በፔንታቱክ ውስጥ የሚገኙ የሥነ ጽሑፍ ዓይነቶች

ፔንታቱክ በአንድ ጸሐፊ (ሙሴ) የተጻፈ የቅዱሳት መጻሕፍት አንድ ክፍል ቢሆንም፥ በውስጡ አራት የተለያዩ የሥነ-ጽሑፍ ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡ አንድ የተወሰነ ክፍል ወስደን ለመተርጎም በምናጠናበት ጊዜ ሰሚገባ እንተረጉመው ዘንድ የሥነ-ጽሑፍ ዓይነት ወስነን በዚያው መልክ መተርጎም ይገባናል። በፔንታቱክ ውስጥ አራት ዋና ዋና የሥነ-ጽሑፍ ዓይነቶች ይገኛሉ።

፩. የታሪክ ጽሑፎች፡- በብሉይ ኪዳን ውስጥ በብዛት የምናገኘው የሥነ -ጽሑፍ ዓይነት የታሪክ ጽሑፍ ወይም ትረካ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችንን በአጠቃላይ በሚመለከትም ይህ እውነት ነው። የብሉይ ኪዳንን ሥነ ጽሑፍ ስንመለከት ከመቶ አርባው እጅ (40%) ትረካ ነው። በታሪክ ጽሑፎች ውስጥ የቅዱሳት መጻሕፍት ጸሐፊው ማንኛውም ሰው በሚረዳው በቀላል ቋንቋ ታሪኩን ይተርካል። የሚናገረውም ምን እንደተፈጸመ ነው። ይህም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስን ልዩ የሚያደርገው የሚናገረው ታሪክ ተራ ያለመሆኑ ነው። ታሪኮቹ የተጻፉት በድሮ ጊዜ ምን እንደተፈጸመ ሊነግሩን ብቻ አይደለም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሮሜ 15፡4 እና 1ኛ ቆሮ. 10፡11 አንብብ። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ዛሬ ለእኛ ያላቸው ዓላማ ምንድን ነው?

እንዳንድ ምሁራን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክን «የድነት (ደኅንነት) ታሪክ» ብለው ይጠሩታል። ሌሎች ደግሞ «የእግዚአብሔር ታሪክ» ይሉታል። የታሪክ ጽሑፎች ዋና ዓላማ እግዚአብሔር በፍጥረት ውስጥና በሕዝቡ መካከል ሲሠራ ማሳየት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዳር እስከ ዳር የምናየው አንድ ዋና ዓላማ እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ በተለያዩ ሰዎች ሕይወትና በልዩ ነገድ ውስጥ ሲሠራ ድነትን (ደኅንነትን) እየገለጠ መሆኑን ነው፤ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ከዚህ በፊት ስለተፈጸሙት እውነተኛ ታሪካዊ ክስተቶች ቢሆንም ጸሐፊው ስለ እነርሱ በሚጽፍበት ጊዜ ሁለት ዓላማዎችን ይዞ ነበር። የመጀመሪያው፥ ባለፈው ጊዜ ምን እንደተፈጸመ በትክክል መናገር ሲሆን፥ ሁለተኛው ደግሞ፥ የእግዚአብሔር ሰዎች ባለፉት ጊዜያት ከኖሩት ሰዎች አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ምሳሌነት በመማር እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕይወት እንዴት መኖር እንደሚችሉ ለማሳየት ነው። ለምሳሌ፡- ሳምሶን በአሉታዊ ምሳሌነቱ ትምህርት ልናገኝበት ለምንችለው ታሪክ አንድ ጥሩ ምሳሌ ነው (መሳ. 13-16)። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን፥ ሳምሶን በፍትወተ ሥጋ ኃጢአት በመውደቁ ሕይወቱን እንዴት እንዳጠፋ በመመልከት። ሕይወታችንና አገልግሎታችን እንዳይበላሽ በፍትወተ ሥጋ ኃጢአት እንዳንወድቅ መጠንቀቅ እንዳለብን እንማራለን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንዳንድ ክርስቲያን መሪዎች ሳምሶን በወደቀበትአኳኋን የሚወድቁት እንዴት ነው? ለ) ከሳምሶን ሕይወት መጥፎ ምሳሌነት ምን ሊማሩ ይገባ ነበር? 

ከታሪኮች በጎ ምሳሌነትም ልንማር ይገባናል። ለምሳሌ፥ አብርሃም ይስሐቅን ለመሠዋት ከፈቀደበት ታሪክ እግዚአብሔር ከማንኛውም ነገር ይልቅ ከቤተሰባችንም በላይ እንዴት እርሱን መውደድ እንዳለብን እንደሚፈልግ እንማራለን (ዘፍ. 22)።

የብሉይ ኪዳንን ታሪካዊ ክፍሉች የምንተረጉምባችው በርካታ መመሪያዎች አሉ። ከዚህ በታች የተሰጡት እግዚአብሔር ከታሪክ ውስጥ ምን ሊያስተምረን እንደሚፈልግ ለመረዳት እንድንችል ሁል ጊዜ በአእምሮአችን ውስጥ ልንጠብቃችው ከሚገቡን ነገሮች ጥቂቶቹ ናቸው።

 1. የብሉይና የአዲስ ኪዳን ታሪኮችን መረዳት የሚገባን በሦስት የተለያዩ ደረጃዎች ነው። በመጀመሪያ፥ እያንዳንዱ ታሪክ ከፍተኛ ደረጃ አለው። ታሪኩ በዚህ ደረጃው ስለ እግዚአብሔር ሰፊ ነገር ያስተምረናል። በዚህ ደረጃ ጸሐፊው ሊነግረን የሚፈልገው፥ እግዚአብሔር በአንድ ሕዝብ ወይም በግለሰቦች ሕይወት ውስጥ ሊሠራ ያለውን ዓለም አቀፋዊ ዕቅድ ነው። አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ስለ እግዚአብሔር አካላዊ ሕልውና፥ ዓለምን ስለ መፍጠሩ፥ ስለ ሰው ልጅ ክፋትና በእግዚአብሔር ስለ መቤዠት አስፈላጊነት አንዳንድ ነገሮችን ያስተምረናል። ይህ ከፍተኛ ደረጃ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ለማስተካከል ስለ ሚሰጠው መሢሕም ይናገራል።

የውይይት ጥያቄ፥ አንድ የብሉይ ኪዳን ታሪክ ምረጥ። ይህ የመረጥከው ታሪክ (ስለ እግዚአብሔር ባሕርይና ዓላማ፥ ከሰው ልጅ ጋር አብሮ ስለ መሥራቱ፥ ለስው ልጅ ኃጢአተኛነት ወይም እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ለመዋጀት ስላለው ዕቅድ ምን ያስተምረናል?

ሁለተኛው፥ የታሪኩ መካከለኛ ክፍል ነው። ይህ ደረጃ ማዕከላዊ የሚያደርገው በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የነበሩትን እስራኤልን ነው። በአዲስ ኪዳን ይህ ደረጃ የሚያተኩረው በኢየሱስና በቤተ ክርስቲያን ጅማሬ ላይ ነው። የብሉይ ኪዳን ታሪክ የሚያተኩረው በእስራኤል ሕዝብ አካባቢ ነው። የእስራኤል ሕዝብ በአብርሃምና በዘሮቹ እንዴት እንደተጀመረ በዘፍጥረት እናነባለን። ከዘጸአት ጀምሮ እስከ 2ኛ ዜና ባለው ክፍል ደግሞ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ የተስፋይቱን ምድር እንዴት እንደሰጣቸው፥ በዳዊት በኩል የተሳካላቸው ሕዝብ አድርጎ እንዴት እንደለወጣችው፥ ሕዝቡ እንዴት በኃጢአት እንደወደቁና እግዚአብሔር እንደቀጣቸው እንመለከታለን። አብዛኛውን ጊዜ የብሉይ ኪዳን ታሪኮች እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር እንዴት ይሠራ እንደነበረ ያመለክታሉ። ስለዚህ አንድን ታሪክ በምናጠናበት ጊዜ እግዚአብሔር ስለ እስራኤል ሕዝብ ምን እንደሚል መገመት አለብን።

የውይይት ጥያቄ፥ ሌላ የብሉይ ኪዳን ታሪክ ምረጥ። ያ ታሪክ በእስራኤል ሕዝብ አጠቃላይ ታሪክ ላይ ምን የሚጨምረው ነገር አለ?

ሦስተኛው፥ የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ የተሟላ የሚያደርጉት የግለሰቦች ታሪኮች አሉ። የአብርሃም፥ የሙሴ፥ የዳዊት፥ ወዘተ ታሪኮች ተጽፈው ይገኛሉ። ከእነዚህ ታሪኮች በርካታ መንፈሳዊ እውነቶችን እንማራለን።

እያንዳንዱ የግለሰብ ታሪክ የመጽሐፍ ቅዱስ ትረካ የተመሠረተበት ነው። ጸሐፊው የእያንዳንዱን ግለሰብ ታሪክ ሲጽፍ ትልቅ ዓላማ ነበረው። ሊነግረን የፈለገው የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ ቢሆንም፥ የእያንዳንዱ ግለሰብ ታሪክ የሚጫወተው ትልቅ ሚና አለው፤ ነገር ግን ከዚህም በላይ ጸሐፊው ሊነግረን የፈለገው ስለ እግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር ስላለው ግንኙነት ነው።

ስለ እግዚአብሔር ማስተማር 

       ስለ እስራኤል ማስተማር 

                ስለ ግለሰቦች ማስተማር

 1. የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች በትምህርት ቤት እንደምናጠናቸው ዓይነት የጥንት ሰዎች ታሪክ ብቻ አይደሉም። ይልቁንም እግዚአብሔርን ለመግለጥና ለሰዎች በሰዎች በኩል ምን እንዳደረገ የሚነግሩን ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት በእግዚአብሔር ላይ እንጂ ሰዎች ባደረጉት ነገር ላይ አይደለም። 
 2. በብሉይ ኪዳን የታሪክ ጽሑፎች ውስጥ የቃላትን ተምሳሌታዊ ትርጉም መፈለግ የለብንም። ታሪኩን ልክ ተጽፎ እንዳለ በቀጥታ ለመረዳት መሞከር ያሻል። ይህም ማለት ድርጊቱ በተፈጸመበት ታሪካዊ መሠረት ልንረዳው ያስፈልጋል ማለት ነው። ለመረዳት የማንችላቸው ባሕላዊ ነገሮች ካሉ ለመረዳት መሞከር አለብን። አንድን ታሪክ ከመተርጎማችን በፊት ባሕላዊ ነገሮችን ስለ መረዳት አስፈላጊነት ጥሩ ምሳሌ የሚሆንን ቦዔዝ በምሽት መጎናጸፊያውን በሩት ላይ ስለማኖሩ የሚናገረው ታሪክ ነው። በአይሁድ ባሕል ይህ አንድ ሰው የማግባት መግለጫ ነው (ሩት 3፡9)። እነዚህን የተለያዩ ባሕላዊ ተግባሮች ለመረዳት ካልቻልን፥ በታሪኩ ውስጥ ልንረዳቸው የማንችላቸው በርካታ ነገሮች ይኖሩና የእግዚአብሔርን ሥራና በታሪኩ ውስጥ በተመለከትነው መንገድ አንድን ነገር የፈጸመበትን ምክንያት ምን እንደሆነ ሳንረዳ እንቀራለን። ታሪኩን ለማሟላት አንዳንድ ነገሮችን በመገመት የራሳችንን አስተሳሰብ እንዳንጨምር መጠንቀቅ አለብን።
 3. አንዳንድ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ዋናውን ትምህርት በቀጥታ አያስተምሩም። እንደ አንዳዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ የማስተሪያ ክፍሎች፥ (ለምሳሌ፡- ሮሜ) እግዚአብሔር እንድናውቅ የሚፈልገውን ነገር በቀጥታ አይናገሩም። ይልቁንም በታሪኩ ውስጥ ያለውን ትምህርት የምናገኘው በተዘዋዋሪ መንገድ ነው። ብዙውን ጊዜ ታሪኮቹ በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚገኙ ቀጥተኛ ትምህርቶችን ይገልጻሉ። ለምሳሌ፡- በዳዊትና በቤርሳቤህ ታሪክ ውስጥ ዝሙት ስሕተት እንደሆነ በቀጥታ አልተናገረም። ይህ ዘጸ. 20፡14 ላይ በቀጥታ ተነግሯል። ይህ ታሪክ ግን በተዘዋዋሪ መንገድ እግዚአብሔር ዝሙትን እንደሚጠላ ያስተምራል።
 4. እያንዳንዱን ታሪክ ለሥነ- ምግባር ወይም ለማስተማሪያነት ከመፈፈለግ ይልቅ አንድ ታሪክ የሌላ ትልቅ ታሪክ ክፍል አካል መሆኑንና ዋናው ትኩረቱም የትልቁን ታሪክ ዋና ትምህርት ማግኘት እንጂ ትንሹ ታሪክ ላይ እንዳልሆነ ልናስታውስ ያስፈልገናል።
 5. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ታሪኮች እያንዳንዳቸው መንፈሳዊ መመሪያን ለማስተማር የተመረጡ ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ በርካታ ታሪኮች ነበሩ። አንድን ታሪክ በተለይ የመረጡበት ምክንያት ምንድን ነው? ምክንያቱም እነዚያ ታሪኮች የሥነ ምግባር ወይም መንፈሳዊ ትምህርት ለማስተማር የተመረጡ ነበሩ፤ ስለዚህ አንድ ታሪክ በባሕላዊ መልኩ አንድ ጊዜ በግልጽ ከተረዳነው በኋላ ከታሪኩ የሚገኘውን ዋና መንፈሳዊ ትምህርት መፈለግ አለብን። ይህ ትምህርት ብዙ ጊዜ የሚገኘው በታሪኩ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ባደረጉት ምርጫ ወይም በፈጸሙት ተግባር ነው። ታሪኩን በመረዳት ሂደት ውስጥ ራሳችንን በውስጡ በማስገባት በዚያን ጊዜ የምንኖር ብንሆን ኖሮ ምን ይሰማን ወይም ምን እናደርግ ነበር? ብሎ መጠየቅ ብዙ ጊዜ በጣም ጠቃሚ ነው።
 6. በትረካው ጽሑፍ ውስጥ ጸሐፊው የተፈጸመውን ነገር በትክክል የሚገልጽ መሆኑን መገንዘብ መልካም ነው። እርሱ ይህ ጥሩ ነው ላይል ይችላል። ለምሳሌ፡- በዘፍ. 38 ይሁዳ ሴተኛ አዳሪ ናት ብሎ ከገመታት ሴት ጋር እንደ አመነዘረ እናነባለን። ይህ ስሕተት እንደሆነ ከሌሎች የቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርቶች በግልጽ እንረዳለን። የጸሐፊው ትኩረት ግን ድርጊቱን መግለጥ ነው እንጂ የሰውዬውን ተግባር መደገፉ አልነበረም፤ ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ በምንመዝንበት ጊዜ ጸሐፊው ዝም ብሉ የተፈጸመውን ድርጊት መግለጥ (ለምሳሌ የአንድን ግለሰብ ኃጢአት) ወይም እነዚያ ታሪኮች የተከበሩና ልንከተላችው የሚገባን መሆናቸውን እያስተማረን እንደሆነ መገንዘብ አለብን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘፍ. 9፡20-27 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ቁጥሮች የተነገረው ታሪክ ምንድን ነው? ለ) በዚህ ታሪክ ውስጥ ልንረዳቸው የሚያስፈልጉ ባሕላዊ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? ሐ) የዚህ ታሪክ የሥነ-ምግባር ትምህርት ምንድን ነው? መ) የሥነ-ምግባር ትምህርቱ የተገኘው ከአዎንታዊ ነው ወይስ ከአሉታዊ ተግባር? አብራራ። ሠ) ጸሐፊው በቀጥታ ስሕተት መሆኑን የማያሳየው፥ ነገር ግን ከሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የምንረዳው ምን ድርጊት ተገልጧል?

፪. ግጥምና ቅኔ፡- በፔንታቱክ ውስጥ የጥንት የዕብራውያን ንግጥምና ቅኔ ተሠራጭቶ እናገኛለን። ሥነ-ግጥምና ቅኔ በተለያዩ ባሕሎች ውስጥ የተለያየ ገጽታ ስላለው፥ አይሁድ እንዴት እንደሚጠቀሙበት ልንገነዘብ ያስፈልጋል። ቆየት ብለን እንደ መዝሙረ ዳዊትና መጽሐፈ ምሳሌ ያሉትን መጻሕፍት በምናጠናበት ጊዜ ሥነ-ግጥምና ቅኔ እንዴት እንደሚተረጎሙ የሚያስረዱ ሕግጋትን እንመረምራለን። ስለ ግጥምና ቅኔ ልንረዳው የሚገባ አንድ ዋና ነገር ብዙ ጊዜ የሚጻፈው በተምሳሌታዊ መግለጫ መልክ እንጂ በቀጥታ አለመሆኑን ነው። ለምሳሌ በመዝሙረ ዳዊት ዛፎች ለእግዚአብሔር ሲዘምሩ እንመለከታለን (መዝ. 96፡ 12 ተመልከት)። እኛ በምንዘምረው ዓይነት ዛፎች እንደማይዘምሩ እናውቃለን፤ ነገር ግን እኛ በቃላችን እግዚአብሔርን እንደምናመሰግን ዛፎችም እርሱ ፈጣሪያቸው በመሆኑ ያመሰግኑታል። ስለሆነም በሥነ-ግጥምና ቅኔ ቋንቋ፥ ቃላት ራሳቸው ተምሳሌታዊ ይሆኑና ከምልክቱ ወይም ከምሳሌው ጋር ተመሳሳይ የሆነ አንድ ተግባር ወይም እውነት ይጠቁማሉ። ሥነ-ግጥምና ቅኔን በምንተረጉምበት ጊዜ ምልክቶቹን ከእውነተኛ ትርጉም ወይም ከተሰወረ እውነት መለየት አለብን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 15፡1-18 አንብብ ሀ) ሙሴ ወደ እግዚአብሔር በዘመረው ዝማሬ ውስጥ የሚገኙትን ተምሳሌቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህ ተምሳሌቶች ምን ያስተምሩናል?

በእነዚህ ቁጥሮች ሙሴ መዝሙሩን የእግዚአብሔርን ታላቅነትና ክብር ለመግለጥ ይጠቀምበታል። በመዝሙሩ ውስጥ በርካታ ተምሳሌቶችን ይጠቀማል። ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር የፈርዖንን ሠራዊት ሊያሸንፍ እንደቻለ አንድ ታላቅ ተዋጊ አድርጎ ያቀርበዋል። ከታሪኩ እንደምናስታውሰው ግን የፈርዖንን ሠራዊት ድል ለማድረግ እግዚአብሔር የተጠቀመው በታላቅ ውኃ ነው። እግዚአብሔር ቀኝ እጅና አፍንጫ እንዳለው ሆኖ ቀርቦ እናየዋለን። ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደምንረዳው ግን እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ እንደ እኛ ሥጋዊ አካል ሊኖረው አይችልም። ሙሴ እግዚአብሔር እንዴት ታላቅ እንደሆነና ለእስራኤል ለመሥራት ሲል ኃይሉን እንዴት እንደተጠቀመበት ለመግለጥ ሰብአዊ አባባሉን በሥነ-ግጥምና በቅኔ መልክ አቅርቧል።

፫. ትንቢት፡- በፔንታቱክ ውስጥ ተሰራጭተው የሚገኙ የተለያዩ ትንቢቶች አሉ። ከእነዚህ ትንቢቶች አንዳንዶቹ በቀጥተኛ ቋንቋ የቀረቡ ሲሆን (ምሳሌ፡- ዘፍጥ. 15፡13)፡ ሌሎቹ ደግሞ በተምሳሌነት ወይም በሥነ-ግጥምና በቅኔ መልክ ቀርበዋል (ምሳሌ፡- ዘፍ. 49፡8-12)። በብሉይ ኪዳን የሚገኙ ትንቢቶች አብዛኛዎቹ በሥነ ግጥምና በቅኔ መልክ የቀረቡ ናቸው። ትንቢት በሥነ-ግጥምና በቅኔ መልክ ቀርቦ ተምሳሌታዊ የሆነ መግለጫ መያዙ ለመተርጎም በጣም ከባድ ያደርገዋል። በብሉይ ኪዳን ትንቢት ሁለት የተለያዩ ትርጉሞች አሉት። በመጀመሪያ፥ ትንቢት የሚለው ቃል በማንኛውም ጊዜ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ቀጥተኛ ትምህርትን ለመስጠት ወይም ፈቃዱን ለመግለጥ አንድን ሰው ተጠቅሞ የሚያመጣው መልእክት ነው። በብሉይ ኪዳን የሚገኙ አብዛኛዎቹ ትንቢቶች ስለ ወደፊቱ ነገር የሚናገሩ አይደሉም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በዚያ ዘመን ለነበሩ ሰዎች እነርሱ ምን እንዲያደርጉ ይፈልግ እንደ ነበር የሚገልጥ መልእክት ነው። ሁለተኛ፥ በአንዳንድ ትንቢቶች እግዚአብሔር ወደ ፊት ምን እንደሚሆን አስቀድሞ ይገልጣል። በዘፍጥረት 49 እግዚአብሔር መሢሑ የሚመጣው ከይሁዳ ነገድ እንደሚሆን አስቀድሞ ለመናገር ያዕቆብን ተጠቅሞበታል፤ ስለዚህ የትንቢት መልክ ወዳለው የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል ስንደርስ የትኛው የወደፊትን ነገር እንደሚያመለክትና የትኛው ደግሞ በዚያን ጊዜ ለሚሆነው ጉዳይ የተለየ ትእዛዝ እንደሆነ መለየት ያስፈልገናል። እንዲሁም ያ ትንቢት የተሰጠው ለምን እንደሆነም በግልጥ መወሰን አለብን። ይህ ትንቢት የተነገረው በዚያን ጊዜ ለነበረ አንድ ሰው፥ ወይም ቡድን ነውን? ወይስ ዛሬ ካለን ሰዎች ሕይወት ጋርም የሚዛመድ ነው? ብለን መጠየቅና ለዚህ መልስ ለማግኘት መቻል አለብን። ከኢሳይያስ እስከ ሚልክያስ ያሉትን የነቢያት መጻሕፍት ስናጠና ይህንን በጥልቀት እንመለከተዋለን። 

፬. ሕግ፡- የፔንታቱክ አብዛኛው ክፍል «ሕግ» የተባለ የተለየ ዓይነት ሥነ-ጽሑፍ ነው። በአንዳንድ ረገድ የምድራችን ሕግጋት ድንጋጌዎች የሆኑት ደንቦች ዝርዝር ነው። አንዳንዶቹ ከዘጸአት እስከ ዘዳግም ባሉት መጻሕፍት ውስጥ ከእግዚአብሔር የተሰጡ ከ600 የሚበልጡ ሕግጋት እንዳሉ ገምተዋል።

እግዚአብሔር ለአይሁድ ይህን ሁሉ ሕግ የሰጠበት ምክንያት ምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ በእግዚአብሔርና በአይሁድ ሕዝብ መካከል ያለ ቃል ኪዳን አንዱ ክፍል ነበር። እግዚአብሔር እውነተኛ የአይሁድ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ሕይወታቸውን በሙሉ የሚገዙበትና የተለዩ «ቅዱስ» ሕዝብ ሆነው ለመኖር የሚችሉባቸውን የተለያዩ ግልጥ ሕግጋት ሰጣቸው። የእግዚአብሔር ልጆች እንደመሆናቸው መጠን ቅዱስ የሆነውን እግዚአብሔርን መምሰል ነበረባቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ቅድስና ዛሬ ለእኛ የሚያስፈልገው እንዴት ነው?

እግዚአብሔር፥ አይሁድ የሕይወታቸውን የተለያዩ አቅጣጫዎች በሙሉ እንዲነካ ግንኙነታችውን በእርሱ ላይ እንዲመሠርቱ ይፈልግ ነበር። እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት የተቀደሰ ሕይወት እስከኖሩና እግዚአብሔር የሰጣቸውን የቃል ኪዳን ግዴታዎች እስካሟሉ ድረስ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ይኖራቸው ነበር። ከዚያም እግዚአብሔር አምላካቸው ይሆንና ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን በማሟላት ከጠላቶቻቸው ሁሉ ይጠብቃቸው ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ለአይሁድ የሰጣቸው ሕግጋት የማይነካው የሕይወታቸው ክፍል አልነበረም። ከጎረቤቶቻቸው፥ ከመሪዎቻቸው ከመንግሥታቸውና ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚናገር ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ኅብረት ሕይወታችንን በሙሉ የሚነካው እንዴት ነው?) በኢየሱስ ላይ ያለ እምነትህ ከቤተሰብህ፥ ከጎረቤትህ፥ ከመንግሥትህ፥ ከሥራህና ወዘተ ጋር ያለህን ግንኙነት እንዴት እንደለወጠ ከራስህ ሕይወት ምሳሌ ስጥ።

እግዚአብሔር በፔንታቱክ ውስጥ ለአይሁድ የሰጣቸው ሕግጋት ሦስት ዋና ዋና የሕይወት ክፍሎችን የሚመለከቱ ነበሩ። በመጀመሪያ፣ የመንግሥት ወይም የሕዝብ ሕጎች ነበሩ። እነዚህ ሕጎች፡- የጋብቻ የቤተሰብ፥ የውርስ፥ የንብረት ባለቤትነት መብት፥ የባሪያ፥ የቀረጥ፥ የደመወዝ ወዘተ ናቸው። ሁለተኛ፥ የሥነ- ምግባር ሕግጋት የነበሩ ሲሆን እነዚህም፡- የነፍስ ግድያ፥ ዝሙት፥ ያለፈቃዷ ሴትን የመድፈር፥ የሌብነት፥ የሐሰት ምስክር የመሳሰሉት ናቸው። ሦስተኛ፥ የሃይማኖት፥ የሥርዓት ሕግጋት ሲሆኑ እነዚህ ሕግጋት እስራኤላውያን እንዴት እግዚአብሔርን ማምለክ እንዳለባቸው፥ መሥዋዕት ማቅረብ እንዳለባቸው፥ በሥርዓት ቅዳሴ እንዴት ንጹሐን መሆን እንዳለባቸውና ሃይማኖታዊ በዓላቸውን መቼ ማክበር እንደሚገባችው ወዘተ የሚናገሩ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ የሚቆጣጠረው የትኞቹን ዓይነት ሕግጋት ነው? ለ) በኢትዮጵያ ያሉ ልዩ ልዩ ሃይማኖቶች የትኞቹ ዓይነት ሕግጋት ናቸው ያሉዋቸው? ሐ) በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ አንዳንድ የሥነ ምግባርና ሃይማኖታዊ ሕግጋት የሚለያዩት እንዴት ነው?

በፔንታቱክ ውስጥ የሚገኙት ሕግጋት የሚከፈሉት በሦስት ዋና ዋና ክፍሉች ቢሆንም በዓይነታቸው ግን አምስት ናቸው። እነርሱም :

 1. በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚነሡ ጉዳዮች የሚሆኑ ሕግጋት፥ እነዚህ ሕግጋት ብዙ ጊዜ «እንዲህ ቢሆን … እንዲህ ይደረግ» የሚሉ ቃላት ይገኙባቸዋል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘዳ. 22፡22-24 ተመልከት። ሀ) ይህ ሕግ የሚጠቅላችው ልዩ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? ለ) የተጠቀሱት ቅጣቶችስ ምንድን ናቸው?

 1. ቀጥተኛ ትእዛዛትን በመስጠት እግዚአብሔር ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግ የሚናገሩ ሕግጋት፡- እነዚህ ሕግጋት አዎንታዊ (አድርግ …) እና አሉታዊ (አታድርግ …) የሚሉ ትእዛዛት ሊሆኑ ይችላሉ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 20፡3-17 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ቁጥሮች የሚገኙትን አዎንታዊ ትእዛዛት ዘርዝር። ለ) በእነዚህ ቁጥሮች የሚገኙትን አሉታዊ ትእዛዛት ዘርዝር።

 1. ሊሆኑ ስለሚችሉ መላምታዊ ነገሮች የሚናገሩ ሕግጋት፥ እነዚህ ሕግጋት ሊሆኑ ስለሚችሉ ተግባራት ምሳሌዎችን ይሰጣሉ፤ ነገር ግን የምናከናውናቸውን ተግባራት በሚመለከት መከተል የሚገባን ብቸኛ ሁኔታዎች አይደሉም። ለምሳሌ በዘሌ. 19፡ 14 እግዚአብሔር እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል፡- «ደንቆሮውን . . . አትሳደብ፥ በዕውርም ፊት ዕንቅፋት አታድርግ፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ» የዚህ ሕግ ዓላማ እነዚህን የተለዩ ሁኔታዎች መቆጣጠር ብቻ አይደለም። ለምሳሌ፡- ይህ ማለት ዕውሩን መስደብና ደንቆሮው ፊት ዕንቅፋት ማድረግ ተፈቅዷል ማለት ነውን? አይደለም። በዚህ ሕግ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ዕውሮችና ደንቆሮዎች የሚገባቸውን ስፍራ ባለመስጠት ከማጉላላት ይልቅ ሊያከብሩአቸው እንደሚገባ ማሳየቱ ነበር። ይህ ሕግ ከእኛ ይልቅ ጉድለት የገጠማቸውን ሰዎች በሚገባ ያለማክበርን የሚቃወም ነው። 
 2. እጅግ የከፋ በደል ከመፈጸም ጋር የተያያዙና ወንጀሉን በፈጸመው ሰው ላይ የሞት ፍርድ የሚያስከትሉ ሕግጋት ናቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 21፡14-17 አንብብ። የማይታዘዘው ሰው እንዲገደል እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ያዘዛቸውን ልዩ ልዩ ሁኔታዎች ዘርዝር።

 1. በምሥጢር የተፈጸሙና ለማረጋገጥ አስቸጋሪ የሆኑ ጉዳዮችን የሚመለከት ሕግ፥ ብዙ ጊዜ ለእነዚህ ሕግጋት የሚሰጠው ቅጣት «እርግማን» ነበር። በምሥጢር የተፈጸመን ነገር መቆጣጠር ለሰው ልጅ አስቸጋሪ ስለሆነ እግዚአብሔር ራሱ ጥፋተኛውን መቅጣት አለበት። እነዚህን ሕግጋት የተላለፉትን ሰዎች እግዚአብሔር እንደሚቀጣቸው (እንደሚረግማቸው) ቃል ገብቶ ነበር። አንድ ሰው እነዚህን ሕግጋት ሲተላለፍ ቢያዝ፥ የሚደርሱበት የተለያዩ ቅጣቶች ቢኖሩም፥ የእነዚህ ዓይነት ሕግጋት ትኩረት ሕጉን የተላለፉ ሰዎች በሰው ባይያዙም እንኳ ሊቀጣቸው የሚችለው እግዚአብሔር እንደሚያያቸው ለመግለጥ ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘዳ. 27፡17-26 አንብብ። ሀ) ሕግጋቱን በተላለፈ ሰው ርግማን እንደሚደርስበት የሚናገሩትን የተለዩ ሕጎች ዘርዝር። ለ) ሰው ኃጢአታችንን ሊያይ ባይችልም እንኳ እግዚአብሔር አይቶ ይቀጣናል። ይህ እውነት ኃጢአትን ከማድረግ እና ቅጣትን እንደምናመልጥ ከማሰብ እንዴት ይጠብቀናል? የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ለክርስቲያኖች ጥቅማቸው ምንድን ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙውን ጊዜ እኛ ልንታዘዛቸው አይገባንም ብለን የምናስባቸው፥ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ግን የሚጠብቋቸውን ሕግጋት ዘርዝር። ለ) የሰባተኛ ቀን አክባሪዎች አድቬንቲስት ልንጠብቃቸው ይገባል የሚሉአቸውን የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ዘርዝር። 

ስለ እነዚህ ሕግጋት ልንጠይቀው የሚገባ አንድ ዋና ጥያቄ «በአዲስ ኪዳን ዘመን የምንኖር ሰዎች ለእነዚህ የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ልንሰጣቸው የሚገባ ስፍራ ምንድን ነው?» የሚል ነው። የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ለእኛ ባላቸው ስፍራ የክርስቲያኖች አመለካከት የተለያየ ነው። በግልጽ ስሕተት የሆኑ ሁለት ዓይነት አመለካከቶች አሉ። የመጀመሪያው፥ የብሉይ ኪዳን ሕግጋት በሙሉ ዛሬ እኛንም ይገዙናል የሚለው አሳብ የተሳሳተ ነው። ከአዲስ ኪዳን ትምህርቶች በግልጽ እንደምንመለከተው ስለ ምግብ የተነገሩ ሕግጋት ዛሬ እኛን አይገዙንም። በብሉይ ኪዳን ሥጋቸው እንዲበላ የተፈቀዱ የተወሰኑ እንስሶች ነበሩ (ማር. 7፡14-23፤ የሐዋ. 10:9-16)። እንዲሁም ቅዳሜን እንደ አምልኮ ቀን የመጠበቅ ሕግ እንደማይገዛን ተገልጾአል (ቆላ. 2፡16-17)። እነዚህን ሕግጋት መጠበቅ ባይከፋም፥ በክርስቲያን ላይ ሊሠለጥኑ የሚችሉ ግን አይደሉም።

ሁለተኛው አመለካከት ደግሞ፤ የትኞቹም የብሉይ ኪዳን ሕግጋት በአሁኑ ጊዜ እኛን የሚመለከቱ አይደሉም የሚለው የተሳሳተ አቋም ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን ከሕዝቡ ጋር የተገናኘባቸው መንገዶች ፍጹም የተለያዩ ናቸው ብለው ያስተምራሉ። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የተገናኘው «በሕግ» አማካይነት ሲሆን በአዲስ ኪዳን ደግሞ ከክርስቲያኖች ወይም ከቤተ ክርስቲያን ጋር የሚገናኘው «በጸጋ» ነው። ይህ አመለካከት የትኞቹንም የብሉይ ኪዳን ሕግጋት መከተል የለብንም ለማለት ከሆነ የተሳሳተ ነው።

የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ዛሬ በእኛ ሕይወት ውስጥ ሊኖራቸው ስለሚገባ ስፍራ አዲስ ኪዳን ምን እንደሚል በምንመረምርበት ጊዜ የሚከተሉትን እውነቶች እናገኛለን፡

 1. የብሉይ ኪዳን ሕግጋት በሙሉ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የጻፉአቸው የእግዚአብሔር ቃል ክፍል ናቸው። እንደቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ለትምህርትና፥ በጽድቅ ላለው ልምምድ የሚጠቅሙ ናቸው (2ኛ ጢሞ. 3፡16)። 
 2. እግዚአብሔርን የሚገደው ሕግጋትን በውጫዊ ገጽታቸው መጠበቁ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የልብን አሳብና መሻት ጭምር ይመረምራል። ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር «አታመንዝር» የሚለውን ሕግ ሲሰጥ የከለከለው በጋብቻ ያልተጣመሩ ሰዎች የሚፈጽሙትን ፍትወት ብቻ ሳይሆን ሰውን ወደምንዝርና ሊመራ የሚችለውን ጽኑ የፍትወተ ሥጋ ፍላጎት አሳብ ጭምር ነበር (ማቴ. 5፡27-30)። እግዚአብሔርን ከልብ መታዘዝና ትእዛዛቱንም መጠበቅ ያለብን በውጫዊ አሳብ ብቻ ሳይሆን ከውስጥ በሆነ እውነተኛ ዝንባሌና ስሜትም ጭምር ነው።

ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች አብልጠው የሚያስቡት ሰዎች እንደ ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ራስን መግዛት፥ ወዘተ (ገላ. 5፡22-23) ካሉት ውስጣዊ ነገሮች ይልቅ ውጫዊ የሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስና የቤተ ክርስቲያን ሕግጋትን እንዲጠብቁ ነው። ይህም «ሕግ አጥባቂነት» በመባል ይታወቃል። እግዚአብሔር የሰጠንን ሕግ እንድንጠብቅ የሚፈልግ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም፥ የምንጠብቃቸው በተገቢ ምክንያቶች ወይም በእውነተኛ ውስጣዊ ዝንባሌዎች መሆኑን ማረጋገጥም ይፈልጋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰዎች እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ዝንባሌ ሊጠብቋቸው የሚችሏቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ወይም የቤተ ክርስቲያን ሕግጋት ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔርን በትክክለኛ ዝንባሌ መታዘዝና በተሳሳተ አመለካከት መታዘዝ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

 1. ሕጉ «ቅዱስ፥ ጻድቅና መልካም» ነው (ሮሜ 7፡12 ተመልከት)። ስለሆነም ይህ ዛሬም ለክርስቲያን ልምምድ ጠቃሚ ነው። ኢየሱስ ሕግን ሊፈጽም እንጂ ሊሽር እንዳልመጣ ተናግሮአል (ማቴ. 5፡17-20)። ስለዚህ ለክርስቲያን የብሉይ ኪዳንን ሕግ ማወቅና መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን ሕግን ራሱን በመጠበቅና በመስጠት ረገድ እግዚአብሔር ባለው ዓላማና ዕቅድ መካከል ግልጥ የሆነ ልዩነት ማድረግ አለብን።
 2. ከሕግ ሁሉ የሚበልጠውና ሕግን በሙሉ የሚፈጽመው የፍቅር ሕግ ነው (ማቴ. 22፡35-40 ተመልከት)። የፍቅር ሕግ ሁለት አቅጣጫዎች አሉት። በመጀመሪያ፥ ፍቅር ወደ እግዚአብሔር ማመልከት አለበት። እግዚአብሔርን በሙሉ ኃይላችን ልንወደው ይገባናል። እግዚአብሔርን እንደምንወደው የምንገልጽበት መንገድ ትእዛዛቱን መጠበቅ ነው (1ኛ ዮሐ. 5፡1-5)። ሁለተኛ፥ የፍቅር ሕግ ወደ ሰዎችም ማመልከት አለበት። በሙሉ ልባችን እግዚአብሔርን ከወደድንና ፍቅራችንን ለሰዎች ከገለጥን የእግዚአብሔርን ሕግጋት ሁሉ እየፈጸምን ነው ማለት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 20፡1-17 አንብብ። ሀ) ለእግዚአብሔርና ለሌሎች ያለን ፍቅር ዓሥርቱን ትእዛዛት የሚፈጽመው እንዴት ነው? ለ) ሌሎች አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ሕግጋትና ትእዛዛትን እንዲጠብቁ ትኩረት ከማድረግ ፈንታ እግዚአብሔርንና ሰዎችን የበለጠ እንዲወዱ እንዴት ግበረታታት እንችላለን? 

