የኢየሱስ ተከታዮች እንደ መሆናችን እንዴት መመላለስ እንዳለብን (ዕብ.13፡1-25)

ጸሐፊው አይሁዳውያን ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን የሚያስከብር ሕይወት ለመኖር ሊያደርጉ የሚገዷቸውን አንዳንድ ነጥቦች በመዘርዘር መልእክቱን ያጠቃልላል። እነዚህ ትምህርቶች ሩጫችንን በሚገባ እንዳንሮጥ የሚከተሉት መሰናክሎች ወይም ኃጢአቶች በመንፈሳዊ ሩጫችን ውስጥ መኖር አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ ደግመን ደጋግመን የምንመለከታቸው ነገሮች ናቸው።

ሀ) በክርስቶስ ወንድሞቻችሁና እኅቶቻችሁን ውደዱ።

ለ) ምንም ያህል ስደት ቢበዛም፥ እማኞችን በእንግድነት ለመቀበል ትጉ።

ሐ) በኢየሱስ በማመናቸው ምክንያት የታሰሩትን ወገኖች አትርሷቸው።

መ) የጋብቻ ሕይወታችሁን ጠብቁ። የወሲብ ሕይወታችሁ ንጹሕ ይሁን። እግዚአብሔር ከሚጠላቸው ኃጢአቶች አንዱ ከትዳር ውጭ የሚፈጸም የግብረ ሥጋ ግንኙነት ነው።

ወ) የገንዘብ ፍቅር ሕይወታችሁን እንዳይቆጣጠር ተጠንቀቁ። እግዚአብሔር በሰጣችሁ መርካትን ተማሩ። ሁልጊዜም ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት አትጣሩ። ሁኔታችሁ ምንም ዓይነት ቢሆን፥ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንደሆነና እንደሚረዳችሁ ተገንዘቡ።

ረ) መንፈሳዊ ሕይወታችሁን የመጠበቅ አስቸጋሪ አገልግሎት የሚወጡትን የቤተ ክርስቲያን መሪዎቻችሁን አክብሩ።

ሰ) ራሳችሁን ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ጠብቁ። በውጫዊ ሕጎችና ደንቦች ላይ ትኩረት አትስጡ። ነገር ግን ከኢየሱስ ጋር ያላችሁን ግንኙነት እንደ መሠዊያ ቁጠሩ። ይህም ተምሳሌታዊ ሲሆን፥ የማያምኑ ሰዎች ከእርሱ መንፈሳዊ ምግብ ሊያገኙ አይችሉም ነበር። (ይህ ከኢየሱስ ጋር ኅብረት የማድረጋችን መሠዊያ የብሉይ ኪዳን ካህናት ከእንስሳት መሥዋዕቶች ወስደው ለመብላት ከነበራቸው ዕድል የሚሻል ነው። ዘሌዋ. 7፡28-34)።

ሸ) ለክርስቶስ ስም ስደትና ውርደትን ለመቀበል ፈቃደኞች ሁኑ። በብሉይ ኪዳን ዘመን የኃጢአት መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ ኃጢአት የፈጸሙት ሰዎች በሚሠዋው እንስሳ ላይ እጆቻቸውን ይጭኑ ነበር። እንስሳው ከታረደ በኋላ፥ ሥጋው በመሠዊያው ላይ ይቃጠላል። ቆዳውና የሆድ ዕቃው ግን ከከተማ ውጭ ተወስዶ ይቃጠሳል (ዘሌዋ. 4፡1-12)። የዕብራውያን ጸሐፊ፥ ይህ በኢየሱስ ላይ የተፈጸመውን ሁኔታ የሚያብራራ መሆኑን ይናገራል። ክርስቶስ የተሰቀለው ከኢየሩሳሌም ከተማ ውጭ ነበር። የአይሁድ ክርስቲኖችም ተመሳሳይ ምርጫ ማድረግ ነበረባቸው። ሰዎችን ለማስደሰት ከሌሎች አይሁዶች ጋር ተባብረው አሕዛብ ክርስቲያኖችን ለማሳደድና ስደትን ፈርተው ክርስቶስን ለመተው በመወሰን፥ በከተማይቱ ውስጥ ለመቆየት ይመርጣሉ? ወይስ የመስቀሉን ስደት የሚያስከትልባቸው ቢሆንም እንኳን ከማኅበረሰቡ ወጥተው ከክርስቶስ ጋር ይተባበራሉ? ከከተማይቱ ወጥተው ከክርስቶስ ጋር የሚተባበሩና ስደትን የሚቀበሉ ሰዎች የተሻለች የመንግሥተ ሰማይ ከተማ እንደ ተዘጋጀችላቸው ያውቃሉ።

ቀ) ሁኔታዎች ያሻቸውን ቅርጽ ቢይዙም እግዚአብሔርን ማመስገናችሁን ቀጥሉ። ከእንግዲህ ወዲህ የእንስሳት መሥዋዕቶች አያስፈልጉንም። አሁን ለእግዚአብሔር ከምናቀርባቸው መሥዋዕቶች አንዱ ምስጋና ነው።

በ) ለሌሎች መልካም ማድረጋችሁን ቀጥሉ። እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ሌላኛው መሥዋዕት ይኼ ነውና።

ተ) ከእግዚአብሔር ሥልጣንን ለተቀበሉና በእግዚአብሔር ፊት ለነፍሳችሁ ተጠያቂዎች ለሆኑት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ተገዙ። በዚህም አገልግሎታቸው ከትግል ይልቅ ደስታ እንዲሆን አድርጉ። ይህም የኋላ ኋላ እናንተኑ ይጠቅማችኋል። ምክንያቱም ደስ በሚሰኙበት ጊዜ የተሻለ አገልግሎት ሊሰጧችሁ ይችላሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህን በሕይወታችን ውስጥ ልንለማመዳቸው የሚገቡንን ነገሮችን ከልስ። እነዚህ ነገሮች ጠቃሚ የሆኑት ለምንድን ነው? በዚህ ክፍል ውስጥ ከተሰጡት ትእዛዛት አንጻር ሕይወትህን ገምግም። ጸሐፊው በዚህ ክፍል ውስጥ ከቀረበው ትምህርት ጋር የሚዛመድ ሕይወት ትመራ ዘንድ በሕይወትህ ውስጥ ሊለወጥ የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

ማጠቃለያ (ዕብ. 13፡18-25)

ጸሐፊው አንባቢያኑ በጸሎት እንዲያግዙት በመጸለይ መልእክቱን ይደመድማል። በቅርቡ ከጢሞቴዎስ ጋር መጥቶ እንደሚጎበኛቸው ይነግራቸዋል። ከኢጣሊያ የሆኑት ወደሚያቀርቡትም ሰላምታ ያልፋል፡፡

ጸሐፊው ለእነዚህ አይሁዳውያን አማኞችና ለእኛ በሚሰጠው ቡራኬ ትምህርቱን ያጠቃልላል። ሀ) የሰላም ምንጭና ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው እግዚአብሔር አብና ለ) የእግዚአብሔር በጎች እረኛ የሆነው ስለ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኘውን ሕይወት እንድንኖር በውስጣችን እንዲሠሩና እርሱን ለማገልገል ብቁዎች እንድንሆን እንዲያስችሉን ይጠይቃል።

የውይይት ጥያቄ፡- ዕብ. 13፡20-21 አንብብ። እግዚአብሔር ለራስህ ሳይሆን ለራሱ ክብር በሕይወትህ ውስጥ እንዲሠራ ጠይቀው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

እግዚአብሔርን ስላለመታዘዝ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (ዕብ. 12፡14-29)

ጸሐፊው ስለ መንፈሳዊ ሩጫችን ከገለጸ በኋላ፥ ለሩጫው ብቁ እንዳንሆን የሚያደርጉትን ነገሮች እንደሚከተለው ይዘረዝራል፡-

ሀ) ቅድስናችንን ማጣት (ባለማቋረጥ በኃጢአት ውስጥ መኖር)። ይህም እግዚአብሔርን እንዳናይ ይከለክለናል።

ለ) በሕይወታችን ውስጥ ባሉት ነገሮች ወይም በጎዱን ሰዎች መማረር፡፡

ሐ) አሁን ሕይወታችንን በምናሻሽልበት ሁኔታ ላይ በማተኮር መንፈሳዊ ውርላችንን መሽጥ። ይህም ኤሳው መንፈሳዊ ብኩርናውን ለምግብ እንደ ሸጠው ማለት ነው። ለሰማያዊ በረከቶች እንደ መኖር አሁን በምንፈልጋቸው ቁሳዊ በረከቶች ላይ እናተኩራለን። ይህም እምነታችንን እንድናመቻምችና በጥሩ ሁኔታ እንዳንሮጥ ይከለክለናል።

ጸሐፊው ከአይሁዳውያን አማኞች ፊት የተጋረጡትን ሁለት ምርጫዎች ለማመልከት እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ለሙሴና ለእግዚአብሔር ሕዝብ ሕጉ ወደተሰጠበት የብሉይ ኪዳን ዘመን ይመለሳል። ጸሐፊው ሁለት ተራሮች እንዳሉ ይገልጻል። አንደኛው ያለፈ ተራራ ሲሆን፥ ሁለተኛው ደግሞ ወደፊት የሚመጣ ተራራ ነው።

ሀ) የሲና ተራራ፡- የቀድሞው ተራራ እግዚአብሔር ወርዶ ለእስራኤል ሕዝብ ሕጉን የሰጠበት የሲና ተራራ ነው። ያ ምን ዓይነት አስፈሪ ጊዜ ይሆን? በዚያ መለከቶች፥ ድምፆችና ታላቅ ፍርሃት ነበር። ማንም ተራራውን ከነካ እስከሚሞት ድረስ የእግዚአብሔር ክብር ኃይለኛ ነበር። ሕጉን መጣስ ትልቅ ፍርድን አስከተለ፡፡ ይህ አይሁዳውያን አማኞች ክርስቶስን በመካድ ወደ ብሉይ ኪዳን አምልኮአቸው ሊመለሱ የተፈተኑበት ተራራ ነው።

ለ) የጽዮን ተራራ፡- ይህ የወደፊቱ (ዘላለማዊ) ተራራ ነው። ዛሬ በእምነት ስንመላለስ በዚሁ ተራራ ላይ እንጓዛለን። የጽዮን ተራራ ስሙን ያገኘው ሰለሞን ቤተ መቅደሱን ወይም የእስራኤል ርእሰ ከተማ የሆነችውን ኢየሩሳሌምን ከገነባበት ኮረብታ ነው። እነዚህ ሁለቱም የሕያው እግዚአብሔር መኖሪያ ወደሆነችው መንግሥተ ሰማይ ያመለክታሉ። ለመሆኑ በዚህች ታላቅ ከተማ ውስጥ የሚኖሩት እነማን ናቸው?

 1. በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መላእክቶች ይኖሩበታል።
 2. ከየዘመናቱ የተውጣጡ አማኞች ይኖሩባታል (እነዚህም በሰማያት እንደ ዜጎች የተጻፉ የበኩራት ማኅበር ተብለው ተገልጸዋል)።
 3. የሁሉም ዳኛ የሆነው እግዚአብሔር አብ አለ፡፡
 4. የብሉይ ኪዳን አማኞች (ፍጹማን የሆኑ የጻድቃን መንፈሶች)።
 5. ደሙ በመስቀሉ ላይ በፈሰሰ ጊዜ አዲሱን ኪዳን ያስተዋወቀው ክርስቶስ በዚያ አለ።

እኔና አንተ የዚህች ታላቅ ከተማ አካል ነን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይህም የሚወሰነው እዚህ ምድር ላይ ሳለን በምናሳልፈው ውሳኔ ላይ ነው።

አይሁዳውያን አማኞች እምነታቸውን ቢክዱ የመንግሥተ ሰማይ ዜግነታቸውን ሊያጡ ይችሉ ነበር። አንድ ቀን በሲና ተራራ ከተፈጸመው የሚበልጥ የመሬት መንቀጥቀጥ ይከሰታል። እግዚአብሔር አዲስ ሰማይንና ምድር ስሚያዘጋጅበት ጊዜ ዓለም ትናወጣለች። በዚህ ጊዜ የሚቀሩት በክርስቶስ ያመኑና የመንግሥተ ሰማይ አባላት የሆኑ ሰዎች ብቻ ይሆናሉ። ወደዚች ከተማ እስከምንደርስ ድረስ ለአሁኑ ዘመን አኗኗራችን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። እግዚአብሔርን በማክበርና በመፍራት ልናመልከው ይገባል። እግዚአብሔር አፍቃሪና ሰላማዊ አባት ብቻ ሳይሆን በፍርዱ የሚባላ እሳትም ጭምር ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህንን ዓለም የሙጥኝ ብለን እንዳንይዝ ዓይኖቻችንን በመንግሥተ ሰማይና በዘላለሙ መንግሥት ላይ መትከሉ ለምን የሚጠቅም ይመስልሃል? ለ) ሌሎች ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሩጫቸውን የሚያደናቅፍ ምን ተግባር ሲፈጽሙ አይተሃል? ሐ) ስለ እግዚአብሔር የፍቅርና የፍርድ ባሕርያት ጥንቃቄ የተሞላበትን ሚዛናዊ አቋም ልንይዝ የምንችለው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ክርስቶስን መከተል ማለት በመንፈሳዊ ሩጫችን መጽናት ማለት ነው (ዕብ. 12፡1-13)

አብዛኞቻችን የምንማረው ሌሎች ሰዎችን፥ በተለይም እንደ መልካም ምሳሌዎች የምንጠራቸውን ግለሰቦች በመመልከት ነው። አሠራራቸውን፥ አኗኗራቸውን፥ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት ሁኔታ፥ ወዘተ.. በመመልከት እኛም ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንዳለብን እንረዳለን። ጸሐፊው ዕብራውያን 11ን የጻፈው እንዴት የእምነትን ሕይወት መኖር እንዳለብን ለማሳየት ነው። በመቀጠልም ጸሐፊው እግዚአብሔርን ለሚያስከብር አኗኗር አቻ የሌለውን የክርስቶስ ሕይወት ምሳሌነት ያቀርብልናል። ጸሐፊው ይህንን ሕይወት በስታድዮም ውስጥ የሚካሄደውን የሩጫ ውድድር ምሳሌነት በማቅረብ ያብራራል። ሕይወታችን በሚከተሉት መንገዶች የማራቶን ሩጫን እንደሚመስል ይገልጻል።

ሀ) በክርስቶስ ካመንንበት ጊዜ ጀምሮ እስከምንሞትበት ቀን ድረስ በሕይወታችን ትልቁ ነገር መንፈሳዊ ሩጫችን ነው። ይህም ሩጫ በምቹ ጎዳናዎች ላይ ቀዝቃዛ አየር እየሳብን የምንሮጠው አይደለም። ነገር ግን የሩጫውን ጎዳናና ቅድመ ሁኔታዎች የሚመርጠው እግዚአብሔር ነው። ይህ ለእኛ የተመደበ ሩጫ ነው። ልንሮጣቸው የምንችላቸው ብዙ መንገዶች ወይም ሃይማኖቶችም የሉም። ጸሐፊው አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ክርስቶስን ትተው የይሁዲነትን መንገድ ለመከተል መፈለጋቸውን ገልጾአል። እግዚአብሔር ልንሮጥ የሚገባን በክርስቶስ ላይ እምነታችንን እንድንጥል በሚጠይቀው መንገድ ላይ ብቻ መሆኑን ገልጾአል።

ለ) በሩጫው ውስጥ ሊኖረን የሚገባው ባህሪ ጽናት ነው። ሩጫው በፍጥነት ሄደን አረፍ የምንልበት የአጭር ርቀት አይደለም። ነገር ግን ሕይወት ዘመናችን በሙሉ እንድንሮጥ የሚጠይቀን ረጅም ሩጫ ነው።

ሐ) ስታዲዮሙ እንደ ታላቅ ደመና በሆኑ ምስክሮች የተሞላ ነው። እነዚህ በብሉይ ኪዳን፥ በአዲስ ኪዳን እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሁሉ ከእኛ አስቀድሞ ሩጫቸውን የተወጡ የእምነት ጀግኖች ናቸው።

መ) ለሩጫችን የምንዘጋጀው ሁለት ነገሮችን በማድረግ ይሆናል። በመጀመሪያ፥ የሚያደናቅፉንን ነገሮች ሁሉ ማስወገድ አለብን። ጸሐፊው እዚህ ጋር የሚናገረው ስለ ኃጢአት ሳይሆን ከሩጫችን ስለሚያሰናክሉን ነገሮች ወይም አላስፈላጊ ሸክሞች ነው፡፡ የማራቶን ሯጮች ሩጫቸውን በሚያካሂዱበት ጊዜ እንደ ወትሮው የሚጠቀሙባቸው ጫማዎች፥ ከባባድ ልብሶች እና ካፖርቶች እንደሚያወልቁ ሁሉ፥ እኛም ከመንፈሳዊ ሩጫችን የሚያደናቅፉንን ነገሮች ማስወገድ ይኖርብናል። እነዚህም ጥሩ ያልሆኑ ጓደኞች፥ ወደ ተሳሳተ መሥመር የሚመራ ሥራ፥ መልካም ያልሆኑ መነሻ አሳቦች፥ ወዘተ ናቸው። ሁለተኛ፥ የሚከበንን ኃጢአት ማስወገድ አለብን። በዚህ ስፍራ ጸሐፊው ለማሳየት የሚፈልገው ሥዕል ፥ የጫማ ክሮችን ላያስሩ መሮጥን የሚያመለክቱ ናቸው። ኃጢአት ተደናቅፈን እንድንወድቅ ያደርገናል። ይህም መንፈሳዊ ሩጫችንን ከባድና አስቸጋሪ በማድረግ፥ ምናልባትም ሩጫውን በድል አጠናቅቀን እንዳንገባ ይከለክለናል።

