የአራቱ ወንጌላት መግቢያ

ወንጌላት እንዴት ተጻፉ?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአማርኛ «ወንጌል» ማለት ምን ማለት ነው? ለ) «የምሥራች» ማለት ምን ማለት ነው? የምሥራች ከሚባሉ ነገሮች አንዳንዶችን ዘርዝር። ሐ) የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የመጀመሪያዎቹን አራት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት «ወንጌላት» ብለው የሰየሙት ለምንድን ነው? (ማር. 1፡1 አንብብ።) መ) ወንጌል ማለት ምን ማለት እንደሆነ በራስህ አገላለጽ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

የመጀመሪያው የአዲስ ኪዳን ክፍል ስለ ክርስቶስ ሕይወት የሚናገሩ አራት መጻሕፍት የሚገኙበት ነው። የጥንት ክርስቲያኖች እነዚህን መጻሕፍት ወንጌል በማለት ጠርተዋቸዋል። «ወንጌል» ማለት «የምሥራች» ማለት ነው። ወንጌል ከሚለው የግእዝ ቃል ይልቅ «የምሥራች» ወይም ብስራት የሚለው የተሻለ ይሆናል።

የጥንት ክርስቲያኖች እነዚህን የመጀመሪያ አራት መጻሕፍት ወንጌል ብለው የጠሩበት ምክንያት፥ እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ አንድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሰው ልጆች ኃጢአት መሥዋዕት እንዲሆንና የሰዎችንም የሞት ፍርድ ዕዳ እንዲከፍል የላከው መሆኑን የሚናገሩ መልካም ዜናዎች በመሆናቸው ነው (2ኛ ቆሮ. 5፡21)። የእግዚአብሔር ልጅ በሰዎች መካከል በመኖር የእግዚአብሔርን ባሕርይና ሕዝቡ እንዲኖሩ የሚፈልገውን ሕይወት አሳይቷቸዋል (ዮሐ. 1፡14)። ክርስቶስ ሞትን ካሽነፈና በእኛም ምትክ ያቀረበውን መሥዋዕት እግዚአብሔር እንደተቀበለው ካረጋገጠ በኋላ፥ ከሞት በመነሣት ወደ ሰማይ አርጓል። በክርስቶስና በማዳኑ የሚያምኑ ሰዎች ለእርሱ እየተገዙ መኖር አለባቸው። የኃጢአት ይቅርታ ካገኘን በኋላ፥ እንደ ልጆቹ በእግዚአብሔር መንፈሳዊ ቤተሰብ ውስጥ ተቀባይነትን እናገኛለን (ዮሐ. 1፡12)። በተጨማሪም እኛ የዓለም ምስክሮች ነን (ማቴ. 28፡19-20)።

የውይይት ጥያቄ፡- በእነዚህ አራት ወንጌላት ውስጥ የሚገኙ እውነቶች መልካም ዜናዎች ከሆኑ፥ ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ለሌሎች ለመናገር የማይፈልጉት ለምን ይመስልሃል?

በእግዚአብሔር ዕቅድ ኢየሱስ ምንም መጽሐፍ አልጻፈም። ሙስሊሞች አላህ ቁርዓን ለመሐመድ ቃል በቃል እያጻፈ ሰጥቶታል ይላሉ። ክርስቶስ ቃሉን ለደቀ መዛሙርቱ ቃል በቃል እየተናገረ አላጻፋቸውም። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በክርስቶስ ተከታዮች ልብ ውስጥ በመሥራት እግዚአብሔር ሰዎች እንዲያውቁ የሚፈልገውን አሳብ እንዲጽፉ አድርጓቸዋል። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ስለ ክርስቶስ ሕይወትና ትምህርት የሚያስረዳውን ታሪክ የጻፉት ክርስቶስ ካረገ ከ30 ዓመት በኋላ ነው።

አራቱ ወንጌላት የተጻፉት በአራት የተለያዩ ደራሲያን ነው። ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት መካከል የነበሩት ማቴዎስና ዮሐንስ የክርስቶስን ሕይወት ከመመልከታቸውም በላይ፥ ትምህርቱን ተከታትለዋል። የተቀሩት ሁለቱ የወንጌላት ጸሐፊዎች ግን የክርስቶስ ሕይወትና ትምህርት ምስክሮች አልነበሩም። ማርቆስና ሉቃስ የክርስቶስን ሕይወት ታሪክ ለመጻፍ የቻሉት ከደቀ መዛሙርቱና ከሌሎች ሰዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ነበር።

ምሑራን ወንጌላት በሂደት መጻፋቸውን ያምናሉ።

1. ወንጌል የሚጀምረው በኢየሱስ ነው። የተመሠረተውም ከሰማይ ወደ ምድር መጥቶ በኖረው በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትና ትምህርት ላይ ነው። ወንጌል የፈጠራ ታሪኮችና ተረቶች ወይም አፈ ታሪኮች ጥርቅም ላይሆን፥ እውነት ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ዮሐንስ የተደረገውን ሁሉ በዓይኖቹ እንደተመለከተ የገለጸው። ክርስቶስ በታሪክ ምዕራፍ ውስጥ የታየ እውነተኛ ሰው ነበር (1ኛ ዮሐ 1፡1-2)። ሐዋርያት ለሌሎች የተናገሯቸውን ነገሮች በዓይኖቻቸው ተመልክተዋል (የሐዋ. 10፡37-39)።

2. ከክርስቶስ ሞት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ያደረገውንና ያስተማረውን ለሌሎች መናገር ጀመሩ። እነዚህ ክርስቲያኖች ታሪኮቹን ለወዳጆቻቸው በመናገራቸው፥ ስለ ክርስቶስ ሕይወትና ትምህርት የሚያስረዱ እውነቶች ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን መተላለፍ ጀመሩ። ሐዋርያት ብሉይ ኪዳንን በሚያጠኑበት ጊዜ፥ በክርስቶስ ሕይወት ብዙ ትንቢቶች እንደ ተፈጸሙ ተገነዘቡ። ስለሆነም እነዚህን የትንቢት ፍጻሜዎች በጽሑፍ እኖሩ። ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን እንደ ፈጸመ የሚያመለክቱ 80 ያህል ጥቅሶች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ይገኛሉ። ሐዋርያት ለመጭው ትውልድ ያስተላለፉት ስለ ክርስቶስ የሚናገሩትን እውነቶች ብቻ ሳይሆን፥ የክርስቶስን ሕይወት ትርጓሜዎች ጭምር ነበር። ሐዋርያት የክርስቶስን ማንነት ይበልጥ በተረዱ ቁጥር፥ ስለ ክርስቶስ ማንነት ትምህርታዊ ገለጻዎችን መስጠት ጀመሩ። አንዳንድ ምሑራን እነዚህ . የክርስቶስ ታሪኮች በቃል የተጠኑ ታሪኮችና በጥንቃቄ ለሌሎች የተላለፉ እንደሆኑ ያስባሉ።

3. በቃል የሚተላለፍ መልእክት ፍጥነት ቢኖረውም፥ ስሕተት ግን ሊኖረው ይችላል። እነዚህ ስሕተቶች አንዳንድ ጠቃሚ እውነቶችን ሊያስቀሩ ወይም ታሪኩን ከመጠን በላይ ሊያጋንኑ ይችላሉ። ስለሆነም ሰዎች እነዚህን ታሪኮች በጽሑፍ ማስፈር ጀመሩ። ሉቃስ በመጽሐፉ መጀመሪያ ላይ እንደገለጸው፥ መጽሐፉን ለመጻፍ የተለያዩ ምንጮችን መርምሯል (ሉቃስ 1፡1-2 አንብብ)። ነገር ግን የተጻፉት ታሪኮች ቅዱሳት መጻሕፍት አልነበሩም። እነዚህ ታሪኮች በስሕተት የተሞሉ ባይሆኑም፥ መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ታሪክ ምንጭ እንዲሆኑ አላደረገም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እያንዳንዱ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ማንነት፥ ስለ ሠራቸው ሥራዎችና በእርሱ ማመን ማለት ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ ማወቁ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) በኢትዮጵያ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አዳዲስ ክርስቲያኖች እነዚህን ነገሮች እንዲያውቁ ጥረት የሚያደርጉ ይመስልሃል? ሐ) እያንዳንዱ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ማንነትና ለምን በእርሱ ማመን እንደሚያስፈልግ ግልጽ መረዳት እንዲኖረው ለማድረግ ቤተ ክርስቲያንን የሚረዳ ምን አሳብ አለህ?

4. መንፈስ ቅዱስ በአራት ሰዎች ሕይወት ውስጥ በመሥራት አራቱን ወንጌላት እንዲጽፉ መርቷቸዋል። ስለ ክርስቶስ ሕይወትና ታሪክ ሥልጣናዊ ጽሑፍ ማዘጋጀት ያስፈለገው ለምን ነበር?

ሀ. ወንጌል በሮም ግዛቶች ሁሉ ሲስፋፋ ስለ ክርስቶስ የሚናገሩ ታሪኮች ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው ሰው ሲተላለፉ መለወጣቸው አልቀረም። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በክርስቶስ ስላመኑ፥ ሐዋርያት ሁሉንም ክርስቲያኖች ለመጎብኘትና ስለ ክርስቶስ ለማስተማር አይችሉም ነበር። ስለሆነም ስለ ክርስቶስ ሕይወት፥ ስላስተማራቸው ነገሮችና ስለ ማንነቱ እውነተኛ ታሪክ ማግኘት አስፈላጊ ሆነ። ይህ በተለይ ክርስቶስን ላላዩትና ስለ ክርስቶስ ግልጽ ግንዛቤ ለማግኘት ለሚፈልጉ ሁለተኛ ትውልድ ክርስቲያኖች የበለጠ አስፈላጊ ነው።

ለ. ብዙዎቹ የዓይን ምስክሮችና ሐዋርያት በሞት እየተለዩ ነው። ሌሎች ደግሞ ከስደት የተነሣ ተበታትነው ነበር። ስለሆነም እነዚህ የዓይን ምስክሮች ከመሞታቸው በፊት በዓይን ምስክሮች የተረጋገጠ ትክክለኛ ታሪክ መጻፍ አስፈላጊ ነበር። ታሪኮቹ የተጻፉት ስለ ክርስቶስ በሰሙት ሰዎች ብቻ ቢሆን ኖሮ፥ ትክክለኛነታቸው አጠራጣሪ ይሆን ነበር። ከክርስቶስ ጋር የነበሩ፥ የተፈወሱ፥ በውኃ ላይ ሲራመድና ሙታንን ሲያስነሣ የተመለከቱ ሰዎች ታሪኩን መናገራቸው አስፈላጊ ነበር።

ሐ. ምናልባትም ትክክለኛ ያልሆኑ ታሪኮችም ሳይጻፉ አልቀረም። ስለሆነም ሐዋርያት ተአማኒነት ያላቸውን የክርስቶስ ሕይወት ታሪኮች መጻፍ አስፈለጋቸው።

መ. አዳዲስ ክርስቲያኖችን ለማስተማር። አንድ ሰው በክርስቶስ ማመኑ ስለ ክርስቶስ ከመመስከር አይገታውም። ይህ የሂደቱ ጅማሬ ብቻ ነው። አዳዲስ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ምን ማመንና እንዴት መኖር እንዳለባቸው መማር አለባቸው። ስለሆነም ወንጌላቱ ከተጻፉበት ዓበይት ምክንያት ውስጥ አንዱ አዳዲስ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስና እርሱን ስለ መከተል ግንዛቤ እንዲያገኙ ለመርዳት ነበር።

ብዙ ሰዎች አራቱ ወንጌላት ስለ አንድ ሰው የሕይወት ታሪክ የሚናገሩ ናቸው ብለው ያስባሉ። ከዚህም የተነሣ ከዝነኛ ሰው ታሪካዊ ዘገባ ጋር ያነጻጽሩታል። ነገር ግን አራቱ ወንጌላት በታሪክ ጸሐፊዎች ከተጻፉ ግለ ታሪኮች ጋር የሚመሳሰሉባቸውና የሚለያዩባቸው መንገዶች እንዳሉ መገንዘብ ጠቃሚ ነው። ወንጌላትን በምናጠናበት ጊዜ የሚከተሉትን ነገሮች እናገኛለን።

ሀ. አራቱ ወንጌላት ክርስቶስ ስላደረጋቸው ነገሮች እውነተኛውን መረጃ ያቀርባሉ። ይህም ከግለሰብ የሕይወት ታሪክ ጋር ያመሳስላቸዋል።

ለ. አራቱ ወንጌላት የክርስቶስን ከፊል ታሪክ ብቻ ይናገራሉ። ከአራቱ ወንጌላት ክርስቶስ ያደረገውንና የተናገረውን ሙሉ በሙሉ በዝርዝር ለማቅረብ የሞከረ የለም። እያንዳንዱ የወንጌል ጸሐፊ የመረጠው የተወሰኑትን ታሪኮች ብቻ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ የኢየሱስ ታሪክ በሙሉ ቢጻፍ ኖሮ፥ በቂ ቀለም ማግኘት እንደማይችል ገልጾአል (ዮሐ. 20፡30-31፤ 21፡25)።

ሐ. አራቱ ወንጌላት የማስተማሪያ መሣሪያዎች ናቸው። እያንዳንዱ የወንጌል ጸሐፊ፥ የተወሰኑ ታሪኮችንና ኢየሱስ ያስተማራቸውን የተወሰኑ ትምህርቶች መርጦ ለክርስቲያኖችና ክርስቲያን ላልሆኑ ሰዎች ለመግለጽ ሞክሮአል። ጸሐፊዎቹ ክርስቲያን ላልሆኑ ሁሉ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅና ብቸኛው የደኅንነት መንገድ እንደሆነ ለማሳመን ጥረዋል። ለምሳሌ፥ ሐዋርያው ዮሐንስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ ወደ ዓለም ከመምጣቱ በፊት ማን እንደነበረ አብራርቷል (ዮሐ 1፡1-14)። በተጨማሪም ጸሐፊዎቹ የሚያድን እምነት ምን እንደሆነና ይህም ሙሉ ታማኝነትን እንዴት እንደሚጠይቅ ለማሳየት ሞክረዋል። የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቶስ አዳኛቸው በመሆኑ፥ በሁኔታዎች ሁሉ በእርሱ መታመን ያስፈልጋቸው ነበር። ዐይነ ስውራንን ያበራው፥ ሙታንን ያስነሣውና ማዕበሉን ጸጥ ያደረገው እርሱ በሚያጋጥማቸው ሁኔታ ውስጥ ሁሉ ከእነርሱ ጋር ነበር።

ወንጌላትን ስናነብና ስናጠና ልናነሣቸው የሚገቡ ሁለት ጥያቄዎች አሉ።

 1. «ስለ ክርስቶስ፥ ስለ ማንነቱና እንድናደርጋቸው ስለሚፈልጋቸው ነገሮች ምን መማር እንችላለን?» ከአንድ ሰው ጋር ያለን ግንኙነት ይበልጥ የሚጠነክረው፥ ስለ ግለሰቡ፥ ስለ ባሕርዩ፥ ዋጋ ስለሚሰጣቸው ነገሮችና ማንነቱን ስለቀረጹት ነገሮች በማወቅ ነው። ከክርስቶስ ጋር ያለንም ግንኙነት የሚጠነክረው እርሱን የበለጠ በማወቅ ነው። ክርስቶስን በበለጠ ለማወቅ ከሚረዱን ነገሮች አንዱ በአራቱ ወንጌላት ውስጥ ስለ እርሱ የተገለጹትን እውነቶች በጥንቃቄ ማጥናት ነው።
 2. «ደራሲው የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን ሊያስተምረን የፈለገው አሳብ ምንድን ነው?» ክርስቶስ እርሱን መከተል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለሦስት ዓመት ያህል ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል። አራቱ ወንጌላትም ይህንኑ አሳብ ዘግበውልናል። የክርስቶስ ተከታዮች ባሕርይ ምን መሆን አለበት? ኢየሱስን መከተል ደቀ መዛሙርቱን ምን ዋጋ ያስከፍላቸዋል? የክርስቶስ ተከታዮች ለሌሎች ሊያስተላልፉ የሚገባው መልእክት ምንድን ነው? ክርስቶስን ለመከተል የሚፈልጉ ሰዎች ዋና ኃላፊነት ምንድን ነው? አራቱ ወንጌላት ለእነዚህ ጥያቄዎች በሙሉ መልስ ይሰጣሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህን ሁለት ጥያቄዎች በተደጋጋሚ መጠየቅ ያለብን ለምንድን ነው? ለ) በቅርቡ ከክርስቶስ ጋር ያለህ ግንኙነትና ዕውቀት እንዴት እያደገ እንደ መጣ ግለጽ። ሐ) ፊልጵስዩስ 3፡10 አንብብና ይህን ጥቅስ በሕይወትህ ተግባራዊ ለማድረግ የምትችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ድካም ከሚታይባቸው ምክንያቶች አንዱ፥ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ አለማወቃቸው ሳይሆን አይቀርም። ደኅንነት ለማግኘት በክርስቶስ ማመን በቂ እንደሆነ እናውቃለን። ነገር ግን ብዙዎቻችን ክርስቶስን መከተል ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልተማርንም። ይህም ብዙ ክርስቲያኖች እንደ ዓለማውያን እንዲመላለሱ አድርጓቸዋል። ችግሮች በሚገጥሙን ጊዜ ማጉረምረም ወይም ከክርስቶስ መንገድ መውጣት እንጀምራለን። ብዙዎቻችን ለዓለማውያን ምን እንደምናካፍል አናውቅም። ምናልባትም አብያተ ክርስቲያናት፥ የጥንት ክርስቲያኖች አዳዲስ ክርስቲያኖችን ለማሠልጠን የተጠቀሙባቸውን መሣሪያዎች ማለትም አራቱን ወንጌላት መጠቀም ይኖርባቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አዳዲስ ክርስቲያኖች አንዱን ወይም ሁሉንም ወንጌላት እንዲያጠኑ በማድረግ ለማስተማር ዐቅድ፡፡ የትኛውን ወንጌል ትመርጣለህ? ለምን? ሥልጠናውን እንዴት ታደራጀዋለህ? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ማንነትና እርሱን መከተል ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም። በግንዛቤያቸው እንዲያድጉ ለማገዝ አራቱን ወንጌላት እንዴት ልትጠቀም ትችላለህ?

አራት ወንጌላት የሆኑት ለምንድን ነው?

የውይይት ጥያቄ፡- እንድ አውቶቡስና የጭነት መኪና በማቋረጫ መንገድ ላይ ተጋጩ እንበል። ይህን አደጋ አራት ሰዎች ተመለከቱት። ከእነዚህ አራት ሰዎች ውስጥ አንዲት ሴት፥ አንድ ፖሊስ፥ አንድ ጠበቃና አንድ መካኒክ ነበሩ። በችሎቱ ፊት ዳኛው ስለተከሰተው አደጋ እንዲያብራሩ ጠየቋቸው። ሀ) አራቱ ሰዎች የተከሰተውን ጉዳይ በዝርዝር ለማስረዳት ይችላሉ? ለ) እነዚህ አራት ምስክሮች ከአንድ ምስክር የሚሻሉት እንዴት ነው?

መንፈስ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ ሕይወት ይጽፉ ዘንድ አራት ሰዎችን ለምን እንደ ተጠቀመ በእርግጠኝነት አናውቅም። ይሁንና ከላይ የቀረበው ማብራሪያ አንድ ፍንጭ የሚሰጠን ይመስላል። ሴት ከወንድ በላይ ነገሮችን የማጤን ጥበብ አላት። ፖሊሱ ደግሞ ከጠበቃውና ከሜካኒኩ በተለየ መንገድ ሪፖርቱን ሊያቀርብ ይችላል። እያንዳንዱ አስተያየት ደግሞ ዳኛው የተፈጸመውን ክስተት ከተለያየ አቅጣጫ እንዲገነዘብ ይረዳዋል። ሴቲቱ ምናልባትም በአደጋው ምክንያት ስለተከሰተው ሥቃይና ሕመም ልትናገር ትችላለች። ፖሊሱ ደግሞ ስለ መኪናው ሕጋዊ ምዝገባና ስለ ሾፌሩ ትክክለኛነት ወይም ጥፋተኛነት ሊያስረዳ ይችላል። ጠበቃው ደግሞ ሕጋዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር፥ ለተከሰተው አደጋ ማን ካሳ ሊከፍል እንደሚገባ ሊገልጽ ይቻላል። ሜካኒኩ ደግሞ ሾፌሩ ፍሬን ስለ መጠቀሙ፥ ወዘተ… በማስረዳት ሜካኒካዊ ጉዳዮችን ያብራራል። ይህ ሁሉ አስተያየት ዳኛው ትክክለኛ ውሳኔ ለመስጠት እንዲችል ይረዱታል።

ልክ እንዲሁ እግዚአብሔር ስለ ልጁ ከተለያዩ እይታዎች አንጻር እንዲመሰክሩ አራት ሰዎችን ተጠቅሟል። ከእያንዳንዱ የወንጌል ጸሐፊ ስለ ክርስቶስ የተለያየ እይታ እናገኛለን። ማቴዎስ አይሁዳዊ ቀራጭ (ግብር ሰብሳቢ) ነበር። እርሱም፥ ለአይሁዶች የዳዊት ልጅ ስለሆነው ስለ ክርስቶስ ጻፈላቸው። ሮም ይኖር የነበረው ማርቆስ፥ «ኢየሱስ ማን እንደሆነ ሥራ ለሚበዛባቸው ሮማውያን» አስረድቷል። የታሪክ ምሑርና ሐኪም የነበረው ሉቃስ ለሰዎች ስሜትና ፍላጎት ትኩረት ሰጥቷል። በተጨማሪም ሉቃስ ክርስቶስ አሕዛብንና ድውያንን፥ መከራ የደረሰባቸውን፥ ድሆችንና ሴቶችን እንዴት እንደረዳ አብራርቷል። ዮሐንስ፥ «ክርስቶስ ማን ነው?» የሚለውን ጥያቄ መልሷል። ከክርስቶስ ሕይወት ወሳኝ ትምህርቶችን እያወጣ አብራርቷል። ይህም እያንዳንዱ የወንጌል ጸሐፊ አንዱን ክርስቶስና ሕይወቱን ከተለያየ አንጻር በመመልከት ሙሉ ገለጻ እንደ ሰጡን ያሳያል። በመሆኑም አራቱ ወንጌላት ከአንድ ወንጌል ይልቅ ስለ ክርስቶስ ግልጽ ምስል እንዲኖረን አድርገዋል።

ብዙ ምሑራን እያንዳንዱ ወንጌል ለተወሰኑ ሕዝቦች የተጻፉ ናቸው የሚል ግምት አላቸው። ማቴዎስ ለአይሁዶች፥ ማርቆስ ለሮሜ ሰዎች፥ ሉቃስ ለግሪኮች፥ ዮሐንስ ለመላው ዓለም እንደ ጻፉ ያስባሉ። በተጨማሪም ምሑራን እያንዳንዱ ደራሲ በክርስቶስ ማንነት ላይ የተለይ ትኩረት እንዳደረገ ያስረዳሉ። ማቴዎስ፥ ክርስቶስ የአይሁድ ንጉሥ እንደሆነ፥ ማርቆስ የእግዚአብሔር አገልጋይ እንደሆነ፥ ሉቃስ ፍጹም የሰው ልጅ እንደሆነ፥ እንዲሁም ዮሐንስ ክርስቶስ ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ያስረዳል ይላሉ።

ሌላው አራቱ ወንጌላት የተጻፉበት ምክንያት ከብሉይ ኪዳን የመጣ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ። በብሉይ ኪዳን ዘመን አንድ ሰው በጥርጣሬ ወይም በአንድ ሰው ምስክርነት ብቻ ሊፈረድበት ወይም ሊገደል አይችልም ነበር። እንዲፈረድበት ቢያንስ ሁለት ወይም ሦስት ምስክሮች ያስፈልጋሉ (ዘዳግ 19፡15)። ስለሆነም እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱ ልጅና ብቸኛው የደኅንነት መንገድ መሆኑን ለመመስከር ከሦስት አልፎ አራት ምስክሮችን ሰጥቷል። የእነዚህ አራት ምስክሮች ቃል ሰዎችን ሊያሳምናቸው ይገባል።

ምስክረ ወንጌላት

የውይይት ጥያቄ፡– እነዚህን ምንባቦች አነጻጽር፡ ማቴ. 9፡2-8፤ ማር. 2፡3-12፤ ሉቃስ 5፡18-26፤ ማቴ. 10፡22፤ ማር. 13፡13 ሉቃስ 21፡17 ምንባቦቹ የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?

ምሑራን ሁለት በባሕርያቸው የሚለያዩ ወንጌላት እንዳሉ አስተውለዋል። ማቴዎስ፥ ማርቆስና ሉቃስ አንደኛው ዐይነት ወንጌል ናቸው። እነዚህ ወንጌላት አስተምህሮአዊ ትንታኔ የላቸውም። ይሁንና ክርስቶስ ያደረገውንና ያስተማረውን አገልግሎት በሰጠበት ታሪካዊ መንገድ ያቀርባሉ። ሦስቱም ክርስቶስ ተአምራትን እንዳደረገና በምሳሌዎች እንዳስተማረ ያስረዳሉ። በእነዚህ ሦስት ወንጌላት ውስጥ ጎልቶ የሚታየው የክርስቶስ አምላክነት ሳይሆን ሰብዓዊነት ነው። ምሑራን እነዚህን ሦስት ወንጌላት «ምስክረ ወንጌላት» በማለት ይጠሯቸዋል። ምስክረ ወንጌላት የተባሉት በቅርጽና በገለጻ ስለ ክርስቶስ ያቀረቡት አሳብ አንድ ዓይነት በመሆኑ ነው።

ነገር ግን የመጨረሻው የዮሐንስ ወንጌል በጣም የተለየ ነው። ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ ካደረጋቸው ተአምራት ሰባቱን ብቻ ጽፎአል። ሐዋርያው ዮሐንስ ያተኮረው በክርስቶስ ረዣዥም ስብከቶች ላይ ነው። ምሳሌዎችን ከመጠቀም ይልቅ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነትን እንዴት በግልጽ እንደ ተናገረ አሳይቷል። በኢየሱስ ሰብአዊነት ላይ ከማተኮር ይልቅ፥ ክርስቶስ አምላክ እንደሆነ በግልጽ ዘግቧል።

የማቴዎስ፥ የማርቆስና የሉቃስ አጻጻፍ በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ እጅግ መመሳሰል፥ ለምሑራኑ ችግሮችን አስከትሏል። የሁለት ተማሪዎች የጽሑፍ ፈተና ቃል በቃል ወይም በአሳብ ደረጃ ተመሳሳይነት ካለው አንዱ የሌላውን እንደ ኮረጀ ያህል ማለት ነው። ሁለት የተለያዩ ሰዎች አንድ ዓይነት ቃላትና የአሳብ አወራረድ ተከትለው ሊጽፉ አይችሉም። ነገር ግን በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወንጌላት ላይ የተካሄደው ጥንቃቄ የተሞላበት ጥናት አንዳንድ ጊዜ ቃላቱ፣ ብዙ ጊዜ ደግሞ አሳቦቹ ተመሳሳይ መሆናቸውን አረጋግጧል። ምሑራን የማርቆስ ወንጌል 93 በመቶ በማቴዎስና በሉቃስ፥ የማቴዎስ ወንጌል 58 በመቶ በማርቆስና በሉቃስ፥ እንዲሁም የሉቃስ ወንጌል 41 በመቶ በማቴዎስና በማርቆስ ውስጥ እንደሚገኝ ገምተዋል፤ በአንጻሩም በሌሎቹ ሦስት ወንጌላት ውስጥ የሚገኘው የዮሐንስ ወንጌል 8 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው።

ስለሆነም ምሑራኑ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ወንጌላት እንዴት እንደ ተጻፉ በሚያቀርቧቸው ጥናቶች ይለያያሉ። አብዛኞቹ የተከተሉት የጥናት አሳብ ማርቆስ መጀመሪያ እንደ ተጻፈ ነው። ማቴዎስም ማርቆስ ከጻፈው ውስጥ ብዙውን በመውሰድ ለራሱ ዓላማ በሚመች መንገድ ጽፎአል። ማቴዎስ ከማርቆስ በተጨማሪ ሌሎች ምንጮችን ተጠቅሟል። ሉቃስም የማቴዎስንና የማርቆስን ወንጌል ሳይጠቀም አይቀርም። አንዳንድ ምሑራን ማቴዎስና ሉቃስ የተጠቀሙበት ሌላም ምንጭ እንዳለ ያምናሉ።

ሌሎች ደግሞ አንዱ ወንጌል ከሌላው በቀጥታ እንዳልቀዳና ይልቁንም የሦስቱ ወንጌላት ጸሐፊዎች ተመሳሳይ ትውፊቶችን እንደ ተጠቀሙ ያስረዳሉ። እነዚህ ምሑራን በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ የሚናገሩ ታሪኮች ባጭር ባጭሩ ተጽፈው ይገኙ ነበር ይላሉ። እነዚህ አጫጭር ታሪኮች በቃል እየተጠኑ ለአዳዲስ ክርስቲያኖች በጥንቃቄ ይተላለፉ ነበር። በመሆኑም ሦስቱ የወንጌላት ጸሐፊዎች እነዚህን በቃል የተጠኑ ታሪኮች ተጠቅመዋል ይላሉ።

በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ሌሎችም ብዙ ግምታዊ አሳቦች አሉ። ለምሳሌ፥ ሦስቱም ወንጌላት አሁን አንድ በጠፉ ጥንታዊ ወንጌል ተጠቅመዋል የሚሉም አሉ። የወንጌላት ጸሐፊዎች ተጽፈው የተቀመጡትን አጫጭር ታሪኮች እንደ ተጠቀሙ የሚናገሩ ምሑራንም ሞልተዋል። አንዳንዶች የማቴዎስ ወንጌል የመጀመሪያው ወንጌል ስለሆነ ሌሎቹ ሁለት ጸሐፊዎች እርሱን እንደ ዐቢይ ምንጭ እንደ ተጠቀሙ ያስባሉ። ስለሆነም ምሑራን እነዚህ ሦስት ወንጌላት ለምን በጣም ሊመሳሰሉ እንደ ቻሉ ሁሉንም የሚያስማማ መልስ ሊሰጡ አልቻሉም። የምናውቀው ነገር ቢኖር መንፈስ ቅዱስ በጽሕፈት ሂደቱ ውስጥ አመራር ሰጪ እንደ ነበረ ነው። መንፈስ ቅዱስ ለሰው ሁሉ እንዲተላለፍ የሚፈልጋቸውን አሳቦች ጸሐፊዎቹ እንዲዘግቡ መርቷቸዋል። በተጨማሪም ታሪኮቹ ክርስቶስ በትክክል ያደረገውንና ያስተማረውን እንዲያንጸባርቁ አድርጓል።

የውይይት ጥያቄ፡- ወንጌላትን የመጻፉ ሂደት የመንፈስ ቅዱስና የሰዎች የጋራ ጥረት ውጤት ነው። ይህ መንፈስ ቅዱስ የሚሠራበት የተለመደ መንገድ መሆኑን ግለጽ። መንፈስ ቅዱስ አንተን፥ ትምህርትህንና ችሎታዎችህን፥ ስለ ተጠቀመበት መንገድ አንዳንድ ማብራሪያዎችን ስጥ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዴት ሊታወቁ ቻሉ?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የተለያዩ ዐበይት ሃይማኖቶችንና ቅዱሳት መጻሕፍቶቻቸውን ዘርዝር። ለ) 2ኛ ጴጥ. 1፡20-21 አንብብ። ጴጥሮስ ስለ ብሉይ ኪዳን ምን ተናገረ? ሐ) 66ቱ መጻሕፍት ብቻ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው የሚለውን መቀበል ወሳኝ የሚሆነው ለምንድን ነው?

እያንዳንዱ ሃይማኖት ከአምላኩ እንደ ተቀበለ የሚያምነው ልዩ መጽሐፍ አለው። ሂንዱዎች ቬዳስ፥ ቡድሒስቶች ቲፒታካ፥ ሙስሊሞች ደግሞ አላህ ለመሐመድ ሰጠው የሚሉት ቁርዓን ከእስትንፋሰ-እግዚአብሔር የተገኙ መጻሕፍት አለን ይላሉ። ለምሳሌ፥ የያህዌ ምስክሮች የመጠባበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ያብራራል በማለት ይናገራሉ። ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ለሰው ልጆች አንድ እስትንፋሰ እግዚአብሔር መጽሐፍ ብቻ እንደ ሰጠ ያምናሉ። ይህም መጽሐፍ፥ ብሉይና አዲስ ኪዳን የተሰኙ ክፍሎች ያሉት መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ምንም እንኳ ሌሎች መጻሕፍት አንዳንድ ጠቃሚ መረጃ ዎችን ሊሰጡን ቢችሉም፥ ምንም ስሕተት የሌለባቸው የእግዚአብሔርን ቃል የያዙ 66ቱ መጻሕፍት ብቻ እንደሆኑ እናምናለን።

በኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን አብዛኞቹ አይሁዶች 39ኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሰዎች መጻፋቸውንና የእግዚአብሔር ቃል እንደሆኑም ተረድተው ነበር። ምንም እንኳ እግዚአብሔር ቃሉን ለመጻፍ ሰዎችን መሣሪያ አድርጎ ቢጠቀምም፥ በእነዚህ 39 መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው አሳብ ሁሉ እግዚአብሔር ራሱ በቀጥታ መጥቶ የተናገረው ሥልጣናዊ ቃል እንደሆነ ተረድተው ነበር። ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ከሦስቱም ዐቢይ የብሉይ ኪዳን ምድቦች፥ ማለትም ከሕግ፥ ከነቢያትና ከጽሑፎች እየጠቀሰ በማስተማር የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን አስረድቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳት ጽሑፎች የሰው ሳይሆኑ፥ የእግዚአብሔር ሥራዎች እንደሆኑ ገልጾአል (2ኛ ጢሞ. 3፡16)።

እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን ዘመን የሠራው፥ በብሉይ ኪዳን በሠራው መንገድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ሥራ ብቻ አይደለም። የእግዚአብሔርም ሥራ ብቻ አይደለም። እግዚአብሔር ሰዎች እንዲጽፉለት የፈለገውን አሳብ ቃል በቃል አልተናገረም። (ይህ ሙስሊሞች መሐመድ ከአላህ ቃል በቃል ተቀብሎ ጽፎአል ብለው ከሚያምኑት የተለየ ነው)። እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የሰውና የእግዚአብሔር ሥራ ውጤት ነው። የተለያዩ የአዲስ ኪዳን ደራሲያን መልእክቶቻቸውን የጻፉት የራሳቸውን ቃል በመጠቀም ነበር። ለዚህም ነው ምሑራን አንዳንድ መጻሕፍት የተጻፉበት የግሪክ ቋንቋ ከሌሎች የላቀ መሆኑን የሚናገሩት። በጽሑፋቸው ውስጥ የእያንዳንዱ ደራሲ ባሕርይ ይታያል። ጳውሎስ በጸጋ፥ ዮሐንስ በእምነት ወይም ብርሃን ላይ ሲያተኩሩ እንመለከታለን። እያንዳንዱ ደራሲ የተወሰኑ ቃላትን ይደጋግማል። ለምሳሌ፥ ዮሐንስ «ብርሃን» እና «ጨለማ» የሚሉትን ቃላት በተደጋጋሚ ጠቅሷል። ይህም መንፈስ ቅዱስ የደራሲያኑን ማንነት ችላ እንዳላለ ያሳያል። ይህ ባይሆን ኖሮ፥ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ተመሳሳይ ቃሎችን፥ አገላለጾችንና ሥነ ጽሑፋዊ ዘዴዎችን ያንጸባርቅ ነበር። ይህን በመጻሕፍቱ ውስጥ አናይም። ምናልባት አብዛኞቹ ደራስያን የእግዚአብሔርን ቃል እየጻፉ መሆናቸውን ላያውቁ ይችሉ ይሆናል። እግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እየተመሩ ቃሉን ከእርሱ ጋር እንዲጽፉ ሲፈቅድ፥ ስለ ጸሐፊዎቹ ምን ልንማር እንደምንችል፥ ያተኮረባቸውን አሳቦች ልንመለከት፥ የወደደችውን ቃላት ልናጤን፥ . . ወዘተ. እንችላለን።

የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የሰው ቃሎች ብቻ አይደሉም። እነዚህ መጻሕፍት በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የተሰጡ የእግዚአብሔር ቃላት እንደሆኑ ተገልጾአል (2ኛ ጴጥ. 1፡20-21)። መንፈስ ቅዱስ የእያንዳንዱ ደራሲ ስብእናና ችሎታ እንዲንጸባረቅ በመፍቀድ የጽሕፈት ሂደቱን ስለ ተቆጣጠረ፥ ሁሉም ነገር ተጽፎ ከተጠናቀቀ በኋላ እግዚአብሔር ሊያስተላልፍ የፈለገው አሳብ ያለምንም ስሕተት በትክክል ሊተላለፍ ችሏል። መንፈስ ቅዱስ የእያንዳንዱን ደራሲ አሳብ፥ ቃልና ዐረፍተ ነገር ስለተቆጣጠረ የመጨረሻ ውጤቱ የእግዚአብሔር እንጂ የሰው ቃል እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ምሑራን በመጽሐፍ ቅዱስና በክርስቶስ መካከል ተመሳሳይነት አለ ይላሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ጊዜ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው እንደሆነ ሁሉ፥ መጽሐፍ ቅዱስም በአንድ ጊዜ የእግዚአብሔርና የሰው ሥራ ነው። ይህም መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሌሎች መጻሕፍት ማጥናት እንደሌለብን ያስገነዝበናል። ይልቁንም እግዚአብሔር በቀጥታ እንደሚናገረን አድርገን ልናጠናው ይገባል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሞቱ በፊት ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን እንደሚቀበሉ ነግሯቸው ነበር። ከመንፈስ ቅዱስ ዐበይት ሥራዎች አንዱ በአንዳንድ ሰዎች ልብ ውስጥ በመሥራት ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲጽፉ ማድረግ ነበር። ክርስቶስ በዮሐ 16፡12-15 እንደተናገረው፥ «የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፥ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፡- ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ።» በተጨማሪም ክርስቶስ፥ «አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል» ብሏል (ዮሐ 14፡26)። አንዳንድ ምሑራን፥ «ያሳስባችኋል» የሚለው አራቱን ወንጌላት እንደሚያመለክትና «ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል» የሚለው መልእክቶችን፥ እንዲሁም «የሚመጣውንም» የሚለው ደግሞ የዮሐንስ ራእይን እንደሚያመለክት ይናገራሉ።

በኋላም ሐዋርያው ጴጥሮስ፥ «የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቁጠሩ። እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ። በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ» (2ኛ ጴጥ. 3፡15-16) ብሏል። ጴጥሮስ፥ ጳውሎስ የጻፋቸው መልእክቶች የብሉይ ኪዳንን ያህል ሥልጣን እንዳላቸው ገልጾአል። ይህም ሐዋርያት ገና በሕይወት ሳሉ እንኳ አንዳንድ መጻሕፍትን ከብሉይ ኪዳን እኩል ማየት እንደ ጀመሩ ያመለክታል። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን 27ቱን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል ናቸው ብላ ለመቀበል 200 ዓመታት ያህል ወስዶባታል።

የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል ካልሆነው ለመለየት፥ ለጥንት ክርስቲያኖች ወሳኝ ተግባር ነበር። በዚያን ጊዜ ሐዋርያት ነን ብለው የተናገሩ ደራሲያን ነበሩ። እነዚህ ሰዎች የጻፉት አሳብ ግን ሐዋርያቱ ከጻፉት ጋር ይጋጭ ነበር። በስደት ወቅት ክርስቲያኖች ለእውነት ለመሞት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ነበረባቸው። ስለዚህ ለውሸት መሞት አይፈልጉም ነበር። መጻሕፍቱን መገልበጡ ደግሞ ረዥም ጊዜ የሚወሰድ ተግባር ነበር። ስለሆነም በዓለም ሁሉ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የእግዚአብሔር ቃል የሆኑትን መጻሕፍት መሰብሰብ ጀመሩ። በተጨማሪም የተሻሉ ናቸው የሚባሉ የቀዳሚ ጽሑፎችን ቅጂ መፈለግ ጀመሩ።

እነዚህ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች አንድ ጽሑፍ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑንና አለመሆኑን ለመለየት የተጠቀሙባቸው መመዘኛዎች ምን ምን ነበሩ?

