አማኝ ከሥራ፣ ከመከራ፣ ከበሽታና ከኃጢአት ጋር ያለው ግንኙነት (ያዕ. 4፡13-5፡20)

፩. አማኝ ከሥራ ጋር ያለው ግንኙነት (ያዕ. 4፡13-5፡6)

አንደበት የመንፈሳዊ ሕይወት አንደኛው ቴርሞ ሜትር እንደሆነ ተመልክተናል። በመቀጠልም ያዕቆብ ሌላኛውን የመንፈሳዊ ሕይወት ቴርሞ ሜትር ያብራራል። ይህም ገንዘባችንና ስለ ገንዘባችን እና የሥራ እንቅስቃሴአችን የምናስብበት ነው። ያዕቆብ ስለ ሕይወታችንና ሥራችን በምናቅድበት ጊዜ ልንጠነቀቅ የሚገባንን ሁለት ሁኔታዎችን ያመለክታል።

ሀ) ለወደፊት ዕቅድ የምናወጣው እንዴት ነው? ብዙውን ጊዜ ዕቅዶችን የምናወጣው ለእግዚአብሔር ሳንገዛና ፈቃዱም ምን እንደሆነ ሳንጠይቅ ነው። ያዕቆብ ይህን ችግር ይገልጻል። አንድ ሰው ለእግዚአብሔር ሳይገዛና በፈቃዱ ላይ ሳይደገፍ ስለ ወደፊት ሕይወቱ ዕቅዶችን ያወጣል። ይህንንም በማድረጉ እግዚአብሔር የወደፊቱን ሁኔታ እንደሚወስንና ሕይወትም አጭር መሆኗን ይዘነጋል። ይህ ምን ያህል ሞኝነት ነው! እግዚአብሔር ዕቅዶችን እንድናወጣ ይፈልጋል። ነገር ግን ዕቅድ ከማውጣታችን በፊት ለእግዚአብሔር ፈቃድ ለመገዛት ከጥቅማችን አስቀድመን እግዚአብሔርንና መንግሥቱን መሻት ይኖርብናል (ማቴ. 6፡33)።

ለ) በገንዘብ ላይ ከመጠን በላይ በማተኮር ፍትሕን መርሳት እንደሌለብን፡- ያዕቆብ በጠንካራ ቃላት ሀብታሞችን አስጠንቅቋቸዋል። ከእነዚህም አብዛኞቹ አማኞች አልነበሩም። እነዚህ ሰዎች ክፉዎች የሆኑት ሀብታሞች ስለሆኑ አልነበረም። ሀብታቸውን ለእግዚአብሔር መንግሥት የሚያውሉ እንደ አርማቲየሱ ዮሴፍ ያሉ መንፈሳዊ ሀብታሞች አሉ (ማቴ. 27፡57-59)። ያዕቆብን ያሳሰበው ገንዘብን አምላካቸው አድርገው የሚሰግዱለት ሀብታሞች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በሕይወታቸው ገንዘብን ከምንም በላይ ያስበልጡታል። ገንዘቡን ስለሚያገኙበት መንገድና በዚህ ሂደት ውስጥ በሌሎች ሰዎች ላይ ስለሚደርሰው አደጋ ቅንጣት ታክል ሳይጨነቁ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ይፍጨረጨራሉ። በፍጥነት ሀብት ለማካበት ሲሉ የሠራተኞቻቸውን ደመወዝ በአግባቡ አይከፍሉም። ድሆችን ለመርዳት ገንዘብ አይሰጡም። ይልቁንም የግል ጥቅማቸውን ለማበራከት ሲሉ ያገኙትን ሁሉ ይሰበስባሉ። እነዚህ ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ ሀብታቸው ከእነርሱ እንደሚወሰድ ዘንግተዋል። ያዕቆብ ይህን የጻፈው በዘመኑ ድሆችን ይበዘብዙ የነበሩትን ሃብታም ነጋዴዎች በማስመልከት መሆኑ አይጠረጠርም። አንድ ቀን ምናልባትም ያዕቆብ እንደ ነቢይ በስምንት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሮማውያን ኢየሩሳሌምን በማፈራረስ የሀብታም ነጋዴዎችንና ሃይማኖታዊ መሪዎችን ንብረት እንደሚዘርፉ ተረድቶ ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ህ) ብዙ አማኞች በእግዚአብሔር ላይ ሳይደገፉ ለወደፊት ዕቅዶች የሚወጥኑባቸውን መንገዶች ግላጽ። ለ) በገንዘብ ላይ የተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ድሆችን ለመርዳት ወይም ፍትሕን ለማስፈን እንደማያስችል የሕይወት ዘይቤ ሰዎችን ሲመራ የተመለከትክበትን ሁኔታ ግለጽ። አማኝ ከመከራ፥ ከበሽታና ከኃጢአት ጋር ያለው ግንኙነት (ያዕ. 5፡7-20)

፪. አማኝ በመከራ ጊዜያት የሚሰጠው ምላሽ (ያዕ. 5፡7-13)

ሀ) ትዕግሥት፡- በያዕቆብ መልእክት የመጨረሻው ክፍል ውስጥ ጸሐፊው ወደ መከራ ርእሰ ጉዳይ በመመለስ አማኝ ለመከራ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት እንዳለበት ያብራራል። ቀደም ሲል ያዕቆብ በመከራ ጊዜ አማኞች መደሰት እንዳለባቸው ገልጾአል (ያዕ. 1፡3)። አሁን ግን ስለ ትዕግሥት ይጽፋል። የትዕግሥት አመለካከት በሁለት መንገዶች ሊታይ ይችላል። ከእነዚህም መካከል እግዚአብሔርን የሚያስከብረው አንደኛው ብቻ ነው።

በመጀመሪያ፥ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች የሚጋሩት ያመጣብኝን ልቻለው ዓይነት ትዕግሥት አለ። የዚህ ዓይነቱ አመለካከት «እግዚአብሔር የሁሉም ተቆጣጣሪ ነው። እርሱ የፈለገውን ያደርጋል። እኔም ላደርግ የምችለው ያመጣውን መሸከም ብቻ ነው» የሚል ነው። የዚህ ዓይነቱ ትዕግሥት እግዚአብሔር ታላቅና ራቅ ብሎ የሚገኝ፥ ተግባራቱም ለእኛ ትርጉም የማይሰጡ መሆኑን ያመለክታል። ይህ አመለካከት ፍጡራን እንደመሆናችን መጠን እግዚአብሔር የሚያደርገውን ሁሉ መቀበልና እንደተጫነች አህያ ሸክምን ሁሉ መቋቋም እንዳለብን ያሳያል።

ሁለተኛ፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትዕግሥት፥ ፥«አፍቃሪ አባቴ ሁኔታዎችን ሁሉ ስለሚቆጣጠር ከሁሉም የሚሻለውን ነገር ያውቃል። ለልጆቹ ሁሉም ነገር ለበጎ እንደሚደረግ ቃል ገብቶልኛል (ሮሜ 8፡28)። ስለሚወደኝ ክርስቶስን እንድመስል እየለወጠኝ ነው። የሚያስፈልገኝን ሁሉ አይነፍገኝም» የሚል አቋም አለው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትዕግሥት እግዚአብሔር ነገሮችን በመቆጣጠር ላይ በመሆኑ እና ሁሉን በማወቁ ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ አመለካከት እግዚአብሔር አፍቃሪ አምላክ በመሆኑ፥ በረጅም ጊዜ ዕቅድ ለሕይወታችን በሚበጀው ነገር ላይ እንደሚያተኩር ያምናል። ያዕቆብ የሚናገረው ስለዚህ ዓይነቱ ትዕግሥት ነው። ገበሬዎች መሬታቸውን ካረሱና ዘር ከዘሩበት በኋላ ሰብላቸውን ከማጨዳቸው በፊት ለስድስት ወራት በተስፋ መጠባበቅ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ፥ «እኛም ጨለማ በነገሠባት የመከራ ጊዜ ውስጥ ሆነን እግዚአብሔር ወደፊት ታላቅ ነገር እንደሚያደርግልን በትዕግሥት እንጠባበቃለን። ብዙውን ጊዜ ይህ ሽልማት ወይም ለውጥ የሚመጣው በሚቀጥሉት ሳምንታት፥ ወራት ወይም ዓመታት ውስጥ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ግን እግዚአብሔር እስክንሞት ድረስ መከራ እንድንቀበል ሊያደርግ ይችላል። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜ ተስፋችን የሚያርፈው በመንግሥተ ሰማይ መከራ፥ ሥቃይ ወይም ሞት እንደማይኖር በመገንዘባችን ላይ ይሆናል (ራእይ 21፡3-4)። መከራን በትክክል ካስተናገድን እግዚአብሔር ይሸልመናል።

የውይይት ጥያቄ፡- አንተ ወይም አንተ የምታውቀው ሰው ያለፈበትን የመከራ ጊዜ ግለጽ። ሀ) ይህን የመከራ ጊዜ እግዚአብሔር ያመጣውን ልቻላው በሚል ስሜት ለመጋፈጥ የቻሉት እንዴት ነበር? ለ) ይህንን የመከራ ጊዜ በተስፋ እና መንፈሳዊ ትዕግሥት መጋፈጥ የቻሉትስ እንዴት ነበር?

በመከራ ጊዜ የመታገሥ ምሳሌ የሆነው ያዕቆብ ለአይሁዳውያን አማኞች በመከራ የታገሡትን የእምነት ጀግኖች ይጠቅስላቸዋል። የብሉይ ኪዳን ነቢያት መከራን በትዕግሥት በመጋፈጣቸው ቀዳማይ ጀግኖች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፥ ኢዮብ ካጋጠመው መከራ ሁሉ ባሻገር ከእግዚአብሔር ፊቱን ለመመለስ ባለመፍቀዱ የተከበረ የእግዚአብሔር ሰው ለመሆን በቅቷል። ከእነዚህ የእምነት ጀግኖች ሕይወት የሚመጣው ትምህርት የኋላ ኋላ እግዚአብሔር ርኅራኄንና ምሕረትን በማሳየት በትዕግሥት የሚጠባበቁትን ሰዎች እንደሚሸልም ነው።

ለ) አለማጉረምረም፡- መከራ በምንቀበልበት ጊዜ ብዙዎቻችን እናጉረመርማለን። አንዳንድ ጊዜ መከራ መቀበላችን ፍትሐዊ እንዳልሆነ በመግለጽ በእግዚአብሔር ላይ እናማርራለን። ብዙ ሰዎች የከረረ ፈተና በሚገጥማቸው ጊዜ እምነታቸውን ይተዋሉ። ነገር ግን በአብዛኛው ቁጣችንን በሌሎች ሰዎች ላይ እንገልጻለን። በትዳር ጓደኞቻችን፥ በልጆቻችን፥ ወዘተ… ላይ እናማርራለን። አንዳንድ ሰዎች መራርነት ያጠቃቸዋል። ያዕቆብ ፈራጁ ክርስቶስ በቅርቡ የሚመጣ መሆኑን በመግለጽ፥ በመከራ ጊዜ ለነበረን ባሕሪ ፍርድን እንደሚሰጠን ያስታውሰናል።

ሐ) የቃላችንን እውነተኛነት ለመግለጽ መማል አያስፈልገንም፡- ምንም እንኳን ይህ ከመከራ ጋር ባይገናኝም፥ ያዕቆብ ከእምነትና መሐላ ጋር በተያያዘ አንደበታችንን ስለምንጠቀምበት ሁኔት ያብራራል። ያዕቆብ ይህንን ትእዛዝ ያገኘው ከክርስቶስ መሆኑ አይጠረጠርም (ማቴ. 5፡33-37)። ኢየሱስም ሆነ ያዕቆብ በሰዎች ሕይወት ውስጥ የእውነትን አለመኖር የሚያመለክት አሳብ ነበር ያስተላለፉት። ያዕቆብ ለሰዎች እውነት መናገራችንን ለማረጋገጥ ምንም ዓይነት መሐላ መጠቀም እንደሌለብን ይናገራል። መሐላ የሚያስፈልገው ሰው ንግግራችንን በሚጠራጠርበት ጊዜ ነው። እውነተኛ ሰዎች ከሆንን፥ የምንናገረው ሁሉ እውነት ይሆናል። ስለሆነም አንድ ሰው በሚጠይቀን ጊዜ «አዎ» ብለን እንመልሳለን። ከዚያም ሁኔታዎች፥ ምንም ያህል ባይመቻቹም እንኳን ቃላችንን እንጠብቃለን። አልያም «አይሆንም» ብለን እንመልሳለን። ከዚያም ሰዎች ምንም ያህል ጫና ቢያሳድሩብንም እንኳ በቃላችን እንጸናለን።