የውይይት ጥያቄ፥ ገላ. 3፡21-25 አንብብ። ሀ) እነዚህ ጥቅሶች ስለ ብሉይ ኪዳን ሕግጋት ዓላማ ምን ያስተምሩናል? ለ) የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ሰውን የሚገዙት እስከ ምን ድረስ ነበር? 

 1. ከብሉይ ኪዳን ሕግ ዋና ዋና ዓላማዎች አንዱ ለሰው ልጆች በሙሉ ኃጢአተኝነታቸውና በእግዚአብሔር ላይ ያለማቋረጥ ማመፃቸውን ማሳየት ነበር። በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ በተፈጥሮ ያደረውን ክፉ ነገር ልክ እንደ መስተዋት ሆኖ ለማሳየት ነው። ሕግ ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች መሆናቸውንና በመልካም ሥራቸው ራሳቸውን ማዳን እንደማይችሉ በግልጥ ያሳያል። እነዚህም ወደ ክርስቶስ ፊታቸውን እንዲመልሱና ከኃጢአታቸው ለመዳን በእርሱ ብቻ እንዲታመኑ ይገፋፋቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) በዚህ ዘመን ሰዎች መዳን ይችሉ ዘንድ ይህንን እውነት ማወቅ ያለባቸው ለምንድን ነው? ለ) ዛሬ ብዙ ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ይችሉ ዘንድ ሕግን ለመጠበቅ እንዴት ይሞክራሉ? ሐ) ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት የሚያበቃ መልካም ተግባር ለመፈጸም ወይም ሕግን ለመጠበቅ የማንችለው ለምንድን ነው?

ለእስራኤላውያንም ሆነ ለመላው ዓለም ያለው የሕግ ዋና ዓላማ ወደ ኢየሱስ ወይም ወደ እግዚአብሔር ጸጋ እንዲመለከቱ መገፋፋት ነው (ገላ. 3፡24 ተመልከት)።

 1. ብዙዎቹ የብሉይ ኪዳን ሕግጋት የክርስቶስ ኢየሱስን መምጣትና በኢየሱስ በማመን እንዴት መዳን እንደሚቻል ያመለክታሉ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሉቃ. 24፡25-27 አንብብ። ኢየሱስ መሞትና ከሞት መነሣት እንዳለበት ለደቀ መዛሙርቱ ለመግለጽ የተጠቀመው በምንድን ነው? 

በብሉይ ኪዳን የተፈጸሙ ብዙ ታሪካዊ ድርጊቶች፡ ሰዎችና ነገሮች ሁሉ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ያመለክታሉ። እርሱ የአምሳላቸው ፍጻሜ ነው። ለምሳሌ አዳም የክርስቶስ አምሳል ነው (ሮሜ 5፡14-19 ተመልከት)። የፋሲካ በዓል የክርስቶስ የመስቀል ሞት አምሳል ነው (1ኛ ቆሮ. 5፡7)። ደግሞም የብሉይ ኪዳን የክህነት አገልግሎት የሊቀ ካህናችን የኢየሱስ ምሳሌ ነው (ዕብ. 7-9)።

የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን በምናጠናበት ጊዜ እንዴት ልንተረጉማቸው ይገባል?

 1. የእነዚህ ሕጎች ውጫዊ ሁኔታ ለአንድ የተለየ ሰው፥ ወይም ቡድን፥ ወይም ሰዎችን ሁሉ የሚመለከት ነውን? ብለን ልንጠይቅ ይገባል። ሕጉ የተሰጠው ለአንድ የተለየ ሰው ወይም ቡድን ከሆነ የሕጉን ውጫዊ አፈጻጸም መከተል አያስፈልገንም፤ ነገር ግን ከሕይወታችን ጋር ልናዛምደው የምንችል የሕጉ ውስጣዊ ዓላማ ብዙ ጊዜ ይኖራል። 
 2. እግዚአብሔር ያንን ሕግ በተለይ የሰጠበትን ምክንያት ለመወሰንም መሞከር አለብን። እግዚአብሔር ውስጣዊ የሆኑ የሕግ ዓላማዎችና ውጫዊ አፈጻጸማቸውንም በሚመለከት ጉዳይ አለው። ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ሕግን የሰጠበት ዓላማ ከሕይወታችን ጋር ሊዛመድ ይችላል።
 3. በብሉይ ኪዳን ከተሰጡት ሕግጋት መካከል እንደገና እንታዘዛቸው ዘንድ በአዲስ ኪዳን የተሰጡ ልዩ ትእዛዛት መኖራቸውን መመልከትና ማረጋገጥ አለብን። በብሉይ ኪዳን የሚገኝ ሕግ በአዲስ ኪዳን ደግሞ ከተሰጠ ዛሬም ልንታዘዘው እንደሚገባ እርግጠኛች እንሆናለን (ለምሳሌ፡- ዝሙት፥ መግደል፥ መዋሸት፥ ወዘተ)። ከብሉይ ኪዳን ሕግጋት መካከል በአዲስ ኪዳን ልንታዘዛቸው አስፈላጊ እንዳልሆነ የተጠቀሱ ሕጎች እንዳሉም ልንመለከት ያስፈልጋል። ለምሳሌ፡- ኢየሱስ ስለ ምግብ የተሰጡ ሕግጋት አስፈላጊ እንዳልሆኑ ተናግሯል። የዕብራውያን መልእክት ደግሞ ከኢየሱስ ሞት በኋላ እንስሳትን የመሠዋት ሥርዓት አስፈላጊ እንዳልሆነ ያስተምራል። 
 4. የተለያዩ የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ፥ ከእርሱ ጋር ስላለንና ከሰዎች ጋር ሊኖረን ስለሚገባ ግንኙነት የሚናገሩት ነገር አለን? ብለን ልንጠይቅ ያስፈልጋል። 
 5. ያ የተሰጠን ሕግ የኢየሱስ ክርስቶስ፥ የድነት (ደኅንነት)፥ ወይም የሌላ የአዲስ ኪዳን ጠቃሚ እውነት አምሳል እንደሆነ ለማወቅ መመርመር ያስፈልገናል፤ ነገር ግን ይህንን ስናደርግ በጣም መጠንቀቅ አለብን። የትኛው የብሉይ ኪዳን ክፍል የክርስቶስ አምሳል እንደሆነ፥ የትኛው እንዳልሆነ ለማወቅ የአዲስ ኪዳን ትምህርት ማረጋገጫ ብዙ ጊዜ ያስፈልገናል። በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ የክርስቶስ አምሳል ባልሆኑት ነገሮች ውስጥ የክርስቶስን አምሳል የመፈለግ ዝንባሌ አለ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 23ን አንብብ። ሀ) እነዚህን ስድስት ደረጃዎች በመጠቀም ልንጠብቃቸው የሚገባንን ሕግጋት ዘርዝር። ለ) ልንጠብቃቸው የማያስፈልጉ ሕግጋትን ዝርዝር ደግሞ ጻፍ። ሐ) አንዳንዶቹን መጠበቅ ሌሎቹን ደግሞ አለመጠበቅ የሚያስፈልግ ለምን እንደሆነ የሚመስልህን ምክንያት ጻፍ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የፔንታቱክ መጻሕፍት ስሞች በውስጣቸው የሚታይ ታሪክ

የፔንታቱክ መጻሕፍት ስሞች

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በፔንታቱክ ውስጥ የሚገኙ የአምስቱን መጻሕፍት ስም ዘርዝር። ለ) በግዕዝ የእያንዳንዳቸው ርዕስ ትርጉም ምንድን ነው? የግዕዝ ትርጉሞቻቸውን ካላወቅህ ግዕዝ የሚያውቅ የኦርቶዶክስ ቄስ እንዲረዳህ ጠይቅ። ሐ) ከዚህ ቀደም በመጽሐፍ ቅዱስ ካለህ እውቀት በመነሣት አምስቱ መጻሕፍት እያንዳንዳችው ስለምን እንደሚያስተምሩ በራስህ አባባል ጠቅለል ባለ መልኩ ጻፍ።

በፔንታቱክ ውስጥ አምስት መጻሕፍት ይገኛሉ። ሙሴ እነዚህን አምስት መጻሕፍት በሚጽፍበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መጽሐፍ ስም ወይም ርዕስ አልሰጠም ነበር። በኋላ አንዱን መጽሐፍ ከሌላው ለመለየት አይሁድ ለእያንዳንዱ ጥቅልል የራሱ የሆነ ስም ሰጡት። የመጻሕፍቱን ርዕስ ብዙ ጊዜ የሚወስዱት በጥቅሱ ውስጥ ከሚገኘው ከመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር መጀመሪያ ቃል ላይ ነበር። ለምሳሌ፡- ዘፍጥ. 1፡1፡- «በመጀመሪያ» … የሚል ቃል እናገኛለን፤ ስለዚህ አይሁድ የመጀመሪያውን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ «መጀመሪያ» አሉት። ኋላም የግሪክ ቋንቋ የሚያውቁ አይሁድ የዕብራይስጡን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ግሪክ ሲተረጉሙትና ሴፕቱዋጀንት የሚባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ሲያዘጋጁ የመጽሐፉን ወይም የጥቅሉን ዋና አሳብ በአጭሩ ሊገልጥ የሚችል የራሳቸው የሆነ ርእስ ሰጡት። የእንግሊዝኛውና የአማርኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ርእሶች የተገኙት በሴፕቱዋጀንት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ርእሶች ነው። በአዲሱ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ስሞቹን ወደ አማርኛ ከመተርጎም ይልቅ ውስጥ ታዋቂነት ያለውን የግዕዙን ስም እንዲይዝ ተደርጓል።

 1. ዘፍጥረት፡- በአማርኛ ዘፍጥረት የሚለው ቃል የመጣው እግዚአብሔር ሰማይን፥ ምድርንና በውስጧ ያሉትን ነገሮች እንዴት እንደፈጠረ ከሚናገረው ከመጽሐፉ የመጀመሪያ ሁለት ምዕራፎች ነው። የዘፍጥረት መጽሐፍ እግዚአብሔር ዓለምን እንዴት እንደፈጠረ ከመናገር እጅግ የሚበልጥ ነገር ስላቀፈ ይህ ስም ከሁሉ የተሻለና ትክክለኛ ስም አይደለም። በግሪክ «ጀነሲስ» የሚባለው የመጽሐፉ ስም «ጅማሬ» የሚል ትርጉም ያለው ነው። ይህ ስም በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ስለሚገኙት ነገሮች የተሻለ መግለጫ ነው። የዘፍጥረት መጽሐፍ ስለ ፍጥረት ሁሉ ጅማሬ ይነግረናል። ስለ ሰው ልጅ ጅማሬ፥ ስለ ኃጢአትና ስለ ሞት ጅማሬ፥ ስለ ሥልጣኔ ጅማሬ፥ በዓለም ስለሚገኙ የተለያዩ ነገዶች ጅማሬና እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ስለገባው ቃል ኪዳን ጅማሬ ይገልጻል። 
 2. ዘጸአት፡- ዘጸአት የሚለው ቃል የአማርኛና የእግሊዝኛ ትርጉም፥ «መልቀቅ» ወይም «መውጣት» ማለት ሲሆን፥ የሚናገረውም እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፅ ባርነት እንዴት ነፃ እንዳወጣ ነው፤ ነገር ግን አብዛኛውን የኦሪት ዘጸአት ክፍል እግዚአብሔር በሲና ተራራ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ስለገባው ቃል ኪዳን ይናገራል። 
 3. ዘሌዋውያን፡-. ዘሌዋውያን የሚለው የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቃል፥ ሌዋውያን ተብለው ከሚጠሩት ከአንዱ የእስራኤል ነገዶች የተገኘ ነው። ሌዋውያን የካህናት ነገድ ሲሆኑ ስሙም የሚያመለክተው በኦሪት ዘሌዋውያን ከተጻፉ ሕጎች አብዛኛው እነርሱ እግዚአብሔርን እንዴት እንደሚያመልኩና በፊቱም በሥነ ምግባራቸው እንዴት ንጹሐን ሆነው መኖር እንዳለባቸው ለማመልከት፥ በተለይ የተሰጣቸው ስለነበር ነው። ነገር ግን እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ የቀሩት እስራኤላውያን በሙሉ ሊከተሉአቸው የሚገባ በርካታ ሕጎችንም በመጽሐፉ ውስጥ እናገኛለን። 
 4. ዘኁልቁ፡- ዘኁልቁ የሚለው የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቃል ትርጉም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የእስራኤል ሕዝብ እንዴት ሁለት ጊዜ እንደተቆጠሩ የሚያሳይ ነው። በመጀመሪያ ልክ ግብፅን ለቀው ሲወጡ ብዛታቸውን ለማወቅ ሲባል ተቆጠሩ። ከዚያም ከ40 ዓመታት በኋላ እንደገና ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በተዘጋጁበት ጊዜ ተቆጠሩ። ኦሪት ዘኁልቁ የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር መግባትን በመቃወማቸው ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ ስለመንከራተታቸው ይናገራል። 
 5. ዘዳግም፡- ዘዳግም የሚለው የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቃል ሕግን ከመድገም ጋር የተያያዘ ነው። በኦሪት ዘዳግም የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በዝግጅት ላይ ነበሩ። ከ40 ዓመታት በፊት በሲና ተራራ እግዚአብሔር ሕግን ለሕዝቡ ሲሰጥ ያልነበረ አዲስ ትውልድ ነበር፤ ስለዚህ ሙሴ ከመሞቱ በፊት ሕጉን ለዚህ አዲስ ትውልድ በድጋሚ ሲሰጥ እናያለን። የኦሪት ዘዳግም አብዛኛው ክፍል እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በሲና ተራራ የገባውን ቃል ኪዳን እንዲፈጽምላቸው መጠበቅ ስለሚገባቸው ሕግጋት የሚናገር ነው።

በፔንታቱክ ውስጥ የሚታይ ታሪክ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በፔንታቱክ ውስጥ የተጠቀሰው የመጀመሪያው ታሪካዊ ተግባር ምንድን ነው? (ዘፍጥ. 1፡)። ለ) በፔንታቱክ ውስጥ የተጠቀሰው የመጨረሻ ታሪካዊ ተግባር ምንድን ነው?

በፔንታቱክ ውስጥ ስለ ጥንቱ ታሪክ የሚገልጡ ሦስት መጻሕፍት አሉ፤ እነዚህ መጻሕፍት ዘፍጥረት፥ ዘጸአትና ዘኁልቁ ናቸው። በፔንታቱክ የተጠቀሰው የመጀመሪያው የዓለም አፈጣጠር ታሪክ ነው። እግዚአብሔር ዓለምን የፈጠረው መቼ እንደሆነ አናውቅም። ይህን በተመለከተ ምሁራን የተለያየ አስተሳሰብ አላቸው። አንዳንዶቹ ይህ የሆነው በ4000 ዓ.ዓ. ገደማ ነበር ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ከ10000 ዓመታት ወይም ከዚያ በፊት ሊሆን ይችላል ይላሉ። ከዘፍጥ. 1-11 ድረስ ያለው ታሪክ መቼ እንደተፈጸመ በትክክል ለማወቅ አይቻልም። በፔንታቱክ ውስጥ ከሚገኙት ታሪኮች መካከል በትክክል ቀኑን ልንገምት የምንችልበት የመጀመሪያ ታሪክ የአብርሃም ሕይወት ታሪክ ነው። አብርሃም የኖረው በ2150 ዓ.ዓ. ገደማ ሲሆን የዘፍጥረት መጽሐፍ ታሪክ ያከተመው በ1800 ዓ.ዓ. አካባቢ ነበር። የቀሩት የፔንታቱክ መጻሕፍት ታሪክ ሙሴ ከተወለደበት ከ1525 ዓ.ዓ. ጀምሮ ሕዝቡ ነጻ እስከወጡበት እስከ 1440፥ ከዚያም እስከ ሙሴ ሞት ድረስ 1400 ዓ.ዓ. ይቀጥላል።

ፔንታቱክ የተጻፈበት ጊዜ

የፔንታቱክ አብዛኛው ክፍል የተጻፈው የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ በተንከራተቱባቸው ዓመታት ነው። ስለዚህ ሁሉም መጻሕፍት ማለትም ዘፍጥረት፥ ዘጸአት፥ ዘሌዋውያን፥ ዘኁልቁና ዘዳግም የተጻፉት ከ1446-1406 ዓ.ዓ. ነው።

ይሁን እንጂ በፔንታቱክ የተጻፉ ታሪካዊ ድርጊቶች የተፈጸሙባቸውን ጊዜያት ለመወሰን ስንሞክር አንድ ዐቢይ ችግር ይገጥመናል። ይህ ችግር የሚነሣው በዘጸአት ውስጥ በዕብራይስጡና በግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ መካከል ባለ የአንድ ጥቅስ ልዩነት ምክንያት ነው። የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ በዘጸ. 12፡40 አይሁድ በግብፅ ለ430 ዓመታት እንደነበሩ ይናገራል። የግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ለ215 ዓመታት ነበሩ ይላል። 430 ዓመታት የሚለው በይበልጥ ትክክል ሳይሆን አይቀርም (1ኛ ነገሥት 6፡1 ተመልከት)። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የቁጥሮችን ወይም የታሪኮችን ትክክለኛነት የማይቀበሉ አንዳንድ ምሁራን ወደኋላ ያደርጉታል።

የፔንታቱክ ታሪክ የተፈጸመው በሦስት የዓለም ክፍሎች ነው። የተጀመረው ከዘፍ. 1-11 ያለው ታሪክ በተፈጸመበትና የዔድን ገነት ባለበት መስጴጦምያ ነው። የእስራኤል ሕዝብ አባት የሆነው አብርሃም የመጣው ከመስጴጦምያ ሲሆን የይስሐቅና የያዕቆብ ሚስቶችም የመጡት ከዚሁ አገር ነበር። ከዚያም ታሪኩ ሦስቱ ዋና ዋና የእስራኤል ሕዝብ አባቶች አብርሃም፥ ይስሐቅና ያዕቆብ በእንግድነት ወደኖሩባት፥ እግዚአብሔር ለእነርሱና ለዘራቸው ሊሰጥ ቃል ወደገባላቸው ወደ ከነዓን ምድር ያመራል። በመጨረሻ ታሪኩ ስለ ጥቂቱ የያዕቆብ ቤተሰብ (70 ሰዎች) እንዴት ወደ ግብፅ እንደሄዱና ቁጥራቸው ወደ 2 ሚሊዮን አድጎ ታላቅ ሕዝብ እንደሆኑ ይነግረናል። ሕዝቡ ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ የግብፅን የባዕድ አምልኮት ባሕል ለመዱ፤ የጣዖት አምልኮአቸውንም ተማሩ (ዘጸ. 32፡1-10)። እናም ግብፅን እንደራሳቸው አገር አድርገው መቁጠር ጀመሩ (ዘኁ. 11፡4-6)።

የውይይት ጥያቄ፥ በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች በምድር ላይ በእንግድነት እንድንኖር የሚገባን ቢሆንም እንኳ ብዙ ጊዜ የባዕድ አምልኮዎችን ልማድ የምንለማመደው እንዴት ነው? (ዕብ. 11፡13 ና 1ኛ ጴጥ. 1፡1 ተመልከት)። 

የፔንታቱክ አብዛኛው ታሪክ የሚያተኩረው የተመረጡት የእግዚአብሔር ሕዝብ ማለት እስራኤላውያን ከዓመታት የባርነት ቆይታ በኋላ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዴት እንደተመለሱ ነው። የፔንታቱክ ታሪክ የሚያበቃው በዘዳግ. 34 ስለ ሙሴ ሞት በተጻፈው ትረካ ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የፔንታቱክ መግቢያ

ከዚህ በፊት በነበሩት ትምህርቶች፥ ስለብሉይ ኪዳን አንዳንድ የመግቢያ አሳቦች አጥንተናል፤ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነም ተመልከተናል። ከብዙ ዓመታት በፊት 39 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል ይሆኑ ዘንድ በአይሁዶች እንዴት እንደተለዩ ተምረናል። በዚህ ሳምንት ፔንታቱክ ወይም የሙሴ ሕግ ተብለው የሚጠሩትን የመጀመሪያዎቹ አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት መመልከት እንጀምራለን። 

ብሉይ ኪዳን የተጻፈው በሁለት ቋንቋዎች ነበር። አብዛኛዎቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት በዘመኑ የአይሁድ ቋንቋ በነበረው በዕብራይስጥ ነበር፤ ነገር ግን የባቢሎንና በመካከለኛው ምሥራቅ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ዋና የንግድ ቋንቋ በነበረው በአራማይክ የተጻፉ አንዳንድ የብሉይ ኪዳን ክፍሎችም አሉ። ለምሳሌ፡- ዳን. 2-7ና የዕዝራ አንዳንድ ክፍሎች የተጻፉት በአራማይክ ቋንቋ ነው። ይህ የሆነው በዚህ ጊዜ ብዙ አይሁድ በመካከለኛው ምሥራቅ ተበትነው በአሕዛብ መካከል በምርኮ ላይ ስለ ነበሩ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፥ ዘዳ. 28፡61፤ ኢያ. 8፡31፤ (ሉቃ. 2፡22)፤ 2ኛ ዜና 31፡3፤ (ሉቃ. 2፡23)፤ ነህ. 8፡3። የመጀመሪያዎቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ብዙ ጊዜ በአይሁድ ምን ተብለው ይጠሩ ነበር?

የመጀመሪያዎቹ አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አንዳንድ ጊዜ «ፔንታቱክ» እየተባሉ ይጠሩ ነበር። ፔንታቱክ የሚለው የግሪክ ቃል ትርጉም «አምስት ጥቅል መጻሕፍት» ማለት ነው። ይህም የሚያመለክተው በሙሴ የተጻፉትና በአይሁድ ዘንድ እንደ አንድ ክፍል የሚቆጠሩትን የመጀመሪያዎቹን አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ነው። ይህን ስም ብዙ ጊዜ የሚገለገሉበት በክርስቶስ ጊዜ የግሪክ ቋንቋ ይናገሩ የነበሩ አይሁድ ነበሩ። የዕብራይስጥ ቋንቋ ይናገሩ የነበሩ አይሁድ ግን ለእነዚሁ መጻሕፍት ሌሎች ስሞች ነበሯቸው። ብዙ ጊዜ «ሕግ» ወይም «ቶራህ» ብለው ይጠሯቸው ነበር። ቶራህ ለሕግ የተሰጠ የዕብራይስጥ ስም ነው። 

በመጽሐፍ ቅዱስ በአጠቃላይ የመጀመሪያዎቹ አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተለያዩ ስሞች ተሰጥተዋቸዋል። አንዳንድ ጊዜ «የሕግ መጻሕፍት»፥ «ሕግ»፥ «የሙሴ የሕግ መጻሕፍት»፥ «የሙሴ ሕግ»፥ «በሙሴ መጽሐፍ ውስጥ ያለ ሕግ»፥ «የጌታ ሕግ»፥ «የጌታ ሕግ መጽሐፍ» እና «የሕግ መጽሐፍ» ተብለው ተጠርተዋል። 

አይሁድ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በሙሉ የሚያከብሩና በእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት መጻፋቸውን የሚያምኑ ቢሆኑም ፔንታቱክ ወይም የሙሴ ሕግ መጻሕፍትን ከሁሉ አብልጠው ያከብሯቸዋል። 

የፔንታቱክ መጻሕፍት ጸሐፊ 

የብሉይ ኪዳን የመጀመሪያ መጻሕፍትን ማን ጻፋቸው? እስካለፈው 100 ዓመታት ድረስ አይሁድም ሆኑ ክርስቲያኖች ሙሴ እንደጻፋቸው ያምኑ ነበር፤ ምክንያታቸውም የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱስና በሽማግሌዎች ወግ ላይ ነው። ቀደም ሲል እንዳየነው፥ ከመጀመሪያዎቹ አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ስሞች አንዱ «የሙሴ ሕግ» የሚለው ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 24፡3-4 እና ዮሐ. 5፡46-47 አንብብ። በእነዚህ ቁጥሮች መሠረት የመጀመሪያዎቹን አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የጻፈው ማን ነው? 

ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም ያሉትን መጻሕፍት የጻፈው ሙሴ ነው ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ባይነግረንም እንኳ በፔንታቱክ ውስጥ የተካተቱ አንዳንድ ነገሮችን እርሱ እንደጻፋቸው ግልጽ ነው። በሲና ተራራ የተቀበላቸውን ሕግጋት እርሱ እንደጻፋቸው እናውቃለን። ከሙሴ ሞት በኋላ ኢያሱ ወዲያውኑ ተተክቶ ሕዝቡን መምራት ሲጀምር እንዲታዘዘው የተሰጠው፥ በሙሴ የተጻፈ መጽሐፍ ነበር፤ (ኢያሱ 1፡7-8 ተመልከት)። ከአዲስ ኪዳን ዘመን ቀደም ብሎ የመጀመሪያዎቹን አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የጻፈው ሙሴ እንደሆነ አይሁድ አምነው ነበር። በአዲስ ኪዳን ውስጥም ቢሆን የፔንታቱክ መጻሕፍት አብዛኛዎቹን ሙሴ እንደጻፈ ተጠቅሶአል። ዘጸአት (ማር. 7፡10)። ዘሌዋውያን (ሮሜ 10፡5)፤ ዘዳግም (ማቴ. 19፡7-8) የተጻፉት በሙሴ እንደሆነ ኢየሱስና ሌሎች በግልጥ ተናግረዋል። የሕግ መጻሕፍት አመዳደብ እንደ ሙሴ መጻሕፍት ሲሆን ይህም ሙሴ በጸሐፊነት የሚታይ መሆኑን ያመለከታል (ሉቃስ 24፡44 ተመልከት)።

በ1900 ዓ.ም. አካባቢ ግን ፔንታቱክን የጻፈው በእርግጥ ሙሴ ለመሆኑ ምሁራን ይጠራጠሩት ጀመር። የፔንታቱክን መጻሕፍት በሚመረምሩበት ጊዜ ከአንድ በላይ የሆኑ ጸሐፊዎች እንደጻፉት የሚያሳዩ በርካታ ነገሮችን አገኙ። ለምሳሌ፡- በኦሪት ዘፍጥረት ሁለት የተለያዩ የፍጥረት ትረካዎች አሉ (ዘፍ. 1 ና 2)፤ ሙሴ ከኖረበት ዘመን ከ500 ዓመታት በኋላ ይኖሩ የነበሩ የእስራኤል ነገሥታት ተጠቅሰዋል (ዘፍጥ. 36፡31)፤ እስከ ዘመነ መሳፍንት ድረስ ወደ ከነዓን ያልመጡ ፍልስጥኤማውያን ተጠቅሰው እናያለን (ዘፍጥ. 21፡34)፤ ደግሞም «እስከ ዛሬ ድረስ» የሚለው ቃል መጽሐፉ የተጻፈው ከሙሴ በኋላ መሆኑን የሚጠቁም ሐረግ ይመስላል (ዘፍጥ. 32፡32)። በተጨማሪም እነዚህ ምሁራን በአጻጻፍ ስልትና በቃላት አጠቃቀም ረገድ ያለው ልዩነት ራሱ የተለያዩ ጸሐፊዎች እንደጻፉት ያሳያል ይላሉ።

በዚህ ምክንያት የፔንታቱክ ጸሐፊ ማን ነው? የሚለውን ጥያቄ በሚመለከት አለመግባባት አለ። እነዚህ አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ስለተገኙበት መንገድ አምስት ዋና አመለካከቶች ወይም አሳቦች አሉ።

 1. የፔንታቱክን መጻሕፍት ሁሉ የጻፈው ሙሴ ነው። ሙሴ ያልጻፈው የፔንታቱክ ክፍል ከእርሱ ሞት በኋላ የተጻፈው ዘዳግም 34 ብቻ ነው። ይህንን አቋም የያዙ ሰዎች እንደሚሉት ሙሴ ሌሉች መጻሕፍት ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን እነዚህን አምስት መጻሕፍት ያዘጋጀና የጻፈ እርሱ ነው ይላሉ። አቋማቸውን ለመደገፍም የሚከተለውን መረጃ ይጠቁማሉ፡-

ሀ. ዘኁል. 33፡2 እና በፔንታቱክ ውስጥ ያሉ ሌሎች ጥቅሶች መጻሕፍቱን የጻፈው ሙሴ ነው ይላሉ። 

ለ. በብሉይና በአዲስ ኪዳን የሚገኙ ሌሎች መጻሕፍት ሙሴ የፔንታቱክ ጸሐፊ እንደሆነ ይናገራሉ፤ (ዘኁል. 24፡3-4ና ዮሐ. 5፡46-47)። 

ሐ. በአይሁድም ሆነ በክርስትና አፈ ታሪክ መሠረት ጸሐፊው ሙሴ እንደሆነ ይነገራል።

መ. መጽሐፉን በጥልቀት በማጥናት የምንረዳው ነገር ጸሐፊው የድርጊቱ የዓይን ምስክር እንዲሁም የግብፅን ቋንቋና ባሕል የሚያውቅ ሰው መሆኑን ነው። እነዚህን መመዘኛዎች ሊያሟላ የሚችል ከሙሴ የተሻለ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጨርሶ አልተጠቀሰም።

