ማርቆስ 9፡1-50

  1. ኢየሱስ ሰማያዊ ክብሩን ገለጸ (ማር. 9፡1-3)።

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ ከመሞታቸው በፊት ክብሩን እንደሚያዩ ከተናገረ በኋላ፥ ጴጥሮስን፥ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ወደ ተራራ ወጣ። በዚያም መለኮታዊ ክብሩን ገለጸ። በዚያም ሕግን የወከለው ሙሴና ነቢያትን የወከለው ኤልያስ ቀርበው ከኢየሱስ ጋር ተነጋገሩ። ለሁለተኛ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር የሚወደው ልዩ ልጁ እንደሆነ ሰሙ። ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ምን ያህል እንደ ተደሰቱ አስቡ። ወዲያው ግን ኢየሱስ አምላክ ቢሆንም እንኳ፥ መከራን እንደሚቀበልና በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን እንደሚያጣ በመግለጽ ደቀ መዛሙርቱን አስደነገጠ። ያዩትን ሁሉ ለሌሎች አለመናገሩ ሳይከብዳቸው አልቀረም።

  1. ኢየሱስ ከአንድ ልጅ አጋንንትን አስወጣ (ማር. 9፡14-32)።

ደቀ መዛሙርቱ ከተራራው ሲወርዱም እንደገና ደነገጡ። ከልጁ አጋንንት ለማውጣት ባለመቻላቸው ወደ ተራራው ያልመጡት ደቀ መዛሙርት፥ ተጨንቀውና አፍረው ቆመው ነበር፡፡ ቀደም ሲል ክርስቶስ ለአገልግሎት በላካቸው ጊዜ ያከናወኑት አጋንንትን የማስወጣት ተግባር፥ ለምን እንደ ተሳናቸው ሊገባቸው አልቻለም ነበር።

ክርስቶስ ይህንን ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ እምነት ለማስተማር ተጠቀመበት፡፡ በመጀመሪያ፡ ለልጁ አባት፥ ለሚያምን ሁሉም እንደሚቻል ገለጸለት (ማር. 9፡23)። ስለ እምነት ልናስታውሳቸው የሚገቡን ሁለት ነገሮች አሉ። ታላላቅ ነገሮችን የሚሠራው ራሱ እምነታችን ሳይሆን፥ የምናምንበት አካል ነው። ስለሆነም በጣዖታት ላይ ከፍተኛ እምነት ያለው ሰው ታላላቅ ነገሮችን ሊያሳካ አይችልም። ነገር ግን በታላቁ አምላክ ላይ አነስተኛ እምነት ያለው ሰው እግዚአብሔር ታላላቅ ተአምራትን ሲሠራ ሊመለከት ይችላል። በተገላቢጦሹ እምነት በማይኖርበት ጊዜ ወይም ሰዎች ለማመን ሳይፈልጉ ሊቀሩ፣ እግዚአብሔር ተአምራትን ለመሥራት አለመቻሉ ሳይሆን፥ ነገር ግን ሰዎች እርሱን ወይም ችሉታውን በሚጠራጠሩበት ጊዜ ለመሥራት አለመምረጡ ነው።

ሁለተኛ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ሥራዎችን ለማከናወን በእምነት መጽናት አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ እንዳለ ተናግሯል። ደቀ መዛሙርቱን ያጋጠቸው ችግር ክርስቶስ በተአምር ለመፈወስ ኃይልን ማጣቱ አልነበረም። ክርስቶስ በአንድ የትእዛዝ ቃል ነበር አጋንንቱን ሁሉ ያስወጣው። ተግቶ የማይሠራ ሰው ጠንካራ ጡንቻ ሊኖረው አይችልም። በተመሳሳይ ሁኔታ በጸሎት ጽኑ ትግል የማያደርግና በጾም በእግዚአብሔር ላይ ጥገኛ መሆኑን የማያሳይ ክርስቲያን መንፈሳዊ ጡንቻ ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለሆነም፥ እግዚአብሔር ቀደም ሲል እኛን ለመርዳት ቢሠራም እንኳ፥ ጥያቄዎቻችንን በፍጥነት የማይመልስባቸው ጊዜያት አሉ። እምነታችንን የሚፈታተን ሁኔታ ሁሉ አዲስ ሁኔታ ነው። በቀድሞው ስኬት ወይም ብርታት ላይ ሳንመሠረት፥ እንደገና በእግዚአብሔር ላይ ጥገኝነታችንን ማኖር አለብን።

የውይይት ጥያቄ- ሀ) ብዙውን ጊዜ አንድ ነገር ከተሳካልን በኋላ፥ በእግዚአብሔር ላይ መደገፋችንን የምናቋርጠው እንዴት ነው? ለ) እግዚአብሔር ለጸሎትህ ፈጣን ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት መንፈሳዊ ብርታትህ የጨመረባቸውን መንገዶች የሚያሳዩ ምሳሌያችን ስጥ።

ማርቆስ ክርስቶስ ለሦስተኛ ጊዜ ስለ መጭው ሞቱ፥ ቀብሩና ትንሣኤው መግለጹን ዘግቧል።

  1. ኢየሱስ በመንግሥቱ ውስጥ አመራር ምን እንደሚመስል አስተማረ (ማር. 9፡33-50)

የተሳሳቱ አመለካከቶችን ማስወገዱ ቀላል አይደለም። እጅግ ከተሳሳቱ እመለካከቶች አንዱ ሥልጣንና የመሪነት ስፍራ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት ነው። በዓለም ሁሉ ያለው ባሕል በራስ ጥቅም ላይ ያተኩራል። ሰዎች መሪ ከሚሆኑባቸው ዋንኛ ምክንያቶች አንዱ ሥልጣን፥ ሀብትና ኀይል ለማግኘት ነው። ይህ አመለካከት ካልተወገደ በስተቀር ቤተ ክርስቲያንን እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ መምራት አይቻልም። ይህ የኀይልና የክብር ፍላጎት ደቀ መዛሙርቱን ይፈታተናቸው ስለ ነበር፥ ክርስቶስ የመንግሥቱ አመራር በአምስት መንገዶች እንደሚለይ አስተምሯል።

ሀ. በክርስቶስ መንግሥት አመራር ከዓለም የተለየ ነው። ታላቅነት የሚለካው አንድ መሪ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከራስ ወዳድነት በጠራ መንፈስ ሌሎችን ለማገልገል በመቻሉ ነው፡፡ እንደ ትልልቅ ሰዎች በችሎታችንና በታላቅነታችን ከመመካት ይልቅ፥ እንደ ልጆች በእግዚአብሔር አብ ላይ ጥገኞች ልንሆን ይገባል።

ለ. በክርስቶስ መንግሥት አመራር የሚያከብረው ታላላቆች ናቸው የተባሉትን ሳይሆን፥ ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸውን ሰዎች ነው። ጠቃሚዎች ናቸው የምንላቸውን ሰዎች (ሀብታሞች፥ ነጋዴዎች፥ ምሁራን) እየወደድን፥ ጠቃሚዎች አይደሉም የምንላቸውን ሰዎች (ልጆች፥ ሴቶች፥ ድሆች፥ መሃይማንን) እንንቃለን። በክርስቶስ መንግሥት ለዓለም የማይጠቅሙ የሚመስሉ ሰዎች አስፈላጊዎች ናቸው።

ሐ የእግዚአብሔር መሪዎች ሌሎች ስኬታማ ሲሆኑና እግዚአብሔር ባልተጠበቁ መንገዶች ሲሠራ በሚመለከቱበት ጊዜ አይቀኑም። አሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ሌላ አማኝ ክርስቶስን ሳያስፈቅድ አጋንንት ሊያወጣ በማየታቸው ቀንተው ክርስቶስ እንዲከለክለው ነገሩት። ክርስቶስ ግን የአመራር ሚና ሰዎችን ማበረታታት እንጂ መቆጣጠር እንዳልሆነ አስተማራቸው። ለእግዚአብሔር ክብርን የሚያመጣ ማንኛውም ነገር በሚከሰትበት ጊዜ መደሰት አለብን። ይህ የግድ «በእኛ» መሪዎች ወይም በምንጠብቃቸው ሰዎች መከናወን የለበትም። ምክንያቱም ለክርስቶስ ክብር የሚሠራ ሰው፥ ወዲያውኑ ተመልሶ የክርስቶስ ጠላት ሊሆን ስለማይችል ነው።

መ. አገልግሎት የሚለካው በምናከናውናቸው ተግባራት ታላቅነት ሳይሆን፥ በታማኝነትና በጥሩ አመለካከት በማገልገላችን ነው። የግድ ታላላቅ ሰባኪያን ወይም አስተማሪዎች መሆን የለብንም። የባሪያን በሚመስል አመለካከት የተሰጠ አንድ ኩባያ ቀዝቃዛ ውኃ ዋጋ አለው።

ሠ. መሪዎችና በሌሎች ላይ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች፥ (ለምሳሌ፥ ወላጆች) በተግባራቸውና በአመለካከታቸው ትንንሽ ልጆችንና የቤተ ክርስቲያን ምእመናንን ወደ ኀጢአት እንዳይገፉ መጠንቀቅ አለባቸው። ክርስቶስ ሌሎችን በኀጢአት ለማሰናከል የተጋነነ ቋንቋ በመጠቀም አንድን ሰው ከማሰናከል ይልቅ፥ የግል አካላዊ ጉዳትን መቀበል እንደሚሻል ተናግሯል። ሌሎችን የሚያሰናክሉ ሰዎች እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ ዛሙርት ባለመሆናቸው፥ ከፍተኛ ቅጣት ይደርስባቸዋል። ተግባሮቻችንና አመለካከቶቻችን እንደ ብርሃን እያንጸባረቁ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ መምራት ይኖርባቸዋል። መንፈሳዊ ባሕርይን በመላበስ (በነፍሳችሁ ጨው ይኑርባችሁ)፥ እርስ በርሳችን በሰላም እንኖራለን።