ሠ) በምንሮጥበት ጊዜ የዘመናት ሁሉ ታላቁ ሯጭ፥ ሊሸልመን ወደሚጠባበቅበት የፍጻሜ መሥመር አቅንተን መመልከት ይኖርብናል። ታላቅ ሯጭ ምሳሌአችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ እርሱም የእምነታችን ጀማሪና ፈጻሚ ነው። የእምነትን ሩጫ እንድንሮጥ የመረጠንም እርሱ ነው። እንዴት አድርገን በተሻለ ሁኔታ እንደምንሮጥ የሚያስተምረንም ክርስቶስ ነው። እርሱ ሩጫውን እንድንጨርስ ይረዳናል። ምሳሌነቱን ከተከተልን ሩጫውን በደህና እንጨርሳለን። ክርስቶስ ሥቃይን፥ መከራን ወይም መስቀልን አልፈራም። ከአብ በስተቀኝ ወደ መቀመጡ የፍጻሜ መሥመር በሚያይበት ጊዜ፥ እነዚህን ሁሉ ከእግዚአብሔር የተቀበለው ሩጫ አካላት አድርጎ ተመለከተ። ሩጫው ቀላል አልነበረም። የእኛም ቢሆን ቀላል ሊሆን አይችልም። ነገር ግን በትኩረት፥ በታማኝነትና በቅድስና ከሮጥን፥ እኛም እንደ ክርስቶስ በመንግሥተ ሰማይ የፍጻሜ መሥመር ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክብርን እናገኛለን።

ረ. በመልካም ሁኔታ እንሮጥ ዘንድ ራሳችንን ማሠልጠንና ማዘጋጀት ይኖርብናል። የትኛውም አትሌት ጠዋት ወይም ማታ እየተነሣ ረዥም ርቀት መለማመዱን አይወደውም። ነገር ግን ያለእነዚህ የልምምድ ሥርዓት የትኛውም አትሌት ሩጫውን በጥሩ ሁኔታ ሊያጠናቅቅ እንደማይችል ያውቃል። በመንፈሳዊ ሩጫም፥ መከራን መታገሥ በጥሩ ሁኔታ እንድንሮጥ ያዘጋጀናል። ጸሐፊው እነዚህ የመከራ ሥራዎች ሕይወታችንን እንደሚገሩ ይናገራል። (ከእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይኸው የመግራት አሳብ «ዲሲፕሊን» በሚል ቃል ተገልጾአል።) ዲሲፕሊን የሚለው ቃል ሁለት ትርጉሞች አሉት። አንደኛው ለመጥፎ ተግባር መቀጣትንና የሚያሳይ ሲሆን፥ ጸሐፊው በዚህ ክፍል ለማስተላለፍ የፈለገው ይህንን መልእክት አይደለም፡፡ ሌላኛው ትርጉም ማረም ማሠልጠን ወይም ማጠናከር ነው፡፡ ጸሐፊው ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ይሄኛው ነው። እግዚአብሔር መንፈሳዊ ሩጫችንን በአግባቡ እንወጣ ዘንድ እኛን የሚያርምበትና ቀዳሚ የመጀመሪያው መንገድ መከራ ወደ ሕይወታችን እንዲመጣ ማድረግ ነው። ይህ በሚገባ እንድንሮጥ የሚያዘጋጀን ከመሆኑም በላይ፥ ጸሐፊው ይህ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የሚያሳይ መሆኑን ያስረዳል። እግዚአብሔር ለሕይወታችን የግል ትኩረት ሰጥቶ መንፈሳዊ ሩጫችንን በሚገባ እንሮጥ ዘንድ ያዘጋጀናል።

ሰ) ብዙውን ጊዜ በሩጫው ውስጥ እጆቻችንና እግሮቻችን ይዝላሉ። ነገር ግን ድካም ወይም የእግር ሕመም ሳይሰማን ሩጫችንን ለመቀጠል እንድንችል በጽናት መበርታት እንዳለብን ተገልጾአል። ዋናው ነገር ሩጫውን መጀመሩ ብቻ አይደለም። ከእግዚአብሔር እጅ ሽልማት እንድንቀበል ሩጫችንን መጨረስ አለብን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) መንፈሳዊ ሕይወትህን በአዲስ አበባ ስታዲዮም ውስጥ ከሚካሄደው የሩጫ ውድድር ጋር አነጻጽር፡፡ ሀ) በመንፈሳዊ ስታዲየም ውስጥ በምትሮጥበት ጊዜ እያጨበጨቡ ሞራል የሚሰጡህን ምስክሮች ዘርዝር። ለ) ከሩጫው የሚያደናቅፉህን አንዳንድ ነገሮች ዝርዝር፡ ሐ) በሕይወትህ ውስጥ እንድትወድቅ የሚታገሉህ አንዳንድ ኃጢአቶች ምን ምንድን ናቸው? መ) እግዚአብሔር እንደ ሥቃይ፥ መከራ ወይም ስደት ያሉትን ነገሮች በመጠቀም ሕይወትህን ለሩጫው ያዘጋጀው እንዴት ነው? ሠ) የክርስቶስ ሕይወት በተሻለ ሁኔታ እንድትሮጥ የሚያበረታታህ እንዴት ነው? ከዚህ ሩጫ ምን ትማራለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ክርስቶስን ለመከተል እምነት ወሳኝ ነው (ዕብ. 11፡1-39)

ብዙውን ጊዜ በክርስቶስ ማመን ምን ማለት እንደሆነ ሰዎች የተሳሳተ አመለካከት አላቸው። ብዙዎቻችን ስለ እውነታው ትክክለኛነት በሚያስረዳው እእምሮአዊ እውቀት ላይ እናተኩራለን። ስለሆነም አንድ ሰው በክርስቶስ እንዲያምን በምንጠይቅበት ጊዜ፥ «ክርስቶስ ለኃጢአትህ እንደ ሞተ እመን» ማለታችን ነው። ነገር ግን በክርስቶስ ማመን እርሱ በሚፈልገው መንገድ መጓዝን እንደሚጠይቅ አንገነዘብም። ከዚህም የተነሣ፥ ብዙ ሰዎች በክርስቶስ እናምናለን ቢሉም፥ ሕይወታቸው ግን አይለወጥም። ብዙ ሰዎች በአእምሮአቸው የሚረዱትን ወይም እሑድ እሑድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ የሚናገሩትን ነገር በአኗኗራቸው አያንጸባርቁም። አይሁዳውያን አማኞች ይኸው ተመሳሳይ ችግር ገጥሟቸው ነበር። አንዳንዶቹ አምልኮአቸውን፥ ከአሕዛብ አማኞች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ሳይቀይሩ፥ ክርስቶስ ለኃጢአታቸው እንደ ሞተ ይናገሩ ነበር። በመሆኑም የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ በምዕራፍ 11 ውስጥ እውነተኛ እምነት ሁልጊዜም በሰዎች አኗኗር ላይ ለውጥ እንደሚያስከትል ከብሉይ ኪዳን ምሳሌዎችን ጠቅሶ ያብራራል። የሚያድን እምነት እንዲኖረን ከተፈለገ አእምሮአዊው እውቀት ወደ ተግባር መለወጥ አለበት።

ሀ) የእውነተኛ እምነት ገለጻ፡ “እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።” እምነት እንዲኖር ከተፈለገ፥ ሦስት ነገሮች መኖር አለባቸው። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር ስለዚሁ ነገር የተስፋ ቃል መስጠት አለበት። እግዚአብሔር አንድ ነገር እንደሚከሰት እስካልተነገረ ድረስ፥ በዚህ ጉዳይ ላይ እምነት ሊኖረን አይችልም። እግዚአብሔር ይህንን ነገር እንደሚያደርግልን ተስፋ ልናደርግ ወይም ልንመኝ እንችላለን። ለምሳሌ፥ እግዚአብሔር መንግሥተ ሰማይ እንዳለች ስለተናገረ መንግሥተ ሰማይ እንዳለች እናምናለን። በመሆኑም ለምድራዊ ጥቅማ ጥቅሞች ብቻ ሳይሆን ለመንግሥተ ሰማይ ሕይወት በመዘጋጀት የዕለት ተዕለት ኑሮአችንን እንገፋለን።

(ማስታወሻ፡ አንዳንድ ሰዎች ይህንን የእምነት ገጽታ በመሳት እግዚአብሔር በግልጽ ተስፋ ያልሰጠው ነገር እንደሚፈጸም ማመናቸው እውነተኛ እምነት እንዳላቸው የሚያሳይ መሆኑን ይናገራሉ። ለምሳሌ፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሽማግሌዎች እግዚአብሔር ትልቅ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ለመገንባት የሚያስችል ገንዘብ እንደሚሰጣቸው በማመን ከእግዚአብሔር ግልጽ ማረጋገጫ ሳይቀበሉ ሥራውን ይጀምራሉ። በሥራው ሂደት የነበራቸው ገንዘብ ሕንጻው ከመጠናቀቁ በፊት ያልቃል። በዚህም ጊዜ በጅምር የቀረውን ሕንጻ እየተመለከተ ኅብረተሰቡ ያላግጥባቸዋል፤ ይሳለቅባቸዋል። እነርሱም ምንተ እፍረታቸውን ወደ ተለያዩ ሰዎች በመሯሯጥ ገንዘብ ይለምናሉ። ይህ አጉል ድፍረት እንጂ እምነት አይደለም። በመሆኑም እኛ እምነት ነው በምንለውና የእግዚአብሔርን ምሪት ባልተቀበልንበት ተግባር ሳቢያ የእግዚአብሔርን ስም እናሰድባለን። እግዚአብሔር ለአንድ ነገር ያለውን ምሪት በተለያዩ መንገዶች ሊገልጽ ይችላል። እርሱ በልባችን ውስጥ አንድን ነገር ለማከናወን መፍቀዱን ሊናገር ይችላል። ሌላ ጊዜ ደግሞ በቃሉ አማካኝነት ሊደርስ ይችላል። ለጠቅላላይቱ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት የተጣለብን ሽማግሌዎች ከሆንን፥ እግዚአብሔር ፈቃዱ የሆነውን ነገር መንፈሳውያን ለሆኑት ሽማግሌዎች ሊናገር ይችላል። እነርሱም ፈቃዱን በመሻት በውሳኔው ይስማማሉ።)

ሁለተኛ፥ እምነት አለ የሚባለው እምነት የተጣለበት ነገር ሳይታይ ሲቀር ነው። ማንም ሰው ከበሽታው ከተፈወሰ በኋላ እግዚአብሔር ያድነኛል ብሎ ማመን አያስፈልገውም። እምነቱ የሚያስፈልገው ፈውሱ ከመምጣቱ በፊት ነው። መንግሥተ ሰማይ ከደረስን በኋላ ስለ መንግሥተ ሰማይ መኖር ማመን አያስፈልገንም። ምክንያቱም በገዛ ዓይኖቻችን እናያታለንና። ስለ መንግሥተ ሰማይ እምነት የሚያስፈልገው አሁን ነው። ምክንያቱም እኛ ባናያትም፥ እግዚአብሔር መንግሥተ ሰማይ እንዳለች ነግሮናልና።

ሦስተኛ፥ እምነት ሊኖር የሚችለው እግዚአብሔር በሰጠን የተስፋ ቃሎች ላይ በእርግጠኝነት በመመሥረት አኗኗራችንን ልንለውጥ ነው። ጸሐፊው በዚህ ምዕራፍ ውስጥ አጽንኦት ሰጥቶ የሚናገረው ስለዚሁ እምነት ነው።

የውይትት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር የአንተን እምነት ተጠቅሞ ያልተጠበቀ ተግባር የፈጸመበትን ሁኔታ በምሳሌነት ጥቀስ። በዚህ ጊዜ እነዚህ የእምነት ክፍሎች የታዩት እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች እምነት አለን በሚል የሞኝነት ተግባራትን በምሳሌነት ግለጽ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተፈጸመው ስሕተት ምንድን ነው? ከእነዚህ ሦስት የእምነት አላባውያን የጎደለው ምንድን ነው?

ለ) የድል ነሺ እምነት ምሳሌዎች (ማስታወሻ፡ የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ፥ እምነት ምን እንደሆነና በሕይወታችን ውስጥ እንዴት መታየት እንዳለበት በአይሁዶች ዘንድ ታላቅ ግምት የሚሰጣቸውን አብርሃምንና ሙሴን ለማብራሪያነት ይጠቀማል።)

ጸሐፊው በብሉይ ኪዳን የነበሩ ሰዎች እምነታቸውን እንዴት እንደ ገለጹና እግዚአብሔርም እንደ ሸለማቸው ሲገልጽ፥ ሀ) ምን ዓይነት እውነታ እንዳመኑ፥ ለ) ከዚሁ እምነት የተነሣ ምን ዓይነት ኑሮ እንደ ኖሩ፥ እና ሐ) የእምነታቸው ውጤት ምን እንደሆነ ያብራራል።

 1. በፍጥረት ማመን፡- ማናችንም እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር ስላልተመለከትን፥ ይህንን እውነት በእምነት መቀበል አለብን። ምክንያቱም እግዚአብሔር ዓለምን እንደ ፈጠረ፥ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ በትእዛዙ ካለመኖር ወደ መኖር እንዳመጣ ይናገራል። ዓለም የዝግመተ ለውጥ (ኢቮሉሽን) ውጤት ናት የሚሉ ብዙ ሳይንቲስቶች ቢኖሩም፥ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያለን እምነት የሳይንቲስቶችን አሳብ በመቃወም መጽሐፍ ቅዱስን እንድናምን ይገፋፋናል።
 2. አቤል፡- እምነት አቤል እግዚአብሔርን እንዲታዘዝና በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን መሥዋዕት እንዲያቀርብ አድርጎታል። ይህም እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ እምነት እንደሌለው ከገለጸው ከወንድሙ ቃየን የተለየ ነበር።
 3. ሄኖክ፡- እንደ ጎረቤቶቹ ላለመኖር በመወሰኑና ከእግዚአብሔር ጋር የግል ኅብረት በመፍጠሩ እምነቱን አሳይቷል። ከዚህም የተነሣ፥ እግዚአብሔር ሳይሞት በፊት ወደ መንግሥተ ሰማይ ወስዶታል።
 4. ኖኅ፡- እግዚአብሔር የጥፋት ውኃ እንደሚመጣ የነገረውን የተስፋ ቃል በማመን (ምንም እንኳን ዝናብ ባይታይም) መርከብ ሠርቶ እምነቱን አሳይቷል። ከዚያም የተነሣ፥ የተቀረው የሰው ልጅ በሙሉ ሲጠፋ እርሱና ቤተሰቡ ሊድኑ ችለዋል።
 5. አብርሃም፡- በተለያዩ መንገዶች እምነቱን አሳይቷል።

ሀ) ወደ አገሩ ወደ ዑር ሳይመለስ እንደ ዘላንና እንግዳ በመኖር። ምንም እንኳን እግዚአብሔር የከነዓንን ምድር እንደሚሰጠው የተስፋ ቃል ቢገባለትም፥ እርሱም ሆነ ልጁ ወይም የልጅ ልጁ ወደ ከነዓን አልገቡም። ነገር ግን እምነት እግዚአብሔር ተስፋ የገባላቸው የተሻለች የመንግሥተ ሰማይ ከተማ እንዲመለከቱ ዓይኖቻቸውን አቅንቶላቸው ነበር።

ለ) ምንም እንኳን የእርሱ እና የሣራ እድሜ ከማርጀቱ የተነሣ ልጅ የሚወልድበት ጊዜ ቢያልፍም፥ እግዚአብሔር ልጅ እንደሚሰጠው በማመን።

ሐ) የተስፋ ቃል ልጅ የነበረውን ይስሐቅን በመሠዋት። አብርሃም ይህንን ሊያደርግ የቻለው እግዚአብሔር ይስሐቅ የቤተሰቡን ዘር እንደሚቀጥል የሰጠውን የተስፋ ቃል እንደሚጠብቅና በቃሉም መሠረት እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባቸውን የተስፋ ቃሎች እንደሚወርስ በመተማመን ነበር። በመሆኑም እግዚአብሔር ከሙታን እንደሚያስነሣው እርግጠኛ ነበር።

 1. ይስሐቅና ያዕቆብ፡- ከአብርሃምና ከእግዚአብሔር የተቀበሏቸውን በረከቶች በማስተላለፍ እምነታቸውን አሳይተዋል።
 2. ዮሴፍ፡- ከግብጽ ይልቅ ከነዓን የበረከት አገር መሆኗን በማመንና ሥጋው ከግብጽ ይልቅ ከነዓን እንዲቀበር በመጠየቅ እምነቱን አሳይቷል።
 3. የሙሴ ወላጆች፡- የፈርዖንን ትእዛዝ ጥሰው ሙሴን ባለመግደላቸው እና የገዛ ሕይወታቸውን ከአደጋ ላይ በመጣላቸው፥ እግዚአብሔር ልዩ የሆነ ልጅ እንደ ሰጣቸው ማመናቸውን ገልጸዋል።
 4. ሙሴ፡- በተለያዩ መንገዶች በእግዚአብሔር ላይ የነበረውን እምነት ገልጾአል።

ሀ) ካሳደጉት ግብጻውያን ገዢዎች ይልቅ የአይሁዳውያን ባሮች ወገን መሆኑን በመግለጽ እምነቱን አሳይቷል። የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ይህ ሙሴ ከምድራዊ ምቾት ይልቅ እግዚአብሔርን (ክርስቶስ) እና የእግዚአብሔርን ሽልማት መምረጡን ያሳየበት መንገድ እንደሆነ ገልጾአል።

ለ) ሙሴ በኃያሉ አምላክ ላይ እምነት ስለነበረው ታላቁ ፈርዖንን ሊጋፈጠው መረጠ።

ሐ) ሙሴ የእግዚአብሔርን የሞት መልአክም ሆነ ቀደም ሲል በተመሳሳይ ሁኔት የተፈጸመ ተአምር ባያይም፥ በዕለተ ፋሲካ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ተግባራዊ ለማድረግ ወስኗል።