 1. ሙሌ የፔንታቱክ ዋነኛው ጸሐፊ ነው። ኦሪት ዘፍጥረትን በሚመለከት የተጻፉት ጽሑፎች በሙሉ ለይቶ፥ አቀናብሮና አስተካክሎ ያዘጋጀ እርሱ ነው። ከቀሩት አራት መጻሕፍትም አብዛኛውን የጻፈው እርሱ ነው፤ ነገር ግን ሙሴ ከሞተ ከረጅም ጊዜ በኋላ አንድ ያልታወቀ ሰው አንዳንድ ጥቃቅን ነገሮችን አክሉባቸዋል። አምስቱ መጻሕፍት ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁት በመጽሐፈ ኢያሱ መጨረሻ አካባቢ ወይም ምናልባት በነቢዩ ሳሙኤል ጊዜ ነው። 
 2. የመጀመሪያዎቹ አምስቱ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት በተለያዩ ሰዎች ሲሆን የተጻፉትም በብዙ መቶ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነው። ይህ አሳብ የተጀመረው በ1876 ሲሆን «በመረጃ የተደገፈ መላምት» ወይም «ጄ.ኢ.ዲ.ፒ. ቲዎሪ» በመባል ይታወቃል። ይህንን አመለካከት የሚደግፉ አብዛኛዎቹ ምሁራን ፔንታቱክም ሆነ የተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስሕተት የሌለበት እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን አያምኑም። የአይሁድን ሃይማኖታዊ ልምምድ ለማሳየት የጥንት ሰዎች የጻፉት አድርገው ማመኑ ይቀላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ዙሪያ እንደሚገኙ እንደ ሌሎች ሃይማኖታዊ መጻሕፍት ነው ይላሉ። እነዚህ ምሁራን በተአምራት፥ በነቢያትም ሆነ በመሳሰለው ለማመን ፈቃደኞች አይደሉም። ትንቢትና ተአምራትን ላለመቀበል አስቀድመው አእምሮአቸውን ያዘጋጁ ናቸው። ይህን መጽሐፍ ቅዱስን በመረዳትና በመተርጎም በኩል ተጽዕኖ ያደርግባቸዋል። ይህ አመለካከት በተለይ ላለፉት 50 ዓመታት ተከታዮች ያተረፈ ቢሆንም፤ በአሁኑ ጊዜ ግን እያሽቆለቆለ በመምጣት ላይ ይገኛል። ይህ አመለካከት ቀደም ብለን ባነሳነው ጉዳይ ላይ በማተኮር፥ ለፔንታቱክ መጻሕፍት አንድ ጸሐፊ ብቻ ሊኖር እንደማይችል ይናገራል። በመሠረቱ ይህ አመለካከት ፔንታቱክ ቢያንስ የአራት ዋና ዋና መጻሕፍት ጥርቅም ሆኖ በአራት መቶ ዓመታት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንደተጻፈ የሚያስተምር ነው።

ሀ. የመጀመሪያው መጽሐፍ የሚጠራው በዕብራይስጥ ቋንቋ የእግዚአብሔር ስም በሚጀመርበት «ጄ» በሚለው ፊደል ነው። ስሙም «ጄሆቫ» (ያህዌ) ነው። ይህ ጽሑፍ በ9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (ዓ.ዓ.) የያህዌ እግዚአብሔርን ታላቅነት ለማግነን በፈለጉ አይሁድ እንደተጻፈ ይናገራል። 

ለ. ሁለተኛው ጽሑፍ የሚጠራው አይሁድ ለእግዚአብሔር ከሰጡት «ኤሎሂም» ከሚለው ስም በተገኘው «ኢ» በሚለው ፊደል ነው። የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ከእስራኤል የሰሜኑ ክፍል የመጣ ሲሆን የጻፈውም በ8ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (ዓ.ዓ.) እንደሆነ የዚህ አመለካከት አራማጆች ይናገራሉ። ይህ ጸሐፊ «ኤሎሂም» በሚለው የእግዚአብሔር ስም ላይ አተኩሯል። 

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ሁለቱ ጽሑፎች ከተጻፉና ሰማርያ በ722 ዓ.ዓ. በአሦራውያን እጅ ከወደቀች በኋላ ከይሁዳ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ የሚታሰብ ሰው ወደ አንድ መጽሐፍ አጣምሮአቸዋል የሚል አሳብ ይሰነዝራሉ።

ሐ. ሦስተኛው ጽሑፍ ከመጨረሻው የፔንታቱክ መጽሐፍ በእንግሊዝኛ ዲዮተሮኖሚ ከሚለው ስም የመጀመሪያ ፊደል በመውሰድ «ዲ» ብለው ሰይመውታል። ይህ ሰው ኦሪት ዘዳግምን ከጻፈ በኋላ ከመጽሐፈ ኢያሱ እስከ 2ኛ ነገሥት ላሉት መጻሕፍት ደግሞ የመጨረሻ ማስተካከያ አድርጓል። ይህ የሆነው ከ630-600 ዓ.ዓ. በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን ሳይሆን አይቀርም ይላሉ። 

መ. አራተኛው ጽሑፍ የተጻፈው በአንድ ካህን (ቄስ) ነው ብለው ስለሚያምኑ በእንግሊዝኛ ካህን (ፕሪስት) ከሚለው ስም የመጀመሪያውን ፊደል በመውሰድ «ፒ» ብለው ሰይመውታል። ይህ መጽሐፍ በአምልኮ ሕግጋትና በፔንታቱክ ውስጥ በሚገኘው የትውልድ የዘር ሐረግ ላይ የሚያተኩር ነው። የተጻፈውም ከ500-450 ዓ.ዓ. ነው።

በመጨረሻ፥ በ450 ዓ.ዓ. ገደማ ካህን የነበረ አንድ የመጻሕፍት አዘጋጅ አራቱንም መጻሕፍት በመውሰድ አሁን ዘፍጥረት፥ ዘጸአት፥ ዘሌዋውያን፥ ዘኁልቁና ዘዳግም ወደምንላቸው መጻሕፍት አቀናጃቸው። የዚህ ፅንሰ አሳብ አራማጆች ይህን ያደረገው ካህን ዕዝራ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ። ይህም ማለት የፔንታቱክ የመጨረሻ ሥራ አሁን በእጃችን ባለው መልኩ የተጻፈው በ450 ዓ.ዓ. ነው ማለት ነው።

ብዙዎቹ የጥንት የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያዎች ፔንታቱክን በሚተረጉሙበት ጊዜ ይህንን ንድፈ ሃሳብ ተከትለዋል። እግዚአብሔር ቃሉን እንዲጽፉ ሰዎችን በመንፈስ ቅዱስ ነድቶአቸዋል፤ ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ፍጹም የተለየ መጽሐፍ ነው ብለን ካመንን፥ ይህ አመለካከት ጨርሶ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው።

 1. አራተኛው አመለካከት፥ በፔንታቱክ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ታሪኮች ከትውልድ ወደ ትውልድ በአፈ ታሪክ (ሥነ-ቃል) ተላልፈዋል የሚል ነው። ከዚያም እነዚህ በአፈ ታሪክ (ሥነ-ቃል) የተላለፉ መልእክቶች በተለያዩ ጸሐፊዎች አማካይነት ተጻፉ። በመጨረሻ እነዚህ መጻሕፍት በአንድ አቀናባሪ ተሰብስበው ተቀናጁ። በ586 ዓ.ዓ. ይሁዳ ከተማረከች በኋላ መጽሐፉ አሁን ባለበት መልኩ ተስተካከለ። 
 2. አንድ የመጨረሻ አመለካከት የሚለው፡- በባቢሎን ምርኮ ጊዜና አይሁድ ወደ ይሁዳ ከተመለሱ በኋላ (586-500 ዓ.ዓ.) የተለያዩ አዘጋጆች የዕብራውያንን ታሪኮች በሙሉ ሰብስበውና አስተካክለው አሁን በመጽሐፍ ቅዱሳችን በሚገኙ አምስት የተለያዩ መጻሕፍት መልክ አቀናበሩአቸው የሚል ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያዎቹን አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጨምሮ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነና ሥልጣኑም እግዚአብሔር ራሱ የተናገረን ያህል መሆኑን የምናምን ክርስቲያኖች በመሆናችን ከላይ የተመለከትናቸውን አብዛኛዎቹን አመለካከቶች መቃወም አለብን። የጻፉት የተለያዩ ሰዎች ናቸው ለሚለው አባባላቸው መልስ አለን። አብዛኞቹን የፔንታቱክ መጻሕፍት ክፍሎች የጻፈው ሙሴ ነው የሚለውን አሳባችንን የምንለውጥበት አንዳችም ምክንያት የለንም፤ ነገር ግን ከሙሴ በኋላ የነበሩ ጸሐፊዎች ሙሴ ከሞተ ከብዙ ዓመታት በኋላ ለኖሩ ሰዎች ግልጥ ለማድረግ የተወሰኑ ቃላትን ጨምረው ሊሆን ይችላል የሚለውን አሳብ ልንቀበል እንችላለን። ለምሳሌ «በእነዚያ ቀናት» እና «ከነዓን የፍልስጥኤም ምድር ሆነች» የሚሉትን ቃላት ጨምረው ይሆናል (ዘፍጥ. 10፡14፤ 21፡32)፤ ነገር ግን የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎችና ጌታ ኢየሱስ ራሱም እንዳረጋገጡት የፔንታቱክ ጸሐፊ ሙሴ ነው በሚለው አቋማችን እንጸናለን።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንድ ሰው ተአምራት የሚባሉ ነገሮች የሉም ብሎ ካመነ ይህ እምነቱ መጽሐፍ ቅዱስን በሚተረጉምበት መንገድ ላይ እንዴት ተጽዕኖ ሊያደርግ ይችላል? ለ) የእግዚአብሔርን ቃል በምንተረጉምበት ጊዜ በእኛ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ በማሰብ አስቀድሞ በአእምሮአችን ስለምንይዘው አሳብ ልንጠነቀቅ እንደሚገባ ይህ ምን ያስተምረናል? ሐ) ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ የተለያዩ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል በሚተረጉሙበት ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ተጽዕኖ ያደረጉባቸውን ትምህርቶች ዘርዝር፤ (ለምሳሌ፡- የይሖዋ ምስክሮች፥ ካቶሊኮች፡ የኦርቶዶክስ አማኞች፥ ቃለ ሕይወት፣ መካነ ኢየሱስ፥ ሰባተኛ ቀን አክባሪ አድቬንቲስቶች፥ ወዘተ)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመካከለኛው ምሥራቅ መልክዓ ምድር

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የአንድን ስፍራ መልክዓ ምድር መረዳት በዚያ ስፍራ የሚኖሩ ሰዎችን አኗኗር ለመረዳት እንዴት ይጠቅማል? ለ) መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳትና ለመተርጎምስ እንዴት ይጠቅማል?

የብሉይ ኪዳን ታሪክ እምብርት የከነዓን ምድር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ ስፍራ አራት ስሞች ተሰጥቶታል። በመጀመሪያ፥ ብዙ ጊዜ የሚጠራበት «ከነዓን» የሚለው ስም ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘፍ. 9፡18-27 ተመልከት። ከነዓን ማን ነው?

የኖኅ የልጅ ልጆች ከነበሩት መካከል ከነዓን የሚባለው አንዱ እንደ ነበረ በብሉይ ኪዳን እናነባለን። አባቱ በሠራው ኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔር ከነዓንን ለሴምና ለያፌት ዘሮች ባሪያ እንዲሆን ረግሞት ነበር። በዘፍጥረት 10 እንደምናነበው የከነዓን ዝርያዎች በዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ በዮርዳኖስ ወንዝና በሜዲትራኒያን ባሕር መካከል ሰፍረው ነበር። ይህ አካባቢ የኖኅ የልጅ ልጅ በሆነው በከነዓን ዝርያዎች ስም ከነዓን ተብሎ ተጠራ። ደግሞም ይህ አካባቢ ከነዓን ይባል የነበረው «የሐምራዊ ምድር» ለማለትም ነው። ምክንያቱም በከነዓን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች በዘመኑ ሀብታሞች ሊለብሱ የሚችሉትን ሐምራዊ ቀለም ያላቸው ልብሶችን ይሠሩ ስለነበር ነው። ጳለስጢና የሚለው ቃል ከኤፍራጥስ ጀምሮ እስከ ግብፅ ያለውን ምድር በሙሉ የሚያጠቃልል ሲሆን፥ ከነዓን የሚለው ቃል ግን በጳለስጢና ውስጥ ያለ አነስተኛ ምድርን የሚጠቅስ ነው።

ሁለተኛ፥ ምድሪቱ አንዳንድ ጊዜ «የተስፋይቱ ምድር» በመባል ትጠራለች። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ (በዘፍ. 15፡7) የከነዓንን ምድር ለአብርሃም ርስት አድርጎ እንደሚሰጠው ቃል ገብቶለታል። አብርሃምና ዝርያዎቹ ከ400 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ምድሪቱን ባይወርሱም እንኳ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል መሠረት የእነርሱ ነበረች። ለእስራኤል በርስትነት ተስፋ የተሰጠች ምድር ስለሆነች «የተስፋይቱ ምድር» ሆና ቆይታለች (ሕዝ. 48 ተመልከት)።

ሦስተኛ፥ ምድሪቱ አንዳንዴ «ጳለስጢና» ተብላ ተጠርታለች። ይህ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም፥ አሕዛብ ለከነዓን ምድር የሚሰጡት የተለመደ ስም ነው። (ስለ ፍልስጥኤማውያን፥ ስለ ለስጢናና ስለ ጳለስጢናውያን በትላንትና ትምህርታችን የተመለከትነውን ከልስ።)

አራተኛ፥ ምድሪቱ አንዳንዴ «እስራኤል» ተብላ ተጠርታለች። ይህ የሚያመለክትው ከ1400 ዓ.ዓ. . 70 ዓ.ም. እና ከ1948 ዓ.ም. ጀምሮ የአይሁድ ምድር መሆንዋን ነው። ከአይሁድ አባቶች አንዱ የሆነው ያዕቆብ በኋላ ስሙ እስራኤል ተብሎ እንደተለወጠ ይታወቃል (ዘፍ. 32፡28)። ስለዚህ እስራኤል የሚለው ስም የሚያመለክተው የያዕቆብን ዝርያዎችና በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ኪዳን መሠረት ስለወረሷት ምድር ነው።

እግዚአብሔር በጣም ትንሽ የሆነችውን የከነዓንን ምድር ይወርሱ ዘንድ ለአይሁድ የሰጠው ለምንድን ነው? እንደ አሜሪካ፥ ኢራቅ ወይም ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ትልልቅ አገሮች ለምን አልሰጣቸውም? ስለከነዓን ምድር በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው?

የከነዓን ምድር ትልቅ አይደለችም። የእስራኤል መንግሥት በጣም ትልቅ የነበረችው በዳዊትና በሰሎሞን ዘመን ሲሆን በዚያን ጊዜም 800 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 200 ኪሎ ሜትር ስፋት ነበራት፤ ይህም ከአሰብ እስከ አዲስ አበባ ያለው ርቀት ማለት ነው። ብዙ ጊዜ ግን የእስራኤል ምድር 225 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 100 ኪሎ ሜትር ስፋት ብቻ ነበራት፤ ይህ ከአዲስ አበባ እስከ ሻሸመኔ ድረስ ካለው ርቀት ጋር የሚወዳደር ነው።

ከነዓን የዓለም እምብርት ለመባል ትችላለች፤ ምክንያቱም ሁለት ዋና ዋና አህጉራት ማለትም አፍሪካና እስያ የሚገናኙባት ቦታ ናት። በጥንት ዘመን ደግሞ በጣም ጠቃሚ የነበረችው:- በአፍሪካ፥ በእስያና እንዲሁም በአውሮጳ ዋና የንግድ መሥመር ላይ ትገኝ ስለነበረ ነው። አሁንም ቢሆን በታሪክ ውስጥ እጅግ ጠቃሚ ሚና መጫወቷን ቀጥላለች፤ ምክንያቱም መካከለኛው ምሥራቅ በነዳጅ ዘይት ከፍተኛ ሀብት ያለው አካባቢ ስለሆነ ነው። የዚህ ዘመን ሥልጣኔ በነዳጅ ዘይት ላይ የተመሠረተ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እነዚህን ስፍራዎች ለመያዝ አሕዛብ በሚያደርጉት ትግል በምድር ላይ የመጨረሻው ጦርነት የሚካሄደው በእስራኤል ነው ይላል። በተጨማሪ፥ የዓለም የሥነ- መለኮት ትምህርት ማዕከልም ናት። የዓለም ሦስቱ ዋና ዋና ሃይማኖቶች ይሁዲነት፥ ክርስትናና እስልምና መሠረታቸውን ያገኙት ከእስራኤል ነው።

በጥንቱ መካከለኛ ምሥራቅ የነበሩ ታላላቅ አገሮች

የተለያዩ የጥንት ሕዝቦች የት እንደ ነበሩና ከአሁኑ ዓለም ጋር እንዴት እንደሚወዳደሩ ለማወቅ የጥንቶቹን ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ሕዝቦችና በጊዜያችን ከየትኛው አገር እንደሆኑ እንመለከታለን። 

፩. ኢትዮጵያ ወይም ኩሽ፡- በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ከግብፅ በስተደቡብ ቀጥሉ የሚገኘው አገር ኩሽ ተብሎ ይጠራ ነበር። ኋላም በሰፕቱዋጀንት የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግሪኮች ይህንን ምድር ኢትዮጵያ ብለው ጠርተዋል፤ ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኩሽና ኢትዮጵያ የአንድ ስፍራ ሁለት ስሞች ናቸው። የእንግሊዝኛና የአማርኛ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱሶች ለዚህ ምድር «ኢትዮጵያ» የሚለውን የግሪክ ስም ይጠቀማሉ። የኩሽ ወይም የኢትዮጵያ ምድር ከአሁንዋ ኢትዮጵያ ጋር አንድ አይደለም፤ ነገር ግን በዓለም ታሪክ ውስጥ «ኑቢያ» ተብላ ትጠራ የነበረችው ዛሬ በሰሜን ሱዳን የምትገኝ አገር ነች። በመጽሐፍ ቅዱስ መልክዓ ምድር መሠረት ኑቢያ የመጨረሻዋ ደቡባዊ ክፍል ያለችው አገር ነች። የአሁንዋ ኢትዮጵያ መጀመሪያ ስምዋን ያገኘችው ከግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ወይም ኩሽ ብሉ መጽሐፍ ቅዱስ ከጠራው ስፍራ ጋር ሙሉ ለሙሉ ተመሳሳይ አይደለችም። የአሁንዋ ኢትዮጵያ ከአክሱም መንግሥት ውስጥ በተለያዩ ነገሥታት አመራር ሥር የነበረችና አሁን ወዳለው የክልል ዳርቻ እያደገች የመጣች ነች።

የሳባ ሕዝብ ዛሬ የመን ተብሎ በሚጠራው በደቡብ ምዕራብ ዐረቢያ የነበረ ሳይሆን አይቀርም። ነገር ግን አንዳንዱ የግዛቱ ክፍል በቀይ ባሕር ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ተስፋፍቶ ሊሆን ይችላል። 

፪. ግብፅ፡- ልክ እንደ ጥንትነቷ ያለች ብቸኛ አገር ግብፅ ናት። በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ የምትገኝና ከጥንቱ ዓለም ታላላቅ ሥልጣኔዎች የአንደኛው ማዕከል የነበረች አገር ናት። በብሉይ ኪዳንም በተደጋጋሚ አገሪቱ በዚህ ሁኔታ ተጠቅሳለች። የሕይወቷ ሁሉ ምንጭ የሆነው ከኢትዮጵያና ከሱዳን የሚፈሰው የዓባይ ወንዝ ነው። የዓባይ ወንዝ በበጋም ሆነ በክረምት ጊዜ ለሰብልና ለከብቶች ውኃን ስለሚሰጥ የግብፅ ምድር ሁልጊዜ ምግብ ያገኛል። አብርሃምና ያዕቆብ በድርቅ ጊዜ ወደ ግብፅ የሄዱት በዚህ ምክንያት ነው። 

፫. ከነዓን፡- የከነዓን ምድር የሚገኘው ከግብፅ በስተሰሜን ነው። በመጠን አነስተኛ ብትሆንም፥ የተለያዩ ሕዝቦችን ይዛለች። በዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ የጥንት እስራኤል ጠላቶች የነበሩ ሦስት የአሕዛብ መንግሥታት ነበሩ። በደቡብ ኤዶም፥ ከኤዶም በስተሰሜን ሞዓብና ከሞዓብ በስተሰሜን ደግሞ አሞን ነበሩ። እነዚህ አገሮች ይገኙ የነበሩት በአሁኑ ጊዜ ዮርዳኖስ ተብሎ በሚታወቀው አገር ምዕራባዊ ጫፍ ነው።

ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ የእስራኤል ምድር ይገኛል። ታሪክ ሁሉ እስራኤላውያን የኖሩት በከነዓን ተራራማ አገር በአገሪቱ በስተ ደቡብ ከቤርሳቤህ በሰሜን እስከሚገኘው ዳን ድረስ ነው። በምዕራብ ሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ በዘመነ መሳፍንት የእስራኤላውያን ዋና ጠላቶች የነበሩት ጳለስጢናውያን ይገኛሉ። ልክ እንደ ጥንቱ ዘመን ይህ ምድር ዛሬ እስራኤል ተብሎ ይጠራል። ነገር ግን ከዚህ አካባቢ የተወሰነው ክፍል በዘመናችን ባሉ ፍልስጥኤማውያን፥ በሶርያና በዮርዳኖስ የይገባኛል ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።

፬. ሶሪያ፡- ከእስራኤል በስተ ምሥራቅ የአራሚያን ወይም የሶርያ ሕዝቦች ይገኛሉ። ዋና ከተማቸው ደማስቆ የሆነው ሶርያውያን ብዙ ጊዜ የእስራኤል ጠላቶች ሆነው ሲቆዩ፥ በተለይ የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ተከፍሎ በነበረ ጊዜ ዋና ጠላቶች ነበሩ። ዛሬ ይህ ሕዝብ ያለበት አገር ሶርያ ተብሎ ይጠራል። 

፭. ፎኒሺያ (ፊንቄ)፡- ከእስራኤል በስተሰሜን ምዕራብ በሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ ፎኒሺያ (ፊንቄ) የምትባል አገር ነበረች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ አካባቢ በተለይ የሚታወቀው በዋና ከተማዎቹ በጢሮስና በሲዶና ነው። ይህ ሕዝብ በጣም የሚታወቀው የሜዲትራኒያን ባሕር በሙሉ ይካሄድ በነበረው የባሕር ላይ ንግድ ነው። ዳዊትና ሰሎሞን ቤተ መቅደሱንና ቤተ መንግሥቱን ለመገንባት የሠለጠነ የሰው ኃይል ፍለጋ ወደ ጢሮስ ሄደው ነበር። በአሁኑ ጊዜ ይህ አካባቢ ሊባኖስ በመባል ይታወቃል።

፮. አሦር፥ ባቢሎን፥ ሜዶንና ፋርስ፡- ከእስራኤል በስተሰሜን ምሥራቅ ራቅ ብሉ አሦር፥ ባቢሎን፥ ሜዶንና ፋርስ የሚባሉ አራት አገሮች ነበሩ። የእነዚህ አራት አገሮች ሕዝቦች በተለይ መስጴጦምያ በሚባለው አካባቢ ይኖሩ ነበር። መስጴጦምያ የሚባለው አካባቢ የፋርስ ባሕረ ሰላጤን ይዞ በስተሰሜን ምዕራብ ከሁለት ታላላቅ ወንዞች ማለትም ከኤፍራጥስና ጤግሮስ አጠገብ የሚገኝ ነው። 

ሀ. አሦር፡- አሦር የሚገኘው ከመስጴጦምያ በስተሰሜን በጤግሮስ ወንዝ አጠገብ ነበር። ዋና ከተማው ነነዌ ነበረ። በ700 ዓ.ዓ. አሦር በመስጴጦምያ፥ ጳለስጢናና በግብፅ ሁሉ ላይ የበላይነት አግኝታ የዓለም ኃያል መንግሥት ሆነች። እግዚአብሔር የሰሜኑን የእስራኤልን መንግሥት ለመቅጣትና ወደ ምርኮ ለመውሰድ አሦርን ተጠቀመ። አሦር ትገኝ የነበረው በአሁኒቱ ኢራቅ ድንበሮች ውስጥ ነው። 

ለ. ባቢሎን፡- ባቢሎን የምትገኘው ከመስጴጦምያ በስተደቡብ ራቅ ብላ ነበር። ዋና ከተማዋም ባቢሎን ተብላ ትጠራ ነበር። በ600 ዓ.ዓ. የባቢሎን መንግሥት የዓለም ኃያል መንግሥት በመሆን መስጴጦምያን፥ ጳለስጢናንና የግብፅን መንግሥታት ተቆጣጠረች። እንደምታስታውሰው፥ የደቡብ ይሁዳን መንግሥት ያሸነፈውና ወደ ግዞት የወሰደው የባቢሎን መንግሥት ነበር። ባቢሎንም ትገኝ የነበረው በአሁኑ የኢራቅ መንግሥት ውስጥ ነበር። 

ሐ. ሜዶን፡- ሜዶን ከመስጴጦምያ በስተሰሜን ምዕራብ የምትገኝ በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሱና በሩቅ ሰሜን ከሚገኙ አገሮች አንዷ ናት። በመጽሐፍ ቅዱስ ከፋርስ መንግሥት ጋር እንደተዋሐደችና የሜዶንና የፋርስ መንግሥትንም እንደመሠረተች ተጽፏል። ይህ መንግሥት በ539 ዓ.ዓ. ተጀምሮ በ331 ዓ.ዓ. ወድቋል። የሜዶን መንግሥት የሚገኘው በሰሜን ኢራን ነበር። 

መ. ፋርስ፡- የፋርስ መንግሥት የሚገኘው ከሜዶን በስተደቡብ ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ አጠገብ ነበር። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ፋርስ ከሜዶን መንግሥት ጋር በመተባበር፥ አይሁድን ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ቤተ መቅደሳቸውን እንዲሠሩ እንደፈቀደ ተጽፏል። ፋርስም የምትገኘው በአሁኗ ኢራን ውስጥ ነበር።

፯. ትንሿ እስያ፡- ጥንታዊት የሆነችው ትንሿ እስያ ብዙ ጊዜ በብሉይ ኪዳን ያልተጠቀሰች ቢሆንም፥ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ግን ሐዋርያው ጳውሎስ በወንጌል አገልግሎት ጉዞው የሄደባት ስለነበረች በተደጋጋሚ ተጠቅሳለች። ነገር ግን በብሉይ ኪዳን ዘመን ትንሿ እስያ የኬጢያውያን ምድር ነበረች። ኬጢያውያን ጳለስጢናን ከ1400 – 1190 ዓ.ዓ. የገዙ ነበሩ። ብዙ ምሁራን እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር በሲና ተራራ ያደረገው ቃል ኪዳን የኬጢያውያን ነገሥታት በቁጥጥራቸው ሥር ካዋሏቸው ሕዝቦች ጋር ካደረጉት ቃል ኪዳን ጋር ተመሳሳይ እንደነበር ይገምታሉ። ትንሿ እስያ በአሁኑ ጊዜ ቱርክ በመባል ትታወቃለች። 

የከነዓን መልክዓ ምድር 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ዓይነት የመሬት አቀማመጦችን ዘርዝር። ለ) ብዙ ሕዝቦች የሚኖሩት በየትኛው ዓይነት ምድር ላይ ነው?

የከነዓን ምድር በአካባቢው ከሚገኙት «ለም አገሮች» ውስጥ አንዱ ነው። ይህ የአዲስ ጨረቃ ቅርፅ ያለው ለም ምድር ከጤግሮስና ኤፍራጥስ ወንዞች አጠገብ ካለው ከመስጴጦምያ ጀምሮ ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር በመዝለቅ፡ ከግብፅ ወንዝ ዳርቻ በስተደቡብና ከዓባይ ወንዝ በስተደቡብ ወዳለው አካባቢ ይደርሳል። በእነዚህ ለም አገሮች ብዙ ዝናብና ወንዞች ስላሉ ሰዎች በቂ እህል ያበቅሉ ነበር። አብዛኛው የጥንት ሥልጣኔ የተጀመረው በዚህ ክልል ነው። በዚህም ለም ክልል ነው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የተፈጸመው።

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የከነዓንም ምድር ብዙ የተለያየ ዓይነት የመሬት አቀማመጥ ነበረው። በሰሜን የሐርሞን ተራራ ነበር። ይህ ተራራ 2800 ሜትር ከፍታ ያለው ረጅም ተራራ ነበር። ተራራው ብዙ ጊዜ በበረዶ የተሸፈነ ነበር። በደቡብ በኩል በዓለም ዝቅተኛ ስፍራ የሆነው ሙት ባሕር ይገኛል። እርሱም ከባሕር ጠለል በታት 400 ሜትር ነበር። ሙት ባሕር የተባለው፥ በውኃው ውስጥ ምንም ነገር በሕይወት እንዳይኖር የሚያደርጉ በርካታ ንጥረ ነገሮች ስላሉበት ነው።

በብሉይ ኪዳን ታላቁ ባሕር በመባል ይታወቅ በነበረው በሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ አጠገብ ያለው የከነዓን ምድር ሜዳማና ለም ነበር። አንድ ሰው ከባሕሩ በስተምሥራቅ ሲጓዝ የምድሪቱ ከፍታ እየጨመረ ይመጣና የከነዓን መካከለኛ ምድር ተራራና ኮረብታ የሚበዛበት ክልል ሆኖ እናገኘዋለን። በጥንት ዘመን የባሕር ዳርቻዎች በአሕዛብ መንግሥታት ተይዘው ስለነበር ከእስራኤላውያን አብዛኛዎቹ የሚኖሩት በእነዚህ ተራሮች ላይ ነበር። ይህ መሬት በባሕር ዳር እንደሚገኘው ለም አልነበረም። ከከነዓን በስተምሥራቅ ሁለት ትላልቅ የውኃ ክፍሎች ነበሩ። በአዲስ ኪዳን ገሊላ በተባለው አካባቢ ማለት በስተሰሜን የገሊላ ባሕር ነበር። ይህ ንጹሕ የሆነ የሐይቅ ውኃ ብዙ የተለያዩ ስሞች ነበሩት። ብዙ ጊዜ በብሉይ ኪዳን የኪኔሬት ባሕር በመባል ይታወቅ ነበር (ዘኁ. 34፡11)። በተጨማሪ «የጌንሳሬጥ ባሕር» (ሉቃስ 5፡1) እና «የጥብርያዶስ ባሕርም» ይባል ነበር (ዮሐ. 6፡ 1)።

የገሊላ ባሕር ከእርሱ ተነሥቶ ወደ ታች ወደ ሙት ባሕር የሚፈሰው የዮርዳኖስ ወንዝ ምንጭ ነበር። ምድሪቱ በመካከለኛው ከነዓን ካሉት ተራራማ ስፍራዎች ወደ ታች በማሽቆልቆል ከባሕር ጠለል በታች ወደ ሆነው ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ትወርዳለች። ምድሪቱ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ ወደ አንድ ሰፊ ሜዳ ፈጥና ትዘረጋለች። በዚህ ደልዳላ ሜዳ ነበር የጋድ፥ የሮቤልና የምናሴ ነገድ እኩሌታዎች የሰፈሩት። በዚህ ደልዳላ ሜዳ በምዕራባዊና ደቡባዊ ክፍል ዘላን ነገዶች ብቻ የሚኖሩበት ድንጋያማ በረሃ ነበር።

የአንድን ሕዝብ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ መረዳት ያንን ሕዝብ ለማወቅ በጣም ይረዳል። ለምሳሌ፡- አንድ ሰው የኦጋዴንን ወይም የሰሜን ኢትዮጵያን መልክዓ ምድር ሳያውቅ ለዘመናት በኢትዮጵያ ላይ የተካሄዱትን የተለያዩ ጦርነቶች ወይም የአውሮጳውያንን ለቅኝ ግዛት መቋመጥ እንዴት እንደተጀመረ መረዳት ያስቸግረዋል። በተመሳሳይ መንገድ የከነዓንን ምድር አቀማመጥ ማወቅ መጽሐፍ ቅዱስን የበለጠ ለመረዳት ይጠቅማል። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ሁልጊዜ ለምን ወደ ኢየሩሳሌም ስለ «መውጣት» ይናገራል? ምክንያቱም ኢየሩሳሌም ያለችው በአቅራቢያዋ ከሚገኙ ሌሎች ስፍራዎች ሁሉ ከፍ ብላ ስለሆነና ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም ለመድረስ ሁልጊዜ ወደ ላይ መውጣት ስላለባቸው ነው።

የከነዓንን መልክዓ ምድር መረዳት ስለ እስራኤል የሚከተሉትን ነገሮች ለመረዳት ይጠቅመናል፡-

 1. እስራኤል በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ የነበረችበትን ምክንያት ለመረዳት ይጠቅመናል። ከነዓን የሦስቱ አህጉራት ማለት (የአውሮጳ፥ የእስያና የአፍሪካ) የንግድ ማዕከል ነበረች። ይህንን የንግድ ማዕከልነት የሚቆጣጠር ሁሉ ኃያልና ሀብታም ይሆን ነበር። 
 2. በነጋዴዎችና በገበሬዎች መካከል ትግል የተፈጠረው ለምን እንደነበር ያስረዳናል። ከነዓን የንግድ መናኸሪያ በመሆንዋ ምክንያት አንዳንድ እስራኤላውያን ከግብርና ይልቅ ንግድን ለመተዳደሪያነት መረጡ። በዚህም ምክንያት ሀብታም ለመሆን ችለው ነበር። ሀብታቸውን ግን ብዙ ጊዜ ድሀ የሆኑ ገበሬዎችን ለመጨቆን ይጠቀሙበት ነበር። በነቢያት መጻሕፍት ውስጥ ከተወገዙ ሥራዎች አንዱ ድሆችን መጨቆን ነው።
 3. የከነዓን ምድር በጣም ትንሽ ነበር። ብዙ ጊዜ ርዝመቱ ከ240 ኪሉ ሜትር ስፋቱ ደግሞ ከ160 ኪሎ ሜትር የማይበልጥ ነበር። ይህች ትንሽ ምድር የአይሁድን ሃይማኖት ላለመቀበል ጸንተው በተቃወሙ የአሕዛብ መንግሥታት ተከብባ ነበር። አይሁድ ከአሕዛብ ጋር በቅርብ ተወዳጅተው መኖራቸው ከእነርሱ ጋር በጋብቻ የመጣመራቸው አንዱ ችግር ሆኖ ቆይቷል። እንዲሁም አሕዛብ የአይሁድን ሃይማኖት ብዙ ጊዜ ለምን እንዳበላሹት ያስረዳናል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን እነዚህ ተመሳሳይ ችግሮች እንዴት ይታያሉ?