1 ደራሲው ማን ነው? ደራሲው የማይታወቅ ወይም አጠራጣሪ ከሆነ፥ መጽሐፉን እንደ ቅዱስ መጽሐፍ አድርገው አይቀበሉም ነበር። ዋናው መመዘኛቸው ደራሲው ከቀደምት ሐዋርያት አንዱ መሆን አለበት የሚል ነበር። የጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች የመጀመሪያው ምእተ ዓመት ሐዋርያት እውነትን የመደንገግ ሥልጣን እንደተሰጣቸው ተረድተው ነበር። ስለሆነም እነዚህ ሐዋርያት እግዚአብሔር ሥልጣን ያለውን ቃሉን ለመጻፍ የሚጠቀምባቸው መሆኑን ያውቁ ነበር።

ደራሲው ሐዋርያ ካልሆነ፥ እንዲህ ብለው ይጠይቃሉ፥ «መጽሐፉ ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ ይህ ጸሐፊ ከሐዋርያት ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበረው?»። ዮሐንስ ማርቆስና ሉቃስ የጳውሎስ የቅርብ ተባባሪዎች ስለነበሩ፥ የጻፉዋቸው መጻሕፍት እንደ እግዚአብሔር ቃል ተቆጥረው ተቀባይነት አግኝተዋል።

2 መጽሐፉ ከብሉይ ኪዳንና ከሐዋርያት አስተምህሮ ጋር ሙሉ ለሙሉ ይስማማል? እግዚአብሔር አይዋሽም፤ ከራሱም ጋር አይቃረንም። ስለሆነም መጽሐፉ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳንና በሐዋርያት አማካይነት ካስተማረው አሳብ ጋር መስማማት አለበት። ካልተስማማ፥ መጽሐፉ የእግዚአብሔር ቃል ሊሆን አይችልም።

3 መልእክቱ የሚጠቅመው ለመላው የክርስቶስ አካል ነው ወይስ ለአንድ ግለሰብ ወይም ቤተ ክርስቲያን? ሐዋርያት የጻፉት ጽሑፍ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ አካል አልሆነም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የጻፈው አንድ መልእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሌለ እናውቃለን። አንዳንድ መልእክቶች ብዙ መንፈሳዊ እውነት ወይም ለቤተ ክርስቲያን የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ አልነበራቸውም። ስለሆነም የጥንት ቤተ ክርስቲያን አባቶች አልተቀበሏቸውም። እንደ ፊልጵስዩስ ዐይነት ሌሎች መልእክቶች ምንም እንኳ ለአንድ ቤተ ክርስቲያን የተላኩ ቢሆኑም በየትኛውም ዘመንና ስፍራ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች የሚጠቅም ትምህርት ይዘዋል። ስለሆነም የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸው ታውቋል።

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የአዲስ ኪዳን አካል የሆኑትን መጻሕፍት ለመወሰን ረዥም ጊዜ የወሰደባቸው ለምን ነበር? በአንድ በኩል አብዛኛዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን ለመለየት ብዙ ጊዜ አልወሰደም ነበር። ጳውሎስ ከሞተ ከጥቂት ትውልዶች በኋላ የእርሱ መልእክቶች፥ አራቱ ወንጌላት፥ 1ኛ ዮሐንስ፥ እንዲሁም የዮሐንስ ራእይ የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸው ተረጋግጧል። ሌሎች መጻሕፍት ረዥም ጊዜ የወሰዱት ለምን ነበር?

 1. የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ከግብፅ እስከ ሮም ድረስ ተስፋፍታ እንደነበር ማስታወስ ይኖርብናል። አንዳንድ መጻሕፍት የተጻፉት በኢየሩሳሌም ሲሆን፥ ሌሎቹ የተጻፉት በሮም ነበር። እነዚህ መጻሕፍት በእጅ ተባዝተው በብዙ መቶ ኪሎ ሜትር ተራርቀው ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እስኪላኩ ድረስ ጊዜ ወስዶ ነበር። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ደግሞ መጽሐፉን አንብበው እስኪረዱ ድረስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ለመወሰን ጊዜ ይወስድባቸው ነበር። ስለዚህ አንድን መጽሐፍ እንደ እግዚአብሔር ቃል መቀበሉ ከባድ ውሳኔ እንደሆነም ተገንዝበው ነበር።
 2. የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ስለ አንድ ጉዳይ ተነጋግረው ለመወሰን ይቸገሩ ነበር። አንድ መሪ ከኢየሩሳሌም ወደ ሮም ለመድረስ በወራት ለሚቆጠር ጊዜ ጉዞ ማድረግ ነበረበት። ስለሆነም በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ቢያገለግሉም፥ መሪዎቹ ተገናኝተው የሚወያዩበትና የሚወስኑበት መድረክ ባለመኖሩ እስከ 350 ዓ.ም. ድረስ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል አካል መሆናቸው በይፋ አልተረጋገጠም ነበር።
 3. የጥንት ክርስቲያኖች እንደ ዕብራውያን ያሉትን መጻሕፍት ማን እንደጻፋቸው አያውቁም ነበር። ስለሆነም መሪዎቹ የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን ከመቀበላቸው በፊት በጸሎት ይገመግሟቸው ነበር።
 4. እንደ 2ኛ ዮሐንስ ያሉት መጻሕፍት ቀን ዓለም አቀፋዊ መልእክት ስላልነበራቸው፥ የእግዚአብሔር ቃል አካል ይሁኑ ወይም አይሁኑ የሚለው ሲያከራክር ቆይቷል።

ይህ የምርጫ ሂደት ሙሉ ለሙሉ የሰው ሥራ ነበር? እነዚህ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የእግዚአብሔር ቃል ለሆኑት «ዕውቅና እንዲሰጡ» መግለጻችን ይታወሳል። መጽሐፎቹ ቢመረጡም ባይመረጡም የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸው አይቀርም። ነገር ግን ቃሉን እንዲጽፉ ሰዎችን የቀሰቀሰው መንፈስ ቅዱስ የምርጫውንም ሂደት መርቷል። በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ በጥንት ክርስቲያኖች ልብ ውስጥ በመሥራት፥ እነዚህ መጻሕፍት ከሌሎች የተለዩ መሆናቸውን እንዲነዘቡ አስችሏቸዋል። እነዚህ የጥንት ክርስቲያኖች የመጽሐፎቹን ጠቃሚነት እንዲገነዘቡ፥ መንፈስ ቅዱስ እነርሱና የቤተ ክርስቲያን መሪዎቻቸው በ27ቱ መጻሕፍት ላይ የነበረውን የእግዚአብሔርን እጅ እንዲመለከቱ መርቷቸዋል። አዲስ ኪዳንን በምናነብበት ጊዜ እነዚህ መጻሕፍት እውነትን በማቅረቡ በኩል ምን ያህል ከፍተኛ ሚና እንደሚወጡ ልንገነዘብ እንችላለን። ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል አንዱ ቢጎድል፥ ስለ እግዚአብሔር አሳብ አንድ ጠቃሚ ነገር ይጎድልብን ነበር።

የይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች 27ቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን ያምናሉ። ታዲያ ብዙ ሰዎች ጊዜ ወስደው የእግዚአብሔርን ቃል የማያጠኑት ለምንድን ነው? ለ) የእግዚአብሔርን ቃል በጥንቃቄ ከማጥናት ይልቅ ቪዲዮ ወይም ሌሎች የማብራሪያ መጻሕፍትን የእምነታችን ምንጮች ስናደርግ መጽሐፍ ቅዱስ የእውነት ዋንኛ ዳኛ ነው የሚለውን በተግባራችን ምን እያደረግን ነው? ሐ) እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር እንድንለካበት እንከን የሌለውና የማይለወጥ ቃል የሰጠን ለምን ይመስልሃል?

በእጃችን ያለው የአዲስ ኪዳን ቅጂ ምን ያህል አስተማማኝ ነው?

የውይይት ጥያቄ፡- ሙስሊሞች ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ለውጠዋል ብለው ይናገራሉ። ሀ) ይህ በእምነታችን ላይ የተሰነዘረ አደገኛ ክስ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ለዚህ ክስ ምን መልስ ትሰጣለህ?

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ታላላቅ ከተሞች፥ በክርስቲያኖች እጅ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ በስሕተት የተሞላና በክርስቲያኖች የተለወጠ እንደሆነ የሚናገሩ ሙስሊሞች ያሳተሟቸው መጻሕፍት ሞልተዋል። ይህም የብዙ ደካማ ክርስቲያኖችን እምነት አሽመድምዷል። ይሁንና ሙስሊሞች የሚናገሩት እውነት ይሆን? ምንም እንኳ ይህ ከዚህ መጽሐፍ ዐላማ ውጭ ቢሆንም፥ የአዲስ ኪዳንን ትክክለኛነት ቀጥለን እንመለከታለን። ለሙስሊሞች እንዴት መልስ መስጠት እንዳለብህ ለማወቅ የሚከተሉትን መጻሕፍት ማንበቡ ጠቃሚ ነው፡- ላለማደናገር፥ ማወዳደር፥ ማሰላሰል፥ ማጠቃለል፤ እንድረስላቸው የክርስቲያን-ሙስሊም ውይይት፡፡

በጥንት ጊዜ ወረቀት አገልግሎት ላይ ከመዋሉ በፊት መጻሕፍት የሚጻፉት ከሚከተሉት ሦስት ነገሮች በአንዱ ላይ ነበር። አንዳንድ አጫጭር አሳቦች በሸክላ ላይ ይጻፉ ነበር። ምንም እንኳ በቀላሉ የሚሰበር ቢሆንም፥ ይህ መጻፊያ ቶሎ ስለማያረጅ ለብዙ ምእተ ዓመት ለመቆየት ይችላል። ዛሬ በጥንት ዘመን እንደ ተጻፉ የሚነገርላቸው ሸክላዎች ቢኖሩም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በሸክላ ላይ አልተጻፈም። ሁለተኛው መጻፊያ የእንስሳት ቆዳ ነበር። ይህም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስትጠቀም የነበረውን ብራና የሚመስል ነው። ብራና ብዙ የመቆየት ዐቅም ቢኖረውም፥ የመድረቅ፥ የመሰንጠቅ ወይም ቀለሙ የመፍዘዝ ባሕርይ አለው። ሦስተኛው መጻፊያ ከፖፒረስ (እንደ ወረቀት የተዘጋጀ ተክል) የሚሠራ ሲሆን፥ ብዙ ሳይቆይ የሚያረጅ መጻፊያ ነው። በጥንት ጊዜ ማተሚያ ቤቶች ስላልነበሩና ዳግም ማተም ስለማይቻል ያረጁትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ለመገልበጥ ወይም ሌላ ቅጂ ለማባዛት የሠለጠኑ ጸሐፍት ያስፈልጉ ነበር። የጥንት ሥነ ጽሑፍ ምሑራን መጽሐፍ ቅዱስን በተለይም የአዲስ ኪዳን ምንባቦችን በመመርመር፥ የሚከተሉትን ነገሮች አጢነዋል፡፡

 1. ጸሐፍቱ የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቃል የሚጽፉ መሆናቸውን ተገንዝበዋል። ይህም ጽሑፉን በሚገለብጡበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል። ጽሑፉን በትክክል መገልበጣቸውን ለማረጋገጥ ደግሞ ሌሎች ጸሐፍት ያመሳክሩት ነበር። ስለሆነም እነዚህ ጸሐፍት እኛ ለጋዜጣ ጽሑፍ ከምናደርገው የበለጠ ጥንቃቄ አድርገዋል።
 2. የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ የተጻፉት በግሪክ ቋንቋ ነው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ብንመረምር፥ የሕትመት ስሕተቶችን ልንመለከት እንችላለን። አንዳንድ ጊዜም የትርጉም ስሕተቶች ያጋጥማሉ። አንድ ሰው ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ ቋንቋ በሚተረጉምበት ጊዜ፥ የምንጭ ቋንቋውን የሚመስል አሳብ ለማቅረብ እንደሚቸገር እንረዳለን። ለዚህም ምክንያቱ ቃላት የተለያየ ትርጉም ስላላቸው ነው። ብዙውን ጊዜ አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የሚወጡት የመጀመሪያውን መጽሐፍ አሳብ ይበልጥ የሚገልጹ ትርጉሞችን ለማዘጋጀት በሚደረግ ጥረት ነው።
 3. እነዚህ ጸሐፍት መጻሕፍቱን በሚገለብጡበት ጊዜ፥ በቅጂው ሂደት ወቅት አንዳንድ ስሕተቶች ለመከሰት ችለዋል። ከጋዜጣ ላይ አንድ ጽሑፍ ወስደህ በእጅህ አምስት ጊዜ ብትገለብጥ፥ በአንድ ወይም በሁለት ቅጂዎች ላይ ስሕተት ልትሠራ ትችላለህ። ከዚያም ቅጂዎቹን ለአምስት ጓደኞችህ ብትልክና ሌሎች አምስት ሰዎች በእጃቸው ገልብጠው እንዲልኩ ብታደርግ፤ ስሕተቶቹ እየበዙ ይሄዳሉ። ስሕተት ያለባቸውን ቅጂዎች የተቀበሉት ሰዎች ስሕተቶቹን ይገለብጣሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ራሳቸው ተጨማሪ ስሕተቶችን ይሠራሉ። ስለሆነም ቅጂዎችን ለሌሎች በሚያስተላልፉበት ጊዜ የአንተን ብቻ ሳይሆን የራሳቸውንም ስሕተቶች አብረው ያስተላልፋሉ። ይህ በአንድ የጋዜጣ ጽሑፍ ላይ ሊከሰት ከቻለ፥ ለብዙ ዓመታት ሲገለበጡ የኖሩት ብዙ የአዲስ ኪዳን ቅጂዎች ሁኔታ ምን ሊመስል እንደሚቻል መገመት ይቻላል።
 1. አዲስ ኪዳን ከጥንቱ ሥነ ጽሑፎች ሁሉ በቅጂው ጥራት ተወዳዳሪ አልተገኘለትም። ምሑራን ከ5000 በላይ ሙሉ ወይም ከፊል የአዲስ ኪዳን ምንባቦችን የያዙ ቅጂዎች አሰባስበዋል። ምሑራን እነዚህን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰበሰቡትን ጥንታዊ ቅጂዎች በሚያነጻጽሩበት ጊዜ፥ አንዳንድ ልዩነቶች ቢኖሩባቸውም የትኛውም ግድፈት የክርስቲያኖችን አስተምህሮ እንደማያፋልስ ተገንዝበዋል። ከሌሎች መዛግብት ጋር ሲነጻጽር፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙ ልዩነቶች በጣም አነስተኛ ናቸው። (ለምሳሌ፥ በሉቃስ 10፡1 እንዳንድ የአዲስ ኪዳን መዛግብት 70፥ ሌሎች ደግሞ 72 ደቀ መዛሙርት እንደ ተላኩ ይናገራሉ።) 
 2. ከጥፋት ተርፈው ከቆዩት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አንዳንዶቹ በጣም አርጅተዋል። አንዳንዶቹ ጥናታዊ መጻሕፍት የተገለበጡት ደራሲው ከጻፋቸው ከ1000 ዓመት በኋላ ሲሆን፥ አዲስ ኪዳንን በተመለከተ ግን የመጀመሪያው ጽሑፍ ከተጻፈ ከአርባ ዓመት በኋላ የተባዙ ቅጂዎች አሉ። ለምሳሌ፥ ምሑራን በ125 ዓ.ም. የተባዛ የዮሐንስ ወንጌል ቅጂ አግኝተዋል። ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው በ90 ዓም አካባቢ በመሆኑ፥ ይህ ከ40 ዓመት ያነሰ ጊዜ እንደሆነ ያመለክታል። እንደዚሁም በ60 ዓም. አካባቢ የተባዛ የማቴዎስ ወንጌል ቅጂ ተገኝቷል። ይህም ብዙዎቹ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ከመጀመሪያው ጽሑፍ ጋር እጅግ የሚቀራረቡ ቅጂዎች እንዳሏቸው ያመለክታል።
 1. ምሑራን አሁን ያሉትን በሺዎች የሚቆጠሩ ልዩ ልዩ ቅጂዎችና ጥንታዊ ትርጉሞችን (ለምሳሌ ላቲን) ካነጻጸሩ በኋላ፥ ጸሐፍት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደገለበጡ አረጋግጠዋል። በተጨማሪም የአዲስ ኪዳን ምንባቦችን የሚጠቅሱ ወይም የሚያብራሩ ጥንታዊ የማብራሪያ መጻሕፍትም አሉ። ይህ ሁሉ ምሑራን ዛሬ በእጃችን ያለው የአዲስ ኪዳን ቅጂ ትክክለኛ እንደሆነ እንዲያረጋግጡ ረድቷቸዋል።

ከነዚህ ሁሉ እውነቶች የተነሣ ምሑራን መዛግብቶችን በማነጻጸርና ስሕተቶችን በማረም በእጃችን ያለው የአዲስ ኪዳን ቅጂ ማቴዎስ፥ ጴጥሮስ ወይም ጳውሎስ በመጀመሪያ ከጻፉት ጋር 95 በመቶ ተመሳሳይ እንዲሆን ለማድረግ ችለዋል። አንዳንድ ጥያቄዎችን የሚያስነሡ ጉዳዮች ቢኖሩም፥ የምንባቡን ፍች የማይለውጡ አነስተኛ ዝርዝር ጉዳዮች ብቻ ናቸው። ቁርዓንን ጨምሮ የትኛውም መጽሓፍ የዚህ ዓይነት ትክክለኛነት የለውም። በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ጥቂት የትክክለኛነት ጥያቄ እንዳለ እሙን ቢሆንም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ለመሆኑ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ሊገባን አይገባም። የመጀመሪያዎቹ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች በጻፉትና ዛሬ በእጃችን በሚገኘው መጽሐፍ መካከል ይህ ነው የሚባል ሁነኛ ለውጥ የለም። ትርጉሞችም በከፍተኛ ጥንቃቄ የተዘጋጁ በመሆናቸው፥ በመጀመሪያው ጽሑፍና በትርጉሞቹ መካከል የሚገኘው ለውጥ በእምነታችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ብለን ሳንጠራጠር እንደ እግዚአብሔር ቃል መቀበል እንችላለን።

ለመሆኑ ክርስቲያኖች ዛሬ በእጃችን ያለው መጽሐፍ ምንም ስሕተት የለውም ለማለት እንችላለን? አንችልም። ነገር ግን ሁለት ነገሮችን መናገር ይቻላል። አንደኛው፥ የመጀመሪያው የሐዋርያት ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔር ቃል ነው። የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑም፥ ሐዋርያቱ የተጠቀሙበትም ቃል ሆነ የጻፉት አሳብ አንዳች ስሕተት የለውም። እንደ እግዚአብሔር ሁሉ፥ እነዚህም መጻሕፍት ውሸት የለባቸውም (ያዕ. 1፡17 ዘኁል. 23፡19)። ሁለተኛው፥ በየዘመኑ የተባዙት ቅጂዎች ስሕተት ባይታጣባቸውም፥ እነዚህ ልዩነቶች ግን አንዳች የአስተምህሮ ለውጥ አላስከተሉም። ስለ እግዚአብሔር፥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ስለ ደኅንነት፥ ስለ መንግሥተ ሰማይ፥ ሲኦል የምናውቀው ሁሉ ምንም ዓይነት ስሕተት የለውም። ስለሆነም ቅጂዎቹ በሚባዙበት ጊዜ ስሕትቶች እንደ ተከሰቱ ብናምንም፥ የትኞቹም ስሕተቶች ስለ ደኅንነትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የምናምነውን እውነት አይለውጡም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች የሚያጠኑት መጽሐፍ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ሙሉ በሙሉ ማመን አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ትክክል ነው ወይስ አይደለም በማለት መጠራጠር ብንጀምር ምን ይከሰታል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

የአዲስ ኪዳን አከፋፈል

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ኢየሱስ ስንት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ጻፈ? ለ) የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን የጻፉ የክርስቶስ ተከታዮችን ስም ዝርዝር።

ኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ ኪዳንን አልጻፈም። አዲስ ኪዳን የተጻፈው እርሱ ከዐረገ ከረዥም ጊዜ በኋላ ነበር። ስለዚህ አዲስ ኪዳን የተጻፈው ክርስቶስ ካረገ ከ20 ዓመት በኋላ ነበር። ምናልባትም በ49 ዓም አካባቢ የተጻፈው የመጀመሪያው መጽሐፍ የገላትያ መልእክት ሳይሆን አይቀርም ተብሎ ይገመታል። የመጨረሻው የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ የሆነው የዮሐንስ ራእይ የተጻፈው በ95 ዓ.ም. አካባቢ ነበር። ክርስቲያኖች በየስፍራው ተበትነው ይኖሩ ስለ ነበር፥ የእግዚአብሔር እስትንፋሰ የሆኑትን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ለመለየት ተጨማሪ 200 ዓመት ወስዷል።

የውይይት ጥያቄ፡– ኤር. 31፡31-34፤ ኢዩ. 2፡28-29፣ ሕዝ. 37፡24-28 አንብብ። እግዚአብሔር ስለሚመጣው ለውጥ ለአይሁዶች የገባው ቃል ኪዳን ምን ነበር?

የጥንት ክርስቲያኖች አሁን አዲስ ኪዳን ብለን በምንጠራው ጥራዝ ውስጥ የሚገኙትን መጻሕፍት ካሰባሰቡ በኋላ፥ መጽሐፍ ቅዱስን ለሁለት ከፈሉ። አይሁዶች እንደ እግዚአብሔር ቃል የተቀበሏቸውን የመጀመሪያዎቹን 39 መጻሕፍት ብሉይ ኪዳን ብለው ሰየሟቸው። (በክርስቶስ ዘመን የነበሩ አብዛኛዎቹ አይሁዶች 39ኙም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን ያምኑ ነበር። የዚህ ስብስብ ስምምነት ተግባራዊ የሆነው በ100 ዓ.ም. አካባቢ በተደረገው የአይሁድ ሸንጎ ነበር።) ክርስቲያኖች ከአይሁዶች ጋር በመስማማት እነዚህ መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን ተቀበሉ። ይህም ሆኖ፥ የክርስቶስ መምጣት ለውጥ እንዳስከተለ ያውቁ ነበር። ኤርምያስ፥ ኢሳይያስና ሌሎችም ነቢያት የተነበዩለት አዲስ ኪዳን፥ በክርስቶስ ሞት ተጀመረ። ስለሆነም ክርስቲያኖች ከክርስቶስ በፊት የተጻፉትን መጻሕፍት «ብሉይ ኪዳን» ብለው ጠሯቸው። ይህም እነዚህ መጻሕፍት ከክርስቶስ በፊት እግዚአብሔር ይሠራ የነበረበትን ሁኔታ የሚገልጹ መሆናቸውን እንዳመኑ ያሳያል። ነገር ግን ክርስቶስ በመምጣቱና በመስቀል ላይ በመሞቱ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፍቷል። ክርስቶስ ደሙ አዲስ ኪዳን» እንደሆነ ገልጾላቸው ነበር (ሉቃስ 22፡20)። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር በአይሁዶች ላይ ብቻ ማተኮሩን ትቶ ለአሕዛብ ሁሉ ዕቅዱን በመፈጸም ላይ ነበር። በመሆኑም የጥንት ክርስቲያኖች 27 መጻሕፍት የሚገኙበትን ሁለተኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አዲስ ኪዳን ብለው ጠሩት።

የውይይት ጥያቄ፡- የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን በቅደም ተከተል ዘርዝራቸው።

የጥንት ቤተ ክርስቲያን መሪዎች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ሲያሰባስቡ፥ ዝርዝራቸውን በጊዜ ቅደም ተከተል አላዘጋጁም ነበር። ነገር ግን በአምስት ዐበይት ምድቦች ከፍለዋቸው ነበር።

የመጀመሪያው ምድብ ወንጌላትን ያካትታል። እነዚህ በተለያዩ ደራሲያን የተጻፉ አራት መጻሕፍት፥ ስለ ክርስቶስ ሕይወትና ሞት ይተርካሉ።

ሁለተኛው ምድብ የሐዋርያት ሥራ ነው። ይህ ታሪካዊ ዘገባ፥ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ከኢየሩሳሌም ወደ ሮም መስፋፋቷን ያብራራል (ከ30 እስከ 40 ዓ.ም.)።

አብዛኛዎቹ መጻሕፍት የሚገኙት በሦስተኛው ምድብ ውስጥ ነው። እነዚህም በሐዋርያው ጳውሎስ የተጻፉ መልእክቶች ናቸው። እነዚህ በጊዜ ቅደም ተከተል የተዘረዘሩ ሳይሆኑ፥ ከረዥሙና በጣም አስፈላጊ (ሮሜ፥ 1ኛ ቆሮንቶስ) ከሆነው ወደ አጭሩ የፊልሞና መልእክት የሚያመሩ ናቸው። እነዚህም የጳውሎስ መልእክቶች በመባል የሚታወቁ ሲሆኑ፥ ለተወሰኑ አብያተ ክርስቲያናት ወይም ግለሰቦች የተላኩ ናቸው። እነዚህ መልእክቶች ሐዋርያው ጳውሎስ ስለተወሰኑ ጉዳዮች የሰጣቸውን ምክሮችና ትምህርቶች የሚያካትቱ ናቸው።

(ማስታወሻ፡- በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ማንነት ለረዥም ጊዜ ሲያከራክር ቆይቷል። አንዳንዶች ጸሐፊው ጳውሎስ እንደሆነ ያምናሉ። ይህም በአማርኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ርእስ ላይ ተንጸባርቋል። ሌሎች ምሑራን ደግሞ ሌላ ሰው እንደ ጻፈው ይገምታሉ። በግሪኩ ቅጂ ላይ መልእክቱ ስለ ደራሲው ማንነት አይናገርም። የዕብራውያን መልእክት በጳውሎስ መጻፉ ስላልተረጋገጠ በቀጣይ የአዲስ ኪዳን ምድብ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል።)

አራተኛው ምድብ እንደ ጴጥሮስ፥ ያዕቆብ (የክርስቶስ ወንድምና) ሐዋርያው ዮሐንስ በመሳሰሉት የተለያዩ ደራሲያን የተጻፉትን መልእክቶች ያጠቃልላል። እነዚህ መልእክቶች ለአንድ ግለሰብ ወይም ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን፥ ለሁሉም ክርስቲያኖች የተጻፉ በመሆናቸው ምሑራን አጠቃላይ መልእክቶች በማለት ይጠሯቸዋል። በዚህ ክፍል ውስጥ ስምንት መጻሕፍት ሲኖሩ፥ እነርሱም ከዕብራውያን እስከ ይሁዳ ያሉት ናቸው። እነዚህ መልእክቶች የተጻፉት ጠለቅ ያሉ ትምህርታዊ ትንታኔዎችን ለመስጠት ሳይሆን፥ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለማመልከት ነው።

በአምስተኛው ምድብ ውስጥ የሚገኘው የዮሐንስ ራእይ ነው። ክርስቲያኖች ይህ መጽሐፍ እግዚአብሔር የዘላለምን መንግሥት ለመመሥረት የወጠነውን አጠቃላይ ዕቅድ የሚያመለክት የመጨረሻው የእስትንፋሰ-እግዚአብሔራዊ ጽሑፍ እንደሆነ ስለ ተንዘቡ፥ በመጨረሻ ላይ አስገብተውታል፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ ይህ የመጨረሻ የእስትንፋሰ እግዚአብሔር መጽሐፍ መሆኑን ስለተገነዘበ የሚከተለውን ጽፎአል። «በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል ለሚሰማ ሁሉ እኔ እመሰክራለሁ፤ ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል፤ ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ዕድሉን ያጎድልበታል» (ራእይ 22፡18-19)፡ ምንም እንኳ ዮሐንስ ይህንን ማስጠንቀቂያ የሰጠው ስለ ራሱ መጽሐፍ ቢሆንም፥ የጥንት ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያው ለአዲስ ኪዳን በሙሉ የሚሠራ መሆኑን ተገንዝበው ነበር። በዚህ መጽሐፍ እግዚአብሔር እንዲጻፍ የፈለገው ሁሉ ተጽፎአል።

በ66ቱ መጻሕፍት ውስጥ እግዚአብሔር ይበልጥ እንዲያብራራልን የምንፈልጋቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም፥ እግዚአብሔር ሰዎች ከእርሱ ጋር ለመዛመድ የሚፈልጓቸውን ነገርች ሁሉ አመልክቷል። ለዚህም ነው ሌሎች መጻሕፍትንና የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እኩል መቁጠር አደገኛ የሚሆነው። እስትንፋሰ እግዚአብሔር የሆነ መጽሐፍ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ለጥያቄዎቻችን ሁሉ መልስ መፈለግ የሚገባንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) 2ኛ ጢሞ. 3፡16–17፤ 2ኛ ጴጥ. 1፡20-21 እንብብ። እነዚህ ጥቅሶች በእስትንፋሰ-እግዚአብሔር ስለተጻፈው ቃል ምን ያስተምራሉ? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች እውነትን ለማወቅ ሌሎች መጻሕፍትን ወይም ሕልሞችን ዋና ምንጭ አድርገው ለመጠቀም የሚፈተኑባቸውን መንገዶች ግለጽ። ሐ) ይህ አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው?

አዲስ ኪዳን እንደ ብሉይ ኪዳን በአንድ ሰው የተጻፈ አይደለም። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ፥ በሁሉም ዘመን የምትኖረው ቤተ ክርስቲያን የምትፈልገውን መልእክት ለመጻፍ የተለያዩ ሰዎችን መርጦ በልባቸውና በአእምሯቸው ውስጥ ተግባሩን አከናውኗል። አዲስ ኪዳንን የጻፉት ማቴዎስ፥ ማርቆስ፥ ሉቃስ፥ ዮሐንስ፥ ጴጥሮስ፥ ያዕቆብ፥ ይሁዳ፥ ጳውሎስና ያልታወቀው የዕብራውያን ጻሐፊ ናቸው። አዲስ ኪዳን የተጻፈበት ዘመን ቅደም ተከተል

ብሉይ ኪዳን የተጻፈው በ1000 ዓመታት ጊዜ ውስጥ (1400-400 ዓ.ዓ) ሲሆን፥ አዲስ ኪዳን የተጻፈው ደግሞ በ50 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነው (48– 100 ዓም)። ምንም እንኳ ምሑራን አንዳንድ መጻሕፍት የተጻፉባቸውን ትክክለኛ ጊዜ ባያውቁም፥ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ከተፈጸሙት ድርጊቶች ጋር በማነጻጸር መሠረታዊ ግምቶችን ለመስጠት ችለዋል። እነዚህ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የሚገኙ ድርጊቶች ደግሞ በዓለም ታሪክ ከተፈጸሙት ድርጊቶች ጋር ይነጻጸራሉ። ከዚህ በታች ስለ አዲስ ኪዳን መጻሕፍት የጊዜ ቅደም ተከተል የተሰጠውን ሠንጠረዥ አጥና። መጻሕፍቱ የተጻፉባቸውን ዓመታትና የተፈጸሙትን ክስተቶች አስተውለህ አጥና።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን አሁን ባሉበት ቅደም ተከተል ዘርዝር። የመጻሕፍቱን ሙሉ መጠሪያ ጻፍ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

የመካከለኛው ምሥራቅና የሮም ግዛት መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ በዕድሜ የገፉ ሰው ፈልግና ልጅ በነበሩበት ጊዜ፥ በኢትዮጵያ ውስጥ መኪና፥ ኤሌክትሪክ ወይም መንገዶች ባልነበሩበት ወቅት ሁኔታዎች ምን ይመስሉ እንደነበር ጠይቃቸው። ሰዎች ምን ያህል ርቀት ይጓዙ ነበር? እንዴት ይጓዙ ነበር? ምን ይለብሱ ነበር? . . . ወዘተ. ለ) ጥንታዊውን የጳለስቲናን ካርታ ተመልከትና ዐበይት ክፍሎችን ዘርዝር። ሐ) የመካከለኛውን ምሥራቅ ዘመናዊ ካርታ ተመልከት። ዛሬ ከጥንታዊ የእስራኤል ግዛቶች የትኞቹን ማን እንደሚያስተዳድር ግለጽ። መ) ጥንታዊ የሮም ግዛትን ካርታ ተመልከት። ጳውሎስ የሄደባቸውንና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ዐበይት ክፍሎች ዘርዝር። እነዚህን ነገሮች ካላወቅሃቸው፥ የጳውሎስን የሚሲዮናዊነት ጉዞ ካርታዎች ተመልከት። ሠ) በጥንታዊ የሮም ግዛት ውስጥ የነበሩትን ዘመናዊ አገሮች ዘርዝር። ከእነዚህ ዘመናዊ አገሮች ሐዋርያው ጳውሎስ የሄደው ወደየትኞቹ ነበር።

የጳለስቲና መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ

መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ በኢየሱስ ዘመን የነበረው ሕይወት በዚህ ዘመን ካለው ሕይወት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ እናስባለን። ነገር ግን በጳለስቲና የነበረው ሕይወት ከጣሊያን ወራሪ በፊት ከነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕይወት ጋር ተመሳሳይ ነው። ያኔ መኪና፥ መንገድ፥ መብራት፥ ኤሌክትሪክ፥ ትምህርት ቤት፥ ጤና ጣቢያ አልነበሩም። ይህን በአእምሮአችን ከያዝን፤ የክርስቶስና የደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ምን ይመስል እንደነበረ ልንገነዘብ እንችላለን። አኗኗራቸው ከትላልቅ ከተሞች ይልቅ በኋላ ቀር የገጠር መንደሮች ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ይመሳሰል ነበር።

ሌላው ብዙውን ጊዜ ለመረዳት የሚከብደን የጳለስቲና ምድር ምን ትመስል እንደነበር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ጳለስቲናን «ማርና ወተት የምታፈልቅ አገር» (ዘዳግ 31፡20) ሲል ይጠራታል። ነገር ግን ከደቡብ ኢትዮጵያ ለም መሬት ጋር ሲነጻጸር፥ ጳለስቲና ምድረ በዳ ናት። በስፋትም ቢሆን እስራኤል ከኢትዮጵያ ታንሳለች። ግዛቱ እጅግ ሰፊ በነበረበት በታላቁ ሄሮድስ ዘመን፥ የግዛቱ ጠቅላላ ርዝመት 400 ኪሎ ሜትር ያህል ነበር። ይህም ከአዲስ አበባ እስከ ወላይታ ሶዶ ያህል ነው። በአብዛኛው ግን ፍልስጥኤም 70 ኪሎ ሜትር ያህል ነች። ይህም ከአዲስ አበባ እስከ ናዝሬት ካለው ርቀት ትንሽ አነስ የሚል ነው። ከሌሎች የዓለም አገሮች ጋር ስትነጻጸር፥ የተስፋይቱ ምድር ትንሽ አገር ናት። በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ግን ይህች አነስተኛ ምድር ልዩ ስፍራ አላት። እግዚአብሔር አነስተኛ ቁጥር የነበራቸውን አይሁዳውያን በዚህች አነስተኛ አገር ምስክሮቹ እንዲሆኑ መረጣቸው። እግዚአብሔር ራሱ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ በተለየ መንገድ አደረ። የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው መሢሕ ለዓለም ኃጢአት ለመሞትና ለመኖር የመጣው ወደ አነስተኛ አገር ነበር።

እንደ ኢትዮጵያ በጳለስቲናም የተለያዩ የመሬት ዐይነቶች አሉ። በጥንቷ ጳለስቲና ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ብንጓዝ፥ በሜድትራኒያን ባሕር አጠገብ ያለው መሬት እንደ ስንዴ የመሳሰሉ ዐበይት እህሎች የሚበቅሉበት ለምለም ሜዳ መሆኑን እንረዳለን። ወደ ምሥራቅ ኢየሩሳሌም ስንጓዝ ደግሞ እንደ ሰንሰለት የተያያዙ ተራሮችና ኮረብታዎችን እናገኛለን። ብዙዎቹ እነዚህ ተራሮች እምብዛም ዛፍ ከሌለበትና ድንጋያማ ከሆነው የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ጋር የሚመሳሰሉ ናቸው። ኢየሩሳሌም የተመሠረተችው ከጠላት ጥቃት ከለላ ታገኝ ዘንድ በተራራው ጫፍ ላይ ነው። (የኢትዮጵያ ነገሥታትም ለደኅንነታቸው ሲሉ በተራሮች ላይ ቤተ መንግሥቶቻቸውን ሠርተው ይቀመጡ ነበር።) ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ ወደ ኢያሪኮ በምንጓዝበት ጊዜ፥ መሬቱ ድንጋያማና ረባዳ ሆኖ እናገኘዋለን። ከ25 ኪሎሜትር ርቀት በኋላ መሬቱ በሙት ባሕር አካባቢ ወደ 1600 ሜትር ዝቅ ይላል። ይህም ከዓለም እጅግ ዝቅተኛና ሞቃታማ ስፍራዎች አንዱ ነው። ይህ ከምሥራቅ ኢትዮጵያ የደንክል ሸለቆ ጋር ይመሳሰላል።