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) ክርስቶስ ስለ መሪነት ያስተማረውን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካለው ሁኔታ ጋር እነጻጽር፡፡ ለ) አመራርን ይበልጥ ክርስቶስ ባየበት ዓይን ለመመመልከት፥ ከተግባራችንና ከእመለካከታችን ሊለወጡ የሚገባቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

 

ማርቆስ 8፡1-38

  1. ኢየሱስ አራት ሺህ ሕዝብን መገበ (ማር. 8፡1-21)

ክርስቶስ ምንም ያህል ሥራ ቢበዛበትም ስለ ሰዎች ጥቅም የሚያስብ ሲሆን፤ ጉዳታቸው ልቡን ይሰማውና ይራራላቸው ነበር። በዚያን ጊዜ ለሰዎች መጎዳት የራራው ክርስቶስ፥ ዛሬም የሚያስፈልገንን ሁሉ በሚመለከትበት ጊዜ ይራራልናል።

ክርስቶስ አሁን አራት ሺህ ሕዝብ ለመመገብ ያነሣሣውን የርኅራኄ ምክንያት ቀደም ሲል አምስት ሺህ ሕዝብ በመገበበት ወቅት፥ ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሮ የነበረውን ትምህርት አጠናክሯል። በዚህም ክርስቶስ ፍላጎታቸውን ሁሉ የሚያሟላ አምላክ መሆኑን አሳይቷል።

ፈሪሳውያን እንዲህ ያለ ታላቅ ተአምራት ቢመለከቱም እንኳ፥ በክርስቶስ ለማመን ፈቃደኞች አልነበሩም። የአንድ ግለሰብ ልብ ከደነደነና በክርስቶስ ላለማመን ከወሰነ፥ ምንም ዓይነት ተአምራት ቢመለከት ሊያምን አይችልም። እግዚአብሔር ኀይሉን ለማሳየት በተአምራት ሊጠቀም ቢችልም፥ ሰዎች ሁልጊዜ በተአምራት ላይ ካተኮሩ፥ ይህ ፍላጎታቸው የእምነት እጥረት እንዳለባቸው ያሳያል። ፈሪሳውያን ክርስቶስ መሢሕነቱን ለማረጋገጥ ከዚያ የበለጡ ተአምራት እንዲሠራ ጠይቀውታል። ክርስቶስ ግን ተአምራት የማያምን ትውልድ ምልክቶች መሆናቸውን በመግለጽ፥ ለማመን ለማይፈልጉ ሰዎች ታምራትን እንደማያደርግላቸው ገልጾአል።

ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ራስን የማጽደቅ አመለካከት እንዳይይዙና ለማመን ተጨማሪ ተአምራትን እንዳይሹ አስጠንቅቋቸዋል። ራስን የማጽደቅ አመለካከት እንደ እርሾ መንፈሳዊነታቸውን በማጥፋት ወደ ሌሎችም ይዛመት ነበር።

12ቱ ደቀ መዛሙርት እንደ ብዙዎቻችን ከመንፈሳዊ እውነት ይልቅ በምድራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮራቸው፥ የክርስቶስን ትምህርት በተሳሳተ መንገድ ተረጎሙ። የሚያስቡት ክርስቶስ ስለ ፈሪሳውያን ባስተማረው ጉዳይ ላይ ሳይሆን፥ ስለ ምግብ ነበር። ይህም ክርስቶስ ፍላጎታቸውን ሊያሟላ እንደሚችል አለማመናቸውን ያሳያል።

  1. ኢየሱስ ዓይነ ስውሩን ፈወሰ (ማር. 8፡22-26)

ይህ ተአምር በሁለት ደረጃዎች የተከናወነ በመሆኑ፥ በክርስቶስ አገልግሎት ውስጥ ለየት ያለ ነበር። ብዙውን ጊዜ የክርስቶስ ተአምራት በአንድ ጊዜ የተሳካ ውጠቶችን የሚያስገኙ ነበሩ። በዚህ ጊዜ ግን ክርስቶስ መጀመሪያ በታወሩት በሰውዬው ዓይኖች ላይ ምራቁን ቀባ። የግለሰቡ ዓይኖች በከፊል ስለ ተፈወሱለት፥ ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አየ። ነገር ግን ክርስቶስ እንደገና ሲዳስሰው ዓይነ ስውር የነበረው ግለሰብ አጥርቶ ለማየት ቻለ።

ይህ ምንን ያሳያል? ይህ አንዳንድ ጊዜ ተአምራት በከፊል ብቻ ውጤታማ እንደሚሆኑ ያሳያል? ዛሬ የመፈወስ ኃይል እንዳላቸው የሚያስቡ አንዳንድ ሰዎች እንደዚያ ይላሉ። ነገር ግን በዚህ ግንዛቤና በክርስቶስ ፈውስ መካከል አንዳንድ ዐበይት ልዩነቶች አሉ። ክርስቶስ አንድም ሰው በከፊል ፈውሶ ብቻ አላሰናበተም። የፈውሱን እርግጠኝነት ተጠራጥሮ እንደገና የተሟላ ፈውስ የሰጠው ራሱ ክርስቶስ ነበር። ማንም ሰው ከክርስቶስ ዘንድ ከፊል ፈውስ አግኝቶ የሄደ የለም። ዛሬም እግዚአብሔር አንድን ሰው በተአምራዊ መንገድ ከፈወሰው፥ ከፊል ሳይሆን ሙሉ ፈውስ ነው።

ክርስቶስ ይህንን ባለ ሁለት ደረጃ ፈውስ ያካሄደው አንዳች መንፈሳዊ እውነት ለማስተማር ይሆን? የአንድን ሰው መንፈሳዊ ዓይኖች መክፈት ማለትም፥ መንፈሳዊ እውነትን መረዳት ብዙውን ጊዜ የሂደት አካል ነው። በአንድ ጊዜ መንፈሳዊ እውነቶችን ሙሉ በሙሉ ሊረዳ የሚችል ሰው የለም። ደቀ መዛሙርቱም አልተገነዘቡም ነበር። ለዚህም ነበር ስለ ክርስቶስ አገልግሎት ብዙ ነገሮችን ከትንሣኤው በፊት ለመረዳት ያልቻሉት። ጳውሎስም ሳይቀር ነገሮችን በድንግዝግዝ እንደሚያይ ለማመን ተገድዷል (1ኛ ቆሮ. 13፡12)። ይህን ስላለ ግን ተስፋ እንቆርጣለን ማለት አይደለም። ይህ ትሑት እንድንሆን ያስተምረናል። በተጨማሪም፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ማደጋችንን እንድንቀጥል ያስተምረናል።

  1. ጴጥሮስ የኢየሱስን መሢሕነት መሰከረ (ማር. 8፡27-30)

የማርቆስ ወንጌል የተመሠረተው በዚህ አጭር ምንባብ ላይ ነው። ማርቆስ ክርስቶስ መሢሑ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በብዙ የተለያዩ መንገዶች አሳይቷል። በመጨረሻም፥ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ግል እምነታቸው የተጠየቁበት ጊዜ ደረሰ። ብዙውን ጊዜ ሌሎች ሰዎች ወይም ወላጆቻችን የሚያምኑትን ሃይማኖት መከተሉ ቀላል ነው። ነገር ግን ጠቅላላው ማንነታችን በእምነታችን ሊለወጥ በሚችልበት መልኩ በግላችን እውነትን ማመን አለብን። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን በጠየቀበት ሰዓት፥ መጀመሪያ ስለ ሌሎች ከጠየቀ በኋላ፥ የራሳቸውን እምነት እንዲገልጹት አድርጓል።

  1. ኢየሱስ ስለ መጭው ሞቱና የደቀ መዝሙርነት መንገድ አስተማረ (ማር. 8፡31-38)።

ጴጥሮስና ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስን መሢሕነት ከተገነዘቡ በኋላ፥ ጠቅላላው የኢየሱስ አገልግሎትና የማርቆስ ወንጌል ትኩረት ተለውጧል። በመጀመሪያ፥ ምን ዓይነት መሢሕ እንደሆነ የነበራቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ ማስተካከል ነበረበት። እርሱ መከራ የሚቀበልና የሚሞት እንጂ፥ ወረራ የሚያካሂድና የሚገዛ ንጉሥ አልነበረም። ሁለተኛ፥ ለደቀ መዛሙርቱ እርሱን መከተል መስቀልን እንደሚያስከትል ነግሯቸዋል። ይህም ክርስቶስን በሚከተሉበት ጊዜ በመንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወታቸው እንደሚሞቱ የሚያመለክት ነበር።

