የሕይወት እንጀራ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

ወንጌል የአብ ዘላለማዊ ዕቅድ ክፍል ነው (1ኛ ቆሮ. 2፡6-9)

ደኅንነት የተገዛው በልጁ ሲሆን የታቀደው ግን በአብ ነው። ስለ «ቀላል ወንጌል» የሚናገሩ ሰዎች ትክክልም ስሕተትም ናቸው። አዎን፥ የወንጌል መልእክት ያልተማረ ሃይማኖት የለሽ ሰው እውቆት፥ አምኖ እስከሚድን ቀላል ነው። ነገር ግን በጣም የመጠቀ የሥነ መለኮት አዋቂ እንኳ እስከማይዘልቅበት ድረስ በጣም የጠለቀ ነው።  በጣም የረቀቀውን አእምሮ እንኳ የሚቋቋም «የእግዚአብሔር ጥበብ» በወንጌል ውስጥ ይገኛል። ይሁንና፥ ይህ ጥበብ ለጠፉ ብዙኃን ኃጢአተኞች ወይም ላልበሰሉ አማኞች አይደለም። በእግዚአብሔር ቃል እውቀታቸው እያደጉ ላሉ በሳል አማኞች ነው። (በቁጥር 6 «ሰበሰሉት» የሚለውን ከ 3፡1–4 ጋር አነጻጸር።) ምናልባት ጳውሎስ እዚህ ላይ ምላሽ የሚሰጠው ማራኪ ንግግርና በጥልቀት የማስተማር ክህሎት የነበረውን አጵሎስን (የሐዋ. 18፡24-28) ለሚደግፉ የቤተክርስቲያን ሰዎች ሳይሆን አይቀርም።  እስኪ የዚህን ጥበብ ባሕርያት እንወቅ።  ይህ ጥበብ የሚመጣው ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው (2፡7)። ይህ ጥበብ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለፍጥረቱ ስላለው ሰፊ ዘላለማዊ ዕቅድ ለበሳሉ ቅዱስ ሰው ይናገራል። «ከዚች ዓለም (የዘመኑ) ገዢዎች የላቁ ጠበብት የተባሉትም ይህን ጳ ውሎስ ከእግዚአብሔር የተካፈለውን አስደናቂ ጥበብ ሊፈላሰፉት ወይም ሊደርሱበት አልቻሉም።  ይህ ጥበብ የተሰወረ ነበር (2፡7)። ስለዚህ ነው ምሥጢር የተባለው። በአዲስ ኪዳን ምሥጢር ማለት «የተቀደሰ ሕቡዕ ነገር» ማለት ነው። ይህ ባለፉት ዘመናት የተደበቀና አሁን በእግዚአብሔር ሕዝብ የተገለጠ እውነት ነው። ከወንጌል ጋር የሚዛመዱትን ልዩ ልዩ ምሥጢራት ለማካፈል እግዚአብሔር በልዩ መንገድ የተጠቀመው ጳውሎስን ነበር (ኤፌ. 3 ተመልከት)፤ ነገር ግን «እኛ» የሚለውን የተውላጠ ስም ድግግሞሽ አስተውል። ጳውሎስ ሌሎችን ሐዋርያት ከዚህ ሁኔታ አላገለላቸውም።  ይህ ጥበብ የእግዚአብሔርን ቅድሚያ ውሳኔ ያካትታል (2፡7)። ይህ ማለት እግዚአብሔር ዕቅዱን ሠራው፤ በእንቅስቃሴ ላይ አደረገው፤ ከዚያም ፍጻሜ ማግኘቱን ይከታተለዋል ማለት ነው። ታላቁ የቤዛነት ዕቅድ እግዚአብሔር ሰው ያደረገውን ከተመለከተ በኋላ ያመጣው የችኮላ ረፋድ አሳብ አይደለም። ምንም እንኳ ይህ አእምሮአችንን ቢያሸብረውም፥ የመለኮታዊ ምርጫንና የቅድሚያ ውሳኔን (የሚሆነው ሁሉ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተወሰነና ሰውም የማይቀይረው መሆኑ) መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ መቀበል አለብን። ምንም እንኳ ለክፋት ድርጊታቸው ሰዎች በኃላፊነት ቢጠየቁበትም፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትም አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተወሰነ ነበር (የሐዋ. 2፡22-23፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡18-20)። የውጤታማ የጸሎት ሕይወት ምሥጢራት አንዱ የእግዚአብሔርን ዓላማዎች በእምነት መጨበጥ ነው (የሐዋ. 4፡23-31)።  ይህ ጥበብ የእግዚአብሔርን ሕዝብ መክበር ያስከትላል (2፡7)። የዚህ «የዘመናት ዕቅድ» ከፍተኛ ገለጣዎች አንዱ በኤፌሶን 1 የሚገኘው ነው። በዚያ ምንባብ ውስጥ ጳ ውሎስ ሦስት ጊዜ፥ ይህ ሁሉ የተደረገው ለእግዚአብሔር ክብር ነው ይላል (ቁ. 6፥12፥ 14)። ይህንኑ የእግዚአብሔር ክብር እኛም አንድ ቀን የምንካፈል መሆኑ በጣም የሚያስደንቅ አሳብ ነው! (ዮሐ 17፡22-24፤ ሮሜ 8፡28-30ን ተመልከት።)  ይህ ጥበብ ካልዳነው ዓለም የተሰወረ ነው (2፡8)። የዚህ ዓለም [የዘመኑ] ገዢዎች ብሎ ጳውሎስ የሚጠቅሳቸው እነማን ናቸው? ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት በመንግሥት ሥልጣን የነበሩት ያለጥርጥር እርሱ ማን እንደነበር አላወቁትም (የሐዋ. 3፡17፤ 4፡25 28)። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ «አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው» (ሉቃ. 23፡34) ብሎ ሲጸልይ ይህን እውነት እያስተጋባ ነበር። በእርግጥ አለማወቃቸው ለኃጢአታቸው ይቅርታን ሊያስገኝላቸው አልቻለም፤ ምክንያቱም ተፈላጊውን ማረጋገጫ ጌታ ሰጥቶአቸው ስለነበር ማመን ነበረባቸው።  ነገር ግን ሌላም አማራጭ ነበር። ጳውሎስ ያጣቅስ የነበረው የዚህን የአሁን ዘመን መንፈሳውያንና አጋንንታዊ ገዢዎችን ሊሆን ይችላል። (ሮሜ 8፡38፤ ቆላ. 2፡15፤ ኤፌ. 6፡12)። ይህ በተለይ በቁጥር 6 ላይ የበለጠ ትርጉም አለው፤ ምክንያቱም በእርግጥ ጲላጦስ፥ ሄሮድስ እና ሌሎች የዘመኑ ገዢዎች የሚታወቁበት ምንም የተለየ ጥበብ አልነበራቸውም። የዘመኑ ጥበብ ምንጩ ከሰይጣን አለቅነት ሥር የነበሩ የዘመኑ ገዢዎች ናቸው (ዮሐ 12፡31፤ 14፡30፤ 16፡11)። እርግጥ ነው፥ መንፈሳውያን ገዢዎች የሚሠሩት በሰብአዊ ገዢዎች ውስጥ እና አማካኝነት ነው። በመሆኑም ልዩነቱን እጅግም ልናጠብቀው አያስፈልግ ይሆናል (ዮሐ 13፡2፥27)።  ነገር ግን ይህ ትርጉም እውነት ከሆነ፥ ጠጣር የእሳቤ አቅጣጫዎችን ይከፍታል። ሰይጣናዊ ኃይላት፥ ሰይጣን ራሱን ጨምሮ የእግዚአብሔርን ታላቅ ዘላለማዊ ዕቅድ እላወቁትም ነበር! የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚወለድና እንደሚሞት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሊያውቁት ችለዋል። የመስቀልን አስፈላጊነት ግን ሊረዱት አልቻሉም ነበር። ምክንያቱም እነዚህ እውነቶች በእግዚአብሔር የተሰወሩ ነበሩ። እንዲያውም እነዚህ እውነቶች አሁን ለአለቆች እና ሥልጣናት እየተገለጠ ያለው በቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ነው (ኤፌ. 3፡10)።  ሰይጣን ቀራኒዮ የእግዚአብሔር ታላቅ ሽንፈት መስሎት ነበር፤ ነገር ግን በተገላቢጦሽ ለእግዚአብሔር ታላቅ ድል ለሰይጣን ደግሞ ሽንፈት ሆነ! (ቆላ. 2፡15)። ጌታችን ተወልዶ ወደዚህ ዓለም ከመጣ ጊዜ ጀምሮ፥ ሰይጣን ሊገድለው ጥረት አድርጓል። ምክንያቱም ሰይጣን የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ሰፊ ውጤት አልተረዳም ነበር። አጋንንታዊ አለቆች አውቀውት ቢሆን ኖሮ የክርስቶስን ሞት አያቀነባብሩትም ነበር። (በእርግጥ፥ ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ አካል ነበር። የሚቆጣጠረው እግዚአብሔር እንጂ ሰይጣን አልነበረም።)  በመጨረሻም፥ ይህ ጥበብ ዛሬም በአማኙ ሕይወት ውስጥ ተግባራዊ የሚሆን ነው (2፡9)። ይህ ቁጥር ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውለው በቀብር ሥነ ሥርዓት ወቅት እና መንግሥተ ሰማያትን በተመለከተ ነው። ነገር ግን መሠረታዊ ተዛምዶው ለዛሬው ክርስቲያን ሕይወት ነው። የሚቀጥለው ቁጥር እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች የሚገልጠው እዚሁ እና አሁኑኑ መሆኑን ግልጽ ያደርጋል።  ይህ ቁጥር በኢሳይያስ 64፡4 በማዛመድ) የተወሰደ ጥቅስ ነው። ዓውዱ በቀጥታ በምርኮ ከነበረችውና የእግዚአብሔርን ነፃ ማውጣት ከምትጠባበቀው ከእስራኤል ጋር ያዛምደዋል። የእስራኤል ሕዝብ ስለበደለ ለቅጣት ወደ ምድረ ባቢሎን ተሰድዶ ነበር። እግዚአብሔር ወርዶ ነፃ እንዲያወጣቸው ጮኹ፤ እርሱም ከ 70 ዓመታት የስደት ዘመናቸው በኋላ ጸሎታቸውን መለሰ። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ዕቅድ ስለነበረው መፍራት አልነበረባቸውም (ኤር. 29፡11)።  ጳውሎስ ይህን መርህ ለቤተክርስቲያን ተጠቅሟል። ያለንበት ሁኔታ የፈለገውን ይሁን የወደፊታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተጠበቀ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ገንዘቡ ላደረጋቸው ያሉት ዕቅዶች ፍጹም ድንቅ ስለሆኑ አእምሮአችን ሊያስበው ወይም ሊያስተውለው ይሳነዋል! እግዚአብሔር ይህንን አስቀድሞ ለክብራችን እንዲሆን ወስኖታል (ቁ 7)። ከምድር እስከ መንግሥተ ሰማይ ድረስ መንገዱ ሁሉ ክብር ነው!  እግዚአብሔርን ለሚወዱት እያንዳንዱ ቀን መልካም ቀን ነው (ሮሜ 8፡28)። መልካም ቀን መስሎ ላይታይ ወይም ላይሰማ ይችላል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ዕቅዱን በሚሠራበት ጊዜ የላቀ እንደሚሆንልን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። እርሱን ከመተማመን ስንጓደል፥ ወይም ሳንታዘዘው ስንቀር፥ ለእርሱ ያለን ፍቅር ሲቀዘቅዝ ያኔ ሕይወት የጽልመት ጭጋግ ትላበሳለች። በእግዚአብሔር ጥበብ ከተመላለስን፥ የእርሱን በረከቶች እናጣጥማለን።  ሁለት የወንጌል እውነቶችን እይተናል። እነዚህም ይህ መልእክት የክርስቶስን ሞት ማዕከል ማድረጉን እና የአብ ሰፊ ዕቅድ አካል መሆኑ ናቸው። በቆሮንቶስ የነበሩ እማኞች የደኅንነታቸውን ዋጋ ዘንግተው ነበር፤ ዓይኖቻቸውን ከመስቀሉ ላይ እንሥተው ነበር። በተጨማሪ በጥቃቅን ነገሮች– (የሕፃናት አሻንጉሊት በሚመስሉ) ተይዘው ነበር- ምክንያቱም እግዚአብሔር ለእነርሱ ለነበረው ዕቅድ ታላቅነት እድናቆት አጥተው ነው። ወደ መንፈስ ቅዱስ አገልግሎት መመለስ አስፈላጊያቸው ነበር። በመሆኑም የጳውሎስ ቀጣዩ ነጥብ ይህን የሚመለከት ይሆናል። ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

ወንጌል የአብ ዘላለማዊ ዕቅድ ክፍል ነው (1ኛ ቆሮ. 2፡6-9) Read More »

ወንጌል የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት ማዕከል ያደርጋል (1ኛ ቆሮ. 2፡1-5)