ከደቡብ ወደ ሰሜን በምንጓዝበት ጊዜ ምድሪቱ የተለያዩ ገጽታዎች እንዳሏት እንረዳለን። በደቡብ ከኬብሮን አጠገብ መሬቱ ደረቅና አለታማ፥ ተራሮች የሚበዙበት፥ ለበጎችና ለፍየሎች መሰማርያ የሚውል ነው። ከኢየሩሳሌም ወደ ሰሜን ስንጓዝ ደግሞ ድንጋያማው ተራራ በሰንሰለታማ ኮረብታዎች ይተካል። ይህም ከደቡብ ኢትዮጵያ ተራሮች ጋር የሚመሳሰል ነው። እነዚህ ተራሮች ለምለምና አረንጓዴ ናቸው። ከሰማርያ በስተሰሜን እስከ ገሊላ ድረስ ጥሩ የእርሻ መሬት ይገኛል። በገሊላ ባሕር ዳርቻ ዓሣ በማጥመድ የሚተዳደሩ ሰዎች የሚገኙበት ብዙ ከተሞች ነበሩ። የክርስቶስ አገልግሎት ያተኮረው በእነዚህ ዓሣ በማጥመድና በግብርና በሚተዳደሩ ማኅበረሰቦች ላይ ነበር። ከሰሜን ገሊላ እስከ ሊባኖስ ድረስ ምድሪቱ አሁንም ተራራማ ገጽታ አላት። እነዚህ ተራሮች በሚዛን ተፈሪ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዱሮች ጋር የሚመሳሰሉ ነበሩ።

ሐዋርያው ጳውሎስ እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ጠቢባንንና ታላላቆችን ሳይሆን ድሆችንና ዓለም እንደ ሞኝነት የሚቆጥረውን ነገር እንደ መረጠ ገልጾአል። እግዚአብሔር መንግሥቱን የሚመሠርተው ዓለም እንደ ምናምንቴ በሚቆጥረው ነገር ላይ ነው (1ኛ ቆሮ. 1፡18-25)። ይህ ሁኔታ አይሁዶችንና አገራቸውን በተመለከተ እውነት ነው። አይሁዶች በጣም የሠለጠኑና በአካባቢያቸው ከሚገኙ አገሮች ሁሉ የተሻሉ ናቸው ብለን እናስብ ይሆናል። እውነቱ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። ጳለስቲናን እንደ ምናምንቴና ኋላቀር አገር ነበር የሚመለከቱት። አሕዛብ ጳለስቲናን ዝቅ አድርገው ይመለከቷት ስለነበረ ያለምንም ስጋት አይሁዶች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ይፈቅዱላቸው ነበር። ጳለስቲና ለአሕዛብ አገር የምትጠቅም ያደረጋት አንድ ነገር ቢኖር ከተለያዩ አገሮች ለሚመጡ ነጋዴዎች ዋነኛ መተላለፊያ መሆኗ ነበር። በግብፅና በሜሶጶጣሚያ፥ እንዲሁም በሳውዲ ዓረቢያና በሜሶጶጣሚያ መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ ይደረግ የነበረው በጳለስቲና በኩል ነበር።

ይህች አነስተኛ የነበረች የዓለም ክፍል፥ እግዚአብሔር ለዓለም ሕዝቦች ለወጠነው ዕቅዱ መዲና ነበረች። እግዚአብሔር ያይ የነበረው ሥልጣኔዋን ወይም ፖለቲካዊ ኃይሏን አልነበረም። እርሱ ይፈልግ የነበረው ከሌሎች ሕዝቦች የተለየ ሕይወት እየኖረ እርሱን የሚያከብርና የሚታዘዝ ሕዝብን ነበር፡ እግዚአብሔር ቁጥራቸው ጥቂት በሆነ ሕዝብ ምሳሌነት ዓለምን ለመለውጥ ይችላል። እግዚአብሔር ልጁን የላከው ወደዚህች ዝቅተኛና ኋላ ቀር አገር ነበር። አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር ኢየሱስ ከጳለስቲና ምድር አይወጣም ነበር። የጳለስቲና የሥልጣን ማዕከል በነበረችው በሮም መወለድ ይችል ነበር። የሥልጣኔ ማዕከል በሆነችው በግሪክ መወለድ ይችል ነበር። ነገር ግን የፖለቲካ ሥልጣንና ሥልጣኔ ክርስቶስን ወደ ጳለስቲና ለላከው እግዚአብሔር ዐቢይ ጉዳዮች አልነበሩም።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ጳለስቲናን የዕቅዱ ማዕከል ካደረገበት ሁኔታ ስለ አሠራሩ ምን እንማራለን? ለ) ይህን እውነት በሕይወትህ እንዴት እንደተመለከትህ ግለጽ።

የሮም ግዛት መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ

እግዚአብሔር በዕቅዱ የሮም ግዛት በምዕራቡ ዓለም ታሪክ፥ ከሁሉም የበለጠ ጠንካራና ለረዥም ጊዜ የቆየ መንግሥት እንዲሆን አድርጓል። የሮም ግዛት ከሕንድ እስከ ታላቋ ብሪታኒያና ከዚያም እስከ ሰሜን አፍሪካ ድረስ የተንሰራፋ ነበር። ለ1600 ዓመታት ቤተ ክርስቲያን በብዛት ያደገችው በዚሁ የዓለም ክፍል ነበር።

በመጀመሪያዎቹ 15 ዓመታት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷ ያተኮረው በጳለስቲና አካባቢ ነበር። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ወንጌልን ወደ ኢየሩሳሌም፥ ይሁዳና ሰማርያ እንዲወስዱ የሰጣቸውን ትእዛዝ በመፈጸም ላይ ነበሩ። ነገር ግን እግዚአብሔር በራሱ መንገድ ሥራውን በመሥራቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ወንጌል ወደ አንጾኪያ ከተማ ደረሰ። አንጾኪያ በመካከለኛው ምሥራቅ የግሪክ መንግሥት ነበረች። እግዚአብሔር ዓለምን በወንጌል ለመድረስ ያዘጋጀው ዕቅድ የጀመረው፥ ወንጌል በአንጾኪያ በአሕዛብ መካከል ሥር ከሰደደ በኋላ ነበር። እንደ ጳውሎስና በርናባስ ባሉት ታላላቅ የወንጌል መልእክተኞች አማካይነት ወንጌል በሮም ግዛት ውስጥ መስፋፋት ጀመረ።

ጥንታዊው ሥልጣኔ ተስፋፍቶ የሚገኘው በሜድትራኒያን ባሕር ዳርቻ 100 ኪሎ ሜትር አካባቢ ነበር። ጳውሎስና በርናባስ ወንጌልን ያደረሱት ወደ ባሕር ዳርቻ አካባቢዎች ነበር። በመጀመሪያው ምእተ ዓመት ወንጌል ሥር የሰደደባቸው እንደ አንጾኪያ፥ ቆላስይስ፥ ኤፌሶን፥ ፊልጵስዩስ፥ ተሰሎንቄ፥ ቆሮንቶስ፥ ሮምና እስክንድርያ የመሳሰሉ አገሮች፥ ለባሕር ዳርቻ ቅርብ ነበሩ። በመጀመሪያው ምእተ ዓመት መጨረሻ ላይ፥ ክርስቲያኖች በዛሬዎቹ ግብፅ፥ እስራኤል፥ ሶሪያ፥ ቱርክ፥ ግሪክና ጣሊያን አገሮች ውስጥ ይኖሩ ነበር።

የጥንቱ ሥልጣኔ የተመሠረተው በሜሶጶጣሚያ ባሕር አካባቢ በመሆኑ፥ ሐዋርያት ሁለት የጉዞ አማራጮች ነበሯቸው። እነዚህን ከተሞች በሚያገናኙ ዋና ዋና መንገዶች በእግራቸው ይጓዙ ነበር። ጳውሎስ በወንጌል አገልግሎት ጉዞው ወቅት በሁለቱም አማራጮች ተጠቅሟል። ብዙውን ጊዜ በሮም ዋና ዋና መንገዶች የሚጓዘው ከከተማ ወደ ከተማ በሚሄድበት ጊዜ ነበር። ነገር ግን ከአንዱ አውራጃ ወደ ሌላው ርቆ በሚሄድበት ጊዜ በመርከቦች ይጓዝ ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

የመጀመሪያው ምእተ ዓመት ሃይማኖቶችና ፍልስፍናዎች

ሰዎችን ለማወቅ በምንፈልግበት ጊዜ ፖለቲካቸውንና ታሪካቸውን ብቻ ሳይሆን፥ ሃይማኖታቸውንም ጭምር መመርመር ይኖርብናል። እግዚአብሔር ሰዎችን ለልጁ መምጣት ለማዘጋጀት የዓለምን ሃይማኖት ይመራ ነበር።

የውይይት ጥያቄ- ወንጌሉን ከማብራራታችን በፊት ስለ አንድ ሰው ሃይማኖት ማወቅ የሚጠቅመን ለምንድን ነው?

ይሁዲነት

በኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን 4 ሚሊዮን የሚሆኑ አይሁዶች እንደ ነበሩ ይገመታል። (ዛሬ 6 ሚሊዮን ያህል አይሁዶች አሉ።) ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በታች የሚሆኑት አይሁዶች በጳለስቲና ውስጥ ይኖሩ ነበር። የቀሩት በሮም ግዛቶች ውስጥ፥ በተለይም በታላላቅ ከተሞች ተበትነው ይኖሩ ነበር። ለአይሁዶች ሁሉ የዳዊት ከተማ የሆነችው ኢየሩሳሌም የይሁዲነት መዲና ነበረች። አይሁዶች የትም ይኑሩ የት፥ ሁልጊዜ ኢየሩሳሌምን እንደ እውነተኛ ቤታቸው ስለሚመለከቷት በሚያስፈልገው ሁሉ፤ በተለይም ገንዘብ በመላክ ይደግፉዋት ነበር።

ዛሬ በክርስቲያን ቤተ እምነቶች መካከል ልዩነት እንዳለ ሁሉ፥ በአይሁድ እምነት ተከታዮች መካከልም ልዩነት አለ። ይህም ሆኖ፥ አይሁዶች ሁሉ በጋራ የሚከተሏቸው አንዳንድ መሠረታዊ እምነቶች አሉ።

 1. አይሁዶች ልዩና የተመረጡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንደሆኑ ያምኑ ነበር። ይህም በአብርሃም፥ በይስሐቅና በያዕቆብ፥ እንዲሁም በሲና ተራራ በሙሴ አማካይነት፥ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር ልዩ ግንኙነትን እንደመሠረተ ይታወቃል። ከዚህም የተነሣ አይሁዶች ልዩ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደሆኑና ከሌሎች ሕዝቦች ይልቅ እግዚአብሔር እነርሱን የመባረክ ዕቅድ እንዳለው ያምኑ ነበር።
 2. አይሁዶች ሰማይንና ምድርን የፈጠረ አንድ እውነተኛ አምላክ ብቻ እንዳለ በጽኑ ያምናሉ። እርሱ መንፈስ ስለሆነ፥ በጣዖት ሊመሰል አይችልም፥ ስለሆነም፥ የትኛውም ዐይነት አምልኮተ ጣዖት የተወገዘ ነው፤ ምክንያቱም ይህ እግዚአብሔርን እንደ መካድ ይቆጠራል ይላሉ።
 3. እግዚአብሔር ለአይሁዶች የራሳቸው መሬት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር። ይህችም የጳሊስትና ምድር ናት። እግዚአብሔር ይህችን ምድር ለዘላለም ሰጥቷቸዋል። እግዚአብሔር የአምልኮቱ ማዕከል የሆነችውን ኢየሩሳሌምን ልዩ አድርጓታል። ይህም የእግዚአብሔር ምድራዊ ዙፋን በኢየሩሳሌም እንደተቀመጠ ያህል አስቆጥሮታል። ስለሆነም አይሁዶች የጳለስቲናን ምድርና ቤተ መቅደስ ለመጠበቅና ለመከላከል ነፍሳቸውን እንኳ አሳልፈው ከመስጠት አይመለሱም ነበር።
 4. አይሁዶች አንድ ቀን እግዚአብሔር የመረጠው የተለየ ሰው ወደ ጳለስቲና እንደሚመጣ ያምኑ ነበር። ይህ መሢሕ ሮማውያንን እንደሚያሸንፍና ሕዝቡን ከአሕዛብ አገዛዝ ነፃ እንደሚያወጣ ተስፋ ነበራቸው። በኢየሩሳሌም ከተማ ሆኖ በመግዛት በዓለም ላይ ሰላም ያሰፍናል ይሉ ነበር።
 5. በመላው ዓለም የተበተኑ አይሁዶች ለአምልኮና ለማኅበራዊ አገልግሎት፥ ምኩራቦችን በማዕከልነት ይጠቀሙ ነበር። በኢየሩሳሌም ከተማ ከ400 በላይ ምኩራቦች የነበሩ ሲሆን፥ በቤተ መቅደሱም ውስጥ ሳይቀር አንድ ምኩራብ ነበር። በአሕዛብ አገዛዝ ዘመን አይሁዶች ሃይማኖታቸውን ከአካባቢያቸው ጋር አስማምተው ለመኖር ተገድደው ነበር። ለምሳሌ፥ ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውጭ እንስሳትን ሊሠዉ አይችሉም ነበር። ለመሆኑ እንስሳትን ሳይሰዉ እግዚአብሔርን የሚያመልኩት እንዴት ነው? ይህን ችግር ለማስወገድ ነበር የአይሁድ ማኅበረሰብ የአምልኮና የትምህርት ማዕከል የሆኑት ምኩራቦች የተመሠረቱት። አይሁዶች በሰንበታት ቀን ከብሉይ ኪዳን እያነበቡና የዳዊትን መዝሙር እየዘመሩ እግዚአብሔርን ያመልኩ ነበር። ከዚያም ስብከት ያዳምጣሉ። ብዙውን ጊዜ ስብከቱን የሚያቀርበው ከሌላ ስፍራ የሚመጣ አገልጋይ ነበር። ክርስቶስ በየሰንበቱ ወደ ምኩራቦች እየሄደ ያመልክ ነበር። ብዙ ጊዜም እንዲሰብክ ይጋበዝ ነበር (ሉቃስ 4፡16-21 አንብብ)። በኋላም ሐዋርያው ጳውሎስ በደረሰበት ከተማ ሁሉ መጀመሪያ በምኩራብ ውስጥ ይሰብክ ነበር። የአይሁድ መሪዎች እስከአባረሩት ጊዜ ድረስ በምኩራብ ውስጥ መስበኩን አልተወም ነበር (የሐዋ. 13፡42-50፤ 14፡1-5)።

ከአምልኮ በተጨማሪ፥ ምኩራቦች የትምህርትም ማዕከል ነበሩ። የአይሁዳውያን ልጆች ስለ ሃይማኖታቸውና ስለ ብሉይ ኪዳን በምኩራቦች ውስጥ ይማሩ ነበር።

 1. ትኩረት የሚሰጠው በአስተምህሮዎች ላይ ሳይሆን፥ በውጫዊ ተግባራት ላይ ነበር። አይሁዶች የተለያየ ሥነ መለኮታዊ አስተምህሮ ቢኖራቸውም በአንድነት ለመኖር ፈቃደኞች ነበሩ። ይህም ሆኖ አይሁድ ሁሉ አንድ ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዐት እየፈጸሙ አንድ ዓይነት የሕይወት ዘይቤ እንዲከተሉ አጥብቀው ይሻሉ።

ከጊዜ በኋላ አይሁዶች ሕያው የሆነውን አምላክ ከማምለክ ይልቅ ሥርዓቶችንና ሕጎችን መከተል ጀመሩ። ስለሆነም በብሉይ ኪዳን ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕጎችን ጨመሩ። እነዚህ ተጨማሪ ሕጎች አይሁዶች የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን እንዴት ከሕይወታቸው ጋር እንደሚያዛምዱ የሚተረጉሙ ነበሩ። ለምሳሌ፥ በብሉይ ኪዳን በሰንበት ቀን ሥራን የሚከለክል ሕግ አለ። ነገር ግን አይሁዶች «ሥራ ምንድን ነው?» የሚል ጥያቄ አንሥተው የራሳቸውን ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህም መሠረት በሰንበት ቀን ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ በእግራቸው አይሄዱም፤ ጉድጓድ ውስጥ የወደቀ ሰው አያወጡም፤ እንዲሁም እህል አያጭዱም። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች እነዚህን ሕጎች ከመጀመሪያዎቹ የብሉይ ኪዳን ሕጎች እኩል ያከብሯቸውና ያስከብሯቸው ነበር። ለሕዝቡ ግን እነዚህ ሕግጋት ተጨማሪ ሸክሞች ነበሩ። ከእነዚህ ሕግጋት የተነሣ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር መዛመዳቸውንና እርሱንም ደስ ማሰኘታቸውን ትተው የሕግ ዝርዝሮችን መከተል ጀመሩ። ክርስቶስ አብዛኛውን ጊዜ ከአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ጋር ሲጋጭ የነበረው እነዚህን ሕግጋትና ሥርዓቶቻቸውን ባለመፈጸሙ ምክንያት ነበር (ማር. 1፡1–15 አንብብ።) ኢየሱስ በሰው ውስጣዊ ነገር ማለትም በልቡና በአመለካከቱ ላይ በማተኮር፥ ውጫዊ ልማዶችን መከተል ምንም ፋይዳ እንደሌለው አስተምሯል። ከዚህም የተነሣ፥ የሃይማኖት መሪዎች ጠሉት።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖች ዛሬም የአንድ ሰው ውጪአዊ ልምምድ ከአመለካከቱና ከእምነቱ እንደሚበልጥ አድርገው የሚያስቡት ለምንድን ነው?

ከጊዜ በኋላ ሁለት ዓይነት የአይሁድ እምነት ተከታዮች ተነሡ። እነርሱም በጳለስቲና አገር ያደጉ አይሁዶች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን እውነተኛና እጅግ ንጹሕ አይሁድ አድርገው ይቆጥሩ ነበር። እነዚህ አይሁዶች ይሁዳዊ አኗኗራችንን በንጽሕና መጠበቅ አለብን ብለው ስላመኑ፥ ከአሕዛብ ባህል ጋር ተስማምቶ የመኖርን ነገር ሙሉ በሙሉ ይቃወሙት ነበር። ሌሎቹ ደግሞ በአሕዛብ አገር ያደጉ አይሁዶች ነበሩ። እነዚህ አይሁዶች የግሪክ እንጂ የአረማይስጥ ቋንቋ ስለማይናገሩና የአሕዛብን ባህል ስለሚከተሉ፥ እንደ ንጹሕ አይሁዶች አይታዩም ነበር። አንዳንድ ጊዜ በእነዚህ ሁለት ቡድኖች መካከል ውጥረቶች ይቀሰቀሱ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋ. 6፡1-7 አንብብ። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ይህ ልዩነት የተንጸባረቀው እንዴት ነው?

የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 3፡7፤ 5፡20፤ 16፡1፤ 22፡23፤ የሐዋ. 23፡6-10 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ የተጠቀሱት የተለያዩ የሃይማኖት ቡድኖች የትኞቹ ናቸው? ለ) እነዚህ ቡድኖች አንዱ ለሌላው የነበራቸው አመለካከት ምን ይመስላል? ሐ) ስለ እነዚህ ቡድኖች የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት የሚሰጠውን ማብራሪያ አንብብና እምነታቸው እንዴት እንደሚለያይ ግለጽ።

አብዛኛውን ጊዜ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች እርስ በርስ ይናቆራሉ፤ ሰዎችም እነርሱንና አመለካከታቸውን እንዲከተሉ ለማድረግ ይጥራሉ። በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ሌሎች ቡድኖችን የሚቃወሙ ቡድኖች አሉ። እነዚህም የኦርቶዶክስና የፕሮቴስታንት፥ ካሪዝማቲክና ኢ-ካሪዝማቲክ፥ የተለያዩ የእምነት ክፍሎች ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱ መከፋፈል በክርስቶስና በሐዋርያት ዘመንም የተለመደ ነበር። በወንጌላት ውስጥ ክርስቶስንና ሐዋርያትን የሚቃወሙ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ድርጅቶች እንደ ነበሩ ብዙ ጊዜ ተጠቅሰዋል። እነዚህ ቡድኖች ክርስቶስን ይጠሉትና እንዲሰቀል ይፈልጉ የነበረው ለምንድን ነው? መልሱ በፖለቲካዊ ፍላጎት ምክንያት ነው የሚል ነው። ኢየሩሳሌም ሃይማኖታዊ ማእከል በመሆኗ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ቁርኝቶች ነበሩ። ሊቀ ካህናቱ የአይሁድ ሃይማኖትና የፖለቲካ መሪ ነበር። ስለሆነም እነዚህ ቡድኖች የሚታገሉት ብዙውን ጊዜ በተለያዩ ሃይማኖታዊ እምነቶች ስም ሳይሆን፥ በአገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ ነበር።

 1. ፈሪሳውያን፡- በመጀመሪያው ምእተ ዓመት ወቅት ፈሪሳውያን በቁጥር የበዙና ኃይልም የነበራቸው ሃይማኖታዊ ቡድኖች ነበሩ። ፈሪሳውያን ምናልባት መሠረታቸውን ያገኙት በ135 ዓ.ዓ አንዳንድ አይሁዶች በይሁዲነት ውስጥ ምግባረ ብልሹነትን ተመልክተው ራሳቸውን ከሕዝቡና ከወቅቱ ፖለቲካዊ ሥልጣን በለዩበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ ይገመታል። ፈሪሳውያን በአብዛኛው የፖለቲካ ሥልጣን ከያዙትና ይስማሙ ከነበሩት፥ እንዲሁም የግሪክን ባህል ለመከተል ይፈልጉ ከነበሩ ሰዱቃውያን ጋር ጠላቶች ነበሩ።

በሥነ መለኮታዊ አቋማቸው ፈሪሳውያን በጣም አክራሪዎች ነበሩ። ሁሉንም የብሉይ ኪዳን ሕጎችና ከዕዝራ ዘመን አንሥቶ የአይሁድ መሪዎች በየጊዜው የደነገጓቸውን ሕጎች በሙሉ ለመከተል የቆረጡ ነበሩ። ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ትንቢተ ሚልክያስ ድረስ ያለው የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ያምናሉ። በሙታን ትንሣኤና እግዚአብሔር በሰዎች ሁሉ ላይ የሚፈርድ አምላክ እንደሆነ ያምናሉ። አምልኮ ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ሕያው ግንኙነት ሳይሆን፥ ሕግን እንደ መጠበቅ አድርገው ይመለከቱ ነበር። ከልባቸው እግዚአብሔርን የሚፈልጉና በሕይወታቸው ደስ ሊያሰኙት የሚፈልጉ ብዙ ፈሪሳውያን ነበሩ። ችግሩ ሃይማኖታዊ ሥርዐታቸው ወደ እግዚአብሔር በትሕትና ቀርበው ምሕረቱን እንዳይሹ ይልቁንም በገዛ ጽድቃቸውና ሥራቸው እንዲታበዩ አድርጓቸዋል (ሉቃስ 18፡9-14)። ኒቆዲሞስና የአርማቲያው ዮሴፍ ክርስቶስን የተከተሉ ፈሪሳውያን ምሳሌዎች ነበሩ።

ፈሪሳውያን ክርስቶስ ሕግ አጥባቂና የአይሁድ አባቶች የደነገጉትን ልማድ የሚያጣጥል ስለመሰላቸው፥ በብርቱ ይቃወሙት ነበር። በተጨማሪም ክርስቶስ ሕግጋትንና ሥርዓቶችን ለመጠበቅ ከመጣር ይልቅ፥ በማኅበረሰቡ ዘንድ ኃጢአተኞች ተብለው ከተገለሉ ከቀራጮች ጋር ይታይ ስለነበርና ሌሎችንም ይረዳ ስለነበር ፈሪሳውያን ሊገድሉት ፈለጉ።

ፈሪሳውያን ጳውሎስንም በብርቱ ተቃውመውት ነበር። ጳውሎስ በክርስቶስ ከማመኑ በፊት ፈሪሳዊ ነበር (የሐዋ. 23፡6)። በዚያን ጊዜ ሳውል ይባል የነበረው ጳውሎስ፥ ሕግን ለመጠበቅ ከነበረው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሣ፥ ለብሉይ ኪዳን እንቅፋት ይሆናሉ ብሎ ያሰባቸውን የክርስቶስን ተከታዮች በብርቱ ያሳድዳቸው ነበር። በአፀፋው ደግሞ ጳውሎስ በክርስቶስ ባመነ ጊዜ ፈሪሳውያን ያሳድዱት ጀመር። ጳውሎስ ደኅንነት ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋ እንደሚገኝ ሲያስተምር፥ የፈሪሳውያንን የእምነት መሠረት እንደሚያናጋ ሰው አድርገው በመቁጠር ተቃወሙት። ከዳኑ በኋላ የአሕዛብ ክርስቲያኖች መገረዝ አለባቸው ያሉት፥ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ ሰዎች አሕዛብ በእግዚአብሔር ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት ለማግኘት እንዲችሉ ወደ ይሁዲነት መለወጥ እንዳለባቸው በየቤተክርስቲያኑ እየዞሩ አስተምረዋል (የሐዋ. 15፡1-2፣ ገላ. 2፡1-15)።

ፈሪሳውያን የአይሁድ እምነት ቅድመ አያቶች ናቸው። መደበኛው የፈሪሳውያን ቡድን ኢየሩሳሌም ከተደመሰሰች በኋላ ቢጠፋም፥ ትምህርታቸው ግን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ቆይቷል።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖችም እግዚአብሔርን በትሕትና ከማፍቀርና ከማምለክ ይልቅ፥ በውጫዊው ሕግ ላይ በማተኮር ራሳቸውን የሚያጸድቁት እንዴት ነው?

 1. ሰዱቃውያን፡- የፈሪሳውያንን ያህል ብዙ ቁጥር አልነበራቸውም። ነገር ግን በአይሁድ ላይ ሊቀ ካህንና ገዥ ሆነው የሠሩና ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው ቡድኖች ነበሩ። ሰዱቃውያን የዘር አመጣጣቸውን የሚቆጥሩት በንጉሥ ዳዊት ዘመን ከነበረው ዛዶክ ከተባለ ካህን ነው። እስከ ምርኮ ዘመን ድረስ ዘሮቻቸው በሊቀ ካህንነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል (2ኛ ዜና 31፡10፤ ሕዝ. 40፡46፤ 44፡15)። አብዛኛዎቹ ሰዱቃውያን በአመዛኙ ካህናት ነበሩ። ለእነርሱ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ሥልጣን ትልቅ ስፍራ ነበረው። ሰዱቃውያን ሥልጣናቸውን ጠብቀው ለማቆየት ሲሉ በሥልጣን ላይ ካለው ከማንኛውም ቡድን ጋር ከመተባበር ወደ ኋላ አይሉም ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ከሌሎች አይሁዶች በላይ የአሕዛብን አገዛዝና የግሪክን ባህል ለመቀበል ፈቃደኞች የነበሩ ናቸው። በክርስቶስና በሐዋርያቱ ዘመን ሰዱቃውያን የቤተ መቅደስ አምልኮና የአይሁዶች ሸንጎ መሪዎች ነበሩ።

ሰዱቃውያን አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት ብቻ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆኑ ስለሚያምኑ እነዚህን መጻሕፍት በጥንቃቄ ይከተሏቸዋል። ሌሎቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል እንደሆኑ አድርገው አያምኑም ነበር። ሰዱቃውያን ለሃይማኖት አባቶች ትውፊት ደንታ የማይሰጣቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፥ በመናፍስቱ ዓለምና በሙታን ትንሣኤ አያምኑም ነበር።

ሰዱቃውያን ክርስቶስን ለመቀበል ያልፈለጉት ይቀናቀነናል ብለው ስለ ሰጉ ነበር። መሲሕ እንደ መሆኑ፥ በሕዝቡ ላይ የነበራቸውን ሥልጣን ይወስድብናል ብለው ፈሩ። ብዙ ሰዎች እየተከተሉት ሲመጡ፥ የሰዱቃውያኑ ስጋት ይበልጥ እያየለ መጣ። እንዲሁም ክርስቶስ በሮም ላይ የዐመፅ እንቅስቃሴ ካቀጣጠለ፥ ሮማውያኑ በዐመፀኞቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በቀሳውስቱም ጭምር (በሰዱቃውያኑም) ላይ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ሲያስቡ እጅግ ፈሩ። ሊቀ ካህናቱ እንደተናገረው ሕዝቡ ከሚጠፋ ክርስቶስ ቢሞት ይመርጡ ነበር (ዮሐ 11፡49-50)። ያም ሆነ ይህ ሕዝቡ ተደምስሶ ነበር። ይህ የሆነው ግን በ64 ዓ.ም. የአገርና የነጻነት ቀናኢ ቡድንና ሌሎችም በማመፃቸው እንጂ፥ በክርስቶስ ምክንያት አልነበረም። በ70 ዓ.ም ሮማውያን ኢየሩሳሌምን በከበቡ ጊዜ፥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዱቃውያን ሞቱ ቡድናቸውም ህልውናውን አጣ።

 1. ጸሐፍት፡- ከዕዝራ ዘመን ጀምሮ «ጸሐፍት» ተብሎ የሚጠራ አንድ ቡድን ነበር። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እነዚህን ሰዎች፥ «የሕግ መምህራን» ብሎ ይጠራቸዋል። አይሁዶች በምርኮ ከተወሰዱ በኋላ፥ የዕብራይስጥ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር እየመነመነ ሄደ። የመግባቢያ ቋንቋቸው አረማይስጥ በመሆኑ፥ ብሉይ ኪዳንን የሚተረጉምላቸው ሌላ ሰው ያስፈልጋቸው ነበር። ይህም የተወሰኑ ሰዎች የብሉይ ኪዳን ምሑራን እንዲሆኑ አደረገ። እነዚህ ሰዎች በዕብራይስጥ ቋንቋና በብሉይ ኪዳን ላይ ጥልቅ ጥናት ስላደረጉ ሊቅ ለመሆን በቁ። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ለማወቅ ሲፈልጉ፥ እነዚህን ሰዎች ይጠይቁ ነበር። ጸሐፍት የተባሉ ሰዎች የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን እንዲጠብቁ ይረዳል ያሉትን ማብራሪያ እየሰጡ፥ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር አብረው ይሠሩ ነበር። እነዚህ ጸሐፍት ብዙውን ጊዜ በምኩራቦችና በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ያስተምሩ ስለ ነበር፥ ራሳቸውን የእውነት ጠባቂዎች አድርገው ይቆጥሩ ነበር።

ጸሐፍት ራሱን የቻለ ቡድን ስላልመሠረቱ፥ በፈሪሳውያንም በሰዱቃውያንም ቡድኖች ውስጥ ነበሩ። ክርስቶስ በሕግ ትርጓሜያቸውና በእነርሱ እገዛ በረቀቁት ደንቦች ላይ ተቃውሞውን ስለ ገለጸ፥ ጸሐፍትም ጠላቶቹ ሆኑ።

 1. ኢሴናውያን፡- አዲስ ኪዳን ይህን ቡድን በስም ባይጠቅሰውም፥ ብዙ ምሑራን በመጥምቁ ዮሐንስ፥ በኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት፥ እንዲሁም በዮሐንስ ጽሑፎች ውስጥ፥ የኢሴናውያን ተጽዕኖ እንዳለ ያምናሉ። ኢሴናውያን ቅድስናን ለማግኘት ከማኅበረሰቡ መገለል አስፈላጊ እንደሆነ ያስተምሩ ነበር። ይህም አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ከሕዝቡ ተለይተው በገዳም ውስጥ በምናኔ ከሚኖሩበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። እነዚህ ሰዎች በሙት ባሕር አካባቢ አያሌ ማኅበረሰቦችን አቋቁመው ይኖሩ ነበር። ሰዎች ከኢሴናውያን ጋር በሚቀላቀሉበት ጊዜ መጠመቅና የዚያን ማኅበረሰብ ሕግ ለማክበር መስማማት ነበረባቸው። በኢሴናውያን ዘንድ ጋብቻ የተከለከለ ሲሆን፥ ሀብታቸውን በጋራ ይጠቀሙ ነበር። እንደ ፈሪሳውያን ሁሉ የተለያዩ ሕጎችንና ደንቦችና በመጠበቁ ላይ እንጂ፥ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት በማድረጉ ላይ አጽንኦት አይሰጡም ነበር። ክፉዎችን አጥፍቶ የጻድቃንን መንግሥት የሚመሠርተው መሢሕ፥ በፍጥነት እንዲመጣላቸው ይናፍቁ ነበር። ከሚወዷቸው አገላለጾች መካከል ኃጢአተኞችን «የጨለማ ልጆች»፥ ጻድቃንን «የብርሃን ልጆች» የሚሉ ይገኙባቸዋል። ምሑራን ከኢየሩሳሌም መውደም በኋላ ይህ ቡድን በምን ምክንያት እንደጠፋ አላወቁም።

የውይይት ጥያቄ፡- የኢሌናውያን ትምህርትና ልምምድ ከጥንቷና ከቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሚመሳሰለውና የሚለያየው እንዴት ነው?

 1. የአገርና የነጻነት ቀናኢ ቡድን፡- ይህ ቡድን ሃይማኖታዊ ቡድን ባይሆንም በክርስቶስና በሐዋርያት ዘመን በዓለም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ ቡድን ነበር። ይህ ቡድን ፖለቲካዊ ቡድን ሲሆን፥ በዐመፅ ተዋግተው ከሮም አገዛዝ ነፃ ለመውጣት የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። እነርሱም ስግደትና አምልኮ የሚገባው ለእግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ፥ ቀረጥም መክፈል ካስፈለገ ለእርሱ ብቻ ሊሰጥ እንደሚገባ ያምኑ ነበር። ሮማውያን በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ በመሠልጠንና ቀረጥም ከእነርሱ በመሰብሰብ በአይሁድ አምልኮ ውስጥ ጣልቃ ይገቡ ነበር። በመሆኑም ቀናተኞች በአነስተኛ ቡድኖች ተደራጅተው ሮማውያንን ይወጓቸው ነበር። ማንኛውንም የተቃውሞ መንገድ ከመጠቀም አይመለሱም ነበር (የሐዋ. 21፡38)። በዚህም ተግባራቸው የመቃብያንን ምሳሌነት እንደሚከተሉ ያምኑ ነበር። ይህ ፓርቲ የገሊላው ይሁዳ በተባለ ግለሰብ በ6 ዓ.ም እንደተመሠረተ ይታመናል (የሐዋ. 5፡37)። አብዛኞቹ ቀናተኞች ገሊላውያን ነበሩ። ከክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ስምዖን በአንድ ወቅት የዚህ ቡድን አባል የነበረ ይመስላል (ሉቃስ 6፡15)።

ከ66-70 ዓ.ም በሮማውያን ላይ ጦርነት የከፈቱት እነዚህ ቡድኖች ነበሩ። የሚያሳዝነው ከሮማውያን ይልቅ እርስ በርሳቸው ወይም ከሌሎች አይሁዶች ጋር ሲዋጉ ቆይተዋል። አንድ ግንባር አለመፍጠራቸው ሮማውያን በቀላሉ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን እንዲቆጣጠሩ አስችሏቸዋል። ከኢየሩሳሌም መፈራረስ በኋላ ውጊያቸውን ቀጥለው በ135 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ በሮማውያን ተደምስሰዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህ ቡድኖች ክርስቶስና የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን በነበሩበት ዘመን ካሳደሩት ተጽዕኖ ምን እንማራለን?

የአሕዛብ ሃይማኖቶች

በኢየሱስ ዘመን አሕዛብ እንዴት በዓይን የማይታይ አምላክ ማምለክ እንደሚቻል ለመገንዘብ ተቸግረው ነበር። የእነርሱ አምልኮ ያተኮረው በዓይን በሚታዩና በጣዖታት በተወከሉ አማልክት ላይ ነበር። በተጨማሪም እያንዳንዱ የሕይወት ክፍል ጣዖታዊ ጥበቃ ይደረግለት ዘንድ ብዙ አማልክትን ያመልኩ ነበር። ስለዚህ የዝናብ፥ የውኃ፥ የመሬት፥ የሰላምና የጦርነት ጣዖቶች ነበሯቸው። የልምላሜና የሌሎችም ጉዳዮች ጣዖቶች ነበሩዋቸው። ሰዎች ከእነዚህ ጣዖቶች ጋር የነበራቸው ግንኙነት በእርዳታና በበረከት ፍለጋ ላይ የተመሠረተ ነበር። ትኩረታቸው ጣዖታቱ እንዴት መመለክ አለባቸው በሚለው ሁኔታ ላይ አልነበረም።

የውይይት ጥያቄ፡– ይህ ለጣዖታት የነበረው ግምት፥ ክርስቲያኖች አንዱን እውነተኛ አምላክ ከሚመለከቱበት ሁኔታ ሊለይ የሚገባው እንዴት ነው? ለ) ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ስላደረገላቸው መልካም ነገርና ስለ አምላክነቱ ከማምለክ ይልቅ ራስ ወዳድ ሆነው እንዲባርካቸውና አንድ ነገር እንዲያደርግላቸው የሚፈልጉት እንዴት ነው?