 1. የእስራኤልም ልጆች በሚከተሉት መንገዶች እምነታቸውን ገልጸዋል።

ሀ) እግዚአብሔርን ታዝዘው ቀይ ባህር ውስጥ በመግባታቸው። በዚህ ጊዜ እነርሱ በደረቅ መሬት ላይ ሲጓዙ፥ ግብጾቹ ግን በባህሩ ውስጥ ሰጥመዋል።

ለ) የሞኝነት ትእዛዝ የሚመስለውን የእግዚአብሔርን ቃል ተቀብለው በኢያሪኮ ዙሪያ ዞረዋል። እግዚአብሔርም የኢያሪኮን ቅጥር በማፍረስ የተስፋ ቃሉን ፈጽሞላቸዋል።

 1. ረዐብ፡– ይህች ሴት ጋለሞታ ብትሆንም፥ ስለ እግዚአብሔር የነበራትን እውቀት በመታመን ሕይወቷን አድናለች። ይህም ሊሆን የቻለው ከአይሁዶች ጋር በመተባበር ሰላዮቹን በመደበቅ ነው።
 2. ማጠቃለያ፡– ጸሐፊው በዕብ. 11፡32-35 በብሉይ ኪዳን ታሪክ ውስጥ እያሌ ክስተቶችንና ሰዎችን ይዘረዝራል። ይህም ታሪክ እግዚአብሔር በተለያዩ ሰዎች እምነትና ተግባራት ሳቢያ ተአምራት መሥራቱን የሚያመለክት ታሪክ ነው። ጸሐፊው ይህንን ያደረገው ለአይሁዳውያን ክርስቲያኖች የብሉይ ኪዳን ጀግኖቻቸው ሁሉ ታላቅነታቸውን ያገኙት ከእምነታቸ የተነሣ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው። ለእግዚአብሔር ታላላቅ ሥራዎች እንዲሠሩ ያስቻላቸውም ይኸው እምነታቸው ነበር። እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል ተቀብለው ተግባራዊ ማድረጋቸው ተአምራዊ ውጤቶችን አስገኝቶላቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡– ከራስህ ገጠመኝ፥ በእግዚአብሔር ላይ የጣልከው እምነት ታላቅ ውጤት ያስገኘበትን ሁኔታ ግለጽ።

ሐ) በምድር ላይ እምነት ስደትንና መከራን እንጂ ድል እንደማያስገኝ የሚያመለክቱ ማብራሪያዎች። ብዙውን ጊዜ ስለ እምነት በምናስብበት ወቅት፥ አእምሮአችን እምነት በሚያስገኛቸው ተአምራት ላይ ያተኩራል። በመሆኑም በዕብራውያን ምዕራፍ 11 የመጀመሪያው ክፍል ላይ አጽንኦት እንሰጣለን። ነገር ግን እምነት ሁልጊዜ የምንፈልገውን ተአምር ላያመጣልን ይችላል። በአብዛኛው እዚህ ምድር ላይ ጊዜያዊ ሥቃይንና መከራን ወይም ሞትን እንድንጋፈጥ ያደርገናል።

ጸሐፊው ይህንን ያልተሟላ የእምነት ገጽታ ለማሳየት፥ ከብሉይ ኪዳን ታሪክ፥ እንዲሁም በብሉይ ኪዳን መጨረሻና በአዲስ ኪዳን መጀመሪያ አካባቢ አይሁዶች ነጻነታቸውን ለማግኘት ጦርነትን ባደረጉባቸው ጊዜያት የተከሰቱትን ሁኔታዎች ይዘረዝራል። (በዚህ ወቅት የተፈጸሙትን አንዳንዶቹን ነገሮች ለመመልከት በአዲስ ኪዳን ቅኝት ክፍል አንድ፥ ትምህርት አንድ ላይ የተሰጠውን ትምህርት አንብብ።) እምነትና ታዛዥነት በእግዚአብሔር ልጆች ላይ ያስከተሏቸው አንዳንድ ችግሮች ምን ምን ነበሩ?

 1. ሥቃይ፥ እምነታቸውን በመካድ ከዚህ ሥቃይ ሊያመልጡ ይችሉ ነበር።
 2. የጓደኞቻቸውና የጎረቤቶቻቸው መሳለቂያ መሆን
 3. እስራት፥
 4. ሞት፣
 5. ድህነት፥ ይህም ቤቶቻቸውና ንብረቶቻቸውን ተነጥቀው በዋሻዎች ውስጥ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።

ጸሐፊው የእግዚአብሔር ሰው ማለት ምን ማለት እንደሆነ በመግለጽ ይህንን ክፍል የሚያጠቃልልበትን ሁኔታ መመልከት ጠቃሚ ነው። እግዚአብሔር በሚመርጥበት ጊዜ እምነት ተአምርን ወይም ታላቅን ድል ሊያስገኝ ይችላል። ብዙውን ጊዜ ግን ስደትንና መከራን ያስከትላል። በዚህም ጊዜ፥ ድል የሚገኘው ከትንሣኤ በኋላ በመንሥተ ሰማይ ይሆናል። በዕብራውያን 11 ውስጥ የተጠቀሱት ሁለቱም ወገኖች እምነት ነበራቸው። ልዩነቱ የእግዚአብሔር ምርጫ ነበር። እርሱ አንዳንዶችን ሲያድን (እንደ ጴጥሮስ፥ የሐዋ. 12፡3–13)፥ ሌሎች ደግሞ መከራን እንዲጋፈጡ ፈቅዷል። (እንደ ያዕቆብ፥ የሐዋ. 12፡2)። ብዙም ሳይቆይ የእነዚህ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች እምነት የሚፈተንበት ሰዓት ይመጣ ነበር። አይሁዳውያን ወገኖቻቸው ስደትን በሚያበዙባቸው ወቅት በክርስቶስ ላይ የነበራቸውን እምነት ይተዉ ይሆን? ወይስ እምነታቸውን ከመካድ ይልቅ ለጊዜው በማይታያቸው የመንግሥተ ሰማይ ተስፋ ላይ ዓይኖቻቸውን ተክለው ስደትን ለመቀበል የመረጡትን ጀግኖች ምሳሌነት ይከተሉ ይሆን? እግዚአብሔር ዓለም አልተገባኝም ብለው በስደት የጸኑትን ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ አክብሮአቸዋል። እኛስ በእምነታችን የእነዚህ የእምነት ጀግኖች ቡድን አባላት ነን?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የእምነት ሕይወት አሁን ስደትን በኋላ ደግሞ ድልን እንደሚያስገኝ ከማሰብ ይልቅ፥ ብዙውን ጊዜ አሁን ድል እንዲያስገኝልን የምንፈልገው ለምንድን ነው? ለእንዲህ ዓይነቱ የሚዛናዊነት መጓደል ከርስቲያኖች የጠበቁት ነገር በማይሳካበት ወቅት (ከበሽታ ወይም ከስደት ሊተርፉ በማይችሉበት ወቅት) እምነታቸው እንዲናጋ የሚያደርገው እንዴት ነው? ሐ) እግዚአብሔር እምነታችንን በማክበር ነፃ የሚያወጣን ጊዜ ይልቅ ነገሮች እንደጠበቅን በማይሆኑበት ጊዜ (በሽታ፥ የቤተሰብ ሞት፥ ስደት) በታማኝነት መጽናቱ እንዴት የበለጠ እምነትን እንደሚጠይቅ ግለጽ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

እስከ መጨረሻው ጸንቶ ስለ መገኘት የቀረበ ጥሪ (ዕብ. 10፡19–39)

የዕብራውያን ጸሐፊ ይህንን የመጨረሻ ክፍል የሚጀምረው ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንዳለብን፥ ይህ ካልሆነ ግን ከእምነት ርቀን በመቅበዝበዝ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንደምንቀበል በማስጠንቀቅ ነው።

ሀ. በግላዊ እና በቅርብ ግንኙነት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አለብን። የክርስቶስ ሞት ኃጢአተኛ ሰዎችን ከተቀደሰው አምላክ የሚለየውን መጋረጃ ስላስወገደው እና ክርስቶስም አሁን በሰማይ በሊቀ ካህንነት እያገለገለ ስለሆነ፥ በጸሎት እግዚአብሔር ወደሚገኝበት ስፍራ የመቅረብ ድፍረት አለን። እግዚአብሔር ወደሚገኝበት ቦታ በድፍረት ለመቅረብ እራት ነገሮች ያስፈልጉናል፡

 1. ንጹህ ልብ ወይም ለእግዚአብሔር እውነተኛ ፍቅር ያለው እና ኢየሱስን ደስ ለማሰኘት የሚፈልግ ልብ። እንዲህ ዓይነቱ ልብ ሰዎችን ለማስደነቅ በመሻት የግብዝነትን ተግባር እያከናውንም። ይህ ሙሉ በሙሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ የሆነ ልብ ነው።
 2. ሙሉ የእምነት ማረጋገጫ፥ ክርስቶስ ለእኛ ሲል እንደ ሞተ ሙሉ በሙሉ ማመን። ይህም ወደ እግዚአብሔር ዘንድ እንድንቀርብ መብትን ይሰጠናል። እንዲህ ዓይነት እምነት ልባችን በጥርጣሬ እንዲሞላ፥ የራሳችንን ጥረት እንድንጨምር ወይም ክርስቶስ ይቀበለን ዘንድ እርሱን ለማስደሰት እንድንሞክር እያደርገንም።
 3. ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን። ይህ ክርስቶስ የኃጢአታችንን ዋጋ በመስቀል ላይ እንደከፈለ እና እግዚአብሔርም ይቅር እንዳለንና ንጹሐን አድርጎ እንደሚቀበለን እና መገንዘባችንን ያሳየናል። እንዲሁም፥ የእግዚአብሔር ልጆች ከመሆናችን የመነጨው ግንኙነት ለኃጢአት የማይቋረጥ እንደሆነና ኃጢአታችን በእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታ እንደተደረገለት መረዳታችንን ያሳያል።
 4. ሰውነታችንን በጥሩ ውኃ ታጥበን። ጸሐፊው ለአዲስ ኪዳን መርሆ የብሉይ ኪዳንን ምሳሌ ሲሰጥ እንመለከታለን። በብሉይ ኪዳን ዘመን፥ ካህኑ በቤተ መቅደሱ ገብቶ ከማገልገሉ በፊት በነሐስ ሳህን ውስጥ በተቀመጠው ውኃ እጁን መታጠብ ያስፈልገው ነበር። ይህም ቅዱሱን አምላክ ለማገልገል በሚዘጋጁበት ወቅት ከኃጢአት መንጻታቸውን በተምሳሌትነት ያሳይ ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ወደ እግዚአብሔር በምንቀርብበት ጊዜ እኛም ኃጢአተኝነትን ለእግዚአብሔር በመናዘዝ ልንታጠብ ይገባል። ክርስቶስ በመስቀል ላይ የኃጢአታችንን ዋጋ ስለከፈለ፥ በእግዚአብሔር ችሎት ፊት ይቅር ተብለናል። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር ግልጽ ግንኙነት ይኖረን ዘንድ ኃጢአታችንን በኑዛዜ ውኃ ታጥበን እናጠራዋለን። (ማስታወሻ፡ ጸሐፊው በዚህ ስፍራ ስለ ጥምቀት ማስተማሩ አይደለም። እዚህ ላይ ለመግለጽ የፈለገው ከንስሐ እና ኃጢአትን ከመናዘዝ ስለሚመጣው መንጻት ነው)

ለ. እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ። ይህ ተስፋ ወንጌል ነው። ይህም መዳናችንን ብቻ ሳይሆን በመንግሥተ ሰማይ እየተጠበቅን መሆናችንን የሚያሳይ ትምህርት ነው። በመሆኑም ያመንበትን እውነት ፍርሀት እንዲነጥቅብን መፍቀድ የለብንም። ነገር ግን ዓይኖቻችንን በሰማይ ላይ ተክለን በዚያ የሚጠባበቁንን ነገሮች ልናስታውስ ይገባል።

ሐ. ለፍቅር እና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ። እያንዳንዱ አማኝ የአማኞች ኅብረት አካል መሆን ይኖርበታል። በዚህ ውስጥ እያንዳንዱ አማኝ ለመንፈሳዊ እድገቱ ተጠያቂነት ይኖረዋል። እነዚህ የቅርብ ጓደኞቻችን በሚገባ ሊያውቁን እና ድክመታችንን ሊገነዘቡ ይገባል። መውደቅ ስንጀምርም በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንድንበረታ ሊያደፋፍሩን ያሻል። እማኞች እንደ መሆናችን፥ ለእራሳችን እምነት ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ወገኖች ኃላፊነት አለብን። ሁሉም አማኞች በሕይወታቸው እንዲያድጉ፥ እንዲሁም እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዲመላለሱ መርዳት ይኖርብናል።

መ. ለአምልኮ መሰባሰብ አለብን። አንዳንድ ምሁራን ከስደት ፍርሃት የተነሣ አንዳንድ አማኞች ወደ ቤተ ክርስቲያን ላለመሄድ ወስነው እንደነበር ይናገራሉ። እናም ቤታቸው ውስጥ ይቀመጣሉ። ሌሎች ደግሞ አይሁዳውያን አማኞች ከአሕዛብ ክርስቲያኖች ጋር እንዳይተባበሩ የሚቀርብባቸውን ትችትና ስደት በመፍራት በአይሁዳውያን የኅብረት ቡድኖች ተወስነው ለመቅረት ያስባሉ። እነዚህ ሁለቱ ክርስቲያኖች ለስደት የሰጧቸው ምላሾች ትክክል አልነበሩም። ምክንያቱም የክርስቶስ አካል ተባብሮ ይጸና ዘንድ አማኞቹ ሁሉ ተሰባስበው እግዚአብሔርን ሊያመልኩ እና እርስ በርሳቸው ሊበረታቱ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከእምነታችን እንዳንወድቅ እነዚህ አራት ነገሮች መንፈሳዊ ሕይወታችንን ለማጠናከር የሚያግዙት እንዴት ነው። ለ) ስደት ወይም ችግሮች በሚመጡበት ጊዜ ሳትሰናከል ጸንተህ ትቆም ዘንድ እነዚህ አራት ነገሮች የሕይወትህ አካላት እንዲሆኑ ምን እያደረግክ ነው?

ጸሐፊው በእምነታችን እንጸና ዘንድ ልናደርጋቸው የሚገቡንን አዎንታዊ ነገሮች መዘርዘሩን አቋርጦ፥ ሌላ ጠንካራ የማስጠንቀቂያ ምንባብ ያቀርባል። አይሁዳውያን አማኞች በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት ትተው ከአሕዛብ አማኞች ጋር መሰባሰባቸውን ቢያቆሙ፥ ይህ ኃጢአት ይሆንባቸዋል።

ጸሐፊው የኃጢአት ይቅርታ የሚገኘው ከክርስቶስ ብቻ መሆኑን ገልጾአል። እነዚህ ሰዎች ክርስቶስን ከተዉት፥ ሌላ የኃጢአትን ይቅርታ የሚያገኙበት መንገድ አይኖራቸውም ነበር። ጸሐፊው በክርስቶስ ላይ የነበረውን እምነት የካደ ሰው፥ «የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፥ ያንንም የተቀደሱበትን የኪዳኑን ደም እንደ እርኩስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያግፋፋ» ሲል ይገልጸዋል። አሮጌውን ኪዳን መተው ከፍተኛ ቅጣት የሚያስከትል ከሆነ፥ ይህንን ታላቅ የመዳን መንገድ ቸል ማለት ደግሞ ከዚያ የከፋ ቅጣት ያስከትል ነበር። የክርስቶስ ደም ኃጢአታቸውን ካልሸፈነው፥ በሕያው እግዚአብሔር እጆች ላይ ወድቀው ፍርድን ይቀበላሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እምነታችንን ለመካድ በምንፈተንበት ጊዜ በአመዛኙ ስለ እግዚአብሔር ባህሪ የምንዘነጋው ምንድን ነው? ለ) እግዚአብሔር እምነታቸውን የሚክዱ ሰዎችን እንደሚቀጣ ማወቁ በእምነታችን እንድንጸና የሚያግዘን እንዴት ነው? ሐ) እምነታቸውን የሚክዱ ሰዎች እንዴት ክርስቶስን በእግራቸው እንደሚረግጡት፥ የክርስቶስን ሞት እንደ ከንቱ ነገር እንደሚቆጥሩና መንፈስ ቅዱስን እንደሚያግፋፉ ግለጽ።

ሠ. እግዚአብሔር ከዚህ በፊት በሕይወታችን ውስጥ እንዴት እንደሠራ ማስታወስ ይኖርብናል። ጸሐፊው እምነታቸውን ለመካድ የሚፈተኑት አይሁዳውያን አማኞች ቀደም ሲል ለክርስቶስ ምን ያህል እንደ ተሰደዱና ከሌሎች ተሰዳጅ አማኞች ጋር በእስር ቤት እንደ ተባበሩ ያስታውሳቸዋል። ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ የቀድሞው የመሥዋዕትነት ሕይወታቸው ታላቅ ሽልማት ያስገኝላቸው ነበር። ነገር ግን እምነታቸውን ለመካድ ቢወስኑ፥ ይህ ሁሉ እርባና አይኖረውም ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የክርስቶስ መሥዋዕት ከእንስሳት መሥዋዕቶች ይበልጣል (ዕብ. 9፡13-10፡18)

እስከአሁን ጸሐፊው ክርስቶስ የሚሻል ሊቀ ካህናት የእውነተኛ አምልኮ መሪ እንዲሁም ለምትበልጥ ሰማያዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚያገለግል መሆኑን ገልጾአል። በመቀጠልም፥ የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ የክርስቶስ መሥዋዕት በምድራዊ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ከቀረቡት መሥዋዕቶች ሁሉ እንደሚበልጥ ያስረዳል። ጸሐፊው አይሁዳውያን ሊቃነ ካህናት ካቀረቧቸው መሥዋዕቶች የክርስቶስ መሥዋዕት ምን ያህል እንደሚበልጥ ለማሳየት የሚከተሉትን እውነቶች ገልጾአል፡