መ) ጸሎት፡- በመከራ ጊዜ መታገሥ ማለት አለመጸለይ ማለት አይደለም። ያዕቆብ በመከራ ጊዜ ተግተን መጸለይ እንዳለብን ይነግረናል። ይህ ጸሎት በቀዳሚነት እግዚአብሔር የመከራውን ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ ለማከናወን የሚፈልገውን ተግባር ለማከናወን፥ ባህሪያችንን ለመለወጥና እኛን ለበለጠ አገልግሎት ለማዘጋጀት እንዲጠቀምበት የምንጠይቅበት ነው። ፈቃዱ ከሆነ መከራን ከሕይወታችን እንዲያርቀው እንጸልያለን።

ሠ) ማመስገን፡- ጳውሎስ ሁልጊዜም ደስ መሰኘት እንዳለብን ነግሮናል (ፊልጵ. 3፡1)። ለአማኞች (በተለይም በመከራ ውስጥ ላሉ) እግዚአብሔር ቀደም ሲል በሕይወታቸው ውስጥ የፈጸማቸውና አሁንም በመፈጸም ላይ ያለውን መልካም ነገር ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። በመከራው ላይ ከማተኮር ይልቅ በረከቶቻችንን መቁጠር ይኖርብናል። ይህንኑ ምሥጋና ለመግለጽ ከሁሉም የሚሻለው መንገድ የምሥጋና መዝሙሮችን መዘመር ነው።

፫. አማኝ በበሽታ ጊዜ የሚሰጠው ምላሽ (ያዕ. 5፡14-18)

በአንድም ሆነ በሌላ ጊዜ፥ አማኞች ሁሉ የሚጋፈጡት አንደኛው የመከራ ዓይነት ሕመም ነው። ለዚህ ዓይነቱ መከራ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት ይኖርብናል? ዝነኛ የፈውስ አገልጋዮችን መሻት ያስፈልገናል? በሐኪሞች ብቻ መታመን አለብን? ምንም እንኳ እግዚአብሔር በሐኪሞች ወይም በፈውስ አገልጋዮች አማካኝነት ፈውሱን ሊያመጣ ቢችልም፥ በምንታመምበት ጊዜ የራሳችን ጸሎትና የሐኪም እርዳታ ሳይፈውሱን ሲቀር ልናደርግ የሚገባን ትክክለኛው ነገር ወደ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች መሄድ ነው። እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለመንጋው እንክብካቤ የሚያደርጉላቸውን ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። ስለሆነም፥ ግለሰቡ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች መጥተው እንዲጸልዩለት ሊጠራቸው ይገባል። በዚህ ጊዜ ሽማግሌዎች ምን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል? ሦስት ነገሮችን ማድረግ የሚያስፈልጋቸው ይመስላል።

ሀ) ሽማግሌዎቹ ታማሚው ኃጢአት ሠርቶ እንደሆነ ሕይወቱን እንዲመረምር መርዳት ይኖርባቸዋል። ምናልባትም በሽታው እግዚአብሔር ግለሰቡን ለመቅጣት የተጠቀመበት መንገድ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሁሉም በሽታ የኃጢአት ውጤት አይደለም። ስለሆነም ሽማግሌዎች በሽታው የደረሰበት ኃጢአት በመሥራቱ ነው ከሚል ድምዳሜ መድረስ የለባቸውም። ነገር ግን ኃጢአት በሽታን ከሚያስከትሉ መንሥዔዎች አንዱ ስለሆነ ሽማግሌዎቹ አማኙ ሕይወቱን እንዲገመግም ማገዝ ይኖርባቸዋል። በአማኙ ሕይወት ውስጥ ንስሐ ያልተገባበት ኃጢአት ካለና እግዚአብሔርም ለዚያው ኃጢአት እየቀጣው ከሆነ፥ መጸለዩ ፋይዳ የለውም። ለፈውስ ከመጸለይ አስቀድሞ ኃጢአትን መናዘዝ አስፈላጊ ነው። መልካሙ ዜና ግለሰቡ ኃጢአቱን ከተናዘዘና አኗኗሩን ለመቀየር ቃል ከገባ እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ይቅር ይለዋል። ይህም አንደኛውን የፈውስ መሰናክል ያስወግደዋል።

ለ) ቀጣዩ ደረጃ ታማሚውን በዘይት መቀባት ነው። ክርስቲያኖች ስለዚህ ጉዳይ የተለያዩ ግንዛቤዎች አሏቸው። በጥንቱ ዓለም ውስጥ ዘይት ከዐበይት መድኃኒቶች እንደ አንዱ ይቆጠር ስለነበር (ሉቃስ 10፡33-34 አንብብ)። አንዳንድ ክርስቲያኖች ይህ የሚያመለክተው ሽማግሌዎች ታማሚውን አማኝ ወደ ሐኪም ቤት መውሰድና ሕክምና እንዲያገኝ መርዳት እንደሚገባቸው ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ዘይት የመንፈስ ቅዱስ ምልክት ስለሆነ፥ ይህ የሚያሳየው መንፈስ ቅዱስ ግለሰቡን እንዲፈውስ ለመጠየቅ ነው ይላሉ። ምናልባትም ያዕቆብ ለማለት የፈለገው እነዚህ ሁለቱንም ሊሆን ይችላል። የታመመ ሰው መድኃኒት እንዲወስድ ማድረግና ዳሩ ግን ፈውስ የሚመጣው ከእግዚአብሔር መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ግለሰቡን የሚፈውሰው ዘይቱ እንዳልሆነ መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። የሚፈውሰው የእምነት ጸሎት መሆኑን ያዕቆብ ገልጿል። ዛሬ ዘይት መጠቀም ያስፈልገናል? ምናልባት አያስፈልገንም። ይህ መንፈስ ቅዱስን የሚያመለክት ነው ብለን ካመንን ዘይት መጠቀም ያስፈልገናል? አዎ። ነገር ግን በዘይቱ ውስጥ አንድ ምትሃታዊ ኃይል እንዳለ ወይም ዘይቱን የሆነ ፈዋሽ መባረክ እንዳለበት ወይም ደግሞ የዘይቱ ዓይነት የተለየ መሆን እንዳለበት ማሰብ የለብንም። ይህ ያዕቆብ የፈውስን በር ይከፍታል ብሎ ከሚናገረው ጸሎት የተለየ ነው።

ሐ) ሽማግሌዎች በእምነት መጸለይ ይኖርባቸዋል። በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ እንደ ፈቃዱ ምላሽ ይሰጣል። ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ፈውስ ለማምጣት ይህን ጸሎት እንደሚጠቀም ይናገራል። እግዚአብሔር የሚጠቀመው መድኃኒቱን ወይም ዘይቱን ሳይሆን ጸሎቱን ነው።

ይህ ማለት እግዚአብሔር እነዚህን ሦስት ደረጃዎች ከተከተልን ሁልጊዜም በሽተኞችን ለመፈወስ ይገደዳል ማለት ነው? አይደለም። አንዳንድ ሰዎች ከተጸለየላቸውና ዘይት ከተቀቡ በኋላ እንኳን ላይፈወሱ ወይም ሊሞቱ ይችላሉ። ይህንን ትምህርት በሌሎች የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ውስጥ ከቀረቡት ትምህርቶች ጋር ሚዛናዊ ማድረግ ይኖርብናል። በሌሎች ክፍሎች እንደተገለጸው፥ ምንም እንኳን በእግዚአብሔር ላይ እምነት ሊኖረን ቢገባም፥ ሁልጊዜም የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲፈጸም መጠየቅ ይኖርብናል። አንዳንድ ጊዜ ፈውሱ የሚመጣው በሞት በኩል ይሆናል፥ ምክንያቱም በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ባለበት መንግሥተ ሰማይ ከምንም ዓይነት በሽታ ተለይቶ ይኖራል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እግዚአብሔር አንድን ግለሰብ እንደሚፈውስ ለአንዳንዶች ይናገራል። ይህ ማረጋገጫ የተሰጠው ሰው በሽተኛው እንደሚፈወስ በመተማመን ሊጸልይ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ምን ለማድረግ እንደሚፈልግ አናውቅም። እግዚአብሔር ፈውስን ያመጣል በሚል እምነት ብንጸልይም፥ የእግዚአብሔር መንገዶች ከእኛ የተሻሉና የተለዩም ሊሆኑ እንደሚችሉ መገንዘብ ይኖርብናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ ሰው በሚታመምበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚደረገው የተለመደ አሠራር ምንድን ነው? ሽማግሌዎች ተጠርተው ይጸልያሉ? ሽማግሌዎች ተጠርተው ሲመጡ ምን ያደርጋሉ? የታመመው ግለሰብ ወደ ፈውስ አገልጋዮች ይሄዳል? ሐኪም ቤት ይሄዳል? ለ) ያዕቆብ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተገቢው የፈውስ ንድፍ ምን መሆን አለበት ይላል? ሐ) በዚህ እግዚአብሔር ስለሚፈውስበት መንገድ በተገለጸው ትምህርትና በ1ኛ ቆሮ. 12 ውስጥ በተገለጸው የፈውስ ስጦታ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? መ) ብዙ ሽማግሌዎች በዚህ ዓይነቱ የፈውስ አገልግሎት ውስጥ የማይሳተፉት ለምንድን ነው? ሠ) እግዚአብሔር ሁልጊዜም የሚፈውስ ይመስልሃል? እግዚአብሔር አንድን ሰው ባይፈውስ መልሱ ምንድን ነው ማለት ነው?

መ) እግዚአብሔር በልጆቹ ሕይወት ውስጥ ፈውስን ሊገልጥ ከሚፈልግበት ዐቢይ መንገድ አማኞች ኃጢአታቸውን ተናዝዘው አንዱ ለሌላው እንዲጸልይ በማድረግ ነው? ያዕቆብ በክርስቶስ አካል ውስጥ ስሜታዊ፥ መንፈሳዊና አካላዊ ጤንነት የሚኖረን ሰዎች ኃጢአታቸውን ተናዝዘው ንጹሕ ግንኙነት በሚመሠርቱበት ጊዜ መሆኑን ይናገራል። ይህ ምናልባትም እያንዳንዱን ኃጢአት በቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ፊት መናዘዝ አለብን ማለት ላይሆን ይችላል። ነገር ግን በአንድ ሰው ላይ ኃጢአት በምንፈጽምበት ጊዜ ለዚያ ሰው ኃጢአታችንን መናዘዝ ይኖርብናል። ይሁንና ኃጢአታችን በቤተ ክርስቲያን አባላት ሁሉ ላይ ተጽዕኖ ካስከተለ፥ በምእመናኑ ሁሉ ፊት ኃጢአታችንን መናዘዝ ይኖርብናል። ይህም አካላዊ ሕመማችን ብቻ ሳይሆን ግንኙነታችን በሙሉ እንዲፈወስ ያደርጋል። በክርስቶስ አካል ውስጥ አንድ ሰው በሚታመምበት ጊዜ የአካሉ ክፍሎች በሙሉ በጸሎት መሳተፍ ይኖርባቸዋል። እግዚአብሔር ቅዱስና ጻድቅ የሆነውን የልጆቹን ጸሎት ያከብራል። ይህም በኤልያስ ጸሎት ውስጥ ተመልክቷል።

፬. አማኝ በኃጢአት የሚወድቁትን ሰዎች ምን ሊያደርግ ይገባል (ያዕ. 5፡19-20)

አዲስ ኪዳን አማኞች እጅግ የተቀራረበ ኅብረት እንደሚኖራቸውና በንጽሕና በመቆየት እርስ በርሳቸው እንደሚረዳዱ ይጠብቃል። ነገር ግን ተፈጥሮአዊ ዝንባሌአችን ከጋራ ተጠያቂነት ራሳችንን ማራቅ ነው። ኃጢአታችንን ማንም ሰው እንዲያውቀው አንፈልግም። ኃጢአት እየሠራን እያለን አንድ ሰው ስለዚያ ጉዳይ ቢያነሣ እንቆጣለን። ሌላ ሰው ኃጢአት እየሠራ ንስሐ ለመግባት አለመፈለጉን ብናውቅ፥ እናማለን ወይም ትከሻችንን ሰብቀን አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደገባ እንናገራለን። ያዕቆብ በክርስቶስ አካል ውስጥ አንዱ ለሌላው ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል ይላል። ፍቅር ማለት ኃጢአትን መደበቅ ወይም ችላ ማለት አይደለም። ፍቅር ማለት ለምንወደው ሰው ከሁሉም የተሻለውን ነገር እንመኝለታለን ማለት ነው። ይህም ከሁሉም የሚሻለው ነገር ግለሰቡ ከኃጢአቱ ጋር መጋፈጥ፥ መናዘዝና ንስሐ መግባት የሚያስፈልገው መሆኑ ነው። ይህም ከእግዚአብሔር ቅጣት እንዲያመልጡ ይረዳቸዋል። ይህም ቅጣት ሞት ሊሆን ይችላል። ኃጢአቱ ምንም ዓይነት ታላቅ ቢሆንም እግዚአብሔር ይቅር ይላል። ብዙዎቻችን ለአማኞች የዚህ ዓይነት ፍቅር በማሳየት በቅድስና እንዲመላለሱ ብናግዝ፥ አብያተ ክርስቲያኖቻችን ተለውጠው የፍቅርና የንጽሕና ሠገነቶች ይሆኑ ነበር። ይህ ለእግዚአብሔር ምን ያህል ታላቅ ክብር እንደሚያመጣ አስብ!