ከዚህ ጊዜ አንሥቶ፥ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለሚመጣው ሞቱ ይናገር ጀመር። መጀመሪያ ይህ ደቀ መዛሙርቱን ስላስደነገጣቸው፥ ጴጥሮስ እንዲህ ዓይነት የመሢሕነት እርምጃ አይድረስብህ አለው። ክርስቶስ ሰይጣን በጴጥሮስ ቃላት ተጠቅሞ ከመስቀል ሊመልሰው የመፈለጉን ፈተና ተገነዘበ። ክርስቶስ ይህን ሁኔታ ስለ ደቀ መዝሙርነትም ለማስተማር ተጠቅሞበታል። ክርስቶስ የሚሞትበትን መስቀል ተሸክሞ ወደ ጎልጎታ በመሄድ ለሰው ልጆች ደኅንነትን አስገኝቷል። ደቀ መዛሙርቱም እያንዳንዳቸው የሚሸከሙት መስቀል ነበራቸው። መስቀላችን መንፈሳዊ ነው። ራሳችን በሕይወታችን ላይ ላለን ቁጥጥር፥ ለዓለማዊ ብልጽግና መሞት አለብን። የደቀ መዝሙርነት መንገድ ማለት ሥጋዊ ሕይወታችንን ጨምሮ በዚህ ዓለም ጠቃሚዎች ናቸው የተባሉትን ነገሮች ሁሉ ማጣትን ያካትታል። ከዚያ በኋላ ለሰው ከሁሉም የበለጠ ዋጋ ያለውን የዘላለምን ሕይወት እናገኛለን። ነገር ግን ሕይወታችንን ብንታደግና በዓለም ጠቃሚዎች የሆኑትን ነገሮች ብንከተል፥ የዘላለም ሕይወታችንን እናጣለን። በስደት ጊዜ፥ በክርስቶስ አፍረን እርሱን ከመከተልና ቃሉን ከማስተማር ብንቆጠብ፥ ዘላለማዊ ጉዳት ይደርስብናል። በዘላለሙ መንግሥት፥ ክርስቶስ በአባቱ ፊት አያከብረንም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች ጠቃሚዎች እንደሆኑ የሚያስቧቸውንና፥ ክርስቲያን ከሆኑ በኋላ ለመተው የሚቸገሩባቸውን ነገሮች ዝርዝር። ለ) ክርስቲያኖች በክርስቶስና በቃሉ ማፈራቸውን የሚያሳዩባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ሐ) የመስቀሉን መንገድ መከተል እንዴት እንደ ለወጠህ ግለጽ።

ከዚህ በኋላ፥ ክርስቶስ በሞቱ ላይ ስላተኮረ ታሪኩ ተለውጧል። እርሱም ቀስ በቀስ ወደሚሞትባት የኢየሩሳሌም ከተማ ተጓዘ፡፡ ለደቀ መዛሙርቱም ስለ ሞቱና ትንሣኤው በተደጋጋሚ ይነግራቸው ጀመር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ማርቆስ 7፡1-37

  1. ክርስቶስ ሰውን ስለሚያረክስ ነገር አስተማረ (ማር. 7፡1-23)

በማርቆስ ወንጌል ውስጥ ከቀረቡት ረዣዥም ታሪኮች አንዱ፥ ሰውን ስለሚያረከሱና ስለሚያነጹ ነገሮች የሚያስረዳው ነው። ይህ ቤተ ክርስቲያን ልትረዳው የሚገባት ጠቃሚ እውነት ነው። በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች ይጠይቋቸው ከነበሩት ዐበይት ጥያቄዎች አንዱ፥ «ሃይማኖታዊ ንጽሕናችንን ለማሳየት ልንጠብቃቸው የሚገቡ ትውፊቶች አሉ ወይ?» የሚል ነበር። ለብዙ ምእተ ዓመታት አይሁዶች የተወሰኑ ነገሮችን በማድረግ ውስጣዊ ሕይወትን በንጽሕና መጠበቅ እንደሚቻል ተምረው ነበር። ለምሳሌ፥ ንጽሕናን በተመለከተ አንዱ መንገድ የተወሰኑ የሥጋ ምግቦችን አለመመገብ ወይም ደሞ እጅን በተወሰነ መንገድ መታጠብ። ይህ ሥርዓት የእግዚአብሔር ፈቃድና ጠቃሚ መሆኑን ሲማሩ የነበሩት አይሁዶች፥ በክርስቶስ ባመኑበት ጊዜ፥ ክርስቲያኖችም ይህንኑ ማድረግ አለባቸው ብለው ያስቡ ነበር። አይሁዶች ብቻ ሳይሆኑ የአሕዛብ ክርስቲያኖችም እነዚህኑ ሥርዓቶች እንዲፈጽሙ ተነግሯቸዋል። ላይ ላዩን ሲታይ የተወሰኑ ምግቦችን መመገቡ ወይም እጅን መታጠቡ ብዙ ለውጥ ስለማያመጣ፥ ለአሕዛብ የአይሁድን የአኗኗር መንገዶች መከተሉ ከባድ አልነበረም። ነገር ግን በውስጡ አደገኛ የሆነ ትምህርት እንደነበረ ግልጽ ነው። ይህም የተወሰኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን በምንፈጽምበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ደስ እንደሚሰኝብን፥ እንዲሁም ለእኛ የተስማማን ነገር ሁሉ ለሁሉም ሰዎች መልካም እንደሆነ አድርገን እንደምንገምት የሚያሳይ ነው። ስለሆነም፥ የኃጢአት ሥር የሚኖርበትን የልባችንን አመለካከት ትተን በሃይማኖታዊ ሥርዓት ላይ እናተኩራለን።

የሃይማኖት መሪዎች፥ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ በእግዚአብሔር ፊት ሰዎችን ንጹሕ ያደርጋሉ የሚሏቸውን አንዳንድ ሥርዓቶች አለመከተላቸውን በመግለጽ በወቀሱዋቸው ጊዜ፥ ክርስቶስ ሁለት ጠቃሚ ነገሮችን አስተማራቸው። በመጀመሪያ፥ በውጫዊ ልማዶችና ሥርዓቶች ላይ በማተኮር፥ ይበልጥ ጠቃሚ የሆነውን ነገር ላለማየት የመታወር አደጋ መኖሩን ገለጸ። ፈሪሳውያን እግዚአብሔርን በአፋቸው እያከበሩ፥ በሕግጋት ላይ ቢያተኩሩም፥ ልባቸው ወደ እግዚአብሔር ስለመቅረቡ ግድ የላቸውም ነበር፡፡ ሕግጋቱን በቀላሉ ወደሚፈጽሙበት አቅጣጫ ጠምዝዘዋቸው ነበር። ይህም እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ እየኖርን ነው ብለው እንዲከራሩ አደረጋቸው። ብዙውን ጊዜ ግን እግዚአብሔር በማይፈልገው መንገድ ይመላለሱ ነበር። ስለዚህ አመለካከታቸው ከእግዚአብሔር ትእዛዛት «መንፈስ» የራቀ ነበር።

ሁለተኛ፣ ጌታችን የትኛውም ሰው ሠራሽ ውጫዊ ተግባር አንድን ሰው ንጹሕ ወይም ርኩስ ሊያደርግ እንደማይችል አስተማረ። መንፈሳዊ ንጽሕና ወይም ርኩሰት የሚመጣው ከልብ ነው። የሰው አመለካከቶች፥ አሳቦችና ፍላጎቶች የሚኖሩት በልብ ውስጥ ነው። ልብ የመልካም ነገሮች (እግዚአብሔርንና ባልንጀራን መውደድ) እና የመጥፎ ነገርች (ጥላቻ፥ ምኞት፥ ቁጣ) ምንጭ ነው። የክርስቶስ ተከታዮች በእነዚህ ነገሮች ላይ ማተኮር አለባቸው፡ ተግባራችን መልካምና እግዚአብሔርን የሚያስከብር ይሆን ዘንድ ከርኩስ ነገሮች መራቅ አለብን። እውነተኛ ሃይማኖት ሰዎች የሚያዩት ሳይሆን፥ በአማኙ ልብ ውስጥ ያለው ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ክርስቲያንነታቸውን የሚያሳዩባቸው፥ ጠቃሚና መልካም ተደርገው የሚወሰዱትን አንዳንድ ክርስቲያናዊ ልምምዶች ለምሳሌ፥ ዓይንን ጨፍኖ መጸለይ፥ በጌጣጌጥ አለመዋብ የመሰሉትን ዘርዝር። ለ) ክርስቶስ ባስተማረው መሠረት፥ ስለ እነዚህ ነገሮች ምን ዓይነት ግንዛቤ ሊኖርህ ይገባል?

ክርስቶስ ፈሪሳውያን ወይም ደቀ መዛሙርት እነዚህን ሰው ሠራሽ ልምምዶች እንዲያቆሙ አልተናገረም። ነገር ግን ስለ ደንቦች ትክክለኛ ጭብጥ ሊኖራቸው እንደሚገባ አስጠንቅቋቸዋል። ከጊዜ በኋላ ሁላችንም ትክክል ናቸው የምንላቸውን ውጫዊ ልምምዶች እናዳብራለን። ለምሳሌ፥ አልኮል አለመጠጣት ጥሩ ክርስቲያን መሆናችንን ያሳያል ብለን እናስባለን። (ማስታወሻ፡- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ ኃጢአት የተጠቀሰው መስከር ብቻ ነው)። ዓይኖቻችንን ጨፍነንና እጆቻችንን አጣጥፈን መጸለይ እንዳለብን እናስባለን፤ ስንዘምርም ዓይኖቻችንን ጨፍነን ራሳችንን ወደ ሰማይ እናቀናለን። በዕልልታ ሃሌ ሉያ እያልን እንጮኻለን። እነዚህ ድርጊቶች ስሕተት ባይሆኑም፥ እንድናደርጋቸው እግዚአብሔር ያዘዘን አይደሉም። መንፈሳዊ ሕይወታችን ምን እንደሚመስል እነዚህ ነገሮች አያሳዩም። ጫማ ሳያወልቁም ሆነ፥ አውልቆ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማምለክ ይቻላል። ዓይንን ጨፍኖ ወይም ሳይጨፍኑ መጸለይ ይቻላል። በዝማሬ ጊዜ ዓይንን መጨፈን ወይም አለመጨፈን እጅን ማንሳት ወይም ማውረድ፥ ማጨብጨብ ወይም አለማጨብጨብ ይቻላል። በአምልኮ ውስጥ እነዚህ ውጫዊ ተግባራት ትክክል ወይም ስሕተት የሚባሉ አይደሉም። ዋናው የልባችን ሁኔታ ነው።