ሀ. ክርስቶስ እራሱን ስለ ሠዋና ሊቃነ ካህናት የእንስሳትን መሥዋዕት ያቀርቡ ስለነበር፥ የክርስቶስ መሥዋዕት ሊቃነ ካህናት በብሉይ ኪዳን ከሰዉአቸው መሥዋዕቶች ሁሉ ይበልጣል። ለስርየት ቀን ሊቃነ ካህናት የፍየሎች እና የኮርማዎችን ደም፥ እንዲሁም የጊደር አመድ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃጢአት የሠጣቸው ጊዜያዊ የማንጫ መንገዶች ተምሳሌቶች ነበሩ። ነገር ግን መለኮታዊ እና ሰብአዊ የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የራሱን ደም ወደ ሰማይ አቀረበ። ክርስቶስ እንከን የለሽ እና ምንም ኃጢአት ያልተገኘበት ሆኖ ለሰው ልጆች ኃጢአት እራሱን ሠውቷል።

ለ. የክርስቶስ ደም የእንስሳት መሥዋዕቶች እንደሚያደርጉት ጊዜያዊ፥ ውጫዊና ሥርዓታዊ መንፃት ሳይሆን፥ ፍጹም መንጻትን በማስከተል ሰዎች ሕያው እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ነፃ አውጥቷቸዋል።

ሐ. ክርስቶስ እግዚአብሔር በአዳምና ሔዋን ውድቀት ጊዜ የመሠረተውን የአምልኮ መርሆ ከፍጻሜ አድርሷል። ይቅርታ የሚመጣው ደም ሲፈስ ወይም የአንዱ ሕይወት በሌላው ሲተካ ብቻ ነው። በብሉይ ኪዳን በእንስሳት ደም የኃጢአት ይቅርታ ይገኝ ነበር። የአምልኮ ስፍራ የሆነው የመገናኛው ድንኳን ሳይቀር በደም መርጨት መንጻት ያስፈልገው ነበር። ክርስቶስ ከእንስሳት ደም የከበረ ደሙን ባቀረበ ጊዜ በሰማያዊቷ ቤተ መቅደስ ውስጥ ይህንኑ የሚመስል ተግባር አከናውኗል።

መ. የክርስቶስ ደም በስርየት ቀን እንደሚቀርቡት የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች ለአንድ ዓመት ብቻ የሚሠራ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሁሉ ለሁልጊዜ ያነጻል። በዚህም ዘላለማዊ ይቅርታን ያስገኝላቸዋል። እንደ አሮጌው የአምልኮ ሥርዐት መሥዋዕቶች በየቀኑ መቅረብ አያስፈልጋቸውም።

ክርስቶስ አንድ ጊዜ ብቻ መሞቱ በቂ ነው። የክርስቶስ መሥዋዕት የሰዎችን ኃጢአት የሚያነጻው ከሞቱ በኋላ ብቻ አይደለም። ነገር ግን ከመሞቱ በፊት በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩትን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአትም ያነጻል። የእርሱ ደም በመጀመሪያው ኪዳን ሥር ለነበሩት እውነተኛ አማኞች ይቅርታን እና ነጻነትን ያስገኝላቸዋል።

ክርስቶስ ለኃጢአታችን ሁሉ ተገቢውን ዋጋ ከፍሏል። ስለሆነም እኛ ለኃጢአታችን የምንከፍለው ነገር አይኖረንም። አይሁዳውያን አማኞች የእንስሳት መሥዋዕት ለማቅረብ በመፈለጋቸው የክርስቶስን ሞት ዋጋ እያሳጡ ነበር። ዛሬም ብዙ ክርስቲያኖች ለኃጢአታቸው ዋጋ ለመክፈል በመፈለጋቸው የክርስቶስን ሞት ከንቱ ያደርጋሉ። (ለምሳሌ፥ ለቄስ መናዘዝ፥ ከሚገባ በላይ ማልቀስ፥ ደረትን መድቃት፥ የምነና ጉዞ ማድረግ፥ ወዘተ. . .)

ክርስቲያኖች ሆነን ሳለ ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ የእግዚአብሔርን ይቅርታ የምንጠይቀው ከሲኦል ዘላለማዊ ፍርድ ለማምለጥ አይደለም (1ኛ ዮሐ 1፡9)። የክርስቶስ ደም ቀድሞውኑ ኃጢአታችንን ሁሉ ሸፍኖታል። ቀደም ሲል ክርስቶስ የበፊቱን፥ የአሁኑን እና የወደፊት ኃጢአታችንን ሁሉ በደሙ ሸፍኖታል። አንድ አማኝ ለኃጢአቱ ይቅርታ በሚጠይቅበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ኅብረት መልሶ ያገኘዋል። ይህም ኅብረት በኃጢአት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ነው።

ሠ. አይሁዳውያን ሊቀ ካህናት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ይቅርታ ለማስገኘት በየዓመቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ሲገቡ ኖረዋል። ክርስቶስ ግን የእግዚአብሔርን ዕቅዶች ለመፈጸም ሁለት ጊዜ ብቻ መምጣት ያስፈልገዋል። ክርስቶስ መጀመሪያ ሲመጣ የእግዚአብሔር ሕዝብ የኃጢአት ይቅርታን አምጥቶላቸዋል። ዳግም በሚመለስበት ጊዜ ደግሞ ሀ) የእግዚአብሔርን ልጆች በመለወጥ እና በማክበር ደኅንነታቸውን ፍጹም ያደርገዋል። ለ) ለማመን በማይፈልጉት ላይ ፍርዱን ይገልጣል።

ረ. የብሉይ ኪዳን ሕግና የአምልኮ ሥርዓት ጊዜያዊ ሲሆኑ ክርስቶስ የጀመረው አዲሱ ኪዳን ግን ዘላለማዊ ነው፡፡ እንደ መገናኛው ድንኳን ሁሉ ሕጉ ወደፊት የሚመጡ የመልካም ነገሮች ጥላ ነበር። ጸሐፊው ይህን ሲል የብሉይ ኪዳን ሕግና የአምልኮ ሥርዓት ጊዜያዊ እና ዝቅተኛ ደረጃ የሚሰጠው መሆኑን መግለጹ ነበር። ይህም ለኃጢአተኞች የሚፈስሰውን የክርስቶስ ደም የሚያካትት የተሻለ እና የተሟላ የአምልኮ ሥርዓት እስኪመጣ ድረስ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሰጠው ሥርዓት ነበር። አዲሱ የእግዚአብሔር ፍጹም የአምልኮ ሥርዓት ከመጣ በኋላ የብሉይ ኪዳኑ ጊዜያዊ አምልኮ አስፈላጊ አልሆነም።

ሰ. የእንስሳት ደም የሰዎችን ኃጢአት የሚያነጻው ለጊዜው ብቻ ነበር። የክርስቶስ ሞት ግን የተሟላ፥ ዘላለማዊ መንጻትንና ይቅርታን ያስገኛል፡፡ የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓት የሚካሄደው በፍየሎች እና በኮርማዎች ደም ነበር። የእንስሳት መሥዋዕት በተደጋጋሚ መቅረቡ እንስሳ ለሰው ልጅ ኃጢአት ምትክ ሊሆን እንደማይችል ያመለክታል። አለዚያ ተከታታይ የእንስሳት መሥዋዕቶች ማቅረብን አስፈላጊ አይሆንም ነበር። የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ራሳቸው እግዚአብሔርን ለማርካት የእንስሳት መሥዋዕቶች መቅረባቸው በቂ እንዳልሆነ ያመለክታሉ (1ኛ ሳሙ. 15፡22፤ መዝ. 51፡17፤ ኢሳ. 1፡11፤ 66፡2-3)። ስለሆነም እግዚአብሔርን የሚያስደስት ሌላ ዓይነት መሥዋዕት ማቅረቡ የግድ ነበር። ክርስቶስ እግዚአብሔር የተሻለ መሥዋዕት እንዲቀርብለት የወጠነውን ዕቅድ በሁለት መንገዶች አሟልቷል። በመጀመሪያ፥ ሰውነቱን እንደ ፈቃደኛ ኃጢአት የሌለውና ታዛዥ መሥዋዕት አቅርቧል። ክርስቶስ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ በመሆኑ፣ የተሻለ መሥዋዕት ሊሆን በቅቷል። ሁለተኛ፥ ኢየሱስ አንድ ጊዜ ብቻ ለሰው ልጅ ኃጢአት ለመሞት መቻሉ እጅግ የሚበልጥ ነበር። ኢየሱስ ለሰው ልጆች ኃጢአት አንድ ጊዜ ብቻ ሊሞት መገደዱ ከሁሉ የተሻለ ነገር ነበር። ይኸው አንድ መሥዋዕት ኃጢአተኛ የነበሩት የእግዚአብሔር ልጆች በሙሉ ፍጹማን፥ ሙሉአን፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሊያደርጋቸው ችሏል።

ሸ. የእንስሳት መሥዋዕቶችን የማቅረቡ ሰብአዊ አገልግሎት ሊጠናቀቅ ባለመቻሉ ቀደም ሲል የነበሩት ሊቃነ ካህናት ተግባራቸውን ፈጽመው ሊቀመጡ አልቻሉም ነበር። ነገር ግን የክርስቶስ የመሥዋዕትነት አገልግሎት ለአንድ ጊዜ ስለተጠናቀቀ እና ሌላ ተጨማሪ መሥዋዕት ስለማያስፈልግ፥ ክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀምጧል። ከመሥዋዕቱ መቅረብ በኋላ የተከሰተው ሁኔታ እግዚአብሔር በክርስቶስ ፍጹም መሥዋዕት እንደረካ ያረጋግጣል። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ወንበር ስላልነበረ እና አገልግሎቱም ስላልተጠናቀቀ፥ ሰአሮጌው ኪዳን ዘመን ሊቀ ካህናቱ ሊቀመጥ አይችልም ነበር። ሊቀ ካህናታችን ኢየሱስ ግን በእግዚአብሔር ቀኝ ሊቀመጥ ችሏል። እራሱን በመስቀል ላይ ለእግዚአብሔር ካቀረበ በኋላ፥ ክርስቶስ ተጨማሪ እንስሳትን ወይም እራሱን እንደገና መሠዋት አላስፈለገውም፤ ምክንያቱም ደሙ የሰውን ልጆች ኃጢአት በሙሉ ያነጻልና። ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ በሚገዛበት በአሁኑ ወቅት እግዚአብሔር ጠላቶቹ ለክርስቶስ እስኪገዙለት ድረስ መሥራቱን ይቀጥላል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ክርስቶስ በሰማይ ቆሞ የምንመለከትበት ብቸኛ ስፍራ ከልጆቹ መካከል ሊሞት የነበረውን አንድ ሰው ወደ መንግሥተ ሰማይ ለመቀበል ብቻ ነው (የሐዋ. 7፡55)።

ጸሐፊው በመልእክቱ ማጠቃለያ ላይ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከተጻፉት የአዲስ ኪዳን ተስፋዎች ሁለት የመጨረሻ ማረጋገጫዎችን ያቀርባል። እነዚህም በአሁኑ የአምልኮ ሥርዓት የእንስሳት መሥዋእቶች ለምን እንደማያስፈልጉ የሚያስረዱ ናቸው (ኤር. 31፡33)። በመጀመሪያ፥ በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ቃል በሕዝቡ ልብ ላይ ስለሚጻፍ፥ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ይፈልጋሉ፥ ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር የሕዝቡን ኃጢአት ይቅር ለማለት ቃል ገብቷል። እግዚአብሔር ይቅርታን ስለሰጠ የእንስሳት መሥዋዕት ማቅረቡ አስፈላጊ አይሆንም። ስለሆነም የአይሁዳውያን ክርስቲያኖች ወደ እንስሳት መሥዋዕት መመለሱ ሞኝነት ነበር። ይህ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሰጠውን የተስፋ ቃል ቸል እንደ ማለት ነበር። እንዲሁም የእግዚአብሔር ልጆች በክርስቶስ ሞት በማመን የሚያገኙትን ፍጹም ይቅርታን አለመቀበልም ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ ክፍል ዛሬ የእንስሳት መሥዋዕቶችን ማቅረብ ከንቱ እንደሆነና በክርስቶስ ሞት አላማመናችንን የሚያሳየው እንዴት ነው። ለ) ሌሎች ክርስቲያኖች ግን የሚያከናውኗቸው እና ክርስቶስ ኃጢአታቸውን ለማስወገድ እንደ ሞተ አለማመናቸውን የሚያጋልጡ አንዳንድ ተግባራት ምን ምንድን ናቸው?

ክርስቶስ አገልግሎቱን የሚሰጠው ከመገናኛው ድንኳን በምትበልጠው ከሰማይቱ ቤተ መቅደስ ውስጥ ነው (ዕብ. 9፡1-12)

የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓት በሚከተሉት ነገሮች ላይ የተመሠረተ ነበር። ሀ) በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የተደረገ ብሉይ ኪዳን (ስምምነት)፥ ለ) አምልኮን የሚመራ ሊቀ ካህናት፥ ሐ) ኃጢአትን የሚሸፍኑ የእንስሳት መሥዋዕቶች፥ እና መ) አምልኮ የሚካሄድበት የመገናኛ ድንኳንና በኋላም ቤተ መቅደስ ናቸው። የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ክርስቶስ ከእነዚህ ሁሉ የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ነገሮች እንደሚበልጥና እነርሱንም እንደሚተካቸው ያስረዳል። ክርስቶስ ከአሮን የዘር ሐረግ ከፈለቁት ሰብአውያን ሊቃነ ካህናት የሚበልጥ ሊቀ ካህናት መሆኑን ያብራራል (ዕብ. 7)። ቀደም ብሎ አዲሱ ኪዳን አሮጌውን ኪዳን እንደሚተካና እንደሚበልጥ አብራርቷል (ዕብ. 8)። አሁን ደግሞ ክርስቶስ በምትሻል ቤተ መቅደስ ውስጥ እንደሚያገለግልና ከብሉይ ኪዳን ዘመናት የበለጠ መሥዋዕት እንደሚሠዋ ያስረዳል።

ጸሐፊው መጀመሪያ በሰሎሞን፥ በዘሩባቤል በታደሰውና በንጉሥ ሄሮድስ በድጋሚ ታድሶ በጥንቱ ዓለም ውስጥ ከነበሩት ታላላቅ ሕንጻዎች አንዱ ሊሆን የቻለው ቤተ መቅደስ ላይ ከማተኮር ይልቅ፥ የመጀመሪያውን የአምልኮ ስፍራ (የመገናኘው ድንኳን) የትምህርቱ መሠረት እንዲሆን አድርጓል። ጸሐፊው የመገናኛውን ድንኳን ለምን እንደመረጠ አናውቅም። ምናልባት የመገናኛው ድንኳን የመጀመሪያ የአምልኮ ስፍራ ስለነበረና ንድፉም በቀጥታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለመጣ ይሆን ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፡– ስለ መገናኛ ድንኳን ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እና ከዘጸአት 37፡1-38፡8 አንብብ። የመገናኛውን ድንኳን ሁለት ክፍሎች እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ውስጥና ውጪ የሚገኙትን የተለያዩ ዕቃዎች የሚያሳይ ሥዕል ሣል። በንድፉና የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚገኙትን ዕቃዎች በሚደረድርበት ሁኔታ መካከል ምን ዓይነት ልዩነቶችን ትመለከታለህ።

ሀ) ሊቀ ካህናቱ የሚያገለግሉበት የመገናኛው ድንኳን

በዕብራውያን 9፡1-10 ጸሐፊው እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ የሰጠውን የመጀመሪያውን የአምልኮ ስፍራ ይገልጣል። አይሁዶች በምድረ በዳ ውስጥ በሚቅበዘበዙበት ጊዜ እና በኋላም በመሳፍንት ዘመን ይጠቀሙበት የነበረው የመገናኛው ድንኳን የተሠራው ሙሴ የብሉይ ኪዳን ሕጎችን ከተቀበለ በኋላ ነበር።

የመገናኛው ድንኳን ተንቀሳቃሽ የአምልኮ ስፍራ ነበር። በዚሁ ሰፊ ትልቅ ድንኳን ውስጥ ሁለት ሰፋፊ ክፍሎች ነበሩ። ከሁለቱም የበለጠ ሰፋ የሚለው ውጫዊው ክፍል ቅዱስ ስፍራ በመባል ይታወቃል። አነስ የሚለው ውስጠኛ ክፍል ቅድስተ ቅዱሳን በመባል ይጠራል። በእነዚህ በሁለት ክፍሎች መካከል ከጣሪያው እስከ ወለሉ የወረደ መጋረጃ ይዘረጋል። በውጭ ሦስት የአምልኮ ዕቃዎች ነበሩ። እነዚህም የኅብስቱ መቀመጫ የሆነው ጠረጴዛ፥ ብርሃን የሚሰጥ መቅረዝና ዕጣን የሚሠዋበት የወርቅ መሠዊያ ነበሩ። የወርቅ መሠዊያው ሁለቱን ክፍሎች ከሚለየው መጋረጃ ፊት ይቀመጥ ነበር። በድንኳኑ ውስጠኛ ክፍል አንድ ዕቃ ብቻ ነበር። እርሱም የቃል ኪዳኑ ታቦት ነበር። ሽፋኑ «የስርየት መክደኛ» በመባል ይጠራ ነበር። ከዚህ መክደኛ በላይ የእግዚአብሔር ህልውና አንጸባራቂ ክብር ነበር። ከታቦቱ ውስጥ መና የአሮን በትርና አሥርቱ ትእዛዛት የተጻፈባቸው ጽላቶች ነበሩ (ዘዳግም 10፡1-15)።

የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ የወርቅ መሠዊያው በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ እንደሚገኝ መግለጹ አስገራሚ ነው። ምናልባትም ይህንን ያደረገው በስርየት ዕለት ላይ ለማተኮር ይሆናል። በዚያን ቅዱስ ዕለት የወርቅ መሠዊያው በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከሚካሄደው አምልኮ ጋር በቅርብ የተሣሠረ ነበር። በዓመት አንድ ጊዜ በሚከበረው የስርየት በዐል ቀን ሊቀ ካህናቱ መጀመሪያ ወደ ቅዱስ ስፍራ ይገባና የዕጣን መሠዊያውን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይወስዳል። ከዚያም ከልዩ የእንስሳት መሥዋዕት ደም የተወሰደውን ይዞ ወደ ውስጠኛው ክፍል ይገባና በቃል ኪዳኑ ታቦት ላይ ደሙን ይረጫል። ይህም ደም እርሱም ሆነ ሕዝቡ ዓመቱን ሙሉ በእግዚአብሔር ላይ የፈጸሙትን ኃጢአት ያነጻላቸዋል።

የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ይህ መንፈስ ቅዱስ ለአይሁዶች ለማሳየት የሚፈልገው ምሳሌያዊ ትምህርት መሆኑን ያመለክታል። በመጀመሪያ ቅዱስ ስፍራን ከቅድስተ ቅዱሳን የሚለየው መጋረጃ ፥ ለአይሁዶች ሁልጊዜም ከእግዚአብሔር ህልውና የተለዩ መሆናቸውን የሚያስረዳ መሆኑን ይገልጻል። የእንስሳት መሥዋዕቶች ኃጢአተኛ ሰዎች እግዚአብሔር ወዳለበት ስፍራ ይገቡ ዘንድ ከኃጢአታቸው ሊያነጹ አይችሉም ነበር። ሁለተኛ፥ ይህ በየዓመቱ የሚደጋገም ሥርዐት ነበር። ድግግሞሹ የሰዎች ኃጢአት ሙሉ በሙሉ እንዳልተሽፈነ እና የእንስሳትን መሥዋዕቶች ወይም ደግሞ ሌሎች የአምልኮ ልምዶች የአምላኪዎችን ሕሊና ሊያነጹ እንደማይችሉ ያስገነዝባል። ስለሆነም ይህ የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዐት ደካማና ክርስቶስ ካከናወነው ተግባር ጋር ሲነጻጸር ያልተሟላ መሆኑን ያሳያል።

ለ) ኢየሱስ በታላቁ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚሰጠው አገልግሎት

በዕብራውያን 9፡11-12 ጸሐፊው ክርስቶስ በሰማያዊቱ እና በምትበልጠው ቤተ መቅደስ ውስጥ ወደሚያከናውነው አገልግሎት ይመለሳል። ጸሐፊው የመገናኛው ድንኳን በሰማይ ያላቸው የታላቋ ቤተ መቅደስ ግልባጭ እንደሆነች አመልክቷል። ሰማያዊው ቤተ መቅደስ ከመገናኛው ድንኳንም ሆነ በምድር ላይ ከተሠሩት ቤተ መቅደሶች የላቀች ነበረች (ዕብ 8፡5-6)። እግዚአብሔር በውበቱ የሚኖረው በሰማይ ነው። አሁን ደግሞ ጸሐፊው በሰማይ የሚካሄደው የክርስቶስ አገልግሎት በማደሪያው የመገናኛ ድንኳን ውስጥ ከሚካሄደው የሰብአዊ ሊቃነ ካህናት አገልግሎቶች እንደሚበልጥ ያስረዳል። ለዚህም ምክንያቱ ክርስቶስ የሚያገለግልበት ሰማያዊቱ ቤተ መቅደስ እንደ የመገናኛው ድንኳን እና ቤተ መቅደስ በሰዎች ሳይሆን በእግዚአብሔር የተሠራች መሆኗ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ ከሰማያዊው እውነተኛ የአምልኮ ስፍራችን በላይ በሰው እጅ በተሠሩት የቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎች ላይ ከመጠን በላይ ትኩረት ስለ መስጠት ምን ያስተምረናል? ለ) ጸሎት በሰማይ ወዳለው የእግዚአብሔር የጸጋ ዙፋን የሚያቀርበን ከሆነ (ዕብ 4፡16)፥ አምልኮን በምናካሂድበት ጊዜ በመንፈሳዊ ሁኔታችን የት ስፍራ እንደምንገኝ ግለጽ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት (ዕብ 8፡1-13)

ጸሐፊው መልእክቱን ካቀረበባቸው ልዩ መንገዶች አንዱ አንድን አዲስ አሳብ ካቀረበ በኋላ መለስ ብሎ በዝርዝር ማቅረቡ ነው። ስለ ክርስቶስ ሊቀ ካህንነት በዝርዝር ከመጻፉ በፊት ጸሐፊው በብዙ ምዕራፎች ውስጥ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት መሆኑን ገልጾአል (ዕብ. 2፡17-18፤ 4፡14-16)። በዕብራውያን 8፡1-6 ደግሞ ሁለት አዳዲስ አሳቦችን ያቀርብልናል። እነዚህንም ወደ በኋላ ዘርዘር አድርጎ ያብራራቸዋል።

ሀ) ክርስቶስ ሊቀ ካህናት እንደ መሆኑ፥ በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ቤተ መቅደስ በተሻለ ሰማያዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ ያገለግላል። ሊቀ ካህናት አገልግሎታቸውን የሚያበረክቱት በቤተ መቅደሶች ውስጥ ነበር። በመሆኑም አይሁዶች ቤተ መቅደሱ የሚሻል ከሆነ፥ አገልግሎቱ የላቀ እንደሚሆን ያስቡ ነበር። ስለሆነም፥ ጸሐፊው ሁለት ዓይነት ሊቃነ ካህናት የሚያገለግሉባቸውን ሁለት ቤተ መቅደሶችን ያነጻጽራል። እነዚህም ሁለት ዓይነት ሊቃነ ካህናት የሚያገለግሉባቸው ነበሩ። አይሁዳውያን ሊቃነ ካህናት የሚያገለግሉበት የኢየሩሳሌሙ ቤተ መቅደስ በሰማይ ያለው ቤተ መቅደስ ግልባጭ (ሞዴል) ነበር። ክርስቶስን የሚያገለግለው በዚሁ ቅዱስና ግልባጭ ባልሆነው ቤተ መቅደስ ውስጥ ነበር። ይኸው ክርስቶስ ከአይሁዳውያን ሊቃነ ካህናት እንደሚበልጥ የሚያመለክት መስፈርት ነው። ጸሐፊው በዕብ 9፡1-10 ይህንኑ አሳብ ሰፋ አድርጎ ያብራራዋል።

ለ) ከሊቀ ካህናት አገልግሎቶች አንዱ መሥዋዕቶችን ማቅረብ በመሆኑ፥ ክርስቶስ ከእንስሳት መሥዋዕቶች የሚበልጥ መሥዋዕት አቅርቧል። በመስቀል ላይ ራሱን በመሞት አቅርቧል። ይህ ዕብ. 8፡3 ፍንጭ የተሰጠው ሲሆን፥ ዕብ 9፡11-10፡18 በሰፊው ተብራርቷል። ይኸው አሳብ ቀደም ሲል በዕብ 7፡26-27 ቀርቧል።

ጸሐፊው የኢየሱስ አገልግሎት ከአሮን አገልግሎት እንዴት እንደሚበልጥ ከማብራራቱ በፊት የኢየሱስን ታላቅነት ለማሳየት ቀጣዩን ዐቢይ ርእሰ ጉዳይ ይጠቅሳል። ካህናት ስለሚያገለግሉበት ሁኔታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ትእዛዛቱን ስለተቀበሉ፥ ጸሐፊው ለሁለቱ ዓይነት ሊቃነ ካህንነት የሚሰጡትን ትእዛዛት ወይም የሚሰጠውን የአገልግሎት መሠረቶች ያነጻጽራል። ጸሐፊው ብሉይና አዲስ ኪዳናትን ያነጻጽራል። አሮጌው ኪዳን እንደ ወደቀ አምልኮ ወይም የመንግሥተ ሥርዐት ነበር። በዚያው አሮጌ የአምልኮ ሥርዓት ውስጥ አምልኮውን የሚመራው አሮን ነበር። አሁን ግን እግዚአብሔር «አዲስ ኪዳን» ሰጥቶናል። ይህም የአዲሱ የአምልኮ ሥርዓት ነው፡፡ አንድ መንግሥት ወድቆ ሌላው ሰሚተካበት ጊዜ፥ በአመዛኙ የሕገ መንግሥት ለውጥ ይደረጋል። ይህም ለአዲሱ መንግሥት አሥራር በሚያመች መልኩ የሚቀረጽ ይሆናል። በተመሳሳይ መንገድ፥ አዲስ ኪዳን በሚመሠረትበት ጊዜ አዲስ ሥርዓትና አዲስ ሊቀ ካህናት አስፈላጊዎች ይሆናሉ። ይህም አዲሱን የአምልኮ መንገድ ለማካሄድ ያስችላል። እግዚአብሔር ይህንን አዲስ ሥርዐት «አዲሱ» ኪዳን ብሎ መጥራቱ የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዐት እንዳከተመለት ያመለክታል። ይህም በ70 ዓመተ ምሕረት ሮማውያን የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ በደመሰሱበት ወቅት ተግባራዊ ሆኗል።

ጸሐፊው፥ «አሁን ግን በሚሻል ተስፋ ቃል በተመሠረተ በሚሻል ኪዳን ደግሞ መካከለኛ እንደሚሆን፥ በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል አገልግሎት አግኝቷል።» ይላል። አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በብሉይ ኪዳን ሥር ወደሚካሄድ አሮጌ ሥርዐት መመለሱ ሞኝነት መሆኑን ለማመልከት ሁለት ነገሮችን ይጠቅሳል።

ሀ) በሲና ተራራ የተጀመረው አሮጌው ኪዳን ከአዲሱ ዝቅ ያለ ነው። እግዚአብሔር በአዲስ የቃል ኪዳን ሥርዐት ለመቀየር የተስፋ ቃል መግባቱ የአሮጌውን ዝቅተኛነት ያሳያል። ማንም ቢሆን ፍጹሙን ነገር አስወግዶ አነስተኛውን ነገር ሊተካ አይፈልግም። የአሮጌው ቃል ኪዳን እንከን ያለበት በመሆኑና የእግዚአብሔርን ዕቅዶች (ሰዎችን ወደ ድነት (ደኅንነት) ሊያመጣ ስላልቻለ፥) እግዚአብሔር የሚሻል አዲስ ኪዳን መሥርቶአል።

ለ) እግዚአብሔር በኤርምያስ 31፡31-34 የተስፋ ቃል የሰጠው አዲሱ ኪዳን በአያሌ መንገዶች ከሲና ተራራው እሮጌ ኪዳን በሚሻሉ የተስፋ ቃሎች ላይ የተመሠረተ ነበር።

 1. አሮጌው ኪዳን በቅድመ-ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነበር። እግዚአብሔር ሕዝቡ ከታዘዙት እንደሚባርካቸው ገልጾ ነበር። ነገር ግን ካልታዘዙት እንደሚቀጣቸው ገልጾአል። የብሉይ ኪዳን ታሪክ እንደሚያሳየው፥ አይሁዶች ቃል ኪዳኑን ሊታዘዙ ባለመቻላቸው የእግዚአብሔርን ቁጣና ፍርድ ሲቀበሉ ኖረዋል፡፡ እንዲያውም፥ እግዚአብሔር ለኤርምያስ አዲሱን ቃል ኪዳን ለመስጠት ቃል በገባ ጊዜ አይሁዶች ወደ ባቢሎን ምርኮ ሊጋዙ ተቃርበው ነበር። በተቃራኒው አዲስ ኪዳን በመታዘዝ ቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ አይደለም። ነገር ግን በልብ መለወጥ ላይ የተመሠረተ ነው። ይህም እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ለሚያምኑ ሁሉ የሚያከናውነው ተግባር ነው።
 2. ብሉይ ኪዳን ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲታዘዙ ቢጠይቅም፥ የሚታዘዙበትን ኃይል አልሰጣቸውም ነበር። በመሆኑም፥ ያ ዘመን ባለመታዘዝ ተለይቶ የሚታወቅ ነበር። በአዲስ ኪዳን፥ እግዚአብሔር ሕጉን በሰዎች አእምሮና ልብ ላይ ለመጻፍ ቃል ገብቷል። ይህም ሰዎች ቃሉን ሊታዘዙ ያስችላቸዋል። በአዲሱ ኪዳን መታዘዝ የሚመጣው ከተለወጠ ልብ ነው። እንደ የብሉይ ኪዳን ዘመን ሰዎች እግዚአብሔርን የሚታዘዙት እንዳይቀጣቸው በመፍራት አይደለም።
 3. በብሉይ ኪዳን ዘመን ሰዎች ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔርን አልታዘዙትም ነበር። እንደ ሙሴና ዳዊት ያሉ ሰዎች እግዚአብሔርን ሲታዘዙት፥ አብዛኞቹ ሰዎች ግን ባለመታዘዝ ነበር የኖሩት። በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ አምላካቸውን በመታዘዛቸው ተለይተው ይታወቃሉ።
 4. በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ ጊዜያዊ ይቅርታና ከኃጢአት መንጻት የሚያገኙት በተደጋጋሚ መሥዋዕቶችን በማቅረብ ነበር። በአዲሱ ኪዳን ግን እግዚአብሔር የሕዝቡን ኃጢአቶች ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይቅር እንደሚልና መልሶም እንደማያስታውስ ቃል ገብቷል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳኑ ለእኛ የሚሰጠን እነዚህ የተስፋ ቃሎች አይሁዶች በብሉይ ኪዳን ዘመን ከተቀበሏቸው የተስፋ ቃሎች የሚበልጡት እንዴት ነው? ለ) የአንተ ሕይወት በብሉይ ኪዳን ዘመን አይሁዶች ከእግዚእብሔር ጋር ከነበራቸው ግንኙነት የሚለየው እንዴት ነው? ሐ) እግዚአብሔርን አሁን ስላለህበት አዲስ ኪዳን ለማመስገን ጊዜ ውሰድ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የክርስቶስ ሊቀ ካህንነት ከአሮን ሊቀ ካህንነት ይበልጣል (ዕብ. 7፡1-28)

የዕብራውያን መልእክት የተጻፈው በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት ትተው ወደ ቀድሞው ኃይማኖታቸው (ይሁዲነት) ለመመለስ ለሚያስቡ ሰዎች ነው። ስደትን ከመፍራታቸው የተነሣ እምነታቸውን ለመካድ በማሰብ ላይ ነበሩ። ምንም እንኳን ቀደም ሲል ስደት የደረሰባቸው ቢሆንም፥ በዚህ ጊዜ በተለይም ከይሁዳውያን ወገኖቻቸው ተጨማሪ ስደት ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም። እንዲሁም እነዚህ አማኞች ክርስቶስ ብቸኛው የድነት (ደኅንነት) መንገድ መሆኑን መጠራጠር ጀምረው ነበር። በብሉይ ኪዳን ዘመን በክርስቶስ ማመን ሳያስፈልጋቸው አይሁዶች በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አግኝተው ስለነበር፥ አሁንም በአይሁዳዊ አምልኮአቸው ብቻ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን የሚያገኙ መሰላቸው። በመሆኑም፥ «በሊቀ ካህናቱ አማካኝነት በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚካሄደውን የእንስሳት መሥዋዕት እያቀረብን በማምለክ ብቻ ድነትን (ደኅንነትን) ልናገኝ ከቻልን፥ ለምን አላስፈላጊ ስደት እንቀበላለን?» ሲሉ አሰቡ። የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ግን ክርስቶስ ከሁሉም የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓቶች እንደሚበልጥና የእነዚህም ሥርዐቶች ፍጻሜ መሆኑን ይገልጽላቸዋል። ክርስቶስን መካድ ወደ ብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዐት እንዲመለሱ አያስችላቸውም ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር የብሉይ ኪዳንን አምልኮ በመዝጋት በክርስቶስ በኩል አዲስ የአምልኮ መንገድ ከፍቶአልና ወደ ይሁዲነት መመለሱ አማራጭ የአምልኮ መንገድ ሊሆን አይችልም። ይልቁንም ይህ በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸም ክህደት ይሆናል። ከዚህም የተነሣ ምርጫቸው እንደ ዓለማውያን ሁሉ ለዘላለማዊ ፍርድ የሚያጋልጣቸው መሆኑን ያስገነዝባቸዋል።

(ማስታወሻ:- የዕብራውያን ምዕራፍ 7 ክርስቶስ ከአሮናዊ ሊቀ ካህንነት የሚበልጥ መሆኑን የሚያሳየው ዐቢይ ትምሕርት ቅጥያ ነው፡፡)

የዕብራውያን ጸሐፊ ክርስቶስ በመልከ ጼዴቅ ሥርዓት ለዘላለም የሚኖር ሊቀ ካህናት መሆኑን ለሁለተኛ ጊዜ ይጠቅሳል። ቀደም ሲል (ዕብ. 5፡1-10) ጸሐፊው ክርስቶስ ሰው እንደ መሆኑ መጠን የሚያስፈልገን ርኅሩኅ ሊቀ ካህናት ሊሆን እንደበቃ አስረድቷል። አሁን ደግሞ ክርስቶስ በምን ሥልጣን ሊቀ ካህናት ሊሆን እንደበቃ ያብራራል። አይሁዳውያን አማኞች ብሉይ ኪዳናቸውን በሚገባ ያውቁት ነበር። እነዚህ ሰዎች ሊቀ ካህንነት ለአሮን የዘር ሐረግ ብቻ እንደተሰጠ ያውቁ ነበር። ስለሆነም ከይሁዳ ነገድ የሆነ ኢየሱስ እንዴት ሊቀ ካህናት ሊሆን እንደሚችል ሳያስቡ አልቀሩም። ጸሐፊው ከአሮን ዘሮች የሚልቁ ሌላ ዓይነት ሊቀ ካህናት እንዳሉ ያስገነዝባቸዋል። ይህም የመልከ ጼዴቅ የዘር ሐረግ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዘፍጥረት 14፡17-20 አንብብ። ይህ ታሪክ ስለ መልከ ጼዴቅ ምን ይነግረናል። አብርሃም ከመልከ ጼዴቅ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ነበረው። ለ) ስለ መልከ ጼዴቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንብብ። መልከ ጼዴቅ ከአሮን የበለጠው ለምንድን ነው?