ባለቤቴ መኪናችንን እየነዳች አጠገቧ ተቀምጬ ወደ ቺካጎ እየሄድን ሳለ እንድ እሳታሚ እንድገመግመው የሰጠኝን የአንድ ደራሲ መጽሐፍ እነብብ ነበር። አልፎ አልፎ የማጉተምተም ከዚያም ማጉረምረም እይሉት ማቃሰት የሚመስል ድምፅ አሰማ ነበር፤ በመጨረሻም ራሴን ነቀነቅሁና፥ «ኦ፥ ፍጹም! ይህን አላምንም!» አልኩኝ።  «መጽሐፉን ያልወደድህ መሰለኝ፥ የሆነ ችግር አለው?» አለችኝ።  «አሳምሮ ነዋ!» አልኳት። «ሁሉም ነገር የተበላሸ ነው ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም ይህ ሰው የወንጌሉ መልእክት በእርግጥ ምን እንደሆነ አያውቅም!»  ይሁንና ደራሲው ለወንጌል ታማኝ የነበረበት ጊዜ ነበር። ነገር ግን በዓመታት መካከል፥ ወንጌልን በፍልስፍናዊ (ይመስለኛል የፖለቲካ) አመለካከት ማየት ጀመረ። ውጤቱ ጭራሽኑ ወንጌል ያልሆነ ቅይጥ መልእክት ነበር።  ጳውሎስ በቆሮንቶስ ያገለግል በነበረ ጊዜ፥ ከጌታችን የተቀበለውን ተልእኮ ይታዘዝና ወንጌልንም ይሰብክ ነበር። በማቴዎስ 28፡18-20 እና በሐዋርያት ሥራ 18፡ 1-11 መካከል ቆንጆ መመሳሰል አለ።  ክርስቶስ የሰጠው ሥራ  ( ማቴ. 28፡18-20) «እንግዲህ ሂዱና» (ቁ. 19) «ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው» [አስተምሩ]ቁ.19) «እያጠመቃችኋቸው»(ቁ19) «እያስተማራችኋቸው» (ቁ.20) «እነሆም እኔ…ከእናንተ ጋር ነኝ» (ቁ 20)  የጳውሎስ አገልግሎት (የሐዋ. 18፡1-11) ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ መጣ (ቁ 1). . . ብዙ በሰሙ ጊዜ እምነው (ቁ. 8) ተጠመቁ (ቁ. 8) በመካከላቸውም የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማረ ዓመት ከስድስት ወር ተቀመጠ (ቁ.11) እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ (ቁ. 10)   በቆሮንቶስ የሆነው ዛሬም በየአብያተ ክርስቲያናቱ እየሆነ ነው። ሰዎች ፍልስፍናን (የሰውን ጥበብ) ከተገለጠው የእግዚአብሔር መልእክት ጋር እየቀየጡት ነው። ይህ ደግሞ ግራ መጋባትን እና ክፍፍልን እየፈጠረ ነው። የተለያዩ ሰባኪያን ለእግዚአብሔር ቃል የተለየ እቀራረብ አላቸው። አንዳንዶቹማ የራሳቸውን ቃል እየፈለሰፉ ናቸው!  ጳውሎስ የወንጌል መልእክት ሦስት ፍሬ እሳቦችን ካብራራ በኋላ አንባቢዎቹ ወደ እነዚህ ፍሬ እሳቦች እንዲመለሱ ያበረታታቸዋል።  ወንጌል የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት ማዕከል ያደርጋል (1ኛ ቆሮ. 2፡1-5)  ጳውሎስ እቀራረቡን ለቆሮንቶሳውያን ያስታውሳቸዋል (2፡1-2)። «እኔም፥» የሚለው መክፈቻ ቃል ሊተረጎም የሚችለው በ 1፡31- በእግዚአብሔር ይመካ በሚለው መሠረት «እንዲስማማ» ሆኖ ነው። ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ የመጣው እግዚአብሔርን ለማክበር ወይም ከፍ ለማድረግ እንጂ ራሱን ከፍ ሊያደርግ (በእርሱ እንዲመኩበት) ወይም ሃይማኖታዊ «አሞካሾችን» ሊመሠርት አልነበረም።  ተዘዋዋሪ ፈላስፋዎች እና አስተማሪዎች ተከታዮችን ለማፍራት በገዛ ጥበባቸው እና በማራኪ አነጋገራቸው ላይ ይመኩ ነበር። የቆሮንቶስ ከተማ እንዲህ ባሉ «ቀልብ ዘራፊዎች» የተሞላች ነበረች። ጳውሎስ ግን በማራኪ እነጋገር ወይም በቀልጣፋ ክርክሮች አልተመካም፣ እንዲሁ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የእግዚአብሔርን ቃል አወጀ። እርሱ አምባሳደር እንጂ «ክርስቲያን ደላላ» አልነበረም።  ጳውሎስ አስደናቂ ንግግር እና ፍልስፍና ተጠቅሞ ቢሆን ኖሮ ራሱን ከፍ አድርጎ ለማወጅ ያቀደውን ክርስቶስን ይደብቀው ነበር! «የክርስቶስም መስቀል ከንቱ እንዳይሆን፥ በሰዎች የንግግር ጥበብ አልሰብክም» (1፡17- አዲሱ መደበኛ ትርጉም)።  በአንድ ቤተ ክርስቲያን ከምስባኩ በስተጀርባ በውብ ቀለማት ያሸበረቀ የመስተዋት መስኮት ነበር። ኢየሱስ በመስቀል እንደተሰቀለ ተሥሎበታል። አንድ እሑድ ዕለት ዘወትር ከሚያገለግለው መጋቢ በጣም አጠር የሚል እንግዳ ሰው አገለገለ። በዚህ ጊዜ አንዲት ትንሽ ልጃገረድ ያን እንግዳ ሰው ለጥቂት ጊዜ ሲናገር ከሰማችው በኋላ፥ ወደ እናቷ ዘወር ብላ እንዲህ ስትል ጠየቀቻት፤ «ብዙ ጊዜ እዚያ ላይ ቆሞ ኢየሱስን ማየት እንዳንችል የሚያደርገው ሰው ዛሬ የት ሄደ?»  በጣም ብዙ የሆኑ የቃሉ ሰባኪያን ራሳቸውን እና ስጦታቸውን ስለሚያጎሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ከመግለጥ ይጎድላሉ። ጳውሎስ በክርስቶስ መስቀል ስለተመካ (ገላ 6፡14) የመልእክቱ ማዕከል አደረገው።  ከዚያም ጳውሎስ ስለ ዝንባሌው ቆሮንቶሳውያንን እሳሰባቸው (2፡3-4)። ሐዋርያ ቢሆንም፥ ጳውሎስ ወደ እነርሱ የመጣው እንደ ትሑት አገልጋይ ነበር። በራሱ አልተመካም ነበር፥ ክርስቶስ ሁሉን ይሆን ዘንድ ራሱን ባዶ አደረገ። በተከታይ ዓመታት፥ ጳውሎስ ይህን ነገር እንደገና እንሥቶ ቆሮንቶስን ከወረሯት የሐሰት አስተማሪዎች (2ኛ ቆሮ. 10፡1-12) ጋር ራሱን አነጻጽሮበታል። በሚደክምበት ጊዜ፤ እግዚአብሔር እንደሚያበረታው ጳውሎስ ተምሮአል።  ጳውሎስ ይመካ የነበረው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ላይ ነው። ለአገልግሎቱ ኃይልን የሰጠው ልምምዱ ወይም ችሎታው አልነበረም፤ ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ ሥራ ነበር። የእርሱ ስብከት «ጭብጥ መግለጫ» እንጂ «የድርጊት ስኬት» አልነበረም። ጭብጥ መግለጫ የሚለው ሐረግ ሲተረጎም «በችሎት የቀረበን ሕጋዊ ማረጋገጫ» ያመለክታል። መንፈስ ቅዱስ የጳውሎስን ስብከት ሕይወትን ለመለወጥ ተጠቅሞበታል፤ ስለሆነም መልእክቱ ከእግዚአብሔር ለመሆኑ የሚፈለገው ማረጋገጫ ይኸው ነበር። በክፋት የተሞሉ ኃጢአተኛች በእግዚአብሔር ኃይል ተለውጠዋል! (1ኛ ቆሮ. 6፡9-11)።  ይሁን እንጂ፥ ጳውሎስ አገልጋዮች ሆን ብለው አድበስብሰው ይስበኩ፥ ወይም እግዚአብሔር የሰጣቸውን ስጦታዎች ይተዉ ማለቱ እንዳይደለ ልብ ልንል ይገባል። እንደነ ቻርልስ ስፐርጀን እና ጆርጅ ዋይትፊልድ ያሉ ሰዎች ኃይል የተላበሱ ቃላትን የሚያዥጎደጉዱ ተናጋሪዎች ነበሩ፤ ሆኖም ግን በተፈጥሮአዊ ችሎታዎቻቸው አልተመኩም። በአድማጮቻቸው ልብ መንፈስ ቅዱስ እንዲሠራ ተማመኑ፤ እርሱም ደግሞ ሠራ። ቃሉን የሚያገለግሉ መዘጋጀትና እግዚአብሔር የሰጣቸውን ማንኛውንም ስጦታ መጠቀም አለባቸው ሆኖም ግን ትምክህትን በራሳቸው ላይ ማኖር የለባቸውም። (2ኛ ቆሮ. 3፡5ን ተመልከት።)  በመጨረሻም፥ ጳውሎስ ስለ ዓላማው እሳሰባቸው (2፡5)። በእግዚአብሔር እንጂ እግዚአብሔር በላከው መልእክተኛ እንዳይተማመኑ ፍላጎቱ ነበር። በሰብአዊ ጥበብ ላይ ተመክቶ የደኅንነትን ዕቅድ እንደ እንድ ሥርዓተ ፍልስፍና አቅርቦት ቢሆን ኖሮ፥ ያኔ ቆሮንቶሳውያን እምነታቸውን በገለጻ ላይ ባደረጉ ነበር። ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል በእግዚአብሔር ኃይል ስላወጀ፥ በእርሱ አማካኝነት ያመኑት እምነታቸውን ያሳረፉት ጭብጥ መግለጫ ላይ ስለነበር እግዚአብሔር በሕይወታቸው መሥራቱን ተለማምደውታል።  ከዓመታት በፊት፥ እንድ ብልኅ ክርስቲያን እንዲህ አለኝ፥ «ሰዎችን ወደ ክርስቶስ በምትመራበት ጊዜ፥ የዳናችሁት ይህን ወይም ያን ስላደረጋችሁ ነው ብለህ ከቶ አትንገራቸው። ለሰዎች እንደዳኑ መመስከር የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው። እርሱ በሥራ ላይ ካልሆነ ደኅንነት ሊመጣ አይችልም።» እውነትም በሳል ምክር ነው!  በመጋቢነት እገለግል በነበርኩበት ቤተክርስቲያን በጣም ጥሩ የሆነ በታማኝነት የሚከታተል ባለሙያ ሰው ነበረ ይህ ሰው ያልዳነ ሆኖም ግን ወንጌልን የማይቃወም ነበር። እርሱ የእግዚአብሔርን ቃል ማድመጡን ቀጥሎ ሳለ ብዙዎቻችን እንጸልይለት ነበር። አንድ ቀን የእርሱ ጓደኛ የሆነ ክርስቲያን ሰው ወደ ክርስቶስ እመልሰዋለሁ ወይ ይለይለታል ብሎ ወሰነ! ለበርካታ ሰዓታት የክርክር ውርጅብኝ አወረደበት እና ሰውየው በመጨረሻ «የኃጢአተኛ ሰው ጸሎት ጸለየ።» ከዚያም ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣቱን አቆመ! ለምን? ምክንያቱም እውነት ያልሆነን ነገር እንዲቀበል ስለነዘነዘው እና እስከ መጨረሻ ሊቀጥል አለመቻሉን ስለተገነዘበ ነበር። በኋላ ግን ክርስቶስን አመነ እና በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት፤ የደኅንነትን ማረጋገጫ አገኘ። እስከዚያ ድረስ፥ ድነሃል ወይ ብሎ ማንም ቢጠይቀው፥ «እዎ=ቶም ድነሃል! ብሎኛል» ይል ነበር። መንፈስ ማረጋገጫ በሚሰጥበት ጊዜ አቤት ያለው ልዩነት!  ወንጌል ዛሬም የሰዎችን ሕይወት የሚለውጥ ኃይል ነው (ሮሜ 1፡16)። የወንጌል ስርጭት ስኬታማነት በክርክራችን ወይም በአባባይ «ሽወዳችን» ላይ የሚመረኮዝ ሳይሆን፥ በሕይወታችን በሚሠራው የእግዚአብሔር መንፈስና በምናካፍለው ቃሉ ላይ የሚደገፍ ነው። ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

ወንጌል የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት ማዕከል ያደርጋል (1ኛ ቆሮ. 2፡1-5) Read More »

እግዚአብሔርን ለማክበር የተጠራችሁ (1ኛ ቆሮ. 1፡26-31)

ቆሮንቶሳውያን በትዕቢት «የመነፋት» አዝማሚያ ነበራቸው (4፡6፥18-19፤ 5፡2)። ነገር ግን የእግዚአብሔር የጸጋ ወንጌል ራስን በትምክህት ለመሙላት ምንም ስፍራ አይሰጥም። መልካችን፥ ማኅበራዊ አቋማችን፥ ደረጃችን፥ የተፈጥሮ ቅርሳችን፥ ወይም የገንዘብ ዓቅማችን የእግዚአብሔርን አድናቆት ወይም አክብሮት አያተርፍልንም። ጳውሎስ ለማንም ሳይሆን ለብዙዎች እንደ ጻፈ ልብ በል። በአዲስ ኪዳን «ከፍተኛ ማኅበራዊ አቋም» ያላቸውን ጥቂት አማኞች እናገኛለን፤ ሆኖም ግን እንዲህ ዓይነቶቹ ብዙ አይደሉም። ለአዲስ አማኞች ጳውሎስ የሰጠው አገላለጽ በእርግጥ የበለጠ አልነበረም (6፡9-11)።  ጳውሎስ ምን እንደነበሩ አስታወሳቸው (1፡26)። ጥበበኞች፥ ኃያል፥ ወይም የተከበሩ አልነበሩም። እግዚአብሔር የጠራቸው የነበራቸውን መነሻ ምክንያት አድርጎ ሳይሆን ያንን ካቁጥር ሳያስገባ ነበር! የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በመሠረቱ የተውጣጣችው በጣም የከፉ ኃጢአተኞች ከነበሩ ተራ ሰዎች ነበር። ጳውሎስ ከመለወጡ በፊት በጣም ተመጻዳቂ ሰው ነበር፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ሃይማኖቱን መተው ግድ ሆነበት! ቆሮንቶሳውያን በሌላኛው ጽንፍ ነበሩ፤ ቢሆንም ቅሉ እግዚአብሔር ደርሶ ማዳን እስከሚያዳግተው ድረስ በጣም ኃጢአተኞች አልነበሩም።  ሮበርት ሙሬይ ማክቼይን የተባለ ብፁዕ የእስኮቲሽ መጋቢ አንድ ቀን ለአንዲት ሴት የወንጌል ትራክት በሰጣት ጊዜ ሴቲቱ በጣም ተቀየመችው። በዚሁ ስሜት ሆና «ማን እንደሆንሁ አላወቅህም!» አለችው። ማክቼይንም መለሰና፥ «እሜቴ፥ የፍርድ ቀን እየመጣ ነው፥ በዚያ ቀን የእርስዎ ማንነት የሚፈይድ አይሆንም» አላት።  ጳውሎስ ቆሮንቶሳውያንን እግዚአብሔር ለምን እንደጠራቸው አስታወሳቸው (1፡27-29)። እግዚአብሔር ለሚታበየው ዓለም ጉድለታቸውን እና የእርሱን ጸጋ ያሳይ ዘንድ ሞኙን፥ ደካማውን፥ ምናምንቴውን («ከዝቅተኛ የተወለደውን») እና የተናቀውን መረጠ። ጠፊዋ ዓለም የዘር ሐረግን፥ ማኅበራዊ አቋምን፥ ጥሪታዊ ስኬትን፥ ኃይልን እና እውቅናን ታደንቃለች። ነገር ግን ከእነዚህ ውስጥ የትኛውም ለዘላለም ሕይወት ዋስትናን አይሰጥም።  መልእክቱ እና በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነው የእግዚአብሔር የጸጋ ተአምር የዚህችን ዓለም ታላላቅ እና ኃያል ሰዎች ያጣጥላቸዋል (ያሳፍራቸዋል)። የዚህች ዓለም ጥበበኞች እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን እንዴት ቅዱሳን አድርጎ እንደሚለውጣቸው ሊገባቸው አይችልም። የዚህች ዓለም ኃያላንም ቢሆኑ ይህን ተአምሩን የመድገም ዓቅም የላቸውም። የእግዚአብሔር «ሞኝነት» ጥበበኛውን ያሳፍረዋል፤ የእግዚአብሔር «ድካም» ኃያሉን ያሳፍረዋል!  የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መዛግብት ሕይወታቸው በወንጌል ኃይል በተለወጠ ታላላቅ ኃጢአተኞች ዝክረ-ነገር የተሞላ ነው። እንደ አብዛኛዎቹ መጋቢያን እና ሰባኪዎች አገልግሎት ሁሉ፥ በእኔ አገልግሎትም የሕግ እና የሥነ ልቡና ጠበብት መረዳት ያልቻሉት አስደናቂ ነገሮች ሲከሰቱ አይቻለሁ። ወጣት አጥፊዎች የተዋጣላቸው ተማሪዎች እና ጠቃሚ ዜጋዎች ሲሆኑ አይተናል። ፍርድ ቤቶች አፋቸውን እስኪይዙ ድረስ ትዳሮች ሕይወት ሲዘሩ እና ወና የቀሩ ቤቶችም ዳግም ሲሟሟቁ ተመልክተናል።  እግዚአብሔር የዚህን የዛሬውን ዓለም ሥርዓት፥ የፍልስፍናውን እና የሃይማኖቱንም ሞኝነት እና ደካማነት የሚገልጠው ለምንድን ነው? «ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ» (ቁ 29) ነው። ደኅንነት ሙሉ ለሙሉ በጸጋ መሆን አለበት፤ አለበለዚያ እግዚአብሔር ክብሩን አይቀዳጅም።  ጳውሎስ ለቆሮንቶሳውያን ለማስተላለፍ የሚሻው ይህን እውነት ነው፤ ምክንያቱም ጥፋታቸው በሰው የመመካት ነበር (3፡2)። በሰዎች፥ እንደ ጴጥሮስ፥ ጳውሎስ እና እጵሎስ ባሱ የእግዚአብሔር ሰዎችም እንኳ የምንመካ ከሆነ- እግዚአብሔር ብቻውን ሊቀዳጅ የሚገባውን ክብር እየተናጠቅን ነን ማለት ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ያደርግ የነበረው ይህ ኃጢአታዊ የትምክህት አመለካከት ነው።  በመጨረሻም፥ ጳውሎስ በኢየሱስ ክርስቶስ የነበራቸውን ሁሉ አስታወሳቸው (1፡30-31)። እያንዳንዱ አማኝ «በክርስቶስ» ስለሆነ እና የሚያስፈልገው ሁሉ ስላለው እርስ በርስ መወዳደር ወይም ራስን ከሌላው ማነጻጸር ለምን ያስፈልጋል? ሁሉንም ያደረገው ጌታ ነው! «የሚመካ በጌታ ይመካ» (ቁጥር 31 ከኤርምያስ 9፡24 የተወሰደ ሲሆን እንደገና በ 2ኛ ቆሮ. 10፡17 ተጠቅሶአል)።  የሚያስፈልጉን መንፈሳዊ በረከቶች ከእጃችን የሚያፈተልኩ ረቂቅ ነገሮች አይደሉም፤ ሁሉም በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። እርሱ ጥበባችን ነው (ቆላ. 2፡3)፥ ጽድቃችን ነው (2ኛ ቆሮ. 5፡2)። ቅድስናችን ነው (ዮሐ 17፡19)፥ እና ቤዛችን ነው (ሮሜ 3፡24)። በእርግጥ እዚህ ላይ እግዚአብሔር በክርስቶስ ባለን ጽድቅ፥ ቅድስና እና ቤዛነት ጥበቡን እንደሚያሳይ አጽንኦት ተደርጎበታል። እነዚህ ሥነ መለኮታዊ ቃላት እያንዳንዳቸው ለክርስቲያኖች ልዩ ትርጉም አላቸው። ጽድቅ በእግዚአብሔር ፊት ያለንን አቋም የሚመለከት ነው። ጸድቀናል። በኢየሱስ ክርስቶስ እንደጻደቅን እግዚአብሔር ይናገራል። ደግሞም ተቀድሰናል፥ የእግዚአብሔር ገንዘብ በመሆን እና እርሱን ለማገልገል ተለይተናል። ቤዛነት በአጽንኦት የሚያሳየው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ዋጋን በመክፈሉ አርነት መውጣታችንን ነው። ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ወደሚጠናቀቀው ፍጹም ቤዛነት ይመራናል።  ስለዚህ በአንድ መልኩ፥ እዚህ ላይ ሦስት የደኅንነት ጊዜያት አሉን ከኃጢአት ቅጣት ድነናል (ጽድቅ)፤ ከኃጢአት ኃይል እየዳንን ነው (ቅድስና)፤ ከኃጢአት ህልውና እንድናለን (ቤዛነት)። በመሆኑም እያንዳንዱ አማኝ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እነዚህ ሁሉ በረከቶች አሉት!  እንግዲህ፥ ለምን በሰው እንመካለን? አንተ የሌለህ ጳውሎስ ያለው ምንድን ነው? ጴጥሮስ ከአንተ ይልቅ ክርስቶስን በብዙ ለራሱ ያደርጋልን? (ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን በብዙ የራሱ አደረገ ማለት ከሆነ የሚመስል ነገር ነው፤ ያ ግን ሌላ ጉዳይ ነው!) መመካት የሚገባን በጌታ እንጂ በራሳችን ወይም በመንፈሳዊ መሪዎቻችን አይደለም።  ይህን ምዕራፍ በምትከልስበት ጊዜ፥ ቆሮንቶሳውያን ይፈጽሙአቸው የነበሩትን ስሕተቶች ማየት ትችላለህ፤ እነዚህ ስሕተቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግሮች እንዲፈጠሩ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የተቀደሰውን ጥሪያቸውን የሚመጥን አኗኗር አልነበራቸውም፤ ይልቁኑ ይከተሉት የነበረው የዓለምን ልኬቶች ነበር። ወደሚደነቀው የጌታ እና የእርስ በርስ መንፈሳዊ ኅብረት የመጠራታቸውን እውነታ ችላ አሉት። በዚህ ፈንታ ከሰብአዊ መሪዎች ጋር ያብሩና በዚህም ተግባራቸው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍልን ይፈጥሩ ነበር። እግዚአብሔርን ጸጋውን ከፍ ከፍ ከማድረግ ይልቅ እንደፈለጋቸው ያደርጉና ሰዎችን ያሞካሹ ነበር።  እነርሱ የረከሰች፥ የተከፋፈለችና ጸጋዋን የተገፈፈች ቤተ ክርስቲያን ነበሩ!  ሆኖም ግን፥ በእነርሱ ላይ ፍርድን ከማሳለፋችን በፊት የራሳችንን ቤተ ክርስቲያንና የግል ሕይወታችንን መመርመር ይገባናል። እኛም እንደ እነርሱ ቅዱስ ለመሆን፥ ወደ ኅብረቱና እግዚአብሔርን ለማክበር ተጠርተናል።  ለዚህ ጥሪ ብቁ ሆነን እየኖርን ነው ወይ? ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