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድን አማኝ ስለፈጸመው ኃጢአት ተጋፍጠኸው ታውቃለህ? ካልሆነ፥ ለምን? ከሆነ፥ የተከሰተውን ሁኔታ ግለጽ። ለ) ብዙዎቻችን ሰዎችን ስለ ኃጢአታቸው ከመጋፈጥ ይልቅ በኃጢአታቸው እንዲቀጥሉ የምናደርገው እንዴት ነው? ሐ) አንዳችን የሌላውን ኃጢአት ብንጋፈጥና ኃጢአት በምንፈጽምበት ጊዜ ወይም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በማንመላለስበት ወቅት ሌሎች ጉድለታችንን እንዲነግሩን ብንጠይቅ፥ አብያተ ክርስቲያኖቻችን እንዴት ይለወጣሉ? መ) በያዕቆብ መጽሐፍ ውስጥ እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ስለመኖር የተረዳሃቸው ሌሎች ጠቃሚ ትምህርቶች ምን ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

አማኝ አንደበቱን ይገዛል፤ ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚያደርገው ግንኙነት እውነተኛ ጥበብን ያሳያል (ያዕ. 3፡1-4፡12)

፩. አማኝ አንደበቱን ይገዛል (ያዕ. 3፡1-12)

በሽተኛ ሰው ወደ ሐኪም በሚሄድበት ጊዜ በቀዳሚነት ከሚከናወኑት ተግባራት መካከል በግለሰቡ አፍ ውስጥ የሙቀት መለኪያ ቴርሞ ሜትር መደረጉ አንደኛው ነው። ይህም ሐኪሙ በሽታው ትኩሳት እያስከተለበት መሆኑን አለመሆኑን እንዲወስን ይረዳዋል። መንፈሳዊ ጤንነታችንን ለመለካትም የሚያገለግል ቴርሞ ሜትር አለ። ያም ቴርሞ ሜትር ምላሳችን ወይም የምንናገራቸው ቃላት ናቸው። መርከብን እንደሚነዳ መቅዘፊያ እና ጫካ እንደሚያቃጥል አነስተኛ የእሳት ፍንጣሪ ጥቂት የተሳሳቱ ቃላት ጥፋት በማስከተል የሕይወታችን፥ የቤተ ክርስቲያናችንና የአገራችን ሕልውና ሊያወድሙ ይችላሉ። ክርስቲያኖች ብንሆንም፥ በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚዋጋው ክፉ ባህሪያችን ብዙውን ጊዜ የሚገለጸው በአንደበታችን ነው። በመሆኑም፥ በቃላችን በሰዎች ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት እናስከትላለን። ነገር ግን አንደበት እግዚአብሔርን ለማስከበር የሚያስችል መሣሪያ ሆኖ ሊያገለግልም ይችላል። የክርስቶስን ቤተሰብ ጭምር በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሰዎች መጉዳትን ከዚያም ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር መዘመር በክርስቶስ እናምናለን ብለን ከምንናገረው እሳብ የሚቃረን ነው። አዲስ ፍጥረት እንደ መሆናችን፥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አንደበታችንን ለመግዛት መማር ይኖርብናል። ከአፋችን የሚወጣው እግዚአብሔርን የሚያስከብርና ሌሎችን የሚያበረታታ ሊሆን ይገባል።

ያዕቆብ በማስተማር አገልግሎት ውስጥ አንደበታቸውን ለሚጠቀሙ ሰዎች ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። አስተማሪና ሰባኪ ሁለቱም ትልቅ አገልግሎት አላቸው። እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚገነቡት ወይም የሚያፈርሱት በቃላቸው ነው። ቃላቸው በሚገባ ያላጠኑትን የተሳሳተ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሊገልጽ ይችላል። ሐሰተኛ ትምህርቶች ወይም ሚዛናዊነት የሚጎድላቸው አሳቦች የሚተላለፉት በቃላቸው ነው። መድረክ ላይ ቆሞ የተሳሳተ መልእክት ከማስተላለፍ ይልቅ ብቃት የሌለው ወይም መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ያላጠና ሰው ባያስተምርና ባይሰብክ ይሻላል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንደበት በቤተሰብ፥ በቤተ ክርስቲያንና በአገር ውስጥ የተለያዩ ነገሮችን ሊያጠፋ ስለሚችልበት ሁኔታ ግለጽ። ለ) አንደበት ሰዎችን ለመገንባትና ለማበረታታት መሣሪያ ሊሆን የሚችልበትን ሁኔታ ግለጽ። ሐ) ባለፈው ሳምንት ውስጥ እንደበትህን እንዴት እንደተጠቀምክ አስብ። ሰዎችን ለመገንባት የተጠቀምከው እንዴት ነው? አንደበትህን ጎጂ በሆነ መልኩ እንዴት ነው የተጠቀምከው? አንደበትህን በተሳሳተ መንገድ ስለተጠቀምከበት ሁኔታ እግዚአብሔር ይቅርታ እንዲያደርግልህና በበለጠ ትቆጣጠረው ዘንድ ኃይልን እንዲሰጥህ ጸልይ። መ) ሰባኪ ወይም አስተማሪ አንደበቱን በተሳሳተ መንገድ ሲጠቀም ያየኸው እንዴት ነው? ከዚህ ሁኔታ ውስጥ የመነጩ አሉታዊ ነገሮች ምን ምን ናቸው?

፪. አማኝ ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚያደርገው ግንኙነት እውነተኛ ጥበብን ያሳያል (ያዕ. 3፡13-4፡12)

ብዙውን ጊዜ «ጥበብ» የሚለውን ቃል ስንሰማ ስለ አንድ ርእሰ ጉዳይ ብዙ እውቀት ያለው ሰው ትዝ ይለናል። ለምሳሌ ያህል፥ ብዙ የፊዚክስ እውቀት ያለው መምህር አዋቂ ነው ይባላል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ጥበብን የሚገልጸው ለየት ባለ መንገድ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥበብ እግዚአብሔርን የሚያስከብር ሕይወት መምራትን ያመለክታል። ለዚህም ነው በብሉይ ኪዳን ውስጥ፥ «የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው» የሚል ሐሳብ በተደጋጋሚ ተገልጾ የምናገኘው (ምሳሌ 9፡10 አንብብ)። «ፍርሃት» የሚለው ቃል አንበሳ ስናይ የሚሰማን ወይም በአንድ ታላቅ ገዢ ፊት ስንቆም የሚወረንን ስሜታዊ ነጸብራቅ የሚያመለክት አይደለም። ነገር ግን ክብርና ታላቅነት ለሚገባው አካል ያለንን አክብሮት ማሳየታችንን የሚያሳይ ነው። ጥበብ ማለት እግዚአብሔርን የሚያስከብር ሕይወት መኖር ማለት ነው። ስለዚህ እንደ አማኞች ጥበብን የምናሳየው እንዴት ነው? ያዕቆብ ከሰዎች ጋር ግንኙነት በምናደርግበት ጊዜ የተባረኩትን ሁለት ዓይነት የአኗኗር ዘይቤዎችን ይገልጻል። እነዚህም ሰማያዊና ምድራዊ ጥበብ ናቸው።

ሀ) ምድራዊ ጥበብ፡- ምድራዊ ጥበብ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ሌሎች እኛ የሌለንን በረከት በሚያገኙበት ጊዜ የሚቀናና የራሱን መንገድ የሚፈልግ ነው። ያዕቆብ ሁሉም ክፉ ተግባራት የሚመጡት ከቅንአትና ከራስ ወዳድነት መሆኑን ይናገራል። አንደበታችንን ለማውደም የምንጠቀመው በአንድ ሰው ላይ በመቅናታችን ወይም ለራሳችን አንድ ነገር በመፈለጋችን ነው። ትዕቢታችን እኛ ከሌሎች እንደምንበልጥ ስለሚያሳየን ስለ እርሱ አሉታዊ ነገሮችን እንናገራለን። ብንሰርቅ፥ ይህንን የምናደርገው እግዚአብሔርን በማያስከብር መልኩ ለራሳችን አንድ ነገር ለማድረግ በመፈለጋችን ነው።

ለ) ሰማያዊ ጥበብ፡- ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ሰማያዊ ጥበብ ንጹሕና ምንም ዓይነት ድብቅ ዓላማ የሌለው ነው። የእግዚአብሔር የሆነው ጥበብ ሰላምን የሚሻ ፥ የሌሎችን ፍላጎቶች የሚያገናዝብ ነው። ሰማያዊ ጥበብ ለሥልጣን ወይም ለተላለፈው ውሳኔ ይገዛል። ሰማያዊ ጥበብ መሐሪ በመሆኑ፥ ሌሎች የማይገባቸው ሆነው ሳለ እንኳ ፍላጎታቸው እንዲሟላ ያደርጋል። ሰማያዊ ጥበብ አድልዎ የሌለበት በመሆኑ፥ በሥጋዊ ዓይኖች ራሳችንን፥ ቤተሰቦቻችንን ወይም የጎሳ አባሎቻችንን እንድንጠቀም አያደርገንም። ሰማያዊ ጥበብ ሰዎችን ለማስደሰት በቃላት የሚያባብል ሳይሆን፥ እውነተኛ ነው። ሰላም፥ ጽድቅና እግዚአብሔርን የሚያስከብሩ ተግባራት የሚመነጩት ከዚህ ዓይነቱ ጥበብ ነው።

ያዕቆብ ምድራዊ ጥበብ እንዴት ራሱን እንደሚገልጽ ያስረዳል። ያዕቆብ በአማኞች መካከል ጸብ የሚከሰተው በቅንአትና ራስ ወዳድነት መሆኑን ይናገራል። የቀናህበት ነገር በጣም አስፈላጊ ከሆነ፥ ወደ እግዚአብሔር ጸልየህ ልትቀበል ይገባል። ነገር ግን ዘዴና ጉልበት በመጠቀም፥ እግዚአብሔርን ከጠየቅህ ደግሞ ከራስ ወዳድነት በመነሳት ልታገኘው ትሞክራለህ። ስለሆነም እግዚአብሔር ይህን ነገር አይሰጥህም። ለምንፈልጋቸው ነገሮች ዘዴና ጉልበት በምንጠቀምበት ጊዜ፥ አመንዝራዎች መሆናችንን እናሳያለን። አመንዝራ የሆነ ሰው ከጋብቻ ግንኙነት ውጭ ወሲብ የሚፈጽም ግለሰብ ነው። መንፈሳዊ አመንዝራ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ግንኙነት ከእግዚአብሔር በተቀበላቸው በረከቶች ካለመርካቱ የተነሣ ከእግዚአብሔር በላይ አንድን ነገር ወይም አንድን ሰው የሚወድ ማለት ነው። ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር ጠቃሚ ናቸው የሚለውን ነገሮች ትተን ዓለም ጠቃሚዎች ናቸው የምትለውን እናሳድዳለን። (ለምሳሌ፥ አዳዲስ ልብሶች፥ የቤተ ክርስቲያን አመራርና የክብር ስፍራ፥ የግል ምቾቶችና ፍላጎቶች።) ያዕቆብ እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዳንይዝ ያስጠነቅቀናል። ምክንያቱም የዓለምን ነገሮች ከወደድን ቀናተኛው አምላካችን ይቀጣናል።

ለመሆኑ አማኞች ሰማያዊ ጥበብን ለመግለጽ ምን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል?