  1. ታላቅ እምነት ያላት አሕዛብ (ማር 7፡24-30)

ክርስቶስ ጎሰኛ ነበር? የገዛ ወገኖቹ ለነበሩት ለአይሁዶች ብቻ ይጨነቅ ነበር? ወይስ ለአሕዛብም ያስብ ነበር? ለሮማውያን አንባቢዎች እነዚህ ጥያቄዎች አስፈላጊዎች ነበሩ። ስለሆነም፥ ማርቆስ ክርስቶስ ወደ ሶርያና ፊንቂ ተጉዞ አሕዛብ የነበረች ሴት እንዳገኘ አብራርቷል። ክርስቶስ በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት አይሁዶችን በመጀመሪያ ለማገልገል መጠራቱን ተናግሯል። ስለዚህ በብሉይ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔር ልጆች የነበሩትን አይሁዶች መግቦ ገና አልረካም ነበር። እግዚአብሔር፥ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ አሕዛብ እንዲሄዱ ገና አላዘዛቸውም ነበር። ይህን ማለት ግን ክርስቶስ ስለ አሕዛቡ ሕዝብ አያስብም ማለት አይደለም። ሴቲቱ ክርስቶስ አጋንንትን ለማውጣት እንደሚችል በመግለጽ እምነቷን ስታሳይና እግዚአብሔር በረከቶቹን ለአሕዛብ የማዳረስ ባሕርይ እንዳለው ስታመለክት፥ ክርስቶስ ልጇን ፈወሰላት፡፡ የሚገርመው የእግዚአብሔር ልጆች የነበሩት አይሁዶች፥ “ውሾች” ናቸው ከሚሏቸው ከአሕዛብ ያነሰ እምነት ነበራቸው።

  1. ኢየሱስ በአጋንንት የተያዘ ደንቆሮና ዲዳ ሰው ፈወሰ (ማር. 7፡31-37)

የክርስቶስ ፈውስ በአንድ መንገድ ብቻ አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ በቃሉ በመናገር፥ ሌላ ጊዜ በእጁ በመዳሰስ ሰዎችን ይፈውስ ነበር። በዚህ ስፍራ ክርስቶስ ሰውዬውን እንትፍ ብሎ በመዳሰስ ፈውሶታል። ይህም የደነቆሩትን ጆሮዎች ነካ፥ መናገር በተሳነው ምላስ ላይ እንትፍ አለ፥ ከዚያም በጸሎት ወደ ሰማይ ተመለከተ። እግዚአብሔር በተለያዩ መንገዶች ለጸሎት መልስ ስለሚሰጥ ሁልጊዜም አንድ ዓይነት ስልት ላይከተል ይችላል። ምሥጢሩና ኀይሉ የሚመጣው ከክርስቶስ ማንነት ነው። ሰዎች መንፈሳዊ ውጤት የሚያመጡት በተወሰነ መንገድ በመሄዳቸው፥ ወይም በመስበካቸው እንደሆነ በማሰብ እንዳንሳሳት መጠንቀቅ አለብን። ውጤቶችን የሚያመጣው የአሠራር መንገድ ሳይሆን፥ እዚአብሔር ራሱ የሚፈጽመው ተግባር ስለሆነ፥ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ከእውነት የራቀ ሊሆን ይችላል። እግዚአብሔር አህያን ለማናገር ከቻለ (ዘኁል. 22፡28) ማንንም ሰው ሊያናገር ወይም የፈለገውን መንገድ ለክብሩ ሊጠቀም ይችላል።

ሰዎችን ያስደነቀው የክርስቶስ መፈወስ ብቻ ሳይሆን፥ ሁሉንም በሚገባ መፈጸሙ ነበር። ነገሮችን የምናከናውንበት መንገድ ነገሮችን ከማከናወን እኩል አስፈላጊ ነው። ያለ መልካም ዝግጅት የይድረስ ይድረስ ተግባር ብናከናውን ድርጊቱ ግምት ላይ ይጥለናል። ይህን ብናደርግ ለእግዚአብሔር ክብር ሳናስብ የራሳችንን ፍላጎት የምንፈጽም መሆናችንን ያሳያል። ዓለምን የፈጠረውና ሁሉም «መልካም ነው» ያለው እግዚአብሔር፥ ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ እንድናከናውን ይፈልጋል። ከሥራ ላለመባረር፥ በትምህርት ቤት ከክፍል ወደ ክፍል ለማለፍ ወይም መንፈሳዊ ለመምሰል ላይ ላዩን ከመጣር ይልቅ፥ ፍሬ ያለው ሥራ ከልባችን ለመሥራት መትጋት አለብን፡፡

የውይይት ጥያቄ ሀ) በግማሽ ልብ የተሠሩ ነገሮች በከፍተኛ ጥንቃቄ ከተሠሩት እንዴት ይነጻጸራሉ? ይህ ምን ልዩነት ያስከትላል? ) ሥራችን ባሕርያችንንና ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያሳየው እንዴት ነው? ሐ) ይህ ትምህርት የማስተማርንና የስብከት አገልግሎታችንን እንዴት ሊለውጠው ይገባል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ማርቆስ 6፡1-56

1. ኢየሱስ ባደገባት የናዝሬት ከተማ ተቀባይነትን አጣ (ማር. 6፡1-6)

ለብዙ ሰዎች፥ በተለይም እርሱን በቅርብ ለሚያውቁት ከስብእናው አልፎ የኢየሱስን መለኮታዊነት መመልከቱ ከባድ ነበር። በሥጋዊ ሁኔታው ኢየሱስን ከሌሎች ሰዎች የሚለይ ምንም ነገር አልነበረም። በአሁኑ ዘመን የክርስቶስን ሥዕል በብርሃን አሸብርቆ መሥራት የተለመደ ቢሆንም፥ ትክክለኛ መልኩ እንደዚህ ዓይነት አልነበረም። የናዝሬት ሰዎች ለምን ሊቀበሉት አልፈቀዱም? ምክንያቱም ከተአምራቱ ሁሉ ባሻገር፥ መለኮታዊነቱን ሊመለከቱ አልቻሉም ነበር። ኢየሱስ እንደ ሰው ተራ የአናጺነት ተግባር የሚያከናውን ሰው ነበር። ቤተሰቦቹ ድሆችና በማኅበረሰቡ ውስጥ የማይታወቁ ነበሩ። በሥጋዊ ሁኔታው መሢሕ የሚያስመስል ምንም ዓይነት ነገር አልነበረውም። ማርቆስ የኢየሱስን መለኮታዊነትና ሰብአዊነት ሚዛናዊ አድርገን ማነጻጸር እንዳለብን ገልጿል። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም፥ ሰው ነው። ግልጽ ተቃውሞ በነበረበት ናዝሬት ኢየሱስ ተአምራትን የማድረግ ኃይል ቢኖረውም፥ ይህንኑ ከማድረግ ተቆጥቧል።

2. ኢየሱስ 12ቱን ደቀ መዛሙርቱን ላከ (ማር. 6፡6-13)።

አንድ ሰው ከተወሰነ ሥራ በላይ ሊያከናውን አይችልም። ስለሆነም፥ አገልግሎቱ እንዲያድግና ወደ ሁሉም ሰው እንዲደርስ ከተፈለገ፥ ክርስቶስ ሥራውን ለማከናወን ሌሎችን ማሠልጠን ያስፈልገው ነበር። ክርስቶስ ለተወሰነ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ሲያሠለጥን ነበር። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ስለ ንስሐ ሲሰብክ፥ አጋንንትን ሲያወጣና ሰዎችን ሲፈውስ ተመልክተዋል። አሁን የተመለከቱትን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ጊዜ ደረሰ። ክርስቶስ ብዙ ሰዎች ወንጌል የሚሰሙበትን አጋጣሚ ለማመቻቸትና ደቀ መዛሙርቱን በመፈተን ለአመራር ለማዘጋጀት ሲል፥ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው። ለዚህም ሁለት ምክንያቶች ነበሩ። በመጀመሪያ፥ እርስ በርሳቸው መደጋገፍ ነበረባቸው። አንድ ሰው (ወንጌላዊ) በቀላሉ ብቸኝነትና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሊሰማው ስለሚችል፥ ሁለት ሆነው ኅብረት ሊያደርጉና ሊበረታቱ ችለው ነበር፡፡ ሁለተኛ፥ በአይሁዶች ልማድ አንድን እውነት ለማጠናከር ቢያንስ የሁለት ሰዎች ምስክርነት ወሳኝ ነበር (ዘዳግ 19:5)። ከዚህ የተነሣ፥ ስለ ክርስቶስ በቂ ምስክሮች ነበሩ። ክርስቶስ ያደረገውን ሁሉ (መስበክ፥ አጋንንትን ማውጣትና መፈወስን) 12ቱ ደቀ መዛሙርት የማከናወን ብቃት ተሰጥቷቸዋል። ማርቆስ ክርስቶስ ይህንን ሥልጣንና ኀይል እንደ ሰጣቸው ያሳያል። በተመሳሳይ መንገድ የእኛም ኃይልና ሥልጣን የሚመነጨው ከራሳችን ሳይሆን ከክርስቶስ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- መሪዎች ብዙውን ጊዜ እንደ ልባቸው የሚረዳቸው ሰው እንደሌለ በመግለጽ ያማርራሉ። ሀ) ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ማሠልጠኑ እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን መሪ አገልግሎቱን ለማስፋትና የቤተ ክርስቲያንን የአመራር ፍላጎቶች ለማሟላት፥ ሊያከናውን ስለሚገባው ተግባር ምን ዓይነት አርአያነትን ይሰጣል? ለ) ይህ ብዙም የማይታየው ለምን ይመስልሃል? ሐ) አንተ የቤተ ክርስቲያን መሪ ከሆንህ፥ እግዚአብሔር አሠልጥነህ በሥራህ ውስጥ የምታሳትፋቸውን አምስት ወጣቶች እንዲሰጥህ በጸሎት ጠይቅ።