በአሕዛብ አገሮች ሁሉ ብዙ ጣዖቶችና ቤተ መቅደሶች ነበሩ። በአቴና ሰዎች የማያውቁትን አምላክ ቅር እንዳያሰኙ በማሰብ፥ «ለማይታወቅ አምላክ» የሚል መሠዊያ ይሠሩ ነበር (የሐዋ.17፡23)። ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ግን፥ ብዙ ሰዎች በእነዚህ ጣዖቶች ላይ የነበራቸውን አመለካከት ቀይረው ነበር። ከሰዎች ብዙም በማይለዩት ደካማ ጣዖታት ላይ መደገፉ ሰልችቷቸው ነበር። የእነዚህም ጣዖታት ምግባረ ብልሹነት ሰልችቷቸው ነበር። ስለሆነም እውነትን መፈለግ ጀመሩ። በመጀመሪያ በአንዱ እውነተኛ ፈጣሪ አምላክ ላይ በሚያተኩረው የአይሁድ ሃይማኖት ትምህርት ተስበው ነበር። እነዚህ አሕዛብ ወደ ምኩራቦች ሄደው የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙና ለእውነተኛው አምላክ ይሰግዱ ነበር። አንዳንድ አሕዛብም ግዝረትን ተቀብለው ወደ ይሁዲነት ተለውጠዋል። ነገር ግን ወደ እውነተኛው አምላክ የተሳቡት አሕዛብ የአይሁዶችን ትዕቢትና እግዚአብሔርን ለማምለክ የአሕዛብን ባህል ሙሉ በሙሉ መተው አለባችሁ የሚለውን የአይሁድ ቃል እምብዛም ባይወዱትም፥ «እግዚአብሔርን የሚፈሩ» አሕዛብ ሆኑ (የሐዋ. 10፡1-2፤ 16፡14፤ 17፡4፥ 17)። እነዚህ አሕዛብ ግዝረትን ሳይቀበሉ እግዚአብሔርን ያመልኩና ይጸልዩ ነበር። እነዚህ እግዚአብሔርን የሚፈሩ አሕዛብ ለደኅንነቱ ወንጌል ዝግጁ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፥ ቆርኔሌዎስ በክርስቶስ በማመን ብቻ ሊድን እንደሚችል ሲሰማ፥ በፍጥነት አምኖ ድኗል (የሐዋ. 10፡24-44)።

በክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ችግር ካስከተሉት ነገሮች አንዱ፥ ነገሥታትን ማምለክ ነበር። እንደ ግብፅ ያሉ ጥንታዊ ሕዝቦችም ንጉሣቸው አምላክ እንደሆነ ያምኑ ነበር። ሮማውያንም ይህንን እምነት መከተል ጀመሩ። ከንጉሡ ሥልጣንና ሕዝቡ ለንጉሡ ያለውን ታማኝነት ከመፈለግ የተነሣ ቄሣር አምላክ ስለ ሆነ መመለክ አለበት የሚል አመለካከት ተንጸባረቀ። ይህ አመለካከት በተለይ በዶሚቲያን ዘመን ይበልጥ አይሎ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ በሮም ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ለንጉሡ እንዲሰግዱና፥ መሥዋዕትም እንዲያቀርቡ የሚደነግግ ሕግ ወጣ። ክርስቲያኖች ይህንን አናደርግም በማለታቸው ሮማውያን እንደ ዐመፅ ቆጠሩት። ለቄሣር መሥዋዕት አናቀርብም በማለታቸው ምክንያት የተከሰተው የመጀመሪያው ስደት የብዙ ክርስቲያኖችን ሕይወት ቀጠፈ። ለ200 ዓመታት ቄሣሮችን አናመልክም በማለታቸው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ተገደሉ።

ሌሎች ሃይማኖቶችም ነበሩ። ከጣዖት ጋር የተለየ ግንኙነት አለን የሚሉ ምሥጢራዊ የሆኑ ማኅበረሰቦች የሚያካሂዷቸው «ምሥጢራዊ ሃይማኖቶች» ነበሩ። በእነዚህ ምሥጢራዊ ማኅበረሰቦች የሚሰጡትን የአምልኮ ትምህርቶች የሚያውቁ ሰዎች ብቻ በረከትን እንደሚያገኙ ይታመን ነበር። ለጥንቆላም ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ ነበር። በምትሐት በመጠቀም፥ የእንስሳትን ሞራ በማንበብ ወይም ከዋክብትን በመቁጠር፥ እነዚህ ጠንቋዮች ከፍተኛ ኃይል አለን ብለው ይመኩ ነበር። ሰዎችን ለመርገምና ለመፈወስ እንደሚችሉ ይናገሩ ነበር። አንድ ሰው በሥራው ስኬታማ መሆን አለመሆኑን ይተነብዩ ነበር። መሪዎችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ጠንቋዩ እስካልነገራቸው ድረስ ምንም ነገር አይፈጽሙም ነበር። ይህ ከዋክብትን የመቁጠርና ሰዎች የተወለዱበት ዓመት በሕይወታቸው ላይ ተጽዕኖ ያደርሳል የሚለው እምነት፥ ዛሬም ትኩረት ተሰጥቶት ሰዎች በጋዜጦች ላይ ሲከታተሉት እንመለከታለን። (ለምሳሌ፥ በአዲስ አበባ በሚታተሙ አንዳንድ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ የሚወጣውን የኮከብ ቆጠራ ዐምድ እየተከታተሉ በሕይወታቸው ላይ ስለሚደርሰው ነገር ለማወቅ የሚጥሩ ሰዎች አሉ።)

ቤተ ክርስቲያን እያደገች ስትሄድ፥ ከእነዚህ ሃይማኖቶች ጋር ትጋፈጥ ጀመር። በተጨማሪም ክርስትናን ከተለያዩ ሃይማኖቶች ጋር የማቀያየጡን ፈተና ተቋቁማለች። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ክርስትናን እንደ ምሥጢራዊ የማኅበረሰብ እምነት ይመለከቱት ጀመር። የቅዱሳን ምስሎችን በማስተዋወቅ አምልኮተ ጦዖት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲገባ አድርገዋል። የክርስቶስም ስም በሚፈሩበት ጊዜ የሚናገሩት ወይም የሚይዙት ምትሐት ሆነ።

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) የጥንት ዘመን ሃይማኖቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ሃይማኖቶች ጋር የሚመሳለሉት ወይም የሚለያዩት እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች በክርስትና ላይ ሌሎች ነገሮችን በመጨመር እንዴት እንዳበላሹት ግለጽ።

በክርስቶስ ዘመን የነበሩት የዓለም ፍልስፍናዎች

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የነገሡትን ሦስት መንግሥታት ግለጽ። ለ) እያንዳንዱ መንግሥት የተመራበት መሠረታዊ ፍልስፍና ምን ነበር?

ለብዙዎቻችን «ፍልስፍና» የሚለው ቃል አስፈሪ ነው። ነገር ግን ፍልስፍና አንድ ሰው ስለሚጠቅመው ነገር ለማሰብ የሚረዳውና አቅጣጫ የሚያሲዘው ነው። ሰዎች ሁሉ ተግባራቸውን የሚመሩበት የየራሳቸው ፍልስፍና አላቸው፡፡ በግለሰብ ደረጃ ሰዎች የተለያዩ ተግባራትን (ሥራዎችን) ያካሂዳሉ። ይህም ሥራ ለሁሉም፥ ለተማሩት ወይም እግዚአብሔር ማንኛውንም ሥራ እንደሚያከብር ባላቸው አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነው። በብሔራዊ ደረጃ አገሮች መንግሥታቸውን ይበጀናል በሚሉት ፍልስፍና መሠረት ያዋቅራሉ። አንዳንዶች ሥልጣንና ኃይል ይወረሳል ብለው (እንደ ፊውዳሉ ሥርዐት) መንግሥታቸውን ያዋቅራሉ። ሌሎች ደግሞ ሰዎች ሁሉ ሀብታቸውን እኩል መካፈል አለባቸው ብለው (እንደ ኮሙኒስቱ ሥርዐት) መንግሥታቸውን ያዋቅራሉ። አንዳንዶች ሰዎች የመምረጥ መብት ስላላቸው ለእነርሱ የሚጠቅመውን ራሳቸው መምረጥ ይኖርባቸዋል ብለው (እንደ ካፒታሊስትና ዴሞክራቲክ ሥርዓት) መንግሥታቸውን ያዋቅራሉ። ክርስቲያኖች እንዲህ የሚል ፍልስፍና ሊኖራቸው ይገባል፡- «ለሰዎች ትልቁ ነገር እግዚአብሔርን ማክበርና በእርሱም ደስ መሰኘት ነው።»

በጥንቱ ዓለም ብዙ የተለያዩ ፍልስፍናዎች ነበሩ። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ፍልስፍናዎች የክርስቲያኖችን አስተምህሮዎች ይፈታተኑ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች የክርስቶስ ትምህርት የበለጠ ተቀባይነት እንዲኖረው በማሰብ፥ ክርስትናን ከእነዚህ ፍልስፍናዎች ጋር ለማስማማት ተፈትነው ነበር።

የጥንቱ ግሪክ ፈላስፋ ፕላቶ ሕይወት በሁለት ደረጃ እንደምትታወቅ እስተምሯል። በመጀመሪያ፥ እጅግ ጠቃሚ የሆነ የማይታይ የአሳቦች ዓለም አለ። ሁለተኛው፥ እንደ ጥላ ዓይነት የሚታይ ዓለም አለ። የሚታየው ነገር የማይታየውን ያህል ጠቃሚ አይደለም። ይህ አመለካከት ከሐዋርያት ዘመን በኋላ በቤተ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ይህ ፍልስፍና ክርስቲያኖች ምግብና ወሲብ የሚፈልገው አካላዊ ሰውነት ክፉ ነው ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ስለሆነም ክርስቲያኖች በዓለም ጠቃሚ ናቸው የተባሉትን ነገሮች ትተው በገዳም ውስጥ መኖር ጀመሩ። ላለማግባት ወስነው ስለ መልካም ነገሮች ብቻ ለማሰብ ይሞክሩ ነበር።

ቁሳዊ ነገሮች መጥፎ እንደሆኑና የማይታዩ ነገሮች መልካም እንደሆኑ ከሚያስረዳው ከዚህ ፍልስፍና ኖስቲሲዝም የተባለ ልዩ ፍልስፍና ፈለቀ። ይህ ፍልስፍና በአንዳንድ የአዲስ ኪዳን እሳቤዎችና በወንጌሎች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። አንዳንድ ሐዋርያት እንደ ቆላስይስና 1ኛ ዮሐንስ በመሳሰሉት መጻሕፍት ውስጥ ኖስቲሲዝምን ተቃውመው ጽፈዋል። ኖስቲኮች መንፈስና መልካም በሆነው አምላክ እና ክፉ በሆነው ሰውና ተፈጥሮ መካከል ትልቅ ገደል እንዳለ አስተምረዋል። ገደሉን ለመደልደል ብዙ ነገሮች ያስፈልጋሉ ይላሉ። ገደሉን የሚሞላ መንፈሳዊ አካል መኖር አለበት። የሰው መንፈስ ከቁሳዊው እስር ቤት እንዲያመልጥ የሚያደርግ ልዩ የእውቀት ቁልፍ ያስፈልጋል ይላሉ። አንዳንድ ክርስቲያኖች ይህን አሳብ በመውሰድ በቅዱሱ አምላክና በክፉዎች ሰዎች መካከል የነበረውን ክፍተት የሞላ መንፈስ የሆነው ኢየሱስ እንደሆነ አስተምረዋል። ስለ ክርስቶስ ያለን ልዩ እውቀት ደኅንነትን እንደሚያስገኝም ገልጸዋል። ኖስቲኮች እግዚአብሔር በጣም ቅዱስ ስለሆነ ቁሳዊ ነገሮችን ሊፈጥር አይችልም ይላሉ። የደኅንነት መንገድ የሆነው ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ሰው ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ሰው ከሆነ ቁሳዊ ነገር ተካፍሏልና ርኩስ ይሆናል በማለት አስተምረዋል። ስለሆነም ክርስቶስ ሰው አልሆነም ይላሉ። ነገር ግን መንፈስ መጥቶ በክርስቶስ ሰውነት ውስጥ እንደኖረና ከትንሣኤ በኋላ እንደተለየው ይናገራሉ። 1ኛ ዮሐንስ 1፡3፣ 4፡1-3 ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ ሰው እንደሆነና እንደ ተዳሰሰ፥ እንደ ታየና እንደ ደማ፥ እንደ ሞተና ከሞት እንደ ተነሣ በመግለጽ ለኖስቲኮች ትምህርት ምላሽ ይሰጣል። ክርስቶስ መንፈስ ብቻ አልነበረም።

ይህን ትምህርት የሚከተሉ ሰዎች በሁለት የተለያዩ መንገዶች መልስ ይሰጡ ነበር። አንዳንዶች ፍጹማዊው ሕይወት በተቻለ መጠን ከቁሳዊ ነገሮች ርቆ በምድረ በዳ ውስጥ መኖር አለበት ይላሉ። ይህም ሰዎች በገዳም ውስጥ ራስን የመጨቆን ሕይወት እንዲመሩ አድርጓቸዋል። ጳውሎስ በቆላስይስ 2፡16-23 ላይ ይህንን አመለካከት ነቅፎ ጽፎአል። ሁለተኛው ምላሽ፥ መንፈሳችን ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት እስካደረገ ድረስ፥ በአካላችን ላይ የሚደርሰው ነገር አሳሳቢ አይደለም ይላሉ። አንዳንድ ሰዎች በሥጋ የምናደርገው ነገር መንፈሳዊ ሕይወታችንን አይጎዳውም ይላሉ። ስለሆነም ሰዎች ከፍተኛ የዝሙት ኃጢአት ሲፈጽሙም እንኳ ችግር እንደማይኖር ያስረዳሉ። ሰይጣን ይህን ውሸት በመጠቀም ብዙ ተከታዮችን አፍርቷል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ ትምህርት ለእምነታችን አደገኛ የሚሆንባቸውን ሦስት ምክንያቶች ጥቀስ። ለ) የዚህን ትምህርት ክፍሎች በኢትዮጵያ ውስጥ የተመለከትነው እንዴት ነው?

በመጀመሪያው ምእተ ዓመት በስፋት ይታወቅ የነበረው ሌላው ፍልስፍና ኤፊቆሮሳውያን የሚባለው ነው። ይህ ፍልስፍና እንደ ዘገምተኛ ለውጥ ፍልስፍና ሁሉ ሕይወት የአጋጣሚ ውጤት እንደሆነችና በአተሞች ግጭት እንደ ተከሰተች ያስተምራል። ይህም መልካም ወይም ክፉ የሚባል ነገር እንደሌለ ያመለክታል። የሕይወት ዓላማ በሕይወት እስካሉ ድረስ መደሰት ብቻ ነው። ይህን አመለካከት ጠቅሶ ጳውሎስ ሲናገር ትንሣኤ ሙታን ከሌለ ከሞት በኋላ ምንም ተስፋ የለም፤ ስለዚህ ትርፉ መብላት፥ መጠጣትና መጋባት ብቻ ነው ብሎ ገልጾአል (1ኛ ቆሮ. 15፡32)። ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ ሙታን ሲያስተምር ያላገጡበት ኤፌቆሮሳውያን ናቸው (የሐዋ. 17፡18፥ 32)።

በመጀመሪያው ምእተ ዓመት በዋነኛነት የሚታወቀው ሌላው ፍልስፍና ስቶይሲዝም ነው። ስቶይኮች ዓለም ሩቅ በሆነው አምላክ እንደምትተዳደርና ሰዎች ሕይወታችውን ለመለወጥ ብዙም ተስፋ እንደሌላቸው ያመኑ ነበር። ስለዚህ ስሜታችንን ገዝተን የሚሆነውን መጠበቅ ይኖርብናል ይላሉ። የሰውን ስሜት የሚቀሰቅሱ እንደ ወሲብና ምግብ የመሳሰሉ ነገሮች መወገድ አለባቸው። ሰው በሚችለው ሁሉ ንጹሕ ሕይወት መኖር አለበት ይላሉ። ይህም ፍልስፍና ወንጌሉን ይቃረን ነበር። እግዚአብሔር የሩቅ ሳይሆን የቅርብ አምላክ ነው። እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም ልኳል። ከዚህም በተጨማሪ፥ እግዚአብሔር ለሰዎች እርሱን ለመታዘዝ ወይም አለመታዘዝ፤ ማክበር ወይም አለማክበር ምርጫ ሰጥቷቸዋል። ይሁንና፥ እግዚአብሔር ሰዎችን በምርጫቸውና በተግባራቸው በኃላፊነት ይጠይቃቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች፥ እነዚህን ሁለት ፍልስፍናዎች ቢከተሉ ኖሮ ክርስትናን እንዴት የሚጎዱ ይመስልሃል? ለ) ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙና ቤተ ክርስቲያን ልትዋጋቸው የሚገቡ ፍልስፍናዎች ምን ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

የሮም ግዛተ ዐፄና ክርስትና

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ወንጌልን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ እንዲስፋፋ የሚያደርገው ምንድን ነው? ለ) ወንጌል በኢትዮጵያ ውስጥ በፍጥነት እንዳይስፋፋ የሚያደርገው ምንድን ነው? ሐ) ኢትዮጵያውያን ወንጌልን ወደ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዳይወስዱ የሚከለክላቸው ምንድን ነው?

እግዚኣብሔር የሮም አገዛዝ እስኪመጣ ድረስ፥ ልጁን ወደዚህ ምድር ለመላክ ጊዜ ሲጠብቅ እንደ ነበር ቀደም ብለን ተመልክተናል። እግዚአብሔር ልጁን በፋርስ ወይም በግሪክ ዘመን መላክ ይችል ነበር፤ ዓለም ግን ዝግጁ አልነበረችም። በመጨረሻውም በሮማውያን ዘመን የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ለሆነው መሢሕ መምጣት ነገሮች ተስተካክለው ነበር። በሮም የአገዛዝ ዘመን ቤተ ክርስቲያን በሁለት ትውልድ ዘመን ውስጥ፥ ከሕንድ እስከ ሰሜን አፍሪካና ከዚያም እስከ ታላቋ ብሪታኒያ ድረስ ለመስፋፋት ችላለች። ለመሆኑ እግዚአብሔር ይህንን ጊዜ ሲጠብቅ የነበረው ለምንድን ነው? 

1. ፖለቲካዊ መረጋጋት፡- በደርግ ጨቋኝ አገዛዝ ወቅት ወንጌልን ማሰራጨት ከባድ እንደነበረ ሁሉ፥ በአንዲት አገር ውስጥም ሆነ በአገሮች መካከል ፖለቲካዊ መረጋጋት ከሌለ ወንጌልን ለማስፋፋት አስቸጋሪ ነው። በመካከለኛው ምሥራቅና በምዕራቡ ዓለም ታሪክ፥ የሮምን ኣገዛዝ ያህል የተረጋጋና ለረዥም ጊዜ የቆየ መንግሥት የለም። ክርስትና በተስፋፋባቸው አገሮች ሁሉ የሮም መንግሥት ከ1000 ዓመት በላይ ኃያል ሆኖ ሲገዛ ቆይቷል። ከሕንድ ጀምሮ እስከ እስፓኝ፥ ከዚያም እስከ ታላቋ ብሪታኒያና ሰሜን ኣፍሪካ ድረስ፥ አንድ መንግሥት ብቻ ነበር። ይህም እንደ ጳውሎስ ያሉ አገልጋዮች የቪዛ፥ ፓስፖርት፥ ወይም ሌሎች የመንግሥት ደንቦች ሳያግዷቸው በቀላሉ እንዲንቀሳቀሱ ረድቷቸዋል። ምንም እንኳ በሮም መንግሥት ውስጥ ተተኪው ንጉሥ ማን ይሆን? በሚለው ጥያቄ ላይ ብርቱ ፍጭት ቢኖርም፥ በጥቅሉ ሲታይ ግን፥ በሮም ግዛት ሁሉ አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ ነበር።

2. ባህላዊ ተመሳሳይነት፤ ከ300 ዓመት በላይ የግሪክ ባህል በኦውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ ተስፋፍቶ ቆይቷል። ግሪኮች ጎይልን ሳይጠቀሙ ሰዎች የግሪክን ቋንቋ እንዲናገሩ፥ በከተሞች ውስጥ እንዲኖሩ አበረታተዋቸዋል። ሮማውያን ሥልጣን ሲይዙ የራሳቸውን ባህልና ቋንቋ በሕዝቡ ላይ ከመጫን ይልቅ፥ የግሪክን ባህልና ቋንቋ መቀጠሉ እንደሚቀል ተገነዘቡ። በአሁኑ ጊዜ የምዕራቡ ዓለም ባህላዊ እሴቶች በትምህርትና በመገናኛ ብዙኀን አማካይነት ሰዎችን አንድ እያደረጉ ከመሆኑ በስተቀር፥ በታሪክ ውስጥ የባህል ተመሳሳይነት ጎልቶ የታየበት እንደዚህ ያለ ዘመን አልነበረም። ብዙ ባህላዊ ልዩነቶች (ለምሳሌ፡- አማራና አፋር፥ ወላይታና ገለብ) በሚታዩበት ጊዜ ወንጌልን ማሰራጨት አስቸጋሪ ስለሆነ፥ ይህ የባህል ተመሳሳይነት ወንጌል በቀላሉ በሮም ግዛት ውስጥ እንዲሰራጭ የበኩሉን እገዛ አድርጓል።

3. ቋንቋ፡- ለወንጌል መስፋፋት ከፍተኛ መሰናክል ከሚሆኑ ነገሮች አንዱ የቋንቋ ልዩነት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ወንጌላውያን ከእንዱ ስፍራ ወደ ሌላው በሚሄዱበት ጊዜ፥ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በቋንቋ ለመግባባት ይቸገራሉ። በኣስተርጓሚ ለመጠቀም ቢፈልጉ እንኳ አንዳንዴ የእሳብ መዛባትን የሚያስከትል ይሆንባቸዋል። ወይም ረዥም ጊዜ ወስደው ቋንቋውን ይማራሉ። ነገር ግን በክርስቶስና በደቀ መዛሙርቱ ዘመን፥ በሮም ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ አንድ ቋንቋ ይናገሩ ነበር። ስለሆነም ሐዋርያትና ወንጌላውያኑ በሚሄዱበት ስፍራ ሁሉ ከሰዎች ጋር በግሪክ ቋንቋ ይግባቡ ነበር።

4. የአዲስ ኪዳን ጽሑፎች፡- ሳይንቲስቶች እንደሚናገሩት ሰዎች ከሚሰሙት ነገር ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነውን በፍጥነት ይዘነጋሉ። ብዙውን ጊዜ በቃል ከኣንዱ ሰው ወደ ሌላው ሰው የሚተላለፉ መልእክቶች፥ ስሕተት የማይጠፋባቸው ለዚህ ነው። እግዚአብሔርም ይህንን በመገንዘብ፥ ሰዎች የማይለወጥና ዘላለማዊ ቃል ይዘው የሚቆዩበትን መንገድ አዘጋጀ። ሐዋርያት በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ የቅዱሳት መጻሕፍት አስፈላጊነት እየጨመረ ሄደ። ነገር ግን በምን ቋንቋ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይጻፉ? የሮም የሥራ ቋንቋ የነበረውንና ምሁራን የሚጠቀሙበትን ላቲን ይምረጡ? የጳለስቲና ነዋሪዎች ቋንቋ የነበረውን ሐዋርያቱ አፋቸውን የፈቱበትን የአረማይስጥ ቋንቋ ይምረጡ? ይህን ሊያደርጉ አይችሉም። ዋናው ነገር የቋንቋው ክብር አይደለም። እግዚአብሔር የሮም መንግሥት ዓለምን በግሪክ ቋንቋ አማካይነት አንድ እንዲያደርግ በመርዳት፥ አዲስ ኪዳን በግሪክ ቋንቋ የሚጻፍበትን ሁኔታ አመቻቸ። ይህም በሮም ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎም ጊዜ ሳያባክኑ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያነቡ አስችሏቸዋል።

5. ትምህርት፡- ቤተ ክርስቲያን እንድትጠነክር ከተፈለገ ምእመናን በየእሑዱ የሚቀርበውን ስብከት መስማት ብቻ ሳይሆን፥ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብ አለባቸው። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚነጋገርበት እጅግ አስፈላጊው መንገድ ቃሉ ነው። ነገር ግን ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብ ይችሉ ዘንድ ከመሃይምነት መላቀቅ አለባቸው። በታሪክ ውስጥ እንደታየው ማንበብ የሚችሉት ሀብታሞች ብቻ ነበሩ። ተራው ሰው ማንበብ አይችልም ነበር። በአዲስ ኪዳን ዘመን ግን ግሪኮች ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ ስለነበር፥ ብዙ ሰዎች ማንበብ ይችሉ ነበር። ከዝቅተኛ መደብ የመጡ ቢሆኑም እንኳ፥ አብዛኞቹ የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ምእመናን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይችሉ ነበር። ቤተ ክርስቲያን ማንበብ በሚችሉ ጥቂት ሰዎች ላይ ብቻ መደገፍ አላስፈለጋትም። ቤተ ክርስቲያን አምልኮዋን የምታካሂደው በግለሰብ ቤቶች በመሆኑ፥ ለእያንዳንዲ ቤተ ክርስቲያን ማንበብ የሚችሉ ሰዎች ይመደቡ ነበር። ይህም የክርስቶስን ትምህርቶች ይበልጥ እንዲረዱ አድርጓቸዋል።

6. ጉዞ፡- የፋርስ፥ የግሪክና የሮም መንግሥታት ዐቢይ ከተሞችን የሚያገናኙ መንገዶችን በመሥራት ረገድ እኩል አስተዋጽኦ አድርገዋል። በሮማውያን አገዛዝ ዘመን ሰዎች በመንገዶችና በመርከብ በመጠቀም ወደ ፈለጉበት አገር መሄድ ይችሉ ነበር። ይህ እንደ ጳውሎስ ላሉ ሰዎችና ወንጌልን በየስፍራው ለሚሰብኩ ልዑካን በጣም ጠቃሚ ነበር።

7. ከተሞች፡- ግሪኮች፥ ከተሞች የትምህርትና የሥልጣኔ ምንጭ ናቸው ብለው ያምኑ ነበር። መላው ሕዝባቸው እንደ አዲስ አበባ ባሉ የከተማ ግዛቶች የሚተዳደር ሲሆን፥ የራሱ አስተዳደራዊ አውራጃ ሆኖ ያገለግል ነበር። ሮማውያንም ክልላዊ ሥልጣን በመስጠት የነዚህን ከተሞች ዕድገት አግዘዋል። ምሑራን በአዲስ ኪዳን ዘመን አብዛኛው ሕዝብ በከተሞች ውስጥ ይኖር እንደነበር ያምናሉ። ይህም ወንጌላውያን በታላላቅ ከተሞች ውስጥ ወንጌልን ለመስበክ ዕድል በማግኘታቸው፥ ለወንጌል መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ሰዎች በትምህርት ቤቶች ወይም በገበያ ቦታዎች እየተገናኙ ስለሚነጋገሩ፥ ወደ ከተሞች የመጣ አዲስ ዜና በቀላሉ እንደሚሰራጭ ግልጽ ነው። የገጠር ሰዎችም ወደ ከተማ ለገበያ በሚወጡበት ጊዜ ዜናውን ይዘው ይመለሳሉ። ቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያው ምእተ ዓመት በከፍተኛ ፍጥነት እንድታድግ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ይሄ ነበር። –

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ሰባት ነገሮች የወንጌልን ስርጭት እንዴት እንደሚያግዙ አብራራ። ለ) የዛሬውን ዓለም ከክርስቶስ ዘመን ጋር በማነጻጸር ልዩነቱንና ተመሳሳይነቱን እስረዳ። ሐ) ዛሬ ወንጌል ለማሰራጨት ከዚያን ዘመን ይልቅ ይቀላል ወይስ ይከብዳል? አሳብህን አብራራ።

ከእግዚአብሔር ሉዓላዊ ዕቅድና ለሕዝቦች ካለው ፈቃድ የተነሣ፥ ክርስትና በሮም አገዛዝ ተወልዶ በፍጥነት አደገ። በመጀመሪያው ምእተ ዓመትና፥ በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምም ከፈረሰች በኋላ የሮም መንግሥት ለአይሁድ ሃይማኖት ትልቅ ግምት ሰጥቶ ነበር። የአይሁድ ሃይማኖት ሕጋዊ በመሆኑ፥ በተከታዮቹ ላይ ስደት አይደርስም ነበር። ከዚህም በተጨማሪ፥ ሮማውያን በሌሎች ሕዝቦች ላይ የሚጭኗቸውን የኣሕዛብ ሃይማኖታዊ ትምህርት በአይሁዶች ላይ ተግባራዊ እንዲሆኑ አይፈቅዱም ነበር። ክርስትናም የይሁዲነት አካል ተደርጎ በመወሰዱ፥ ከሮማውያን ይፋዊ ስደት ለመትረፍ በቅቷል።

በበዓለ ኀምሳ ዕለት ቤተ ክርስቲያን በኢየሩሳሌም ከተማ ተጀመረች (የሐዋ. 2)። በመጀመሪያዎቹ 20 ወይም ከዚያ በላይ ዓመታት፥ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አባላት ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል፥ አይሁዶች ነበሩ። የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ክርስትና ከተለመደው የአይሁዳውያን እምነት የተለየ መሆኑን ተረድተው ነበር። ስለዚህ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የጥንት ክርስቲያኖችን እንቅስቃሴ ለማገድና እነርሱንም ለማሳደድ ይጥሩ ነበር። በመጀመሪያዎቹ 40 የከርስትና ዓመታት ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ዋነኛ አሳዳጆች አይሁዶች ነበሩ። ነገር ግን ብዙ አይሁዶች ክርስትናን እንደ አዲስ ሃይማኖት ስላላዩት አንዳንዶች ነገሩን ለመቀበል ፍላጎት ሲያድርባቸው፥ ሌሎች ደግሞ ነገሩን ታግሠው በአክብሮት ይመለከቱት ነበር።

እንደ ሮማውያን ያሉ የውጭ ሰዎች በክርስትናና በይሁዲነት መካከል የጎላ ልዩነት ስላልታያቸው፥ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ አልሞከሩም። ሮማውያን ክርስትና ከይሁዲነት የተለየ መሆኑን ተረድተው ማሳደድ የጀመሩት፥ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተች ከሠላሳ ዓመት በኋላ ነበር። በመጀመሪያው ምእተ ዓመት መጨረሻ አካባቢ፥ ሮማውያን በክርስትና ላይ መደበኛ ስደት በመቀስቀለ ክርስትና ሕገ ወጥ ሃይማኖት መሆኑን አወጁ።

በመጀመሪያ በክርስቲያኖችና በሮም ባለሥልጣናት መካከል የነበረው ግንኙነት የጠበቀ አልነበረም። ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ አውግስጦስ ቄሣር (30 ዓ.ዓ. -14 ዓ.ም.) አገረ ገዥ ነበር (ሉቃስ 2፡1)። ክርስቶስ አገልግሎቱን በጳለስቲና ሲጀምር ደግሞ፥ ጢባርዮስ ቄሣር (14-37 ዓ.ም.) አገር ገዥ ሆኖ ይሠራ ነበር (ሉቃስ 3፡1)። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዘመን ይገዛ የነበረውና የንጉሦችን አምልኮ የጀመረው ጋይዮስ ካሊጉላ ነበር (37-41 ዓ.ም.)። ካሊጉላ በቤተ መቅደሱ ውስጥ እርሱ የሚመለክበት መሠዊያ እንዲታነጽ ሲያደርግ፥ ክርስቲያኖች ማዘናቸው አልቀረም ነበር። በንጉሥ ቀላውዴዎስ ዘመን (41-54 ዓ.ም) በሮም በሚኖሩ ክርስቲያን ባልሆኑ አይሁዶችና ክርስቲያን በሆኑ አይሁዶች መካከል ብጥብጥ የተከሰተ ይመስላል። ይህም ቀላውዴዎስን ስላስቆጣው፥ አይሁዶችን ከሮም አባረራቸው። አቂላና ጵርስቅላ ወደ ቆሮንቶስ የሄዱት በዚህ ጊዜ ነበር (የሐዋ. 18፡2)።

ክርስቲያኖች ከአይሁዶች ይበልጥ እየተለዩ ሲመጡ፥ ብርቱ ስደት ይደርስባቸው ጀመር። በኔሮ ዘመን (54-68 ዓ.ም) ነገሮች ይበልጥ እየከፉ መጡ። ኔሮ በሮም ትልቅ ቤተ መንግሥት ለማሠራት ይፈልጋል የሚል ወሬ ተሰማ። ስለዚህ በተወሰነው የከተማይቱ ክፍል ላይ እሳት ለቀቀበት። እሳቱ ከቁጥጥር ውጭ በመውጣቱ ከሮም ከተማ ብዙው ክፍል ወደመ። ሕዝቡ በቁጣ ይነሣብኛል ብሎ የፈራው ኔሮ፥ አደጋውን ብዙም ከማይታወቁ ክርስቲያኖች ጋር አያያዘው። ብዙ ክርስቲያኖች ታድነው እንዲገደሉ አደረገ። ይህ ስደት በግዛቱ ሁሉ የተከሰተ ሳይሆን፥ በሮም ከተማ ብቻ የተደረገ ነበር።

በተከታዮቹ ሠላሳ ዓመታት ውስጥ ስለ ክርስቲያኖች አኗኗር ሁኔታ የምናውቀው ምንም ነገር የለም። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መሪዎች ካደረሱት ስደት በቀር የሚነግረን ሌላ መረጃ የለም። ይህ ግን ዶሚቲያን (81-96 ዓ.ም.) የንጉሥ ነገሥትነቱን ሥልጣን ሲረከብ ተለውጧል። ዶሚቲያን የሮምን ሃይማኖት ለማስፋፋት ዕቅድ ስለ ነበረው፥ እያረጁ የሄዱትን ቤተ መቅደሶች ማደስ ጀመረ። ከዚያም ሕጋዊ ባልሆኑ ሃይማኖቶች ላይ ጫና አሳደረ። በሮም ንጉሥና በክርስቲያኖች መካከል ችግር የተነሣው ሰዎች እርሱን እንደ አምላክ ቆጥረው መሥዋዕት እንዲያቀርቡለት ባዘዘ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ይህ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ሰዎች በፈቃደኛነት የሚያከናውኑት የነበረ ተግባር ነበር። ክርስቲያኖች ይህን አናደርግም በማለታቸው ምክንያት፥ የተቀሰቀሰው ስደት ምን ያህል እንደተስፋፋ ኣናውቅም። የምናውቀው ነገር ቢኖር በዚህ ጊዜ ሐዋርያው ዮሐንስ በስደት ወደ ፍጥሞ ደሴት እንደተላከ ብቻ ነው (ራእይ 1፡9)። ነገሥታትን ማምለክ የተለመደ በሆነባት በትንሿ እስያ ስደቱ ሳያይል አልቀረም። ብዙ ምሑራን ዮሐንስ በራእዩ ውስጥ ክርስቲያኖችን ስለ መጭው ስደት እያስጠነቀቃቸው እንደነበረ ያምናሉ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

የሮም ግዛተ ዐፄና የሄሮድስ አገዛዝ

ኢየሱስ በጳለስቲና በተወለደበት ወቅት በተለያዩ ቡድኖች መካከል ፖለቲካዊ ትግልና ሽኩቻ ነበር። ለሥልጣን ሲባል በቤተ ሰብ አባላት መካከል እንኳ እርስ በርስ መገዳደል ይፈጸም ነበር። ይህ ሁሉ ትግል በተራው ኅብረተሰቡ ላይ የሚያስከትለው የኑሮ ጫና ቀላል አልነበረም። የተለያዩ ቡድኖች በሥልጣን ላይ ካሉትና ከሮማውያን ጋር ለሚያካሂዱት ትግል የተራውን ሕዝብ ድጋፍ ይፈልጉ ነበር። ግብር እየጨመረ ሲሄድ፥ የኑሮ ውድነቱም እንደዚያው ይከፋ ጀመር። ሰላምና መረጋጋት ታጣ። ከአሕዛብም አገዛዝ ነፃ ለመውጣት አልተቻለም።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቶስ የኖረበት ዘመን ከእኛ ዘመን ጋር የሚመሳሰለው ወይም የሚለያየው እንዴት ነው?

«ንጉሣችን የታለ? ነፃ አውጪያችን የት አለ? መሢሑስ?» የሚሉ ጥያቄዎች ለ400 ዓመታት ያህል ሲነሡ ቆይተዋል። አይሁዶች በመቃብያን አማካኝነት ለአጭር ጊዜ ነጻነታቸውን ካገኙና መልሰውም ከተነጠቁ በኋላ፥ ከፍተኛ የነጻነት ጥማት አደረባቸው። በኢየሩሳሌም ከተማ የተለያዩ ቡድኖችና መሪዎች የሚያካሂዷቸው ትግሎች፥ እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ የፍትሕና ቅድስና አለመኖር የሕዝቡን ሕይወት ለምሬት ዳረገው።

እርስ በርሳቸው፥ «እግዚኣብሔር ተስፋ የሰጠን የሰላምና የጽድቅ አገዛዝ የታለ?» እያሉ ይጠያየቁ ነበር። ሕዝቡ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሚፈልጉት ከፖለቲካዊ መሢሕ ነበር። ነገር ግን የነገሥታት ንጉሥ በመካከላቸው ተገኝቶ የውስጥ ሰላምና ጽድቅ ያለበትን መንፈሳዊ መንግሥት በሰበከላቸው ጊዜ ሊቀበሉ አልፈለጉም። ሕዝቡ የሚፈልጉትን ፖለቲካዊ መልስ ሊሰጣቸው ስላልቻለ መሢሑን አንቀበልህም አሉት።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ የምንጠብቃቸውን መልሶች ባለመስጠቱ ምክንያት ለችግሮቻችን የሚያቀርባቸውን መፍትሔዎች የምንቀበለው እንዴት ነው?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ማቴ. 2፡7-18 አንብብ። ስለ ሄሮድስ ባሕርይ የቀረበው ገለጻ ምንድን ነው? ) ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ስለ ሄሮድስ እንብብና ስለ ሕይወቱና አገዛዙ አጭር ነገር ጻፍ።

ታላቁ ሄሮድስ (37-4 ዓ.ዓ.)

ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ሄሮድስ ክፉ ሰው እንደነበረ ቢገልጽም፥ የዓለም ታሪክ ከይሁዳ ታላላቅ መሪዎች እንደ አንዱ ይዘክረዋል። ሄሮድስ በአንድ ወቅት ንጉሥ ዳዊትና ሰሎሞን የያዙትን የጳለስቲና ግዛት በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ የቻለ ንጉሥ ነበር። ሄሮድስ በአገሪቱ ሁሉ አምባዎችን የገነባ ታላቅ ወታደራዊ መሪ ነበር። ይህ ሰው ራሱን ችሎ እንደሚገዛ ንጉሥ ይሁዳን እያስተዳደረ ከሮም ጋር ሰላማዊ ግንኙነቶችን ለመመሥረት የቻለ ብልህ ፖለቲካዊ መሪ ነበር፡፡ ሄሮድስ በይሁዳ ብቻ ሳይሆን፥ በሌሎች የዓለም ክፍሎችም በገነባቸው ሕንፃዎች፥ በጥንቱ ዓለም ውስጥ የታወቀ ሰው ነው። ከታላላቅ ሥራዎቹ መካከል አሻሽሎ ያሠራው የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ኣንዱ ነው። በ19 ዓ.ዓ የተጀመረው ይህ ሥራ እስከ 63 ዓ.ም ድረስ ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቀም ነበር። የኢየሩሳሌሙ ቤተ መቅደስ በጥንቱ ዘመን ከሚገኙ ሕንፃዎች መካከል እጅግ ውብ ሕንፃ ነበር። ስለሆነም ሕዝቡ፥ ንጉሥ ሄሮድስን እንደ ታላቅ መሪ ይመለከቱት ነበር።

ይህም ሆኖ፥ አይሁዶች ስለ ሄሮድስ ፍጹም የተለየ አመለካከት ነበራቸው። አንደኛው፥ ሄሮድስ ንጹሕ አይሁዳዊ ሳይሆን፥ ከፊል ኢዱሚያዊ (የአይሁዶች የረዥም ጊዜ ጠላት ከነበሩት ኤዶማውያን ትውልድ) እና ከፊል አይሁዳዊ መሆኑ ነበር። ስለሆነም፥ በጳለስቲና የሚኖሩ አይሁዶች ሙሉ በሙሉ አልተቀበሉትም ነበር። ሁለተኛው፥ ከዳዊትም ሆነ ከሃስሞኒያን የዘር ሐረግ ባለመምጣቱ፥ ሕጋዊ ገዥ ነው ብለው አያምኑም ነበር። እንዲያውም ሄሮድስ በሥልጣን ወንበር ላይ የተቀመጠው የሃስሞኒያኖችን ዘሮች በመጨረሱ ነበር። ሦስተኛው፥ የሮማውያን ወዳጅ ነበር። አይሁዶች ሙሉ ነጻነታቸውን ይፈልጉ ስለ ነበር፥ በአገራቸው ላይ የሚደርሰውን የአሕዛብ ተጽዕኖ አጥብቀው ይጠሉ ነበር። ምንም እንኳ ሄሮድስ የአይሁድ ሃይማኖት ተከታይ ቢሆንም፥ ሮማውያንን ይደግፍና ለፖለቲካው አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የአሕዛብ ጣዖትን ለማምለክ ፈቃደኛ ነበር።

ከፍተኛ የአስተዳደር ችሎታ ቢኖረውም፥ ሄሮድስ አንድ ሰው እርሱን ገድሎ ዙፋኑን እንዳይወስድበት ይሰጋ ነበር። ምክንያቱም በሃስሞኒያኖች ታሪክ ብዙውን ጊዜ ወንድም ወንድሙን ገልብጦና ገድሎ ስፍራውን ይወስድ ነበር። ሄሮድስ ይህ አደጋ በእርሱ ላይ እንዳይደርስ ፈራ። አጥብቆ ይፈራ የነበረው ደግሞ ቤተሰቡን ነበር። ስለሆነም ያሤሩብኛል ብሎ በመፍራቱ አጎቱን፥ ሚስቱንና ብዙ ልጆቹን አስገድሏል።

የክርስቶስ ታሪክ የሚጀምረው ከሄሮድስ የአገዛዝ ዘመን ነው። ክርስቶስ ወደ ምድር በመጣበት የመጀመሪያ ዓመት፥ ሄሮድስ ንጉሥ ነበር። እውነተኛ የአይሁድ ንጉሥ በቤተልሔም እንደተወለደ ሲነገር የሰጠው ምላሽ ሄሮድስ አንድ ሰው እርሱን ገድሎ ፖለቲካዊ ሥልጣኑን እንዳይወስድሰት መስጋቱን ያሳያል። ሄሮድስ ክርስቶስ መሢሕ ነው ብሎ ባያምንም፥ ማንም ሰው የኢየሩሳሌሙን ዙፋን እንዳይቀናቀንበት ፈራ።

ሰብአ ሰገል ከኢየሩሳሌም ወጣ ብላ በምትገኘው አነስተኛ የቤተልሔም ከተማ የአይሁድ ንጉሥ እንደ ተወለደ በነገሩት ጊዜ፥ ንጉሥ ሄሮድስ በከተማይቱ ውስጥ በቅርብ ጊዜ የተወለዱትን ወንድ ልጆች በሙሉ አስገደለ። እግዚአብሔር ግን ሄሮድስ ሕፃኑን ክርስቶስን እንዳያገኘው ከዮሴፍና ከማርያም ጋር ወደ ግብፅ አገር ላከው። ሄሮድስ ከ30 ዓመት በላይ ከገዛ በኋላ ክርስቶስ እንደ ተወለደ ብዙም ሳይቆይ ሞተ።

ይህም ክርስቶስ ከ6-4 ባለው ዓ.ዓ መካከል እንደተወለደ ይጠቁማል። ምሁራን ክርስቶስ የተወለደበትን ትክክለኛ ዓመት ባያውቁም፥ ሄሮድስ በሞተበት ከ4 ዓ.ዓ. በፊት መሆኑ ይገመታል። የዓለም የቀን መቁጠሪያ በሁለት ዐበይት የዘመናት ቀመር ተከፍሏል። አንደኛው ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው ዘመን ሲሆን ዓ.ዓ. (ዓመተ ዓለም) ሲባል፥ ሁለተኛው ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለው ዘመን ዓ.ም. (ዓመተ ምሕረት) ተብሎ ይታወቃል። ዓመተ ምሕረት ክርስቶስ ለተወለደበት የዘመን ቀመር የተሰጠ መጠሪያ ነው። ይህ ዘመናዊ የቀን መቁጠሪያ በክርስቶስ መምጣት ምክንያት በዓለም ታሪክ ዘንድ ፍጹም ኣዲስ ምዕራፍ እንደ ተጀመረ የሚያበሥርና የክርስቲያኖችን እምነት የሚያንጸባርቅ ነው።

እንግዲህ በቀን መቁጠሪያችንና በትክክል በተፈጸመው ነገር መካከል ልዩነት የሚታየው ለምንድን ነው? በኢትዮጵያና በአውሮፓ የቀን መቁጠሪያ መካከል ልዩነት የሚታየው ለምንድ ነው? ምንም እንኳ ምክንያቶቹን በሙሉ ባናውቅም፥ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚሰጠን መልስ አለ። ይህም ከክርስቶስ ሞት በኋላ ለ500 ዓመታት ያህል እያንዳንዱ አገር የየራሱ የቀን መቁጠሪያ ነበረው። አይሁዶች ዓለም የተፈጠረችበት ዘመን እንደሆነ ከሚያምኑበት ጊዜ የሚነሣ የቀን መቁጠሪያ ነበራቸው። የሮማውያን የቀን መቁጠሪያ ደግሞ የሮም ከተማ ከተመሠረተችበት ጊዜ የሚጀምር ነበር። ግሪኮች፥ ቻይናውያንና ሌሎችም አገሮች ከተለያዩ አጋጣሚዎች የሚነሡ የቀን መቁጠሪያዎች ነበሯቸው።

በመካከለኛው ዘመን ግን ክርስትና እየተስፋፋና ታላቅ እምነት እየሆነ ሲሄድ፥ ከክርስቶስ ልደት የሚጀምር የቀን መቁጠሪያ መጠቀሙ አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ። ይህ ሲሆን፥ ብዙ ዘመን አልፎ ነበር። በ525 ዓ.ም አንድ ካህን ኢየሱስ የተወለደበትን ዘመን ለመወሰን ፈልጎ ታሪክን መከለስ ጀመረ። ስለሆነም ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበሩትን ዓመታት “ክርስቶስ በፊት”፥ ከዚያ በኋላ ያሉትን ደግሞ “የምሕረት ዘመን” ብለው ለመጥራት ወሰኑ። አብዛኞቹ ምሑራን ክርስቶስ ከ4-6 ዓ.ዓ ባለው ጊዜ እንደተወለደ ያምናሉ።

በምዕራባውያንና በኢትዮጵያ የቀን መቁጠሪያ መካከል የ7(8) ዓመት ልዩነት የሚታየውስ ለምንድን ነው? ለዚህ ምክንያቱን መናገር አስቸጋሪ ቢሆንም፥ ሁለት አማራጭ መልሶች አሉ። አንደኛው፥ የኢትዮጵያ የቀን መቁጠሪያ የፀሐይን ሳይሆን የጨረቃን ዑደት ይከተል እንደ ነበር የሚያመለክቱ ጽሑፎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሉ። የጨረቃ ዑደት ከፀሐይ ስለሚያጥር፥ ይህን የጊዜ ለውጥ ሊያስከትል ይችላል። ሁለተኛው፥ ከጁሊያን ወደ ግሪጎሪያን የቀን መቁጠሪያ በተደረገው ለውጥ የተከሰተ ለውጥ አለ። ከ46 እስከ 1582 ዓ.ም. ድረስ በሮም ግዛት ውስጥ የሚኖሩ «የጁሊያን ቀን መቁጠሪያ» በመባል የሚታወቀውን የጊዜ መቁጠሪያ ይከተሉ ነበር። ይህ የቀን መቁጠሪያ የፀሐይን ዑደት የሚከተልና አንድን ዓመት ለ365 1/4ኛ ቀናት የሚከፍል ነበር። ይህም በየአራት ዓመቱ 366 ቀናት እንደሚኖሩ ያመለክት ነበር። ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የምንከተለው የቀን መቁጠሪያ ይሄ ነው።

ነገር ግን ጳጳስ ግሪጎሪ በ82 ዓ.ም አብዛኞቹ የክርስቲያኖች በዓላት በትክክለኛው ቀን አይከበሩም በማለት የተሰማቸውን ኀዘን አስታወቁ። የፀሐይ ዓመት ከጁሊያን ዓመት 11 ደቂቃ ከ14 ሰኮንዶች ስለሚረዝም፥ ቀስ በቀስ የጁሊያን ቀን መቁጠሪያ ወደኋላ በመቅረት ላይ ነበር። ስለሆነም ከቀን መቁጠሪያው ላይ 10 ቀናትን አነሡ። በ1752 ዓ.ም ደግሞ ተጨማሪ ማሻሻያ ተደርጎ በምዕራቡ ዓለም የቀን መቁጠሪያ ላይ 11 ቀናት ተጨመሩ።

ከግሪክ ኦርቶዶክስ ጋር የሚዛመዱ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በጁሊያን የቀን መቁጠሪያ ላይ ምንም ማስተካከያ ሳያደርጉ በመገልገል ላይ ይገኛሉ።

እንግዲህ የክርስቶስን የልደት ዘመን በመገመቱ ረገድ ትክክለኛው ማን ነው? ምሑራን ሁለቱም የቀን መቁጠሪያዎች ትክክል እንዳልሆኑ ያስባሉ። የምራባውያኑ የቀን መቁጠሪያ አራት ወይም አምስት ዓመቶችን እንደሚያጎድልና፥ የኢትዮጵያ የቀን መቁጠሪያ ደግሞ ሁለት ወይም ሦስት ዓመቶችን እንደሚያጎድል ይገምታሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ የሄሮድስን ልጆች «ሄሮድስ» እያለ ስለሚጠራ ስለየትኛው ሄሮድስ እንደሚናገር በጥንቃቄ ማስተዋል ይኖርብናል። ከማቴዎስ ምዕራፍ 2 በስተቀር፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «ሄሮድስ» የሚለው ስም የመጀመሪያውን ንጉሥ ትውልዶች የሚያሳይ ነው።

ታላቁ ሄሮድስ ለ30 ዓመት ያህል የተረጋጋ መንግሥት ሲያስተዳድር ቆይቶ ሲሞት፥ ሮም ይሁዳን እስከ ተቆጣጠረችበት ጊዜ ድረስ አለመረጋጋት ሰፈነ። ሄሮድስ መንግሥቱን ለሦስት ቦታ ከፋፍሎ ለአርኬላዎስ፥ ለሄሮድስ አንቲጳስና ለሄሮድስ ፊልጶስ ሰጠ። ዋናው ግን ሮም መንግሥቱን ማን እንዲያስተዳድር የመወሰኗ ጉዳይ ነበር። ስለሆነም፥ የሄሮድስ መንግሥት ሕጋዊ ወራሾች ሆነው ለመሾም እያንዳንዳቸው የሄሮድስ ትውልዶች ወደ ሮም ተጓዙ። አይሁዶችም ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው አርኬላዎስ በግዛታቸው እንዳይነግሥ የሮም ባለሥልጣናትን ጠየቁ። የሮም መንግሥት ግን አርኬላዎስ ይሁዳንና ሰማርያን፥ አንቲጳስ ገሊላንና ጳራያን፣ ፊልጶስ ደግሞ የገሊላን ባሕር ሰሜን – ምዕራባዊ አካባቢዎች እንዲያስተዳድሩ ወሰነ። የሮም መንግሥት ለማናቸውም የንግሥና ሥልጣን ሳይሰጥ እነዚህን አካባቢዎች እንዲያስተዳድሩ ሾማቸው። የሄሮድስ ዋንኛ ወራሽ የሆነው አርኬላዎስ ከሁለቱ የበለጠ ሹመት ነበር የተሰጠው። ሮማውያን ይህንን ያደረጉት ለአሠራራቸው የሚያመች ሰው ሆኖ ከተገኘ ንጉሥ አድርጎ ለመሰየምና ከዚህ በፊት አባቱ ይገዛው የነበረውን ግዛት ሁሉ ለመስጠት አስበው ነበር።

የአርኬላዎስ አገዛዝ (4 ዓ.ዓ. – 6 ዓ.ም) እና የሮም ገዥዎች (6-41ዓ.ም፥ 44-70 ዓ.ም)

በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም ሰላም ጠፍቶ የማያቋርጥ ሁከትና ዐመፅ ነበር። ይህ ሁኔታ እየተባባሰ በመሄዱ ሮማውያን ከአንጾኪያ ወታደሮችን ለማስመጣት ተገደዱ። ለሌሎች ማስጠንቀቂያ እንዲሆን በማለት አንድ የሮም ጄኔራል 2000 አይሁዶችን በዋና ዋና መንገዶች ላይ አሰቅሏል።

በአርኬላዎስ ዘመን በይሁዳ ውስጥ የተረጋጋ ሁኔታ አልነበረም። ኣርኬላዎስ በነገሠባቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ (ከ4ዓ.ዓ – 6ዓ.ም) ሕዝቡን ይቀሰቅሉብኛል በሚል ፍርሃት ሊቀ ካህናትን ሦስት ጊዜ ቀይሯል። ምንም እንኳ ኣርኬላዎስ የአባቱን የሕንጻ ፕሮጀክቶች ለመቀጠል ቢፈልግም፥ አይሁዶች አጥብቀው ስለ ጠሉት የሳምራውያንና የአይሁዳውያን መሪዎች ወደ ሮም አንድ መልእክተኛ ልከው በአገዛዙ ላይ የነበራቸውን ቅሬታ ገለጹ። ይህም አርኬላዎስ ከሥልጣን እንዲባረር አደረገ። በዚህ ጊዜ ሮማውያን የራሳቸውን ገዥዎች በይሁዳ ላይ ለመሾምና የይሁዳ ኣውራጃ ለማድረግ በመፈለጋቸው፥ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ አሕዛብ በኢየሩሳሌም ላይ ነገሡ።

የይሁዲነት ማዕከል በሆነችው በይሁዳ ላይ የተካሄደው የሮማውያን አገዛዝ የኢየሩሳሌምን አቋም ለወጠው። ከዚያን ጊዜ አንሥቶ የኢየሩሳሌም ከፊል ነጻነትና ሉዓላዊነት አበቃ። ነገር ግን ኢየሩሳሌም የሮም አውራጃ በመሆኗ፥ ንጉሡ የራሱን አስተዳዳሪ ይሾምባት ጀመር። ሰላም ለማስጠበቅና ሕዝቡ ለሮም ሥልጣን እንዲገዙ ለማስገደድ ንጉሡ የሮምን አስተዳዳሪና ወታደሮች የግሪክ ከተማ በሆነችው ቂሣሪያ አሰፈረ። የሮም አስተዳዳሪ ብዙውን ጊዜ በአይሁዶች ጉዳይ በቀጥታ ጣልቃ አይገባም ነበር። የአይሁዶችን ጉዳይ በማስተዳደሩ በኩል ሊቀ ካህናቱን የአይሁድ ሸንጎ (የኣይሁድ ገዥ ጉባዔ) ዋንኛውን ተግባር እንዲያከናውን ያደርግ ነበር።

አይሁዶች ቀደም ሲል ይሰበስቡት የነበረውን ግብር እዚያው ይጠቀሙበት ነበር፤ አሁን ግን በቀጥታ ወደ ሮም እንዲልኩ ተደረገ። አይሁዶች ከሮም ግዛት ሥር መሆናቸውን የሚያመለክተውን ይህን ግልጽ ተግባር አጥብቀው ይጠሉት ነበር። የግብር አሰባሰቡን ለማገዝ የሚሾሙ ቀራጮች የይሁዲነት ጠላት ተደርገው ታሰቡ። ሮማውያን አይሁዶች ሊከፍሉ የሚገባቸውን የቀረጥ መጠን ለመወሰን የሕዝብ አስተያየት በሚሰበስቡበት ወቅት ይሁዳ በተባለ የገሊላ ሰው የተመራ ዐመፅ ተካሄደ (የሐዋ. 5፡7 አንብብ።) አንድ ታማኝ አይሁዳዊ ከእግዚአብሔር በተጨማሪ ለሮማውያን ቀረጥ መክፈል አለበት ወይስ የለበትም? የሚለው አከራካሪ ጉዳይ ሆነ፡፡ ብዙ አይሁዶች ለሮማውያን ቀረጥ ኣንከፍልም በማለት የአሕዛብን አገዛዝ መቃወማቸውን ገለጹ።

የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 22፡15-21 ኣንብብ። ሀ) ግብር ስለ መክፈል የቀረበው ጥያቄ ክርስቶስን ለማጥመድ ያገለገለው እንዴት ነው? ለ) ክርስቶስ በጥበብ ባይመልስ ኖሮ ከአይሁዶች ወይም ከሮማውያን ዘንድ ምን ዐይነት ችግር ይገጥመው ነበር።

በተለይ በገሊላ ሮማውያን የአይሁዶችን ሉዓላዊነት መጋፋታቸውን በመቃወም የተጀመረው እንቅስቃሴ ለእናት ኣገራቸውና ለነጻነታቸው ቀናኢ የሆኑ አይሁዶች ቡድን እንዲመሠረት አደረገ። ይህ ቡድን ይበጀኛል በሚለው መንገድ ሁሉ የሮምን አገዛዝ ለማስወገድ ይጥር ነበር (ማቴ. 10፡4)።

ምናልባትም ይሁዳ ክርስቶስን አሳልፎ ከሰጠባቸው ምክንያቶች አንዱ፥ ክርስቶስ በሮማውያን ላይ አብዮት እንዲያካሂድ ለማስገደድ ሳይሆን አይቀርም። የዚህ ቡድን ተቃውሞ እየተካረረ በመሄዱ፥ በ66 ዓ.ም የትጥቅ ትግልን ኣስከትሏል። ይህም ሮማውያን የኢየሩሳሌምን ከተማና ቤተ መቅደስ በማፈራረስ የአይሁድን ሕዝብ እንዲደመስሱ አድርጓል።

ሮማውያን የይሁዳን ሕዝብ ለመቆጣጠር ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ ሊቀ ካህናትን መሾምና መሻር ነበር። ብዙውን ጊዜ ሊቀ ካህናት የሚመረጡት ለሮማውያን ያላቸውን ታማኝነት ያሳዩ እንደ ሆነ ወይም ጉቦ ሲሰጡ ነበር። ሮማውያን የሾሙት የመጀመሪያው ሊቀ ካህናት ለሮም መንግሥት ታማኝና ከሰዱቃውያን ወገን የነበረው ሐናንያ ነበር። ሐናንያ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ በሮማውያን ቢሻርም፥ ለብዙ ዓመታት ከሊቃነ ካህናቱ በስተጀርባ ሆኖ ሲሠራ ቆይቷል። ከእርሱ በኋላ የተሾሙት ሊቃነ ካህናት በአመዛኙ አንድም የእርሱ ልጆች፥ አልያም በጋብቻ የሚዛመዱት ነበሩ። ሐናንያ ኢየሱስ በሚመረመርበት ጊዜ ሕጋዊ ሊቀ ካህን ባይሆንም፥ የመስቀል ሞት ፍርድ ሊፈረድበት ምርመራውን ተከታትሏል (ዮሐ 18፡1214)። ሮማውያን ብዙ የተለያዩ ሊቃነ ካህናት ከሾሙ በኋላ፥ የሐናንያ አማች የነበረውን ቀያፋን መረጡ። ቀያፋ በክርስቶስ ምድራዊ የአገልግሎት ዘመን ሁሉ ሕጋዊ ሊቀ ካህናት የነበረ ሲሆን፥ ክርስቶስ እንዲሰቀል የወሰነው እርሱ ነበር (ማቴ. 26፡3-4)።

የይሁዳ አገር በኋላ ቀርነቷና በዐመፀኛነቷ የምትታወቅ የሮም ግዛት ነበረች። ምንም እንኳ ብዙ የሮም ኣስተዳዳሪዎች ይሁዳን ያስተዳደሩ ቢሆንም፥ እጅግ የሚታወቀው ግን ጴንጤናዊው ጲላጦስ ነበር። ጲላጦስ ከ26 እስከ 36 ዓ.ም ድረስ ለ10 ዓመት ይሁዳን ገዝቷል። ጲላጦስ ልበ ደንዳናና ጨካኝ መሪ የነበረ ሲሆን፥ በኣገዛዝ ዘመኑ ብዙ ችግሮች ተከስተዋል። ኃይሉን ለማሳየት ሲል፥ የሮም ወታደራዊ ሰንደቅ ዓላማ በኢየሩሳሌም እንዲውለበለብ አድርጓል። ይህ ለአይሁዶች ትልቅ ስድብ በመሆኑ ባንዲራው ካልወረደ እንደሚያምፁ ገለጹ። በሌላ ጊዜ ለከተማይቱና ለቤተ መቅደሱ ውኃ ለማስመጣት የቤተ መቅደሱን ገንዘብ ለመጠቀም ሲሞክር፥ ተመሳሳይ የዐመፅ እንቅስቃሴ ተጀመረ። ጲላጦስ በተደጋጋሚ የዚህ ዓይነት በደል ይፈጽምባቸው ስለ ነበረ፥ አይሁዶችም ለሮማው ቄሣር አቤቱታ ያቀርቡ ነበር። ክርስቶስ የሚሰቀልበት ጊዜ ሲደርስ፥ የአይሁድ መሪዎች አሁንም ለቄሣር ጉዳዩን እንደሚያሳውቁ በመግለጽ ጲላጦስ እነርሱ የሚፈልጉትን እንዲያደርግ ጫና አሳደሩበት። ጲላጦስ የክርስቶስን ንጽሕና እያወቀ አይሁድን በመፍራትና ለፖለቲካዊ ሹመቱ በመስጋት አሳልፎ ሰጠው (ዮሐ. 19፡4-16)።

የሄሮድስ ፊልጶስ አገዛዝ (4 ዓ.ዓ34 ዓም) እና ሄሮድስ አንቲጳስ (4 ዓ.ዓ–39 ዓ.ም)

ሄሮድስ ፊልጶስ መልካም አስተዳዳሪ ነበር። የአገዛዝ ክልሉ የወንጌል ታሪክ ከተፈጸመበት ውጭ በመሆኑና ጭፍሮቹም አሕዛብ በመሆናቸው፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም። አብዛኛው የክርስቶስ አገልግሎት በእርሱ ክልል ውስጥ በመሆኑ፥ የገሊላ ገዥ የነበረው ሄሮድስ አንቲጳስ በወንጌላቱ ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። ከታሪክ አንጻር፥ ሄሮድስ አንቲጳስ እንደ አባቱ ታላቅ መሪ ነበር። በገሊላ ባሕር ዳር የገነባትን ጥብርያዶስ የመሰሉ አዳዲስ ከተሞችን ኣንጾአል። የመከላከያ አምባዎችንም ገንብቷል። የናባጢያን 4ኛ ንጉሥን ልጅ አግብቶ ከእርሱም ጋር ቃል ኪዳን መሥርቷል። ነገር ግን ይህቺን የንጉሥ ልጅ ፈትቶ የወንድሙን የሄሮድስ ፊልጶስን ሚስት አገባ። ይህ የብሉይ ኪዳንን ሕግ የሚሽር ቀጥተኛ በደል ስለነበር መጥምቁ ዮሐንስ ድርጊቱን አውግዞታል። (አንዳንድ ምሑራን ክርስቶስ በማቴዎስ 5፡31-32 አንድ ሰው ሚስቱን ፈትቶ ሌላይቱን ቢያገባ አመንዝራ ይሆናል በማለት የገለጸው ይህንኑ የሄሮድስን ተግባር እያሰበ መሆኑን ያምናሉ)። በኋላ ሄሮድስ አንቲጳስ ሚስቱንና ልጇን ለማስደሰት ሲል፥ የመጥምቁ ዮሐንስ አንገት እንዲሰየፍ አድርጓል። ክርስቶስ ቀርቦ የተመረመረው በዚሁ በሄሮድስ አንቲጳስ ፊት ነበር (ሉቃስ 23፡7-15)። የናባጢያኑ ንጉሥ አሬታስ 4ኛ፥ ሄሮድስ አንቲጳስ ልጁን ፈትቶ ሌላ ስላገባ በዚህም እጅግ በመቀየሙ ውጊያ ከፍቶ አሸንፎታል።

የሄሮድስ አግሪጳ አገዛዝ (37–44 ዓ.ም)

ታላቁ ሄሮድስ ያምፁብኛል ብሎ ከገደላቸው ልጆቹ መካከል አሪስቶቡሉስ የሚባለው ኣንዱ ነበር። አሪስቶቡሉስ ሄሮድስ አግሪጳ የሚባል ልጅ ነበረው። ሄሮድስ አግሪጳ አባቱ ከተገደለ በኋላ፥ ከእናቱ ጋር ወደ ሮም ሽሽቶ በዚያ ከንጉሣውያን ቤተ ሰቦች ጋር ተወዳጀ። የሮም ንጉሥ የሆነው ጋይዮስ ካሊጉላ (37-41 ዓ.ም.) ወደ ሥልጣን ሲወጣ፥ አግሪጳን በሄሮድስ ፊልጶስ ግዛት ላይ ሾመው። ይህን የሰማው የገሊላው ገዥ ሄሮድስ አንቲጳስ ወደ ሮም ሄዶ የንግሥና ማዕረግ እንዲሰጠው ጠየቀ። ነገር ግን ንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳ ተጨማሪ ግዛት ስለ ፈለገ፥ እጎቱ አግሪጳ አንቲጳስ በሮም ላይ ለማመፅ እንዳቀደ ለሮሙ ንጉሥ ገለጸለት። ከአግሪጳ ጋር ወዳጅ የነበረው ካሊጉላ የተነገረውን አምኖ በመቀበል ሄሮድስ አንቲጳስን ወደ ምርኮ ሰደደው። በአንቲጳስ ሥር የነበሩትን የገሊላና የጴሪያ ግዛቶችም ለአግሪጳ ሰጠው።

በንጉሥ ካሊጉላ ዘመን፥ አይሁዶች በተደጋጋሚ ብርቱ ችግር ገጥሞአቸዋል። በመጀመሪያ አይሁዶች ከሮም ባለሥልጣናት ልዩ ድጋፍ በሚያገኙበት በእስክንድርያ ከተማ በአይሁዶች ላይ ሁከት ተነሣ። የእስክንድርያ ሰዎች ለሮም ባቀረቡት አቤቱታ፥ አይሁዶች ካሊጉላን እንደ አምላክ እንደማያመልኩትና መሥዋዕትም እንደማያቀርቡለት አስረዱ። ይህም ካሊጉላን አስቆጣው። ከይሁዳ ውጭ በምትገኝ አንዲት አውራጃ ውስጥ የሚኖሩ አሕዛብ ለካሊጉላ መሠዊያ ሠርተው መሥዋዕት ማቅረባቸው ደግሞ ችግሩን አባባሰው። በአካባቢው የነበሩት አይሁዶች በሁኔታው ተቆጥተው መሠዊያውን ኣፈራረሱት። ካሊጉላ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ። ከዚህም የተነሣ በቤተ መቅደሱ አካባቢ ለራሱ መሠዊያ ለማሠራትና መሥዋዕቶች እንዲቀርቡለት ለማድረግ ቆረጠ። ይህ አይሁዶችን እንደሚያስቆጣ ስለሚያውቅ፥ የጦር ሠራዊት ወደ ኢየሩሳሌም ላከ። የአይሁድ መሪዎች ሰአንቲዮከስ ኤፕፋነስ ዘመን የተከሰተውን የእርስ በርስ ጦርነትና እልቂት በማስታወስ፥ የተቆጣው የሠራዊቱ ጄኔራል ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ከመግባቱ በፊት ጄኔራሉ ይህን ተግባር እንዳይፈጽም ተማጸኑት። ጄኔራሉ ሊነሣ የሚችለውን ጦርነት ለማስቀረት ሲል የንጉሡን ትእዛዝ ቀስ በቀስ ለመፈጸም ወሰነ። (አንዳንድ ምሑራን ጳውሎስ በ2ኛ ተሰሎንቄ 28 ስለ ዐመፅ ሰው የጻፈው፥ ይህንን ሁኔታ እያስታወሰ ነው ብለው ያምናሉ።) በዚህ ጊዜ፥ ሄሮድስ አግሪጳ ወደ ሮም ሄዶ ንጉሡ ትእዛዙን እንዲለውጥ ተማጠነው። ብዙም ሳይቆይ ንጉሡን በጭካኔው የተበሳጩበት ሮማውያን ገደሉት።

ሄሮድስ አግሪጳ የተተኪው ንጉሥ ቀላውዴዎስ ወዳጅ ነበር። ቀላውዴዎስ በእስክንድርያ የተካሄደውን የፀረ-አይሁዳውያን ዓመፅ ከመግታቱም በላይ፥ ይሁዳንና ሰማርያን በመስጠት የአግሪጳን ግዛት አስፍቶላታል። ይህም ንጉሥ ኣግሪጳ የአያቱን የታላቁ ሄሮድስን አብዛኛውን ግዛት እንዲይዝ አድርጎታል።

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋ. 12፡1-23 አንብብ። ሀ) ንጉሥ አግሪጳ ለክርስቲያኖች ምን ፈጸመ? ለ) እግዚኣብሔር ጴጥርስን ለማዳን ምን አደረገ? ሐ) እግዚአብሔር ሄርድስ አግሪጳን የቀጣው በምን መንገድ ነበር? መ) እግዚአብሔር በገዥዎች ላይ ስለሚያመጣው ፍርድ ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን? ይህን ሁኔታ የተመለከትህባቸውን አንዳንድ ምሳሌዎች ዘርዝር።

ሄሮድስ አግሪጳ በአዲሱ የይሁዳ ግዛቱ አይሁዶችን ደስ ለማሰኘት ስለፈለገ፥ በክርስቲያኖች ላይ የሚያደርሱትን ስደት ይደግፍ ጀመር። ሐዋርያው ያዕቆብን ካስገደለ በኋላ፥ ሐዋርያው ጴጥሮስንም ሊጨምር ሲል የእግዚአብሔር መልአክ አዳነው። ኣግሪጳ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ሦስተኛ የንብ በማሠራት አይሁዶችን ለማስደሰት ቢፈልግም፥ ቀላውዴዎስ ወደፊት አይሁዶች ዐመፅ ቢያስነሡ ይህ ለሮም አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚያስከትል ስለተገነዘበ ፈቃድ ሊሰጠው አልፈለገም። አግሪጳ በ44 ዓ.ም በቂሣርያ ከፍተኛ በዓል ከተከበረ በኋላ በድንገት ሞተ። ክርስቲያኖች ይህ ቀጥተኛ የእግዚአብሔር ፍርድ እንደሆነ ተመለከቱ። ፍርዱም የደረሰበት ያዕቆብን ስላስገደለ ብቻ ሳይሆን፥ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚገባውን አምልኮና ክብር ስለተቀበለ ጭምር ነበር።

ሄሮድስ አግሪጳ ዳግማዊ (50-75 ዓም)

ምንም እንኳ ቀላውዴዎስ የሄሮድስ አግሪጳን ልጅ ለማንገሥ ቢፈልግም፥ የሮም መማክርት ጉባዔ ለዚህ ትልቅ ኃላፊነት ዕድሜው እንደማይፈቅድለት ወሰነ። ስለሆነም ቀላውዴዎስ ለአግሪጳ ዳግማዊ በሊባኖስ ትንሽ ግዛት ሰጠው። አግሪጳ ዳግማዊ በኋላ ያንን ግዛት እስከ ጳለስቲና ድንበር ድረስ ሊያሰፋው ችሏል። ከዚያም ኔሮ ከገሊላ አጠገብ የነበረውን ተጨማሪ መሬት ሰጥቶታል።

በዚህ ጊዜ ይሁዳ በሮም ባለሥልጣናት አገዛዝ ሥር ወደቀች፡፡ አይሁዶች በሄሮድስ አግሪጳ ዘመን ሰላማዊ ሕይወት ለመኖር ቢችሉም፥ ከ44 እስከ 66 ዓ.ም ድረስ ሮማውያን በአይሁዶች ላይ ተቃውሟቸውን እያጠናከሩ መጡ። በዚህ ጊዜ አይሁዶችን ከፖለቲካዊ ባርነት እናወጣለን የሚሉ ብዙ “መሢሖች” ብቅ ብቅ ማለት ጀምረው ነበር። እውነተኛውን መሢሕ አንቀበልም ያሉት አይሁዶች መሢሕ መጥቶ ነፃ እንዲያወጣቸው ይፈልጉ ነበር። የሮም መሪዎች እነዚህን መሢሖችና መሪዎቻቸውን በፍጥነት ይገድሉ ነበር። በይሁዳ የሚካሄደው ተከታታይ ዐመፅ ሰላም ስለነሣቸው የሮም ነገሥታት አይሁዶች ለብዙ ዓመታት የተሰጣቸውን መብት ነፈጓቸው። የይሁዳ መቃቢያውያንን ዘመን በማስታወስ አይሁዶች ነፃ የሚያወጧቸውን ወታደራዊ መሪዎች ተመኙ። ሕዝቡ ለነጻነቱ ተዋግቶ ለመሞት ፈቃደኛ ነበር።

አንዳንድ ምሑራን ይህ ታላቅ ዐመፅና የብሔርተኝነት ስሜት፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአይሁድና አሕዛብ ክርስቲያኖች መካከል ለተከሰተው ትግል መንሥዔ እንደሆነ ይናገራሉ። የብሔራዊ ነጻነት ፍላጎት የተስፋፋው በኢየሩሳሌምና በጳለስቲና ብቻ አልነበረም። በዓለም ሁሉ ተበትነው የሚገኙ አይሁዶች ለነጻነት የሚደረገውን ትግል ለመደገፍ በመቁረጣቸው፥ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል የነበረው ልዩነት በአዲስ መልክ አገረሸ። ምሑራን በዚህ ጊዜ ክርስቲያን አይሁዶች አንዱን አቅጣጫ ለመምረጥ ተገድደው እንደነበረ ያስባሉ። ለአይሁዶች ያላቸውን ታማኝነት በማሳየት አሕዛብን መጥላትና ምንም ዓይነት ግንኙነት አለማድረግን፥ ለጳለስቲና ነጻነት በመዋጋት የእንስሳት መሥዋዕትና የአባቶች ትውፊት እንደገና እንዲቀጥል፥ የኣምልኮውም ሥርዐት እንዲመለስ ማድረግ? ወይስ ከአሕዛብ አማኞች ጋር መወገን? እዚህ ላይ አንዳንድ የአይሁድ ክርስቲያኖች ክርስትናቸውን ደብቀው እንደ አይሁዶች በማምለክ ከዚህ አጣብቂኝ ለመውጣት ሞክረዋል። ከአሕዛብ ክርስቲያኖች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ለማቋረጥ ስላልፈለጉ ኣሕዛብም እንደ እነርሱ እንዲገረዙ ጠየቁ። ይህ አሕዛብን ወደ ይሁዲነት መለወጥ አብረዋቸው ለማምለክ እንዲችሉና ታማኝ አይሁዶች ብቻ ሳይሆኑ ጀግናም እንደሆኑ እንዲሰማቸው አደረጋቸው። ወይም ደግሞ ከአሕዛብ ጋር ማንኛውንም ዐይነት ኅብረት ላለማድረግ ይወስኑ ነበር። ይህም በብሔርተኝነት ላይ የተመሠረቱ ሁለት አብያተ ክርስቲያናት እንዲመሠረቱ አደረጉ ምንም እንኳ ይህ ትምህርት አይሁድ ክርስቲያኖች በሌሎች አይሁዶች እንዳይሰደዱ ለመከላከል ቢያስችልም፥ እንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ አሕዛብ በክርስቶስ እንዳያምኑ ያደርግ ነበር። ይህ ደኅንነትን እነርሱ የሚፈጽሙት «ተግባር» ከማድረጉም በላይ፥ የክርስቶስን የአካል አንድነት ያናጋል። የአሕዛብ ሐዋርያ የነበረው ጳውሎስ ይህን ትምህርት በብርቱ ተቃውሟል፤ እንደ ጳውሎስ እምነት አንድ አዲስ አካል አለ፤ በዚህም አካል ውስጥ መንፈሳዊ ዝምድና እንጂ ሥጋዊ ዝምድና ስፍራ የለውም (ቆላ. 3፡1)። በዚህ አዲስ አካል ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም ዐይነት መከፋፈል ክርስቶስ የሞተለትን እውነት ይጎዳዋል። ከዚህም በተጨማሪ ደኅንነትና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት ሁልጊዜ የእምነት እንጂ ባህልን የመለወጥ ወይም አንድን ተግባር የመፈጸም ጉዳይ አይደለም። የዕብራውያን ጸሐፊ የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዐት በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ጊዜያዊ በመሆኑ መወገዱ እንደማይቀር ገልጾአል (ዕብ 8፡13)። የአይሁዶችን ስደት ፈርቶ እምነትን መደበቅ፥ በእግዚአብሔር ፊት ዐመፅ ስለሆነ፥ ፍርድን ያስከትላል (ዕብ 10፡15-39)።

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) ከራሳችን ጎሳ ወይም ቤተ ሰብ እባላት በላይ ክርስቲያኖችን መደገፍ ለምን እንደሚከብድ ግለጽ። ለ) የቤተ ክርስቲያን ምእመናን ጎሰኝነት ተጠናውቷቸው፥ እንደ ክርስቲያን ግን መንፈሳዊ ቤተ ሰባቸው የበለጠ ኣስፈላጊ መሆኑን የዘነጉበትን አጋጣሚ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን አቅርብ። ከዚህ የተነሣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የታዘብካቸው ችግሮች ምን ምንድን ናቸው?

