዊ ሕይወቱ የሞተ ሲሆን፥ በሥጋ ከሞተ በኋላ የዘላለምን ሞት ይጋፈጣል። የኃጢአት ባሕሪያችንን ለማስደሰት ስንል የምንኖረው ሕይወት በቤተሰባችን፥ በቤተ ክርስቲያናችንና በማኅበረሰባችን ውስጥ የሚኖረንን ግንኙነት ያበላሻል። ነገር ግን በሚያስበው አሳብ መንፈስ ቅዱስን ለማክበር የሚፈልግ ሰው መንፈሳዊ ሕይወት ያለው ሲሆን፥ በሥጋ በሚሞትበት ጊዜ የዘላለም ሕይወትን ይቀበላል። እንዲህ ዓይነቱ አኗኗር ለሚኖሩን ለግንኙነቶቻችን ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል።

ሐ. በኃጢአት የተበላሸ አእምሮ ማረጋገጫው ግለሰቡ እግዚአብሔርን ለማስደሰት የማይኖር መሆኑ ነው። ለእግዚአብሔር ስፍራ የለውም ወይም ይጠላዋል። ለእግዚአብሔር ሕግጋት የመገዛት ፍላጎት የሌለው ሲሆን፥ ትእዛዛቱን ለመታዘዝ የሚያስችል ኃይል የለውም። ግለሰቡ መልካምና ግብረገባዊ ቢመስልም፥ እግዚአብሔርን ሊያስከብር ወይም ሊያስደስት አይችልም። እግዚአብሔርን ልናስደስትና እርሱ የሚፈልገውን ተግባር ልናከናውን የምንችለው አእምሯችን፥ ሕይወታችንና ልባችን በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር ሲውል ብቻ ነው።

 1. እግዚአብሔር የኃጢአትን ባሕርይ እንቋቋም ዘንድ ለእያንዳንዱ አማኝ መንፈስ ቅዱስን ሰጥቷል (ሮሜ 8፡9-17)። ክርስቲያኖች በምንሆንበት ጊዜ አዲስ ባሕርይ ከመቀበላችን በላይ፥ እግዚአብሔር ራሱ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በሕይወታችን ውስጥ ይኖራል። ምንም እንኳ አንዳንድ ሰዎች ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስን የሚቀበሉት ከዳኑ በኋላ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሲያድጉ ነው ብለው ቢያስተምሩም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አስተምህሮ አይደግፍም። ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያኑ ውስጥ ከሌለ፥ ያ ሰው ከክርስቶስ ጋር ኅብረት እንደ ሌለው ገልጾአል (ሮሜ 8፡9)። መንፈስ ቅዱስ በእያንዳንዱ አማኝ ውስጥ በመኖሩ ምክንያት የሚፈጸሙ አያሌ ነገሮች አሉ።

ሀ. ከእንግዲህ የሚቆጣጠረን የኃጢአት ባሕርይ ሳይሆን በውስጣችን የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ነው። ጳውሎስ፥ «ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው። መንፈሳችሁ በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው» (ሮሜ 8፡10)። ሊል ምን ለማለት እንደፈለገ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ምናልባትም ጳውሎስ ይህን ሲል የወደቀው ሰብአዊ አካል በመሆናችን በሥጋ እንደምንሞትና፥ መንፈሳዊ ሕይወት ስለተሰጠንና እግዚአብሔርም ጻድቃን ብሎ ስለጠራን፥ ከሞት ተነሥተን ለዘላለም ሕያዋን እንደምንሆን መግለጹ ይሆናል። ወይም ደግሞ ለኃጢአት ባሕሪያችን ቁጥጥር እንደሞትንና እግዚአብሔር የሚፈልገውን መንገድ ለመከተል ሕያዋን እንደሆንን መግለጹ ይሆናል።

ለ. መንፈስ ቅዱስ በሚፈልገው መንገድ ለመኖር መምረጥ አለብን። አንዳንድ ክርስቲያኖች ምንም መልካም ነገር ልንፈጽም እንችልም ብለው ያስተምራሉ። ስለሆነም፥ ዝም ብለን መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ነገር እንዲያደርግልን መጠበቅ አለብን ይላሉ። ነገር ግን ጳውሎስና ሌሎችም አገልጋዮች እግዚአብሔርን ስለሚያስከብሩት ነገሮች ለማሰብ መምረጥ እንዳለብን ያሳስባሉ። የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ለመጠበቅና መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ እንዲሠራ ልንፈቅድለትና ራሳችንን ልንሰጠው ይገባል። ኃይል የሚመጣው ከመንፈስ ቅዱስ ነው፥ ያለ እርሱ ኃይል እግዚአብሔርን ልናስደስት አንችልም። መንፈስ ቅዱስ በአእምሯችንና በፈቃዳችን ውስጥ ስለሚሠራ፥ እርሱን ለመከተል ወይም ላለመከተል መምረጥ አለብን። እግዚአብሔር ከሕይወታችን የሚፈልገውን በመቃወም ፀረ-እግዚአብሔር የሆኑትን ነገሮች ብንመርጥ፥ በኃጢአት ተፈጥሯችን ቁጥጥር ሥር እንኖራለን ማለት ነው። እነዚህ ምርጫዎች የልባችንን ሁኔታ በማሳየት ክርስቲያኖች መሆን አለመሆናችንን ያሳያሉ። ምንም እንኳ ክርስቲያኖች በኃጢአት ቢወድቁም፥ መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ስለሚኖር ባለማቋረጥ የኃጢአት ተፈጥሯቸውን ለመከተል አይመርጡም። የኃጢአት ባሕርያችንን የመግደል ወይም ያለመከተል ልማድ ልናዳብር ይገባል።

ሐ. መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ያደርገናል። የግሪኩ ቃል የሚያመለክተው ትንሽን ልጅ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ኃላፊነት ሊቀበል የሚችለውን የበሰለ ልጅ ነው። መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር መንግሥት ሕጋዊ ወራሾች ያደርገናል። እንዲያውም ከክርስቶስ ጋር አብረን እንደምንወርስ ተገልጾአል። በሌላ አገላለጽ፥ ክርስቶስ ያለ እኛ መንግሥቱን ከእግዚአብሔር ዘንድ አይቀበልም ማለት ነው። መንግሥቱን አብረን ተቀብለን ከክርስቶስ ጋር እንነግሣለን። ባይታዘዝ ጌታው ምን ዓይነት ቅጣት እንደሚያደርስበት በማሰብ ከሚፈራው ባሪያ በተቃራኒ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዕርዳታ ለመጠየቅ የልጅነት ነጻነት አለን። በተለይም የኃጢአትን ተፈጥሮ ስበት ለመቋቋም የእርሱን እገዛ ልንጠይቅ እንችላለን። «አባ» የሚለው ቃል አንድ ትንሽ አይሁዳዊ ልጅ በፍቅር አባቱን የሚጠራበት ነው። ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ሳይቀር መንፈስ ቅዱስ ባለማቋረጥ ስለሚያሳስበን በእግዚአብሔር የተወደድን ልዩ ልጆቹ እንጂ ከኩነኔው ሥር የወደቅን አይደለንም።