3. የመጥምቁ ዮሐንስ አንገት መቀላት (ማር. 6፡14-29)

ማርቆስ የዮሐንስን መሞት የገለጸው አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችን በመጨመር ነበር። ለምን? ምናልባትም የመጥምቁ ዮሐንስ ሞት በሌሎች ላይ ለሚደርሰው ስደት አርአያነት ያለው ተግባር ሳይሆን አይቀርም። መጥምቁ ዮሐንስ ክፋትን ስለ ተቃወመ ታስሮ ነበር። ሰዎች በኃጢአታቸው ሲቀጥሉ ዝም ብሎ ሊመለከታቸው ይችል የነበረ ቢሆንም፥ ይህን አላደረገም። እኛም በተመሳሳይ መንገድ የሰዎችንና የአገራችንን ኃጢአት ማጋለጥ አለብን። ይህንን በምናደርግበት ጊዜ ግን ስደት ሊገጥመን እንደሚችል ማወቅ አለብን።

4. ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን መገበ (ማር 6፡30-44)።

ማርቆስ ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን እንደ መገበ በገለጸበት ታሪክ ውስጥ፥ ስለ ጠቅላላዎቹ ደቀ መዛሙርት የስብከት ጉዞ ዘግቧል። «ሐዋርያ» የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ ሌላውን ሰው ወክሎ አንድን ተግባር የማከናወን ሥልጣን የተሰጠውን ሰው ያመለክታል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ፥ ይህ ቃል በሁለት የተለያዩ መንገዶች አገልግሏል። በመጀመሪያ፥ ይህ ለ12ቱ ደቀ መዛሙርት የተሰጠ ስያሜ ነው። አዲስ ኪዳን ሁልጊዜም እነዚህ 12 ደቀ መዛሙርት ቤተ ክርስቲያንን ለመምራትና ከእግዚአብሔር የሆነውንና ያልሆነውን ለመበየን ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው አድርጎ ያቀርባል። በተጨማሪም፥ አዲስ ኪዳን ጳውሎስም የ12ቱን ያህል ሥልጣን እንዳለው ያስተምራል (ሮሜ 1፡1)። ከጳውሎስና ከ12ቱ ሐዋርያት ሞት በኋላ በቤተ ክርስቲያን እንዲህ ዓይነት ልዩ ስፍራ የነበረው ሰው እንደ ነበር የሚያመለክት መረጃ የለም። ከእነዚህ መሪዎች ሞት በኋላ የዚህ ዓይነቱ ሥልጣን እንዳበቃ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ጸሐፊዎች ጠቅሰዋል። ስለዚህ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሰዎች ምን ሊያደርጉ እንደሚገባ ለመናገር የሚያስችል ፍጹም ሥልጣን ያላቸው ሐዋርያት ይኖራሉ ብለን መጠበቅ የለብንም። በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በቤተ ክርስቲያን ላይ ሙሉ ሥልጣን ያለን ሐዋርያት ነን የሚሉ ሰዎች ተግባር፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው አደገኛ ትምህርት ነው።

ሁለተኛ፥ ሌሎችም ሐዋርያት ተብለው ተጠርተዋል። ምንም እንኳ የተለየ ሥልጣን ቢኖራቸውም፥ የ12ቱንና የጳውሎስን የሚያህል ሥልጣን አልነበራቸውም። እነዚህ አገልጋዮች (እና የአዲስ ኪዳን የትንቢት ስጦታ የነበራቸው ሰዎች) ዐበይት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ተደርገው የሚቆጠሩ ሲሆን፥ ምናልባትም እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን የመትከልና በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የመምራት ስጦታ ከሰጣቸው ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ሳይሆኑ አይቀሩም። በርናባስ (የሐዋ. 14፡14፥ የጌታ ወንድም የሆነው ያዕቆብ (ገላ. 1፡19)፥ አንዲራኒቆንና ዩልያን (ሮሜ 16፡7) ሐዋርያት መሆናቸው ተጠቅሷል።

ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን ከመገበበት ታሪክ፥ ስለ ኢየሱስ አያሌ እውነቶችን እንመለከታለን። በመጀመሪያ፥ ኢየሱስ የሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት፥ ነገሮችን የመለወጥና የማብዛት ሥልጣን ያለው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ሁለተኛ፣ ኢየሱስ መልካም እረኛ መሆኑን እንመለከታለን። በመዝሙር 23፡1 እንደ ተመለከተው፥ ክርስቶስ የበጎቹን ፍላጎት ያሟላል። ይህ ታሪክ የክርስቶስ ተከታዮች ለሥጋዊ ፍላጎቶቻቸው፥ በተለይም ለሚበሉት ምግብ መጨነቅ እንደሌለባቸው ያስተምራል። ክርስቶስ ሁልጊዜም ለተከታዮቹ በመራራት ፍላጎታቸውን ያሟላላቸዋል። በመጨረሻም፥ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት (በተለይም ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች) ያላቸውን ትንሽ ነገር ወስዶ በማብዛት የእግዚአብሔርን መንጋ ፍላጎቶች እንደሚያሟላ የሚያስገነዝብ ነው። እንዲሁም፥ የሰዎችን ፍላጎቶች እንዴት እናሟላለን ብለን ሳንጨነቅ፥ ለእግዚአብሔር ያለንን በልግስና ልንሰጥና እግዚአብሔር እንደሚያባዛው ልንተማመንበት ይገባል። ምክንያቱም ሕዝቡ የእግዚአብሔር ሀብት በመሆናቸው፥ እግዚአብሔር ይራራላቸዋል፤ ስለሆነም፥ መሪዎቹ የሕዝቡን ፍላጎቶች እንዲያሟሉም ይጠቀምባቸዋል።

5. የኢየሱስ በውኃ ላይ መራመድ (ማር. 6፡45-56)

አንዳንድ ጊዜ ፍርሃት ተፈጥሯዊና ጠቃሚ ምላሽ ነው። በመኪና መንገድ ላይ ተጠንቅቀን እየሄድን ሳለ፥ ጥሩምባው ሲነፋና ፍሬኑ በሚያዝበት ወቅት ሰቅጣጭ ድምፅ ሲሰማ፥ በፍርሃት ከመንገዱ ፈቀቅ እንላለን። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ፍርሃት ያለማመን ምልክት ይሆናል። የክርስቶስ ተከታዮች እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ በእምነት ለመመላለስ ከፈለጉ፥ የስደትንና የችግሮችን ፍርሃት ማስወገድ አለባቸው። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በውኃ ላይ ሲራመድ በማየታቸው፥ (አይሁዶች) መናፍስት ከውኃ ውስጥ ወደ ላይ እንደሚወጡ የሚያስረዳ ባሕል ነበራቸው) እና በነፋሳት ላይ ባሳየው ኀይል በመደነቃቸው፥ «ያለ መጠን እጅግ ተገረሙ ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር።” (ማር. 6፡51-52)። ክርስቶስን በበለጠ ስናውቅ፥ እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንዳለ ሁልጊዜም ማስታወስ አለብን። እርሱ ከእኛ ጋር ካለ የሚያስፈራን ነገር አይኖርም። ክርስቶስ ፍላጎታችንን ሁሉ ከማሟላቱም በላይ፥ የተፈጥሮንም ኃይል ይቆጣጠራል። ነፋስን መቆጣጠር ከቻለ፥ ማዕበልንም ሊቆጣጠር ይችላል። ማዕበሉን እንደተቆጣጠረ ሁሉ፥ ደቀ መዛሙርቱ የሚጋፈጧቸውን ችግሮችና ስደትም ሊቆጣጠር ይችላል። የሕይወት ማዕበል በሚያጋጥመን ጊዜ የምንፈራ ከሆነ ክርስቶስ ነገሮችን ሁሉ የሚቆጣጠር የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆኑ እምነት የለንም ማለት ነው። እምነት በቃል ወይም በዝማሬ ብቻ የሚገለጽ አይደለምና። ሕይወታችንን በምናምነው እውነት ላይ ተመሥርተን ልንመራ ይገባል። ክርስቶስ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ ካመንን፥ እርሱ ነገሮችን እንደሚቆጣጠር በማወቅ ወደ ሕይወታችን ለሚመጡ ጉዳዮች ሁሉ በእርሱ ልንተማመን ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በፍርሃት ስለተያዝክበት ጊዜ ግለጽ። ይህ በክርስቶስ ላይ ስላለህ የእምነት ጥልቀት ምን ያሳያል? ለ) ፍርሃት፥ አንድ ክርስቲያን እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ እንዳይኖር የሚያደርገው እንዴት ነው? ሐ) የፍርሃት መድኃኒቱ ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢየሱስ የሞተች ልጅ አስነሣ፥ የታመመች ሴት ፈወሰ (ማር. 5፡21–43)