በብሉይ ኪዳን የአይሁድ በእስራኤል ምድር የመኖር አሳብ ጥልቅ የሆነ የሥነ- መለኮት ትምህርት ነበረው። እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳንን ባደረገ ጊዜ፥ የቃል ኪዳኑ አንድ ክፍል ምድራዊ የሆነው ከነዓን ነበር። እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጠው ተስፋ ነበር። ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ መሳፍንት ድረስ ያለው ታሪክ በአብዛኛው የሚናገረው እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን ለመጠበቅ የከነዓንን ምድር እንዴት ለአይሁድ እንደሰጠ ነው። እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር በገባው ቃል ኪዳን መሠረት የእርሱን ሕግ የመታዘዝ ሽልማት በምድሪቱ ያለማቋረጥ መኖር እንደሚሆን ተናግሮ ነበር። ሰላምና ብልጽግና ይኖራቸዋል፤ ነገር ግን በቃል ኪዳኑ መሠረት የእርሱን ሕግ ያለመጠበቅ ከምድሪቱ የመውጣትን ችግር እንደሚያመጣም ሳያስጠነቅቃቸው አላለፈም። የቀረው አብዛኛው የብሉይ ኪዳን ታሪክ የሚያሳየው እስራኤላውያን ባለማቋረጥ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው ከአሕዛብ ጋር ጦርነት ወደማድረግና ከዚያም ተሸንፈው በአሕዛብ መንግሥታት ወደ ምርኮ የመወሰዳቸው ታሪክ ነው። በነቢያት መጻሕፍት እግዚአብሔር ወደ ምድሪቱ እንደገና እንደሚመልሳቸውና በሰላም እንደሚኖሩ ለአይሁድ ቃል ገብቶላቸው ነበር። በእርግጥ አይሁድ ከተበተኑበት የዓለም ክፍል እንደሚመለሱና በከነዓን እንደሚኖሩ ቃል ተገብቶላቸዋል። በዚያን ጊዜ መሢሐቸው ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በእነርሱ ላይ ይነግሣል። አይሁድ ለእስራኤል ምድር ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር ለመረዳት በጣም አዳጋች ቢሆንም፥ የብሉይ ኪዳን ቃል ኪዳኖችን በሙሉ ከተመለከትንና ከምድራዊቷ የእስራኤል ምድር ጋር ያለውን ግንኙነት ከተገነዘብን፥ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ብቻ ሳይሆን የእስራኤል ሕዝብ የጥንት ግዛታቸውን በሙሉ ለመቆጣጠር ያላቸውን ጥብቅ ፍላጎትም እንረዳለን። ዛሬ የእስራኤል ሕዝብ በምድር መኖሩ እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እያከበረ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ብሉይ ኪዳንን ማወቅ በዚህ ዘመን በአይሁድና በዐረብ መካከል ስላለው ትግል ለመገንዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?

ይህ የእስራኤል ጥንታዊ ታሪክ ክለሳና የመልክዓ ምድር መለስተኛ ጥናት ብሉይ ኪዳን የተጻፈበትን ጊዜ ለመረዳት እጅግ የሚጠቅም ነው። የጥንት ሰዎች የኖሩበትን ዘመንና ቦታ ስናውቅ እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን ለእነርሱ ሲገልጥ ምን ማለቱ እንደ ነበር የበለጠ እንረዳለን። ይህ ለቃሉ የምንሰጠውን ትርጉም የበለጠ ትክክል ያደርገውና በምናስተምርበትና በምንሰብክበት ጊዜ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» በማለት እንደ ጥንት ሰዎች መናገር እንድንችል ያደርገናል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ታሪክ ጥናት

የውይይት ጥያቄ፥ የዓለምን፥ የኢትዮጵያንና የራስህንም ነገድ የሚመለከቱ ታሪኮችን ማወቅ ለምን ያስፈልጋል?

ሕይወታችን በሙሉ በታሪክ፥ ወይም ባለፈው ጊዜ በእኛ ሕይወት ውስጥ በተፈጸመውም ሆነ በዓለም ዙሪያ በመሆን ላይ ባሉት ክስተቶች ተጽእኖ ሥር ነው። ለምሳሌ፡- ኢጣሊያን፥ ሩሲያን፥ አሜሪካን፥ እንግሊዝን፥ ወዘተ ሳናውቅና ከኢትዮጵያ ጋር ስላላቸው ግንኙነት ሳንረዳ፥ አዲሲቷን ኢትዮጵያ መረዳት ያስቸግረናል። እነዚህ ሕዝቦች ሁሉ በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተጽእኖ ስለነበራቸው ያ ተጽዕኖ አሁንም ድረስ ውጤት አለው። እንዲሁም ደግሞ የምኒልክን ወይም የኃይለ ሥላሴን መንግሥት ሥረ-መሠረት ሳናውቅ አዲሲቷን ኢትዮጵያን ለመረዳት አንችልም። ለእነዚህ የተለያዩ ሕዝቦችና አገሮች ያለን አመለካከት የተለያየ ቢሆንም፥ ሁሉም ግን በእኛ ላይ ያሳደሩት ተጽዕኖ አለ። ያለፉትን ክስተቶች የበለጠ በተረዳን ቁጥር በአሁኑ ጊዜ በአገራችን የሚደረገውን ነገር በተሻለ ሁኔታ እየተረዳን እንሄዳለን። 

መጽሐፍ ቅዱስን ስለመረዳትም ተመሳሳይ ነገር ማለት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ መጽሐፍ ነው። በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተጻፉ ታሪኮች ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጸሙ የእውነተኛ ክስተቶች ታሪክ ነው። በዚያ ዘመን የነበሩ ታሪኮችንና የምድሪቱን ሁኔታ የበለጠ በተረዳን ቁጥር፥ መጽሐፍ ቅዱስን በተሻለ ሁኔታ እንረዳለን። ለምሳሌ በከነዓን ምድር ላይ የነበራቸውን ሚና ለመረዳት ስለ ግብፅ፥ ባቢሎን፥ ፋርስ፥ ሮም፥ ግሪክ ወዘተ ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። የአይሁድና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ከዓለም ታሪክ ጋር የተሳሰረ ነው። ይሁን እንጂ ከዓለም አመለካከት አንጻር አይሁድ በዓለም ታሪክ ውስጥ መጠነኛ ሚና ተጫውተዋል። ከእግዚአብሔር አመለካከት አንጻር ግን የታሪክ እምብርት ናቸው። እግዚአብሔር ስለመረጣቸው፥ መጽሐፍ ቅዱስን በእነርሱ በኩል ስለሰጠ፥ መሢሑ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደዚህ ዓለም በእነርሱ በኩል ስለላከ ወዘተ. አይሁድ ከሌላው ሕዝብ ሁሉ ይልቅ እጅግ አስፈላጊ ሕዝብ ናቸው። ይህም ማለት አይሁድ በትውልዳቸው ከሌላ ዘር የተሻሉ ናቸው ማለት አይደለም። ነገር ግን ዓለምን በካህንነት እንዲያገለግሉ በእግዚአብሔር ተመርጠው ነበር፤ (ዘጸ. 19፡5-6)።

ብሉይ ኪዳን የዓለምን ሕዝቦች ታሪክ ለመናገር አይፈልግም። በግብፅና በመሰጴጦምያ ስለነበሩት አስደናቂ የሥልጣኔ ክስተቶች አያስተምርም፡፡ እነዚህን ሕዝቦች የሚጠቅሰው ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በነበራቸው ግንኙነት አንጻር ብቻ ነው። ብሉይ ኪዳን ከምዕራቡ ዓለምና ከመካከለኛው ምሥራቅ አስቀድሞ ስለታየው የቻይና ታላቅ ሥልጣኔ የሚናገረው ነገር የለም።

ብሉይ ኪዳን እጅግ ጥንታዊ መጽሐፍ ነው። በውስጡ የያዛቸው ታሪኮች ወደማይታወቅ ኋለኛ ዘመን ይሄዳሉ፤ ስለዚህ አንዳንድ ድርጊቶች የተፈጸሙበትን ዘመን መናገር አስቸጋሪ ነው። ለምሳሌ፡- ዓለም የተፈጠረችበትን አዳምና ሔዋን በምድር ላይ መኖር የጀመሩበትን ዘመን በትክክል መናገር የሚቻልበት መንገድ የለም፤ ነገር ግን በከርሰ-ምድር ጥናት አማካይነት እርግጠኛ ልንሆንባቸው የምንችል ድርጊቶች የተፈጸሙባቸው ዘመናትም አሉ። ለምሳሌ፡- አብዛኛዎቹ የእስራኤል ነገሥታት የነገሡበትን ጊዜ በአንድና በሁለት ዓመት ልዩነት መወሰን ይቻላል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የሚከተሉትን ሰዎች በታሪካዊ ቅደም ተከተል አስቀምጥ፡- ዳዊት፥ አዳምና ሔዋን፥ ሄኖክ፥ ኖኅ፥ ሳኦል፥ አብርሃም፥ ሰሎሞን። ለ) በብሉይ ኪዳን ታሪክ ውስጥ እጅግ ጠቃሚ ሚና የተጫወቱ ሌሎች የብሉይ ኪዳን ሰዎችን ጥቀስ።

የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች የታሪክን ዘመናት ይቆጥራሉ። ቻይናዎች የራሳቸው መንገድ አላቸው። አይሁድ ከፍጥረት ጀመረ ብለው የሚናገሩት የራሳቸው መንገድ አላቸው። ክርስቲያኖችም የራሳቸው መንገድ አላቸው። ዛሬ አብዛኛው የዓለም ሕዝብ የክርስቲያንን የቀን መቁጠሪያ ይከተላል። ክርስቲያኖች ታሪክን በሁለት ታላላቅ ዘመናት ይከፍሉታል። የመጀመሪያው ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት (ዓመተ ዓለም) ይባላል። ይህ ዘመን ከዓለም ፍጥረት ይጀምርና እስከ ክርስቶስ መወለድ ድረስ ይቀጥላል። ሁለተኛው ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለው ሲሆን በአማርኛ ዓመተ ምሕረት (ዓ.ም.) ብለን እንጠራዋለን። (በእንግሊዝኛ ኤ.ዲ. ተብሎ ሲታወቅ የመጣውም ከላቲኑ «አኖ ዶሚኒ» ማለትም «የጌታችን ዓመት» ነው።) በክርስቲያኖች የቀን መቁጠሪያ ዓመቱ ወደ ኢየሱስ ልደት በቀረበ መጠን ቁጥሩ እየቀነሰ ይመጣል። ከክርስቶስ ልደት በኋላ ቁጥሩ እየጨመረ ይመጣል። የሚከተለውን መግለጫ ተመልከት፡-

አብርሃም (2000 ዓ.ዓ.) 

                  ዳዊት (1000 ዓ.ዓ.)

                                 ክርስቶስ (አልቦ ዜሮ (0) ዓ.ዓ.)

                                                          አሁን (2019 ዓ.ም.)

በብሉይ ኪዳን ዘመን ቁጥሩ እንዴት እያነሰ ይሄድ እንደነበር ወደ ክርስቶስ ደግሞ እየቀረበ እንደመጣ ከከላይ የቀረበወን ገለጻ ልብ በል። ከክርስቶስ በፊት በ2000 ዓመታት ገደማ የኖረው አብርሃም ከክርስቶስ ልደት በፊት 1000 ዓ.ዓ. ገደማ ከኖረው ከዳዊት ዘመን የበለጠ ቁጥር አለው። በሌላ አንጻር ስናየው ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደ ሁለት ሺህ አስራ ዘጠኝ ዓመታት አልፈዋል ማለት ነው።

በኢትዮጵያና በአውርጳ የዘመን አቆጣጠር መካከል ልዩነት የሚታየው ለምንድነው? ምክንያቱ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ጊዜ በሚመለከት አለመግባባት በመኖሩ ነው። ሰዎች የክርስቲያንን የቀን መቁጠሪያ ይጠቀማሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ዘመን ቀን አቆጣጠርን ማንም አልጀመረም። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ መቼ እንደተወለደ ትክክለኛውን ጊዜ ሊያውቁ አልቻሉም። ምዕራባውያን አገሮች የተከተሉት ግሪጐሪ የተባለው ሰው የጀመረበትን የቀን አቆጣጠር ነበር። ይህም የቀን መቁጠሪያ በ1582 ዓ.ም. የጀመረ ሲሆን የግሪጐሪያን የቀን መቁጠሪያ በመባል ይታወቃል። ኢትዮጵያ ደግሞ ሌላ ቀን መቁጠሪያን ትጠቀማለች። ሁለቱም የቀን መቁጠሪያዎች አዲሱን ዘመን የሚጀምሩት ከኢየሱስ ልደት ቢሆንም፣ እነዚህ የቀን መቁጠሪያዎች በስምንት ዓመታት ይለያያሉ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ በተለያዩ ክፍለ ጊዜያት ይከፍላሉ። ቀጥሉ በብሉይ ኪዳን ያለውን የእስራኤል ታሪክ ባጭሩ እንመለከታለን።

፩. ከአይሁድ የእምነት አባቶች (ፓትሪያርኮች) በፊት የነበረው ዘመን (2500-2000 ዓ.ዓ.)

ከዘፍ. 1-11 የጥንት ታሪኮችን አጭር መግለጫ እንመለከታለን። ታሪኩ የሚጀምረው የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ከተፈጠሩበት አጠቃላይ ታሪክ አጀማመር ነው። እግዚአብሔር ዓለምን እንዲሁም አዳምንና ሔዋንን የፈጠረበትን ጊዜ የሚያውቅ ማንም የለም። በእነዚህ የኦሪት ዘፍጥረት 11 ምዕራፎች የብዙ ሺህ ዓመታት ታሪክ አጠር ባለ መልኩ ቀርቧል። የእነዚህ ምዕራፎች ዋና ዓላማ ዓለም እንዴት እንደተጀመረች፥ ኃጢአት በዓለም እንዴት እንደተስፋፋ እንዲሁም ከአዳም እስከ አብርሃም ያለውን የአይሁድ የዘር ሐረግ ለመከተል ነው። 

አይሁድ ሴማውያን ከተባሉ ዘሮች የተገኙ ነገዶች ወይም የሴም ዝርያ ናቸው። ሴማውያን በብዛት የሚኖሩት በመካከለኛው ምሥራቅ፥ በኤፍራጥስና በጤግሮስ ወንዞች መካከል በሚገኘውና መሰጴጦምይ በተባለው ሥፍራ ነው። የጥንት ሥልጣኔ የተጀመረው በዚያ ስፍራ ነው። ጽሑፍ፥ ሒሣብ፥ ሥነ ጥበብ፥ ሕግ፥ ሕክምና፥ ወዘተ በመጀመሪያ የተጀመረው በዚህ ስፍራ ነው። በ2100 ዓ.ዓ. ገደማ የመሰጴጦምያ ዋና ከተማ በደቡብ መሰጴጦምያ የምትገኘው የዑር ከተማ ነበረች። የደቡብ መሰጴጦምያን አብዛኛዎቹን ክፍሎች በሚቆጣጠር በአንድ ንጉሥ ሥር የምትገዛ ነበረች። ይህ ሁኔታ ባስገኘው ሰላም ምክንያት ለሥልጣኔ በፍጥነት ማደግ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። አብርሃምና አባቱ ካራን የመጡት ከዚህ ስፍራ እንደነበር እናያለን። አብርሃም የኖረበትን ትክክለኛ ዘመን ባናውቅም እንኳ፥ ዑርን ትቶ ወደ ከነዓን የሄደው በዚህ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ 

ይህ ከተማ በሥልጣኔ ያደገና የላቀ እንደነበረ ማወቃችን፥ አብርሃም በሥልጣኔ እጅግ የበለፀገችውን አገር ትቶ ኋላ ቀር ወደ ሆነችው ወደ ከነዓን ለመሄድ ያደረገውን አስቸጋሪ ምርጫ ያሳየናል። እግዚአብሔር ሰውን ከአዲስ አበባ ወጥቶ በሐመር ባኮ፥ ወይም ራቅ ካሉ አካባቢዎች በአንዱ እንዲኖር የተናገረውን ያህል ነው። ምርጫው አስቸጋሪ ነበር። አብርሃም ያደረገውን በእምነት የመታዘዝ ከፍተኛ እርምጃ ያሳየናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዑርን ለቆ እንዲወጣ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው ትእዛዝ አስቸጋሪ የነበረው ለምንድነው? ለ) ዛሬ እግዚአብሔር ለእኛ የሚሰጠን አስቸጋሪ የሆነ ተመሳሳይ ትእዛዝ ምንድነው? (ማቴ. 28፡19-20 ተመልከት)። ሐ) በአሁኑ ጊዜ የአብርሃም ምሳሌነት ለእኛ መልካም ትምህርት የሚሰጠን እንዴት ነው? 

፪. የአይሁድ የእምነት አባቶች (የፓትሪያርኮች) ዘመን (2000-1600 ዓ.ዓ.)

በእነዚህ ዓመታት የዑር ከተማ ኃይል ማሽቆልቆል ጀመረ። መሰጴጦምያ በአንድ ንጉሥ መገዛቷ ቀረና «የከተማ ግዛቶች» ወደሚባሉ ትናንሽ ክልሉች ተከፋፈለች። ይህም ማለት ዋና ዋናዎቹ ከተሞች በአካባቢያቸው ያሉ ክልሉችን ሁሉ መቆጣጠር ጀመሩ። በእያንዳንዱ ከተማም ንጉሥ ነበር። ይሁን እንጂ ሕዝቡ እንደ ቀድሞው ታላቅና ኃያላን አልነበሩም። ይህም በተለይ የከነዓንን ምድር በሚመለከት እውነት ነበር። እያንዳንዱ ከተማ በንጉሥ ቁጥጥር ሥር ነበር።

አብርሃም፥ ይስሐቅና ያዕቆብ በከነዓን ምድር ይኖሩ በነበሩበት ጊዜ ምድሪቱ በሕዝብ ብዛት አልተጨናነቀችም ነበር። ይህ ማለት ከተለያዩ ነገዶች ጋር ሳይጋጩ በነፃነት ይንቀሳቀሱ ነበር ማለት ነው።

በእነዚህ ዓመታት የግብፅ አገር በአካባቢው ባሉ አገሮች ላይ የነበራት የበላይነት እያየለ መጣ። የከነዓንን ምድር ክልል ከዕለት ወደ ዕለት እየተቆጣጠረች መጣች። እንደሚታወሰው አብርሃም፥ ያዕቆብና ዮሴፍ ግብፅን ጎብኝተዋል። በእነዚህ ዓመታት ዮሴፍ በግብፅ ውስጥ በይበልጥ ሁለተኛው ኃያል መሪ ሆኖ ነበር።

ከዘፍጥረት 12-50 ያሉት ታሪኮችና መጽሐፈ ኢዮብ በዚህ የታሪክ ክፍለ ጊዜ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። 

፫. ግብፅ እስከ ዘመነ መሳፍንት (1600-1200 ዓ.ዓ.) 

የግብፅ አገር ሥልጣኔ የጀመረው በ3100 ዓ.ዓ. ነው። ከ2700-2200 ዓ.ዓ. ባሉት ዘመናት ግብፅ እጅግ ኃያል ሆነች በከነዓንም ላይ በከፍተኛ ደረጃ የበላይ ሆነች። እስካሁን ድረስ በግብፅ የሚታዩት አንዳንዶቹ ትላልቅ ፒራሚዶች የተሠሩት በዚህ ጊዜ ነው።

ነገር ግን ከ1800-1600 ዓ.ዓ. ከሶርያና ከከነዓን የመጡ «ሐይክሰስ» የተባሉ ነገዶች ግብፅን ተቆጣጠሩ። ይህም የግብፅ ኃይል እየተዳከመ የመጣበት ጊዜ ነበር። በእነዚህ ዓመታት ነበር በግብፅ የነበሩ ከ70 የማይበልጡ አይሁድ እስከ ከ1 ሚሊዮን በላይ የሆኑት።

በ1600 ዓ.ዓ. አካባቢ ግብፆች ዓመፁና እንደገና የራሳቸውን አገር ማስተዳደር ጀመሩ። ግብፆች የምድራቸው አብዛኛውን ክፍል የወሰዱባቸውን «የውጭ አገር ዜጎች» ጠሏቸው። ስለዚህ የቻሏቸውን ባሪያዎች ሲያደርጉ፥ ሌሎቹን ከአገር አስወጧቸው። አይሁድ በግብፃውያን ባርነት ቀንበር ሥር የወደቁት በዚህ ዘመን ነበር። በዚህ ጊዜ ግብፃውያን ደቡብ ሱዳንን፥ ከነዓንን በሙሉ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያሉትን መንገዶች ያዙ። ግብፅ እንደገና ኃያል አገር ሆነች።

ነገር ግን በ1400 ዓ.ዓ. የግብፅ ኃይልና የበላይነት ማሽቆልቆል ጀመረ። በፍልስጥኤም ላይ የነበራቸውን አገዛዝ አጡ። ብዙዎቹ ምሁራን እንደሚያስቡት አይሁድ በግብፅ ከነበሩበት ግዞት ወጥተው ከነዓን በመድረስ የራሳቸውን አገር ያቋቋሙት በዚህ ጊዜ ነበር። ይህንን ከኦሪት ዘጸአት ጀምሮ እስከ መሳፍንት ባሉት ክፍሎች ውስጥ እናገኘዋለን። መጽሐፈ ሩት የተፈጸመውም በዚህ የታሪክ ወቅት ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር የግብፅን ታሪክ በመቆጣጠር ለሕዝቡ ጥቅም ያዋለው እንዴት ነው? ከ1400-1200 ዓ.ዓ. ከነዓን የታላላቅ ኃያላን መንግሥታት የጦርነት ሜዳ ሆነች። በሰሜን በኩል ወደ ከነዓን ዘልቀው በመግባት ጥቃት የሚያደርሱ ኬጢያውያን በመባል የሚታወቁ ነገዶች ነበሩ። በደቡብ በኩል ግብፆች የከነዓንን ድንበር ተቆጣጥረው ለመቆየት ይዋጉ ነበር።

ከነዓን በጣም ጠቃሚ የነበረችው ለምንድነው? የተለያዩ ሁለት አህጉሮች መገናኛ ስለነበረች ነው:- በደቡብ በኩል አፍሪካ፥ በሰሜን ደግሞ እስያ፡፡ ከግብፅ ወደ መሰጴጦምያ የሚያልፉ ሁለት እጅግ ጠቃሚ የንግድ መሥመሮች ነበሩ። ከነዓን በስተምሥራቅ ያለው ምድረ በዳ ብቻ ስለሆነና በምዕራብ በኩል ደግሞ የሜዴትራኒያን ባሕር ስለነበር፥ ነጋዴዎች በደቡብ በኩል ካለው ከግብፅ ወደ ሰሜኑ መሰጴጦምያ ለመሄድ በከነዓን ማለፍ ግድ ሆኖባቸው ነበር፤ እነዚህን የንግድ መሥመሮች የተቆጣጠረ ማንኛውም ከፍል ባለጸጋ ሆነ፤ ስለዚህ ውሾች በአጥንት ላይ እንደሚጣሉ እነዚህ አገሮች በከነዓን ላይ የበላይ ለመሆን ይዋጉ ነበር።

በዚህ ጊዜ ነበር መሳፍንት በእስራኤል የገዙት። በመሳፍንት ክፍለ ዘመን ያለማቋረጥ የምናነበው እግዚአብሔር ረድቶአቸው ነፃ እስኪያወጣቸው ድረስ የተለያዩ ነገዶች እስራኤልን ይገዙ እንደ ነበር ነው።

በ1200 ዓ.ዓ. ግብፅ ኃይሏን አስተባበረችና ከነዓንን መቆጣጠር ጀመረች። ይህ ማለት በግብፆችና በኬጢያውያን መካከል ከፍተኛ ጦርነት ነበር ማለት ነው። ኬጢያውያን ተሸነፉ። ዳሩ ግን በጦርነቱ ጦስ በከነዓን ዙሪያ የነበሩ በርካታ ከተሞች ተደመሰሱ።

፬. የኋለኛው የመሳፍንት ዘመንና የሳኦል ዘመን (1200-1000 ዓ.ዓ.)

ግብፆች ኬጢያውያንን ቢያሸንፉም እንኳ ኃይላቸው ለረጅም ጊዜ አልቆየም። ኃይላችው ወዲያውኑ ያሽቆለቁል ጀመር። በውጤቱም በከነዓን ላይ የነበራቸውን አንዳንድ የበላይነት አጡ። በእነዚህ ዓመታት አንድ አዲስ ነገድ ወደ ከነዓን ምድር መግባት ጀመረ። ከሜዲትራኒያን ባሕር ደሴቶች የመጡ በመሆናቸው «የባሕር ሰዎች» በመባል ይታወቁ ነበር። ከባሕር ሰዎች መካከል አንዱ ቡድን ፍልስጥኤማውያን በመባል ይታወቁ ነበር። ከዘመነ መሳፍንት መጨረሻ ጀምሮ በዘመነ ነገሥታት ሁሉ ፍልስጥኤማውያን ዋናዎቹ የአይሁድ ጠላቶች ነበሩ። ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤላውያን የበለጠ በእውቀት የላቁ ነበሩ። በዚህ ዘመን ነበር የብረት መሣሪያዎችን የመሥራት ዘዴዎች ማወቅ የጀመሩት። 

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ሳሙ. 13፡19-23 አንብብ። ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን እንዲቆጣጠሩ ይህ እውቀት እንዴት ረዳቸው?

የመጨረሻዎቹ መሳፍንት ከነበሩት ከሳምሶንና ከሳሙኤል ጀምሮ እስከ ዳዊት መንገሥ ድረስ ፍልስጥኤማውያን አብዛኛውን እስራኤልን ይቆጣጠሩ ነበር። በእነዚህ ዓመታት ማንም እንደ ግብፅ ያለ ታላቅ መንግሥት ፍልስጥኤምን የገዛ አልነበረም። ይህ ዘመን የታየው በዘመነ መሳፍንት መጨረሻና በ1ኛ ሳሙኤል ላይ ነው።

* (ማሳሰቢያ፡- ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በእነዚህ ጳለስጢና፥ ጳለስጢናውያንና ፍልስጥኤማውያን የተባሉት የተለያዩ ስሞች የግንዛቤ ችግር አለ። ጳለስጢና የሚለው ስም ከሜዲትራኒያን ደሴቶች ፈልሰው ወደ ከነዓን ለመጡ ሰዎች የተሰጠ ነው። ፍልስጥኤማውያን የእስራኤልን ጠረፍ መቆጣጠር ከጀመሩ ወዲህ በግብፅና በመስጴጦምያ መካከል የነበረውን ዋናውን መንገድ ያዙ። በውጤቱም የአሕዛብ መንግሥታት ሕዝቦች ያለማቋረጥ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ያደርጉ ነበር። ምድሪቱንም «የፍልስጥኤሞች» ምድር ወይም ጳለስጢና በመባል ተጠራች። ጳለስጢና በዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ ከግብፅ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለው አገር በሙሉ የተለመደ መጠሪያ ሆኖአል። ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ከቀርጤስ ደሴት የመጡ አውሮጳውያንን ይመስላሉ። በአሁኑ ዘመን ያሉ ግን ፍልስጥኤማውያን ዐረቦች ናቸው፤ ስለዚህ ከቀድሞዎቹ ጋር አንድ ዓይነት አይደሉም። ከ700 ዓ.ም. በኋላ የዐረብ መንግሥታት እስራኤልን አሸንፈው በዚያ ይኖሩ ጀመር። እስራኤል በ1948 ዓ.ም. እንደገና የራሷን መንግሥት ስታቋቁም በዚያ የነበሩ አንዳንድ ዐረቦች ከዚያ ለቀቁ፤ ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን በዘመናዊቷ እስራኤል ውስጥ የነበሩ አሁንም በእስራኤል ውስጥ በአንዳንድ ስፍራዎች ወይም ከእስራኤል ውጭ በስደት የሚኖሩ ዐረቦች ናቸው። የዘመናችን ፍልስጥኤማውያንና አይሁድ የሚያደርጉት ትግል እስራኤል የእኔ ነው የምትለውን ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንም የእኛ ነው በማለታቸው ነው።) 

፭. የዊትና የሰሎሞን መንግሥት (ከ1000 – 900 ዓ.ዓ.)

የውይይት ጥያቄ፦ 1ኛ ነገሥት 4፡21-24 አንብብ። በሰሎሞን አመራር ጊዜ የእስራኤል መንግሥት ይዞታ ምን ያህል ነበር?

ግብፅ በፍልስጥኤም ላይ የነበራት ቁጥጥር እየቀነሰ ሲሄድና በመሰጴጦምያ አንድ ኃያል መንግሥት ባለመተካቱ፥ የእስራኤል መንግሥት ኃይል እየጨመረ ሊሄድ ቻለ። በዳዊት የጦር አመራር የእስራኤል መንግሥት በደቡብ በኩል እስከ ግብፅ፥ በሰሜን በኩል ደግሞ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ተስፋፋ። በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ 12 የተለያየ ነገድ ከመሆን በአንድ ንጉሥ የሚተዳደር አንድ ሕዝብ ሆነ። ዋና ከተማዋ ኢየሩሳሌምም ተገነባች።

ዳዊት ተዋግቶ የሕዝቡን የግዛት ዳርቻ ያሰፋ ሲሆን፥ ሰሎሞን ከአባቱ ወረሰ። በአብዛኛው የሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ሰላም የነበረ ሲሆን የአባቱን የዳዊትን ምድር በሚገባ ተቆጣጥሮ ነበር፤ ነገር ግን በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ የተለያዩ መንግሥታት ዓመፅ እያየለበት ሄዶ ነበር። እርሱ ሲሞት አንድ የነበረው የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ተከፈለ። የሰሜኑ መንግሥት «እስራኤል» ሲባል የደቡቡ «ይሁዳ» ተባለ።

ይህ ዘመን ለአይሁድ ሕዝብ «ወርቃማው ዘመን» በመባል ይታወቃል። ይህ ኃይላቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ዘመን ነበር። አስደናቂ የሆኑ አንዳንዶቹ ጽሑፎቻቸውም የተጻፉት በዚህ ጊዜ ነበር፤ በአይሁድ ታሪክ ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ ሕዝቡ እግዚአብሔርን የተከተለበት ጊዜ ይህ ነበር። ምክንያቱም መሪዎቻቸው እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ነበሩ፤ ስለዚህ ዘመን በ2ኛ ሳሙኤል፥ 1ኛ ነገሥት 11ና 1ኛ ዜና፥ 2ኛ ዜና እስከ 9 ተጽፎ እናገኛለን። አብዛኛዎቹ የግጥምና የቅኔ መጻሕፍት (መዝሙረ ዳዊት፥ ምሳሌ፥ መክብብና መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን) የተጻፉት በዚህ ዘመን ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ የአንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ መንፈሳዊ ሕይወት በቤተ ክርቲያኒቱ አባሎች ሕይወት ላይ እንዴት ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል? 

፮. የሶርያውያን በኃይል መነሣት (900-800 ዓ.ዓ.)

ከሰሎሞን ሞት በኋላ ኃያል የነበረው የእስራኤል መንግሥት ተከፋፍሉ መውደቅ ጀመረ። በዳዊትና በሰሎሞን ጊዜ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር የነበሩ ሶርያውያን (አራማውያን ተብለውም ይጠሩ ነበር) ሰሎሞን ከሞተ በኋላ ማመፅ ጀመሩ። ወዲያውኑ ዋና ከተማቸውን ደማስቆ በማድረግ ኃያል መንግሥታት ሆኑ። በእነዚህ ዓመታት ጳለስጢና ውስጥ ሶርያውያን ኃያላን በመሆን አብዛኛውን የእስራኤልን ምድር ተቆጣጠሩ።

ሁለቱ ታላላቅ ነቢያት ኤልያስና ኤልሳዕ ያገለገሉትም በእነዚህ ዓመታት ነበር። የእስራኤልና የይሁዳ መንግሥታት ታሪክ ከ1ኛ ነገሥት 12 – 2ኛ ነገሥት 14 ድረስ ይገኛል። በተጨማሪ በ2ኛ ዜና ምዕራፍ 10-27 ተጽፎ እናገኛለን። ትናንሽ መጻሕፍት ከጻፉ ነቢያት አንዳንዶቹም መጻሕፍቶቻቸውን የጻፉት በዚህ ዘመን ነው። 

፯. የአሦር ጊዜ (850-650 ዓ.ዓ.)

ሶርያ ኃያል መንግሥት መሆን በጀመረችበት ጊዜ በሰሜን በኩል ደግሞ ሌላ በጤግሮስ ወንዝ የነበረው መንግሥትም ኃያል ሆነ። ይህ መንግሥት የአሦር መንግሥት ነበር። አሦራውያን መስጴጦምያን ተቆጣጠሩና በደቡብ በኩል ያሉትን ሶርያውያንን መዋጋት ጀመሩ። በመጨረሻም ሶርያውያንና የእስራኤል የሰሜኑ መንግሥት በአሦራውያን ተሸነፉ። በ722 ዓ.ዓ. የእስራኤል መንግሥት ተሸነፈና ሕዝቡ በአሦራውያን ተማርከው በመስጴጦምያ ሁሉ ተበተኑ። አሦራውያን አብዛኛውን የይሁዳን መንግሥት ቢቆጣጠሩም እንኳ በሕዝቅያስ ምሪት እግዚአብሔር ይሁዳን ታደገና ኢየሩሳሌም በአሦራውያን እጅ እንዳትወድቅ አደረገ።

የዚህ ዘመን ታሪክ በ2ኛ ነገሥት 15-23ና 2ኛ ዜና 28-36፡4 ይገኛል። አንዳንዶቹ ትናንሽ የነቢያት መጻሕፍትና ኢሳይያስም የተጻፉት በዚህ ጊዜ ነው። 

፰. የባቢሎን መንግሥት የአገዛዝ ዘመን 650-550 ዓ.ዓ. 