የውይይት ጥያቄ፡– በኃጢአት፥ በኃጢአት ባሕርይና እነዚህን ማሸነፍ በሚቻልበት መንገድ መካከል ስላለው ግንኙነት በራስህ አገላለጽ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

፪. የእግዚአብሔር ልጅ የኋላ ኋላ እንደሚከበርና የእግዚአብሔርን የማያቋርጥ ፍቅር እንደሚያገኝ ማረጋገጫ ተሰጥቶታል (ሮሜ 8፡18-39)።

በምድር ላይ በሚያጋጥመን መከራ ምክንያት ክርስቲያኖች ለክርስቶስ ለመኖር እንደክማለን። በሽታ አጥቅቶን ሳለ እግዚአብሔር ጸሎታችንን የማይመልስ የሚመስልበት ጊዜ አለ። ክርስቲያንነታችንን ባለመደበቃችን ሥራ ወይም የትምህርት ዕድል የምንነፈግባቸው ጊዜያት አሉ ወይም ትምህርታችንን ለመቀጠል እንቸገራለን፥ ነገር ግን ብናጭበረብር ወይም እምነታችንን ብንደብቅ ይህንን ሁሉ የማግኘት ዕድላችን ሰፊ ይሆን ነበር። ባል ሚስቱንና ልጆቹን ትቶ በሞት ያልፋል። ከኃጢአት ባሕርይ ጋር የማያቋርጥ ትግል ይካሄዳል። ከዚህ ሁሉ በላይ፥ የክርስቶስ ተከታዮች በመሆናችን የማያቋርጥ ጥቃትና ስደት ይደርስብናል። እስከ መጨረሻው ድረስ በታማኝነት እንድንጸና የሚያደርገን ምንድን ነው? ጳውሎስ ሁኔታዎች አመቺ በማይሆኑባቸው ጊዜያት ሳይቀር በእምነታችን እንድንጸና የሚያደርጉትን የድነት (ደኅንነት) ሂደትና ፍጻሜ እውነቶች ገልጾአል።

ሀ. የእግዚአብሔር ልጆች ከክርስቶስ ጋር ይከብራሉ (ሮሜ 8፡18-25)። የሥነ መለኮት ምሁራን ድነትን (ደኅንነትን) በሦስት የጊዜ አስተሳሰቦች (frames) ይከፍላሉ። በክርስቶስ አምነን ከኃጢአታችን የዳንንበት «የአንድ ጊዜ» ኃላፊ የድነት ገጠመኝ አለ። ይህም ጳውሎስ በሮሜ 1-5 እንዳብራራው፥ መጽደቅ ይባላል። ከዚያም ከኃጢአት ኃይል እየተላቀቅን በቅድስና የምናድግበት «ቀጣይ» የድነት ልምምድ አለ። ይህም መቀደስ ይበላል። ጳውሎስ ስለ መቀደሱ በሮሜ 6፡1-8፡17 አስተምሯል። አሁን ጳውሎስ ወደ መንግሥተ ሰማይ ደርሰን ከምድራዊ ትግሎቻችን ሁሉ ስለምናርፍበት ጊዜ ማብራራት ይጀምራል፡፡ እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስን የምንመስል ቅዱሳን ልጆች እንሆናለን (1ኛ ዮሐ 3፡2 አንብብ።) ይህም «መከበር» ይባላል።

ጳውሎስ ይህን ክፍል የሚጀምረው፥ «አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾችን ነን» በሚል ማስጠንቀቂያ ነው (ሮሜ 8፡17)። ብዙ ክርስቲያኖች ክርስቶስን በመከተላችን ችግሮቻችን ሁሉ ይወገዳሉ ብለው ያስተምራሉ። በሽታም ሆነ ድህነት እንደማያጠቃን ያስባሉ። ሀብትን እንደምናካብትና ከስደት እንደምንተርፍ ያምናሉ። ጳውሎስ ግን ከክርስቶስ ጋር አብረን የምንወርስ ከሆነ፣ አሁን የመከራው ተካፋዮች መሆን እንዳለብን ያስጠነቅቀናል። ጳውሎስ ሁኔታዎችን በተስፋ መቁረጥ ወይም እንደ ዕድል ቆጥሮ በመቀበል ፈንታ እነዚህ ጊዜያት እንዴት ትርፋማ እንደሆኑ ይናገራል።

አዲስ ኪዳን ክርስቲያን በማንኛውም ጊዜ መከራን ሊቀበል እንደሚችል ያስተምራል። በተለይም ለእምነቱ መከራ በሚቀበልበት ጊዜ እውነተኛው የመከራ ተቀባይ ክርስቶስ እንደሆነ ያስተምራል። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ስለሆነች፥ ቤተ ክርስቲያን ስትሠቃይ እርሱም ይሠቃያል። የተፈጥሮ ዝንባሌያችን ግን ከስደት ለመሸሽ ይጥራል። ጳውሎስ ግን ክርስቶስ በሚከብርበት ጊዜ እኛም የተዘጋጀልንን ክብር የምናገኘው ወደ ሕይወታችን የሚመጣውን መከራ (ሥጋዊ ችግሮችና ስደት) ከተቀበልን ብቻ መሆኑን ያስረዳል።

ጳውሎስን ጨምሮ መከራን የሚወድ ማንም ሰው የለም። (ጳውሎስ ለወንጌል ሲል የተዘረዘሩትን መከራዎች ሁሉ ተቀብሏል። ከ2ኛ ቆሮንቶስ 11፡16-33 አንብብ።) ነገር ግን ጳውሎስ ጊዜያዊውን ምድራዊ መከራ ክርስቶስን በታማኝነት ለሚከተሉ ሰዎች ከተዘጋጀው ዘላለማዊ ክብርና ሽልማት ጋር ያነጻጽራል። በ2ኛ ቆሮንቶስ 4፡16-18 ጳውሎስ መከራዎቹ «ቀላል» እና «ጊዜያዊ» መሆናቸውን ገልጾአል። በአዳም ኃጢአት ምክንያት የተጎዱትን ጨምሮ ፍጥረት ሁሉ ክርስቶስ በክብሩ የሚመለስበትን ጊዜ አብሮን ይጠብቃል። ብዙ ዓይነት መከራዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ሥቃይ፥ መከራ፥ መለየትና ሞት የማይኖርበትን የነጻነት ጊዜ እንናፍቃለን። እንዲሁም፥ ሙሉ ለሙሉ ከኃጢአት ባሕሪያችን የምንገላገልበትንና ክርስቶስን እንደሚገባ የምናከብርበትን ጊዜ እንናፍቃለን። ዛሬ ተስፋ ቆርጠን ለኃጢአት ባሕሪያችን እንዳንገዛ የሚያደርገን አንድ ቀን የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች በሙሉ በዓይኖቻችን ፊት ይፈጸማሉ የሚል እምነት ነው። ግለኝነታችንን ለማሸነፍና የኃጢአት ተፈጥሯችንን ላለመስማት ከፈለግን ዓይኖቻችንን ወደፊት በሚሆነው ሰማያዊ ክብር ላይ ማነጣጠር አለብን።