በሰዎች ላይ ከፍተኛ ፍርሃትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚያስከትሉ ሁለት ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ፥ ከሁሉም የከፋው የሰው ልጅ ጠላት ሞት ነው። ኢየሱስ በሞት ላይ ምን ሥልጣን አለው? የሚለው ምላሽን የሚሻ ጥያቄ ነበር። ሁለተኛ፥ የረዥም ጊዜ ሕመም አለ። ኢየሱስ ለረዥም ጊዜያት ሐኪሞችን ሁሉ አሸንፎ የቆየን በሽታ ሊፈውስ ይችላል? ማርቆስ እነዚህን ሁለት ታሪኮች በመጠቀም የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ፥ እነዚህን ሁለት ጠላቶች ሊያሸንፍ እንደሚችል አሳይቷል።

የመጀመሪያው ታሪክ ለ 12 ዓመታት ደም ስለሚፈሳት ሴት የሚናገር ነበር። ከዚህ በሽታ የተነሣ ሴትዮዋ ከማኅበረሰቡ ተገልላ ትኖር ነበር። የዚህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ብዙ ሴቶች ከትዳራቸው ለመፈናቀል ተገድደዋል። ይህች ሴት መፍትሔ ለማግኘት ወደ ብዙ ሐኪሞች ዘንድ ብትሄድም አልተሳካለትም ነበር። የመጨረሻ ተስፋዋ ኢየሱስ ስለነበር፥ በሕዝብ መካከል እየተጋፋች ሄዳ ልብሱን ነካችው። ወዲያውም ተፈወሰች።

ኢየሱስ በነበረበት ስፍራ እንዲቆምና ይህች ሴት እንደነካችው እንድታምን ያስገደዳት ለምን ነበር? ኢየሱስ ሁሉንም ነገር ስለሚያውቅ፥ እንደ ነካችው ቀድሞውኑ ተረድቶ ነበር። ክርስቶስ ይህንን ያደረገው የመፈወስ ችሎታውን ለማሳየት አልነበረም። ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ስለ ተአምራቱ ለሌሎች እንዳይናገሩ ሰዎችን ያስጠነቅቅ ነበርና። ነገር ግን ኢየሱስ ለዚህች ሴት ስለ ራሱ አንድ ነገር ለማስተማርና ወደ መንፈሳዊ ፈውስም ለመምራት ፈልጎ ነበር። ኢየሱስ ምንጊዜም በሥጋዊ ፈውስ ብቻ ስለማይረካ፥ ለእያንዳንዱ ሰው የመንፈሳዊ ፈውስ ዕድል ለመስጠት ይፈልጋል። ለዚህም ነው ሕዝቡን ሁሉ ከመፈወስ ይልቅ በግለሰብ ደረጃ መፈወስን የመረጠው። ስለሆነም ኢየሱስ ሴቲቱ የተከሰተውን ሁኔታ እንድታምን በማድረግ፥ እምነቷ ሥር እንዲሰድ እያደረገ ነበር። ሴትዮዋ ሥጋዊ ፈውስ ብታገኝም፥ መንፈሳዊ ፈውስና እውነተኛ ሰላምን ማግኘት ያስፈልጋት ነበር። በማርቆስ ወንጌል ኢየሱስ ለፈውስ የተጠቀመው ቃል «መዳን» ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ስለሆነም ሥጋዊ ፈውስ አግኝታ ከመከራዋ የዳነችው ይህች ሴት፥ አሁን ደግሞ መንፈሳዊ ፈውስን አግኝታ ሰላምን ተጎናጽፋለች።

በሁለተኛው ታሪክ፥ ኢየሱስ በቀላል የትእዛዝ ቃል የኢያኢሮስን ልጅ ከሞት አስነሥቷል። ከኢየሱስ ጋር ሲነጻጸር ሞት ኀይል ያለው ጠላት አይደለም። በቀላል የትእዛዝ ቃል ሁላችንም ከሞት እንነሣለን። ለዚህም ነው ጳውሎስ ለክርስቲያኖች የሞት መውጊያ እንደ ተሰበረ የጻፈው (1ኛ ቆሮ. 15፡53-56)።

በዚህ ታሪክ ውስጥ ሌላም አስገራሚ ነገር ተከስቷል። ኢየሱስ ተአምሩን ለማሳየት ደቀ መዛሙርቱን ሁሉ ከመውሰድ ይልቅ፥ ዮሐንስን፥ ያዕቆብንና ጴጥሮስን ብቻ ወሰደ። ይህ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ቁልፍ መሪዎች ለሚሆኑት ለእነዚህ ሦስት ደቀ መዛሙርት፥ የሥልጠና ዓይነት ተግባር ነበር። ኢየሱስ ከ12ቱ በላይ በጥልቀት አስተምሯቸዋል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ማርቆስ 5:1-20

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የሰይጣን ኀይል አይሎ ያየህበትን ጊዜ ግለጽ። ለ) የኢየሱስ ኀይል ሰይጣንን ሲያሸንፍ ያየህበትን ሁኔታ ዓለጽ፡፡ ይህ ስለ ኢየሱስ ምን ያስተምረናል? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች ሰይጣንን፡ ቡዳን፥ እርግማንን የመሳሰሉትን የሚፈሩት ለምንድን ነው? መ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ፍርሃት ምን ያስተምራል?

የግርማ አባት ጠንቋይ ነበሩ። እርሱ ከልጅነቱ ጀምሮ ለሰይጣን የተሰጠ በመሆኑ ብዙ ክፉ መናፍስት ሰፍረውበት ነበር። እያደገ ሲመጣ የሰይጣን ጭቆና በዛበት። አንድ ቀን ጭንቀቱን መቋቋም ተስኖት ራሱን ለማጥፋት ሞከረ። በዚህ ጊዜ አንድ ክርስቲያን ሕይወቱን አተረፈለት። ክርስቲያኑ በኢየሱስ ክርስቶስ ቢያምን ከሰይጣን ነፃ እንደሚወጣ ገለጸለት፡ ግርማም ምስክርነቱን ሰምቶ አመነ። ወዲያውኑ ክፉ መናፍስት ወደ መሬት ጣሉት። እዚያ ወድቆ ይንፈራፈርና ያጓራ ጀመር። ክርስቲያኑ ወዳጆቹን ሰብስቦ ብዙ ጸሎት ካደረገ በኋላ፥ መናፍስቱ ለቅቀውት ወጡ።

በቀጣዩ እሑድ ግርማ በአቅራቢያው ወደምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ሄደ። በአምልኮው ጊዜ አንድ ሰው፥ ሰይጣን ታስሮ ወደ ጥልቁ እንዲወርድ እያዘዘ ሲጸልይ ሰማ። ሰዎች፥ «በኢየሱሱሱሱሱሱስ ስም?» እያሉ ይጮኹ ጀመር፡ «ሰዎች የኢየሱስን ስም እንዲህ የሚጠሩት ለምንድን ነው?» ሲል አሰበ። ክርስቲያኖቹ የግርማ አባት ኃይል አላቸው ብሎ የሚያምንባቸውን ቃላት በሚደጋግምበት መንገድ የኢየሱስ ስም ምትሐታዊ ኃይል አለው ብለው ስለሚያምኑ ይሆን?

በሌላ ስፍራ ከአንድ ጠንቋይ አጠገብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተከፍቶ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ጠንቋዩ ሌሊት ሌሊት ከበሮውን እየመታ በማጓራት ክርስቲያኖችን ይረግም ነበር። በዚህ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤት ተማሪዎች ይፈራሉ። ከመኝታ ክፍላቸው ተሯሩጠው በመውጣት፥ «በኢየሱሱሱሱስም ስም!» እያሉ ድምፃቸውን አጉልተው ይጮኻሉ፡፡

ኢየሱስ ከሰይጣን ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት አለው? እኛ በሰይጣን ላይ ምን ሥልጣን አለን? የኢየሱስ «ስም» ከሥልጣናችን ጋር ምን ግንኙነት አለው? የኢየሱስን ስም እየደጋገሙ መጥራቱ ተጨማሪ ኃይል ይሰጠዋል?

ይሄ የሚያጠራጥር አይደለም። የምንፋጠጠው ከሰይጣን፥ ከትልቅ ጠላት ጋር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሊውጠን ፈልጎ ከሚያገሳ አንበሳ ጋር ያነጻጽረዋል (1ኛ ጴጥ. 5፡8)። ጎይሉ ከፍተኛ ነው። ተአምራትን መሥራት ይችላል፥ ተፈጻሚነት የሚኖራቸውን እርግማኖችና ሌላም ሊያደርግ ይችላል። ነገር ግን ኢየሱስን በመታዘዝ ከሚመላለሱ ክርስቲያኖች ጋር ሲነጻጸር፥ ጎይሉ ምንድን ነው? ከዚህ በበለጠ ደግሞ ከኢየሱስ ጋር ሊነጻጸር፥ ኀይሉ ምንድን ነው? ለክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን እውነት በግልጽ መረዳቱ አስፈላጊ ነው። ልናስወግዳቸው የሚገቡን ሁለት አክራሪ አቋሞች አሉ። ብዙ የተማሩ በተለይም በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች ሰይጣንን ችላ ይላሉ። ሰይጣን መኖሩን ሊያምኑ ቢችሉም፥ ስለ እርሱ አያሳስባቸውም። ዛሬ እንደምንመለከተው ሰይጣን ብርቱ ጠላት ስለሆነ፥ እነዚህ ክርስቲያኖች በእርሱ ተሸንፈዋል። ሰይጣን ክርስቲያኖችን ለማሸነፍ የሚሠራባቸውን መንገዶች የማያውቁትን ክርስቲያኖች በቀላሉ ያጠቃቸዋል። ሌሎች ደግሞ ስለ ሰይጣን ሁልጊዜም ያስባሉ። በሚጸልዩበት ጊዜ ሁሉ ሰይጣን ወደ ጥልቁ እንዲጣል ያዝዛሉ። የሚደርሰው ጉዳት ሁሉ የሰይጣን ጥቃት እንደሆነ ያምናሉ። ብዙውን ጊዜ የሰይጣንን ኀይል ይፈራሉ። እርሱን እየፈሩ ስለሚኖሩ ሰይጣን እነርሱንም አሸንፎአቸዋል። ይህም መንፈሳዊ ሕይወታቸው ጠንካራና በድፍረት የተሞላ እንዳይሆን ያደርገዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰይጣን ብዙ ያስተምራል። አራት ዐበይት እውነቶችን ማስታወስ አለብን፡