ጸሐፊው የአይሁዶችን የክርክር ዘዴ በመጠቀም፥ ክርስቶስ ከአሮን እንደሚበልጥ ያረጋግጥላቸዋል። ይህንን ያደረገው መልከ ጼዴቅ ከአሮን እንደሚበልጥ በማሳየት ነው። ጸሐፊው ክርክሩን በማስደገፍ የተጠቀመባቸውን ነጥቦች ከዚህ በታች ተመልከት።

ሀ) መልከ ጼዴቅ ካህንና ንጉሥ በመሆኑ ከአሮን ይበልጣል። በሌላ በኩል፥ በአብርሃም ዘር የተወለደው አሮን ካህን ብቻ በመሆኑ ከመልከ ጼዴቅ ያንሳል። ክርስቶስም እንደ መልከ ጼዴቅ ካህንና ንጉሥ ነበር።

ለ) ስፍራውንና ሥልጣኑን የሚያመለክተው የመልከ ጼዴቅ ስም «የጽድቅ ንጉሥ» የሚል ፍች ይሰጣል። በመሆኑም መልከ ጼዴቅ የጽድቅ ንጉሥ የሆነው (ኤር. 23፡5-6) የክርስቶስ ተምሳሌት ነበር። የአሮን ትውልዶች ግን በአመዛኙ በክፋት የተሞሉና ከጽድቅ የራቁ ነበሩ።

ሐ) መልከ ጼዴቅ በኋላ ኢየሩሳሌም ተብላ የተጠራችው የሳሌም ከተማ ንጉሥ ነበር። ሳሌም የሚለው ቃል ሰላም የሚል ፍቺ አለው። ስለሆነም መልከ ጼዴቅ የሰላም ንጉሥ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። የመሢሑም ግዛት መለያ ሰላም እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ኢሳ. 9፡6-7)። የአሮን ሊቀ ካህናት ግን በውጫዊም ሆነ በውስጣዊ ረገድ ለአይሁዶች ሰላምን አላሰፈነም።

መ) መልከ ጼዴቅ የትውልድ ሐረግም ሆነ የዘመን መጀመሪያና መጨረሻ አልነበረውም። እርሱ ለዘላለም ካህን ነበረ። የመልከ ጼዴቅ ታሪክ በዘፍጥረት መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ሆኖ እናገኘዋለን። በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ሁሉም ዐበይት ገጸ ባሕርያት ከማን እንደ ተወለዱና መቼ እንደ ሞቱ የሚያሳይ የዘር ሐረግ አላቸው። ምንም እንኳን መልከ ጼዴቅ በአንድ ወቅት የሞተ ታሪካዊ ሰው ቢሆንም፥ ስለ ዘር ሐረጉም ሆነ ስለ ሞቱ የተገለጸ ነገር የለም። በመሆኑም፥ መጀመሪያና መጨረሻ እንደሌለው በሚያሳይ መልኩ ተተርኮ እናገኘዋለን። በዚህ ረገድ መልከ ጼዴቅ መጀመሪያና መጨረሻ እንደሌለው ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ እናገኘዋለን። ስለሆነም በመሞታቸው ከሚታወቁ የአሮን የዘር ሐረግ ሊቀ ካህናት በተቃራኒ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለም ይኖራል።

ሠ) የአይሁዶች አባት የሆነው አብርሃም የጦርነት ምርኮውን ለመልከ ጼዴቅ በአስራት መልክ ስለሰጠውና ከመልከ ጼዴቅም በረከትን ስለተቀበለ፥ መልከ ጼዴቅ ከአይሁዶች አሮን ይበልጣል። የአስራት እና የበኩራት መርህ ትንሹ ለትልቁ አሥራትን እንደሚሰጥ፥ ትልቁ ደግሞ ትንሹን እንደሚባርክ ያሳያል። ስለሆነም በአይሁዶች አስተሳሰብ፥ አሮን ከአብርሃም ዘር ስለተወለደ አብርሃም ለመልከ ጼዴቅ አሥራትን በመክፈል እና በእርሱም በመባረክ ታላቅነቱን በገለጸ ጊዜ፥ አሮን በአብርሃም ዘር ውስጥ ነበረ። ስለሆነም እንደ መልከ ጼዴቅ ካህን የሆነው ክርስቶስ ከአብርሃም ከተወለደ ከአሮን ይበልጣል።

ረ) እግዚአብሔር ከመልከ ጼዴቅ የዘር ሐረግ ሌላ ካህን እንደሚመጣ በመተንበይ ከአሮን የዘር ሐረግ የሚመጡ ሊቀ ካህናት ብቁዎች አለመሆናቸውን ገልጾአል። (መዝሙር 110፡4 አንብብ)። እግዚአብሔር የአሮን የዘር ሐረግ ሥልጣን የያዘበትን የብሉይ ኪዳን በአዲሱ የጎልጎታ ኪዳን መተካቱ ለአዲሱ ሥርዓት አዲስ የካህናት የዘር ሐረግ እንዲመሠረት እድርጓል። ክርስቶስ ለማይጠፋ ሕይወት ከሞት ስለተነሣ እግዚአብሔር የአዲሱ ኪዳን ዘላለማዊ ሊቀ ካህናት አድርጎ ሾሞታል።

(ማስታወሻ፡ ጸሐፊው በሰብአውያን ሊቀ ካህናት የሚመራው የመጀመሪያው ቃል ኪዳን ደካማ መሆኑን ምን ያህል በተደጋጋሚ እንደሚገልጽ ልብ በል። አይሁዶች ወደዚሁ ቃል ኪዳን ነበር ለመመለስ የተፈተኑት። በዕብራውያን 7፡11፡ ጸሐፊው የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶችና ሊቀ ካህናት ፍጹምነትን ሊያስገኙ እንደማይችሉ ያስረዳል። ከዚያም በዕብራውያን 7፡18፥ «ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥ ስለዚህ የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትዕዛዝ ተሽራለች» ይላል። ጸሐፊው ከዚህ ይልቅ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት «የሚሻል ተስፋ» እንደተገባልን ይናገራል።

ከዚያም ጸሐፊው የአሮንን ሰብአዊ ሊቀ ካህንነት ከክርስቶስ መለኮታዊ ሊቀ ካህንነት ጋር ያነጻጽራል።

ሀ) የአሮን ክህነት ጊዜያዊ ሲሆን፥ የክርስቶስ ሊቀ ካህንነት ግን ዘላለማዊ ነው። ከሞት የተነሣ፣ የአሮን ሊቀ ካህንነት ብዙ ሊቀ ካህናት ተከታትለው እንዲያገለግሉ አስገድዷቸዋል። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያደረባቸው፥ ሌሎች ደግሞ እግዚአብሔርን የማያስከብሩ ነበሩ። ክርስቶስ ግን ከሞት ስለተነሣና ዘላለማዊ ስለሆነ፥ ለአዲስ ኪዳን ዘመን ብቸኛው ሊቀ ካህናት ነው።

ለ) የአሮን ክህነት ጊዜያዊ እገዛ ሲያመጣ፥ የክርስቶስ ክህነት ግን ለኃጢአተኞች ሁሉ የተሟላ ድነት (ደኅንነት) አስከትሏል። የአሮን ሊቀ ካህንነት አገልግሎት በሞት ምክንያት የሚቋረጥና ከዚህም የተነሣ ለሰዎች ሙሉ ድነት (ደኅንነት) ሊያስገኝ ያልቻለ ሲሆን፥ የኢየሱስ ዘላለማዊ ሊቀ ካህንነት ግን ሙሉ ድነት (ደኅንነት) ያመጣል። እርሱ ሁልጊዜም ለአማኞች ሊያማልድ ይችላል። ሞት የማማለድ አገልግሎቱን ሊያቋርጥበት አይችልም።

ሐ) የአሮን ካህናት ኃጢአተኞች ነበሩ ክርስቶስ ግን ቅዱስ ነው። የአሮን የዘር ሐረግ ካህናት ኃጢአተኞች መሆናቸው አገልግሎታቸውን አደናቅፎታል። ለሰዎች የኃጢአት ይቅርታ መሥዋዕት ከማቅረባቸው በፊት ለራሳቸው ኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ ያስፈልጋቸው ነበር። ክርስቶስ ግን፥ «ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውር የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ» ነው። ስለሆነም አገግልግሎቱ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አለው። እርሱ ኃጢአት ስለሌለበት፥ የኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ አላስፈለገውም።

መ) አሮን ባለማቋረጥ የእንስሳትን መሥዋዕቶች በመሠዋት ጊዜያዊ የኃጢአት ይቅርታን ሲያስገኝ፥ ክርስቶስ ራሱን በመሠዋት ዘላለማዊ ይቅርታን አስገኝቷል። አሮንና ትውልዶቹ በተደጋጋሚ ኃጢአትን ስለ ሠሩ፥ በተደጋጋሚ ለራሳቸው ኃጢአቶች መሥዋዕቶች ማቅረብ ያስፈልጋቸው ነበር። የእንስሳት መሥዋዕቶች ለራሳቸውና ለሌሎች ሰዎች ኃጢአቶች ዘለቄታዊ መፍትሔዎችን የማይሰጡ፥ የእንስሳት መሥዋዕቶች ዕለት በዕለት፥ ዓመት በዓመት ያለማቋረጥ ይቀርቡ ነበር። ክርስቶስ ግን ራሱን በመሠዋት አንድ ጊዜ ብቻ መሞት ያስፈልገው ነበር። ሌላ የኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንተ አይሁዳዊ ክርስቲያን ብትሆን ይህ ክርክር የክርስቶስን መሥዋዕት ትቶ ወደ ብሉይ ኪዳን የአምልኮ መንገድ መመለሱ ሞኝነት እንደሆነ ያሳምንህ ነበር? ለምን? ለ) ክርስቶስን ክዶ ወደ ቀድሞው ሃይማኖት ወይም ወደ ዓለም መመለስ ሞኝነት የሚሆንበትን ምክንያት አብራራ። ሐ) በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ከሚቆም ሰብአዊ ሊቀ ካህናት ይልቅ የክርስቶስ ሊቀ ካህንነት የሚሻለው ለምንድን ነው? የክርስቶስን ሊቀ ካህንነት ትቶ መፍትሔ ፍለጋ ወደ ሰዎች ፊትን ማዞር ሞኝነት የሚሆነው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

በእምነት ስላለመጽናት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (ዕብ. 5፡11-6፡20)

ይህ ራስን ለእግዚአብሔር ለማስገዛትና ለመታዘዝ ትምህርት ጸሐፊው እንደገና ቆም ብሎ በክርስቶስ ላይ የነበራቸውን እምነት ለመተው እያሰቡ ላሉት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ እንዲሰነዝር ገፋፋው። ይህ በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ላሉት የማስጠንቀቂያ ምንባቦች ሁሉ ረጅሙ ሲሆን፥ በአራት ዐበይት ክፍሎች ሊከፈል ይችላል።

ሀ) ጸሐፊው በዕብራውያን 5፡11-14 አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በእምነታቸው ባለማደጋቸው ማዘኑን ይገልጻል። በክርስትና እምነታቸው የቆዩ በመሆናቸው የክርስትናን መሠረታዊ ትምህርቶች ከመከታተል ይልቅ፥ እነርሱ እራሳቸው አዳዲስ አማኞችን ማስተማር ይገባቸው ነበር። ጸሐፊው በአዲስ አማኝነታቸው ጊዜ ሊማሩአቸው የሚገባቸውን ትምህርቶች ደግሞ ለማስተማር መገደዱን ያስረዳል። አይሁዳውያን አማኞች የእግዚአብሔርን መርሆች ተግባራዊ ሊያደርጉ ከሚገዟቸው መንገዶች አንዱ ከቀድሞው ሃይማኖታዊ ልምምዳቸው ጋር የነበራቸውን ግንኙነትና ክርስቶስ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበትን መንገድ እንዴት እንደ ለወጠ መረዳትን የሚጨምር ነበር። አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ወደ ይሁዲነት ለመመለስ ማሰባቸው የእግዚአብሔር ቃል አስተሳሰባቸውን በጥልቀት እንዲቀይር አለመፍቀዳቸውን ያሳያል።

ጸሐፊው የሚፈልገው የብስለት ምልክት ምንድን ነው? ብስለት የሚገለጠው አስቸጋሪ እውነትን በመረዳት ሳይሆን፥ የዕብራውያን ክርስቲያኖች እምነታቸውን በጽድቅ መንገድ በመግለጣቸው ነበር። በጽድቅ በመመላለስ በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት ጠበቅ አድርገው ሊይዙና ምንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍሉአቸውም እግዚአብሔርን በመታዘዝ ሊኖሩ ይገባቸው ነበር። እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ መኖር ማለት ደግሞ የእግዚአብሔር እውነት በሁኔታዎች ሁሉ ውስጥ አኗኗራችንን እንደሚለውጥ ማሳየትን ይጠይቃል። ጸሐፊው ይህንን ሂደት ሲገልጽ «ክፉውንና መልካሙን ለመለየት ብስለታቸው የለመደ ልቦና ላላቸው» ብሏል። መንፈሳዊ ብስለት ያለው ሰው ሕይወቱን በሙሉ (ባህሪውን፥ ቤተሰባዊ ሕይወቱን፥ ሥራውን፥ በማኅበረሰብ ውስጥ ያለውን ግንኙነት፥ ወዘተ…) መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው መሠረት ይገመግማል። ብስለት ያለው አማኝ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው፥ እንዲሁም ለራሱ ግላዊ መንፈሳዊ እድገት የሚበጀውን ያውቃል። በእነዚህ የሕይወት ክፍሎቹ ሁሉ ሌሎችን የሚያንጽ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆኖ እንዴት ሊመላለስ እንደሚችልም ያውቃል። አለዚያም የእግዚአብሔር ቃል በሚሰጣቸው መርሆች መሠረት ሕይወቱን ይመራል። ጸሐፊው ይህ ቀላል ተግባር ነው አላለም። ነገር ግን ሥልጠናና ትምህርትን ይጠይቃል፡፡

የውይይት ጥይቄ፡- ሀ) በመልካሙና በክፉ መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት ትችል ዘንድ ራስህን በጽድቅ የምታሠለጥንባቸውን መንገዶች ዘርዝር። እንደ ባህሪ፥ ቤተሰብ፥ ቤተ ክርስቲያን፥ ሥራና ማኅበረሰብ ያሉትን የሕይወትህን ክፍሎች ገምግምና በመንፈሳዊ መረዳትና ተግባር ያደግህባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) በዚህ ረገድ አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን አባሎች «በሳሎች» ተብለው ሊመደቡ የሚችሉ ይመስልሃል? ካልሆነ፥ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ያልበሰሉት ለምንድን ነው? ቤተ ክርስቲያንን እነዚህ ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ ለማገዝ ምን ልታደርግ ትችላለች?

ለ) በዕብራውያን 6፡1-3፥ ጸሐፊው የክርስቶስን የመጀመሪያ ትምህርት የእግዚአብሔርን ቃል መሠረታዊ እውነቶች ይዘረዝራል። እነዚህ የአይሁዳውያን ክርስቲያኖች የሃይማኖት መሠረቶች ሲሆኑ፥ በሕይወታቸው ከእነዚህ አልፈው ማደግ ያስፈልጋቸው ነበር። ምሁራን እነዚህ ስድስት ነገሮች ከይሁዲነት ወይም ከክርስትና ትምህርቶች በመምጣታቸው ላይ ይከራከራሉ። ምናልባት ሁለቱም ሃይማኖቶች እነዚህን ነገሮች መሠረታዊ ትምህርቶቻቸው አድርገው ሳይወስዱ አይቀሩም። እነዚህ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ምናልባትም ከአሕዛብ ክርስቲያኖች በላይ እነዚህ ነገሮች ከሁሉም በላይ አስፈላጊዎች እንደሆኑ ላያስቡ አልቀሩም። ይህም ስለ ክርስቶስ በሚናገሩ እውነቶች ሥር ሰድደው እንዳይመሠረቱ እና ለእርሱ እንዳይኖሩ አድርጓቸው ነበር።

 1. ከሞተ ሥራ ንስሐ፡- ብሉይ ኪዳን (2ኛ ዜና 6፡36-39። ኢሳ. 30፡15፥ 9፣ ኤር. 15፡9፤ ሕዝ. 18፡30) እና አዲስ ኪዳን የንስሐ አስፈላጊነትን ያስተምራሉ። መጥምቁ ዮሐንስ (ማቴ. 3፡1-2)፣ ኢየሱስ (ማቴ. 4፡17)፣ እንዲሁም ጴጥሮስ (የሐዋ. 2፡38) ሁሉም ንስሐ አስፈላጊ መሆኑን አስተምረዋል። አንድ ሰው ወደ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ በመጀመሪያ ከሚማራቸው ነገሮች አንዱ ንስሐ ነው። ሰዎች ወደ ክርስቶስ በሚመጡበት ጊዜ ኃጢአተኞችና በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ ላይ መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ከዐመፀኝነት መንገዳቸው ተመልሰው እግዚአብሔርን ለመታዘዝ መፍቀድ ይኖርባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንስሐ ሁልጊዜም የሚጀምረው ቅዱሱን አምላክ ደስ የሚያሰኝ ተግባር በመፈጸም ላይ ያለን ኃጢአኞች የመሆናችን ምክንያት በመገንዘብ ነው።