ሀ) የራሳችንን መንገድ ከመፈለግ ይልቅ ትሕትናን ማሳየት አለብን።

ለ) አማኞች በሕይወታችን ለእግዚአብሔር ፈቃድና መንገድ መገዛት አለብን።

ሐ) ከእግዚአብሔር ያልመጣውንና የዓለምን ነገሮች ለማግኘት እንድንጋደል የሚያበረታታንን የጠላት ውሸት ከመቀበል መቆጠብ ይኖርብናል።

መ) ሕይወታችንን በመመርመር ስለ ቅንአታችንና ራስ ወዳድነታችን ንስሐ መግባት አለብን።

ሠ) አማኞች እርስ በርሳቸው አንደበታቸውን ለአጥፊ ተግባር ማዋል የለባቸውም።

ረ) በሰው ልብ ውስጥ ያለውን አሳብ ለመመልከት በትክክል ከሚፈርድ ከብቸኛው ዳኛ ፊት እንደምንቀርብ ማስታወስ አለብን። የሰውን ልብ አይቶ በትክክል ሊፈርድ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። እኛ ይህንን ማድረግ ስለማንችል፥ የሰዎችን ዓላማ እንደምናውቅ እየተናገርን መተማማት የለብንም።

የውይይት ጥያቄ፡- እንበልና ለቤተ ክርስቲያን ጊታር ለመግዛት ገንዘብ ይውጣ ወይም አይውጣ በሚለው አሳብ ላይ ከአንድ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ጋር በአሳብ ተለያይተሃል። ሀ) ዓለማዊ ጥበብ ያለው ሰው ለዚህ አለመስማማት ምላሽ ሊሰጥ የሚችለው እንዴት ነው? ለ) ሰማያዊ ጥበብ ያለው ሰውስ? ሐ) ከላይ የቀረቡት መርሆች በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተገቢውን ምላሽ እንድትሰጥ እንዴት ይረዱሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

አማኝ እምነቱን ተግባራዊ የሚያደርግባቸው መንገዶች (ያዕ. 1፡19-2፡26)

በዚህ ክፍል ውስጥ ያዕቆብ ብዙዎቻችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት በሚያንጸባርቅ መልኩ ለመኖር የተቸገርንባቸውን ጉዳዮች ይዘረዝራል።

፩. እውነተኛ አማኞች ቁጣቸውንና አንደበታቸውን ይቆጣጠራሉ (ያዕ. 1፡19-20)

በአማኞች መካከል የተከሰቱትን አብዛኞቹን ክፍፍሎች ብንመለከት፥ በአብዛኛው የችግሩ መንሥኤ አንደበታችንን አለአግባብ መጠቀማችን መሆኑን እንገነዘባለን። ይህም እንደ እሳት እየተቀጣጠለ ክፍፍሉ እንዲፈጠርና እያደገ እንዲሄድ ያደርጋል። ከያዕቆብ ዐበይት ትምህርቶች አንዱ አንደበታችንን የሚመለከት ነው። ብዙውን ጊዜ ስንቆጣ የተሳሳቱ ነገሮችን እንናገራለን። ወደ ውስጥ አጥልቀን ብንቆፍር በአመዛኙ ቁጣችንን የሚቆሰቁሰው ራስ ወዳድነታችንና ትዕቢታችን ነው። ያዕቆብ ንዴታችንንና አንደበታችንን ለመቆጣጠር እንድንማር ይነግረናል። ብዙውን ጊዜ በጥንቃቄ ሳናስብ የምንናገራቸው ነገሮች ለችግር ስለሚያጋልጡን ትንሽ የመናገርና ብዙ የማድመጥ ክህሎት ልናዳብር ይገባል።

፪. እውነተኛ አማኞች የቃሉን እውነት ተግባራዊ ለማድረግ አኗኗራቸውን ይለውጣሉ (ያዕ. 1፡21-27)

ያዕቆብ እንዴት ልንኖር እንደሚገባ በዝርዝር ማብራሪያዎችን ከሰጠ በኋላ ከትምህርቶቹ ሁሉ በስተጀርባ መሠረታዊ መርሆ ይጠቅሳል። እውነተኛ አማኞች ከሆንን፥ መጽሐፍ ቅዱስን እንደምንወድና ልንታዘዘው እንደምንፈልግ የምንናገር ከሆነ፥ በሕይወታችን ክፍሎች ሁሉ ሕይወታችንን ተግባራዊ ለማድረግ መቁረጥ ይኖርብናል። ዋናው መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቡ አይደለም፥ ያነበብነውን መታዘዙ እንጂ፤ ስብከት መስማቱ አስፈላጊ ቢሆንም ዋናው ግን የተሰጠውን ትምህርት ተግባራዊ ማድረጉ ነው። ለብዙዎቻችን ችግሩ የእውቀት ማነስ አይደለም፥ ነገር ግን በምናውቀው መሠረት አንኖርም። መስታወት አይተው እንደሚዘነጉት ሰዎች ነን። መስታወቱን አይተን ጸጉራችንን በማበጠር እንዳላስተካከሉት ሰዎች ነን።

ያዕቆብ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የምንመለከተውን ነገር ከሕይወታችን ጋር የማናዛምድባቸውን ነገሮች በምሳሌነት ይዘረዝራል። ሃይማኖተኞች ነን ብንልም፥ አንደበታችንን አንገዛም። የክርስቶስ ተከታዮች ነን ብንልም፥ ለመበለቶችና ለእጓለማውታዎች በመከራ ውስጥ ላሉትም ሰዎች ፍቅርንና ርኅራኄን አናሳይም። የተቀደሰ ሕይወትም አንኖርም። (ማስታወሻ፡ መጽሐፍ ቅዱስን፥ በተለይም የብሉይ ኪዳንን የትንቢት መጻሕፍት በጥንቃቄ ብናነብ እግዚአብሔር ለድሆች፥ ለእጓለማውታዎችና ለመበለቶች ልዩ ርኅራኄ እንዳለው እንረዳለን። ልጆቹ እንደዚህ ያሉትን ድሆች ለመርዳት ግዴለሾች በሚሆኑበት ጊዜ በጣም ይቆጣል። ነገር ግን በዘመናችን፥ ራስ ወዳዶች በመሆናችን እግዚአብሔር የሰጠንን የእኛን ያህል ላልታደሉት ከማካፈል ይልቅ የበለጠ ቁሳዊ ሀብት ለማሰባሰብ እንፈልጋለን።)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ያዕቆብ እግዚአብሔር የሚቀበለው እውነተኛ ሃይማኖት ምን ዓይነት ነው ይላል? ለ) ያዕቆብ የእውነተኛ አምልኮ እምብርቶች ናቸው ብሎ የሚዘረዝራቸውን ነገሮች እምብዛም የማንጠቅሰው ለምንድን ነው? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ እውነተኛ ሃይማኖትን የምታሳየው እንዴት ነው? መ) እውነተኛውን ሃይማኖት የምታሳይባቸው ተግባራዊ መንገዶች ምን ምን ናቸው?

፫. እውነተኛ አማኞች በሃብታምና በድሃ እማኞች መካከል መድልዎ አይፈጽሙም (ያዕ. 2፡1-13)

እግዚአብሔር ከሚጠላቸው ኃጢአቶች አንዱ አድልዎ ነው። በያዕቆብ ዘመን ይህ የአድልዎ ኃጢአት በሃብታምና ደሃ አይሁዳውያን አማኞች መካከል ይታያል። ሀብታምና ደሃ አማኞች ወደ ቤተ ክርስቲያን በሚመጡበት ጊዜ የሚሆነው ነገር አድልዎ መኖሩን ያሳይ ነበር። ሀብታም አማኞች ከመድረኩ ፊት ያማረ ስፍራ ይሰጣቸዋል። ድሆች ግን ከወለሉ ላይ ወይም ከኋላ እንዲቀመጡ ይደረጋል። ያዕቆብ ይህ በሁለት ምክንያቶች የተሳሳተ አመለካከት መሆኑን ይናገራል።

ሀ) ይህ አማኞች የሚያሳድዷቸውን ሰዎች እንዲያከብሩ ያደርጋል። ብዙውን ጊዜ ስደት የሚመጣው ከድሆች አይደለም። አሳዳጆች ሀብታሞችና ኃይለኞች ናቸው። እነዚህም ነጋዴዎች፥ የሃይማኖት መሪዎችና የፖለቲካ መሪዎች ናቸው። ለሃብታሞች ማዳላቱ ሞኝነት መሆኑን ለማመልክት ያዕቆብ እነዚህ ሰዎች በአብዛኛው አሳዳጆቻችን መሆናቸውን ይናገራል።

ለ) ይህ የእግዚአብሔርን ሕግ ይተላለፋል። ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ሕግጋት አንዱን «የንጉሥ ሕግ» ይለዋል። ይህ ሕግ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ወደድ» የሚለው ነው። ሀብታሙን ማክበርና ድሃውን መናቅ ሰዎች ሁሉ፥ ሀብታሙም ድሃውም ባልንጀሮቻችን ስለሆኑ እኩል አክብሮት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጣስ ይሆናል። ይህን ሕግ በምንተላለፍበት ጊዜ (አድልዎ በማሳየት) ሕግ ተላላፊዎች ሆነናል ማለት ነው። ይህም እንደ አመንዝራነት ወይም ነፍሰ ገዳይነት መሆኑ ነው። ስለሆነም፥ አድልዎ በምንፈጽምበት ጊዜ ሕግን ስለተላለፍን የእግዚአብሔር ፍርድ ይጠብቀናል።

ዛሬ አብያተ ክርስቲያኖቻችን በዚህ ኃጢአት ተበክለዋል። በያዕቆብ ዘመን እንደነበሩት አይሁዶች፥ ሀብታሞችን በማክበር ከቤተ ክርስቲያን የስብከት መድረክ ፊት ለፊት እናስቀምጣቸዋለን። ድሆችን ግን እንንቃቸዋለን። የተማሩትን እያከበርን፥ ያልተማሩትን ግን እንንቃለን። ነጋዴዎችን እያከበርን፥ ባሪያዎችን ወይም ብረት ሠሪዎችን እንንቃቸዋለን። አንዱን ጎሣ ከሌላው እናስበልጣለን። ቤተሰባችንን ስናከብር፥ ቤተሰባችን ያልሆኑትን እንንቃለን። (ለምሳሌ፥ ልጆቻችንን የመዘምራን ቡድን ውስጥ እናስገባለን። ነገር ግን የድሆች ልጆች ብዙም ወደ ኳየሩ እንዲገቡ አይደረግም።) ዝሙት ላንፈጽም ብንችልም፥ ያዕቆብ በእግዚአብሔር ዐይኖች ፊት አድልዎ እንደ ዝሙት የከፋ መሆኑን ይናገራል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ቤተ ክርስቲያንህን ገምግም። ምን ዓይነት አድልዎዎች ታያለህ? ለ) እግዚአብሔር ይህን ሁኔታ እንዴት የሚመለከት ይመስልሃል? ሐ) እግዚአብሔር እነዚህን የተለያዩ ዓይነት ሰዎች እንድናስተናግድ የሚፈልገው እንዴት ይመስልሃል?

፬. እውነተኛ አማኞች የእምነታቸውን እውነተኛነት በተግባራቸው ያሳያሉ (ያዕ. 2፡14–26)

ያዕቆብ አድልዎ የዝሙትን ያህል የከፋ መሆኑን በሚናገርበት ጊዜ አንድ ሰው ክርክር የገጠመው በሚመስል ሁኔታ ይጽፋል። ያ ክርክር የገጠመው ሰው፥ ሰዎች እውነት የሆነውን እስካመኑ ድረስ እግዚአብሔር ደስ ይለዋል ሲል ይናገራል። ሰዎች ኢየሱስ አምላክ እንደሆነና ለኃጢአታቸው እንደ ሞተ ካመኑ፥ እግዚአብሔር ደስ ይለዋል «እግዚአብሔር የሚፈልገው ትክክለኛ እውቀትን ነው። ምንም እንኳን የሚገባኝን ያህል ለድሆች ፍቅር ባላሳይም፥ ይህ በቂ ይሆናል» ሲል ይከራከራል።

ይህ ክፍል ምናልባትም ያዕቆብ አማኞችን ለማስተማር የፈለገው ዐቢይ እውነት ሳይሆን አይቀርም። «መዳናችንን እንዴት እናሳያለን? ይህንን የምናደርገው ትክክለኛ እውነቶችን በማመን ነው? ወይስ የተለወጠ ሕይወት በመኖር?» የያዕቆብ ምላሽ መዳናችንን የምናሳየው በተግባራችን እንጂ በቃላችን አይደለም የሚል ነው። ትክክለኛ ቃላትን ተናግሮ በተለወጠ ሕይወት ራሱን የማይገልጥ እምነት «የሞተ እምነት» ነው። አጋንንት እንኳን እግዚአብሔር እንዳለ በትክክል ያውቃሉ። ትክክለኛ እምነታቸው ግን አያድናቸውም። ምክንያቱም በተግባራቸው ልባቸው እንዳልተለወጠ ያሳያሉ። እምነት ከሥራ ተለይቶ ሊታይ አይችልም። ያዕቆብ እውነተኛ እምነት በሰዎች ተግባራት የተገለጠባቸውን የብሉይ ኪዳን ምሳሌዎች ይገልጻል።

ሀ) አብርሃም፡- አብርሃም በእግዚአብሔር ላይ የነበረውን እምነት የገለጸው ይስሐቅን በመሠዋት ነበር። ለአብርሃም፥ «ከይስሐቅ በላይ እወድሃለሁ። ይስሐቅን ከሞት ልታነሣው እንደምችትል አውቃለሁ» የሚል ቃል ለእግዚአብሔር መናገሩ ብቻ በቂ አይሆንም ነበር። ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅርና እግዚአብሔር ይስሐቅን ከሞት እንደሚያስነሣው ማመኑን ልጁን ወደ ሞሪያ ተራራ ወስዶ በመሠዋት ማሳየት ነበረበት። እምነቱን በተገቢ ተግባራት በተጨባጭ ማሳየት ያስፈልገው ነበር።