ሀ. ሰይጣን ህልውናው የተረጋገጠ ኀይለኛ ጠላታችን ነው። የእግዚአብሔር መራራ ጠላት ሲሆን፥ ሰዎችን በራሱ የጨለማ መንግሥት ለማቆየት ወይም የእግዚአብሔር መንግሥት አካል የሆኑትን ወገኖች ውጤታማነት ለመቀነስ ተግቶ ይሠራል።

ለ. ኢየሱስ በሰይጣን ላይ ሙሉ ሥልጣንና ኀይል አለው። ሰይጣንና አጋንንት ኢየሱስ ማን እንደሆነ ስለሚያውቁ ይፈሩታል (ያዕ. 2፡19)። ይታዘዙታል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንደተጻፈው ኢየሱስ ከሰይጣን ወይም ከአጋንንት ጋር ሲገናኝ፥ በአንዲት የትእዛዝ ቃል ያሸንፋቸው ነበር።

ሐ. ሰይጣን ተሸንፎአል። ኢየሱስ በመስቀል ላይ የኀጢአታችንን ዕዳ በመክፈል ሰይጣን የእግዚአብሔርን ልጆች ለመክሰስ የሚጠቀምበትን ሥልጣን አስወግዷል። በዚያም የፍጻሜያቸውን እርግጠኛነት በማሳየት ምርኮ ወስዷል (ቆላ. 2፡13-15)። በሰይጣን ላይ ዐቢዩን ድል ከተጎናጸፍን በኋላ፥ ሰይጣን የሽንፈት ጦርነት በሚያካሂድበት ዘመን ውስጥ እንኖራለን። ኢየሱስ በዳግም ምጽአቱ ሰይጣንና አጋንንቱን ወደ ሲኦል በመስደድ ሙሉ በሙሉ ያሸንፋቸዋል (ራእይ 20፡7-10)።

መ. ክርስቲያኖች “በክርስቶስ” ስለሆንን፥ ጥበቃውና ሥልጣኑ አይለየንም። መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎቻችንን እስከ ለበስን ድረስ (አፌ. 6፡10-18 አንብብ)፥ የሰይጣንን ጥቃት መፍራት የለብንም። ሰይጣን አምልኳችንን እንዳይረብሽ ወይም በሕይወታችን ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ፥ እያሰርነው እንድንጸልይ የተሰጠ ትእዛዝ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አይገኝም። ትኩረት የተሰጠው መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎችን በመልበስ፥ ከሰይጣን ጥቃት የተጠበቅን መሆናችንን በማረጋገጡ ላይ ነው። በብቁ ሁኔታ የታጠቀ ሠራዊት የተሸነፈን ዓማፂ መፍራት የለበትም። እናም ሰይጣንን መፍራት የለብንም። በክርስቶስ ሥልጣን ሥር እስከ ተጠለልን ድረስ ሰይጣንን እናሸንፋለን። በራሳችን ኀይል ብንዋጋ ግን ምንጊዜም አናሸንፍም። “በኢየሱስ ስም” ከታገልነው በራሳችን ላይሆን፥ በክርስቶስ ኃይል እናሸንፋለን።

ይሁንና ብዙ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ስም እየጸለዩ ሰይጣንን መዋጋት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በትክክል አያውቁም። «በኢየሱሱሱሱስ. . . ስም» የሚሉት፥ ስሙን እየጠሩ የሚጮኹት፥ ወይም የኢየሱስን ስም ሦስት ጊዜ የሚጠሩት ለምንድን ነው? ይህ ሁሉ የመጣው መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ ስም ስላለን ሥልጣን የሚያስተምረውን ጠንቅቆ ካለማወቅ ነው። «በኢየሱስ ለም» መጸለይ ማለት ምን ማለት ነው? በመጀመሪያ፥ ኀይልን የምናገኘው በኢየሱስ ስም ብለን በመጮኻችን አይደለም። ስለሆነም «በኢየሱሱሉሱስ ስም» ማለቱም ሆነ መጮኹ ወይም ሦስት ጊዜ መደጋገሙ የሚጨምረው ነገር አይኖርም። ስለዚህ የኢየሱስን ስም እንደ ምትሐታዊ ቃል ከመጠቀም መጠንቀቅ አለብን። ይህን በማድረግ ክፉ መናፍስትን ለመቋቋም ክታቦችን ከሚያንጠለጥሉ ሰዎች ጋር እንዳንመሳሰል ልንጠነቀቅ ይገባል። ሁለተኛ፥ በራሳችን ኀይልና ሥልጣን እንደሌለን ለሰይጣን መናገራችን ነው። የጸሎታችንና የትእዛዛችን ሥልጣን ሁሉ የሚመጣው ከክርስቶስ ኀይል ነው። እኛ ያለን በውክልና የተሰጠን ኀይልና ሥልጣን ብቻ ነው። ስለዚህም፥ በኢየሱስ ክርስቶስ የምናምንና ሰይጣንን ለማሸነፍ፥ ከክርስቶስ ሥልጣን የተሰጠን ሰዎች በመሆናችን፥ ሰይጣንን እናዝዘዋለን። (ማስታወሻ፡- ይህ ጸሎታችንን “በኢየሱስ ስም” ብለን ከምንፈጽምበት ሁኔታ ጋር አንድ ዓይነት ፍች አለው። ይህን ስንል ወደ ሁሉን ቻይ አምላክ ለመምጣትና ከእርሱ ዘንድ መልስ ለመጠበቅ የቻልነው፥ ከክርስቶስ ጋር ባለን ግንኙነትና ወደ እግዚአብሔር እንድንመጣ በሰጠን ሥልጣን ምክንያት መሆኑን መግለጻችን ነው። ይህም በእግዚአብሔር ፊት የቀረብነው በራሳችን ጽድቅና የብቃት ስሜት እንዳልሆነ የምንገልጽበት ነው።)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች የኢየሱስን ስም ጮክ ብለው የሚጠሩት ወይም የሚደጋግሙት ለምንድን ነው? ለ) ከላይ ከቀረበው ትምህርት አንጻር፥ ጸሎታችን እንዴት ሊለወጥ ይገባል?

ኢየሱስ በሰይጣን ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው በግልጽ ከሚያሳዩት ነገሮች አንዱ፥ በጌርጌሴኖን አካባቢ በብዙ ክፉ መናፍስት የተያዘውን ግለሰብ ባዳነበት ሁኔታ ተገልጾአል። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው፥ እነዚህ ክፉ መናፍስት ክርስቶስን ለይተው አውቀውታል። ስለዚህም፥ ኢየሱስ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ” እንደሆነ በግልጽ አውጀዋል። ይህም ኢየሱስ ራሱ አምላክ እንደሆነ የሚያመለክት ነበር። ኢየሱስ በእነርሱ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለውና እግዚአብሔር ለዘመናት የወጠነው ዕቅድ በሚፈጸምበት ጊዜ፥ ኢየሱስ ወደ ሥቃይ ስፍራ (ሲዖል) እንደሚልካቸው ያውቁ ነበር።

ይሁንና፥ የኢየሱስ ጎይል ከሰይጣን ጋር የሚነጻጸረው እንዴት ነው? ኢየሱስ ከሰይጣን የሚበልጠው ትንሽ ብቻ ነው? ማርቆስ የኢየሱስ ኀይል ፍጹማዊ እንደሆነና መጨረሻ በሌለው ሁኔታ ከሰይጣን ኀይል እንደሚለቅ አሳይቷል። በሮም ሠራዊት፥ አንድ ሌጌዎን (ጭፍራ) 6,000 ወታደሮችን ይይዛል። አጋንንት መንፈሳዊ ፍጥረታት ስለሆኑና አካላዊ ስፍራ ስለማይይዙ፥ በዚህ አንድ ግለሰብ ሰውነት ውስጥ 6,000 ክፉ መናፍስት ነበሩ። ነገር ግን ኢየሱስ ይህን የአጋንንት ሠራዊት ምን አደረገው? ፈራቸው? በፍጹም። አጋንንቱ እርሱን እንዳዩ በፍርሃት ተሸበሩ። ወደ ሥቃይ ስፍራ እንዳይልዳቸው ኢየሱስን ለመኑት። ቀላል ትእዛዙን ሰምተው ለመታዘዝ ተገደዱ። ክፋት በባሕርዩ ራሱ ያጠፋል። ይህንኑ ለማሳየት፥ ክፉ መናፍስት ወደ እሪያዎች ገብተው ገደሏቸው። ክፉ መናፍስቱ አልሞቱም ነበር። ነገር ግን የመኖሪያ ስፍራቸው ተወሰደባቸው።