ለ. ከኃጢአት ጋር በምናደርገው ትግልና በመከራችን ወቅት መንፈስ ቅዱስ በቅርባችን ሆኖ ይማልድልናል (ሮሜ 8፡26-27)። አንዳንድ ሰዎች በሚጸልዩበት ጊዜ የሚያሰሙት የመቃተት ድምፅ መንፈስ ቅዱስ ለእነርሱ መጸለዩን እንደሚያሳይ ይናገራሉ። የጳውሎስ ትኩረት ግን ይሄ አልነበረም። እርሱ የሚናገረው ስለ መከራ፥ በተለይም ከኃጢአት ጋር ስንታገል ስለሚገጥመን መከራ ነው። በእነዚህ ጊዜያት ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። በውስጣችን የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ እኛን ከማወቁም በላይ፥ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፈቃድም ያውቃል። አንዳንድ ጊዜ የራቀን ቢመስልም እንኳ እርሱ ከእኛ የራቀ አይደለም። ይልቁንም በጸሎታችን አብሮን ይቃትታል። ራስ ወዳድነት ከሚታይባቸው ጸሎቶቻችን በተቃራኒ፥ የመንፈስ ቅዱስ ጸሎት እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ የሚካሄድ በመሆኑ ምላሽን ያገኛል። ይህም ታላቅ ተስፋ ሊያስጨብጠን ይገባል።

ሐ. እግዚአብሔርን ብንወድደው ሁሉንም ነገር ወደ በጎ እንደሚለውጠው ተስፋ ሰጥቶናል (ሮሜ 8፡28)። አንዳንድ ክርስቲያኖች ይህን ጥቅስ በተሳሳተ መንገድ ይገነዘባሉ። ይህ ጥቅስ እግዚአብሔር በክርስቲያን ላይ ምንም ዓይነት ክፉ ነገር እንደማይደርስበት የሚገልጽ መሆኑን ይናገራሉ። ጳውሎስ ክርስቲያን በስደት ሊሞት እንደሚችል ስለሚናገር፥ እግዚአብሔር ከየትኛውም ዓይነት ክፉ ነገር ይጠብቀናል ማለቱ አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንዳለና ሁሉንም ነገር እንደሚቆጣጠር ማወቅ ይኖርብናል። በታማኝነት ካከብርነው እግዚአብሔር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለበጎነት ሊጠቀም ይችላል። ያም በጎነት መንፈሳዊ ዕድገት ወይም የሌላ ሰው ድነትን (ደኅንነትን) ማግኘት ሊሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ ግን በጎነቱን ምን እንደሆነ አናውቅም። ነገር ግን እግዚአብሔር በልጆቹ ሕይወት ውስጥ በቅርብ እንደሚሠራና የሚከሰተውን ነገር ሁሉ እንደሚቆጣጠር ማወቅ እንችላለን።

መ. እግዚአብሔር ከአንድ ሰው ጋር ግንኙነት የሚያደርገው በአጋጣሚ ወይም በግለሰቡ ምርጫ ብቻ ሳይሆን በራሱ አሠራር ነው (ሮሜ 8፡28-30)። ብዙውን ጊዜ ድነትን (ደኅንነትን) ከሰው አንጻር በመመልከት፥ እንዴት በእግዚአብሔር እንዳመንን እናስባለን። ጳውሎስ ግን በመከራ ውስጥ ለነበሩት ክርስቲያኖች ድነትን ከእግዚአብሔር አንጻር ለማሳየት ፈለገ። በሕይወታቸው ውስጥ ችግሮች መከሰታቸው በእግዚአብሔር መተዋቸውን አያመለክትም። ጳውሎስ እግዚአብሔር በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ የሚያስደንቅ ተግባር እንደሚያከናውን አስረድቷል። ጳውሎስ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ አማኝ እንዳከናወነ የዘረዘራቸውን የድነት (ደኅንነት) ደረጃዎች ከዚህ በታች ተመልከት።

 1. እግዚአብሔር በዓላማው መሠረት ጠርቶናል። በዓለም ውስጥ ከሚገኙ በቢሊዮኖች ከሚቆጠሩ ሰዎች እግዚአብሔር አንተን መርጦሃል። ለምን? ከሌሎች ስለምትሻል ነው? አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር በፍቅሩ ስለመረጠህ ነው።
 2. እግዚአብሔር አስቀድሞ አውቆሃል። ከመወለድህ በፊት ጀምሮ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር የቃል ኪዳን ግንኙነት አድርጓል። በዕብራይስጥ የዚህ ቃል ትርጉም እግዚአብሔር በእርሱ እንደምታምን ያውቃል ከማለት ያለፈ ነው። እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ለማድረግ የወሰነውን ግንኙነት ያመለክታል።
 3. የልጁን መልክ እንድትመስል አስቀድሞ ወስኗል። በክርስቶስ ከማመንህ በፊት፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ግንኙነት እንደሚያደርግ አስቀድሞ ወስኗል። መንግሥተ ሰማይ በደረስህ ጊዜ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን ትመስል ዘንድ በሕይወትህ ውስጥ ለመሥራት ቃል ገብቷል። አመለካከቶችህ፥ ባሕርይህና ተግባራትህ የክርስቶስን ይመስሉ ዘንድ ይለወጣሉ።
 4. እግዚአብሔር በጊዜው ጠርቶሃል። እግዚአብሔር ጥሪውን እንኳ ለመስማት የማትችል ሙት ኃጢአተኛ ሆነህ ሳለ፥ መንፈሳዊ ዓይኖችህንና ጆሮዎችህን በመክፈት፥ ጠራህና በእርሱ እንድታምን አድርጎሃል።
 5. እግዚአብሔር ለፈጸምሃቸው ኃጢአቶች ሁሉ ተጠያቂ እንዳልሆንህ በማወጅ አጽድቆሃል።
 6. እግዚአብሔር አክብሮሃል። ድነትህ (ደኅንነትህ) በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት አስተማማኝ ነው። እርሱ በሕይወትህ መልካሙን ሥራ ከጀመረ ወዲያ እንደሚፈጽመው ቃል ገብቷል (ፊልጵ. 1፡6)። ማንም ከእጁ ሊነጥቅህ እንደማይችል ተናግሮሃል (ዮሐ. 10፡28-29)። በተጨማሪም፥ እግዚአብሔር ወደ መንግሥተ ሰማይ እስክትደርስና ለእግዚአብሔር ልጅ የተዘጋጀውን ክብር እስክትቀበል ድረስ የድነት (ደኅንነት) ሂደቱ እንደማይቋረጥ የተስፋ ቃሉን ሰጥቷል።