ለ) ረአብ፡- በኢያሱ ዘመን ሁለት ሰላዮች ከተማይቱን ለመሰለል ወደ ኢያሪኮ ተልከው ነበር። ጋለሞታ የነበረችው ረአብ እነዚህ ሰዎች እስራኤላውያን ሰላዮች መሆናቸውን ተገነዘበች። ነገር ግን ስለ ታላቁና ኃያሉ አምላካቸው ቀደም ሲል ሰምታ ነበርና በእርሱ አመነች። ይሁንና እምነቷ እውነት መሆኑን እንዴት እናውቃለን? ከተጋረጠባት አደገኛ ሁኔታ ባሻገር፥ ረአብ ሰላዮቹን በቤቷ ውስጥ ደበቀች።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በእግዚአብሔር ማመን አስቸጋሪ ተግባር እንድናከናውን የሚጠይቀን መሆኑን ለማሳየት ከዛሬው ዓለም ሁለት ምሳሌዎችን ጥቀስ። ለ) እምነት እንዳለን በሚያሳይ መልኩ ቀጣይ እርምጃ በማንወስድበት ጊዜ ስለ እምነታችን ምን እናሳያለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

ክርስቲያን ለፈተናና መከራ የሚሰጠው ምላሽ (ያዕ. 1፡1-18)

ሔለን ተወልዳ ያደገችው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ነበር። በሕይወት ዘመኗ ሁልጊዜም ወንጌልን ዓላማ አድርጋ ኖራለች። በየጊዜው ወደ ቤተ ክርስቲያን ትሄድና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ታካሂድ ነበር። እንዲሁም በመዘምራን ቡድን (ኳየር) ውስጥ ትዘምር ነበር። አዝማቾችን መዘመር ትወዳለች። ማንም ሰው «ክርስቶስ ለኃጢአትሽ የሞተ ጌታ መሆኑን ታምኚያለሽ?» ብሎ ሲጠይቃት፥ በፍጥነት፥ አዎን» ስትል ትመልሳለች። እንዴት ክርስቲያን ልትሆን እንደቻለች ብትጠየቅም፥ «ሁልጊዜም ክርስቲያን ሆኜ ኖሬአለሁ፥ ወላጆቼ ክርስቲያኖች ናቸው» ትላለች። ነገር ግን ሔለን በቤተ ክርስቲያንና በትምህርት ቤት የምታሳየው ሁኔታ ጭራሽ የተለያየ ነበር። ሔለን ቆንጆ ልጅ ነበረች። ይህን ቁንጅናዋን በአጭር ቀሚሶች፥ ጌጣጌጦችና ሜካፖች አጉልታ ታሳይ ነበር። ሔለን ማጥናት ስለማትወድ ከክፍሉ ውስጥ አንደኛ ከሚወጣው ልጅ ጎን ተቀምጣ ትኮርጅ ነበር። ታዋቂነትን ለማትረፍ በመፈለጓ በትምህርት ቤት ውስጥ ታዋቂ የነበረውን ልጅ የወንድ ጓደኛዋ አድርጋ ያዘች።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሔለን በቤተ ክርስቲያንና በትምህርት ቤት ውስጥ በምታከናውናቸው ተግባራት መካከል የሚታዩት ልዩነቶች ምን ምንድን ናቸው? ለ) ልዩነቱ የተከሰተው ለምን ይመስልሃል? ይህ ስለ ሔለን እምነት እውነተኛነት ወይም ጥልቀት ምን ያሳያል? ሐ) በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ የሚያድጉ ብዙ ልጆች ወደ ዩኒቨርስቲ በሚገቡበት ጊዜ እምነታቸውን ጠብቀው ለማቆየት የሚችገሩት ለምንድን ነው? መ) ቤተሰቦችና ቤተ ክርስቲያን ልጆቻቸው እምነታቸውን እንዲረዱና ይህም እኗኗራቸውን እንዲቆጣጠር ለማድረግ ምን ሊያከናውኑ ይችላሉ?

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሙሉ ኃይላችን ልንዘምር፥ ልንጸልይ፥ ብዙ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ልናካሂድ፥ ወዘተ… በምንችልበት አስደሳች ዘመን ውስጥ እንኖራለን። በዚህ ደስታ ውስጥ ግን እናምናለን በምንለውና በዓለም ውስጥ በምንኖርበት ሁኔታ መካከል እያደገ የሚሄድ ክፍተት ይታያል። አማኞችም እንደማያምኑ ሰዎች ሁሉ ወሲባዊ ኃጢአቶችን ይፈጽማሉ። ክርስቲያኖች ጉቦ፥ ማጭበርበር ወይም መስረቅ የመሳሰሉትን ኃጢአቶች ይለማመዳሉ። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጸብ በመፍጠር በአብያተ ክርስቲያናት ክፍፍሎችን ያስከትላሉ። ለሴተኛ አዳሪዎች ወይም ለጎዳና ተዳዳሪዎች ብዙም ደንታ የለንም። ይህ እናምናለን በምንለውና በአኗኗራችን መካከል ያለው ክፍተት የግብዝነት ኃጢአት በመባል ይታወቃል። ይህም ኃጢአት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚታዩ አደገኛ ኃጢአቶች አንዱ ነው። አይሁዳውያን አማኞች ከዚህ ችግር ጋር ተጋፍጠው ነበር። ያዕቆብ ድፍረት በተሞላበት ነቢያዊ መንገድ በእርግጥም በክርስቶስ ካመንን፥ ይህም እምነታችን ከአእምሮ እውቀት ያለፈ እንደሆነ፥ አኗኗራችን መለውጥ አለበት ሲል አጽንኦት ሰጥቶ ያስተምራል። የምናምነው ነገር አኗኗራችንን መለወጥ አለበት። የያዕቆብ መልእክት እግዚአብሔርን የሚያስከብር ሕይወት በመምራቱ ምን ያህል እንደተዋጣለት ለመመርመር የሚያስችል መንገድ ይሰጠናል።

፩. ለመከራ ሊሰጥ የሚገባው ምላሽ (ያዕ. 1፡1-13)

ያዕቆብ ራሱን የሚገልጽበትን ሁኔታ መመልከቱ ጠቃሚ ነው። ምንም እንኳን ከማርያም የተወለዱና የኢየሱስ ወንድሞች ለመሆን የቻሉ ብዙ ሰዎች ባይኖሩም፥ ያዕቆብ በቤተሰባዊ ግንኙነቱ ሲመካ አንመለከትም። ወይም ደግሞ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ታላቅ መሪ በመሆኑ አይኩራራም። የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ወቅት እናት ቤተ ክርስቲያን ነበረች። ነገር ግን ያዕቆብ ራሱን «ባሪያ» ሲል ይጠራል። የሕይወቱ ዓላማ እግዚአብሔር አብን ማገልገል ነበር። በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ኢየሱስ፥ ያ ታላቅና ኃይል ያለው ወንድሙ ብቻ ሳይሆን አምላክ መሆኑንም ተረድቷል። ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር እኩል መሆኑን ይገልጻል። (ማስታወሻ፡ ይህ የ«ኢየሱስ ብቻ» ተከታዮች እግዚአብሔር አብና ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ አካል መሆናቸውን በመግለጽ ስለ ሥላሴ የተሳሳተ እምነታቸውን የሚያሳየው ነጥብ ነው)።

ክርስቲያኖች ነን ብንልና እርሱን ለመከተል ብንፈልግ፥ ብዙውን ጊዜ የሚከሰቱ ነገሮች አሉ። ይኸውም ስደት ነው። ያዕቆብ መልእክቱን የሚጽፍላቸው አይሁዳውያን አማኞች ክርስቶስን መድኅናቸውና ጌታቸው አድርገው መከተላቸውን በመምረጥ ሳይሆን አይቀርም። ለአይሁዶች የኢየሱስን መሢሕነት መቀበሉ ከባድ ነበር። ከዚህ አልፎ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነው ማለቱ ስድብ ነበር። አይሁዶች ክርስቶስን ለመከተል በሚወስኑባት ጊዜ ብዙውን ጊዜ አይሁዳውያን ወገኖቻቸው ያሳድዷቸው ነበር። ብዙውን ጊዜ ከምኩራብና ከአይሁዶች ኅብረት ይባረሩ ነበር። ከእነርሱ ጋር የንግድ ግንኙነት የሚያደርጉት ሀብታም ነጋዴዎች ያገልሏቸው ነበር። ድህነቱ እየጠና ሲሄድ ሕይወት ከባድ ትሆንባቸው ጀመር። ይህም አማኞችን ለተስፋ መቁረጥ ዳረጋቸው። ያዕቆብ እነዚህን የተበተኑና የተሰደዱ አይሁዶች ለማበረታታት ሲል ስለ መከራ ይጽፋል።

ከያዕቆብ 1፡2-18 ያለውን ትምህርት ለመረዳት «ፈተና» የሚለው የአማርኛ ቃል ሁለት የተለያዩ ትርጉሞች እንዳሉት መረዳት ይኖርብናል። በመጀመሪያ፥ ይህ ቃል ወደ ኃጢአት የሚመራንን የኃጢአት ባሕሪ ወይም የሰይጣን ፈተና ሊያመለክት ይችላል። ያዕቆብ በ1፡13-18 ስለዚህ ዓይነቱ ፈተና ይናገራል። ሁለተኛ፥ ይህ ቃል ግምገማን ወይም ምርመራን ሊያላይ ይችላል፤ ይህም እግዚአብሔር እምነታችንን ለመገምገምና ለማጠንከር፥ ችግሮች ወደ ሕይወታችን እንዲመጡ የሚፈቅድበት ነው። ያዕቆብ 1፡3-12 የሚያቀርበው ይህንኑ ዓይነት ፈተና ነው። ስደት ወይም እንደ በሽታና የወዳጅ ሞት ያለ ሌላ ፈተና ወደ ሕይወታችን በሚመጣበት ጊዜ እንደ አማኞች ምን ማድረግ ይኖርብናል? ያዕቆብ እምነታችን በሚፈተንበት ጊዜ ልናደርጋቸው የሚገቡንን አንዳንድ ነገሮች ይዘረዝራል።

ሀ. ችግሮችን በሩጫ ልንመልሳቸው እንደሚገቡ ጠላቶች ሳይሆን፥ እምነታችንን እንደሚያጠነክሩ መሣሪያዎች መመልከት ይኖርብናል። ያዕቆብ በዚህ ጊዜ ደስ መሰኘት እንዳለብን ይነግረናል። የምንደሰተው ስደቱ በሚያመጣብን ሥቃይ ላይሆን፥ እግዚአብሔር እኛን ለመለወጥ ይህንኑ ሥቃይ እየተጠቀመ መሆኑን በማወቃችን ነው። ያዕቆብ እነዚህን የመከራ ጊዜያት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ብናስተናግድ በሕይወታችን ውስጥ የሚመጡትን ለውጦች ያሳየናል። በፈተና ጊዜ ጠንክረን ብንቆም፥ እምነታችን ጽናትን ያፈራል። ይህም የኋላ ኋላ ወደ ብስለት ይመራናል። ነገር ግን ያዕቆብ ጽናት ሥራውን እንዲያጠናቅቅ መፍቀድ እንዳለብን፥ ይህ ካልሆነ ግን ወደ ብስለት እንደማይመራን ያስጠነቅቀናል። ከችግሩ ፊትን ማዞር፥ ማጉረምረም ወይም እጅን መስጠት መከራው በሕይወታችን እንድናድግ እንዳያግዘን ያደርጋል።

ይህ እውነት በአብያተ ክርስቲያኖቻችን የተወደደ ትምህርት አይደለም። ክርስቶስ መከራን ድል መንሣቱን ለመዘመር እንፈልጋለን። ስለ ቅጽበታዊ ፈውስና ከክርስቶስ ስለምናገኛቸው በረከቶች ለመደሰት እንፈልጋለን። እርሱም አንዳንድ ጊዜ ፈውስና ቀለል ያለ አኗኗርን ይሰጠናል። ነገር ግን በእርግጥ ልጆቹ ከሆንን፥ እግዚአብሔር እንዴት በመንፈሳዊ ሕይወታችን እያደግን እንዳለን ለመፈተንና የበለጠ እንድናድግ ለማገዝ ችግሮችን ወደ ሕይወታችን ማምጣቱ የማይቀር ነው። ሚዛናዊ የክርስትና አመለካከት እግዚአብሔር መከራን ወደ ሕይወታችን እንደሚያመጣ የሚያሳይ ነው። ድል የሚገኘው ደግሞ እግዚአብሔር መከራውን ከእኛ እንዲወስድ በማድረግ ሳይሆን፥ በችግር ጊዜ በእርሱ ብርታት ጸንቶ በመቆም ነው። በዚህ ሁሉ ደስታ የተሞላበት እምነት ይዞ መዝለቁ ወሳኝ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለመጨረሻ ጊዜ ስለ አማኞች መከራ መቀበል የሚያስረዳ ስብከት የሰማኸው መቼ ነው? ለ) ብዙውን ጊዜ የሚቀርበው ስብከት እግዚአብሔር ከመከራ እንደሚያድነን የሚያስረዳ ነው ወይስ እግዚአብሔር በሕይወታችን እንድናድግ መከራውን የሚጠቀምበት መሆኑ ነው? ሰዎች አንደኛውን ዓይነት ስብከት የሚወዱትና ሌላኛውን ዓይነት የማይወዱት ለምንድን ነው? ሐ) እግዚአብሔር ከመከራ እንድናመልጥ እንደረዳን ተነግሮን ሳለ ይህ ሳይሆን በሚቀርበት ጊዜ እምነታችን ምን ይሆናል?