በተጨማሪም፥ ማርቆስ ለዚህ የኢየሱስ ታላቅ ተግባር ሁለት የተለያዩ ምላሾችን ያነጻጽራል። አብዛኞቹ ሰዎች ለኢየሱስ ለመገዛትና እርሱን ለማክበር ስላልፈለጉ፥ ከአካባቢያቸው ለቅቆ እንዲሄድ ጠየቁት። በአጋንንት ተይዞ የነበረው ሰውዩ ግን ኢየሱስን ለመከተል ፈለገ። ኢየሱስ ግን ለዚህ ሰው የተሻለ አገልግሎት ሰጠው። ክርስቶስ ግለሰቡ ወደ ቤተሰቡ ተመልሶ እግዚአብሔር ስላደረገለት ምሕረት እንዲመሰክር ነገረው። ከደቀ መዛሙርት የሚጠበቀው ምንድን ነው? ማርቆስ ደቀ መዛሙርት ለሌሎች ስለ ክርስቶስ መመስከር እንዳለባቸው አመልክቷል። ነገር ግን የምስክርነታችን ዋና ነገር ምን መሆን አለበት? የተወሳሰበ ክርክር ወይም ሥነ መለኮታዊ እውነቶችን ማስተማር መሆን አለበት? አይደለም። ክርስቶስ ከሁሉም የሚበልጠውን ታላቅ ምስክርነት እኛን ለማዳን ያከናወነውንና አሁንም እኛን ለመርዳት እያከናወነ ያለውን ተግባር ለሌሎች ማካፈል እንደሆነ አሳይቷል። ብዙ ሰዎች ወደ ክርስቶስ የሚመለሱት ጥሩ በሚመስሉ ክርክሮች አማካኝነት ሳይሆን፥ በሚያውቋቸው ሰዎች ሕይወት ክርስቶስ የሚሠራውን በማየት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቅርቡ ኢየሱስ በሕይወትህ እየሠራ ያለው እንዴት ነው? ለ) ይህንን ለሦስት የማያምኑ ሰዎች አካፍልና ውጤቱን ለጥናት ቡድንህ ለማካፈል ተዘጋጅ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ማርቆስ 4፡1-41

ሀ. ክርስቶስ ስለ መንግሥቱ አስተማረ (ማር. 4፡1-34)። እንደ ማቴዎስ ሁሉ፥ ማርቆስም የክርስቶስን ምሳሌዎች በአንድ ክፍል ውስጥ አስቀምጧል። ይህ ማርቆስ ስለ ክርስቶስ ትምህርት ከገለጸባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች አንዱ ነው። ክርስቶስ በእርሱ ላለማመን ልባቸውን ያደነደኑት አይሁዶች ፍርድን እንደሚቀበሉ ለማሳየት፥ በምሳሌ እንደሚናገር ለደቀ መዛሙርቱ ተናግሯል። ነገር ግን ለጥሪው ምላሽ ሰጥተው የተከተሉት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት፥ እውነትን የበለጠ እንዲረዱ በምሳሌ ያስተምራቸዋል። እነዚህ ምሳሌዎች እያንዳንዳቸው በክርስቶስ መንግሥት፣ ሕይወት ምን እንደሚመስል ያስተምራሉ።

1. የአራት ዓይነት መሬት ምሳሌ (ማር. 4፡1-20)። ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስን መልካም የምሥራች ካካፈሉ በኋላ ምን ሊጠብቁ ይገባል? ክርስቶስ ሰዎች በሦስት መንገዶች ምላሽ እንደሚሰጧቸው አስተምሯል። በመንገድ ላይ እንደወደቀው ዘር፥ ከመጀመሪያው ለመቀበል የማይፈልጉ ሰዎች ይኖራሉ። የሚያምኑ መስለው ከቀረቡ በኋላ ችግር ወይም ስደት በደረሰባቸው ጊዜ በጭንጫ መሬት ላይ እንደተዘራው ዘር የሚክዱም ይኖራሉ። አማኞች መስለው ከቀረቡ በኋላ ከደቀ መዝሙርነት ጎዳና ይልቅ የዓለምን መንገድ በመውደዳቸው ምክንያት፥ በእሾህ መካከል እንደተዘራው ዘር ወደ ኋላ የሚመለሱ ሰዎች ይኖራሉ። በአንጻሩ በመልካም መሬት ላይ እንደወደቀው ዘር እምነታቸውን በተለያዩ መንገዶች ሊገልጹ የሚችሉት ጥቂቶች ብቻ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች እነዚህን አራት ምላሾች ሲሰጡ ያየህባቸውን ሁኔታዎች በምሳሌዎች አብራራ። ለ) ለደቀ መዛሙርት እነዚህን አራት መንገዶች ማወቁ ለምን ያስፈልጋል?

2. የመቅረዝ ምሳሌ (ማር. 4፡21-25)። ክርስቶስን ለመከተል የሚፈልጉ ሰዎች የሮም ክርስቲያኖች የሚጋፈጡት ዓይነት ስደት ቢኖርም እንኳ፥ እምነታቸውን ከመደበቅ ይልቅ የእምነታቸው ብርሃን ለሁሉም እንዲያበራ ማድረግ እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባ ነበር። ከሰዎች የተሸሸጉ ምሥጢራዊ ማኅበረሰብ ከመሆን ይልቅ፥ በቃላቸው ብቻ ሳይሆን በሕይወታቸው ጭምር የክርስቶስ መንግሥት ተከታዮች መሆናቸውን ማሳየት ያስፈልጋቸው ነበር። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናቸውን ማሳየት ያስፈልጋቸው ነበር። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እርሱን ለመስማትና በሕይወታቸው ውስጥ እውነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ባይፈልጉ፥ ፍርድ እንደሚደርስባቸው አስጠንቅቋቸዋል። የክርስቶስን ትምህርት ይበልጥ ተግባራዊ ባደረጉ ቁጥር፥ ተጨማሪ መንፈሳዊ እውነቶችና ግንዛቤዎችን ይሰጧቸዋል። እኛም መንፈሳዊ እውነቶችን ተግባራዊ የማናደርግ ከሆነ፥ መንፈሳዊ እውነቶችን የመገንዘብ ችሎታችን ይቀንሳል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ መንፈስ ቅዱስ የሚያስተምረንን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብን የሚያስጠነቅቀን እንዴት ነው? ለ) በቅርቡ መንፈስ ቅዱስ ያስተማረህን ሁለት እውነቶች ግለጽ። እንዴት ተግባራዊ እያደረግህ እንደሆነ አብራራ።

3. የአዳጊ ዘር ምሳሌ (ማር. 4፡26-29)። ይህ ምሳሌ የሚገኘው በማርቆስ ወንጌል ውስጥ ብቻ ነው። ክርስቶስ በዚህ ምሳሌ፥ መንግሥቱና ቤተ ክርስቲያኑ፥ እንደ ዘር በምሥጢራዊ መንገድ በራሷ የማደግ ኀይል እንዳላት አስተምሯል። ሰዎች ዕድገቱ እንዴት እንደሚካሄድ ለመገንዘብ ቢሞክሩም፥ ሁልጊዜም ምሥጢር ይሆናል።

4 የሰናፍጭ ቅንጣት ምሳሌ (ማር. 4፡30-34)። የኢየሱስ መንግሥት፥ ጅማሬዋ ልክ እንደ ኢየሱስና 12ቱ ሐዋርያት፥ አነስተኛ ይመስላል። ኃያል መንግሥት ባላቸው በሮማውያን ዓይን ፊት፥ በጣም አነስተኛና ምንም ያማያሳስብ ሆኖ ታያቸው። ነገር ግን ያቺ አነስተኛ መንግሥት በአስደናቂ መንገድ አድጋ፥ ታላቁ የሮም መንግሥት እንዲለወጥ ታደርጋለች። ቤተ ክርስቲያንም አድጋ፥ ከሮም መንግሥት በበለጠ መልኩ ዓለምን ታዳርሳለች።

ለ. ኢየሱስ በተፈጥሮ ላይ ኃይሉን አሳየ (ማር. 4፡35-41)። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፥ በፍጥረቱ ላይ ምን ኃይል አለው? ማርቆስ ይህን ታሪክ በመናገር፥ ክርስቶስ በፈጠራት ዓለም ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው አመልክቷል። ማዕበሎችና ነፋሳት ሁሉ ለክርስቶስ ቃል ታዝዘዋል። የክርስቶስ ጎይል በደቀ መዛሙርቱ ላይ ከፍተኛ ስሜት በማሳደሩ «ፈሩ»። በተጨማሪም እርሱ ከተራ ሰው የላቀ መሆኑን ስለ ተገነዘቡ፥ ትክክለኛ ማንነቱን ለመረዳት ተገድደው ነበር።

ነገር ግን ይህ ታሪክ እካላዊም ሆነ የስደት ማዕበል፥ በክርስቶስ ተከታዮች ላይ እንደሚደርስ ያሳያል። ከዚህ ማዕበል ማምለጥ አይቻልም። በዚህም ጊዜ በፍርሃት ልንኖር ወይም ክርስቶስ ከእኛ ጋር እንዳለ በመገንዘብ በእርሱና ማዕበሉን በመቆጣጠር ችሎታው ልንታመን እንችላለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስላጋጠመህ አንድ ማዕበል ግላጽ። በዚህ ጊዜ ከምን ዓይነት ልማቶች ጋር ታግለሃል። እምነት ነበረህ ወይስ አልነበረህም? ለ) ለማዕበሉች የምንሰጠው ምላሽ በክርስቶስ ላይ ያለንን የእምነት መጠን የሚያመለክተው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)