እግዚአብሔርን ለማክበር የተጠራችሁ (1ኛ ቆሮ. 1፡26-31) Read More »

ወደ ኅብረት የተጠራችሁ (1ኛ ቆሮ. 1፡10–25)

ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረውን የርኩሰት ችግር ከጠቀሰ በኋላ ወደ ክፍፍሉ ጉዳይ ተመለሰ። ክፍፍል በእግዚአብሔር ሰዎች መካከል ሁልጊዜ የነበረ ችግር ነው። ስለሆነም ሁሉም የአዲስ ኪዳን መልእክቶች ማለት ይቻላል ይህን ርእስ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ይነኩታል ወይም ይጠቅሱታል። አሥራ ሁለቱ ሐዋርያትም እንኳ እርስ በርስ ሁልጊዜ የተስማሙበት ወቅት አልነበረም።  ከምንወዳቸው ቅዱሳን በከፍታ መኖር፥  ይህ በእርግጥም ነው ክብር!  በዝቅታ መኖር ከምናውቃቸው ቅዱሳን፥  ያ ደግሞ ሌላ ታሪክ ነው የሚከነክን!  በቁጥር 13፥ ጳውሎስ አንባቢዎቹን ሦስት አስፈላጊ ጥያቄዎችን ጠየቃቸው፥ ታዲያ እነዚህ ጥያቄዎች ለዚህ ረጅም አንቀጽ ቁልፍ ናቸው።  ክርስቶስ ተከፋፍሎአልን? (1፡10-13) የግሡ ትርጉም፥ «ክርስቶስ ተከፋፍሎ የተለያዩ ክፍሎቹ ለተለያዩ ሰዎች ታድለዋልን?» የሚል ነው። ይህ አሳብ ራሱ አስጠሊታ ስለሆነ መጣል የሚገባው ነው። ጳውሎስ አንድ ክርስቶስን፥ አጵሎስ ደግሞ የተለየ ክርስቶስን፥ ጴጥሮስም እንዲሁ ሌላ ክርስቶስን አልሰበኩም። ያለው አንድ ወንጌል እና አንድ አዳኝ ብቻ ነው (ገላ. 1፡6-9)። ታዲያ ቆሮንቶሳውያን ይህን የአራት አቅጣጫ ክፍፍል እንዴት ፈጠሩት? በመካከላቸው ለምን ጠብ (“ውድድር ) ሆነ?  አንደኛው መልስ ወንጌልን ይመለከቱት የነበረው ከፍልስፍና እቅጣጫ ስለሆነ ነው። ቆሮንቶስ «ጥበባቸውን» በማሰራጨት በሚሽቀዳደሙ አስተማሪዎች እና ፈላስፋዎች የተሞላች ነበረች።  ሌላኛው መልስ ሰብአዊ ተፈጥሮ ሰብአዊ መሪዎችን በመከተል የመርካቱ ጉዳይ ነው። ከሚረዱን፤ አገልግሎታቸው ከሚገባን እና ከሚያስደስተን መንፈሳውያን መሪዎች ራሳችንን የበለጠ ወደ ማዛመዱ እናዘነብላለን። እነርሱ አጽንኦት የሰጡት ከቃሉ መልእክት ይልቅ ለመልእክተኛው ነበር፤ ዓይኖቻቸውን ከጌታ ላይ እንሥተው በጌታ ባሪያ ላይ አደረጉ፤ ይህ ደግሞ ወደ ውድድር መራቸው።  ጳውሎስ በምዕራፍ 3 ላይ በእውነተኛ የእግዚአብሔር ባሪያዎች መካከል ውድድር ወይም እሽቅድምድም ሊኖር እንደማይችል ያመለክታል። ለቤተ ክርስቲያን አባላት መጋቢያንን ማወዳደር ኃጢአት ነው፥ ወይም አማኞች እንደ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሆናቸው ቀርቶ እንደ ሰዎች ደቀ መዛሙርት በመሆን ሰብአዊ መሪዎችን ከተከተሉአቸው ይህም ኃጢአት ነው። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የሚገኙ «ሰው አድናቂ ክፍሎች» ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ግንባር ለግንባር በሚጋጭ ዓመፅ ላይ ናቸው። ከፍተኛውን ስፍራ መያዝ ያለበት ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው (ቆላ. 1፡18)።  ጳውሎስ በዚህ ክፍል ውስጥ ቅዱሳን በክርስቶስ ስላላቸው አንድነት አጽንኦት ለመስጠት በርካታ ቁልፍ ቃላትን ተጠቅሞአል። የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን ለአንባቢዎቹ ለማሳሰብ ወንድሞች ብሎ ጠራቸው። «የተባበራችሁ» የሚለው ቃል የተሳሰረውን የሰው አካል የሚገልጽ የሕክምና ቃል ነው። ስለዚህ፥ የአካሉ ብልቶች እንደመሆናቸው የፍቅር አንድነት ነበራቸው። በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም የታወቁ ነበሩ። ይህ ምናልባት ጥምቀታቸውን የሚያመለክት ነበር።  «የቀሎዔ ቤተሰቦች» አባላት እነማን እንደነበሩ አናውቅም፥ ሆኖም ግን ለጽናታቸውና ለመሰጠታቸው እናደንቃቸዋለን። ችግሮችን ለመሽሽግ አልሞከሩም። ተጨንቀውባቸው ስለነበር ከችግሮቻቸው ጋር ወደ ትክክለኛው ሰው ቀረቡ፤ እንዲሁም ጳውሎስ ስለ እነርሱ መጥቀሱ አላሸማቀቃቸውም። ይህ በእነርሱ ዘንድ ብዙ ጊዜ በየቤተክርስቲያኑ እንደምናያቸው -ችግሩን የባሰ እንጂ ምንም የተሻለ እንደማያደርጉ ድርጊቶች «ምሥጢራዊ ጉዳይ» አልነበረም።  ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱን የመሠረተ አገልጋይ ነበር፤ በመሆኑም አብዛኛዎቹ ምእመናን በእርሱ እገልግሎት የተለወጡ ሊሆኑ ይችላሉ። አጵሎስ ጳውሎስን የተከተለ ሲሆን (የሐዋ. 18፡24-28)፥ ውጤታማ  አገልግሎትም ነበረው። ጴጥሮስ (ኬፋ) 1ኛ ቆሮ. 9፡5 ከሚዘግበው በቀር ቆሮንቶስን ስለመጎብኘቱ ምንም መረጃ የለንም። እነዚህ ሰዎች እያንዳንዳቸው የተለያዩ ባሕርያት እና ቃሉን የሚያገለግሉበትም የተለያዩ እቀራረቦች ነበሩአቸው፤ እንዲሁም ሆኖ ግን አንድ ነበሩ (3፡3-8፤ 4፡6)።  ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን? (1፡13-17) በአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ጥምቀት አስፈላጊ ነገር እንደነበር ልብ በል። አንድ ኃጢአተኛ ክርስቶስን አምኖ በሚጠመቅበት ጊዜ፥ ራሱን ከቀድሞ ሕይወቱ ስለሚለይ ብዙ ጊዜ በቤተሰቡ እና በጓደኞቹ ዘንድ ተቀባይነት ያጣ ነበር። በዚያን ዘመን መጠመቅ አንድን ነገር (ዋጋ) ያስከፍል ነበር።  ኢየሱስ ሰዎችን እንዳላጠመቀ ሁሉ (ዮሐ. 4፡1-2)፥ ጴጥሮስ (የሐዋ. 10፡48) እና ጳውሎስም እንዲሁ አዳዲስ አማኞችን እንዲያጠምቁ ለሥራ ተባባሪዎቻቸው ተዉላቸው። በቆሮንቶስ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን እስከምታድግ ድረስ፥ ጳውሎስ ጥቂት የማጥመቅ ሥራ ሠርቶ ነበር፤ ሆኖም ያ የእርሱ ዋነኛ አገልግሎት አልነበረም። በዚህ ክፍል ውስጥ የሚታየው ጳውሎስ ጥምቀትን ማሳነሱ ሳይሆን፥ ይልቁንም በተገቢ ስፍራው ማስቀመጡ ነበር። ምክንያቱም ቆሮንቶሳውያን የጥምቀትን ተግባር በጣም ያዋድዱት ስለነበር ነው። «እኔ በአጵሎስ ተጠምቄአለሁ!» በማለት አንዱ ሲመጻደቅ፥ ሌላው ደግሞ «የለም እኔስ በጳውሎስ ነው የተጠመቅሁት!» ይል ነበር።  ከኢየሱስ ክርስቶስ ስም በቀር የማንንም ስም ከጥምቀትህ ጋር ማዛመዱ አግባብ አይደለም። ይህን ማድረግ ክፍፍልን መፍጠር ነው። ድርጊቱ ሁሉ በጣም አስፈላጊ ይመስል፥ ለጥምቀታቸው የተለየ ሰባኪ፥ የተለየ ውኃ (ብዙውን ጊዜ ከዮርዳኖስ ወንዝ የመጣህ፥ የተለየ ቀን የሚጠቀሙ ሰዎች ስለመኖራቸው የተጻፈ ነገር አንብቤአለሁ! ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በማክበርና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በማዳበር ፈንታ፥ እነዚህ ሰዎች ግለሰቦችን ከፍ ከፍ በማድረግ ክፍፍልን ይፈጥራሉ።  ቀርስጶስ በቆሮንቶስ ለነበረው ምኵራብ አለቃ ነበር (የሐዋ. 18፡8)፤ ጋይዮስ ደግሞ ምናልባት ጳውሎስ የሮሜን መልእክት በሚጽፍበት ጊዜ አብሮት የኖረ ሰው ሳይሆን አይቀርም (ሮሜ 16፡23)። ስለ «የእስጢፋኖስ ቤተሰዎች» (1ኛ ቆሮ. 1፡16) ምናልባት በ 1ኛ ቆሮ. 16፡15-18 በከፊል ተገልጾአል። በእግዚአብሔር መጽሐፍ መጻፋቸው በቂ ስለነበር፥ ጳውሎስ ያጠመቃቸውን ሰዎች ስም ሁሉ ስመዝገብ የያዘ አይመስልም።  ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቀለን? (1፡18-25) በቁጥር 7 የተጠቀሰው መስቀል ከሰው ጥበብ ደካማነት አንፃር የወንጌል ኃይል የተገለጸበትን ይህን ረጅም ክፍል እስተዋወቀ። በቤተ ክርስቲያን የተከሰተውን ይህን የክፍፍል ችግር ጳውሎስ እንዴት እንዳስተናገደው ማየቱ በጣም አጓጊ ነው። በመጀመሪያ፥ እንድ እዳኝና አንድ አካል በማለት ወደ ክርስቶስ አንድነት አመለከተ። ቀጥሎ ስለ ጥምቀታቸው አሳሰባቸው፣ ይህም በክርስቶስ አካል የመጠመቃቸው አምሳል ነበረ (12፡13)። እንዲህ አድርጎ፥ ወደ መስቀል አደረሳቸው።  ስቅለት ዘግናኝ ሞት ብቻ አልነበረም፤ የውርደት ሞትም እንጂ። ሮማዊ ዜጋን መስቀል ሕገወጥ ነበር። እኛ ዛሬ እራት እየበላን፥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመኑ ሂትለር አይሁዳውያንን ስለፈጀበት ስለ መርዝ ጋዝ ክፍል ወይም በአሜሪካን የሞት ቅጣት ስለሚፈጸምበት ስለ ኤሌክትሪክ ወንበር እንደማንነጋገር ሁሉ፥ በጨዋ ማኅበረሰብ ውስጥ ስቅለት ተጠቅሶ አይታወቅም።  በዚህ አንቀጽ ውስጥ ቁልፍ ቃል ጥበብ ሲሆን፤ ስምንት ጊዜ ተጠቅሶአል። ጳ ውሎስ የሚናገረው ቁልፍ አሳብ ሰብአዊውን ጥበብ ከተገለጠው የእግዚአብሔር መልእክት ጋር ለመቀየጥ እንዳንዳፈር ነው። ስለ ጥበብ የሚናገረው መላው ክፍል (1፡17-2፡16) በተገለጠው የእግዚአብሔር ቃልና በሰዎች ጥበብ መካከል በርከት ያሉ ንጽጽሮችን ይሰጣል።  የእግዚአብሔር ጥበብ በመጀመሪያ የተገለጠው በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ነው፤ ይሁንና ይህን ሁሉም ሰው እያየውም። ጳውሎስ መስቀልን በተመለከተ ሦስት የተለያዩ አመለካከቶች እንዳሉ አመልክቶአል።  እንዳንዶች በመስቀል ይሰናከላሉ። ይህ የአይሁዶች አመለካከት ነበር፤ ምክንያቱም አጽንኦታቸው በተአምራታዊ ምልክቶች ላይ ስለሆነ መስቀል ደግሞ ደካማነት ሆነባቸው። ከግብፅ መውጣታቸው አንሥቶ እስከ ኤልያስና ኤልሳዕ ዘመን ድረስ የአይሁድ ታሪክ በተአምራት የተሞላ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በሚያገለግልበት ወቅት፥ የአይሁድ መሪዎች በተደጋጋሚ ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠይቀውት ነበር፤ እርሱ ግን እምቢ አለ።  የአይሁድ ሕዝብ የራሳቸውን የተቀደሱ መጻሕፍት አላስተዋሉአቸውም ነበር። ጽኑ ኃይል ተላብሶ የሚመጣ እና ጠላቶቻቸውን በሞላ ድባቅ የሚመታ መሢሕ ይጠባበቁ ነበር። ይህ ሰው መንግሥትን አቋቁሞ ለእስራኤል ክብርን የሚመልስ መሆን ነበረበት። በሐዋርያት ሥራ 1፡6 ላይ የተነሣው የሐዋርያት ጥያቄ ይህ ተስፋ በአይሁድ መካከል ምን ያክል ጠንካራ እንደነበረ ያሳያል።  በተመሳሳይ ጊዜ፥ ጸሐፊዎቻቸው መሢሑ እንደሚሠቃይ እና እንደሚሞትም ከብሉይ ኪዳን ያውቁ ነበር። እንደ መዝሙረ ዳዊት 22 እና ኢሳይያስ 53 ያሉ ምንባቦች ያመለከቱት ወደተለየ ዓይነት መሢሕ ነበር፥ ጠበብቱም እነዚህን ሁለት ተጻራሪ መሰል ገጽታዎች ሊያስታርቁ አልቻሉም። መሢሓቸው ወደ ክብሩ ከመግባቱ በፊት መሠቃየት እና መሞት እንደነበረበት (ሉቃ. 24፡13-35ን ተመልከት)፥ እንዲሁም የሚመጣውን የመሢሑ መንግሥት የቤተ ክርስቲያን ዘመን እንደሚቀድመው አልተረዱም ነበር።  አይሁዶች ኃይልን እና ታላቅ ከብርን ይፈልጉ ስለነበር የመስቀል ደካማነት ዕንቅፋት ሆነባቸው። የተራ ወንጀለኛን የውርደት ሞት በሞተ የናዝሬቱ ሥራአጥ አናጢ ላይ ሰው እንዴት እምነቱን መጣል ይቻል? ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል «የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው» (ሮሜ 1፡16)። መስቀል የድካም ምስክርነት ከመሆን ይልቅ ከፍተኛ የኃይል መሣሪያ ነው! ለነገሩ፥ «የእግዚአብሔር ድካም [በመስቀል] ከሰው ይልቅ ይበረታልና» (1ኛ ቆሮ. 1፡25)። 