ይህ ምናልባት እንግዳ ነገር ሊመስልህ ይችላል። በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙዎቻችን ትኩረት የምንሰጠው በሰዎች የማመን ኃላፊነት ላይ ነው። ጳውሎስ ግን ድነትን (ደኅንነትን) ከመለኮታዊ እይታ አንጻር ይመለከታል። ይህም እግዚአብሔር ሰዎች ከማመናቸው በፊት ጀምሮ ወደ መንግሥተ ሰማይ እስከሚደርሱበት ጊዜ ሙሉ በሙሉ ተግቶ የሚሠራ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ምናልባትም የድነት ሥራ እንዴት እንደሚካሄድ፥ በድነት ሥራ ውስጥ ምን ድርሻ እንዳለንና (እንድናምንና ፍቃዱን እንድንፈጽም ታዘናል)፥ የእግዚአብሔርም ድርሻ ምን እንደሆነ በትክክል አናውቅም ይሆናል። ጳውሎስ ግን በእግዚአብሔር ፍቅርና ወደ ቤተሰቡ ከመጣን ወደ ሰማይ እስክንደርስ ድረስ እንደሚጠብቀን እርግጠኞች ልንሆን እንደምንችል ገልጾአል።

ሠ. ከእግዚአብሔር ፍቅር ምንም ነገር ሊለየን አይችልም (ሮሜ 8፡31-39)። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ እጅግ አጽናኝ ከሆኑ ክፍሎች አንዱ ነው። ሁላችንም በቃል ልናጠናቸውና እግዚአብሔር የማይጠነቀቅልን በሚመስለን ጊዜ ሁሉ ልንናገራቸው ይገባል። ጳውሎስ እግዚአብሔር በሰማይ ውስጥ ተቀምጦ ስለ እኛ ከማስብ የሚቆጠብ የሚመስልባቸው ጊዜያት እንዳሉ ያውቅ ነበር። ምንም ያህል ተግተን ብንጸልይ የምንፈልገውን ምላሽ አናገኝም። ጳውሎስ እግዚአብሔርን ከመጠራጠር ወይም በዚህ ሁኔታ ውስጥ የእግዚአብሔር ዓላማ ምን እንደሆነ ለማወቅ ከመሞከር ይልቅ እግዚአብሔር ለእኛ ስላለው አስደናቂ ፍቅሩ እንድናስብ ያበረታታናል። ጳውሎስ ከዚህ አስደናቂ የእግዚአብሔር ፍቅር ይመነጫሉ ያላቸውን ነገሮች ቀጥለን እንመልከት።

 1. እግዚአብሔር ለኃጢአታችን የመጨረሻውን መሥዋዕትነት ከፍሏል። እግዚአብሔር ከፍቅሩ የተነሣ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ እንዲሞት ልኮታል። የሚያጋጥሙን ሌሎች ችግሮች ሁሉ ለእግዚአብሔር ከእኛ ኃጢአት ያነሰና ዝቅ ያለ ዋጋ የሚያስከፍሉ ናቸው። ስለሆነም፥ በአንድ ሁኔታ ውስጥ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት እንደሚንጸባረቅ በማናውቅበት ጊዜ እንኳ አባታችን እጅግ የተወደደውን የትኛውንም ነገር እንደማይነፍገን ልናስታውስ ይገባል። ወላጆች ልጆቻቸውን ቢወዱም እንኳ የሚጠይቋቸው ነገሮች ሁሉ እንደማይጠቅሟቸው ስለሚያውቁ ይነፍጓቸዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ እግዚአብሔርም ለእኛ ከሁሉም የሚሻለውን ያውቃል። በፍቅሩ ለእኛ ከሁሉም የሚሻለንን እንጂ የጠየቅነውን ሁሉ አይሰጠንም።
 2. እግዚአብሔር ያለፈውን፥ የአሁኑንና የወደፊቱን ኃጢአታችንን ሁሉ ሙሉ በሙሉ ይቅር ብሎናል። እግዚአብሔር የመጨረሻው ይግባኝ የማይጠየቅበት ዳኛ ስለሆነና ኃጢአታችንን ሙሉ በሙሉ ይቅር ስላለ፥ በእነዚያ ኃጢአቶች ምክንያት ማንም ወደ ሲኦል ሊሰድደን አይችልም።
 3. ክርስቶስ ለኃጢአታችን ከመሞቱ በተጨማሪ፥ በእኛ ፈንታ ተግባሩን ይቀጥላል። እንደ መንፈስ ቅዱስ እንደሚማልድልን ሁሉ፥ ክርስቶስም በሰማይ ሆኖ ይማልድልናል። ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ ባለማቋረጥ በሕይወታችን ውስጥ የሚሠሩ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ሁሉንም አሸንፈን ወደ መንግሥተ ሰማይ እንድንደርስ እንደሚረዳን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
 4. በምድርም ሆነ በሰማያዊ ስፍራ ያለው መንግሥት ወይም ገዥ (ሰይጣን)፥ እንዲሁም ምድራዊ ችግር (መገደል እንኳ ቢሆን)፥ እግዚአብሔር ለልጆቹ ካለው ፍቅር ሊለየን አይችልም። በበሽታ ወይም በስደት ምክንያት ልንሞት ብንችልም፥ እነዚህ እግዚአብሔር ወደ ዘላለማዊ ቤታችን እኛን ለመውሰድ የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች እንደሆኑ ልንገነዘብ ይገባል። እንደ ሰይጣን፥ የማያምኑ ሰዎች ወይም ክፉ መንግሥታት ባሉ ጠላቶች እየተጠቃን ቢመስለንም፥ አሸናፊዎቹ እኛው ነን። ፍጻሜያችን የተረጋገጠ ነው።

ምክንያቱም እኛ የዘላለማዊው ንጉሥ መንፈሳዊ ልጆች ነን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ ጓደኛህ በአደጋ ምክንያት ሚስቱንና ልጁን አጥቷል እንበል። ከዚህ ክፍል፥ እምነቱ በክርስቶስ እንዲጸና ምን ብለህ ታበረታታዋለ? ለ) በግልህ ተስፋ ቆርጠህ እግዚአብሔር እንደማያስብልህ ያሰብክበትን ጊዜ አስታውስ። በእግዚአብሔር ፍቅር ላይ የጠበቀ እምነት መያዝ እነዚህን የተስፋ መቁረጥ ጊዜያት እንድናሸንፍ የሚረዳን እንዴት ነው? ሮሜ 8፡31-39ን በቃልህ አጥና።