ለ. መከራ በሚመጣበት ጊዜ እግዚአብሔር ዓላማውን ለመረዳትና በመንፈሳዊ ሁኔታ ለመኖር ጥበብን እንዲሰጠን መጠየቅ ይኖርብናል። የዚህ ተወዳጅ ጥቅስ (ያዕ. 1:5) ዐውደ ምንባብ መከራ ነው። ችግሮች የጠለቀ ሥቃይ በሚያስከትሉበት ጊዜ (ለምሳሌ፥ ስደት፥ በሽታ) ለዚህ ሁኔታ ምላሽ የምንሰጥበትን ጥበብ ማግኘቱ ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥበብ ስለ አንድ ነገር እውነቶችን ማወቅ ብቻ ሳይሆን፥ በመንፈሳዊ ሁኔታ እንዴት መኖር እንዳለብን ማወቁ ጭምር ነው። ያዕቆብ፥ ግራ በተጋባንና ለአንድ ሁኔታ እንዴት ምላሽ መስጠት እንዳለብን በማናውቅበት ጊዜ እግዚአብሔር ሁልጊዜም ሊረዳን ዝግጁ መሆኑን ይነግረናል። እንዴት መመላለስና መጽናት እንዳለብን ስንጠይቀው እግዚአብሔር በቂ የሆነ ተግባራዊ ጥበብ ያፈስልናል። እግዚአብሔር እንደሚወደን መጠራጠር የለብንም። ጥያቄዎቻችን እኛ በምንፈልጋቸው መንገዶች በማይመለሱበት ጊዜ እግዚአብሔር ጸሎትን እንደሚመልስ መጠራጠር የለብንም። ነገር ግን አፍቃሪና ኃያሉ አምላካችን ሁልጊዜም እርሱ የሰጠንን ፈተና የምንቋቋምበትን ጥበብ እየሰጠን ጸሎታችንን በራሱ ጊዜና መንገድ እንደሚመልስ መረዳት ይኖርብናል።

አይሁዳውያን አማኞች ከተጋፈጧቸው ችግሮች አንዱ የኢኮኖሚ ችግር ነበር። ሕይወታቸውን ለመግፋት የሚያስችል ገቢ ለማግኘት የሚሯሯጡ ድሆች ነበሩ። አይሁዶች ልክ እንደኛዎቹ የጉራጌ ሕዝቦች ሠርቶ ገንዘብ የማግኘት ብቃት ነበራቸው። ለእነርሱ ድህነቱ ተስፋ የሚያስቆርጥ ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር በቁሳዊ ሀብት ስላልባረካቸው የማይወዳቸው መሆኑን የሚያመለክት ጭምር ነበር። ከዚህም የተነሣ፥ አይሁዳውያን አማኞች ሀብታምና ዳሩ ግን በክርስቶስ የማያምኑ አይሁዶችን ለመለማመጥ ተገደዱ። ያዕቆብ የዛሬውን የድህነት ኑሮአቸውን ረስተው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ያገኙትን በረከት እንዲመለከቱ ያሳስባቸዋል። ክርስቲያኖች ከፍ ያለ ደረጃ አላቸው። እኛ የራሱ የእግዚአብሔር ልጆች፥ የሰማይና የዘላለም በረከቶች ሁሉ ወራሾች ነን። በመንፈሳዊ ብልጽግናችን ደስ ብንሰኝ፥ ጊዜያዊውን ድህነት ተቋቁመን ልንኖር እንችላለን። ያዕቆብ ሀብታም ዓለማውያን ስለ ገንዘብ ባላቸው አመለካከት ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመክራቸዋል። ምክንያቱም ያላቸው ነገር ዝቅተኛ ግምት የሚሰጠው ወይም የተዋረደ ብቻ ነውና። ሰዎች በመሆናቸው ሀብታቸው እስኪሞቱ ድረስ ላላቸው አጭር ጊዜ ብቻ የሚያገለግል ይሆናል። እንደ አበቦች ለጊዜው ደስ ሊላቸው ቢችልም፥ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጠውልገው ይሞታሉ።

ሐ. መከራ የሚቀበሉ ክርስቲያኖች ዓይኖቻቸውን በሕይወት አክሊል (የዘላለም ሕይወት) ላይ ማሳረፍ ይኖርባቸዋል። ይህም እግዚአብሔር እርሱን ለሚወዱትና በመከራ ጊዜ በታማኝነት ጸንተው ይህንኑ ፍቅራቸውን ለሚያሳዩ አማኞች ተስፋ የገባላቸው ጉዳይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የፈተናን ጊዜ ከመጋፈጣችን በፊት አማኞች ሁሉ እነዚህን ሦስት ነጥቦች መረዳት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ለ) ከፍተኛ መከራ የገጠመህ መቼ ነው? እግዚአብሔር በሕይወትህ እንድታድግ ይሄንን መከራ የተጠቀመው እንዴት ነው?

፪. ለፈተና እንዴት ምላሽ መስጠት እንደሚገባ (ያዕ. 1፡13-18)

ያዕቆብ ከእምነት ግምገማ ወደ ሌላው ዓይነት ፈተና ይመለሳል። ይህም አንድን ሰው ወደ ኃጢአት የመምራት ፈተና ነው። አማኞች ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ በአመዛኙ ጥፋቱ የሌላ ሰው ነው ወደ ማለቱ ያደላሉ።

ቤተሰብን፥ ሰይጣንን፥ ወይም ራሱ እግዚአብሔርን እንወቅሳለን። «እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ የሚቆጣጠር ከሆነ ከጋብቻ ውጭ የወሲብ ግንኙነት ወደማድረጉ ፈተና ያመጣኝ እግዚአብሔር አይደለምን?» ብለን እንጠይቃለን። «እግዚአብሔር ገንዘብ ቢሰጠኝ ኖሮ መስረቅ አያስፈልገኝም ነበር። እግዚአብሔር እንደነ እገሌ በትምህርት ቤት ጎበዝ ስላላደረገኝ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ፈተና መኮረጅ አለብኝ። እግዚአብሔር ወሲባዊ ፍላጎቴን ስለፈጠረው፥ የዚህ ዓይነቱን ኃጢአት በመፈጸሜ የእርሱ ጥፋት ነው» የሚል ምክንያት እናቀርባለን። ያዕቆብ እንዲህ ዓይነቱን እግዚአብሔርን የመወንጀል ዝንባሌ በሁለት መንገዶች ያስተባብላል።

ሀ) እግዚአብሔር ሰዎች ክፉ ነገር እንዲያደርጉ አይፈትንም። እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ፥ ቅዱስ የሆነው አምላክ ሰዎች ኃጢአት የሆነውን ተግባር እንዲያከናውኑ አያደርግም። እርሱ የበጎ ነገር ሁሉ ምንጭ እንጂ የክፉ ነገር ምንጭ አይደለም። እግዚአብሔር ኃጢአትን እንድንሠራ አድርጎናል ማለቱ በእግዚአብሔር ባሕሪ ላይ የሚሰነዘር ስድብና የሚገባንን ያህል እርሱን እንደማናውቅ የሚያመለክት ነው።

ለ) ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ መወቀስ አለብን። እግዚአብሔርን ልንወቅስ አንችልም። ሌላውንም ሰው ልንወቅስ አንችልም። ሰይጣንን ጭምር መውቀስ አይኖርብንም። ሰይጣንን ጨምሮ ማንም ኃጢአትን እንድንሠራ ሊያስገድደን አይችልም። ሰይጣን ፈተናውን ከፊታችን ሊያስቀምጥ ይችላል። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ የሆነ ነገር ለማድረግ በምንመርጥበት ጊዜ ኃጢአትን እንሠራለን። ያዕቆብ ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ የሚከሰተውን ሁኔታ አይጦችን ከምንይዝበት ሁኔታ ጋር ያነጻጽራል። ይህ ሁሉ የሚጀምረው ስሕተት መሆኑን የምናውቀውን ነገር ከመመልከት ነው። አይጥ ለመያዝ አይጧ የምትወደውን ምግብ ከወጥመዱ ላይ እንደምንጨምር፣ ሰይጣንም እግዚአብሔር የማይፈልገውንና እኛ የምንወደውን ነገር ከፊታችን ያኖራል። ይህ ወደ ክፉ ምኞት ይመራናል። የተሳሳተ መሆኑን ብናውቅም ይህንኑ ነገር ለመቀበል እንፈልጋለን። በሌላ አገላለጽ፥ የኃጢአት ተፈጥሮአችን ማለትም ትክክል ያልሆኑትን ነገሮች የሚፈልገው ውስጣዊ ማንነታችን ሰይጣን ከፊታችን ይህንን ነገር እንዳስቀመጠ በመመልከት «አድርገው» ይለናል። እስከ አሁን ገና ኃጢአት አልሠራንም። ፈተና በራሱ ኃጢአት አይደለም። ክፉውን ምኞት ካልተቃወምን ፈተና በኃጢአት ለመውደቅ የመጀመሪያው ደረጃ ነው። አይጥ አንድ የምትወደውን ነገር ስትመለከት ወደ ወጥመዱ ትጓዛለች። ማጥመጃዋን ታሸታለች። ነገር ግን እስከ አሁን ገና በወጥመዱ አልተያዘችም። ይሁንና ፍላጎታችን ካልተገታ፥ «አይሆንም» ካላልን፥ ቀጣዩ እርምጃ ይከተላል። ይኸውም በወጥመዱ መያዝ ነው። እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ ኃጢአት እንሠራለን፥ ወደ ወጥመዱ ዘላ እንደምትሄድ አይጥ እንያዛለን ማለት ነው። ያዕቆብ ወደ ኃጢአት የሚገፋፋ ስሜታችንን ካልተቆጣጠርን፥ የኋላ ኋላ ወደ ሞት እንደሚመራን ይናገራል። ይህም የግንኙነቶች፥ የሥጋዊና ምናልባትም መንፈሳዊ ሞት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም የማያቋርጥ ልማዳዊ ኃጢአት በእምነታችን ውስጥ አንድ ነገር እንደ ጎደለ ያሳያል።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) በተደጋጋሚ ስለፈጸምከው ኃጢአት ከክፉ ምኞት ኃጢአቱን እስከ መፈጸም ድረስ ያሉትን ደረጃ ዎች ዘርዝር። ለ) የኃጢአት ሕይወት መደጋገሙ ወደ አንድ ዓይነት ሞት ሲመራ ያየህበትን ሁኔታ ግለጽ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

የያዕቆብ መግቢያ

ጳውሎስ በሮሜና ገላትያ መልእክቶች ውስጥ፥ «እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል» ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጣል። አይሁዳውያን አማኞች ድነትን (ደኅንነትን) እና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ውጫዊ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው ስለሚያስቡ፥ ጳውሎስ ድነት (ደኅንነት) ሁልጊዜም ክርስቶስ ለእርሱ ኃጢአት እንደ ሞተ ለሚያምን ሰው እግዚአብሔር በነፃ የሚሰጠው ስጦታ እንደሆነ ያስተምራል። የያዕቆብ መጽሐፍ ግን፥ «አሁን ድነትን እንዳገኝ ምን ማድረግ ይገባኛል?» የሚለውን ጥያቄ ይመልሳል። ይህ መጽሐፍ እግዚአብሔርን የሚያሳስበው ሰው በክርስቶስ አምኖ መዳኑ እስከሆነ ድረስ አንድ ክርስቲያን ስለ አኗኗሩ መጨነቅ የለበትም ብለው ያስቡ ለነበሩ ሰዎች ምላሽ ይሰጣል። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች አንድ ሰው ድነትን የሚያገኘው ስለ ክርስቶስ የተገለጠውን እውነት በዕውቀት ደረጃ በማመን እንደሆነ ያስቡ ነበር። በእነርሱ አስተሳሰብ ድነት በተለወጠ ሕይወት መገለጡ አስፈላጊ አልነበረም። የያዕቆብ መልእክት የአንድ ሰው እምነት ከእውነት ጋር ከሚደረግ አእምሮአዊ ስምምነት ያለፈ እንደሆነ፥ የግለሰቡ የሕይወት ክፍሎች ሁሉ ለክርስቶስ መገዛት እንዳለባቸው ያስረዳል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ ሰው ይድን ዘንድ ምን ማድረግ እንደሚገባው ቢጠይቅህ፥ ምን ብለህ ትመልስለታለህ? ለ) አዳዲስ አማኞች ድነትን (ደኅንነትን) ካገኙ በኋላ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲጠይቁህ ምን ታስተምራቸዋለህ?

የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ያዕቆብ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በመዝገበ ቃላት ውስጥ ስለ ጸሐፊው፥ መጽሐፉ ስለ ተጻፈበት ጊዜ፥ ስለ አንባቢዎቹ እና ስለ ዓላማው የተገለጹትን አሰቦች ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። ለ) ያዕ. 1፡1 አንብብ። የዚህ መልእክት ጸሐፊ ነኝ ያለው ማን ነው? ራሱን እንዴት ይገልጻል?

፩. የያዕቆብ ጸሐፊ

ጥንታዊ የደብዳቤ አጻጻፍ ስልት በመከተል ጸሐፊው ከደብዳቤው መጀመሪያ ላይ ስሙን ይጠቅሳል። እራሱን «ያዕቆብ» ሲል ያስተዋውቃል። ለመሆኑ ጸሐፊው የትኛው ያዕቆብ ነበር? በአዲስ ኪዳን ውስጥ በዚህ ስም የሚጠሩ አራት ሰዎች አሉ።

 1. የዘብዴዎስ ልጅና የዮሐንስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ። በኢየሱስ ዘመን፥ ያዕቆብ ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነበር። ክርስቶስ ካረገ በኋላ ያዕቆብ የኢየሩሳሌምን ቤተ ክርስቲያን ከሚያስተዳድሩ ቁልፍ መሪዎች አንዱ ነበር። ነገር ግን በ44 ዓ.ም ንጉሥ ሄሮድስ ያዕቆብ እንዲገደል አዘዘ። ምንም እንኳን የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ የጌታ ደቀ መዝሙር የነበረው ያዕቆብ ሊሆን ቢችልም ክርስቶስ ካረገ ብዙም ሳይቆይ፥ ቤተ ክርስቲያን ከመስፋፋቷ በፊትና በመጽሐፉ ውስጥ የተገለጠው ርእሰ ጉዳይ ከመታየቱ በፊት ስለተገደለ ይህን መልእክት የጻፈው የጌታ ደቀ መዝሙር የነበረው ያዕቆብ አይመስልም።
 2. የእልፍዮስ ልጅና ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ የነበረው ያዕቆብ (ማቴ. 10፡3 አንብብ)። ይህ ደቀ መዝሙር አንዳንድ ጊዜ ትንሹ ያዕቆብ በመባል ይታወቃል። ከክርስቶስ እርገት በኋላ በዚህ ደቀ መዝሙር ላይ ስለደረሰው ሁኔታ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ብዙም መረጃ ስለማይሰጠን፥ ምሁራን ይህን መልእክት የጻፈው የእልፍዮስ ልጅ የነበረው ያዕቆብ ነው የሚል ግምት የላቸውም።
 3. የይሁዳ አባት (ይህ አስቆሮቱ ይሁዳ አይደለም)፥ እንዲሁም ታዲዮስ በመባል የሚጠራውና ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ የሆነው ያዕቆብ (ሉቃስ 6፡16፥ ማር. 3፡18)።
 4. የክርስቶስ ግማሽ ወንድምና የዮሴፍና ማርያም ልጅ የነበረው ያዕቆብ። አብዛኞቹ ምሁራን የያዕቆብን መልእክት የጻፈው ይሄኛው ያዕቆብ እንደሆነ ያስባሉ። ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት ሐዋርያው ዮሐንስ ምናልባትም መልእክቱ ከመጻፉ በፊት እንደ ሞተ፥ ሌሎች ሁለቱ ያዕቆቦች ይህን ያህል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የታወቁ ባለመሆናቸው መልእክቱን ሊጽፉ እንደማይችሉ በመገመት ነው። ያዕቆብ ከሚለው ስም በስተቀር ሌላ መግለጫ አለመጠቀሱ የመልእክቱ ጸሐፊ በአይሁዳውያን ማኅበረሰብ ውስጥ በሚገባ የታወቀ አገልጋይ መሆኑን ያመለክታል። ያዕቆብ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን መሪ ስለነበር፥ ይህን መልእክት ለመጻፍ የሚያስችል ደረጃና አይሁዳዊ ዳራ አለው። እንዲያውም ምሁራን ያዕቆብ በያዕቆብ መልእክትና ያዕቆብ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ውስጥ ባቀረበው ንግግር ውስጥ ተመሳሳይነቶች መኖራቸውን ይናገራሉ።

የክርስቶስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ምናልባትም ማርያምና ዮሴፍ ከወለዷቸው ከሦስቱ ልጆች ታላቁ ሳይሆን አይቀርም። ሌሎች ሁለቱ ልጆች ስምኦንና ይሁዳ በመባል ይታወቃሉ። (ማቴ. 13፡15 አንብብ።) እነዚህ ልጆች የተወለዱት ክርስቶስ ከተወለደ በኋላ ነበር። ምንም እንኳ ያዕቆብ በአንድ ቤት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር አብሮ ቢያድግም፥ ክርስቶስ በሕይወት በነበረበት ወቅት ያዕቆብ ሊያምንበት አልፈለገም ነበር። እንዲያውም፥ እርሱና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ክርስቶስ እንዳበደ በማሰብ ወደ ቤት ሊወስዱት መጥተው ነበር (ማር. 3፡21፤ ዮሐ 7፡3-5)። ያዕቆብ በክርስቶስ ባያምንም ትምህርቱን ሲሰማ የኖረ ይመስላል። ምክንያቱም በመጽሐፉ ውስጥ ሁሉ የክርስቶስን ትምህርቶች ይጠቅሳል። ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ የያዕቆብን ሕይወት የለወጠ አንድ ነገር ተከሰተ። ያዕቆብ ክርስቶስ በቀጥታ ራሱን ለወንድሞች እንደገለጸ ይነግረናል (1ኛ ቆሮ. 15፡7)። ክርስቶስ ከተነሣ ከ50 ቀን በኋላ በበዓለ ኀምሳ (በ30 ዓ.ም)፥ ያዕቆብ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በሰገነቱ ላይ እንደነበረ ተገልጾአል (የሐዋ. 1፡14)። ያዕቆብ ድነትን ካገኘ በኋላ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረው ሥልጣን በፍጥነት እያደገ ሄደ። የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብ በተገደለበት ወቅት የክርስቶስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ታላቅ መሪ እስከ መሆን ደርሶ ነበር። በመሆኑም ጴጥሮስ መልአክ ከእስር ቤት እንዴት እንዳወጣው ለያዕቆብ እንዲናገሩ ጠይቋቸዋል (የሐዋ 12፡17)። ጳውሎስ፥ ያዕቆብ ከኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን «አዕማዶች» እንዱ እንደነበር ይናገራል (ገላ. 2፡9)። በሐዋርያት ሥራ 15 በተገለጸው የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ወቅት ያዕቆብ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን መሪ ነበር። አሕዛብ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ግርዛትን ተቀብለው አይሁዳውያን መሆን እንደማያስፈልጋቸው በመግለጽ ጉባኤውን ከፍጻሜ ያደረሰው እርሱ ነበር (የሐዋ. 15፡13)። ጳውሎስ በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው መጨረሻ ላይ ራሱን ለያዕቆብ አቅርቧል። በአሕዛብና አይሁዳውያን አማኞች መካከል የነበረውን ክፍፍልና ጳውሎስ ጸረ አይሁዳዊ ነው የሚለውን አሉባልታ ለማክተም፥ ያዕቆብ ጳውሎስ በቤተ መቅደስ ውስጥ መሥዋዕት ለማቅረብ ለአይሁዶች ያለውን ድጋፍ እንዲገልጽ ተጠየቀ። ጳውሎስ ይህንን በታዘዘ ጊዜ ታስሮ ወደ ሮም የሚሄድበት ሁኔታ ተፈጥሮአል (የሐዋ. 21፡18-26)። የሚያምኑ ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ በኢየሩሳሌም የነበሩ የሚያምኑ አይሁዶች ጭምር ያዕቆብን ያከብሩ ነበር። ያዕቆብ በመንፈሳዊ ጉጉቱና ለአይሁድ ልማዶች በነበረው ታማኝነት የታወቀ ነበር። አይሁዶች የጽድቅ ባህሪውን ለማመልከት «ጻድቁ ያዕቆብ» ብለው ይጠሩት ነበር። ጳውሎስ ከታሰረ ብዙም ሳይቆይ ፊስጦ በድንገት ሲሞት፥ ሀናንያ የተባለ የአይሁድ ሊቀ ካህናትና የቤተ ክርስቲያን ጠላት ያዕቆብ ክርስቶስን እንዲክድ ጠየቀው። ያዕቆብ ይህንን ለማድረግ ባልፈቀደ ጊዜ ተገድሏል።

፪. ያዕቆብ መልእክቱን የጻፈው ለማን ነው?

የውይይት ጥያቄ፡- ያዕ. 1፡2 አንብብ። መልእክቱ የተጻፈው ለማን ነበር?

ያዕቆብ «ለተበተኑ ለ12 ወገኖች» እንደጻፈው ይናገራል። ምሁራን ይህንን አሳብ በሁለት መንገዶች ይረዳሉ። በመጀመሪያ፥ አንዳንድ ምሁራን «12 ነገዶች» የሚለው ቃል ክርስቲያኖችን ሁሉ የሚያመለክት ተምሳሌታዊ አገላለጽ ነው ይላሉ። አዲስ ኪዳን የአብርሃም እምነት ስላለን እውነተኛ አይሁዶች መሆናችንን ስለሚያመለክት (ገላ. 3፡26-29)፥ ያዕቆብ የሚጽፈው ለመንፈሳውያን አይሁዶች እንደሆነ ይናገራል።

ሁለተኛ፥ በአመዛኙ ግን መልእክቱ የተጻፈው በሮም ግዛት ውስጥ ለሚኖሩ ክርስቲያን አይሁዶች ይመስላል። በግሪክ ቋንቋ «የተበተኑ» የሚለው ቃል ከፓለስታይን ውጪ በሮም ግዛቶች ውስጥ ተበታትነው የሚኖሩትን አይሁዶች የሚያመለክት ሙያዊ ቃል ነበር። የያዕቆብ መልእክት የአይሁድ አገላለጾችን ይጠቀማል። የአጻጻፍ ስልቱም የብሉይ ኪዳንን የትንቢት ወይም የጥበብ ሥነ ጽሑፎች ይመስላል። ይህ መልእክት ቤተ ክርስቲያንን ምኩራብ ሲል ይጠራታል። ይህም ከቤተ መቅደስ ውጪ አይሁዶች ለአምልኮ የሚሰበሰቡበት ስፍራ ነው።

ምናልባትም ያዕቆብ መልእክቱን የጻፈው ከእስጢፋኖስ ጀምሮ ሲሰደዱ ለነበሩትና በመካከለኛው ምሥራቅ ሁሉ ለተበተኑት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ሳይሆን አይቀርም። (የሐዋ. 8፡1-4፤ 9፡1-2፤ 11፡9 አንብብ።) እነዚህ ሰዎች የያዕቆብ ቤተ ክርስቲያን አባላት በመሆናቸው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ለማበረታታትና በክርስትና እምነት ላይ ስለነበሯቸው የተዛቡ አመለካከቶች ለማስጠንቀቅ ይህን መልእክት ጽፎ ይሆናል።

ከያዕቆብ መልእክት ለመረዳት እንደሚቻለው፥ አብዛኛዎቹ አይሁዳውያን አማኞች ድሆች በመሆናቸው ሀብታም የመሬት ባለቤቶች እና ነጋዴዎች የተጠቀሙባቸው ይመስላል። ምናልባትም ክርስቶስን በመከተላቸው የተሰደዱም ይመስላል። የይሁዲነት አማኞች ክርስትናን አይወዱም ነበር። አንዳንድ ምሁራን ሁለተኛው የአማኞች ትውልድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣ እንደነበር ያስባሉ። እነዚህ አማኞች ስለ ክርስቶስ የአእምሮ እውቀት ያላቸው እና እምነታቸውን ተግባራዊ የሚማያደርጉ ነበሩ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙውን ጊዜ ሁለተኛ ትውልድ አማኞች እንደ መጀመሪያው ትውልድ በእምነታቸው የተሟሟቁና እምነታቸውን ተግባራዊ የማያደርጉ የሚሆኑት እንዴት ነው? ይህ እውነት የሆነው ለምን ይመስልሃል? ለ) የሁለተኛ ትውልዶችን አማኞች እምነት እውን ለማድረግና ከሕይወታቸው ጋር በማዛመድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