ምንም እንኳ አብዛኞቹ የአይሁድ ክርስቲያኖች በእምነታቸው ለመጽናት ቢወስኑም፥ አንዳንዶች ከአሕዛብ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸው ግልጽ ነው። የአይሁድ ክርስቲያኖች ከአሮጌው አምልኳቸው ጋር እንዴት እንደሚዛመዱና የአይሁድን ሕዝብ እንዴት እንደሚደግፉ ለማወቅ ተቸግረው ነበር። በሐዋርያት ሥራ 21፡17-24 ላይ የአይሁድ ክርስቲያኖች ጳውሎስ መሥዋዕት በማቅረብ ለብሉይ ኪዳን አምልኮ ሥርዐት ያለውን ታማኝነት እንዲያሳይ ጠይቀውታል። ጳውሎስም አይሁዶችን በመፍራት ሳይሆን፥ ክርስቲያን በሆኑትና ባልሆኑ አይሁዶች መካከል የነበረውን የተቃውሞና የጥርጣሬ ግድግዳ ለማፍረስ ሊል የጠየቁትን ፈጽሟል። በእርሱ ዘንድ አንድ ሰው የሚያመልክበት ሁኔታ ትልቅ ለውጥ የለውም። ከመልእክቶቹ እንደምንረዳው ጳውሎስ ያድናቸው ዘንድ ከአይሁዳውያን ጋር አይሁዳዊ፥ ከአሕዛብም ጋር አሕዛብ ሆኖ አገልግሏል (1ኛ ቆሮ. 9፡20)። ይህ ተግባሩ በኢየሩሳሌምና በሮም ለአራት ዓመት እንዲታሰር አድርጎታል።

ምንም እንኳ ከአይሁድ መሪዎች ስደት ቢኖርም፥ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ብዙ አይሁዶች በአይሁድ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሕይወት ተስበው በክርስቶስ ሊያምኑ ችለዋል። ነገር ግን የአይሁዶች ብሔርተኝነት እየጠነከረ በመሄዱና በአይሁዶችና በአሕዛብ መካከል ያለውም ልዩነት እየሰፋ ስለመጣ፥ የኣይሁድ ክርስቲያኖች ክርስቶስን በመከተል ከሕዝባቸው ወይም ከትውፊታዊው ይሁዲነት የመገንጠሉን ከባድ ምርጫ ለማድረግ ተገደዱ። የአሕዛብ ክርስቲያኖች በቁጥር እየበዙ ሲሄዱ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበራቸውን ኃይል ያጡ ጀመር። ይህም ብዙ ኣይሁዶች ክርስቶስን እንዳይከተሉ አድርጓቸዋል። ብዙዎቹ እምነታቸውን ትተው ወደ ይሁዲነት ለመመለስና ከስደት ነፃ ለመሆን ወሰኑ። የዕብራውያን ጸሐፊ እነዚህ አይሁዶች ወደ ይሁዲነት ቢመለሱ ከዚያ በኋላ ደኅንነትን ለማግኘት እንደማይችሉና ይልቁንም የእግዚአብሔርን ፍርድ እንደሚቀበሉ በመግለጽ አስጠንቅቋቸዋል (ዕብ. 10፡15-39)።

የውይይት ጥያቄ:- ቤተ ክርስቲያንህ፥ ቤተ ሰቦቻቸው ወይም የጎሳ አባሎቻቸው ከባህላዊ ሃይማኖታቸው እንዳይወጡ ለሚከለክሏቸው ሰዎች፥ የደኅንነት ተስፋ በክርስቶስ ብቻ እንደሚገኝና በቤተ ክርስቲያን የጎሳ ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ ኣንድ ቤተ ሰብ መሆናቸውን በግልጽ ለማስተማር ምን እያደረገች ነው?

የሮም ቀንደኛ ደጋፊ የነበረው ዳግማዊ አግሪጳ ብዙውን ጊዜ በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ የሮም ገዥና አማካሪ ሆኖ ይሠራ ነበር (የሐዋ. 26፡24-32)። በ62 ዓ.ም. ፊስጦስ ከሞተ በኋላ ለሦስት ዓመት ያህል የሮም ገዥ አልተተካም ነበር። ዳግማዊ ሐናንያ የሚባል ሊቀ ካህናት ይህን አጋጣሚ በመጠቀም፥ ለክርስቲያኖች የነበረውን ጥላቻ ማንጸባረቅ ጀመረ። ምንም እንኳ የክርስቶስ ወንድም የነበረው ያዕቆብ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚያመልክና ለመንፈሳዊነቱም በአይሁዶች የተከበረ ቢሆንም፥ ሐናንያ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን መሪ የነበረውን ያዕቆብን አስገደለው።

ሁከትና ብጥብጥ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ አይሁዶች የዕለት ተዕለት ክስተት ሆነ፡፡ እያንዳንዱ ተተኪ የሮም ገዥ አይሁዶችን ደስ ማሰኘት አልቻለም። እነዚህ የሮም ገዥዎች ብዙውን ጊዜ ለዐመፅ ኃይልን የሚጠቀሙ ጨካኞች ነበሩ፡፡ በሮም ላይ የሚያምፁ ሰዎች በተገደሉ ቁጥር፥ የአይሁዶች ቁጣ እየጨመረ ይሄድ ጀመር። የሮም ባለሥልጣናት በበኩላቸው ከሰዎች ገንዘብ ለመሰብሰብ ይስገበገቡ ነበር። አይሁዶች በሃስሞኒያን አገዛዝ ዘመን ነጻነትን ይፈልጉ ነበር። አንድ ሰው ከዳዊት የዘር ሐረግ ተነሥቶ የአይሁድ ጠላቶችን በመደምሰስና ሰላማዊ መንግሥት በመመሥረት የብሉይ ኪዳንን ትንቢት እንዲፈጽም ይናፍቁ ነበር። በመጨረሻም በ66 ዓም. ይህ በሮማውያን ላይ የነበረው ቁጣ ገንፍሎ ጦርነትን ቀሰቀሰ።

የመጨረሻው የሮም ገዥ ፍሎረስ የተዋጣለት የአስተዳደር ችሎታ ያልነበረውና በይሁዳም ውስጥ ለሚቀሰቀሉት ዐመፆች ግድ ያልነበረው ሰው ነበር። ይህ ሰው አሕዛብ በአይሁዶችና በሃይማኖታቸው ላይ እንዲያላግጡ አድርጓል። የቤተ መቅደስ ሀብት የነበረ ብዙ ገንዘብ ከመውሰዱም በላይ፥ ስለተቃወሙት ብቻ ብዙ ሰዎችን አስገድሏል። በርካታ ሀብታም ነጋዴዎችና ዳግማዊ ኣግሪጳ ሕዝቡ እንዳያምፁ ቢለምኗቸውም ሊሰሟቸው ግን ፈቃደኞች አልነበሩም። ስለሆነም በአንድ ካህን እየተመሩ በመዋጋት፥ በኢየሩሳሌም የነበረውን የሮማውያን ሰፈር ወረሩ። ለአገራቸውና ለነጻነታቸው ቀናኢዎች የነበሩ የእንቅስቃሴው አባላት ወዲያውኑ ከዚህ ቡድን ጋር በመቀላቀል ሌላውን የሮም ሰፈር ያዙ። ከዚያም የኢየሩሳሌምን ከተማ ወረሩ። አለመታደል ሆነና፥ ቀደም ሲል ቤተ መቅደሱን የተቆጣጠረው ቡድን የቀናኢውን ቡድን በስግደት ላይ እያለ ተኩሰው በመግደላቸው፥ የእርስ በርስ ውጊያ ገጠሙ። ሮማውያን ዐመፁን ለማስቆም ከሶርያ የላኩት ሠራዊት በቁጥሩ አነስተኛ በመሆኑ፥ ብዙ ወታደሮች ከሞቱበት በኋላ አፈገፈገ። ይህ የሮም ሠራዊት መሸነፍ ታላቅ ተስፋ በማስገኘቱ፥ ሌሎችም አገሮች በውጊያው ተባበሩ።

ሮም በጳለስቲና የተቀሰቀሰውን ዐመፅ ለመቆጣጠር ቁርጥ ውሳኔ ስላደረገች፥ ምርጥ ተዋጊ እንደሆነ የሚነገርለትን ቪስፓሲያን የተባለ ጄነራሏንና 60,000 ወታደሮች እንደገና ላከች። ከሰሜን የመጡት እነዚህ ወታደሮች ብዙም ሳይቆዩ ገሊላንና የኢየሩሳሌምን አካባቢዎች ተቆጣጠሩ። ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ በቀረቡ ጊዜ ንጉሥ ኔሮ ራሱን በመግደሉ፥ በሮም የእርስ በርስ ጦርንት ተቀሰቀሰ፡ ቪስፓሲያን በኢየሩሳሌም ላይ ለመክፈት ያሰበውን ጦርነት ለጊዜው ገትቶ የሚሆነውን ይጠባበቅ ጀመር። አይሁዶች ይህ ሁኔታ እግዚአብሔር ለእነርሱ የመዋጋቱ ምልክት እንደሆነ በማሰብ፥ ሮም በእርስ በርስ ውጊያ እንደምትወድም ገመቱ። ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ነገሮች በመለወጣቸው ቬስጋሲያን ወጊያውን ቀጥሎ፥ ከኢየሩሳሌምና ከሌሎች ሦስት ሰፈሮች በስተቀር አገሩን ሁሉ በፍጥነት ተቆጣጠረ። ብዙም ሳይቆይ ቬስፓልያን የንጉሠ ነገሥትነቱን ሥልጣን ስላገኘ፥ ልጁ ቲቶ ውጊያውን እንዲያጠናቅቅ ሾመው።

በዚህ ጊዜ ግንባር ፈጥረው የጋራ ጠላታቸውን መውጋት ሲገባቸው፥ የተለያዩ የአይሁድ መሪዎች፥ ኢየሩሳሌምን ለመቆጣጠር እርስ በርሳቸው ይዋጉ ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን በዓለ ኀምሳን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ መጥተው ስለነበር የምግብና የውኃ እጥረት ሆነ። ሰዎች ሰዎችን ለመብላት ተገደዱ። ከብዙ ወራት በኋላ ነሐሴ 27 ቀን 70 ዓ.ም. ባቢሎናውያን የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ በደመሰሱበት ቀን ሮማውያንም ቤተ መቀደሱን ደመሰሱ። በዚህ ውጊያ ከሮማውያን ጋር የተባበረው ዳግማዊ አግሪጳ፣ ምናልባትም ከቲቶ ፍላጎት ውጭ ከወታደሮቹ ጋር በመሆን ያንን ታላቅ ቤተ መቅደስ እሳት ለኩሰው አነደዱት። ቤተ መቅደሱን፤ የኢየሩሳሌምን ቅጥርና በከተማይቱ ውስጥ የነበሩትን ቤቶች ሁሉ አፈራረሱ። ብዙ ምሑራን ይህ ክርስቶስ ስለ «ጥፋት ርኩሰት» የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ ይናገራሉ (ማቴ. 24፡15)። በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዶች ሲገደሉ፥ ሌሎቹ ለባርነት ተዳርገዋል። ከዚህ በኋላ፥ በጳለስቲና የሚኖሩ አይሁዶች ኃይል ተዳከመ። የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ እንደተናገረው ብሉይ ኪዳን ከእንስሳቱ መሥዋዕት ጋር ተፈጸመ (ዕብ. 8፡13)። ከዚህ በኋላ አይሁዶች ለ2000 ዓመታት ያህል ቤተ መቅደስም ሆነ የእንስሳት መሥዋዕት ለማቅረብ ዕድል አልነበራቸውም። አሁን ግን የአይሁድ መሪዎች ቤተ መቅደሱን እንደገና ለመሥራትና መሥዋቶችን ለማቅረብ እያቀዱ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- በጳለስቲና እገር የምትኖር አይሁዳዊ ክርስቲያን ብትሆን ኖሮ፥ ሕዝብህና ከተማህ ሲወድሙ መመልከት ምን ዓይነት ስሜት ያሳድርብህ ነበር?

ምንም እንኳ ብዙ አይሁዶች ቢገደሉና ለባርነት ሲሸጡም፥ ጥቂት አይሁዶች በፈራረሰችው ኢየሩሳሌም ውስጥ ቤቶቻቸውን መልሰው ይገነቡ ጀመር። ከኢየሩሳሌም ውጭ ሌሎች ሦስት ሰፈሮችን የተቆጣጠሩት የአገርና የነጻነት ቀናኢ ቡድኖች ለሦስት ዓመት ያህል መዋጋታቸውን ቀጠሉ። እነዚህ ቡድኖች ለሮማውያን እጅ ከመስጠት ይልቅ፥ ራሳቸውን በራሳቸው አጠፉ። በ135 ዓ.ም አይሁዶች በሮም ላይ እንደገና ዐምፀው በግብፅና በቀሬና ላይ ጥቃት ሰነዘሩ። ሮማውያን ይህን ዐመፅ በፍጥነት ከተቆጣጠሩ በኋላ እንድም አይሁዳዊ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይገባ ከለከሉ። ቤተ መቅደሱ በነበረበት ስፍራ ለሮም ጣዖት ቤተ መቅደስ በመሥራት አረማዊ መሥዋዕቶችን ያቀርቡ ጀመር። በ70 ዓ.ም ኢየሩሳሌም ስትፈራርስ ከሰዱቃውያን ኣብዛኞቹ ተገድለዋል። ፈሪሳውያንና ብዙ የአይሁድ ክርስቲያኖች ጃምኒያ ወደተባለች ከተማ ፈልሰው ያለ ቤተ መቅደስና መሥዋዕት ሃይማኖታቸውን መከተል ጀመሩ።

በዚህ ጊዜ ክርስቲያኖች ምን ሆኑ? ሮማውያን ከተማይቱን ከመደምሰሳቸው በፊት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ለቅቀው ሳይወጡ እንዳልቀሩ ይገመታል። በጃምኒያ ከተማ ሳይሰፍሩ አልቀሩም። ነገር ግን ጊዜው እያለፈ ሲሄድ ቁጥራቸው እየተመናመነ ስለመጣ፥ በመጀመሪያው ምእተ ዓመት መጨረሻ ላይ በስፍራው የቀሩት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ቁጥር አነስተኛ ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

የሴሉሲድ አገዛዝ ዘመንና ነጻነት

«ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ» (ገላ. 4፡4)።

ከብሉይ ኪዳን መጨረሻ (ሚልክያስ) አንሥቶ እስከ መጥምቁ ዮሐንስ መምጣት ድረስ በነበረው 400 የዝምታ ዓመታት ውስጥ በመንፈስ ተመርቶ የእግዚአብሔርን ቃል የሚናገር ነቢይ አልተነሣም ነበር። በዚህ ወቅት በባቢሎናውያን፥ በፋርሳውያን፥ በግሪካውያንና በአይሁዳውያን አማካይነት የዓለም ሕዝብ ባህል መለወጥ ችሏል። በዚህም እግዚአብሔር ዓለምን ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት እያዘጋጀ ነበር።

ፖለቲካና ሃይማኖት ብዙም አይጣጣሙም። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በፖለቲካ ውስጥ እጃቸውን በሚያስገቡበት ጊዜ ለእግዚአብሔር መንግሥትና ለዚህ ዓለም መንግሥት በሚጠቅሙ ነገሮች መካከል ግጭት ይከሰታል። መገዛት ያለብን ለየትኛው መንግሥት ነው? ለምድራዊው መንግሥት ወይስ ለሰማያዊው መንግሥት? ለክርስቲያኖች በፖለቲካ ውስጥ መሳተፉ መልካም ቢሆንም፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ግን ሃይማኖትንና ፖለቲካን ከመቀላቀል መጠንቀቅ አለባቸው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የአንድን ፖለቲካ አጀንዳ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ደግፈው መታገል የለባቸውም። ነገር ግን ሰዎች በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመሥርተው መንፈሳዊ ውሳኔዎችን እንዲያስተላልፉ መርዳት አለባቸው። እንደ ብሉይ ኪዳን ነቢያት፥ የእግዚአብሔርን ቃል መርሆዎችን አለመከተል ስለሚያመጣው ጥፋት ማስጠንቀቅ አለባቸው። በፖለቲካ ተግባሮች ላይ የሚሳተፉ ክርስቲያኖች ከሁሉ በፊት ለእግዚአብሔር ታማኝ በመሆን በመጽሐፍ ቅዱስ መርሆዎች መሠረት መኖርና መተዳደር ይኖርባቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች በአገራቸው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት መሳተፍ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሃይማኖተኞችና ፖለቲከኞች በመሆናቸው ምክንያት ችግሮች ሲከሰቱ የተመለከትከው እንዴት ነው? ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በፖለቲካና በአገራችን ጉዳዮች ላይ ምን ምን ኣስተዋጽኦዎችን ሊያበረክቱ ይችላሉ?

ጊዜው እየገፋ ሲሄድ፥ በኢየሩሳሌም ከተማ በተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች መካከል ዐቢይ ትግል ይካሄድ ጀመር። ካህናት የሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎች ሲሆኑ፥ የፖለቲካ ሥልጣን ከተቀደሰ አኗኗር በላይ አስፈላጊ እየሆነ መጣ። ብዙም ሳይቆይ የሃይማኖት መሪዎች ልክ እንደ ዓለማውያን ዐይነት ፖለቲካዊ አቅጣጫ በመያዝ፥ እግዚአብሔር በማይፈልጋቸው መንገዶች ይጓዙ ጀመር። አይሁዶችን በመንፈሳዊ አምልኮ የመምራት ኃላፊነት ከተሰጣቸው ካህናት መካከል ሁለት ዐበይት የፖለቲካ ቡድኖች ብቅ አሉ። እነዚህ ሁለቱ ቡድኖች በአይሁድ ሕዝብ ላይ ለመንገሥ ይችሉ ዘንድ ከአሕዛብ ሞገስ ለማግኘት አጥብቀው ታገሉ። እነዚህ ሁለቱ ቡድኖች ወይም ቤተሰቦች ኦኒያዶችና ጦቢያቶች ይባላሉ። ኦኒያዶች አክራሪዎች ነበሩ። ኦኒያዶች የአይሁድን ባህል ጠብቆ ለማቆየት ባላቸው ጽኑ ፍላጎት መሠረት፥ ከግሪክ ባህል ጋር የሚደረገውን ውህደት በመጠኑ ብቻ ለማድረግ ፈለጉ። ጦቢያዶች የአሕዛብ ባህልን ለመከተል የተዘጋጁ በመሆናቸው፥ አይሁዶች አንዳንድ ጥብቅ ባህላዊ ልማዶቻቸውን ትተው የግሪኮችን የአኗኗር ስልት እንዲከተሉ ያበረታቷቸው ነበር። ጦቢያዶች መጀመሪያ ከፕቶሎሚዎች በኋላም ከሴሉሲዶች ግብር ለመሰብሰብ ውክልና በማግኘታቸው፥ በይሁዳ ሕዝብ ላይ ፖለቲካዊ ሥልጣንን ጨበጡ። እነዚህ ሰዎች በአብዛኛው ስግብግቦች ነበሩ። ጦቢያዶች ግሪኮች የሚጠይቁትን ግብር ብቻ ሳይሆን ለራሳቸው ጭምር ሕዝቡን እያስገደዱ ግብር ይሰበስቡ ነበር። ይህም የኋላ ኋላ፥ ተራ ሕይወት በሚመሩት ሰዎች ዘንድ እንዲጠሉ አድርጓቸዋል። የሀብታም ነጋዴ ቤተሰቦች ግን የጥቅሙ ተካፋዮች ነበሩ።

ጦቢያዶችን የሚከተሉ ሀብታም ቤተሰቦች የአይሁድን ባህል ለመለወጥና ለአሕዛብ ተስማሚ ለማድረግ ፈለጉ። ስለሆነም፥ አይሁዶች ወደ «ዘመናዊነቱ» በማድላት ባህላቸውንና አምልኳቸውን ሳይቀር ከአሕዛብ ጋር እንዲያስማሙ አበረታቷቸው። በአዲስ ኪዳን ዘመን የጦቢያድ ቡድን ትውልዶች፥ ሰዱቃውያን ይባሉ ነበር። እነዚህ ገዥዎቻቸው ከነበሩት አሕዛብ (ማለትም፥ ግሪካውያንና ሮማውያን) ጋር ለመስማማት የሚችሉትን ሁሉ ከማድረግ የማይመለሱና የፖለቲካ ሥልጣን የነበራቸው ቡድኖች ነበሩ።

የውይይት ጥያቄ፡- የዓለም ባህል በክርስቲያኖች በተለይም በወጣቶች ላይ ተጽዕኖ በማድረስ፥ እንዴት ከንጹሕ አኗኗር እንደሚመልሳቸው አንዳንድ ምሳሌዎችን ስጥ።

ለብሉይ ኪዳን ታማኝ ሆነው ልዩ ባህላቸውንና እምነታቸውን ጠብቀው ለመኖር የፈለጉ ብዙ አይሁዶች ነበሩ። እነዚህ ኣይሁዶች ጦቢያዶችን በመቃወም ሃሲዲያን የተባለ ሌላ ቡድን መሠረቱ። በይሁዳ ይህ ቡድን በአሕዛብና የአሕዛብን ባህል በመደገፍ አይሁዶች የግሪኮችን ባህል ይበልጥ እንዲቀበሉ ባደረጉት ሀብታም የአይሁድ መሪዎች ላይ ዐመፅ እንዲቀሰቀስ ኣደረጉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ዳን. 11፡36-45 አንብብ። ሀ) በዚህ ክፍል የታየው ባህላዊ ትግል ምንድን ነው? ለ) ከሰሜን ንጉሥ ትውልዶች አንደኛው በኢየሩሳሌም ላይ ምን ያደርጋል? ሐ) ዳንኤል ይህ ዘመን ለአይሁዶች ምን ዓይነት ዘመን እንደሚሆን ገለጸ?

በዚህ ጊዜ ሴሉሲዶች ፕቶሎሚዎችን አሸንፈው ጳለስቲናን ተቆጣጠሩ። የሴሉሲድ መሪ የነበረው አንቲዮክስ ግልላዊ መንግሥቱን ለማስፋፋት አሰበ። ነገር ግን አዲሱ የሮም መንግሥት በዚህ ጊዜ በመስፋፋት ላይ ነበር። አንቲዮክስ ግሪክን ለመቆጣጠር በሞከረ ጊዜ ሮማውያን አሸነፉት። ከዚያም ለጦር ጉዳት ካሳ እንዲከፍል አስገደዱት። አንቲዮከስ እየተዳከመ ሲሄድ በመንግሥቱ ውስጥ የነበሩ ጠንካራ ፓርቲዎች ዐመፁበት። እርሱ ከሞተ በኋላ በእግሩ የተተካው የሴሉሲድ ንጉሥ ለሮም የሚከፍለውን ገንዘብ የግድ ማግኘት ነበረበት። ስለሆነም፥ አይሁዶች ቀደም ሲል ይከፍሉት ከነበረው ግብር በተጨማሪ እጥፍ እንዲከፍሉ መጣሉ ብቻ ሳይሆን፥ ወደ የቤተ መቅደሱ የሚመጣውንም ገንዘብ በሙሉ እንዲሰጡት ጠየቀ። አይሁዶች በዚህ ፖሊሲ ላይ ከማመፃቸው በፊት ተገደለ።

ይህ መሪ በሞተበት ወቅት ልጆቹ ገና ሕፃናት በመሆናቸው፥ አንቲዮከስ ኤፕፋነስ (ትርጉሙ የእግዚአብሔር መገለጥ) የተባለ ወንድሙ ዙፋኑን ያዘ። ይህኛው አንቲዮከስ የአይሁዶች ብርቱ ጠላት ሆነ። እንደ ታላቁ እስክንድር ድል ነሺ በመሆን፥ የግሪክን (ሴሉሲድ) መንግሥት ክብር ለመመለስና ሰዎች ሁሉ የግሪክን ባህል እንዲከተሉ ለማስገደድ ጣረ። ይህ ሰው ንጉሠ ነገሥት ከሆነ በኋላ፥ ሁለት አይሁዶች ከአንቲዮከስ ጋር ለመነጋገር ወደ አንጾኪያ ሄዱ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ስለ ግብሩ መጨመርና ከቤተ መቅደሱ ስለሚወሰደው ገንዘብ በማማረር የገለጸው የአይሁድ ሊቀ ካህናት ነበር። ሌላው ደግሞ የሊቀ ካህናቱን ወንበር ለመውሰድ የፈለገው ጄሰን የተባለ የገዛ ወንድሙ ነበር። ጄሰን የሊቀ ካህንነቱን ወንበር ከያዘ የግሪክን ባህል እንደሚያስፋፋና ለአንቲዮከስም ጠቀም ያለ ገንዘብ ከቤተ መቅደሱ ካዝና ለመስጠት እንደሚችል ገልጾ ኣግባባው። አንቲዮከስ የግሪክን ባህል ለማስፋፋት ፍላጎት ስለ ነበረው፥ ጄሰንን ሊቀ ካህናት አደረገው። (ከዚህ ጊዜ ጀምሮ፥ ግሪኮች የእነርሱን ፖሊሲ የሚደግፍ ሊቀ ካህናት ሲሾሙ ኖረዋል።)

ጄሰን ወደ አገሩ እንደተመለሰ የግሪክን ባህል ለማስተዋወቅ ደፋ ቀና ይል ጀመር። የአይሁድ ወጣቶች የግሪኮችን ባህልና ስፖርት የሚለማመዱበትን ጂምናዚየም ገነባ። አይሁዶች ግሪኮች እንዳለመሠልጠን አድርገው የሚመለከቱትን ወንድ ልጆችን የመግረዝ ባህላቸውን እንዲያቆሙ አዘዘ።

የሊቀ ካህናቱን መንበር ለመጨበጥ ግን ፖለቲካዊ ትግሉ ተጧጡፎ ቀጠለ። መነሊስ የተባለ አንድ የቤተ መቅደስ ወታደር ዓመታዊ ግብሩን እንዲያስረክብ ወደ አንጾኪያ ተልኮ ነበር። ምንም እንኳ ይህ ሰው በብሉይ ኪዳን ሕግ መሠረት ከኣሮን የትውልድ ሐረግ ወገን ባለመሆኑ ሊቀ ካህን መሆን ባይችልም፥ መነሊስ ለአነቲዮከስ ጉቦ በመስጠት ይህን ሥልጣን እንዲሰጠው ጠየቀ። መነሊስ የሊቀ ካህንነቱን ሥልጣን ከመያዝም አልፎ፥ ትክክለኛ ሊቀ ካህን ሊሆን የሚገባውን የጄሰንን ወንድም መግደሉ አይሁዶችን ይበልጥ አስቆጣ።

በተከታዩ ዓመት ማለትም በ168 ዓ.ዓ. አንቲዮከስ ግብፅን በመውጋት ዋና ከተማዋን ለመያዝና ራሱንም ንጉሥ አድርጎ ለመሾም አሰበ። ነገር ግን ሮማውያን ኣንድ የልዑካን ቡድን ልከው አንቲዮከስ የግብፅ ንጉሥ ለመሆን የነበረውን ምኞት እንዲሰርዝ አስገደዱት። ከዚህ ጊዜ ኣንሥቶ ሮም ለቀጣይ 100 ዓመት የዓለም ኃያል አገር ሆነች። ነገር ግን እንቅስቃሴአቸው በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይም በኢየሩሳሌም ጎልቶ አይታይም ነበር።

አንቲዮከስ በሮማውያን ተገድሏል የሚል አንድ የሐሰት ወሬ ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ፥ የቀድሞው ሊቀ ካህናት ጄሰን 1000 ወታደሮችን ኣስከትሎ በመምጣት መነሊስን ሽሮ ቤተ መቅደሱን ተቆጣጠረ። አንቲዮከስ ይህን ዐመፅ ሲሰማ፥ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ በዐመፁ ተግባር ላይ እንደ ተሳተፉና ከእርሱ ይልቅ ፕቶሎሚዎችን የደገፉ መሰለው። ስለሆነም፥ ሠራዊቱን ወደ ኢየሩሳሌም ላከ። ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ተገደሉ፤ በባርነትም ተወሰዱ። መነሊስም ተመልሶ በሥልጣኑ ላይ ተቀመጠ። በተጨማሪም፥ አንቲዮከስ ብዙ ወታደሮችን በኢየሩሳሌም አሰፈረ። በዚህ ጊዜ አንቲዮከስ ኢየሩሳሌምን ከሃይማኖታዊ መንበርነት ወደ ግሪክ ከተማነት ለመለወጥ ቆርጦ ተነሣ። በመሆኑም፥ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ማፈራረስ ጀመረ። በተጨማሪም፥ የኣይሁድን ሃይማኖት ለማዳከም ሲል አይሁዶች የግሪክ ጣዖትን እንዲያመልኩ አስገደደ። የሃይማኖቷ ኃይል እስካልተደመሰሰ ድረስ ይሁዳ የግሪክን ባህል እንደማትቀበል ተገነዘበ። ስለሆነም፥ ባለፉት 300 ዓመታት ሲደረጉ የነበሩት የቤተ መቅደስ መሥዋዕቶች እንዲቀሩና ብሉይ ኪዳንም እንዲወገድ አዘዘ። ሰዎች የሰንበትን ኣምልኮና ወንድ ልጆችን የመግረዝ ሥርዐታቸውን እንዲያቆሙ አስጠነቀቀ። በ197 ዓ.ዓ. በቤተ መቅደሱ አካባቢ ሌላ መሠዊያ ሠርቶ ዜውስ ለተባለ የግሪክ ጣዖት መሥዋዕት አቀረበ። ይህ ዳንኤል ስለ “ጥፋት ርኩሰት” የተናገረውን ትንቢት በከፊል ይፈጽመዋል (ዳን. 9፡27፤ 11፡31)። [ክርስቶስ ወደፊት ሌላ የጥፋት ርኩሰት እንደሚነሣ ተንብዮአል (ማቴ. 24፡5)።] በአይሁድ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ፥ በሃይማኖታቸው ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ተሰነዘረ። አንቲዮክስ የአይሁዶችን ሃይማኖት ለመቆጣጠር የፈለገው በሕይወታቸው ላይ የነበረውን ቁጥጥር አሜን ብላው በተገዥነት መንፈስ እንዲቀበሉ ለማድረግ መሆኑ አይጠረጠርም። ነገር ግን ለ300 ዓመታት ያህል በራሳቸው መንገድ እንዲያመልኩ በተፈቀደላቸው አይሁዶች ላይ ይህን የፖሊሲ ለውጥ ማምጣቱ አይሁዶችን ለቁጣ ቀስቅሷል።

በይሁዳ ውስጥ በምትገኝ አነስተኛ ከተማ ማታቲያ የሚባል አንድ ካህን ነበር። ከአንቲዮከስ የተላከ አንድ ሰው ወደ እርሱ መጥቶ በኢየሩሳሌም በተሠራው መሠዊያ ላይ ለዜውስ እንዲሰግድ ሲጠይቀው ፈቃደኛ ሆኖ አልተገኘም። ማታቲያ ለዜውስ ጣዖት ለመሠዋት የተስማሙትን አንዳንድ አይሁዶችና ተልከው የመጡትን ሰዎች ከገደለ በኋላ፥ ለእግዚአብሔር ለመቆም የፈለጉ ሰዎች እንዲከተሉት ጠየቀ። አንቲዮከስንም ለመውጋትና ለመቋቋም ወሰኑ። ወዲያውም በእግዚአብሔር ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመቋቋም የፈለጉ ሰዎች ሁሉ ተባበሯቸው። እነዚህ ዐማፅያን የጣዖት ኣምልኮን በመደምሰስ፥ የግሪክን አምልኮና ባህል የተቀበሉትን አይሁዶች በመግደልና የኣይሁድ ወንድ ልጆችን በመግረዝ ተቃውሟቸውን አቀጣጠሉ። ይህም በአይሁድ ታሪክ የመቃብያን ዘመን የሚባለውን ጊዜ አበሰረ። በኋላ የመቃብያን ትውልዶች ሃስሞኒያን ተብለዋል። የሃስሞኒያን ሥርወ መንግሥት በዚያች አጭር የነጻነት ጊዜ (ከ142-63 ዓ.ዓ) በይሁዳ የሊቀ ካህንነቱን አገዛዝ የተቆጣጠሩ የማታቲያ ትውልዶች ናቸው። ሥርወ መንግሥታቸው ከፍጻሜ የደረሰው ሮማውያን ኢየሩሳሌምን በወረሩና ታላቁ ሄሮድስ የይሁዳ ንጉሥ በሆነ ጊዜ ነበር።

ማታቲያ ከሞተ በኋላ፥ ከአምስት ልጆቹ አንዱ የነበረው ይሁዳ መቃቢ (ትርጉሙ «መዶሻ » ማለት ነው) የዐማፅያኑን ቡድን መምራት ጀመረ። ከ400 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አይሁዶች ጦርነት አካሄዱ። ዐማፂ ተዋጊ በመሆኑ፥ አንዳንድ የሴሉሲድ ሠራዊቶችን ሊያሸንፍ ቻለ። ይህን ድል ሲያዩ ሌሎችም ጦሮች ተቀላቀሉ። ሁኔታው ያበሳጨው አንቲዮከስ ዐመፁን እንዲያስቆምና አይሁዶችን ከይሁዳ እንዲያግዙ ብዙ ወታደሮችን ወደ ኢየሩሳሌም ሰደደ። በቁጥር ባይመጣጠኑም እንኳ አይሁዶች ለጊዜው የሴሉሲድን ጦር ለማሸነፍ ችለው ነበር። በመጨረሻም፥ አንቲዮክስ ከአይሁዶች ጋር በመደራደር እንደ ቀድሞው አምላካቸውን እያመለኩ በሰላም መኖር እንደሚችሉ አስታወቀ። ይሁዳና ሠራዊቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ከተማይቱን ተቆጣጠሩ። የዜውስን የጣዖት መሠዊያዎችን አፈራርሰው በብሉይ ኪዳን እንደተደነገገው የእግዚአብሔርን የቤተ መቅደስ አምልኮ ጀመሩ።

ይሁዳና ሌሎችም አይሁዳውያን ለሃይማኖታቸው ነጻነት ታግለው ባገኙት ድልና ሞራል ለፖለቲካ ድል ይታገሉ ጀመር። ስለሆነም ከሴሉሲድ ጋር ጦርነት ገጠሙ። በመጀመሪያ ትንሽ ድል የቀናው የይሁዳ ጦር ተሸነፈ። ሴሉሲዶች አይሁዶች በጥንታዊ መንገዳቸው እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ቢፈቅዱላቸውም ፖለቲካዊ ነጻነት ሊሰጧቸው አልፈቀዱም። ይሁዳ በዚህ ሁኔታ ስላልረካ በሴሉሲድ አገዛዝ ላይ ማመፁን ቀጠለ። በኋላም ይሁዳ በጦርነት ላይ ሲሞት፥ ዮናታን የተባለ ወንድሙ ተካው።

በዚህ ጊዜ፥ በአንጾኪያ በሴሉሲድ መንግሥት ዙሪያ ለመግዛት መብት ያለው ማን ነው በሚለው ላይ ትግል ይካሄድ ነበር። ትክክለኛው ንጉሥ እኔ ነኝ እያሉ ከሚፋለሙት ሰዎች መካከል አንዱ ወደ ዮናታን መጥቶ ድጋፍ ከሰጠው የሊቀ ካህንነቱን ሥልጣን እንደሚሰጠው ነገረው። ዮናታን ፈተናውን ለመቋቋም ስላልቻለ ከሰውየው ጋር ተስማምቶ የሊቀ ካህንነቱን ሹመት ተቀበለ። ይህም ዮናታን ሃይማኖታዊና ወታደራዊ ሥልጣንን አጣምሮ መያዙ በወጥመድ እንዲያዝ አደረገው። ዮናታን ድጋፉን የሰጠው ባላስ የንግሥናውን መንበር ሲይዝ፥ ዮናታን የይሁዳ ገዥ በመሆን የፖለቲካውንም ሥልጣን ጨበጠ። በአንጾኪያ የሚካሄደው የዙፋን ትግል ለብዙ ዓመታት ቀጠለ። ዮናታና አታላይ መሪ በመሆኑ በይሁዳ ላይ የበለጠ ሥልጣን ያስገኛል ብሎ ያሰበውን ቡድን ሲደግፍ ቆየ። ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የጳለስቲናን አገዛዝ እያሰፋ እንዲሄድ ረዳው። ይሁንና አንድ የሴሉሲድ መሪ ዮናታንን አታሎ ከማረከው በኋላ ገደለው። ይህም በይሁዳ የነጻነት ትግሉ አመራር ከማታቲያ ልጆች መካከል በሕይወት በነበረው በስምዖን ጫንቃ ላይ እንዲወድቅ አደረገ።

በ142 ዓ.ዓ. ስምዖን ለይሁዳ መሠረታዊ ነጻነት የሚያስገኝ ድርድር ከሴሉሊድ መንግሥት ጋር ለማድረግ ችሎ ነበር። የሌሉሲድን ኃይል ለማዳከም ይፈልግ በነበረው በሮም መንግሥት ድጋፍ፥ ይሁዳ ለ80 ዓመታት ነፃ ሆና ቆይታለች። በዚህ ነጻነት የተደሰቱት አይሁዶች ለስምዖን የሊቀ ካህንነቱን ሹመት ሰጡት። ምንም እንኳ ስምዖን ብሉይ ኪዳን ከሚደነግገው የሊቀ ካህናት ዘር ሐረግ ወገን ባይሆንም፥ ዘሩ ለዘላለም የሊቀ ካህንነት መብት እንዲኖረው ወሰኑ። ነገር ግን ስምዖን በልጁ ባል ስለተገደለ በሊቀ ካህንነት መሪነቱ ብዙም አልቆየም። ዮሐንስ ሂርካነስ የተባለው የስምዖን ልጅ የሃይማኖቱንና የፖለቲካ ሥልጣኑን ተረከበ።

የሚያሳዝነው የውጭ ወራሪን ለመቋቋም የሚተባበሩ ሰዎች በሰላም ጊዜ እርስ በርሳቸው ይዋጋሉ። በመሆኑም፥ በዚህ የሰላም ጊዜ አይሁዶች እርስ በርሳቸው መዋጋት ጀመሩ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ውስጣዊ ትግል ሲካሄድ ያየህበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) ይህ ለምን የሚሆን ይመስልሃል?

ዮሐንስ ሂርካነስ ንጉሥ ሲሆን፥ ሶርያውያን ምንም እንኳ ኢየሩሳሌምን ድል ማድረግ ቢችሉም ረዥም ጊዜ የሚወስድ ጦርነት ለማካሄድ ስላልፈለጉ ከእርሱ ጋር ስምምነት አደረጉ። የበላይነታቸውን እስካከበረላቸው ድረስ ነጻነት ሊሰጡት ተስማሙ። በዚህ ጊዜ የተነሣው ኣዲስ ትውልድ ምንም እንኳ በወታደራዊ ድሎቹ ደስ ቢሰኝም፥ ሰላምን ይናፍቅ ነበር። የሚዋጉትም ለሃይማኖት ነጻነት ባለመሆኑ፥ ብዙም የመዋጋት ፍላጎት አልነበራቸውም። ከሶርያውያን ጋር ስምምነት የተፈራረመው ዮሐንስ እንደ አባቱ የግሪክን ባህል አይቃወምም ነበር። ይህም የግሪክን ባህል የሚከተሉትን የአይሁድ ሀብታሞች ደስ አሰኛቸው። ስለሆነም፥ ከሶርያ ጋር ተስማምቶ አገሪቱን ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ ጀመሩ። እነዚህ ዮሐንስን የደገፉትና የግሪክን ባህል የተከተሉት ሀብታም ኣይሁዶች በኋላ የሰዱቃውያንን ቡድን መሥርተዋል።

ኣንዳንድ አጥባቂ አይሁዶች ዮሐንስ ከትክክለኛው የካህናት ዘር ሐረግ ወገን ሳይሆን የሊቀ ካህንነቱን ስፍራ በመያዙ ቅር ተሰኙ። ስለሆነም ዮሐንስ ይህን ሥልጣን እንዲለቅ ጠየቁት። ፈቃደኛ ኣለመሆኑን ሲገነዘቡ እነርሱም ለእርሱ ድጋፍ ከመስጠት ተቆጠቡ። ብዙ ምሁራን የፈሪሳውያን ቡድን በዚህ ጊዜ እንደተጀመረ ይናገራሉ፡፡ (ፈሪሳዊ ማለት የተለየ ማለት ሲሆን፥ የዮሐንስን አገዛዝ ከመደገፍ መለየታቸውን ያሳያል። እነዚህ ሰዎች ሃይማኖታዊ ኣጥባቂነትን ይከተሉ የነበሩ ሲሆን፥ በኋላም የክርስቶስ ጠላቶች ሆነው ተገኝተዋል።) ፈሪሳውያን የገዥው ቡድንና የሰዱቃውያን ፖለቲካ ቡድን አባላት የሆኑት የነጋዴ ቤተሰቦች ጠላቶች ሆኑ። በታሪክ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሱት በዚህ ጊዜ ነበር። በ70 ዓም. ሮማውያን ሰዱቃውያንን እስከደመሰሱበት ጊዜ ድረስ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ትግል ሲካሄድ ቆይቷል። እነዚህ ሁለቱ ቡድኖች ተባብረው የሠሩበት ጊዜ ቢኖር የሁለታችንም ጠላት ነው ብለው ያሰቡትን ክርስቶስን ለመስቀል በተነሡበት ወቅት ብቻ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋ. 23፡6-10 አንብብ። ይህ ክፍል በእነዚህ ሁለት ቡድኖች መካከል የነበረውን ጥላቻ የሚያሳየው እንዴት ነው?