የውይይት ጥያቄ፡- እስካሁን በሮሜ ውስጥ የተመለከትናቸውን ጠቃሚ ቃላት አብራራ። ሀ) መጽደቅ፥ ለ) መቀደስ፥ ሐ) መክበር፥ መ) ቁጣውን ማብረድ፥ ሠ) እምነት፥ ረ) ስርየት። የቃላቱን ፍቺ ካላወቅህ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተጠቀም።

የውይይት ጥያቄ፡- ጳውሎስ በሮሜ 1-8 ያስተማረውን በራስህ አገላለጽ ጻፍ። ሰው ከኃጢአት የሚድነው እንዴት ነው? ኃጢአትን ሊያሸንፍ የሚችለውስ እንዴት ነው? በመከራ ውስጥ በልበ-ሙሉነት ሊኖር የሚችለው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

አማኞች ብዙውን ጊዜ ከኃጢአት ባሕርያቸው ጋር ይዋጋሉ። ለሽንፈትም ይዳረጋሉ (ሮሜ 7፡7-25)።

ጳውሎስ ሕጉ የገለጣቸው የኃጢአት ምኞቶች በሕይወታችን ውስጥ የሚታየው የኃጢአት ችግር አካላት መሆናቸውን ገልጾአል። የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን ለሚያከብረው አይሁዳዊ ይህን መቀበሉ አስቸጋሪ ነበር። የእግዚአብሔር ሕግ መልካም ነው። መልካም የሆኑት የእግዚአብሔር ሕግጋት እንዴት የክፋት መሣሪያ ሊሆኑ ይችላሉ? ጳውሎስ ችግሩ ያለው ከሕጉ ሳይሆን ከኃጢአት ባሕሪያችንና ለእግዚአብሔር ሕግጋት ከሚሰጠው ምላሽ እንደሆነ ገልጾአል። ለልጅ፥ «ድስቱ ይፈጅሃልና አትንካው» ብትለው፥ ምን ያደርጋል? እጁን ዘርግቶ ወዲያውኑ ወደ ድስቱ ሄዶ ይነካዋል። የሕግም ሁኔታ እንዲሁ ነው። ጳውሎስ የራሱን ገጠመኝ ጠቅሶ አሳቡን ያብራራል። ይህ ምናልባትም በ13 ዓመቱ መደበኛ የሕግ ትምህርት በሚከታተልበት ጊዜ የገጠመው ሁኔታ ሊሆን ይችላል። ሕጉ እንደ እግዚአብሔር መልካም፥ ቅዱስና ጻድቅ ነው። ነገር ግን የኃጢአት ባሕሪያችን ስለ ሕግ በሚሰማበት ጊዜ፥ በመጀመሪያ ማድረግ የምንፈልገው ነገር ሕጉን መጣስ ነው፡፡ ሕይወትን ሊያመጣልን የተገባው ሕግም በተዘዋዋሪ መንገድ ግለሰቡ ኃጢአት ሠርቶ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንዲጋፈጥ ይገፋፋዋል። ችግሩ ያለው ከሕጉ ሳይሆን ከኃጢአተኛው ባሕሪያችን ነው። ስለሆነም፥ ሕጉ የዘላለምን ሕይወት ለማምጣት የሚያገለግል መሣሪያ ሳይሆን፥ የሰውን ልብ ኃጢአተኝነት በማሳየት የእግዚአብሔርን ጸጋና ጽድቅ እንዲሻ የሚያደርግ ነው።

ሮሜ 7፡14-25 በክርስቲያኖች መካከል ብዙ ክርክር አስነሥቷል። ይህ የጳውሎስ ምስክርነት ነው ወይስ ምሳሌ ብቻ? ጳውሎስ የሚጽፈው ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ስለተከሰተው ሁኔታ ነው ወይስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት? ይህ ጳውሎስ ክርስቶስን አግኝቶ ከመፈወሱ በፊት ያጋጠመው ሁኔታ እንደሆነ የሚናገሩ ሰዎች የሚከተሉትን አሳቦች ይጠቅሳሉ። 1) የኃጢአት ባሪያ ለመሆን የተሸጥሁ፥ በእኔ ምንም መልካም የለም፥ ምንኛ ጎስቋላ ነኝ የሚሉ ዓይነት አገላለጾች ለክርስቲያኖች ያገለገሉ አይደሉም። 2) ጳውሎስ በሮሜ 8 ውስጥ ከሚያስተምረው አሳብ ጋር አይመሳሰልም። 3) እግዚአብሔር የሚሰጠን ድነት (ደኅንነት) ከኃጢአት ያወጣናል እንጂ በባርነት ውስጥ አያኖረንም። ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ያጋጠመውን ሁኔታ እየገለጸ ነው የሚሉት ደግሞ የሚከተለውን አሳብ ይሰነዝራሉ። 1) ጳውሎስ የተጠቀመባቸው የአሁኑ ጊዜ መግለጫ ግሦች የድሮውን ሳይሆን የአሁኑን ሕይወት ያሳያሉ። 2) በዓውደ ንባቡ ውስጥ ጳውሎስ የሚናገረው አንድ ሰው ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ሳይሆን ክርስቲያን ከሆነ በኋላ እንዴት የተቀደሰ ሕይወት እንደሚኖር ነው። 3) ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር ሕግጋት መልካምነትና ለእግዚአብሔር ሕግጋት መልካምነት የሰጠው ምስክርነት ክርስቲያን ያልሆነ ሰው የሚያደርገው ነው።

24ኛ ጥያቄ ሀ) በሕይወትህ እንደ ጳውሎስ ከኃጢአት ጋር ታግለሃል? ትግሉ እንዴት እንደተካሄደ ግለጽ። ለ) ጳውሎስ የጠቀሰው ገጠመኝ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ወይስ በኋላ የተፈጸመ ይመስልሃል? ለምን?