ይህም ወደ ኑዛዜ፥ ማለትም በእግዚአብሔር ላይ እያመጽን መሆናችንን ወደምንገነዘብበት ደረጃ ይመራናል። በዚህ ጊዜ ባህሪያችን ይለወጥና ተግባራችንም እንዲሁ ይለወጣል። ከዚያም እንደ ቀድሞው መመላለሳችን ያከትማል። ምናልባትም የሞተ ሥራ (ወደ ሞት የሚመራ) የሚያመለክተው አይሁዶች በሰናይ ምግባራት የእግዚአብሔርን ይቅርታ ማግኘት መሞከራቸውንና የኋላ ኋላ ግን መንፈሳዊ ሙታን መሆናቸውን ይሆናል። ነገር ግን ይህ አሳብ ከተገለጸው የእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ፊት ለፊት መላተምን ሊያመለክት ይችላል። እነዚህም ነገሮች መንፈሳዊ ሙታኖች መሆናችንን ያሳያሉ።

 1. በእግዚአብሔር ማመን፡- ጸሐፊው በክርስቶስ ማመን የሚለውን ሐረግ አለመጠቀሙ ብዙ ሰዎች እነዚህ ትምህርቶች የብሉይ ኪዳን እንጂ የአዲስ ኪዳን ይዘት የላቸውም ብለው እንዲደመድሙ አድርጓቸዋል። ነገር ግን የዕብራውያን መልእክት ጻሐፊ በእግዚአብሔር ስለማመንና በክርስቶስ ስለማመን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚያብራራ መገንዘቡ ጠቃሚ ነው (ዕብ 11)። እምነት የእግዚአብሔርን መኖር ወይም የክርስቶስን በመስቀል ላይ መሞት የምንገነዘብበት አእምሮአዊ እውቀት ብቻ አይደለም። ነገር ግን እውነተኛ እምነት እውነትን ማወቅንና ይህንኑ እውነት በሚያንጸባርቅ መልኩ መኖርን ያመለክታል። የሰውን ሕይወት የሚለውጠው እውነት ነው። የማይቻል፥ የማይመችና ስደትን የሚጋብዝ በሚሆንበት ጊዜ ሳይቀር ሰው ለእውነት ይኖራል።
 2. የጥምቀት ትምህርት፡- ጥምቀት የአይሁዶችም ሆነ የክርስቲያኖች እምነት መሠረታዊ ክፍል ነው። አይሁዶች በየቀኑ ልዩ በዐላት ባሉባቸው ጊዜያት ሁሉ ሥርዐታዊ በውኃ የመታጠብ ተግባር ያከናውናሉ። (ጥምቀት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ በነጠላ ሳይሆን በብዙ ቁጥር እንደ ተገለጠ መመልከቱ ጠቃሚ ነው።)

መጥምቁ ዮሐንስ ጥምቀትን የሰው ሕይወት ከኃጢአት መንጻቱንና ንስሐ መግባቱን የሚያመለክት ውጫዊ ተግባር አድርጎ ተጠቅሞአል። ክርስቲያኖችም ስለ ጥምቀት የመጥምቁ ዮሐንስን የመሰለ አስተሳሰብ ነበራቸው። ይህም አንድ ሰው በኢየሱስ በሚያምንበት ጊዜ ኃጢአቶቹ ሁሉ መታጠብን የሚያመለክት በአንድ ጊዜ የሚፈጸም ተምሳሌታዊ ድርጊት መሆኑን ነው (ቲቶ 3፡5)።

 1. እጆችን መጫን፡ አይሁዶችና ክርስቲያኖች ይህንን ልምምድ ያካሂዱ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ይህ ጥምቀትን ተከትሎ የሚከናወን ሲሆን፥ በመንፈስ ቅዱስ መሞላትና ወይም መንፈሳዊ ስጦታ መቀበልን ያስከትል ነበር (የሐዋ. 8፡14-17፤ 19፡4-7)። (ማስታወሻ፡ ምንም እንኳ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ሐዋርያት እጆቻቸውን በሰዎች ላይ በመጫን እንዴት መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉና የጸጋ ስጦታዎችን እንዲያገኙ እንዳደረጉ በብዙ ስፍራዎች ላይ ቢጠቅስም፥ እግዚአብሔር ለሰዎች ስጦታዎችን የሚሰጥበት ተለምዶአዊው መንገድ ይኸው እንደሆነ አያብራራም። በሰዎች ላይ እጅ ሳይጫን መንፈስ ቅዱስ የወረደባቸው ብዙ ጊዜያት አሉ። ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ወይም መንፈሳዊ ስጦታዎችን እንዲቀበሉ እጆቻችንን እንድንጭንባቸውም አልተነገረንም ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው በክርስቶስ በሚያምንበት ጊዜ እግዚአብሔር በቀጥታ ያለምንም የእጅ መጫን መንፈስ ቅዱስንና መንፈሳዊ ስጦታዎችን ያጎናጽፈዋል።)

በሌሎች ጊዜያት፥ ሰዎች ለመሪነት አገልግሎት ወይም ለሌሎች የቤተ ክርስቲያን ተግባራት በሚለዩበት ጊዜ እጅ ተጭኖ ይጸለይላቸዋል (የሐዋ. 6፡6፤ 1ኛ ጢሞ. 5፡22፤ 2ኛ ጢሞ. 1፡6)። ለታመሙት ሰዎችም አገልጋዮች እጃቸውን ጭነው ይጻልዩላቸው ነበር (ማር. 6፡5፤ የሐዋ. 28፡8)። በረከትን ለማውረድም እንዲሁ እጆችን የመጫን ተግባር ይከናወናል (ማቴ. 19፡13-15)። በይሁዲነትም ሆነ በክርስትና ይህ ተግባር የተለያዩ ዓላማዎች የነበሩት ቢሆንም፥ እጅን መጫን የመጀመሪያ እውነት በመሆኑ አማኞች ከዚያ እልፍ ብለው መሄድ ይኖርባቸው ነበር።

 1. የሙታን ትንሣኤ፡- አብዛኞቹ አይሁዶችና ሁሉም ክርስቲያኖች ከሞት እንደሚነሡ በመሠረታዊነት ያምኑ ነበር። ይህ በተለይም የትንሣኤ ሙታንን መኖርና አማኞችም በሚሞቱበት ጊዜ ከሞት እንደሚነሡ በማመልከት የክርስቶስን ከሞት መነሣት በመረጃነት በሚጠቅሰው ክርስትና ማዕከላዊ ትምህርት ነው። ጳውሎስ ትንሣኤ፥ በተለይም የኢየሱስ ትንሳኤ ከሌለ፥ እምነታችን ከንቱ ነው ብሏል (1ኛ ቆሮ. 15፡12-14)።
 2. ዘላለማዊ ፍርድ፡- አይሁዶችም ሆኑ ክስቲያኖች ከሞት በኋላ እግዚአብሔር በሙታንና በሕያዋን ላይ ፍርዱን በመስጠት በምድር ላይ ባከናወናቸው ተግባራት ሳቢያ ቅጣቶችንና ሽልማቶችን የሚሰጥበት ቀን እንደሚመጣ ያምናሉ።

ጸሐፊው እነዚህ እውነቶች አስፈላጊዎች አይደሉም አላለም። እነዚህ ስድስት ነገሮች አስፈላጊዎች ናቸው። ይሁንና አይሁዳውያን አማኞች ከእነዚህ መሠረታዊ እውነቶች (ወተት) ፈቀቅ ብለው ወደ ጠለቁ እውነቶች ሊያድጉና በሳል አማኞች ሊሆኑ ይገባ ነበር። ወደ አንደኛ ክፍል ገብቶ ፊደል መቁጠር ትምህርትን ለመጀመር አስፈላጊ ቢሆንም፥ እዚያው አንደኛ ክፍል ውስጥ «ሀ ሁ»ን ብቻ እየተማሩ መኖሩ ሞኝነትና አሰልቺም ነው። እንደዚሁም ደግሞ ወደ ጠለቁት እውቀቶች ሳይደርሱ ሁልጊዜም አንድ ዓይነት እውነቶችን መደጋገሙ ለክርስቲያኖች ሞኝነት ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ አብዛኛዎች አማኞች ዘመናቸውን የሚጨርሱት የክርስትናን ሀ፥ሁ፥ በመማር ነው። ይህም ወደ ጠለቁ ትምህርቶች ሳይደርሱ እንደ ድነት (ደኅንነት)፥ ክርስቲያን አኗኗር፥ ወዘተ… ባሉት ነገሮች ላይ ማተኮር ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚታየው ትልቁ ችግር እሑድ እሑድ ተከታታይነት ያለው ትምህርት ስለማይሰጥ እና ባመዛኙ ተጋባዥ ሰባኪዎች እንዲያገለግሉ ስለሚያደርጉ፥ ሁልጊዜም የሚሰጠው መሠረታዊ ትምህርት ይሆናል። ይህም አማኞች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ጠለቅ ብለው እንዲያድጉ አያደርጋቸውም። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደ ዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ በእነዚህ መሠረታዊ እውነቶች ላይ ሌሎች ጠንካራ ትምህርቶችን እየገነቡ ምእመኖቻቸውን ወደ ጠለቁ እውነቶች ሊወስዷቸው ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አማኞች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉና የጠለቁ እውነቶች ከሕይወታቸው ጋር እንዲያዛምዱ ከማገዝ ይልቅ ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመሠረታዊ ትምህርቶች ላይ የምናተኩርባቸውን ሁኔታዎች የሚያሳዩ ምሳሌዎች ስጥ። ለ) ላለፉት 6 ወራት የሰማሃቸውን ስብከቶች አስታውስ፤ ከእነዚህ ስብከቶች መካከል መሠረታዊ የሆኑትና ለበሳል ክርስቲያኖች የተዘጋጁ ጥልቅ እውነቶች የትኞቹ ናቸው? ሐ) የጠለቁ እውነቶች የማይሰበኩ ከሆነ፥ ቤተ ክርስቲያን በሳል አማኞች ወደ ጠለቀ እውነት እንዲዘልቁ ልታደርግ የምትችልበት ሌላ ምን አማራጭ ይኖራታል?

ሐ) ዕብራውያን 6፡4-6 ከእውነት ተመልሰው ወደ ይሁዲነትም ወይም ወደ ቀድሞው አኗኗራቸው የሚመለሱ አማኞች ጠንካራ ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጣል። ይህ ክፍል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመተርጎም እጅግ አስቸጋሪ ከሆኑት ምንባቦች አንዱ ነው። ቃላቱ ራሳቸው ለመረዳት የሚያስቸግሩ አይደሉም። ነገር ግን ይህ ምንባብ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር የሚቃረን አሳብ የሚያስተላልፍ ስለሚመስል፥ ከተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ ጋር ማስታረቁ አስቸጋሪ ይሆናል። በዚህ ምንባብ ላይ የተለያዩ ምሁራን የሚያቀርቡአቸውን አመለካከቶች ለመረዳት እንዲያግዘን በመጀመሪያ አንድ ሰው እምነቱን በመካድ ደኅንነቱን ሊያጣ ስለሚችልበት ሁኔታ ምሁራን የሚያቀርቡአቸውን ሦስት ዓይነት አመለካከቶች መረዳት ጠቃሚ ይሆናል።

 1. እውነተኛ ድነት (ደኅንነት) ያገኘ ሰው ደኅንነቱን ሊያጣ እንደማይችል የሚያስተምሩ ምሁራን። በዮሐንስ 10፡27-30 ኢየሱስ ከአብ የተቀበላቸውን አማኞች ሁሉ እንደሚጠብቅ የተስፋ ቃል ሰጥቷል። ከእነዚህም አንዱ እንኳን አይጠፋም። ማንም ከኢየሱስ እጆች ሊነጥቃቸውና ሊያጠፋቸው አይችልም፡፡ በዚህና በሌሎችም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ በመመሥረት (ሮሜ 8፡28-39)፣ ብዙ ክርስቲያኖች አንድ ሰው ከዳነ በኋላ ምንጊዜም ደኅንነቱን ሊያጣ አይችልም ብለው ያስተምራሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር ቃላዊ እምነትን ሳይሆን የልብን እምነት እንደሚያይ እነዚህ አማኞች አጽንኦት ሰጥተው ያስተምራሉ። ስለሆነም የአንድን ሰው ልብ ማወቅ ስለማይቻል፥ የአንድን ሰው መዳን ወይም አለመዳን ማወቅ አይቻልም። አንድ ሰው መዳን አለመዳኑን ማወቅ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ በሕይወቱ ውስጥ ለውጦች (ፍሬዎች) መኖር አለመኖራቸውን መመልከትና በእምነቱ እስከ መጨረሻው ድረስ መጽናቱን ማረጋገጥ ነው። የዚህ አመለካከት አራማጆች አንድ ሰው እምነቱን ከካደ ቀድሞውንም አልዳነም ነበር ይላሉ። ይህን አቋም የሚይዙ ክርስቲያኖች አማኞች ወደ ኋላ እንዳይመለሱና እምነታቸውን እንዳይክዱ የሚያስጠነቅቁትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ለመረዳት ይቸገራሉ። የዚህ አመለካከት አራማጆች በዕብራውያን 6፡4-6 ሦስት አተረጓጎሞችን ያቀርባሉ።

ሀ) ይህ ምንባብ ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱትንና እውነተኞቹ አማኞች የሚያገኟቸውን ብዙ በረከቶች የሚካፈሉትን ሰዎች ያመለክታል። እነዚህ ሰዎች ግን በልባቸው በክርስቶስ ስላላመኑ ክርስቲያኖች አልነበሩም። ይህን አመለካከት የሚያራምዱት ሰዎች አይሁዳውያን ክርስቲያኖች አማኞች መሆናቸውን የሚያመለክቱትን ዕረፍተ ነገሮች ለማብራራት ይቸገራሉ።

ለ) ጸሐፊው ያቀረበው ሊሆን የማይችል መላምታዊ ሁኔታ ነው። ይህንን ያደረገው አይሁዳውያን አማኞች እምነታቸውን እንዳይክዱ ለማስፈራራት ነው። ነገር ግን በዕብራውያን 6፡9 እንደተመለከተው፥ ጸሐፊው እነዚህ አማኞች እውነተኛ አማኞችና ደኅንነታቸውንም ሊያጡ የማይችሉ መሆናቸውን ገልጾአል። ይህ የማስጠንቀቂያ ክፍል መሆኑና መላምታዊ አሳቦችን ለማቅረብ የማይመች ክፍል መሆኑ፥ ይህን አቋም ውድቅ ያደርገዋል።

ሐ) ሌሎች ደግሞ ድነት (ደኅንነት) ከተለያዩ የእይታ መነጽሮች አንጻር ሊታይ ይችላል ይላሉ። ከእግዚአብሔር የእይታ መነጽር ሲታይ፥ እርሱ የእያንዳንዱን ሰው ልብ ስለሚያይና የእምነቱን እውነተኛነት ስለሚያውቅ የዳነ ሰው ደኅንነቱን ሊያጣ አይችልም ይላሉ። ከሰው የእይታ መነጽር ሲታይ ግን የሰውን ልብ ማየት ስለማንችል እምነቱ እውነተኛ ወይም የውሸት መሆኑን ልናረጋግጥ አንችልም ብለው ያስተምራሉ። እምነቱ የአዕምሮ እውቀት ብቻ የሆነበት ሰው በቀላሉ ከእምነቱ ፈቀቅ ሊል ይችላል። የራሳችንንም ሆነ የሌሎችን ሰዎችን ልብ ለማየት ስለማንችል፥ የሰዎችን ድነት (ደኅንነት) በእርግጠኝነት ለመናገር አንችልም። በመሆኑም የዕብራውያን ጸሐፊ ሕይወታችንን አጥብቀን እንድንጠብቅ ያስጠነቅቀናል። እውነተኛ እምነት እንዳለን ወይም እንደሌለን ከምናውቅባቸው ነገሮች አንዱ እስክንሞት ድረስ በእምነት መጽናታችን ነው። እምነታችንን ከካድን፥ እውነተኛ እምነት እንዳልነበረን ይታወቃል። በዕብራውያን 6፡4-6 የተጠቀሱት አምስት በረከቶች በክርስቶስ ላይ እውነተኛ እምነት ወይም የአእምሮ እውቀት ብቻ ካላቸው ሰዎች ሕይወት ውስጥ ሊገለጽ ይችላሉ። ጸሐፊው አይሁዳውያኑ እማኞች በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት አጥብቀው እንዲይዙ፥ ካልሆነም ቀድሞውንም እውነተኛ አማኞች እንዳልሆኑና የእግዚአብሔር ፍርድ እንደሚደርስባቸው እያስጠነቀቁ ነው ሲሉ ያስተምራሉ።

 1. ሌሎች ክርስቲያኖች አንድ ሰው ትልቅ ኃጢአት ከሠራና በተለይም እምነቱን ከካደ ደኅንነቱን ሊያጣ እንደሚችል ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች ከእምነታቸው የወደቁትን ግለሰቦች እንደሚያውቁም ይጠቅሳሉ። እንደ ዕብራውያን 6፡4-6 ያሉትን ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በመጥቀስ፥ እንድ አማኝ እምነቱን ሊያጣ (ሊተው) እንደሚችል ያስተምራሉ። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከፍርሃት የተነሣ እምነታቸውን የሚክዱ አማኞች እንዳሉ ለመግለጽ የሚያስተምሩ መሆናቸውን ይናገራሉ። አንድ ሰው ደኅንነቱን ሊያጣ እንደሚችል እና ንስሐ ገብቶ እንደገና ሊያምን እንደሚችል ያስተምራሉ። እነዚህ ሰዎች አንድ አማኝ እምነቱን ከካደ በኋላ በንስሐ ሊመለስ እንደማይችል የሚያመለክተውን የዕብራውያን 6፡6 አሳብ ለማብራራት ይቸገራሉ። እንዲሁም፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አንድ ሰው በክርስቶስ አምኖ ከካደ በኋላ የዘላለም ሕይወት እንዳለውና ከዘላለማዊ ፍርድ እንደዳነ የሚያመለክቱትን ምንባቦች ለመረዳት ይቸገራሉ (ዮሐ. 6፡39-40፤ 10፡27-29፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡5)።
 2. ሌሎች አማኞች ከመጀመሪያው ቡድን ጋር የሚመሳሰል አቋም ይይዛሉ። እነዚህ ሰዎች አንድ ሰው በክርስቶስ ላይ እውነተኛ እምነት ካለው ደኅንነቱን ሊያጣና ወደ ሲኦል ሊወርድ እንደማይችል ያስተምራሉ። የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆኑ እግዚአብሔር ልጆቹን ሊክድ አይችልም። ነገር ግን እነዚህ ክርስቲያኖች አንድ አማኝ በእግዚአብሔር ላይ ሊያምጽ እንደሚችል ያስተምራሉ። ይህንንም በሚያደርግበት ጊዜ ድነትን (ደኅንነትን) ሳይሆን፥ ዘላለማዊውን የክብርና የበረከት ሽልማት ያጣል። በትልቅ ኃጢአት ውስጥ ወድቆ ንስሐ ያልገባ አማኝ ወይም ደግሞ ክርስቶስን የሚክድ ክርስቲያን ወደ መንግሥተ ሰማይ ይገባል። ነገር ግን በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ የመግዛት ሥልጣን አይኖረውም። ከእሣት እንደሚድን ግን ይድናል (1ኛ ቆሮ. 3፡12-15)። ይህ አመለካከት ይህ ምንባብ ጸሐፊው እውነተኛ ክርስቲያኖችን እየገለጸ መሆኑን ይገልጻል። ነገር ግን ጸሐፊው አጥብቆ የሚያስጠነቅቃቸው ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ከተመለሱ ሰማያዊውን በረከት (ሽልማት) እንደሚያጡ ነው። እነዚህ አማኞች ክርስቲያኖች የሚያጡት ሽልማትን ሳይሆን ድነትን (ደኅንነትን) እንደሆነ የሚያመለክቱትን ጥቅሶች ለማብራራት ይቸገራሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ዕብ. 6፡4-6 እንደገና አንብብ። እነዚህንና ሌሎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ጥቅሶች ለማብራራት ከሁሉም የበለጠ ትክክለኛው አቋም የትኛው ይመስልሃል? ለምን?