ወደ ኅብረት የተጠራችሁ (1ኛ ቆሮ. 1፡10–25) Read More »

ቅዱሳን ለመሆን እንደተጠሩ (1ኛ ቆሮ. 1፡1-9)

«ለኢየሱስ፥ እሺ! ለቤተ ክርስቲያን፥ እምቢ!»  በ1960ዎቹ ይህ መፈክር በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ የነበረበትን ጊዜ ታስታውሳለህን? በወቅቱ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን በከፋ ችግር ውስጥ ስለነበረች፥ ይህን አባባል በ 56 ዓ.ም በቆሮንቶስ የነበሩት ያለ ጥርጥር በቅንነት በተጠቀሙት ነበር። የሚያሳዝነው፥ ችግሮቹ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቤተሰቦች መካከል የቀሩ ሳይሆኑ፥ በውጭ ባሉ በማያምኑትም ዘንድ የታወቁ መሆናቸው ነበር።  በመጀመሪያ ደረጃ በቆሮንቶስ የነበረችው ቤተክርስቲያን የረከሰች ቤተ ክርስቲያን ነበረች። ከአባሎቿ አንዳንዶቹ በዝሙት ኃጢአት የወደቁ ነበሩ፤ ሌሎች ሰካራሞች ነበሩ፤ እንደዚሁም ሌሎቹ ለዓለማዊ አኗኗራቸው የእግዚአብሔርን ጸጋ እንደ ማመካኛ የሚጠቀሙ ነበሩ። ከዚህም ባሻገር ይህች ቤተ ክርስቲያን በአመራር ትንቅንቅ በገጠሙ (1፡12) በትንሹ አራት የተለያዩ ቡድኖች የተከፋፈለች ነበረች። ይህም ጸጋዋ የተገፈፈ ቤተ ክርስቲያን ነበረች ማለት ነው። እግዚአብሔርን በማስከበር ፈንታ፥ የወንጌልን ግሥጋሤ የምትገታ ነበረች።   ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነበር? የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት የከተማዪቱ ኃጢአት ወደ ጉባኤያቸው ሰርጎ እንዲገባ ስለፈቀዱ ነበር። ቆሮንቶስ ሁሉም ዓይነት ክፋትና ዓለማዊ ተድላ ያጨናነቃት የረከሰች ከተማ ነበረች። በዚያን ዘመን የመጨረሻው ቀላል ክስ አንድን ሰው «ቆሮንቶሳዊ» ብሎ በመወንጀል ሊመሠረት ይችል ነበር። በአባባሉ ምን ለማለት እንደፈለገ ሰዎች ወዲያው ይገባቸዋል።  በተጨማሪም ቆሮንቶስ ንድፈ አሳባቸውን የሚያራምዱ በርካታ ተዘዋዋሪ አስተማሪዎች የነበሩባት፥ በትዕቢቷ የተወጠረች የፍልስፍና ከተማ ነበረች። የሚያሳዝነው፥ ይህ ፍልስፍናዊ አካሄድ በወንጌል ላይም እንዲተገበር በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት አማካኝነት በመደረጉ ክፍፍሉን አጧጡፎአል። ምእመናኑ ከወንጌል መልእክት በስተጀርባ በኅብረት ከመሰለፍ ይልቅ የተለያየ «የአመለካከት ጎራዎች» ባሉአቸው ቡድኖች የተዋቀሩ ነበሩ።  ቆሮንቶስ ምን ዓይነት እንደነበረች ለማወቅ ከፈለግህ ሮሜ 1፡18-32ን አንብብ። ጳውሎስ የሮሜን መልእክት በሚጽፍበት ጊዜ በቆሮንቶስ ነበር። በመሆኑም የዘረዘራቸውን ኃጢአቶች ሁሉ ሰመስኮቱ አሻግሮ በዓይኑ ሊያያቸው ይችል ነበር!  በእርግጥ በሰብአዊ ጥበብ የሚመኩ፥ ዓለማዊ አኗኗርን የተላበሱ ዕቡያን ሰዎች ሲኖሩ ችግሮች እንደሚከሰቱ የታወቀ ነው። ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንዲችሉ ለመርዳት ጳውሎስ በክርስቶስ የተደረገላቸውን ጥሪ በማሳሰብ መልእክቱን አሃዱ በማለት የዚህን ጥሪ ሦስት ጠቃሚ ገጽታዎች አመለከተ።  ቅዱሳን ለመሆን እንደተጠሩ (1ኛ ቆሮ. 1፡1-9)  ጳውሎስ በመጀመሪያ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረውን የርኵሰትን ጽኑ ችግር አጥብቆ ተቃወመ፥ ሆኖም ግን ስለ ችግሩ የተናገረው ምንም ነገር አልነበረም። በዚህ ፈንታ አዎንታዊ አቀራረብ ተጠቀመና እማኞች በክርስቶስ ስላላቸው የከበረና የተቀደሰ ስፍራ አሳሰባቸው። ከቁጥር 1-9 ባለው ውስጥ እግዚአብሔር ስለሚያያት ቤተ ክርስቲያን ገለጸ፥ ከቁጥር 10-31 ባለው ውስጥ ደግሞ ሰዎች ስለሚያዩአት ቤተክርስቲያን አብራራ። በኢየሱስ ክርስቶስ የያዝነው ስፍራ በዕለታዊ ኑሮአችን ተተግብሮ መታየት ያለበት መሆን ሲገባው፥ ብዙ ጊዜ ግን ይህን አናደርግም።  በኢየሱስ ክርስቶስ ከተደረገልን ቅዱስ ጥሪ የተነሣ ቤተ ክርስቲያን የሚኖሩአትን ባሕርያት ልብ በል።  በእግዚአብሔር የተለየች (1፡1-3)። በግሪክ ቋንቋ ቤተክርስቲያን ማለት ተጠርተው የወጡ ሰዎች» ማለት ነው። እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ሁለት አድራሻዎች አሉአት። መልክዓ ምድራዊ አድራሻ (“በቆሮንቶስኝ እና መንፈሳዊ አድራሻ (“በክርስቶስ ኢየሱስ ዘንድን። ቤተ ክርስቲያን የተዋቀረችው ከቅዱሳን፥ ማለትም በእግዚአብሔር «ከተቀደሱ» ወይም «ከተለዩ» ሰዎች ነው። ቅዱስ ማለት ከኖረው የተቀደሰ ሕይወት የተነሣ ሰዎች የሚያከብሩት የሞተ ሰው ማለት አይደለም። የለም፥ ጳውሎስ የጻፈው ሕያው ለሆኑ ቅዱሳን፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ካላቸው እምነት የተነሣ ለእግዚአብሔር ልዩ ፍስሐ እና ግልጋሎት ለተለዩ ሰዎች ነው።  በሌላ አባባል፥ ማንኛውም እውነተኛ አማኝ በእግዚአብሔር እና ለእግዚአብሔር ስለሆነ፥ ሁሉም አማኝ ቅዱስ ነው ማለት ነው።  አንድ ክርስቲያን ፎቶ አንሺ ጓደኛዬ «ስላነሣው» እንድ ቆንጆ ሠርግ አጫውቶኝ ነበር። ሙሽራዪቱና ሙሽራው ከቤተክርስቲያን ተያይዘው ወጥተው፥ ወደ ተዘጋጀላቸው የሙሽራ መኪናቸው በማምራት ላይ እያሉ ድንገት ሳይታሰብ ሙሽራዪቱ ባሏን ጥላ በመንገድ ዳር ቆሞ ወደነበረ መኪና ከነፈች! ሞተሩ እየሠራ ሰውየውም መሪውን እንደ ጨበጠ ነበርና ምስኪኑን ባል ባለበት «የጨው -ዓምድ» አድርገውት ተያይዘው ፈረጠጡ። «የፈርጣጩ መኪና» ነጂ ለካስ «በፈለገው ማንኛውም ጊዜ ሊያገኛት እንደሚችል ይፎክር የነበረ» የቀድሞ የወንድ ጓደኛዋ ኖሯል። በዚህም ሊገመት እንደሚቻለው ባል ጋብቻው ውድቅ ሆኖበት ቀረ።  ወንድና ሴት ተጋቢዎች እርስ በርስ የፍቅር ቃል ኪዳን ከተለዋወጡ በኋላ አንዳቸው ለሌላቸው የተለዩ ይሆናሉ፥ በመሆኑም ከጋብቻ ውጭ የሆነ ማንኛውም ግንኙነት ኃጢአት የሞላበት ተግባር ነው። ልክ እንደዚሁ ክርስቲያን ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍጹም የተሰጠ ነው፣ ለእርሱ እና ለእርሱ ብቻ የተለየ ነው። ከዚህም በላይ «የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ሁሉ ከሚጠሩት ጋር» (ቁ2)። የዓለም አቀፍ ኅብረት ማለትም የቤተ ክርስቲያን አካልም ነው፥ የረከሰ እና ታማኝ ያልሆነ አማኝ ኃጢአት የሚሠራው በጌታ ላይ ብቻ ሳይሆን፥ በክርስቲያን ወገኖቹም ላይ ነው።  በእግዚአብሔር ጸጋ ባለጠጎች የሆነች (1፡4-6)። ደኅንነት ከእግዚአብሔር የተሰጠ የጸጋ ስጦታ ነው፣ ይሁንና ስትድን ወዲያው መንፈሳዊ ስጦታዎችም ታድለውሃል። (ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ በምዕራፍ 12-14 በዝርዝር ያስረዳል)። የግሪኩ ቃል ባለጠጎች እንድትሆኑ የተደረጋችሁ የሚለውን በጣም ሀብታም ሰው ብሎ ይፈታዋል። በተለይ ቆሮንቶሳውያን በመንፈሳዊ ስጦታዎች ባለጠጋዎች ነበሩ (2ኛ ቆሮ. 8፡7)፥ ሆኖም ግን እነዚህን ስጦታዎች በመንፈሳዊ መንገድ አይጠቀሙባቸውም ነበር። እግዚአብሔር እኛን የመጥራቱ፥ የመለየቱና ባለጠጋ የማድረጉ እውነት የተቀደሰ አኗኗር እንድንኖር ሊያበረታታን ይገባል።  የኢየሱስን መገለጥ የምትጠባበቅ (1፡7)። ጳውሎስ ስለዚህ እውነት በምዕራፍ 15 የሚለው ብዙ አለው። አዳኛቸውን የሚጠባበቁ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን ከነቀፋ በላይ አድርገው መያዝ ይፈልጋሉ (1ኛ ዮሐ 2፡28-3፡3)።  በእግዚአብሔር ታማኝነት ላይ የምትደገፍ (1፡8-9)። የእግዚአብሔር ሥራ በእነርሱ ውስጥ የጸና (ቁ.6)፥ ደግሞም በቃሉ በኩል ለእነርሱ የጸና ነበር። ይህ ቃል የንግድ ልውውጥ ዋስትና ለመስጠት የሚያገለግል የሕግ ቃልን ያመለክታል። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የገባውን «ውል» እንደሚጠብቅና እስከ ፍጻሜው እንደሚያድነን  ዋስትና የሚሰጥ የመንፈስ ምስክርነት በውስጣችን፥ የቃሉ ምስክርነት ደግሞ በፊታችን አለን። ይህ ዋስትና ያለ ጥርጥር ለኃጢአት ማመካኛ አይደለም! ይልቁኑ ለሚያድግ የፍቅር፥ የመተማመን እና የታዛዥነት ግንኙነት መሠረት ነው።  ታዲያ፥ እነዚህ ታላላቅ እውነቶች በገሃድ እየታዩ፥ የቆሮንቶስ ጉባኤ እንዴት አድርጎ በዓለም እና በሥጋ ሊጠመድ ቻለ? ቆሮንቶሳውያን የተመረጡ፥ ባለጠጎች የተደረጉ እና የተደላደሉ ሰዎች ነበሩ። ለእግዚአብሔር ክብር የተለዩ ቅዱሳን ነበሩ ያሳዝናል፥ ተግባራቸው ከይዞታቸው የተለየ ሆነ።  ጳውሎስ ኅብረት የሚለውን ቃል በቁጥር 9 ላይ በመጥቀስ ሁለተኛውን የክርስቲያን ጥሪ ገጽታ አስተዋወቀ። ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

ቅዱሳን ለመሆን እንደተጠሩ (1ኛ ቆሮ. 1፡1-9) Read More »