ጳውሎስ አንድ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ሕይወቱ እያደገ በሚሄድበት ጊዜ ስለሚያጋጥመው ተከታታይ ጦርነት የሚናገር ይመስላል። አንድ ሰው ክርስቲያን ከሆነበት ጊዜ አንሥቶ፥ ከኃጢአተኛ ተፈጥሮው ጋር ለመታገል እንደሚገደድ ገላትያ 5፡16-26 ያስረዳል። እግዚአብሔርን ለማክበር የሚፈልገው አዲሱ መንፈሳዊ ባሕርዩ ባለማቋረጥ ከአሮጌው የኃጢአት ባሕርዩ ጋር ይዋጋል። ጳውሎስ ችግሩ ትክክል የሆነውንና ያልሆነውን አለማወቁ ሳይሆን ለመፈጸም አለመቻሉ እንደሆነ ገልጾአል። ንጹሕና ቅዱስ ለመሆን የሚደረገው ጦርነት ቀጣይነት ያለው ሲሆን፥ ብዙውን ጊዜ የኃጢአት ባሕርይ የሚያሸንፍ ይመስላል። ለመፈጸም የማንፈልጋቸውን ኃጢአቶች እንፈጽማለን።

(ማስታወሻ፡ «አሮጌ ተፈጥሮ» እና «ሥጋ» የሰውን ውጫዊ የሥጋ አካል የሚያመለክቱ አይደሉም። ነገር ግን በውስጣችን ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ለማመፅ የሚፈልገውንና ከመገዛት ይልቅ መግዛት የሚሻውን የኃጢአት ባሕርይ የሚያመለክቱ ናቸው። የተለያዩ የኃጢአት ውጤቶች የሚመጡት ከዚህ የኃጢአት ባሕርይ ነው።)

ሁኔታው ተስፋ የሌለው ነውን? ለዚህ የማያቋርጥ ውጊያ ምላሽ አለን? የእግዚአብሔርን ሕግ ለመታዘዝ እየፈለግሁ ብዙውን ጊዜ የምተላለፍ ከሆነ፥ እግዚአብሔር የሚመለከተኝ እንዴት ነው? ይኮንነኛል? መልሱ በሮሜ 8 ውስጥ ሰፍሯል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ከኃጢአት ተፈጥሯችን ጋር ያለን ግንኙነትና እግዚአብሔር ኃጢአትን እንድናሸንፍ እንዴት እንደሚረዳን መገንዘብ (ሮሜ 6፡1-7፡6)

ዘሪሁን ወደ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የታወቀ ኃጢአተኛ ነበር። ብዙውን ጊዜ ጠጥቶ የሚሰክር ሲሆን፥ ወደ ሴተኛ አዳሪዎች ይሄድ፥ ዕጽ ይወስድና መጥፎ ዐመሉን ለማስታመም ገንዘብ ይሰርቅ ነበር። አንድ ሰው በክርስቶስ ካመነ እግዚአብሔር ኃጢአቶችን ይቅር እንደሚል ሲገለጽለት፥ ዘሪሁን በክርስቶስ አመነ። በዚህ ጊዜ የክርስቶስ ፍቅርና ጸጋ አስደነቀው፥ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ልጅ ሊመራ ስለሚገባው ሕይወት ያስተማረው ሰው አልነበረም። ዘሪሁን ኃጢአቱን እየፈጸመ የክርስቶስን ይቅርታ ከመጠየቅ የተለየ ነገር እንደማይጠበቅበት አስቦ ነበር። እግዚአብሔር ቸር ስለሆነ ኃጢአታችንን ይቅር እንደሚል እውነት ነው። ዘሪሁን ግን እግዚአብሔር የጠራው የተቀደሰ አኗኗር እንዲኖር እንደነበረ አያውቅም ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዘሪሁን ስለ እግዚአብሔር ጸጋ የተሳሳተ ግንዛቤ መያዙ ወደ ተሳሳተ ክርስቲያናዊ አኗኗር እንዴት እንደመራው ግለጽ። ለ) በሕይወትህ አሁንም ከኃጢአት ጋር እንዴት እንደምትታገል አብራራ። ገላ. 5፡16-26 አንብብና ይህ መንፈሳዊ ትግል በሕይወትህ ውስጥ እንዴት እንደታየ ግለጽ።

«የእኔ ኃጢአት የእግዚአብሔርን የይቅርታ ኃይል ካሳየ፥ ይህ የእግዚአብሔር ጸጋ በሕይወቴ የበለጠ እንዲገለጥ የበለጠ ኃጢአት መሥራት አለብኝ ማለት ነውን? ድነት (ደኅንነት) ንጹሕ ሕይወት በመኖር ሳይሆን በእምነት

ብቻ የሚገኝ የእግዚአብሔር ነፃ ስጦታ ከሆነ፥ የተቀደሰ አኗኗር የመኖር ትርጉሙ ምንድን ነው?» ጳውሎስ ስለ ድነት (ደኅንነት) የሰጠውን ትምህርት ለመረዳት በሚሞክሩበት ጊዜ የአይሁድ ክርስቲያኖች ያስቸገሯቸው ጥያቄዎች እነዚህ ነበሩ። «ብዙ ኃጢአት በሚኖርበት ጊዜ የእግዚአብሔር ጸጋ በብዛት ይገለጣል የሚለው እምነት ክርስቲያኖችን ወደ በለጠ ኃጢአት አይመራምን? ሲሉ አሰቡ (ሮሜ 5፡20)። ብዙዎቹም ግራ ተጋቡ። አንዳንድ ክርስቲያኖች የጳውሎስን ትምህርት በተሳሳተ መንገድ በመረዳታቸው ብዙ ኃጢአት በሠራን ቁጥር እግዚአብሔር ጸጋውንና ይቅርታውን እንዲያሳይ የበለጠ ዕድል እንሰጠዋለን ወደሚል አቅጣጫ ያዘመሙ ይመስላል። ስለሆነም፥ አንድ ሰው የእግዚአብሔርን ይቅርታ እስከጠየቀ ድረስ ብዙ ኃጢአት መሥራቱ አሳሳቢ አይደለም ብለው ደመደሙ። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከአባቱ ሚስት ጋር ግልጽ ኃጢአት የሚያደርግ ግለሰብ በመካከላቸው እንዲኖር በፈቀዱ ጊዜ እግዚአብሔር ለኃጢአት የሚያሳየውን ጸጋና ይቅርታ እያሳየን ነው ብለው አስበው ነበር (1ኛ ቆሮ. 5፡1-13)።

ሰዎች እግዚአብሔርን ለማስደሰት ብዙ ሰው ሠራሽ ደንቦችን መከተላቸው ትክክል እንዳልሆነ ሁሉ፥ ክርስቲያኖች የተቀደሰ ሕይወት መምራት የለብንም ብለው በኃጢአት መመላለሳቸውም አደገኛ ነው። ጳውሎስ ወንጌሉንና በመስቀል ላይ የተፈጸመውን ነገር በትክክል መገንዘቡ በንጽሕና እንድንኖር የሚያግዝ መሆኑን አመልክቷል። የእግዚአብሔር ጸጋና የኃጢአት ይቅርታው የኃጢአት ሕይወት ለመምራት ማመካኛ አይሆነንም።

የውይይት ጥያቄ፡– ሮሜ 6—7 አንብብ። ሀ) እንደ ዘሪሁን ላሉ ክርስቲያኖች ለኃጢአት አነስተኛ ግምት መስጠትና እግዚአብሔር ይቅር ይለኛል በሚል አሳብ በኃጢአት መቀጠሉ ስሕተት የሆነበትን ምክንያት ጠቅለል አድርገህ ግለጽ። ለ) ይህ ክፍል ስለ አማኝና ስለ ኃጢአት ምን ያስተምራል?