በ650 ዓ.ዓ. ታላቁ የእሶር መንግሥት የተለያዩ ሕዝቦች ስለ ዓመፁበት መውደቅ ጀመረ። የአሦር መንግሥት በ612 ዓ.ዓ. በመስጴጦምያ ባቢሎን ተብሎ በሚጠራ መንግሥት ተሸነፈ። ባቢሎን ከአሦር ደቡብ በኤፍራጥስ ወንዝ አካባቢ የሚገኝ ነው። የባቢሎን መንግሥት በታላቁ መሪው በናቡከደነፆር በታላቅ ፍጥነት አድጎ ከባቢሎን ጀምሮ እስከ ግብፅ ያሉትን አካባቢዎች ተቆጣጠረ። ከ606-586 ዓ.ዓ. ሦስት ተከታታይ ዘመቻዎች ተደርጎው የደቡብ ይሁዳ መንግሥት ተሸነፈና ሕዝቡም በምርኮኛነት ተወሰደ።

2ኛ ነገሥት 24-25ና 2ኛ ዜና 36 ስለዚህ ዘመን ይናገራሉ። ከታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት አንዳንዶቹ፥ እንዲሁም ኤርምያስ፥ ሕዝቅኤልና ዳንኤል የተጻፉት በዚህ ጊዜ ነው። 

፱. የሜዶንና የፋርስ የአገዛዝ ዘመን 550-331 ዓ.ዓ. 

በ550 ዓ.ዓ. የሜዶንና የፋርስ መንግሥታት በባቢሎን መንግሥት ላይ ዓመፁና በ539 ዓ.ዓ. አሸነፏት። ባቢሎን ይዛው የነበረውን ምድር በሙሉ ተቆጣጠሩና በዛሬ ጊዜ ቱርክ እስከሚባለው እስከትንሹ እስያ ድረስ ተስፋፉ። በቁጥጥራቸው ሥር ካሉ መንግሥታት ጋር በሰላም ለመኖር ስለፈለጉ የሜዶንና የፋርስ መንግሥታት ባቢሎናውያንና አሦራውያን የማረካቸውን ሕዝቦች በሙሉ ወደየአገሮቻቸው እንዲሄዱና ቤተ መቅደሶቻቸውን እንዲሠሩ ፈቀዱላቸው። እንዲመለሱና ቤተ መቅደሳቸውን እንዲሠሩ ከተፈቀደላቸው መንግሥታት መካከል አንዱ የይሁዳ መንግሥት ነበር። በዘሩባቤል፥ በዕዝራና በነህምያ መሪነት ቤተ መቅደሱና የኢየሩሳሌም ቅጥሮች እንደገና ተሠሩ።

በብሉይ ኪዳን ውስጥ የምናነበው የመጨረሻው ኃያል መንግሥት ይህ ነው። እያንዳንዱን ታሪክ በመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ውስጥ እናነባለን። የመጽሐፈ አስቴር ታሪክም የተፈጸመው በዚህ ጊዜ ነው። የሐጌ፥ የዘካርያስና የሚልክያስ መጻሕፍትም የተጻፉት የፋርስ መንግሥት በሥልጣን ላይ በነበረበት በ400 ዓ.ዓ. ነው።

ከዘመነ ብሉይ በኋላና በሁለቱ ኪዳኖች መካከል በነበረው ዘመን (400-0 ዓ.ዓ.)፣ አይሁድ ከ166-63 ዓ.ዓ. ለአጭር ጊዜ ነፃነት ከማግኘታቸው በስተቀር ብዙውን ጊዜ በሌላ ሕዝብ ቁጥጥር ሥር ኖረዋል። በ331 ዓ.ዓ. ሜዶንና ፋርስ በግሪክ መንግሥት እጅ ወደቁ። በኋላም የግሪክ መንግሥት በተራው ክርስቶስ በተወለደበትና የአዲስ ኪዳን ዘመን በተጀመረበት ጊዜ ጳለስጢናን ይቆጣጠር በነበረው በሮም መንግሥት እጅ ወደቀ።

የብሉይ ኪዳን የዓለምንና የእስራኤልን ታሪክ በምንመረምርበት ጊዜ በርካታ ነገሮችን ለማየት እንችላለን። እስራኤል በጣም ጠቃሚ የሆነችው በእግዚአብሔር እንጂ በሰው ዓይን እንዳልሆነ ማስታወስ አለብን። በአካባቢው ከነበሩ መንግሥታት ጋር ስትወዳደር ሁልጊዜ ከቁጥር የማትገባ ነበረች፤ ነገር ግን እስራኤል ለእግዚአብሔር በታዘዘች ጊዜ በአካባቢዋ ካሉ ሕዝቦች ሁሉ ይልቅ ብርቱ ነበረች። እግዚአብሔርን አልታዘዝም ስትልና በሕይወቷም ሆነ በአምልኮዋ አንዳንድ ነገሮችን ስትቀይጥ እግዚአብሔር ሊቀጣት ለአሕዛብ መንግሥታት አሳልፎ ይሰጣት ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ጉዳይ ቤተ ክርስቲያን ከዓለም ጋር በሚኖራት ግንኙነት አንፃርና እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚሠራበት መንገድ ጋር ያለው ተመሳሳይነት ምንድን ነው?

የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ በምናጠናበት ጊዜ አንድ ሌላ መሠረታዊ እውነት እናያለን። በዓለም ላይ ያሉ ክስተቶች የሚፈጸሙት ያለ እግዚአብሔር ቀጥተኛ ቁጥጥር ሳይሆን፥ ታሪክን በሙሉ የሚመራው እርሱ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። አንዳንድ ነገሥታትና መንግሥታትን የሚያስነሣ ደግሞም የሚጥል እርሱ ነው። በዘመናችን ሳይቀር በዓለምም ሆነ በአገራችን የሚፈጸሙትን ታሪኮችንና ክስተቶችን ሁሉ የሚቆጣጠር አምላካችን እንደሆነ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።

የውይይት ጥያቄ፥ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ይህ እውነት ክርስቲያኖችን እንዴት ያበረታታቸዋል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንዴት እንደተሰበሰቡ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ቅደም ተከተል ከአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ቅደም ተከተል ጋር አወዳድር። የተለያየ ቅደም ተከተል ያላቸው መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው? ለ) የካቶሊክ እምነት ተከታይን መጽሐፍ ቅዱሱን እንዲያሳይህ ጠይቀው። ከአንተ መጽሐፍ ቅዱስ ይለያልን? በእነርሱ ብሉይ ኪዳን ውስጥ ስንት መጻሕፍት አሉ? ሐ) በመጽሐፍ ቅዱሳቸው ውስጥ ስንት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንዳሉ አንዱን የኦርቶዶክስ ቄስ ጠይቅ።

ለመጀመሪያዎቹ 39 መጻሕፍት የቀድሞ ክርስቲያኖች እንዴት «ብሉይ ኪዳን» የሚል ስያሜ እንደሰጡ ተመልክተናል። ነገር ግን የብሉይ ኪዳን ክፍል መሆን ያለባቸው መጻሕፍት የትኞቹ እንደሆኑ ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ እንደሆኑ ሊቆጠሩ የሚገባቸው መጻሕፍትስ የትኞቹ እንደሆኑ ክርስቲያኖች ከስምምነት ላይ የደረሱት እንዴት ነው? 

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የተለያዩ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፉ የእግዚአብሔር ቃል ስለመሆናቸው ይከራከራሉ። እንደምታስታውሰው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ተጽፈው የተጠናቀቁት በ1000 ዓመታት ውስጥ ነው። ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ዘዳግም ያሉት የመጀመሪያዎቹ መጻሕፍት የተጻፉት በ1400 ዓ.ዓ. ነው። የመጨረሻ የሆነው መጽሐፍ ትንቢተ ሚልክያስ የተጻፈው በ400 ዓ.ዓ. ነው። በእነዚህ የ1000 ዓመታት ጊዜ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ እግዚአብሔር በተለያዩ ሰዎች ተጠቅሞአል። በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ከክርስቶስ ልደት ወዲህ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ያሉት 39 መጻሕፍት በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት የተጻፉ እንደሆነ እናውቃለን።

የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት በአንድ ላይ ለማቀናጀት ብዙ ደረጃዎችን ማለፍ እንዳስፈለገ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይገምታሉ።

የመጀመሪያ ደረጃ፡- በንግግር የማስተላለፍ ባሕል ነው። የመጀመሪያው ደረጃ የእግዚአብሔርን ቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ በንግግር የማስተላለፍ ዘዴ ነው። የእግዚአብሔር ነቢያት በእግዚአብሔር ሕዝቦች ፊት ቆመው «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» በማለት የእግዚአብሔርን መልእክት ያስተላልፉ ነበር (ሕዝ.5፡5 ተመልከት)። በዚህ የንግግር ዘዴ ይተላለፉ የነበሩ አንዳንድ መልእክቶች ሳይጻፉ ብዙ ዘመን ሳያልፋቸው አይቀርም። ለምሳሌ፡- ከዘፍጥረት 1-50 ያሉት ሲሆኑ፥ ሌሎቹ ደግሞ ቶሉ የመጻፍ ዕድል አግኝተዋል።

ሁለተኛ ደረጃ፡- የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ተጻፉ። የተለያዩ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች በመንፈስ ቅዱስ ምሪት አማካይነት የእግዚአብሔርን ቃል በተለያዩ መጻሕፍት ጽፈዋል።

ሦስተኛ ደረጃ፡- አይሁድ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን የተለያዩ መጻሕፍት መሰብሰብ ጀመሩ። ይህ ረጅም ጊዜ የወሰደ ሥራ ነው። ለምሳሌ፡- መዝሙረ ዳዊት በአንድ ላይ ተጠርዞ ለመቀመጥ ብዙ መቶ ዓመታት ወስዶአል። አንዳንዶቹ መዝሙሮች የተጻፉት በ1400 ዓ.ዓ. በሙሴ፥ ሌሎቹ ደግሞ በ500 ዓ.ዓ. በዕዝራ የተጻፉ ናቸው። የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በማሰባሰብና በማደራጀት ረገድ ዕዝራ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ ብዙ ምሁራን ይገምታሉ።

አራተኛ ደረጃ፡- አይሁድ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው ብለው የተቀበሏቸውን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ ሰብስበው ቅደም ተከተል በማስያዝ አስቀመጡአቸው። ይህ ማለት አንዳንዶቹን መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል እንዳልሆኑ ቆጥረው አገለሉዋቸው ማለት ነው።

አይሁዳውያን እስከ መጀመሪያው መቶ ዓመት መጨረሻ ድረስ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው ብለው የሚያምኑባቸውን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በአሁኑ መልካቸው ስለማስቀመጣቸው መረጃ የለንም። ዳሩ ግን ከክርስቶስ መምጣት በፊት 200 ዓ.ዓ. ማለትም የመጨረሻው መጻሕፍት ከተጻፈ ከ200 ዓመት በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው ብለው አይሁድ የገመቱአቸውን መጻሕፍት በሙሉ አይሁዳውያን አውቀውና መርጠው እንደነበር የሚገልጥ ማስረጃ አለ።

ይህ ሂደት በጣም የተወሳሰበ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ቃሉን በመጻፍ ሂደት ውስጥ ከሰዎች ጋር የሠራው እግዚአብሔር የተጻፉትን መጻሕፍት ያለአንዳች ስሕተት ሰዎች እንዲለዩ በማድረግ ረገድም እንደሠራ እናምናለን። እነዚህ መጻሕፍት የእግዚአብሔርን ቃልና ሥልጣን ይዘዋል።

የቀድሞ አይሁዳውያን የእግዚአብሔር ቃል የሆኑትን ክፍሎች ከብዙ መጻሕፍት መካከል ለመለየት የተጠቀሙበት መመዘኛ ምንድነው? በአዲስ ኪዳን ዋናው መመዘኛ፡- «ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በአንድ ሐዋርያ ነው ወይስ አብሮት በሚሠራ ሰው?» የሚል ነበር። የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ለመለየት ግን አራት ዋና ዋና መመዘኛዎች የነበሩ ይመስላል። እነርሱም፡-

 1. መጽሐፉ በውስጣዊ ብቃቱና በመልእክቱ የእግዚአብሔር ሥልጣን እንዳለውና በእርሱ መንፈስ እንደተጻፈ የሚያሳይ ነገር አለን? የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች መጻሕፍቱን በሚመዝኑበት ጊዜ የእግዚአብሔር ጣት እንዳለበት እንዲያዩ መንፈስ ቅዱስ መርቶአቸዋል።
 2. የመጽሐፉ ጸሐፊ እግዚአብሔር በመለኮታዊነቱ መሪ እንዲሆን የመረጠው ሰው ነበርን? ለምሳሌ ንጉሥ፥ ካህን፡ ነቢይ፥ ወይም እግዚአብሔር በኃይል የተጠቀመበት በእስራኤል ላይ የሚፈርድ ሰው ነበርን? 
 3. በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙ ትምህርቶች በሙሉ እርስ በእርስና እንዲሁም የእግዚአብሔር ቃል መሆኑ በታወቀ በሌላ መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙ ትምህርቶች ጋር የሚስማማ ነውን? ለምሳሌ፡-በትንቢት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ትምህርቶች በመጀመሪያዎቹ አምስት የሙሴ መጻሕፍት ውስጥ እግዚአብሔር ከተናገረው ነገር ጋር የሚስማሙ ናቸውን?
 4. መጻሕፍቱ በአይሁድ የአምልኮ ጊዜ በተግባር ላይ ሊውሉ የቻሉ ናቸውን ወይስ ለሌላ ለተለየ ዓላማ ምንም አገልግሎት የማይሰጡ ናቸው? እያንዳንዱን መጽሐፍ በእጅ መገልበጥ ከባድ ድካም የሚጠይቅ ስለነበር፥ አይሁዳውያን ይገለብጡ የነበረው የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን ያወቁዋቸውና ለእግዚአብሔር በሚሰጡት አምልኮ ውስጥ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉትን ዓይነት ብቻ ነበር።

እነዚህ አይሁዳውያን፥ እግዚአብሔር በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እንዲካተት የፈለገውን ነገር ብቻ መምረጣቸውን እንዴት እናውቃለን? በአንድ በኩል ስናየው፥ ልናውቅ አንችልም። ሰዎች ቃሉን እንዲጽፉ በማድረግ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ያደረገው እግዚአብሔር፥ በዓለም ላሉ ሰዎች ሁሉ እንዲደርስ የፈለገው ቃሉ ብቻ ተጠብቆ እንዲቆይ እንዳደረገ ማመን አለብን። በሌላ አንፃር ስናየው ግን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ሁሉ በምንመረምርበትና ዛሬ ካሉ ሌሎች መጻሕፍት ጋር በምናወዳድርበት ጊዜ ልዩነቱን ለማየት እንችላለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተካተቱት መጻሕፍት የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ጥራትና ብቃት ያለው መልእክት የላቸውም። በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት እንደ ሌሎቹ መጻሕፍት ሳይሆኑ ምንም ዓይነት ያለመስማማት በማይታይበት ሁኔታ የመልእክት አንድነት ይታይባቸዋል። ሌሎች መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል አለመሆናቸውን የምናየው እርስ በርስ የሚቃረኑ ትምህርቶች ስላሉባቸው ነው። እግዚአብሔር ብሉይ ኪዳንን እንዲጽፉ የተጠቀመባቸው የተለያዩ ሰዎች ቢሆኑም የብሉይ ኪዳን የመልእክት አንድነት ግን የሚያስደንቅ ነው። በተለያዩ መጻሕፍት መካከል ያሉ ትምህርቶች የተጻፉት በመቶ ዓመታት ልዩነት ቢሆንም፥ አንዳቸው ከሌላቸው ጋር በማይቃረን ሁኔታ ይስማማሉ። የእግዚአብሔር ልጆች መጻሕፍት እንደመሆናችን መጠን ዛሬ በእጃችን ያሉት ቅዱሳት የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። የእግዚአብሔር ሥልጣን ይገኝባቸዋል፤ ስሕተት አያስተምሩም፤ ስለ እውነተኛው እግዚአብሔርና ከእርሱ ጋር ሊኖረን ስለሚገባ ግንኙነትም በትክክል ያስተምሩናል። የእግዚአብሔር ቃል የሆነውንና ያልሆነውን የወሰኑት አይሁድ እንዳልሆኑ ማስታወስ ጠቃሚ ነው። ይልቁንም እግዚአብሔር በእስትንፋሱ የተጻፈውንና በእርሱ መሪነት የተሰጠውን ቃል ለመለየት ሰዎችን ተጠቀመባቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ክርስቲያኖች ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል እንደሆኑ እርግጠኞች መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የተሟላና አንዳችም ስሕተት የሌለበት የእግዚአብሔር ቃል ከሆነ፥ ዛሬ እኛ በምንጽፋቸው መጻሕፍትና በምናዘጋጃቸው መልእክቶች ላይ እንዴት ተጽእኖ ያሳድርባቸዋል? ለ) እነዚህስ ጽሑፎቻችንና መልእክቶቻችን «የእግዚአብሔር ቃል» መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? ሐ) «መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው» ከምንለው አሳብ ጋር ( የእኛ መልእክት በምን ይለያል?

ዛሬ ሰዎች በሚሰጡት ስብከትና በሚጽፏቸው መልእክቶች አማካይነት እግዚአብሔር የሚናገር ቢሆንም፥ ለእነዚህ ጽሑፎችና ትምህርቶች ስለምንሰጠው የሥልጣን መጠን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። የእግዚአብሔርን ሙሉ ሥልጣን የያዘው፥ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ምንም ስሕተት የሌለበት እርሱ ብቻ ነው። የትኛውም መጽሐፍ ወይም ስብከት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳችም ስሕተት የሌለበት ሊሆን አይችልም። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ያለው መልእክትም ሆነ መጽሐፍ የለም፤ የምንጽፈውም ሆነ የምንናገረው ነገር የሚመዘነው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው። ሰባኪዎችና ጸሐፊዎች እንደመሆናችን መጠን መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ማጥናት የእኛ ሐላፊነት ነው። በመጨረሻ ግን ደካሞችና ኃጢአተኞች መሆናችንን በትሕትና መቀበል አለብን። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለን መረዳት ውሱን ነው። ምንም ነቀፋና ስሕተት የለብንም ብለን ለመናገር አንችልም።

የውይይት ጥያቄ፥ ጸሐፊዎች፥ አስተማሪዎችና ሰባኪዎች ይህንን መገንዘብ የሚያስፈልጋቸው ለምንድነው? ክርስቲያኖች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተሟላ መሆኑን ያምናሉ፤ (ራእ. 22፡18-19)። የዮሐንስ ራእይ ከተጻፈ ወዲህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ምንም ዓይነት መጽሐፍ መጨመር አይቻልም። ይህም ማለት ዛሬ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መጨመር ያለባቸው በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መጻሕፍት አሉ የሚሉ ዛሬ የተነሡ የሐሰት ትምህርት አራማጅ ክፍሎች ተሳስተዋል ማለት ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እኩል አድርገው የሚያስተምሩትም ስሕተት ነው።

በ200 ዓ.ዓ. እይሁድ እንደ እግዚአብሔር ቃል መቆጠር አለባቸው ስለሚሉአቸው መጻሕፍት ግልጽ የሆነ አሳብ ነበራቸው፤ ነገር ግን በቅዱሳት መጻሕፍት የአቀማመጥ ቅደም ተከተል አልተስማሙም ነበር። ጸሐፊዎቹ ሲጽፉ ርእስ አልነበራቸውም። በኋላ ግን በመጽሐፉ የመጀመሪያ ዐረፍተ ነገር፥ ወይም መጽሐፉ የሚናገርለት ዋና ሰው ወይም መጽሐፉን ጽፎታል ብለው ይገምቱ በነበረው ሰው ስም በመሰየም ርእስ ይሰጡት ጀመር። በእንግሊዝኛውም ሆነ በአማርኛው (ግዕዝ) መጽሐፍ ቅዱስ ያሉት መጻሕፍት ርእሶች የተገኙት መጀመሪያ ሴፕቱዋጀንት ከሚባለው የግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የላቲን ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በመጀመሪያዎቹ መጻሕፍት ውስጥ ምዕራፍና ቁጥሮች አልነበሩም። ለመጽሐፍ ቅዱስ የምዕራፍ ክፍፍል የተሰጠው በ1228 ዓ.ም. ሲሆን፥ የቁጥር ክፍፍሎች የተደረጉት ደግሞ በ1547 ዓ.ም. ነበር።

አይሁድ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው ብለው ያመኑባቸውን መጻሕፍት ሲያደራጁ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ከፍለዋቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሉቃ. 24፡44 አንብብ። ኢየሱስ በዚህ ስፍራ የሚጠቅሳቸው ሦስት የብሉይ ኪዳን ክፍሎች የትኞቹ ናቸው?

በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ አይሁድ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፋፈሉ ሃያ አራት መጻሕፍት ብቻ ነበራቸው። የመጀመሪያው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ዋና ክፍል ዛሬ አይሁድ ቶራኽ የሚሉት የሕግ ክፍል ነው። የሕግ መጻሕፍት የመጀመሪያዎቹን አምስት መጻሕፍት ማለትም ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ኦሪት ዘዳግም ያሉትን የያዙ ናቸው።

ሁለተኛው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ዋና ክፍል ነቢያት በመባል ሲታወቅ፥ በዚህ ክፍል ስምንት መጻሕፍት ይገኛሉ፡- ኢያሱ፥ መሳፍንት፥ ሳሙኤል፥ ነገሥት፥ ኢሳይያስ፥ ኤርምያስ፥ ሕዝቅኤል፡ እንዲሁም 12ቱ ነቢያት ናቸው። ከዚህ የምንመለከተው ሳሙኤል፥ ነገሥት እና 12ቱ ነቢያት (ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ) ራሳቸውን የቻሉ አንዳንድ መጻሕፍት ብቻ የሆኑ ናቸው። በአሁኑ መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እንዳለው የተለያዩ መጻሕፍት አልነበሩም።

ሦስተኛው ዋና ክፍል «ጽሑፎች» በመባል ይታወቃል። በዚህ ክፍል ውስጥ በሦስት ንዑሳን ክፍሎች የተከፈሉ 11 መጻሕፍት አሉ። በመጀመሪያው ክፍል ሦስት የግጥምና የቅኔ መጻሕፍት (መዝሙረ ዳዊት፥ ምሳሌና ኢዮብ) ሲገኙ፥ በሁለተኛው ክፍል አምስት ጥቅል መጻሕፍት ነበሩ (መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን፥ ሩት፥ ሰቆቃወ ኤርምያስ፥ መክብብና አስቴር)። በሦስተኛው ክፍል ደግሞ «ታሪክ» ተብለው የሚጠሩ ዳንኤል፥ ከዕዝራ እስከ ነህምያ (አንድ መጽሐፍ)፥ ዜና መዋዕል (አንድ መጽሐፍ) ብቻ ነበሩ። 

ዛሬ በምንገለገልበት መጽሐፍ ቅዱስ 39 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አሉ። ይህ የሆነው አንዳንድ መጻሕፍት ለሁለት ስለተከፈሉ ነው። ለምሳሌ ዕዝራና ነህምያ አሁን ሁለት መጻሕፍት ናቸው። 1ኛና 2ኛ ሳሙኤል፥ 1ኛና 2ኛ ነገሥት እንዲሁም 1ኛና 2ኛ ዜና መዋዕል ተከፍለዋል። የመጻሕፍቱ ቁጥር በዚህ ዓይነት የተለያዩ ቢሆኑም፥ አይሁዶችና ክርስቲያኖች እነዚህ መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን ያምናሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ የመጽሐፍ ቅዱስህን ማውጫ ተመልከት። በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገኙትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ቅደም ተከተል በመጠበቅ ሆሄያቸውን ጭምር በቃል አጥና። 

ነገር ግን የካቶሊክና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ከእኛ መጽሐፍ ቅዱስ ለምን ተለየ? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ትንቢተ ሚልክያስ ከተጻፈ በኋላ እስከ ኢየሱስ መምጣት ድረስ ወደነበረው ዘመን መመለስ አለብን። ይህ ዘመን 400 «የጸጥታ ዘመናት» በመባል ይታወቃል፤ ምክንያቱም በዚህ ጊዜ እስከ ሚልክያስ ዘመን እንደነበረው በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርተው የእግዚአብሔርን ቃል የጻፉ ምንም ነቢያት እንዳልነበሩ አይሁድ ስለሚያምኑ ነው። እነዚህ ዘመናት በብሉይና በአዲስ ኪዳን ዘመናት መካከል ያሉ ስለሆኑ «በኪዳናት መካከል ያሉ ዘመናት» በመባል ይታወቃሉ። በተጨማሪ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ምን እንደተፈጸመ መመልከት አለብን።

በብሉይና በአዲስ ኪዳን ዘመናት መካከል የተጻፉ ሁለት ዓይነት ሥነ ጽሑፎች ነበሩ። የመጀመሪያው ዓይነት ጽሑፍ «አፖክሪፋ» በመባል ይታወቃል። እነዚህ ጽሑፎች ከ300 ዓ.ዓ. እስከ 100 ዓ.ም. የተጻፉ ናቸው። አፖክሪፋ ማለት ድብቅ ማለት ነው። በዚህ ስም የተሰየሙበት ሁለት ምክንያቶች አሉ፤ የመጀመሪያው፥ ብዙዎቹ መጻሕፍት የተደበቀ ወይም ምሥጢራዊ መልእክት ስለያዙ ሲሆን፥ ሁለተኛው ምክንያት፥ አይሁድ ከሌሉች ቅዱሳት መጻሕፍት ጋር እኩል ሥልጣን እንዳላቸው ስላላመኑበት ነበር። እነዚህ መጻሕፍት የተጻፉት በዕብራይስጥና በአራማይክ ቋንቋ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ከብሉይ ኪዳን ጋር ተያይዘው ይቀርባሉ። 

አሥራ አራት ወይም አሥራ አምስት የሚሆኑት የአፖክሪፋ መጻሕፍት በመጀመሪያ የታዩት ሴፕቱዋጀንት ተብሎ በሚጠራው በግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። አንዳንዶቹ በባሕሪያቸው ታሪካዊ ናቸው። በአዲስና በብሉይ ኪዳን መካከል የነበረውን ታሪክ ይናገራሉ። ሌሎቹ የፍቅር ታሪኮች እንዲሁም የነቢያት መጻሕፍት ናቸው። አይሁድ እነዚህ መጻሕፍት የብሉይ ኪዳን ክፍል መሆናቸውን የተቀበሉበት ጊዜ ጨርሶ የለም፤ ነገር ግን ደስ ስለ ተሰኙባቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንዲቀመጡ ፈቅደው ነበር። በኋላ ግን አይሁድ እነዚህን መጻሕፍት እንደ እግዚአብሔር ቃል እንደማያይዋቸው ያልተገነዘቡና ሴፕቱዋጀንት በተባለው የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ይጠቀሙ የነበሩ ግሪክኛ ተናጋሪ ክርስቲያኖች እንደ እግዚአብሔር ቃል ይመለከቱአቸው ጀመር። ክርስትና አይሁድ ባልሆኑ ሕዝቦች መካከል እየተስፋፋ በሄደ ቁጥር፥ እነዚህ መጻሕፍት እንደ እግዚአብሔር ቃል መታየታቸው እየጨመረ መጣ። ይህ ቢሆንም እንኳ የዕብራይስጥን ቋንቋ የሚያውቁ አብዛኛዎቹ ምሁራን የአፖክሪፋ መጻሕፍት በመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳልነበሩ ተገንዝበው ነበር። ከ382 እስከ 405 ዓ. ም. ጄሮም የተባለው ሰው መጽሐፉን የሮማ ንጉሠ ነገሥት ቋንቋ በነበረው በላቲን እንዲተረጉም በሮማ ቤተ ክርስቲያን ተጠይቆ ነበር። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በይፋ የምትጠቀምበት መጽሐፍ ሲሆን ቨልጌት በመባል ይታወቃል። ጄሮም አፖክሪፋ የተባሉት መጻሕፍት የመጽሐፍ ቅዱስ አካል እንዳልሆኑ ቢያስብም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲጨምራቸው ታዘዘ፤ ስለዚህ ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ እነዚህ መጻሕፍት የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሆነው ቀሩ። ከ1500 ዓ.ም በኋላ ግን የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት (ሉተራን፥ ባፕቲስት ወዘተ) በመሠረታዊ የክርስትና ትምህርት ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተነጥለው ሲወጡና በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈውን የመጀመሪያውን መጽሐፍ ቅዱስ ሲመረምሩ የአፖክሪፋ መጻሕፍት በእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት ከተጻፉትና የእግዚአብሔር ቃል ከሆኑት መጻሕፍት መካከል እንዳልሆኑ ተገነዘቡ፤ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ሲተረጉሙ እነዚህን መጻሕፍት መተው ጀመሩ። አንዳንድ የትርጉም ዓይነቶች እነዚህን መጻሕፍት በብሉይ ኪዳን መጨረሻ በተለየ ክፍል ያደርጉአቸዋል። 

የአፖክሪፋ መጻሕፍት ኢየሱስ በምድር ይኖር በነበረበት ዘመን የነበሩትን አይሁድ ታሪክና አስተሳሰብ ለመረዳት የሚያስችሉን የሚያጓጉ ነገሮች ያሉባቸው ቢሆንም እንኳ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሊቆጠሩ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስን የበለጠ ለመረዳት ስንፈልግ ልናነባቸው እንችላለን፤ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ልናከብራችው ግን አይገባም። ከሌሎች የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች ጋር የማይስማሙ ግልጽ የሆነ ስሕተቶች ይታዩባቸዋል። ከካቶሊኮች ልዩ እምነቶች መካከል ፑርጋቶሪ ወይም ዓፀፋ-ንስሐ የሚባል፥ ሰዎች ከሞቱ በኋላ በሕይወት ሳሉ ስለሠሩት ክፉ ሥራ የሚዳኙበት ቦታ መኖሩ፥ መልካም ተግባር ከፈጸምን በእግዚአብሔር ዘንድ የተሻለ ምሕረትን እናገኛለን የሚለውና የሞተ ሰው ሬሳ ከመቀበሩ በፊት ጸሎተ ፍትሐት ማድረግና የመሳሰለው ሁሉ ከእነዚህ መጽሐፍ የተገኘ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ በዛሬዪቱ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት እነዚህ አመለካከቶች እንዴት ይታያሉ? 

አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በመጽሐፍ ቅዱሳቸው የሚጨምሩት አንድ ሌላ ዓይነት ሥነ-ጽሑፍም አለ። በሁለተኛው ዓይነት የሥነ ጽሑፍ ሥራ «ሱደፒግራፋ» በመባል ይታወቃል። «በሌላ ሰው ስም የተጻፈ መጽሐፍ» ማለት ነው። እነዚህ መጻሕፍት የተጻፉት ከ200 ዓ.ዓ. እስከ 200 ዓ.ም. ነው። የተጻፉትም በሰዎች ዘንድ የበለጠ ተቀባይነት እንዲያገኙ በሚጥሩ ሰዎች አማካይነት ነው፤ ስለዚህ በሚጽፉበት ጊዜ በራሳቸው ስም ፈንታ የታወቀ የብሉይ ኪዳን ሰው ስም ይጠቀማሉ። ለምሳሌ «የአዳምና የሔዋን መጽሐፍ» እና «መጽሐፈ ሄኖክ» በመባል የሚታወቁ አሉ። የካቶሊክም ሆኑ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት እነዚህ መጻሕፍት በእግዚአብሔር ምሪት የተጻፉ እንዳይደሉ ይስማማሉ። የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግን እነዚህ መጻሕፍት የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል ናቸው ብላ ታምናለች፤ ስለዚህ ነው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስዋ ውስጥ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የሚበልጡ መጻሕፍት ያሏት። የካቶሊክም ሆነ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ሠላሳ ዘጠኝ መጻሕፍት ያሉበትን የእኛን መጽሐፍ ቅዱስ ቢጠቀሙም እንኳ የታወቀው አቋማቸው እኛ የእግዚአብሔር ቃል ነው ብለን ከምናስበው የበለጡ መጻሕፍት እንደ አሏቸው ነው። ይሁዳ በመልእክቱ ከቁጥር 14-15 ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል ከአንዱ ይጠቅሳል። ይህ ማለት ግን መጽሐፉ በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው ማለት አይደለም።

** በአማርኛና በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ያሉት መጻሕፍት አንድ ዓይነት ቢሆኑም፥ በመጻሕፍቱ አቀማመጥ ቅደም ተከተል፥ ምዕራፍና ቁጥሮቹ በተጻፉበት ሁኔታ አልፎ አልፎ ልዩነት አለ። ይህንን በተለይ የምናየው በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ ሲሆን በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቅንፍ ያለው ቁጥር ከእንግሊዝኛው ጋር አንድ ዓይነት ነው። ይህ የሆነው የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ለመጻሕፍቱ ቅደም ተከተል፥ ለምዕራፎቹና ለቁጥሮቹ የተጠቀመው የሴፕቱዋጀንቱን ትርጉም ስለሆነ ነው።

** የኦርቶዶክስ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው 58 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትና 27 የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሲሆን በጠቅላላው 85 (ሰማንያ አምስት) ነው። የአሁኑ የፕሮቴስታንት መጽሐፍ ቅዱስ የአዋልድ መጻሕፍትን አስቀርቶ በካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን የቩልጌትን ቅደም ተከተል ይከተላል። ይሁን እንጂ የፕሮቴስታንት አማኞች በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ እግዚአብሔር ቃል የሚቆጠሩትን ብቻ ይቀበላሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ በእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት የተጻፉ የትኞቹ መጻሕፍት እንደሆኑና እንደ እግዚአብሔር ቃል መቆጠር የሌለባቸው መጻሕፍት የትኞቹ እንደሆኑ ማወቅ ጠቃሚ የሚመስልህ ለምንድን ነው? 

የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የጊዜ ቅደም ተከተል

የውይይት ጥይቄ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ያለውን ማውጫ ተመልከት። ቀደም ሲል ባነበብከውና ባጠናኸው የእግዚአብሔር ቃል መሠረት፥ የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት? ለመመደብ ከሚከተሉት የተሻለ ዘዴ ነው በምትለው ከፋፍላቸው። ሀ) በታሪክ መጻሕፍት፥ ለ) በግጥምና ቅኔ መጽሐፍ፥ ወይም ሐ) በነቢያት መጽሐፍ ውስጥ።

ብሉይ ኪዳንን በተለያዩ ክፍሎች መክፈል እንችላለን። በመጀመሪያ ፔንታቱክ የተባለ ክፍል አለ። ፔንታቱክ ወይም የሙሴ ሕግ የመጀመሪያዎቹን አምስት ቅዱሳት መጻሕፍት ይዞአል። በእነዚህ አምስት መጻሕፍት ውስጥ ብዙ የተለያዩ የሥነ -ጽሑፍ ዓይነቶች አሉ፡- ታሪክ፥ ግጥምና ቅኔ፥ ሕግና ትንቢት። ከአምስቱ ሦስቱ የሚናገሩት ከታሪክ ጋር የተያያዘ ነገር ነው። እነዚህም ዘፍጥረት፥ ዘጸአትና ዘኁልቁ ናቸው። የዘጸአትና የዘኁልቁ መጻሕፍት አንዳንድ ሕጎችን ይዘዋል። ደግሞም የተመረጠውን የአይሁድን ሕዝብ ታሪክ የሚናገር ክፍል ነው። ሁለት መጻሕፍት ማለት ዘሌዋውያንና ዘዳግም በአብዛኛው እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ስለ ሰጣቸው ሕግ ይናገራሉ። ዘሌዋውያን በተለይ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ በሲና ተራራ ላይ ሕግን ስለሰጠበት ሁኔታ ይናገራል። ዘዳግም ደግሞ ሙሴ ከ38 ዓመታት በኋላ እስራኤላውያን ወደ ተስፋዪቱ ምድር ከመግባታቸው ጥቂት ቀደም ብሉ እንዴት ሕጉን እንደደገመው የሚነግረን ነው።

በሁለተኛ ደረጃ ታሪክ የሚባል ክፍል አለ። በብሉይ ኪዳን ሁለተኛ ክፍል ውስጥ 12 መጻሕፍት አሉ። እነዚህ መጻሕፍት በኢያሱ መሪነት ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ ከነዓን ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ (ኢያሱ)፥ ከ1000 ዓመታት በኋላ ከባቢሎን ምርኮ እስከተመለሱበት ጊዜ ድረስ (መጽሐፈ ነህምያ)፥ ያለውን የአይሁድ ሕዝብ ታሪክ ይናገራል። እነዚህ መጻሕፍት በአብዛኛው ጊዜ በቅደም ተከተል የተቀመጡ ናቸው። የቀሩት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በተለያዩ ጊዜያት በዚህ የታሪክ ወቅት የተጻፉ ናቸው።

ሦስተኛው ክፍል፥ ግጥምና ቅኔ ይባላል። እነዚህ ከኢዮብ ጀምሮ እሰከ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ባሉት ጊዘያት ውስጥ የተጻፉ ናቸው። መጽሐፈ ኢዮብ በሙሴ ተጽፎ ይሆናል። አብዛኛዎቹ የግጥምና የቅኔ መጻሕፍት የተጻፉት በዳዊትና በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ነው። አንዳንዶቹ መዝሙሮች የተጻፉት ዘግየት ብለው በ400 ዓ.ዓ. በዕዝራ ነው ስለዚህ እነዚህ አምስት የጥምና የቅኔ መጻሕፍት የተጻፉት ረዘም ባለ ጊዜ ውስጥ ነው። ቅደም ተከተላቸው ግን ጊዜን የሚመለከት አይደለም፡፡

አራተኛው ክፍላችን፥ ትንቢት ይባላል። በብሉይ ኪዳን ትንቢት ውስጥ የተመደቡ 17 መጻሕፍት አሉ። እነዚህ መጻሕፍት በተጨማሪ በ2 ምድብ ተከፍለዋል። የመጀመሪያው የታላቅ ነቢያት መጻሕፍት ሲሆን፥ በዚህ ክፍል ውስጥ አምስት መጻሕፍት ይገኛሉ፥ እነርሱም ከኢሳይያስ እስከ ዳንኤል ያሉት ናቸው። ታላቅ የተባሉትም በመልእክታቸው ርዝመትና ጥልቀት ነው።

ሁለተኛ የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት ናቸው። ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ ያሉት እነዚህ 12 መጻሕፍት በመጀመሪያው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ መጽሐፍ ነበሩ።

በመጀመሪያ፥ የእስራኤልን ታሪክ የጊዜ ቅደም ተከተል መግለጫ የሚሰጡ 11 መጻሕፍት ብቻ አሉ። እነዚህ መጻሕፍት ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ እስራኤላውያን ከምርኮ እስከ ተመለሱ ድረስ ያለውን ታሪክ የሚያካትቱ ናቸው። በሌላ አነጋገር ከቀድሞው ዘመን ጀምሮ እስከ 400 ዓ.ዓ. ማለት ነው። የእነዚህ መጻሕፍት ታሪክ አብዛኛው ከ1450 እስከ 400 ዓ.ዓ. ያሉትን ዘመናት የሚያጠቃልል ነው። 

በርካታ የሆኑት ሌሎች መጻሕፍት ታሪካዊ ናቸው፤ ነገር ግን ታሪካቸው የተፈጸመው በሌላ ታሪካዊ መጽሐፍ ዘመን ነው። ለምሳሌ የሩት ታሪክ የተፈጸመው በመሳፍንት ዘመን ነው። 1ኛና 2ኛ ዜና መጻሕፍት ከ2ኛ ሳሙኤል እስከ 2ኛ ነገሥት ያሉትን ታሪኮች ይደግማል። የመጽሐፈ አስቴር ታሪክ የተፈጸመው ደግሞ በዕዝራ መጽሐፍ ታሪክ ዘመን ነው። 

ሁለተኛ፥ አብዛኞቹ መጻሕፍት የተጻፉት በእስራኤል ታሪክ ውስጥ በነበሩ ሦስት ጊዜያት ነው። በቅድሚያ፥ የመጀመሪያዎቹ አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት (ፔንታቱክ) በሙሴ የተጻፉት እስራኤላውያን ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ በተንከራተቱበት ጊዜ ነው። ሁለተኛ ጊዜ፥ አብዛኛዎቹ የግጥምና የቅኔ መጻሕፍት የተጻፉት በዳዊትና በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ነው። ሦስተኛ፥ ይሁዳ ከመማረኩ ጥቂት ቀደም ብሉ፥ ወዲያው ከምርኮ እንደተመለሱም በርካታ የነቢያት መጻሕፍት ተጽፈዋል። እነዚህ መጻሕፍት የተጻፉት እግዚአብሔር ኃጢአተኛ የሆኑት እስራኤላውያን ወደ ንሥሐ እንዲደርሱ ፈልጎ በላካቸው ነቢያት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ክፍፍል በቃልህ አጥናና በእያንዳንዱ ክፍፍል ውስጥ ሊሆኑ የሚችሉትን መጻሕፍት ለይ። ለ) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ጊዜ ቅደም ተከተል በቃልህ አጥና።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ትምህርት ብሉይ ኪዳን

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የትኞቹ ናቸው? ለ) እንደዚያ ተብለው ለምን ተጠሩ? ሐ) ኪዳን የሚለውን ቃል ትርጉም ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በመመልከት የተሟላ ትርጉም ጻፍ። መ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ኪዳኖችን ዘርዝር። ሠ) ኪዳን የሚለው ቃል ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት እንዴት ይገልጻል?

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን እናምናለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ ይገልጥልናል። እርሱ ምን እንደሚመስልና ከእርሱ ጋርም ሕያው የሆነ ግንኙነት እንዲኖረን ከእኛ ምን እንደሚፈልግ እንማራለን። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ስለ እግዚአብሔር ማንነት፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ስለሚወስደው መንገድ፥ ለእግዚአብሔር ስለመኖር ያለንን አሳብ ሁሉ የምንበይንበት መመዘኛ ነው። ማንኛውም አሳባችን፣ የባሕላችን አስተምህሮት፥ ወይም የሌሎች ሰዎች ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መመዘን አለበት። ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የማይስማማ ማንኛውም ትምህርት መወገዝ አለበት። እንዲሁም እግዚአብሔር ስለ ራሱና ስለ ፈቃዱ የገለጠውን ነገር በሚገባ እንድንረዳ መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል መተርጎም እንዳለብን ተምረናል። ይህንን ካላደረግን ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የራሳችንን አሳብ እንጨምራለን፥ መጽሐፍ ቅዱስንም እንዳይናገረን እናደርገዋለን።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) «ብሉይ» የሚለው ቃል ትርጉም ምን እንደሆነ አንድን የኦርቶዶክስ ካህን ወይም ሌላ ሰው ጠይቅ። ለ) «ኪዳን» የሚለው ቃል ትርጉም በአማርኛ ምንድን ነው?

እኛ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ዋና ክፍሎች እንዳሉት እናውቃለን። የመጀመሪያው ክፍል «ብሉይ ኪዳን» ሲባል፥ ሁለተኛው ደግሞ «አዲስ ኪዳን» ይባላል። በኢየሱስ የማያምኑ አይሁድ የዕብራውያን መጽሐፍ ቅዱስ በሚባለው ብሉይ ኪዳን ብቻ ያምናሉ። ለእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሁለቱ ስሞች ለምን እንደተሰጡ ለመረዳት ሁለት ዋና ዋና ቃላትን መመልከት ያስፈልገናል።

፩. ኪዳን፡-. ኪዳን የሚለው ቃል ትርጉሙን የወሰደው ሁለት ሰዎች ወይም ቡድኖች በመካከላቸው እርስ በርስ ከሚያደርጉት ስምምነት ነው። ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ከሞተና አሁን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያሉ በርካታ መጻሕፍት ከተጻፉ በኋላ ክርስቲያኖች ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመግለጥ «ኪዳን» የሚለውን ቃል መጠቀም ጀመሩ። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን የገለጠበት መሆኑና እግዚአብሔር ራሱን ከሰው ልጆች ጋር በኪዳን ወይም በስምምነት ግንኙነት እንዲኖረው እንዳደረገ ተገነዘቡ። በማንኛውም «ኪዳን» ውስጥ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች አሉ፡- በመጀመሪያ፥ በኪዳኑ ውስጥ የሚካተቱ አባላት አሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ «ኪዳን» የሚለው ቃል የሚናገረው እግዚአብሔር ከተለያዩ ሰዎች ጋር ኅብረት እንዳደረገ ነው። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር እንደ አብርሃምና ዳዊት ካሉ ጋር ስምምነት አድርጓል። በሌላ ጊዜ ደግሞ እግዚአብሔር ከኖኅ ጋር እንዳደረገው ዓይነት ከሰው ልጆች ሁሉ ጋራ ስምምነት አድርጓል። የብሉይ ኪዳን ዋና ክፍል ግን እግዚአብሔር ከአብርሃም ልጆች ጋር (ማለትም ከአይሁድ ጋር) ስላደረገው ኪዳን የሚናገር ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ የአዲሱ ኪዳን ስምምነት የተደረገው ከማን ጋር ነው? ]

ሁለተኛ፥ ቃል ኪዳኑ እንዲጠበቅ እንዲሟላና እንዲፈጸም በአንዱ ወይም በሁለቱም የኪዳኑ አባላት መጠበቅ ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በኪዳኑ ውስጥ መኖር አለባቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁለት ዓይነት ኪዳኖች ይገኛሉ። በሲና ተራራ ለአይሁድ ተሰጥቶ እንደነበረው (ዘጸ. 19:24) ዓይነት ያሉ አንዳንድ ኪዳኖች ቅድመ ሁኔታዎች ነበሩዋቸው። በሌላ አባባል እግዚአብሔር «እነዚህን ትእዛዛት ከጠበቃችሁ ለእናንተ እንደዚህ አደርግላችኋላሁ» ብሏል። ሌላው ዓይነት ኪዳን ግን ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ የሌለው የተስፋ ቃል ኪዳን ብቻ ነበር። የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ግን ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ የሌለው የተስፋ ቃል ብቻ ነበር። እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ለገባላቸው ሰዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አንድ ነገር እንደሚያደርግላቸው ተናግሯል (ዘፍ. 12፡1-3)። የዚህ ቃል ኪዳን ምሳሌ እግዚአብሔር ከአብርሃም፥ ከዳዊትና ዛሬም ከክርስቲያኖች ጋር ያለው አዲሱ ቃል ኪዳን ዓይነት ነው። እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰጣቸውን ኪዳኖች በምናጠናበት ጊዜ ቅድመ ሁኔታ ያላቸውንና የሌላቸውን ለይቶ ማየት አስፈላጊ ነው።

ሦስተኛ፡ በኪዳኑ ውስጥ አንዱ ክፍል ለሌላው የሚሰጣቸው ተስፋዎች አሉ። በብሉይ ኪዳን ብዙ ጊዜ ኪዳኑን የሚጀምር እግዚአብሔር ስለሆነ፥ ተስፋንም ለተለያዩ ሰዎች የሚሰጥ እርሱ ነው። እነዚህ ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ጥርጥር የለም። ምክንያቱም ተስፋውን የሰጠው ሊዋሽ ወይም አሳቡን ሊቀይር የማይቻለው አምላክ ስለሆነ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ኤር. 31፡31-34 አንብብ። በእነዚህ ቁጥሮች እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ተስፋ ምንድነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ማቴ. 26፡26-29 አንብብ። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠውን ጽዋ ምን ብሎ ጠራው? የመጀመሪያዎቹ 39 መጻሕፍት ብሉይ ኪዳን፥ 27ቱ ደግሞ አዲስ ኪዳን ተብለው እንዲጠሩ የወሰኑት የጥንት ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ያለው ኅብረት እምብርት የኪዳኑ አሳብ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር።

በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጣቸው አያሌ የተለያዩ ኪዳኖች ይገኛሉ። 

 1. ከኖኅና ከሰው ልጆች ሁሉ ጋር የተደረገ ኪዳን (ዘፍጥ. 9፡1-17)፥ – የሰውን ዘር ካጠፋው ውኃ በኋላ እግዚአብሔር ከኖኅና ከእርሱ በኋላ ከተነሡ የሰው ልጆች ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። በዚህ ኪዳን ውስጥ ይታዘዙት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣቸው ግልጥ የሆኑ ትእዛዛት ነበሩ። ደግሞም በዚያ ቃል ኪዳን ውስጥ የሰውን ልጆች በውኃ ላያጠፋ እግዚአብሔር የገባውም ቃል ኪዳን ነበር። ብዙውን ጊዜ በሰማይ ላይ የምናየው ቀስተ ደመና ያንን ቃል ኪዳን የሚያስታውስ ነው። 
 2. ከአብርሃምና ከዘሩ ጋር የተገባ ቃል ኪዳን (ዘፍጥ. 12፡1-3)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘፍ. 12፡1-3 አንብብ። እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን የተለያዩ ቃል ኪዳኖች ዘርዝር።

በብሉይ ኪዳን ከምናያቸው ቃል ኪዳኖች ሁሉ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነው እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ያደረገው ነው። እግዚአብሔር ከዘፍጥ. 12-25 እንዲሁም በአጠቃላይ በብሉይ ኪዳን ላይ በዚህ ቃል ኪዳን ላይ መመሥረቱን ቀጠለ። ይህ ቃል ኪዳን በብሉይና በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያሉትን ሌሎች ቃል ኪዳኖች ለመረዳት የሚያስችል መሠረት ነው። ከአብርሃም ጋር በተገባው ቃል ኪዳን ውስጥ በቀጥታ አብርሃምን ራሱን ብቻ የሚመለከቱ በርካታ የተስፋ ቃሎች አሉ፤ ነገር ግን ለብሉይ ኪዳን ትምህርቶችና ታሪክ መሠረት የሆኑ ሌሎች በርካታ የተስፋ ቃሉችም አሉ።

ሀ. እግዚአብሔር የአብርሃም ዘሮች የሆኑትን አይሁድ ወይም እስራኤላውያን ታላቅ ሕዝብ እንደሚሆኑ የተስፋ ቃል ሰጣቸው። የብሉይ ኪዳን የታሪክ መጻሕፍት ከዘጸአት ጀምሮ እስከ 2ኛ ዜና ድረስ ይህ ሕዝብ እዚህ ግባ ከማይባል ከአንድ ቤተሰብ ወደ ታላቅ ሕዝብነት እንዴት እንዳደገ የሚናገሩ ናቸው።

ለ. እግዚአብሔር የአብርሃም ዘሮች የተስፋ ምድር የሆነችውን ከነዓንን እንደሚወርሱ ተናገረ። ይህች ምድር የእነርሱ ርስት ትሆናለች አለ። የኢያሱ፥ የመሳፍንትና የ1ኛና 2ኛ ሳሙኤል መጻሕፍት እነዚህ የተስፋ ቃሉች በረጅም ጊዜ ውስጥ እንዴት እንደተፈጸሙ የሚናገሩ ናቸው።

ሐ. እግዚአብሔር ከአብርሃም በተለይም ከይሁዳ የዘር ግንድ አንድ ልዩ የሆነ ንጉሥ እንደሚወጣ የተስፋ ቃል ሰጣቸው (ዘፍጥ. 17፡6፥16፤ 49፡10)። ይህ የተስፋ ቃል በመጀመሪያ በዳዊት ተፈጸመ። በመጨረሻም በኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጽሟል። 

 1. እግዚአብሔር በሲና ተራራ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳንን አደረገ (ዘጸ. 19-24)። እግዚአብሔር ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታዎችን ከሰዎች ካልጠየቀባቸው ከሌሉቹ ቃል ኪዳኖች በተቃራኒ፥ በሲና ተራራ እግዚአብሔር ከአይሁድ ሕዝብ ጋር ያደረገው ስምምነት ቃል ኪዳኑ ይፈጽም ዘንድ እነርሱም ሊያሟሉት የሚገባ ቅድመ ሁኔታ ነበር። ብሉይ ኪዳን ብለን ከምንጠራቸው ከሠላሳ ዘጠኙ መጻሕፍት መካከል አብዛኛዎቹ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ስለገባው ቃል ኪዳን ከሚናገሩ ነገሮች ጋር የተያያዙ ነበሩ። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን እንዴት እንደጀመረ (ዘፍጥረት እስከ ዘዳግም)፥ ለእስራኤላውያን የከነዓንን ምድር በመስጠት የገባላቸውን ተስፋ እንዴት እንዳከበረ (ኢያሱ እስከ 2ኛ ሳሙኤል)፥ እንዲሁም እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ቃል ኪዳን እንዴት እንዳፈረሱና ለጊዜው እንደተፈረደባቸው (1ኛ ነገሥት እስከ ሚልክያስ) እናነባለን። 
 2. ከካህኑ ከፊንሐስ ጋር የተገባ ቃል ኪዳን (ዘኁል. 25፡10-13)። በዚህ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ለፊንሐስ ዘሮች ካህናት የመሆን መብት ሰጥቷል።
 3. ከንጉሥ ዳዊት ጋር የተገባ ቃል ኪዳን (2ኛ ሳሙ. 7፡5-16)፡ እግዚአብሔር ለዳዊት የእርሱ ዘሮች በእስራኤል ሕዝብ ላይ ንጉሥ የመሆን መብት እንዳላችው ቃል ኪዳን ገባለት። በ መጨረሻ ይህ ቃል ኪዳን የይሁዳ አንበሳ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጸመ። እርሱ በእስራኤልና በሕዝቦች ሁሉ ላይ ንጉሥ ነው። አንድ ቀን ኢየሱስ ወደዚህች ምድር በመመለስ እንደገና ይነግሣል (ራዕ. 20፡4)። 
 4. አዲስ ቃል ኪዳን (ኤር. 31፡31-34)፥ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ከቃል ኪዳኑ ጋር የሰጣቸውን ቅድመ ሁኔታ መጠበቅ ስላልቻሉ፥ እግዚአብሔር አዲስ ቃል ኪዳን እንደሚሰጥ አስታወቀ። በዚህ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ሕግን እንደሚያደርግና ለሰዎችም ይህንን ሕግ የመታዘዝ ችሉታ በልባቸው እንደሚሰጣቸው ተስፋ ሰጥቷል። ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ይህንን አዲስ ቃል ኪዳን እንደጀመረው ሐዋርያት በኋላ ተገነዘቡ። 

፪. ብሉይ ኪዳን፡- የመጀመሪያዎቹን 39 ቅዱስ መጻሕፍት «ብሉይ» ብለው በመጥራታቸው የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ከኢየሱስ መምጣት ጀምሮ አንድ አዲስ ነገር እንደተፈጸመ ያሳዩናል። በኤር. 31 የተሰጡት ተስፋዎች ተፈጽመዋል። እነዚህ የቀድሞ ክርስቲያኖች የመጀመሪያዎቹን 39 መጻሕፍት ብሉይ ብለው የጠሩባቸው ሦስት ምክንያቶች አሉ፡-

ሀ. እግዚአብሔር አዲስ ቃል ኪዳንን በኤር. 31፡31-34 ላይ ስለሰጠ የቀድሞው ቃል ኪዳን አሮጌ ወይም ጊዜ ያለፈበት ሆኗል፡፡

ለ. ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ሌሊት የሚያፈሰው ደም ይቅርታን የሚያስገኝ የቃል ኪዳን ደም እንደሆነ ተናግሮ ነበር። ይህንን ቃል ኪዳን ኢየሱስ አዲስ ቃል ኪዳን ብሎ ባይጠራውም እንኳ እግዚአብሔር እውነተኛ የኃጢአት ይቅርታ የሰጠበት በትንቢተ ኤርምያስ የምናገኘው አሳብ መሆኑ ግልጽ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዕብ. 7፡ 18-22፤ 8፡6-13 አንብብ። ሀ) የዕብራውያን ጸሐፊ የቀድሞውን ቃል ኪዳን የጠራባቸውን ስሞች ዘርዝር። ለ) ይህ ጸሐፊ አዲሱን ቃል ኪዳን የጠራባቸውን ስሞች ዘርዝር። ሐ) ጸሐፊው ስለ ቀድሞው ቃል ኪዳን ምን ይላል?

ሐ. በሲና ተራራ የተሰጠው ቃል ኪዳን በዕብራውያን መልእክት «የቀድሞው፥ አሮጌው፥ የፊተኛውና ዘመኑ ያለፈበት» ተብሏል። በሌላ በኩል ኢየሱስ የጀመረው ቃል ኪዳን «አዲስ፥ የተሻለና የላቀ» ቃል ኪዳን ተብሉአል። እነዚህ ቃላት ሁሉ የሚያሳዩት ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ከእግዚአብሔር ጋር አዲስ ስምምነት የተደረገበት አዲስ ዘመን መጀመሩን የቀድሞ ክርስቲያኖች ምን ያህል ተገንዝበውት እንደነበር ነው። እንደ አንዳንድ የብሉይ ኪዳን ቃል ኪዳኖች፣ ይህ አዲስ ቃል ኪዳን በቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ ነው፤ በሰው ፍጹም መታዘዝ ላይ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃላት ላይ የተመሠረተ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የአዲስ ኪዳን የተስፋ ቃል በሲና ተራራ የተሰጠውን ሕግ በሙሉ ስለመጠበቅ አስፈላጊነት ለእኛ ምንን ያመለክታል? ለ) በአሁኑ ጊዜ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች በሲና ተራራ ለአይሁዳውያን ከተሰጡት ሕጎች አንዳንዶቹን የሚከተሉት ለምንድነው? ሐ) እነርሱ ከሚከተሏቸው ሕጎች አንዳንዶቹን ዘርዝር።

ስለ ብሉይ ኪዳን ቃል ኪዳኖችና ከአዲስ ኪዳን ጋር ስላላቸው ግንኙነት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን አስተሳሰብ የተለያየ ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ቃል ኪዳን አንድ ብቻ ነው፤ ይህም ብቸኛ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ነው ይላሉ። በብሉይ ኪዳን ቃል ኪዳን የተደረገው በሥጋም በመንፈስም የአብርሃም ልጆች ከነበሩት አይሁዳውያን ጋር ሲሆን፥ በአዲስ ኪዳን ደግሞ የአብርሃም መንፈሳዊ ልጆች ከሆኑት ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር ነው (ገላ. 4፡21-31 ተመልከት)። ሌሉች ክርስቲያኖች ደግሞ ፍጹም የተለያዩ ሁለት ቃል ኪዳኖች ናቸው ይላሉ። የመጀመሪያው ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የተሠዋው ለኃጢአታቸው እንደሆነ ከተቀበሉት ሰዎች ሁሉ ጋር ነው። እነዚህኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እግዚአብሔር በሥጋ የአብርሃም ዘር ለሆኑ የገባቸው ቃል ኪዳኖችና ለቤተ ክርስቲያን የገባቸው ቃል ኪዳኖች በግልጽ መለየት አለባቸው ይላሉ። እነዚህ ልዩነቶች እንደዋና ነገር የማይታዩ ቢሆኑም እንኳ ብሉይ ኪዳንን የምንረዳበትና የምንተረጉምበት አብዛኛው መንገድ የተመሠረተው የብሉይና የአዲስ ኪዳን ልዩነቶች ምን እንደሆኑ ባለን መረዳት ላይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በብሉይ ኪዳን የሚገኙ ቃል ኪዳኖችን በሙሉ ከልስ። ለ) የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎችን በሙሉ አንብብ። ሐ) በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃላት ዘርዝር። መ) ለእነዚህ የተስፋ ቃላት የተሰጡ ሌሉች ቅድመ ሁኔታዎችን ዘርዝር። ሠ) ዛሬ ከእኛ ጋር በቀጥታ የሚያያዙ የተስፋ ቃላት የትኞቹ ናቸው? ረ) በብሉይ ኪዳን ዘመን ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች ብቻ የሚሆኑትስ የተስፋ ቃላት የትኞቹ ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም የሚጠቅሙ አጠቃላይ ሕጎች

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ለአንተ የተናገረባቸውን የተለያዩ መንገዶች ዘርዝር። ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ለሰዎች የተናገረባቸውን የተለያዩ መንገዶች ዘርዝር (ዕብ. 1፡1-2 ተመልከት)።

በዘመናት ሁሉ እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን ለሰዎች በተለያዩ መንገዶች ገልጿል። ለአንዳንዶች እግዚአብሔር በቀጥታ በሚሰማ ድምፅ ተናግሯል። ለሌሎች በሕልምና በራእይ ተናግሯቸዋል። አንዳንዶች የእግዚአብሔር ግፊት በልባቸው ይሰማቸዋል። እግዚአብሔር እስካሁንም ድረስ ራሱንና ፈቃዱን በእነዚህ መንገዶች የሚገልጽ ቢሆንም፥ ዛሬ ራሱንና ፈቃዱን የሚገልጥበት ዋና መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ይህ እውነት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሁለት ጭብጦችን ያስተምረናል፡

 1. እያንዳንዱ ክርስቲያን እግዚአብሔርን በጥልቀት ለማወቅ ብቻ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅና ለመታዘዝ ቃሉን የማንበብና የማጥናት ኃላፊነት አለበት። ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብ ስለሚችል እግዚአብሔርን ላለመታዘዝ ምንም ምክንያት ማቅረብ አይችልም። ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ክርስቲያኖች እንዲማሩ የሚያነቃቃቸው አንዱ ነገር የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብ እንዲችሉ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በእያንዳንዱ ነገድ ቋንቋ እንዲተረጎም የሚያስፈልግበት አንዱ ዋና ምክንያት ይህ ነው። እግዚአብሔር ፈቃዱ ከእኛ እንዲሰወር አይሻም፤ ይልቁንም እርሱን እንድናውቀውና በፈቃዱ እንድንኖር ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ በእያንዳንዱ ሰው ቋንቋ ሊጻፍ ይገባዋል፤ ምክንያቱም ይህ ሲሆን ሰዎች ያነበቡትን ነገር በግልጥ ይረዱታል። በዚህ መንገድ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግና እርሱን የበለጠ በማወቅ ለፈቃዱ ታዛዥ መሆን ይቻላል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ለመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ ሥራ ድጋፍ ለማድረግ ስለ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ኃላፊነት ይህ ምን ሊያስተምረን ይገባል? ለ) የቤተ ክርስቲያን አባላት በግላቸው መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ ዘንድ ለማበረታታት ስለ መሪዎች ኃላፊነት ይህ ምን ያስተምረናል? 

 1. እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ግንኙነት ማድረግ የሚችልባቸው የተለያዩ መንገዶች በመጽሐፍ ቅዱስ ዳኝነት መመዘን አለባቸው። ብዙ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ብድግ እያሉ እግዚአብሔር ተናግሮአል ይላሉ፤ ነገር ግን ተናግሮናል የሚሉት ነገር እግዚአብሔር በቃሉ በግልጥ ከተናገረው ነገር ጋር የሚቃረን ነው። ሰይጣንም ሕልምን መስጠት ይችላል። ሰይጣንም አንዳንድ ነገሮችን እንድናደርግ በልባችን ሊያነሣሣን ይችላል። እውነትን ከውሸት ለመለየት የምንችለው ሐሰተኛ አስተማሪዎች የሚናገሩትን ነገር ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በማወዳደር ብቻ ነው። እግዚአብሔር የማይዋሽና የማይለወጥ ስለሆነ ዛሬ ለእኛ የሚገለጥልን ነገር ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ከገለጠው ነገር ጋር የግድ መስማማት አለበት። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔር ተናገረን የሚሉበትን መንገድ ለመግለጥ የሚያስችሉ መግለጫዎችን ዘርዝር። ለ) ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ስታወዳድረው እነዚህ ሰዎች የሚሉት ነገር ከእግዚአብሔር ጋር ይስማማል ወይስ ይቃረናል? ሐ) ሐሰተኛ አስተማሪዎች እግዚአብሔር ተናገረን ሲሉ ሰምተህ ታውቃለህን? መ) እግዚአብሔር በቃሉ እንዴት እንደተናገረህ የሚያስረዱ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን ለሰው ልጆች የገለጠበትና ዛሬም የሚገልጥበት መንገድ ነው ካልን፥ ልጆቹ እንደ መሆናችን ቃሉን ማጥናት ተቀዳሚ ተግባራችን መሆን አለበት። እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስን የሰጠን ከእርሱ ጋር የግል ግንኙነት ለመመሥረት እንድንችል ነው፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት ብቻ ሳይሆን ያለማቋረጥ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ካልተገናኘን እግዚአብሔር እንድናውቀው የሚፈልገውን ያህል እርሱን አናውቀውም። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብ በጣም ጥቂት ጊዜ የሚሰጡት ለምንድነው? ለ) የእግዚአብሔርን ቃል ከማንበብና ከመጸለይ በጣም አስፈላጊ የሆነው የትኛው ይመስልሃል? ለምን?

ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ያለማቋረጥ ልንከተላቸው የሚገባን ሁለት መንፈሳዊ ሥርዓቶች አሉ። ከእነዚህም አንዱ ጸሎት ነው። ብዙ ሰዎች በጸሎት ጊዜያቸውን ማሳለፍ ይወዳሉ። ለመጸለይ በማለዳ ይነቃሉ። ስለብዙ ነገር ይጸልያሉ። አንዳንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር የልመና ጸሎት ብቻ ስለሚያቀርቡ ጸሎታቸው የስስታምነት ይሆናል። በጸሎታቸው እግዚአብሔርን ለማምለክና ለማመስገን ጥቂት ጊዜ ብቻ ይሰጣሉ። በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር እንነጋገራለን፥ እናመልከዋለንም። ደግሞም የከበደንን ነገር ወደ እርሱ ዘንድ በማምጣት እርሱ እንዲያቃልለው እንለምነዋለን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ለእኛ ሊናገረንና እርሱን ልናደምጠውም ይገባል። ሁለተኛው መንፈሳዊ ሥርዓት የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብ ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እኛን የሚናገረን፥ የሚያበረታታን፥ የሚመራን፥ ራሱንና ፈቃዱን ለእኛ የሚገልጠው ወዘተ በቃሉ ነው። ክርስቲያን በመንፈሳዊ ሕይወቱ እንዲያድግ መጸለይና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ሊከናወኑ ይገባል። ሁለቱም እኩል አስፈላጊዎች ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ የዚህ ሳምንት የጸሎት ጊዜህን መርምር። ሀ) የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብ ምን ያህል ጊዜ እንደወሰድክ ተከታተል። ል) ለመጸለይ ምን ያህል ጊዜ እንደወሰድህ ጻፍ። ሐ አንተ ልታደርገው ቀለል የሚልህ የትኛውን ነው? ለምን? መ) በሕይወትህ ውስጥ ጸሎትንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን እንዴት የማያቋርጥ ልምምድ ማድረግ ትችላለህ? 

ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በተለይም ብሉይ ኪዳንን ለመረዳት በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ አድርገው ይገምታሉ፤ ስለዚህ የሚወዱአቸውንና የሚረዱአችውን ክፍሎች ያነብባሉ። ለመረዳት የሚከብዱትንና አስቸጋሪ የሆኑትን ክፍሎች አያነብቧቸውም።

የውይይት ጥያቄ፥ ብዙ ጊዜ የማታነብባቸውንና ለመረዳት አስቸጋሪ የሚሆኑብህ ክፍሎች ያሉባቸውን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዘርዝር።

ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉ የእግዚአብሔር ቃል ከሆነ፥ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ መጽሐፍና ምንባብ ዓላማ አለው፤ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ ማንበብና መረዳት ለሁላችንም ጠቃሚ ነው። በጣም አስቸጋሪ የሆኑ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች እንኳ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ፈቃዱ የሚገልጡት ነገር አላቸው። እጅግ ከባድ የምንላቸው ክፍሎች ሁሉ «ለትምህርት፥ ለተግሣጽ፥ ልብን ለማቅናትና ጻድቅ ለሆነ ምክር» የሚጠቅሙ ናቸው (2ኛ ጢሞ. 3፡16)፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በቃሉ በሚገኙ የተለያዩ ክፍሎች በኩል ለእኛ ሊገልጥ የፈለገውን ፈቃዱን መረዳት ጠቃሚ ነው። ብሉይ ኪዳንን በምናጠናበት ጊዜ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ መጻሕፍት ውስጥ እንኳ የእግዚአብሔር ዓላማና መልእክት ምን እንደሆነ ለመረዳት እንጥራለን። መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳትና በትክክል ለመተርጎም ስንፈልግ ልናስታውሳቸው የሚገቡ ሦስት መሠረታዊ እውነቶች አሉ፡-

 1. የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርት (መልእክት) ግልጥ ነው፤ ማንኛውም ክርስቲያን ሊያነበውና ሊረዳው ይችላል።

እግዚአብሔር የጻፈው የተደበቀ መልእክት አይደለም። ፈቃዱ እንዲታወቅና ልጆቹ ሁሉ እንዲከተሉት ይፈልጋል። እኛ ልጆቻችን በሚገባቸው መንገድ አንድን ነገር እንዲያደርጉ ትእዛዝ እንደምንሰጣቸው ሁሉ እግዚአብሔርም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትእዛዛቱን የሰጠው ክርስቲያኖች ሁሉ እርሱ የገለጠውን ነገር መረዳት በሚችሉበት መንገድ ነው። የእግዚአብሔርን ቃል በማስተዋል የሚያነብ ማንኛውም ክርስቲያን እግዚአብሔር ማን እንደሆነ፥ ሰዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑና ክርስቶስ ለሰዎች ኃጢአት ሁሉ በመስቀል ላይ እንዴት እንደሞተ በቂ ግንዛቤ ያገኛል። የእግዚአብሔር ቃል መረዳት የተሰጠው «ለተማሩ» ወይም «በመጽሐፍ ቅዱስ» ወይም በሥነ መለኮት ትምህርት ዲግሪ ላላቸው ብቻ አይደለም። የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናት ሰፊ ጊዜ የሰጡና የብሉይ ኪዳንን ዘመንና ባሕል በከፍተኛ ሁኔታ የተገነዘቡ ሰዎች የበለጠ ሊረዱአቸው የሚችሉአቸው አስቸጋሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ቢኖሩም፥ መሪዎች እንደመሆናችን መጠን መጽሐፍ ቅዱስ እኛ ብቻ ልንረዳው የምንችልና ለእነርሱ ግን በጣም ከባድ ነው ብለን ለቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን በፍጹም መናገር የለብንም። በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት ክርስቲያኖች ሁሉ የእግዚአብሔር ካህናት ስለሆኑ፥ የእግዚአብሔርን ቃል በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ሊያጠኑና ሊተረጉሙት ይችላሉ (1ኛ ጴጥ. 2፡4-10፤ 1ኛ ዮሐ. 2፡27 ተመልከት)።

የውይይት ጥያቄ፥ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት የሚችሉት ልዩ መሪዎች ብቻ እንደሆኑ በማሰብ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ለራሳቸው ማጥናት በሚያቆሙበት ጊዜ አደገኛ የሚሆነው ለምንድነው?

 1. እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን ለሰው ልጆች ሁሉ በግልጽ ገልጧል። የጻፈው የተደበቀ መልእክት አይደለም።

ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስን የጻፈው «በሰምና ወርቅ» ነው ብለው ያስባሉ። እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲጻፍ በሚያደርግብት ጊዜ የተጻፈውን ነገር እውነተኛ ትርጉም ከቃላቱ በስተጀርባ ሰውሮታል ብለው ይገምታሉ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም በሚሞክሩበት ጊዜ ዘወትር የተሰወረ ትርጉምን ይፈልጋሉ። የምናመልከው አምላክ ግን ራሱንና ፈቃዱን በምሥጢራዊ ቃላት የሚሰውር አይደለም። እግዚአብሔር እኛን በቀጥታ ይናገረናል፤ እንድናውቀውና እንድንታዘዘውም ይፈልጋል።

ጓደኛችን ስለ ሕይወት በማንሣት አንድ ነገር እንድናደርግለት በመጠየቅ ደብዳቤ ቢጽፍልን የተሰወረ ትርጉም ከደብዳቤው መፈለግ የተለመደ አይደለም። የጻፈውን መልእክት እንዳለ እንቀበለዋለን። የእግዚአብሔርም ቃል ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። በአንድ በኩል ስናየው እግዚአብሔር ለእኛ የጻፈው ደብዳቤ ነው። እግዚአብሔር ስለ ራሱ ይነግረናል። ደግሞም እስካሁን ምን ሲያደርግ እንደነበረና እኛ ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግ ይነግረናል። እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን ምሥጢራዊ ትርጉም ያላቸውን ቃላት በመጠቀም መደበቅ ልማዱ አይደለም።

 1. ብዙ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነው ከእኛ የተለየ ቋንቋ ለሚናገሩና በተለየ ባሕል ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የተጻፈ በመሆኑ ነው።

ሁላችንም ብንሆን አንድን ነገር በምንሠራበት ወይም በምንናገርበት ጊዜ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ይረዱን ይሆንን? የሚል ፍርሃት ያደረብን ጊዜ ነበር። የራሳችንን ቋንቋ የሚናገሩና ከሁሉ በተሻለ ሁኔታ የሚያውቁን ቤተሰቦቻችን እንኳ አንዳንድ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ ይረዱናል። በዕድሜ የገፉ አዛውንት ወጣቶችን፥ ወጣቶች ደግሞ አዛውንትን በተሳሳተ መንገድ ይረዷቸዋል። ይህ ደግሞ የተለያየ ቋንቋ በሚናገሩና የተለያየ ባሕል ባላችው ሰዎች መካከል ያለ ነው። በርካታ ያለመግባባቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ። በተለይም በተሳሳተ መንገድ መረዳት ሊኖር የሚችልባቸው ሁለት ሁኔታዎች አሉ፡-

ሀ. የሰዎችን ቋንቋ በተሳሳተ መንገድ መረዳት፥ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የምታውቁ ሰዎች ከአፍ መፍቻ ቋንቋችሁ ጋር አንድ ዓይነት ወይም ፍጹም ተመሳሳይ የሆነ ትርጉም የሌላቸው በርካታ የእንግሊዝኛ ቃላት እንዳሉ ትገነዘባላችሁ። በቋንቋችሁ ሁለት ዓይነት ትርጉም የሚሰጡ ቃላት ከእንግሊዝኛው ትርጉም የተለዩ ናቸው። ብሉይ ኪዳን የአይሁድ ቋንቋ በሆነው ዕብራይስጥ ተጻፈ። ወደ አማርኛ፥ ወደ ኦሮምኛ፥ ወይም ወደ እንግሊዝኛ በሚተረጎምበት ጊዜ መጀመሪያ በተጻፈበት በዕብራይስጥ የነበረውን ዓይነት ትርጉም እንዲሰጥ ማድረግ ከባድ ነው፤ ስለዚህ ነው ለአንድ ቃል የተለያዩ ትርጉሞች የሚሰጡት። የግዕዝን ቋንቋ የማያውቁ ወይም አማርኛ የመጀመሪያ ቋንቋቸው ያልሆነ ብዙ ኢትዮጵያውያን በቀድሞው የአማርኛ ትርጉም ውስጥ ያሉ አንዳንድ ቃላት ምንም ስሜት አይሰጧቸውም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ሊለው የፈለገውን ነገር በተሳሳተ መንገድ ሊረዱ ወይም የእግዚአብሔርን ቃል መረዳት ከባድ ሊሆንባችው ይችላል።

ለ. የሌሎችን ብሔረሰቦች ባሕል በተሳሳተ መንገድ መረዳት፥ ሁላችንም የምንኖረው በኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆንም በአገሪቱ ውስጥ የተለያዩ ብሔረሰቦች መኖራቸው እርግጥ ነው። እያንዳንዱ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ ባሕል ስላለው ከተለያዩ ብሔረሰቦች የሆኑ ሰዎች በአንድ ላይ ሲሆኑ፥ ብዙ ጊዜ አንዱ ሌላውን በተሳሳተ መንገድ ይረዳዋል፤ ለምሳሌ በአንዳንድ ባሕሎች ለአንድ ሰው አንድን ነገር በግራ እጅ መስጠት ነውር ነው። በሌሉች ባሕሎች ደግሞ በግራም ሆነ በቀኝ መስጠት ምንም ልዩነት አያመጣም። ለአንድ ባሕል ነውር የሆነው ነገር ለሌላው ባሕል ምንም አይደለም። ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ቀላል ነገር ሳይቀር በሰዎች መካከል ያለመግባባትን ሊያመጣ ይችላል። በተመሳሳይ መንገድ ብሉይ ኪዳን የተጻፈው የራሳቸው ባሕል ላላቸው አይሁድ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ለምንኖረው ለእኛ ወይም በተለይ ላለንበት ብሔረሰብ የተጻፈ አይደለም። ይህም ማለት አንዳንድ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን አንዳንድ ክስተቶች በተሳሳተ መንገድ ልንረዳ እንችላለን ማለት ነው። ወይም ደግሞ አንድን ተግባር ላንረዳው ስለምንችል የብሉይ ኪዳንን አንዳንድ ክፍሎች ከሕይወታችን ጋር ለማዛመድ በጣም ልንቸገር እንችላለን።

በእነዚህ ሁለት መንገዶች መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ መረዳት በጣም ቀላል ስለሆነ ሁለት ነገሮችን በማድረግ በተሻለ መንገድ ለመረዳት መሞከር አለብን፡- የመጀመሪያው በዚያ ስፍራ በሥራ ላይ የዋሉትን ቃላት ትክክለኛ ትርጉም መረዳታችንን ማረጋገጥ አለብን። ለእግዚአብሔር ቃል ያለንን ትክክለኛ መረዳት ያዛቡብናል ብለን የምናስባቸውን ቃላት በትክክል ለመረዳት የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትና ሌሎች የማብራሪያ መጻሕፍትን መጠቀም ይኖርብናል። ለምሳሌ፡- ድነት (ደኅንነት)፥ መዋጀት፥ ቅድስናና ጽድቅ የሚሉት ቃላት ለአይሁዳውያን የሚሰጡትን ትርጉም መረዳት አለብን። ሁለተኛው ነገር፥ የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል መተርጎም እንችል ዘንድና የአይሁዳውያንን ባሕል በትከክል ለመረዳት በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትና በሌሉች የማብራሪያ መጻሕፍት መጠቀሙ አስፈላጊ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበትና በምንተረጉምበት ጊዜ ከላይ የተጠቀሱትን ሦስት እውነቶች ልናስተውሳቸው የሚገባን ለምንድን ነው ብለህ ታስባለህ? ለ) እነዚህን መመሪያዎች የማይከተሉ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት የእግዚአብሔርን ቃል በተሰሳተ መንገድ እንደተረጎሙት ግለጥ።

ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል በተሻለ ሁኔታ እንዲረዱና እንዲተረጉሙት ለመርዳት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ልንከተላቸው የሚገባን አንዳንድ መመሪያዎችን አዘጋጅተዋል። ዋናውና ጠቃሚው የእግዚአብሔር ቃል ምን እንደሚል እኛ የምናስበው ሳይሆን የእግዚአብሔር ሥልጣን ያለው፣ እርሱ በቃሉ የሚለውና የተናገረው እንደሆነ ልብ ማለት ያሻል። የራሳችንን መረዳት ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደተገኘ ከመቁጠር ይልቅ፥ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በእርግጥ የሚለውን ነገር ለመረዳት መሻት በጣም አስፈላጊ ነው። የሚከተሉት ነገሮች ለእነዚህ ሕግጋት መግቢያ ብቻ ናቸው፡-

 1. የመተርጎም ሂደት በትክክለኛ ቅደም ተከተላችው ልናሟላቸው የሚገቡን የሁለት ጥያቄዎችን ቅርፅ የሚይዝ ነው። መጀመሪያ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ለመተርጎም የሚፈልግ ሰው:- «መጀመሪያ ለጻፈው ሰውና መጀመሪያ ደርሶት ለሚያነበው ማለትም ለተጻፈለት ሰው የሚሰጠው ትርጉም ምንድነው?» ብሎ መጠየቅ አለበት። ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሉ ምን እንደሚል ከመወሰናቸው በፊት፥ ከግል ሕይወታቸው ጋር ሊያዛምዱት ይሞክራሉ፤ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ከአንድ ክፍል ውስጥ ምን እንደሚያስተምረን ከመወሰናችን በፊት በውስጡ ባስቀመጠው መልእክት አማካይነት ለተጻፈላቸው ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች ምን ለማለት እንደፈለገ መረዳታችንን ማረጋገጥ አለብን። ይህንን ካደረግን ብቻ ክፍሉን ከራሳችን ሕይወት ጋር እግዚአብሔር እንድናዛምደው በሚፈልገው መንገድ ልናዛምደው እንችላለን። 

በሁለተኛ ደረጃ፥ «ይህ ክፍል ዛሬ ለእኛ ምን ማለት ነው?» የሚለውን ጥያቄ ለእራሳችን ማቅረብ አለብን ይህ ጥያቄ ሁልጊዜ ከመጀመሪያው ጥያቄ ቀጥሎ ሊመጣና ከእርሱም መልስ ጋር አብሮ ሊሄድ ይገባል። መጽሐፉ መጀመሪያ ሲጻፍ ምን ማለቱ እንደነበር በትክክል ለመወሰን ከቻልን ብቻ፥ ይህ ቃል ለዚህም ዘመን የሚሆን የእግዚአብሔር ቃል ነው ብለን በእርግጠኝነት ከሕይወታችን ጋር ልናዛምደው እንችላለን።

ብዙ ሰባኪዎችና አስተማሪዎች በዚህ ይሳሳታሉ። ብዙ ጊዜ ሊሰብኩት የሚፈልጉት ርእስ ይኖራቸዋል። ያንን ርእስ በአእምሮአቸው ይዘው ከርእሱ ጋር በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የሚያያዙትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይፈልጋሉ። የጥቅሶቹን ዓውደ-ንባብ በማጥናት መልእክቱ የተጻፈላቸው የመጀመሪያዎቹ ሰዎች የተረዱት ነገር ምን እንደሆነ ለማረጋገጥ ብዙም አይጥሩም።

እንዲሁም ቀድሞ ለነበሩት ሰዎች የተጻፈውን ብቻ በማጥናት፥ ዛሬ ከሕይወታችን ጋር በማዛመድ ልናገኘው የምንችለውን ትምህርት መተውም ስሕተት ነው። በክርስትና ሕይወት ውስጥ ሊያጋጥሙ ከሚችሉ አደጋዎች አንዱ የእግዚአብሔርን ቃል እንደታሪክ፥ ሒሳብ፥ ወይም ሳይንስ ለእውቀት ብቻ ማጥናት ነው። የእግዚአብሔር ቃል ሕይወታችንን ለመለወጥ የተሰጠ ነው። ሊለውጠን እንዲችል ካልፈቀድንለት፥ መንፈሳዊ ሕይወታችን ወዲያውኑ ይደርቃል። 

 1. ክፍሉን መጀመሪያ እንደተጻፈላቸው ሰዎች ለመረዳት እንድንችል የሚከተሉትን ነገሮች ማድረግ ያስፈልገናል፡-

ሀ. የምናጠናው የሥነ-ጽሑፍ ዓይነት ምን እንደሆነ በመወሰን በተጻፈበት የሥነ ጽሑፍ ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሉን ለመተርጎም መሞከር አለብን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በጽሑፋችን ወይም በስብከታችን የምንጠቀምባቸውን የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ዓይነቶች ዘርዝር። ለ) ከግልጋሎት ላይ የዋለው የሥነ -ጽሑፍ ወይም የንግግር ዓይነት ምን እንደሆነ መወሰን ለምን ይጠቅማል?

በየዕለቱ በምንገለገልበት ቋንቋ የተለያዩ ዓይነት የንግግር ዘዴዎችን እንጠቀማለን። በየዕለቱ ከምንጠቀምባቸው እነዚህን ከመሰሉ የንግግር ዓይነቶች በጣም ስለተላመድን የንግግሩን ዓይነት መሠረት በማድረግ በምናስብበት ጊዜ እንኳ መረዳትንና ትርጉሙን በሚመለከት እንለያያለን። ለምሳሌ፡- «እንቁላል ቀስ በቀስ በእግሩ ይሄዳል» የሚለውን ምሳሌ ስንሰማ ወዲያውኑ በዚህ ምሳሌ ውስጥ በጣም አስፈላጊው ነገር ቀጥተኞቹ ቃላት ሳይሆኑ ከምሳሌው በስተጀርባ ያሉ የሥነ-ምግባር ትምህርቶች እንደሆኑ እንረዳለን። በተጨማሪም «ሰምና ወርቅ»፥ ግጥሞች ታሪኮች ደብዳቤዎችና ልብ ወለድ ታሪኮች ወዘተ እንጠቀማለን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አራት ዋና ዋና የሥነ – ጽሑፍ ዓይነቶች አሉ። መጀመሪያ፥ በዘጸአት፥ በዘሌዋውያንና በዘዳግም እንዳሉት ዓይነት ሕጎች አሉ። በሁለተኛ ደረጃ፥ የታሪክ መጻሕፍት አሉ። እነዚህ የታሪክ የአጻጻፍ ስልቶች እንደ መጽሐፈ ኢያሱና መሳፍንት ባሉ በአብዛኛዎቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ይገኛሉ። ሦስተኛ፥ የግጥም መጻሕፍት ናቸው። አብዛኛው የብሉይ ኪዳን ክፍሎችና በተለይም መዝሙረ ዳዊት በግጥም የተጻፉ ሲሆን መልእክቱንም ለመግለጥ በተለያዩ ሥዕላዊ አገላለጾች ይጠቀማሉ። (ለምሳሌ፡- ዛፎች ሲዘምሩ እናያለን፤ (መዝ. [96]፡ 12)። አራተኛ፥ የነቢያት ቋንቋ ነው። እንደ ኢሳይያስና ኤርምያስ ባሉ አብዛኛዎቹ የትንቢት መጻሕፍት እንደሚታየው የነቢያት ቋንቋ የታሪክና የግጥም ድብልቆች ናቸው። ይህም የነቢያትን መልእክት ትክክለኛ አተረጓጎም የበለጠ ከባድ ያደርገዋል። ከእነዚህ አራት የሥነ ጽሑፍ ዓይነቶች የትኛውንም በምናጠናበት ጊዜ ልንጠቀምባችው የሚገባን የትርጉም ሕግጋት አሉ። ጥቂት ቆይተን የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ዓይነቶችን እንዴት እንደምንተረጉም የበለጠ እናጠናለን።

ለ. በክፍሉ የሚገኙ ቃላት መጀመሪያ መልእክቱን ለጻፈው ሰውና ለመጀመሪያዎቹ የመልእክቱ አንባቢዎች ምን መልእክት እንደሚያስተላልፍ አስቀድመን መረዳት አለብን። ይህም በተለይ በጣም አስፈላጊ የሚሆነው እንደ ጽድቅ፥ ቅድስና፥ ወዘተ ያሉ የሥነ መለኮት ትምህርት ቃላትን ስናጠና ነው። ደግሞም «የተቀደሰ እጃችሁን አንሡ፤ በጠንካራው የቀኝ ክንዱ፥ በተቀደሰ መሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ፤» ወዘተ ያሉትን ሥዕላዊ አነጋገሮች መጠቀም በሚመለከትም ረገድ ትክክለኛ ግንዛቤ መጨበጡ አስፈላጊ ነው። 

ሐ. መልእክቱ በተጻፈበት ጊዜ ስለነበረው ባሕልና የመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሰዎች የቻልነውን ያህል ለመረዳት መጣር አለብን። መልእክቱ የተጻፈው አይሁድ በምርኮ በነበሩ ጊዜ ነው ወይስ በነፃነትና በብልጽግና ሳሉ ነው? በባርነት አገር ነበሩ ወይስ በራሳቸው ምድር? ገበሬዎች ነበሩ ወይስ የከተማ ነዋሪዎች? «እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ እግዚአብሔር ዓለቴ ነው፤» ወዘተ የሚሉትን ቁልፍ አሳቦች ለመረዳት እነዚህ አስፈላጊዎች ናቸው። ለእግዚአብሔር የተሰጡት እነዚህ ስሞች የወጡት ከእስራኤላውያን የሕይወት ዘይቤ ሲሆን፥ በዚህ ዘመን ያላቸው መልእክት አንድ ላይሆን ይችላል። 

የውይይት ጥያቄ፥ መዝ. (18)፡2 ተመልከት። የብሉይ ኪዳን ጸሐፊ «እግዚአብሔር ዓለቴ፥ አምባዬ፥ መሸሸጊያ፥ ጋሻዬ፥ የደኅንነቴ ቀንድና መጠጊያዬ ነው» ሲል ምን ማለቱ ይመስልሃል?

የአይሁድን ባሕል ማወቅም በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ አህያ ስለማንነዳ፥ የአይሁድ አህያን የመንዳት ሥዕላዊ ገለጻ አይገባንም። የአይሁድ ነገሥታት የመጡት በሰላም እንጂ እንደ ወራሪ ንጉሥ አለመሆኑን በአህያ ላይ ተቀምጠው በመሄድ ያሳዩ ነበር። ኢየሱስ በአህያ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ እንደ ድል ነሺ ሳይሆን እንደ ሰላም ንጉሥ መምጣቱን ያመለክት ነበር።

መ. የምናጠናውን ክፍል ዓውደ ንባብ መመልከት አለብን። የምንመለከተው አንድ ቁጥርን ብቻ ከሆነ፥ ቁጥሩ ባለበት ክፍል የሚገኘውን ምዕራፍ በሙሉ ማጥናት አለብን። ከምናጠናው ክፍል ፊትና ኋላ ስላሉት ምዕራፎችም ማወቅ አለብን። ደግሞም ጸሐፍቱ ያንን መጽሐፍ በሚጽፉበት ጊዜ የነበራቸውን ዓላማ ማወቅ ይገባናል። ይህን የብሉይ ኪዳን ጥናት የምናጠናበት አንዱ ምክንያት የጸሐፊውን አጠቃላይ ዓላማ በተሻለ ሁኔታ እንድንረዳና ከዚያም የየክፍሎቹን ትርጉሞች ማስተዋል እንድንችል ነው።

አንድ ቃልና አንድ ቁጥር ትርጉም የሚያገኙት ባሉበት አንቀጽ ውስጥ ነው። ለምሳሌ በ1ኛ ቆሮ. 7፡2 ጳውሎስ ሲጽፍ፥ «ከሴት ጋር አለመገናኘት (አለማግባት) ለሰው መልካም ነው» ብሏል። ይህንን ጥቅስ ብቻ ብንመለከት፥ ማንም ሰው ማግባት የለበትም የሚል ትምህርት ልናስተምር ነው። ክርስቲያኖች ሁሉ ያላገቡ መሆን አለባቸው ልንል ነው፤ ነገር ግን አንቀጹን በጥንቃቄ ብንመረምረው ጳውሎስ ሳያገቡ እንዲኖሩ ሰዎችን የሚመክረው እግዚአብሔርን በተሻለ መንገድ ለማገልገል ዓላማ እንደሆነ እንመለከታለን። ጳውሎስ ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት እንድትኖረውም ይመክራል።

እንደ ይሖዋ ምስክሮች፥ ኢየሱስ ብቻ፥ ወዘተ ያሉ በርካታ የሐሰት መምህራን ትምህርታቸው የተመሠረተው ዓውደ ንባቡን በጥንቃቄ ባልተመራመሩባቸው አንድ ወይም ሁለት ጥቅሶች ላይ ነው።

ሠ. አንድን ጥቅስ ወይም ንባብ መተርጎም ያለብን በቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት ነው። እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጻፍ ብዙ የተለያዩ ሰዎችን ቢጠቀምም፥ ጸሐፊው ራሱ ስለሆነ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ አሳቦች በሙሉ እርስ በርስ መስማማት አለባቸው። እግዚአብሔር አይዋሽም፤ ደግሞም አይለወጥም፤ ስለዚህ በዘፍጥረት ያስተማራቸው ትምህርቶች ከሐዋርያት ሥራና ከራእይ ጋር የሚስማሙ መሆን አለባቸው። የአንድን ጥቅስ ትምህርት በማንረዳበት ጊዜ የቀረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በመመልከት መሠረታዊ ትምህርቱን ልንረዳ እንችላለን።

ረ. መጽሐፍ ቅዱስ አንዳች ስሕተት የሌለበት ቢሆንም፥ የእኛ ማስተዋልና ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች የምንሰጠው ትርጉም ከስሕተት የጠራ ሊሆን አይችልም። መረዳታችን ውሱን የሆነ የሰው ልጆች እስከሆንን ድረስ፥ የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ ትምህርት በሙላት ልንረዳ አንችልም። የእግዚአብሔርን ቃል ምን እንደሚል ለመረዳት የምንችለውን ያህል መጣር አለብን፤ ነገር ግን በአተረጓጎማቸው ከሌሎች ሰዎች ጋር ሳንስማማ ስንቀር ትሑታን ልንሆንና ልዩነቶችን ልናስተናግድ ይገባል። ይህም ማለት የትኛውም የጥናት መጽሐፍ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ መቶ በመቶ ትክክል ሊሆን አይችልም ማለት ነው። ጸሐፊዎቹ ስሕተትን ላለማስገባት የሞከሩ ቢሆንም፥ ውሱን መረዳት ያላቸው ሰዎች ናቸውና መሳሳታቸው አይቀሬ ነው። ይኸውም ሰባኪዎችና የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም ሳይቀሩ ስሕተት ሊሠሩ ይችላሉ ማለት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ የሐዋ. 17፡11 ተመልከት። ሀ) የቤርያ ሰዎች የተመሰገኑባችው ነገሮች ምን ነበሩ? ለ) ሰባኪዎችን በምናዳምጥበት ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያዎችን በምናነብበት ጊዜ የቤርያ ሰዎችን ምሳሌነት መከተል ያለብን ለምንድነው?

ነገር ግን ልዩነቶች እንዲኖሩ በምንፈቅድበት ጊዜ ከመጠን በላይ ቻይና ታጋሽ (አቋም የሌለን) እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን። በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ መሠረታዊ ትምህርቶች ላይ የአመለካከት ልዩነት ቢኖርም ትምህርቶችን በቀጥታ የሚቃወም ትርጉም ሊኖር አይችልም። ለምሳሌ «ኢየሱስ ብቻ» የሚባለው የሐሰት ትምህርት በተመረጡ ጥቂት ጥቅሶች ላይ ተመሥርቶ ሥላሴ እንደሌለ በመናገር መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ያቀረበውን ትምህርት ይቃረናል፤ ስለዚህ ለተከታዮቹ ትክክል አለመሆናቸው ሊነገራቸው ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰዎች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ በሚሰብኩበት ጊዜ ከእነዚህ ውስጥ በሚገባ ያልተጠቀሙባቸው ሕግጋት የትኞቹ ናቸው? ለ) የምንባብ አተረጓጎምን ለማረጋገጥ የሚረዱ፥ የምታውቃቸውን መጻሕፍት ዝርዝር ጻፍ። ሐ) የአንዳንድ ቃላትን ትርጉም ለመረዳት የሚጠቅሙ መጻሕፍትን ዝርዝር ጻፍ። መ) የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳን ባሕል ለመረዳት የሚያስፈልጉ መጻሕፍትን ዘርዝር።

ለትክክለኛ ትርጉም ቁልፉ ምንድነው? በተቻለን መጠን የመጀመሪያው የመልእክቱ ተቀባይ አካል ለመሆን መጣር አለብን። አንድ ጊዜ የጸሐፊውን ዓላማ፥ የተጻፈላቸው ሰዎች የነበሩበትን ሁኔታ፥ ጸሐፊው የተጠቀመበትን የሥነ-ጽሑፍ ዓይነት ከተረዳን፥ እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ተቀባዮች ያስተላለፈውን የመልእክት ትርጉም ለመረዳት እንችላለን። በዚህ ጊዜ ብቻ ከዘመናችን ጋር በትክክል እናዛምደዋለን። የእግዚአብሔር ቃል በታሪካዊ ዓውደ ንባቡ መሠረት ስንመለከተውና ስንረዳው በሥልጣን ልንሰብክና ልናስተምር፥ እንደ ብሉይ ኪዳን ነቢያትም «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» ልንል እንችላለን።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የብሉይ ኪዳን ቅጂዎቻችን እንዴት ሊደርሱን እንደቻሉ

እኛ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቃል ነው ብለን የምናምነው መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ነው። የእግዚአብሔርን ሙሉ ሥልጣን የያዘ ከመሆኑም ሌላ ክርስቲያን እውነትን የሚረዳበት መሠረት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ማንነቱን፥ ሰው ማን እንደሆነ፥ ከዘላለማዊ አምላክም ጋር ግንኙነት ለማድረግና እርሱን ደስ ለማሰኘት ምን ማድረግ እንዳለበት አስፈላጊውን እውነት ሁሉ እንደገለጠ እናምናለን። ዳሩ ግን ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ ሌላም እውነት ገልጾልናል። ይህም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የምናምነው እውነት አንዳችም ስሕተት የሌለበት የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ነው የሚል ነው። ዛሬ በእጃችን የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ የያዛቸው ዋና ዋና ትምህርቶች ምንም ስሕተት የሌለባችው ቢሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን በመገልበጥ ረገድ የታዩ አንዳንድ ስሕተቶች እንዳሉ እንገነዘባለን። ዛሬ በእጃችን ስላለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ጥቂት ነገሮችን እናጠናለን።

ብሉይ ኪዳን ረጅም ዕድሜ ያለው መጽሐፍ ነው። በ1400 ዓ.ዓ. አካባቢ ሙሴ የመጀመሪያዎቹን አምስት መጻሕፍት መጻፍ ጀመረ። ይህም ከ3500 ዓመታት ያህል በፊት ማለት ነው። የመጨረሻው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ የተጻፈው በ400 ዓ.ዓ. ገደማ ነበር፤ ስለዚህ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሙሉ ተጽፈው ለማለቅ 1000 ዓመታት ያህል ወስደዋል። በሌላ በኩል አዲስ ኪዳን ተጽፎ ያለቀው በ100 ዓ.ም. ነው። የአዲስ ኪዳን ዕድሜ በ2000 ዓመታት ያነሠ ነው፤ ስለዚህ አዲስ ኪዳንን በመገልበጥ ረገድ የተሠራው ስሕተት በብሉይ ኪዳን ከተሠራው ስሕተት ያነሰ ነው፤ ደግሞም ምሁራን የመጀመሪያዎቹ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ከተጻፉ በኋላ በ150 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተሠርተው የነበሩ ቅጂዎችን በከርሰ ምድር ጥናት አማካኝነት አግኝተዋል፤ ስለዚህ ምሁራን ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ይበልጥ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ችለዋል። ምሁራን ያገኙአቸው አብዛኛዎቹ የብሉይ ኪዳን ቅጂዎች የመጀመሪያዎቹ መጻሕፍት ከተጻፉ ከብዙ መቶዎች ወይም ከአንድ ሺህ ዓመታት በኋላ የተገለበጡ ናቸው፤ ስለዚህ ከአዲስ ኪዳን ይልቅ በርካታ ስሕተት የመፈጸም ዕድል ያለው በብሉይ ኪዳን ውስጥ ነው።

በጥንቱ ዓለም የጽሕፈት መኪናዎች፡ የጽሑፍ ማባዣዎችም ሆነ ወረቀት አልነበሩም። መጻሕፍት ሁሉ በእጅ መጻፍ ነበረባቸው። በጥንት ዘመን ሰዎች ለመጻፍ ይጠቀሙ የነበረው በተለያዩ ነገሮች ነበር። አንዳንዶች እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ትእዛዝን በሚሰጥበት ጊዜ እንደተጠቀመው በድንጋይ ይጠቀማሉ (ዘጸ. 24፡12፤ 31፡18፤ ኢያ. 8፡32-35 ተመልከት)። ሌሉች በእርጥብ ሸክላ ላይ ይጽፉ ነበር። እርጥቡ ሸክላ ሲደርቅ በላዩ ላይ የተጻፈው ነገር ቋሚ ሆኖ ይቀራል። ሌሉች በእንስሳት ቆዳ ላይ ይጽፉ ነበር። በኋላ ደግሞ ሰዎች ፓፒረስ ተብሎ በሚጠራ ከሸምበቆ በተሠራ ነገር ላይ ይጽፉ ነበር። በድንጋይና በሸክላ የተጻፉት ነገሮች ለብዙ መቶ ዓመታት የቆዩ ቢሆኑም በእንስሳት ቆዳና በፓፒረስ የተጻፉት ግን ጊዜያዊና የሚበሰብሱ ነበሩ፤ ስለዚህ በሚያረጁበት ጊዜ ተገልብጠው ሌላ ቅጂ ሊዘጋጅላቸው ያስፈልግ ነበር። ሰዎች ለራሳቸው የግል ቅጂ እንዲኖራቸው ሲፈልጉም በእጃቸው በመጻፍ ሊገለብጡት ያስፈልግ ነበር። አይሁድ ብዙ ጊዜ የሚጽፉት በእንስሳት ቆዳ ላይ ሲሆን፥ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በብራና ጥቅል ላይ ይጻፍ ነበር። (ለምሳሌ ሉቃ. 4፡16-21)። 

በጥንት ዘመን ብዙ ሰዎች ማንበብ አይችሉም ነበር። ጸሐፍት የተባሉ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ማንበብና መጻፍ ይችሉ ነበር። እነዚህ ሰዎች የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ደብተራዎችን የሚመስሉ ነበሩ። እነዚህ ጸሐፍት ለጥንታዊቷ እስራኤል በጣም አስፈላጊ ሰዎች ነበሩ። ለነገሥታቱ ልዩ አማካሪዎች በመሆናቸው፥ እንደ ዲፕሉማትና አምባሳደር ሆነው ወደ ሌሉች አገሮች ይላኩ ነበር። ለአይሁድ ግን ከሁሉ የሚበልጠው የእነዚህ ሰዎች ሥራ ቅዱሳት መጻሕፍትን መገልበጣቸው ነበር። ቅዱሳት መጻሕፍቱ ይቀመጡ የነበሩት ሰዎች በሚያመልኩበት በቤተ መቅደስ ስለነበር፥ በጥንቷ እስራኤል ጸሐፍቱ የአምልኮ መሪዎች የሆኑት ካህናትና ሌዋውያን ነበሩ። እነዚህ የጥንት ጸሐፍት የእግዚአብሔር ቃል ቅዱስ መሆኑን ያውቁ ስለነበር፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን በጥንቃቄ ይገለብጡ ነበር። በ586 ዓ.ዓ. የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ከተደመሰሰና እስራኤላውያን በአሕዛብ መካከል ከተበተኑ በኋላ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይገለብጡ የነበሩ ጸሐፍት ለአይሁድ ሕዝብ በጣም አስፈላጊ ሰዎች ሆኑ። እንደ ዕዝራ ያሉ ካህናት ጸሐፍት የሃይማኖት ሰዎች ሆኑ። እነዚህ ጸሐፍት (አንዳንድ ጊዜ «የሕግ መምህራን» ይባሉ የነበሩ) ኢየሱስ በኖረበት ዘመን በሕዝቡ ላይ ታላቅ ሥልጣን ያላቸው ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኑ። የኢየሱስ ጠላቶችም ነበሩ (ማቴ. 12፡38-39 ተመልከት)። 

የውይይት ጥያቄ፡- የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ለመጠበቅ አይሁድ ያደረጉት ነገር ወይም ሁኔታ ከጥቂት ትውልድ በፊት የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በኢትዮጵያ ያደርጉት ከነበረው ሁኔታ ጋር እንዴት ይመሳሰላል?