መግቢያ

መቅድም  በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የነበሩ ክርስቲያኖች በነበሩአቸው መንፈሳዊ ስጦታዎች እና እውቀት ይታበዩ ነበር። እንዲህም ሆኖ በግል ሕይወታቸው ውስጥ እና በጉባኤያቸው መካከል ጉልህ ስሕተት ነበረባቸው።  ጳውሎስ የሚያስፈልጋቸው እውነተኛ መንፈሳዊ ጥበብ መሆኑን ደርሶበታል። ይህም የዓለም ጥበብ ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ብቻ የሚፈልቅ ጥበብ ነው።  እኛም ዛሬ የሚያስፈልገን ይኸው ጥበብ ሲሆን የሚገኝበትን እንድናውቅ ይህ መልእክት ጥሩ መነሻ ይሆነናል። ሃይማኖታዊ መሪነታችን «ለቀዳሽ አወዳሾች» ወጥመድ እንዳያደርገን፥ ጳውሎስ ስለ ወንጌል መልእክት እና አገልግሎት እንዴት ልባም መሆን እንደሚገባን ይናገረናል። በአምልኮአችን ምን ዓይነት ሥርዓት ልንይዝ እንደሚገባና መንፈሳዊ ስጦታዎቻችንን እንዴት እንደምናውቃቸውና እንደምናዳብራቸው ይነግረናል። እግዚአብሔርን ለማክበርና ከዓለም እድፈት ለማምለጥ ይቻለን ዘንድ እንዴት ራሳችንን በንጽሕና መጠበቅ እንዳለብንም ይነግረናል።  በዚህ አጭር የገለጣ ጥናት፥ አንደኛ ቆሮንቶስን በመሰለ ሰፊ መልእክት ውስጥ ያሉትን ዝርዝር ጠጣር አሳቦች ሁሉ ማጠናቀቅ አንችልም። የእኔ ዓላማ የመልእክቱን አንኳር ትምህርቶች ማብራራት እና ለሕይወታችንና ለቤተ ክርስቲያኖቻችን ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። የእርሱን መንፈሳዊ ጥበብ እንድንቀበል እና በግል ሕይወታችንም ተግባራዊ ማድረግ እንድንችል ጌታ ይርዳን።  ዋረን ደብልዩ ዌርዝቢ  በቆሮንቶስ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን መሠረተ  አቋም  ጳውሎስ በ 50 ዓ.ም መኸር ወቅት አካባቢ ወደ ቆሮንቶስ መጥቶ 18 ወራት በዚያው በመቆየት (የሐዋ. ሥራ 18፡1-17) ቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረተ። ከዚያም ቀጥሎ ወደ ኤፌሶን ተጓዘ (ቁ 18– 19)።  በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ችግሮች አሉ በሚል የደረሰው ዜና ዛሬ በእጃችን ያልገባውን መልእክት እንዲጽፍ አነሣሣው (1ኛ ቆሮ. 5፡9)። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን መካከል የከፉ ችግሮች ስለመኖራቸው ከቀሎዔ ቤተሰቦች የመጣው ተጨማሪ መልእክት (1ኛ ቆሮ. 1፡1ህ የሚያመለክተው፥ ይህ «የጠፋ ደብዳቤ» የጳውሎስን ፍላጎት እንዳልፈጸመለት ነበር። ከዚያ በኋላ ቤተክርስቲያኒቱ፥ ስለ ቤተ ክርስቲያን ልምምድ እና ዶክትሪን ጥያቄዎችን ያዘለ ደብዳቤ አስይዛ አንድ ልዑክ ወደ ጳውሎስ ላከች (1ኛ ቆሮ. 7፡1፤ 16፡17–18)።  በዚህ ደብዳቤ ስለደረሰው የከፋ ዜና ምላሽ፥ ጳውሎስ፥ 1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ሲባል የምናውቀውን ደብዳቤ ጻፈ። የጻፈውም በ57 ዓ.ም. አካባቢ በኤፌሶን ሆኖ ነበር።  በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የጳውሎስን ሐዋሪያዊ ሥልጣን የማይቀበል ቡድን ተነሥቶ ነበር። በመሆኑም ሐዋርያው ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ «ኦስቸኳይ ጉብኝት» አደረገ፥ ይሁን እንጂ ውጤቶቹ አርኪ አልነበሩም (2ኛ ቆሮ. 2፡1፤ 12፡14፤ 13፡1)። ከዚያ በኋላ «የሰላ ደብዳቤ» (2ኛ ቆሮ. 7፡8-12) ጽፎ በቲቶ አማካኝነት ላከባቸው።  ጳውሎስ ቲቶን በጢሮአዳ አግኝቶ (2ኛ ቆሮ. 2፡12-13፤ 7፡6-16) ቤተ ክርስቲያን የጳውሎስን ትእዛዝ ስለ መቀበሏና የተቃዋሚዎቹን መሪም እንደቀጣች መልካም ዜና ሰማ። ከዚያ በኋላ ጳውሎስ 2ኛ ቆሮንቶስን ጻፈ።  የ 1ኛ ቆሮንቶስ አስተዋጽኦ  1. ሰላምታ- 1፡1-3  2. ግሣጼ፡- በቤተ ክርስቲያን ስለነበረው ኃጢአት ዘገባ- 1፡4-6፡20  ሀ. መከፋፍል በቤተ ክርስቲያን – 1፡4-4፡21  ለ. ፍርድ በቤተክርስቲያን ውስጥ –  5፡1-13  ሐ. በችሎት ፊት መፋረድ (መካሰስ) – 6፡1-8  መ. በዓለም ውስጥ መርከስ – 6፡9-20  3. መመሪያ፡- ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ – 7፡1-16፡12  ሀ. ጋብቻ 7፡1-40  ለ. ለጣዖት ስለተሠዋ ምግብ– 8፡1-10።3  ሐ. የቤተ ክርስቲያን ሥልጣናዊ አመራር- 11፡1-34  መ. መንፈሳዊ ስጦታዎች– 12፡1-14፡40  ሠ. ትንሣኤ-15፡1-58  ረ የገንዘብ መዋጮ – 16፡1-12  4. መደምደሚያ – 16፡13-24 ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

መግቢያ Read More »

የብሉይ ኪዳን ጥናት ክለሳ

የብሉይ ኪዳንን የተለያዩ መጻሕፍት ስናጠና ቆይተናል። የእያንዳንዱ መጽሐፍ ጸሐፊ ማን እንደሆነ፥ የመጽሐፉን ታሪካዊ ሥረ-መሠረት፥ ዓላማና ዐበይት ትምህርቶች ተመልክተናል። እያንዳንዱን መጽሐፍ ያጠናነው በግል ስለሆነ በመጨረሻ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሙሉ በአንድነት እንዴት እንደተዋሀዱ ለመረዳት ጠቃሚ የሆነውን የመጻሕፍቱን ክለሳ መመልከት አስፈላጊ ነው። የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) በብሉይ ኪዳን የሚገኙ መጻሕፍት ስንት ናቸው? ለ) የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ዋና ዋና ክፍሎች ጥቀስና በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙትን መጻሕፍት ዘርዝር። 1. ፔንታቱክ (አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት) ብሉይ ኪዳን በአራት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላል። የመጀመሪያው ዋና ክፍል ፔንታቱክ ወይም አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት የሚባለው ሲሆን፥ የብሉይ ኪዳንን የመጀመሪያ አምስት መጻሕፍት የያዘ ነው። እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረጋቸውን ቃል ኪዳኖች ስለሚገልጹ በብዙ አንጻር በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ መጻሕፍት ሁሉ እጅግ አስፈላጊ መጻሕፍት ናቸው። እነዚህ ቃል ኪዳኖች ብሉይና አዲስ ኪዳን የተመሠረቱባቸው መሠረች ናቸው። ከፔንታቱክ መጻሕፍት ግማሽ ያህሉ ታሪካዊ መጻሕፍትን የያዘ ነው፡- (ዘፍጥረት፥ ዘጸአት፥ ዘኁልቁ)። ቀሪው ግማሽ ያህል ደግሞ ይኖሩበት ዘንድ እግዚአብሔር ለአይሁድ የሰጣቸውን ቃል ኪዳንና ሕግጋት የያዘ ነው (ዘጸአት፥ ዘሌዋውያን፥ ዘዳግም)። ታሪክ የሚጀምረው ስለ ፍጥረታት አጀማመር የሚናገሩ ታሪኮችን በያዘው በኦሪት ዘፍጥረት ነው። ይህ መጽሐፍ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከአንድ ሰው፥ ማለትም ከአብርሃም በመጀመር፥ በግብፅ ታላቅ ሕዝብ እስኪሆኑ ድረስ እንዴት እንደበዙ ያሳየናል። የኦሪት ዘጸአት የመጀመሪያ ግማሽ ክፍል፥ እግዚአብሔር ሕዝቡ በግብፅ የነበሩበትን ቀንበር ለመስበርና ነፃ ለማውጣት በኃይልና በሥልጣን እንዴት እንደሠራ ያሳየናል። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ወዳደረገበት ወደ ሲና ተራራ መራቸው። የመጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል ይህን ቃል ኪዳን በዝርዝር ያሳየናል። ቃል ኪዳኑ በቅድመ-ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ስለነበር ለሕጉ በመታዘዝ ሲኖሩ እግዚአብሔር እንደሚባርካቸው፥ ካልታዘዙት ደግሞ እንደሚቀጣቸው ተናግሮ ነበር። የቃል ኪዳኑ ማዕከል በመካከላቸው የእግዚአብሔርን ዙፋን መገኘት የሚያመለክተው የቃል ኪዳኑ ታቦት የነበረበት የመገናኛው ድንኳን ነበር። እስራኤላውያን የሲናን ተራራ ከመልቀቃቸው በፊት ዕቅዱ በእግዚአብሔር የተነደፈውን የመገናኛ ድንኳን ሠሩ። ኦሪት ዘሌዋውያን፥ እስራኤላውያን በእግዚአብሔር የተመረጡ ቅዱስ ሕዝብ እንደመሆናቸው መጠን እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚያሳዩ ሕግጋትን ይዟል። እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ለማምለክ ሊያቀርቧቸው ስለሚገቡ የተለያዩ መሥዋዕቶች ይገልጻል። ሕዝቡ እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ነገሮች የሚያስታውሱባቸው የተለያዩ የሃይማኖት በዓላትን ይደነግጋል። ካህናት ደግሞ ሕዝቡን በተቀደሰ አምልኮ መምራት ይችሉ ዘንድ እንዴት መኖር እንዳለባቸው ይዘረዝራል። አይሁድ ሁሉ በየዕለቱ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሁኔታ እንዴት እንደሚኖሩና የእግዚአብሔርን በረከቶች ለማግኘት እንዴት እርግጠኛች መሆን እንደሚችሉ ግልጽ መመሪያዎችን ይሰጣል። ኦሪት ዘኍልቍ የሚያተኩረው የእግዚአብሔር ሕዝብ በተስፋዪቱ ምድር ያሉ ጠላቶቻቸውን ለማሸነፍ በእግዚአብሔር መታመን ስላቃታቸው በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት መንከራተታቸውን በሚናገረው አሳዛኝ ታሪክ ላይ ነው፡፡ አንድ ትውልድ ባለመታዘዙ ምክንያት ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን የሚናገር ታሪክ ነው። ኦሪት ዘኁልቁ የሚጠናቀቀው አይሁድ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ የሚገኘውን ምድር ወርረው በማሸነፍ እግዚአብሔር ወደሰጣቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት እንደተዘጋጁ በመናገር ነው። በኦሪት ዘዳግም ውስጥ ሙሴ በሲና ተራራ የተሰጡትን ሕግጋት ለአዲሱ ትውልድ በድጋሚ ሲናገር እንመለከታለን። ሙሴ የተስፋይቱን ምድር ከሩቅ አሻግሮ ቢመለከትም እንኳ ወደ ከነዓን ሳይገባ ሞተ። የፔንታቱክ ታሪክ የሚጀምረው እግዚአብሔር ምድርን ከፈጠረበት ካልታወቀ ጊዜ ሲሆን፥ የሚደመደመው ደግሞ በ1400 ዓ.ዓ. ገደማ ነው።  2. የታሪክ መጻሕፍት ከመጽሐፈ ኢያሱ እስከ አስቴር ድረስ ያሉት የሚቀጥሉት አሥራ ሁለት መጻሕፍት በብሉይ ኪዳን ዘመን የተፈጸመውን የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ የሚናገሩ ናቸው። ይህም ከነዓን ድል ከሆነችበት ከ1400 ዓ.ዓ. ጀምሮ፥ ከምርኮ መልስ የኢየሩሳሌም ቅጥር እስከተሠራበት እስከ 400 ዓ.ዓ. ድረስ የነበረውን ታሪክ ያጠቃልላል።  ኢያሱ ስለ ከነዓን ድል መሆን ይናገራል። የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ላይ በነበራቸው እምነት ምክንያት አብዛኞቹን የከነዓንን ምድር ከተሞች ለማሸነፍና በዚያ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ማንበርከክ ችለው ነበር። መጽሐፈ መሳፍንት የሚናገረው ግን እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ፍጹም ታዝዘው ከነዓናውያንን ባለማጥፋታቸው ምን እንደ ተፈጸመ ነው። አይሁድ ከከነዓናውያን ጋር ጎን ለጎን በመኖራቸው፥ ወዲያውኑ በባዕድ አምልኮ ኃጢአት ወደቁ። እግዚአብሔር በባርነት ይገዟቸው ዘንድ ለተለያዩ ከነዓናውያን መንግሥታት አሳልፎ በመስጠት ቀጣቸው። እስራኤላውያን ንስሐ በሚገቡበትና ወደ እግዚአብሔር በሚጮሁበት ጊዜ ከጠላቶቻቸው የሚታደጉአቸው የተለያዩ ተዋጊዎችን (መሳፍንትን) ያስነሣላቸው ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ወደ ቀድሞው የኃጢአት መንገዳቸው ይመለሱና እግዚአብሔር ይቀጣቸው ነበር። በዘመነ መሳፍንት ለእግዚአብሔር በታማኝነት የቆሙ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። ለዚህ ምሳሌ ከሚሆኑት መካከል ሩትና ቦዔዝ ይገኛሉ። ለእግዚአብሔር ተስፋ ታማኞች ሆነው በመቆየታቸው በእስራኤል ላይ ከነገሡ ነገሥታት ሁሉ በላይ የሆነው የንጉሥ ዳዊት አያቶች እንዲሆኑ እግዚአብሔር ፈቀደ። 1ኛ ሳሙኤል የሚያስተዋውቀን ከመሳፍንት ወደ ነገሥታት ዘመን የተደረገውን የሽግግር ወቅት ነው። የመጨረሻዎቹ ሁለት መሳፍንት ዔሊና ሳሙኤል ነበሩ። ይህ ማለት የግል ነፃነትን ማጣትና ከፍተኛ ግብር መገበር ማለት ቢሆንም እንኳ ሕዝቡ እንደቀሩት አሕዛብ ንጉሥ እንዲኖራቸው ፈለጉ። ሳኦል የእስራኤል ሕዝብ የመጀመሪያ ንጉሥ ነበር። ሳኦል አጀማመሩ መልካም ቢሆንም፥ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ባለመጠበቁ፥ መንግሥቱ ከእርሱ ተወስዳ ለዳዊት ተሰጠች። የ1ኛ ሳሙኤል አብዛኛው ታሪክ የያዘው ሳኦል፥ ዳዊት ንጉሥ እንዳይሆን ባደረበት ቅንዓት እርሱን ለመግደል ያደረጋቸውን የተለያዩ ሙከራዎች ነው። 2ኛ ሳሙኤል በእስራኤል ላይ ከነገሡት ነገሥታት ሁሉ በላይ የሆነውን የንጉሥ ዳዊትን ታሪክ ይናገራል። ዳዊት እግዚአብሔርን ይወድ ነበር። ምንም እንኳ በኃጢአት ቢወድቅም፥ ዝርያዎቹ የእስራኤልን ዙፋን እንደሚቆጣጠሩ የተስፋ ቃል በመስጠት እግዚአብሔር አከበረው። ይህም የዳዊት ልጅ በሆነው በመሢሑ በኢየሱስ ሙሉ ለሙሉ ይፈጸማል። 1ኛ መጽሐፈ ነገሥት የነገሥታትን ታሪክ መናገሩን ይቀጥላል። የሚጀምረው በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ የላቀ ጥበበኛ በነበረው በዳዊት ልጅ በሰሎሞን ነው። ዳሩ ግን ሰሎሞን ለሴቶች የነበረው ፍቅር ወደ ጣዖት አምልኮ መርቶት፥ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንዲቀበል አደረገው። ከሰሎሞን ሞት በኋላ እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት የሰሜኑን ክፍል የእስራኤል መንግሥትና የደቡቡን የይሁዳ መንግሥት ተብሎ እንዲከፈል አደረገ፡፡ የቀረው 1ኛ እና 2ኛ መጽሐፈ ነገሥት እግዚአብሔር ሰሜኑ የእስራኤልን መንግሥት ወደ አሦር፣ ደቡቡ የይሁዳን መንግሥት ወደ ባቢሎን በምርኮ እንዲወሰድ ከማድረጉ በፊት የነበሩትን ነገሥታት ታሪክ በአጭሩ ያብራራል። 1ኛ- 2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ከዳዊት እስከ ምርኮ ድረስ ያለውን የደቡቡ የዳዊትን ዝርያ የሆኑ ነገሥታት ታሪክ በድጋሚ ይተርካል። እነዚህን ጊዜያት ከታሪክ አቅጣጫ ከመመልከት ይልቅ አንድ ንጉሥ እግዚአብሔርን በሚያከብርበት ጊዜ መንግሥቱና ሕዝቡ እንደሚባረክ። ንጉሡ ለእግዚአብሔርና ለሕግጋቱ በማይታዘዝበት ጊዜ መንግሥቱና ሕዝቡ እንደሚፈረድበት እነዚህ መጻሕፍት ይናገራሉ። መጽሐፈ ዕዝራ፥ ነህምያና አስቴር የይሁዳ ሕዝብ ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ ስለተፈጸሙ ድርጊቶች የሚናገሩ ናቸው። መጽሐፈ ዕዝራ የሚገልጸው ከባቢሎን ወደ ምድራቸው ስለተመለሱት ሁለት የመጀመሪያ የአይሁድ ቡድኖች ጉዳይና ስለ ቤተ መቅደሱ መሠራት ነው። ነህምያ ደግሞ ወደ ምድሪቱ ስለተመለሰ ሌላ ቡድን ስለ ኢየሩሳሌም ቅጥር መሠራት ይናገራል። መጽሐፈ አስቴር በንጉሥ አርጤክስስ ዘመን እግዚአብሔር አይሁድን በአሕዛብ ፈጽመው ከመደምሰስ እንዴት እንደጠበቃቸው ይናገራል። ከእዚህ አሥራ ሁለት መጻሕፍት በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ትረካ ያበቃል። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ለመኖር እስከመጣበት ጊዜ ድረስ 400 የጸጥታ ዘመናት ነበሩ። የእነዚህን የጸጥታ ዘመናት ታሪክ ሌሎች መጻሕፍት የዘገቡት ቢሆንም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለ እርሱ ምንም አይናገርም።  3. የግጥምና የጥበብ መጻሕፍት በብሉይ ኪዳን ውስጥ እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ መጻሕፍት መካከል አምስቱ የግጥምና የጥበብ መጻሕፍት ይገኛሉ። እነርሱም መጽሐፈ ኢዮብ መዝሙረ ዳዊት መጽሐፈ ምሳሌ፥ መጽሐፈ መክብብና መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ናቸው። መዝሙረ ዳዊት የአይሁድ የአምልኮ መዝሙራት መጽሐፍ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ መዝሙራት የተጻፉት ለእግዚአብሔር ምስጋናን በሚገልጡና እግዚአብሔር ክፉዎችን በመቅጣት ጻድቃንን እንደሚባርክ በሚያስረዱ መንገዶች ነው። ሌሎቹ መጻሕፍት የጥበብ መጻሕፍት በመባል ይታወቃሉ፤ ምክንያቱም አይሁድ እርሱን በሚያስከብር መንገድ እንዲኖሩ እግዚአብሔር ስለሰጣቸው ጥበብና በጊዜው ይቸገሩባቸው ስለነበሩ አንዳንድ የፍልስፍና ጥያቄዎች የሰጣቸውን መልስ ስለሚያስረዱ ነው። መጽሐፈ ኢዮብ የሚያስተምረን ጻድቅ ሰው ከቶ ባልታወቀ ምክንያት መከራን ቢቀበል እንኳ በእግዚአብሔር ታምኖ መከራውን በትዕግሥት ሊቀበለው እንደሚገባ ነው። መጽሐፈ ምሳሌ ደግሞ ማንኛውም የሕይወት ሁኔታ ውስጥ በጥበብ መኖር እንዴት