በ ሮሜ 6፡1-8፡39 ውስጥ ጳውሎስ ወንጌሉ የተቀደሰ ሕይወት እንድንኖር እንዴት እንደሚረዳን ያብራራል፡፡ ሮሜ 1-5፥ «አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ሕይወቱን የሚያስተካክለው እንዴት ነው? እንዴትስ እርሷ ልትድን ወይም ሊድን ይችላል?» ለሚለው ጥያቄ ጳውሎስ መልስ በመስጠት ላይ ነበር። አሁን በሮሜ 6-8 ጳውሎስ፥ «ከዳንሁ በኋላ፥ ከኃጢአት ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ይኖረኛል?» የሚለውን ጥያቄ ሲመልስ፥ በሦስት እውነቶች ላይ አተኩሯል። አንድ ሰው በክርስቶስ ላይ እውነተኛ እምነት ሲኖረው የሚከተሉት ነገሮች ተግባራዊ ይሆናሉ።

1) በክርስቲያኖች ላይ የሚኖረው የኃጢአት ኃይል ስለተሰበረ እንደ ቀድሞው ኃጢአትን ለመፈጸም አንገደድም። ከኃጢአት ቁጥጥር ነፃ ነን።

2) አሁን ክርስቶስን ለማስከበር በመሻት ባሪያዎቹ ሆነን እንመላለሳለን። የተቀደሰ ሕይወት በመኖር ክርስቶስን እናስከብራለን።

3) እግዚአብሔር የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ የተቀደሰ ሕይወት የምኖርበትን ኃይል ይሰጠናል። ከእንግዲህ ኃይል አጥተን በኃጢአታችን አንቀጥልም። በሕይወታችን ኃጢአትን አሸንፈን በቅድስናና ክርስቶስን በመምሰል ልናድግ እንችላለን።

ከኃጢአት ተፈጥሯችን ጋር ያለን ግንኙነትና እግዚአብሔር ኃጢአትን እንድናሸንፍ እንዴት እንደሚረዳን መገንዘብ (ሮሜ 6፡1-7፡6)

ጳውሎስ የሚከተሉትን ዐበይት ነጥቦች በማቅረብ ለምን በኃጢአት ሕይወታችን ልንቀጥል እንደማንችል የሚከራከርበት መንገድ ውስብስብ ነው።)

ሀ. በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት፥ በክርስቶስ ባመንህ ጊዜ ከእርሱ ጋር ተዋህደሃል። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ አንተም ለአሮጌው የኃጢአት ሕይወትህ ሞተሃል። ክርስቶስ ለአዲስ ሕይወት በተነሣ ጊዜ፥ አንተም እግዚአብሔርን ለምትታዘዝበት አዲስ ሕይወት ተነሥተሃል (ሮሜ 6፡1-11)። ክርስቶስ በመስቀል ላይ እንደ ሞተ ሁሉ፥ አንተም በክርስቶስ ላይ ባለህ እምነት ለአሮጌው ሕይወትህ ሞተሃል (ተሰቅለሃል)። በዚያን ጊዜ በሕይወትህ ላይ የነበረው የኃጢአት ኃይልና የበላይነትም ሞቷል። ከእንግዲህ፥ «የኃጢአት ባሪያ» አይደለህም። ክርስቶስ የሞትን ኃይል አሸንፎ ከሞት እንደ ተነሣ ሁሉ፥ አንተም ኃጢአት ጨርሶ ለተደመሰሰበት ለአዲስ ሕይወት ከሞት ተነሥተሃል። አሁን ሕይወትህን ለእግዚአብሔር እየታዘዝህ የመኖር ነጻነት አለህ።

ጳውሎስ ይህንን አማኙ ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር የሚተባበርበትን ሁኔታ «በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ መጠመቅ» ሲል ይጠራዋል። ይህ አገላለጽ የሚያሳየው የአማኙን የመጀመሪያ የድነት (ደኅንነት) ልምምድ እንጂ የውኃ ጥምቀት አይደለም። አሁን በአብያተ ክርስቲያናችን አንድ ሰው በክርስቶስ ካመነ በኋላ እስኪጠመቅ ድረስ ለስድስት ወራት ወይም ለአንድ ዓመት የክትትል ትምህርት እንዲወስድ ይደረጋል። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ግን ከዚያ በተቃራኒ ያመኑትን ወዲያውኑ ታጠምቅ ነበር። ስለሆነም፥ አዲስ ኪዳን ብዙውን ጊዜ እምነትንና ጥምቀትን አንዳንድ ክስተት አጠቃልሎ ድነት (ደኅንነት) ሲል ይጠራዋል (የሐዋ. 2፡38)።

ጳውሎስ በእምነት ወደ ክርስቶስ በተመለስን ጊዜ የተከሰተውን ሁኔታ ለመግለጽ የድርጊት ፈጻሚ የኃላፊ ጊዜ መግለጫ ግሥ ይጠቀማል። ብናስተውለውም ባናስተውለውም፥ በሕይወታችን ተግባራዊ ብናደርገውም ባናደርገውም፥ በሞቱና በትንሣኤው ከክርስቶስ ጋር ተባብረናል። በመሆኑም፥ አሁን የኃጢአት ተፈጥሯችን ስለማይቆጣጠረንና ለመታዘዝ ልንመርጥ ስለምንችል፥ ኃጢአትን መፈጸም የለብንም።

በሕይወታችን ኃጢአትን ድል የምናደርግበት የመጀመሪያው እርምጃ ኃጢአት የመፈጸም ግዴታ እንደሌለብን ማወቅ ነው። ጳውሎስ ለኃጢአት ሞተን በክርስቶስ በኩል ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደሆንን እንድንቆጥር መክሮናል (ሮሜ 6፡11)። ለእግዚአብሔር ንጹሕ ሕይወት ለመኖር አንችልም ብለን ካሰብን፥ ሰይጣንና የኃጢአት ተፈጥሯችን በቀላሉ ያሸንፉናል። ነገር ግን እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ልንመርጥ እንደምንችል ካወቅን፥ ኃጢአትን ለማሸነፍና በቅድስና ለማደግ የመጀመሪያውን እርምጃ ወስደናል ማለት ነው።