ዮሐንስ ሂርካነስ የጥንቱን የአይሁድ ሕዝብ ክብር ለመመለስ ቆርጦ ተነሥቶ ነበር። በዚህ ጊዜ የሴሉሲድ ግዛት ተዳክሞ ስለ ነበር አዳዲስ ግዛቶችን መውረር ያዘ። በደቡብ የኢዱሚያን ሕዝብ በመውረር ተገርዘው አይሁዳውያን እንዲሆኑ አደረገ። ይህን በሚያደርግበት ጊዜ ከኢዱሚያን ተወላጆች አንዱ የሆነው ታላቁ ሄሮድስ ዙፋኑን ከትውልዶቹ እንደሚወስድ አላወቀም ነበር። ከዚያም ዮሐንስ ወደ ሰሜን ገስግሶ ሰማርያን ያዘ፡፡ ዮሐንስ ሳምራውያንን ከሚገባው በላይ ይጠላቸው ስለ ነበር፥ ቤተ መቅደሳቸውን አፍርሶ ብዙ ሳምራውያንን ገደለ። ይህም ተግባር በአይሁዶችና በሳምራውያን መካከል የነበረውን ጥላቻ አባባሰው።

የዮሐንስ ዘሮችም እርሱ የጀመራቸውን ተግባሮች መፈጸም ቀጠሉ። ከሰማርያ በስተሰሜን የምትገኘው ገሊላ አይሁዶች የሰፈሩባት ኣካባቢ ብትሆንም ብዙ ኣሕዛብ ነበሩባት። የዮሐንስ ልጅ የሆነው አሪስቶሉሉስ ገሊላን ለመቆጣጠር ቻለ። ይህ ሰው ብዙ አይሁዶችን ወደ ገሊላ ከመላኩም በላይ፥ በዚያ የነበሩትንም ሰዎች ወደ ይሁዲነት እንዲለወጡ አድርጓል። ምናልባት የዮሴፍና የማርያም ቅድመ ኣያቶች ከቤተልሔም ወደ ገሊላ የሄዱት በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ የተወለደው በገሊላ ሲሆን፥ አብዛኛውን አገልግሎቱንም ያደረገው በዚያ ነው። አብዛኞቹ ደቀ መዛሙርትም የገሊላ ሰዎች ናቸው። ሁልጊዜ በይሁዳ አገዛዝ ላይ ጥላቻዋን ከምታሳየው ከሰማርያ በተቃራኒ፥ ገሊላ በከፍተኛ ደረጃ ኣይሁዶችን ትደግፍ ነበር። እንዲያውም፥ በአዲስ ኪዳን ዘመን ከሮማውያን ነፃ ለመውጣት ከፍተኛ ትግል ያካሄዱት የገሊላ ኣይሁዶች ነበሩ።

ጊዜው እየገፋ ሲሄድ፥ የሃስሞኒያን መሪዎች አንድ ጊዜ በወረራ ሌላ ጊዜ ድግሞ በስምምነት ግዛታቸውን ለማስፋፋት ፈለጉ። ከዚህም በተጨማሪ፥ የአይሁድን ሃይማኖት በማጣጣል አይሁዶች እንደ ኣሕዛብ እንዲኖሩ አደረጉ። ይህም አይሁዶች በፈሪሳውያን እየተመሩ በጨቋኝ አገዛዛቸው ላይ እንዲነሡ አደረገ። ይህም በሃስሞኒያን ዘሮች መካከል ወደ ተደረገው የጦርነት ዘመን መራቸው፡፡ ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን በሁለት ተቃራኒ ጎራዎች ተሰልፈው እንዲዋጉ ያደረገው ይኸው ጦርነት፥ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊም ነበር። ነገሮች እየከረሩ በመሄዳቸው ፈሪሳውያን ሴሉሲዶች መጥተው ኢየሩሳሌምን እንዲያጠቋትና እንዲቆጣጠሯት ጋበዟቸው። የሶርያ ሠራዊት ሲሸነፍ፥ ከ800 ፈሪሳውያን በላይ ተገደሉ።

በሃስሞኒያን ዘመን የሮም ግዛት እየተስፋፋ በመሄዱ በጥንቱ ዓለም እጅግ ታላቅ ስፍራ ለመያዝ በቃ። በመጀመሪያ ሮማውያን የሴሉሲድን መንግሥት ለማዳከም ሲሉ ብዙም አቅም ያልነበራት ይሁዳ ነፃ እንድትሆን ፈቅደው ነበር። ነገር ግን ሮማውያን በ66 ዓ.ዓ የሴሉሲድን አዛዝ ገርስሶ የአይሁዶችን ነጻነት ማከበሩ አስፈላጊ ሆኖ አላገኙትም። በይሁዳ የሮም አገዛዝ ተቃውሞ ሲገጥመው በ64 ዓ.ዓ. ፖምፔ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ።

ለተወሰነ ጊዜ ውጊያ ከተካሄደ በኋላ ብዙ ሰዎች ተገደሉ፤ የኢየሩሳሌምም ከተማ ተሸነፈች። የነጻነት ዘመኗም አበቃ። ፖምፔ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ አንድ የተለየ ነገር ይኖራል ብሎ ስላሰበ ወደዚያው ለመግባት ፈለገ። ይህም ነጻነታቸውን በመገፈፋቸው ብቻ ሳይሆን በሃይማኖታቸውም ላይ አስከፊ ተግባር እንደ ተፈጸመ በሚቆጥሩ ኣይሁዶች ጥላቻን አተረፈ።

ምንም እንኳ ይሁዳ ነጻነቷን ብታጣም፥ የሃስሞኒያን ገዥዎች የሊቀ ካህንነቱንና የገዥነቱን ሥልጣን ለመያዝ ይሻኮቱ ጀመር። በተጨማሪም፥ አይሁዶች በሮም አገዛዝ ላይ የማያቋርጥ ተቃውሞ ያካሄዱ ነበር። በዚህ ጊዜ አንቲፓር የተባለ ኢዱሚን ወደ ሥልጣን የሚወጣበትን መሰላል ተመለከተ። ይህ ሰው ከሃስሞኒያን ገዥዎች የአንዱ ዋንኛ ደጋፊ በመሆን ሮማውያን የአንቲፓርን ጓደኛ ሊቀ ካህናት አድርገው እንዲሾሙት ተጽዕኖ አሳደረ። የሮም ጀኔራሎች በሚቸገሩበት ጊዜ አንቲፓር እነርሱን ለመርዳት የሚችለውን ሁሉ አደረገ። ለዚህ ተግባሩ ብድር ለመመለስ ሮማውያን ልጆቹን በቀድሞው የሃስሞኒያን ግዛት ውስጥ ሾሟቸው። ከልጆቹ አንዱ የሆነው ሄሮድስ ገሊላን እንዲገዛ ተደረገ።

በዚህ ጊዜ ሁለት ጄኔራሎች እርስ በርሳቸው በመዋጋታቸው በሮማውያን መካከል ውስጣዊ ትግል ይካሄድ ጀመር። ሄሮድስ ከአንደኛው ጄኔራል ጎን ሲሰለፍ፥ ይህ ሰው የኋላ ኋላ የንጉሠ ነገሥትነቱን አክሊል ሊደፋ ቻለ። በዚህ ጊዜ ሄሮድስ ለፈጸመው ተግባር የንግሥና ሹመት ተሰጠው። አሁንም የሊቀ ክህነትና የፖለቲካ መሪነት ሥልጣን ተነጣጠሉ፤ ሊቀ ካህናቱ ከፖለቲካ መሪ ሥር እንዲሆን ተደረገ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በዚያን ዘመን የምትኖር ኣይሁዳዊ ብትሆን ኖሮ፥ ትልቁ ናፍቆትህ ምን ይሆን ነበር? የሰላም ንጉሥ የሆነው መሢሕ እንዲመጣ ምን ያህል ትፈልግ ነበር? ለ) እግዚአብሔር አይሁዶችን ለመሢሑ መምጣት ለማዘጋጀት ይህንን የነጻነትና የብጥብጥ ጊዜ የተጠቀመው እንዴት ነው? ሐ) ከአይሁድ መሪዎች አሉታዊ ምሳሌነት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ስለ ኣመራር ምን ሊማሩ ይችላሉ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

ግሪክ ግዛተ ዐፄ (ክፍል 1)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የምዕራቡ ዓለም ባህል የኢትዮጵያን ባህል የለወጠባቸውን መንገዶች ግለጽ። መልካም የምትላቸው ለውጦች የትኞቹ ናቸው? መጥፎ የምትላቸውስ የትኞቹ ናቸው? ለ) ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት የተከሰቱ ነገሮች በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ተጽዕኖ የሚያደርሱት እንዴት ነው?

ሳይለወጥ እንዳለ የሚኖር ባህል የለም። የአንድ አገር ባህል በየጊዜው ይለወጣል። ለውጦች በአንድ ባህል ውስጥ ከሚገኙ እንቅስቃሴዎች ይመነጫሉ። ለአብነት ያህል ወጣቶች ከተለመደው ባሕል በተለየ መንገድ በማሰብ ለውጦችን ያመጣሉ። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ እነዚህ ለውጦች ከባህሉ ውጭ የሚመነጩ ናቸው። በተለይ ዛሬ ያለነው ብዙ ፈጣን ባህላዊ ለውጦች በሚካሄዱበት ዘመን ነው። ከእነዚህ ለውጦች አብዛኞቹ ከውጭ አገሮች ተጽዕኖ የሚመጡ ናቸው። ሰዎች የምዕራባውያኑን ባህል ለመከተል ሲሉ የእነርሱን አለባበስ፥ ሙዚቃና ቪዲዮ ይቀዳሉ። አንዳንዶቹ መልካም ቢሆኑ፥ ብዙዎቹ ግን መጥፎ ናቸው። በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ሁኔታው ተመሳሳይ እየሆነ ነው። ባለፉት 20 ዓመታት ኣምልኮንና መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ ያሉት አስተሳሰቦች በእጅጉ ተለውጠዋል። እነዚህም በዓለም አቀፍዋ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተከሰቱትን ለውጦች የሚያንጸባርቁ ናቸው።

በዓለም ታሪክ ውስጥ፥ የግሪክን ያህል በዓለም ላይ ብርቱ ተጽዕኖ ያስከተለ ባህል የለም። ዛሬ ስለ ሰዎች፥ ስለ ዲሞክራሲ፥ ስለ ስፖርት፥ ስለ መናገር ነጻነትና ስለ ትምህርት ያለን ግንዛቤ የመጣው በግሪክ ተወልዶ በዓለም ሁሉ ከተስፋፋው ባህል ነው። የታሪክ ምሑራን ይህንን ባህል «ሄለናዊነት» ብለው ይጠሩታል።

አይሁዶችን የተቆጣጠረውና ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ሦስተኛው መንግሥት የግሪክ ግዛተ ዐፄ ነበር። ታላቁ እስክንድር ትንሹን እስያና ፓለስቲናን ባሸነፈባት ወቅት የግሪክን ባህል ይዞ መጣ። ይህ ባህል በቀጣዩ 400 ዓመታት በመላው ዓለምና በአይሁዶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖን አስከትሏል። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፓና እስያ በኣንድ ግዛተ ዐፄ ሥር ሲዋሃዱ ሁለቱ በጣም የተለያዩ የአውሮፓና የእስያ ባህሎች እርስ በርስ ይታገሉ ጀመር፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- ዳንኤል ምዕራፍ 8ን አንብብ። የፋርስና የግሪክ መንግሥታት ግጭት የተገለጸው እንዴት ነው?

ለ150 ዓመታት ያህል የፋርስ መንግሥት የግሪክን መንግሥት ለማንበርከክ ቢሞክርም ሊሳካለት አልቻለም። ስለሆነም፥ የፋርስ መንግሥት መፈራረስ ሊጀምር፥ የታላቁ እስክንድር አባት በሆነው በፊሊፕ የሚመራው የግሪክ መንግሥት ማንሰራራት ጀመረ፡፡ በ338 ዓ.ዓ የተለያዩ የግሪክ ከተሞችና አውራጃዎች በሙሉ ተዋሃዱ። ፊሊፕ በ336 ዓ.ዓ ሲገደል፥ ልጁ ታላቁ እስክንድር ንጉሠ ነገሥት ሆነ። እርሱም ከሁለት ዓመት በኋላ የፋርስን መንግሥት መውጋት ጀመረ። በ331 ዓ.ዓ ትንሹ እስያን፥ ጳለስቲናንና ግብፅን ድል አድርጎ ያዘ።

ታላቁ እስክንድር ጳለስቲናን ድል ሊያደርግ አሳቡ የኢየሩሳሌምን ከተማ መደምሰስ ነበር። ነገር ግን የአይሁድ ትውፊት እንደሚለው በወቅቱ የአይሁድ ሊቀ ካህናት የነበረ አንድ ሰው ሃይማኖታዊ ልብሱን ተጎናጽፎ ወደ እስክንድር ዘንድ በመቅረብ፥ በዳንኤል 8 ላይ የተጻፈውንና ፋርስን እንደሚደመስስ የተነገረለትን ትንቢት አስነበበው። እስክንድር በሁኔታው እጅግ በመደነቁ ኢየሩሳሌምን እንደ ሌሎቹ ከተሞች ሳይደመስሳት ቀርቷል። እስክንድር የአይሁዶች አምላክ ሂድና አሸንፍ በማለት በራእይ እንደ ተገለጠለት ገልጾአል። ስለሆነም፥ ምንም እንኳ ጳለስቲናን የግሪክ መንግሥት አካል ቢያደርጋትም፥ አይሁዶች ከፊል ነጻነት ኖሯቸው የራሳቸውን ጉዳዮችና ሃይማኖታዊ ተግባሮች እንዲያካሂዱ ፈቀደላቸው።

ከዚያ በኋላ እክንድር ወደ ሰሜን ተመልሶ እስከ ሕንድ ድረስ የተለያዩ አገርችን ድል እየመታ ተጓዘ። እስክንድር ወደ ግሪክ በመመለስ ላይ ሳለ ብዙ አገሮችን ድል ካደረገ በኋላ በ323 ዓ.ዓ በሞት ተለየ። እርሱ ግን የገዛ ሕይወቱን ድል ማድረግ አልቻለም ነበር፡፡ ብዙ አልኮል ይጠጣ እንደ ነበር ይነገራል። የሞተው ገና በወጣትነቱ ስለ ነበር ታላቅ መንግሥቱን የሚረከብ የደረሰ ልጅ አልነበረውም። ነገር ግን የግሪክን ባህል ለማስተላለፍ ችሏል። ስለዚህ በመካከለኛው ምሥራቅ የመሠረተው ባህላዊ ጥምረት ለ1000 ዓመታት ሊቀጥል ችሏል።

ከእስክንድር ሞት በኋላ በግሪክ አመራር ውስጥ ቀውስ ተከሰተ። የእስክንድር ልጅ የተወለደው እርሱ ከሞተ በኋላ በመሆኑ ሥልጣን ለመጨበጥ ገና ብቁ አልነበረም። በመሆኑም አራት ጄኔራሎቹ የግሪክን መንግሥት ተከፋፈሉት። በመጀመሪያ ያሰቡት በእስክንድር ልጅ ሥልጣን ሥር ለመግዛት ነበር። ይሁንና የእስክንድር ዘሮች በሙሉ ስለ ተገደሉ፥ ሁሉም ጄኔራሎች በያዟቸው ግዛቶች ላይ ንጉሥ ሆኑ። የግሪክ መንግሥት መልክዐ ምድራዊ ውህደት አልነበረውም። ሆኖም ግዛተ ዐፄውን አንድ አድርጎ ያቆየው ባህላዊ ትስስሩና እነዚህ ጄኔራሎች ለሚገዛቸው አገሮች የግሪክን ባህል ለማስተላለፍ የነበራቸው ቁርጠኝነት ነበር።

በመጀመሪያ በአራቱ ጄኔራሎች መካከል ብርቱ የሥልጣን ትግል ተከስቶ ነበር፤ ይህም ሁሉም በግሪክ ግዛተ ዐፄ ላይ ታላቅ መሪ ለመሆን ይመኙ ነበር። በመጨረሻም፥ የግሪክ መንግሥት በሚከተለው ሁኔታ ተከፋፈለ። የመጀመሪያው ጄኔራል አንቲፓር ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ በግሪክና መቄዶኒያ ላይ ገዝቷል፡፡ ሁለተኛውና አንቲጎነስ የተሰኘው ጄነራል በትንሹ እስያ ላይ ነገሰ፡፡ ሲሉክስ የተባለው ሦስተኛው ጀኔራል በባቢሎንና በአካባቢዋ ላይ ነገሰ፡፡ አራተኛው ጀኔራል ፕቶሎሚ ሲሰኝ፥ ግብፅን ተቆጣጠረ። እነዚህ አራቱ ጀኔራሎች እያንዳንዳቸው የራሳቸውን ሥርወ መንግሥት መሥርተዋል። በመሆኑም የባቢሎንና ሰሜናዊ መካከለኛ ምሥራቅ ገዥዎች የሴሉሲጅ ገዥዎች ሲሰኙ፥ የግብፅና ደቡባዊ መካከለኛ ምሥራቅ ገዥዎች ፕቶሌሚክ ገዥዎች ተብለው ተጠርተዋል።

በአይሁዶች ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩት ሁለቱ ጄኔራሎች ፕቶሎሚና ሴሉከስ ነበሩ። ጳለስቲና ትገኝ የነበረችው ፕቶሎሚና ሴሉከስ በሚገዟቸው አገሮች መካከል ነበር። ውሾች አጥንት ሲያዩ እንደሚጣሉ ሁሉ፥ እስራኤል ብዙውን ጊዜ የእነዚህ ሁለት ጄኔራሎች መፋለሚያ ሜዳ ሆና ነበር። ከ331 እስከ 200 ዓ.ዓ ድረስ እስራኤል ግብፅን በሚገዙት ፕቶሎሚዎች ሥር ነበረች። ከ200 እስከ 64 ዓ.ዓ ድረስ ደግሞ ሴሉሲዶች አዲሷ መዲናቸው ከነበረችው ከአንጾኪያ ሆነው ጳለስቲናን ይቆጣጠሯት ነበር።

እግዚአብሔር በዚህ የግሪክ አገዛዝ ተጠቅሞበታል። የግሪክ መንግሥት በብዙ መንገድ ዓለምን ለመሢሑ ምጽአት አዘጋጅቷል።

1 በመላው የግሪክ ግዛት «ኮይኔ» በመባል የሚታወቀው ቀላል ቋንቋ ይነገር ነበር። እያንዳንዱ አገር የራሱ ቋንቋ ስለነበረው በቀላሉ ለመግባባትና አንድ ለመሆን አይችልም ነበር። ይህ ቀላል የግሪክ ቋንቋ በአገልግሎት ላይ በመዋሉ በግሪክና በሮም ግዛት ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ሰዎች በግሪክ ቋንቋ ይግባቡ ጀመር። ይህ በሁለት መንገድ ለወንጌል ጠቃሚ ሆኖ ነበር። በመጀመሪያ፥ ሐዋርያትና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወንጌልን ይዘው ከስፍራ ስፍራ በሚጓዙበት ጊዜ አዳዲስ ቋንቋዎችን መማር አያስፈልጋቸውም ነበር። ምክንያቱም በሚሄዱበት አገር ሁሉ የኮይኔ ግሪክ ይነገር ነበርና ነው። አዲስ ቋንቋ መማር ብዙ ጊዜ የማስተማርና የመስበክ አገልግሎቶችን እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንን ምሥረታ ያጓትታል። አስተርጓሚ መጠቀሙም ቢሆን የወንጌሉ መልእክት ግልጽ ሆኖ እንዳይተላለፍ ሊያደርግ ይችላል። እንደ ጳውሎስ ያሉ ሓዋርያት ከግብፅ እስከ ሮም፥ ከዚያም እስከ ሕንድ ድረስ በግሪክ ቋንቋ መጠቀም በመቻላቸው የወንጌሉን ምስክርነት ቀላል አድርጎታል።

ሁለተኛው፥ አዲስ ኪዳን ብዙ ሰዎች በሚያውቁት ኣንድ ቋንቋ ሊጻፍ ችሏል። ይህም የእግዚአብሔርን ቃል ወደ ተለያዩ ሰዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ ለመተርጎም የሚደረገውን አድካሚ ተግባር አስቀርቷል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሰዎች ሁሉ በአንድ ቋንቋ ለመግባባት ቢችሉ በኢትዮጵያ የወንጌል ስርጭት ቀላል የሚሆነው እንዴት ነው?

2 ግሪኮች ሰዎች ትምህርትና ሥልጣኔ በቀላሉ ለማግኘት በሚችሉባቸው ከተሞች እንዲቀመጡ ያበረታቱ ነበር። ታላቁ እስክንድር በሄደባቸው አገሮች የአካባቢውን ባህሎች በይፋ ባይደመስስም፥ የግሪክ ከተሞችን በመመሥረት የራሱን ባህል ያስፋፋ ነበር። ስለሆነም፥ ከግሪክ እስከ ሕንድና ግብጽ ድረስ፥ እስክንድርና ከእርሱ በኋላ የተነሡት የግሪክ መሪዎች የግሪክን ባህልና የአኗኗር ዘይቤ የሚያስተዋውቁ ቁልፍ ከተሞችን ይመሠርቱ ነበር። ምናልባትም በጥንቱ ዓለም ውስጥ ዐበይት የትምህርት ማዕከላት ከነበሩት የግሪክ ከተሞች እንዷ የግብፅ እስክንድርያ ሳትሆን አትቀርም። እነዚህ ከተሞች በራሳቸው ጉዳይ ላይ የመወሰን አካባቢያዊ ሥልጣን ነበራቸው። በሶርያ የምትገኘው አንጾኪያ ከእነዚህ ከተሞች አንዷ ስትሆን፥ በኋላም የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዐቢይ መዲና ሆናለች። ቤተ ክርስቲያን ጳውሎስና በርናባስ ወንጌልን ለተቀረው የዓለም ክፍል እንዲያደርሱ የላከቻቸው ከዚህች የግሪክ ከተማ ከሆነችው ከአንጾኪያ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በኢትዮጵያ የከተሞች ዕድገት የወንጌሉን ስርጭት ቀላል ያደረገው እንዴት ነው? ለ) በዚህ የከተሞች ዕድገት ምክንያት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተለወጠችው እንዴት ነው?

እግዚአብሔር የከተሞችን መስፋፋት ለወንጌሉ ስርጭት ተጠቅሞበታል። አንደኛው፥ ተራርቀው ከሚኖሩ ሰዎች ይልቅ በከተሞች ውስጥ ተቀራርበው የሚኖሩ ሰዎች ወንጌሉን ለመስማት የላቀ ዕድል አላቸው። ወደፊት እንደምንመለከተው፥ ጳውሎስ ወንጌሉን ይሰብክ የነበረው ከአንዱ ዐቢይ ከተማ ወደ ሌላው ዐቢይ ከተማ በመሄድ ነበር። ስለ ኢየሱስ የሚያወሳውን ወንጌል በከተሞች ሁሉ ለማሰራጨት የቻለው እነዚህን ከተሞች በመድረሱ ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ወንጌል ወደ ትንሹ እስያ በደረሰ በጥቂት ዓመት ውስጥ የአካባቢው ነዋሪዎች በሙሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ሰሙ ለመናገር ችሏል (የሐዋ. 9፡10)። ሁለተኛው፥ እነዚህ ከተሞች ከፍተኛ ሥልጣን ስላላቸው አዲስ በተመሠረተችው ቤተ ክርስቲያን ላይ የተቀናጀ ስደት እንዳይነሣ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል። የሮም መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ላይ የተቀናጀ ስደት ለማድረስ የሞከረው ቤተ ክርስቲያን በሚገባ ከተመሠረተች በኋላ ነበር።

ጳለስቲና በፕቶሎሚዎች አገዛዝ ሥር (ከ323–198 ዓ.ዓ.)

በጥቅሉ ሲታይ የፕቶሎሚያውያን አገዛዝ ለአይሁዶች መልካም ጊዜ ነበር። ፕቶሎሚ በ331 ዓ.ዓ. ወደ ኢየሩሳሌም በመዝመት ብዙ አይሁዶችን በግብጽ ወደምትገኘው ርእሰ ከተማው ምርኮኛ አድርጎ ወሰደ። ወዲያውም ነፃ ሕዝቦች መሆናቸውን በመግለጽ እንዳሻቸው ለመኖርና ኣምላካቸውን ለማምለክ እንደሚችሉ ገለጸላቸው። በእስክንድርያ ሕይወት መልካም በመሆኑ ሌሎች አይሁዶችም ወደዚያው ይፈልሱ ጀመር። ከዚህም የተነሣ፥ የከተማዪቱ አንዱ ክፍል የራሳቸው ሕገ መንግሥትና አመራር ባላቸው አይሁዶች ሊሞላ ቻለ። ብዙም ሳይቆይ በእስክንድርያ የሚገኙ አይሁዶች በአረማይስጥ ቋንቋ መናገራቸውን አቁመው በግሪክ ቋንቋ ይግባቡ ጀመር። በኋላም እስክንድርያ ከተማ ለክርስትና መስፋፋት ቁልፍ ድርሻ ካበረከቱት ከተሞች መካከል አንዱ ለመሆን በቅታለች።

ከዳግማዊ ፕቶሎሚያ (285-246 ዓ.ዓ) በተደረገላቸው ድጋፍ መሠረት በእስክንድርያ የነበሩት አይሁዶች የመጀመሪያዎቹን አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ ቋንቋ ተረጎሙ። በ72 ምሁራን የተተረጎመ በመሆኑ ይህ መጽሐፍ “የሰብዐ ሊቃናት ትርጉም” (በግሪክ 70) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። በኋላም መላው ብሉይ ኪዳን ወደ ግሪክ ቋንቋ ተተረጎመ። ይህን የግሪክ ብሉይ ኪዳን ትርጉም በግሪክና በሮም የተበተኑ አይሁዶችና ክርስቲያኖች ይጠቀሙበት ነበር። እንዲያውም፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሱ በርካታ ምንባቦች የተወሰዱት ከዚሁ ከሰብዐ ሊቃናቱ ትርጉም ነው። ከብዙ ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው የግእዝ መጽሐፍ ቅዱስ የተተረጎመው ከግሪኩ የሰብዐ ሊቃናት ትርጉም ነው፡፡ ለዚህም ነው የግእዙ (ኣማርኛው) መጽሐፍ ቅዱስ መዝሙረ ዳዊት ቁጥሮች አጠቃቀም ከዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ከተተረጎመው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለየው።

ቀጣዮቹ የፕቶሎሚ ነገሥታት ኢየሩሳሌም የተወሰነ ነጻነት ያላት ከተማ ሆና እንድትቀጥልና በሊቀ ካህናቱ እንድትመራ ፈቀዱ። አይሁዶች ከሴሉሲድ አገዛዝም ልዩ ድጋፍ ነበራቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ዳንኤል 11፡1-35 አንብቡ። ዳንኤል በፕቶሎሚና በሴሉሲድ(የሰሜን ነገሥታት) መንግሥታት መካከል እንደሚካሄድ ያመለከተውን ጦርነት ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

በ275 ዓ.ዓ. የግብፅ ፕቶሎሚዎች ከአንጾኪያ ሴሉሲዶች ጋር ጦርነት ገጠሙ። በመጀመሪያ ፕቶሎሚዎች ከዚያም ሴሉሲዶች ጦርነት ለመግጠም በጳለስቲና በኩል እያለፉ ሲሄዱ ጦርነቱ ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ ለ100 ዓመታት ቀጠለ። ምንም እንኳ ይሁዳ በእነዚህ ጠላቶች ባትጠቃም፣ አይሁዶች ከሁለቱ ቡድኖች አንዱን ለመምረጥ የተገደዱበት ጊዜ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ፥ ሠራዊቶቹ በጳለስቲን ምድር በኩል በሚያልፉበት ጊዜ ሕዝቡን መዝረፋቸውና መበዝበዛቸው እንዲሁም ግብር መጠየቃቸውና ወታደር መመልመላቸው አልቀረም። ይህም ለአይሁዶች የአሕዛብ ሠራዊት በምድራቸው ውስጥ እያቋረጡ ሲሄዱ መመልከት የሚያበላጭና ነፃ ሕዝብ ሳይሆኑ በአሕዛብ ቁጥጥር ሥር የሚኖሩ መሆናቸውን የሚያመለክታቸው ነበር። በዚህ ጊዜ በሚልክያስ ስለ መሢሑ መምጣት የተነገረው የተስፋ ቃል 200 ዓመት ያህል ሆኖት ነበር። ይህም አይሁዶችን ከአሕዛብ ኣገዛዝ ነፃ አውጥቶ እንደ ዳዊት ወይም ሰሎሞን ያለ ንጉሥ መጥቶ በእርሱ ሥር የከበረ ሕይወት እንዲኖሩ የሚያደርግ መሢሕ የሚመጣበትን ጊዜ እንዲናፍቁ ሳያደርጋቸው አልቀረም።

የውይይት ጥያቄ፡- አንድ ቀን ታላቅ እዳኝ መጥቶ ነፃ እንደሚያወጣህ የሚገልጽ የተስፋ ቃል ይዘህ በኢየሩሳሌም የምትኖር አይሁዳዊ ብትሆን፥ በዚህ የግሪክ አገዛዝ ዘመን ምን ዓይነት አስተሳሰብ ይኖርህ ነበር? ለ) የግሪክ መንግሥትና ባህል በኢየሩሳሌም ከተማ በነበሩት አይሁዶች ላይ ተጽዕኖ ያሳደረባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል የነበረው ዘመን

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ታሪካችን ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚፈጸሙት ነገሮች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? ለ) ታሪክን ማጥናት የሚጠቅመው ለምንድን ነው?

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸሙት ነገሮች ባለፉት 100 ዓመታት ከተፈጸሙት ድርጊቶች ጋር የሚተሳሰሩ ናቸው። የምኒልክ፥ የኃይለ ሥላሴ፥ የደርግና የኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመናት ዛሬ በአገሪቱ ውስጥ የሚፈጸሙትን ክስተቶች ይወስናሉ። የኢትዮጵያ ድንበሮች፥ የመሬት ይዞታ አመለካከቶች፥ የኦርቶዶክስና የእስልምና ሃይማኖት ግንኙነቶችና የመሳሰሉት ታሪካዊ መሠረት ያላቸው ነገሮች ናቸው። ስለዚህም ዛሬ ፍሬያቸውን እንመገባለን።

ይህም ሆኖ ዛሬ የሚከሰቱት ነገሮች ሁሉ የኢትዮጵያ ታሪክ ውጤቶች ብቻ አይደሉም። በሰፊው ዓለም ውስጥ የተፈጸሙት ነገሮችም በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል። በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አውሮፓውያን ኣፍሪካን በቅኝ ለመግዛት ያካሄዷቸው ተግባራት፥ ለምሳሌ ጣሊያኖች አንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎችን መግዛታቸው በዛሬዎቹ ክስተቶች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። በኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመን፥ በሩሲያና በአሜሪካ መካከል የነበረው ትግል ዛሬም በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ቀጥሏል። ለምሳሌ፥ የምዕራቡ ዓለም ፈሊጥ የሆነው ፋሽን፥ ቪዲዮና የእንግሊዝኛ ቋንቋ በወጣቶቻችን ስሜት ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ላይ ይገኛል።

በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ከአዲስ ኪዳን ዘመን በፊትም ሆነ በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ በእስራኤልና በሌሎች አገሮች ውስጥ ይካሄዱ የነበሩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን በምንገነዘብበት ጊዜ፥ ስለ አዲስ ኪዳንና የቤተ ክርስቲያን ዕድገት ግልጽ አሳብ ይኖረናል። ክርስቶስ በእስራኤል ኣገር በተወለደ ጊዜ አገሪቱ በሮማውያን ኣስተዳደር ሥር ነበረች። ክርስቶስ ከመወለዱ ከ400 ዓመታት በፊት በእስራኤልና በአሕዛቡ ዓለም የተፈጸሙት ክስተቶችም በእስራኤልና በኣይሁድ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል።

ጳውሎስ በገላትያ 4፡4-5 ላይ እንደ ገለጻው፥ ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ»። ጳውሎስ ይህን ሲል ክርስቶስ ወደ ምድር መጥቶ እንዲሞትና ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሠርት፥ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ሁሉም ነገር እንደ ተዘጋጀ መግለጹ ነበር። ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት ልታድግና በአንድ ትውልድ ዘመን ወንጌል በጥንቱ ዓለም እንዲህ ሊስፋፋ የቻለው ለምን ነበር? መልሱን የምናገኘው እግዚአብሔር የዓለምን ታሪክ ካደራጀበት ሁኔታ ነው። ምንም እንኳ ኢየሱስ ክርስቶስ በአዳምና በሔዋን፥ ወይም በዳዊት ወይም በኢሳይያስ ዘመን ወይም ዛሬ ሊመጣ ቢችልም፥ እነዚህ ሁሉ ጊዜዎች/ዘመኖች ከእግዚኣብሔር እይታ አንጻር ትክክል አልነበሩም። ነገር ግን በእስራኤልና በአሕዛብ አገሮች የነበረው ጊዜ ምቹ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ልጁን ላከው። ይህን ጊዜ ምቹ እንዲሆን ያደረጉት ነገሮች ምን ምን ነበሩ? ይህን ጥያቄ ለመመለስ የእስራኤል ሕዝብ በ586 ዓ.ዓ. በምርኮ ከተወሰደ በኋላ በዓለም ውስጥ የተፈጸሙትን ክስተቶች መመርመር ይኖርብናል።

የውይይት ጥያቄ፡– ዳንኤል ምዕራፍ 7ን አንብብና ዳንኤል በራእዩ የተመለከታቸውን የተለያዩ እንስሳት ዘርዝር። እነዚህ እንስሳት ያመለከቱት የትኞቹን መንግሥታት ነበር?

በባቢሎን ምርኮ ጊዜ እግዚአብሔር ለዳንኤል በቀጣይ 600 ዓመታት ውስጥ በአይሁዶች ታሪክ ውስጥ ስለሚፈጸሙት ነገሮች ገልጾለታል። በአራት እንስሳት የተመሰሉት አራት የተለያዩ የአሕዛብ መንግሥታት አይሁዶችን እንደሚገዙ እግዚአብሔር ለዳንኤል አሳይቶታል። አንበሳው ዳንኤል የነበረበትን የወቅቱን የባቢሎን መንግሥት ሲያመለክት፥ ድቡ የሜዶን/ፋርስ መንግሥት ነበር። ከባቢሎን በኋላ ሜዶን/ፋርስ ሁለተኛው የዓለም ኃያል አገር ለመሆን ችሏል። ነብር የግሪኮች መንግሥት ነበር። አራተኛውና እጅግ የሚያስፈራው እንስሳ የተመሰለው ደግሞ በሮም መንግሥት ተምሳሌት ነበር። እነዚህ አራት መንግሥታት የአይሁድን ሕዝብ ገዝተውት ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር የመሲሑንና የቤተ ክርስቲያንን መንገድ ለማዘጋጀት ሲል፥ እነዚህን መንግሥታት መልሶ ይቆጣጠር ነበር። እነዚህ መንግሥታት እያንዳንዳቸው እግዚአብሔር ለአይሁዶች በነበረው ታሪካዊ ዕቅድ ውስጥ የየራሳቸው ድርሻ ነበራቸው።

የባቢሎን መንግሥት (626 ዓ.ዓ. – 539 ዓ.ዓ.)

የውይይት ጥያቄ፡– 2ኛ ነገሥት 25ን አንብብ። ሀ) በይሁዳ ላይ ምን እንደ ተፈጸመ በአጭሩ ግለጽ። ለ) የባቢሎን ምርኮ የአይሁዳውያንን ሕይወት እንዴት የለወጠው ይመስልሃል? ሐ) ከመጽሐፉ መጨረሻ ላይ ያለውን ካርታ ተመልከትና በባቢሎን ግዛት ውስጥ የተካተቱትን ዘመናዊ ኣገሮች ዘርዝር።

አልፎ አልፎ የአሕዛብ አገሮች ከሚሠነዝሩባት ጥቃት ውጭ እስራኤል ለ900 ዓመታት ያህል (ከ1400-586 ዓ.ዓ.) ነፃ አገር ነበረች። አይሁዶች «የእግዚአብሔር ፈቃድ ሁልጊዜም ከውጭ አገሮች ጥቃት ይጠብቀናል። ተግባራችንም ሆነ ማንኛውንም ጣዖት ማምለካችን አሳሳቢ ጉዳይ አይደለም። እኛ የእግዚአብሔር ልዩ ሕዝብ ስለሆንን፥ ወደ ምርኮ ሊሰድደንና ሊያጠፋን አይፈልግም» ብለው ያስቡ ነበር። እግዚአብሔር ነቢያትን እየላከ ሕዝቡን እንደሚቀጣ ቢያስጠነቅቅም፤ ሕዝቡ አልሰሟቸውም። የባቢሎን ጦር በድንገት ኢየሩሳሌምን በመያዝ ከ605 እስከ 586 ዓ.ም ድረስ ሦስት ዐበይት ወረራዎችን አካሄደባት። በዚህ ጊዜ የይሁዳ አገር ፈጽማ ወደመች። ቤተ መቅደሱ ሲፈርስና የእንስሳት መሥዋዕቱ ሊቆም፥ ለ500 ዓመት ሲካሄድ የነበረው የቤተ መቅደሱ አምልኮ ተቋረጠ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሁልጊዜ በቅድስና ባይኖሩም እንኳ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል በመሆናቸው፥ እግዚአብሔር ለስደት አሳልፎ እንደማይሰጣቸው የሚያስቡት እንዴት ነው? ለ) የመጽሐፍ ቅዱስን ማስጠንቀቂያዎች ችላ እያልን፥ ክርስቲያኖች በመሆናችን ብቻ ነገሮች ቀላል እንደሚሆኑልን የምናስበው እንዴት ነው? ሐ) እግዚኣብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን ሕዝቡ የነበሩትን አይሁድ ወደ ምርኮ በመውሰድ ከቀጣበት ሁኔታ ምን እንማራለን?