ከእነዚህ አመለካከቶች እውነተኛው የቱ ነው? የዚህ የጥናት መምሪያ ጸሐፊ እንደሚያምነው ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔር መንገዶች ከእኛ ግንዛቤ በላይ ናቸው። መንግሥተ ሰማይ ደርሰን ከእግዚአብሔር የዕይታ መነጽር አንጻር እስክንረዳቸው ድረስ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ የሚመስሉትን ምንባቦች (አንዳንዶቹ ሰው ደኅንነቱን ሊያጣ አይችልም ሲሉ፥ ሌሎቹ ያጣል ይላሉ) ወደ ሰማይ ሄደን እስክንረዳቸው ድረስ ሙሉ ለሙሉ ልናስታርቃቸው አንችልም። እነዚህ በዕብራውያን 6፡4-6 የተጠቀሱት ባሕርያት ክርስቲያኖች እንደሚያመለክቱ የሚያሳዩ ብዙ ደረጃዎች አሉ። ጸሐፊው እነዚህኑ በክርስቶስ ላይ የነበራቸውን አምነት ክደው ወደ ይሁዲነት ለመመለስ የሚያስቡትን አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በማስጠንቀቅ ላይ መሆኑ ግልጽ ነው። ጸሐፊው እርምጃቸው ከእግዚአብሔር ቤተሰብነት ውጭ ከማድረጉም በላይ፥ የዚህ ዓይነቱ ውሳኔ ወደ ክርስቶስ ተመልሰው ደግሞ ይቅርታ የሚያገኙበት መንገድ እንደሚዘጋባቸውም ያብራራል።

ክርስቶስን ለመካድ ለሚያስቡ ሰዎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ፡- የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ለክርስቶስ ጀርባቸውን መስጠት ለሚፈልጉ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተሰጡት ጠንካራ ከሚባሉ ማስጠንቀቂያዎች አንዱን ሲሰነዘር እንመለከታለን። እነዚህን አምስት በረከቶች ተጠቃሚ የሆኑ (ዕብ. 6፡4-6) ከዚያ በኋላ ጀርባቸውን ለክርስቶስ የሰጡ ሰዎች፥ ደግሞ በንስሐ ሊታደሱ እንደማይችሉ ያስረዳል። መጽሐፍ ቅዱስን በምልአቱ በምንመለከትበት ጊዜ ይህንን ጠንካራ ማስጠንቀቂያ እንድናውቅ የሚያግዙንን እውነቶች እናገኛለን። ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል።

አንደኛ፥ አንድ ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ምንም ዓይነት በደል ቢፈጽምም እንኳን እግዚአብሔር ሁልጊዜም ወደ ድነት (ደኅንነት) ሲጋብዘው ይኖራል። ቀደም ሲል የዕብራውያን ጸሐፊ እንደገለጸው፥ «ዛሬ» ሁልጊዜም ሰዎች በክርስቶስ አምነው ወደ እግዚአብሔር የድነት (ደኅንነት) እረፍት ይገቡ ዘንድ ክፍት ነው (ዕብ. 4፡7)።

ሁለተኛ፥ አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ፈልጎ፥ እግዚአብሔር ግን፥ «አዝናለሁ፥ ይቅር ልልህ አልችልም፥ የሠራኸው ኃጢአት በጣም ትልቅ ነው። ቀደም ሲል ክደኸኛል፥ ስለሆነም ሁለተኛ ዕድል ልሰጥህ አልችልም» ያለበትን ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንመለከትም። ማንም ሰው ንስሐ ገብቶ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሰ፥ እግዚአብሔር ይቀበለዋል። ክርስቶስን የካደው ጴጥሮስ እንኳን እንደገና በንስሐ ተመልሷል።

ሦስተኛ፣ በእግዚአብሔር ሥራ ላይ ልባቸውን ያጠነከሩ እንደ ፈርኦን ያሉ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰዋል። እነዚህ ሰዎች ልባቸውን ስላደነደኑ እግዚአብሔር ልባቸው ሁልጊዜም ይደነድን ዘንድ ፍርዱን ሰጥቷቸዋል። ከዚህም የተነሣ፥ በእግዚአብሔር ለማመን አልቻሉም። እነዚህ ሰዎች በእግዚአብሔር ለማመን ፈልገው እግዚአብሔር አልቀበላችሁም አላለም። ነገር ግን እግዚአብሔር እርሱን ለመከተል አለመፈለጋቸውን በማክበር ልባቸውን ወደ እርሱ ለመመለስ እስከማያስቡበት ድረስ አደንድኖታል።

ከእነዚህ እውነቶች ስንነሣ ይህ ምንባብ የሚያስጠነቅቀው። ሀ) እግዚአብሔር በሕይወታቸው ውስጥ የፈጸማቸውን በረከቶች ሁሉ በመተው ክርስቶስን ለመከተል ያልፈለጉትን፥ ወይም ለ) እውነትን እያወቁ ለክርስቶስ ሕይወታቸውን ለማስገዛት የማይፈልጉትን ሰዎች ይመስላል። እነዚህ ሰዎች ምናልባትም እንደገና ንስሐ ገብተው በክርስቶስ ሊያምኑ በማይችሉበት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ሳይሆኑ አይቀርም።

ንስሐ ሊገቡ የማይችሉበት ምክንያት፥ የዕብራውያን ጸሐፊ ንስሐ የላቸውም ያለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች እውነትን እያወቁ ለክርስቶስ ለመታዘዝ አልፈለጉም። ጀርባቸውን ለክርስቶስ ሰጥተው ነበር። እነዚህ ሰዎች ልክ ከፈሪሳውያንና ከሌሎችም ክርስቶስን ከሰቀሉ ሰዎች ጎን ቆመው «ስቀለው ስቀለው!» እያሉ ይጮኹ እንደነበረ ያህል ነበር። በአንድ ወቅት ክርስቲያን ተብለው ይጠሩ ስለነበረ የክርስቶስን ስም አሰድባዋል። ክርስቶስ ከሙታን የተነሣ አምላክ እንደሆነ እያወቁ በሥራቸው ግድ የለኝም የሚል አኗኗር ተከትለዋል። ክርስቶስ ዳግም ላይነሣ እንደገና ቢሞትም ግድ የለኝም የሚል ዓይነት አመለካከት ነበራቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ዕብ 6፡4-6 አንብብ። የዕብራውያን ጸሐፊ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ከተቀበሏቸውና እሁን ባለማመናቸው ምክንያት የሚያጧቸው በረከቶች ምን ምንድን ናቸው ይላል? እነዚህ አምስት በረከቶች ዛሬም በእኛ ሕይወት ውስጥም የሚሠሩት እንዴት ነው?

ማስጠንቀቂያው የተሰጠው ለማን ነበር? ይህ ክፍል ስለ ክርስቶስ ሰምተው ለማያውቁ ወይም እርሱን ለመከተል ቃል ገብተው ለማያውቁ ሰዎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ አይደለም። ይህ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ለአማኞች ማኅበረሰብ አባል ብቻ ሳይሆን፥ በክርስቶስ አምነናል ብለው የእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ደስ የሚሰኙባቸውን በረከቶች ለተቀበሉት ሰዎች ነው፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ አምስት በረከቶች ክርስቲያኖች ነን የሚሉትን (እንደ የክርስቲያኖች ልጆች) ሊያመለክቱ ቢችሉም፥ እነዚህ በረከቶች ክርስቲያኖች የሚያገኟቸውን ነገሮች በትክክል የሚያሳዩ ይመስላል።

ሀ) አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ብርሃን በርቶላቸው ነበር። የመረዳት ዓይናቸው ተከፍቶ ስለ ክርስቶስና የእግዚአብሔር የማዳን መንገድ ለመረዳት ችለው ነበር።

ለ) ሰማያዊውን ስጦታ ቀምሰዋል። ጸሐፊው ይህን ሲል ምን ለማለት እንደ ፈለገ በግል ለመረዳት ያስቸግራል። ምናልባትም ድነትን (የዘላለም ሕይወትን) ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር እንደሚመጡ የሚናገራቸውን ሌሎች በረከቶች ማመልከቱ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ምሁራን የዕብራውያን ጸሐፊ የቀመሱ ሲል እነዚህ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስን ስጦታና እግዚአብሔር ሊሰጣቸው ቃል የገባውን መንፈስ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ እንዳልበሉ ወይም እንዳላገኙ መናገሩ ነው ይላሉ። ይህም ስጦታ ከወላጆቻቸው ወይም ከሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባላት ሕይወት ውስጥ በመመልከት ብቻ ሊለማመዱ እንደቻሉ ያስረዳሉ። ነገር ግን ለሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መቅመስ የሚያመለክተው የእግዚአብሔርን በረከት ሙሉ በሙሉ ማግኘት ነው (ለምሳሌ፥ መዝሙር 34፡8)።

ሐ) አይሁዳውያን አማኞች የመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች ነበሩ። እነዚህ አማኞች እንደ ሌሎች አማኞች ሁሉ ባመኑ ጊዜ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ተቀብለው ነበር።

መ) መልካሙን የእግዚአብሔር ቃል ቀምሰው ነበር። የእግዚአብሔርን ቃል በማጥናትና ስብከቶችን በማዳመጥ መልካምነቱን ተረድተው ነበር። ዳዊት እንዳለው የእግዚአብሔር ቃል ከወርቅ ወይም ከማር የበለጠ ነው (መዝ. 19፡10)።

ሠ) ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል ቀምሰው ነበር። ይህ መጪው ዘመን ክርስቶስ የሚመለስበትንና በመንግሥተ ሰማይ የሚመሠረተውን ዘላለማዊ መንግሥት ያመለክታል። ጸሐፊው ይህን ሲል መንፈስ ቅዱስ በመካከላቸው ከፈጸመው ተአምር የተነሣ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ኃይል እንደ ተመለከቱ መግለጹ ነበር። ይህም የእግዚአብሔር ኃይል በሰማይ በበለጠ ይገለጣል።

ሰዎች እማኞች ነን እያሉ ይህንኑ በእምነታቸው ጸንተው በተግባር በሚያሳዩበት ጊዜ ምን እንደሚከሰት ለማሳየት፥ ጸሐፊው ስለ እርሻ ቦታ ይናገራል። ገበሬው መልካም ፍሬ በመሻት ጥሩ ዘር ሲዘራ ቆየ። ነገር ግን በመልካም እርሻ ፈንታ ሁልጊዜም እሾህ የሚበቅል ከሆነ፥ እሾሁን ለማቃጠል ሲባል በመሬቷ ላይ እሳት ይለቀቃል፡፡ ይህም እሳት በመሬቱ ላይ ያለውን አነስተኛ እህል ያጠፋዋል። በሚቀጥለው ዓመት እሾህ የሌለበት መልካም ሰብል ማግኘት የሚቻለው በዚሁ መንገድ ነውና። እንደዚሁም እግዚአብሔር እማኞች ነን እያሉ በጽናት ወይም በመልካም ሥራ እምነታቸውን በተግባር በማያሳዩት ሰዎች ላይ ፍርዱን ይገልጣል።

ምንም እንኳን የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች እምነታቸውን ይክዳሉ ብሎ ቢሰጋም፥ ሙሉ በሙሉ ተስፋ አልቆረጠም። እነዚህ ሰዎች በታሪካቸው እግዚአብሔርን በማገልገልና ከፍቅር የተነሣ ሌሎችን ሰዎች በመርዳት የእምነታቸውን እውነተኛነት ገልጸዋል። ይህም አማኞቹ እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውንና እግዚአብሔርም በእምነታቸው እንዲጸኑ እንደሚረዳቸው የሚያሳይ ማረጋገጫ ነበር። ይሁንና እግዚአብሔር መንፈሳዊ ሕይወታችንን ጠንካራና የተሟሟቀ በማድረግ (በጸሎት፥ በጾም፥ የእግዚአብሔርን ቃል በማንበብና ለሌሎች በመመስከር) ከእርሱ ጋር እንድንተባበር ይፈልጋል። ይህም ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ግድየለሾች ከመሆን የተሻለ አማራጭ ነው።

ረ. አብርሃም የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ስለ ማመንና ለእርሱ በታማኝነት ስለ መጽናት መልካም ምሳሌአችን ነው (ዕብ. 6፡13-20)። እግዚአብሔር በታማኝነት ለሚጸና አማኝ ሁሉ የዘላለም ሕይወትና የዘላለማዊ በረከትን የተስፋ ቃል ሰጥቶአል። ለዚህ የተስፋ ቃል የእኛ ምላሽ ምን መሆን አለበት? የተስፋው ቃል እስኪፈጸም ድረስ ምንም ያህል ቢቆይ ተስፋውን በማመን በታማኝነት መጽናት ይኖርብናል። ምናልባትም አይሁዳውያን ክርስቲያኖች «ክርስቶስ ዳግም እንደሚመለስና መንግሥቱን እንደሚመሠርት ተናግሮ ነበር። ይሄ እስካሁን አልሆነም፡፡ ምናልባት ተሳስቶ ይሆናል፡፡ አልያም እርሱ መሢህ አልነበረም ማለት ነው» ብለው ሳያስቡ እልቀሩም። ጸሐፊው ከብሉይ ኪዳን የአብርሃምን ምሳሌነት በመጠቀም የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች የሚፈጸሙ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ይህም የተስፋ ቃሎቹ እኛ እንደፈለግነው በፍጥነት ባይመጡም እንኳን መፈጸማቸው የማይቀር መሆኑን ያመለክታል።

እግዚአብሔር አብርሃምን በጠራው ጊዜ (ዘፍጥ. 12፡1-3፤ 22፡15-18)፥ አብርሃምን እንደሚባርከውና ብዙ ልጆች እንደሚሰጠው የተስፋ ቃል ገባለት። አብርሃም እግዚአብሔርን አመነ። ነገር ግን እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን በመፈጸም ይስሐቅን የሰጠው ከ25 ዓመታት በኋላ ነበር። እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሮቹ የሰጣቸው ሌሎች የተስፋ ቃሎች (ለምሳሌ የከነዓን ምድር) ከመፈጸማቸው በፊት 400 ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህም አብርሃም ከሞተ ከብዙ ዓመታት በኋላ የተፈጸመ መሆኑን እንረዳለን።

እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት ተስፋ ሰጥቶናል። ሊዋሽ የማይችለው አምላክ ተስፋ የገባልንን ነገር ሁሉ ይፈጽምልናል። ነገር ግን እግዚአብሔር የገባልንን የተስፋ ቃል እስኪፈጽምልን ድረስ ተግተን ልንጠብቀው ይገባል። የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ በረከት ያመጣልናል። በክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት መተው ማለት እግዚአብሔር ተስፋ የገባልንን ነገር ሁሉ ማጣት ማለት ነው። ስደት በሚበዛበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ለእኛ ግድ የሌለውና የተስፋ ቃሎቹም የማይፈጸሙ ሊመስል ይችላል። ይሁንና የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል በትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርብናል። ማዕበል በሚነሣበት ጊዜ መልሕቅ መርከብን ከመስመጥ እንደሚታደግ እንዲሁም ጥልቀት ያላቸው ሥሮች ዛፋቹን በኃይለኛ ነፋስ ተገፍተው እንዳይወድቁ እንደሚይዙ ሁሉ፥ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ሁሉ ያለን ጽኑ ተስፋ ወይም ልበ ሙሉነት በስደትና መከራ ጊዜ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ዋስትና ይሰጠናል፡፡ የእምነታችን መልሕቅ ክርስቶስ ነው። ክርስቶስ ሊቀ ካህናችንን እንደ መሆኑ መጠን፥ ወደ ሰማይ ገብቶ ለእኛ በመማለድ ላይ ይገኛል።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ስለ መንግሥተ ሰማይ የሰጣቸውን የተስፋ ቃሎች ዘርዝር። ተስፍ ሳይቆርጡ እነዚህን የተስፋ ቃሉች መጠባበቅ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች በግልጽ መረዳቱ በችግር ጊዜ ጸንተን እንድንቆም የሚያግዘን እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)