ለ. አማኞች ከኃጢአት ቁጥጥር ነፃ ስለሆንን፥ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ፥ የተቀደሰ ሕይወት ለመምረጥና የጽድቅ ባሪያዎች ለመሆን የመምረጥ ብቃት አለን (ሮሜ 6፡12-23)። ጳውሎስ ከኃላፊ የጊዜ መግለጫ ጊዜ ወደ ቀጣይ የአሁን ጊዜ መግለጫ ግሥ መሸጋገሩን ማጤኑ ጠቃሚ ነው። ይህም ባለማቋረጥ ልንፈጽመው የሚገባን ቀጣይነት ያለው ትእዛዝ እንደ ሰጠን ያሳያል። በሕይወታችን ላይ ያለውን የኃጢአት ኃይል የመግደል ኃላፊነት ባይኖርብንም (ባመንን ጊዜ እግዚአብሔር ይህንኑ ስላደረገ)፥ በሕይወታችን ኃጢአትን ስለምናስተናግድበት ሁኔታ ግን ኃላፊነት አለብን። ጳውሎስ በኃጢአት ላይ ድል ማግኘታችን የሚወሰነው በምርጫችን እንደሆነ ያስረዳል። መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ትእዛዝ በሚሰጠን ጊዜ ሁሉ ምርጫ ልናደርግና የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንድናበረክት ያዘናል። ጳውሎስ አማኞች ባለማቋረጥ ሊፈጽሟቸው የሚገሷቸውን ሦስት ተግባራት ዘርዝሯል።

 1. መሻቱን ታሟሉለት ዘንድ ኃጢአት በሰውነታችሁ አይንገሥ። በጥንት ዘመን ሁለት ዓይነት ባሪያዎች ነበሩ። እነዚህም ያለ ምርጫቸው በትውልድ ባሪያዎች የሆኑና ለሚወዱት ሰው በራሳቸው ምርጫ ባሪያዎች የሆኑ ነበሩ። ጳውሎስ እግዚአብሔር በክርስቶስ ባመንን ጊዜ ለክፉ የኃጢአት ተፈጥሯችን በግድ ከምንገዛበት ሁኔታ እንዳወጣን ያስረዳናል። አሁን በፈቃዳችን የጽድቅ ባሪያዎች መሆን አለብን። እንደገና ለዚያ ክፉ የኃጢአት ተፈጥሮ ባሪያ መሆን ሞኝነት ነው። የኃጢአት ተፈጥሯችን ወደ ኃጢአት እንዲወስደን በምንፈቅድበት ጊዜ ሁሉ ባሪያዎቹ ለመሆን ፈቅደናል ማለት ነው።
 2. ብልቶቻችሁን ለኃጢአት አታቅርቡ። ሰይጣንም ሆነ የኃጢአት ተፈጥሯችን ኃጢአትን እንድናደርግ ከመፈተን አልፈው ሊያስገድዱን አይችሉም። ኃጢአትን የምንፈጽመው በምርጫችን ነው። ይህ ከአይጥ ወጥመድ ጋር ተመሳሳይ ነው። አይጥ ወደ ወጥመዱ እንድትገባ የሚፈትናት ምግብ እንጭምራለን እንጂ አይጧን በግድ በወጥመዱ እንድትያዝ ልናስገድዳት አንችልም። አይጧ ልትያዝ የምትችለው በፈተናው የተሸነፈች እንደሆነ ብቻ ነው። ጳውሎስ በፈተናው ወድቀን ሰውነታችንን ለኃጢአት እንዳናስገዛ ይመክራል። ምናልባትም ጳውሎስ የሚያስበው ብዙ ክርስቲያኖችን ስለሚፈትነው የወሲብ ኃጢአት ይሆናል።

በኃጢአት ላይ ድልን ለመቀዳጀት የሚያስችል ሁለተኛው እርምጃ እንደገና የኃጢአት ባሪያ ላለመሆን መወሰን ነው።

 1. ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ። ኃጢአት በባርነት እንዲገዛን ከማድረግ ይልቅ እንደ ጻድቅ ባሪያዎች ራሳችንን ለእግዚአብሔር ማቅረብ ይኖርብናል። ለእርሱ ካለን ፍቅር የተነሣ በፈቃዳችን ለእግዚአብሔር ባሪያዎች መሆን ይኖርብናል። ይህንንም የምናደርገው እንድ ባሪያ ጌታውን ለማስደሰት እንደሚኖር ሁሉ በየቀኑ እግዚአብሔር የሚፈልገውን በመፈጸም ነው። የኃጢአት ተፈጥሮ ከሚመራን መንገድ እየራቅን፥ እግዚአብሔር የሚፈልጋቸውን ነገሮች ማከናወን አለብን። ኃጢአት ሁልጊዜም ጥፋትን ያስከትላል። ለምሳሌ ያህል፥ ግንኙነቶችን፥ ባሕርይን፥ ቤተሰብን ያጠፋል።) ስለሆነም፥ ወደ ሕይወትና ቅድስና የሚወስደውን እግዚአብሔርን የመታዘዝ አቅጣጫ ልንከተል ይገባል። በኃጢአት ላይ ድልን ለመቀዳጀት የሚያስችለን ሦስተኛው እርምጃ እግዚአብሔርን ለመታዘዝና እርሱን ለማክበር ሕይወታችንን አሳልፎ መስጠት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ወሲባዊ ኃጢአት ለመፈጸም ተፈትነሃል እንበል። ጳውሎስ የገለጻቸውን ሦስት ደረጃዎች በመከተል፥ ይህን ፈተና እንዴት ትቋቋመዋለህ?

ጳውሎስ አማኞች በክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት ያገኙትን ሕይወት ካገባች ሴት ጋር ያነጻጽረዋል። ባሏ በሕይወት እስካለ ድረስ ሴቲቱ በታማኝነት አብራው ልትኖር ይገባል። እርሷም ሆነች እርሱ ወሲባዊ ታማኝነት ሊኖራቸው እንደሚገባ «የጋብቻ ሕግ» ያዛል። ነገር ግን ባለቤቷ በሚሞትበት ጊዜ ወሲባዊ ግንኙነቱን የሚቆጣጠረው የጋብቻ ሕግ ይለወጣል። ባሏም ከእንግዲህ በእርሷ ላይ ቁጥጥር አይኖረውም። በዚህ ጊዜ ሌላ ባል ብታገባ አመንዝራ አትባልም።

በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ከመዳናችን በፊት በኃጢአት ተፈጥሯችን «ሕግ» እንገዛ ነበር። (በዚህ ስፍራ «ሕግ» የሚያመለክተው ብሉይ ኪዳንን ሳይሆን፥ የክፉ ተፈጥሯችንን ኃይልና ፍላጎት ነው።) በዳንን ጊዜ ግን ከዚያ የኃጢአት ተፈጥሮ ቁጥጥር ነፃ ወጥተናል። ምክንያቱም በእኛ ላይ የነበረው ኃይሉ ሞቷልና። አሁን አዲሱ ባላችን የሆነውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በማስደሰት ልንመላለስ እንችላለን።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)