የሰባ ዓመቱ ምርኮ የአይሁድ ሕዝቦችን ሕይወት ሙሉ በሙሉ የለወጠ ሂደት ነበር። ክርስቶስ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ የአይሁዶች አኗኗርና የአምልኮ ሁኔታ በዳዊትና በኢሳይያስ ዘመን ከነበረው የተለየ ነበር። በምርኮ ዘመን የተለወጡ አምስት ነገሮች ነበሩ።

1.  አይሁዶች «በዳዊት ልጅ» የሚመራ የራሳቸው ነፃ መንግሥት አልነበራቸውም። ከ166-63 ዓ.ም. ከነበሩት ጥቂት ዓመታት በስተቀር እስከ 1948 ዓ.ም. ባሉት 2500 ዓመታት፥ አይሁዶች በአሕዛብ አገዛዝ ሥር ነበሩ። ዘመኑ እያለፈ በሄደ ቁጥር አይሁዶች «የዳዊት ልጅ የሆነው መሢሑ» የሚመጣበትን ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ይናፍቁ ጀመር። ይሁን እንጂ ክርስቶስ መንግሥቱን ለመመሥረት እስከሚመለስበት ጊዜ ድረስ አይሁዶች በዳዊት ልጅ አይገዙም። 

2. አይሁዶች በቤተ መቅደስ እንስሳት በመሠዊያ ላይ በማይሠዉበት አገር፥ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበትን መንገድ ማግኘት ነበረባቸው። ይህ ሁኔታ ቀስ በቀስ አይሁዶች ምኩራቦችን ገንብተው በዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና የዳዊት መዝሙር ዝማሬ እንዲያደርጉ አስቻላቸው።

3. ኣይሁዶች በዓለም ሁሉ ተበተኑ። ከ1000 ዓመታት በፊት በትንሽዋ የእስራኤል አገር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች፥ በተለያዩ አገሮች ተበተኑ። በመጀመሪያ የሰሜኑ የእስራኤል ሕዝብ በአሦራውያን አማካይነት ሲበተን፥ በባቢሎናውያን ደግሞ ደቡባዊውን የይሁዳ ሕዝብ በተኑት። በዚህ ሁኔታ ቀስ በቀስ አይሁዶች በዓለም ሁሉ ላይ ተሰራጩ። ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን አይሁዶች ከስፔይን እስከ ሕንድ በሚደርስ ሰፊው የሮም ግዛት ውስጥ በነበሩ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ ይገኙ ነበር። ወደ ጳለስቲና የሚመለሱበት ሁኔታ ከተመቻቸ በኋላ እንኳ አብዛኞቹ አይሁዶች በአሕዛብ አገሮች የተመቻቸ ኑሯቸውን መምራታቸንው እንደቀጠሉ ነበር። በኣሕዛብ አገሮች ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች በጳለስቲና አገር እንደነበሩት አይሁዶች እምነታቸውን አጥባቂ አልነበሩም። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አብዛኛውን ጊዜ ምስክርነቷን የምትጀምረው ክርስቶስ መሲሕ መሆኑን አምነው ለመቀበል ዝግጁ በሆኑት በእነዚህ አይሁዶች ነበር። (የሐዋ. 14፡1፤ 21 አንብብ።)

4. አይሁዶች የእግዚአብሔርን ቃል ማክበርና በጥንቃቄ መታዘዝን ተማሩ። እንደ ዕዝራ የእግዚአብሔርን ቃል በጥንቃቄ የሚያጠኑ ሰዎች ነበሩባቸው። ይህም ጸሐፍት ብለው የሚጠሯቸውና የእግዚአብሔርን ቃል በሚገባ ያጠኑ የነበሩ አይሁዳውያን ምሁራን እንዲገኙ አደረገ። ሕዝቡም ቀደም ሲል ያልነበረውን የእግዚአብሔርን ቃል በትጋት የማጥናት ተግባር ያከናውን ጀመር። ከሁሉም በላይ ሕዝቡ በአሕዛብ አገሮች ሐሰተኛ በሆኑ ኣማልክትና ጣዖታት ተከብበው እያሉ እንኳ ጣዖታትን ከማምለክ ተቆጠቡ።

የአይሁድ ሃይማኖት ምሁራን ይህ ለእግዚአብሔር ቃል የነበራቸው ቅንአት፥ ሌሎች ሕግጋትንም እንዲያወጡ አደረጋቸው። እነዚህ ሕግጋት ሁለት ዓላማ ነበራቸው። አንደኛው፥ አይሁዶች በምርኮ አገር ከአሕዛብ ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ረዱዋቸው። ሁለተኛ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ሕግ ለመጠበቅ አስተዋጽኦ አድርገውላቸዋል። አንድ አይሁዳዊ የተጨመሩትን ሕግጋት ቢተላለፍ እንኳ፥ ከተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ስለማይወጣ እግዚአብሔር አይቀጣውም ነበር። እነዚህ የተጨመሩ ሕግጋት በክርስቶስ ዘመን ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይ ወሳኝ ሆነው መገኘታቸው አሳዛኝ ነበር።። 

5. የአይሁዶች ቋንቋ መለወጥ ጀመረ። እስከዚህ ጊዜ ድረስ አይሁዶች ይናገሩት የነበረው የዕብራይስጥ ቋንቋ ነበር። በአንጻሩ የሶርያ ቋንቋ የነበረውን አረማይስጥ ይናገሩ የነበሩት የተማሩና የንግድ ሰዎች ብቻ ነበሩ። አይሁዶች በመካከለኛው ምሥራቅ ሲበተኑ ግን የአረማይስጥን ቋንቋ ለመማር ተገደዱ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ፥ አይሁዶች የአረማይስጥን ቋንቋ እየለመዱ የዕብራይስጥን ቋንቋ እየረሱ ሄዱ። በክርስቶስ ዘመን የዕብራይስጥን ቋንቋ የሚናገሩ አይሁዶች ጥቂቶች ሲሆኑ፥ አረማይስጥ ግን ዋንኛው ቋንቋቸው ሆነ።

የፋርስ መንግሥት (539-331 ዓ.ዓ.)

የውይይት ጥያቄ፡– ዳንኤል 8ን አንብብ። ሀ) ዳንኤል በራእይ ያያቸው ሁለቱ እንስሳት ምንና ምን ነበሩ? ለ) ኢሳይያስ 45፡1-13ን ኣንብብ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከምርኮ ነፃ ያወጣል ያለው ማንን ነው? እግዚአብሔር እርሱን የማያመልከውን ቂሮስን የመረጠው ለምንድን ነው? ሐ) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካርታ ተመልከትና ፋርስን፥ ሜዶንን፥ እንዲሁም የግዛቱን ስፋት አሳይ። ዛሬ በሜዶንና ፋርስ ግዛት ውስጥ የሚገኙትን አገሮች ዘርዝር።

የሜዶንና የፋርስ መንግሥታት ኃይልን ከማግኘታቸው ከ200 ዓመታት በፊት፥ እግዚአብሔር ቂሮስ የተባለ ሰው እንደሚያስነሣ ለነቢዩ ኢሳይያስ ገለጠለት። ምንም እንኳ ቂሮስ እግዚኣብሔርን ባያውቅም፥ እግዚአብሔር ግን እርሱን ወደ መሪነት በማምጣት ሕዝቡን እንዲድዳቸውና እነርሱም ወደ አገራቸው ተመልሰው ቤተ መቅደሱንና ኢየሩሳሌምን እንዲገነቡ እንደሚያደርግ ተናገረ። ሁለተኛው ዐቢይ ግዛት የተዋሃደው የሜዶንና የፋርስ መንግሥት ነበር። የባቢሎን መንግሥት በሥልጣን ላይ የሚቆየው ለ70 ዓመት ብቻ ሲሆን፥ የሜዶንና የፋርስ መንግሥታት ግን ለ200 ዓመት ይቆያሉ። ይህም የፋርስ መንግሥት በእነዚያ ረዥም ዘመኖች በአይሁዶችና በባህላቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ለማሳደር ችሎ ነበር።

የሜዶንና የፋርስ መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጣው በፍጥነት ነበር። ፋርሳዊው ቂሮስ ሜዶንን ከፋርስ ጋር በማዋሃድ አነስተኛ የነበረችውን አገር በ550 ዓ.ዓ. ኃያል የዓለም አገር ሊያደርጋት ችሏል። ቂሮስ በ546 ዓ.ዓ. ታላቁን የሊዲያን መንግሥት ሲያሸንፍ፥ በ539 ዓ.ዓ. በአነስተኛ ጦርነት ባቢሎንን ወግቶ በማሸነፍ የፋርስና የሜዶን አካል አድርጓል። ስለሆነም በ11 ዓመት ውስጥ ቂሮስ ፋርስን በምሥራቅ ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ ወደ ምዕራብ ቱርክና ወደ ደቡብ ግብጽ ለማስፋፋት ቻለ። ይህም የፋርስን መንግሥት በዘመኑ ከነበሩት ሁሉ ታላቅ አድርጎታል።

የአይሁድ ትውፊት እንደሚለው፥ ቂሮስ ወደ ባቢሎን በመጣ ጊዜ የአይሁድ መሪዎች የእርሱ መምጣትና ስሙም እንኳ ሳይቀር ከ200 ዓመት በፊት በነቢዩ ኢሳይያስ መተንበዩን ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩት። ቂሮስ አይሁዶችን የደገፈውና በእግዚአብሔር ስም እንደሚያሸንፍ ከተናገረባቸው ምክንያቶች አንዱ ይህ ነበር።

የቂሮስ አገዛዝ ስልት ከባቢሎናውያኑ እና ከአሦራውያኑ በጣም የተለየ ነበር። ሰዎችን አስገድዶ ወደ ምርኮ ከመስደድ ይልቅ፥ በአገራቸው እየኖሩ ለፋርስ መንግሥት እንዲገዙ ያበረታታቸው ነበር። በመሆኑም፥ ቂሮስ በአዲሱ የፋርስ መንግሥት ውስጥ በነበሩት ሰዎች ተወዳጅነት ያተረፉለትን ሁለት ተግባራት አከናውኗል። አንደኛው፥ የየአገሮቹን ሃይማኖቶች ያከብር ነበር። ለምሳሌ፡- ወደ ባቢሎን ከተማ በገባ ጊዜ ማርዱክ የተባለው የከተማይቱ ጣዖት ሥልጣንን እንደሰጠውና የባቢሎን ንጉሥ ችላ ያለውን የማርዱክን አምልኮ ለመመለስ እንደ መጣ ተናግሯል። ለአይሁዶችም ይህንኑ ነበር የተናገረው። እግዚአብሔር የባቢሎንን ግዛት እንደሰጠው በመግለጽ፥ አይሁዶች ወደ አገራቸው ተመልሰው ለአምላካቸው ቤተ መቅደስ እንዲሠሩ ፈቀደላቸው።

ሁለተኛ፥ የባቢሎን ግዛት በተፈናቃዮች የተሞላ ሲሆን፥ ነዋሪዎቹም እዚያ በነበራቸው ሕይወት ደስተኞች አልነበሩም። ስለሆነም ቂሮስ አይሁዶችና ሌሎችም በባቢሎን የነበሩ ሕዝቦች ወደየአገሮቻቸው እንዲሄዱ ፈቀደላቸው። ይህም አይሁዶች በዘሩባቤል ወይም ሽሽባዛር (539 ዓ.ዓ.) [ዕዝራ 1:8፥ 11፥ በኋላም በዕዝራ (458 ዓ.ዓ) [ዕዝራ 7፡6-9] እና በነህምያ (445 ዓ.ዓ.) [ነህ. 2፡1) አማካይነት አይሁዶች ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ አደረገ። በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ቂሮስንና ሌሎች የፋርስ መሪዎችን እርሱ በሚፈልገው መንገድ እየመራቸው እንደሆነ ለአይሁዶች ግልጽ ነበር። በመጀመሪያው ዙር በሽሽባዛር አማካይነት 50,000 አይሁዶች ብቻ ተመለሱ። ይህም አብዛኞቹ አይሁዶች በባቢሎን የተደላደለ ሕይወት ይመሩ ስለነበር፥ ኋላቀርና በኢኮኖሚም ወደ ደቀቀችው ኢየሩሳሌም ለመመለስ አለመፈለጋቸውን ያሳያል። ይህ ዛሬ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ገጠሪቱ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተመልሰው ለመኖር ከማይፈልጉበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው። ይህ የዓለም ፍቅር አብዛኞቹ አይሁዶች እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሮቹ ተስፋ ወደ ገባላቸው አገር እንዳይመጡ ከለከላቸው።

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) ይህ የዓለምና የምድር በረከቶች ፍቅር ክርስቲያኖች እግዚኣብሔር የሚፈልገውን እንዳያደርጉ የሚከለክላቸው እንዴት ነው? ለ) ከዚህ ችግር ጋር የታገልኸው እንዴት ነው?

አነስተኛ የአይሁድ ማኅበረሰብ ወደ ይሁዳ ሲመለስ፥ ቅድሚያ የተሰጠው የቤተ መቅደሱ ግንባታ ጉዳይ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ተቃውሞ ተነሣበት። በአሦራውያን አስተዳደር ሥር በነበረችው ሰሜን ፍልስጥኤም ከፊል አይሁዳዊና ከፊል አሕዛብ የሆኑ ሰዎች ነበሩ። በኣዲስ ኪዳን ዘመን፥ እነዚህ ሰዎች ሳምራውያን ተብለው ተጠርተዋል። ሳምራውያን አይሁዶች ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ከተማ መልሰው ለመገንባት ቆርጠው እንደ ተነሡ ሲያዩ፥ መልእክተኞችን ልከው በሥራው ሊተባበሯቸው እንደሚፈልጉ አስታወቋቸው። እነዚህ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዶች፥ ሳምራውያኑ እንዳይቆጣጠሯቸውና ንጹሑ የአይሁድ አምልኳቸው እንዳይረክስ በመስጋት ይመስላል የሥራ ትብብሩን ለመቀበል አልፈለጉም። ይህም በኢየሩሳሌም በነበሩት አይሁዶችና በሰማርያ በነበሩት ከፊል አይሁዶች መካከል ለዓመታት የዘለቀ ግጭትን አቀጣጠለ።

የውይይት ጥያቄ፡- ዮሐንስ 4፡9 አንብብ። በዚህ ክፍል አይሁዶች በሳምራውያን ላይ የነበራቸው ጥላቻ የተመለከተው እንዴት ነው?

አይሁዶች ትብብራቸውን ላለመቀበል ሲወስኑ፥ በአገሪቱ የመንግሥት ሥልጣን የነበራቸው ሳምራውያን የቤተ መቅደሱን ሥራ ለማስቆም ጥረት አደረጉ። ይህም የቤተ መቅደሱ ሥራ ለ5 ዓመታት እንዲስተጓጎል አደረገ።

በፋርስ መንበረ ሥልጣን ላይ አለመረጋጋት ከተከሰተ በኋላ ንጉሥ ዳርዮስ (521-486 ዓ.ዓ.) ወደ ሥልጣን መጣ። ይህ ንጉሥ ሁለት ነገሮችን አድርጓል። አንደኛው፥ ለአካባቢው ገዥዎች የበለጠ የቁጥጥር ሥልጣን ሰጣቸው። ከደቡብ ሜሶፖታሚያ እስከ ግብጽ ድረስ ያለው ግዛት ሁሉ፥ «ከወንዝ ማዶ» ተብሎ ይጠራ ነበር። መንበረ ሥልጣኑም ሰማርያ ላይ ነበር። ዳርዮስ አብዛኛውን ጊዜ በፋርስ መንግሥት ላይ የሚያምጸውን የግብጽ አካባቢ ግዛት ይበልጥ ለመቆጣጠር ሲል ለኢየሩሳሌም መገንባት ድጋፉን ይሰጥ ጀመር። በዚህም መሠረት፥ በ520 ዓ.ዓ. አይሁዶች ቤተ መቅደላቸውን መልሰው እንዲገነቡ ፈቀደላቸው። የቤተ መቅደሱ ሥራ በ55 ዓ.ዓ. ተጠናቀቀ። ከብዙ ዓመታት በኋላ ታላቁ ሄሮድስ ይህንኑ ቤተ መቅደስ በማሻሻል በጥንቱ ዓለም ውስጥ ከነበሩት ሕንጻዎች እጅግ አስደናቂ ይዘት እንዲኖረው አድርጓል። ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ ያመልኩ የነበሩት በዚሁ ሄሮድስ አሻሽሎ ባሠራው ቤተ መቅደስ ውስጥ ነበረ። አይሁዶችም በዚህ ቤተ መቅደስ ይኩራሩ ነበር። ክርስቶስ ግን ሙሉ በሙሉ ስለሚወድምበት ጊዜ ተነበየ (ማቴ. 24፡2)። አይሁዶች በሮም ላይ ካመፁ በኋላ በ70 ዓ.ም. የሮም ሠራዊት ሁለተኛውን ቤተ መቅደስ ሙሉ በሙሉ ደምስሶታል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ አይሁዶች የብሉይ ኪዳንን ሥርዓት ተከትለው የሚያመልኩበት ቤተ መቅደስ የላቸውም። ብዙ ምሁራን አይሁዶች ክርስቶስ ዳግም ሊመለስ ሲል ቤተ መቅደሳቸውን እንደገና የመገንባት ፈቃድ እንደሚያገኙ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ይህም ቤተ መቅደስ ይፈርስና ክርስቶስ በሺሁ ዓመት መንግሥቱ ጊዜ ሌላ ቤተ መቅደስ ይገነባል (ራእይ 20፡4-6)። እነዚህ ምሁራን ሕዝቅኤል 40 ይህንኑ የሺህ ዓመቱን ቤተ መቅደስ እንደሚያመለክት ያምናሉ።

ከቤተ መቅደሱ ዳግም ግንባታ በኋላ አይሁዶች በብዙ ችግር ተወጠሩ። በንጉሥ አርጤክስስ (Xerxes) ዘመን (486–465 ዓ.ዓ.) በፋርስ ግዛት ውስጥ የነበሩትን አይሁዶች ሁሉ ለማጥፋት ጥረቶች ይደረጉ ነበር። ነገር ግን እግዚኣብሔር ሁኔታዎችን በመቆጣጠሩ ሐማና ሌሎችም የአይሁድ ጠላቶች ተገደሉ።

በእርጤክስስ (Artaxerxes) ዘመን (465-423 ዓ.ዓ.) ግብጽ በፋርስ መንግሥት ላይ ዐመፀች። በተመሳሳይ ዘመን በኢየሩሳሌም የነበሩ አይሁዶች በኢየሩሳሌም ከተማ ዙሪያ ያለውን ቅጥር እንደገና ለመገንባት ፈለጉ። በጥንት ዘመን ቅጥር የሌላት ከተማ ክብር ስለማይሰጣት እንደ መንደር ትቆጠር ነበር። በተጨማሪም ለጠላት ጥቃት ትጋለጥ ነበር። ስለሆነም አይሁዶች የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ለመሥራትና የጥንት ክብሯን ለመመለስ ተነሣሡ። እነዚህ ቅጥሮች ከጠላት ጥቃትም እንዲከላከሏት ፈልገው ነበር። ነገር ግን ያለ መንግሥት ፈቃድ ከተሞችን መገንባት የተከለከለ ነበር። ሳምራውያን አይሁዶች የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ዳግም እየገነቡ መሆናቸውን ሲገነዘቡ፥ ሥራውን አስቁመው ለፋርስ መንግሥት ሪፖርት ላኩ። አርጤክስስ አይሁዶች ሳምራውያን ከግብጾች ጋር ተባብረው ያምፁብኛል በሚል ፍርሃት ሥራውን አስቆመ። ሳምራውያን ለአሁዶች የነበራቸውን ጥላቻ ለማሳየት ሲሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው የተሠራውን ቅጥር አፈረሱ።

አርጤክስስ ለስድስት ዓመት ከግብጾች ጋር ተዋግቶ በመጨረሻው አሸነፋቸው። ከዚያም በ445 ዓ.ዓ ነገሮች የተለየ ቅርጽ ያዙ። ምሑራን አርጤክስስ፥ ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እንዲሠራ የፈቀደበትን ምክንያት አያውቁም። አንዳንዶች እንደሚሉት፥ በሰማርያ አነስተኛ ዓመፅ ስለነበረ የኢየሩሳሌምን ይዞታ ለማጠናከር ፈልጎ ይሆናል ይላሉ። ሌሎች ደግሞ አርጤክስስ የኢየሩሳሌምን መጠናከር የፈለገው ግብፆች ዳግም ሊያምፁ ይችላሉ ከሚል ፍርሃት ነው ይላሉ። በተጨማሪም፥ ኢየሩሳሌም በምቹ የንግድ ስፍራ የምትገኝ ከተማ በመሆኗ አርጤክስስ ለዚሁ ዓላማ ሊጠቀምባት ፈልጎ ሊሆን ይችላል ይላሉ።

እግዚአብሔር በነህምያ የተጠቀመው የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች መልሶ ለመገንባት ብቻ ሳይሆን፥ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ አይሁዶች መንፈሳዊ መነቃቃትን እንዲያመጣ ጭምር ነበር። እግዚአብሔር በነህምያና በዕዝራ በመጠቀም ሕዝቡ በአምልኮና በመታዘዝ ላይ እንዲያተኩር አድርጓል። እንደ ብዙዎቻችን ሁሉ ጊዜው እየገፋ ሲሄድ ሕዝቡ ከእግዚኣብሔር ይልቅ በግል ጉዳዮቻቸው ተጠምደው ነበር። ስለሆነም እግዚአብሔር መነቃቃትን አመጣላቸው።

ዕዝራ በአይሁድ ታሪክ ውስጥ ደምቀው ከሚታዩት ታላላቅ ሰዎች አንዱ ለመሆን በቃ። ሥራውም ለብዙ መቶ ዓመታት በአይሁዶች ሃይማኖታዊ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ሲያደርግ ቆይቷል። በእርሱ ሥራ ምክንያት በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል፡-

1. ዕዝራ አይሁዶች ለሙሴ ሕግ እንዲታዘዙ አስተምሯል። አይሁዶች በአሕዛብ አገሮች በመኖራቸው ምክንያት፥ የሙሴን ሕግ ለመጠበቅ ተቸግረው ነበር። አሁን ግን ወደ አገራቸው ስለተመለሱና ስራሳቸው ቤተ መቅደስ ውስጥ ስለሚያመልኩ– የሙሴን ሕግ ለመጠበቅ ይችሉ ነበር። በዕዝራ ዘመን የሙሴ ሕግ በፍልስጥኤም የሚኖሩ አይሁዶች የሚተዳደሩበት ሕገ መንግሥት ሆነ። በአካባቢያቸው በሚኖሩት አሕዛብ ባህል ከመዋጥ ይልቅ ዕዝራና ከእርሱ በኋላ የተነሡት መሪዎች ከአሕዛብ መለየቱ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አበክረው ተናግረዋል። ከአሕዛብ ጋር መጋባትንም ከልክለዋል።

2. ከጊዜ በኋላ ብሉይ ኪዳን የሚል ስም የተሰጣቸው መጻሕፍት እንዲሰበሰቡ ያደረገው ዕዝራ እንደ ሆነ የአይሁድ ትውፊት ይናገራል።

3. በዕዝራ አማካይነት የኢየሩሳሌም ይዞታ ተለውጧል። ኢየሩሳሌም ትንሽ መንደር ወይም የፖለቲካ ከተማ መሆኗ ቀርቶ፥ ሃይማኖታዊ ከተማ ሆነች። ስለሆነም፥ አይሁዶችና ኢየሩሳሌም በእንክብካቤ ይያዙ ጀመር። (ይህ በምኒልክና በኃይለ ሥላሴ ዘመን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ከፍተኛ ድጋፍ ያገኙ ከነበረበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው)። ግብር እንዲከፍሉ አይጠየቁም ነበር። ኣይሁዶች በካህናት አመራር- አብዛኛውን ጉዳያቸውን ለመቆጣጠር ይችሉ ነበር። ይህ ልዩ ሃይማኖታዊ ክንዋኔ በግሪክና በሮም ግዛቶችም ቀጥሎ ነበር። እግዚአብሔር በዚህ መንገድ ሕዝቡን በአሕዛብ ባህሎች ከመዋጥ ጠብቋል።

4. ዕዝራ በአይሁድ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱት ጸሐፍት ግንባር ቀደም ሰው ነበር። በዕዝራ ዘመን አብዛኛዎቹ አይሁዶች የዕብራይስጥ ቋንቋ ረስተው በአረማይስጥ ቋንቋ ብቻ ይግባቡ ስለነበር፥ ብሉይ ኪዳንን ማንበብ አይችሉም ነበር (ነህ. 8፡1-8 አንብብ)። ስለሆነም ጸሐፍት የሚባሉ እንደ ዕዝራ ያሉ ሃይማኖታዊ ምሁራን ለሕዝቡ የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ተርጉመው ያብራሩላቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ጸሐፍት የብሉይ ኪዳንን ሕግ እየተረጎሙ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ካልተጠቀሰው የአይሁዶች ታሪክ ጋር ያዛምዱ ነበር። ከዚያም አይሁዶች የብሉይ ኪዳንን ሕግ ከልብ እንዲታዘዙ ለማድረግ እነዚህ ጸሐፍት ሌሎች ሕጎችን ጨምረው ማስተማር ጀመሩ። እነዚህ የተጨመሩት ሕጎች «ሚሽና» በተባለ መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱ ሲሆኑ፥ በኋላ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን ያህል ጥብቅ እየሆኑ ሄዱ። ይህ ይሁዲነት የተባለው የአምልኮ ዘይቤ በቀጣይ ምእተ ዓመታት እየተስፋፋ ሄደ። ዛሬ ኦርቶዶክስ አይሁዶች የአምልኮ ዘዬአቸውን የሚያያይዙት ከዕዝራና ይህንኑ አዲስ አምልኮ ከመሠረቱት ጸሐፍት ጋር ነው። ሚሽና ጊዜው እያለፈበት ሲሄድ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች እነዚህን አዳዲስ ሕግጋት የሚያብራሩ አሳቦችን ጽፈው በታልሙድ ውስጥ እንዲካተት ኣደረጉ።

5. ምንም እንኳ አንዳንድ ምሁራን በምኩራብ የሚደረገውን አምልኮ መሪዎቹ እንደጀመሩት ቢናገሩም፥ ታላቁን ምኩራብ የመሠረተው ዕዝራ እንደሆነ ይታመናል። ይህ የአይሁዶችን ሃይማኖታዊ ሕይወት የሚቆጣጠሩ አንድ መቶ ሃያ ቁልፍ ሃይማኖታዊ መሪዎች የሚገኙበት መማክርት ነበር። ከጊዜ በኋላ ይህ ታላቅ ምኩራብ ተለውጦ የአይሁዶች ዐቢይ ፖለቲካዊ አካል ሆኗል። በክርስቶስ ዘመን፥ ይህ የመማክርት ጉባኤ የአይሁድ ሸንጎ (Sanhedrin) ይባል ነበር። ክርስቶስ የተመረመረውና የሞት ቅጣት የተበየነበት በዚህ ሸንጎ ፊት ነበር (ማቴ. 26፡59-60)።

የውይይት ጥያቄ፡– ማቴ. 2፡4፤ 5፡20፤ 9፡3፤ 16፡21፤ 23፡25 26፡51 አንብብ። የሕግ መምህራን (ጸሐፍት) ምን ምን ደረጃዎችና ሥልጣን እንደነበራቸው ግለጽ። ከክርስቶስ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንደነበራቸው ግለጽ።

በክርስቶስ ዘመን፥ የአይሁድን ሕይወት በሙሉ የሚዳስሱ እጅግ ብዙ ሕጎች ወጥተው ነበር። ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ እነዚህን ሕጎች ባለማክበራቸው ምክንያት ጸሐፍትና ቀናተኛ ፈሪሳውያን በቁጣ ገንፍለው በክርስቶስ ላይ ተነሡ። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ክርስቶስን ለመስቀል ከፈለጉባቸው ምክንያቶች አንዱ በብሉይ ኪዳን ላይ የጨመሯቸውን በርካታ ሕግጋት ስላላከበራቸው ነበር።

ዕዝራና የመጨረሻው የብሉይ ኪዳን ነቢይ የሆነው ሚልክያስ ከሞቱ በኋላ፥ የአይሁድ ሕዝብ፥ «400 የፀጥታ ዓመት» ወደሚባለው ዘመን ገቡ። በእነዚህ ዓመታት እግዚአብሔር ምንም ዓይነት አዲስ ቃል ሳይሰጣቸው በዝምታ ተቀመጠ። ብሉይ ኪዳን የሚጠናቀቀው «ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ» በፊት ኢሳይያስ እንደሚመጣ በመግለጽ ነው (ሚልክ. 4፡5)። ከዚህ የመጨረሻ ትንቢት በኋላ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ እንዲያዘጋጅ መጥምቁ ዮሐንስን እስከላከበት ጊዜ ድረስ ለ400 ዓመታት በነቢያቱ በኩል አልተናገረም (ማቴ. 1፡2-8)።

በፋርስ መንግሥት ጊዜ የታዩ ሌሎች ዕድገቶች

የፋርስ መንግሥት እየተስፋፋ ሲሄድ፥ ወደፊት በኣዲስ ኪዳን ዘመን ከፍተኛ ስፍራ የሚኖራቸው ሌሎች ነገሮች ይከሰቱ ጀመር። 

1. በአይሁዶችና በሰማርያ ሰዎች መካከል የማያቋርጥ መከፋፈል ተከሰተ። በሰማርያ ብዙ ሰንበላጦች ስለ ነገሡ፥ የታሪክ ጸሐፊዎች የነገሮችን የአፈጻጸም ቅደም ተከተል ለማወቅ ይቸገራሉ። ነገር ግን ነህምያ የኢየሩሳሌም መሪ በነበረበት ዘመን መጨረሻ ላይ ይሁን (ነህ. 13፡8) ወይም ከዚያ በኋላ፥ ምናሴ የሚባል አንድ ኣይሁዳዊ ከሰንበላጥ ቤተሰብ ጋር በጋብቻ በመዛመድ በቤተ መቅደስ ኣካባቢ መኖር ጀምሮ ነበር። እርሱም ሳምራዊት ሚስቱን ለመፍታት ባለመፈለጉ ከቤተ መቅደሱ ተባሯል። በዚህ ጊዜ ምናሴ ወደ ሰንበላጥ ተመለሰ። ሁለቱ ሰዎች በትብብር ከጥንታዊቷ የሴኬም ከተማ አጠገብ በሚገኘው የገሪዛም ተራራ ላይ ከኢየሩሳሌሙ ቤተ መቅደስ ጋር የሚመሳሰል ቤተ መቅደስ ገነቡ። ምናሴ የዚህ ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህናት ሆነ። ሳምራውያን የሚቀበሉት 39ኙን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሳይሆን፥ 5ቱን የሙሴ መጻሕፍት ብቻ ነበር። ይህ እስከ ዛሬ ድረስ ያለው የአምልኮ ሥርዓት በኢየሩሳሌም በሚኖሩ አይሁዶች ዘንድ የተወገዘ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ዮሐ 4፡19-24 አንብብ። ሀ) ይህ ተቀናቃኝ የአምልኮ ስፍራና ሥርዓት በዚህ ታሪክ ውስጥ የታየው እንዴት ነው? ለ) ክርስቶስ እውነት ማን ዘንድ እንዳለና እውነተኛ አምልኮ ምን ዐይነት እንደ ሆነ የገለጸው እንዴት ነው? 

2. በዚህ ጊዜ የሊቀ ካህናቱ ኃይል እየበረታ ሄደ። የፋርስ መንግሥት ለይሁዳ ሃይማኖታዊ መንግሥት የበለጠ ኃይል በመስጠቱ፥ ሊቀ ካህናቱ የአይሁድን ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን ፖለቲካውን ጭምር ሊቆጣጠር ቻለ። ከፋርስ መንግሥት ጀምሮ እስከ 70 ዓ.ም. ድረስ ሊቀ ካህናቱ የአይሁድ ሕዝብ የፖለቲካ መሪም ጭምር ነበር። ይህም በአዲስ ኪዳን ክርስቶስ በሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ፊት ለምርመራ በቀረበበት ጊዜ ተስተውሏል (ማቴ. 26፡57)።

3. አይሁዶች ራሳቸውን እያሳዩና ፀረ አሕዛብም እየሆኑ መጡ። እግዚአብሔር አይሁዶችን የጠራቸው ለአሕዛብ ብርሃን እንዲሆኑ ነበር (ኢሳ. 42:6-7)። እግዚአብሔር የፈለገው አይሁዶች በሥነ ምግባራቸውና በአምልኳቸው ንጹሓን እንዲሆኑና ስለ እርሱ ለአሕዛብ እንዲመሰክሩ ነበር። አይሁዶች ግን ለንጽሕናቸው በማሰብ ሌላ መንገድ መረጡ። ከአሕዛብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ላለማድረግና አይሁዳዊነታቸውን አጉልተው ለማሳየት ፈለጉ፡ በክርስቶስ ዘመን፥ እግዚአብሔር አሕዛብን የፈጠረው ሊፈርድባቸው ብቻ ነው የሚል አመለካከት የያዙ አይሁዶች ነበሩ። ብዙ አይሁዶች እግዚኣብሔር ለአሕዛብም ዕቅድ እንዳለው ወይም ከእርሱ ጋር ኅብረት ያደርጉ ዘንድ እንደሚፈልግ አያምኑም ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖች ከማያምኑ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ባለድረግ ክርስቶስ የሞተላቸውን ወገኖች ሊጠሉ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች በምሳሌዎች አብራራ።

4. ምኩራብ የአይሁድ ሕይወት ማዕከል ሆነ። ምሑራን ምኩራቦች መቼ እንደ ተጀመሩ አያውቁም። የአይሁድ ትውፊት እንደሚለው ከሆነ በባቢሎን ምርኮ ወቅት ተጀምረው በፋርስ መንግሥት ዘመን ሊስፋፉ ችለዋል። ምኩራብ ማለት «ማኅበረ ምእመናን» ማለት ነው። ይህ የአይሁዶች ስብስብ ሲሆን፥ በኋላ ምኩራብ የሚለው ቃል አይሁዶች ለአምልኮ የሚሰባሰቡበትን ስፍራ በማመልከት አገልግሏል። አይሁዶች በተበተኑባቸው አገሮች ሁሉ ምኩራቦችን ማነጽ ጀመሩ። ምንም እንኳ በእነዚህ ምኩራቦች ውስጥ የእንስሳት መሥዋዕቶች ባይቀርቡም፥ አይሁዶች እየተሰባሰቡ የብሉይ ኪዳኑን አምላክ ያመልኩ ነበር። ዛሬም እንኳ ቁጥራቸው በርከት ያለ ኣይሁዶች በሚኖሩባቸው ኣገሮች ምኩራቦችን ይሠራሉ። በዚያም የብሉይ ኪዳንን ሕጎች የሃይማኖት መሪዎችን ሕግ ለልጆቻቸው ያስተምራሉ። በዚህ ዓይነት አይሁዶች በየትኛውም የዓለም ክፍል ሲቀመጡ ለ2500 ዓመታት ያህል የዘርና የሃይማኖት መለያቸውን ጠብቀው ቆይተዋል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ወንጌልን ለጥንቱ ዓለም በሰበከበት ጊዜ፥ መጀመሪያ ይሰብክ የነበረው በምኩራቦች ነበር (የሐዋ. 14:1)። እነዚህ ምኩራቦች ለጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የስብክት ሞዴሎች ሆነዋል። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የኣምልኮ ስልት ከምኩራብ የተወሰደ ይመስላል። በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል የሚያመለክተው ሕንፃውን ሳይሆን የክርስቶስ ተከታዮችን ነበር። እንዲያውም የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የማምለኪያ ሕንፃ ስላልነበራት ስብሰባው የሚካሄደው በግለሰብ ቤቶች ነበር። የአምልኮ ሕንፃዎች መሠራት የጀመሩት ክርስቶስ ከሞተ ከአያሌ መቶ ዓመታት በኋላ ነበር።

5. አረማይስጥ የአይሁዶች የኣፍ መፍቻ ስለመሆኑ፡- በክርስቶስ ዘመን በጳለስቲና ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች በብሉይ ኪዳን ዘመን ይነገር የነበረውን የዕብራይስጥ ቋንቋ ሳይሆን የአረማይስጥን ቋንቋ ይጠቀሙ ነበር። እንደ ግእዝ ቋንቋ ሁሉ፥ ዕብራይስጥም ለንግግር የማይውል ቋንቋ ሆኖ ነበር።

6. ሁለት ዐበይት የአይሁድ እምነት ማዕከላት ተመሠረቱ። ዋንኛይቱ የዳዊት ከተማ የምትባለውና የይሁዳ ታሪካዊት መዲና የሆነችው ኢየሩሳሌም ነበረች። በፋርስ መንግሥት ዘመን ግን ጥቂት አይሁዶች የሚኖሩባት አነስተኛ ከተማ ነበረች። እንዲያውም ብዙ አይሁዶች በዚያ ለመኖር ስላልፈለጉ ነህምያ በይሁዳ የነበሩ አይሁዶች ዕጣ እንዲያወጡና ዕጣው የወጣላቸው ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው እንዲኖሩ ለማድረግ ተገድዶ ነበር (ነህ.11፡1-4)።

ሁለተኛዪቱ ዐቢይ ማዕከል ባቢሎን ነበረች። በፋርስ መንግሥት ዘመን አይሁዶች በባቢሎን በልጽገው ይኖሩ ነበር። አይሁዶች እንደ ጉራጌ ሕዝቦች የንግድ ስጦታ ስለ ነበራቸው፥ ብዙ አይሁዶች ሀብት አፍርተው ነበር። በባቢሎን ብዙ አይሁዶች ይኖሩ ስለ ነበር፥ ባቢሎን የሃይማኖቱ ማዕከል ሆነች። በባቢሎን የነበሩት አይሁዶች የራሳቸውን ባሕልና ሃይማኖታዊ ትምህርት ያሳድጉ ነበር። እንደ ዕዝራ ያሉ ሰዎች አይሁዶች በባቢሎን ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው እንዲኖሩ ለማድረግ ጥረዋል። በኢየሩሳሌም የነበሩ አይሁዶች ችግር በገጠማቸው ጊዜ፥ በባቢሎን (ዕዝራ) እና የፋርስ መዲና በሆነችው ሱሳ (ነህምያ) የነበሩት እነዚህ ሰዎች ነበሩ የረዷቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህ ተጽዕኖዎችና የፋርስ ግዛት ዕድገቶች በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንዴት እንደታዩ ምሳሌዎችን በመስጠት አብራራ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)