፫. የያዕቆብ መልእክት የተጻፈበት ዘመንና ስፍራ

የጌታ ወንድም የሆነው ያዕቆብ በ62 ዓ.ም ስለ ሞተ ይህ መጽሐፍ ከዚያ በፊት መጻፍ ይኖርበታል። በመጽሐፉ ውስጥ አይሁዳውያን አማኞች በሮም ግዛት ሁሉ መበታተናቸው ስለተገለጸ ይህ መጽሐፍ ከክርስቶስ እርገት በኋላ የተጻፈ ይመስላል። ስለ አሕዛብ አማኞች የተጠቀሰ ነገር አለመኖሩ መጽሐፉ የተጻፈው ወንጌል ወደ አሕዛብ ከመሰራጨቱ በፊት እንደነበር ያመለክታል። እንዲያውም አንዳንድ ምሁራን ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በፎኔሽያ፥ ቆጵሮስ፥ እንዲሁም የሶሪያ አንጾኪያ ለተበተኑ አይሁዳውያን እማኞች እንደሆነ ይናገራሉ። እነዚህ አማኞች የተበተኑት ከእስጢፋኖስ ሞት በኋላ በተከሰተው – ስደት ምክንያት ነበር (የሐዋ. 8፡1፤ 11፡19)። ሌሎች ምሁራን ደግሞ ይህ መልእክት የተጻፈው ከጳውሎስ የመጀመሪያው ወይም ሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ በኋላ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ይህ መልእክት በክርስቶስ ማመን የሚጠይቀው ከተለወጠ ሕይወት ይልቅ በክርስቶስ የማመን አእምሯዊ ስምምነት ብዙ እንደሆነ ብቻ የሚናገሩ አንዳንድ አማኛችን ለማረም ነበር። ይህ መጽሐፍ በ44 ና 50 ዓ.ም መካከል የተጻፈ ይመስላል። ይህም የያዕቆብ መልእክት ከመጀመሪያዎቹ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት (ምናልባትም የመጀመሪያው) ሊሆን እንደሚችል ያሳያል። (ማስታወሻ፡ ምናልባት ከዚህ መልእክት ሊቀድም የሚችለው የገላትያ መልእክት ይሆናል።)

የያዕቆብ መልእክት የት እንደ ተጻፈ የሚያሳዩ ብዙ መረጃዎች ባይኖሩም፥ ያዕቆብ ይህንን መእልክት የጻፈው በኢየሩሳሌም በነበረበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። ያዕቆብ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን መሪ ነበር።

፬. የያዕቆብ መልእክት ዓላማ

የመጀመሪያው ዓላማ፡ በተለያዩ መከራዎች ውስጥ የነበሩትን አማኞች ማበረታታት። ከእነዚህ አማኞች አንዳንዶቹ በአይሁዳውያን ወገኖቻቸው ይሰደዱ ነበር። ሌሎቹ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ነበሩባቸው። ያዕቆብ እነዚህ ድሀ አይሁዳውያን ከስደት እንዳይሸሹና ዳሩ ግን በደስታ እንዲቀበሉት ያበረታታቸዋል። ለዚህም ምክንያቱ እግዚአብሔር ስደትን እና መከራን በመጠቀም የክርስቲያኖችን ባሕሪ የሚቀርጽ መሆኑ ነው።

ሁለተኛ ዓላማ፡ እውነትን በተግባራዊ መንገዶች ሳያሳዩ ለአእምሮ ማወቅ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያስቡትን አማኞች ለመገሠጽ። እውነተኛ እምነት አነጋገራችንን፥ በእምነት የሚዛመዱንን ሰዎች የምናስተናግድበትን ሁኔታ፥ ድሆችን እና ሀብታሞችን የምናቀርብበትን መንገድ፥ የጸሎት ሕይወታችንን፥ ወዘተ… ይለውጣል። የእምነታችንን እውነተኛነት የምናሳየው በአኗኗራችን ነው።

፭. የያዕቆብ መልእክት ልዩ ባሕርያት

 1. ምሁራን የያዕቆብ መልእክት የትንቢትና የጥበብ መጻሕፍትን በሚመስል ስልት እንደተጻፈ ያስባሉ (ከኢዮብ-መኃልየ መኃልይ ያሉትን መጻሕፍት ይመስላል)። ያዕቆብ እንደ ነቢይ በማኅበረሰብ ውስጥ የተመለከታቸውን አንዳንድ ኃጢአቶች፥ በተለይም የድሆችን በደል (በአማኞች መካከል ሳይቀር) በግልጽ ነቅሶ ያወጣል። የያዕቆብ ትእዛዛትና ማስጠንቀቂያዎች የሰሉ ናቸው። አማኞችን ሳይቀር «የተከፈለ ልብ ያላችሁ» ሲል ይጠራቸዋል። እንደ የብሉይ ኪዳን የጥበብ መጻሕፍት በተለይም እንደ መጽሐፈ ምሳሌ፥ ያዕቆብ መንፈሳዊ ጥበብ ምን እንደሆነና ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በአኗኗራችን በተግባር እንድንገልጽ እንደሚጠይቀን ያስረዳል። እንደ መጽሐፈ ምሳሌ ያዕቆብ በፍጥነት ከአንዱ ጭብጥ ወደ አንዱ ጭብጥ ይጓዛል።
 2. የያዕቆብ መልእክት በትእዛዛት የተሞላ ነው። በ108 ጥቅሶች ውስጥ ከ50 የሚበልጡ ልዩ ትእዛዛት አሉ።
 3. ያዕቆብ ከሚናገረው ነገሮች አብዛኛዎቹ የክርስቶስን ትምህርቶች፥ በተለይም፥ የተራራውን ስብከት (ማቴ. 5-7) ይዳስሳሉ። ያዕቆብ እንደ ክርስቶስ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያደፋፍራል (ያዕ. 1፡22-25 ከማቴ. 7፡26 ጋር አነጻጽር። ያዕቆብ በተጨማሪም የክርስቶስን ዓይነት ምሳሌዎች ይጠቀማል (ያዕ. 2፡5 እና ማቴ. 5፡3፤ ያዕ. 3፡10-12 እና ማቴ. 7፡15-20፥ ያዕ. 3፡18 እና ማቴ. 5፡9፥ ያዕ. 5፡2-3 እና ማቴ. 6፡19-20፥ ያዕ. 5፡12 እና ማቴ. 5፡33-37 አነጻጽር)።
 4. የያዕቆብ መልእክት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙት ዐበይት መጻሕፍት መካከል ጥቂት አስተምህሮ እና ብዙ ተግባራዊ ትምህርት የሚገኝበት መጽሐፍ ነው። ያዕቆብ የሚያተኩረው መንፈሳዊ እውነትን በማብራራቱ ላይ ሳይሆን፥ እምነታችን በአኗኗራችን ላይ ሊያስከትል የሚገባቸውን ለውጦች ይዘረዝራል።
 5. ያዕቆብ በአማኞች አነጋገር ላይ ያተኩራል። ሁሉም ምዕራፎች ማለት ይቻላል እንደበታችንን እንዴት እንደምንገዛ እግዚአብሔርን ለማክበርና ለንስሐ እንጂ እርስ በርሳችን ለመቦጫጨቅ ልንጠቀም እንደማይገባም ይናገራል። ያዕቆብ አንደበት የአንድ አማኝ የመንፈሳዊነቱ መልካም አመልካች መሆኑን ያስረዳል።
 6. ያዕቆብ በዚህ መልእክት ውስጥ ብዙ ዘይቤያዊ አነጋገሮችንና ምሳሌዎችን ይጠቀማል። ከዓሣ አጥማጅነት፥ ከባህር፥ ከአበቦች፥ ከሚነድድ ቁጥቋጥ፥ ወዘተ… ምሳሌዎችን ይጠቀማል።
 7. ብዙ ምሁራን የያዕቆብ መልእክትን በተለይም ያዕቆብ 2፡14-16 ጳውሎስ በእምነት ስለ መጽደቅ ካስተማረው ጋር አነጻጽረው ለማብራራት ሞክረዋል (ሮሜ 3፡28-30)። እነዚህ ምሁራን እንደሚሉት፥ ያዕቆብ አንድ ሰው የሚድነው በሥራና በእምነት መሆኑን ያስተምራል። ጳውሎስ ግን ጽድቅ የሚገኘው በእምነት ብቻ መሆኑን ያስረዳል። አንዳንድ ምሁራን በእነዚህ ሁለት አመለካከቶች ላይ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን የተከፋፋለችበት ወቅት እንደነበረ ጭምር ይናገራሉ። ነገር ግን ዐውደ ንባቡን በጥንቃቄ በምንመረምርበት ጊዜ ሁለቱም ጸሐፊያን ስለ ጽድቅ ከሁለት የተለያዩ ገጽታዎች አንጻር የሚናገሩ መሆናቸውን እንረዳለን። ጳውሎስ ጽድቅን የተመለከተው ከሕጋዊ ገጽታው ሲሆን፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ጻድቅ መባልን አጉልቶ ያሳያል። ያዕቆብ ጽድቅን የተመለከተው በሰዎች ፊት ጻድቅ ወይም እውነተኛ ሆኖ ለመታየት ከሚል ገጽታ ነበር። ስለሆነም ጳውሎስ እግዚአብሔር ድነትን ስለሚሰጥበት ሁኔታ ሲናገር፥ ያዕቆብ ግን ሰዎች በራሳቸው መዳናቸውን ለሌሎች ሰዎች በሚያሳዩበት ሁኔታ ላይ ያተኩራል። የዚህ ቡድን ሌላው ግንዛቤ ጳውሎስ በእግዚአብሔር ፊት አሁን ትክክል ስለሆነበት ሁኔታ ሲናገር (ክርስቶስ በማመን)፥ ያዕቆብ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ በምንቀርብበት ጊዜ እንዴት ከፍርዱ እንደምናመልጥ (ሽልማትን እንዳናጣ) ያስረዳል የሚለው ነው። አዲስ ኪዳን ሁለት የድነት (ደኅንነት) ገጽታዎችን ያሳያል። እግዚአብሔር አንድ ነገር በማድረጋችን ወይም ጥሩዎች በመሆናችን ሳይሆን፥ በክርስቶስ በማመናችን፥ የድነትን (ደኅንነትን) ስጦታ ይሰጠናል። ይህ ጳውሎስ ያተኮረበት ርእሰ ጉዳይ ነው። ያዕቆብ ያተኮረበት ደግሞ በእርግጥ ድነትን ካገኘን፥ አዳዲስ ፍጥረታት ከሆንን፥ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ካለ፥ ሕይወታችን ይለወጥና በአኗኗራችን ይህንኑ እናሳያለን የሚለው ነው።

፮. የያዕቆብ መዋቅር

የያዕቆብ መልእክት ግልጽ የሆነ መዋቅር የለውም። ልክ እንደ መጽሐፈ ምሳሌ እርሱ ሊያስተላልፈው የፈለገው መልእክት በአጫጭር አባባሎች ወይም አጫጭር ርእሰ ጉዳዮች ወይም ችግሮች የተሞላ ሆኖ እንመለከተዋለን።

፯. የያዕቆብ አስተዋጽኦ

 1. በመከራና ፈተና ወቅት የአማኝ ኃላፊነት (ያዕ. 1፡1-18)

ሀ) ለመከራዎች ሊሰጥ የሚገባው ምላሽ (ያዕ. 1፡1-13)

ለ) ለፈተናዎች ሊሰጥ የሚገባው ምላሽ (ያዕ. 1፡13-18)

 1. አማኝ እምነቱን ተግባራዊ የሚያደርግባቸው መንገዶች (ያዕ. 1፡19-2፡26)

ሀ) እውነተኛ እማኞች ቁጣቸውንና አንደበታቸውን ይገዛሉ (ያዕ. 1፡19-20)።

ለ) እውነተኛ አማኞች የቃሉን እውነት ተግባራዊ በማድረግ አኗኗራቸውን ይለውጣሉ (ያዕ. 1፡21-27)።

ሐ) እውነተኛ አማኞች በድሃና በሀብታም አማኞች መካከል መድልዎ አይፈጽሙም (ያዕ. 2፡1-13)።

መ) እውነተኛ አማኞች በተግባራቸው የእምነታቸውን እውነተኛነት ያሳያሉ (ያዕ. 2፡ 14-26)።

 1. አማኝ አንደበቱን ይቆጣጠራል (ያዕ. 3፡1-12)።
 2. አማኝ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ውስጥ እውነተኛ ጥበብን ያሳያል (ያዕ. 3፡13-4፡12)።
 3. አማኝ ከሥራው ጋር ያለው ግንኙነት (ያዕ. 4፡13-5፡6)
 4. አማኝ ከመከራ፥ ከበሽታና ከኃጢአት ጋር ያለው ግንኙነት (ያዕ. 5፡7-20)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)