በ586 ዓ.ዓ. የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እስከተደመሰሰበት ጊዜ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን በመገልበጥ ረገድ ስሕተት ለመሥራት የሚያደርስ በቂ ምክንያት አልነበረም። ዋናው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ያለው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ ነበር። እንደ እስራኤል ነገሥታት ያሉ አንዳንድ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ቢገለብጡም (ዘዳግ. 17፡18፤ 2ኛ ነገሥት 11፡12 ተመልከት)፤ ዛሬ በእጃችን እንዳለው የእግዚአብሔር ቃል በበርካታ ቁጥር አልነበረም። የእስራኤል ሕዝብ በዓለም ሁሉ በተበተኑበት ጊዜ ግን የተለያዩ ቅጅዎችና ትርጉሞች መኖር አስፈላጊ ሆነ። ለምሳሌ፡- እንደ ዳንኤልና ሕዝቅኤል ያሉ ሰዎች በባቢሎን ነበሩ። በባቢሎን ይኖሩ የነበሩ አይሁድ የራሳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ማግኘት አስፈለጋቸው። ብዙዎቹ አይሁድ በኋላ ወደ እስራኤል ቢመለሱም፥ ሌሎች በርካታ አይሁድ በባቢሎን ቀሩ። በባቢሎንም ሆነው ቅዱሳት መጻሕፍትን መገልበጥ ቀጠሉ። በባቢሎንና በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ጸሐፍት ቅጂዎቻቸውን ለማወዳደር ዕድሉ አልነበራቸውም፤ ስለዚህ በየስፍራው ባሉት ቅጂዎች መካከል ልዩነቶች መታየት ጀመሩ። ደግሞም በ200 ዓ.ዓ. አንዳንድ አይሁድ በግሪክ ቋንቋ የእግዚአብሔር ቃል አስፈለጋቸው። በግብፅና በሌሎች አካባቢዎች ስለኖሩና መጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን የዕብራይስጥን ቋንቋ ስለረሱ በሚናገሩት በግሪክ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ አስፈለጋቸው፤ ስለዚህ ምሁራን ብሉይ ኪዳንን ወደ ግሪክ ቋንቋ ተረጎሙት። ይህም ትርጉም ሴፕቱዋጀንት በመባል ይታወቅ ጀመር። ክርስቶስ በኖረበት ዘመን ሴፕቱዋጀንት እጅግ ተወዳጅ ቅዱስ መጽሐፍ ሲሆን፥ ብዙ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎችም ከዚህ ትርጉም ይጠቅሱ ነበር፤ ስለዚህ ሦስት ዋና ዋና የብሉይ ኪዳን ቅጂዎች አሉን። እነርሱም በኢየሩሳሌም የነበረው፥ በባቢሎን የነበረውና በግሪክ ቋንቋ የተጻፈው ናቸው፡፡ በሌሉች ስፍራዎች የነበሩ ሰዎችም የየራሳቸውን ቅጅ መገልበጥ ጀመሩ። ለምሳሌ:- ሳምራውያን አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት (ፔንታቱክ) ለራሳቸው አምልኮ ገለበጡ፤ ስለዚህ በአዲስ ኪዳን ዘመን በርካታ የብሉይ ኪዳን ቅጂዎች ሲኖሩ፥ ማንም ሰው በቅጂው ውስጥ ስሕተት እንደነበረና እንዳልነበረ ለማወቅ አላወዳደረም፤ ስለዚህ በትርጉሞች ውስጥ ስሕተቶች እየጨመሩ መጡ። የትርጉሞች ወይም የቅጂዎች ስሕተቶችም እየጨመሩ የመጡት ጸሐፊዎቹ በሚገለብጡበት ጊዜ በሠሩት ስሕተት ምክንያት ነው።

የመጻሕፍቱን ቅጂዎች በመገልበጥ እንዴት ስሕተቱ ሊፈጸም እንደሚችል የሚከተለውን መግለጫ እንመልከት፡- የማዕከላዊው ቤተ ክርስቲያን ጽሕፈት ቤት በየአውራጃው ለሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት ጽሕፈት ቤቶች አንድ ደብዳቤ እንደላከ አስብ። በደብዳቤውም ውስጥ የተወሰኑ መመሪያዎችና ደንቦች ነበሩ። እነዚህ የአውራጃ አብያተ ክርስቲያናት ይህንን ደብዳቤ በእጃቸው ገልብጠው ለወረዳ አብያተ ክርስቲያናት ቢሮዎች ይልካሉ፤ የወረዳ አብያተ ክርስቲያናት ቢሮዎች ደግሞ ይህን ደብዳቤ በእጃቸው ገልብጠው ለየአብያተ ክርስቲያናት ቢሮዎች ይልካሉ። እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ደብዳቤዎችን በእጁ ገልብጦ ለየአባላቱ ማደል ነበረበት እንበል። ይህን ነገር ማድረግ ቢኖርብን በዚህ ሂደት ውስጥ የሚሆኑ ሁለት ዋና ነገሮች ሲፈጸሙ እናይ ነበር። የመጀመሪያው፥ በእጅ በመገልበጥ ረገድ ስሕተት መታየት መጀመሩ ነው። ሰዎች በእጃቸው በመጻፍ በሚገለብጡበት ጊዜ አንዳንድ ፊደላትን ወይም ቃላትን ይተዋሉ። ደብዳቤው ከማዕከላዊው ቢሮ ማለትም መጀመሪያ ከተጻፈበት ቦታ እየራቀ በሄደ ቁጥር የስሕተቱ መጠን እየጨመረ ይሄዳል። ሁለተኛው፥ ስሕተቶቹ አንድ የተወሰነ መንገድ የሚከተሉ መሆናቸው ነው። አንድ የአውራጃ ቤተ ክርስቲያን ጽሕፈት ቤት ከማዕከላዊ ቤተ ክርስቲያን ጽሕፈት ቤት የመጣውን ደብዳቤ በሚገለብጥበት ጊዜ አንድ ቃል ቢተው ከዚያ አውራጃ ቤተ ክርስቲያን ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ የሚደርሳቸው የወረዳ ቤተ ክርስቲያን ጽሕፈት ቤቶች ሁሉ ተመሳሳይ ስሕተት የያዙ ይሆናሉ። ይህም ስሕተት ያንን ቃል ያለመያዝ ይሆናል። 

የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በተለያዩ ስፍራዎች በእጅ ጽሑፍ በሚገለበጡበት ጊዜም የተሠራው ስሕተት ይህንኑ የመሰለ ነበር፤ ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ያደረጉት አንድ ዋና ነገር ስሕተቱ ከየት እንደመጣ ለማወቅ የተገኙትን የተለያዩ ቅጂዎች ማወዳደር ነበር። በኢየሩሳሌም የተገለበጡትን መዛግብት ከባቢሎን፥ ከግሪክ እንዲሁም በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከሚገኘው የግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሁሉ ያመሳክራሉ። በዚህ ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ከመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ጋር የበለጠ የሚቀራረበው የትኛው እንደሆነ ለመወሰን የማያቋርጥ ጥረት እያደረጉ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይህን በማድረግ ረገድ እርስ በእርስ ያልተስማሙበት ነገር ስለሚኖር ዛሬ በእጃችን ባሉ መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል የትርጉም ልዩነት ሊኖር ቻለ።

በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ አብዛኞቹ ቅዱሳት መጻሕፍት የተመሠረቱት ማሶሬቲክ በአይሁዶች በመባል በሚታወቁ አንዳንድ አይሁዳዊያን በተዘጋጀው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው። እነዚህ አይሁድ የኖሩትና የሠሩት ከ500-900 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ነው። በዚያን ጊዜ ያገኙትን ሁሉንም መጽሐፍ ቅዱስ ወስደው የበለጠ ትክክል ነው ብለው ያሰቡትን ቅጂ ጻፉ። የላቲኑ (የሮማ ካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስና) በአሁኑ ጊዜ ብዙ የምንጠቀምባቸው ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሶች የተተረጎሙት በእነዚህ አይሁድ ሥራ ላይ በመመሥረት ነው። እንደ ሶርያ፥ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት የሚጠቀሙበት መጽሐፍ ቅዱስና የግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ ዋና ምንጫቸው ሴፕቱዋጀንት የተባለው የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (ሴፕቱዋጀንት ማለት ሰባ ማለት ነው። ይህ ስም የተሰጠው ብሉይ ኪዳንን ሰባ የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን በሰባ ቀናት ውስጥ ተርጉመውታል ተብሎ ስለሚታመን ነው)። ይህም ዛሬ በምንጠቀምበት በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዴት መጠነኛ ልዩነት እንዳመጣ በኋላ እንመለከታለን።

በ1948 ዓ.ም. የከርሰ ምድር አጥኚዎች በእስራኤል ውስጥ ሙት ባሕር በሚባለው አካባቢ ባለ ዋሻ ውስጥ በ200 ዓ.ዓ. የተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍትን አገኙ። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እነዚህን ቅዱሳት መጻሕፍት (የሙት ባሕር ብራናዎች በመባል የታወቁትን) አሁን በእጃችን ከሚገኙ ቅጂዎች ጋር ሲያወዳድሩአቸው አንዳንድ ልዩነት ቢያገኙም በተመሳሳይነታቸውና የእግዚአብሔር ቃል በዘመናት ሁሉ በሚገለበጥበት ጊዜ በአንፃራዊነት ሲታይ በተገኘው ጥቂት ስሕተት ተደንቀዋል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? እኛ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ ለመለወጥ ይቃጣ የነበረውን የተለመደ አዝማሚያ እንደተቋቋመው እናምናለን። ትላንትና እንዳየነው እግዚአብሔር ቃሉን በሚያስደንቅ መንገድ ስለጠበቀው ዛሬ በእጃችን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን ስለማወቅና ከእርሱ ጋር እንዴት ግንኙነት እንደምናደርግ የሚያስፈልገንን እንደሚነግረን እርግጠኞች ነን። 

የውይይት ጥያቄ፥ አንድ ሙስሊም መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት የሞላበት ነው፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል አይደለም ቢልህ እንዴት ትመልስለታለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ቃል ነው

የውይይት ጥያቄ፡- 2ኛ ጢሞ. 3፡16-17 ና 2ኛ ጴጥ. 1፡20-21 አንብብ። ሀ) እነዚህ ቁጥሮች መጽሐፍ ቅዱስን በማስገኘት ረገድ ስለ እግዚአብሔር ድርሻ ምን ይናገራሉ? ለ) እነዚህ ቁጥሮች መጽሐፍ ቅዱስን በማስገኘት ረገድ የሰው ድርሻ ምንድን ነው ብለው ያስተምራሉ? ሐ) እነዚህ ቁጥሮች እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስን ለእኛ የሰጠበት ምክንያት ምንድነው ብለው ያስተምራሉ? መ) መጽሐፍ ቅዱስ በአንተ ሕይወት ውስጥ ለትምህርት፥ ለተግሣጽ፥ ልብን ለማቅናትና በጽድቅ ላለው ምክር እንዴት እንዳገለገለ ግለጥ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምንድን ነው? እንደ ቁርአንና ሌሎች ሃይማኖታዊ ጽሑፎች ሁሉ የሰው ሥራ ነውን? ወይስ ሰውን መሣሪያ አድርጎ ሳይጠቀም እግዚአብሔር በቀጥታ ለሰዎች የሰጠው ነው? ዓላማውስ ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በራሱ ኃይል ያለው የምትሀት መጽሐፍ ነውን? እነዚህ ብሉይ ኪዳንን ማጥናት ከመጀመራችን በፊት ልንመልሳቸው የሚገቡ በጣም አስፈላጊ ጥያቄዎች ናቸው። ክርስቲያኖችም ሆኑ አይሁዶች ብሉይ ኪዳን የተለየ የእግዚአብሔር ቃልና በውስጡም እግዚአብሔር ራሱንና ዓላማውን ለሰው ልጅ የገለጠበት መጽሐፍ እንደሆነ ይናገራሉ። ክርስቲያኖች ከአይሁዶች የሚለዩት አዲስ ኪዳንም የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ስለሚያምኑ ነው።

ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች ስለ እግዚአብሔር ቃል ሁለት የተሳሳቱ ግንዛቤዎች አሉአቸው። የመጀመሪያው፥ ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር እንዲጻፍ የፈለገውን ቃል ለተለያዩ ሰዎች ቃል በቃል አጽፎአቸዋል ብለው ያስባሉ፤ ስለዚህ አንዳንዶች ብሉይ ኪዳን በሚጻፍበት ጊዜ ጸሐፊዎቹ ምንም ድርሻ አልነበራቸውም ብለው ያስተምራሉ። በዚህ መልክ የተጻፉ አንዳንድ ክፍሎች ቢኖሩም (ለምሳሌ ዘጸ. 24፡4-7)። እነዚህን የብሉይ ኪዳን ክፍሎች የጻፉት ጸሐፊዎች ግን የሚጽፉት ጉዳይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገባ የቅዱሳት መጻሕፍት አካል መሆኑን እንኳ አያውቁም ነበር። አልፎ አልፎም ጸሐፊዎቹ ከሌሎች መጻሕፍት የቀዱበት አጋጣሚ ነበር (ለምሳሌ፡- ዘኁል. 22፡14-15፤ ኢያ. 10፡13)።

በሁለተኛ ደረጃ፥ እራሳቸውን ክርስቲያን አድርገው የሚቆጥሩ አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ያለማሰባቸው ነው። ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ሥራ እንደሆነ ያስተምራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የአይሁድን ሃይማኖታዊ ልምምድ ለመረዳት የሚጠቅም እንጂ፥ እውነት አይደለም ብለው ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ቁርአን ወይም እንደ ሂንዱ እምነት መጻሕፍት ነው፤ ምክንያቱም ሁሉም የሚናገሩት ሰው እግዚአብሔርን ለማወቅ ያደረገውን ጥረት ነው ይላሉ። አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ገና ተጽፎ አላለቀም በማለት ዛሬም ቢሆን «የእግዚአብሔር ቃል» የሚሏቸውን ብዙ የሐሰት ትምህርቶች (ኑፋቄዎች) በመጨመር ላይ ይገኛሉ። የእነዚህ ትምህርቶች አመንጪ የሆኑት ሰዎች አሳባቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ እኩል በመቁጠር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያክላሉ፤ (ለምሳሌ፡- የይሖዋ ምስክሮች፥ የክርስቲያን ሳይንስ አማኞች፥ የሞርሞን ተከታዮች፥ ወዘተ)።

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በርካታ የተሳሳቱ አሳቦች በመኖራቸው፥ እምነታችን የተመሠረተውም በእርሱ ላይ በመሆኑ፥ ክርስቲያን የሆንነው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማመን ያለብን ነገር ምን እንደሆነ ግልጽ አሳብ ሊኖረን ያስፈልጋል። ስለዚህ ጉዳይ አጭር አሳብ ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

 1. መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በ2ኛ ጢሞ. 3፡16 እና 2ኛ ጴጥ. 1፡19 መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ እንደሆነና ጸሐፊዎቹ በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው እንደጻፉት እናነባለን። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ራሱ በግልጥ ይናገራል፤ ስለዚህ እኛ ክርስቲያኖች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተሉትን ነገሮች እናምናለን፡-

ሀ. መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሙሉ ሥልጣን አለው። የእግዚአብሔርን ቃልና ፍላጎቶች ይዟል፥ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ እግዚአብሔር በመካከላችን ያለና የሚናገረን ያህል ነው። እግዚአብሔር የተናገረውም የተጻፈውም ቃሉ እኩል ሥልጣን አላቸው። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የእግዚአብሔርን ቃል ስለ መስበክም ሆነ ስለ ማስተማር ይህ ምንን ያስተምረናል? ለ) ሥልጣኑ ያለው የት ላይ ነው? (ኢሳ. 55፡11 ተመልከት)። 

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደ መሆናችን መጠን ሥልጣን ያለው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ እንደሆነ ማስታወስ አለብን። የእኛ ቃላት ሥልጣን የሌላቸውና ስሕተት ሊገኝባቸው የሚችሉ ናቸው፤ ስለዚህ በምንሰብክበትና በምናስተምርበት ጊዜ የእኛ ኃላፊነት ሰዎች የእኛን አሳብ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል እንዲሰሙ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ አንዳች ስሕተት በግልጥ ማወጅ ነው (2ኛ ቆሮ. 4፡1-5፤ 2ኛ ጢሞ. 2፡15 ተመልከት)። ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል በሚሰሙበት ጊዜ ሥልጣኑና ኃይሉ ሕይወታቸውን ይለውጠዋል።

ለ. መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርም የሰውም ሥራ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ለማስገኘት እግዚአብሔር ሰዎችን በመሣሪያነት በመጠቀም በራሳቸው ቃላትና የአስተሳሰብ መንገድ እንዲጽፉት አደረገ፤ ነገር ግን የጻፉት ቃል ውጤት ብሉይ ኪዳንን ጨምሮ በሙሉ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ኢየሱስ እንዳለው በመጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የምታንሰው ፊደል ወይም ነጥብ እንኳ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ስለ ተጻፈ ሳይፈጸም አያልፍም (ማቴ. 5፡18 ተመልከት)። 

ሐ. መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሥራ ስለሆነ አንዳችም ስሕተት የለበትም። እግዚአብሔር ሊዋሽና ስሕተት ሊሠራ ጨርሶ እንደማይችል ሁሉ (ዕብ. 6፡ 18) ቃሉም አይዋሽም። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል በግልጥ ከሚያስተምረው ነገር ጋር የማይስማማ ማንኛውም ዓይነት አመለካከት ስሕተት ነው። እውነት ምን እንደሆነ የሚተረጉመው የእግዚአብሔር ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በማንኛውም ጊዜ እኛም ሆንን ሌሉች የአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን እውነትነት በሚመለከት መጠየቅ ስንጀምር፥ በእግዚአብሔር ቃል ላይ እንፈርዳለን፥ በእግዚአብሔር ላይም ፈራጆች ሆንን ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሥልጣን አለው እያልን ትክክል መሆን አለመሆኑን መጠየቅ አንችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት ካለው በሕይወታችን ላይ ምንም ሥልጣን ሊኖረው አይችልም።

ይሁን እንጂ ይህንን ዐረፍተ ነገር በመጠኑ ግልጽ ማድረግ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ በቅጅዎቹ ሳይሆን በመጀመሪያው አንዳችም ስሕተት የለበትም። ይህም ማለት ሙሴ፥ ዳዊት፥ ጳውሎስ ወይም ሉቃስ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሲጽፉ ሙሉ ለሙሉ የእግዚአብሔር ቃልና አንዳችም ስሕተት የሌለበት ነገር ጽፈዋል፤ ነገር ግን ሌሎች ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል በሚገለብጡበት (በሚቀዱበት) ጊዜ አንዳንድ ስሕተቶች ነበሩ ማለት ነው። በጥንት ዘመን በርካታ መጻሕፍትን ለማባዛት የሚያስችሉ ማተሚያ ቤቶች እንዳልነበሩ ማስታወስ ያስፈልጋል። ዛሬ እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ በሚታተምበት ጊዜ የሆሄያት ስሕተት ሊኖር ይችላል፤ ስለዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት በእጅ ሲጻፉ በዘመናት ሁሉ የነበሩ ጸሐፊዎች አንዳንድ ስሕተቶችን ሠርተዋል፥ ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ባሉት በርካታ ትርጉሞች ውስጥ ተርጓሚዎቹ አንዳንድ ጥቅሶችን በተለየ መንገድ ሊተረጉሙ እንደሚችሉ በመግለጥ የግርጌ ማስታወሻዎችን ጽፈዋል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ማር.16ን በአዲሱ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ተመልከት። ከ9-20 ስላሉት ቁጥሮች በገጹ በስተግርጌ ላይ ምን ተጽፏል?

ይህንን ሐቅ ለመረዳት ያስቸግራል። በአሁኑ ዘመን፣ የመጀመሪያዎቹ ጹሑፎች የትኞቹ እንደነበሩ ለመወሰን ዐብይ ሥራቸው አድርገው የያዙት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን አሉ። በሺህ የሚቆጠሩ የብሉይና የአዲስ ኪዳን ቅጂዎችን በመመልከት፣ የመጀመሪያው ቃል የቱ እንደነበር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመወሰን ይታገላሉ። የእነዚህ ምሁራን ሥራ ያላለቀ ስለሆነና እኛም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላሉ ጥቅሶች መቶ በመቶ እርግጠኞች መሆን ባንችልም፥ ሆኖም ግን ምሁራኑ የሚከተሉትን ነገሮች ይነግሩናል። 

 1. መጽሐፍ ቅዱስ ከማንኛውም ሌላ ጥንታዊ መጽሐፍ በተሻለ ሁኔታ ተጠብቋል፤ ምክንያቱም አይሁዶችና ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ያምኑ ስለነበር በትክክል ሊገለብጡት ይችሉ ዘንድ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገዋል፤ ስለዚህ ከቁርአንም ሆነ ከማንኛውም ሌላ ጥንታዊ መጽሐፍ በተሻለ ሁኔታ ትክክለኛነቱ የተጠበቀ ነው። ደግሞም በሚጽፉበት ጊዜ ጸሐፊዎቹን የመራቸው መንፈስ ቅዱስ በመሆኑ፥ ቅጂዎቹ ለዘመናት በሚጻፉበት ጊዜ ሁሉ ጉልህ ስሕተት እንዳይፈጽሙ ረድቶአቸዋል። 
 2. በተለያዩ ቅጂዎች መካከል ያሉት ልዩነቶች በአንድነት ሲታዩ፥ የአጠቃላዩ መጽሐፍ ቅዱስ ትንሽ ክፍል ናቸው። በሁሉም ቅዱሳት መጻሕፍት መካከል ስምምነት ስላለ፥ በእጃችን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ዘጠና ከመቶ በላይ (90%) ከመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ጋር አንድ ዓይነት እንደሆነ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። 
 3. በቅዱሳት መጻሕፍት ቅጂዎች መካከል ያለው ማንኛውም ልዩነት በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ትምህርት ላይ ለውጥ የሚያመጣ አይደለም። ስለ እግዚአብሔር፥ ስለ ክርስቶስ ወይም ስለ መንፈስ ቅዱስ ማንነት፥ ስለ ድነት (ደኅንነት) መንገድ፥ ወዘተ ባለን ግንዛቤ ላይ የሚያመጡት አንዳችም ለውጥ የለም፤ ልዩነቶቹ እምነታችንን የሚለውጡ አይደሉም (ለምሳሌ በዕዝ. 2፡3-70 እና በነህ. 7፡6-73 ያሉትን ዝርዝሮች አነጻጽር። በእነዚህ ሁለት ዝርዝሮች ውስጥ ያሉትን ልዩነቶች ጥቀስ)።

መ. መጽሐፍ ቅዱስ በነገሮች ሁሉ ላይ የመጨረሻው ባለሥልጣን ነው። እግዚአብሔር ማን እንደሆነ፥ ቀድሞ ምን እንዳደረገና ወደፊትም ምን እንደሚያደርግ፥ እንዲሁም ከፍጥረቱ የሚፈልገው ነገር ምን እንደሆነ በመናገር ረገድ የመጨረሻው ባለሥልጣን መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ሌሎች እምነቶችና ልምምዶች በሙሉ መመዘን ያለባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት የሚቃወም ማንኛውም ነገር ሊወገድ ይገባል። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እንደ እግዚአብሔር ቃል ስሕተት ቢሆንም፥ በሰዎች ዘንድ ግን እንደ መልካም የሚቆጠር አንድ ምሳሌ ከሕይወት ልምድህ ወይም ከምትኖርበት ባሕል ጥቀስ። ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ሐሰተኛ ትምህርትን ለማሸነፍ ወይም እግዚአብሔር ከሰዎች ሕይወት የሚጠብቀው ነገር ምን እንደሆነ ለማስረዳት መጽሐፍ ቅዱስን በተሻለ ሁኔታ በንቃት ልትጠቀምበት የምትችልባቸውን መንገዶች ጥቀስ።

ሠ. የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ፈቃዱ ልናውቀው የሚገባንን ሁሉ መንገር እንጂ እውነቶችን ሁሉ ማሳወቅ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ አሳብ የማይሰጥባችውና ዳሩ ግን ልናውቃቸው የምንፈልጋቸው በርካታ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር ዓለምን እንዴት እንደ ፈጠረ በግልጥ ለማወቅ እንጠይቅ ይሆናል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለዚህ በቂ ገለጣ አይሰጠንም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር በእምነት እንድንራመድ የሚያስችሉን ነገሮች በሙሉ ተጠቅሰዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ እምብርት እግዚአብሔር እንጂ ሰው አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ እግዚአብሔር ማን እንደሆነ፥ ምን እንደሠራና ከሰው ምን እንደሚፈልግ መግለጥ ነው፤ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ጊዜ ተቀዳሚው ትኩረታችን በእግዚአብሔር ላይ መሆን አለበት። እርሱንና ፈቃዱን በበለጠ ለመረዳት መጣር አለብን። እግዚአብሔርን እያወቅንና በትእዛዙ ብቻ ስንሄድ እንባረካለን። 

የውይይት ጥያቄ፡- ዳን. 11፡31-32 አንብብ። እግዚአብሔርን ለሚያውቁት የተሰጣቸው ተስፋ ምንድነው?

ረ. መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ቢሆንም እንደ እግዚአብሔር ሊመለክ ግን አይገባውም። እኛ የምናመልከው እራሱን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የገለጠውን እግዚአብሔርን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን አይደለም። ይህ ማለት መጽሐፍ ቅዱስ በራሱ ምትሐት ወይም ኃይል የለውም ማለት ነው። እንደ መድኃኒት ልንጠቀምበት አይገባም። ለምሳሌ፡- አንዳንድ ሰዎች አንድ ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያጽፉና በአንገታቸው ላይ ያደርጋሉ፤ ከአደጋ ግን አይጠብቃቸውም፥ ወይም ቁስል ላይ ቢደረግ ፈውስ አይሰጥም። የመፈወስና የመጠበቅ ኃይል ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በእጃችን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ በግዑዝ አካልነቱ የተለየ ኃይል እንዳለው የሚያምኑ ክርስቲያኖች አሉን? ለ) እንዴት አድርገው ይጠቀሙበታል? ሐ) ይህ ስሕተት የሆነው ለምንድን ነው? መ) የእግዚአብሔር ቃል ዓላማ ምንድን ነው?

ሰ. መጽሐፍ ቅዱስ አንዳች ስሕተት የሌለበትና የተሟላ የእግዚአብሔር ቃል ነው። የአዲስ ኪዳን መደምደሚያ የሆነው የዮሐንስ ራእይ፥ ለመጽሐፍ ቅዱስም የመጨረሻው መጽሐፍ ነው (ራእይ 22፡18-20 ተመልከት)። የምንጽፈው ወይም የምንናገረው ነገር እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት የሌለበት ነው ልንል አንችልም። ይህ ማለት፡-

 1. ማንም ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚጨመር ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ የሚያደርግ ሌላ መጽሐፍ ጽፌአለሁ ሊል አይችልም። ሌላ ወንጌል ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እኩል ሥልጣን ያለው መጽሐፍ አለኝ የሚል ሰው ተሳስቶአል።
 2. አንድ ሰባኪ በሚሰብክበት ጊዜ ወይም አንድ ጸሐፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ ወይም ለጥናት የሚያገለግል መጽሐፍ በሚጽፍበት ጊዜ፥ በተቻለው መጠን ትክክል የመሆን ሐላፊነት ያለበት ቢሆንም የሚናገረውና የሚጽፈው ነገር ስሕተት ሊኖርበት ይችላል። መጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን የጻፉ ሰዎች የነበራቸው ሥልጣንና ብቃት ሊኖረው የሚችል ሌላ ተናጋሪ ወይም ጸሐፊ ጨርሶ ሊኖር አይችልም። 

የውይይት ጥያቄ፡- ይህ እውነት ለሰባኪዎችና ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መጻሕፍት ጸሐፊዎች ምን ማስተማር አለበት?

በምንሰብክበትና በምንጽፍበት ጊዜ ሁሉ በአእምሮአችን ልናስታውሳቸው የሚገባን ሁለት ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው እየሰበክን ወይም እየጻፍን ያለነው የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ሁልጊዜ የማስታወስ አስፈላጊነት ነው፤ ስለዚህ ዓቅማችን የፈቀደውን ያህል ትክክለኛ ሥራ ለመሥራት መጣር አለብን። ይህ ማለት ከመስበካችን ወይም ከመጻፋችን በፊት በሚገባ ልናጠናውና በምንሰጠው ትርጉም ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል ማለት ነው። ሁለተኛው ሰባክያን፥ አስተማሪዎች እንዲሁም ጸሐፊዎች እንደመሆናችን መጠን ትሑታን መሆን አለብን። በምድር ላይ ሳለን እውቀታችን ከፊል መሆኑንና ሁልጊዜ ትክክለኛ ሊሆን እንደማይችል እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ማስታወስ አለብን (1ኛ ቆሮ. 13፡12 ተመልከት)። ስለዚህ ሰዎች አንድን ክፍል የተረዱበት ሁኔታና ለእርሱም የሰጡት ትርጉም ከእኛ የተለየ ሲሆን እውነትን ሁሉ በሚገባ አለማወቃችንን በትሕትና ልንቀበል፥ የሌሎችን ሰዎች አተረጓጎም ለማዳመጥና በእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ብርሃን ለመመርመር ፈቃደኞች መሆን አለብን። የመጽሐፍ ቅዱስን ግልጥ ትምህርት የሚቃወም ማንኛውም ነገር ስሕተት መሆኑ እርግጥ ነው፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ግልጥ የሆነ ትምህርት የማይሰጥባቸውን ርእሶች በሚመለከት ትሕትና ልናሳይና ለሌሎችም ሰዎች የተለየ አመለካከት እንዲኖራችው ልንፈቅድ ይገባል።

ብሉይና አዲስ ኪዳንን ጨምሮ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ የእግዚአብሔር ቃል ነው ብለን ካመንን፥ አንድ ሌላ ነገር ግልጥ ሆነ ማለት ነው። አዲስ ኪዳን በመጻፉ ስለ እግዚአብሔርና በሕይወታችን ውስጥ ስላለው ፈቃዱ ልናውቀው የሚገባን ነገር ሙሉ ሆኖአል ማለት ነው። ክርስቲያኖች ስለዚህ «አዲስ እውቀት» መፈለግ የለባቸውም። ይልቁንም እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በገለጠው መሠረት ከእርሱ ጋር ያለንን ኅብረት ለማጽናት፥ በቃሉ ውስጥ ፈቃዱ እንደሆነ በግልጥ ያሳየንን ነገር ልንታዘዝ ይገባል። ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ኅብረት እያደግን ስንሄድ አስደናቂ እውነቱን እንድንረዳ ማስተዋልንና ጥበብን አብዝቶ ይሰጠናል።

እነዚህ እውነቶች ስለ ብሉይ ኪዳን ምን ያስተምሩናል? ክርስቲያኖች እንደመሆናችን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሙሉ የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን መገንዘብ አለብን፤ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል በሙሉ ማጥናት የእኛ ኃላፊነት ነው። አምላካችን ማን እንደሆነና ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ማወቅ አለብን። ስለዚህ የምንወደውንና የምናውቀውን ክፍል ብቻ ሳይሆን ብሉይ ኪዳንን በሙሉ ማጥናት አለብን። ኦሪት ዘሌዋውያን የመዝሙረ ዳዊትን ያህል ወይም ትንቢተ ሕዝቅኤል የ1ኛ ሳሙኤልን ያህል የእግዚአብሔር ቃል ነው። እያንዳንዱ መጽሐፍ ስለ እግዚአብሒርና ስለ ፈቃዱ የተወሰነ ነገር ያስተምረናል፤ ስለዚህ ከምንወደው ክፍል ብቻ ሳይሆን፥ ከሁሉም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ልናጠናና ልናስተምር ያስፈልጋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ጊዜ የማናጠናቸውንና የማንሰብካቸውን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዘርዝር። ለ) የእግዚአብሔር ሰዎች ብዙውን ጊዜ እነዚህን መጻሕፍት የሚያልፉአቸው ለምንድነው? ሐ) ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ የተሟላ አሳብና ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረን ቃሉን በሙሉ በቤተ ክርስቲያናችን ልናጠና የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? መ) የእግዚአብሔርን ፈቃድ በከፊል ሳይሆን በሙሉ መረዳት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)