የብሉይ ኪዳን ጥናት ክለሳ Read More »

አራት መቶ የጸጥታ ዓመታት

የብሉይ ኪዳን ታሪክ የሚደመደመው በመጽሐፈ ነህምያ ሲሆን፥ ትንቢታዊ መልእክቶች የሚጠቃለሉት ደግሞ በትንቢተ ሚልክያስ ነው። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለእስራኤላውያን የሚሰጠው መልእክት ተፈጸመ። እግዚአብሔር ኤልያስንና መሢሑን እንዲጠባበቁ ለእስራኤላውያን መልእክት ከሰጣቸው በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚያክሉት ሌላ ተጨማሪ መልእክት አልሰጣቸውም። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ከሚልክያስ ዘመን ጀምሮ (400 ዓ.ዓ.) ኢየሱስ እስከ መጣበት (5 ዓ.ዓ.) ድረስ የነበረውን ጊዜ «400 የጸጥታ ዓመታት» ብለው የሚጠሩት ስለዚህ ነበር። አይሁድ የአዋልድ መጻሕፍት (አፖክሪፋ) በመባል የሚታወቁ ሌሎች ተጨማሪ መጻሕፍት የጻፉ ቢሆንም፥ እነዚህ መጻሕፍት ከብሉይ ኪዳን 39 መጻሕፍት ጋር እኩል እንዳይደሉ ተገንዝበው ነበር።  እነዚህ አራት መቶ ዓመታት ለአይሁድ እጅግ ወሳኝ ስለነበሩ በእነዚህ ዓመታት ምን እንደተደረገ ማወቅ አስፈላጊ ነው። እነዚህን አራት መቶ ዓመታት የበለጠ በተረዳን ቁጥር፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተፈጸሙትን አንዳንድ ነገሮች በይበልጥ እንረዳለን። ከጊዜና ከቦታ እጥረት የተነሣ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ጥቂት አሳቦች ብቻ ተጠቃልለው ቀርበዋል። 1. የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ግዛቶች (539-331 ዓ.ዓ.)፡- የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በተደመደመበት ጊዜ፥ የፋርስ መንግሥት ነገሥታት አይሁድን ራቅ ብሎ እንደሚገኝ የግዛታቸው ክፍለ ሀገር ይዙዋቸው ነበር። በፖለቲካ ረገድ ከታላቁ የፋርስ የሥልጣን ማዕከል እጅግ ርቀው ይገኙ ስለነበር የፋርስ መንግሥት አይሁዳውያንን የራሳቸውን ጉዳይ እንዲያከናውኑ ትተዋቸው ነበር። ኢየሩሳሌም ከፍተኛ የንግድ ዕከልና የጳለስጢን ዋናዋ የፖለቲካ ሥልጣን ቁንጮ ነበረች። በፋርስ የንጉሠ ነገሥት ግዛት የሥልጣን ዘመን ውስጥ፥ የኋላ ኋላ በአዲስ ኪዳን ዘመን ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ ብዙ ነገሮች ተፈጽመዋል።  ሀ. አይሁድ በዓለም ዙሪያ ሁሉ መሠራጨታቸውን ቀጠሉ። አብዛኛዎቹ አይሁድ የሚኖሩት ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ውጭ ነበር። እንደ ሀገራችን የጉራጌ ብሔር አባሉች የተዋጣላቸው ነጋዴዎች በመሆን፥ በጥንቱ ዓለም በነበሩ በአብዛኛዎቹ ከተሞች ይገኙ ነበር። ይህ በየስፍራው ተበትኖ የመኖር ነገር በሚቀጥለው የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛትም እየጨመረ ሄዶ ነበር። በአዲስ ኪዳን ዘመን በግልጽ እንደሚታየው ጳውሎስ ወንጌልን ይዞ በተዘዋወረባቸው ስፍራዎች ሁሉ፥ በቅድሚያ ይሰብክ የነበረው የተበተኑት አይሁድ ወደሚሰበሰቡበት ምኩራብ በመሄድ ነበር። ለ. የአይሁድ ዋና ቋንቋ ተለወጠ። አብዛኛዎቹ አይሁድ በእስራኤል ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ሳይቀሩ አራማይክ የተባለውን የንግድ ቋንቋ ይናገሩ ነበር። የብሉይ ኪዳን ቋንቋ የሆነውን ዕብራይስጥ ይጠቀሙ የነበሩት በአምልኮ ፕሮግራም ብቻ ነበር። ለምሳሌ የእግዚአብሔር ቃል በሚነበብበት ጊዜ ዕዝራ የተረጐመበት አንዱ ምክንያት ይህ ነበር (ነህምያ 8፡7-8)። ኢየሱስ አገልግሎቱን የሰጠው በአራማይክ ቋንቋ ነው።  ሐ. የምኩራቦች አጀማመር፡- የአይሁድ ማኅበረሰብ ባሉበት ስፍራ ሁሉ፥ የማኅብረሰብ ማዕከልና ምኩራብ የተባለ የአምልኮ ስፍራ ይሠሩ ጀመር። በእነዚህ ምኩራቦች ውስጥ መሥዋዕት ባያቀርቡም እንኳ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ይሰበሰቡ ነበር። እነዚህ ምኩራቦች በኋላ የጣዖት አምልኮ የሰለቻቸው አሕዛብ ስለ እውነተኛው አምላክ ለመስማት የሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች ሆኑ። ጳውሎስና ሌሎች አገልጋዮች ወንጌልን ለመስበክ ወደ እነዚህ ስፍራዎች እንደሄዱ እነዚህ አሕዛብ ፈጥነው በክርስቶስ በማመን ተለወጡ፡፡  መ. የካህናት ሥልጣን እየጨመረ መምጣት፡- ገና ከመጀመሪያው በኢየሩሳሌም የነበረው የአይሁድ ማኅበረሰብ አንድ የፖለቲካ (ለምሳሌ ዘሩባቤል)፥ ሌላ የሃይኖት (ለምሳሌ ታላቁ ካህን ኢያሱ) መሪ የነበረው ቢሆንም፥ ካህናቱ የፖለቲካና የሃይማኖት መሪነቱን ጠቅልለው ለመያዝ ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር። ይህም ካህናቱ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ረገድ ከመምራት ይልቅ በፖለቲ ጉዳይ ላይ በማተኮር በሥልጣን እንዲባልጉ አደረጋቸው። ሠ. “ጸሐፍት” የተባሉ አይሁድ ያሉብት መደብ ፈጠር፡- ጸሐፍት በሕግ እውቀትና ትርጓሜ ሥራ የተካኑ ነበሩ፡፡ እነርሱም የእስራኤል ቁልፍ የሕግ መምህራን ሆኑ፡፡ ሕዝቡ የብሉይ ኪዳንን ተዛዛት እንዳይጥሱ ለማረጋገጥ በመፈለጋቸው፣ ሕዝቡ ለተጻፉት ሕግጋት አንታዘዝም እንዳይሉ ለመጠበቅ ሲሉ እንደ “አጥር” የሚሆኑ ሌሎች ሕግጋትን ጨመሩ፡፡ በኋላ ለእነዚህ ሕግጋት ወግ ከመጀመሪያው የእግዚአብሔር ሕግ የበለጠ ስፍራ ይሰጣቸው ጀመር፡፡ ይህም ወዲያውኑ ይሑዲነትን ልባዊ ሳይሆን ሕጋዊነት ወደሚንጸባረቅበት “አድረግ፣ አታድርግ” የአይሁድ የሃይማኖት ሥርአት ለወጠው፡፡ ጸሕፍትም በተራቸው የፖለቲካ መሪዎች እስኪሆኑ ድረስ በስልጣን መጥቀው ሄዱ፡፡ በመጨረሻም ጸሐፍት፣ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሌዎች “ሸንጎ” የተባል ጉባኤ በማቋቋም የአይሁድን የአስተዳደር አካል መሠረቱ፡፡  ረ. የሳምራውያንና የአይሁድ ጥላቻ አጀማመር፡- እስራኤላውያን በአሦር እጅ በወደቁና በተማረኩ ጊዜ ከሌላ ስፍራ አሕዛብን ወደ እስራኤል በማምጣት ከቀሩት አይሁድ ጋር ለመቀላቀል እንደሞከሩ ታስታውሳለህ፡፡ አይሁድና አሕዛብ በመጋባታቸው ምክንያት የተወለዱት ልጆች ሳምራውያን ተባሉ፡፡ ከአይሁድ ወደባቢሎን ተወስደው የነበሩት አይሁድ ወደ እስራኤል በተመለሱ ጊዜ የእስራኤል ሃይማኖት ከይሁዲነትና ከአሕዛብ የጣዖት አምልኮ ጋር ተደባልቆ ነበር። እነዚህ ሳምራውያን ከአይሁድ ጋር ተባብረው ቤተ መቅደሱን ለመሥራት በመጡ ጊዜ አይሁድ ተቃወሙ። አምልኮአቸው ንጹሕ ሆኖ እንዲቆይ ይፈልጉ ነበር። ይህም ሳምራውያንን አስቆጣቸውና የአይሁድ ጠላቶች እንዲሆኑ አደረጋቸው። ቆየት ብለው ሳምራውያን ከአይሁድ ተለዩ። ገረዚም በተባለ ተራራ ላይ የራሳቸውን ቤተ መቅደስ ሠሩ። ከአይሁድ የአምልኮ ሥርዓት ጋር የሚመሳሰል የራሳቸው የአምልኮ መዋቅር አበጁ። በተቀዳሚ አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት የያዙ የራሳቸው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ነበሯቸው። ይህም አይሁድን እጅግ አስቆጥቷቸው ስለነበር በነጻነታቸው ጊዜ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሳምራውያንን ገደሉ። በአይሁድና በሳምራውያን መካከል የነበረው ይህ ጠላትነት፥ በአዲስ ኪዳን ዘመን ኢየሱስ በሰማርያ ሲያልፍና በተለይ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ሲነጋገር ደቀ መዛሙርቱ አይተው በመደነቃቸው ይስተዋላል (ዮሐንስ 4)።  ሰ. ምሁራን የአይሁድ መሠረታዊ ትምህርቶች በአንዳንድ መንገዶች የፋርስ ሃይማኖት ተጽዕኖ አድሮባቸዋል ብለው ያስባሉ። በፋርስ ዘመን የፋርስ ሰዎች ያደርጉት እንደነበረው አይሁዶች በመለኮታዊ ፍርድ፥ በሙታን ትንሣኤ፥ በአጋንንትና በመላእክት ሕልውና፥ ወዘተ. ላይ ያተኩሩ ነበር።  2. የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛት (331-142 ዓ.ዓ.) የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛት በታላቁ እስክንድር መሪነት፥ በዓለም ላይ እስከዚያ ዘመን ድረስ ተነሥተው ከነበሩ መንግሥታት ሁሉ በላቀ ሁኔታ ተስፋፍቶ ነበር። የፋርስን የንጉሠ ነገሥት ግዛት በሙሉ ከመጠቅለል አልፎ፥ ወደ ታች ወደ ግብፅና ሕንድ ድረስ ተስፋፋ። በጥንት ታሪክ ለመጀመሪያው ጊዜ አንድ የአውሮፓ አገር ግዛቱን እስከ ትንሹ እስያ ድረስ በማስፋፋት፥ በአንዳንድ ረገድ ከነበረው ተመሳሳይነት በስተቀር በወረራቸው ሕዝቦች ላይ በእጅጉ የተለየ ባህል አመጣ። ሆኖም ታላቁ እስክንድር የፋርስን መንግሥት መዋቅርንም ሆነ የክልል መንግሥታት አደረጃጀትን ለመደምሰስ አልሞከረም። ታላቁ እስክንድር በዘመኑ የታወቁ የዓለም ክፍሎችን በሙሉ ወርሮ ከያዘ በኋላ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ገና በወጣትነት ዘመኑ በ323 ዓ.ዓ. ሞተ። በ301 ዓ.ዓ. የታላቁ እስክንድር ጦር ሜጀር ጄኔራሎች እያንዳንዳቸው አንዳንድ ከፍል በመያዛቸው መንግሥቱ ለአራት ተከፈለ። በይሁዳ ላይ ተጽዕኖ አሳድረው የነበሩት ሁለቱ መንግሥታት ግብፅንና ሊቢያን ይዞ የነበረው የፕቶሎሜካዊ ንጉሠ ነገሥት ግዛትና ሶርያና ፋርስን ተቆጣጥሮ የነበረው የሲሉሲድ ንጉሠ ነገሥት ግዛት ነበሩ። በእነዚህ ሁለት የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛቶች መካከል ወዳጅነት አልነበረም። እነዚህ ሁለት መንግሥታት ጳለስጢናን ለመቆጣጠር በመምከር ያለማቋረጥ ይዋጉ ነበር። ይህ ማለት አይሁድ ያለማቋረጥ እርስ በርሳቸው በሚጋጩና አብረዋቸው እንዲምቱ በሚጠይቋቸው ባዕዳን ሠራዊት ይጠቁ ነበር ማለት ነው። ከ320-200 ዓ.ዓ. ፕቶሎሚዎች ጳለስጢናን ተቆጣጠሩ። በይሁዳ ይኖሩ የነበሩትን አይሁድ እንደፈለጋቸው እንዲኖሩ ለቀቋቸው። በዚህ ጊዜ የአይሁድ ገዢዎች ካህናት ነበሩ። ከ200-142 ዓ.ዓ. ሲሉሲዶች ጳለስጢናን ተቆጣጠሩ። ከፍተኛው ትኩረታቸው አይሁድ የግሪክን ባህል እንዲለምዱ ማድረግ ነበር። ቀረጥ እንዲከፍሉ አይሁድን አስገደዷቸው። በጭካኔ ከሁሉ የከፋው መሪ፥ ከ175-164 ዓ.ዓ. የገዛው አንቲዩከስ 4ኛ ኤፒፋነስ የተባለው ነው። አይሁድ የጣዖት አምልኮ ያካትት የነበረውን የግሪኮችን ባህል እንዲለማመዱ ለማስገደድ ሞከረ። በኃላፊነት ላይ የነበረውን የአይሁድ ሊቀ ካህን አባርሮ የግሪክን ባህል ለመቀበል ይፈልግ የነበረውን የራሱን አይሁዳዊ ሊቀ ካህን በሕዝቡ ላይ ሾመ። ከግብፅ ጋር ይዋጋ ለነበረው ጦሩ ለመክፈል በቤተ መቅደስ የነበረውን ገንዘብ ሁሉ ወሰደ። ሮማውያን ግብጽን ወርሮ እንዳይዝ በከለከሉት ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። በቤተ መቅደስ ውስጥ ይቀርብ የነበረው መሥዋዕት ሁሉ እንዲቆም በማድረግና በመሠዊያው ላይ አሳማ በመሠዋት መሠዊያውን አረከሰው። ዚዩስ ለተባለው የግሪክ ጣዖት መሥዋዕት ማቅረቢያ የሚሆን መሠዊያ በማሠራት ለዚዩስ መሥዋዕትን እንዲያቀርቡ አዘዘ። (በዳንኤል 11፡31-36 ስለዚህ ዘመን የተነገረውን ትንቢት ተመልከት)። ከ167-164 ዓ.ዓ. ለሦስት ዓመታት በቤተ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ማንኛውም መሥዋዕት ቆመ፡፡  ይህ የአንቲዩከስ ተግባር አይሁድን ለዓመፅ አነሣማቸው፡፡ መቃብያን ተብለው ይጠሩ በነበሩ በአንድ ካህንና በሁለት ልጆቹ መሪነት አይሁድ በመካከላቸው የነበረውን የግሪክ ባህል መስፋፋት

አራት መቶ የጸጥታ ዓመታት Read More »

የትንቢተ ሚልክያስ ዐበይት ትምህርቶች

1. ለቃል ኪዳኑ ሕግ መታዘዝ በማይኖርበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የገባነውን ቃል ኪዳን አንፈጽምም። ዳሩ ግን የገባነውን ቃል ኪዳን የምንፈጽመው መታዘዛችን ከንጹሕ ልብና ከትክክለኛ ዝንባሌ ሲሆን ነው። ለእግዚአብሔር የሚቀርብ እውነተኛ አምልኮ ትክክለኛ ድርጊቶችን (ተገቢ የሆኑ ሥርዓቶች) የሚያካትት ብቻ መሆን የለበትም። ነገር ግን ለእግዚአብሔር ከሚገዛ ልብ የሚመነጭ፥ ለእግዚአብሔር ሕግ የሚታዘዝ፥ ከኃጢአት የነጻ፥ ከቤተሰብና ከጎረቤቶች ጋር ትክክለኛ በሆነ ግንኙነት መኖርን ጭምር የሚያጠቃልል ነው።  የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰዎች እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ሳይሆን፥ ከአምልኮ ሥርዓት አንጻር ብቻ አምልኮአቸውን ሊያቀርቡ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ግለጽ። ለ) ይህን ዝንባሌ ለማረም ምን ማድረግ ትችላለህ? 2. ጋብቻና ፍቺ (ሚልክያስ 2፡10-16)፡- ከሚስቶቻችን ወይም ከባሎቻችን ጋር በትክክለኛ ግንኙነት ውስጥ ካልሆንን ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ በሆነ ግንኙነት ልንኖር አንችልም። ሚልክያስ ስለ ጋብቻ ሁለት ዐበይት እውነቶችን ያስተምረናል፡-  ሀ) አንድ ሰው ማንን እንደሚያገባ ወይም ሴት ከሆነች ማንን እንደምታገባ ጠንቅቆ መወሰን አለበት ወይም አለባት። ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ካደረግነው ውሳኔ ቀጥሎ ያለን ከፍተኛ ውሳኔ ማንን እንደምናገባ መወሰን ነው። አንድን ሰው የማያምን ወይም ሥጋዊ ክርስቲያን ብቻ መሆኑን እያወቅን ለቤተሰብ ውርስ፥ ለመልክ፥ ለሀብት ስንል ብናገባ እጅግ አስቸጋሪና ከባድ በሆነ ሕይወት ውስጥ እናልፋለን። ዘይትና ውኃ ሊቀላቀሉ እንደማይችሉ ወይም ብርሃን ከጨለማ ጋር ሊስማማ እንደማይችል ሁሉ በዚህ ዓይነቱ ጋብቻ ውስጥ በፍጹም ስምምነት ሊኖር አይችልም (2ኛ ቆሮንቶስ 6፡14-16 ተመልከት)። በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረን ግንኙነት ይለወጥና እግዚአብሔርን በምንፈልገው መንገድ ሳናገለግለው እንቀራለን። እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ሊያከብር በማይችል ቤተሰብ ውስጥ ስለሚያድጉ ጉዳቱ ለልጆቻችንም ይተርፋል። የእግዚአብሔር ቃል ግልጽ ነው፡- የማያምን ሰው ልናገባ አይገባም። ሚስትን ወይም ባልን ለመምረጥ ዋናው መመዘኛ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ነው። ሥጋዊ የሆነ ክርስቲያን ብናገባ የሚያጋጥመን ችግር የማያምን ሰው በማግባት ከሚገጥመን ችግር የተለየ አይደለም። ዳሩ ግን እንደ እኛው እግዚአብሔርን ለማገልገልና ለመታዘዝ ጥማት ያለውን ሰው ካገባን፥ የቤተሰቡ ውርስ ወይም ውበት ወይም ሀብት ምንም ዓይነት ቢሆን በትዳራችን ውስጥ ስምምነት፥ ሰላምና ፍቅር ይኖራል። ለ. አንድ ሰው ያገባውን ሰው መፍታት የለበትም። የሚያሳዝነው ነገር አይሁዶች ፍቺ ምንም ችግር የሚያስከትል አይመስላቸውም ነበር። እንዲያውም ኢየሱስ በኖረበት ዘመን አንዲት ሴት እንጀራ ወይም ወጥ ብታሳርር ወይም ጥሩ ምግብ ለማዘጋጀት ባትችል፥ ባሏ ሊፈታት ይችል ነበር። ፍቺ በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ በዘዳግም 24፡1-4 የሚገኘውን ጥቅስ እንደ ይለፍ ፈቃድ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር። ለእስራኤላውያን ፍቺ የሚፈቀደው በሕይወታቸው ውስጥ ባለ ኃጢአት ምክንያት ብቻ ነበር (ማቴዎስ 19፡8)። እግዚአብሔር የደገፈው አማራጭ አልነበረም። ጋብቻ ሴትና ወንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገቡት የተቀደሰ ቃል ኪዳን ነው። ይህም እግዚአብሔር የሚያከብረውና የሚባርከው ነው። ጋብቻ ማለት ፍጹም መጣመርና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ልጆችን ማፍራት ማለት ነው። ሚልክያስ ሚስትን «ባልንጀራ» ብሎ ይጠራታል (ሚልክያስ 2፡14)። ይህንን አሳብ የሚገልጠው የዕብራይስጡ ቃል ሁለት እንጨቶች ሊለያዩ በማይችሉበት መንገድ በምስማር ማጣበቅን የሚያመለክት ነው። የእግዚአብሔር ፍላጎት ጋብቻን በምንመሠርትበት ጊዜ ከትዳር ጓደኛችን ጋር በአካል፥ በስሜትና በመንፈስ አንድ እንድንሆን ነው። ፍላጎቶቻችን አንድ ይሆናሉ። ዕቅዶቻችን አንድ ይሆናሉ። ኑሮአችን ፍጹም በሆነ መግባባት፥ በስምምነትና በፍቅር የተመሠረተ ይሆናል። ባል ለሚስቱ ምን ማድረግ፥ ምን ማመን ወይም ምን ማቀድ እንዳለባት ያዛታል ማለት አይደለም። በአንድነትና በኅብረት ይሠራሉ። የእስራኤልና የቤተ ክርስቲያን ባል በሆነው በእግዚአብሔርና ሚስት በሆነችው በእስራኤል ወይም በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ በሙላት ሊፈጸም የሚችለው የዚህ ዓይነቱ ኅብረትና ግንኙነት በተገቢው ሁኔታ ሲኖር ብቻ ነው (ኤርምያስ 2፡1-3፤ 31፡32፤ ሕዝቅኤል 16፤ ሆሴዕ 2፡1-9። እስራኤልና እግዚአብሔር የሚስትና የባል ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ጥቅሶች ስለሆኑ ተመልከታቸው)። አዲስ ኪዳን ፍቺ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳልሆነ ያስተምረናል (ማቴዎስ 5፡31-32፤ 19፡1-10፤ ማርቆስ 10፡1-10፤ ሮሜ 7፡13፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡10-16፥ 39)። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ሚስት ወይም ባል በሚመርጡበት ጊዜ የተሳሳተ መመዘኛ የሚጠቀሙት እንዴት ነው? ለ) ወንድ ወይም ሴት የትዳር ጓደኛ በሚመርጡበት ጊዜ ሊጠቀሙበት የሚገባ አንዳንድ መመዘኛዎችን ዘርዝር። ሐ) ከላይ የጠቀስነው እግዚአብሔር ለጋብቻ ያለው ዓላማ የሚፈጸመው በጥቂት ክርስቲያናዊ ጋብቻዎች ብቻ የሚሆነው ለምን ይመስልሃል? 3. ነቢዩ ኤልያስ (ሚልክያስ 4፡5-6)፡- ትንቢተ ሚልክያስ የሚጠቃለለው የነቢዩ ኤልያስን መምጣት እንዲጠባበቁ ለእስራኤል ሕዝብ በመንገር ነው። የዚህ ነቢይ መምጣት «የጌታን ቀን» የሚቀድም ሲሆን፥ የልጆችን ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኤልያስ የእግዚአብሔር ነቢይ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚገልጽና ከሌሉች ነቢያት መካከል አብዛኛዎቹ የተከተሉት ዐቢይ ምሳሌ ነበር። ምክንያቱም፡- ሀ) ኤልያስ የሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎችን በድፍረት በመቃወም፥ ከአባቶቻቸው እምነት ዞር በማለታቸው፥ በሥነ ምግባር ጉድለታቸውና ማኅበራዊ ፍትሕን በማዛባት ኃጢአታቸው ወቅሶአቸዋል።  ለ) ኤልያስ ንስሐ የመግባትን አስፈላጊነት፥ ይህ ካልሆነ ግን ሰው የእግዚአብሔር ፍርድ እንደሚጠብቀው በግልጽ አስተምሯል።  ሐ) የኤልያስ መልእክቶች እውነትነት በተአምራት የተረጋገጠ ነበር። መ) ኤልያስ ከሃይማኖት መሪዎች አንዱ አልነበረም፤ ዳሩ ግን ከተመሠረተው ሃይማኖታዊ መዋቅር ውጭ ሆኖ ሕዝቡ ወደ እውነተኛ ሃይማኖት እንዲመለሱ ለማድረግ ሠራ። ኢየሱስ በተራራ ላይ በተለወጠ ጊዜ ከሙሴና ከኤልያስ ጋር ተገናኝቶ ነበር (ማቴዎስ 17፡1-8)። ሙሴ ሕግን፥ ኤልያስ ደግሞ ነቢያትን የሚወክሉ ሲሆን፥ ሁለቱም የመሢሑን መምጣት የሚያመለክቱ ነበሩ። የእነርሱ መገለጥ ኢየሱስ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የነበሩት የሕግና የነቢያት ፍጻሜ መሆኑን ማሳየት ነበር። ሚልክያስ በዚህ ስፍራ የተናገረው፥ አንድ ቀን ኤልያስን የሚመስል ሰው እንደሚመጣ ነው። የእርሱ መምጣት ከመጨረሻዎቹ ቀናትና ከመሢሑ መምጣት በፊት ይሆናል። ሚልክያስ ይኖር በነበረበትና መጥምቁ ዮሐንስ በተነሣበት ዘመን መካከል በነበሩት 400 ዓመታት ውስጥ አይሁድ ስለዚህ ኤልያስ የነበራቸው ወግ ዕድገት እያሳየ መጥቶ ነበር። ይህ የኤልያስ ተምሳሌት ይሁን ወይም የኤልያስ ከሞት ተነሥቶ መምጣት የሚያውቁት ነገር አልነበረም። መጥምቁ ዮሐንስ በመጣ ጊዜ በአለባበስና በመልእክቱ እነርሱ የሚጠብቁትን ኤልያስ ይመስል ነበር። ብዙ ሕዝብ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ የመጡበትና በእርሱ ያመኑበት አንዱ ምክንያት ይህ ነበር። በኋላ ጌታ ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስ ይህን ትንቢት እንደፈጸመ ተናገረ (ማቴዎስ 11፡7-15)። ብዙ ምሁራን ከዘመናት መጨረሻ ጥቂት ቀደም ብሎ የሚመጣ ሌላ “ኤልያስ” አለ ብለው ያስባሉ። ይህ ሰው ከዘመኑ ፍጻሜ በፊት ሕዝቡን ለንስሐ የሚጋብዝ የመጨረሻ መልእክተኛ ይሆናል። በራእይ 11፡1-12 ከምናያቸው ሁለት ነቢያት አንዱ ኤልያስን የሚመስል ነቢይ ነው ብለው ያስባሉ። የውይይት ጥያቄ፥ ክርስቲያኖች እነዚህን እውነቶች ሊያውቋቸውና ሊታዘዟቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? የውይይት ጥያቄ፥ ሚልክያስ 1-4 አንብብ። ሀ) አይሁድ ለእግዚአብሔር ያቀረቧቸውን የተለያዩ ጥያቄዎች ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር እነዚህን ጥያቄዎች የመለሰላቸው እንዴት ነበር? ሐ) ከእነዚህ ጥያቄዎችና ትምህርቶች አብዛኛዎቹ በዚህ ዘመን ላሉ ክርስቲያኖች ጠቃሚ የሚሆኑት እንዴት ነው? እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሰጣቸው ኃላፊነቶች አንዱ፥ ለእግዚአብሔር ሕዝብ «ነቢይ» የመሆን ኃላፊነት ነው። ይህን ስል የእግዚአብሔር ሕዝብ ኃጢአታቸውን እንዲያዩ ማድረግና የተሳሳተ ዝንባሌያቸውን ሁሉ በግልጽ መቃወም አለባቸው ማለቴ ነው። እግዚአብሔር በረከቱን ያለማቋረጥ እንዲሰጥ የእግዚአብሔር ሕዝብ ንጹሕ አምልኮና ኑሮ እንዲኖሩ የማስተማርና የማበረታታት ኃላፊነት አለባቸው። እግዚአብሔር የሕዝቡን ንጽሕና ጠብቆ ለማቆየት በቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንዴት እንደሚጠቀም የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ሚልክያስ ነው። ሚልክያስ በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ ያሉትን ችግሮች የሚጠቁሙ አጫጭር መልእክቶችን በመጽሐፉ ውስጥ አቅርቧል። ብዙ ጊዜ የሚጀምረው እውነታን ወይም ጭብጥን የያዙ አጫጭር ዐረፍተ ነገሮችን በማቅረብ ሲሆን፥ ሕዝቡ ከእነዚህ ዐረፍተ ነገሮች በመነሣት እግዚአብሔርን ይጠይቃሉ።  1.1ኛ ጥያቄ፥ እግዚአብሔር እኛን የወደደን እንዴት ነው? (ሚልክያስ 1፡1-5)  ሰዎች ሁሉ የኢኮኖሚ ችግር ወይም በሥጋቸው ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነገር ሲገጥማቸው የሚሰጡት ምላሽ ከሚከተሉት ሁለት ነገሮች አንዱን ነው:- አንዳንዶች ትከሻቸውን በመስበቅ ይህንን ችግር በሕይወቴ ላይ ያመጣ እግዚአብሔር ስለሆነ ምንም ማድረግ አልችልም ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ወደ አለማመንና የተጣመመ ትርጉም ወደ መስጠቱ በመቻኰል የእግዚአብሔርን ፍቅር በጥያቄ ምልክት ያስቀምጡታል። አይሁድ ተጠራጣሪና ጠማማ በሆን ልባቸው ወደ እግዚአብሔር በመመልከት፥ እርሱ በእርግጥ ይወዳቸው እንደሆነ መጠየቅ ጀምረው ነበር። እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ፍቅር ለማረጋገጥ

የትንቢተ ሚልክያስ ዐበይት ትምህርቶች Read More »

የትንቢተ ሚልክያስ አስተዋጽኦ እና ዓላማ

የትንቢተ ሚልክያስ አስተዋጽኦ የውይይት ጥያቄ፥ ) ስለሚልክያስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ለ) በዚህ ስፍራ ስለ ሚልክያስ የተጠቀሱትን ዐበይት እውነቶችን ዘርዝር። ሚልክያስ የተጻፈው እጅግ ልዩ በሆነ መንገድ ነበር። በመጀመሪያ አብዛኛው የመጽሐፉ ክፍል የተጻፈው ሚልክያስ እግዚአብሔርን ወክሎ እንደሚናገር ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ራሱ ለእስራኤላውያን በቀጥታ እንደሚናገር ሆኖ ነው። በመጽሐፉ አብዛኛ ክፍል ውስጥ እግዚአብሔር ለአይሁድ የሚናገረው «እኔ» የሚለውን ተውላጠ ስም በመጠቀም ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ሚልክያስ በጽሑፉ የተጠቀመው ልዩ የሆነ የአጻጻፍ ሥልትን ነው። አብዛኛዎቹ መልእክቶቹ የሚከተለውን አደረጃጀት የተከተሉ ናቸው፡- ሀ. እግዚአብሔር ስለ ራሱ ወይም ስለ እስራኤላውያን መንፈሳዊ እውነትን ይናገራል። ለ. ቀጥሉ እስራኤላውያን በዚህ የእግዚአብሔር ንግግር ላይ ተመሥርተው የሚያነሡት ጥያቄ በመላ ምት ይቀርባል።  ሐ. እግዚአብሔር፥ ጥያቄአቸው ትክክል አለመሆኑን በሚያስረዳ መንገድ ለእስራኤላውያን ጥያቄ መልስ ይሰጣል። መ. እግዚአብሔር ለተናገረው ቃል ማረጋገጫ ያቀርባል። የውይይት ጥያቄ፥ ሚልክያስ 1፡2-5 አንብብ። በዚህ ክፍል ውስጥ እነዚህ አራት ደረጃዎች የሚታዩት እንዴት ነው? ትንቢተ ሚልክያስ መልእክቱን የመሠረተባቸውን ስድስት ስብከቶች ይዟል። እነዚህ ስድስት መልእክቶች መልሶችን የያዙ ጥያቄዎች ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ።  እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ያቀረበው ክስ 1ኛ ጥያቄ፡- እግዚአብሔር እኛን የወደደን እንዴት ነው? (ሚልክያስ 1፡1-5)። መልስ፡- ሀ) እግዚአብሔርን እስራኤልን የራሱ አድርጎ መርጧታል፤ ለ) እግዚአብሔር እስራኤልን ይጠብቃታል።  2ኛ ጥያቄ፡- እኛ ካህናት የእግዚአብሔርን ስም የናቅነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 1፡6-2፡9)። መልስ፡- ሀ) ካህናቱ እግዚአብሔርን አያከብሩም፤ ለ) ካህናቱ ለእግዚአብሔር ተገቢ ያልሆነ መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ ሐ) ካህናቱ ለእግዚአብሔር ስም ክብር አይሰጡም፤ መ) ካህናቱ ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግ አያስተምሩም።  3ኛ ጥያቄ፡- እኛ እስራኤላውያን ለቃል ኪዳኑ ታማኞች ያልሆንነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 2፡10-16)።  መልስ፡- ሀ) ሕዝቡ ሌሎች አማልክትን ከሚያመልኩ አሕዛብ መካከል ሚስቶችን አግብተዋል፤ ለ) ሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት በቃል ኪዳን ያገቧቸውን ሚስቶቻቸውን ፈትተዋል።  እግዚአብሔር በፍርድና በመቤዥት ወደ ሕዝቡ እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል  4ኛ ጥያቄ፡- እግዚአብሔርን ያሰለቸነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 2፡17-3፡6)። መልስ፡- ሀ) ሕዝቡ እግዚአብሔር ጻድቅ አይደለህም ብለው ይከሱት ነበር፤ ለ) እግዚአብሔር በቃላቸውና በተግባራቸው ታማኝ ባልሆኑት ሕዝቡ ላይ ፍርድን ያመጣና ይቀጣቸዋል፤ ያነጻቸዋልም።  5ኛ ጥያቄ፡- ወደ እግዚአብሔር መመለስ የምንችለው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 3፡7-12)። መልስ፡- ሀ) ከእግዚአብሔር መስረቅን በማቆምና ለእግዚአብሔር መክፈል የሚገባውን አሥራትና መባ በመስጠት። ለ) ለእግዚአብሔር በሚሰጡበት ጊዜ እርሱ በረከቱን ያፈስላቸዋል።  6ኛ ጥያቄ፡- በእግዚአብሔር ላይ በድፍረት የተናገርነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 3፡13-4፡3)። መልስ፡– ሀ) እግዚአብሔርን ማገልገል ምንም ጥቅም የለውም ብላችኋል፤ ለ) የሚያከብሩኝንና የሚታዘዙኝን አስባቸዋለሁ፤ ደግሞም እሸልማቸዋለሁ፤ ሐ) እኔን ባለመታዘዝ የማያከብሩኝን እቀጣቸዋለሁ፤ መ) «የጽድቅ ፀሐይ» በምትወጣበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር በረከትና ፍርድን ያመጣል።  7. ለሕዝቡ የተሰጠ የመጨረሻ ግሣጹ (ሚልክያስ 4፡4-6) ሀ) የእግዚአብሔርን ሕግጋት መጠበቅን አስታውሱ፤ ለ) ሕዝቡን ለመሢሑ ለማዘጋጀት ከመሢሑ በፊት የሚመጣውን ኤልያስን ጠብቁ።  የትንቢተ ሚልክያስ ዓላማ የብሉይ ኪዳን ትምህርቶች እምብርት ቃል ኪዳንን የሚመለከት አሳብ ያዘለ ነው። እግዚአብሔር በጸጋውና በፍቅሩ የቃል ኪዳኑ ሕዝብ እንዲሆኑ እስራኤላውያንን መረጣቸው። ይህም የተጀመረው እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ባደረገው ቃል ኪዳን ነበር። ይህ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ለአይሁድ በሲና ተራራ ቃል ኪዳን በሰጣቸው ጊዜ ሊስፋፋ ችሏል። ይህም ከካህናት፥ በኋላም ከዳዊት ጋር የተደረገውን ቃል ኪዳን ይጨምር ነበር። ቃል ኪዳኖቹ የእግዚአብሔርን ፍቅርና ጸጋ የሚያስረዱ ናቸው። የቃል ኪዳኑ ጀማሪ እርሱ ሲሆን፥ ሕዝቡ በቃል ኪዳኑ ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ነገር ባላደረጉ ጊዜ እንኳ ሊለውጠው አልፈለገም። ይሁን እንጂ ብሉይ ኪዳን የሚያስተምረን በቃል ኪዳኑ ውስጥ የተጠቀሱትን በረከቶች ለመቀበል ለቃል ኪዳኑ ታዛዥ መሆናቸው አስፈላጊ እንደ ነበር ነው። ይህ መታዘዝ በውጫዊ ሥርዓት ብቻ የሚሆን ሳይሆን፥ ከሕዝቡ ልብ የሚመነጭ መሆን ነበረበት። እግዚአብሔር ሚልክያስን በጠራው ጊዜ ሕዝቡ በቃል ኪዳኑ ውስጥ የታዘዙትን አብዛኛዎቹን ሥርዓቶች እየተከተሉ ነበር። ዳሩ ግን እግዚአብሔርን ከልባቸው አያመልኩትም ነበር። መሥዋዕቶችንም ያቀርቡ ነበር፤ ነገር ግን ለእነርሱ የማይጠቅሙትን ሽባ ወይም ዕውር እንስሳት በመስጠት እግዚአብሔርን ያቃልሉት ነበር። እንደ ቀደምት አባቶቻቸው ጣዖትን አያመልኩም ነበር፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ የመሆናቸውን እውነታ ለመቀበልና ልባቸውን ለመለወጥ አይፈቅዱም ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ነቢዩን ሚልክያስን ማስጠንቀቂያ የሚሰጣቸው የመጨረሻ መልእክተኛ አድርጎ ላከው። ሚልክያስ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር በገባው ቃል ኪዳን ላይ ያተኵር ነበር። ይህ ለእስራኤላውያን የእግዚአብሔር ፍቅር ማረጋገጫ ነበር። ካህናቱ በእግዚአብሔር ፊት አገልግሎታቸውን የሚፈጽሙበት መሠረት ነበር። ሚልክያስ የቃል ኪዳኑ ውጤት በእስራኤላውያን ሕይወት ምን መሆን እንዳለበት ተመለከተ። የቃል ኪዳኑ እምብርት ወደ እግዚአብሔር የሚመለከት ትክክለኛ ዝንባሌ ነበር። ቃል ኪዳኑ እግዚአብሔርን እንደ ቅዱስነቱ በክበርና በሙሉ ሕይወታቸው እርሱን ለማክበር ባላቸው ፍላጎት ላይ መመሥረት ነበረበት። ያ አክብሮት ለእግዚአብሔር ወደሚቀርብ እውነተኛ አምልኮ ሊመራቸውና ለእግዚአብሔር የማይረባውን ሳይሆን ከሁሉም የተሻለውን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ሊያደርጋቸው ይገባ ነበር። መሪዎችና ሕዝቡ እርስ በርስ በመከባበር እንዲነጋገሩና በተለይም ለሚስቶቻቸው የገቡትን ቃል ኪዳን በመጠበቅ ከመፋታት እንዲታቀቡ ሊያደርጋቸው ይገባ ነበር። በእግዚአብሔር የማያምኑትን እንዳያገቡ እምነታቸውን በንጽሕና የመጠበቅ ፍላጎት ሊያሳድርባቸው ይገባ ነበር። ይህንንም እግዚአብሔር ከሰጣቸው ነገር አሥራታቸውን በታማኝነት በመስጠት ማረጋገጥ ነበረባቸው። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአዲስ ኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ቃል ኪዳን ከዚህ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ በመሆናችን ምክንያት በሕይወታችን ሊለወጡ የሚገባቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ሐ) ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ እንደሆኑ የሚናገሩባቸው፥ ዳሩ ግን ለዚህ ቃል ኪዳን ባለመታዘዝ እግዚአብሔርን የማያስከብሩባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ነቢዩ ሚልክያስ በእግዚአብሔር የተጠራው አይሁድ ለቃል ኪዳኑ ታዛዦች ይሆኑ ዘንድ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ነበር። እግዚአብሔር በሚልክያስ በኩል አይሁድን ስለ ኃጢአታቸው ሊወቅሳቸውና ወደ እርሱ እንዲመለሱ ሊጠራቸው ፈልጎ ነበር። ሚልክያስ ሕዝቡን፥ በተለይም የሃይማኖት መሪዎችን መሢሑ በሚመጣበት ጊዜ ስለ ኃጢአታቸው እንደሚፈርድባቸውና ለእግዚአብሔር ታማኞች የሆኑትን ደግሞ እንደሚሸልማቸው ያስታውሳቸዋል። ልዑል አባት፥ የፍጥረታት ሁሉ ጌታና የቃል ኪዳኑ መሥራች የሆነው እግዚአብሔር ሊከበር፥ ከእርሱ ጋር ግንኙነት የሚያደርጉ ሰዎች ደግሞ በቃል ኪዳኑ ውስጥ በተመለከተው መንገድ በተገቢ ሁኔታ ግንኙነት ሊያደርጉ ይገባል (ዘጸአት 20፡12፤ ዘዳግም 31፡1-10)። እግዚአብሔር ሕዝቡ ንስሐ እንዲገባና ከእርሱ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን እንዲያድሱ ጥሪ ያደርጋል። በዚህ መሠረት፡- ሀ) የተበላሽውን የክህነት አገልግሎት ማንጻት ነበረባቸው፤  ለ) ሥርዓታዊውን አምልኮ ሐሤትና ደስታ ወደሞላበት አምልኮ መለወጥ ነበረባቸው፤  ሐ) አሥራት በመክፈልና መሥዋዕት በማቅረብ በኩል የሚታዩትን ድክመቶች ማስተካከል ነበረባቸው፤  መ) ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ተገቢ የሆነ ግንኙነት ሊያደርጉ ይገባቸው ነበር፤  ሠ) ከጎረቤቶቻቸው ጋር በማኅበራዊ ፍትሕ መኖር ነበረባቸው። የትንቢተ ሚልክያስ መልእክት ውጤት ምን እንደነበር አልተነገረንም። በቅድሚያ ሕዝቡ መጠነኛ የሆነ ምላሽ ሳይሰጡና ንስሐ ሳይገቡ አልቀሩም። ዳሩ ግን አይሁድ ብዙም ሳይቆዩ ወደ ቀድምው ዝንባሌያቸው ተመለሱ። ኢየሱስ በምድር ላይ ይመላለስ በነበረ ጊዜ ሕዝቡ በተለይም ፈሪሳውያን የዚህ ዓይነት ዝንባሌ ነበራቸው። የልባቸው ዝንባሌ ትክክል ባይሆንም እንኳ ይከተሉት የነበረው ሥርዓታዊ አምልኮ እግዚአብሔርን ደስ እንደሚያሰኝ አስበው ነበር። ኢየሱስ ስለነበራቸው ዝንባሌ በግልጽ እየወቀሳቸው፥ በልባቸው ተለውጠው እግዚአብሔርን በተገቢው ሁኔታ እንዲያመልኩ በነገራቸው ጊዜ ተቃወሙት፤ በመጨረሻም ሰቅለው ገደሉት። ይህ ብዙ ጊዜ በግልጽ የሚታይ እውነታ ነው። ለትምህርቶቻቸውና ለሥርዓተቸው ጥብቅና ለመቆም የሚፈልጉ የሃይማኖት መሪዎች ሁልጊዜ እውነትን ይቃወማሉ። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በሚልክያስ ዘመን የነበሩት ካህናትና በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ፈሪሳውያን ያደርጉት እንደነበረው በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ዝንባሌ ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚወቀሱበትን ማንኛውንም ስሕተት ላለመቀበል የሚቃወሙትና ከዚህ ቀደም የለመዷቸውን ሥርዓቶች ለመጠበቅ የሚጥሩት ለምን ይመስልሃል? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ሚልክያስ አስተዋጽኦ እና ዓላማ Read More »